መንገድ አቋርጣለሁ፡፡ በእግሬ፡፡ ሁለት ጎልማሶች በመንገዱ ማቋረጫ ላይ ተገናኙ፡፡ ከሁለት አንዳቸው ቀድመው ወይም ተከትለው ማለፍ አለባቸው፡፡ ሁለቱም ቆሙ፡፡ ከዚያም አንዱ ሌላኛው ቀድሞ ያልፍ ዘንድ ጋበዘ፤ የተጋበዘውም ጋባዡ  እንዲያልፍ ለመነ፡፡ ግብዣው ጥቂት ደቂቃዎች ፈጀ፡፡ እኛም ከኋላ ያለነው ትኅትናቸውን አድንቀን በትዕግሥት ቆምን፡፡ በመጨረሻ አንደኛው እያመሰገነ አለፈ፡፡ ሌላኛውም ‹ምን አይደል›› እያለ አሳልፎ አለፈ፡፡ 
ደግሞ ሄድኩኝ፤ እነሆም በአንድ መስቀለኛ የአስፋልት መንገድ ላይ ደረስኩ፡፡ መኪኖቹ ከአራቱም አቅጣጫ ይመጣሉ፡፡ ሁሉም ወደ መስቀለኛው መጋጠሚያ ይገባሉ፡፡ አራቱም በአንድ ጊዜ ለማለፍ ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን አይችሉምና የመኪኖቹ አፍንጫዎቻቸው ተፋጥጠው ይቆማሉ፡፡ ለማለፍ እንጂ ለማሳለፍ የሚጥር አላይም፡፡ አራቱም በመስኮት ብቅ ብለው ‹ወደ ኋላ በልልኝ ልለፍ› ይላሉ፡፡ እነርሱ ሲከራከሩ ሌሎች ባለመኪኖችም ይመጣሉ፡፡ እንደ ዘንዶ ተጣጥፈው በአራቱ መኪኖች መካከል ለማለፍ ይሞክራሉ፡፡ እነዚያ ቀድመው የመጡትም ይናደዱና ወደ ፊት ገፍተው መንገዱን ያጠባሉ፡፡ በዚህ የተነሣም እነዚያም ከኋላ የመጡት በተራቸው ይቆማሉ፡፡ ሁሉም ቀድሞ ለማለፍ በሚያደርገው ፍትጊያ ሁሉም ይቆማሉ፡፡ እለፍ፣ እለፍ ተባብሎ መገባበዝ የለም፡፡ 
እየገረመኝ አልፋለሁ፡፡
አልፌም አንድ ያረጀ የዕድር ድንኳን የተጣለበት ጋ እደርሳለሁ፡፡ ድንኳኑ ለሁሉም አይበቃምና ከድንኳኑ ውጭ አግዳሚ ወንበር ላይ ሰዎች ተቀምጠዋል፡፡ ሌሎች ልቅሶ ደራሾ ሲመጡ ቀድመው ተቀምጠው የነበሩት ግር ብለው ይነሡና ወንበር ይለቃሉ፡፡ ‹ይቀመጡ አልቀመጥም› የግብዣ ግብግብ ይፈጠራል፡፡ በመካከል ገላጋይ ገብቶ እንግዳ ይቀመጣል፡፡ ‹ኖር› መባባል መልቶ ሰፍቶ ይከናወናል፡፡ ሰውን በአግዳሚዎቹ መካከል ለማሳለፍ ሁሉም እግሩን ያነሣል፣ ወይ ራሱ ይነሣል፡፡
እያደነቅኩ አለፍኩ፡፡
የማልፍበት መንገድ በግራ በቀኝ ቤት ሠሪዎች አሸዋና ጠጠር፣ ድንጋይና ብረት አውርደውበታል፡፡ እዚህም እዚያም ተጀምረው ያላለቁ፣ አልቀው ደግሞ ሰው የገባባቸው ቤቶች አሉ፡፡ አሸዋውና ድንጋዩ፣ ጠጠሩና ብረቱ መሐል መንገድ ላይ ይቆለላል፡፡ ሰው በምን ይተላለፋል? መኪና በምን ያልፋል? ብሎ ነገር የለም፡፡ ሁሉም በቤቱ ፊት ለፊት ይደፋል፡፡ ሲብሰው ደግሞ መሐል መንገድ ላይ ሲሚንቶ ያቦካል፣ ድንጋይ ይፈልጣል፡፡ እዚያ ድንኳን ውስጥ የነበረው ‹ኖር› መባባል፣ በአግዳሚዎች መካከል ሰው ለማሳለፍ መከራ መቀበል፣ እንግዳ ሲመጣ ከመቀመጫ ተነሥቶ ክብር መስጠት በቤት ሠሪዎቹ ዘንድ የለም፡፡
ይህንንም አለፍኩት፡፡
እነሆም በኑሮ ደከም ያሉ ሰዎች ወደሚኖሩበት መንደር ደረስኩ፤ የቆርቆሮ ጣራና የቆርቆሮ ግድግዳ ወደሚበዛባቸው፡፡ አቡኪዎቻቸው በእድሜ ገፍተው በሞቱ የጭቃ ግድግዳዎች ወደተሠሩ፤ ተቃቅፈው እንደሚሄዱ የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ትከሻ ለትከሻ የተደጋገፉ ግድግዳዎች ወዳሏቸው ቤቶች መንደር፡፡ በዚያም ሳቋርጥ ‹‹ወ/ሮ እንትና ደኅና አደሩ፤ ምነው ሰሞኑን አላየሁዎትም› የሚል የጎረቤት ድምጽ ሰማሁ፡፡ ወ/ሮ እንትናም አብራሩ፡፡ እልፍ ስል ደግሞ ‹‹እ-ን-ት-ና፣ ቡ-ና-ው ፈ-ል-ቷ-ል› የሚል ዘለግ ያለ የግብዣ ጥሪ አዳመጥኩ፡፡ ደግሞ ልጆቹም ሰብሰብ ብለው በመንደሩ መካከል ከምትገኘው የእጣቢ መድፊያ መስክ ላይ አፈር ልሰው አፈር መስለው ይጫወታሉ፡፡ ውሾም ከልጆቹ ጋ ይዘላሉ፡፡
እነሆ ያንንም መንደር አለፍኩትና ከመንገዱ ማዶ ተሻገርኩ፡፡
ይኼ ደግሞ የባዕለ ጸጎች ሠፈር ነው፡፡ እያንዳንዱ ግን በአጥር ተከልሏል፡፡ ወደዚያ መንደር ለማለፍም እንደ መንግሥት መሥሪያ ቤት መታወቂያ ይጠየቃል፤ ወደ ውስጥ ስትዘልቁ እንደ ሙታን መንደር ጭር ያለ ነው፡፡ መስክ ላይ ተሰባስበው የሚጫወቱ ልጆች አታዩም፤ ሁሉም ወይ ጌም ላይ ናቸው ወይም ቲቪ እያዩ ነው፡፡ አለያም ግቢያቸው ውስጥ ናቸው፡፡ ወላጆቻቸውም ግቢ ግቢያቸውን ዘግተው አይጠያየቁም፡፡ እንዲያውም ጎረቤታቸው ማን እንደሆነ የማያውቁም አሉ፤ ከግቢያቸው ሲወጡ ‹‹ወ/ሮ እገሊት ደኅና አደሩ፤ ምነው ሰሞኑን አይታዩምሳ›› ብለው አይጠይቁም፡፡
በዚህም ተገረምኩ፤ አለፍኩም፡፡
እነሆም ሰዎች ታክሲ ለመሣፈር ወረፋ የያዙበት ቦታ ደረስኩ፡፡ ረዥም ሰልፍ፡፡ ልጆች፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን፣ በከዘራ የሚሄዱ፣ ጎንበስ ብለው መሬት መሬት የሚያዩ፣ ጥላ የያዙ፣ በወረቀት ፀሐይን የሚከልሉ፣ ሁሉም ተሰልፈው የታክሲውን መምጣት ይጠባበቃሉ፡፡ ቆምኩና አየኋቸው፡፡ ታክሲዎቹ በመጡ ቁጥር የቻሉትን ሰው ይጭናሉ፡፡ በዚያ ፀሐይ ጨዋነታቸው ይነበባል፡፡ ራሳቸው ተራ አስከባሪዎች ከሚፈጥሩት ግርግር በቀር ግርግር ለመፍጠር የሚቻኮል ያንን ያህል ሰው የለም፡፡
ይህንንም አይቼ አለፍኩ፡፡
አለፍኩና ወደ አንድ ማደያ ዘንድ ደረስኩ፡፡ የነዳጅ ወረፋው የመንገዱን ጥግ የመኪና መሸጫ አስመስሎታል፡፡ ወደ ማደያው አካባቢ ሸውደው ለማለፍ የሚሞክሩ፤ አልፈው የሚሄዱ መስለው በሰው ሰልፍ የሚገቡ፣ ያንን ረዥም ሰልፍ እያዩ ሌላ ሰልፍ የሚፈጥሩ፣ መኪናቸውን አቁመው ጓደኛቸውን የሚያስገቡ ባለመኪኖች ይታያሉ፡፡ ከመኪኖቻቸው ውስጥ የብልግና ስድቦች ይወጣሉ፤ ይወራረፋሉ፤ ታክሲ እንደሚጠብቁት ሰዎች ፀሐይና አቧራ አያገኛቸውም፤ ከታክሲ ጠባቂዎቹ በላይ ግን ትዕግሥት የለሾች ናቸው፡፡ በመካከል ነዳጅ አልቋል ሊባል እንደሚችል ያውቃሉ፤ ነገር ግን ከኋላቸው የተሰለፉት ሰዎች ድካም ምንም ሳይመስላቸው ከነዳጅ ታንከራቸው በተጨማሪ በጀሪካቻኖቸው ይሞላሉ፡፡
እነሆ ይህንንም ታዝቤ አለፍኩ፡፡
አሁን ግን ዝም ብዬ አላለፍኩም፤ ያሳስበኝ ጀመር፡፡ እንዴው የኛ በጎ በጎ ባሕላችን በድህነት ላይ ነው እንዴ የተመሠረተው? አልኩ፡፡ በድሃው ማኅበረሰብ አካባቢ የምናያቸው የመከባበር፣ የመተባበር፣ የመጠያየቅ፣ የመረዳዳት፣ የመተሳሰብ ባሕሎች የተሻለ ገቢ ያለው ማኅበረሰባችን ላይ ሲታዩ ወይ ጠፍተዋል ወይም ቀንሰዋል፡፡ የዘመዶቻቸውን ልጆች እንደራሳቸው አድርገው የሚያሳድጉ ክቡራን ወላጆችን በብዛት የምናየው ድሃው ወገናችን ዘንድ ነው፡፡ የአንድ ሰው ጉዳይ አሳስቦት የት ነበርክ? ብሎ የሚየጠይቀው፣ ያለውን ተካፍሎ ለመብላት የሚተጋው፣ ጉርብትናው የሚያምረው፣ መከባበሩ ሞልቶ የሚፈሰው እዚህ ደሃው ወገናችን ላይ ነው፡፡
የተሻለ ኑሮና ዕውቀት ያለው ጋ ስትሄዱ ግለሰባዊነት፣ ብቸኛነትና ድንበርተኛነት ሠፍኖ ታዩታላችሁ፡፡ የማይለብሳቸው ብዙ ልብሶች አሉት፣ ግን አይሰጥም፤ የማይመገበው ትርፍ ምግብ አለው ግን፤ ግን አይመጸውተውም፡፡ ታላላቅ ግቢ አለ፤ ነገር ግን ተረት የሚያወሩ፣ ባሕል የሚያስተምሩ አክስቶች፣ አጎቶችና አያቶች አይኖሩበትም፡፡
እነዚያን የመንደር ሐኪሞች፣ እነዚያን እጆቻችንን አሽተው ያዳኑን ወጌሾች፣ እነዚያን ሐረግሬሳ በጥሰው፣ ስሚዛ ጨምቀው ያዳኑንን የመንደር እናቶችን አስቡና የአሁኑን የሕክምና ሥነ ምግባር አስቡት፡፡ ጠዋት ከዕንቅልፍ ብንቀሰቅሳቸው፣ በምሳ ሰዓት ብንሄድባቸው፣ በእኩለ ሌሊት ብንጠራቸው ለመንደሩ ሰዎች የነበራቸው ትጋት፤ ዛሬ ከዘመናዊ የሕክምና ተቋማት ለምን ተወሰደ? ይበልጥ ባወቅንና ይበልጥ ባገኘን ቁጥር ይበልጥ ጨዋነት ይጠፋብናል ማለት ነው? ከጉልት ሻጮች ይልቅ በሱፐር ማርኬቶች፣ ከመንደር ሱቆች ይልቅ በገበያ አዳራሾች ለምን ማጭበርበሩ በዛ?
ከተለያየ ጎሳና ነገድ ይበልጥ ተዋሕዶ፣ ተጋብቶና ተዛምዶ የምናገኘው የትኛውን ኅብረተሰብ ነው? ከውስኪ ቤትና ከጠጅ ቤት ኢትዮጵያን የሚያሳየን የትኛው ነው? በሀገር ቤት ከሚኖረውና በውጭ ከሚኖረው የትኛው ነው ጠባቡ? በአውቶቡስ ከሚሄድና በአውሮፕላን ከሚሄደው የትኛው ነው የሚገባበዘው? የትኛውስ ነው የሚጨዋወተው?   
ባደግንና በተለወጥን ቁጥር፣ ዕውቀትና ሀብትም ባፈራን ቁጥር፣ የኑሮ መደባችንም በተቀየረ ቁጥር እነዚያን የኛ ናቸው የምንላቸውን ወጎች፣ ልማዶች፣ ሥነ ምግባሮችና ባሕሎች እየተውናቸው እንሄዳለን ማለት ነው? ሥልጣኔና ብልጽግና የበጎ ባሕል ማጥፊያ ናቸው እንዴ? ኢትዮጵያዊ የምላቸው ባሕሎች፣ ወጎችና ልማዶች ካልተማረው ይልቅ በተማረው፣ ከሀብታሙ ይልቅ በደሃው ማኅረሰብ ዘንድ ይበልጥ የሚከበሩትና የሚጠበቁት ለምንድን ነው? ይበልጥ በበለጸግን ቁጥር፣ ይበልጥስ በተማርን ቁጥር ይበልጥ ኢትዮጵያዊነታችንን እንለቃለን ወይስ?

አፍሪካውያን ቀደምት አያቶቻችን እንዲህ የሚል ትንቢት አዘል አባባል ነበራቸው፡፡ ‹‹የዚህ ትውልድ ትልቁ አደጋ ራታቸውን በቁርስ ሰዓት ለመብላት መፈለጋቸው ነው››፡፡ ሰው እንደ መላእክት አይደለምና በሂደት እየበሰለ፣ በሂደት እየተገነባ፣ በሂደትም የበለጠ እየተማረ የሚሄድ ፍጡር ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የመንፈስ፣ የአካል፣ የስሜትና የአእምሮ ዕድገትና ለውጥን ይጠይቃል፡፡ ሰው ሲወለድ ለማደግና ለመለወጥ ከሚያስችል ዐቅም ጋር ነው፡፡ ይህንን ዐቅም ተጠቅሞ ለማደግና ለመለወጥ ግን ልምድ፣ ትምህርትና የሰውነት ግንባታ ያስፈልጉታል፡፡ ልምድ የሚባለው ከተወለደ ጊዜ ጀምሮ በሕይወት ውጣ ውረድ የሚደርስበት ተሞክሮ ነው፡፡ ይህም የሕይወት ተጋድሎ ይባላል፡፡ ትምህርት ከሰዎች፣ ከትምህርት ቤት፣ ከመጻሕፍት፣ ከአካባቢውና ከሌሎችም የዕውቀት ምንጮች የሚያገኘው ጥበብ ነው፡፡ የሰውነት ግንባታ የሚባለው ደግሞ በምግብና በእንቅስቃሴ የሚያበለጽገውን አካል ነው፡፡
እነዚህ ነገሮች የሚመጡትና የሚከናወኑት በሂደት ውስጥ በመሆኑ ሰዎች ለተለያዩ የኑሮ ደረጃዎች የሚበቁበት ጊዜ ይለያያል፡፡ በልጅነት፣ በወጣትነት፣ በዐዋቂነትና በአረጋዊነት ጊዜ የሚከናወኑት ተግባራት በዚያው በየዘመናቸው እንዲከናወኑ የሚያስገድዱት ሰዎች እነዚህን ነገሮች ለማከናወን የብስለታቸው ደረጃ እንደ ዕድሜያቸውና በዚያ ዕድሜ የተነሣ እንደሚያገኙት ልምድና ዕውቀት ብሎም አካላዊ ዝግጁነት ስለሚለያይ ነው፡፡ የልጆች ጋብቻንና የልጅነት ጊዜ ወሊድን የምንቃወመው፣ ጋብቻም ሆነ ወላጅነት የሚፈልጓቸው የመንፈስ፣ የአካል፣ የስሜትና የአእምሮ የዕድገት ደረጃዎች ስላሉ ነው፡፡

የመንፈስ ዕድገት የምንለው በመንፈሳዊው ዓለም ሰው የሚኖረው ዕድገትና ለውጥ ነው፡፡ በእምነት፣ በአመለካከት፣ በመርሕና በአተያይ የሚኖረው የብስለት ደረጃ፡፡ የስሜት ዕድገት ለነገሮች የሚኖረንን ፍቅርና ጥላቻ፣ ቀረቤታና ርቀት፣ ሙቀትና ቅዝቃዜ፣ ስበትና ግፊት የምንለካበት የዐቅም መጠን ማደግ ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች ለመቆጣጠር፣  ሕጋዊ፣ ሰላማዊ፣ ትክክልና ተገቢ በሆነው መንገድ ለመምራት ያለን ዐቅም ማለት ነው፡፡ የአእምሮ ዕድገት ስንል ደግሞ በዕውቀት ማደግን ነው፡፡
በትምህርት፣በልምድና በሰውነት ግንባታ እያደገና እየተለወጠ የሚሄደው ሰው፣ ሕይወቱ ተከታትለው በሚመጡ ሦስ ነገሮች  የሚዘወር ነው፡፡ ዐሉላ ጥላሁን ‹‹የሕይወት ሙሻዙር›› ይለዋል፡፡ እነዚህ ሦስቱ ጉጉት፣ ተጋድሎና ስኬት ይባላሉ፡፡ በሰው ሕይወት ውስጥ የሚያጓጓ፣ ይደረስበታል ተብሎ የሚታሰብ፣ የሚናፈቅና ተስፋ የሚደረግ ነገር ከሌለ ተጋድሎ የሚባለው የሕይወት ዋነኛ አጣፋጭ፣ ሰውንም ወደ ሙሉ ሰውነት የሚያደርሰው ታላቁ ድልድይ ተሰብሯል ማለት ነው፡፡ እርሱ ከተሰበረ ደግሞ ስኬት የሚባለው  ነገር አይታሰብም፡፡ በዓለማችን ላይ ከፍተኛ ሥልጣኔ የተመዘገበባቸው ሀገሮችና ዘመናትን ታሪክ ብናጠና እነዚህ ሦስቱ ነገሮች ገንዘባቸው የነበሩ መሪዎችን፣ ሊቃውንትንና ሕዝቦችን እናገኛለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በኋላ ቀርነት ይሰቃዩ የነበሩና አሁንም የሚሰቃዩትን ሕዝቦች ስናይም እነዚህ ነገሮች ሲያጥሯቸው እናስተውላለን፡፡
ሰው ይህንን የሕይወት ሙሻዙር ዘውሮ ሕይወቱን ወደ ልዕልና እንዳያደርሳት የጉጉት፣ ተጋድሎና ስኬትን መሥመር የሚሰብሩ አራት ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ዋናን የሚያጠፋ ርዳታ ነው፡፡ ርዳታ ወይም እገዛ መልካም የሚሆነው ዓሣ ሊያሰግር የወጣውን ሰው በቀላሉ ብዙ ዓሣዎች እንዲያሰግር የሚያስችለውና እርሱም የተሻለ ማስገሪያ እንዲሠራ የሚያበቃው ዓይነት ርዳታ ከሆነ ነው፡፡ ሰውዬው ቁጭ ብሎ ዓሣ እንዲያገኝና ምንም እንዳያስብ የሚያደርገው ርዳታ ግን ርዳታ ሳይሆን ግድያ ነው፡፡ መጀመሪያ ብዙ ዓሣ ለማስገር የነበረውን ጉጉት ይገድልበታል፡፡ ቀጥሎ ያንን ጉጉት ለማሟላት እንዳይጋደል ያሰንፈዋል፡፡ በመጨረሻም ስኬት አይኖረውም፡፡ ስኬት ማለት የጥረት ውጤት ነውና፡፡ ያለ ጥረት በዱብ ዕዳ የተገኘ ነገር ሁሉ ስኬት አይደለም፡፡ ዕድል፣ ዕጣ ወይም ስጦታ ይሆናል እንጂ፡፡ ሰውን ወደ ዕድል፣ ዕጣና ስጦታ ደረጃ ማውረድ ደግሞ ከሰውነት አሳንሶ ‹መትኅተ ሰብእ መልዕልተ እንስሳት› ማድረግ ነው፡፡ ራቱን ቁርሱ ላይ እንዲበላው ማድረግ፡፡ ነገ ልታገኘው የምታስበውና የምትለፋለት አዲስ ነገር ከሌለህ ‹ነገ› ለምን ይምጣ? ‹ነገ› ስ  ከአንድ ተጨማሪ ቀን ውጭ ሌላ ምንድን ነው?
ሁለተኛው ሰባሪ አደጋ ደግሞ በወንጀል የተገመደ አቋራጭ መንገድ ነው፡፡ በስርቆት፣ በጉቦ፣ በማስመሰል፣ በሥልጣን በመባለግ፣ የሰዎችን ዕድል በማበላሸት፣ ትውልድን በመግደል፣ ሀገርን በማጥፋት፣ ወዘተ በኩል የሚገኝ አቋራጭ መንገድ፡፡ በቀላሉ ሥልጣን፣ ገንዘብ፣ ክብር፣ ስምና ዝና የሚገኝበት፡፡ ይህ መንድ ምናልባት ገንዘብ፣ ስምና ክብር፣ ሥልጣንና ዝና ያስገኝ ይሆናል፡፡ ውስጣዊ ደስታ ግን አያስገኝም፡፡ ደስታ ከስኬት የሚገኝ ነውና፡፡ ሌሎቹን ነገሮች ማስመሰል ቢቻልም ውስጥን ማስመሰል ግን አይቻለም፡፡ ደስታ ውስጣዊ ስለሆነ ነው አስመስሎ መሥራት የማይቻለው፡፡
እንዲህ ባደረገ ሰው ውስጥ የሚፈጠረው ጦርነት የትም ቦታ የማይፈጠር ነው፡፡ የሕግ መውጣት፣ የሥርዓት መለወጥ፣ የዳኝነት ሥርዓት መጠንከር፣ የሚዲያ ምርመራ መጀመር፣ የሰዎች ዕውቀት መጨመር፣ እርሱ የፈጸማቸውን ነገሮች የሚቃወሙ አሠራሮች መምጣት፣ የዓለም አስተሳሰብ እየተቀየረ መሄድ ያሳስበዋል፡፡ ያስጨንቀዋል፡፡ ለዚህም ነው እውነተኛውን ደስታ የማያገኘው፡፡ ድሮ ‹‹ከዕለታት አንድ ቀን›› የሚለው መግቢያ ለተረት የሚያገለግል ነበረ፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን ለሰዎችም ያገለግል ጀምሯል፡፡ ‹‹ከዕለታት አንድ ቀን እገሌ ድንገት ኢንቨስተር ሆነ፣ ድንገት ባለ ሀብት ሆነ፣ ድንገት ባለ ዘጠኝ ፎቅ ሆነ፣ ድንገት ባለ ሥልጣን ሆነ፣ ድንገት ባለ ኩባንያ ሆነ፣›› ከየት ተነሥቶ፣ በየት በኩል ሄዶ፣ ምንም አድርጎ? መልስ የለም፡፡ ‹‹እንዴው ከዕለታት በአንድ ቀን›› ነው መልሱ፡፡ በዚህ መንድ የሚመጡ ሰዎች ስኬታማ አይደሉምና ደስተኛም አይደሉም፡፡ ደስተኛ ግን ይመስላሉ፡፡ ራታቸውን ቁርሳቸው ላይ ስለበሉት ምንጊዜም የራት ነገር ሲያሳስባቸው ይኖራል፡፡ ራት ያልበላ ሰው የሚተኛውን የረሃብ ዕንቅልፍ ስለሚተኙ፤ አልጋ እንጂ ዕንቅልፍ አይኖራቸውም፡፡ ቅዠት እንጂ ሕልም አይታያቸውም፡፡
ሦስተኛው ሰባሪ አደጋ ዕድል፣ አጋጣሚና የተመቻቸ ሁኔታ የሚፈጥሩት ግሽበት ነው፡፡ የማስተማሪያ ዐቅምና ዕድል ስላገኘን ብቻ ልጃችንን ያለ ዕድሜው ወደ ትምህርት ቤት ብንልከው ልጁ እየተማረረ እንጂ እየተማረ አይመጣም፡፡ በኋላም ከፍ ሲል ትምህርት ጠል ከሚሆንባቸው ምክንያቶች አንዱ ያለ ዕድሜ ወደ ትምህርት ቤት መግባትና መደበኛ ትምህርት መጀመር ናቸው፡፡ ዕድልና አጋጣሚ አገጣጥሞላቸው ያለ ከዕድሜና ከዕውቀት በፊት ገንዘብ ማግኘት ያቻሉ አንዳንድ ሰዎች ገንዘቡ መጥፊያቸው ሲሆን አይተናል፡፡ አካባቢያቸውን ለማስተዳደር መጀመር ባለባቸው ጊዜ አገር ማስተዳደር የሚጀምሩ፣ ቤተሰባቸውን መምራት ከመጀመራቸው በፊት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መምራት የጀመሩ ሰዎች ዕድሉን ለስኬት ከመጠቅም ይልቅ ሀገር ለማጥፋት የሚጠቀሙበት በዚህ ስኬት ሰባሪ አደጋ የተነሣ ነው፡፡ ራታቸውን ቁርስ ላይ በልተውት፡፡ 
ዛሬ ዛሬ በጋብቻ ውስጥ ብቻ ሊደረጉ የሚገባቸው ነገሮች ከጋብቻ በፊት፣ በበሳል ዕድሜ ሊፈጸሙ የሚገባቸው ጾታዊ ግንኙነቶች በሚዲያ፣ በፊልም፣ በማኅበራዊ ድረ ገጾችና በአንዳንድ አቀንቃኞች ምክንያት በሚፈጠሩ የስሜት መመቻቸቶች የተነሣ በልጅነት ዕድሜ እየተፈጸሙ በመምጣታቸው ሰዎች ራታቸውን ቁርስ ላይ በልተው የሚጓጉለት ነገር እንዳይኖር አድርጓቸዋል፡፡ ልጆች ተምረው ሊያገኙት የሚገባውን ነገር የድመት ፍቅር በያዛቸው ወላጆች ምክንያት ሳይማሩ ስለሚያገኙት ለትምህርት ሊያውሉት የሚያስፈልግ ጉጉትና ጥረት ተሟጥጦባቸዋል፡፡ በምዕራቡ ዓለም ታላላቅ ሰዎች ልጆቻቸውን በኩባንያቸውና በፖለቲካ መሥመራቸው መተካት የቻሉት፣ ልጆቹ መሥመሩን ተከትለው በመጋደል መሥመሩ የሚያስገኝላቸውን እያገኙ እንዲያድጉ በማድረጋቸው ነው፡፡ የአባታቸው ሀብት ስለሆነ ብቻ አያገኙትም፤ ተምረው፣ ሠርተው፣ ከሌሎቹ ጋር ተወዳድረው፣ ከታች እስከ ላይ ያለውን የዕድገት መሰላል በመንፈስ፣ በትምህርት፣ በልምድና በአካላዊ ዕድገት እየዳበሩ አልፈው፣ በተወዳዳሪነትና በአሸናፊነት ተጋድሎ ተፈትነው ሲደርሱ፤ ያን ጊዜ ወላጆቻቸው ‹ተቀመጥ በወንበሬ፣ ተናገር በከንፈሬ› ብለው ያስረክቧቸዋል፡፡ ሳንቲሞች እንዴት እንደመጡ ሳያውቁ ብሮችን አያስነኳቸውም፡፡ ነገ ሊደርሱበት የሚገባውን ራት ዛሬ በቁርስ ሰዓት አያበሏቸውም፡፡ ልጅ ምንም ያህል ቢፈለግ በሦስት ወር ይወለድ አይባልምና፡፡
አራተኛው ሰባሪ አደጋ የሚመጣው በጋሸበ አድናቆትና ግፊት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከሰዎች የሚሰጠንን አስተያየት፣ ድጋፍ፣ ተቃውሞ፣ ክብር፣ ዝና፣ ስምና ታላቅነት ከውስጣችን ዐቅም ጋር መዝነን ካላስተናገድነው አደጋ ያስከትላል፡፡ ሰዎች ትችላላችሁ፣ ያለ እናንተ ሰው የለንም፣ ጀግና ናችሁ፣ ስላሉን ያሉንን ሁሉ አንሆንም፡፡ ጭብጨባውን፣ ሙገሳውን፣ አድናቆቱን ለችሎታ መመዘኛነት ከወሰድነው ከራሳችን ጋር እንጣላለን፡፡ ቀስ በቀስ በዕድገትና በልምድ፣ በትምህርትና በተጋድሎ ልንደርስበት የሚገባንን ገፋፍተው ሲያወጡን ከተቀበልንና ‹ሕዝብ ከመረጠኝ፣ ሕዝብ ካለ፣ ሕዝቡ ከደገፈኝ› ካልን ራታችንን ቁርስ ላይ ያስበሉናል፡፡ እላይ ከወጣን በኋላም የምናደርገው ይጠፋናል፡፡ በውጫዊ ግፊትና አድናቆት ‹ነህ› የሚሉንን ከመቀበል በውስጣዊ ዕውቀት ‹አይደለህም› የሚለንን መቀበሉ ያዋጣናል፡፡ ዛሬ ዓለምን ለበሽታ የዳረጓት ዕንቁላል ሳይሆኑ ዶሮ የሆኑት ናቸው፡፡
ሰው በሂደት የሚሟላ ፍጡር ነው፡፡ የሚያሟሉትም ትምህርት፣ ልምድና የሰውነት ግንባታ ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ የሚፈጸሙት በጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ አንድን ነገር ዕድል ስላገኘን፣ ነገሮች ስለተመቻቹ፣ አቋራጭ መንገድ ስላለው፤ በአድናቆትም ሆነ በተቃውሞ ስለተገፋፋን፣ ጊዜ የሰጠው ቅል ስለሆንን ወይም ደግሞ በምናያቸው ፊልሞች፣ በምናነባቸው ስሜት ቀስቃሽ ጽሑፎች፣ ከጓደኞቻችን በሚፈጠሩብን ግፊቶች ተስበንና ተገፍተን ራታችንን ቁርስ ላይ መብላት የለብንም፡፡ ጉጉት የሌለው ነገ፣ የማይጋደሉበትም ሕይወት ስኬትን አያመጣምና፡፡ ስኬትን የማያጣጥም ሰውነት ደግሞ ምንጊዜም ውስጡ ክፍተት ይኖረዋል፡፡ ያ ክፍተት ነው ተስፋ መቁረጥን፣ ትካዜን፣ ራስን መጥላትን፣ የበታችነትን፣ ወራዳነትንና ራስን መጥፋትን የሚፈጥረው፡፡   


እኔና ባለቤቴ ልክ እንዳንቺ ሆነን ነበር፡፡ ነገራችን ሁሉ ችኮ ሆኖ፡፡ ያ ድሮ እንደ መልካም ሙዚቃ ጆሮሽን አዘንብለሽ የምትሰሚው የባልሽ ድምጽ ፍሬን እንደያዘ መኪና ድምጽ ሲሆንብሽ ይሰማሻል፡፡ ይናፍቅሽ የነበረው ድምጽ ሲደውል ሐሳብ ውስጥ ይጥልሻል፡፡ ደግሞ ምን ሊል ይሆን? ትያለሽ፡፡ ስልክ ከማንሳት ይልቅ ስልኩን ለመዝጋት ትቸኩያለሽ፡፡ ለመሆኑ ባል ማለት ምንድን ነው? ለእኔ ከባልሽ ጋር ብቻ የምታደርጊያቸው ነገሮች ስላሉ ነው፡፡ ከእርሱ ጋር ብቻ የምትቀልጃቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምታወሪያቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምትሠሪያቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምትወስኛቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምትባልጊያቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምታኮርፊያቸው፡፡

ለአንቺ ብቻ የሚቀጸሉ፣ለአንቺ ብቻ የሚውሉ፣ ለአንቺ ብቻ የሚነገሩ፣ ለአንቺ ብቻ የሚገለጡ፣ ለአንቺ ብቻ የሚደረጉ፣ ለአንቺ ብቻ የሚሰሙ የተለዩ ነገሮች ከሌሉ ምኑን ሚስት ሆንሺው፡፡ ባልሽ ደግ፣ ሩኅሩኅ፣ ትዕግሥተኛ፣ የማይሰክር፣ ገንዘብ የማያባክን፣ ታማኝ፣ መልከ ቀና  ቢሆን እጅግ የታደልሽ ትባያለሽ፡፡ ይኼ ሁሉ ግን መልካም ሰውነቱን እንጂ መልካም ባልነቱን አያሳይም፡፡ ደግ ሰው፣ ቆንጆ ሰው፣ ትጉኅ ሰው፣ ፍጹም ሰው ያሰኘዋል እንጂ ብቻውን መልካም ባል አያሰኘውም፡፡
መልካም ባል ለመሆን በመልካም ሰውነት ላይ ሊጨመሩ የሚገባቸው ሌሎች የባልነት ነገሮች አሉ፡፡ በመልካም ባል ውስጥ ሚስትነት፣ በመልካም ሚስት ውስጥ ደግሞ ባልነት መኖር አለባቸው፡፡ መልካም ባል ማለት ሚስት መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚረዳ፣ ሚስትነት በውስጡ ያለው ባል ማለት ነው፡፡ መልካም ሚስትም እንዲሁ፡፡ መልካም ባል ማለት የሚስትን ስሜት፣ ልብና ኩላሊት ለማወቅ የሚችል ማለት ሳይሆን ሊረዳውና ሊሰማው የሚችል ማለት ነው፡፡
እንዲህ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቼ ሳስበው ለካ እኛ ቤት ውስጥ የነበሩት ባልና ሚስት ጠፍተው አንድ ወንድና አንዲት ሴት ቀርተዋል፡፡ አብረው የሚኖሩ፣ አብረው የሚሠሩ፣ አብረው የሚያድሩ፣ አብረው የሚበሉ፣ አብረው ልጅ የሚያሳድጉ ሁለት ወንድና ሴት፡፡ ባለ ትዳሮቹ ጠፍተው ትዳሩ ቀርቷል፡፡ አንድ ነገር የሚመሠረተው፣ ለመመሥረቱ በሚኖረው ቀዳሚ ምክንያት ነው፡፡ ያ ምክንያት ነው ለዚያ ነገር የህልውናው ሞተር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ምክንያቱ ይጠፋና ነገሩ ብቻውን ይኖራል፡፡ የምክንያቱ ሳይሆን ምክንያቱ የፈጠረው ተቋም ወይም ቡድን አባል ትሆኛለሽ፡፡
ከዚያ በኋላ የምትኖሪው ወይም የምትንቀሳቀሽው ለምክንያቱ ሳይሆን በምክንያቱ የተነሣ ለተፈጠረው ተቋም ወይም ቡድን ይሆናል፡፡ ያ ተቋም የተመሠረተበትን ምክንያት ለመፈጸም ሲል የፈጠራቸው ሕጎች፣ ሥርዓቶች፣ ደንቦች፣ ባሕሎች፣ ልማዶች፣ ወጎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች በሰው ውስጥ ሰርጸው የመኖር ዐቅም ስላላቸው፤ አንቺም ለእነዚህ እየተገዛሽ መኖር ትቀጥያለሽ፡፡ ያን ጊዜ ሕይወት አዙሪት ይሆንብሻል፡፡ ሥራ ስላለሽ ከቤት ትወጫለሽ፣ ቤት ስላለሽ ብቻ ተመልሰሽ ትመጫለሽ፤ ልጆች ስለወለድሽ ለእነርሱ ስትዪ ትዳርሽን ትቀጥዪዋለሽ፣ ባል ስላለሽ ብቻ አብረሽ ትተኛለሽ፤ የጋራ ጉዳይ ስላለሽ ብቻ ተነጋገሪያለሽ፤ እያለ ይቀጥላል፡፡
እኔ እንዳየሁት አንቺ በትዳር ውስጥ ስትሆኚና ትዳሩ አንቺ ውስጥ ሲሆን ይለያያል፡፡ አንቺ በትዳር ውስጥ ስትሆኚ፣ በውስጥሽ ምንም ስሜት ሳይኖርሽ፣ ነፍስሽ ምንም ሳይሰማት እንዴው ማድረግ ስላለብሽ ብቻ ስታደርጊው ነው፡፡ ምግብን ሆድሽ ብቻ ሲበላውና ኅሊናሽ ጭምር ሲበላው አይለያይም? ለመኖር መብላት ስላለብሽ ብቻ ስትበዪና ደስ ብሎሽ፣ ኅሊናሽ ረክቶ፣ ዘና ብለሽ ስትበዪ ማለቴ ነው፡፡ አንቺ በትዳር ውስጥ ስትሆኚ ለመኖር ብቻ ሲባል ምግብ እንደመብላት ነው፡፡ ትዳር በአንቺ ውስጥ ሲሆን ግን ሌላ ነው፡፡ ስትሄጂ፣ ስትሠሪ፣ ስትተኚ፣ ሲደክምሽና ስትበረቺ እንኳን ትዳርሽን ባሰብሽ ቁጥር አንዳች ልዩ የሆነ የደስታና የእርካታ ስሜት ሲሰማሽ፤ ገብተሸ ስትዋኚበት፣ ያወራችሁትን፣ ያደረጋችሁትን፣ የሆናችሁትን፣ ሌላው፤ ቀርቶ የተኳረፋችሁትን እንኳን እንደ ቤት እንስሳ መልሰሽ ስታመነዥኪው እንደ መልካም ጠጅ በኅሊናሽ ኩልል ብሎ ሲንቆረቆር፤ ከቤትሽ ስትወጭ ለመመለስ ስትቸኩዪ፤ ከባልሽ ስትለዪ ለመገናኘት ስትጣደፊ፤ ባልሽን፣ ልጆችሺን፣ ቤትሽን ይዘሺው ስትሄጂ – ያ ነው – ትዳር በአንቺ ውስጥ ሲኖር ማለት፡፡
ትዳር ስንጀምር ትዳር ውስጣችን ገብቶ ነበር፡፡ ስንቆይ ግን እኛ እንገባና እርሱ ይወጣል፡፡ ያኔ ነው ‹መነጋገር› መነጋገር ብቻ የሚሆነው፡፡ መነጋገር የፍቅር መግለጫ፣ በነፍስ የመዛመድ ምልክት፣ በሐሳብ የመገናዘብ ማሳያ መሆኑ ይቀርና መነጋገር መነጋገር ብቻ ይሆናል፡፡ እኔም እንዲህ ሆኖብኝ ብዙ ጊዜ ተቸገርኩ፡፡ ስነጫነጭ፣ ስብሰከሰክ፣ ስማረርና ስቆርጥ ስቀጥል ኖርኩ፡፡ አንድ ቀን እንደ ድንገት ጋብቻን ስለማደስ የተጻፈ መጽሐፍ አገኘሁ፡፡ በፈረንጆቹ ባሕል ጋብቻን ማደስ (marriage renewal) የተለመደ ባሕል ነው፡፡ ለምን ወደ እኛ አንቀይረውም ብዬ አሰብኩ፡፡
በዚያ መጽሐፍ ላይ አንድ ቁም ነገር አየሁ፡፡ ከትዳር ልምድ ያገኘሺውን ነገር ተጠቅመሽ አዲስ የቃል ኪዳን ሰነድ አዘጋጂ ይላል፡፡ ለባለቤቴ ወሰድኩና አሳየሁት፡፡ ሲያነበው ወደደው፡፡ ያ ነገር ምክንያት ሆነንና ስለትዳር ማደስ አወራን፡፡ እኔም የራሴን እርሱም የራሱን ሰነድ አዘጋጀ፡፡ በቃል ኪዳን ሰነዱ ሞዴል ላይ ያለፈውን የትዳር ዘመን፣ ባለፈው ዘመን በክፉም በደጉም ለቆየንባቸው ዘመናት ለፈጣሪ ምስጋና፣ ለፈጠርናቸው ስሕተቶች ይቅርታ፣ ከዚያ ደግሞ ለወደፊቱ በትዳራችን እንድናደርግ የምንፈልገውን ነገር ይዘረዝራል፡፡ እኔ የርሱን እርሱም የእኔን ልናዘጋጅ ተስማማን፡፡ ባሌ ምን ቢሆንልኝ እንደምፈልግ ለብዙ ጊዜ አሰብኩበት፤ እርሱም አስቦበታል፡፡
ያዘጋጀነው ሰነድ ከትዳራችን ምን እንደምንፈልግና፣ ምን እንደማንፈልግ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነበር፡፡ ትዳራችንን የፈተሽንብት መልካም አጋጣሚ ሆነልን፡፡ ሁለታችንም በተዘጋጀልን ሰነድ ላይ መጠነኛ ማሻሻያ ከማድረግ ያለፈ አልተጓዝንም፡፡ አሁን በስለናል፤ ከልምድ ብዙ ነገር አግኝተናል፤ በፊት በትዳር ውስጥ እናስባቸው ያልነበሩ ነገሮችን ማሰብ ጀምረናል፤ ተፈታትነናል፤ ተዋውቀናልም፡፡ አንዳችን የሌላችንን በማዘጋጀታችን የተነሣ ነገሮች በዝርዝር ቀርበው ነበር፡፡ አናደርግም የምንለው፣ እናደርጋለን የምንለው ቁልጭ ብሎ ቀርቧል፡፡
በጣም የሚገርምሽ ነገር ችግር የማይመስሉን ነገሮች ሁሉ በሌላችን ተነቅሰው ሲመጡ ችግር መሆናቸውን ለመረዳት አስችሎናል፡፡ ቀላል የሚመስሉ፣ እንደዋዛ የምንዘላቸው፣ ነገር ግን ሌላችንን የሚያናድዱና የሚያሳዝኑ ነገሮች ሁሉ መጡ፡፡  በፈጣሪ ፊት ቆምንና ሁለታችንም እንደገና ቃል ገባን፡፡ እንደገናም ተጋባን፤ ለትዳራችን አዲስ እሴት ጨመርንለት፣ እንደገና የመኖሪያ ምክንያታችንን አደስነው፤ እርሱ ወደ እኔ፣ እኔም ወደ እርሱ ውስጥ ገባን፡፡ ትዳራችንም ወደ እኛ ገባ፡፡ ያንን ሰነድ በየጊዜው እያየሁ ራሴን አረጋግጥ ነበር፡፡ ቃሌን እየጠበቅኩ ነውን? እል ነበር፡፡ እንደ አዲስ ተጋቢ ነበር የሚሰማኝ፡፡
እንዳየሁት ከሆነ ትዳርና አትክልት በየጊዜው ካልተከታተሉት አረም ይበቅልበታል፡፡ ሲብስም አትክልቱ ይጠፋና አረሙ መታየት ይጀምራል፡፡ ያኔ ነው እንጨት እንጨት የሚለው፡፡ ጎበዝ ሰው ቶሎ ብሎ ያርምና አትክልቱ እንዲያብብ ያደርገዋል፡፡ እንደገና መኮትኮት፣ እንደገና ማዳበሪያ ማድረግ፣ እንደገና አፈር መከለስ፣ እንደገና ውኃ ማጠጣት፣ እንደገና አጥር ማጠር ይጠይቅ ይሆናል፡፡ ድሮ አፈር አድርጌ ነበር፣ ማዳበሪያ ነበረው፣ አጠጥቼው ነበር፣ ኮትኩቼው ነበር አይሠራም ወዳጄ፡፡ አንዳንዴም እርሻው ብቻ ቀርቶ ተክሉ ሊጠፋ ይችላል፡፡
እና እስኪ ቆም ብለሽ ተመልከቺው፤ እንደገና መጋባት፣ ጋብቻውን እንደገና ማደስ፣ ለአዲሱ ሰብእናሽ አዲስ ሐሳብ መፈለግ፣ አሁን ለደረስሽበት ነገር አዲስ ቃል ኪዳን መግባት ያስፈልጋችሁ ይሆናል፡፡ ትዳርሽ አርጅቶ ይሆናል፡፡ ትዳር ይፀነሳል፣ ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ያረጃል፣ ዝም ካሉትም ይሞታል፡፡ ጀግኖች ደግሞ እንዳያረጅና እንዳይሞት እንደ አዲስ ያድሱታል፡፡ አንቺም ትዳርሽ እንደ ንሥር አድሽው፤ ያለበለዚያ መጀመሪያ ያረጃል፤ ከዚያም ከባሰ ይሞታል፡፡ እሳትን እንጨት ላይ እያለ መልሶ ማቀጣጠል መልካም ነው፤በእንጨትነቱ ካልተደረሰም እንጨቱ ከሰል ሲሆን ቶሎ መድረስ ነው፤ ከሰሉ አመድ ከሆነ በኋላ ግን እንደገና ማቀጣጠል አስቸጋሪ ነው፡፡ ›› ነበር ያለቺኝ፡፡
አሁን  ሳስበው እርሷ ያለቺኝ ሳይሻል አይቀርም፡፡
‹እውነትሽ ነው› አለቺ ጓደኛዋ ‹‹ሁላችንም ብንሞክረው ሳይሻል አይቀርም››
ዑራኤል የኤሌክትሪክ ሱቆች ጋር ደርሼ ተለየኋቸው፡፡ እነርሱ ግን ቀጠሉ፡፡
ፍራንክፈርት አውሮፕላን ጣቢያ


click here for pdf

ከለም ሆቴል ወደ ካዛንቺስ የሚሄድ ታክሲ ውስጥ ገብቼ ከኋላ ወንበር ተቀመጥኩ፡፡ ከጎኔ ሁለት በዕድሜ ወደ ሠላሳዎቹ አጋማሽ የሚሆኑ ሴቶች ተቀምጠዋል፡፡ ታክሲው ሲንቀሳቀስ ‹‹ለመሆኑ ምን ዓይነት ነገር ቢገጥምሽ ነው ለመንገር ያስቸግራል የምትይኝ›› አለቻት መካከል ያለቺዋ ወደ መስኮቱ ጥግ የተቀመጠችውን፡፡ እንደ ታክሲ መቼም ማኅበራዊ ኑሯችንን የምናውቅበት ምቹ መድረክ የለምና ጆሮዬን ጣል አደረግኩ፡፡ ‹‹ባክሽ ችግሩን ከመሸከሙ ችግሩን መግለጡ ይከብዳል›› አለች ያችኛዋ፡፡
 
አንድ ሊቅ ‹‹እጅግ አስቸጋሪው ችግር ሊገልጡት የሚያስቸግር ችግር ነው›› ያሉትን አስታወሰኝ፡፡ ምን እንደገጠማት ባላውቅም አንዳንድ ችግር ግን የሕመሙን ያህል መግለጫ ነገር አይገኝለትም፡፡ ሲናሩት ተራ ወይም ቀላል ይሆናል፡፡ ሰሚውም ‹‹አሁን ይኼ ችግር ነው?›› ይላል፡፡ ተናጋሪውም ንግግሩ ቀላል ስለሚሆንበት ከችግሩ በላይ ያመዋል፡፡

 ‹‹ግዴለሽም እንደምንም ብለሽ ንገሪኝ›› አለቻት፡፡

‹‹አንቺና ባለቤትሽ ስታወሩ እንዴት ነው?›› ስትል ጥያቄዋን በጥያቄ መለሰችው፡፡
‹‹እንዴት?በቃ ማውራት ነዋ፡፡››
‹‹ስታወሩ ምን ይሰማሻል?››
‹‹ፊዚክስ አደረግሽዋኮ›› አለች እየሳቀች፡፡
‹‹እኔ ግን ከእርሱ ጋር ሳወራ ያመኛል፡፡››
‹‹እንዴት? ይሰድብሻል፤ ይቆጣል፤ ምን ዓይነት ክፉ ቃል ቢናገርሽ ነው››
በመስኮቱ ጥግ ያለችው ሴት አንገቷን ስትነቀንቅ በዚህኛው መስኮት ነጸብራቅ በኩል አያታለሁ፡፡
‹‹ሁሉም አይደለም›› አለቻት፡፡ ጠያቂዋ የእፎይታ ትንፋሽ በረጅሙ ተነፈሰች፡፡
‹‹ታድያ ምድን ነው?›› አለች ጠያቂዋ፡፡
‹‹አየሽ ለመናገር አስቸጋሪ የሚሆነው አሁን ካልሻቸው ነገሮች አንዱን እንኳን ስላልሆነ ነው፡፡ እስካሁን ስም የወጣለት አይመስለኝም፡፡ ስድብ አይደለም፤ ቁጣ አይደለም፤ ማመናጨቅ አይደለም፤ ሽሙጥ አይደለም፤ ጭቅጭቅ አይደለም፣ ንትርክ አይደለም፤ ክርክር አይደለም፤ ሌላ ነው››
 
‹‹እንዴ እንትናዬ(ስሟን እያቆላመጠች) ምንድን ነው የሆንሽው? ምንድን ነው የሚያደርግሽ?››
 
‹‹የሁለታችን ወሬ ያማል፤ ጣዕም የለውም፡፡ እንጨት እንጨት የሚል፡፡ ምንም ነገር የሌለው፤ በቴፕ ተቀድቶ ብትሰሚው ባልና ሚስት እያወሩ ነው የማትዪው ዓይነት››
 
ወደራሴ ተመለስኩ፡፡ ‹የሚያም ንግግር› ብላ የጠቀሰችው ምንድን ነው? ስድብ ካልሆነ፣ ግልምጫ ካልሆነ፣ ቁጣ ካልሆነ፣ አግቦ ካልሆነ፣ ክርክር ካልሆነ፣ ጭቅጭቅ ካልሆነ፣ ንትርክ ካልሆነ፣ እንካ ሰላንትያ ካልሆነ፤ ታድያ ምንድን ነው?  ‹እንጨት እንጨት የሚል› ያለችው ምንድን ነው?
 
ሰውን ከሰው ጋር የሚያግባባው ዋናው ነገር ቋንቋ ነው፡፡ ካልተናገረ አይታይ ብልሃቱ፣ ካልታረደ አይታይ ስባቱ የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ ከአያያዝ ይቀደዳል፣ ከአነጋገር ይፈረዳል የሚልም ተጨምሮበታል፡፡ ግን መናገር ማለት ምን ማለት ነው? ንግግር ሁሉ መልእክት ያስተላልፋል? ንግግር ሁሉ ያግባባል? ሰው በቋንቋ እንደሚግባባው ሁሉ የማይግባባውም በቋንቋ ነው፡፡ ኤፍሬም እሸቴ ‹‹ቋንቋ መግባቢያ አይደለም›› የሚል ጽሑፍ ነበረው፡፡ ‹ቋንቋ ከሌላቸው እንስሳት በላይ ቋንቋ ያለው ሰው አለ መግባባት ከቻለ ቋንቋ ምኑን መግባቢያ ሆነው› ይላል፡፡ 
 
ቋንቋ ግን ብቻውን አያግባባም፡፡ ሐሳብ፣ ቃላት፣ ሰዋስውና ንግግር ብቻቸውን ሰዎችን አያግባቡም፡፡ ብቻቸውንም ውስጣችንን አይገልጡም፡፡ የእጆቻችን ወንጫፊዎች፣ የፊታችን ኩስታሬ፣ የዓይኖቻችን እንቅስቃሴ፣ የድምጻችን ቃና፣ የአንገታችን ንቅናቄ እንኳን ተጨምሮበት በሚፈለገው መጠን ሊያግባባን ዐቅም የሚያንሰው ጊዜ አለ፡፡ በመናገርና በመሰማት መካከል ልዩነት የሚፈጥረው፣ በማስረዳትና በመረዳት መካከል ያለውን ክፍተት የሚያሰፋውና የሚያጠበው፣ በሚወረወረው መልእክትና በሚፈጠረው ምላሽ መካከል ያለውን የተገቢነት ምጣኔ የሚለካው አንዱ ነገር – የቋንቋው ጣዕም ነው፡፡
 
ልክ እንደ ምግብ ጣዕም፡፡ አንድ ሰው አንድን ምግብ ለጤና ተስማሚ፣ የተመጣጠነ ምግብ የያዘ፣ በውድ ዋጋ የተገዛ ስለሆነ ብቻ አይመገበውም፡፡ እጅ የሚያስቆረጥም፣ ምላስ የሚያስቀረጥፍ፣ ሰሐኑን ብሉት ብሉት የሚያሰኝ የሚባልለት ሌላ ነገር ያስፈልገዋል – ጣዕም፡፡ ከአሠራሩ፣ ከይዘቱ፣ ከቁሌቱ፣ ከቅመሙ፣ ከውሕደቱ፣ ከአበሳሰሉ፣ ከቅንብሩ የሚመጣ፡፡ ለዚህም ነው መጋቢዎችና አስመጋቢዎች ከምግቡ ይዘት ባሻገር ለምግቡ ጣዕምና ለምግቡም አቀራረብ የሚጨነቁት፡፡ በምግብ ሂደት አንዱ ወሳኝ ነገር በምግቡና በበላተኛው መካከል ያለው ክፍተት ነው፡፡ በላተኛውን ወደ ምግቡ የሚወስደው፣ ያንን ምግብ እንዲመርጥ፣ ከመረጠም በኋላ ወዶትና ጣፍጦት እንዲበላ የሚያደርገው ነገር ነው – ይኼ በምግብና በበላተኛ መካከል ያለው ነገር፡፡ የገዛነውን ሁሉ ወደ ሆዳችን አንልከውምኮ፤ ገዝተነው የማንበላው ምግብ አለ፡፡ 
 
ከፍትፍቱ ፊቱ የሚለው ነገርኮ እንዲሁ አልመጣም፡፡ ያ ሁሉ ጣዕም ያለው ምግብ ቢዘጋጅ እንኳን ‹‹ብሉልኝ፣ ጠጡልኝ፣ በሞቴ፣ አፈር ስሆን፣›› እያለ ጠብ እርግፍ ብሎ የሚጋብዝ፣ ፊቱ ለምግብ የተፈጠረ ጋባዥ ካላገኘ ያቅራል ማለት ነው፡፡ ‹ሲያዩት ያላማረ ሲበሉት ያቅራል› እንዲሉ፡፡ እስኪ አስቡት እንደ ድሮ የአንደኛ ክፍል አለቃ፣ አርጩሜ ይዞ የተኮሳተረና ‹ብላ! አርፈህ ብላ! ውሰድ! ከቀይ ወጡ ውሰድ! አልጫ ጨመር! ዋ!›› የሚል አስተናጋጅ ከጎኑ የቆመበት ግብዣ ቢገጥማችሁ እንዴት ነው የሚበላችሁ፡፡ 
 
ንግግርም እንደዚያው ነው፡፡ ቀልዶች፣ ምሳሌዎች፣ ሰምና ወርቆች፣ አባባሎች፣ ግጥሞች፣ ተረቶች፣ ዘይቤዎች የተፈጠሩት ቃላት ቃላት ስለሆኑ ብቻ የልባችንን ስለማይገልጡት ነው፡፡ የንግግር ዜማ፣ የአወራር ዘይቤ፣ የአገላለጥ መንገድ፣ የነገር ክዋኔና  የአነጋገር ቃና ንግግሩ እንዲሰማ ሳይሆን እንዲበላ ያደርገዋል፡፡ ከሆድ ጠብ እንዲል፣ አንጀት እንዲያላውስ፣ ቁጣን አቀዝቅዞ፣ ፈገግታ እንዲጨምር፣ ኀዘንን አስረስቶ ደስታን እንዲያስከትል ያስችለዋል፡፡ 
 
ያቺ በመስኮቱ ጥግ የነበረችው ሴት እንዲህ ብላ ነበር ለጓደኛዋ ምሳሌ የሰጠቻት፡፡
ዛሬ ጠዋት የተነጋገርነውን ነገር ልንገርሽ፡፡
ደወለና ‹ልጆቹን ዛሬ ማነው ከትምህርት ቤት የሚያወጣቸው?›
‹አንተ አትችልም እንዴ?›
‹አልችልም›
‹ምን ይሻላል?›
‹እንትና ያውጣቸው ንገሪው›
‹አንተ ብትደውልለት አይሻልም?›
‹አንቺ ደውዪ›
‹ስልኩን ትሰጠኝ?›
‹ቴክስት አደርጋለሁ›
‹ኦኬ›
‹ቻዎ›
አሁን እዚህ ውስጥ ፍቅር፣ ናፍቆት፣ ደግነት፣ ቤተሰባዊነት፣ ኀዘኔታ፣ አክብሮት፣ ባልነት፣ ሚስትነት አሉ? አሁን ይኼ ንግግር በሁለት አማርኛ በሚችሉ ሰዎች መካከል የተደረገ መሆኑን እንጂ በሚዋደዱ ባልና ሚስት መካከል የተደረገ መሆኑን የሚያሳይ አንዳች ነገር ልታሳዪኝ ትችያለሽ፡፡ እንዲህ ነውኮ ሁሌም የምናወራው፡፡ ቃላት መለዋወጥ ብቻ፡፡ ዜማ የለው፣ ፍቅር የለው፣ አክብሮት የለው፣ ትኅትና የለው፣ ናፍቆት የለው፡፡ ባዶ ቃላት ብቻ፡፡ የተሰበሰበ ድንች፡፡
 
‹የተሰበሰበ ድንች› ነበር ያልኩት ለራሴ፡፡ ‹እምቦቲቶ› ሲበላ እንኳን በሚንተከተክ ብረት ድስት ተቀቅሎ፣ በሚጥሚጣ፣ በቁንዶ በርበሬ፣ በጨው ጣፍጦ ነው፡፡ ‹የተሰበሰበ ድንች› አለች፡፡ አንድ የቢሮ ጓደኛዬ ምን እንዳለችኝ ልንገርሽ.. ስትል የመውረጃ ቦታችን ደረስን፡፡ – ካዛንቺስ፡፡ ወረድን፡፡ ወደ ኡራኤል አቅጣጫ እየወረዱ ተረከችላት፡፡
(ይቀጥላል)
    

አንድ ወዳጄ በየገጸ ድሩና በየውይይት መድረኩ የሚሰማውን ‹መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ፣ መጀመሪያ ትግሬ ነኝ፣ መጀመሪያ አማራ ነኝ› የሚል ክርክር አየና ‹አንተ መጀመሪያ ምድንነህ?›› ሲል ጠየቀኝ፡፡ 

እኔ መጀመሪያ ሰው ነኝ፡፡ የተፈጠርኩትም ሰው ሆኜ ነው፡፡ አምላክም የፈጠረው ሰውን ነው፡፡ ቡድን፣ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ጎሳ፣ ነገድ የሚባሉ ነገሮችን ፈጠረ የሚል መጽሐፍም ትምህርትም አላገኘሁም፡፡ ክብርም፣ ሥልጣንም፣ ጥበብም፣ ፈጣሪውን መምሰልም የተሰጠው ለሰው ነው፡፡ መላእክት ሲፈጠሩ በማኅበር ነው የተፈጠሩት፡፡ አንድ ላይ ነው የተገኙት፡፡ ሰው ግን ሲፈጠር በየተራ ነው፡፡ መጀመሪያ አዳም፣ ከዚያ ሔዋን፣ ከዚያ ቃየል፣ ከዚያ አቤል እያለ ተራ በተራ፡፡ ቡድኖቹን ሰው በኋላ ራሱ ፈጠራቸው እንጂ አብረውት አልተፈጠሩም፡፡
መጀመሪያ ሰውነቴ ነበረ፡፡ በኋ ቡድኔ መጣ፡፡ በኋላ የመጣው ቡድኔ በፊት የነበረውን ሰውነቴን ከዚህ አትለፍ ከዚህ አትውጣ፣ ከዚህ አትዝለል ከዚህ አትሻገር አለው፡፡ ቡድኔ በእኔ መጠራት ሲገባው እኔ በቡድኔ ተጠራሁ፡፡ ለእርሱ ህልውና ሲል እኔን ሰዋኝ፡፡ እርሱ ሳይመጣ በፊት ግን እኔ ሰውዬው ነበርኩ፡፡

መጀመሪያ ሰው ስለነበርኩ መጀመሪያ ሰው ነው መከበር ያለበት፣ መጀመሪያ ሰውነቴ ነው መብት የሚያስፈልገው፣ ሰውነቴን አሥረህ፣ ገርፈህ፣ ገድለህ፣ ነጥቀህ፣ ቀምተህ ቡድኔን ከየት ታገኘዋለህ? እኔን ትተህ እንዴት እኔ ለፈጠርኩት ቅድሚያ ትሰጣለህ? እኔን ንቀህ እንዴት እኔነት ተሰባስቦ ላቋቋመው ቡድን ክብር ትሰጣለህ? ይኼማ ሐሰት ነው፡፡ ሴሎቹን ገድለህ ሰውየውን ማኖር ትችላለህ? ገጾቹን ገንጥለህስ መጽሐፉን ታኖራለህን? ከብቶቹን አርደህ ስለ መንጋው መጨነቅስ ምን ማለት ነው?
ሀገር ይቀየራል፣ ቋንቋ ይቀየራል፣ ባሕል ይለወጣል፣ እምነት ይለወጣል፣ ጎሳ ይለወጣል፤ ሰውነት ግን እኔ ነኝ፡፡ እነዚህን ሁሉ መቀየር የቻልኩት ሰው ስለሆንኩ ነው፡፡ ሰው ሆኜ ስለተፈጠርኩ ከሰዎች ጋር እኖራለሁ፡፡ ለብቻዬ የማልችላቸውን  ነገሮች በጋራ ለመከወን፡፡ ያን ጊዜ የጋራ መግባቢያ ያስፈልገኛል፡፡ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ልማድ፣ ወግ፣ ሥርዓት ይመጣሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ሰዎችን በጋራ ለማኖር፣ ሲኖሩም ተግባብተውና የጋራ የሆነ እሴት ኖሯቸው እንዲኖሩ ለማድረግ በእኔ በሰውየው የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ሊተውኝ አይችሉም፤ ልተዋቸው ግን እችላለሁ፡፡ ያለ እነርሱ መኖር እችላለሁ፤ ያለ እኔ መኖር ግን አይችሉም፡፡ እኔ ነኛ ዋናው፡፡
ስለዚህ ነው መጀመሪያ ሰው ነኝ ያልኩት፡፡ ሰው ስለሆንኩ የሰው ሁሉ ነገር ይመለከተኛል፡፡ የሰውም ሁሉ ነገር ያሳስበኛል፡፡ ያ ሰው ማንም ይሁን፣ ምንም ዓይነት ቋንቋ ይኑረው፤ የትኛውንም ዓይነት ባሕል ይከተል፡፡ እርሱ እኔና እርሱን አያገናኘንም፡፡ መገናኛችን ሰውነት ነው፡፡ የእሥረኛው ነገር ይመለከተኛል፤ ምክንያቱም ሰው ስለታሠረ፤ የሟቹ ነገር ይቆረቁረኛል፤ ምንያቱም ሰው ስለሞተ፤ የተገፋው ልቅሶ ይሰማኛል፤ ምክንያቱም ሰው ስለተገፋ፤ የተቀማው ዕንባ ያርሰኛል፤ ምክንያቱም ሰው ስለተቀማ፡፡
እንደሰው በፈጠረው ነገር መልሶ የሚጠፋ፣ በሠራው ነገር መከራ የሚያይ፣ ባመጣው ነገር የሚሄድ፣ ባስገኘው ነገር የሚታሠር ፍጡር የለም፡፡ ራሱ ያመጣቸው ጎሳዎች፣ ነገዶች፣ ቡድኖች ራሱን እንዳያይና የተፈጠረበትን እንዲረሳ አድርገውታል፡፡ ሰው ሆኖ ተፈጥሮ ሰውነትን እንዲረሳ፡፡  ‹እገሌ እንዲህ ሆነ› ሲሉት ‹ሀገሩ የት ነው፣ የማን ወገን ነው፣ የኛ ሰው ነው፣› ጎሳ ነገዱ፣ ወንዙ ጎጡ እያለ እያጠበበ ይጠይቃል፡፡ የሰውየው ማንነት ከእርሱ ቡድን እየራቀ በሄደ ቁጥር ጭንቀቱ ይቀንሳል፡፡ አንዳንዴም እንደ ድል ይቆጥረዋል፡፡ ‹የራሱ ወገን› የተጠቃ ሲመስለው ግን አራስ ነበር ሆኖ ይነሣል፡፡ ራሱ በፈጠረው አጥር ራሱን አጥሮ፤ መገናኛውን ሰውነትን ሰብሮታል፡፡ ያም ሰውኮ ሰው ነው፡፤ መጀመሪያ ሰው ነው፡፡ ሰው ስለሆነ ነው እንደዚያም የሆነው፡፡ ሃይማኖት የኖረው ሰው ስለሆነ ነው፣ ባሕልም የኖረው ሰው ስለሆነ ነው፣ በቋንቋም ያወራው ሰው ስለሆነ ነው፡፡ የተለየ አመለካከትም የያዘው ሰው ስለሆነ ነው፡፡ የሚቃወምህም ሰው ስለሆነ ነው፡፡ መጀመሪያ ሰው ነው፡፡
ያኛው ባሕል፣ ያኛው እምነት፣ ያኛው ቋንቋ፣ ያኛው አስተሳሰብ፣ ያኛው ልማድ፣ እንዲከበር፣ መብቱም እንይደፈር፣ ዋጋም እንዳያጣ የምፈልገው – የሰው ስለሆነ ነው፡፡ እዚያ ውስጥ ሰው ስላለበት ነው፡፡ የዚያኛው ፓርቲ፣ የዚያኛው ማኅበር፣ የዚያኛው ቡድን መብትና ክብር እንዲጠበቅ የምሟገተው ስለማምንበት፣ ስለምቀበለውና ስለሚስማማኝ አይደለም – ሰው ስላለበት ነው፡፡ የሰው ስለሆነ ነው፡፡ በተለየ መንገድ የተደራጀው፣ በተለየ መንገድ ያሰበው፣ በተለየ መንገድ የሄደው፣ በተለየ መንገድ ያመነው፣ በተለየ መንገድ የተፈላሰፈው ሰው ስለሆነ ነው፡፡
ልዩነቱን እንኳን መፍጠር የቻለ – ሰውኮ ነው፡፡ ሌሎቹ ፍጡራን ልዩነታቸው ተፈጠረላቸው እንጂ ልዩነትን አልፈጠሩትም፡፡ ሰው ግን ባሕል፣ ቋንቋ፣ ልማድ፣ ሥርዓት፣ ሀገር፣ አመለካከት፣ አስተሳሰብ የሚባሉ ነገሮችን አምጥቶ የገዛ ልዩነቱን ራሱ የፈጠረ ነው፡፡ ለምን? ቢሉ ሰው ስለሆነ፡፡ እነዚህ ሁሉ የሚከብሩት ሰው ሲከብር ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ህልው የሚሆኑት ሰው ህልው ሲሆን ነው፡፡ አማራ ሆኖ፣ ኦሮሞ ሆኖ፣ ሶማሌ ሆኖ፣ ሕንድና ቻይና ሆኖ፣ እንግሊዝና ጣልያን ሆኖ የተወለደ የለም፡፡ ሁሉም ሰው ሆኖ ነው የተወለደው፡፡ ባሕሉን ለመደው፣ ቋንቋውን ለመደው፣ አለባበሱን ለመደው፣ ሀገሩን ለመደው እንጂ ራቁቱን፣ ቋንቋ ሳያውቅ፣ ወገን ሳይኖረው ነው የተወለደው፡፡
አሁን አሉኝ የምላቸው ልዩነቶች በሙሉ ቢነሡ፣ ከልዩነቶቹ ሥር እኔ ሰውዬው ብቻዬን ቆሜ እገኛለሁ፡፡ ሰው ነኛ፡፡ መጀመሪያም ሰው ነኝ፤ መጨረሻ ሰው ነኝ፡፡ 


‹ሐተታ ዘርአ ያዕቆብ› የተሰኘውን መጽሐፍ በተመለከተ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ(እድሜያቸውን ያርዝምና) ከመልካም ሐተታ ጋር አዘጋጅተውታል፡፡ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ማን ጻፈው? ዘርአ ያዕቆብ ማነው? ትውልዱስ የት ነው? ፍልስፍናው ከየት መጣ? እውነት ኢትዮጵያዊ ነው ወይስ የውጭ ሰው? ኢትዮጵያዊ ነው ብሎ ለመከራከር በመጽሐፉ ውስጥ ማስረጃዎች አሉን? የሚሉትንና ሌሎች ጥያቄዎችን አንሥተው ይተነትናሉ፡፡ መጽሐፉንም ተርጉመውና አትተው አቅርበውታል፡፡ የሚከተለውን ሊንክ ተጫኑና በነጻ አንብቡት፡፡

ፎቶ – ሐራ ተዋሕዶ

ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያንን ሕግ በተመለከተ አሠረ ሐዋርያትን የተከተለ ሆኖ እንዲጸድቅ አድርጓል፡፡ አባቶቻችን በቤተ ክርስቲያን ላይ ግለሰባዊ አምባገነንነትን አልፈቀዱም፡፡ ጸሎተ ሃይማኖቱም ‹ነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት›› በማት ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ዘሐዋርያት መሆንዋን ያመለክታል፡፡ በ50/51 ዓም በኢየሩሳሌም የተሰበሰበችው ሲኖዶስም ‹እኛና መንፈስ ቅዱስ› አለች እንጂ  ‹እኔ› የሚል ግለሰባዊ ድምጽ አልተሰማባትም፡፡
ኢትዮጵያውያን አበው የቅዱስ ሲኖዶስን ሥርዓት ብቻ ሳይሆን ሌሎችን የቤተ ክርስቲያን የአመራር ሥርዓቶች ከግለሰብ አምባገነንነት ለማውጣት መልካም የሆነ ሥርዓት ሠርተዋል፡፡ ቅዳሴው በአምስት ልዑካን እንዲሆን፣ አጥቢያው በሰበካ ጉባኤ እንዲመራ፣ ገዳማት በምርፋቅ (ጉባኤ አበው) ወይም በማኅበር እንዲመሩ፣ ጵጵስናን አንድ ጳጳስ (ፓትርያርክ እንኳን ቢሆን) ብቻውን እንዳይሰጥ፣ ቢያንስ ሦስት አበው ሊኖሩ እንደሚገባ፤ አንድ አባት ብቻውን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንዳይለውጥ፤ አድርገው የሠሩበት አንዱ ምክንያት ግለሰባዊ አምባገነንነትን ለመቋቋም እንዲቻል ነው፡፡
ይህንን ማኅበራዊና ጉባኤያዊ የሆነ የቤተ ክርስቲያን አሠራርና አመራር ለማስወገድ በየዘመናቱ ጥረት ተደርጓል፡፡ የዚህም ምክያቱ ግልጽ ነው፡፡ ግለሰባዊ የሆነ አመራር ለሦስት ነገሮች የተጋለጠ ነውና፡፡ የመጀመሪያው ክህደትንና ኑፋቄን ለማስገባት ይመቻል፡፡ አንዱ ወሳኝ ሌላው ‹ኦሆ በሃሊ› ስለሚሆን እርሱ ትክክል ነው ያለው ትክክል፣ ስሕተት ነው ያለው ደግሞ ስሕተት ይሆናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጉባኤያዊት በመሆንዋ አንዳንድ ግለሰቦች በየዘመናቱ ያመጡትን ክህደት በጉባኤ ተመልክታ በጉባኤ ለማውገዝ ጠቅሟታል፡፡ ደገኛ ትምርትና ድርሰት ሲገኝ ደግሞ እንዲሁ በጉባኤ ተመልክታ ለመቀበል ረድቷታል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ መጽሐፈ ምሥጢርን ጽፎ በጨረሰ ጊዜ ጉባ ሊቃውንቱ ተመልክተው ‹አማንኬ ዮሐንስ አፈወርቅ ወቄርሎስ አፈ በረከት ተንሥኡ በመዋዕሊነ፡፤ ኢትዮጵያ ተመሰለት በቁስጥንጥንያ፤ ወተአረየታ ላዕለ እስክንድርያ – በእውነት ዮሐንስ አፈወርቅና አፈ በረከት የሆነው ቄርሎስ በዘመናችን ተነሥተዋ፡፡ ኢትዮጵያም ቁስጥንጥንያን መስላለች፤ ከእስክንድርያም ልቃ ከፍ ከፍ ብላለች›› ብለው ምስክርነታቸውን ሰጥተው ነበር፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ለሌሎች አካላት ቁጥጥር ስለሚመች ነው፡፡ ጌታችን አስቀድሞ ኃይለኛውን ማሠር እንዳለው መሪውን የያዘ ቤተ ክርስቲያኒቱን አን ልቡ ለመዘወር ይመቸዋል፡፡

ይኼ ነገር በዘመነ ሱስንዮስ ጊዜ ታይቷል፡፡ ሮማውያን ግብጻዊውን ጳጳስ በሮማዊ ጳጳስ በመተካት ቤተ ክርስቲያኒቱን በሮማዊ ጳጳስ ለማስመራትና ለመቆጣጠር ፈልገው ነበር፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጠባይ ማኅበራዊና ጉባኤያዊ በመሆኑ ጉባኤ ሊቃውንቱ ከግብጹ ጳጳስ ጋር ሆኖ ተቃወማቸው፡፡ ጳጳሱና ሊቃውንቱም እስከ ደም ማፍሰስ ድረስ መሥዋዕት ሆኑ፡፡ ጥቅምት 19 ቀን 1621 ዓም በምዕራብ ጎጃም በምትገኘው ደብረ መዊዕ የተሰበሰቡት የቤተ ክርስቲያን ማኅበርተኞች ለዚህ ማስረጃ ናቸው፡፡ በዚህ የደብረ መዊዕ ጉባኤ እስከ 7000 የሚደርሱ ምእመናን፣ ካህናት፣ መነኮሳትና ሊቃውንት ተሰባስበው ነበር፡፡ የጉባኤው መሪዎችም እነ አባ ተስፋ ኢየሱስ፣ አባ ዘጊዮርጊስ ዘዋሸራ፣ አባ እንጦንዮስ፣ አባ ግርማ ሥሉስ ዘውይት ነበሩ፡፡ የጉባኤው አፈ ጉባኤ ደግሞ አባ ግርማ ሥሉስ ነበሩ፡፡በዚህ ጉባኤ የተገኙት ሁሉ ንጉሡንና አዲሶቹን ሮማውያን የሃይማኖት መሪዎች ተቃውመው እንደ አንድ ልብ መክረው እንደ አንድ ቃል ተናግረው በተዋሕዶ ጸኑ፡፡ የንጉሥ ሱስንዮስም ጦር ጥቅምት 19 ቀን ከብቦ ፈጃቸው፡፡ 
እነዚህ ጽኑአን ጉባኤተኞች ነበሩ በኋላ ዐፄ ሱስንዮስ ሐሳባቸውን እንዲቀይሩና ‹ፋሲል ይንገሥ፣ ሃይማኖት ይመለስ› እንዲሉ ያደረጋቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንደ መኪና መሪውን የያዘ መኪናውን ወደ ፈለገው ሊወስደው የሚችልባት ቦታ ብትሆን ኖሮ ዘመነ ሱስንዮስን መሻገር ባልቻለች ነበር፡፡ 
ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ዘመን የፈቀደለት ሁሉ ልቡ የወደደውን በቤተ ክርስቲያን ላይ እንዳይጭን ነው፡፡ በተለያዩ ዘመናት የተነሡ መንግሥታት ለራሳቸው የሚመቻቸው መሪ በቤተ ክርስቲያን ላይ ለማስቀመጥ ሞክረው ነበር፡፡ የቤተ ከርስቲያን አሠራር፣ ሕግና ሥርዓት ግን በአንድ ሰው የሚዘወር ባለመሆኑ ገመዱን ከመበጣጠስ ያለፈ ጀነሬተሩን ማቋረጥ አልተቻላቸውም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ውሳኔዎችም በጉባኤ እንጂ በአንድ ሰው ኅሊና ብቻ የሚወሰኑ ባለመሆናቸው አስተዳደራዊ ጥቅም ከማግኘትና በደል ከማድረስ ባለፈ አጥንቷን ለመስበር ዐቅም አላገኙም፡፡ 
ይህንን ታሪካዊና ቤተ ክርስቲያናዊ ሐሳብ ጠንቅቆ በመረዳት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ ግለሰባዊ አምባገነንነት የሚወስደውን  መንገድ በማረም የቤተ ክርስቲያኒቱ ራስ ክርስቶስ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱም የበላይ ወሳኝ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ መሆኑን በሕገ ቤተ ክርስቲያን አጽንቶታል፡፡ 
የሀገራችን ሰው ሲተርት ‹የማያለቅስ ልጅ በእናቱ ጀርባ ይሞታል› ይላል፡፡ ይራበው አይራበው፣ ይታፈን አይታፈን፣ ይመመው አይመመው፣ ይመቸው አይመቸው አይታወቅምና፡፡ ምናልባትም ዝምታው እንደ ጨዋነት ታስቦለት ዘወር ብሎ የሚያየው ላይኖርም ይችላል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በቤተ ክርስቲያን ላይ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ላይና በሊቃነ ጳጳሳት መብት ላይ፣ ቤተ ክርስቲያንን ሊያገለግሉ በተነሡ ማኅበራትና ወጣቶች ላይ፣ በየገጠሩ በተሠማሩና የመከራ ገፈት በሚቀምሱ ካህናትና ምእመናን ላይ የሚደርሰውን በደልና ጫና እየሰሙና እያዩ ዝም ቢሉ በእናታቸው ጀርባ ላይ ሆነው መሞታቸው የማይቀር ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን መብት ለማስከበር ደግሞ አስቀድሞ የቅዱስ ሲኖዶሱ መብት መከበር አለበት፡፡ ያልቆመ አንገት ራስን አይሸከምም እንዲሉ፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አንድ ሆነው የቅዱስ ሲኖዶሱን መብት እንዳስጠበቁትና ቤተ ክርስቲያኒቱንም ከግለሰብ አገዛዝ እንደታደጓት ሁሉ በአጠቃላይ የሰበካ ጉባኤውና በቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤ የቀረቡትን በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሱ ያሉ ችግሮችን አንድ ሆነው ለመፍታት በቀጣይ  መነሣት አለባቸው፡፡    

ዓርብ ዕለት የተከበረውን የአቡነ አረጋዊ በዓል ለማክበር አውስትራልያ አደላይድ ነበርኩ፡፡ እዚያ ከተማ የሚገኝ አንድ የድሮ ወዳጄ በፌስ ቡክ አገኘኝና አደላይድ መሆኔን ነገርኩት፡፡ ‹‹የት እንገናኝ›› ሲለኝ ‹‹ነገ (ቅዳሜ) የአቡነ አረጋዊን በዓል ለማክበር ስለምሄድ እዚያ እንገናኝ›› አልኩት፡፡ ‹‹አንተም እርሱን በዓል ታከብራለህ?›› አለኝ፡፡ በዓይነ ኅሊናየ ራሱን እየነቀነቀ ታየኝ፡፡ ‹‹እንዴት?›› አልኩት፡፡ ‹‹የእነ እንትና ታቦት አይደል እንዴ›› አለኝ የሆነ የኢትዮጵያ አካባቢ ጠርቶ፡፡ ‹‹ማን እንደዚያ አለ?›› ስል ጠየቅኩት፡፡ ‹‹ምን፣ የታወቀኮ ነው›› አለኝ፡፡ እየገረመኝ ተለያየን፡፡

በማግሥቱ በዓሉ ላይ ተገኘሁ፡፡ በዓሉን እኩለ ቀን ላይ ጨርሼ ስወጣ ሌላ የጥንት ዘመዴን አገኘሁት፡፡ ያ ትናንት ማታው ጓደኛዬ እዚህ ከተማ እንዳለ የማላውቅ መስሎት ይኼኛው ነገረኝ፡፡ እኔም ሰው ላለማጋጨት ብዬ ያለኝን ሳልዘረዝር እንዴው በደፈናው ደውዬለት መምጣት አልችልም እንዳለኝ ነገርኩት፡፡ ይኼኛውም እኔ እንዳልነግረው የደበቅኩትን እርሱ ገልብጦ ነገረኝ ‹‹የኛ ታቦት ሲሆንኮ እነ እንትና አይመጡም›› አለኝ ፈገግ እያለ፡፡ ‹‹ማን ነው የእናንተ ታቦት ያደረገው›› አልኩ በአግራሞት›› ‹‹ያው አቡነ አረጋዊ የኛ ሀገር ሰው አይደሉ›› አለኝ የሠፈሩ ሰው ያህል ርግጠኛ ሆኖ፡፡ ወይ ግሩም፣ ይኼ በሽታ ለካ ማናችንንም ሳይለይ በደንብ ይዞናል አልኩ በልቤ፡፡

ጋሽ ግርማ ከበደ ‹‹ሰው የሚጠላውን ኃጢአት ደጋግሞ ይሠራዋል›› ይል ነበር፡፡ ብዙዎቻችን የሌላውን ሰው ዘረኛነት ለመግለጥ የምንጠቀምበት መንገድ ራሱ ዘረኛ ነው፡፡ አሁን እየተጓዝንበት ያለው አቅጣጫ በመካከላችን ምንም ዓይነት የጋራ ነገር እንዳይኖረን የሚያደርግ ነው፡፡ የጋራ ሆነው የቆዩትን ነገሮች እንኳን አሁን አሁን ወደ ራስ መውሰድ፣ አለበለዚያም ደግሞ የሌላው ብቻ አድርጎ ከራስ ክልል ማስወጣት ጀምረናል፡፡ ምንም እንኳን የኔታ እሸቱ ‹‹የጎጥ ጀግና የለም፤ ጀግና ከሆነ የሁላችንም ነው፤ ያለበለዚያ ደግሞ ጀግና አይደለም›› ቢሉም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ምንኖርባትንና የቆምንባትን ኢትዮጵያ ያወቅናት አልመሰለኝም፡፡ ከሰሜን የጀመረ መስቀል ደቡብ፣ ከደቡብ የጀመረ ቆጮ ሰሜን በዘለቀባት ሀገር፤ የኮንሶ የእርከን ሥራ የትግሬ ገበሬ ገንዘብ፣ የትግራይ አምባሻ የደቡብ የቅንጦት ምግብ በሆነባት ሀገር፣ የኦሮሞ ጉዲፊቻ የሁሉም ባህል በሆነባት ምድር፣ ይኼ የእነ እገሌ ብቻ ነው፣ እኛን አይመለከትም ብሎ ለመናገር እንደመድፈር ያለ የአላዋቂ ድፍረት የለም፡፡

ማንኛውም ነገር መነሻ ይኖረዋል፡፡ ዓባይ ከግሼ ዓባይ እንደሚመነጨው፡፡ ነገር ግን መነሻው መድረሻው አይደለም፡፡ ዓባይ ከግሼ ዓባይ ስለመነጨ የጎጃም ቀርቶ የኢትዮጵያ ብቻ ሊሆን አልቻለም፡፡ አዋሳኙ ሁሉ የእኔም ነው ብሎ ሲመክርበት ይኖራል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ የተጀመሩትን ኦሪትን፣ ክርስትናንና እስልምናን የኛ አድርገን እየኖርንባቸው አይደል እንዴ ? ከአውሮፓ የወረስነውን ኮትና ሱሪ ቂቅ ብለንበት እየተዳርንበት አይደለም እንዴ? በፖርቹጋሎች በኩል ከሜክሲኮ የደረሰን በርበሬ ይኼው የአበሻ መለያ ሆኖ የለም እንዴ፤ የአውስትራልያ ባሕር ዛፍ ኢትዮጵያዊ ሆኖ የለም እንዴ፤ እንዴት ነው ጎበዝ፡፡ ጤፍ ለምግብነት ዋለ የሚባለው ከክርስቶስ ልደት በፊት 5000 ዓመት ቀደም ብሎ በሰሜን ደጋማ ቦታዎች ነው፡፡ ዛሬ ግን ይኼው ድፍን ሐበሻ ባሕሉ አድርጎት፤ ዘልቆም ድፍን ዓለም ሊበላው እየተሻማ ይገኛል፡፡ የሰሜን ነው ብሎ ማን ተወው፡፡

መልካም ነገር ከአንድ ቦታ ይነሣል፡፡ ከዚያም ሌላውም ከባሕሉና እምነቱ ጋር እያዛመደ ይዋረሰዋል፤ ወይም ገንዘብ ያደርገዋል፡፡ ከዚያም የእርሱም ጭምር ይሆናል፡፡ በተለይ በታሪካችን ውስጥ ከአንዱ የተነሣ ነገር ሰፍቶና መልቶ የሌላውም ገንዘብ የሆነበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ እንዲያውም በሚያስደንቅ መልኩ ከመነሻው ጠፍቶ ከመድረሻው የተገኘ ብዙ ነገር አለ፡፡

ከላይ መነሻዬ ከሆነው የአቡነ አረጋዊ ነገር ልጀምር፡፡ አቡነ አረጋዊ ሀገራቸው ኢትዮጵያ አይደለም፡፡ ሮማዊ ናቸው፡፡ በ5ኛው መክዘ ከተሰዓቱ ቅዱሳን አንዱ ሆነው ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ አቡነ አረጋዊ መጨረሻቸውን በደብረ ዳሞ፣ ትግራይ ቢያደርጉትም በወሎ፣ በጎንደር፣ በጎጃም፣ በሸዋና በደቡብ ታሪክ ውስጥ ግን አሉ፡፡ ደቡብ ጎንደር ውስጥ ጥንታዊው ገዳማቸውና የዝማሬ መዋሥዕት ማስመስከሪያው ዙር አባ አረጋዊ አለ፡፡ ጣና ቂርቆስ፣ አዲስ አበባ አጠገብ የሚገኘው የረር፣ እንዲያውም ከዚያ ተሻግሮ ጋሞጎፋ የምትገኘው ብርብር ማርያም ታሪካቸውን ከእርሳቸው ጋር ያገናኛሉ፡፡ የመጨረሻውና ታላቁ ገዳማቸው ደብረ ዳሞ ስለሆነ የኛ አይደሉም ብለው አያውቁም፡፡ የጎንደር ሊቃውንት በ17ኛውና በ18ኛው መክዘ ለዓመት የሚቆመውን ዚቅ ሲያዘጋጁ ቦታ ከሰጧቸው ቅዱሳን አንዱ አቡነ አረጋዊ ናቸው፡፡ የአቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱ ድንበር ጠባቂ ሆኖ ሞያሌ ላይ ይገኛል፡፡ ለሁለቱ ኢትዮጵያውያን የምንኩስና መሠረቶች ለአቡነ ተክለ ሃይማኖትና አቡነ ኢየሱስ ሞአ ምንኩስናን የሰጠው ደብረ ዳሞ ነው፡፡ ዋርካው ሲሰፋ እዩት፡፡

እንግዲህ እኒህን ከሁሉም በላይ ሆነው፣ የሁሉም የሆኑትን አባት ነው አንዳች ጎጥ ውስጥ ልንከታቸው መከራ የምናየው፡፡ ልክ አንዳንዶቹ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ከሸዋ ብሎም ከአማራ ጋር ለማያያዝ እንደሚሞክሩት፡፡ እንዲያውም በሚገርም ሁኔታ ገድላቸው የአያቶቻቸውን ጥንተ መሠረት ከትግራይ፣ በኋላም ከዋድላ ጋር ነው የሚያያይዘው፡፡ በኋላም ሥርዓተ ምንኩስናን የፈጸሙት በአምሐራና በሐይቅ እስጢፋኖስ(ወሎ)፣ በስተ መጨረሻም በደብረ ዳሞ(ትግራይ) ነው፡፡ በውስጣቸውም የትግራይ ገዳማትን የመጎብኘት ልዩ ፍላጎት ስለነበራቸው ለብዙ ዓመታት በዚያው በትግራይ እየተዘዋወሩ አገልግለዋል፣ ተሳልመዋልም፡፡ ታላቁንና የሰሜን ኢትዮጵያ የምንኩስና መሠረት ከሆኑት አንዱ የሆኑትን አቡነ መድኃኒነ እግዚእንም አመንኩሰዋል፡፡ እንዲያውም እዚያው ትግራይ ውስጥ ቀንጦራር በተባለ ቦታ(በደቡብ ምሥራቅ ትግራይ?) ለመቅረትና ገዳም ለመመሥረት ፈልገው ነበር፡፡

አያሌ የኤርትራና የትግራይ ገዳማት የምንኩስና ሐረጋቸውን ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚጀምሩትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ እንደ አጭር ማሳያ የዋልድባውን አቡነ ሳሙኤልና የቆየጻውን አቡነ ሳሙኤል መጥራቱ ብቻ ይበቃል፡፡ በጣና ገዳማት የሚገኙት የግድግዳ ላይ ሥዕሎች ሁለቱን አባቶች – አቡነ ተክለ ሃይማኖትንና አቡነ ኤዎስጣቴዎስን ጎን ለጎን ነው የሚሥሏቸው፡፡

ከሰሜን ተነሥቶ ደቡብ መምጣት፣ ከደቡብ ተነሥቶም ሰሜን መሄድ እንዲህ እንዳሁኑ ከባድ አልነበረም፡፡ እነ አቡነ ፊልጶስና አቡነ አኖሬዎስ ነገሥታቱ ሲያሳድዷቸው የተጠለሉት በትግራይ ገዳማት ነበር፡፡ የተጋዙትም ወደ ዝዋይና አርሲ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሠራዔው አቡነ ኤዎስጣቴዎስ እስከ ሸዋ ምድር ድረስ ደርሰው አስተምረዋል፡፡ የአኩስም ጽዮን ካህናት ከዮዲት መዓት ለማምለጥ ወደ ዝዋይ ነበር የመጡት፡፡ ያለ ሀገራችሁ፣ ያለ ክልላችሁ ያላቸው አልነበረም፡፡ በ14ኛው መክዘ በነበረው የሰንበት ክርክር ጊዜ የሞረቱ ዜና ማርቆስ ገዳም መነኮሳት በቦታ ከሚቀርባቸው ደብረ ሊባኖስ ገዳም ይልቅ የኤርትራ ገዳማት የያዙትን አቋም ደግፈው ነበር፡፡ የሙገርን ቅዱሳን ያስተማረው ሐራንኪስ የአኩስም ተወላጅ ሲሆን የቡልጋን ቅዱሳን ያስተማረው ሕይወት ብን በጽዮን ደግሞ የተማረውና የማስተማሪያ መጽሐፉን ያገኘው ከትግራይ ገዳማት ነው፡፡ እንዲያውም ለብዙ ዓመታት በትግራይ ገዳማት ቆይቶ ተምሮ ሲመለስ የተወለደባትን ዞረሬን ባያት ጊዜ ‹‹እንደ ሀገሬ እንደ አኩስም መሰለችኝ›› ነበር ያላት፡፡

በኤርትራ ታላቅ ቦታ ያላቸው አቡነ አብራንዮስ የጎጃም ሁለት እጁ እነሴ ተወላጅ ሲሆኑ፣ በምሥራቅ ጎጃምና በደቡብ ጎንደር ታላቅ ቦታ ያላቸው አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ደግሞ የኤርትራ ተወላጅ ናቸው፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ገበሬ በኤዎስጣቴዎስ ከማለ መላሽ የለውም፡፡ የሙገሩ አቡነ አኖሬዎስ በሸዋ የነበረው ገዳማቸው ሲጠፋ በላስታና በደቡብ ወሎ ግን  ገዳማቸው አሁንም በክብር አለ፡፡ እንዲያውም ልብሳቸው፣ መስቀላቸው፣ የጸሎት መጽሐፋቸው የሚገኘው ላስታ፣ ዋናው ገድላቸው የሚገኘው ተንቤን ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ አኩስም ቢወለድም ድጓው የሚገኘው ደቡብ ጎንደር ቤተልሔም፣ ዝማሬ መዋሥዕቱ የሚገኘው ደቡብ ጎንደር ዙር አምባ ነው፡፡ አሁን በያሬድ ዜማ ሲዘም ማን አኩስምነቱ ትዝ ይለዋል፡፡ የላስታው ላሊበላ በላስታ ካለው ደብር በላይ በምዕራብ ጎጃም ያለው ይልጣል፡፡ በዚያ ከአምስት በላይ በስሙ የሚጠሩ አድባራት አለው፡፡ በጉራጌ ትልቁን ሐዋርያነት የሠሩት የሰሜን ሸዋው አቡነ ዜና ማርቆስ ናቸው፡፡ በጎንደር ደግሞ ትልቁን ሥራ የሠሩት የጉራጌ ሊቃውንት ናቸው፡፡

በግራኝ አሕመድ ዘመን ከሆነው ጥፋት በኋላ ጎንደርን ሊያቀና የተነሣው ዐፄ ሠርፀ ድንግል ትልቅ ችግር የሆነበት ለጎንደር አድባራት የሚሆኑ ሊቃውንትን ማግኘት ነበር፡፡ በኋላ ግን እነዚህ ሊቃውንት ከጉራጌ ምሑር ኢየሱስ ገዳም ተገኙ፡፡ እነዚህ ‹‹አርባዕቱ ሊቃውንተ ምሑር›› በመባል የሚታወቁት አባ መሰንቆ ድንግል ዘቤተ ልሔም፣ አባ ለባዌ ክርስቶስ ዘዙር አምባ፣ አባ ብእሴ እግዚአብሔር እና መምህር ተክለ ወልድ ዘለገደባ ማርያም ናቸው፡፡ በላይ ጋይንት ደብረ ማርያም የሚገኘው ሃይማኖተ አበው ‹‹ዐርባዕቲሆሙ ኅቡረ፣ ቃላቲሆሙ ሥሙረ – አራቱም አንድ ነበሩ፣ ቃላቸውም የሠመረ ነበረ›› ይላቸዋል፡፡ እነዚህ ሊቃውንት ነበሩ እየተማከሩ ጎንደርን እንደገና አቅንተው የሊቃውንት መፍለቂያ ያደረጓት፡፡ በጎንደር ከተማ የዘር ነገር የማይነሳው ለዚያ ይሆን?

ከጎንደር ሳንወጣ ዛሬ አደባባይ ኢየሱስ የሚባለው ቤተ ክርስቲያን ታቦት ጥንት የነበረው ከምባታ ነበር፡፡ (በገድለ ተክለ ሃይማኖት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አካባቢው ባደረጉት ጉዞ መጀመሪያ የተከሉት ታቦተ ኢየሱስን መሆኑ ይናገራል፤ ምናልባት እርሱ ሊሆን ይችላል) በግራኝ ጊዜ በተፈጠረው ስደት ካህናቱ ተሰደዱ፡፡ ታቦቱንም በአንድ ቦታ ሠረወሩት፡፡ የመከራው ጊዜ ሲያልፍ ደብሩን እንደገና ቢደብሩትም ታቦቱን ግን ማግኘት አልቻሉም፡፡ በዐፄ ሠርፀ ድንግል ዘመን አባ ንዋይ የተባሉ አባት ወደ ከምባታ ወርደው ታቦቱ ያለበትን ቦታ ለ47 ዓመት ሲፈልጉ ቆይተው በ1570 ዓም አካባቢ አገኙት፡፡ ወደ ንጉሡም ይዘውት መጡ፡፡ ዐፄ ሠርፀ ድንግልም ያመፀውን ባሕረ ነጋሽ ይስሐቅንና ቱርኮችን ለመውጋት በዝግጅት ላይ ስለነበሩ በ1572 ዓም ደንቢያ ላይ እያሉ ከአባ ንዋይ ጋር ተገናኙ፡፡ በዚህ ጊዜ የባሕረ ነጋሽ የትዕቢት መልእክት ከሁለት ጥይት ጋር መጥቶላቸው ነበርና አንዱን በታቦተ ኢየሱስ፣ ሌላውን በግምጃ ቤት ማርያም ላይ አድርገው እንዲጸልዩበት አዘዙ፡፡

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ታቦተ ኢየሱስ ከንጉሡ አልተለየም፡፡ በ1572 ረዳዒ የተባለውን የቤተ እሥራኤል መሪ፣ በ1579 ጎሼን ለመውጋት ሲዘምቱ አብሮ ነበረ፡፡ በኋላ በዐፄ ፋሲል ዘመን አደባባይ ኢየሱስን ሠርተው ታቦቱን በዚያ አኖሩት፡፡ ይኼው ከከምባታ መጥቶ ጎንደር ላይ ተተክሎ ይኖራል፡፡ ልክ ወሎ መካነ ሥላሴ የነበረውና በግራኝ ተቃጥሎ ፍራሹ የሚታየው የመካነ ሥላሴ ታቦት አሁን አራት ኪሎ ሥላሴ ካቴድራል እንደሚገኝው ማለት ነው፡፡ የቁልቢ ገብርኤል ታሪክ ከአኩስምና ከቡልጋ ጋር እንደተያያዘው፡፡

መርጡለ ማርያምን ቤተ ክርስቲያንን ከግራኝ ዘመን ትንሽ ቀደም ብሎ ባመረ ሁኔታ እንደገና አሠርተዋት የነበሩት እቴጌ ዕሌኒ የሐድያ ተወላጅ ነበሩ፡፡ ሕዝቡ በደግነታቸው ስለሚወዳቸው በሞቱ ጊዜ ከሩቅ ሀገር ሳይቀር እየሄደ መርጡለ ማርያም ከመቃብራቸው ላይ ያለቅስ ነበር ይላል አልቫሬዝ፡፡

እንዴው ባጠቃላይ እንደ ዘሐ ዘጊ ወዲህና ወዲያ እንዲህና እንዲያ በተዋረሰውና በተወራረሰው ሕዝብ መካከል ‹‹የዚያ ብቻ›› ወይም ‹‹የእኔ ብቻ›› የሚል ነገር ማምጣት ካለ ማምጣቱ ይልቅ የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ እንኳን ደጉ ነገር ክፉው ነገራችን እንኳን ተዋርሶ ተዋርሶ የሁላችን ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን የራሳችን ቋንቋ፣ ባሕልና ማንነት ቢኖረንም፣ የበለጠ የሚያዋጣን የኛንም ሸጠን፣ የሌላውንም ገዝተን የተዋርሶና የተገናዝቦ ማንነት ብንፈጥር ነው፡፡ ከአጥሩ ይልቅ ድልድዩ ያተርፈናል፡፡ ሀገር እንደ ገና ዳቦ ስትያያዝ እንጂ እንደ ቡሄ ዳቦ ስትነጣጠል ዘላቂ አትሆንም፡፡

አደላይድ፣ አውስትራልያ

ርብራብ

ኃይለ ልዑልና ዶ/ር ብርሃነ ከቀድሞው የአውስትራልያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኬቪ ሩድ ጋር

በየሀገሩ ስዞር ለሀገራቸውና ለወገናቸው ልዕልና ያለው ሥራ የሚሠሩ፣ ወግ ያለው ታሪክ ያላቸው፡፤ ከመንደርተኛነትና ወንዘኛነት ድንበር ተነጥቀው በሉላዊነት መንበር ላይ የተቀመጡ፣ ከምድጃ ሥር ወሬ ርቀው ዓለም ተኮር ነገር ውስጥ የሚዘውሩ ዜጎቻችንን ሳይ ትፍትፍ እላለሁ፡፡ እሥራኤሎች በልዩ ልዩ ሀገር ሆነው ለሀገራቸው የሠሩ ዜጎችን ታሪክ ሲጽፉ ‹የኛ ሰው በዚህ ቦታ› የሚሉት ዓይነት ርእስ ይሰጣሉ፡፡ ‹የኛ ሰው በደማስቆ› እንዲል ማሞ ውድነህ፡፡

ባለፈው ኀሙስ ጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓም እናንተ አቦን ስታከብሩ እኔ ደግሞ እዚህ ሜልበርን ለየት ያለ ግብዣ ደረሰኝ፡፡ የጋበዘኝ የአፍሪካና አውስትራልያ ማኅበር(African Australian Association – AAA ) ዋና ዳይሬክተሩ በሆነው ኃይለ ልዑል ገብረ ሥላሴ በኩል ነው፡፡ ኃይለ ልዑል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ካበረከተቻቸው አዳጊ የማኅበረሰብ መሪዎች አንዱ ነው፡፡ ከ ላ ቶቤ የኑቨርሲቲ በ2000 በዓለም አቀፋዊ ልማት ማስተርስ ያገኘ፣ በ2008 ከሜልበርን ዩኒቨርሲቲ በማኅበረሰባዊ ፖሊሲና አስተዳደር በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀ ሰው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከ22 ዓመታት በፊት በሜልበርን እንድትተከል ከመልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን ጋር የተላከውና ዛሬ በአውስትራልያ ለምትገኘው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመሠረት ድንጋይዋን ያስቀመጠው ኃይለ ልዑል አፍሪካ በአውስትራልያ ገንዘብ፣ ዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንድትጠቀም በአውስትራልያ የሚገኙ የአፍሪካ ዳያስጶራዎችም አህጉራቸውን እንዲጠቅሙ ለማድረግ የተመሠረተውን የአፍሪካ አውስትራልያ ማኅበር ከመሠረቱትና ከሚመሩት ልሂቃን አንዱ ነው፡፡

በሚኖርበት በቪክቶርያ ግዛት ለአፍሪካውያን የመሪነት ኮርስ ለመስጠት የሚያስችል መርሐ ግብር እንዲቀረጽ ከዶክተር ብርሃን አሕመድ ጋር የተጋ፣ ሥራውም ውጤታማና ተቀባይነት አግኝቶ እስከ 2018 የሚዘልቅ መርሐ ግብር በቪክቶርያ መንግሥት የተያዘለት፤ እስካሁንም ከ30 የአፍሪካ ሀገሮች የመጡ 140 አዳጊ የአፍሪካ ማኅበረሰባዊ መሪዎችን በዚህ መርሐ ግብር ማስመረቅ የቻለ ፕሮጀክት ለመዘርጋት የቻለ ሰዋችን ነው፡፡

የፉት ስክሬይ ማኅበረሰብ የሥነ ጥበብ ማዕከል የቦርድ አባል፣ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን የአውስትራልያ ማኅበረሰቦች የሚያካትተው Ethnic Communities’ Council of Victoria ሊቀ መንበር፣ የአፍሪካ የሐሳብ ማዕከል (African Think Thank) ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ማኅበረሰቡን እያገለገለ ነው፡፡ ለዚህና ለሌሎቹ አገልግሎቶቹ  የዊኒስተን ቼርቺል ፌሎው – ሽልማት(2008)፣ የዊልያምሰን ማኅበረሰብ አመራር መርሐ ግብር- ሽልማት(2009)፣ የጋራ ብልጽግና አገሮች የሚኒስትሮች አማካሪ ኮሚቴ ለአፍሪካ – ሽልማት(2012)፣ እጅግ የተዋጣለት የማኅበረሰብ መሪ – ሽልማት(2011)፣ እንዲሁም በብዝሐ ባሕል የተዋጣለት ሥራ ለሠሩ የአውስትራልያ ሰዎች የሚሰጠውን (Meritorious service in the community) ሽልማት ከቀድሞው የቪክቶርያ ገዥ(Premier) በ2004 ተቀብሏል፡፡

በዓለም አቀፍ ትምህርትና ሥልጠና፡ ዕድሎችና ተግዳሮቶች

ዘንድሮ በሜልበርን ከተማ ቪክቶርያ ዩኒቨርሲቲ ኣዳራሽ የተካሄደው የአፍሪካ አውስትራልያ ማኅበር ዋና አጀንዳ በትምህርትና ሥልጠና ላይ ያተኮረ ነበር (Doing Business in Africa: Opportunities in International Education and Training)፡፡

በዚህ ጉባኤ ላይ ከቪክቶሪያ ግዛት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከኩባንያዎችና አፍሪካ ላይ ከሚሠሩ ተቋማት የመጡ ተወካዮች ሐሳቦቻቸውን፣ ሥራዎቻቸውንና ያጋጠማቸውን ነገር አቅርበው ነበር፡፡ በተለይም ባለ ሥልጣናቱ አውስትራልያ ከአፍሪካ ጋር እስከ ዛሬ የነበራት ግንኙነት ማዕድንን የተንተራሰ እንደነበርና ከ65 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሆነ የአውስትራልያ ኢንቨስትመንት በአፍሪካ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የትምህርት ግንኙነት ለአውስትራልያ 4ኛው የገቢ ምንጭ መሆኑንና ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በየዓመቱ ለሀገሪቱ ሲያስገኝ ከ100 ሺ ሰዎች በላይ ደግሞ በሥሩ ተሠማርተው ገቢ እያገኙበት መሆኑን ነግረውናል፡፡ አውስትራልያ ትምህርት አሰጣጧን በማስተካከል፣ የተሻለ ልምድ ካላቸው ሀገሮች ደረጃዎችን በመውሰድ፣ ለተማሪዎች የሚሻሉ መንገዶችን በመዘርጋት በዓለም ከሚመረጡ የትምህርት ተቋማት ወገን የሆኑ ተቋማትን ለመመሥረት መቻሏን ነግረውናል፡፡ ‹በዓለም ላይ የትምህርት ልዕለ ኃያል ሀገር – super power in Education› ብለዋታል፡፡ የትምህርት ጥራትና ደረጃ አካዳሚያዊ ነጻነትን፣ በባለሞያ የሚመራ የትምህርት ሥርዓትንና ገለልተኛ የሆነ ገምጋሚ አካልን እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡ እኔም የሀገሬን ከፍተኛ ተቋማት እንዳስብ አድርገውኛል፡፡


 በተለይም ከትምህርት ተቋማት የመጡት ባለሞያዎችና ባለሥልጣናት በአንድ ነገር ላይ ተስማምተው ሲናገሩ ነበር፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ላይ የበጀት፣ የሰው ኃይልና የአሠራር ድጋፍ በማድረግ የአውስትራልያ መንግሥት በየጊዜው የተሻለ ሥራ ቢሠራም ሁለት ነገሮች ግን ለውጤቱ እጅግ በጣም አስፈላጊ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ነገሮች ደግሞ የሚገኙት ከተማሪዎች ነው፡፡ እነርሱም ፍላጎትና የተፎካካሪነት ስሜት(Interest and Competitiveness)፡፡ የምዕራቡ ዓለም ተማሪዎች የተሻለ ትምህርትና የትምህርት መሣሪያዎች ቢሟሉላቸውም ፍላጎትና ተፎካካሪነትታቸው ግን የእስያ ተማሪዎችን ያህል መሆን አልቻለም፡፡ በዚህም የተነሣ በአነስተኛ ወጭና ባልተሟሉ ሁኔታዎች ውስጥ የሚማሩት የእስያ ተማሪዎች የተሻለ ፍላጎትና የተሻለ ተፎካካሪነት ስለሚያሳዩ በተሻለ በጀት ከሚማሩት የምዕራቡ ተማሪዎች ይልቅ በውጤትማነት የተሻሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የተከበሩ ፊል ሀኔውድ የተባሉ የሥነ ትምህርት ባለሞያና የአውስትራልያ ዓለም ዐቀፍ የትምህርት ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዳሉት ለተማሪዎች ውጤታማነት ወሳኞቹ ነገሮች ከውስጥ የሚመነጩት ሁለቱ ኃይሎች – ፍላጎትና የተፎካካሪነት ስሜት ናቸው፡፡

የአፍሪካ ተማሪዎች ለትምህርት ያላቸው ፍላጎትና ተፎካካሪነት የተሻለ በመሆኑ በአውስትራልያ ትምህርት ቤቶች በተመደበላቸው ትምህርት ጊዜ በመጨረስ የአፍሪካ ተማሪዎች ውጤታማ ሆነዋል፡፡ የሀገሬው ተማሪዎች የመጨረስ ዐቅም 70 ከመቶ ሲሆን የአፍሪካ ተማሪዎች ግን 94 በመቶ ነው፡፡

ይህንን ልምድ በመያዝም በስኮላርሺፕ ብቻ ከመገናኘት ይልቅ ከአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ለመሥራት እየጣሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እስካሁንም 20 የአውስትራልያ ዩኒቨርሲቲዎች ከ51 የአፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ግንኙነት በመመሥረት ይህንን ሥራ ለማስፋፋት እየሠሩ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በተመለከተ ከቴክኒክና ሞያ ኮሌጆች ድጋፍ ያለፈ ሪፖርት አልሰማሁም፡፡ በዚህ ረገድ ኬንያና ናይጄርያ የአንበሳውን ድርሻ መያዛቸው ነው የተነገረው፡፡

የአፍሪካ ተማሪዎች የበጀትና ትምህርት አመራር ድጋፍ ከተሰጣቸው የተሻለ ፍላጎትና ተፎካካሪነት አላቸው፡፡ በመሆኑም የአውስትራልያ ዩኒቨርሲቲዎች ከአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት በአውስትራልያ የትምህርት ደረጃና ጥራት የሚሰጡ መርሐ ግብሮችን በአፍሪካ ለመዘርጋት እየተሞከረ ነው፡፡ ይኼ ሁኔታ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መልካም ዕድል በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎቹ የሚጠየቁትን ዝግጅት ከኤምባሲው በመውሰድ በጋራ ለመሥራት ቢነሡ ሀገራቸውን ለመጥቀም ይችላሉ፡፡ ተማሪዎቻችንን እንዲህ ባለ ዕድልና ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንጅ በስብሰባ ብቻ ብቁ ዜጋ ማድረግ አይቻልምና፡፡

click here for pdf


ሚሲስ ጃኩሊን ዝዋምቢላ የተባሉ በዚምባብዌ የቀድሞ የአውስትራልያ አምባሳደር እንደገለጡት የአውስትራልያ ዩኒቨርሲቲዎች ገንዘብና የሰው ኃይላቸውን ይዘው፣ በአውስትራልያ ደረጃ ከአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት አራት መሠረታዊ ችግሮች ገጥመዋቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ብዙዎቹ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ሳይሆኑ የማስተማሪያ ዩኒቨርሲቲዎች (lecturing rather than research) መሆናቸው ከዓለም የጥናት ሥራዎች አስተዋጽዖ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች 1% ብቻ እንዲያበረክቱ አድርጓቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኞቹ የሚያሠለጥኑት ለመንግሥት ሥራ(educating for public sector) እንጂ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት በሚችሉ መስኮች አይደለም፡፡ ሦስተኛ ሆኖ የተነሣው የአፍሪካ ብዙዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸውን ችግር ሊፈታ የሚችል፣ ራስ ተኮርና ራስ ፈጠር የሆነ መንገድና ደረጃ በመከተል፣ ዘላቂና ወጥ የሆነ፣ ብሔራዊ ቀለም ያለው የትምህርት ፖሊሲና ስትራቴጂ ከመቅረጽና በርሱም በቁርጠኛነት ከመመራት ይልቅ አውሮፓ ተኮር(Euro centric) መሆናቸው ነው፡፡ አራተኛው ብዙዎቹ ሀገሮች ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቂ በጀት ለመስጠት ባለመቻላቸው  በአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃና በዩኒቨርሲቲዎች መካከል ያለው ልዩነት የሰርተፊኬቱ ደረጃ ብቻ እንዲሆን ማድረጉ ነው፡፡ በአንድ ጥናት ላይ እንደተመለከተው ከአፍሪካ ዓመታዊ ገቢ(GDP)1% ብቻ ለከፍተኛ ትምህርት ይመደባል፡፡

ፕሮፌሰር ዴቪድ ሞሪሰን የተባሉ የሞርዶክ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ምክትል ቻንስለር አውስትራልያ በሚከተሉት ጉዳዮች በአፍሪካ ትኩረት እንደሰጠች ገልጠዋል (በአውስትራልያ ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር ለምታስቡ ተማሪዎች ወይም በጋራ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለመሥራት ለምትፈልጉ ተቋማት)፡፡ በአርብቶ አድር ልማት፣ በእርሻና ማዕድን፣ ለእናቶችና ሕጻናት ደኅንነት የዐቅም ግንባታ፡፡ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ከአውስትራልያ ተቋማት ጋር አብረው ከሚሠሩ ወይም ከሚያጠኑ ጋር ለመቀናጀት መርሐ ግብር አላቸው፡፡ ‹‹ትልቁ ችግር›› አሉ ፕሮፌሰሩ ‹‹የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ምርምር ላይ ትኩረት ስለማይሰጡ የጥናት ባሕላቸው ዝቅተኛ ነው(underdeveloped research culture)፡፡ በዚህም ምክንያት የአውስትራልያ ተቋማት እንዲደረግ የሚፈልጉት ጥናትና የአጥኝው ዐቅም አለመጣጣም ይከሰታል፡፡ እኒህ የጥናት ባለሞያ ደጋግመው እንደገለጡት ‹የአንዲት ሀገር የመፍጠር ዐቅም በሳይንስ መሠረቷ የተጽዕኖ ዐቅም ይወሰናል(the country’s ability to innovate is influenced by the size of its science base)፡፡››

በአሁኑ ጊዜ 4.5 ሚሊዮን ዓለም አቀፍ ተማሪዎች በየሀገሩ ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹ የአፍሪካ ተማሪዎች በፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካና ሳዑዲ ዐረቢያ ነው የሚማሩት፡፡ በአውስትራልያ ከሚማሩ ዓለም ዐቀፍ ተማሪዎች መካከል ቻይናውያን 27.4፣ ሕንዶች 10.4፣ ቬትናማውያን 5.1 በመቶውን ይዘዋል፡፡ በአውስትራልያ ትምህርት ቤቶች ለመማር ከሚያመለክቱት መካከል አፍሪካውያን ከ1 – 15 ከሚገኙ ዋና አመልካች ሀገሮች ውስጥ የሉበትም፡፡ ለዚህ ዋና ምክንያቱ ቪዛ ለማግኘት ያለው ጣጣ፣ በቂ የመኖሪያ ወጭ ሽፋን አለመኖር(10 በመቶዎቹ ብቻ በተማሪዎች መኖሪያ ይኖራሉ)፣ አውስትራልያ እስያ ላይ በማተኮሯ፣ በአፍሪካ የሚገኙ ትምህርት ኤጀንሲዎች ስለ አውስትራልያ ትምህርት ዕድሎች በቂ ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑ፣ ቻይና ለአፍሪካ የተሻለ ስኮላርሺፕ በመስጠቷ መሆኑ ተገልጧል፡፡ በአውስትራልያ ለመማር የሚያስቡ ይኼንን ገጸ ድር ቢያዩት ተመክረዋል –

   www.studyinaustralia.gov.au

ከ2012 ጀምሮ ከ8000 በላይ የአፍሪካ ተማሪዎች በአውስትራልያ ዩኒቨርሲቲዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከልም 1500ዎቹ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ሲሆኑ 40ዎቹ የዶክትሬት ዲግሪ እየሠሩ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሁሉም የአውስትራልያ የትምህርት ተቋማት 14000 አፍሪካውያን ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ናቸው፡፡ የአውስትራልያ መንግሥትም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት 5000 የማስትሬትና የአጫጭር ኮርሶች ዕድል ለአፍሪካውያን ማዘጋጀቱ ተገልጧል፡፡ ለአጫጭር ኮርሶች ይህንን ድረ ገጽ በማየት መጠቀሙ መልካም ነው –

www.australiaawardsafrica.org

ለቢዝነስ ጉዳዮች ደግሞ ወደዚህ ይዙሩ

www.dfat.gov.au

በጉባኤው ከነበሩት አቅራቢዎች ለአፍሪካውያን ስኮላርሺፕ ትልቁ ተግዳሮት ሆኖ የተነሣው ለትምህርት የሚመጡ ተማሪዎች ወደ ሀገራቸው ያለመመለሳቸው ችግር ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም የስኮላርሺፕ ዕድላቸው የተንጠለጠለባቸው ሀገሮች አሉ፡፡ አንዳንድ የጉባኤው ተሳታፊዎች በኮሪደር ወሬ ኢትዮጵያ ከእነዚህ አንዷ መሆኗን ነግረውኛል፡፡

ነፍሱን ይማረውና ጋዳፊ በአንድ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ ‹የአደጉትን ሀገሮች የአየር መበከል፣ የጦርነትና የፖለቲካ ችግር እንደምንካፈለው ሁሉ የእነርሱን ሀብትና ዕድገትም መካፈል አለብን‹ ብሎ ነበር፡፡ ናይጄርያውያንና ኬንያውያን ከአፍሪካ፤ ሕንድ፣ ቻይናና ቬትናም ከእስያ የአውስትራልያን የትምህርት ስጦታና ዕድል በሚገባ እንደሚጠቀበሙት ሁሉ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የትምህርት ተቋማትና በአውስትራልያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዳያስጶራ ተጋግዘን ዕድሉን ብንጠቀምበትና ለሀገራችን ሰው ብናፈራበት መልካም ይመስለኛል፡፡ በተለይም በሀገር ውስጥ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና መካከለኛ ተቋማት ከአውስትራልያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለመሥራት የተዘጋጀውን መርሐ ግብር ተሻምቶ በመጠቀም በትንንሹ ዳቦ ከምንራኮት ትልቁን እንጀራ እንቁረስ፡፡ ወደ 310 ሚሊዮን ዶላር ለስኮላርሺፕ መንግሥት መመደቡን አብሥረዋል በጉባኤው ላይ፡፡ መልካም ዕድል፡፡

ሜልበርን፣ አውስትራልያ

ቅዱስ ጳውሎስ ተከስሶ በቂሣርያው ገዥ በፊስጦስ ፊት በቀረበ ጊዜ አይሁድ ለብቻቸው ቀርበው በቅዱስ ጳውሎስ ላይ ይፈርድበት ዘንድ ጎትጉተውት፣ እነርሱ ማስረጃ ያሉትንም አቅርበውለት፣ ሕጋቸውንም ጠቅሰው ማሳመኛ አቅርበውለት ነበር፡፡ አሕዛባዊው ገዥ ፊስጦስ ግን እግዚአብሔርን እናውቃለንም፣ እንፈራለንም ከሚሉት አይሁድ ተሽሎ ያሉትን ከማድረግ ራሱን ከለከለ፡፡

ከጥቂት ቀናት በኋላ ንጉሥ አግሪጳና በርኒቄ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ ጉዳዩን አቀረበላቸው፡፡ ፊስጦስ አይሁድ ያቀረቡትን ስሞታ፣ ውትወታና ክስ ተቀብሎ በቅዱስ ጳውሎስ ላይ ያልፈረደበትን ምክንያት ለአግሪጳ ሲገልጥለት ‹‹ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ለፊት ሳይቆም፣ ለተከሰሰበትም መልስ ይሰጥ ዘንድ ፈንታ ሳያገኝ፣ ማንንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሥርዓት አይደለም›› ብሎ መሆኑን ነግሮታል (የሐዋ.25÷16)፡፡

ይህ በሮማውያን ዘመን እጅግ የታወቀውን ራስን በእኩል ደረጃ የመከላከል መብት በተመለከተ ሮማዊው ታሪክ ጸሐፊ አፒያን (95-165ዓም) በጻፈው Civil War በተሰኘው መጽሐፉ (3:54) ላይ ‹‹የምክር ቤት አባሎች፣ ሕጉ የተከሰሰ ሰው የተከሰሰበትን ሰምቶ በእርሱ ላይ ከመፈረዱ በፊት መልስ የመስጠት መብት አለው ይላል›› ሲል አሥፍሮት ነበር፡፡ ፊሊክስ የጠቀሰው ይኼንን ነው፡፡ አበው በትርጓሜያቸው ‹አሕዛብ ፍርድ ይጠነቅቃሉ›› ሲሉ የመሰከሩት እንዲህ ያለው የሮማውያንን ሕግ ነው፡፡ ለዚህ ጥንቁቅ የፍርድ ሥርዓትም ሲሉ አያሌ የሮማውያንን የፍተሕና የፍርድ ሐሳቦች በቤተ ክርስቲያን የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ (በቀኖና) እንዲገቡና እንዲሠራባቸው አድርገዋል፡፡

ይህንን የምትተረጉምና የምታስተምርን ቤተ ክርስቲያን እንወክላለን የሚሉ ሰዎች ናቸው ሰሞኑን ተሰብስበው ተከሳሹ በሌለበት ፍርድ ሲሰጡ ያየናቸው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ተሳሳተ ተብሎ እንኳን ቢሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ ለአርዮስና ለንስጥሮስ፣ ለመቅዶንዮስና ለሰባልዮስ የሰጠችውን መብት ቤተ ክህነቱ ለማኅበረ ቅዱሳን ሊነፍገው አይገባም ነበር፡፡ በቀደዱላቸው ቦይ መንጎድ፣ ተጠልቷል ብለው በሚያስቡት ላይ መፍረድ ሃይማኖታቸው የሆነ፤ ፓትርያርኩን ምን ያስደስታቸዋል እንጂ የትኛው እውነት ነው ለሚለው የማይጨነቁ ሰዎች የክስ መዓታቸውን ሲያዘንቡ ማኅበሩ መልስ እንዲሰጥ ዕድል ሊሰጠው ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ሰዎቹ ለበዓሉ የሚስማማውን ቀለም ትተው ለባለ ሥልጣኑ የሚስማማውን ቀለም መረጡ፡፡ ሊቁ ክፍለ ዮሐንስ ‹ካህን ከመሆን እረኛ መሆን ይሻላል› እንዳለው ከቤተ ክህነት ፊልክስ ተሽሏል፡፡

ፊሊክስ ለቅዱስ ጳውሎስ፣ ሠለስቱ ምእት ለአርዮስ፣ ማኅበረ ኤፌሶን ለንስጥሮስ የሰጡትን ዕድል ቤተ ክህነቱ ለማኅበረ ቅዱሳን ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ለምን?

ሰዎቹ እውነቱን ለመጋፈጥ ዐቅም አንሷቸዋል ማለት ነው፡፡ የሚሉት ነገር የሆኑ አካላትን ስለማስደሰቱ እንጂ እውነት ስለመሆኑ ርግጠኞች አይደሉም፡፡ ስለዚህም ተከራካሪያቸውን ለመስማትና የእነርሱ ‹እውነት› ሲሞገት ለማየት ዐቅም ያንሳቸዋል፡፡ ወይም ደግሞ

ከክርክሩ በፊት ውሳኔውን ወስነው ጨርሰዋል፡፡ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስን ለደርግ አሳልፈው የሰጡት የቤተ ክህነት ሰዎች እንዲህ ነበር ያደረጉት፡፡ ፓትርያርኩን አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ውሳኔውን ወስነዋል፡፡ ነገር ግን ለውሳኔው ምክንያት መፈለግ ነበረባቸው፡፡ ስለዚህም አቡነ ቴዎፍሎስ ሠሩ ያሏቸውን ጥፋቶች ለብቻቸው ተሰብስበው፣ ‹በደላቸውን› ዘርዝረው፣ እርሳቸው መልስ ሊሰጡ በማይችሉበት ሁኔታ ለደርግ አስተላለፉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለብቻቸው መሰብሰብ የፈለጉት፣ የፓትርያርኩንም መልስ የመስጠት መብት የነፈጉበት አንዱ ምክንያት ፓትርያርኩ በሚሰጡት መልስና በሚያቀርቡት ማስረጃ እውነታቸው ነፋስ ያየው ገለባ እንዳይሆንባቸው ነው፡፡ ወይም

እነዚህ ሰዎች የራሳቸውን ሥራ አይደለም እየሠሩ ያሉት፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲበጠብጡ የኖሩት ካህናተ ደብተራ (ከቤተ ክህነት ደመወዝ እየወሰዱ ለቤተ መንግሥት ሲሠሩ የኖሩ ካህናት ነን ባዮች) ዋናው መለያቸው የሚሠሩት የራሳቸውን ሥራ አለመሆኑ ነው፡፡ የመለካዊነት ጠባይ ስላላቸው ሌሎች ተናገሩ የሚሏቸውን ይናገራሉ፣ ፈጽሙልን የሚሏቸውን ይፈጽማሉ፤ አውግዙልን የሚሏቸውን ያወግዛሉ፤ አጽድቁልን የሚሏቸውንም ያጸድቃሉ፡፡ የሚሠሩት ሥራ የላኳቸውን ሰዎች ማርካቱን እንጂ የሚያስከትለውን ነገርና የሚያስከፍለውን ዋጋ አያውቁትም፡፡ እነዚህ ነበሩ አባ በጸሎተ ሚካኤልን ያሰደዱት፣ እነዚህ ነበሩ አባ ፊልጶስን ያንከራተቱት፣ እነዚህ ነበሩ እጨጌ ዕንባቆምን ለልብነ ድንግል ከስሰው ምንም ባላጠፋው ጥፋት ‹ጉንጽ› በተባለው ዓለም በቃኝ እስር ቤት ያሳሠሩት፤ በኋላም ለሀገሪቱ ጥፋትን ያመጡት፡፡ ጥይት የመታው ሰው ተናድዶ ‹‹ምነው እንዲህ ታበላሸኝ›› ቢለው ‹‹እባክህ እኔ አይደለሁም፣ እኔ ተተኮስኩ እንጂ ተኳሹ ሌላ ነው፤ እኔ መልክተኛ ነኝ›› አለው፡፡ ‹‹ተኳሹ የት አለ?›› ቢለው ‹‹እርሱማ አይታይም ተደብቆ ነው የሚተኩሰው፤ እርሱ ስለሚደበቅኮ ነው እኔ የመጣሁት›› አለው ይባላል፡፡

ወይም እነዚህ ሰዎች ስንፍናቸውን የሚያሳይባቸውን፣ ድካማቸውን የሚገልጥባቸውን፣ ሊያጠፉት ወድደዋል፡፡ ሰውዬው ዶሮውን በጦም አርዶ ለምን አረድከው ቢባል ‹‹እሱ ነው ጠዋት እየተነሣ መንጋቱን የሚያሳብቅብኝ፣ አርፌ እንዳልተኛበት፡፡እርሱ ባይጮህ ኖሮ መንጋቱን ማን ያውቅ ነበር? ተኛህ ብሎስ ማን ይከሰኝ ነበር›› አለ አሉ፡፡ ከመንቃት ይልቅ ማንቂያውን ማጥፋት፡፡ የ13ኛው መክዘ የደቡብ ሐዋርያ አቡነ አኖሬዎስ ታላቁ በካህናተ ደብተራ ተከስሶ ወደ ንጉሥ ሰይፈ አርእድ የቀረበበት ክስ አስቂኝ ነበር፡፡ ‹‹ከንጉሡ የሚበልጥ ቤተ ክርስቲያን ሠርቷል›› ነበር የተባለው፡፡ ጉዳዩን ሊያጣራ የሄደው የጉዳም አለቃ ያገኘው ቤተ ክርስቲያን ግን እንደተባለው አልነበረም፡፡ ነገር ግን ከክሱ ንጹሕ መሆኑ ቅጣቱን አላስቀረለትም፡፡ ከገዳሙ ወጥቶ በወለቃ በረሃ እንዲከራተት ሆኗል፡፡ ምናለ ከንጉሡ የሚበልጥ ቤተ ክርስቲያን ቢሠራ? የሚያስመሰግነው እንጂ የሚያስነቅፈው አልነበረም፡፡ ለካህናተ ደብተራ ግን ይኼ ስንፍናቸውን ይገልጠዋል፣ እንደ አውራ ዶሮውም መተኛታቸውን ያሳይባቸዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ አሁን መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆሟል፡፡ የሚቀርቡት ክሶች ለምን ቀረቡ ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን በአይሁድ አደባባይ ፍርድ ሲጓደል፣ እንደ ጲላጦስ ሚስት የሚያስጠነቅቅ ያስፈልጋል፡፡ ገለልተኛ አካል አቋቁሞ የተባሉትን ያጣራ፡፡ ራሱ የማኅበሩ አመራር ለተከሰሰበት መልስ ይስጥ፡፡ አሕዛባዊው ፊሊክስ ለቅዱስ ጳውሎስ የሰጠውን መብት ሲኖዶሱ ለማኅበሩ መስጠት አለበት፡፡ ተጣርቶ በተገኘው ማስረጃና ምስክር መሠረት ውሳኔ ይሰጥ፡፡ ጥፋተኛው ይታረም፤ እውነተኛው ይገለጥ፡፡

በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ቀራንዮ መድኃኔዓለም አለቅነት ተሾመው የሄዱትን አባት ካህናቱ አስቸገሯቸው፡፡ ለጥቂት ጊዜ የተላኩበትን ሊሠሩ ሞከሩ ግን አልሆነም፡፡ በመጨረሻም ለንጉሡ እንዲቀይሯቸው አመለከቱ፡፡ ንጉሡም ምነው ምን ገጠመህ? ቢሏቸው ‹‹ካህናቱም ካህናቱ፣ ቀራንዮም ቀራንዮ፣ መድኃኔዓለምም መድኃኔዓለም›› አሉ ይባላል፡፡ ሰቃይ ተሰቃይና የመስቀያ ቦታ አንድ ሲገናኙ ያ ነው ክፉ ዘመን፡፡

ማኅበሩን እንደ ተቋም፣ እንደ ጽ/ቤትና እንደ ድርጅት ማፍረስ ቀላል ነው፤ እንደ አስተሳሰብ፣ እንደ አመለካከት፣ እንደ የአገልግሎት መሥመርና አተያይ ግን ማፍረስ አይቻልም፡፡ ዛሬ ማኅበሩን በማፍረስ የሚጀመረው አጥር ንቅነቃ ግን መጨረሻው ሲኖዶሱን በማደንበሽ እንዳይጠናቀቅ ያሰጋል፡፡ ባለቤቱን ካልናቁ ነውና፡፡ 

ዐጽሟ ያረፈበት አርመን የሚገኘው ቤተ ክርስቲያን

ቅድስት አርሴማ በ290 ዓም በአርመን በሰማዕትነት ያረፈች ወጣት ክርስቲያን ሰማዕት ናት፡፡ ትውልዷ ሮም ሲሆን ሰማዕትነት የተቀበለችው አርመን ነው፡፡ እኛ አርሴማ ስንላት እነርሱ Saint Hripsime ይሏታል፡፡ ታሪኳን የፈለገ ሰው በዚህ ስሟ ጎጉል ላይ ቢፈልግ በቀላሉ ያገኘዋል፡፡ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ መስከረም 29 ቀን ወይም ኦክቶበር 9 ሰማዕትነት የተቀበለችበትን ቀን ያከብራሉ፡፡ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን በስሟ የተሠራውም አርመን ኤችሚዚን ውስጥ በ395 ዓም ነው፡፡ ይህ የአርሴማ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ላይ ሳይፈርሱ ከኖሩት እጅግ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ ነው፡፡

የዚህች ወጣት ሰማዕት ታሪክ በስንክሳር በመስከረም 29 ቀን ተጽፏል፡፡ በሀገራችን ገድላቸው ከተተረጎመላቸው የውጭ ቅዱሳን አንዷ አርሴማ ናት፡፡ የዚህ ምክንያቱ የታወቀ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ አርመን ከአርመንም ወደ ኢትዮጵያ የሚሄዱና የሚመጡ ቅዱሳን ነበሩ፡፡ በ10ኛው መክዘ አካባቢ በአርመን የደረሰውን የፋርሶችን ወረራ በመሸሽ አያሌ አርመናውያን ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውንና ዛሬ ሐይቅ እስጢፋኖስ በተባለው ቦታ መሥፈራቸውን የአርመን ታሪክ ይነግረናል፡፡ በአርመንኛ ‹ሐይቅ› ማለትም ገዳም ማለት ነው ይላሉ፡፡
                        በአርመን ቤተ ክርስቲያንዋ የሚታወቀው ሥዕል ይህ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በ13ኛው መክዘ ኢትዮጵያዊው አቡነ ኤዎስጣቴዎስ መጀመሪያ ወደ ግብጽ (1330-32 ዓም)፣ ከዚያም ወደ እሥራኤል በመጨረሻም ወደ አርመን ተጉዘው በዚያ ለአሥራ አራት ዓመታት ከቆዩ በኋላ በ1352 ዓም ዐርፈዋል፡፡ ከእርሳቸው ዕረፍት በኋላም ደቀ መዝሙሮቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡ እነዚህ የተመለሱ የአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ደቀ መዛሙርት ብዙ የውጭ ሀገር ቅዱሳት መጻሕፍትን ይዘው በመምጣትና ወደ ግእዝ በመበተርጎም ታላቅ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ (ዝርዝር ታሪኩን የፈለገ ‹አራቱ ኃያላንን› መመልከት ነው)፡፡ በጎንደር መንግሥት ጊዜም አቡነ ዮሐንስ የተባሉ ቆሞስ የአቡነ ኤዎስጣቴዎስን ተረፈ ዐጽም ይዘው በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን መጥተው ነበር፡፡ እነዚህ ከወዲህና ከወዲያ የነበሩ ግንኙነቶች ቅድስት አርሴማን በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንድትታወቅ አድርጓታል፡፡ ገድሏም ወደ ግእዝ ሊተረጎም ችሏል፡፡

በአሁኑ ዘመን አርሴማ በኢትዮጵያውያን ወጣቶች ዘንድ ይበልጥ እየታወቀችና እየተከበረች መጥታለች፡፡ ወጣቱ የወጣቷን ሰማዕት አርአያ ማንሣቱ የሚያስመሰግን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ስለ ክርስቶስ ስትል የከፈለችውን ሰማዕትነት፣ ድንግልናን በብጽዐት ለመጠበቅ ስትል የተቀበለችውን መከራ፣ ወጣትነቷ ሳያጓጓት ለእምነት የከፈለችውን ዋጋ፣ በሕይወቷ ሳለች ከሠራችውም በላይ በሰማዕትነቷ ያፈራችውን ፍሬ በማሰብና ከእርሱም በመማር ዘመኑን ከመዋጀት ይልቅ የሰማዕቷን ዝክር ከትዳርና ከፍቅረኞች፣ ከጥራጥሬና ከታሪኳ ጋር ከማይሄዱ ነገሮች ጋር ማገናኘቱ መልካም አይደለም፡፡

                                                    ቅድስት ባርባር
ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ጊዜ የቅድስት አርሴማ ሥዕል ነው ተብሎ በስፋት የሚታወቀው ሥዕል በኦርቶዶክስ ሥነ ሥዕል (አይኮኖግራፊ) የቅድስት ባርባራ ሥዕል ነው፡፡ አርመን ኤችሚዚን በሚገኘው መቃብሯ ላይ የሚገኘው ሥዕሏ ከታች የተገለጠው ነው፡፡ ጣና ደሴት ውስጥ በሚገኘው ቤተ ክርስቲያንዋም ኢትዮጵያዊውን ሥዕል ማግኘት ይቻላል፡፡

                በመቃብሯ ላይ የሚገኘው ሥዕል

በአጠቃላይ ቅድስት አርሴማ ታሪኳ በመላው ዓለም ክርስቲያኖች ዘንድ የታወቀ፣ ከንጽሕናና ቅድስና ጋር በእጅጉ የተገናኘ፣ ለወጣት ሰማዕታት ታላቅ አርአያ የሚሆን፣ ንጽሕናን ለመጠበቅ ፈታኝ በሆነበት በዚህ ዘመን ምሳሌ የሚሆን፣ ቀደምት እናቶቻችንና እኅቶቻችን ስለ ክርስቶስ ሲሉ የከፈሉትን ዋጋ የሚያሳይ በመሆኑ በዓሏም በዚህ መንፈስ መከበር ይኖርበታል፡፡ 
ሜልበርን፣ አውስትራልያ

በሜልበርን እምብርት እየተሽረከርን በያራ ወንዝ ዳርቻ ስንዋብ ወደ ሌላ አቅጣጫ የመሻገሪያ የእግረኞች ድልድይ ላይ ደረስን፡፡ የያራ ወንዝ ዓባይን በሰኔ መስሏል፡፡ እዚህ ወንዝ ዳር ነው የዛሬ 179 ዓም እኤአ 1835 የሜልበርን ከተማ የተቆረቆረችው፡፡ ከ242 ኪሎ ሜትር በላይ ይጓዛል ያራ ወንዝ፡፡ የመሻገሪያው ድልድይ ወንዙ መካከል በአንዲት አነስተኛ ጀልባ በምትመስል ኮንክሪት መሬት ላይ ቆሟል፡፡ ሀገሬዎቹ ደሴት ብርቃቸው ነው መሰለኝ ‹ፖኒ ፊሽ ደሴት› ይሏታል፡፡ መቼም ፈረንጅ ትንሽን ነገር ታላቅ በማድረግ የሚተካከለው የለም፡፡

ይህንን ድልድይ እያቋረጥን ስንሄድ በግራና ቀኝ በድልድዩ መደገፊያ ላይ የታሠሩና የተቆለፉ ቁልፎችን አየሁ፡፡ ሙሉ የድልድዩን ብረት ከጫፍ እስከ ጫፍ ይዘውታል፡፡ አንዳንዶቹ በሀገራችን ለስታድዮም በር ብቻ ሊውሉ የሚችሉ ቁልፎች ናቸው፡፡ እነዚህ በፍቅራቸው ላይ ሥጋት ሳይኖርባቸው አይቀርም፡፡ አንዳንዶቹ ቁልፎችም ከቻይኖች ዓይን እንኳን ያነሱ ናቸው፡፡ ይህንን ዓይነት ነገር የገጠመኝ ፓሪስ ነበረ፡፡ በፓሪስ የሚገኙ ድልድዮች በዚያ ስማቸውን ጽፈውና ቁልፋቸውን ቆልፈው በሚያንጠለጥሉ ፍቅረኞች ምክንያት ለአደጋ መጋለጣቸውን የከተማው ማዘጋጃ ቤት ቢጮህ እንኳን ሰሚ አላገኘም፡፡ በተለይ ፖንቴ ደስ አርትስ በዚህ የተቸገረ ድልድ ነው፡፡እዚህ ሜልበርንም ተመሳሳይ ሥጋት ከመዘጋጃ ቤቱ እየተሰማ ፍቅረኞች ግን ከድልድዩ ይልቅ ፍቅራቸው ያሳስባቸዋል፡፡ ድልድዩ ቢሰበር እኛ ደኅና እንሁን እንጂ መልሰን እንሠራዋለን፡፡ የኛ ፍቅር ከተሰበረ ማን ይጠግነዋል? ይላሉ፡፡

ይኼ ደግሞ ባልተጠገነ ፍቅር ምክንያት በልብ ሕመም የሞተችውን ሰርቢያዊቷን ናዳን ያስታውሳቸዋል፡፡ ናዳ በአንድ ትምህርት ቤት የምታስተምር ሴት ነበረች፡፡ ከሕይወት በአንዱ ቀን ሬልጃ ከተባለ የሰርቢያ የጦር መኮንን ጋር በፍቅር ወደቀች፡፡ ዘመኑ የአንደኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ነበርና ሬልጃ ለጦርነት ወደ ግሪክ ሄደ፡፡ በሄደበት ግሪክ ‹‹እኔስ በአገሬ እንኳን ሰው ወፍ አለምዳለሁ›› የምትል ቆንጆ አገኘና ከእርሷም ጋር በፍቅር ወደቀ፡፡ በዚህም ምክንያት ናዳና ሬልጃ ተለያዩ፡፡ ናዳ በዚህ የተነሣ ኀዘንተኛና በሽተኛ ሆነች፡፡ ኀዘኑ ባስከተለባት የልብ ችግርም ምክንያት ገና በወጣትነቷ ሞተች፡፡

ይህ የናዳ ታሪክ የሰርቢያን ወጣቶች አስደነገጣቸው፡፡ የመጀመሪያውና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አያሌ ወዳጆቻቸውን ያሳጣቸው የአውሮፓ ወጣት ፍቅረኞችንም ልብ ነካ፡፡ በዚህም የተነሣ የሚፋቀሩ ወጣቶች ላለመለያየት ብለው፣ የናዳም ዕጣ ፈንታ እንዳይደርስባቸው ፈርተው ቁልፍ እየቆለፉ ናዳና ራጃ አዘውትረው ይገናኙበት ነበር በተባለው ድልድይ ላይ ማንጠልጠል ጀመሩ፡፡ ከሺ ዘመናት በፊት በአውሮፓ የነበረው ይህ ባሕል በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ምክንያት እንደገና አገረሸና አያሌ ድልድዮችን አጥለቀለቀ፡፡

የፓሪሱ የፍቅር ድልድይ

ከቀድሞ ጀምሮ የሰውን ልጅ ሲያስጨንቁት ከኖሩት ሰብአዊ ጸጋዎች አንዱ ፍቅር ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው አፍቃሪ ፍጡር ሆኖ ነው፡፡ እንስሳት ይኼ የላቸውም፡፡ እንስሳት ለአንድ ነገር የሚኖር አዝማሚያ (affection) ነው ያላቸው፡፡ ፍቅር የአምላክ ጸጋ ነውና ይህ ሊኖራቸው የሚችለው ሰውና መላእክት ናቸው፡፡ ሰው ሥጋዊ ፍጡር ስለሆነ ነው ስሜትም የሚኖረው፡፡ ስሜት በመላእክት ዘንድ የለም፡፡ ፍቅር ግን አለ፡፡ ማሰብ ከሌለ ስሜት እንጂ ፍቅር አይኖርም፡፡ ፍቅር አንድን ነገር መፈለግ፣ ወደ አንድ ነገር መሳብና ከአንድ ነገር ጋር መቆራኘት ብቻ ሳይሆን አብሮ የሞራልና የእምነት ሕግጋትም አሉት፡፡ ለዚህ ደግሞ ማሰብን ይፈልጋል፡፡ ፍቅር በውስጡ ጽጌረዳ ብቻ ሳይሆን እሾህ፣ የዓሣ ሥጋ ብቻ ሳይሆን የዓሣ እሾህ፣ ማር ብቻ ሳይሆን የንብ ንድፊያ፣ አለው፡፡ አንዳንዴ ለመዳን መርፌን እንደምንወጋው፤ መርፌውም እንደሚያም፣ ነገር ግን መድኃኒቱ እንደሚያድነን፤ ለመድኃኒቱም ብለን የሚያመውን መርፌ እንደምንታገሠው፤ ፍቅርም እንዲህ ይሆናል፡፡ መድኃኒት የያዘ መርፌ ይሆናል፡፡ ይህንን ሁሉ ለማመዛዘንና ለመቀበል ደግሞ አሳቢ ፍጡር መሆን ግድ ነው፡፡ ስሜት የሚያውረውን ፍቅር ነው የሚያበራለት፡፡ ፍቅር ዓይናማ ነውና፡፡ ያውም የልቡና ዓይን፡፡
ሳውዝ ባንክ የእግረኞች ማቋረጫ
ሰው ፍቅርንና ስሜትን መለየት እያቃተው፣ አንዳንድ ጊዜም ከፍቅር ይልቅ ስሜቱን እያስበለጠ ነው ራሱን መከራ ውስጥ የሚጥለው፡፡ ስሜት ለፍቅር አንዱ ግብዐት እንጂ ብቸኛው ነገር አይደለም፡፡ በፍቅር ውስጥ ከስሜት ሌላ ማሰብ፣ መታገሥ፣ ራስን መግዛት፣ መሸከም፣ ቆራጥ፣ ኃላፊነትን መውሰድ፣ ይቅር ማለትና ሌሎችም አሉበት፡፡ ስሜት ግን የፍቅር ማስጀመሪያ እና ፍቅር ማለስለሻ ነው፡፡ ለአንድ መኪና ባትሪው የሞተሩ ማስነሻ እንደሆነው ሁሉ፤ በባትሪ ብቻ ግን መሄድ እንደማይቻል፤ ያለ ባትሪም መሄድ እንደማይቻል ማለት ነው፡፡ ስሜት እንደ መኪና ቅባቶችና ዘይቶች ያለ ነው፡፡ ቅባትና ዘይት ያነሰው መኪና ችሎ ችሎ አንድ ቀን ወይ ይነጫነጫል፣ ወይ ይቆማል፣ ወይ እሳት ያስነሣል፣ ወይ ሞተር ይነክሳል፡፡ ስሜት ጠፍቶባቸው ሞተር የነከሱ ብዙዎች ናቸው፡፡
ቅባትና ዘይት ግን ለሞተሩና ለሌሎች ዕቃዎች ሕልውና ሲባል የሚደረግ እንጂ በራሱ ሕልውናውን ለብቻ የሚያስቀጥል አይደለም፡፡ ለዘይቱ አይደለም ሞተሩ፤ ለሞተሩ ነው እንጂ ዘይቱ፡፡ እንደዚሁም ነው፡፡ በፍቅር ውስጥ ለሚገኙት ወሳኝ ነገሮች ነው ስሜት የሚያስፈልጋቸው፡፡ እንጂ ለስሜቱ አይደለም እነርሱ የሚያስፈልጉት፡፡ ስሜት ብቻ የያዙ ‹‹ፍቅረኞች›› ናቸው እንደ ሬልጃ እዚህም እዚያም መሄድ፣ ያዩዋትንም ሁሉ መመኘትና እንደ ተረት ገጸ ባሕርይ ‹‹ሲሄዱ፣ ሲሄዱ፣ ሲሄዱ›› የሚኖሩት፡፡

ይኼ እንግዲህ የሰው ዘር ሁሉ ጭንቀት ነውና እስኪ በቁልፍ አሥረን እንሞክረው ብለው ነው ስማቸውን ጽፈው፣ ቁልፍ ላይ ለጥፈው፣ ቁልፉንም ቆልፈው ድልድይ ላይ የሚያስቀምጡት፡፡እንዲህ ዘወትር ሳንለያይ ያኑረን ብለው፡፡ በተለይ በዚህ እና ባለንበት ዘመን ሰው የሰውን ጸባይ ቀርቶ የራሱን ጠባይ መቻል እያቃተው፣ ሰው አንዳች መሥዋዕትነትን ለመክፈል እየሰሰተ ባለበት ጊዜ መሸከምንና መሥዋዕትነትን የሚፈልገው ፍቅር በስሜትና በጊዜያዊ ፍላጎት (ፈቲው) እየተተካ በመሄድ ላይ ነው፡፡ ለዚህ ነው የሰው ልብ መሸከም ያቃተውን ነገር ድልድዮችን ለማሸከም መከራ የሚያየው፡፡ ድልድዮች ደግሞ ‹እናንተ ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ›› አላሉም፡፡ በምን ዐቅማቸው ይሸከሙታል፡፡
ፍቅር ፍቅር አሉት ስሙን አሳንሰው

ከድንጋይ ይከብዳል ለተሸከመው ሰው

አለ የሀገሬ ገጣሚ፡፡

ሜልበርን፣ አውስትራልያ፡፡

በ1768 እኤአ የተጻፈና ጥንታዊ አባባሎችን የያዘ አንድ ‹‹AN ETHIOPIAN SAGA›› የተሰኘ መጽሐፍ ሳነብ ‹‹ጨረቃዋን እያየህ፣ ጨለማውን ግን እየተጠነቀቅ ተጓዝ›› የሚል ጥንታዊ ብሂል አየሁ፡፡ ይህ ለጥንቱ መንገደኛ የተሰጠ የጠቢብ ምክር ነው፡፡

የጥንቱ ተጓዥ ጤፍ በምታስለቅመው ጨረቃ መጓዙ ሁለት ጥቅሞች ይሰጡት ነበር፡፡ በአንድ በኩል በቀን ከሚገጥመው ሙቀትና የፀሐይ ቃጠሎ ይድናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንገዱን በሩቁ ስለማያየው ‹ለካ ገና ብዙ መንገድ ይቀረኛል› እያለ መንፈሱ እንዳይደክም ያደርገዋል፡፡

በተለይም ደግሞ መንገደኞቹ በዛ ካሉ፣ ሰብሰብ ብለው በአንድ ቤት ታዛ ሥር ወይም በአንድ ዛፍ ጥላ ሥር ያርፉና በአራተኛው ክፍለ ሌሊት(ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በኋላ) ተነሥተው የጨረቃዋን ብርሃን እየተከተሉ መጓዝ ነው፡፡ ያን ጊዜ  ነው እንግዲህ ‹ከጨለማው እየተጠነቀቁ፣ ነገር ግን ጨረቃዋን እያዩ›› የሚጓዙት፡፡

መንገደኞቹ ጨረቃዋን የሚያዩዋት ለሁለት ነገር ነው፡፡ በአንድ በኩል ጨረቃዋ መጀመሪያ እየደመቀች፣ በኋላ ደግሞ እየደበዘዘች መጓዟ የሌሊቱን ማለፍና የቀኑን መምጣት ይነግራቸዋል፡፡ በተለይ የበረሐ መንገደኞች ከሆኑ የጨረቃዋ እየደበዘዘች መሄድ ለእነርሱ መልካም ዜና አይደለም፡፡ የሙቀቱን መምጣት እያረዳቸው ነውና፡፡ የፀሐዩን ግለትም እነርሱም ሆኑ የጭነት ከብቶቻቸው አይቋቋሙትም፡፡ በሌላም በኩል የጨረቃዋን ብርሃን እየተከተሉ የሚጓዙት፣ በአካባቢው ሌላ ብርሃን የለምና፣ አንዳንድ ጊዜ ጨረቃዋን ደመና ሲጋርዳት ተግ እያሉ፣ በጠራ ሰማይ ላይ ፍንትው ብላ ስትወጣ ደግሞ መንገዱን ያዝ ያዝ እያደረጉ ስለሚገሠግሡ ነው፡፡

በዚህ ጉዟቸው የሚከተሉት የሚያተኩሩት በጨረቃዋን ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን ጨረቃዋ መንገዱን ብታሳያቸውም ጫካው፣ ሸለቆውና ገደላ ገደሉ ደግሞ በተቃራኒው ድቅድቅ የሆነ ጨለማን ይፈጥራል፡፡ ጥጋጥጉ ሁሉ ከጨረቃዋ ደማቅ ብርሃን ተጋርዶ አንዳች መርግ የመሰለ ጽልመት ይጋርደዋል፡፡ ይኼ ደግሞ የጨረቃዋ ብርሃን ላጋለጣቸው አራዊት ዋና መደበቂያ፣ ለሽፍቶች ዋና መሸሸጊያ ነው፡፡ አንዳንዴም ጨረቃዋ ፍንትው ብላ ስትወጣ ከተገለጠው አካባቢ ግራና ቀኝ ያለው አስፈሪና ምን እንደያዘ የማይታወቅ ሥርቻ ይሆናል፡፡

የጨረቃ ብርሃን እንደ ፀሐይ አይደለም፡፡ የፀሐይ ብርሃን ከሙቀቱ ጋር ስለሚመጣ አካባቢውን ይቀይረዋል፡፡ የብርሃኑ ወገግታም መከለያዎችን እንኳን ተሻግሮ የብርሃን ፍንጣቂ ይለቅበታል፡፡ የፀሐይ ብርሃን ከጨረቃ የተሻለ ምለክዐት አለው፡፡ ጨረቃ ግን ድምቀት ነው ያላት፡፡ አካባቢውን ታስውበዋለች እንጂ አታሞቀውም፡፡ በዚህ የተነሣ ለጨረቃ መንገደኞች ግራ ቀኙ አስፈሪ ነው፡፡  ከሆነ ርቀት በላይም በጨረቃ ብርሃን መንገዱን ማየት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ጨለማውን ተጠንቀቅ›› የተባለው፡፡

አንዳንድ ጊዜ ሕይወት የጨረቃ መንገድ ትሆናለች፡፡ ብርሃንና ጨለማ፣ ድምቀትና ፍርሃት አብረው የሚገኙባት፡፡ መንገድህን ታውቀዋለህ፤ ነገር ግን ከመንገድህ ግራና ቀኝ የሚጠብቅህን ወጥመድ በሚገባ ላታውቀው ትችላለህ፡፡ ቀና ስትል እንደምታያት ጨረቃ እጅግ የደመቁ ተስፋዎችን፣ ድሎችንና አጋጣሚዎችን ታገኛለህ፡፡ ነገር ግን ጨረቃ ጨረቃዋን ብቻ ስታይና ነፍስህን በሐሴት ስታጥለቀልቅ ደግሞ ከግራና ቀኝህ ከሚገኙት ጉድባዎች፣ ሸለቆዎች፣ ጥሻዎችና ጥጋጥጎች  የደበተ ጨለማ፣ የሚያስፈራም አውሬ፣ የሸመቀም ጠላት ያጋጥምሃል፡፡

መንገደኛው ጨረቃዋን ለማድነቅ በቂ ዕድልን አያገኝም፡፡ መጓዝ ስላለበት፡፡ አንድ ቦታ ቆሞ፣ በደስታ ተደሞ፣ በፍቅሯ ተውጦ፣ በብርሃንዋ ተመስጦ ‹ጨረቃ ድንቡል ቦቃ፣ ዐጤ ቤት ገባች ዐውቃ›› እላለሁ ቢል፣ እርሱ በጨረቃዋ ውበት በተመሰጠበት ጊዜ ከማያውቀው ጥሻ ብቅ የሚል አውሬ ወይም ጠላት አይጠፋም፡፡ አለበለዚያም ደግሞ የሚጣላ ባይሆንም የሚያስደነግጥ ኮሽታ አያጣም፡፡ ስለዚህም በአንድ ልቡ ቀና ብሎ ውበቷን እያየ፣ በአንድ ልቡም መንገድ መንገዱን እያስተዋለ፡፡ አልፎ አልፎም ደግሞ ግራና ቀኙን እየገላመጠ ይጓዛል፡፡

ሕይወት እንደ ጨረቃዋም የምታምር፣ የምትስብ፣ ኑሩብኝ ኑሩብኝ የምትል፣ አንዴ እየጎደለች ሌላ ጊዜ ብትሞላም፣ የምትፈነጥቅና መንገድ የምታሳይ፣ በተስፋና በጉጉትም የተሞላች ናት፡፡ ሕይወት እንደ ጨረቃዋ ፍስስ የምትል፣ የሚዜምላትና የምትናፈቅም ናት፡፡

በሌላም በኩል ደግሞ ሕይወት ተስፋና ደስታ፣ ርካታና ሰላም ብቻ አይደለችም፡፡ መንገደኛው ጨረቃዋን ብቻ እያየና በእርሷም እየተደሰተ ብቻ መጓዝ እንደማይችለው፡፡ ሕይወት ጥሻዎችና ገደሎች፣ ጫካዎችና ጉድባዎችም አሏት፡፡ የጨረቃዋ ብርሃን እንደሚያስደስተው ሁሉ የጫካዎቹ ጥላ፣ የጥሻዎቹ ዝምታ፣ የገደሎቹ ድብታና የገደሎቹም ጨለማ ያስፈራል፡፡ አንድም እዚያ ምን እንዳለ አለመታወቁ፣ አንድም ደግሞ እዚያ አውሬና ጠላት ሊኖር መቻሉ፡፡ የጨረቃዋን ብርሃንና ድምቀት ምን ብንወድደው፣ ጊዜ ሰጥተን ልናጣጥመውም ብንፈልግ እንኳን በግራ በቀኝ ያለው ጨለማና ፍርሃት ግን በቂ ጊዜም በቂ ልብም አይሰጠንም፡፡ ደግሞ እርሱንም እናስባለን፤ ደግሞ እርሱንም ማየት እንፈልጋለን፤ ደግሞ የእርሱንም ዝምታና ጨለማም ማጥናት እናስባለን፤ ምን ሊኖር እንደሚችል፣ ከማናውቀው ምንም ውስጥ ምን ሊወጣ እንደሚችል እንገምታለን፡፡ ከግምታችን ተነሥተንም እንሠጋለን፡፡

ያለፈውን እናስታውሳለን፡፡ ያለፉትንም እናስባለን፡፡ በዚህ ዓይነት መንገድ ስለተጓዙ ሰዎች የተነገረውንም ታሪክና ትርክት እናስታውሳለን፡፡ ተረቶቹንና ንግሮቹን እናመጣለን፡፡ ለጨለማውና ለዝምታው ትርጉም እንሰጣለን፡፡ እንጠረጥራለን፡፡ ኮሽታዎችንና ንቅናቄዎችን ሁሉ እናዳምጣለን፡፡ ለእያንዳንዱ ድምጽ ትርጉም እንሰጣለን፡፡ እንዲህ እያልንም በጨረቃ ድምቀት ተደስተን፣ በግራ ቀኙ ጨለማ ደግሞ ሠግተን እንጓዛለን፡፡ እንዲህ ናት ሕይወት፡፤ ተስፋ ብቻ አይደለችም ሥጋት አላት፣ ደስታ ብቻም አይደለችም ኀዘን አላት፤ የምትታይ ብቻ አይደለችም የማይታይም ክፍል አላት፡፡ የሚታወቅ ብቻ አይደለችም የማይታወቅም አካል አላት፡፡ ለዚህም ነው ቀደምቶቻችን ‹ጨረቃዋን እያየህ፣ ጨለማውን ግን እየተጠነቀቅክ ተጓዝ› ያሉን፡፡

ጨረቃዋን ለማያዩ ሰዎች ሕይወት ጎምዛዛ ብቻ ናት፡፡ ድብርትና ሥጋት የሞላባት፡፡ ምንም ዓይነት የደስታ ፍንጣቂ የማይታይባት፡፡ ከንቱ ብቻ ናት፡፡ ችግርና ጉስቁልና ብቻ የሰፈነባት፡፡ ጨለማውን ለማያዩ ሰዎች ደግሞ ሕይወት ደስታና ፈንጠዝያ፣ ሰላምና እርካታ፣ ፌሽታና ዝላይ ብቻ ናት፡፡ ሁለቱም ግን ይጎዳሉ፡፡ ጨረቃን የማያዩ ሰዎች ሕይወትን ለማጣጣም ዕድል አያገኙም፡፡ ምንም ዓይነት በጎ ነገርንም ከሕይወት አይጠብቁም፡፡ ምንም ዓይነት ደግ ነገር አይታያቸውም፡፡ ምንም ዓይነት ውበት አይገለጥላቸውም፡፡ ሁሉም ጨለማ ብቻ ነው፡፡ ጨለማውን የማያዩ ሰዎች ደግሞ ምንም ዓይነት ዝግጁነት፣ ጥንቃቄና ችግርን የመፍታት ጥበብ የላቸውም፡፡ ሣር ሣሩን ብቻ ሲያዩ ገደል ውስጥ የመግባት ዕጣ ይገጥማቸዋል፡፡ ማሩን እንጂ የንቧን መናደፍ፣ ጽጌረዳውን እንጂ እሾሁን አያዩም፡፡ ሕይወት መዝለልና መዘነጥ፣ መብላትና መተጣት፣ መሳቅና መጫወት ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ ስለዚህም በተወጉና በተነደፉ ጊዜ ይደናገጣሉ፡፡ በቶሎም ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡

በሕይወት በጤነኛ መንገድ ለመጓዝ የተሻለው ጥበብ ጨረቃዋን ማድነቅና በብርሃኗ መሄድ፣ ጨለማውንም መጠንቀቅ ነው፡፡ ሕይወት በጨረቃ ብርሃንና በጨለማው መካከል የተሠመረች ስላች መንገድ ናትና፡፡ እዚህ ላይ ጠቢብ ሰው ሚዛኑን ይጠብቃል፡፡ እዚህ ላይ ጠቢብ ሰው አንድ ዓይኑን በጨረቃዋ ሌላውንም ዓይኑን በጨለማው ላይ ተክሎ ይጓዛል፡፡ ጠቢብ ሰው ሁለቱን ዓኖቹን አንድ ነገር ላይ አይተክልም፡፡ ብዙ ጊዜ አንድን ነገር በሁለት ዓይኖቻችን ነው የምናየው፡፡ ማየት ያለብን ግን የዚያን ነገር ጨረቃና ጨለማ ነው፡፡ ጨረቃዋን በአንድ ዓይን ጨለማውን ደግሞ በሌላው ዓይን፡፡ ሕይወት በጨለማና በጨረቃ መካከል መጓዝ ነውና፡፡

ሜልበርን፣ አውስትራልያ

ደራሲ – እንዳለ ጌታ ከበደ

ዋጋ – 49 ብር

አታሚ – ኤች ዋይ ማተሚያ ቤት

እንዳለ ጌታ የጻፈውን እምቢታ መጽሐፍ ከአዲስ አበባ ወደ አውስትራልያ እየተጓዝኩ አውሮፕላን ውስጥ ነው ያነበብኩት፡፡ መጽሐፉ ለገበያ ሲቀርብ እንደማልኖር ስላወቀ ቀድሜ እንዳገኘው በማድረጉ አመሰግነዋለሁ፡፡ ይኼ በታሪክና በሥነ ቃል(ፎክሎር) ላይ የተመሠረተ ልቦለድ በአንዲት ብዙዎቻችን በማናውቃት ከዘመን የቀደመች ሴት ጀግና ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡

ቃቄ ወርድወት ትባላለች፡፡ በነገራችን ላይ ቃቄ የአባቷ ስም ነው፡፡ የእርሷ ስም ወርድወት ነው፡፡ በጉራጌ ባሕል የአባትን ስም ከልጅ የሚያስቀድም ጥንታዊ ሥርዓት ነበረ ማለት ነው፡፡ ምናልባትም በዕውቀቱ ስዩም ‹በኢትዮጵያ ከልጅ ስም በፊት የአባት እንደሚቀድም ማስረጃ አለኝ› ያለው አንዱ ይኼንን ሳይሆን አይቀርም ብዬ ገምቻለሁ፡፡ የመጽሐፉን ረቂቅ መመልከቱን መግቢያው ላይ ያሳያልና፡፡

ቃቄ ወርድወት በ1840ዎቹ አካባቢ ከጉራጌ ማኅበረሰብ የፈነጠቀች ኢትዮጵያዊት ኮከብ ነበረች፡፡ በሴቶች ላይ የነበረውን አድሏዊ ልማዳዊ ሥርዓት ለመታገል፣ በጋብቻ ሥርዓት ወንዶቹ ከሴቶቹ ይልቅ ሥልጣን ለማደላደል፤ ሴቶች ከለፉበት ትዳራቸው ያለ አንዳች ንብረት በፍቺ መባረራቸውን ለማስቀረት የታገለች ጀግና፡፡ ዛሬ እንኳን ለብዙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች አስቸጋሪ የሆነውን ‹ሴት ልጅ ተመርጣ ብቻ ሳይሆን መርጣም ማግባት አለባት› የሚለውን ሐሳብ ይዛ የታገለች፤ ታግላም በራሷ ላይ የፈጸመች ጀግና ሴት ናት፡፡

በዚያ የሴቶች መብት፣ የጾታ እኩልነት የሚሉ ዘመናዊ ሐሳቦች ባልዳበሩበት፤ ለሴቶች መብት ቆመናል የሚሉ ተቋማት ባልነበሩበት ዘመን ከዘመኗ ቀድማ ችግሩን የተረዳች፤ የሴቶችን ችግር ለመቅረፍና እናቶቻችን ፍትሕ እንዲያገኙ ለማድረግ በጉራጌ ማኅበረሰብ ባሕል ከፍተኛው ሸንጎ እስከሆነው ኧጆካ አደባባይ ድረስ የተሟገተች ጀግና ናት፡፡

እንዳለ ጌታ የዚህችን የማናውቃትን ጀግናችንን የተጋድሎ ታሪክ ከልዩ ልዩ ምንጮች ሰብስቦ፣ ሥነ ቃሉን አስማምቶ፣ ከሀገራችን ታሪካዊ መዛግብት ጋር አዋሕዶ በልቦለድ መልክ አቅርቦልናል፡፡ ወጥ ልቦለዶች እያነሡ፣ የትርጉም ሥራዎች ቦታችንን እየወሰዱ ባሉበት ዘመን የራሳችንን ታሪክ መልሰን እንድናይ የሚያደርግ እንዲህ ያለውን ሥራ ማግኘት ለሥነ ጽሑፋችን አንድ እመርታ ነው፡፡

ሰው የሚያውቀውን ሲያቀርብ፣ የሚያቀርበውንም ሲያውቅ ደስ ይላል፡፡ የኖረበትን፣ የተሠራበትንና የተዋሐደውን ነገር ሲተርክ ከውስጡ ስለሚመነጭ ከዛፍ ሥር የሚመነጭን ውኃ እንደመጠጣት ይቆጠራል፡፡ አንድን ማኅበረሰብ በዕንግዳ ዓይን ማየት ተለምዶ የሚመስሉትን ነገሮች በሚገባ ለማንጠር ይረዳል፡፡ የውስጡ ሰው ለምዶት የሚያልፈውን ዕንግዳ ሰው ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ አንድን ማኅበረሰብ በውስጥ ሰው ማየት ደግሞ የሚያውቁትን፣ የኖሩበትንና ትርጉሙንም በሚገባ የሚያውቁትን ነገር እንደ ልብ ምት አዳምጦ ለማቅረብ ይረዳል፡፡ የቃቄ ወርድወት ታሪክ እንዲህ ሆኖ ነው የቀረበው፡፡ ማኅበረሰቡ የተሰፋበትን እያንዳንዷን ሰበዝ ታዩበታላችሁ፡፤ ያውም ሳይታወቃችሁ፡፡

የእንዳለ ጌታ መጽሐፍም የኖረበትንና ያጠናውን ማኅበረሰብ ያቀረበበት ስለሆነ ሁለት መቶ ዓመታትን ተሻግራችሁ ትነጉዱና ከቃቄ ወርድወት ጋር ለመብት ትታገላላችሁ፣ ጉራጌ ገብታችሁ ደመራ ታበራላችሁ፣ መስቀል ታከብራላችሁ፣ ክትፎ ትበላላችሁ፣ ከነገሥታቱና መኳንንቱ ጋር ትዋጋላችሁ፡፡ ኧጆካ ትወጣላችሁ፣ ጀፎረ ላይ ትቀመጣላችሁ፡፡

በጉራጌ ማኅበረሰብና በማዕከላዊው መንግሥት መካከል፣ በጉራጌ ማኅበረሰብና በሌሎች የአካባቢው ማኅበረሰቦች መካከል ፍቅርም፣ ጠብም፣ ጦርነትም፣ ዕርቅም ነበረ፡፡ እነዚህ ግንኙነቶች በማኅበረሰብ ውስጥ የሚፈጥሩትን አሉታዊና አዎንታዊ ነገሮች በእንዳለ ጌታ ዓይን ስናያቸው አንድን ታላቅ ማኅበረሰብ በመፍጠር ሂደት ውስጥ የተከናወኑ የሂደቱ መገለጫዎች እንጂ የቂም መቋጠሪያዎች ሆነው አናገኛቸውም፡፡ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ በሚገኙ ልጆች መካከል የሚኖር መጣላትና መዋደድ የልጆቹ የዕድገታቸው ሂደት አካል እንደሚሆነው ማለት ነው፡፡

በየአካባቢው የሚገኘውና የማናውቀው ታሪካችንና ባሕላችን እንዲህ ለነገዋ ሀገራችን መቀመሚያ በሚሆን፣ ያለፈውንም ለማወቂያና ለማረሚያ በሚያገለግል፣ በሌላ በኩል ደግሞ አቃፊ እንጂ አግላይ ባልሆነ መንገድ ቢቀርብልን የአንዱ አካባቢ ታሪክ የሁላችንም እየሆነ ‹የኢትዮጵያ› ስንል የሚጎድለን አይኖርም ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን ‹የኢትዮጵያ› ስንል የሚጎድሉን ነገሮች አሉ፡፡ አንድም አንዳንዶች ‹የኼማ የራሳችን ብቻ ነው› ብለው ቆርጠው በማስቀረታቸው፣ አንድም ደግሞ ‹የኢትዮጵያ› የተባለው ነገር አንዳንዶችን አግልሎ በማስቀረቱ፡፡ ሁለቱም ግን እኩል ነው የሚጎዱት፡፡ የጉራጌ ክትፎ የሁላችንም እንደሆነው ሁሉ የየአካባቢው ሥነ ቃል፣ ታሪክ፣ ባሕልና ቅርስ እየወጣ የሁላችንም እየሆነ መሄድና ወደ ዋናው አካል እየተቀለቀለ፣ ለዋናው አካል ግንባታም አስተዋጽዖ እያደረገ መሄድ አለበት፡፡ ማግለልም መገለልም አንድ ናቸው፡፡

የአካባቢውን ሥነ ቃል፣ ታሪክና ባሕል ከምናገኝባቸውና የራሳችን ከምናደርግባቸው መንገዶች አንዱ ኪነ ጥበባዊ በሆነ መንገድ ማግኘታችን ነው፡፡ ‹የእገሌ ብሔረሰብ ታሪክና ባሕል› እየተባሉ ብቻ የሚወጡ፣ ሲጀምሩ ሌላውን አውግዘው፣ ኮንነውና ጠልተው የሚነሡ ‹መጻሕፍት› አጥሩን በአደገኛ አጥር ከማጠናከር ያለፈ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ ቁስሉን ማሳየት እንጂ ማሻርም አይፈልጉም፡፡ ምናልባትም የጉዳዩ ባለቤት ነኝ ብሎ ከሚያስበው አካል በቀር የሌላውን ልብ ለመማረክም አይችሉም፡፡ ጎጣዊ ጀግና ከመፍጠር ባለፈ ሀገራዊ ጀግና አያስገኙም፡፡ በላይ ዘለቀን የጎጃም፣ ዐፄ ዮሐንስን የትግሬ፣ ቃቄ ወርድወትን የጉራጌ ብቻ አድርገው ለማስቀረት የሚያልሙ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያዊ ጀግና፣ ሀገራዊ ታሪክ፣ ሀገራዊም ማንነት ሊፈጠር የሚችለው እንዲህ የአንዱ አካባቢ ታሪክ የሌላው እንዲሆን አድርጎ በማቅረብና ለታሪኩና ሥነ ቃሉ ብቻ ሳይሆን ለአቀራረቡም ጭምር በመጨነቅ ነው፡፡ ‹ሲያዩት ያላመረ ሲበሉት ያቅራል› ይባል የለ፡፡ የእንዳለ ጌታን መጽሐፍ አንብቡት የምላችሁም ለዚህ ነው፡፡ በሞቴ አንብቡት፡፡  

ነሐሴ 23 ቀን 2006 ዓም ማለዳ 10 ሰዓት ነው ከዕንቅልፌ የነቃሁት፡፡ ዲያቆን  ሙሉቀን ብርሃን ከጎንደር፣ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ ከፍኖተ ሰላም መንገድ ላይ ይጠብቁኛል፡፡ ለመንገዱ የሚሆነውን የቱሪስት መኪና ያዘጋጀልኝ የኦሪጂንስ ኢትዮጵያ አስጎብኝ ድርጅትባለቤት ሳምሶን ተሾመ ነው፡፡ ክብር ይስጥልኝ ብያለሁ፡፡ የምተርክላችሁን ታሪክ ስትጨርሱ ትመርቁታላችሁ ብየ አምናለሁ፡፡ የምጓዘው አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ለማደርገው ጥናት ተጨማሪ መረጃዎችን ፍለጋ ነው፡፡

ሾፌራችን ደምስ ይባላል፡፡ ዝምታና ትኩረት ገንዘቦቹ የሆኑ፣ በሁሉም ነገር ለመንገድ የተዘጋጀ፡፡ ለተራራ ቢሉ ለቁልቁለት፣ ለበረሐ ቢባል ለደጋ የሚሆኑ መሣሪያዎችን ሸክፎ የያዘ ልምድ ያለው ሾፌር ነው፡፡

ዓባይ በረሐ መግቢያ ላይ

የምንጓዘው ከምድር ሥር ከሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎቻችን ወደ አንዱ ነው፡፡ በጎጃም በር በኩል ወጥተን ፍቼና ጎሐ ጽዮንን አቋርጠን በክረምት ውበቱ እጥፍ ድርብ ወደሚሆነው ዓባይ በረሐ መንደርደር ቀጥለናል፡፡ ዓባይ በረሐ የሚባል ቦታ መቼም አያልፍለት፡፡ አበሻ ቢሠራው፣ ጣልያን ቢሠራው፣ ጃፓን ቢሠራው መሬቱ እንደሆነ ድንጋይ ላይ እንዳስቀመጡት ሰው ሲንቀሳቀስ ይኖራል፡፡
ይንሸራተታል ተጠንቀቁ

ተሻገርንና ደጀንን አለፍናት፡፡ ከደጀን እስከ ደብረ ማርቆስ ያለው መንገድ በመሠራት ላይ ስለሆነ መኪኖቹን ሁሉ ለአካባቢው መንደሮች እጅ ሲያስነሣቸው ይውላል፡፡ አንዳንዱን መንገድ እንኳን መኪና ዝንጀሮም ያለ ስዕለት የሚወጣው አይመስልም፡፡ በግራ በቀኝ ሽው እልም እያሉ የሚከንፉት መኪኖች ሁሉ መዘጋጃ ቤት እንደ ረሳው ጎዳና በተቆፋፈረው መንገድ ላይ ሲደርሱ ለቆጠራ እንደወጣ እሥረኛ ሰልፍ ይይዛሉ፡፡ 
እኛም ስንችል ስንበር፣ ሳንችል ስንሰለፍ ደብረ ማርቆስን አልፈን ወደ ደምበጫ ማቅናቱን ተያያዝነው፡፡ ሙሉቀንና ስምዐ ኮነ ከአዲስ አበባ 360 ኪሎ ሜትር ርቀት ደምበጫ ላይ ነው የሚጠብቁን፡፡ እነርሱን ከምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት የቅርሳ ቅርስ ክፍል ኃላፊና ከደጋ ዳሞት ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ጋር አሳፍረን የባሕርዳርን መንገድ ትተን ወደ ቀኝ በመታጠፍ የፈረስ ቤትን መንገድ ተያያዝነው፡፡

ሰቀላ ማርያም ደን
ከፊት ለፊታችን የሰቀላ ማርያም ደን ጫፍና ጫፉን ገጥሞ በመካከሉ ሲያሳልፈን ሙሽራ ለመቀበል የወጣ የአዲስ አበባ ሚዜ ይመስል ነበር፡፡ በአንጀኒን በኩል አለፍንና ሰነቦ ተራራው ላይ ደረስን፡፡ መቼም የፈረስ ቤት የጠጠር መንገድ ከአንዳንዱ የአዲስ አበባ አስፓልት ይመረጣል፡፡ በስተግራችን ተራራውን ተደግፈን፤ በስተ ቀኛችን በረሐውን እያማተርን መኪናችንን ከአካባቢው ፖሊስ መጠበቂያ ጎን አቆምናት፡፡


አሁን ከባዱ መንገድ ሊመጣ ነው፡፡ የምንወርደው ከምድር ሥር ወደ ታች ነው፡፡ በተራራው ወገብ እየታከክን፣ እንደ ዝንጀሮ ተንሸራትተን እንደ ጦጣ እየዘለልን መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡ ዕቃዎቻችንን ሁሉ ሸከፍንና የማይቀረውን ቁልቁለት ተያያዝነው፡፡ ለጉልበት ፋታ የማይሰጠው ቁልቁለት መቅኔያችን ያለቀ እስኪመስለን ድረስ ያንተፋትፈናል፡፡ የገበሬዎችን እርሻና መንደር እያቆራረጥን፣ ወንዝና ገደሉን እየተሻገርን የተራራውን ሥር ለማግኘት እንኳትናለን፡፡

ውረድ- ወደ ሰነቦ
የተራራውን ወገብ ካለፍን በኋላ ዓለምን ተሰናብተናት ዓለምን ወደረሳና ዓለምም ወደረሳችው ክልል ወረድን፡፡ በጫካ የተሞላ፣ የፏፏቴ ድምጽ ከሩቅ የሚጣራበት፣ ወፎቹ በተሲዓት የሚዘምሩበት፣ የፋርስ ምንጣፍ የተነጠፈበት የሚመስል ሸለቆ ተቀበለን፡፡ እስካሁን ዋሻውን አላገኘነውም፡፡

ወደ ቀኝ ታጥፈን አንዲት ጅረት መሰል ውኃ ከተሻገርን በኋላ የግቢው መግቢያ በር ጋ ደረስን፡፡ ጭንቁ እዚህ ላይ ይጀምራል፡፡ እኔ ለራሴ ቁልቁለቱን ለመውረድ እንደ ቅቤ ቅል ስናጥ ስለቆየሁ ጉልበቴና እግሬ ተለያይተው ለየብቻ የሚሄዱ መምሰል ጀምረዋል፡፡ እዚህ ደግሞ ለከተማ ሰው የከበደ ቀኖና ጠበቀን፡፡ ከገዳሙ ክልል መግቢያ ጀምሮ በባዶ እግር ነው የሚገባው፡፡ ፊት ለፊት የማያቸው ደንጋዮች ሆያ ሆዬ እንደሚሉ ልጆች እጅብ እጅብ ብለው ቆመው፣ እንደ ፋስ መጥረቢያ የተሳሉ ናቸው፡፡ አንድ እግሬን የመግቢያው ርብራብ ላይ አሳርፌ ሁለተኛውን የት ላድርገው፡፡ በግራ በቀኝ የማያቸው ድንጋዮች እንደ ጥሬ ሥጋ ቆራጭ ቢላዋቸውን አሹለው ይጠብቁኛል፡፡ በብኾር ላይ ቆረቆር እንዲሉ ከተራራው ላይ ባለማቋረጥ የሚወርደው ውኃ አካባቢውን ስላራሰው እግሬ በብርዱ ወደ መደንዘዝ ደርሷል፡፡


መጨነቄን ያየው የቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪ የሆነው የዐቢ እንደ አቡነ ገሪማ አገልጋይ በግራ ጎኔ በኩል መጥቶ ደገፍ አደረገኝ፡፡ አይቀርምና እግሬን ወደ አንዱ ሹል ባልጩት ሰደድኩት፡፡ የእግሬ ድንዛዜና የባልጩቱ ስለት ተባብረው ዋጋዬን ሰጡኝ፡፡ ድምጽ እንደሰማች ዕንቁራሪት ዘልዬ ወደ ሌላው ድንጋይ ተሻገርኩ፤ እርሱም እንደ ጓደኞቹ በጠረባ አወራረደኝ፡፡ የዐቢ እየደገፈኝ፣ እኔ ጥርሴን ነክሼ እየዘለልኩ የውኃው ድምጽ እንደ ነጎድጓድ ከሚያስገመግምበት ሥፍራ ደረስን፡፡ ሰነቦ ተክለ ሃይማኖት፡፡


ጠበሉ ከቤተ ክርስቲያኑ በላይ ካለው ተራራ ላይ ነው የሚወርደው፡፡ በሦስት ቦታ ተጠማቂዎቹ ይገለገላሉ፡፡ ለሴቶች፣ ለወንዶችና ለካህናት የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በሌሎች የመጠመቂያ ቦታዎች ለካህናት የተዘጋጀ የተለየ ቦታ አልገጠመኝም፡፡ በዚህ ሰነቦዎች ይመሰገናሉ፡፡ የቤተ መቅደሱ በር ከተራራው ሥር ይታያል፡፡ ዋሻው ግራና ቀኝ ተገንብቶ በበር ተዘግቷል፡፡ በስተ ግራ በኩል የካህናት መግቢያ ሌላ ሰርጥ አለ፡፡ ዋናው በር ተከፈተልንና ገባን፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ስትገቡ በስተግራ ይገኛል፡፡ መጀመሪያ ቅኔ ማኅሌቱን፣ በእንጨት በተከለለው ሥፍራ ደግሞ መቅደሱን የዋሻው ውስጥ ደግሞ ቅድስቱን ታገኛላችሁ፡፡ 
የመቅደሱ ግንብ
ከቤተ ክርስቲያኑ በስተ ቀኝ ማለቂያው የማይታወቅ የዋሻ  ውስጥ መንገድ ይገኛል፡፡ ያውም መንገዱ በውኃ የተሞላ ነው፡፡ አንዳንድ አገልጋዮች የአራት ሰዓት መንገድ ተጉዘው መጨረሻውን ሊያገኙት እንዳልቻሉ ገልጠውልናል፡፡ እንደ አካባቢው ቃላዊ ታሪክ ከሆነ ዋሻው ከደብረ ሊባኖስ ጋር ይገናኛል፡፡ ገዳሙ ‹ሰነቦ ደብረ ሊባኖስ ተክለ ሃይማኖት ገዳም› የተባለውም ለዚህ ነው ይላሉ፡፡
የገዳሙን የምሥረታ ጊዜ በትክክል ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ አገልጋዮቹ ከሚተርኩት ትረካና በትረካቸው ውስጥ ከሚጠሯቸው ሰዎች ስንነሣ ግን ከግራኝ ዘመን ቀደም ብሎ የተተከለ መሆኑን ለመገመት ይቻላል፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ የተተከለው በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን(1674-1698ዓም) መሆኑን አንዳንድ የገዳሙ መዛግብት ያሳያሉ፡፡ አድያም ሰገድ ኢያሱ በዚህ ዋሻ ውስጥ አንድ መነኩሴ ጽላት እንደያዙ መስቀል ጨብጠው ዐጽማቸው እንደሚገኝ የሰሙትን ለማረጋገጥ ከጎንደር ተነሥተው መጡ፡፡ ሲመጡም የሰሙት ትክክል መሆኑን አዩ፡፡ ገዳሙን ገድመው፣ ርስት ሰጥተው አከበሩት፡፡ በወቅቱ 500 መነኮሳት ነበሩት(300 ወንዶችና 200 ሴቶች)፡፡

ወደ ዋሻው በዐለት ፍላጭ ላይ ጉዞ
አድያም ሰገድ ኢያሱ ያሠሩት የቤተ መቅደሱ ግንብ ፍርስራሹ አሁንም ይታያል፡፡ የመንበሩን ሥዕል ያሠሩት ወ/ሮ መለኮታዊት (ያረፉት በ1618 ዓም ነው) መሆናቸውን የገዳሙ ካህናት ይገልጣሉ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የገዳሙ ትክል ከአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን ቀደም ይላል ማለት ነው፡፡ ወ/ሮ መለኮታዊት የነበሩት በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን ነው፡፡ ካልሆነ ደግሞ በዐፄ ቴዎፍሎስ ዘመን የነበሩትና በ1701 ያረፉት መለኮታዊት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በአንዳንዱ የገዳሙ መጻሕፍት ላይ ከዐፄ ፋሲል የተሰጠ መሆኑን ስለሚገልጥ ታሪኩ ከአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን ቀደም ያለ መሆኑን ያሳየናል፡፡

የዋሻው ውስጥ መንገድ
ምሽቱን የአካባቢው ሕዝብ ከዝናብና ጭቃ ጋር እየታገለ ለክብረ በዓሉ ሲጎርፍ ነው ያመሸው፡፡ ያች ዋሻ ከአፍ እስከ ገደፏ ሞላች፡፡ ማኅሌቱ ሌሊቱን በሙሉ ከዋሻው ሲሰማ አደረ፡፡ ቅዳሴውን ያስቀደስነው ከታች ካለው ቅዝቃዜና ከጎን ከሚመጣው ብርድ ጋር እየታገልን ነው፡፡ ፈውስ ፍለጋ ከየቦታው የመጡት ሕሙማን እንደ ሰሊሆም መጠመቂያ ማለዳውን ይጠብቃሉ፡፡ ቅዳሴው እንዳለቀ የሚጀመረውን የዋሻ ውስጥ ጥምቀት፡፡

የሌሊት ማኅሌት
ቅዳሴው አብቅቶ ትምህርት ከተሰጠ በኋላ ለደመራ የሚበራውን ችቦ የሚያስንቁ አራት አምስት ችቦዎች በርተው መጡ፡፡ ሕዝቡም ወደ ዋሻው መንገድ ተሰባሰበ፡፡ ከግራ ከቀኝ በአገልጋዮች ተደግፌ ከተሳሉት የዋሻ ውስጥ ድንጋዮች ላይ እግሬን እያሳረፍኩ፣ በብርዱ የደነዘዘውን እግሬንም ትቼው የመጣሁ እስኪመስለኝ እየረሳሁ ከካህናቱ ጋር ወደ ዋሻው ውሳጣዊ ክፍል ገባን፡፡ በዐለቶች ላይ እንደ ጦጣ ተንጠላጥለን የጠበሉ ጫፍ ላይ ደረስን፡፡

ይህ አሁን ከፊታችን የሚታየው ጠበሉ ነው፡፡ ተጠማቂው ወገቡን በገመድ ይታሠርና ወደ ጠበሉ ይገባል፡፡ ወገቡን የሚታሠረው የዋሻው ጥልቀት ስለማይታወቅ ነው፡፡ አንድ ሰው አራት ሸንበቆ ተቀጣጥሎ ወለሉን እንዳልደረሰበት ነግረውኛል፡፡ በኋላ እንደገመትነው ጥልቀቱ ከ20 ሜትር በላይ ነው ማለት ነው፡፡ ጥልቀቱ ብቻ ሳይሆን የዋሻው መጨረሻም አይታወቅም፡፡ ቆርጦ ከሄደ መመለሻውን እንጃ፡፡ ‹ተክልየ ነው የሚይዙት›› ብለውኛል፡፡ እውነትም፡፡
በጨለማው ውስጥ ወደ ጠበሉ ጉዞ
ካህኑ መስቀል ይዘው እያጠኑ መጡ፡፡ ተጠማቂውም እየጮኸ ወገቡን በገመድ ታሥሮ ቀረበ፡፡ እርሳቸው ወደ ጠበሉ ዳር ገቡና ተጠማቂውን ጠሩት፡፡ ገባ፡፡ ታሪክ ተጀመረ፡፡ መስቀል ከመያዝና ጸሎት ከመድገም በቀር ካህኑ ምንም አላደረጉትም፡፡ እርሱ ግን መናገር ጀመረ፡፡ የተደረገበትን፣ ማን መድኃኒት እንዳደረገበት፣ ለምን እንዳደረገበት፣ ይለፈልፍ ጀመር፡፡ በአራት ጎረምሶች ተይዞ የገባው ጎልማሳ ኅሊናው ተመልሶለት ራሱ ከጠበሉ ወጣ፡፡ እንዲህ እያለ አንድ ሦስት ሰው ተጠመቀ፡፡

ካህኑ ወደ ጠበሉ ሲገቡ

ካህኑ በቃ አሉ፡፡ እንደሰማነው በወር አንድ ወይም ሁለት ቀን ወደ ዋሻው ጠበል ይገባል፡፡ እዚያ ገብቶ ሳይድን የሚወጣ የለም፡፡ ሕሙማኑም እነዚያን ሁለትና ሦስት ቀናት በተስፋ ነው የሚጠብቋቸው፡፡
በውኃው ላይ ወደ ጠበሉ ጉዞ

ከአንድ ሰዓት በኋላ ከዋሻው ወጣን፡፡ እኔም ከሹሉ ድንጋይ ላይ ዝናብ፣ ብርድና ጭቃ ተጨምረውበት እየዘለልኩና እየተደገፍኩ የገዳሙን ክልል ለቅቀን ወጣን፡፡ ወደ ማረፊያችን ገብተን ምሳ ከበላን በኋላ ከጫማችን ጋር ተገናኘን፡፡ ለካስ ጫማም ይናፍቃል፡፡

ተጠማቂው በገመድ ታሥሮ ወደ ጠበሉ ኩሬ ሲገባ

ስንመጣ ቁልቁል ያየነውን አሁን ቀና ብለን ልናየው ነው፡፡ በትናንቱ መንገድ ላይ ዝናብና ጭቃ ተጨምሮበታል፡፡  የጫማዬ መልክና ቁመና ጠፍቶ ከተራራው ጋር እየታገልኩ መውጣት ቀጠልኩ፡፡ አንድ ጎኔን የዐቢ ደግፎኝ በአንድ እጄ መቋሚያ ይዣለሁ፡፡ የተጎረዱ መሬቶችን መዝለል፣ በጭቃው ተንሸራትቶ ወደ ኋላ መመለስ፣ ከፊት ለፊት እንደ ጅብራ የተገተረ ተራራን ማየት እንዴት አድካሚ መሰላችሁ፡፡ 
ተራራውን ከታች ወደ ላይ ሲያዩት

ይባስ ብለው ሙሉቀንና ስምዐ ኮነ እየጣሉኝ ወደ ተራራው ጫፍ መድረሳቸውን ሳይ የምደርስ አልመስልህ አለኝ፡፡ የዐቢ እኔን ደግፎ ተራራውን ለመውጣት ይፈጋል፡፡ የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የአካባቢው ካህናት ‹በርታ በርታ› ይላሉ፡፡ አሳብ የለሽ ሀብታሙ ደግሞ ከጎኔ ሆኖ ‹ምክርና ቡጢ ለሰጭው ይቀላል› ይላል፡፡ ልቤ እንደ ጾም ፍርፍር ፍርስ ልትል ነው፡፡

በተስፋ፣ ከታች ወደ ላይ

ተመስገን የተራራው መጨረሻ ላይ ደረስኩ፡፡ የቀደሙኝን ሁሉ መንገዱ ዳር መኪናው ጋ አገኘኋቸው፡፡ ጫማየን አውልቄ በፌስታል ጠቅልየ መኪናው ላይ ጣልኩት፡፡ ከዚያም ወደ ኋላ ተመልሼ የመጣነውን ተራራ አየሁት፡፡ 
ሸለቆው ከሩቁ

ድካሙ ሲቀነስ ውበቱ አሁንም አለ፡፡ ከእኔ እናንተ ትበረታላችሁና ሰነቦን እዩት፡፡ በተለይ ከአኩስምና ላሊበላ በጎንደርና ባሕርዳር በኩል የምትመጡ ተጓዦች ጎራ ብትሉ ቅርብ ነው፡፡ ሌሎቻችሁም ዛሬ ሄዳችሁ ነገ መምጣት ትችላላችሁና ተነሥታችሁ ሂዱ፡፡ ውጣ ውረዱ ራሱ እንዴት ልዩ ትዝታና በረከት መሰላችሁ፡፡ ደኅና እንሰንብት፡፡
ተራራው ላይ ደረስን


የመግቢያ ማስታወሻ

በጽሑፉ ውስጥ በግእዝ ቁጥሮች በቅንፍ ውስጥ የተጻፉት ሐሳቡን እንዲወክሉ ብቻ ነው፡፡ በኋላ (ቁጥር ፭ ተመልከት ቢል ያንን ሐሳብ መልሶ ለማየት እንዲረዳ ነው፡፡

የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ጳጉሜ የምትባል አሥራ ሦስተኛ ወር ስላለችን ነው፡፡ የቤት ኪራይና የወር ደመወዝ የማንከፍልባትና የማንቀበልባት፤ መብራትና ውኃ ግን ከነሐሴ ወር ጋር ጨምረው የሚያስከፍሉባት፤ ሲሻት አምስት፣ ሲያስፈልጋት ስድስት፣ ስትፈልግ ደግሞ ሰባት የምትሆን ወር ናት፡፡ እንዲያውም ከአሥራ ሁለቱ የኢትዮጵያ ወሮች ጳጉሜ በብዙ መንገድ የተለየች ናት፡፡

በአንድ በኩል በጣም ትንሿ ወር ናት፡፡ ሲቀጥልም ወርኃዊ በዓላት የማይውሉባት ወር ናት፡፡ እንዲያም ሲል ደግሞ ከሌሎች ወሮች በተለየ የቀኖቿ መጠን የሚቀያየሩ ብቸኛ ወር ናት፡፡ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወሮች በተለየም ስሟ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ወር ናት፡፡ በሁለት ዘመናት መካከልም እንደ መሸጋገሪያ የምትታይ ወርም ናት፡፡  

ጳጉሜ ማለት በግሪክ ‹ጭማሪ› ማለት ሲሆን ዓመቱን በሠላሳ ቀናት ስንከፍለው የሚተርፉትን ዕለታት ሰብስበው የሰየሟት ተጨማሪ ወር ናት፡፡ ወይም በየዕለቱ በፀሐይና በጨረቃ አቆጣጠር መካከል የሚፈጠረውን ልዩነት ሰብስበው ያከማቹባት ወር ትባላለች፡፡ ዓመቱ በዐውደ ፀሐይ ሲለካ 365 ቀናት ከ15 ኬክሮስ 6 ካልዒት ሲሆን በጨረቃ ሲለካ ደግሞ 354 ቀናት ከ22 ኬክሮስ፣ 1 ካልዒት፣ 36 ሣልሲት፣ 52 ራብዒት፣ 48 ኀምሲት ነው፡፡ (60 ኬክሮስ አንድ ቀን ነው)በሁለቱ መካከል(በፀሐይና በጨረቃ) በዓመት ውስጥ ያለው ልዩነት 11 ቀናት ከ7 ኬክሮስ ይሆናል፡፡ [በነገራችን ላይ በዘመን አቆጣጠራችን ውስጥ ከዕለት በታች የምንቆጥርባቸው ስድስት መለኪያዎች አሉ፡፡ ኬክሮስ፣ ካልዒት፣ ሣልሲት፣ ራብዒት፣ ኀምሲትና ሳድሲት፡፡ 60 ሳድሲት አንድ ኀምሲት፣ 60 ኀምሲት አንድ ራብዒት፣ 60 ራብዒት አንድ ሣልሲት፣ 60 ሳልሲት አንድ ካልዒት፣ 60 ካልዒት ደግሞ 1 ኬክሮስ ይሆናል፡፡ 60 ኬክሮስ ደግሞ 1 ዕለት፡፡ 1 ኬክሮስ 24 ደቂቃ ነው]

ጳጉሜን ለማግኘት የሚጠቅመን የየዕለቱን ልዩነታቸውን መመልከቱ ነው፡፡ በየዕለቱ በጨረቃና በፀሐይ መካከል 1 ኬክሮስ 52 ካልዒት(60 ካልዒት አንድ ኬክሮስ ነው)፣ ከ 31 ሣልሲት(60 ሣልሲት አንድ ካልዒት ነው) ይሆናል፡፡[ይህም ማለት 5 ሰዓት ከ48 ደቂቃ ከ46 ካልዒት(ሴኮንድ?)] ይህ ልዩነት በአንድ ወር ምን እንደሚደርስ ለማወቅ በ30 እናባዛው፡፡ 30 ኬክሮስ፣ 1560 ካልዒት፣ ከ930 ሣልሲት ይሆናል፡፡ የዓመቱን ለማግኘት ደግሞ በ12 እናባዛው፡፡ 360 ኬክሮስ(፩)፣ 18720 ካልዒት(፪)፣ 11160 ሣልሲት(፫) ይመጣል፡፡

ቀደም ብለን 60 ኬክሮስ አንድ ዕለት ይሆናል ባልነው መሠረት 360 ኬክሮስ ለ60 ሲካፈል 6 ዕለታትን ይሰጠናል(፩)፡፡ 18720 ካልዒትን(፪) በስድሳ በማካፈል 312 ኬክሮስን እናገኛለን፡፡ ያም ማለት ትርፉን 12 ኬክሮስ ትተን 300ውን ኬክሮስ ለ60 በማካፈል 5 ዕለት እናገኛለን፡፡ ይኼም ማለት 5 ዕለት ከ12 ኬክሮስ(፬) ይሆናል፡፡ 11160 ሣልሲትን(፫)ለ60 ብናካፍለው 186 ካልዒት ወይም ደግሞ 3 ኬክሮስና 6 ካልዒት(፭) ይሆናል ማለት ነው፡፡

ከላይ ኬክሮስን በዓመቱ ቀናት አባዝተን ያገኘነው(፩) 6 ዕለት አለ፡፡ ይኼ ዕለት ሕጸጽ ይባላል፡፡ ፀሐይና ጨረቃን እኩል መስከረም አንድ ላይ ዓመቱን ብናስጀምራቸው ፀሐይ የወሯ መጠን ምንጊዜም ሠላሳ ሲሆን ጨረቃ ግን በአንደኛው ወር 29 በሌላኛው ወር ግን 30 ስለምትሆን ዓመቱ እኩል አያልቅም የጨረቃ ዓመት ነሐሴ 24 ቀን ያልቃል፡፡ ይህም ማለት ጨረቃ በሁለት ወር አንድ ጉድለት ታመጣለች፡፡ ያንን ነው ሊቃውንቱ ሕጸጽ(ጉድለት) ያሉት፡፡ በዚህም መሠረት ከላይ ኬክሮሱን(፩) በዓመቱ ቀናት አባዝተን ያገኘነውን 6 ዕለት ለጨረቃ ሕጸጽ ስንሰጠው የመስከረም/ ጥቅምት (1)፣ የጥቅምት/ ኅዳር(2)፣ የጥር/ የካቲት(3)፣ የመጋቢት/ ሚያዝያ(4)፣ የግንቦት/ ሰኔ (5)፣ የሐምሌ ነሐሴ (6) ሆነው ተካፍለው ያልቃሉ፡፡

በሌላም በኩል ደግሞ በጨረቃና በፀሐይ ዑደት መካከል በዓመት ያለው ልዩነት 11 ቀናት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት) ይሆናል፡፡ ስድስቱን ዕለታት ጨረቃ ለምታጎልበት (ሕጸጽ) ብንሰጠው ቀሪ 5 ዕለት ይኖረናል፡፡ ጳጉሜ ማለት እነዚህ 5 ቀናት ናቸው፡፡ አሁን የአሥራ አንዱን ዕለታት ከፈጸምን ሽርፍራፊዎቹን (15 ኬክሮስና 6 ካልዒት) እንይ፡፡

ከላይ እንዳየነው በፀሐይና ጨረቃ ዓመታት መካከል የተፈጠሩትን 11 ቀናት ስድስቱ ለሕጸጽ ማሟያ ሲገቡ የቀሩት 5 ዕለታት ናቸው ጳጉሜ የምትባለውን ወር በመሠረታዊነት የፈጠሯት፡፡ በጎርጎርዮሳውያኑ አቆጣጠር እነዚህ 5 ተጨማሪ ዕለታት በጃንዋሪ፣ ማርች፣ ሜይ፣ ጁላይና ኦገስት ላይ ስለተጨመሩ እነዚህ ወራት 31 ለመሆን ተገድደዋል፡፡ (ይህንን የከፈለው በ46 ቅልክ የነበረው ዩልየስ ቄሣር ነው፡፡ ለአራቱ ወሮች 30 ቀን፣ ለአንዱ 28/29 (በየአራት ዓመቱ)፣ ለቀሩት ሰባት ወሮች ደግሞ 31 ሰጥቷቸዋል፤ ለአምስቱ ወሮች 31 ያደረጋቸው ከጳጉሜ ወስዶ ሲሆን ለሁለቱ ወሮች አንዳንድ ቀን የጨመረላቸው ከፌቡርዋሪ 2 ቀናት ወስዶና ወሩን 28 አድርጎ ነው)፡፡

ከእንግዲህ የሚቀሩን ከላይ የየዕለቱን ልዩነት ለዓመት ስናባዛ (ቁጥር ፪ና ፫ ተመልከት) የቀሩን 15 ኬክሮስና 6 ካልዒት ናቸው፡፡ ሁለቱን  ከላይ ያየናቸውን (፬ና፭) ስንደምራቸው (12 ኬክሮስ + 3 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት) 15 ኬክሮስ ከ 6 ካልዒት ይመጣሉ፡፡

ቀደም ብለን አንድ ዕለት 60 ኬክሮስ ነው ብለናል፡፡ ስለዚህም አንድ ዕለት (60 ኬክሮስ) ለማግኘት ከላይ ያገኘነውን 15 ኬክሮስ በ 4 ማባዛት አለብን፡፡ በአራት ዓመት አንዴ ጳጉሜ 6 የምትሆነው እነዚህ በየዓመቱ የተጠራቀሙት 15 ኬክሮሶች አንድ ላይ መጥተው በአራት ዓመት አንድ ጊዜ አንድ ዕለት ስለሚሆኑ ነው፡፡ እርሷም ሠግር(leap year) ትባላለች፡፡ ጎርጎርዮሳውያኑ ይህቺን ሠግር በፌቡርዋሪ ወር ላይ ጨምረው ወሩን በየአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ 29 ቀን ያደርጉታል፡፡

15ቱ ኬክሮስ በአራት ዓመት ተደምረው አንድ ዕለት መጡና በአራት ዓመት አንዴ ጳጉሜን ስድስት አደረጓት፡፡ የቀረችው 6 ካልዒትስ (ቁጥር ፭) የት ትግባ?

ካልዒት አንዲት ዕለት ትሆን ዘንድ 3600 ካልዒት ያስፈልጋሉ፡፡ ይህንን ያህል ካልዒት ለማግኘት 600 ዓመታት ያስፈልጉናል፡፡ ለዚህ ነው ጳጉሜ በየስድስት መቶ ዓመታት ሰባት የምትሆነው፡፡ እስካን የጠየቅኳቸው የባሕረ ሐሳብና የታሪክ ሊቃውንት በታሪካችን ውስጥ ጳጉሜን 7 የሆነችበትን ዘመን እንደማያውቁ ነግረውኛል፡፡ ሒሳቡ ሲሰላ በየ 600 ዓመቱ ሰባት ትሆናለች ቢባልም አስቦ በስድስት መቶኛው ዓመት ሰባት የሚያደርጋት እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ በፈረንጆቹ ብሂል ‹ፌብሩዋሪ 30› ማለት የመሆን ዕድል ያለው ነገር ግን ሆኖሞ የማያውቅ ሊሆንም የማይችል(possible but never happen)› ተደርጎ እንደተወሰደው ሁሉ ምናልባት በኛም ጳጉሜን 7 ማለት እንደዚያው ይሆን ይሆናል፡፡

በነገራችን ላይ ጳጉሜን 5 ቀን በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ ‹ዕለተ ምሪያ› ወይም የተመረጠች ቀን ትባላለች፡፡ የጌታችን ልደት ለመጠበቅ ሊቃውንቱ ሲያሰሉባት የቆየችው ዕለት በመሆኗ ነው ይህንን ስያሜ ያገኘችው፡፡ የጌታችንን ልደት ቀን የምትወስነው ጳጉሜ 5 ቀን ናት፡፡ ልደት የሚውለው ጳጉሜ 5 በዋለበት ቀን ነው፡፡ ለምሳሌ ዘንድሮ ጳጉሜን 5 ቀን ረቡዕ ነው የምትውለው፤ ስለዚህም በ2007 ዓም ልደት የሚውለው ረቡዕ ነው፡፡ በየአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ ጳጉሜን 6 ስትሆን ልደት በ28 የሚከበረው ዕለተ ምሪያን ስለማይለቅ ነው፡፡ ስድስተኛዋ ቀን ልደትን በአንድ ቀን ስታዘልለው እኛ በ28 እናከብረዋለን፡፡ ልደት ጳጉሜ 5 ቀንን(ዕለተ ምሪያን) ስለማይለቅ፡፡ ታድያ ምነው እነ ጥምቀትና ግዝረት አይለወጡም? ቢሉ፡፡ ሊቃውንቱ የሚሰጡት መልስ ‹ትውልድ ሱባኤ እየቆጠረ በተስፋ የጠበቃት ዕለተ ልደትን ስለሆነ ነው፤ ሌሎቹ የመጡት በልደቱ ምክንያት ነው›› የሚል ነው፡፡

በጎርጎርዮሳውያንም ቢሆን በአራት ዓመት አንዴ ልደት ዝቅ ትላለች፡፡ የእነርሱ የማይታወቀን ጭማሪዋ ፌብርዋሪ ላይ ስለሆነች ነው፡፡ ያ ደግሞ አዲሱን ዓመት ካከበሩ በኋላ ስለሚመጣ ነው፡፡ የእኛ ግን የምትወድቀው ጳጉሜን መጨረሻ ላይ በመሆኗ ከአዲስ ዓመት በፊት ስለምትጨመር ጎልቶ ይታወቃል፡፡

እንግዲህ ጳጉሜ የምትባለው አስገራሚ ትንሷ ወራችን እንዲህ በስሌት የተሞላች፣ አምስት ሆና ቆይታ በየአራት ዓመቱ አንዴ ስድስት፣ በየስድስት መቶ ዓመቱ ደግሞ ሰባት የምትሆን ናት፡፡ ታላላቆቹ ወሮች ምንም ሳይፈጥሩ የልደትን ቀን የምትወስን፣ የዓመቱን ሠግር የምታመጣ፣ ታሪከኛ ወር ናት፡፡ ትንሽ ትልቅ ማለት እንዲህ ነው፡፡

ዝሆኖች አንድ የታመመ ወይም የቆሰለ ወገን ካላቸው እስኪድን ድረስ ይከባከቡታል፡፡ ምግብ ያቀርቡለታል፤ ከአደጋም ይጠብቁታል፡፡ ለዚህ ሁሉ ድካማቸው በኩምቢ የሚገለጥ ‹እግዜር ይስጥልኝ› በቂያቸው ነው፡፡ አንድ ቀን ግማሽ ኪሎ ብርቱካን ይዘን የጠየቅነውን በሽተኛ ሁሉ ውለታችንን ካልመለሰ ለምንል ሰዎች ከእኛ የሚሻሉ እንስሳት መኖራቸውን ማወቅ እንዴት መልካም መሰላችሁ፡፡

ዝሆኖች ይቅር ባዮች ናቸው፡፡ ዝሆን አደጋ የደረሰበትንም ያደረሰበትንም አይረሳም ይባላል፡፡ ጊዜ ጠብቆ የመበቀል አመል አለው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ችግር የፈጠረባቸው ኅብረተሰብ ወይም ግለሰብ ሲከባከባቸውና ለእነርሱ መልካምን ነገር ሲያደርግ ከተመለከቱ በቀላቸውን ሁሉ ለመተውና ይቅር ለማለት ፈጣኖች ናቸው፡፡ ይቅርታ ለመበቀል አለመቻል አይደለም፡፡ አለመፈለግ እንጂ፡፡ ይቅርታ ከዐቅም ማጣት ሳይሆን ከዐቅም ማግኘት የሚፈጠር ነው፡፡ በዝሆኖች መንጋ መካከል ችግር ፈጣሪ ከተገኘና ከተቀጣ ሁሉም ዝሆኖች ያገሉታል፡፡ ተስተካክሎ ከመጣ ግን ኩምቢያቸው በማነካካት ይቅር ማለታቸውንና መተዋቸውን ይገልጡለታል፡፡ ከዚያ በኋላ አለቀ፡፡ ሰውን ‹እንስሳ› ብለን የምንሳደብ እኛ ለይቅርታ የተዘጋጀ ልብ የለንም ማለት ከዝሆን ያነስን ነን ማለታችን ነው፡፡

ጉልበተኛነት ነውር ነው፡፡ በዝሆኖች ዘንድ ከባዱን ቅጣት የሚያስቀጣው በሌላው ወገን ላይ የኃይል ጥቃት ማድረስ ነው፡፡ ድብድብ ፈጽሞ ነውር ነው፡፡ በተለይም ወጣት ዝሆኖች ሲደባደቡ ከተገኙ መሪዋ እናት ዝሆን  ትቀጣቸዋለች፡፡ በቀላል ቅጣት ያልታረመ ጉልበተኛ ከመንጋው እስከመገለለ የሚደርስ ከባድ ቅጣት ሊጠብቀው ይችላል፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ከእርሱ ጋር የሚሠማራ አያገኝም፡፡ ‹ዝሆኖቹ ሲጣሉ የሚጎዳው ሣሩ ነው› የሚለው አባባል ዱርዬ ዝሆኖችን ብቻ የሚመለከት ነው፡፡ ዝሆኖቹ ሣሩ እስኪጎዳ ድረስ በዝምታ የሚያዩ አይደሉም፡፡ ርምጃ ይወስዳሉ፡፡ በእነርሱ ዘንድ ሕግና ሥርዓት እንጂ ጉልበት ቦታ የለውም፡፡ ዐቅም ስላለህ፣ ጉልበት ስላለህ ወይም ታላቅ ስለሆንክ ወይም ደካማ ስላገኘህ ብቻ ተነሥተህ ቡጢህን ማሳረፍ አትችልም፡፡ በሥርዓት መቅጣት የመንጋው መሪ ድርሻ ነው፡፡ ማንም ጉልበት ያለው ሁሉ ተነሥቶ ጉልበቱን አይሞክርብህም፡፡ አንዳንዴ ጉልበተኛ የሚበዛው አለቃ ሲበዛ ነው፡፡ ሁሉም ቀጭ ሲሆን፣ ሁሉ አሣሪ ሲሆን፣ ሁሉም ፈራጅ ሲሆን፣ ሁሉም አስከፋይ ሲሆን፣ ሁሉም ሰጭና ነሽ ሲሆን ‹ምነው ዝሆን በሆንኩ› ያሰኛል፡፡

በዝሆን የአንዱ ችግር የሁሉም ነው፡፡ ችግርን በመረዳዳት ከሚወጡ እንስሳት ወገን ናቸው – ዝሆኖች፡፡ ‹የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ› ብለን እኛ ላለመስማት ምሳሌ ብናደርገውም የዝሆን ጆሮ ግን ለመስማትም ሙቀቱን ለማብረድም የሚረዳው አካል ነው፡፡ የዝሆን ጆሮ ከእግሩና ከኩምቢው ጋር ተጣምሮ ከሩቅ ድምጾችን ለመስማት ይችላል፡፡ እንዲያውም እጅግ በጣም ሹክሹክታዊ የሆኑ (low pitch) ድምጾችን የመስማት ችሎታ አለው፡፡ በአማካኝ አንድ ዝሆን ከ4 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚመጡ ድምጾችን የመስማት ዐቅም አለው፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎችም እስከ ዐሥር ኪሎ ሜትር ድረስ መስማት እንደሚችል ተረጋግጧል፡፡ አንድ ዝሆን ከሌላው ዝሆን ከሚወጣው የድምጽ ቅላጼ በመነሣት የቦታውን ርቀት እስከመገመትም ይደርሳል፡፡
አንድ ዝሆን ችግር ሲደርስበትና ርዳታ ሲፈልግ የሚያሰማው ልዩ የሆነ ድምጽ አለ፡፡ እያንዳንዱ ችግር በተለየ ድምጽ ነው የሚገለጠው፡፡ ያንን የሰማ ማንኛውም ዓይነት ዝሆን ለርዳታ ይንቀሳቀሳል፡፡ ለጠላት የተጋለጠውን፣ በአረንቋ የተያዘውን፣ ወንዝ ማቋረጥ ያቃተውን፣ መንገድ የጠፋበትን ለመርዳታ ከየአቅጣጫው የዝሆን መንጋ ይተማል፡፡ ተረዳድተው ከአደጋ ካተረፉት በኋላ ኩምቢ ለኩምቢ በሚደረግ መተሻሸት ብቻ ውለታው ይከፈላል፡፡ ‹እግዜር ይስጥልኝ› መሆኑ ነው፡፡ ያውም ከአደጋ የተረፈው ብቻ ሳይሆን ሁሉም ለአደጋ መከላከል የመጡ ዝሆኖች ችግሩን እንደራሳቸው ቆጥረው አጋና ይመታታሉ፡፡ የአንዱ ችግር የሁላችንም ነው ማለታቸው ነው፡፡ ‹አይመለከተኝም፣ አላውቀውም፣ ዘመዴ አይደለም፣ ምን ይከፈለኛል፣ በኋላ ጣጣ ቢመጣብኝስ፣ ከዚህ በፊት ለእኔ ማን ደረሰልኝ፣ ሁሉም ሥራው ያውጣው፣ ይኼ የእገሌ ድርሻ ነው› ለምንል ሰዎች ‹ወደ ዝሆን ተመልከቱ› የሚል ጸሎት ሳያሻን አይቀርም፡፡


ዝሆን አደጋን የመለየት ዐቅም አለው፡፡ በቅርብ ዘመናት የተደረጉ ጥናቶች ዝሆኖች አደጋን ቀድመው የመለየት ወይም ደግሞ አደጋዎችን ለይተው ተገቢ መፍትሔ የመስጠት ዐቅም እንዳላቸው አሳይተዋል፡፡ ከሁሉም ጋር አይጋጩም፤ ሁሉንም ንቀው አይተውም፤ ሁሉንም አይፈሩም፣ ሁሉንም አያባርሩም፤ ከሁሉም አይሸሹም፤ ከሁሉም ጋርም አይፋለሙም፡፡ የትኛው ዓይነት አደጋ ቀላል፣ የትኛውም አስጊ እንደሆነ ለይተው እንደ ሁኔታው ይቀበሉታል እንጂ፡፡

በኬንያ ማሳይና ካምባ የሚባሉ ጎሳዎች አሉ፡፡ ማሳዮች በዝሆን አደን የታወቁ ናቸው፡፡ ካምባዎች ደግሞ ዝሆኖችን ማደንን እንደነውር ይቆጥራሉ፡፡ ዝሆኖቹ ይህንን ሁኔታ አስተዋሉ፡፡ አደጋ የሚመጣበትንና የማይመጣበትን ማኅበረሰብ ለዩ፡፡ ሁለቱ ማኅበረሰቦች የሚኖሩበትን ክልልም ተረዱ፡፡ በመጨረሻም አያሌ ዝሆኖች ከማሳይ ጎሳ አካባቢዎች በመሸሽ ወደ ካምባ ጎሳዎች ክልል ገቡ፡፡ ጠቢባን እንዲህ ይላሉ ‹ብዙ ጊዜ ውድቀት የሚመጣው ምን ማድረግ እንዳለብን ባለማወቃችን ምክንያት አይደለም፤ ምን ማድረግ እንዳለብን የምናውቀውን ነገር ባለማድረጋችን እንጂ›፡፡ በችግር ውስጥ ተተብትቦ ከመነጫነጭ፣ ከማማረር፣ ከማላዘንና ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ከተቻለ አስቀድሞ ማወቅ፤ ካልተቻለም ከችግሩ በኋላ አመጣጡንና መንሥኤውን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በችግሩ ላይ አጠንጥኖ ‹አይይ› እያሉ ቀንን ከመርገምና እንዴት እንደማይቻል ከማሰብ ይልቅ በግድግዳው መሐል ስንጥቅ፤ በግንቡ መካከልም ቀዳዳ መኖሩ ስለማይቀር ያንን መፈለግ እጅግ የተሻለው ነው፡፡ ለሁሉም በሽታ አንድ ዓይነት መድኃኒት እንደሌለው ሁሉ ለሁሉም ችግር አንድ ዓይነት መፍትሔ የለውም፡፡ መጀመሪያ ማጥናት፣ ከዚያም ማወቅ፣ ቀጥሎም በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ መወሰን፣ በመጨረሻም የወሰኑትን መፈጸም- ያ ነው መንገዱ፡፡

ዝሆኖች በጥቂት ያገኙትን በብዙ በመከባከብ እልፍ ያደርጉታል፡፡ ከአጥቢ እንስሳት ሁሉ የዝሆንን ያህል ረዥም ጊዜ የሚያረግዝ የለም፡፡ የእርግዝናዋ ወራት 22 ወራት ነው፡፡ አንድ ዓመት ከዐሥር ወር ማለት ነው፡፡ ያውም ደግሞ ቤተሰብ መምሪያ ያላወቀውን የቤተሰብ ምጣኔ ስለሚጠቀሙ ነው መሰል የሚወልዱት በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ዝሆኖች በጥቂቱ ያገኙትን በብዙ ክብካቤ ማበርከት ባይችሉበት ኖሮ የዝሆን ጥርስ አደን ተጨምሮበት ዛሬ ከምደረ ገጽ በጠፉ ነበር፡፡ ዋናው ጥያቄ ምን አለህ? አይደለም፡፡ እንዴት ይዘህ እንዴትስ ትጠቀምበታለህ? ነው እንጂ፡፡ ‹ከአያያዝ ይቀደዳል፣ ከአነጋገር ይፈረዳል› አይደል የሚባለው፡፡

ዝሆኖች በጭንቅ ያገኙትን ፍሬ በሚገባ በመከባከብ፣ ከአደጋ በመጠበቅ፣ ያንን ፍሬም ሥነ ሥርዓት አስይዘው በማሳደግ ዘራቸው እንዲቀጥል ያደርጋሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንጋው አባላት ሁሉም እኩል ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አፍሪካውያን ‹አንድን ልጅ በብቃት ለማሳደግ መንደሩ ሁሉ ሊተባበር ይገባዋል – It takes a village to raise a child› የሚል አባባል አላቸው፡፡ ልጅን ለብቻ በብቃት ማሳደግ አይቻልም፡፡ ቤተሰብ ሲቀርጸው ማኅበረሰብ ካበላሸው፣ ትምህርት ቤት ሲያንጸው ሚዲያ ካፈረሰው፣ ሃይማኖት ሲያቃና ጫት ቤት ካጣመመው፣ ወላጅ ሲያለማው ጓደኛ ካጠፋው ፣ ልጅ ምን ፍሬ ይወጣዋል፡፡
በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ሳይሆን አይቀርም ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ሥዕሎች፣ ተረቶች፣ የፍልስፍናና የጥበብ ማስተማሪያዎች ለዝሆን ቦታ የሰጡት፡፡ በሀገራችን ትርጓሜያትና በፊሳሎጎስ መጽሐፍ ዝሆን የማስተማሪያነት ቦታውን ይዟል፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ከብሔራዊ ሎተሪ ዓርማነት ባሻገር ስንናገርለት አልታየንም፡፡ እስኪ ‹ሔርማዝ› እንሁን፡፡

ዝሆኖች ለቤተሰባዊ ሕይወት ልዩ ቦታ አላቸው፡፡ የዝሆን መንጋ በእናት የሚመራ ነው፡፡ የሰው ልጅ ሴቶችን ወደ መሪነት ሳያመጣ፣ እነ ንግሥተ ሳባና ንግሥት ሕንደኬም ሀገር ሳይመሩ በፊት ዝሆኖች የእናቶችን መሪነት ተቀብለዋል፡፡ በዝሆኖች መንጋ ውስጥ ታላቅ መሆን ክብርንም ያመጣል ኃላፊነትንም ያስከትላል፡፡ እኛ ሀገር ብዙ ጊዜ ‹ታላቅነት› ክብርን ብቻ እንዲያመጣ ይታሰባል እንጂ ኃላፊነትን እንዲያስከትል አይፈለግም፡፡ በዝሆኖች ዘንድ ግን ታላቅ እናት ትከበራለችም፣ ኃላፊነት ትወስዳለችም፡፡

በማለዳ የዝሆኖች ውሎ ሲጀመር የዝሆን ቤተሰብ ለተግባር ሥምሪት ይወጣል፡፡ ብዙ ጊዜ አንድ ቤተሰብ ከ12 አባላት በላይ አይበልጥም፡፡ ይህም ልጆችንና የቅርብ ዘመዶችን ያካትታል፡፡ እናት ዝሆን ይህን ቤተሰብ በመምራት ወደ ምግብ ሥምሪት ስትነቃነቅ አመራርዋን የሚፈልጉ ሌሎች ዝሆኖች ይቀላቀሏታል፡፡ ወደ ረፋድ ላይ የመንጋው ቁጥር ወደ 25 ይደርሳል፡፡ ፀሐይ ልታቆለቁል ስታስፈራራ የመንጋው ቁጥር ወደ አንድ መቶ ያሻቅባል፡፡ ሲመሽ የመንጋው ቁጥር እየቀነሰና ሁሉም በየቤቱ እየገባ ይሄድና ወደ ቀደመው አሥራ ሁለት የቤተሰብ አባላት ይመለሳል፡፡ ይህ ሁሉ የሚመራው በአንዲት አረጋዊት ታላቅ እናት ነው፡፡

አንዳንድ የዝሆንን ጠባይ ያጠኑ ሊቃውንት ይህንን የዝሆኖች የዕለት ጉዞ ከሰዎች የዕለት ጉዞ ጋር አያይዘው አይተውታል፡፡ በየማለዳው ኑሮን ስንወጥን የምንጀምረው ከቤተሰባችን ነው፡፡ ወጣ ብለን ሠፈርተኛውን እናገኛለን፤ በመንገዳችንና በሥራ ቦታችን ደግሞ ከከተማው ነዋሪ፣ ከደንበኞች፣ ከሻጮች፣ ከተማሪዎች፣ ከገበያተኞች፣ ከተሳፋሪዎችና ከሌሎቹም ጋር እየተቀላቀልን ቁጥራችን እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ፀሐይ ወደ ማደሪያዋ ልትገባ ስትል በሄድንበት መንገድ ወደ ኋላ በመመለስ ቁጥራችን እየቀነሰ ይመጣና የመጨረሻ ማረፊያችን ቤተሰባችን ይሆናል፡፡


በዝሆኖች ላይ ጥናት ያደረጉ ሊቃውንት ለመሪነት የምትመረጠው ታላቅ እናት ሁለት ዋና ዋና ብቃቶች እንዳሏት አስተውለዋል፡፡ ጽናትና ችግርን የመፍታት ብቃት፡፡ ባለሞያዎቹ ‹ጽናት› ሲሉ ‹‹ችግርን የመቋቋም ችሎታ፣ ከፈተና ለመውጣት መንገዶችን የመተለም ዐቅም፣ ከችግር በአፋጣኝ ወጥቶ በአስቸኳይ ወደ ነበሩበት ጤናማ ሁኔታ ለመመለስ መቻልና ሳይረበሹ፣ ሳይደናገጡና ተስፋ ሳይቆርጡ ከችግሮች በኋላ አመራርን በብስለት ለመቀጠል መቻል› ማለታቸው ነው፡፡ የሀገራችንን የመልካም አስተዳደር እጦት ችግር ለመፍታትም እነዚህ ሁለቱ ችሎታዎች ያሏቸውን መሪዎች መመደብ ሳይኖርብ አይቀርም፡፡ ችግር ፈጣሪዎችን ሳይሆን ችግር ፈችዎችን፡፡ በሚከሰቱ ነገሮች ተደናግጠው መሥመራቸውን የሚስቱትን ሳይሆን ማዕበሉን ተቋቁመው ወደ ጥንት ግብራቸው ለመመለስ ዐቅም ያላቸውን፡፡

የዝሆንን መንጋ የምትመራው ታላቅ እናት እንዲሁ አትመረጥም፡፡ ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ቀድማ የመገመት፣ የተሻለውን የምግብ ማግኛ ቦታ የማወቅ፣ ለግልገል ዝሆኖች ልምዷን የማካፈል፣ አስቸጋሪ ዝሆኖችን ሊታረሙ በሚችሉበት መንገድ የመቅጣት የካበተ ልምድ ያላት ናት፡፡ ብዙ ጊዜ መሪ እናቶች በጠባያቸው ጭምቶች፣ የተረጋጉ፣ ከግንፍልተኛነት የጸዱ እንደሆኑ ጥናቶቹ አሳይተዋል፡፡ የሚያስቆጡና ግብታዊ ርምጃ እንዲወሰድ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ እንኳን ቀድማ የኃይልና የጉልበት ርምጃ ለመውሰድ አትቸኩልም፡፡ መንጋውን ማረጋጋትና ችግሩ ሳይከሰት ከፈተናው የሚወጣበትን መንገድ ማመላከትን ታስቀድማች፡፡ ግልገሎቹ ሲያጠፉም ማረምን እንጂ መቅጣትን የመጀመሪያ ተግባሯ አታደርገውም፡፡

ዝሆን ቆዳው ጠንካራ ነው፡፡ አያሌ ቆንጥሮችን፣ እሾህና አሜከላዎችን፣ ቁጥቆጦዎችንና ጥሻዎችን ያቋርጣል፡፡ ቅጠሎችን ለማግኘት ወደ ዛፎቹ ሲንጠራራ ከተጎረዱ ቅርንጫፎችና ካገጠጡ ቅርፊቶች ጋር ይታገላል፡፡ ይህንን ሁሉ እንዲቋቋም ፈጣሪ ለዝሆን ደንዳና ቆዳ ሰጥቶታል፡፡ የዝሆን ቆዳ እስከ አንድ ኢንች የሚደርስ ውፍረት አለው፡፡ ይህ የቆዳ ውፍረት ለሁለት ነገሮች ጠቅሞታል፡፤ በአንድ በኩል በመቧጨርና በመጎንተል ከሚመጡበት አደጋዎች ለመቋቋም በሌላ በኩል ደግሞ በመንገዱ ላይ የሚገኙ ቆንጥሮች እሾሆች፣ ቁጥቋዎችና ጥሻዎች እዚህመ፣ እዚያም ለሚፈጥሩበት ውጋትና ቡጭረት ትኩረት ሳይሰጥ መንገዱን እንዲቀጥል፡፡


ሰው እንደ ዝሆን ቢሆን እንዴት መልካም ነበር፡፡ በመንገድ ላይ ለሚገኙት ቁጥቋጦዎች፣ ቡጭሪያዎችና ውጊያዎች ሁሉ ተበሳጭተን፣ አልቅሰን፣ ተናድደን፣ መልስ ሰጥተን እንዴት እንችለዋለን፡፡ ታማን፣ ተሰደብን፣ ስማችን ጠፋ፣ ተነካን፣ እያልን በየዕለቱ የምንንገበገብ ከሆነ ወደ ዓላማችን መድረስ እጅግ ከባድ ይሆንብናል፡፡ ለዋናው ግብ ሲባል አንዳንዱን ነገር መሻገር፣ አንዳንዱን ነገር ችሎ ማለፍ፣ አንዳንዱን ነገር እንዳላዩ መሆን፣ አንዳንዱንም ነገር ቁብ አለመስጠት ይገባል፡፡ አቡነ ጎርጎርዮስ ታላቁ ‹ሥራህን ሥራ፤ አንበሳው ሲያጓራ ፍንክች አትበል፤ የሰይጣንን ውሻዎች ለመውገር አትቁም፤ ጥንቸሎቹን በማባረር ጊዜህን አታጥፋ፤ ዝም ብለህ ሥራህን ሥራ› ሲሉ የመከሩት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ዝሆኖች ወገኖቻቸውን አይረሱም፡፡ የሞቱ ወገኖቻቸውን ከማይረሱ ጥቂት እንስሳት መካከል ዝሆኖች አንዱ ናቸው፡፡ የሞተበትን አካባቢ በተደጋጋሚ ይጎበኙታል፡፡ አንድ ዝሆን ከመንጋው ተለይቶ ለብዙ ጊዜ ቆይቶ ቢመለስ ልዩ የሆነ የደስታ አቀባበል ይጠብቀዋል፡፡ ኩንቢያቸውን በማነካካትና በማጠላለፍ አገላብጠው ይስሙታል፡፡ ጤንነቱን በሚጠይቅ መልኩ የሚያወጡት የተለየ ድምጽም አላቸው፡፡ ፍቅርና ደኅንነት ተሰምቶት ከመንጋው ጋር እንደገና እንዲቀላቀል እንጂ እንዲገለል አያደርጉም፡፡ እንዲያውም ሰዎች በዚህ ረገድ ሲቸግረን ያታያል፡፡ አንድን ያጠፋ ሰው መልሶ ለመቀበል፤ አንድን የበደለንን ሰው ይቅር ብሎ እንደ ቀደመው ለመሆን፣ ወይም አንድን ከወኅኒ ታርሞ የመጣን ሰው ደኅና ነው ብሎ ለመቀበል ይቸግረናል፡፡

(ይቀጥላል)

(ክፍል አንድ)
የዝሆን ሥዕል፣ ወሎ ገነተማርያም ቤተ ክርስቲያን
በሰው ልጆች የአደን፣ የጦርነት፣ የንግድ፣ የባሕልና የሃይማኖት ታሪክ ውስጥ ቦታ ካላቸው እንስሳት አንዱ ዝሆን ነው፡፡ ዝሆን ማደን የጀግንነት መገለጫ ሆኖ አዳኞቹን ሲያስመሰግንና ሲያስወድስ ኖሯል፡፡ በቀደምት ዘመናት በተደረጉ ጦርነቶችም ዝሆኖች የዛሬዎቹን ታንኮች ቦታ ተክተው አገልግለዋል፡፡ የአኩስሙ አብርሃ ከደቡብ የመን ወደ መካ ባደረገው የጦርነት ጉዞ አያሌ ዝሆኖችን ተጠቅሞ ስለነበር ዘመኑ ‹የዝሆኖች ዓመት› እየተባለ እስከ መጠራት ደርሶ ነበር፡፡ በበጥሊሞሳያን ዘመንም ግብጻውያን ከኢትዮጵያና አካባቢዋ ዝሆኖችን በመውሰድ ለጦርነት ተጠቅመውባቸዋል፡፡ 

የዝሆን ጥርስ ለጌጣጌጥ መሥሪያ መዋል የጀመረው ከክርስቶስ ልደት በፊት በነበሩ ጥንታውያን ሥልጣኔዎች ዘመን ነው፡፡ ይህ የዝሆን ጥርስ ንግድ ዝሆኖችን ከልዩ ልዩ አካባቢዎች እንዲጠፉና ዛሬም ቁጥራቸው እንዲመነምን ዋናውን ክፉ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡

ዝሆን በልዩ ልዩ ባሕሎችና ሃይማኖቶች ዘንድ የጥንካሬ፣ ወድቆ የመነሣት፣ ታላቅን የማክበርና የማስታወስ ተምሳሌት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ ላይ የምናገኘው የ‹ዐቢይ ነጌና የውርዝው ነጌያት› ምሳሌ ለዚህ ማሳያ ይሆናል፡፡ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍልም ‹ሔርማዝ› የሚለው ጥንታዊ የዝሆን መጠሪያ  ለ‹ጀግና› የሚሰጥ ስያሜ ሆኗል፡፡ በሀገራችን የአደን ታሪክ ውስጥ ከአንበሳ ገዳይ ቀጥሎ ክብር የነበረው ዝሆን ገዳይ መሆኑ ይነገራል፡፡

በሀገራችን ጥንታዊ ሥዕሎች ውስጥ የዝሆንን ሥዕል በስፋት እናገኛለን፡፡ በተለይም ከ15ኛው መክዘ በፊት የተሣሉ የግድግዳ ሥዕሎች ዝሆንን በየማዕዘናቱ ያስቀምጡታል፡፡ በወሎ እመኪና ልደታ ለማርያምና ገነተ ማርያም አብያተ ክርስቲያናት ግድግዳ ላይ የሚገኘው የ14ኛው መክዘና ከዚያ ቀደም ብሎ የተሳሉት የዝሆን ሥዕሎች ለዚህ ምሳሌ ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡
የዝሆን ሥዕል፣ ወሎ እመኪና ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን

በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ወደ ስድስት መቶ ሺ፣ በሕንድ ደግሞ ከ30 እስከ ሃምሳ ሺ የሚደርሱ ዝሆኖች እንደሚገኙ ይገመታል፡፡ 1.3 ሚሊዮን ይደርስ የነበረው የአፍሪካ ዝሆኖች ቁጥር አሁን ወዳለበት መጠን ያሽቆለቆለው እኤአ ከ1979-1989 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እኤአ በ2007 ዓም በተደረገው ጥናት 1200 የሚደርሱ ዝሆኖች እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዓለም እንደደረሰው የዝሆኖች እልቂት ሁሉ በ1980ዎቹ ብቻ 90 በመቶ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ዝሆኖች ከምድረ ገጽ ጠፍተዋል፡፡
የጥንት ሰዎች የዝሆንን የተፈጥሮ ጠባያት በመረዳት ለእምነታቸው መግለጫ፣ ለሥነ ምግባራቸው ማስተማሪያና ለፍልስፍናቸው ማሳያ አድርገውት ነበር፡፡ በሕንድ፣ በፋርስና በመካከለኛው ምሥራቅ ከ8ኛው መክዘ ጀምሮ የታወቀው ‹የዝሆኑና የስድስቱ ዓይነ ሥውራን› ታሪክ በብዙ ጥንታውያን አስተምህሮዎች ውስጥ ለልዩ ልዩ ጥበብ፣ ፍልስፍናና ሞራል ማስተማሪያነት ውሎ ነበር፡፡

ዝሆን የጠንካራ ነገር ግን ተጣጣፊ ኩምቢ ባለቤት ነው፡፡ ይህ 150 ሺ ጡንቻዎች ያሉት የዝሆን ኩምቢ 600 ጡንቻዎችን ብቻ ከያዘው የሰው ዘር ጋር ሲነጻጻር ጥንካሬውን ማሳየት ይችላል፡፡ የዝሆን ኩምቢ ይህንን ያህል ጠንካራ ቢሆንም አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ግን የሚገባውን አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችለው ወደፈለገው አቅጣጫ ያጣጥፈዋል፡፡ ሰውም በአቋሙ እንደ ዝሆን ኩምቢ ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ከነገሮችም ጋር አብሮ ለመጓዝ የሚችል፡፡ ጥንካሬው እንደ እንጨት ሳይሆን እንደ ብረት፡፡ እንጨት ይሰበራል እንጂ መተጣጠፍ አይችልም፡፡ ብረት ግን ጠንካራ ቢሆንም ተጣጣፊ ነው፡፡ የሰው ዓላማ ተጣጣፊ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ እንዲያ ከሆነ የመጣ ጎርፍ ሁሉ የሚወስደው፣ የበረታ ዱላ ሁሉ የሚነዳው ይሆናል፡፡ በሌላም በኩል ደግሞ ሰው እንደ ጅብራ የሚገተር፣ እንደ እንጨትም ደርቆ የሚቀር መሆን የለበትም፡፡ እንዲያ ከሆነ እኔ ብቻ ትክክል ነኝ፣ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን የሚል ግለኝነት ይጠናወተዋል፡፡ ሰው እንደ ዝሆን ኩምቢ በዓላማው ጠንካራ ሆኖ፣ ደግሞም ዓላማውን ሳይለቅ አማራጮችንና የተሻሉ መንገዶችን ለማየት ዕድል የሚሰጥ፣ አመዛዝኖ ለመቀበልና ከተሻለው ነገር ጋር ለመራመድ የሚችል መሆን አለበት፡፡

የዝሆን ኩምቢ

ዝሆን ሚዛናዊ ነው፡፡ ዝሆን በዓለማችን ትልቁ አጥቢ እንስሳ ነው፡፡ ክብደቱ እስከ ስድስት ሺ ኪሎ ግራም ይደርሳል፡፡ ይህንን ያህል ክብደቱን እስከ 3.3 ሜትር በሚደርሰው ቁመቱ ውስጥ ይይዘዋል፡፡ ይህንን ሁሉ ክብደት የያዘው ዝሆን ቅጠል በል መሆኑ የተነሣ የዛፎቹን ቁመት ተከትሎ ቀጭኔ በአንገቷ የምትደርስበት ቦታ ድረስ መድረስ የግድ ይለዋል፡፡ እዚህ ላይ ትልቁ ጥያቄ እንዴት? የሚለው ነው፡፡

የዝሆን አንዱ ችሎታ የሚለካው ለዚህ ጥያቄ በሚሰጠው መልስ ነው፡፡ ሁለት የፊት እግሮቹን ወደ ላይ በማውጣት በሁለት የኋላ እግሮቹ መሬቱን እንደ ችካል ተክሎ ይይዘዋል፡፡ ከዚያም ኩምቢውን እንደ ሰጎን አንገት በመምዘዝ የዛፉ ጫፍ ላይ ይደርሳል፡፡ ይህንን ተግባር ለማከናወን የሚችለው ዝሆን ሚዛናዊ ስለሆነ ነው፡፡ ክብደቱን፣ ቁመቱን፣ የነፋሱን ኃይል፣ የዛፎቹን ንቅናቄና የሚገነድሰውን ዛፍ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሚዛኑን ሳያዛንፍ በሁለት እግሮቹ መጠበቅ ይችላል፡፡ ጠንካራ ሰው ማለትም እንዲህ ነው፡፡ ምንም ያህል ከባድ ኃላፊነት ቢኖርበት፣ ምንም ያህል አስቸጋሪ ሥራ ቢሠራ፣ ምንም ያህል ወደ ላይ ቢንጠራራ፣ ምንም ያህል እንደ ነፋስ ጠንካራ የሆነ ፈተናና ትችት ቢዘንብበትም ሚዛኑን ሳይስት ወደ ዓላማው መጓዝ አለበት፡፡ ለዚያ ደግሞ ሁለት ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡ እንደ ዝሆን ሁለት እግሮች ጸንተው የሚተከሉ መሠረታዊ እምነቶች፣ እንደ ሁለቱ የፊት እግሮችም ወደ ላይ የሚንጠራሩ ራእዮችና ግቦች ያስፈልጋሉ፡፡

ወደፊት ለመጓዝ ዛሬ የምንተከልበት፣ ተተክለንም የምንቆምበት ነገር ያስፈልጋል፡፡ ትናንት ላይ ሳይተከሉ ወደ ዛሬ፣ ዛሬ ላይ ሳይተከሉ ወደ ነገ መጓዝ አይቻልም፡፡ ማንኛውም አውሮፕላን በሰማይ ላይ ለመብረር ከፈለገ ማኮብኮቢያ ሜዳ ያስፈልገዋል፡፡ ወደ ነገ የሚጓዝ ማንም ቢኖር የሚተከልበት የትናንት ታሪክ፣ ባሕል፣ ቅርስና ጥሪት ያስፈልገዋል፡፡
ዝሆን የሚተኛው ለመነሣት እንዲመቸው ሆኖ ነው፡፡ መሬት ላይ ከወደቀ ለመነሣት ይቸገራል፡፡ ክብደቱ ትልቅ ነውና፡፡ ስለዚህም የሚተኛው ዛፍ ተደግፎ ነው፡፡ የዝሆን ዕንቅልፍ ፍጹም ዕንቅልፍ አይደለም፡፡ ለመነሣት ያኮበኮበ ዕንቅልፍ ነው፡፡ የሚተኛው ለመነሣት በሚችልበት መንገድ ነው፡፡ ሰውም ሞቱ ለትንሣኤ፣ ድካሙ ለብርታት፣ ዕረፍቱ ለሥራ፣ ኀዘኑ ለደስታ፣ ውድቀቱ ለመነሣት፣ ስሕተቱ ለእርማት፣ ማጣቱ ለማግኘት፣ ሕመሙ ለድኅነት በሚሆን መልኩ መሆን አለበት፡፡ እንዳይነሣ ሆኖ መውደቅ፣ እንዳይተርፍ ሆኖ መክሰር፣ እንዳይከብር ሆኖ መዋረድ፣ እንዳይፈታ ሆኖ መታሠር፣ እንዳይመለስ ሆኖ መሄድ፣ እንዳይታረቅ ሆኖ መጣላት የለበትም፡፡ የማርያም መንገድ መተው ያስፈልጋል፡፡ የአንድ ነገር መጨረሻ የሌላ ነገር መጀመሪያ መሆን አለበት፡፡ ከሥራ ማረፍ ለሌላ ሥራ መዘጋጃ፣ የዛሬ ዕንቅልፍ ለነገ ብርታት ኃይል መሰብሰቢያ፣ የዛሬ ሞት ለነገ ትንሣኤ መራመጃ መሆን አለበት፡፡

በዝሆን መንጋ ዘንድ ታላላቆች ወሳኝ ቦታ አላቸው፡፡ ይከበራሉ፤ ይሰማሉ፤ ይመራሉ፤ ያስተምራሉ፤ ትውልድም ቀርፀው ያፈራሉ፡፡ መንጋው ሲጓዝ መንገድ የሚመሩት፤ ለአዳጊዎች ልምዳቸውን የሚያካፍሉት፤ መንጋውን ከአደጋ የሚጠብቁት፤ ጥፋተኛውን ጎረምሳም የሚቀጡት ታላላቆች ናቸው፡፡ ታላላቆች የሌሉበት መንጋ እሥር ቤት እንደሰበረ ማፊያ ይሆናል፡፡ በአንድ ወቅት በደቡብ አፍሪካ ክሩገር ፓርክ ውስጥ የሚገኙ ዝሆኖች ቁጥራቸው ጨመረና ከፓርኩ ዐቅም በላይ ሆኑ፡፡ ቁጥራቸውን ከፓርኩ ዐቅም ጋር ለማመጣጠን እንዲቻል የተወሰኑትን ዝሆኖች ወደ ሌላ ፓርክ ለመውሰድ ተወሰነ፡፡ ዝሆኖቹ እንዲሄዱ የታሰበው በሄሊኮፕተር እየተንጠለጠሉ ነበር፡፡ ሄሊኮፕተሩ ትልልቆቹን ዝሆኖች ለመጫን ዐቅም ስላነሰው ወጣቶቹ ዝሆኖች እየተመረጡ ወደ ሌላኛው ፓርክ ተወሰዱ፡፡

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወጣቶቹ ዝሆኖች የገቡበት ፓርክ ተናወጠ፡፡ በፓርኩ ውስጥ የሚገኙት አውራሪሶች በየቀኑ ይገደሉ ጀመር፤ ዛፎች ይገነደሳሉ፤ ቁጥቋጦዎች ይተራመሳሉ፤ በዝሆኖቹ መካከል ጦርነት ተፈጠረ፡፡ በዚህም ምክንያት ዐቅመ ደካሞቹ እንስሳት ይጎዱ ጀመር፡፡ ነገሩ ያሳሰባቸው የፓርኩ ኃላፊዎች ሥውር ካሜራ ገጥመው ሁኔታውን መከታተል ያዙ፡፡ በመጨረሻም ወጣቶቹ ዝሆኖች የዚህ ሁሉ ችግር ፈጣሪዎች መሆናቸውን ደረሱበት፡፡ ሳይታሰብ አንድ ‹የዱርዬ ዝሆኖች ቡድን› ተመሥርቷል፡፡

የዝሆን አመራር
አንድ የጥናት ቡድን ተቀዋቁሞ የችግሩን መነሻ ማጣራት ሲጀምር ዋናው ጉድለት በዝሆኖቹ መካከል የሚመራና የሚፈራ ሽማግሌ አለመኖሩ መሆኑ ተደረሰበት፡፡ ወዲያውም የተወሰኑ ታላላቅ ዝሆኖችን እንደምንም ብለው ወደ ፓርኩ ሲያመጧቸው ሁሉም ነገር ሥነ ሥርዓት ያዘ፡፡ ‹መካሪ ዘካሪ አያሳጣ› ይባል የለ፡፡

በሰው ልጆችም ውስጥ ታላላቆች ተመሳሳይ ሚና አላቸው፡፡ ወላጆች ልጆችን፣ አያቶች የልጅ ልጆችን፤ ሽማግሌዎች መንደርተኞችን በባሕል፣ በእምነት፣ በሞራል ይመራሉ፡፡ አንዲት ሀገር ተው የሚል አባትና እናት፣ የሚያስታርቅ ሽማግሌ፤ ተሞክሮውን የሚያካፍል ታላቅ፤ ታሪክና ባሕል ዐዋቂ ጠቢብ፤ የሚፈራና የሚታፈር፣ የሚታይና የሚከበር ልዑል ዜጋ (Senior citizen) ከሌላት ሕግና ሥርዓት፣ ባሕልና ሞራል፣ የሀገርና የወገን ክብር ገደል ይገባሉ፡፡

ሀገር ከፍ ብለው የሚታዩ ኮከቦችን ትፈልጋለች፤ ትውልድ አርአያ የሚያደርጋቸው፡፡ ከጣት ጣት እንደሚበልጠው ሁሉ ከዜጋም ዜጋ ይከብራል፡፡ ለሀገር በዋለው ውለታ፣ ለትውልድ በሠራው ሥራ፣ በከፈለው መሥዋዕትነትና ባመጣው ውጤት ዜጋ ከዜጋ ይለያል፡፡ እንደ ብርሃ ድምቀት፣ እንደ ጥበቡ ምጥቀት ከዜጋ ዜጋ ይበልጣል፡፡ ‹ኮከብ እም ኮከብ ይኄይስ ክብሩ- ኮከብ ከኮከብ ክብሩ ይበልጣል› እንዲል፡፡ እነዚህ ዜጎች ናቸው የመንጋው አባቶችና እናቶች፡፡ ትውልዱን በሞራል፣ በባሕል፣ በእምነት፣ በሥራ፣ በሕግና በሥርዓት የሚቀርጹ፡፡ የሚፈራና የሚታፈር በሌለበት ሀገር የዱርዬ ቡድን መመሥረቱ አይቀሬ ነው፡፡ ሀገርን ሲዘርፍ፣ ዜጋን ሲገድል፣ ፍርድ ሲያጓድል፣ ድኻን ሲበድል፣ በሥልጣን ሲባልግ፣ በዘመድ ሲሠራ ምንም የማይመስለው፡፡ ነውሩ ክብሩ የሆነ፡፡ ‹እንብላት እንዝራት› ሲሉት ‹እንብላት› ብቻ የሚል ቡድን መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡

(ይቀጥላል)

አሜሪካ ውስጥ በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ስዘዋወር ከአስተባባሪዎቹ የምሰማው ተመሳሳይ ሮሮ አለ፡፡ ብዙዎቹ አብያተ ክርስቲያናት የራሳቸው ሕንጻ እስኪያገኙ ድረስ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ተከራይተው ይገለገላሉ፡፡ የራሳቸው ሕንጸ ያላቸውም ቢሆኑ ከአሜሪካዊው ማኅበረሰብ ጋር ይጎራበታሉ፡፡ በሰንበት ቅዳሴና የንግሥ በዓላት በሚከበሩባቸው ቀናት በመኪና ማቆሚያ፣ በድምጽ፣ በአካባቢው በብዛት በመገኘትና በጽዳት ጉዳዮች አብያተ ክርስቲያናቱ ካሉባቸው መንደሮች ነዋሪዎች ጋር ይገናኛሉ፡፡

እነዚህ ግንኙነቶች ግን ብዙውን ጊዜ ሰላማውያን አይሆኑም፡፡ አልፎ አልፎ ችግሩ ከሌሎች ወገን ቢመነጭም ዋናው ችግር ግን ከራሳችን የሚመጣ መሆኑን አስተባባሪዎችም ማኅበረሰቡም ያምኑበታል፡፡ ፈታኙ ነገር ችግሩን ለማስተካከል አለመቻሉ ነው፡፡ ‹ከተማ የጉርብትና ሥርዓት ነው› የሚለውን የከተሞችን አንዱን መርሕ በጉልሕ ለማየት ከሚቻልባው ሀገሮች አንዷ በሆነችው አሜሪካ የመንደርተኞች ሕጎችና ባሕሎች ጥብቅ ናቸው፡፡ በተለይም ግለሰባዊ ኑሮን መሠረት ባደረገው የአሜሪካ የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ በአንድ መንደር የሚከናወኑ ተግባራት የግለሰቦችን መብቶች እንዳይነኩ ጥንቃቄ ይደረግባቸዋል፡፡


አንድ የመንደሩ ነዋሪ የራሱን መብት አስጠብቆ፣ በሌሎቹ መብት ላይ ሳይደርስ፣ ነገር ግን ደግሞ አካባቢያዊ ግዴታውን ተወጥቶ የሚኖርበት የመንደር ሕግ ነው ያላቸው፡፡ እያንዳንዱ ነዋሪ ቤቱንና በቤቱ ዙሪያ ያለውን አካባቢ ያጸዳል፡፡ በተመደበለትና በተፈቀደለት ቦታ ብቻ መኪናውን ያቆማል፡፡ በተመደበው ጊዜ ቆሻሻውን ለሰብሳቢዎቹ ያስረክባል፡፡ ከተፈቀደለት መጠንና ሰዓት በላይ ድምፅ አያወጣም ፤ አይጠቀምም፤ በአካባቢው የተለየ እንቅስቃሴ ሲኖር ለፖሊስ ያሳውቃል፤ መንደሩን የሚነካ ጉዳይ ሲኖረው አስቀድሞ ያሳውቃል፤ በአካባቢው  የመንደሩን ገጽታና አነዋዋር የሚቀይር ነገር ሲኖር መንደርተኛው ይጠየቃል፤ ይወስናልም፡፡ እነዚህን መሰሉ መንደር ተኮር ሕጎች ናቸው ነዋሪዎቹ ተከባብረውና ተጠባብቀው በሰላም እንዲኖሩ የሚያደርጓቸው፡፡  


በሌላ በኩል ግን በሀገራችን መንደርን መንደር ያደረገው በታሪክ አጋጣሚ በአንድ አካባቢ ተሠርቶ መገኘቱ፤ ያለበለዚያም  በሆነ ፕሮጀክት በአንድ አካባቢ እነዚህ ቤቶች በመገንባታቸው እንጂ መንደርተኛውን የሚያስተባበረው፣ ተከባብሮና መብቱን ተጠባብቆ እንዲኖር፣ ግዴታውንም እንዲወጣ የሚያደርገው የመንደር ባሕልና ሕግ የለውም፡፡ አብዛኞቹ የመንደር ሕጎች እንደ ዕድርና ዕቁብ፣ ማኅበራዊ ኑሮን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ የጉርብትና ሕጎች አይደሉም፡፡ ቀበሌ ሲመሠረት ዝቅተኛ የመንደር መዋቅርን ለመትከል ታስቦ እንደነበረ ይነገራል፡፡ በኋላ ግን ከመንደር አልፎ የአንድ ከተማ መዋቅር ያዘ፤ አሁን ደግሞ የወረዳ መዋቅር ሆኗል፡፡

እናንተ ሥራ ውላችሁ ስትመጡ ድንገት የመንደራችሁ መንገድ ተቆፍሮ ልታገኙት ትችላላችሁ፡፡ ቀድሞ ለማሳወቅ ግዴታ ያለበት አካል የለም፡፡ ወይም ከበራችሁ አጠገብ የዕድር ድንኳን ሊተከል መሆኑን የሚነግራችሁ የለም፡፡ ልጆቻችን እናጫውትበታለን ያላችሁት ሜዳ በድንገት አንድ ቀን የሠፈሩን ማንነት የሚቀይር ሕንፃ እንዲሠራበት ሲቆፈር ታዩት ይሆናል፡፡ ጎረቤቶቻችሁ ሦስት መኪኖቻቸውን አቁመው እርስዎ ለአንድ መኪና ቦታ ቢያጡ የማመልከቻ ቢሮ የለዎት ይሆናል፡፡ የሠፈሩ ሜዳ በሙሉ የቴሌቭዥን ዲሽ መትከያ ሲሆን ሥርዓት የሚያስይዝ አካል አይኖርም፤ ድግስ በተደገሰ፣ ማኅበር በተጠጣ፣ ሰው በተሰበሰበ ቁጥር እስከ ላንቃው በተከፈተ ሙዚቃና ጭፈራ ሲረበሹ ወይ ቀድሞ የሚነግርዎት አለያም እስከ መቼ አንድሚቀጥል የሚያሳውቅዎት አይኖርም፡፡

ይህንን በመሰለው የመንደር አኗኗር የኖረው ማኅበረሰባችን ነው እዚህ አሜሪካ ሲመጣ ችግር የሚገጥመው፡፡ 

ምንም እንኳን በአብያተ ክርስቲያናት አካባቢ ለመኪና ማቆሚያ የተፈቀደና የተከለከለውን ሥፍራ የሚገልጥ ማስታወቂያ ቢኖርም በተከለከለው ቦታ መኪኖቹ ይቆማሉ፡፡ ሲብስም የነዋሪዎቹ የግል የመኪና ማቆሚያ ላይ እንዲቆሙ ይደረጋሉ፡፡ የከፋው ዘመዳችንም የነዋሪዎቹን የመውጫ መግቢያ በር ዘግቶ መኪናውን ያቆማል፡፡ በብዙዎቹ መንደሮች በሣር ላይ መጓዝና መንዳት ክልክል ቢሆንም እኛ ስንሰበሰብ ግን ሣሮች መከራቸውን ያያሉ፤ አንዳንዴም ቀድመው እንዲያውቁ ሳይደረግ ድንገት የከበሮው ድምጽ አካባቢውን ያናውጠዋል፡፡ የመኪና ጥሩንባ ሠፈሩን ያተራምሰዋል፡፡ 

ብዙዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ምግብና መጠጥ ወደ ውስጥ እንዳይገባ ይከለክላሉ፤ በጉልሕ ጽፈው በሚታይ ቦታ ያስቀምጣሉ፡፡ እኛ ግን ጥሰን ይዘን እንገባለን፡፡ የሚያስደንቀው ደግሞ እዚያው ጥለነው እንወጣለን፡፡ መጽሐፎቻቸው ይበላሻሉ፤ ዕቃዎቻቸው ይተራመሳሉ፤ መጸዳጃዎቻቸው ይዝረከረካሉ፤ ጽዳቱ ይጓደላል፤ ዕቃቸው ይሰበራል፡፡  

አሜሪካውያን ሌሎች ማኅበረሰቦችን በፍርሃት ማየታቸው፣ በሌላም በኩል በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮበት ፖሊስ በአካባቢው ሰዎች የቅሬታ ስልክ ይጨናነቃል፡፡ የፈቀዱ አካላትም ጫና ይበዛባቸዋል፡፡ ያስፈቀዱ አካላትም ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡ አንድ ላይ ተዳምሮም በአንዳንድ አካባቢዎች ለኢትዮጵያውያን ማኅበረሰቦች አዳራሽ የሚያከራይ፣ የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ የሚሸጥ፣ መስኮችንና ሜዳዎችን የሚፈቅድ እየጠፋ መጥቷል፡፡ ቢፈቀድ እንኳን እጅግ ጥብቅ በሆነ ግዴታና እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ እየሆነ ነው፡፡ አንዳንድ ቦታዎችም የፖሊስ ኃይል ለማቆም፣ የጽዳት ሰዎች ለመመደብ፤ እንቅስቃሴውን የሚከታተሉ የድርጅቱ ሰዎችን ለማሠማራትና የሚበላሹ ዕቃዎችን ለመከታተል እያሉ የሚቆልሉት ዋጋ አስመራሪ ሆኗል፡፡

በአንድ በኩል በጉርብትና ሕግ ውስጥ አለማደጋችንና የልምድ ችግራችን ለዚህ ዳርጎናል፡፡ ለሕግና ሥርዓት ያለን ቦታና የተገዥነት ልምድ ማነስ ጉዳት አስከትሎብናል፡፡ ከሕግ አውጭው እስከ ሕግ ተመሪው ድረስ ሕግንና ሥርዓትን መጣስ ልማድ በሆነበት ማኅረሰብ ውስጥ ማደጋችንም አጋልጦናል፡፡ የሠለጠነ ማኅበረሰብ ከሚገለጥባቸው ነገሮች አንዱ ‹በሕግና ሥርዓት መመራት› ነው፡፡ እኛ ዘንድ ግን በተለይ ‹ከተሜ በሚባለው አካባቢ› በሕግና ሥርዓት አስከባሪው እንጂ በሕጉና ሥርዓቱ የመመራቱ ባሕል እምብዛም ነው፡፡ ከሕጉ ይልቅ የሕግ አስከባሪው ይፈራል፤ ይከበራልም፡፡ በዚህም ምክንያት ሕጉ ሰውየው ሆኗል፡፡ ለዚህም ይመስላል የትራፊክ ፖሊስ ሲኖርና ሳይኖር የትራፊክ ሕጉ አከባበር የሚለየው፡፡ ሕጉ የባለሥልጣኑ መሪ ሳይሆን፣ ሕጉ የባለሥልጣኑ ተገዥ ነው፡፡ 

ዕቃ ስንገዛ ማንዋሉን፣ ልብስ ስንገዛ ስለ አስተጣጠብና አተኳኮሱ የሚገልጠውን አብሮት የተሰፋውን መግለጫ የማንበብና በዚያ የመመራት ልማድ ያለን ስንቶቻችን ነን?  

ሌላው ችግር ደግሞ ለራሳችን የምንሰጠው ዋጋ ነው፡፡ ጽዳት፣ ሥርዓት፣ ፕሮቶኮል፣ ውበትና ሥምረት ለራስ ከሚሰጥ ዋጋ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ጃፓኖች ተቀምጠውበት የነበረውን ስታዲዮም አጽደተው ሲወጡ የተመለከተው ዓለም አድናቆቱን ችሯቸዋል፡፡ ለራሳቸው ያላቸውን ዋጋም አሳይተውናል፡፡ እነርሱ ለዓለም በጎን ነገር እንጂ አንዳች ክፉ ነገርን ለማበርከት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ነግረውናል፡፡ የሚመጥናቸው ምን እንደሆነ እንድናይም አድርገዋል፡፡

ሌላው ደግሞ መዋቅራዊ ያልሆነን ኃላፊነት የመወጣት ልማዳችን አነስተኛ መሆኑ ነው፡፡ መዋቅራዊ ኃላፊነት ማለት በአንድ የተወሰነ መዋቅር ወይም ድርጅት ወይም ደግሞ አሠራር ውስጥ በመመረጥ፣ በምደባ ወይም ደግሞ በሹመት የሚመጣ ኃላፊነት ነው፡፡ የዚህ ክፍል አባል፣ ኃላፊ፣ ጸሐፊ፣ ተጠሪ፣ ሰብሳቢ፣ እየተባለ የሚጠራው፡፡ ኃላፊነትን እንዲህ ላሉ አካላትና ግለሰቦች እንሰጥና ‹እኔን አይመለከተኝም› እንላለን፡፡ ሥልጡን ማኅበረሰብ ግን ኃላፊነት የሚሰማውን ዜጋ መፍጠር የቻለ ነው፡፡ ‹ለአካባቢው ሰላም፣ ጽዳት፣ ዕድገት፣ ጤናና ማኅበራዊ ደኅንነት እኔም ድርሻ አለኝ› የሚል ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ፡፡ እስኪታዘዝ፣ እስኪነገረው፣ እስኪጨቀጨቅ የማይጠብቅ ዜጋ፡፡

በገቢ ማሰባሰቢያ፣ በኮሚቴ ምሥረታ፣ በማኅበር ማቋቋም ወቅት ሰዎች ኃላፊነትን ወስደው፣ ቃል ገብተውና ምለው ተገዝተው ይመረጡና በኋላ ዘወር የሚሉት፣ ካልተለመኑና ካልተጨቀጨቁ የማይሰበሰቡትና የማይሠሩት ውስጣቸው ‹ኃላፊነት› የሚባለው ነገር ስለሌለ ነው፡፡ በየውይይቱ ‹እገሌ ለምን እንዲህ አያደርግም› እንጂ ‹እኔ ለምን እንዲህ አላደርግም› የሚል ቁጭት የጠፋው ‹ኃላፊነት መውሰድ› የሚባለው ነገር ስለሌለ ነው፡፡  

ሠለጠኑ በሚባሉ ሀገሮች ከሚገኙ ወገኖቻችን ከሽቱና ቦርሳ፣ ከልብስና ቀሚስ በላይ ዕውቀትና ሥልጣኔን እንጠብቃለን፡፡ ሌሎቹ ቁሳቁሶች እነዚህ ሲገኙ እዚያው ይመረታሉና፡፡ አልፎ አልፎ እንደሚታየው ግን ሕግና ሥርዓትን በማወቅና በማክበር ረገድ በአንድ ቀን የፖሊስ ትምህርት ተለውጦ የግራ ጠርዙን ይዞ የሚጓዘው የሀገሬ ገበሬ እጅግ ተሽሎ ይታያል፡፡ ያ ሁሉ ገበሬ መሥመር ጠብቆ ሲሄድ አንድም የትራፊክ ፖሊስ በአካባቢው አይታይም፡፡ ታድያ ቦታ ተቀያይራችሁ ትሞክሩት እንዴǃ  

ሚነሶታ፣ሚንያፖሊስ

ንሥር ሳይፈትን አያምንም፤ አይተማመንምም፡፡ ሴቷ ንሥር ባል ማግባት ስትፈልግ አንድ እንጨት ታነሣና ወንዱ እየተከተላት ወደ ላይ ትመጥቃለች፡፡ እስከ ሰማይ ጥግ ከደረሰች በኋላም ያንን እንጨት ትለቀዋለች፡፡ ያን ጊዜ ወንዱ እንጨቱ መሬት ከመድረሱ በፊት በፍጥነት በመወርወር መያዝና ለሴቷ መልሶ ማምጣት ይጠበቅበታል፡፡ ሴቷም እንጨቱን ተቀብላ እንደገና ወደ ቀጣዩ ከፍታ ትመጥቅና እንጨቱን መልሳ ትጥለዋለች፡፡ አሁንም ወንዱ ንሥር ከእንጨቱ የውድቀት ፍጥነት ቀድሞ ያንን እንጨት በመያዝ ለሴቷ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ እንዲህ ያለው ፈተና ወንዱን ለሰዓታት ያህል ይጠብቃዋል፡፡ ከፍታው እየጨመረ፣ እንጨቱም ይበልጥ እየተወረወረ ይሄዳል፡፡ ሴቷ ንሥር ወንዱ ንሥር ፈጣንና የተወረወረለትን ለመያዝ ያለውን ቆራጥነት እስክታረጋግጥ ድረስ ፈተናው ይቀጥላል፡፡ በመጨረሻም ቆራጥና ፈጣን፣ ማንኛውም ችግር የማይበግረው መሆኑን ስታረጋግጥ ባልነቱን ትፈቅድለታለች፡፡

ንሥርም እንዲህ ትልሃለች፡- በግላዊ ሕይወትህ፣ በንግድህም ሆነ በሌላው ኑሮህ ከሰዎች ጋር መወዳጀት፣ አብሮ መሥራትና መንገድ መጀመር ያለብህ ለዓላማቸው ምን ያህል ጽኑና ቆራጥ፣ ትጉና አይበገሬ መሆናቸውን አረጋግጠህ መሆን አለበት፡፡ ሳታረጋግጥ መግባት ትርፉ ፀፀት ነው፡፡ እንኳን ሌሎችን ራስህንም ለአዲስ ተልዕኮ ከማሠማራትህ በፊት ፈትነው፡፡

ንሥር በሕይወቱ የሚመጡ ለውጦችን እንደመጡ በአጋጣሚ አይቀበላቸውም፡፡ ተዘጋጅቶና ዐቅዶ እንጂ፡፡ ሴቷ ዕንቁላል የመጣያ ጊዜዋ ሲደርስ ባልና ሚስቱ ዕንቁላል ለመጣያ ምቹና ተስማሚ የሆነውን ቦታ ያፈላልጋሉ፡፡ ያ ቦታ ማንኛውም ዓይነት ጠላት የማይደርስበት፣ ከከፍታዎች ሁሉ በላይ የሆነና ከማንኛውም ዓይነት አደጋ  ራስንና ልጆችን ለመከላከል የሚመች መሆን አለበት፡፡ ቦታው በባልና ሚስቱ ከተመረጠ በኋላ ወንዱ ወደ መሬት ወርዶ እሾህ ለቅሞ ወደ ተራራው ንቃቃት ያመራል፡፡ በዚያም ይደለድለዋል፡፡ ከዚያም ለሁለተኛ ጊዜ ወርዶ አስፈላጊ የሆኑትን እንጨቶች ሰብስቦ ወደ ንቃቃቱ ይመጣና በእሾሁ ላይ ይረመርመዋል፡፡ እንደገና ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ምድር ይመለስና እሾህ ሰብስቦ ወደ ጎጆው ያመራል፤ በእንጨቱም ላይ ይረበርበዋል፡፡ ለአራተኛ ጊዜ ወደ መሬት ተመልሶም ለስላሳ ሣር ያመጣና በእሾሁ ላይ ያነጥፋል፡፡ በአምስተኛ ጉዞውም እሾህ አምጥቶ በሣሩ ላይ ያደርጋል፡፡ በስድስተኛ ጉዞውም በእሾሁም ላይ ሣር ይነሰንሳል፡፡ በመጨረሻውና በሰባተኛ ሥራው ላባዎቹን በመካከል ላይ ያደላድላቸዋል፡፡ በጎጆው ዙሪያ የተደረገው እሾህም ዙሪያውን ከጠላት ያጥርለታል፡፡
እነሆ ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- ምንጊዜም ለለውጥ ራስህን አዘጋጅ፡፡ ነገሮች ድንገት እንዲደርሱብህ ዕድል አትስጣቸው፡፡ አስበህ፣ ተዘጋጅተህ፣ ወስነህ፣ ሂሳብ ሠርተህ እንጂ፡፡ ኑሮህ በድንገቴና በአጋጣሚ የተሞላ አይሁን፡፡ የቻልከውን መጠን ያህል ተዘጋጅ እንጂ፡፡ መጽሐፉስ ‹ተዘጋጅታችሁ ተቀመጡ› አይደል የሚለው፡፡ ለማደግ ተዘጋጅ፣ ለመማር ተዘጋጅ፣ ለጓደኝነት ተዘጋጅ፣ ለማግባት ተዘጋጅ፣ ለመውለድ ተዘጋጅ፣ አዲስ ሥራ ለመሥራት ተዘጋጅ፣ ቤት ለመሥራት ተዘጋጅ፣ መኪና ለመግዛት ተዘጋጅ፣ ለምትለውጣቸው ነገሮች ሁሉ ቅድመ ዝግጅት ይኑርህ፡፡
ንሥር ትዳሩን በእኩልነት ነው የሚመራው፡፡ ወንዱ ንሥር ጎጆውን ሠርቶ ሲጨርስ ሴቷ ወደ ጎጆው ትገባና ዕንቁላል መጣል ትጀምራለች፡፡ ትዳርን በእኩልነት ነው የሚመሩት፡፡ እርሷ ዕንቁላል ስትጥል እርሱ ደግሞ አካባቢውን ከጠላት ይጠብቃል፡፡ ወደ መሬት እየተመላለሰም ምግብ ይሰበስባል፡፡ ልጆችን መመገብ፣ ማሳደግ፣ በረራ ማለማመድ፣ ከጎጇቸው ርቀው እንዲያድኑ ማሠልጠን የሁለቱም የጋራ ኃላፊነት ነው፡፡ ድርሻ ይካፈላሉ እንጂ አንዱ የበላይ አንዱ የበታች አይሆኑም፡፡
ስለዚህም ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- ትዳር የእኩልነት ጉዞ ነው፡፡ የሥራ ድርሻ ክፍፍል እንጂ የበታችና የበላይ ክፍፍል አይኖረውም፡፡ ሁሉም የችሎታውንና የተፈጥሮውን የሚያደርግበት፣ የጋራ ኃላፊነት የሚወሰድበት ቤት ነው ትዳር፡፡
ንሥር ልጆቹን ደስታንም መከራንም ያስተምራቸዋል፡፡ የንሥር ጫጩቶች አምሮና ደኅንነቱ ተጠብቆ በተሠራው ጎጆ ይፈለፈሉና ወላጆቻቸው እየመገቧቸው እዚያ ጥቂት ያድጋሉ፡፡ ለዐቅመ ንሥር ሲደርሱ የምቾቱ ድልቅቂያ ያበቃና ሴቷ ንሥር ጫጩቶቹን ከጎጆዋ እያወጣች ዐለቱ ላይ ትጥላቸዋለች፡፡ ጫጩቶቹ በፍርሃት ይዋጡና ተመልሰው ወደ ጎጆው እየዘለሉ ይገባሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ማደፋፈሪያ ነው፡፡ የማያድሩበት ቤት አያመሻሹበትም ይባል የለ፡፡‹ሰው እናትና አባቱን ይተዋል› የሚለው በእነርሱም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሊኖር ይችላል ማን ያውቃል፡፡ ለጥቂት ጊዜያት እንዲህ ታለማምዳቸውና በቀጣዩ ጊዜ ከጎጆው አውጥታ ወደ ዐለቱ በመጣል የጎጆውን ለስላሳውን ክፍል ታነሣባቸዋለች፡፡ እነርሱም እንደለመዱት ወደ ጎጆው ሮጠው ዘለው ሲገቡ እሾሁ ይቀበላቸዋል፤ ያቆስላቸዋል፣ ያደማቸዋልም፡፡ እነርሱም እንዲያ የሚወዷቸው እናትና አባታቸው ለምን እንደሚያሰቃዩዋቸው ግራ እየገባቸው ወደ ዐለቱ ተመልሰው ይወጣሉ፡፡
ከጎጆው ውጭ በአድናቆት መቆማቸውን የምታየው ኣናታቸው ከዐለቱ ገፋ ታደርጋቸውና አየር ላይ እንዲንሳፈፉ ትለቃቸዋለች፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ አየሩን የቀዘፉት ጫጩት ንሥሮች በፍርሃትና በድንጋጤ ተውጠው ወደ ታች ሲወረወሩ አባታቸው ይመጣና ከመውደቃቸው በፊት ቀልቦ በትከሻው ተሸክሞ ወደ ዐለቱ ያወጣቸዋል፡፡ እነርሱም በደስታ ይዋኛሉ፡፡ እናት ስትወረውር፣ አባት በአየር ላይ ሲቀልብ፣ ልጆችም ሲወረወሩና ሲጨነቁ፣ አባታቸው ሲቀልባቸው ሲደሰቱ ጥቂት ጊዜያት ያልፋሉ፡፡ በአካል እየጠነከሩ፣ ከመከራውም ከደስታውም እየተማሩ፣ አካባቢውንም እየለመዱት ይሄዳሉ፡፡ በመጨረሻም ራሳቸውን ችለው ይበራሉ፡፡ ከወላጆቹ ጋር ኖሮ የሚያረጀውን ቢያዩ ኖሮ ንሥሮች ምን ይሉ ይሆን?
ለዚህ ነው ንሥር እንዲህ የሚለው፡- ለልጆቻችን ከልክ ያለፈ ክብካቤ መስጠት የትም አያደርሳቸውም፡፡ መከራውንም፣ ችግሩንም፣ ፈተናውንም፣ ትግሉንም፣ ተግዳሮቱንም እንዲለምዱት ማድረግ አለብን፡፡ አፈር አይንካህ፣ የፈሰሰ ውኃ አታቅና፣ ማንም በክፉ አይይህ፣ እንደ ዕንቁላል ትሰበራለህ፣ እንደ መስተዋት ትሰነጠቃለህ እያሉ ነገ በእውኑ ዓለም የማያገኙትን ቅንጦትና ምቾት ብቻ ማሳየቱ የትም አያድርሳቸውም፡፡ እሾሁንም፣ ዐለቱንም፣ መወርወሩንም፣ መውደቁንም፣ መታገሉንም፣ ማሸነፉንም ይልመዱት፡፡ ነገን በጥቂቱ ዛሬ እናሳያቸው፡፡ የሚወዱን ሰዎች ማለት የሌለ ገነት ፈጥረው የሚከባከቡን ማለት ብቻ አይደሉም፡፡ ሰው መሆን ለሚያጋጥመው ተግዳሮት ሁሉ ዝግጁ እንድንሆን የሚያደርጉን እንጂ፡፡ ቤት ሣርና ላባ ብቻ ሳይሆን እሾህም ሊኖረው ይገባል፡፡
ንሥር ሲዳከም የት መሄድ እንዳለበት ያውቃል፡፡ ንሥር ሲዳከም ላባዎቹ ደካሞች ይሆናሉ፡፡ እንደቀድሞው በፍጥነት እንዲበር፣ ወደ ላይም እንዲመጥቅ አያስችሉትም፡፡ እንደ በረቱ መዝለቅ የለ፡፡ ጉልበቱ ሲደክም፣ ላባው ሲነጫጭና የሞት ሽታ ሲሸተው፣ ጉልበቱ ሳይከዳው በፊት ወደ አንድ ማንም ወደማይደርስበት የተራራ ጫፍ ያመራና በንቃቃቶቹ መካከል ጎጆ ሠርቶ ይቀመጣል፡፡ እዚያ ምግቡን አከማችቶ ያርፋል፡፡ የጽሞና ጊዜም ይወስዳል፡፡ የተረፉትን ላባዎቹን እየነጨ መለመላውን ይቀራል፡፡ ቀስ በቀስም አዲስ ላባ ያበቅላል፡፡ ኃይሉም እንደ ጥንቱ ይታደሳል፡፡ ያን ጊዜ ወደ ቀድሞ ኑሮው በአዲስ ጉልበትና በአዲስ መንፈስ ይመለሳል፡፡
እናም ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- ጉልበትህና መንፈስህ፣ ሐሳብህና የማመንጨት ዐቅምህ ሲዳከም ዝም ብለህ አትናውዝ፤ እስክትደከርትም አትሟዘዝ፡፡ ነገሮች እንጨት እንጨት ሲሉህ፣ የማስቲካው ቃና ሲያልቅ፣ የሸንኮራው ጣዕም ሲሟጠጥ ‹ደኅና ነኝ› እያልክ ራስህን አትሸንግል፡፡ ይልቅ የት መሄድ እንዳለብህ አስብ፡፡ የጽሞና ጊዜ ውሰድ፤ ለአእምሮህ ምግብ የሚሆኑህን ሰብስብና መንን፡፡ የማሰቢያ፣ የማሰላሰያም ጊዜ ውሰድ፡፡ የድሮ ሐሳቦችህን እንደ ላባዎቹ ነቃቅል፡፡ በቃኝ በል፡፡ ጊዜ ወስደህ ካሰብክ፣ ካነበብክ፣ ከመረመርክ፣ ካሰላሰልክ፣ ካወጣህና ካወረድክ አዳዲስ መንገዶች፣ አዳዲስ ሐሳቦች፣ አዳዲስ ነገሮች፣ አዳዲስ አመለካከቶችን ማብቀል ትችላለህ፡፡ ያን ጊዜ በአዲስ ጉልበት እንደገና ለመመለስ ትበቃለህ፡፡
እንደ ሰው ብትፈጠርም እንደ ንሥር ኑር፡፡
(መረጃ የሰጠኝን የሲያትሉን ኃይለ ኢየሱስ አመሰግነዋለሁ)
© ሁለቱም ክፍሎች በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ወጥተዋል

ንሥር እጅግ ግዙፍ ከሆኑ የአዕዋፍ ዝርያዎች አንዱ ነው፡፡ ክብደቱ እስከ 6.7 ኪሎ ሲደርስ ቁመቱ ደግሞ ከአንዱ ክንፉ ጫፍ እስከ ሌላው ጫፍ ድረስ 2 ሜትር ተኩል ይደርሳል፡፡ በዓለም ላይ እስከ ስድሳ የሚደርሱ የንሥር ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡
በኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ንሥር የትንሣኤ ሙታን፣ አርቆ የማሰብ፣ ወደ ላይ የመምጠቅና የመነጠቅ፣ የጥበቃና የምናኔ ተምሳሌት ሆኖ ተገልጧል፡፡ ግብጻውያን ደግሞ የተቀበሩ ሰዎችን አጋንንት እንዳይደርሱባቸው በመቃብራቸው በር በድንጋይ ላይ የንሥርን ምስል ያስቀርጹ ነበር፡፡ ይጠብቃቸዋል ብለው፡፡ በግሪክ አፈ ታሪክ የአማልክት ንጉሥ የሚባለው ዜውስ በንሥር የሚመሰል ነበር፡፡ ጥንታውያን የአሜሪካ ሕዝቦች እጅግ ለሚያከብሩት የሌላ ወገን ሰው የንሥርን ላባ በመስጠት ክብራቸውንና ፍቅራቸውን ይገልጡ ነበር፡፡ ሞቼ የተባሉት የፔሩ ሕዝቦችም ንሥርን ያመልኩት ነበር ይባላል፡፡
ንሥር ይህንን ያህል ቦታ በሕዝቦች ባሕል ውስጥ ሊይዝ የቻለው በተፈጥሮው በታደላቸው የተለያዩ ጸጋዎች የተነሣ ነው፡፡ 

ንሥር ከእንስሳት ሁሉ ወደ ሰማይ በመነጠቅ የሚተካከለው የለም፡፡ እርሱ የሚደርስበትን የሕዋ ከፍታ የትኛውም ዓይነት ወፍ አይደርስበትም፡፡ አንዳንድ አዕዋፍ እስከ ተወሰነ ድረስ ቢከተሉትም እንኳ እርሱ ግን ጥሏቸው ማንም በማይደርስበት የሰማይ ጥግ ብቻውን ይንሸራሸራል፡፡ ለዚህም ነው ጥንታውያን ሰዎች በሐሳብ የመምጠቅ፣ ማንም ከማይደርስበት የጸጥታ ሕዋ ላይ አእምሮን የማሳረግ፣ ተራ ነገር ማሰብና ተራ ነገር መሥራት ከሚችሉ ደካማ ልቦች ርቆ በሉዓላዊ ሐሳብ ላይ የመምጠቅ ምሳሌ ያደረጉት፡፡
ታድያ ይኼ ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- ከቁራዎችና፣ ከሌሊት ወፎች፣ ከጥንብ አናሣዎችና ከድንቢጦች፣ ከተባዮችና ከነፍሳት ጋር እዚህ ምን ታደርጋለህ? በወረደ ሐሳብ ለምን ትመስላቸዋለህ? ውጣ ወደላይ፤ ሂድ ዐርግ፣ ምጠቅ ተመሰጥ፣ እስከ ተወሰነ ቦታ ድረስ ዝንብና ትንኝ፣ እስከ ተወሰነ ቦታ ድረስም ነፍሳት፣ እስከ ተወሰነም ቦታ ድንቢጦችና የሌሊት ወፎች፣ እስከ ተወሰነውም ቁራዎችና ጥንብ አንሣዎች ይከተሉህ ይሆናል፡፡ ሐሳብህን ከፍ፣ አእምሮህንም ሉዓላዊ፣ ልቡናህንም ምጡቅ፣ አመለካከትህንም ከፍ ያለ ባደረግከው ቁጥር ግን ደካቹ ከሥር እየቀሩ ከሚመስሉህ ከንሥሮች ጋር ብቻ በጸጥታው ሕዋ ላይ ትንሳፈፋለህ፡፤ ሂድ ዐርግ፡፡
ንሥር እጅግ አስደናቂ የሆነ የማየት ችሎታ የተሰጠው ፍጡር ነው፡፡ እስከ አምስት ኪሎ ሜትር በሚደርስ ርቀት ውስጥ አንዲትን ትንሽ ጥንቸልን አንጥሮ ማየት ይችላል፡፡ የንሥር ዓይን ከጭንቅላቱ በተነጻጻሪ ሲታይ እጅግ ታላቅ ነው፡፡በንሥር ዓይን ውስጥ በአንድ ሚሊ ሜትር ስኩዌር ረቲና አንድ ሚሊዮን ለብርሃን ስሱ የሆኑ ሴሎች አሉት፡፡ ሰዎች ስንት ያለን ይመስላችኋል? ሁለት መቶ ሺ ብቻ፡፡ የንሥር አንድ አምስተኛ ማለት ነው፡፡ ሰው ሦስቱን መሠረታዊ ቀለሞች ብቻ ማየት ሲችል ንሥር ግን አምስቱን ማየት ይቻለዋል፡፡ እንዲያውም ከሩቁ አንጥሮ በማየት ንሥርን የሚተካከለው እንስሳ የለም የሚሉ ጥናቶችም አሉ፡፡
ንሥር የሚፈልገውን ለማሰስ እስከ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ዙሪያ ይዞራል፡፡ ሲያገኝ ግን ሌላውን ነገር ሁሉ ትቶ በሚያድነው ነገር ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ ‹ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት› የሚለውን የአማርኛ ብሂልና ‹jack of every thing master of non› የሚለውን የእንግሊዝኛ አባባል በደመ ነፍስ ዐውቆታል፡፡ ከትኩረቱ ፈጽሞ ንቅንቅ የለም፡፡ ምንም ዓይነት ግርዶሽ፣ ምንም ዓይነት መሰናክል፣ ምን ዓይነት መደለያ አያዘናጋውም፣ ተስፋም አያስቆርጠውም፡፡ የዚያን የአደኑን ነገር በንቃትና በትጋት እስከ መጨረሻ ይከታተለዋል፡፡ እንዲሁ አይወረወርም፤ ጊዜና ሁኔታ ይመርጣል፡፡ ጊዜና ሁኔታ ሲገጥሙለት ትኩረቱን ሰብስቦ በመወርወር ታዳኙን ይሞጨልፈዋል፡፡
ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- ደጋግመህ አስብ፤ ለመወሰን ጊዜ ውሰድ፤ ዙር ተዟዟር፡፡ ልፋ ድከም፤ አንድ ጊዜ ለመቁረጥ ሺ ጊዜ ለካ፡፡ በመጨረሻም ዒላማህን ለይ፡፡ አስተካክል፡፡ ትኩረትህንም በዒላማህ ላይ ብቻ አድርግ፤ ምንም ዓይነት ማታለያ፣ ምንም ዓይነት መደለያ፣ ምንም ዓይነት ማሰናከያ፣ ምንም ዓይነት ፈተና፣ ምንም ዓይነት ተስፋ መቁረጥ ከዓላማህ ሊያግድህ አይገባም፡፡ ማየትና ማሰብ ያለብህ ሁሉም ሊያየውና ሊያስበው የሚችለውን ተራ ነገር አይደለም፡፡ ሊታይ የማይችለውን ለማየት፣ ሊለይ የማይችለውን ለመለየት፣ ሊተኮርበት ያልቻለውን ለማተኮር ጣር፡፡ ዒላማህን ካገኘህ አትልቀቅ፤ ጊዜና ሁኔታ አመቻችና ዒላማህ ላይ ተወርወር፡፡ ያንተ ከመሆን ማንም አያግደውም፡፡
ንሥር በምንም ዓይነት የሞቱ እንስሳትን አይበላም፡፡ እርሱ እቴ፡፡ በሕይወት ያለውን እንስሳ የገባበት አሳድዶ፣ ከተደበቀበት ጠብቆ አድኖ ይበላዋል እንጂ እርሱ እንደ ቁራና ጥንብ አንሣ የሞተ ላይ አያንዣብብም፡፡ እንደ አራዳ ልጆች ከተበላ ዕቁብ ጋር አይጨቃጨቅም፡፡ ቀላል ነገር ቢያጣ በግና ፍየልም ቢሆን ተወርውሮ አድኖ፣ ከዐለት ላይ ፈጥፍጦ እንደ አጥንት ወዳጅ አበሻ ቅልጥም ሰብሮ ይበላል እንጂ የሞተ ጥንብ ሲያልፍም አይነካው፡፡ ያቺን ከባዷንና በድንጋይ የተሸፈነችውን ዔሊ እንኳን ከዐለት ስባሪ ላይ ከስክሶ ድንጋይዋን አራግፎ ይበላታል እንጂ  እንደ አበሻ ማን እንዳረደው ያላወቀውን ነገር አይበላም፡፡
ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- ልቡናህንና ኅሊናህን፣ አእምሮህንና መንፈስህን ምን እንደምትመግባቸው አስብ፡፡ የሞተ፣ የማይሠራ፣ የተበላሸ፣ ጊዜው ያለፈበት፣ ቁራና ጥንብ አንሣ የሚጫወቱበትን አትመግበው፡፡ ፊልምና ፕሮፓጋንዳ፣ ዋዛና ፈዛዛ፣ የወረዱና የበከቱ አስተሳሰቦችን አትመግበው፡፡ ከተፋና ለብለብ ሐሳቦችን አትጋተው፡፡ ይልቅ አድን፣ ድከም፣ ልፋ፣ ተሟገት፣ ተመራመር፣ እንደ ዔሊ ድንጋይ የከበደውን አስተሳሰብ ገልብጠህ፣ ፈንክተህ ተመገብ፤ ድካምና፣ ጽሞና፤ ማሰብና መመርመር የሚሻውን ንባብ ውደድ፤ ሳይለፉና ሳይደክሙ እንደ ሞተ እንስሳ ሥጋ የትም የሚገኘውን ነገር ሳይሆን ጥረትና ግረት የሚሻውን፤ ላብ ጠብ የሚያደርገውን ሞያና እንጀራ ፈልግ፡፡
ንሥር ዐውሎ ይወዳል፡፡ ሰማዩ ሲጠቁርና ደመናው ሲሰበሰብ ወጀቡም ሲያይል ሌሎች አዕዋፍ በዐለት ንቃቃትና በጫካው ችፍርግ ውስጥ ይደበቃሉ፤ በቤት ታዛ ሥርም ይሠወራሉ፡፡ ንሥር ግን ደስ ይለዋል፡፡ ወጀቡና ዐውሎው ሲጀምር ንሥር የንፋሱን ኃይል በመሞገት የራሱን ጥንካሬ ይለካበታል፡፡ የነፋሱን አቅጣጫ በመከተልም ይበራል፡፡ ራሱን ወደ ላይ ለማምጠቅና የከፍታውን ጫፍ ለመጨበጥ ይጠቀምበታል፡፡ በዚያ ጠንካራ ነፋስ ትከሻ ላይ ሲጫን ነው ንሥር ዕረፍት የሚወስደው፡፡ ክንፉን ብቻ ዘርግቶ በዕረፍት ስሜት ከደመና በላይ የኃያሉን ዐውሎ ዐቅም ተጠቅሞ ይንሸራሸራል፡፡
አንተንም ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- መከራንና ፈተናን አትፍራ፤ በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥም ቢሆን መንገድ አለና፡፡ መከራውንና ችግሩን፤ ፈተናውንና ግብግቡን የአዳዲስ ሐሳቦች መነሻ፤ የጥንካሬህ መለኪያ፤ ዐቅምህን የምትሰበስብበት አጋጣሚ፣ ወደላይ የምትመጥቅበትና ከችግር ደመናዎች በላይ የምትንሳፈፍበት ዕድል አድርገው፡፡ እንደ ሌሎች ወፎች ከመከራው አትሽሽ፤ ከችግሩም አትደበቅ፤ መከራን ለበረከት ተጠቀምበት፡፡

(ይቀጥላል)

ይኼ የመጨረሻዬ ደብዳቤ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ወይ እንደገና እንጋባለን አለበለዚያም እኅትና ወንድም ሆነን እንቀጥላለን፡፡ አሁን ‹እኅትና ወንድም ሆኖ መቀጠል›› ሲባል ቀላል ነገር ይመስላልኮ፡፡ የተለያዩ ባልና ሚስቶች ‹እኅትና ወንድም› ሆነው ለመቀጠል ሦስት ነገሮች ሳያስፈልጋቸው አይቀርም፡፡ ጠላትነትን ማጥፋት፣ ሌላ ዓይነት ወዳጅነትን መቀጠልና በአዲሱ መንገድ የሚመጡትን አስከፊ ነገሮች ሁሉ ለመቀበል መቻል፡፡ አንዳንድ ተጋቢዎች ሲለያዩ በጋብቻ ምትክ ጠላትነትን ተክተው ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ እንኳን ከዚህ በፊት አንድ ሆነው የኖሩና አንድ ሆነው ያደሩ፣ የተዋወቁም አይመስሉ፡፡ አንዱ ሌላውን ሲያስበው ያንገሸግሸዋል፡፡ ‹‹በለው በለው፣ ግደለው ግደለው› የሚለው ስሜት ይመጣበታል፡፡ ከፍቺ በኋላ ለሚፈጠሩ አሰቃቂ ወንጀሎች አንዱ ምክንያትም ይኼው ነው፡፡ ንብረት ክፍፍል ላይ ‹‹ይህንንማ አትገኛትም፣ አያገኛትም›› እየተባባሉ ምርኮ ስብሰባ የሚያስመስሉትም ለዚህ ነው፡፡

‹ሌላ ዓይነት ወዳጅነት› ያልኩሽ ቢያንስ ለመጠያየቅ፣ ተገናኝቶም ቢሆን ሻሂ ለመጠጣት፣ ስለ ልጆች ለመነጋገር፣ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠያየቅ መግባባት ላይ መድረስ ማለት ነው፡፡ በትዳሩ ጉዳይ ለጊዜው ባይግባቡም ሌላ የሚያግባባቸው ነገር አያጡም፡፡ ትዳሩ ቢፈርስ እንኳን ትውውቁና ዝምድናው እንዲቀጥል ለማድረግ መጣር አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ አንዳቸው ስለሌላቸው ክፉ ላለማውራት፣ ምሥጢሮቻቸውንም ጠብቀው ለመኖር መስማማት ኑሮን ሰላማዊ ለማድረግ ሳይጠቅም አይቀርም፡፡ ይኼ ነገር ለሁለቱም ሰላማዊ ኅሊና ይሰጣቸዋል፡፡ ከጠብ ስሜት፣ ከበቀል መንፈስ፣ ያድናቸዋል፡፡ ስለ ሌላ ሰው በክፉ ማሰብ ከሚታሰብለት ሰው በላይ ክፉ አሳቢውን ይጎዳዋል፡፡ ለስንት በጎ ነገር ሊጠቀምበት የሚችለውን የኅሊና ጉልበት ለማይጠቅም ጠብና ሐሜት፣ ጥላቻና ክፋት እንዲጠቀምበት በማድረግ ውሳጣዊ ሰላሙን ያሳጣዋል፡፡ በሌላም በኩል ደግሞ በሰላም ተለያይተው በሰላም የሚኖሩ ተፋቺዎች በጠብ ከተለያዩት ይልቅ እንደገና ለመጋባት የቀና መንገድ ይኖራቸዋል፡፡ ለፍቺ ያበቃቸው ቁስል እንዲድን ዕድል ሰጥተውታልና፡፡ ከፍቺ በኋላ በክፉ በመፈላለግ ቁስሉ ይበልጥ እንዲያመረቅዝ አላደረጉትምና፡፡

በአዲሱ መንገድ የሚመጡትን አስከፊ ነገሮች ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ መሆን ሲባል መለያየቱ የሚያመጣቸውን አሳዛኝና አስከፊ ነገሮችም ለመቀበል ዐቅም ማግኘት ማለት ነው፡፡ ተለያይቶ መኖሩን፣ የሀብት መካፈሉን፣ የአንደኛው ወገን ከሌላ የጾታ ጓደኛ ጋር መታየቱን፣ ከልጆች መለየትን የመሰሉ ነገሮችን ‹አስፈላጊ ሰይጣን› ናቸው ብሎ ለመቀበል መቻል ነው፡፡ ይህንን ለመቀበል ዐቅም ያጡ ተፋቺዎች ትልቁን ትዳር አፍርሰው ለትንሹ ንብረት ሲሟገቱ፤ እንዴት እገሌን ከሌላ ጋር አየዋለሁ፣ እንዴት እገሊትን የእገሌ ሆና አያታለሁ እያሉ ደም ሲለብሱ፤ ቆይተውም ወደ በቀል መንገድ ሲገሠግሡ ይታያሉ፡፡ ለዚህ ነው ‹እኅትና ወንድም ሆነን እንቀጥላለን›› ያልኩሽ፡፡ እርሱም ዛሬ ዛሬ ለብዙዎቻችን እያስቸገረን ነውና፡፡

የመጨረሻው ደብዳቤዬ ነውና ‹ባለቤቴ› ስለሚለው ነገር እነግርሻለሁ ያልኩትን ነግሬሽ ልጨርስ፡፡ በግእዙ ‹በዐለ ቤት› ማለት ‹የቤት ጌታ፣ የቤት አለቃ› ማለት ነው፡፡ ‹ቤት› ደግሞ በምሥራቃውያን ባሕል ብዙ ነገርን የሚይዝ ነው፡፡ ቤት ነገድ ነው ‹ቤተ እሥራኤል እንዲሉ› ቤት ሀገር ነው ‹ቤተ አምሐራ›› ብለው እንዲጠሩ፡፡ ቤት  በማኅደሩ አዳሪውን ጠርተው ‹ነዋሪ› ማለት ነው፡፡ ‹‹ቤቶች›› እንዲሉ፡፡ ቤት ‹የቅርብ ዘመድ› ማለት ነው፡፡ ‹ቤተሰብ› እንዲሉ፡፡ ቤት ወገንን ያሳያል ‹ሥራ ቤቶች›  ሲል የቤት ውስጥ ሥራ የሚሠረቱትን አንድ አድርጎ እንዲገልጥ፡፡ ባለ ይዞታነትንና ባለሀብትነትንም ይገልጣል፡፡ ‹ባለቤት› ሲል ባለሀብት ማለት እንደሆነው፡፡ ቤት ልብስም ይሆናል ‹ቤተ እግር› ሲል ካልሲ፣ ገምባሌ ማለት ነውና፡፡ ቤተ እድ ሲልም ‹እጀ ጠባብ፣ እጅጌ፣ ቀለበት› ማለት ነው፡፡ የተሸለመ እልፍኝ ማለትም ይሆናል፡፡ ‹ቤተ አንስት› ሲል የተሸለመ የተጌጠ ቤት ማለት ነው፡፡

ባለትዳሮችም ‹ባለቤቴ› ሲባባሉ የቤቴ ጌታ፣ የቤቴ አለቃ፣ ወገኔ፣ ነገዴ፣ አብሮኝ የሚኖር፣ የቅርብ ዘመዴ፣ በአንድ አብረን የምንሠራ፣ የሀብቴ የንብረቴ ባለሀብት ባለይዞታ የሆነ፣ ጌጠየ፣ ሽልማቴ፣ ልብሴ፣ ሞገሴ፣ እልፍኜ› ማለት ነው፡፡ በሌላም በኩል ‹ቤተ› ማለት ‹አደረ፣ ኖረ› ማለት ነው፡፡ ባለቤቴ ማለት ደግሞ አብረን የምናድር አብረን የምንኖር፣ ልቤ መኖሪያዋ፣ ማደሪያዋ ልቧ መኖሪያዬ፣ ማደሪያዬ የሆነ ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ሊቃውንትም ‹ጉዳዩን በቤት በኩል ብቻ ሳይሆን በ‹በዐል› በኩልም ይፈቱታል፡፡ ‹በዐለ› – ከበረ፣ ከፍ ከፍ አለ፡፡ በዐለ – ቻለ፣ ዐወቀ፣ ሠለጠነ፣ ገዛ ማለት› ነው፡፡ ‹በዐለ መድኃኒት› ሲል መድኃኒት ያለው የሚያውቅ ማለት ነው፡፡ ‹በዐለ ሥልጣን› ሲል ሥልጣን ያለው ማለቱ ነው፡፡  ‹በዐለ ቤት› ሲል ‹የቤቱ ሠራዒ መጋቢ› ማለቱ ይሆናል፡፡ ባለቤቴ የሚለው ነገር እኩል ሥልጣንን፣ እኩል ባለሀብትነትን፣ እኩል አለቅነትንና እኩል መብትን ያሳያል፡፡ በእኔ ላይ ሥልጣን ያለው፣ ሥልጣን ያላት፣ እኔን የምታውቅ፣ በእኔ ላይ የሠለጠነ፣ የሠለጠነች፣ ማለት ነው፡፡

ለዚህ ይመስለኛል በባሕላችን ‹ከባለቤትዎ ጋር› እየተባለ ጥሪ የሚተላለፈው፡፡ ሰውየው ለብቻው ሙሉ አይሆንም፣ ሴትዮዋም ለብቻዋ ሙሉ አትሆንምና፣ ሥልጣንም የላትም የለውምና፣ ስጦታ እሰጣለሁ፣ ቃል እገባለሁ፣ ብትልና ቢል አይችልምና ሙሉ አድርገን እንጥራቸው ብለው ነው ‹ከባለቤትዎ ጋር› ብለው የሚጋብዙን፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በአብርሐና አጽብሐ ዘመን ብቻ ነው ይባላል ሁለት ነገሥታት በአንድ መንበር የገዙት፡፡ ከአብርሐ አጽብሐ ወዲህ በትዳር ብቻ ይመስለኛል ሁለት ነገሥታት በአንድ መንበር የሚነግሡት፡፡ ይህንን በአንድ መንበር ሁለት ነገሥታት መንገሣቸውን ነው ‹ባለቤቴ፣ ባለቤቴ› እየተባባልን የምንጠራው፡፡

አንዱ ለሌላው ታዛዥ፣ ተገዥ ሆኖ፤ እርሱም በሌላው ላይ ገዥ፣ አዛዥ ሆኖ፣ የመኖርን ስልት ለማምጣት ነው ‹ባለቤቴ› ማለት፡፡ በፈቃድ መገዛትን፣ በፈቃድም ራስን መስጠትን ለማመልከት ነው ‹ባለቤቴ› ማለት፡፡ አንዱ የኔና ያንቺ ችግር ‹ብቻችንን ባለቤት እንሁን› እያልን ይመስለኛል፡፡ ሥልጣናችንን ስንጠቀመው ሌላውን ባለ ሥልጣን እየረሳን ስለሆነ መሰለኝ ችግራችን፡፡

እና እስኪ ከራስሽ ጋር ብቻ ተወያይና ለእኔም ባትጽፊልኝ ለራስሽ መልስ ስጭ፡፡ እኔ ለአንቺ፣ አንቺም ለእኔ ክፉ ብትሆኚ እንኳን የተሻልን ክፉዎች የምንሆን ይመስለኛል፡፡ ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይባል የለ፡፡

በይ ደኅና ሁኚ፡፡ ምንም ብንለያይ ደኅና መሆንሽ ሁላችንንም ይጠቅማልና፡፡ 

© ሦስቱም ደብዳቤዎች በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ወጥተዋል

አዘጋጅ፡- ደረጀ ትእዛዙ

ኅትመት፡- 2006 ዓም

የገጽ ብዛት፡- 308

ዋጋ፡– 84 ብር

ስለ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የታሪክ ሰው ጳውሎስ ኞኞ ታሪክ፣ ሥራዎችና ሀገራዊ አስተዋጽዖ የተጻፈ መጽሐፍ ነው፡፡ ደረጀ የጳውሎስ ጎረቤት ነበረ፡፡ ያደገውም እነ ጳውሎስ ሠፈር ነው፡፡ የልጅነቱ ትዝታ ስለ ጳውሎስ እንዲያጠና እንዳደረገው ይነግረናል፡፡ የጳውሎስን ሥራዎችና ስለ እርሱ የተጻፉ መዛግብትን አገላብጦ፤ ዛሬም በሕይወት ለታሪክ ቆይተው ያገኛቸውን የቅርብ ሰዎቹን አናግሮ ዙሪያ መለስ የሆነ ሥራ አቅርቦልናል፡፡




የጳውሎስን ጉዞ ከትውልድ መንደሩ እስከ ተጓዘባቸው የዓለም ክፍሎች፣ ከትውልድ ሥፍራው ቁልቢ እስከ መቀበሪያው ቀጨኔ መድኃኔዓለም፣ ከእናቱ ቤት እስከ ሠፈረ ሰላም ዕድር፣ ከቁርጥራጭ ጋዜጣ ንባብ እስከ ‹የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒድያ› ዝግጅቱ፣ ከምስጋናው እስከ ክሱ፣ ከሽልማቱ እስከ ውግዘቱ ያለውን ታሪክና ገጠመኝ ይዳስሳል፡፡

ደረጀ ስለ ጳውሎስ የሚመሰገንበትን ብቻ ሳይሆን የሚወቀስበትን፣ የሚደነቅበትን ብቻ ሳይሆን የሚነቀፍበትን፣ ብርታቱን ብቻ ሳይሆን ድክመቱንም እንድናየው አድርጎናል፡፡ ከጠባዩ እስከ ችሎታው፣ ከእምነቱ እስከ ፍልስፍናው፣ ከኩርፊያው እስከ ደግነቱ ያሳየናል፡፡ 

በጳውሎስ ኞኞ ታሪክ በኩል የኢትዮጵያን ፕሬስ ጉዞ፣ የነበሩትን ዋና ዋና ተዋናዮች፣ የነበረባቸውን ፈተና፣ አስተዳደራዊ፣ ፖለቲካዊና ፍልስፍናዊ ተግዳሮት፣ በየዘመናቱ የተነሡ ጋዜጠኞች ለፕሬስ ነጻነት እንዴት ይጋደሉ እንደነበር፣ ከንጉሥ እስከ ሰካራም፣ ከአንባቢ እስከ አለቃ ይደርስባቸው የነበረውን መከራ ያሳየናል፡፡

ጳውሎስ ጋዜጠኛ ብቻ ሳይሆን ራሱን በራሱ ያስተማረ፣ ታሪካችንን ፈልፍሎ በራሳችን ቋንቋ ሊያቀርብልን የሞከረ፣ በሀገሪቱ በተከሰቱ ልዩ ልዩ ችግሮች ወቅት ወገቡን ታጥቆ ለወገኑ የለፋ፣ ከመንደሩ ማኅበራዊ ግንኙነት እስከ ብሔራዊ ችግሮች ድረስ፣ ከድርቅ እስከ ሶማሌ ጦርነት ድረስ ለሀገሩ የደከመ ክቡር ዜጋ መሆኑን መጽሐፉ ያሳየናል፡፡

ጳውሎስ የተማረው እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ብቻ ነው፡፡ ራሱን በራሱ አስተምሮ ግን ከሊቃውንቱ በላይ ለመሥራት ችሏል፡፡ መማርን ለደመወዝና ለግድግዳ የምረቃ ፎቶ ብቻ ለሚያደርጉ ሰዎች ጳውሎስ ታላቅ ማስተማሪያ ነው፡፡ የውጤት መንገዱ ፍላጎት፣ ጥረትና ያለ መታከት መሆኑን ጳውሎስ ያሳየናል፡፡ ዛሬ ብዙ ዕድሎች ተመቻችተውልን ጊዜውን በቀልድ ለምናሳልፍ ሰዎች ጳውሎስ መውቀሻ ነው፡፡

ወጣቶች የከተፋና የቶሎ ቶሎ ሥራዎች ላይ ተጠምደዋል እየተባለ በሚተችበት በዘህ ጊዜ ደረጀ ትችቱን ሐሰት አድርጎ ጊዜ የሚወስድ፣ ሰነድ ማገላበጥን የሚጠይቅ፣ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ አያሌ ደጅ መጥናቶችን የግድ የሚል ሥራ ይዞ መምጣቱ ያስመሰግነዋል፡፡

ጳውሎስ ኞኞን የምታውቁት ትዝታችሁን ይጭርላችኋል፡፡ የማታውቁት ታሪኩን አብራችሁ የነበራችሁ ያህል ያሳያችኋል፡፡ በዚያውም የአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ታሪክ የሀገሪቱ ታሪክ መሆኑን በሚገባ ያሳያችኋል፡፡ ጥላሁን ገሠሠ ‹‹ምናለ አንዳንዱ ሰው ዳግመኛ ቢፈጠር›› ያለው ሊሠራባቸው ከሚገቡት አንዱ ጳውሎስ ኞኞ መሆኑን መጽሐፉን ስታነቡ ታረጋግጣላችሁ፡፡ 

መልካም ንባብ፡፡

(አርቲስቱና ሽቅርቅሩ የድሬዳዋ ሕዝብ)


ደራሲ፡- አፈንዲ ሙተቂ

የገጽ ብዛት፡-191

ዋጋ፡- 60 ብር

የኅትመት ዘመን፡- 2006 ዓም

አፈንዲ ሙተቂ ያበረከተልንን መጽሐፍ አነበብኩት፡፡ ከአዋሽ ወዲያ ማዶ ያለውን ሀገራችንን ሙልጭ አድርገን ለማወቅ የሚጎድለን ነገር መኖሩን የምንረዳው የእርሱን መጽሐፍ ስናነብ ነው፡፡ እንኳን እንደ እኔ በጎብኝነት የሚያውቀው ቀርቶ ተወልጄበታለሁ አድጌበታለሁ የሚለው ሁሉ የቀበሌ መታወቂያውን እንደገና እንዲያወጣ የሚያደርግ መጽሐፍ ነው፡፡

ሰው የሚያውቀውን ሲጽፍ ወይም የሚጽፈውን ሲያውቅ እንዲህ ያለ መጽሐፍ ይገኛል፡፡ ባሕሉ አልቀረ፣ ትውፊቱ አልቀረ፣ አባባሉ አልቀረ፣ ታሪኩ አልተዘለለ፣ መልክዐ ምድራዊ መረጃው አልተዘነጋ፣ አፈ ታሪኩ ቦታውን አልሳተ፣ ሁሉም በመልክ በመልኩ ተሰድሮ እንደ መልካም የወታደር ሠልፍ የቀረበበት መጽሐፍ ነው፡፡

አፈንዲ ለአካባቢው ወግና ታሪክ ቅርበት ብቻ ሳይሆን ፍቅርም እንዳለው፣ ፍቅር ብቻም ሳይሆን ጥናትም እንዳለው፣ ጥናትም ብቻ ሳይሆን ትኩረትም እንዳለው መጽሐፉ ያሳየናል፡፡ የሕዝቡን ፍቅርና አንድነት፣ መተሳሰብና አብሮነት፣ የቆየውን የመተጋገዝ ልማድና ተግባቦት ያሳየባቸው ወጎቹ የመለያየት ጥላ ላጠላበት ህልውናችን ፈዋሾ ናቸው፡፡

በተለይም የሐረርጌ ኦሮሞን ትውፊትና ባሕል፣ የአስተዳደር ታሪክና ዕምቅ ብቃት ያሳየበት ጹሑፉ እዚያው ሕዝቡ ውስጥ ያለን ያህል እንድንረዳው የሚያደርግ ነው፡፡ አፈንዲ የአካባቢውን ነገር ሲነግረን በአንዳንዶች ዘንድ እንደሚታየው እንድንጠብ አድርጎ ሳይሆን እንድንሰፋ አድርጎ ነው፡፡ ያንን አካባቢ ከእኛ ውጭ አድርገን እንድናየው አድርጎ ሳይሆን ውስጡ እንድንገባበት አድርጎ ነው፡፡

አፈንዲ ሦስት ነገሮች አሉት፡፡ ርትዕ፣ ዕውቀትና የኃላፊነት ስሜት፡፡ ነገሮችን ያየበት መንገድ ርትዕ እንዳለው የሚያሳይ ነው፡፡ በአካባቢው ለተደረጉ ነገሮች ሁሉ ሃይማኖትና ዘርን ሳይለይ ለሁሉም የድርሻውን ሰጥቷል፡፡ የተለያዩ እምነቶች፣ ባሕሎችና ግለሰቦች በአካባቢው የነበራቸውን በጎ ሚና ለማጉላት፣ ክፉውንም በጨዋነት ለማረም ያደረገው ጥንቃቄ የሚያስመሰግነው ነው፡፡

አፈንዲ በተለይ ከአዋሽ ማዶ ስላለው ታሪክ፣ ባሕል፣ ትውፊትና መልክዐ ምድር ለሌላውም ሊተርፍ የሚችል ዕውቀት ስላለው የሚጽፈው የቃላት ስብስብ አይደለም፡፡ በእያንዳንዱ ቃል ላይ ዕውቀት ያዘለ ነገር አለው፡፡ የሚጽፍ ሰው የሚጽፈው ነገር የት እንደሚደርስ አያውቅምና በኃላፊነት ስሜት እንዲጽፍ ይመከራል፡፡ አፈንዲ በዚህ መጽሐፉ በእምነቶች፣ በሕዝቦች፣ በጎሳችና በፖለቲካ መሪዎች መካከል ተግባቦት ይፈጠር ዘንድ፣ መደናነቅና መከባበር እንዲኖር የሚያደርጉ ሐሳቦችን በኃላፊነት መንፈስ ጽፏል፡፡ ‹‹እንዴው ዘራዋ›› የሚል ነገር አላየሁበትም፡፡ ታላቅ ችሎታና ብስለት ነው፡፡

አንቡት፡፡ ታውቃላችሁ፣ ትዝናናላችሁ፣ ትጨምራላችሁ፡፡

ይህንን ደብዳቤ ስጽፍ ፊት ለፊቴ የቤተሰባችንን ፎቶ ግድግዳው ላይ እያየሁ ነው፡፡ ‹‹ይናገራል ፎቶ›› አሉ፡፡ አቤት በፎቶማ እንዴት ያምርብናል፡፡ ፎቶ ላይ ያለው ፈገግታ እንዲሁ ትዳር ውስጥም ቢቀጥል እንዴት ጥሩ ነበር፡፡ ግርም ይላልኮ፡፡ፎቶ አንሺዎች ሁሉ ከአንድ እናት የተወለዱ ይመስል ለምንድን ነው በግድ ‹‹ፈገግ በሉ›› የሚሉት፡፡ በቃ ፎቶ ማለት ደስታን ማሳያ ብቻ ነው እንዴ፡፡ የከፋው ሰው ፎቶ አይነሳም ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ፎቶ አንሺዎችና ቪዲዮ ቀራጮችኮ በገዛ ሠርጋችን ተዋንያን ያደርጉናል፡፡ እንደ ራሳችን ሳይሆን እንደ እነርሱ ፈቃድ ያስኬዱናል፣ ያሳስሙናል፣ ያስተቃቅፉናል፣ ያሰልፉናል፣ ያጣምሙናል፣ ያቃኑናል፡፡ እነርሱ ግን የፊልም ዳይሬክተር ናቸው ወይስ የሠርግ ቪዲዮ ቀራጮች? እኛስ ሙሽሮች ነን ወይስ ተዋንያን?

ከተለያየን ጀምሮ ይህንን ፎቶ ደጋግሜ እያየሁ ደጋግሜ አስባለሁ፡፡ ለብቻ መሆን አንድ የሚጠቅመው ነገር ቢኖር የማሰቢያ ጊዜ መስጠቱ ነው፡፡ ሰው ለመኖር ለካ ከምግብና መጠለያ እኩል የማሰቢያ ጊዜም ያስፈልገዋል፡፡ እንዲሁ ስንዞር፣ እንዲሁ ስንወጣና ስንወርድ፣ እንዲሁ ቀዳዳ ለመሙላት ወዲህ ወዲያ ስንል፣ እንዲሁ ጠዋት ወጥተን ማታ ስንገባ አይደል እንዴ የኖርነው? አሁን ሳስበውኮ የኑሮ ወንዝ ወደወሰደን ፈሰስን እንጂ አስበን አልኖርንም፡፡

እስኪ ልጠይቅሽ ለመሆኑ ለኛ ትዳር ምንድን ነበር? አንድ ቤት መኖር፣ አንድ አልጋ ላይ መተኛት፣ ልጆች መውለድ፣ ወላጆቻችን ቤት አንድ ላይ መሄድ፣ መጎራረስ፣ <ከባለቤትዎ ጋር> ተብሎ መጠራት፣ ምንድን ነው ግን ትዳር? ለመሆኑ ሠርገን ነበር ወይስ ተጋብተን ነበር? ጋብቻ ነበረን ወይስ ትዳር? አቤት ለሠርጋችን እንዴት ነበር የለፋነው፡፡ ‹‹ጋብቻ የትዳር መጀመሪያው ሥነ ሥርዓቱ ነው፤ ሠርግ ማጀቢያው ድግስ ሲሆን፣ ትዳር ደግሞ በዚህ በኩል ተገብቶ የሚኖረው ኑሮ ነው›› የሚል ካነበብኩ በኋላ ይህንን ጥያቄ መጠየቅ ጀምሬያለሁ፡፡ አዳራሽ ለማግኘት፣ መኪና ለማግኘት፣ የሠርግ ልብስ ለመምረጥና ለማሰፋት፣ ድግሱን ለማሣመር፣ የሚጠሩ ሰዎችን ለመምረጥ፣ ሚዜዎቻችንን ለመምረጥ ስንቴ ነበር ያሰብነው፤ ሰሐንና ብርጭቆ እንኳን ሳይቀር አስበንበት፣ ሰው አማክረን፣ ዙረን መርጠን፣ ከሌሎች ልምድ ወስደን ነበር የተከራየነው፡፡

በእኔና ባንቺ ሠርግ ስንት ሰዎች ተሳተፉ፣ ስንቶች ለፉ፣ የስንት ሰዎች ሐሳብ ተዋጣ፣ የስንቶች ልምድ ተቀሰመ፣ የስንቶች ጉልበትስ ፈሰሰ፡፡ በያንዳንዱ ጉዳይ እንወያይ፣ እንከራከር፣ እንጨቃጨቅ፣ እንለያይ ነበር፡፡ በያንዳንዱ ጉዳይ እንደገና እንገናኝ፣ እንግባባ፣ እንስማማና እንታረቅ ነበር፡፡ በብዙ ሰዎች ታግዘን አግብተን ትዳርን ብቻችንን ገጠምነውና አልቻልነውም፡፡ ሠርግ ላይ ያለው እገዛ ትዳር ላይ ቢሆን እንዴት ጥሩ ነበር፡፡

አሁን ሳስበው የለፋነው ለሠርጋችን እንጂ ለትዳራችን አልነበረም፡፡ እስኪ ትዝ ይበልሽ፡፡ ከኛ በፊት የተጋቡ ሙሽሮችን ልምድ የወሰድው ስለ ሙሽራ ልብስ፣ ስለ ቬሎ፣ ስለ ሚዜ፣ ስለ መኪና፣ ስለ ድግስ፣ ስለ አዳራሽ፣ ስለ መጥሪያ ካርድ፣ ስለ ባንድ፣ ስለ ቪዲዮ እንጂ ስለ ኑሯቸው አልነበረም፡፡ እነርሱምኮ ‹ዲል› ባለ ድግስ፣ የሁላችንንም ቀልብ በማረከ ሥነ ሥርዓት ተጋብተው ይሆናል፡፡ ከዚያስ? ነው ጥያቄው፡፡ የኛስ ሠርግ ጉ-ድ የተባለ አልነበረም፡፡ እስካሁን ድረስ የእኔና የአንቺን ሠርግ እንደ ትንግርት የሚያወሩት አሉኮ፡፡ ከሠርጉ በኋላ የሆንነውን ስለማያውቁ፡፡

አንድ ወዳጄ ትዳርና ችግኝ አንድ ነው ብሎኛል፡፡ ሁለቱም ክብካቤ ይፈልጋሉ፡፤ ሁለቱም በየጊዜው መኮትኮትና ማሳደግን ይጠይቃሉ፡፡ ሁለቱም መከርከምና ድንጋይና አረሙን እንዲያስወግዱላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ሁለቱም የዕለት ተዕለት ትኩረት ይሻሉ፡፡ እኛ ግን እንደዚያ ያደረግን አይመስለኝም፡፡ ጉልበታችን ሁሉ ለሠርጉ ፈሰሰና ትዳሩ ላይ አቅም ጠፋ፡፡ ‹‹ዳገት ላይ ሰው ጠፋ›› አሉ ፕሮፌሰር መስፍን፡፡ ድሮ ልጆች ሆነን

ገንዘባችን ሁሉ አለቀ በሻይ

ሚስት ሳናገባ ዓለምን ሳናይ – እንል ነበር፡፡ ከየት የመጣ ግጥም እንደሆነ እንጃ፡፡ የኛም ጉልበታችንና ዐቅማችን ሁሉ ሠርጋችን ላይ ፈሰሰና ‹ዓለምን ሳናይ› ቀረን፡፡ ይገርምሻል፡፡ በቴሌቭዥን ሰሞኑን የችግኝ ተከላ ዜና ሲነገር ትዝ የሚለኝ የእኔና የአንቺ ትዳር ነው፡፡ ድሮ በሠፈራችን በሚገኝ ጋራ ላይ ሰኔ በመጣ ቁጥር በቀበሌ ትእዛዝ እየወጣን የምንተክለው ችግኝ ነበር፡፡ ከተከልነው በኋላ ግን ዞር ብሎ የሚያየው የለም፡፡ ሰኔና ሰኞ የገጠመለት  ችግኝ ይጸድቃል፡፡ ሌላው ግን ደርቆ ይቀራል፡፡ ቀበሌውም ማስተከል እንጂ ማሳደግ አያውቅበትም፡፡ የብዙዎቻችን ትዳር እንደዚያ ይመስለኛል፡፡ ልክ አንድ አገር ሰው ተሰብስቦ ችግኝ እንደሚተክለው ሁሉ አንድ አገር ሰው ተሰብስቦ ትዳር የሚባለውን ችግኝ የሠርግ ቀን ይተክለዋል፡፡ ችግኙን ማንም ዞር ብሎ እንደማያየው ሁሉ ትዳርን የሚከባከበው፣ ውኃ የሚያጠጣው፣ አረም የሚነቅልለት፣ አፈር የሚያደርግለት፣ ፋንድያ የሚደፋለት፣ አውሬ እንዳያበላሸው አጥር የሚቀጥርለት የለም፡፡ ልክ ያደለው ችግኝ በዕድል አድጎ እንደሚገኘው ሁሉ፣ ያደለው ትዳርም አድጎ ተመንድጎ እናየው ይሆናል፡፡ ‹‹አፍራ ያለው ተኝቶም ያፈራል›› ይባል የለ፡፡ ብዙ ትዳሮች ግን እንደ ብዙዎቹ ችግኞች ከስመው ቀርተዋል፡፡

እኔማ አንዳንዴ ‹ለሠርጋችን ከተጨነቅነው ግማሹን እንኳን ለትዳራችን አድርገነው ቢሆን ኖሮ እንደዚህ ባልሆንን ነበር› እላለሁ፡፡ እንዴው ብቻዬን ስለሆንኩ ሰው አያየኝም እንጂ፣ ያበድኩኮ ነው የምመስለው፡፡ ብቻዬን እስቃለሁ፤ ብቻዬንም አወራለሁ፡፡ ባለፉት ዓመታት ያወራናቸውን ሳስባቸው ስለ ቤት ወጭ፣ ስለ ልጆች ትምህርት ቤት፣ ስለ ወላጆቻችን፣ ስለ ጎረቤቶቻችን፣ ስለ ልቅሶና ሠርግ፣ ስለ ርዳታና መዋጮ፣ ስለ መኪናና የቤት ዕቃ፣ ስለ ሥራ ቦታ ችግሮች ሆነው አገኛቸዋለሁ፡፡ እነዚህ ነገሮች ግን ብቻ እንዴት ትዳርን ያሳድጉታል? እንዴትስ ፍሬያማ ያደርጉታል? ስለ እኔና ስለ አንቺ፣ ስለምትወጅውና ስለምትጠይው፣ ስለምንጨምረውና ስለምናርመው፣ አንቺን ይበልጥ ስለማስደሰትና እኔን ይበልጥ ስለማርካት፣ እኔ ላንቺ ማድረግ ስላለብኝና አንቺ ለእኔ ማድረግ ስላለብሽ ነገር ማውራታችንን፣ መወሰናችንንም አላስታውስም፡፡

ደግሞ የሚገርምሽ ነገር፤ ዛሬ ዛሬ ሳስበው ግርም የሚለኝ፣ የምንነጋገረውኮ በሚያጋጥሙን ነገሮች ላይ ብቻ ነው፡፡ አንዳች ነገር ካልገጠመን አንነጋገርም፡፡ ለነገሩማ በዝምታ አድገን እንዴት መነጋገር እንልመድ ብለሽ ነው፡፡ ‹‹ጥፋቱስ አይደለም ካንቺ ወይም  ከእኔ፣

ፍቅር በመሆኑ እንጂ ጽድቅና ኩነኔ፣

አንቺ አንቺን መሆንሽ እኔ እኔን መሆኔ››

አሉ አብዬ መንግሥቱ እውነታቸውን ነው፡፡ እንዴው ጊዜ ወስደን፣ ከሌላው ነገር ወጣ ብለን፣ እየተዝናናንም ቢሉ ወይም ለራሳችን ጊዜ ሰጥተን ስለ ወደፊት ኑሮአችን፣ ስለ እኔና አንቺ ጉዳይ፣ ልናደርገው ስለምንፈልገው ነገር ወይም መሆን ስለምንሻው ጉዳይ አውርተን እናውቃለን ብለሽ ነው? እንዴው ሊመጣልኝ አልቻለም፡፡ አንድ ነገር ይገጥመናል፣ በዚያ ላይ እናወራለን፣ ጉዳዩ ከእኔ ወይንም ካንቺ ጋር ይገናኝና አንዳችን አጥቂ ሌላችን ተከላካይ እንሆናለን፡፡ ከዚያማ ‹‹ጨሰ አቧራው ጨሰ›› ማለት ያኔ ነው፡፡ ግን ለመሆኑ ይህንን ‹‹ጨሰ አቧራው ጨሰ›› የሚል የሠርግ ዘፈን ያመጣው ማነው? መቼም እንደኔ አግብቶ የፈታ ሰው መሆን አለበት፡፡

በተለይማ ልጆች ከመጡ በኋላ ባሰብን፡፡ እኔም ባልሽ መሆኔ ቀርቶ የልጆችሽ አባት ሆንኩ፤ እንቺም ሚስቴ መሆንሽ ቀርቶ የልጆቼ እናት ሆንሽ፡፡ ለመሆኑ ግን ከኛ የሚተርፈንን ጊዜ ነው ለልጆች መስጠት ያለብን ወይስ ከልጆች የሚተርፈውን ጊዜ ነበር እኛ መውሰድ የነበረብን? ለመሆኑ በትዳር ውስጥ ዋናው ጉዳይ ምንድን ነው? ‹ባለቤቴ› የሚለውን ባሕላዊ አጠራር የወደድኩትም ያደነቅኩትም አሁን ነው፡፡ ለምን መሰለሽ? በቀጣዩ ደብዳቤዬ እነግርሻለሁ፡፡

ብንጣላም፣ ብንለያይም፣ ባንግባባም፣ ግን ደኅና ሁኚ፡፡

ያንቺው የቀድሞ ባለቤት

(ሳምንት ይቀጥላል)

 © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

ሰሞኑን ከአንድ ሰው ‹የማጭበርበር› ነገር ጋር በተያያዝ ከዚህም ከዚያም አስተያየት ይሰጣል፡፡ አብዛኞቹ የመገናኛ ብዙኃንም ትኩረታቸውን በሰውዬው ላይ አድርገው እንዴት እንዲህ ሊያደርግ ቻለ? ለምን እንዲህ አደረገ?ምን ነክቶት ነው? እያሉ ጉዳዩን ከማኅበረሰብ ሳይንስ፣ ከሥነ ልቡና፣ ከእምነትና ከባሕል አንጻር እየተነተኑ ይገኛሉ፡፡

እኔ ግን ይህን ጉዳይ ስከታተል ትዝ የሚለኝ አንድ የሀገራችን ተረት ነው፡፡ ሰውዬው መንገድ ላይ ሲሄድ በሩ ወለል ብሎ የተከፈተ ቤት ያገኛል፡፡ ለጥቂት ቆም ብሎ ሁኔታውን ሲያይ ማንም በአካባቢው ዝር የሚል አልነበረም፡፡ ነገሩ የተከፈተ በር ብቻ ሳይሆን ‹የተከፈተ ዕድልም› የሆነለት ሰውዬ የተከፈተው ቤት ውስጥ ዘው ብሎ ይገባል፡፡ማንም አልነበረም፡፡ ወዲያና ወዲህ እየተንጎራደደ ቤቱን ቃኘና ዓይኑ ያረፈበትን ዕቃ ይዞ ላጥ አለ፡፡ መንገድ ላይ ያዩት ሰዎች የሚያውቁትን ዕቃ አንድ ሰው ይዞ ሲሸመጥጥ በማየታቸው ይጠራጠሩና ያስቆሙታል፡፡ ፖሊስም በነገሩ ይገባበታል፡፡ ሰውም ከዚህም ከዚያም ይወርድበታል፡፡

ግርግሩ በዚህ መልክ እየቀጠለ ዕቃቸው የተሰረቀባቸው ሰዎች ኡኡ እያሉ ይደርሳሉ፡፡ ሲደርሱም የቤት ዕቃቸው በአንድ በማያውቁት ሰው ትከሻ ላይ ያገኛሉ፡፡ ግርግሩን ሰንጥቀው ይገቡና ‹‹ሞላጫ ሌባ›› እያሉ ሌባውን በጥፊ ሲመቱት ሌባው ተናድዶ ዕቃውን ያወርድና ጥፊውን በጥፊ ይመልሳል፡፡ ፖሊስ በድርጊቱ ተገርሞ ከዚያ ሁሉ ሰው ይልቅ ለባለቤቶቹ ጥፊ ለምን መልስ እንደሰጠ ሲጠይቀው ‹‹ቤታቸውን ከፍተው እየሄዱ ሰው ሌባ ያደርጋሉ›› አለ ይባላል፡፡

የሰሞኑ ሁኔታም ይህን ነገር እንድናየው የሚያደርግ ነው፡፡ ለመጭበርበርና ለመታለል የሚችል አሠራር፣ አካሄድና አፈጻጸም የዘረጋነው እኛው ነን፡፡ ነገሮችን በመረጃና በማስረጃ ላይ ተመርኩዘን ከመወሰን ይልቅ በሚወራ ወሬ፣ በሚገነባ ገጽታና ከሚዲያ በምንሰማው ነገር ላይ ብቻ የመመራትን አሠራር ያሰፈንነው እኛው ነን፡፡ ዛሬ ቀን ጥሎት የተጋለጠው ሰው ላይ በወደቀ ዛፍ ላይ የሚበዛውን ምሣር ሁሉ እናዘንብበታለን እንጂ ሌሎች ወደፊት እንዳይከሰቱ የሚያደርግ አደረጃጀት፣ አሠራርና አስተሳሰብ ግን አልዘረጋንም፡፡  

እንዲያውም የዚህን ሰው በዚህ መልኩ መምጣት ለሀገራችን ተቋማትና ኃላፊዎች ‹በረከተ መርገም› የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ‹ዓመት ባል ካልመጣ ሁሉ ሴት፣ ክረምት ካልመጣ ሁሉ ቤት› የሚባል አባባል አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ባይኖሩ የኃላፊዎቻችንን፣የምሁሮቻችንንና የመሥሪያ ቤቶቻችንን የተዝረከረከ አሠራር እንድናይ ማን ያደርገን ነበር፡፡ እዚህ ሀገር ምን ዓይነት ሰዎች ምን ዓይነት ቦታ እንደሚይዙ አሳይቶናል፤ ሴትዮዋ ‹አፍ ያለው ያግባሽ ከብት ያለው› ስትባል ‹‹አፍ ያለው ያግባኝ፣ አፍ ያለው ከብቱን ያመጣዋልና›› ያለችው እውነቷን ነው እንድንል አስችሎናል፡፡ አፍ ካለ፣ መናገር ከተቻለ፣ መስጠት ከተቻለ፣ እዚህ ሀገር ውስጥ ዕድሉም መንገዱም ወለል ብሎ እንደሚከፈት አይተናል፡፡ ሚዲያዎቻችንም የማጣረት፣ የመመርመርና ከግራ ቀኝ የማየት ዐቅማቸው የት ድረስ እንደሆነ አሳይቶናል፡፡ ‹ማን ምን አለ› እንጂ ‹ያለው ልክ ነው ወይ?› ብሎ ለማረጋገጥ ጥቂት እርምጃዎች መሄድ የሚችሉ ሚዲያዎች እንደዋልያ ‹ብርቅዬ ድንቅየ›› መሆናቸውን ተምረንበታል፡፡

እንዲህ ያለ ሰውማ ይምጣ፡፡ እዚህ ሀገር ድፍረት እንጂ ዕውቀት፣ ትውውቅ እንጂ ዕውውቅ፣ ዘመድ እንጂ ችሎታ፣ ቅልጥፍና እንጂ ጉብዝና ዋጋ እንደሌላቸው እናይ ዘንድ፡፡

እኔን ምን አገባኝ የሚሉት አጉል ወግ

እርሱ ነው ሀገሬን ያረዳት እንደ በግ

የሚል ግጥም ልጽፍ ተነሣሁኝና

ምን አገባኝ ብዬ ተውኩት እንደገና

ብሎ የጻፈውን ባለ ቅኔ እውነት እንድናየው አድርጎናልና እንዲህ ያለ ሰውማ ይኑር፡፡

ምሁሮቻችን ያላስተማሩት ተማሪ ከፊታቸው ቆሞ አስተምራችሁኛል ሲላቸው፣ ተማሪዎቹ ብቃት አንሷችሁ እኔን ማየት ሳትችሉ ቀርታችሁ ነው እንጂ አብሬያችሁ ተምሬ ነበር ሲላቸው፣ የዩኒቨርሲቲዎች አስተዳደሮች ረስታችሁኝ ነው እንጂ ሸልማችሁኝ ነበር ሲላቸው፣ በቅቼ ተሠውሬ ነው እንጂ አብሬያችሁኮ ነው የምሠራው ሲላቸው፤ የቤተ መንግሥት ሰዎች በእሳት ሠረገላ ገብቼ አላያችሁኝም እንጂ ከአቶ መለስ ጋር አብሬ ነበርኩኮ ሲላቸው ዝም ያሉት ‹ዝምታ ወርቅ ነው›› ብለው አይደል፡፡ የዝምታችን ነገር የት ድረስ እንደሚደርስ፣ ስሕተትን የመቻል ዐቅማችን የት ድረስ እንደሆነ፣ የተበላሸን ነገር የመሸከም ችሎታችን ምን ያህል እንዳደገ፣ ውሸትን የመቀበል ብቃታችን ጨምሮ ጨምሮ እዚህ መድረሱን በሚገባ አሳይቶናል፡፡ ኑርልን ባክህ፡፡

ባለፈው ጊዜ በዓለም ዋንጫ ጉዟችን አንድ ተጨዋች ሁለት ቢጫ ካየ በኋላ እንደገና ተሰልፎ በመጨዋቱ ፊፋ ቀጣን፡፡ ይህ ቅጣት ብዙ ሰዎችን አሳዘነ፡፡ ያ ቅጣት ግን ብናውቅበት ኖሮ በረከተ መርገም ነበር፡፡ የፌዴሬሽናችንን አሠራር ቁልጭ አድርጎ በአደባባይ ያሳየን፡፡ እንኳንም ተጨዋቹ ተቀጣ፣ እንኳን ፌዴሬሽኑም ተዝረከረከ፡፡ ያንን ዝርክርክነት እንዴት አድርገን እናየው ነበር፡፡ ከዚያ በፊትምኮ ከዚያ የባሱ ዝርክርክ አሠራሮች ይኖሩ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በድብብቁ አሠራራችን ምክንያት ‹ሽል ሆነው ከመግፋት ይልቅ ቂጣ ሆነው እየጠፉ› ሳናያቸው ኖርን፡፡ ያንን አጋጣሚ ማለፍ ግን አልተቻለም፡፡ ዓለም ያወቀው፣ ዓለም ሊያውቀውም ግድ የሚለው ጥፋት ነበረና፡፡

የሚገርመው ነገር እንዲያ ዓይነት አገርን አንገት ያስደፋን ጥፋት ሲሆን እንዳይፈጸም፣ ካልሆነም እንዲታረም የሚያደርግ አሠራር ባለመዘርጋታችንና አመለካከታችንንም ባለማስተካከላችን በሴቶች እግር ኳስ ላይ ተደገመና የፓስፖርት መጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባትን ተጨዋች ለማሰለፍ ሜዳ ውስጥ እስከማስገባት ደረስን፡፡ ይኼኛውን ዝርክርክነት ለማወቅ የቻልነው ለማወቅና ለመታወቅ የግድ የሚለው ዓለም አቀፋዊ አሠራር በመኖሩ የተነሣ ነው፡፡

ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ(ገሞራው) ‹በረከተ መርገም› በሚለው ግጥሙ ላይ ‹ድኻው ምን አረገ ሊቆቹን ነው መርገም› ይላል፡፡ አሁን መረገም ያለበት ተቋማዊ አሠራራችን፣ አስተሳሰባችን፣ የመረጃ አያያዛችን፣ ነገሮችን በንሥር ዓይን ከማየት ይልቅ በተወራውና በተባለው ብቻ መመራታችን፣ የዘመድ አዝማድ አካሄዳችን፣ የተጠጋጋውን ሁሉ የሚያምነው አሠራራችን ነው፡፡ መረገም ያለበት ለመታለል፣ ለመሞኘት፣ ለመሸወድ፣ ለመጭበርበር እጅግ ቀላልና እጅግም ዝግጁ የሆነው ቢሮክራሲያችን ነው፡፡

ይህን መሰል ሰዎች መምጣታቸው በሀገራችን እጅግ ተወዳጁ ምግብ ‹ምላስና ሰንበር› መሆኑን እንድናውቅ አድርጎናል፡፡ ምላስና ሰንበር ካለህ የፈለግከውን ተናገር – ትሰማለህ፤ ምላስና ሰንበር ካለህ የፈለግከውን ነኝ በል – ትታመናለህ፤ ምላስና ሰንበር ካለህ የፈለግከው ቦታ ደርሻለሁ በል – ትደነቃለህ፤ ምላስና ሰንበር ካለህ እንደ ኢዲ አሚን ሁሉንም መዓርግ ለራስህ ስጥ – ትሞገሳለህ፤ ምላስና ሰንበር ካለህ ዐዋቄ ኩሉ ነኝ በል – ተከታይ ታገኛለህ፡፡ የዚህን መሰል ሰዎች መነሣት ይህንን አሳይቶናል፡፡ እንኳንም ተነሣችሁ፡፡

ደግሞስ እነርሱ ባይኖሩ ይህንን መሰሉን የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የተወካዮች ምክር ቤት፣ ዋናው ኦዲተር፣ ያልደረሰባቸውን የተበላሹ አሠራሮች እንዴት እናያቸው ነበር? ኧረ እንኳን ኖራችሁ፤ ለኛ በረከተ መርገም ናችሁ፡፡ 

 © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

<<ስኩል ኦፍ ኖርዘርን ስታር›› ከሚባለው ውድ ትምህርት ቤቱ የአያቱ ሾፌር ወደ ቤቱ ሲያመጣው ልቡ ከመኪናው ፍጥነት በላይ ነበር ወደ ቤቱ የሚሮጠው፡፡ ያየውንማ ለአያቱ መንገር አለበት፡፡ አያቱ እንዲህ ታዋቂ  አክተር መሆናቸውን አያውቅም ነበር፡፡ ፊልሙን ሲመለከት አያቱን በመሪ ተዋናይነት በማግኘቱ ከትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር በኩራት ነበር ያወራው፡፡ እነርሱም የታዋቂ ሰው የልጅ ልጅ በመሆኑ ከፊልሙ በኋላ እንደ ንብ ነበር የከበቡት፡፡ ብዙዎቹ እንዲያውም በወረቀት ላይ አያቱን አስፈርሞ እንዲያመጣላቸው፣ ከተቻለም ፎቷቸውን እንዲሰጣቸው ለምነውታል፡፡  

ቤቱ ሲገባ አያቱ የሉም፡፡ ደወለላቸው፡፡ እየመጡ መሆናቸውን ነገሩት፡፡ መክሰስ ለመብላት እንኳን ሆድ አልቀረለትም፡፡ ይህን አስገራሚ ነገር ከአያቱ ጋር ማውራት እጅግ አጓጉቶታል፡፡ እየደጋገመ ‹ፐ› ይላል፡፡ አባቱና እናቱ ራሳቸው ይህንን የሚያውቁ አልመሰለውም፡፡ ይህንን ነገር ያወቀ የመጀመሪያ ሰው እርሱ ብቻ ሊሆን እንደሚችል ገምቷል፡፡ ‹ፐ›፡፡

አያቱ መጡ፡፡

‹‹አያቴ ቴክ ፋይቭ›› አለና በአምስት ጣቱ አምስት ጣታቸውን ገጨ፡፡

‹‹ምን ተገኘ ዛሬ›› አሉ አያትዬው ደንቋቸው፡፡

‹‹እኔኮ አክተር መሆንህን አላውቅም ነበር፡፡ ጓደኞቼ ሁሉ አያቴ አክተር መሆኑን ሲያውቁ ሪስፔክት አደረጉኝ›› አላቸው በሳቅ እየተፍለቀለቀ፡፡ በጣቱ እንደ ሽጉጥ ያለ ነገር ሠርቶ፣ በእግሩ ተንበረከከና በግድግዳው ላይ ‹‹ቷ-ቷ-ቷ-ቷ›› አደረገ፡፡

‹‹የምን አክተር ነው››

‹‹እንዴ የሠራኸውን ፊልምኮ አየነው፡፡ ትምህርት ቤታችን ውስጥ አየነው፤ መሥራትህን ረሳኽው እንዴ››

‹‹የምን ፊልም ነው የሠራሁት››

‹‹አክሽን ፊልም ሠርተኻልኮ፤ ፓ ትልቅ ገን ይዘህ ተርርርርር ስታደርግ ጓደኞቼ አጨበጨቡልህ፤ ስታሩ አንተ ነበርክ እንዴ? ኢነሚዎችህ ሲተኩሱብህኮ ዘለህ ገደል ውስጥ ገባህ፤ ተንከረባበትክኮ፤ ከዚያ ደግሞ ቦንብ በጥርስህ ነቅለህ ወረወርክና ቦዋ ሰጠኸው፤ ከዚያ ታንኩ ሲተኩስብህ በገደሉ ውስጥ ገብተህ አመለጥካቸው፡፡ ልክ ስታመልጥ ጓደኞቼ እያፏጩ አጨበጨቡ፡፡››

አያት ሊገባቸው አልቻለም፡፡ ለልጁ ምን አሳይተውት እንደሆነ ግራ ገባቸው፡፡

‹‹እስኪ ያየህውን ቀስ ብለህ ንገረኝ››

‹‹እይ፣ በትምህርት ቤታችን ‹ሂስትሪ ዊክ› አለ፡፡ ትናንት ፊልም ነበር፡፡ ‹ዘ ፋይተርስ› የሚል የኢትዮጵያ ፊልም አሳዩን፡፡ የድሮ ታሪክ ነው ብለዋል፡፡ እና – እና እዚያ ላይ አየሁህ፤ አሪፍ አክተር ነበርክ ለካ፡፡ ለምን ግን አክተርነት ተውክ? ነጋዴ ከመሆንኮ አክተር መሆን ይበልጣል፡፡ ዳድ ነጋዴ ነው፡፡ ጓደኞቼ ግን አድንቀውት አያውቁም፡፡ አንተ አክተር መሆንህን ሲያዩ ግን ከበቡኝኮ››

አሁን አያትዬው ገባቸው፡፡

‹‹ያየህውኮ እውነተኛ ታሪክ ነው›› አሉት፡፡

‹‹ቤዝድ ኦን ትሩ ስቶሪ – ነው››

‹‹ኖ ኖ ኖ ኖ፣ ያ የኛ የታጋዮች ታሪክ ነው፡፡ አክተር ሆኜ አይደለም፡፡ ከደርግ ጋር ያደረግነውን ውጊያ ፊልም ነው ያሳዩዋችሁ››

‹‹እንደ ደርግ ሆኖ የሠራው አክተር ማን ነበር? ታንክ ምናምን እየነዳ – ቡልቅ አድርጎ ሲተኩስ – ፓ››

‹‹ይህኮ ፊልም አይደለም፤ የተደረገ ታሪክ ነው፡፡

‹‹እንዴ አያቴ፣ አንተ ፋይተር ነበርክ እንዴ?››

‹‹አዎ››

‹‹ገን ምናምን ይዘህ›

‹‹አዎ››

‹‹ኦ- ማይ ጋድ -እና ሰው ገድለሃል?›› ስቅጥጥ አለው ልጁ

አሁን አያት እንዴት እንደሚያስረዱት ግራ ገባቸው፡፡ እርሱ ደግሞ አያቴ አክተር ነበሩ ብሎ ያገኘው ክብር ሲናድበት ታየው፡፡

‹‹አየህ ድሮ ደርግ የሚባል መንግሥት ነበረ›› ብለው ሲጀምሩለት

‹‹ደርግ ምን ማለት ነው? እዚያ ፊልሙ ውስጥም ደርግ ደርግ ይል ነበር፤ እኛኮ የአክተር ስም መስሎን ነበር››

አንገታቸውን ከግራ ወደ ቀኝ እየነቀነቁ ለማስረዳት ቃላት ፍለጋ ገቡ፡፡

‹‹እርሱን ለማስወገድ ጫካ ገብተን ብዙ ዓመት ተዋግተናል››

‹ለምን ታወግዳላችሁ?ፊልሙ ራሱ ያልቅ ለም እንዴ››

‹‹ፊልም አይደለም ብዬህ››

‹‹ቆይ ግን ቢች አካባቢ ብቻ ነበር እንዴ ፋይት የምታደርጉት››

‹‹እንዴት›› አሉ ገርሟቸው

‹‹ቁምጣ ብቻ ነበራ ሁላችሁም ያረጋችሁት››

ሳቁ፣ እስኪበቃቸው ሳቁ፡፡

‹‹ግንኮ እይ›› አለና አንድ መጽሔት ይዞላቸው መጣ፡፡ የፋሽን መጽሔት ነው፡፡ እዚያ ቤት ደንበኛ የሆነ መጽሔት ነው፡፡ ‹‹እይ ፀጉራቸውን እንደ እናንተ አቁመው የሚበትኑትኮ ሴለብሪቲስ ናቸው፡፡ እይ›› ዘፋኞችና የፊልም ተዋንያን እዚያ መጽሔት የፊት ለፊት ሽፋን ላይ ፀጉራቸውን አንጨብረው ተነሥተዋል፡፡ ‹አክተር ካልሆናችሁ ፀጉራችሁን ለምን እንደዚህ አደረጋችሁት?››

‹‹እኛኮ ትግል ላይ ነበርን፤ እንደ እናንተ ንጽሕና ለመጠበቅ፣ ገላ ለመታጠብ፣ ፀጉር ለመቆረጥ ጊዜ አልነበረንም››

‹‹እና ሻወር አትወስዱም ማለት ነው? ሚስ ዝም ትላችኋለች?››

‹‹በኛ ጊዜ ሚስ የለም›› አሉ ለመገላገል፡፡

‹‹እንዴት፣ ሚስ የሌለው ትምህርት ቤት አለ እንዴ? እንደዚያ ዓይነት ትምህርት ቤት በ‹አይስ ኤጅ› ጊዜ ብቻ ነው የሚኖረው››

‹‹እኛ እንደናንተ የመማር ዕድል አላገኘንም፣ትግል ላይ ነበርን››

‹‹ፋይት ብቻ ነበር ሥራችሁ ማለት ነው፤ እኛን ግን ዳድ ፋይት አታድርጉ ይለናል፡፡ እኔና ሳሚኮ ዋተር ገን ይዘን ፋይት ስናደርግ፣ ፋይት ጥሩ አይደለም ይላል፡፡ እናንተን ግን አባታችሁ ዝም ይላችኋል አይደል? ታድላችሁ፤ እስኪ ዳድን አስፈቅድልን››

‹‹ፋይት ማድረግማ ጥሩ አይደለምኮ››

‹‹ታድያ እናንተ ለምን ፋይት አደረጋችሁ››

‹‹እኛኮ ከደርግ ጋር ነው ፋይት ያደረግነው››

‹‹በቃ ወይ እኔ ወይ ሳሚ ደርግ እንሆናለና››

‹‹እይውልህ ጃክየ ወደፊት በደንብ አስረዳሃለሁ፤ አሁን ገና ልጅ ነህ››

‹‹ቆይ ቆይ አያቴ፣ እነዚያኞቹ፣ ኢነሚዎቹ ደርግ ናቸው ብለሃል፣ እናንተ ማንን ሆናችሁ ነው ፊልሙን የሠራችሁት›› ፊልም የሚለው ነገር ከልቡ ሊወጣ ባለመቻሉ እያዘኑ

‹‹የኛ ስም ኢሕአዴግ ይባላል››

‹‹እኛ ግን ሁለቱንም ስሞች አማርኛ ስንማር አልተማርናቸውም፤ ሚስም አታውቃቸውም ማለት ነው›› አለና በሳሎኑ መስኮት ውጭ ውጪውን ማየት ጀመረ፡፡

‹‹ጃክ ምነው አያትህ ፋይተር በመሆኔ ከፋህ እንዴ›› አሉት አያቱ፡፡

‹‹እኔ ግን ፋይተር ከምትሆን አክተር ብትሆን ነበር ደስ የሚለኝ፡፡ ጓደኞቼ ሁሉ አያቴ አክተር ነው ስላቸው ጎል እንዳገባ ተጫዋች ነበር ያቀፉኝ››

‹‹ፋይተር ነበር፣ ፈሪደም ፋይተር ነበር በላቸዋ››

‹‹እና ከዚያ ሰው ገድሏል ወይ? ለምን ገደለ? ማንን ነው የገደለው? ቢሉኝስ፤ እኔንስ ቢፈሩኝስ፣ አያቱ ቁምጣ ለብሶ አየነው ብለው ቢስቁብኝስ፤ የአያቱ ፀጉር ተንጨብሯል ቢሉኝስ፤ በ‹አይስ ኤጅ› ጊዜ የነበረ ነው ቢሉኝስ፣ አልነግራቸውም››

አያቱም በተራቸው በመስኮቱ በኩል ወደ ውጭ ማየት ጀመሩ፡፡ ‹‹ተተኪው ትውልድ ግን እንዲህ ነው የሚረዳን ማለት ነው? የእርሱ ዘመን ጀግኖች ሌሎች ናቸው ማለት ነው? ወታደራዊ ታሪክን ማድነቅ ትቶ መዝናኛዊ ሰብእናን የሚያደንቅ ትውልድ ነው ያፈራነው ማለት ነው? ምናልባት ከኛ በፊት ለነበሩት ሌሎች ታጋዮችና አርበኞች ቦታ ባለመስጠታችን አዙሪቱ እኛም ላይ እየደረሰ ይሆን? ውጊያችንን እንደ ፊልም ነው የሚቆጥሩት ማለት ነው? ›› ማለቂያ የሌላቸውን ጥያቄዎች በመስኮቱ በኩል ይወረውራሉ፤ ጥያቄዎቹ ግን በመስኮት እንደወጡ ነው የቀሩት፤ አልተመለሱም፡፡

 © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

ሁለት ፈረሶች እንደነበሩ ተነገረ፡፡ አንደኛው እጅግ ለምለም በሆነ ሰፊ ሜዳ ላይ ተሠማርቶ፣ ሲያሻው ደግሞ በግራ በቀኝ ገብስ ፈስሶለት፣ ሲጠማው የሚጠጣው ውኃ በሜዳው መካከል ኩልል ብሎ እየወረደለት፣ አውሬ እንዳይተናኮለው ዙሪያውን በውሻ እየተጠበቀ ይኖር ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የሣር ዘር ለአመል ያህል ብቻ እዚህም እዚያም በበቀለበት፣ ጭው ባለ ደረቅ ሜዳ ላይ ተሠማርቶ ያገኛትን እየነጨ፣ ከዕለታት በአንድ ቀን ከደጋ የዘነበ ዝናብ በአካባቢው ሲያልፍ የሚያገኘውን ጥፍጣፊ ውኃ እየተጎነጨ፣ ሌትና ቀን ምን ዓይነት አውሬ መጥቶ ይዘነጥለኝ ይሆን? እያለ በሥጋት ይኖር ነበር፡፡

ምንም እንኳን ሁለቱም ፈረሶች በኑሮ በማይቀራረብ ሜዳ ላይ በመከራና በቅንጦት ተለያይተው ቢኖሩም የኑሮ ጥያቄ ግን አገናኝቷቸው ኖሯል፡፡ ያ እንዲያ በለመለመ መስክ ተሠማርቶ እምብርቱ እስኪነፋ ሆዱ እስኪቆዘር እየበላ ሲተኛ ሲነሣ የሚውለው ፈረስ ‹‹ይኼ ሣር ያለቀ ዕለት፣ ይኼም ውኃ የነጠፈ ጊዜ፣ እነዚህም ውሾች እኔን መጠበቅ ትተው የሄዱ ጊዜ፣ ይኼስ ገብስ የጠፋ ቀን ምን ይውጠኝ ይሆን? ያስ ቀን መቼ ይሆን? ይል ነበር፡፡ ይኼ ጥያቄ ምንጊዜም ይረብሸው ነበር፡፡

ያ በደረቅ ሜዳ ላይ እዚህም እዚያም የበቀለች ሣር እየነጨ ከርሱን ሲደልል የሚውለው ፈረስ ደግሞ ‹‹መቼ ይሆን አልፎልኝ ለምለም መስክ ላይ ውዬ፣ ከፈሰሰ ውኃ እንደ ልቤ ተጎንጭቼ፣ ያለ ሥጋት አድሬ የሚነጋልኝ? ያ ቀን መቼ ይሆን?ይል ነበር፡፡

እዚህ ሀገር ያለን ሰዎች በሁለቱ ፈረሶች ጥያቄ ውስጥ ወድቀናል፡፡ አንደኛው መስኩ ለምልሞለት፣ ውኃው መንጭቶለት፣ ሥጋቱ ጠፍቶለት፣ ሕይወቱ ቀንቶለት የሚኖረው ሰው ጥያቄ ነው፡፡ እንዴት ሜዳው ላይ እንደደረሰ አያውቀውም፤ ብቻ አንድ ቀን ተቀለጣጥፎም፣ ተጣጥፎም፣ ተለጣጥፎም፣ ራሱን ሜዳ ላይ አግኝቶታል፡፡ ለስንትና ስንት ፈረስ የሚበቃውን መስክ ብቻውን ተሠማርቶበታል፡፡ አገር የሚያጠጣውን ወንዝ ብቻውን ይንቦራችበታል፡፡ ጥጋብን ከልኩ በላይ፣ ምቾትንም ከመጠን አልፎ ቀምሶታል፡፡ ድህነትን ረስቶ የት መጣውን ዘንግቶታል፡፡ ግን ሥጋት አልለቀቀውም፡፡

ይኼ መሥመር የተበጠሰ ዕለት፣ ይኼ ሥርዓት ያለፈ ቀን፣ ከእገሌ ጋር የተጣላሁ ጊዜ፣ ቀን የዞረችበኝ ሰዓት፣ የተነቃ ለታ፣ ዕቁቡ የተበላ ጊዜ፣ ካርታው ያለቀ ቀን፣ መንገዱ የታወቀ እንደሆን፣ ሕግ የተቀየረ ቀን፣ ምን ይውጠኝ ይሆን? ያችስ ቀን መቼ ትሆን? እያለ ይጠይቃል፡፡ እየበላ ይሠጋል፣ እየጠጣም ይጨነቃል፤ አይቷል፣ ሰምቷል፡፡ ድንገት ለምለሙ  ሜዳ ላይ ተገኝተው ድንገት ከሜዳው የጠፉ አሉና፡፡

አሁን ሆዱ ተቀይሯል፤ አንገቱ ተቀይሯል፤ እጁ ተቀይሯል፤ መቀመጫው ተቀይሯል፤ ማረፊያና መዋያው ተቀይሯል፡፡ ይህንን ያጣ ዕለት ምን ይውጠዋል?

ያኛውም ፈረስ አለ፡፡ እንደ ዐርባ ቀን ዕድል ሆኖ የደረቀ መስክ ላይ ውሎ እንዲያደር የተፈረደበት፤ ቢሄድ ቢመጣ፣ ቢወርድ ቢወጣ ከዚያ መስክ መላቀቅ ያቃተው፡፡ መቼ ይሆን የእኔስ ሜዳ በሣር ተሞልቶ እንደነዚያ ሣር የምጠግበው እያለ ምኞት የገደለው፡፡ የእኔስ ወንዝ መቼ ይሆን ውኃ ሞልቶት ሳልጨነቅ የምጠጣው? እያለ ሃሳብ ያናወዘው፡፡ የእርሱ ቤት እየፈረሰች ከጎረቤቱ ዘጠኝ ፎቅ ሲበቅል አይቷል፡፡ ስትተከል፣ ውኃ ስትጠጣ፣ አላያትም፡፡ እንዲሁ ብቻ ፎቋ በቀለች፡፡ ስትገዛ ያላያት፣ ፍንጥር ያልጠጣባት መኪና እንዲሁ ሽው እልም ስትል አያት፤ እናም ምን ዓይነት ፈረሶች ይሆኑ ለዚህ የሚበቁት እያለ ይጠይቃል፡፡ ዝርያቸው ምን ቢሆን ነው? መልካቸውስ ምን ቢሆን ነው? የፈረስ ጉልበታቸውስ ምን ያህል ቢሆነ ነው? ፍጥነታቸውና ቅልጥፍናቸውስ እንዴት ያለ ቢሆን ነው? ጌቶቻቸውንስ እንዴት አድርገው ቢያገለግሏቸው ነው? እንዲህ ለምለም መስክ ላይ የለቀቋቸው? እኛም ስናገለግል ኖረናል፤ ጋሪ ስንጎትት፣ እህል ስንሸከም፣ ዕቃ ስናጓጉዝ ኖረናል፤ ጌቶቻችን ሲጋልቡን ኖረናል፤ ግን እነርሱ ምን ያህል ቢያስደስቷቸው ነው ይህንን ዕድል የሰጧቸው? እያለ ይጠይቃል፡፡

ለመሆኑ እነርሱ ናቸው ወደ እኛ የሚመጡት ወይስ እኛ ነን ወደ እነርሱ የምንሄደው? ለመሆኑ የኛን ድህነት ነው ወይስ የእነርሱን ሀብት ነው የምንካፈለው? በርግጥ ከኛም የሄዱ አሉ፤ ከእነርሱም የሚመጡ አሉ? ይላል፡፡ አንዱ ሜዳ ላይ ተሠማርተን እንደ አቅማችንና እንደ ችሎታችን መጋጥ ሲገባን ለምን ሁለት ዓይነት ሜዳ ሆነ፡፡ አሁን እኛና እነርሱ እኩል ‹‹ፈረስ›› ተብለን እንጠራለን? እኛ ‹‹ሌጣ ፈረስ›› ነን፣ እነርሱ ደግሞ ‹‹ባለ ወግ ፈረስ›› ናቸው፡፡

ግን ይሁን፤ እሺ መቼ ይሆን እኛስ እንደነርሱ የምንሆነው? መቼ ይሆን ያለ ሥጋት ውለን የምናድረው? ለምለሙን መስክ ማን ይነካዋል፤ ላለው ነው ድሮም የሚጨመርለት፤ የኛ የድኾቹን መስክ ነው ለሀብታሞቹ የሚሰጡት፤ የድኾቹን ደረቅ መስክ ሀብታሞቹ የሚቀኑበትን ያህል እኛ በእነርሱ ለምለም መስክ አንቀናም፡፡ ደግሞ አንድ ቀን ይመጣሉ፡፡ ‹‹ይህንን መስክ ለምለም ማድረግ እንፈልጋለን›› ይላሉ፡፡ እኛም ደስ ይለናል፡፡ የዘመናት ምኞታችን አይደል? መንገዱ ጠፍቶን እንጂ እኛም ለምለም ማድረግ እንፈልግ ነበርኮ? መንገዱን ያወቀው ሰው ሲመጣ ለምን እንቃወመዋለን፡፡

ግን ይቀጥሉና ሌላ ነገር ይሉናል፡፡ ‹‹መስኩን ግን ለምለም የምናደርገው ለእኛ እንጂ ለእናንተ አይደለም›› ይሉናል፡፡ ለምን? ለምን? እኛ ለምለም ሣር አይወድልንም? እኛ ለምለም የምናደርግበትን መንገድ ለምን አያሳዩንም? ባያሳዩንስ ለምን አይፈቅዱልንም? ባይፈቅዱልንስ ለምን አይተውንም? እንላለን፡፡ ይህ ግን ጥያቄ ነው እንጂ መልስ የለውም፡፡ እኛም ጥያቄውን የምናውቀውን ያህል መልሱን አናውቀውም፡፡ ስንጠይቅም ‹‹ምላሽ›› እንጂ ‹‹መልስ›› የሚሰጥ አናገኝም፡፡

እኛም ከዚያ መስክ እንወጣለን፣ ወደሌላ መስክም እንዛወራለን፤ አሁንም ቅንጥብጣቢ ሣር እንፈልጋለን፤ ጥፍጣፊ ውኃ እናስሳለን፡፡ ያ እኛ የነበርንበት መስክ ግን በአንድ ጊዜ ይለመልማል፡፡ ውኅው ጅረት ሆኖ ይፈስበታል፡፡ ይገርመናል፡፡ እኛ እዚያ ሳለን፡፡ ውኃ አልነበረም፡፡ እንደ ወር በዓል ቀን ቆጥረን ነበር የምናገኘው፡፡ አሁን ግን ይንፎለፎላል? ለመሆኑ እኛ ምን ብለን መጠየቅ ነበረብን? ይኼ ራሱ ሌላ ጥያቄ ይሆንብናል፡፡ መቼ ይሆን እኛስ እንዲህ ባለው መስክ ላይ የምንሠማረው? እንላለን፡፡ የማይሳካ ምኞት እንመኛለን፤ የማይመለስ ጥያቄ እንጠይቃለን፡፡

እዚያም ቤት ሌላ ጥያቄ አለ፡፡ ፀሐይዋ እንደወጣች ትቀጥል ይሆን? ወንዙ እንደፈሰሰ ይቀጥል ይሆን? ነፋሱ እንደነፈሰ ይቀጥል ይሆን? ሣሩ እንደለመለመ ይዘልቅ ይሆን? እኔስ እንደተወደድኩና ሞገስ እንዳገኘሁ እኖር ይሆን?

ሰውየው ስለ አውሮፕላን አነዳድ የሚገልጥ ማኑዋል አገኘና አውሮፕላኑን አስነሥቶ አበረረ፡፡ ገጹን ይገልጣል፤ የተጻፈውን ይፈጽማል፤ አውሮፕላኑም ይበራል፡፡ በቀጣዩ ገጽ ላይ ምን እንዳለ የሚያውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ገጹ ተገንጥሎ ቢገኝ ምን ማድረግ እንዳለበትም የሚያውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ብቻ ይገልጣል፣ ያነባል፣ ይነካካል፣ ይበራል፡፡ አውሮፕላኑ ተነሥቶ በሃያ አምስት ሺ ጫማ ከፍታ ላይ ሲደርስ የመጨረሻው ገጽ ላይ ደረሰ፡፡ ‹‹ክፍል ሁለትን በክፍል ሁለት መጽሐፍ ይመልከቱ›› ይላል፡፡ ክፍል ሁለት መጽሐፍ ግን የለውም፤ የት እንዳለም አያውቅም፡፡ ምን ማድረግ እንዳለበትም አልተዘጋጀም፡፡ ስለዚህም እንደወጣ መውረድ ጀመረ፡፡ ያውም በዝግታ ሳይሆን እየተምዘገዘገ፡፡

እናም እኛ በለምለም መስክ ላይ ያለን ፈረሶች፣ አንድ ክፉ ቀን መጥቶ ‹‹ክፍል ሁለትን በሌላ መጽሐፍ›› ቢለንስ? ምን ይውጠናል? ለመሆኑ ክፍል ሁለት የት ነው ያለው? እስካሁን ያሳየን የለም፡፡ እኛ የምናውቀው የየዕለቱን ምዕራፍ ብቻ ነው፡፡ ያንን እናነባለን፣ በእርሱ እንኖራለን፣ ቀጣዩን ምዕራፍ አናውቀውም? ስለዚህም እኛም እንጠይቃለን? እንዲሁ እንዘልቅ ይሆን? ብለን፡፡

© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በእንግዶች ተጨናንቋል፡፡ በአዲስ አበባ ለሚዘጋጀው ዓለም አቀፍ ጉባኤ የሚመጡ እንግዶች አሁንም አሁንም የፍተሻውን መሥመር እያለፉ ሌሎች አገልግሎቶችን ለማግኘት ይሰለፋሉ፡፡ ብዙዎቹ የሞባይል ስልክ ለማግኘት የተሰለፉ ናቸው፡፡ የቪዛ አገልግሎት ለማግኘት እንኳን ያንን ያህል አልተሰለፉም፡፡ አንዳንዶቹ ያማርራሉ፣ አንዳንዶቹም ያመራሉ፡፡

ሰልፉ እየተቃለለ መጥቶ ሁሉም እንግዶች ወደየማረፊያቸው ተጓዙ፤ ጉባኤው የሚጀመረው ነገ ነው፡፡

በማግሥቱ የሀገሩም የውጭውም ሰው በአዳራሹ ከተተ፡፡ መርሐ ግብሩ እስኪጀመር ድረስ ንዴትና ብስጭት፣ ቁጣና ርግማን የተቀላቀለባቸው ንግግሮች ከእንግዶቹ እዚህም እዚያም ይሠነዘሩ ጀመር፡፡ ‹‹እንዴት ለሀገራቸው ሰው ብቻ የሚሠራ ስልክ ይሰጣሉ፤ ነውር አይደለም እንዴ›› ይላሉ እዚህም እዚያም፡፡ አንዳንዱ ስልኩን መሬት ላይ ቢፈጠፍጠው ንዴቱ የሚበርድለት ይመስል አሥር ጊዜ ይሠነዝረዋል፡፡ ወዲያው አንድ አካባቢ ሰዎቹ ከበው ቆሙ፤ ቀጥሎም ቁጣ ቀላቅሎ የሚዘንብ የውግዘት ዝናብ አወረዱ፡፡

ለካስ ከጉባኤው አስተናጋጆች መካከል አንዱን አግኝተውት ነው፡፡ ‹‹እንዴት ከስልክ ዐቅም የሀገር ሰውና የውጭ ትለያላችሁ፤ ሌላ ሀገርኮ ስልክ በሳንቲም ከሱቅ የሚሸመት ነው፤ የኛ ሳይሠራ እንዴት የናንተ ብቻ ተለይቶ ሠራ›› ባለሥልጣን እንዳጀበ መኪና ጥያቄው ተከታትሎ ወረደ፡፡ ‹‹ተአምኁ በበይናቲክሙ›› እንደተባለ አስቀዳሽ አንገቱን በአራቱም አቅጣጫ አዞረ፡፡ የቴሌውን ሰው ከሩቁ አየው፡፡ ክበቡን ጥሶ መሄድ ስለከበደው ሞባይሉን አወጣና በማዶ ለሚያየው የቴሌ ሹም ደወለ፡፡ ‹‹የደወሉላቸው ደንበኛ ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጭ ናቸው›› ስትለው ደንግጦ ዘጋው፡፡ እንግዶቹ በእንግሊዝኛ የምትለውን ቢሰሙ ጭራሽ ያብዳሉ ብሎ ፈራ፡፡ ‹‹ይኼ ታላቅ ስብሰባ የሚደረግበት አዳራሽ ራሱ ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጭ ነው ማለት ነው›› አለና አፈረ፡፡ ታድያ የቱ ነው ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውስጥ የሆነው? ለመሆኑ ይኼ ቴሌ የመሠረታቸው ‹የአገልግሎት ክልል› እና ‹ከአገልግሎት መስጫ ውጭ የሆነ ክልል› በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ያገኙ ክልሎች ናቸው?ቴሌስ የራሱን ክልል መመሥረት ይችላል እንዴ? ስንት ባልና ሚስት ‹የት ሄደህ ነበር፣ የት ሄደሽ ነበር› እየተባባለ የተጣላው ያቺ የቴሌ ሴትዮ ‹‹ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጭ ናቸው›› እያለች የሌለ ነገር አውርታ አይደል እንዴ?

አስተናጋጁ ይቅርታ ጠየቀና የቴሌውን ሹም ሊጣራ ሄደ፡፡ ‹‹እርሱ የቴሌ ባለሞያ ነው፤ ጠይቁት›› ብሎ ሹልክ ብሎ  ከክበቡ ወጣ፡፡ ወደ መድረኩ ሲያቀና ‹‹እንኳን እኔ አለቆቹ የማያውቁትን ጥያቄ ያዘንቡብኛል እንዴ›› ወደ መድረኩ ሲወጣ የቴሌውን ሹም የከበቡት እንግዶች የላምበረትን አውቶቡስ ተራ ጠሪዎች የመሰለ መዓት ድምጽ ሲያወርዱበት ሰማ፡፡ ‹‹ቻለው እንግዲህ፤ ኔት ወርኩ ያልቻለውን እናንተ ቻሉት›› አለ በልቡ፡፡

‹‹እንዴት ትናንትና የገዛነው ስልክ እስከ ዛሬ አይሠራም፤ የተሳሳተ ሲም ካርድ ነው የሰጣችሁን፤ አታላችሁናል፤ ገንዘባችንን መልሱ›› እንደ ሲሚንቶ አቡኪ ከየማዕዘኑ እንደ አሸዋ የበዛ ጥያቄ ጣሉበት፡፡ ፈገግ ለማለት ሞከረ፡፡ ፈረንጅ ፈገግታ ይወዳል የሚባለው ትዝ ብሎት፡፡ ‹‹ችግራችሁ ይገባኛል፡፡ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ አገልግሎቱን እንድታገኙ እናደርጋለን፤ ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ እንጠይቃለን›› ሲል አሁኑኑ መፍትሔ አምጣ የሚል ወጣሪ ገጠመው፡፡ የሚያደርገውን ሲያጣ ስልኩን አወጣና ‹‹አንዴ ኃላፊውን ላናግረው›› አለና ደወለ፡፡ ‹‹የደወሉት ቁጥር የተሳሳተ ነው›› ስትለው እንግዶቹ እንግሊዝኛውን እንዳይሰሙ ሰግቶ እዘጋለሁ ሲል ጭራሽ ድምጽ ማጉያውን ከፈተውና አሰማቸው፡፡ ሰሚዎቹ ጎል እንደገባበት ስታዲዮም አንድ ላይ ጮኹ፡፡

እያመመው ፈገግ አለና ‹‹ሶሪ›› ብሎ ቀና ሲል የስብሰባው መጀመር ገላገለው፡፡ እንግዶቹ ወደመቀመጫቸው ሲያመሩ እርሱም አንገቱን ደፍቶ ወደ ቢሮው ገባ፡፡ ‹‹ምን ዓይነት መከራ ነው፡፡ ባለፈው ጊዜ ከስድስት መቶ ቦታዎች ስድሳውን ሠርተን ጨርሰናል ተብሎ ተነገረ፤ ሰውም ‹ጤፍ እየዘራን ነውና ራብህን ቻለው ማለት ነው› ብሎ ተረተብን፡፡ አሁን ደግሞ ምን ሊባል ነው፡፡ ያ የመሥመር ስልክ ይሻለን ነበር፡፡ በሞባይል የተላከ ቴክስትና በፖስታ የተላከ መልእክት እኩል እየደረሱ ቴሌ ምን ያደርጋል?

ስልኩን አነሣና ወደ ዋናው ቢሮ ደወለ፡፡

‹‹ኧረ ሰው ሊበላን ነው አንድ ነገር ይደረግ›› አለ በማዶ ላለው ሰውዬ፡፡

‹‹ገና ምኑን አይተህ ከዘጠና ሺ በላይ የሆኑ ደንበኞች ያወጡት ሲም ካርድ ሊሠራላቸው አልቻለም፡፡ ሲስተሙ ተበላሽቷል››

‹‹ታድያ መፍትሔው ምንድን ነው?››

‹‹እኛም አለቆቻችንን ስንጠይቅ ‹በቃ ታገሡ በሏቸው› ነው ያሉን››

‹‹እነዚህኮ ነገ ተሰብስበው ወደ ሀገራቸው ይሄዳሉ››

‹‹አገራቸው ከገቡ በኋላ በአድራሻቸው እንልክላቸዋለን›› ሣቀ፡፡

‹‹ታድያ ለምን ሸጥንላቸው››

‹‹እና ኢትዮጵያ የሞባይል ሲም አትሸጥም ይባል? ይኼማ ለገጽታችን ጥሩ አይደለም››

‹‹የኢትዮጵያ ሞባይል አይሠራም መባሉስ ገጽታ ይገነባል?››

ስልኩ ተዘጋ፡፡

የጉባኤው የመጀመሪያ ክፍል አብቅቶ እንግዶቹ የሻሂ ግብዣ ላይ ናቸው፡፡ መድረክ አካባቢ የነበሩት ባለ ሥልጣናትም ወደ እንግዶቹ መጥተው አብረው ሻሂ መጠጣት ጀመሩ፡፡ ሁለት ባለ ሥልጣናት ክብ ሠርተው ወደሚገኙ እንግዶች መጡና ተቀላቀሉ፡፡ ሁለቱም ራሳቸውን አስተዋወቁ፡፡ አንደኛው የቴሌ ዋናው ሰው ነበሩ፡፡ ‹የሰው ሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል› እንዲል መጽሐፍ ሁሉም ዓይናቸውን በእርሳቸው ላይ ተከሉ፡፡ ሁሉም ቅሬታውን አዘነበ፡፡ ባለ ሥልጣኑም ራሳቸውን እየነቀነቁ ሰሙና ስልካቸውን አወጡ፡፡ ደወሉ፡፡

‹‹ቴሌፎኑ ለጊዜው ጥሪ አይቀበልም፣ ወይም ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጭ ነው›› ሲል ሰሙት፡፡ እንደገና ወደ ሥራ አስኪያጁ ሞከሩ ‹‹የደወሉት ቁጥር አገልግሎት ላይ ያልዋለ ነው፡፡›› የቴሌው ሥራ አስኪያጅ ቁጥር እንዴት አገልግሎት ላይ አልዋለም፤ እነዚህ ሰዎች ጠንቋይ ይመስል ለረሳቸው አያውቁም እንዴ›› ብለው ፈገግ አሉና ለመጨረሻ ጊዜ ሌላ ኃላፊ ጋ ደወሉ ‹‹ይህንን ጥሪ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ሂሳብ የለዎትም›› ስትል ደነገጡና ‹‹ዋት፣ ይኼኮ ካርድ የሚሞላበት ስልክ አይደለም፤ ምን ማለቷ ነው›› የከበቧቸው ሰዎች የሚሉት ነገር አልገባቸውም፡፡

‹‹የሚመለከታቸውን ላናግር ነበር፤ የኔም ስልክ ግን እንደናንተው አይሠራም፤ ከመታገሥ በቀር ሌላ አማራጭ የለንም›› አሉ፡፡

‹‹እስከ መቼ ነው ግን የምንታገሠው? ስብሰባውኮ ነገ ያልቃል››

‹‹ልክ ናችሁ ብዙ ስብሰባዎችም እንዲሁ በትዕግሥታችን ነው ያጠናነቅናቸው››

‹‹ታግሠን ግን ምን ይገኛል››

‹‹ስብሰባው ያልቅና አገራችሁ ትገባላችሁ፤ ያን ጊዜ ሲም ካርድ ለምን አልሠራም? ማለት ታቆማላችሁ፤ ጥያቄውን መመለስ ካልተቻለ ሌላው አማራጭ ጥያቄውን እንዳይጠየቅ ማድረግ ነው››

ምሽት ላይ ስብሰባው ሲያልቅ መሬቱን የሞላው የተወረወረ ሲም ካርድ ነው፡፡ ለጽዳት ሠራተኞች ግን ሠርግና ምላሽ ሆኖላቸዋል፡፡

© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው


ሁለተኛው የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት ሲከናወን ከተፈጸሙት ነገሮች አንዱ የተሸላሚዎችን ታሪክ የያዝ መጽሔት መታተሙ ነው፡፡ መጽሔቱን በፒዲኤፍ ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡፡ የመጽሔቱን ጠንካራ ቅጅ የምትፈልጉ ካላችሁ ለም ሆቴል ማትያስ ሕንጻ በሚገኘው የአግስዮ መጻሕፍት መደብር በነጻ ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ በተለይም አብያተ መጻሕፍት፣ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶችና የወጣት ማኅበራት መጽሔቱን እንዲወስዱ ይበረታታሉ፡፡

የመጽሔቱ ሽፋን(cover page)
የመጽሔቱ ይዘት(bego sew bulletin pdf)

ከ120 ተጠቋሚ ኢትዮጵያውያን መካከል በበጎ ሰው ዳኞች የተመረጡት ሰባት ኢትዮጵያውያን ‹በጎ ሰዎች› ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2006 ዓም በኢሊሊ ሆቴል በተከናወነ ሥነ ሥርዓት ተሸለሙ፡፡


የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ከየትምህርት ቤቱ የተጋበዙ ወጣቶችና ሌሎችም በተገኙበት በተከናወነው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ በግብርና፣ ኢንዱስትሪና ኢንተርፕርነርሺፕ ዘርፍ ወ/ሮ ቤተ ልሔም ጥላሁን፣ በማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፍ ብጹዕ አቡነ ዮናስ፣ በርዳታና ሰብአዊ ሥራ ዘርፍ ዶክተር በላይ አበጋዝ፣ መንግሥታዊ  የሥራ ኃላፊነትን በመወጣት ዘርፍ አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ፣ በጥናትና ምርምር ዘርፍ አምባሳደር ዘውዴ ረታ፣ በቅርስ፣ ባሕልና ቱሪዝም ዘርፍ አብዱላሂ ሸሪፍ፣ በኪነ ጥበብ ዘርፍ ደግሞ አባባ ተስፋዬ ሣሕሉ ተሸልመዋል፡፡

ሽልማቶቹን የተለያዩ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን የሸለሙ ሲሆን ከተሸላሚዎቹ መካከል አምባሳደር ዘውዴ፣ አምባሳደር ቆንጂትና  ወ/ሮ ቤተ ልሔም ጥላሁን ለሥራ ከሀገር ውጭ በመሆናቸው በተወካዮቻቸው በኩል ተቀብለዋል፡፡


ለሀገር በጎ ሥራ መሥራትንና ያለውንም በጎ ተጽዕኖ በተመለከተ ዶክተር እሌኒ(የ2005 የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ) እና ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋየ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ገጣሚ አበባው መላኩና ገጣሚ ምንተስኖት ደግሞ ግጥሞችን አቅርበዋል፡፡

የመዝጊያ ንግግሩን ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መሥራችና የ2006 የበጎ ሰው ሽልማት ዕጩ አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም የአምባሳደር ልብስ ስፌት ባለቤት አቶ ሰይድ ለአባባ ተስፋየ አሥር ሺ ብርና ሙሉ ልብስ ሲሸልሙ የሊንከን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ለሜሪ ጆይ አሥር ሺ ብር ለግሰዋል፡፡


ዳሽን ቢራ መርሐ ግብሩን በክብር ስፖንሰር አድርጓል


ሸገር ሬዲዮ፣ ኢቢኤስ ቴሌቭዥን፣ ኢሊሊ ሆቴል፣ ምርፋቅ ካፌና ሬስቶራንት አጋሮቻችን ሆነው ለሰጡን አገልግሎት እናመሰግናለን

ይሄ ልጅ ለምን እዚህ እንደመጣ ግልጽ አልሆነላቸውም፡፡ ከሃያ ዓመት በኋላ ነው እንዲህ ቤት ውሎ ቤት ሲያድር ያዩት፡፡ ሥራ አለው፣ በትምህርት ተወጥሯል፤ ንግዱን እያጧጧፈ ነው ሲባል ነበር የሚሰሙት፡፡ በቤቱ ውስጥ የተሻለ የተማረ ሰው እርሱ በመሆኑ ሠርግና ልቅሶ ለምን አልመጣህም ብሎ የሚወቅሰው ቤተ ዘመድ አልነበረም፡፡ አንዳንዶቹም ስሙን ሰምተው እንዲሁ ያደንቁታል እንጂ አይተውት አያውቁም፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ድሮ በልጅነቱ እንዳዩት ናቸው፡፡

አሁን ግን ነገር ዓለሙን ሁሉ ትቶ እዚህ አያቱ ቤት መዋል ማደር ከጀመረ ሰነባበተ፡፡ አያቱ ደግሞ ይሳቀቃል ብለው ለምን መጣህ? ሥራና ትምህርትህንስ የት ተውከው? ብለው መጠየቅ ከብዷቸዋል፡፡ እጅግ በጣም የገረማቸው ደግሞ መቀመጫው ላይ ወስፌ እንደተተከለበት ሁሉ ለአፍታ ቁጭ ማለት የማይችለው ሰውዬ ደርሶ ቀኑን ሙሉ ቤት ውስጥ ተቀምጦ ሲቆዝም መዋሉ ነው፡፡

አንድ ቀን ግን ደፍረው መጠየቅ እንዳለባቸው ወሰኑና ወደ እልፍኛቸው አስጠሩት፡፡ ‹‹ልጄ በደኅህ ነው? እንደዚያ ለምግብ እንኳን ጊዜ የለኝም የምትለው ሰውዬ ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብለህ የምትውለው›› አሉና ጠየቁት፡፡ አንገቱን ደፍቶ መሬቱን በመነጽሩ ጫፍ እየጫረ ዝም አላቸው፡፡ ‹‹የሆንከው ነገር አለ? ምናልባትኮ ለእኔ ቀላል ይሆናል፡፡ መቼም የዛሬ ልጆች ትንሹን ነገር ሁሉ አክብዳችሁ ነው የምታዩት፡፡ ሰውዬው እህል ሊሸከም ተጠርቶ ዋጋ ሲነጋገር ‹ለመሆኑ ሸክሙ ከባድ ነው ቀላል?› ብሎ ቢጠይቅ አሸካሚው ሰው ‹እንደ ተሸካሚው ነው› ብሎ መለሰለት አሉ፡፡ነገር እንዳያያዝህ ነው››

‹‹አያቴ ለአንተ ምንም አያደርግልህም፤ ምናልባትም ደግሞ አያስደስትህም›› አላቸው ጭኑን በመዳፉ እየመታ፡፡

‹‹ሲያደርጉት ነበር እንጂ ይህንን ማሰብ፤ ከሆነ ወዲያ መናገር ምን ያከብዳል››

‹‹ከወንድሜ ጋር ተጣላን› አላቸው ቀለል አድርጎ››

‹‹እና ወንድምና ወንድም መጣላቱ አዲስ ነገር ነው እንዴ››

‹‹ጠቡ ከበድ ያለ ነው››

‹‹ማቃለሉን ትታችሁ ማካበዱን እንዴት ቻላችሁበት››

‹‹መጀመሪያም የከበደ ነበር››

‹‹እንዴት እንዴት ሆኖ››

‹‹አንተኮ ሁሉን ታውቀዋለህ አያቴ፤ ዝም ብለህ ነው የምታስለፈልፈኝ››

‹‹ዕውቀት ብዙ ዓይነት ነው ልጄ፡፡ አሟልተህ የማታውቀው አለ፤ አዛብተህ የምታውቀው አለ፤ ጨርሰህ የማታውቀው አለ፤ የምታውቀውም ነገር አለ፡፡ ለመሆኑ ምንድን ነው ያጣላችሁ?››

‹‹እስከ ዛሬ ማንነቱን አላውቀውም ነበር፤ በእኔ ላይ ሲጫወት የኖረ መሆኑን አላውቅም ነበር፤ ሲጨቁነኝና ሲበድለኝ የኖረ፣ እንዲህ ሆኜ እንድቀር ያደረገኝ መሆኑን ዛሬ ዐወቅኩት›› አላቸው እያንገፈገፈው፡፡

‹‹ሌላስ ያወቅከው ነገር የለህም›› አሉት ጋቢያቸውን ከራሳቸው ወደ ትከሻቸው ወረድ እያደረጉ፡፡

‹‹ታላቅ ነኝ ብሎ ስንት ስቃይ ሲያደርስብኝ ነው የኖረው፡፡ ይደበድበኝ ነበር፤ ይቀማኝ ነበር፣ ይንቀኝ ነበር፣ ጉልበቴን ይበዘብዝ ነበር፤ ምርጥ ምርጡን ለራሱ ብቻ ይወስድ ነበር፤ ስሜን እንኳን በትክክል አይጠራኝም ነበር፤ ለራሱ በሚስማማው የማሾፊያ ስም ነበር የሚጠራኝ ፡፡››

‹‹ይህ ሁሉ ሲሆን ለመሆኑ አንተ ነበርክ››

‹‹የተወሰነው ደርሼበታለሁ፣ ሌላውን አንብቤያለሁ፣ ሌላውን ደግሞ ከሰው ሰምቻለሁ››

‹‹መልካም ይህንን ብቻ ነው የነገሩህ ሌላ ነገር አልነገሩህም፤ ላንተ ያደረገልህን ነገርስ አልነገሩህም፤ አንተ በእርሱ ላይ ያደረግክበትን ነገርስ አልነገሩህም?››

ዝም አለ፡፡

‹‹አየህ የምንሰማውና የምንናገረው የምንፈልገውን ብቻ ከሆነ ችግር ነው፡፡ ወይ ጨርሰን አለመስማት አለማየት ነው፡፡ እንሰማለን እናያለን ካልን ደግሞ ሁሉንም ማየትና መስማት ነው፡፡ የዛሬ ልጆች ችግራችሁ መርጣችሁ ነው የምታዩትና የምትሰሙት፡፡ በከፊል ሰምታችሁ በሙሉ ትፈርዳላችሁ፣ በጥቂት ዐውቃችሁ በብዛት ትደመድማላችሁ፤ መርጣችሁ ሰምታችሁ ሳትመርጡ ታወግዛላችሁ፡፡ ስማ ልንገርህ፤ አንተምኮ ብዙ ነገር አድርገህዋል፡፡ በድንጋይ መተህዋል፤ ደብተሩንና መጽሐፉን ቀዳደህበታል፤ የሚያጠናበትን ክፍል በድንጋይ እየደበደብክ ከሠፈሩ እንዲለቅ አድርገህዋል፡፡ ስንት የለፋበትንና የደከመበትን የሥዕልና የቅርጻ ቅርጽ ሥራውን ድምጥማጡን አጥፍተህበታል፡፡ ይህንንስ አልነገሩህም፡፡ አንተ ምንም ሳታጠፋ ከመላእክት ጋር ነው የኖርከው አሉህ? አንተ ተመታህ እንጂ አልተማታህም፤ ተሰደብክ እንጂ አልተሳደብክም አሉህ?እርሱስ ላንተ ያደረገልህ ነገር የለም? አላስተማረህም? የእናት የአባታችሁን ርስት ለመጠበቅ ደም አልከፈለም? አንተን የሠፈር ጎረምሶች በተተናኮሉህ ቁጥር የግንባር ሥጋ ሆኖ አልመከተልህም? በክፉው ቀን አዝሎህ ለስንት ቀን የተጓዘበትን፣ በረሃብ ቀን አንተን አስቀድሞ ያበላበትን፣ ይህንን አልነገሩህም፣ አልጻፉልህም?››

ዓይኑን ከግራ ቀኝ እያንከባለለ ያያቸው ጀመር፡፡

‹‹ሴትዮዋ ጆሮዬ ታሟል አልሰማም ብለው ከዘመድ ተጠግተው ይኖሩ ነበር አሉ፡፡ አንድ ቀን ታድያ ዘመዶቻቸው ቡና እየጠጡ ያሟቸዋል፡፡ አልሰማም ብለዋልና ምንም ነገሩ ቢያበግናቸው ዝም አሉ፡፡ ሐሜቱ እየቀጠለ ሲሄድ ግን አልቻሉምና ‹‹ምነው እናንተ፣ ሳልሞት በቁሜ ታወራርዱኛላችሁ›› ብለው ተናገሯቸው፡፡ ሰዎቹም ደንግጠው ‹እማማ አልሰማም አላሉም እንዴ?› አሉና ጠየቋቸው፡፡ ሴትዮዋም ‹ክፉ ክፉውንማ እሰማለሁ› አሉ ይባላል፡፡ እናንተም ክፉ ክፉውን ብቻ ነው እንዴ የምትሰሙት፡፡ ዝንጀሮ የራሷ ጠባሳ አይታያትም እንደሚባለው እናንተስ የሠራችሁት ስሕተት የለም?

‹‹ልጄ የተነገረህን ተወው አልልህም፤ እንዴ ሰምተህዋልና፡፡ ነገር ግን ያልተነገረህን ፈልግ፡፡ ያልተነገረህ ብዙ ነገር አለ፡፡ ስለወንድምህ ያልሰማህው ብዙ ነገር አለ፡፡ ደግነቱንና መልካምነቱን የነገረህ የለም፤ ጥፋቱንና ድክመቱን ግንቅመም እየጨመሩ በደንብ አስጨብጠውሃል፡፡ ጎዱህ እንጂ አልጠቀሙህም፡፡ እኛ ድሮ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ሂሳብ ስንሠራ ‹ተንጠልጣይ ሂሳብ› የሚባል ነገር ነበር፡፡ ሳይወራረድ፣ ሳይዘጋ እንዲሁ ከዓመት ዓመት ሲንከባለል የሚኖር ሂሳብ ነው፡፡ የእርሱ መዝጊያ ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ውሳኔ ነው፡፡ በውሳኔ ይዘጋል፡፡ ያለበለዚያማ የርሱ አለመወራረድ አንሶ የቀጣዩን ዓመት ሂሳብም ይበጠብጠዋል፡፡ ያልተዘጋ ቁርሾም እንዲህ ነው፡፡ አልዘጋ ካለ ወስኖ መዝጋት ነው፡፡ ከዚያ ወደፊት መሄድ ነው፡፡ ወደማትቆጣጠረው ትናንት ሄዶ መከራ ከማየት ወደምትቆጣጠረው ነገ መሄድ ይሻልሃል፡፡

‹‹እኔ ልምከርህ፤ የሰማኸውን ብቻ ሰምተህ አትፍረድ፤ ያልሰማኸውን ደግሞ ፈልግ፡፡ አንዳንዴም ከሰማኽው ያልሰማኸው ይበልጣል፡፡ የለም ብለህ አትደምድም፤ ቢኖር ትደነግጣለህ፤ አለ ብለህ ባይኖር ግን ምንም አትሆንም፡፡

‹‹ልገድለው እያሰብኩ ነበር፡፡ መንገድ እየፈለግኩ ነበር፤ ከራሴ ጋር እየተሟገትኩ ነበር፡፡ አተረፍከኝ፡፡ እስኪ እውነትም ያልሰማሁት ነገር ካለ ልፈልገው፡፡ አሁን እንኳን አንተ ብዙ ያልሰማሁትን ነገር ነገርከኝ፡፡ ለካስ ያወቅኩ መስሎኝ ባላወቅኩት ነው ልፈርድ የነበረው››

ያን ምሽት እዚያ ቤት አላደረም፡፡

© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው፡፡

የ2006 ዓም ‹‹የዓመቱ በጎ ሰው›› ሽልማት በሰባት ዘርፎች የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች ታውቀዋል፡፡ በልዩ ልዩ ዘርፎች ዕውቀትና ተሞክሮ ያላቸው፣ በሞያው ለረዥም ዘመን ያገለገሉ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ደራስያን፣ የዜማ ሰዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ የባሕል ባለሞያዎች፣ የሚገኙበት 21 ዳኞች የመጨረሻዎቹን ሰባት ተሸላሚዎች ለመለየት ድምፅ እየሰጡ ነው፡፡ ዳኞቹ እርስ በርሳቸው የማይተዋወቁ ሲሆን በዘርፋቸው የራሳቸውን ድምፅ ብቻ ይሰጣሉ፡፡ የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች የሚታወቁት በሚቀጥለው ሳምንት ውስጥ ነው፡፡
የሽልማቱ ዲዛይን የታዋቂው ሰዓሊ የእሸቱ ጥሩነህ ነው፡፡ ‹‹ጀ›› ፊደል ኢትዮጵያዊ ፊደል በመሆኑ ኢትዮጵያዊነትን የሚወክል ሲሆን ‹በ› ና ‹ሰ› የሚሉ ፊደላት ተቀጣጥለውበታል፡፡ ይህም የበጎ ሰው ሽልማትን የሚገልጥ ነው፡፡ ከላይ ደግሞ የ‹ሽ› ምልክት አለው፡፡ ይህም ሽልማትነቱን ያሳያል፡፡ ከላይ ያለው የፊደሉ ቅጥያ የቁልፍ መክፈቻ ምልክት ያለው ይኼም የተሸላሚዎቹን ቁልፍ ማኅበረሰባዊ ሚና ያመለክታል፡፡ ከፊደሉ ሥር የሚገኘው ደረጃ ደግሞ ተሸላሚዎቹ ደረጃ በደረጃ የደረሱበትን የሰብእና  ልዕልና ያሳያል፡፡

ዕጩዎች በየዘርፉ

ኪነጥበብ ዘርፍ

  1. ሙላቱ አስታጥቄ

  2. ተስፋየ አበበ

  3. አባባ ተስፋየ ሳሕሉ

  4. ይልማ ሀብተየስ

  5. ታደሰ መስፍን

 ማኅበራዊ አገልግሎት
 1.         ዶ/ር አበበ በጂጋ
2.       ዶ/ር ሚናስ ኅሩይ

3.       ቄስ አሰፋ ሰጠኝ(ትግራይ)

4.       ብጹዕ አቡነ ዮናስ(አፋር)

5.       ደበበ ኃይለ ገብርኤል

ርዳታና ሰብአዊ ሥራ

  1. ዶ/ር ተዋበች ቢሻው

  2. ዶ/ር በላይ አበጋዝ

  3. ወ/ት ሮማን መስፍን

  4. ሲ/ር ዘቢደር ዘውዴ

  5. ወ/ሮ አበበች ጎበና

ግብርና፣ ኢንዱስትሪና ኢንተርፕርነርሺፕ

  1. ቤተልሔም ጥላሁን

  2. ዶ/ር ኢንጅነር ዳንኤል ቅጣው

  3. ዶ/ር ወሮታው በዛብህ

  4. አሶሴሽን ኦፍ ዉሜን ኢን ቢዝነስ

  5. ካፒቴን ሰሎሞን ግዛው

መንግሥታዊ ኃላፊነትን መወጣት

1.         አምባሳደር ቆንጅት ሥነ ጊዮርጊስ

2.       ኢንጅነር ስመኘው በቀለ

3.       አቶ በድሉ አሰፋ

4.       አቶ ይርጋ ታደሰ

5.       አቶ አድማሱ ታደሰ

ቅርስ፣ ባሕልና ቱሪዝም

  1. አቶ ዓለሙ አጋ

  2. አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ

  3. ሼህ አብዱላሂ ሸሪፍ

  4. ዶ/ር ዘረ ሠናይ ዓለም ሰገድ

  5. የኢትዮጵያ ቅርስ ባለ አደራ ማኅበር

ጥናትና ምርምር

1.         አምባሳደር ዘውዴ ረታ

2.       ፕ/ር አሥራት ኃይሉ

3.       ፕ/ር ዓለም ፀሐይ መኮነን

                                            መርሐ ግብሩን ዳሽን ቢራ በዋናነት ስፖንሰር አድርጎታል

ኢሊሊ ሆቴል አዳራሹን በመስጠትና ለሌሎችም ተግባራት በመተባበር፣ ሸገር ሬዲዮና ኢቢኤስ ቴሌቭዥን የሚዲያ አጋር በመሆን፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች ማስታወቂያዎችንና መረጃዎችን በነጻ በማውጣት እየተባበሩ ይገኛሉ፡፡

 ክፍል አንድ
1.1 አጠቃላይ የግእዝ ሥነ ጽሑፋዊ ሀብት

የግእዝ ቋንቋ ከሁለት ሺ ዓመታት በላይ ጊዜ ያስቆጠረ የሥነ ጽሑፍ ሀብት ያለው ቋንቋ ነው፡፡ እስካሁን የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የግእዝ ሥነ ጽሑፍ በተጻፉበት ቁስ በሦስት መልኮች ቀርበዋል፡፡ በድንጋይ ላይ፣ በብራና ላይና በወረቀት ላይ፡፡

  1. የድንጋይ ላይ ጽሑፎች፡- በድንጋይ ላይ የተጻፉት የግእዝ ሥነ ጽሑፎች በአኩስም አካባቢ የተገኙትንና የነገሥታቱን የጦርነት ታሪኮችንና ሌሎች ዘገባዎችን የያዙትን ጽሑፎች ይመለከታል፡፡  የተገኙት የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ከአራተኛው መክዘ(ቅልክ) እስከ 8ኛው መክዘ(ድልክ) የሚደርሱ ናቸው፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ ጥንታዊው የሚባለው የድንጋይ ላይ ጽሑፍ በመጣራ ኤርትራ በሐውልቲ የተገኘው(5ኛው መክዘ ቅልክ) ጽሑፍ ነው፡፡

‹ዝ ሐውልት ዘአገበረ

አገዘ ለአበዊሁ ወሰ

ሐበ ሙሓዛተ አውዐ

አለፈነ ወጸበለነ›› የሚለው ነው፡፡

እነዚህ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች አብዛኞቹ ዘገባዎችና ታሪኮች ሃይማኖታውያን አይደሉም፡፡

  1. የብራና ላይ ጽሑፎች፡- ሁለተኛው የግእዝ ሥነ ጽሑፍ የብራና ሥነ ጽሑፎች መልክ ነው፡፡ የብራና ላይ የግእዝ ጽሑፍ ከ6ኛው መክዘ እስከ አሁን ዘመን የቀጠለ ሲሆን በማይክሮፊልም በተነሡት የብራና መጻሕፍት ቁጥር የሄድን እንደሆነ ቁጥራቸው እስከ 12,000 ይደርሳል፡፡ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ ጠፍተው የቀሩትን፣ በየቦታው ተደብቀውም አድራሻቸው ያልታወቁትን ሳይጨምር ማለት ነው፡፡ እስካሁን በተገኘው መረጃ ጥንታዊው የሚባለው የብራና የግእዝ መጽሐፍ በእንዳ አባ ገሪማ የሚገኘው ወንጌል ሲሆን የተጻፈውም በ6ኛው መክዘ ነው፡፡

  2. የወረቀት ላይ ጽሑፎች፡- ሦስተኛው የግእዝ ሥነ ጽሑፍ መልክ በወረቀት የታተሙ መጻሕፍት ናቸው፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በብራና የሚገኙትን የግእዝ መጻሕፍት ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የቀረቡ እንጂ አዳዲስ ድርሰቶች አይደሉም፡፡ የግእዝ የታተሙ መጻሕፍት ታሪክ ጉተንበርግ የግእዙን ዳዊት ጀርመን ላይ ካሳተመበት ጊዜ ይጀምራል፡፡ ይህም የአራት መቶ ዓመታት ታሪክ ይኖረዋል፡፡

 1.2 የሦስቱ የግእዝ ሥነ ጽሑፍ መልኮች ልዩ ባሕርይ
የድንጋይ ላይ ጽሑፎች

የድንጋይ ላይ ጽሑፎቹ የዘገባ መልክ ያላቸው፣ ታሪካዊ መረጃ የሚሰጡና በአብዛኛውም ሃይማኖታዊ ይዘት የሌላቸው ናቸው፡፡ ሃይማኖታዊ መረጃ ቢሰጡንም ነገሥታቱ ፈጣሪያቸውን ሲያመሰግኑ፣ ለፈጣሪያቸው የሰጡትን መሥዋዕት ሲገልጡ፣ ወይም የሙታን መታሰቢያ ሐውልቶቹ ደግሞ እግረ መንገዳቸውን በሚሰጡን መረጃ አማካኝነት ነው፡፡ የድንጋይ ላይ ጹሑፎቹ በሁለት ዓይነት አጻጻፍ የተጻፉ ናቸው፡፡ በጥንታዊና አናባቢ በሌለው ግእዝ ‹‹ሐወለተ፣ አከሰመ›› በሚለው መንገድና አናባቢ በተፈጠረለት ዘመናዊው ግእዝ የተጻፉ ናቸው፡፡ የድንጋይ ላይ ጽሑፎቹ በቅድመ አኩስምና በአኩስም ዘመን የተሠሩ ሲሆኑ የሚያንጸባርቁትም ያንኑ ዘመን ነው፡፡

የብራና ጽሑፎች

የብራና የግእዝ መጻሕፍት ከ6ኛው መክዘ ጀምረው እስካሁን የዘለቁና በሀገራችን የሥነ ጽሑፍ ዘመን በጥንታዊነትም ሆነ ለረዥም ዘመን በመዝለቅ ተወዳዳሪ የሌላቸው ናቸው፡፡ የብራና የግእዝ የጽሑፍ ሀብቶች ሦስት ዓይነት ናቸው፡፡

  1. ሃይማኖታውያን፣

  2. በዋናነት ሃይማኖታውያን ያልሆኑ ጉዳዮችን የያዙና

  3. ደብዳቤዎች

ሃይማኖታውያንየምንላቸው የተጻፉበት ዓላማ ሃይማኖትን ለማስተማር(ዶግማን፣ ቀኖናን፣ ትውፊትን፣ ታሪክን) ወይም ለአምልኮ ሥርዓት መፈጸሚያነት(ለጸሎት፣ ቅዳሴ፣ ውዳሴ፣ ዝማሬ፣ ሃይማኖታዊ ክዋኔ) የሆኑ ጽሑፎች ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ አብዛኞቹ የግእዝ የብራና ጽሑፎች ሃይማኖታውያን ናቸው፡፡ እነዚህ ሃይማኖታውያን የግእዝ ጽሑፎች ሦስት እምነቶችን የያዙ ናቸው፡፡ የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክና የይሁዲነት፡፡ የኦርቶዶክስ እምነትን የሚገልጡ መጻሕፍት በብዛትም ሆነ በቀደምትነት የግእዝን ጽሑፎች ይይዛሉ፡፡ ከ16ኛው መክዘ በኋላ ደግሞ የካቶሊክ እምነትን የሚገልጡ የግእዝ የብራና መጻሕፍትን እናገኛለን፡፡ የይሁዲነትን እምነት የሚገልጡት ጽሑፎች በኢትዮጵያ ከሚገኙ የቤተ እሥራኤል ወገኖች ጋር የተያያዙ ሲሆኑ እስካሁን ባሉን መረጃዎች ከመካከለኛው ዘመን ወደ ኋላ የዘለሉ አላገኘንም፡፡

የታተሙ የግእዝ የጽሑፍ ሀብቶች

የታተሙት የግእዝ ጽሑፎች የብራና ጽሑፎች ቅጅዎች ናቸው፡፡ እስካሁን ድረስ በግእዝ የተጻፉ ኣዳዲስ ድርሰቶችን በኅትመት አላገኘንም፡፡ አብዛኞቹ የታተሙ የግእዝ ጽሑፎች ግእዝና አማርኛን፣ ግእዝና ትግርኛን፣ ግእዝና እንግሊዝኛን፣ ግእዝና ጀርመንኛን፣ ግእዝና ስፓኒሽን፣ ግእዝና ፈረንሳይኛን፣ ግእዝና ፖርቹጊዝን ጎን ለጎን ያደረጉ ሲሆኑ ለሁለት ዓይነት ተግባራት የታተሙ ናቸው፡፡ ለሃይማኖታዊ አገልግሎትና ለምርምር አገልግሎት፡፡ ለሃይማኖታዊ አገልግሎት የሚውሉት የግእዝ ኅትመቶች የሚታተሙት በአብዛኛው በኢትዮጵያና በኤርትራ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ትንሣኤ ዘጉባኤ አሳታሚ፣ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ ተስፋ ገብረ ሥላሴ፣ አኩስም ማተሚያ ቤት፣ ማኅበረ ቅዱሳንና የየአጥቢያው አብያተ ክርስቲያናት ሲያሳትሟቸው፤ በኤርትራ ዋናው አሳታሚ ማኅበረ ሐዋርያት ፍሬ ሃይማኖት ነው፡፡

ለምርምር የሚውሉት የግእዝ ኅትመቶች በአብዛኛው የሚታተሙት በውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች በኩል ነው፡፡ እነዚህ ኅትመቶች በጥናታዊ መጽሔቶች ውስጥና ራሳቸውን ችለው በመጽሐፍ መልክ የሚወጡ ሲሆኑ ከግእዙ በተጨማሪ የመቅረቢያ ቋንቋውን ትርጉም፣ ስለ ጽሑፉ ዳራና የጽሑፉ ምሁራዊ ሐተታ ይቀርቡባቸዋል፡፡ አብዛኞቹም የተለያዩ ቅጅዎች ንጽጽር አሏቸው፡፡ በዚህ ረገድ የጣልያን፣ የእንግሊዝ፣ የጀርመን፣ የፈረንሳይና የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ብዙ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ለጥናት የሚታተሙ የግእዝ ጽሑፎችን በማተም ቤልጅየም የሚገኘውን ፒተርስ አሳታሚ የሚያህለው የለም፡፡

በግለሰብ ደረጃ ከጥንቶቹ እንግሊዛዊው ዋሊስ በጅ፣ ጀርመናዊው ኤድዋርድ ኡልንዶርፍና ኢዮብ ሉዶልፍ፣ ጣልያናዊዎቹ ኮንቲ ሮሲኒ፣ ኤንሪኮ ቼሩሊና ጉይዲ፤ ፈረንሳዊዎቹ ሬኔ ባሴ፣ ዣን ፕሩሶ፤ ራሺያዊውቢ ቱራየቭ ይጠቀሳሉ፡፡ ከዘመናችን ደግሞ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን የሚስተካከል የለም፡፡

ክፍል ሁለት

ሃይማኖታውያን ያልሆኑ የግእዝ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች

ስለ ግእዝ ሥነ ጽሑፍ ብዙ ጊዜ ሲነገር ከሃይማኖታውያን የጽሑፍ ሀብቶቹ ጋር በተያያዘ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሊሆን የቻለውም በሦስት ምክንያቶች ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡

  1. የግእዝ ቋንቋ በአሁኑ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መገልገያ ቋንቋ በመሆኑ

  2. አብዛኞቹ የግእዝ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች ሃይማኖታውያን በመሆናቸው እና/ወይም

  3. ሃይማኖታውያን ስላልሆኑት የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች በብዛት ባለመነገሩና ባለመታተማቸው

ምንም እንኳን ከላይ የተገለጠው ግእዝን ከሃይማኖታዊ ድርሰቶች ጋር የማያያዝ ትርክት ጊዜ ጠገብ ቢሆንም በግእዝ ቋንቋ ተጽፈው የምናገኛቸው አያሌ ሃይማኖታውያን ያልሆኑ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች ግን አሉ፡፡ እነዚህ ሃይማኖታውያን ያልሆኑት የግእዝ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች ከሁለት ምንጮች የተገኙ ናቸው፡፡

  1. ከሀገር ውጭ

  2. ከሀገር ውስጥ

ከሀገር ውጭ የምንላቸው ከኢትዮጵያ ውጭ ተደርሰው ወደ ግእዝ ቋንቋ የተተረጎሙ ሲሆኑ እነርሱም ከግሪክ፣ ላቲን፣ ዓረብና ቅብጥ የተተረጎሙ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን መገኛ ቋንቋዎቻቸው እነዚህ ቢሆኑም በእነርሱ በኩል ግን ከምሥራቅ ሕንድ እስከ ምዕራብ ሮም የሚደርሱ ድርሰቶችን አግኝተናል፡፡

ከሀገር ውስጥ የምንላቸው ደግሞ በኢትዮጵያውያን ደራስያን የተደረሱና በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ ናቸው፡፡ እነዚህም በተለይ በመካከለኛው ዘመን ተጀምረው እስከ 18ኛው መክዘ የዘለቁ የግእዝ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች ናቸው፡፡ የዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ይህ በመሆኑ በዚህ ጽሑፍ ላይ የተወሰኑትን እናያቸዋለን፡፡

  1. ፊሳሎጎስ፡- ፊሳሎጎስ ከግሪክ ወደ ግእዝ በ6ኛው መክዘ የተተረጎመ መጽሐፍ ነው፡፡ ፊሳሎጎስ በብዙ ቋንቋዎች የታወቀ መጽሐፍ ሲሆን የስሙ መጠሪያ ‹ፊዚዮሎጎስ› ከሚለው የግሪኩ ስም የመጣ ሆኖ በ200 ዓም አካባቢ በእስክንድርያ ውስጥ በግሪክ ቋንቋ የተጻፈ ነው፡፡ መጽሐፉ 48 ምእራፎች ሲኖሩት 42ቱ በእንስሳት፣ 2ቱ በዕጽዋት፣ 4ቱ ደግሞ በማዕድናት ላይ መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ምእራፍ አንድ እንስሳ፣ ዕጽ ወይም ማዕድንን በማንሳት፣ ጠባዩንም በመተንተን ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጋር አጣምሮ የሚያቀርብ ነው፡፡

ይህ መጽሐፍ በትውፊታዊው የኢትዮጵያ ትምህርት ውስጥ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ማስተማሪያ ዋና ምንጭ ሆኖ ያገለገለ ነው፡፡

  1. ፈውስ ሥጋዊ፡- ይህ መጽሐፍ በአብዛኛው የሚታወቀው ፈውስ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ በሚል ነው፡፡ ነገር ግን ሁለቱ መጻሕፍት የተለያዩ ናቸው፡፡ ፈውስ መንፈሳዊ ምናልባት ከ13-16ኛው መክዘ ባለው ጊዜ ወደ ግእዝ የተተረጎመ መንፈሳዊ መጽሐፍ ነው፡፡ ዓላማውም በኃጢአት የቆሰለችን ነፍስ በመንፈሳዊ ሕክምና ማከም ነው፡፡ ፈውስ ሥጋዊ ግን በትክክል እስካሁን ያልተጠና ምናልባት ግን ከ17ኛው መክዘ በፊት የተደረሰ(ከሀገር ውስጥና ከውጭ ምንጮች) መጽሐፍ ይመስለኛል፡፡ በውስጡ ለሥጋዊ ሕመም ፈውስ ሊሰጡ የሚችሉ የተለያዩ የዕጽዋትንና የእንስሳትን ውጤቶች የያዘ ነው፡፡

  2. መጽሐፈ አዕባን፡- እስካሁን ባለኝ መረጃ መሠረት ስለዚህ መጽሐፍ ጥናት አልተደረገም፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ብቻ በዚሁ ስም አንዲት አነስተኛ መጽሐፍ አሳትሟል፡ የተጠቀመው ይህንን ምንጭ ይሁን ወይም ሌላ አልተገለጠም፡፡ መጽሐፉ ለልዩ ልዩ ተግባር ሊውሉ የሚችሉ ድንጋዮችን በተመለከተ የተጻፈ የጂኦሎጂ መጽሐፍ ነው፡፡ አልፎ አልፎም ድንጋዮቹ በምን ዓይነት አካባቢ እንደሚገኙ ይናገራል፡፡ በኋላ ዘመን የድንጋይ ትርጉምና ጥቅም ተብሎ የተተረጎመውና በEMML 6815 የምናገኘው ከዚህ የተወሰደ ሳይሆን አይቀርም፡፡

  3. ዜና እስክንድር፡- ይህ መጽሐፍ በጥንታዊው ዓለም ታሪክ የተጻፈውን የታላቁን የግሪክ ንጉሥ የእስክንድርን ታሪክ በግእዝ የሚያቀርብ ነው፡፡ መጽሐፉ ምንጩ ግሪክ ሲሆን ከግሪክ ወደ ሶርያ፣ ከሶርያ ወደ ዓረብኛ፣ ከዓረብኛ ወደ ግእዝ የተተረጎመ ነው፡፡ የተተረጎመውም በ16ኛው መክዘ ምናልባት በ11ኛው የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት በዕጨጌ ዕንባቆም የመናዊ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ፡፡ መጽሐፉ ሲተረጎም ርእሱ ‹‹ሑረቱ ለእስክንድር›› የሚል ነበር፡፡

እስክንድርን በተመለከተ በ14ኛው መክዘ እንደዚሁ አንድ ትርጉም ተከናውኖ ነበር፡፡ ‹‹ዜና እስክንድር›› የተባለው ይህኛው መጽሐፍ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ መጽሐፍ ለመጨረሻ ጊዜ የታየው በትግራይ አካባቢ በሚገኙ ገዳማት ውስጥ ነው፡፡ ዜና እስክንድርየእስክንድርን የጀግንነት ታሪክ በክርስትና የሞራል ትምህርት ውስጥ ለማሳየት የሚሞክር ሲሆን ዋናው ዓላማውም ነገሥታቱን፣ መኳንንቱንና ወታደሮችን ማጀገን ነው፡፡

5.       ፍትሐ ነገሥት፡- ፍትሐ ነገሥት ሁለት ክፍል አለው፡፤ ፍትሕ ሥጋዊና ፍትሕ መንፈሳዊ፡፤ ትኩረታችን በፍትሕ ሥጋዊ ላይ ነው፡፡ ፍትሐ ነገሥትን ያዘጋጀው በ13ኛው መክዘ ግብጽ ውስጥ የነበረው እብን- እል አሳል የተባለ ባለሞያ ነው፡፡ መንፈሳዊ ሕግጋቱን ከተለያዩ የቀኖና መጻሕፍት ሲወስድ ሥጋዊ ሕግጋቱን ደግሞ ከሮም፣ ከባዛንታይምና ከሌሎች ሀገሮች ሕግጋት ወስዷቸዋል፡፡

መጽሐፉ ወደ ግእዝ የተተረጎመው በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሀገሪቱ እስከዚያ ድረስ ትጠቀም የነበረው የኦሪቱን የሕግ መንገድ በመሆኑ ንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ይህንን ሕግ ለመቀየር በማሰቡ ነው፡፡ ይህንን ሃሳቡን የነገረውና በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ጴጥሮስ አብደል ሰይድ የተባለ ግብጻዊ ፍትሐ ነገሥትን ንጉሡ ከግብጽ እንዲያስመጣ መከረው፡፡ ጴጥሮስ አብደል ሰይድም በንጉሡ ተልኮ መጽሐፉን ካመጣው በኋላ ወደ ግእዝ ተረጎመው፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ ግን ፍትሐ ነገሥት በሥራ ላይ ለመዋሉ ምንጭ የተገኘለት በዐፄ ሠርፀ ድንግል ዘመን ነው፡፡ ፍትሐ ነገሥት ኢትዮጵያ ዘመናዊ ሕግ እስክትቀርጽ ድረስ የተጠቀመችበት ለ600 ዓመታት ያህል ያገለገለ የሕግ ምንጭ ነው፡፡

6.       ዜና ስክንድስ፡- ስክንድስ በክርስትና የመጀመሪያዎቹ ዘመን የነበረ የግሪክ ፈላስፋ ነው፡፡ እናትና አባቱ የፍልስፍናን ነገር እንዲያጠና ወደ አቴንስ ልከውት የተመራመረውን ነገር ነው መጽሐፉ የሚገልጥልን፡፡ ይህ መጽሐፍ በሁለት የምዕራብ ቋንቋዎች(ላቲንና ግሪክ)ና በሦስት የምሥራቅ ቋንቋዎች(ሲርያክ፣ዓረብኛና ግእዝ) ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያው መጽሐፍ ከዐረብኛ የተተረጎመ ይመስላል፡፡ ወደ ግእዝ የተመለሰውም በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን መሆኑን ይገልጣል፡፡

ግእዙ ሦስት ክፍሎች አሉት፡፡ የመጀመርያው ክፍል የስክንድስን ሕይወት ይይዛል፣ ሁለተኛው ደግሞ የ55 ፍልስፍናዊ ጥያቄዎችንና መልሶችን የያዘ ሲሆን ሦስተኛው ክፍል 108 ጥያቄዎችን እያነሣ ያትታል፡፡


7. መጽሐፈ ፈላስፋ ጠቢባን፡- ይህ ከ1503 – 1515 ዓም ባለው ዘመን የተተረጎመው መጽሐፍ በግእዝ ሊቃውንት ዘንድ እጅግ የታወቀ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ የግሪክና የሌሎች ሀገሮች ፈላስፎችን አባባሎችና ትምህርቶች የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡


8. በርለዓም ወየወሴፍ፡- በርለዓም ወየወሴፍ የተለያዩ ምሳሌዎችንና ተረቶችን የያዘ የሕንድ መጽሐፍ ነው፡፡ የተወሰደውም ከትውፊታዊው የጉተማ ቡድሐ የሕይወት ታሪክ ነው፡፡ ታሪኩ የፍቅር ታሪክ ነው፡፡ የዚህ መጽሐፍ ቅጅዎች በአይሁድ፣ በማኒያውያን፣ በሙስሊሞችና በክርስቲያኖች ዘንድ ይገኛሉ፡፡


ዋዳጎስ የተባለ እጅግ ባዕለ ጸጋ የሆነ ኃይለኛ የሕንድ ንጉሥ በሕንድ የሚገኙ ክርስቲያኖችን ጨፈጨፈ፡፡ አንድ ቀን ዋዳጎስ የወሴፍ የሚባል ወንድ ልጅ ወለደ፡፡ ኮከብ ቆጠሪዎችና ጠንቋዮች ስለ ልጁ ዕጣ ፈንታ ሲጠየቁ ልጁ ወደፊት ክርስቲያን እንደሚሆንና የክርስቶስን ሃይማኖትንም ከፍ ከፍ እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡ ይህንን በመፍራት ንጉሡ ልጁን በአንድ ቤተ መንግሥት ውስጥ ወስኖ አስቀመጠው፡፡ ኀዘን፣ ድክመት፣ ሞት የሚባሉትን ነገሮች እንዳያውቅ እርሱንም ከደስታ የሚያወጣውን ነገር እንዳያጋጥመው አደረገው፡፡


እያደገ ሲሄድ ግን መስፍኑ ከዚያ ቤተ መንግሥት ውጭ ያለውን ዓለምም ለማወቅ ፈለገ፡፡ ከቤተ መንግሥቱ ውጭም ኀዘን፣ በሽታ፣ ልቅሶ፣ ረሃብና ሞት መኖራቸውን ዐወቀ፡፡ ታዋቂው መናኝ መምህር በርለዓምም መስፍኑን አገኘው፡፡ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ክርስትናም አስተማረው፡፡ ይህንንም ያስተማረው የተለያዩ ታሪኮችንና አባባሎችን በመጠቀም ነበር፡፡


መስፍኑ የወሴፍ ዓለምን ለመካድ ከበርለዓም ጋር ያለውንም ግንኙነት አባቱ ሳይሰማ ለማቆም ፈለገ፡፡ አባቱ ነገሩን ከመስማቱ በፊትም በርለዓም ከእርሱ ተለየ፡፡ ንጉሡም ነገሩን ሲሰማ እጅግ ተበሳጨ፡፡ የወሴፍን ወደ ጥንት እምነቱ ለመመለስም የቻለውን ሁሉ አደረገ፡፡ የመንግሥቱን አንድ ሦስተኛ ለመስጠት ቃል እስከ መግባትም ደረሰ፡፡ የወሴፍ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ በመጨረሻም ንጉሡ ራሱ ስሕተቱ ገባው፡፡ አማካሪዎቹ ሁሉ ክርስቲያን ከሆኑ በኋላም ንጉሡም ክርስትናን ተቀበለ፡፡


አባቱ ከሞተ በኋላ የወሴፍ መንግሥቱን ተወ፡፡ እጅግ ለሚያምነው ተከታዩ ዙፋኑን በመስጠትም መምህሩ በርለዓም ለመፈለግ ወደ በረሃ ሄደ፡፡ እዚያ በርለዓምን ሲያገኘውም ሁለቱም የምናኔ ሕይወታቸውን እስከ ዕለተ ሞታቸው ቀጠሉ፡፡


መጽሐፉን ያስተረጎመው ዐፄ ገላውዴዎስ ሲሆን የተረጎመው ደግሞ እጨጌ ዕንባቆም ነው፡፡ ትርጉሙም የተከናወነው በ1546 ዓም ነው፡፡ በርለዓም ወየወሴፍ ከሕንድ ተወስዶ በክርስቲያናዊ መንገድ የቀረበ የሥነ ምግባር ማስተማሪያ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ በሦስቱ ዋና ዋና እምነቶች (አይሁድ፣ ክርስትናና እስልምና) ተቀባይነት ያገኘ መጽሐፍ ነው፡፡


9. አቡሻክር

አቡ ሻክር ቢን አቢ ኤል ከሪም ቡጥሮስ ቢን አል ሙሐዲብ ያዘጋጀው የዓለምን ታሪክ የያዘ መጽሐፍ፡፡ የኖረው ከ1200/ 10 እስከ 1295 እኤአ  ካይሮ ውስጥ ነው፡፡ አቡሻክር የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ዲያቆንና የቅዱሳት መጻሕፍት ደራሲ ነበር፡፡ ከእርሱ መጻሕፍት መካከል በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ዘንድ እጅግ የታወቀው ‹‹ኪታብ – አት – ታዋሪህ›› የተባለውና የዓለምን ታሪክ በአጭር በአጭሩ የሚገልጠው ‹አቡሻክር፣ ሐሳበ አቡሻክር›› እየተባለ የሚጠራው መጽሐፍ ነው፡፡


ከ1626 እስከ 1630 ዓም ባለው ዘመን መካከል የተጻፈ አንድ አቡሻክር እንዲህ ይላል ‹‹ዝንቱ መጽሐፍ ብሩክ ዘደረሰ እግዚእ ትሩፈ ምግባር ማእምረ መጻሕፍት አቡሻክር ወልደ አቡእልከረም ጴጥሮስ መነኮስ እብንልመሐድብ ዘበትርጓሜሁ ወልደ ግሡጽ ወእመአኮ ወልደ ምሁር ዘእሙር በሪሺ ዘተሠይመ ዲያቆነ በቤተ ክርስቲያን ዘመዐልቃ፡፡ እንዘ ይነግር በእንተ ሐሳበ ዐለም፡፡››

የዐረብኛው መጽሐፍ የተጻፈው በ1250 ዓም ነው፡፡ በኢትዮጵያ አንድ የብራና መጽፈፍ ላይ መጽሐፉ የተጻፈው በ6750 ዓመተ ዓለም፣ በ655 ዓመተ ተንባላት (በእስልምና አቆጣጠር) መሆኑን ይገልጣል፡፡ ይህም በ1250 ዓም መሆኑን ያመለክታል፡፡


10.     በአርመንኛ የሚገኙ ቁጥሮች ትርጉም፡- ይህ መጽሐፍ እስካሁን አልተገኘም፡፡ የተጻፈው በ11ኛው የደብረ ሊባኖስ እጨጌ በአቡነ ዕንባቆም የመናዊ ነው፡፡ ከስሙ ለመገመት እንደሚቻለው የአርመንኛ ቁጥሮችን ኮድ የሚተረጉም ይመስላል፡፡ ስለ መጽሐፉ ፍንጭ የሰጠን አልቫሬዝ ነው፡፡


11.       የላቲን ቃላት ዝርዝር፡- ይኼኛውም መጽሐፍ የዕንባቆም መጽሐፍ ነው፡፡ እስካሁን ግን አልተገኘም፡፡ ከስሙ ለመገመት እንደሚቻለው የላቲን ቃላትን የሚዘረዝርና የሚተረጉም ይመስላል፡፡ አልቫሬዝ ዕንባቆም ላቲን እንደሚችል ይነግረናል፡፡ ምናልባትም ጥንታዊ መዝገበ ቃላትም ይሆናል፡፡


12.     በሮማን ዘየ(dialect) የተጻፉ ቁጥሮች ትርጉም፡- ይህ መጽሐፍ የዕጨጌ ዕንባቆም መጽሐፍ ሲሆን የሮምን ቁጥሮችን መንፈሳዊ/ የኮድ ትርጉም የያዘ ይመስላል፡፡ መጽሐፉ እስካሁን አልተገኘም፡፡


13. ዮሐንስ መደብር፡- ይህ መጽሐፍ በግእዝ ሊቃውንት ዘንድ እጅግ የታወቀ የታሪክ መጽሐፍ ነው፡፡ ዲያቆን ቅብርያል በ16ኛው መክዘ የነበረ ግብጻዊ ነው፡፡ ዐረብኛና ግእዝ ይችል ነበር፡፡ በሠራዊቱ አለቃ በአትናቴዎስና በእቴጌ ማርያም ሥና ትእዛዝ ‹‹ዮሐንስ መደብር›› የተሰኘውን የነቅዩስ ጳጳስ የዮሐንስን መጽሐፍ በ1594 ዓም በዐፄ ያዕቆብ ዘመን በአራተኛው ዓመት ተርጉሟል፡፡


በአንድ መጽሐፍ መጨረሻ ላይ እንዲህ ይላል ‹‹ወተርጎምና በአስተሐምሞ ብዙኅ ለዝንቱ መጽሐፍ እም ዓረቢ ለግእዝ አነ ምስኪን ምኑን በኀበ ሰብእ ወትኁት በውስተ ሕዝብ ወዲያቆን ቅብርያል ግብጻዊ ወልደ ሰማዕት ዮሐንስ ዘቀልዩቢ በትእዛዘ አትናቴዎስ ሊቀ ሠራዊት ዘኢትዮጵያ፡፡ ወበትእዛዘ ንግሥት ማርያም ሥና››


14. አንጋረ ፈላስፋ፡- ይህ የተለያዩ ፈላስፎችን አነጋገር የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ የአሪስቶትል(አርስጣጣሊስ)፣ የፕሉቶ (አፍላጦን) የሶቅራጥስ ና የሌሎችንም ፈላስፎች ንግግሮች ይዟል፡፡ መጽሐፈ ፈላስፋ ጠቢባን በመባልም ይታወቃል፡፡


15. ሐተታ ዘርዐ ያዕቆብ አኩስማዊ ወወልደ ሕይወት እንፍራንዛዊ፡- ይህ የ17ኛው መክዘ ኢትዮጵያዊ የፍልስፍና መጽሐፍ ሲሆን በሁለት ኢትዮጵያውያን የተዘጋጀ ነው፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ በተባለ የአኩስም ተወላጅና ወልደ ሕይወት በሚባል የጎንደር (እንፍራንዝ) ተወላጅ፡፡ ሁለቱን ያገናኛቸው አመለካከት ነው፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ በወቅቱ ይታሰብ ከነበረው የእምነት፣ የባሕልና የአስተዳደር አስተሳሰብ ወጣ ብሎ ነገሮችን በሰላ ዓይን ይመረምር ነበር፡፡ ደቀ መዝሙሩ ወልደ ሕይወትም ይህንኑ መሥመሩን ተከትሎታል፡፡


16. መጽሐፈ ማስያስ፡- አባ ማስያስ በጣና ገዳማት በ15ኛው መክዘ የነበሩ ኢትዮጵያዊ መነኮስ ናቸው፡፡ ስለ ዓለም ነገር ማወቅ ይፈልጉ ነበር፡፡ ይህንንም በጾምና በጸሎት ከፈጣሪያቸ&#481

ከግንቦት 9 እስከ 11 ቀን ድረስ በትግራይ ክልል አኩስም ከተማ ‹ሀገር አቀፍ የግእዝ ዐውደ ጥናት ተደርጎ ነበር፡፡ ይህ በዓይነቱ በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ሲዘጋጅ የመጀመሪያ የሆነው ዐውደ ጥናት የትግራይ ክልል ባሕል ቱሪዝም ኤጀንሲ ከፌዴራል ባሕል ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆን ያዘጋጀው ነበር፡፡




የክልሉ ባሕል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች እንደገለጡት ይህ ዐውደ ጥናት በትግራይ ክልል ደረጃ ሲከናወን ለስድስተኛ ጊዜ ነው፡፡ የዘንድሮውን ልዩ የሚያደርገው በሀገር አቀፍ ደረጃ መከናወኑ ነው፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ ከጎንደርና ከሌሎችም አካባቢዎች የተጋበዙ ጉምቱ ጉምቱ ሊቃውንት የተገኙ ሲሆን እስከ ዛሬ ትውፊታውያን ሊቃውንት እንዲህ በብዛትና በዓይነት ተገኝተው ከዘመናውያን ምሁራን ጋር ሲገናኙ ዕድል ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ በዚህም የክልሉ ባሕል ቱሪዝም ኤጀንሲና የፌዴራሉ ባሕል ቱሪዝም ሚኒስቴር ተመስጋኞች ናቸው፡፡

ከልዩ ልዩ ቦታ የተጋበዙ ምሁራንና ሊቃውንት

ከተለያዩ ዩኒቨረሲቲዎች ባለሞያዎች እንዲጋበዙ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም እንዲገኙ መደረጉ፤ መርሐ ግብሩ ግንቦት 11 ከሚከበረው የቅዱስ ያሬድ በዓል ጋር እንዲሠምር መደረጉ፣ ለበዓሉም የተሰጠው ቦታ ሊቃውንቱ ሁሉ ቅኔ ሲያዘንቡበት የዋሉት ጉዳይ ነው፡፡ ቅኔ ልብስ ቢሆን ኖሮ የክልሉና የፌዴራሉ ቢሮዎች እስከ እድሜ ልካቸው የሚሆን ልብስ በሁለቱ ቀን ጉባኤ ያገኙ ነበር፡፡ በበዓሉ መጨረሻ የሐን፣ ማይ ኬራህንና ሙራደ ቃልን ለመጎብኘት መርሐ ግብር መዘጋጀቱ ዝግጅቱን ሙሉ አድርጎት ነበር፡፡

በዐውደ ጥናቱ ላይ ልዩ ልዩ ጽሑፎች ቀርበው ነበር፡፡

ዶ/ር ሥርግው ገላው፣ ፕ/ር ባየ ይማም እና ዶ/ር ኃይሉ ሀብቱ

የግእዝ ሥነ ጽሑፍ ሀብት ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች ያበረከተው አስተዋጽዖ(ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም)፣ የግእዝ ጥናት ከጥንት እስከ ዛሬ(ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ)፣ የግእዝ ቅኔያት ይዘትና ቅርጽ (ዶ/ር ሥርግው ገላው)፣ የ‹‹ትቤ አክሱም መኑ አንተ›› መጽሐፍ ትንታኔ(ዶ/ር ኃይሉ ሀብቱ)፣ በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ ሃይማኖታውያን ያልሆኑ መጻሕፍት (ዳንኤል ክብረት)፣ ግእዝና ቅዱስ ያሬድ(መ/ር ተስፋይ ሀደራ) ቀርበው ነበር፡፡ 
መ/ር ደሴ ቀለብ፣ ዶር ታየ አሰፋ እና ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ

በመጨረሻም ለወደፊቱ የግእዝ ዓመታዊ ዐውደ ጥናት በምን መልኩ መቀጠል እንዳለበት፣ ግእዝ በሀገር ፖሊሲ ደረጃ እንዴት ሊታቀፍ እንደሚገባው፣ ልዩ ልዩ አካላት ስለሚኖራቸው ድርሻ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡
መሪጌታ ልሳነ ወርቅ ገብረ ጊዮርጊስ

ክልሉም ሆነ የፌዴራሉ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ግእዝን በተመለከተ የያዙት አቋም የሚበረታታና የሚደገፍም ነው፡፡ ግእዝ የሀገሪቱ የእምነት፣ የባሕል፣ የዕውቀት፣ የሥራ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፖለቲካ፣ የፍልስፍና፣ የኢኮኖሚና የማኅበራ ግንኙነት ቋንቋ ሆኖ ከ2000 ዓመታት በላይ በመኖሩ በውስጡ የያዛቸውን ዕውቀቶች ፈትሾ ለሀገር ጥቅም ማዋል ይጋባልና በነካ እጃችሁ ወደፊት ቀጥሉ እንላለን፡፡
የጋዜጠኞችና የአዘጋጆች ቡድን
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ‹‹የጎረቤት ጠበል የቆዳ መንከሪያ ነው›› ብሎ ነው መሰል የአኩስም ዩኒቨርሲቲ ከተሳትፎ መራቁ ሁሉንም ሰው ያስገረመ ነበር፡፡ ከእርሱ ይልቅ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በግእዝ ተናግረው በግእዝ የሚያሳምኑ እሳት የላሱ ወጣቶችን ይዞ መጥቶ ያሳየው ተሳትፎ እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭን ነበር፡፡ ወጣቶቹ ግእዝ ተምረው በግእዝ አፋቸውን የፈቱ እስኪመስል ድረስ ያቀርቡት የነበረው ዲስኩር ተስፋ የሚያለመልም ነበር፡፡

የበጎ ሰው ሽልማት መርሐ ግብር ግንቦት 30 ቀን 2006 ዓም በኢሊሊ ሆቴል ይካሄዳል፡፡ ‹‹በጎ ሰዎችን በመሸለምና በማክበር፣ ሌሎች በጎ ሰዎችን እናፍራ›› በሚል ሐሳብ የተጀመረው መርሐ ግብር ወደ ማጠናቀቂያው እየተጓዘ ነው፡፡ በሰባቱ ዘርፎች የሚወዳደሩት 35 ዕጩዎች የታወቁ ሲሆን ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2006 ዓም በኢሊሊ ሆቴል ከጠዋቱ 4 ሰዓት ላይ በሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ይሆናሉ፡፡
መርሐ ግብሩን ለማገዝ አያሌ ድርጅቶችና ባለሞያዎች ከኮሚቴው ጎን ቆመዋል፡፡ ዳሽን ቢራ ለዝግጅቱ የሚሆነውን ወጭ ለመሸፈን ግንባር ቀደሙን ቦታ የያዘ ሲሆን ሸገር ሬዲዮና ኢ ቢ ኤስ ቴሌቭዥን የዝግጅቱ አጋር በመሆን ማስታወቂያዎችንና የዝግጅቱን መርሐ ግብሮች በነጻ ለማስተላለፍ ወስነዋል፡፡ ኢሊሊ ሆቴል ደግሞ አዳራሹን በነጻ በሚባል ዋጋ በመስጠት ትብብሩን ለግሷል፡፡ የሽልማቱን ምስል ታዋቂው ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ አዘጋጅተውታል፡፡

መርሐ ግብሩን ለመሳተፍ ለሚፈልጉ 100 የዚህ ጦማር ተከታታዮች ካርድ ተዘጋጅቷል፡፡ ካርዱን ለማግኘት በሚከተለው የኢሜይል አድራሻ ይመዝገቡ፡፡ [email protected] 
ሥራው የሁላችሁንም ጸሎትና እገዛ ይጠይቃል፡፡ 

ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ በሊቅነታቸው፣ በቆራጥነታቸው፣ ለየት ባለ አስተሳሰባቸውና ለነገሮች በሚሰጡት አስደናቂ ምላሽ የሚታወቁ የትግራይ ሊቀ ጳጳስ ነበሩ፡፡ እስካሁንም እርሳቸውን በተመለከተ የሚተረኩ እጅግ አስገራሚ ታሪኮች አሏቸው፡፡ አንዱ እንዲህ ይላል፡፡ አቡነ ዮሐንስ በዓላትን በተመለከተ የነበራቸው አስተሳሰብ ከብዙው ሰው ለየት ያለ ነበር፡፡ ‹‹በዓል መከበር ያለበት በሥራ ነው›› ብለው ያምኑ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት እንዲያውም በቀዳሚት ሰንበት ሥራ ሲሠሩ ያያቸው ሰው ‹‹እንዴት ጌታ ባረፈበት ቀን ይሠራሉ›› ቢላቸው ‹‹እርሱኮ ያረፈው ሥራውን ጨርሶ ነው፡፡ እኔ መች ሥራዬን ጨረስኩ ብለህ ነው›› ብለው መመለሳቸው ይነገራል፡፡

‹‹የበዓላትን ቀናት ለበዓሉ የሚስማማ ሥራ በመሥራት እንጂ እጅና እግርን አጣጥፎ በመቀመጥ፣ መጠጥ ቤትና ጭፈራ ቤት በመዋል ማክበር ከማክበር አይቆጠርም፡፡ ሰው ምንጊዜም መቦዘን የለበትም፡፡ በየዕለቱ ለዕለቱ ተስማሚ የሆነ ሥራ መሥራት አለበት›› ብለው ያም ይህንንም ያስተምሩ ነበር፡፡

ታድያ በአንድ ወቅት በበዓል ቀን ቤተ ክርስቲያን ሲያሠሩ ውለው ለጉዳይ ወደ ሌላ ቦታ ይሄዳሉ፡፡ ለአቤቱታ ወደ እርሳቸው ዘንድ ከገጠር የመጣ አንድ ካህን እርሳቸውን ፍለጋ ወደሚያሠሩት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ይመጣል፡፡ ሲመጣ እርሳቸው የሉም ነገር ግን ሠራተኞቹ በሥራ ተጠምደዋል፡፡ ተገረመም፣ ተናደደም፡፡ ‹‹እንዴት በበዓሉ ቀን ትሠራላችሁ›› ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ያዘዟቸው አቡነ ዮሐንስ መሆናቸውን ነገሩት፡፡ እርሱ ግን አልተቀበለውም፡፡ ከኖረበትና ከተማረው ውጭ የሆነ ነገር ሲፈጸም እያየ ዝም ማለቱን ኅሊናው አልተቀበለውም፡፡ በርግጥ ያዘዙት ሊቀ ጳጳሱ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሊቀ ጳጳሱም ቢሆኑ ሊሳሳቱ ይችላሉ አለና አሰበ፡፡

አስቦም አልቀረ ወደ ሠራተኞቹ ሄደና ‹‹በሉ ሥራችሁን አቁሙ›› አላቸው፡፡ እነርሱ ግን ሊቀ ጳጳሱ ያዘዙትን እንደማያቆሙ ነገሩት፡፡ በዚህ ጊዜ መስቀሉን አወጣና አወገዛቸው፡፡ ያን ጊዜም ሠራተኞቹ ሥራቸውን አቆሙና ቁጭ አሉ፡፡ እርሱም ሊቀ ጳጳሱን ፍለጋ ሄደ፡፡

አቡነ ዮሐንስ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሲመጡ ሠራተኞቹ ሁሉ ቁጭ ብለዋል፡፡ ‹‹ለምን ሥራ ፈትታችሁ ተቀመጣችሁ?›› አሏቸው፡፡ ‹‹አንድ ካህን መጥቶ አወገዘን›› አሉና መለሱላቸው፡፡ ካህኑ ይጠራ ተባለና ተፈልጎ መጣ፡፡ ‹‹አንተ ነህ ወይ ያወገዝካቸው›› አሉት፡፡ ‹‹አዎ›› አለ፡፡ ‹‹ለምን?›› ሲሉ መልሰው ጠየቁት፡፡ ‹‹አባቶቻችን ያቆዩትን ሥርዓት ጥሰው ለምን በዓል ይሽራሉ ብዬ‹‹ አላቸው፡፡ ‹‹ያዘዝኳቸውኮ እኔ ነኝ›› አሉት፡፡ ‹‹ቢሆኑም ስሕተት ነው፡፡ ስሕተቱን እያየሁ ዝም ማለትም ሌላ ስሕተት ነው›› አላቸው፡፡

አቡነ ዮሐንስ ተገረሙ፡፡ ካህኑን በመኪናቸው አሳፈሩና ወደ ቤታቸው ወሰዱት፡፡ ‹‹በል ያንተን ጉዳይ በጉባኤ ነው የማየው፤ እስከዚያ እዚሁ እኔ ቤት እየበላህ እየጠጣህ ተቀመጥ›› አሉት፡፡ አቡነ ዮሐንስ ለጉዳይ የሚመጣ የገጠር ሰው ከገጠማቸው ከተቻለ ጉዳዩን ዕለቱኑ ይፈጽሙለታል፡፡ ካልተቻለ ደግሞ እዚያው ራሳቸው ቤት አስቀምጠው ጉዳዩ እስኪያልቅ ያስተናግዱታል፡፡ ክሱ የሚቀርበው በእርሳቸው ላይ ቢሆንም ሰውዬው በቤታቸው መስተናገዱ ግን አይቀርም፡፡

ቀን ተቀጠረና በሀገረ ስብከቱ አዳራሽ ጉዳዩ ታየ፡፡ የመቀሌ ከተማ ሕዝብ፣ ካህናትና ሊቃውንት ተሰበሰቡ፡፡ አቡነ ዮሐንስ በሚሰጡት ለየት ያለ ፍርድ፣ በሚናገሩት ዘመን ተሻጋሪ ንግግር ይታወቃሉ፡፡ በአንድ ወቅት ወደ እርሳቸው የመጣ ሰው ‹‹ተማር›› ቢሉት ‹‹ምን እየበላሁ ልማር›› አላቸው፡፡ እርሳቸውም ‹‹ታድያ የደነቆርከው ምን እየበላህ ነው›› ብለው ጠይቀውታል ይባላል፡፡

ያ ካህን ቀረበ፡፡ ‹‹ለምንድን ነው ሠራተኞቹን የገዘትካቸው?›› ተብሎ ተጠየቀ፡፡ ‹‹አባቶቻችን ባቆዩን ሥርዓት በበዓል እንዲህ ያለ ሥራ መሠራት የለበትም ብዬ ነው›› አላቸው፡፡ ‹‹ያዘዝኩት እኔ ነኝ፣ አንተ ይህንን ስታደርግ ሊቀ ጳጳሱ ይቀጡኛል፣ ከሥራ ያባርሩኛል፣ ክህነቴን ይይዙብኛል ብለህ አላሰብክም›› አሉት፡፡ ‹‹ቢያባርሩኝም፣ ክህነቴን ቢይዙብኝም መቀበል ነው እንጂ ምን ይደረጋል፡፡ ስሕተት እያየሁ ግን እንዴት አልፈዋለሁ፡፡›› አላቸው፡፡ ‹‹እና የሚመጣብህን ሁሉ ለመቀበል ተዘጋጅተሃል›› አሉት ‹‹ከመጣ ምን ይደረጋል›› አለ ካህኑ፡፡ ‹‹ከምቀጣህ ለምን ግዝትህን አታነሣም›› አሉት፡፡ ‹‹እርሱማ አቋም ነው፡፡ እምነቴ ነው፡፡ ቃሌ ነው፡፡ ይኼማ ከእርስዎ የባሰ ስሕተት መሥራት ነው›› አላቸው፡፡

ያን ጊዜ አቡነ ዮሐንስ ተነሡ፡፡ ሕዝቡም ምን ሊፈርዱበት ይሆን? እያለ በጉጉት ጠበቀ፡፡ ግማሹ እንዲያ ግማሹም እንዲህ አሰበ፡፡ አቡነ ዮሐንስም የመጣበትን አውራጃ ጠየቁት፡፡ ነገራቸው፡፡ አሁን ሕዝቡ የቅጣቱ ደብዳቤ ለአውራጃው እንደሚጻፍ አረጋገጠ፡፡ አቡነ ዮሐንስም አውራጃውን ከሰሙ በኋላ ‹‹እገሌ የተባለው የዚህ አውራጃ ሊቀ ካህናት እንዲህ ወደተባለ አውራጃ ተዛውሯል›› አሉ፡፡ ያን ጊዜ ሕዝቡ ‹‹የኃጥኡ ዳፋ ጻድቁን ያዳፋ›› ብሎ ተረተ፡፡ በዚህ ካህን ዕዳ ሊቀ ካህናቱ በመቀጣቱ አዘነ፡፡ አቡነ ዮሐንስም ቀጠሉ፡፡ ‹‹የዚህ አውራጃ ሊቀ ካህናት ግን ይህ ቄስ ይሆናል›› ሲሉ ሕዝቡ በአግራሞት አጨበጨበ፡፡ካህኑም ግራ ገባው፡፡ የጠበቀውና ያገኘውም ተለያየበት፡፡ ሕዝቡም በጥያቄ ተወጠረ፡፡ ለምን?

‹‹አያችሁ ወገኖቼ›› አሉ አቡነ ዮሐንስ፡፡ ይህ ሰው ሊቀ ጳጳሱን አወገዘ፡፡ እንደ ሥርዓታችን ልክ አልነበረም፡፡ ቢያንስ ለምን እንደዚያ እንዳደረግን እንኳን መጠየቅ ነበረበት፡፡ ነገር ግን በአቋሙ ትክክል ነው፡፡ ሰው ማለት፤ ጀግና ማለት፣ ጎበዝ ማለት አቋም ያለው ሰው ነው፡፡ የበላዩን የማይፈራ፤ ፈጣሪውን ብቻ የሚፈራ፡፡ ላመነበት እውነት የሚቆም፡፡ በአቋሙ ምክንያት የሚመጣበትን ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ የሆነ፡፡ አሁን እኔ ሥልጣኑን ልይዝበት፣ ከሥራ ላግደው፣ ጨርሶም ላወግዘው እንደምችል ያውቃል፡፡ ይህንን ሁሉ እያወቀ ግን ላመነበት እውነት መጽናቱ ጀግና ያደርገዋል፡፡ ማክበር ያለብን የሚፈሩንን፣ ቅዱስ ቅዱስ የሚሉንን፣ የሠራነውንም ያልሠራነውም የሚያደንቁልንን፣ የሚያወድሱንን ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ይህማ የማንም ሰው ጠባይ ነው፡፤ አክባሪውን የማይወድ ማን አለ፡፡ እኛም ጀግና የምንሆነው የሚገሥፁንን፣ የሚቆጡንን፣ ስሕተታችንን በድፍረት የሚናገሩንን፣ ሥልጣናችንን ሳይፈሩ ያመኑበትን እውነት የሚመሰክሩልንን ጭምር መውደድና ማክበር አለብን፡፡

እናንተ እንደምቀጣው ነው የጠበቃችሁት፡፡ የሚገሥጹንን ሁሉ ግን መቅጣት የለብንም፡፡ ያመኑበትን ስሕተታችንን የሚነግሩንን፣ በአቋም የሚሞግቱንን ሁሉ መቅጣት የለብንም፡፡ እንዲያውም መሸለም አለብን፡፡ ለዚህ ካህን ክህነቱን የሰጠሁት እኔ ነኝ፡፡ ስሰጠውም ‹ደኻ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ በል› ያልኩት እኔ ነኝ፡፡ ያን የሰጠሁትን እኔ ላይ ሲፈጽመው መናደድ የለብኝም፡፡ ፍርደ ገምድል መሆንም የለብኝም፡፡ እንዲያውም እንዲህ ያለ ልጅ በማድረሴ ልኮራ ይገባል፡፡ ሞኞች የሚገሥጽዋቸውን አይወዱም፡፡ ግን ቢሆንም እየመረረን እንኳን መቀበል አለብን፡፡ አሠራሩ ስሕተት ቢሆንም አቋሙ ግን ልክ ነው፡፡ ቆራጥነቱ ግን ልክ ነው፡፡ ማንንም አለመፍራቱ፣ ላመነው እውነት ብቻ መቆሙ፣ የሚመጣበትን ለመቀበል መዘጋጀቱ ግን ልክ ነው፡፡ ስለዚህ ሸልሜዋለሁ፡፡

አዳራሹ በጭብጨባ ተሞላ፡፡ ካህኑም መሬት ወድቆ እጅ ነሣ፡፡ ታሪክም ለእኛ እንዲህ ሲል አቆየን፡፡

 © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

እሥራኤላውያን እንዲህ ይተርካሉ፡፡

በኢየሩሳሌም ከተማ የሚኖሩ ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ፡፡ አንደኛው ባለ ትዳርና የቤተሰብ አስተዳዳሪ፣ ሌላኛው ደግሞ ላጤ ነበሩ፡፡ ሁለቱም የሚተዳደሩት በአንድ የእርሻ መሬት ነው፡፡ ጠንክረው በጋራ በመሥራት ያመርቱና ምርቱን በእኩል ይካፈላሉ፡፡ በሥራና በኑሮ ያላቸው መተጋገዝና መጠቃቀም ለአካባቢው ሰዎች ሁሉ እጅግ የሚያሰቀና ነበር፡፡ አንደኛው ለሌላኛው የሚያስበውን ያህል ለራሱ አያስብም ነበር፡፡

አንድ ቀን ላጤው ለባለ ትዳር ወንድሙ እንዲህ አሰበ፡፡ ‹‹ወንድሜ የቤተሰብ ኃላፊ ነው፡፡ ባለቤቱን፣ ልጆቹን፣ የባለቤቱን ወላጆችና የቤቱን ሠራተኞች ማስተዳደር አለበት፡፡ ምርቱን ከእኔ ጋር እኩል መካፈል የለበትም፡፡ እርሱ ከእኔ የሚበልጥ ምርት ማግኘት አለበት፡፡ ነገር ግን አሁን ከእኔ የተሻለ እህል ውሰድ ብለው አይቀበለኝም፡፡ ስለዚህ በሌላ መንገድ መርዳት አለብኝ፡፡››

አውጥቶ አውርዶም በጎተራ ካለው የእርሱ እህል እየወሰደ ማታ ማታ ተደብቆ በወንድሙ ጎተራ ውስጥ ለማስቀመጥ ወሰነ፡፡ ማታ ማታ ተደብቆ በመውጣት ከራሱ ጎተራ ወደ ወንድሙ ጎተራ እህል ይገለብጥ ነበር፡፡ ነገር ግን ጠዋት ጎተራውን ሲያየው እንኳንስ ሊጎድል ካለፈው የበለጠ ሞልቶ ያገኘው ነበር፡፡ ይህም እጅግ ይገርመው ነበር፡፡ ፈጣሪ በጎ ሥራዬን አይቶ እየባረከኝ ነው ብሎም አመሰገነ፡፡

ባለትዳሩም እንዲሁ ለብቻው ‹‹ወንድሜ እንደ እኔ አላገባም፡፡ ለወደፊትም ከባድ ኃላፊነት ይጠብቀዋል፡፡ ትዳር መመሥረት አለበት፣ልጆች መውለድ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ አሁን የሚያገኘው ምርት በቂው አይደለም፡፡እኔ የራሴን ኑሮ አደላድያለሁ፡፡፡ እርሱ ግን ገና አዳጊ ነው፡፡ አሁን እርሱን የሚበልጠውን ምርት ውሰድ ብዬ ብነግረው አይቀበለኝም፡፡ ስለዚህ በድብቅ ልረዳው ይገባኛል›› ብሎ አሰበ፡፡

ወንድሙ ለእርሱ የሚያደርገውን ያላወቀው ባለ ትዳሩ ወንድምም ሊነጋጋ ሲል እየተነሣ ከራሱ ጎተራ ወደ ወንድሙ ጎተራ እህል ይጨምር ነበር፡፡ ጠዋት ሲነሣ ግን ጎተራው ሳይጎድል ያገኘዋል፡፡ ይህም ሁልጊዜ ይገርመዋል፡፡ መስጠቴን ተመልክቶ ፈጣሪ ነው የሞላልኝ እያለም ያመሰግን ነበር፡፡

እንዲህ እያደረጉ ለብዙ ጊዜ ከኖሩ በኋላ በአንድ ሌሊት አንደኛው እህሉን ተሸክሞ ወደሌላው ጎተራ ሲሄድ በድንገት መንገድ ላይ ተገናኙ፡፡ ሁለቱም በነገሩ ተገርመው ተቃቅፈው እየተላቀሱ የነበረውን ነገር ተነጋገሩ፡፡ ከበፊቱ ይልቅም ፍቅራቸው እጅግ ጸና፡፡ እግዚአብሔርም ተገኝቶ ለዚህ ፍቅራቸው መታሰቢያ እንዲሆን በእነርሱ የእርሻ ቦታ ላይ ቤተ መቅደሱ እንደሚሠራ ቃል ገባላቸው፡፡ ንጉሥ ሰሎሞን ታላቁን ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ውስጥ የሠራው በእነዚህ ወንድማማቾች የእርሻ ቦታ ላይ ነው ይባላል፡፡

ከፍቅር መገለጫዎች ዋናው መሟላት ነው፡፡ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ዘርዐ ያዕቆብ ሰው ማለት የሚሟላ ፍጡር ነው ይላል፡፡ ሙሉ እንዲሆን እንጂ ተሟልቶ አልተፈጠረም፡፡ ለመሟላት ሌላ ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ሰው የፈለገውን ያህል የበቃ የነቃ ቢሆንም ሙሉ ሰው ለመሆን ግን ሌላ ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ሰውን በመተቸት፣ ስሕተቱን በመግለጥ፣በመውቀስና ጎደሎነቱን በማሳየት ከምናርመውና ከምናስተካክለው በላይ የጎደለውን በመሙላት እናስተካክለዋለን፡፡ የምንወደው ሰው፣ የምናስብለት ሰው፣ የምናወቀው ሰው፣ ማለት የምናሟላው ሰው ማለት ነው፡፡

በወዳጅና ወዳጅ ባልሆነ መካከል ያለው አንዱ ዋና ልዩነት አብሮ ከመብላት፣ አብሮ ከመጠጣት፣ ልቅሶና ደስታ ከመደራረስ፣ ከመደዋወልና ከመጠያየቅ፣ ከመዛመድና አብሮ ከመኖር የሚመጣ አይደለም፡፡ ሰውን ለምን እናውቀዋለን? ለምንስ ማወቅ እንፈልጋለን? ለምንስ እንቀርበዋለን? ሰው ስለሆንን፣ የሚጠይቅ ኅሊና የሚያስብ ልቡና ስላለን ማወቅ የመጀመሪያው ነው፡፡ ይህንን መከላከል አንችልም፡፡ የግድ ከልዩ ልዩ ምንጮች ስለ አንድ ሰው እናውቃለን፡፡ ይህ ማወቅ ግን መተዋወቅን አይፈልግም፤ መቀራረብንም የግድ አያመጣም፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መተዋወቅ ነው፡፡ ይኼኛው መቀራረብን ያስከትላል፡፡ መስተጋብርን ይፈጥራል፡፡ በዚህ መልኩ የምናገኘው መተዋወቅ ኃላፊነትን ይወልዳል፡፡ የመሟላትን ኃላፊነት፡፡

መተዋወቅ ለመሟላት ካልሆነ ስለ ሰዎች ያለንን ፋይል መቀነስ ያስፈልገናል፡፡ ዐወቅኩት፣ ቀረብኩት፣ እገሌንኮ ዐውቀዋለሁ፣ እቀርበዋለሁ ለማለት መተዋወቅ አያስፈልገንም፡፡ ግንኙነታችን መሟላትን የማያመጣ ከሆነ ዕውቀት መቀነስ ታላቅ ብልሃት ነው፡፡ ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት በሦስት መልኩ ብናደርገው ግንኙነታችን የታሰበበትና የተሟላ ይሆንልናል፡፡

የማናውቃቸው ሰዎች፡፡ እነዚህ ሰዎች ከኛ ጋር ለመተዋወቅም ሆነ በእኛ ለመታወቅ ዕድል የሌላቸው ወይም ዕድል የሌለን ናቸው፡፡ የሚበዙትም እነርሱ ናቸው፡፡ በማወቃችን የምናተርፈው ወይም የሚያተርፉት ነገር ከሌለ አለማወቃችን ምንም ጉዳት የለውም፡፡ ያገኙትን ሰው ሁሉ ስልክ የሚቀበሉ፣ ደግመው የማያገኙትን ሰው የሚተዋወቁ ሰዎች ሊያውቋቸው በማይገቡ ሰዎች ፋይላቸውን የሚያጨናንቁ ናቸው፡፡

ሁለተኛዎቹ የምናውቃቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱ ሊያውቁንም ላያውቁንም ይችላሉ፡፡ ያ ደግሞ የእነርሱ ፋይል ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሥራ ባልደረቦቻችን፣ ጎረቤቶቻችን፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ደንበኞቻችን፣ ዕውቀትን የምንሸምትባቸው ሰዎች፣ በልዩ ልዩ ምክንያት የምናገኛቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ከእነርሱ የምንፈልገው፣ ለእነርሱም የምንሰጠው ነገር ስላለ እናውቃቸዋለን፡፡ አንዳንዶቹንም ማወቅ የግድ ይለናል፡፡ ሌሎቹን ደግሞ አለማወቅ አንችልም፡፡ እነዚህን ሰዎች የግድ መቀራረብ፣ መተዋወቅ፣ ወይም የተለየ ተግባቦት መፍጠር ላያስፈልገን ይችላል፡፡ ግንኙነታችን አንድን ጉዳይ፣ ተግባር፣ ኃላፊነት፣ መሥመር ወይም ደግሞ ሁኔታ መሠረት ያደረገ ነውና፡፡

ሦስተኛው መተዋወቅ የሚባለው ነው፡፡ መቀራረብንና መግባባትን የሚያመጣው፡፡ በውስጡም መዋደድ ያለበት፡፡ ከላይ በሚገኙት ሁለቱ መውደድ እንጂ መዋደድ የለባቸውም፡፡ የማናውቃቸውንም ሰዎች፣ የምናውቃቸውንም ሰዎች ልንወዳቸው እንችላለን፡፡ ግንኙነት የሚያመጣው መዋደድ ግን ላይኖር ይችላል፡፡ እኛ ስለ እነርሱ እናስብ ይሆናል፣ እነርሱ ስለ እኛ እንዲያስቡ አይጠበቅምና መተሳሰብ ላይኖር ይችላል፡፡ በመተዋወቅ ውስጥ ግን ሦስቱም አሉ፡፡ መግባባት፣ መተሳሰብና መዋደድ፡፡ እነዚህ ሦስቱ ነገሮች ወዳጃዊ ኃላፊነትን ያስከትላሉ፡፡ አንዱ ለሌላው በጎ መሆን፣ ስኬትና ደኅንነት ኃላፊነት ይሰማዋል፡፡ ይህ ኃላፊነት ከመጠየቅ፣ ከመለመን ወይም ከመወትወት የሚመጣ አይደለም፡፡ ከመተዋወቅ የሚመጣ ራስ ወሰድ ኃላፊነት ነው፡፡

ለሌላው ሕይወት የማይገደን ወይም ኃላፊነት የማይሰማን ከሆነ የተሻለው መንገድ ዕውቀት መቀነስ ነው፡፡ ለምን እንቀራረባለን? ለምን እንወያያለን? ለምንስ የማንሸከመውን የሰው ‹ውስጥ› እናውቃለን? ለምንስ የማንጋራውን የሰው ችግር እናውቃለን? ለምንስ የማንሞላውን ጉድለት እንሰማዋለን? ለምንስ የማናክመውን ቁስል እንመረምረዋለን? አንዳንድ ሰው አመል ሆኖበት ‹‹ይህ ነገር አይመለከተኝም፣ ይህ ነገር ልሸከመው አልችልም፣ ይህንን ነገር መስማት የለብኝም፣ ይህ ነገር የሰውየው የራሱ ብቻ ነው›› ማለት አይችልም፡፡ በሁሉም ነገር ውስጥ ይገባል፣ ሁሉም ነገር ይመለከተኛል ይላል፣ ሁሉንም ነገር በዝርዝር ያውቃል፣ የሁሉም ሰው ጓዳ ዘው ይላል፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት ኃላፊነት አይወስድም፡፡ ከማወቅና ሲወራ አብሮ ከማውራት፣ ባስ ሲልም ‹ገመናን ከማጋለጥ› ያለፈ ሚናም የለውም፡፡ መሸሽ እንዲህ ካለው ሰው ነው፡፡

የሰሎሞን ቤተ መቅደስ በእነዚህ በመሟላት በሚኖሩ ወንድማማቾች እርሻ ላይ እንደተገነባው ሁሉ የኛም የትዳር፣ የወዳጅነት፣ የጓደኛነት፣ የሥራና የጉርብትና መቅደሳችን በመሟላት ላይ ቢመሠረት ኖሮ፣ ተባብሮ ከመውደቅ ተባብሮ ወደ ማደግ፣ ተያይዞ ከመጠፋፋት፣ ተያይዞ ወደ መመንደግ፤ ጥሎ ከማለፍ ይዞ ወደማለፍ ይሸጋገር ነበር፡፡ ይኼው ሦስቱንም ታላላቅ እምነቶች(እስልምና፣ ይሁዲነትንና ክርስትና) አስተሳሥሯል የሰሎሞን መቅደስ፡፡ ሁሉም እዚያ ቦታ አለው፤ ልብም አለው፡፡ ሁሉም እዚያ ይጸልያል፤ ሁሉም ያንን ቦታ ያከብራል፡፡ መግባባትን ከመነጋገር በላይ ይበልጥ የሚያጠነክረው ‹መሟላት› ነው፡፡ አብሮ መኖርን አብሮ ከመሥራት በላይ ‹መሟላት› የተሟላ ያደርገዋል፡፡ ወዳጅነትን አብሮ ከመብላት በላይ ‹መሟላት› ያጸናዋል፡፡

መሟላት መጓደልን የሚያጠፋ ነው፡፡ በመሟላት የሚኖሩ ወዳጆች የሚሞሉትን ያህል ይሞላላቸዋል፡፡ ሳያጎድሉ መስጠት የሚቻለው በመሟላት ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ተረት እዚህ ላይ ትዝ አለኝ፡፡ በወዳጁ ሀብት የሚቀና አንድ ጎረቤት ከወዳጁ አሞሌ ጨው ይበደራል፡፡ብድሩን ክፈል ሲባል ‹‹አሞሌውኮ ድንጋይ ሆነብኝ›› ብሎ ይመልሳል፡፡ ያ ጎረቤትም ተንኮሉን ቢያውቅም የሚያደርገው ስላልነበረው ዝም ብሎ ኖረ፡፡ አንድ ቀንም ‹እባክህ ሴት ልጅህ ባለቤቴን የድግስ ሥራ ታግዛት›› ብሎ ለመነውና የጎረቤቱን ሴት ልጅ ወሰደ፡፡ ልጂቱም ትመጣለች ተበላ ብትጠበቅ በዚያው ቀረች፡፡ ልጂቱን የወሰደው ጎረቤትም ‹‹ልጂቱማ ዝንጀሮ ሆነችብኝ›› ብሎ መለሰ፡፡ ያም ድሮ በአሞሌው ላይ የሠራውን ያውቅ ነበርና ውጦ ዝም አለ፡፡

ከብዙ ጊዜ በኋላ ሁለቱም ጠዋት ከብት አውጥተው ሲያሠማሩ ተገናኙ፡፡ አስቀድሞም ልጁ ዝንጀሮ ሆነች የተባለበት አባት እንዲህ ብሎ አንጎራጎረ፡-

‹‹ወይ ዘንድሮ ወይ ዘንድሮ

ልጄ ሆነች ዝንጀሮ››

አሞሌው ድንጋይ የሆነበትም

‹‹ወይ ጉባይ ወይ ጉባይ

አሞሌ ሆነ ድንጋይ››

ሲል መለሰ፡፡

የልጂቱ አባትም

‹‹አሞሌስ አለ ከጎታ

የልጄን ነገር እንዴታ›› ሲል ጠየቀ፡፡

የአሞሌው ጌታም፡-

‹‹አሞሌስ ካለ ከጎታ

ልጂቱም አለች ካጎቷ›› ሲል አበሠረው ይባላል፡፡ ስንሟላ እንጂ ስንባላ አናድግም፡፡

© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው፡፡

ባለፈው ጊዜ በተከታታይ የዴር ሡልጣንና ከዚያም ጋር የሚያያዙ ጉዳዮችን ስናነሣ ነበር፡፡ ምን መደረግ አለበት በሚለውም ዙሪያ ስድስት ነጥቦችን አንሥተናል ዛሬ የመጨረሻውን ክፍል እነሆ፡፡

7. ዲያስጶራውን ማንቀሳቀስ

ወደ ኢየሩሳሌም ቅዱሳት መካናትን በመሳለም ረገድ ዲያስጶራ ኢትዮጵያውያን ብዛታቸው እየጨመረ ነው፡፡ በውጭ የሚገኙት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትም ቁጥር ከዓመት ዓመት እጨመረ ይገኛል፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን እንዲሆን ለኢትዮጵያ ታሪክ፣ ቅርስና ዝና ተቆርቋሪ የሆኑትን ሌሎች ወገኖች በማስተባበር ዲያስጶራው የዴር ሡልጣንን  ይዞታ በማስጠበቅ፣ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ በመሥራትና የሕግ ድጋፍ በማድረግ ተግባራት ላይ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ይገባል፡፡

አንዳንድ በአሜሪካን ሀገር የሚገኙና ከሲኖዶሱ የተለዩ ወገኖች ክፍፍሉን ወደ ኢየሩሳሌም ለማዝመትና በቅድስቲቱ ሀገር እርስ በርሳቸው የማይስማሙ ሁለት ማኅበረሰቦችን ለመፍጠር፣ ጥንታዊው ቦታም ተረስቶ እንዲቀር የሚያደርጉትን ጥረት በመግታት በኢየሩሳሌም ቅዱሳት መካናት ጉዳይ የተባበረ እና የማይከፋፈል የኢትዮጵያውያን ድምጽ እንዲኖር ማድረግ ያሻል፡፡

በእሥራኤል የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅዱሳት መካናትን በተመለከተ ዓለም ዐቀፋዊ ሲምፖዝየምና የውይይት መድረክ በማዘጋጀት፣ ዐውደ ርእዮችን በማቅረብ፣ ግብጾች በገዳሙ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ በዓለም ዐቀፍ መድረኮች በመገዳደር፣ ጉዳዩ የዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት እንዲያገኝ በማድረግ፣ የዴር ሡልጣን መነኮሳት እየኖሩበት ያለው የአኗኗር ሁኔታ ከዓለም ዐቀፍ የሰዎች የመኖርና የመኖሪያ ቦታ መብት አንጻር ያለበትን ደረጃ በማሳየት፣ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ለመነኮሳቱ የመኖርና ለመኖር የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች የማግኘት መብት እንዲሟገቱ በመወትወት ዲያስጶራው የማይናቅ አስተዋጽዖ ሊያደርግ ይችላል፡፡

8. ቤተ እሥራኤላውያንን ማንቀሳቀስ

ኢትዮጵያ ውስጥ ለሺ ዓመታት የኖሩ ቤተ እሥራኤላውያን ዛሬ በእሥራኤል ይገኛሉ፡፡ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ፍቅርና ክብር ያላቸው፣ ጉዳያችንንም ጉዳያቸው የሚያደርጉ ቤተ እሥራኤላውያንም አሉ፡፡ የሩሲያ ቤተ ክርስቲያን ከሩሲያ በመጡ ቤተ እሥራኤላውያን የምታገኘውን ድጋፍ ምሳሌ ያደረገ ድጋፍ እንዲያደርጉ ቤተ እሥራኤላውያንን ማስተባበር ይቻላል፡፡

በእሥራኤል ፓርላማ ጉዳዩ እንዲታይ፣ የግብጻውያን ጫና እንዲቀንስ፣ የኢትዮጵያውያን መነኮሳት የመኖር መብት እንዲከበር፣ የቦታው የባለቤትነት ክርክር እንዳለ ሆኖ ነገር ግን በእሥራኤል የኑሮ ደረጃ ለአንድ ሰው የሚያስፈልጉት መሠረታዊ ፍላጎቶች ለዴር ሡልጣን መነኮሳት እንዲሟሉ፣ በዴር ሡልጣን በሚገኙት የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ማኅበረሰቦች መካከል መለስተኛ ውይይቶች እንዲጀመሩ በማድረግ ረገድ ቤተ እሥራኤላውያን የማይተካ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡

9. ጠንካራ የገዳም ሕግ ማውጣት

በእሥራኤል የሚገኙት የኢትዮጵያ ገዳማትና ገዳማውያንን የሚመለከት ጠንካራ ገዳማዊ ሕግ ያስፈልጋል፡፡ ትምህርትና፣ አገልግሎትን፣ ሥራን፣ ጸሎትን፣ የንብረት አስተዳደርን፣ ከገዳም መውጣትንና መግባትን፣ ሀብትን፣ የዲሲፕሊን ሕጎችንና ሌሎች ጉዳዮችን የተመለከቱ ሕጎች ያስፈልጋሉ፡፡ ለመሆኑ ቅዳሴ በፍላጎት ነው የሚከናወነው? ሰው የሚጠፋበት ጊዜ የለም? የሌሊቱ አገልግሎትስ ሰላም ነው? አንድ መነኮስ ጠዋት ኪዳን ካደረሰ ወይም የአገልግሎት ተረኛ ካልሆነ ምን ሲሠራ ነው መዋል ያለበት? ለአስጎብኝነት ተግባርስ የሚመድበው ማነው? ወደ ሌሎች አገሮች የሚደረገው ጉዞስ እንዴት ነው መፈቀድ ያለበት? አንድ መነኮስ ንግድ ማካሄድ ይችላል? ለመሆኑ ሁሉን መነኮሳት የሚመለከት የጸሎት መርሐ ግብር አለ? ወይስ ለጸሎት የሄዱ መነኮሳት ሰሞነኛ መሆን አለባቸው? ገዳሞቻችን ጠንካራ የዲስፕሊን ሕግ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መነኮሳትን በተመለከተ የኢየሩሳሌም ተሳላሚ አውሮፓውያን የጻፏቸው መዛግብት ሁሉ ለጸሎት፣ ለትምህርትና ለፍጹማዊ ምናኔ የሚሰጡትን ቦታ በአድናቆት የሚያነሡ ናቸው፡፡ በ18ኛው መክዘ በሊባስ የነበረ አንቶንዮ የተባለ ፍራንቺስካን ስለ ኢየሩሳሌም መነኮሳት በጻፈው አንድ የጉዞ ማስተዋሻ ላይ ‹‹ወደ ጎልጎታ በሚወስደው መንገድ ላይ በአነስተኛ ቤተ መቅደሶች የሚገለገሉ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ፡፡ እነዚህ መነኮሳት ወደ ሊባኖስ በየዓመቱ ይዘልቃሉ፡፡ እነርሱ ሲመጡ ለመባረክ የኛ ምእመናን ሳይቀሩ ትተውን ይሄዳሉ፡፡ ልብሳቸው አዳፋ ነው፡፡ አንዳንዶቹም ቆዳ ይለብሳሉ፡፡ ሕዝቡ ልብሳቸውን ቀድዶ ይወስደዋል፡፡ ለእነርሱም የሚበቃቸውን እህል ይሰጧቸዋል፡፡ የሚመጡበት ወቅት እዚህ በጉጉት ነው የሚጠበቀው›› ይላል፡፡ ይኼ ነገር ዛሬ እንጥፍጣፊውስ አለ?

10. የተቀናጅ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ

ዴር ሡልጣንንና ሌሎች በቅድስት ሀገር የሚገኙ ቦታዎቻችንን በተመለከተ የሚነሡ ነገሮች ሁሉ ድንገቴዎች ናቸው፡፡ አሁን ባሳለፍነው የትንሣኤ በዓል እንኳን ስምንት መቶ ሺ ዶላር ስለሚያወጣ ቦታ ግዥ ሲነገር ነበር፡፡ ከዚህ በፊትም ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የተጠመቀበትን ቦታ ስለመግዛት ይነሣ ነበር፡፡ ጃንደረባው የተጠመቀበት ቦታ ግዥ የት እንደደረሰ ሳይታወቅ አሁን ደግሞ ሌላ ሃሳብ መጣ፡፡ የዚህኛው ግዥም ቢሆን ዝርዝር ፕሮጀክቱ አልተገለጠም፡፡ እንዴው ብቻ ገንዘብ አዋጡ ነው የተባለው፡፡

የኢየሩሳሌም ቅዱሳት መካናትን በተመለከተ ሊኖረን የሚገባው አሠራር የተቀናጀና የታሰበበት ስትራቴጂያዊ ዕቅድን የተከተለ መሆን አለበት፡፡ አባቶች በተቀያየሩ ቁጥር የማይቀየር፣ በሚገባ ታስቦበት ቢያንስ ለዐሥር ዓመት እንዲያገለግል ሆኖ የተዘጋጀ፣ የሁሉንም ተሳትፎ ያካተተ መሆን ይገባዋል፡፡ አንዱ ተነሥቶ ይህንን እንገንባ፣ ሌላው ተነሥቶ ያኛውን እንግዛ፣ ሌላው ተነሥቶ ይህን እናሠራ ማለት የለበትም፡፡ የገዳሙ የወደፊት ዕድገት፣ ያሉበት ችግሮች፣ ችግሮቹን እንዴት በቅደም ተከተል መፍታት እንደሚቻል፣ ለዚህ የሚያስፈልገው ወጭ፣ ወጭው ከየት እንደሚሸፈን፣ የሚሠራው ነገር የአስተዳደሩ ጉዳይ፣ በሚገባ ሊመለሱ ይገባቸዋል፡፡

በጣም የሚገርመው ነገር ኢየሩሳሌም ላይ ሕዝቡን አስተባብሮ ዘመን የሚሻገር ሥራ መሥራት ሲቻል ምእመናን ሁልጊዜ የሚነገራቸው በአልዓዛር ለሚገኙ አረጋውያን ጋቢ እንዲያመጡ ነው፡፡ ለምን ዘላቂ በሆነ መንገድ ችግራቸውን አንፈታውም? ዛሬ ወጣት መስለው የሚታዩት መነኮሳትስ ነገ እዚያ አይደለም እንዴ የሚጦሩት? ያ ሁሉ ጋቢ እዚያ ምን እንደሚሠራ መድኃኔዓለም ይወቀው፡፡

በአሁኑ ጊዜ አስጎብኝዎቹ በዝተዋል፡፡ ሁኔታውን ስናየው የማስጎብኘቱ ሥራ ከመጀመሪያው ትውልድ ወደ ሁለተኛው ትውልድ እየተሸጋገረ ነው፡፡ ከዛሬ አርባና ሃምሳ ዓመታት በፊት ማስጎብኘቱን የጀመሩት አካላት በአዳዲስ ትኩስ ኃይሎች እየተተኩ ነው፡፡ ይህንን ዕድል በተቀናጀ ስትራቴጂ መምራት ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ አስጎብኝ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ዐውቆ፣ ለዚያም ተዘጋጅቶ እንዲሠራ ያደርገዋል፡፡ ለተሳላሚነት የሚመጣው ሕዝብም በየዓመቱ በተሠራው ላይ እየተወያየ በቀረው ላይ እየጨመረና የራሱን ኃላፊነት እየወሰደ እንዲያበረክት ያደርገዋል፡፡ አንድ ትውልድ ሲያልፍ አሻራውን አስቀምጦ እንዲያልፍም ያደርጋል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ወደ ኢየሩሳሌም በአዲስ መንገድ ጉዞ የተጀመረበትን ሃምሳኛ ዓመት እያከበርን ባለንበት ዘመን ላይ ሆነን የሠራነውን ሥራ ብንገመግመው ሕዝብ ከማጓጓዝ የዘለለ ውጤት አናገኝበትም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ገዳሞቻችን የዕጣን መቀመሚያ፣ የሻማ መሥሪያ፣ የጠበል ማሸጊያ፣ የቅብዐ ቅዱስ ማዘጋጃ፣ የቅዱሳት ሥዕላት ማተሚያ፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ማዘጋጃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ያ ሁሉ ተሳላሚ ወደ ገዳሞቻችን ሲሄድ የሚገዛው ቅብዐ ቅዱስ፣ ዕጣንና ጠበል ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በርካሽ ተገዝቶ የሚከፋፈል እንጂ በኛው ቤተ ክርስቲያን የተዘጋጀ አይደለም፡፡ ይህ አሳዛኝም አሳፋሪም ነው፡፡ ሁሉም ነገር እያለ፣ የሰው ኃይሉም ተከማችቶ፣ ለመሥሪያ የሚሆን ቦታ ሳይጠፋ የሰው ንብረት ማከፋፈያ እንደመሆን ያለ አሳዛኝ ነገር አልነበረም፡፡

ሲሆን የኢየሩሳሌም ገዳማት ለሀገር ውስጥ አብያተ ክርስቲያናት መትረፍ ነበረባቸው(‹ጳጳሱ ቄስ ናቸው ወይ ቢሉ ተርፏቸው ለሰው ይናኛሉ› እንደተባለው) ካልሆነ ደግሞ ቢያንስ ለራሳቸውና ለተሳላሚዎች የሚተርፍ ነገር መኖር ነበረበት፡፡ በጣም የሚገርመው ነገር በገዳሞቻችን የገዳማቱን ታሪክ እንኳን የሚገልጥ በራሪ ወረቀት አይገኝም፡፡ ፖስት ካርድማ በሥዕለትም አታገኙ፡፡ በሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት ያያችሁ እንደሆነ እስከ 11 በሚደርሱ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ገዳማቱን የሚገልጡ ወረቀቶች ታገኛላችሁ፡፡ አንድ ሸክል(የእሥራኤል ገንዘብ) አስቀምጡና ውሰዱ ይሏችኋል፡፡ ሞያ ከጎረቤት መማር ለምን እንዳቃተን እንጃ፡፡

ባለፈው በክፍል አንድ ላይ ይህንን ሃሳብ በመጠኑ ተነሥቶ ነበር፡፡ የገዳሙ መነኮሳት በምሳ ሰዓት ተሰብስበው በወሰኑት መሠረት በሰጡት መልስ ግን የኛ ሥራ ጸሎት እንጂ ተግባረ ዕድ አይደለም ብለዋል፡፡ ለዚህ እኔ መልስ ከምሰጣቸው የመነኮሳት አባቶች ከሚባሉት አንዱ አባ ስልዋኖስ ያደረገውን ልንገራቸው፡፡ አንድ ወንድም አባ ስልዋኖስን ለማየት ወደ ደብረ ሲና ወጣ፡፡ በዚያ የሚገኙ ወንድሞችም ተግተው ሲሠሩ ተመለከተና ለአባ ስልዋኖስ ‹‹ለሚጠፋ ምግብ አትድከሙ፣ ማርያምስ የማይቀሟትን ዕድል መረጠች ተብሏል›› አለው፡፡ አባ ስልዋኖስም ዘካርያስ የተባለ ረድኡን ጠርቶ ‹‹ይህንን ወንድም መጽሐፍ ስጠውና በበኣት ውስጥ አስቀምጠው›› አለና አዘዘው፡፡

ያ እንግዳ ወንድምም ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ምናልባት አንድ ሰው ለማዕድ ይጠራኝ ይሆናል ብሎ ጠበቀ፡፡ የጠራው የለም፡፡ የሚጠራው ሲያጣ ወደ አባ ስልዋኖስ ሄደና ‹‹ዛሬ ወንድሞች ምግብ አይመገቡም እንዴ›› ሲል ጠየቀው፡፡ አባ ስልዋኖስም ተመግበው መጨረሻቸውን ነገረው፡፡ ያ ወንድምም ‹‹ታድያ እኔን ለምን አልጠሩኝም›› አለው፡፡ አባ ስልዋኖስም ‹‹አንተ መንፈሳዊ ስለሆንክ ይህንን መሰሉን ምግባር አትፈልገውም ብለን ነው፤ እኛ ግን ሥጋውያን ስለሆንን እንመገባለን፡፡ የምንሠራውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ አንተ ግን የማይቀሙህን ዕድል መርጠሃልና ቀኑን ሙሉ መጽሐፍ ብቻ ታነባለህ፡፡ አላፊ ጠፊ ምግብ አያስፈልግህም›› አለው፡፡ ይህንን ሲሰማ ያ ወንድም በግንባሩ ተደፍቶ ‹‹ይቅር በለኝ›› አለው፡፡ አባ ስልዋኖስም ‹‹ለማርያም ማርታ ታስፈልጋታለች፤ ማርያም የተመሰገነችው በማርታ ምክንያት ነውና ለማርታ ምስጋና ይግባት›› አለው፡፡

ከትናንት ብንዘገይ ከነገ መቅደም አለብንና ስንፍናውን አስወግደን ዛሬ ብንነሣ እንደርሳለን፡፡ በገዳማቱ ውስጥ ነገሩ እንደ እግር እሳት የሚለበልባቸው፣ ለተልዕኮ ለመፋጠን የማይሰለቹ፣ ገዳማቸውን ከሌሎች እኩል ሆኖ ለማየት የሚተጉ ብርቱ መነኮሳት መኖራቸውን ማንም ያየዋል፡፡ ምንም ጥቂት ቢሆኑ፡፡ እነርሱን አንቀሳቃሽ ሞተር አድርጎ ሥራውን መሥራት ነው፡፡ ኢየሩሳሌም ላይ እንደዚህ የተቀናጀና መሥመር ያለው ሃይማኖታዊ ሥራ መሥራት የሀገር ቤቶቹን ገዳማትና አድባራት መንፈስም የሚቀሰቅስ ይሆናል፡፡ እነዚህ አባቶች ነገ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታላላቅ ኃላፊነት ላይ ሲመደቡም በኢየሩሳሌም የለመዱትን እዚህ ሀገር ቤትም እንዲተገብሩት ያደርጋቸዋል፡፡

ማጠቃለያ

የኢየሩሳሌም ገዳማት ጉዳይ በማንም እጅ ላይ አይደለም፡፡ በራሳችን እጅ ላይ ነው፡፡ የደከምነውም እኛ ነን የምንበረታውም እኛው ነን፡፡ ግብጾች በደንባራ በቅሎ ላይ ቃጭል ይጨምራሉ እንጂ ደንባራዋን በቅሎ አያመጧትም፡፡ በብኾር ላይ ቆረቆር ያመጣሉ እንጂ ብኾሩ የኛው ነው፡፡ እኛን ለመጥረቢያ እጀታ ሆኖ የፈጀን የራሳችን ጠማማ ነው እንዳሉት ዛፎች ችግሩ እኛው ነን፡፡ ስለዚህም ቁጭ ብሎ መነጋገር፣ መፍትሔ መፈለግና ዕቅድ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ዓለም በፈጣን ሁኔታ እየተቀያየረ ነው፤ ሁል ጊዜ እየየ አያዋጣም፡፡ የሚያዋጣው መንፈሳዊ ሆኖ፣ ሠርቶ፣ ተግቶና ዓለምን አሸንፎ መለወጥ ነው፡፡ ለጊዜው እኔም በዚሁ ላብቃ፡፡ ጽሑፉ ከተጀመረ በኋላ የገዳሙ መነኮሳትና ሌሎች ምእመናን የላኩልኝን ሰነድና መረጃ አጠናክሬ ደግሞ ሌላ ጊዜ እመለሳለሁ፡፡ ቸር ይቆየን፡፡

ከዚህ በፊት በዚሁ ጦማርና በልዩ ልዩ ሚዲያዎችም በተነገረው መሠረት ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው መልካም ሠርተዋል የተባሉ ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያን ተጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ እጅግ የተሻሉትን ለመምረጥ የመጨረሻው ሂደት እየተከናወነ ነው፡፡

መርሐ ግብሩ የሚካሄደው ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን ከቀኑ በ 8 ሰዓት አዲስ አበባ ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው እሊሌ ሆቴል ሲሆን፣ ተሸላሚዎች፣ ተጋባዥ እንግዶች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎችም በተገኙበት ይከናወናል፡፡ ሽልማቱ የሚከናወነው በሰባት ዘርፎች ነው፡፡

  1. የሀገራዊ ዕርቅና ሰላም ዘርፍ

  2. የበጎ አድራጎት(ሰብአዊነት) ዘርፍ

  3. የኪነ ጥበብ/ ሥነ ጥበብ ዘርፍ

  4. ግብርናና ኢንዱስትሪ ዘርፍ

  5. መንግሥታዊ ኃላፊነትን በብቃት የመወጣት ዘርፍ

  6. ቅርስ ጥበቃ፣ ባሕልና ቱሪዝም ዘርፍ

  7. ሳይንስና ቴክኖሎጂ/ ጥናትና ምርምር ዘርፍ

በእነዚህ ዘርፎች የተመረጡ ተሸላሚዎች በመጨረሻ መራጮች ድምጽ ከተሰጠባቸው በኋላ ይታወቃሉ፡፡ የሽልማቱ ዋና ዓላማ ገንዘብ አይደለም፡፡ በጎ ሰዎችን በማበረታታት፣ ለበጎ ሰዎችም ዕውቅና በመስጠት ለሀገር ሰው ማትረፍ እንጂ፡፡ ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያ ወዳጆች የሆኑ ጀግኖችን ማሳወቅ ሥራቸውም ለትውልድ አርአያ እንዲሆን ማድረግ እንጂ፡፡ የመመሰጋገንንና የመበረታታትን ባሕልም ማበልጸግ እንጂ፡፡

በዕለቱ መገኘት ለሚፈልጉ በቅርቡ የመግቢያ ካርዱ የሚገኝበትን መንገድ እንጠቁማለን፡፡

5. መዝየም

ኢትዮጵያውያን አባቶችና ምእመናን በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም መንፈሳዊ ተጋድሎ ለመፈጸምና መንፈሳዊ ርስትን ለትውልድ ለማኖር ታላቅ መሥዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ይህንን የዘመናት ተጋድሎ የሚያሳይ አንዳች ሙዝየም ግን የለንም፡፡ የገዳሞቻችንን ታሪክ፣ የተጻጻፍናቸውን ደብዳቤዎች፣ በየጊዜው ከሀገር ቤት የተላኩትን መጻሕፍትና ሌሎች ንዋያተ ቅድሳት፣ የዘመናቱን አሻራ የሚያሳዩ የሥዕልና የፎቶ ግራፍ መረጃዎች፣ ካርታዎች፣ ተጓዦችና ታሪክ ጸሐፊዎች የከተቧቸው ማስረጃዎች፣ በየዘመናቱ የተሰጡ ስጦታዎችን የሚያሳዩ መዛግብት፣ የተሾሙ ራይሶችንና ሊቃነ ጳጳሳትን የሚያሳዩ ዝርዝሮችና ፎቶዎች፣ የተሳላሚዎችን ሁኔታ የሚያሳዩ ፎቶዎችና መዛግብት የተከማቹበት፤ ከዚያም አልፎ የእናት ቤተ ክርስቲያንን ማንነት፣ ታሪክና ቅርሶች የሚያሳይ አንድ ታላቅ ሙዝየም በደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ግቢ ውስጥ ወይም በአካባቢው ያስፈልገናል፡፡

ይህ ሙዝየም ሦስት ጥቅሞች ይኖሩታል፡፡ በአንድ በኩል ከሁለት ሺ ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን የቅድስት ሀገር ርስታችንን ታሪክ በተጨባጭ የምናሳይበት፣ ከንግግር የዘለለ ማስረጃ እንዲኖረንና ያንንም ለዓለም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንድናሳይ ያደርገናል፡፡ ከኢየሩሳሌም ከተማ አንዱ የቱሪስት መዳረሻ በመሆንም የኢትዮጵያውያንን የተጋድሎ ታሪክ ለጎብኝዎች እናሳይበታለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኢየሩሳሌም የመላው ዓለም አማኞች መናኸሪያ በመሆኗ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለማስተዋወቂያ ወሳኝ መድረክ ይሆናል፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነው ኢትዮጵያንና ቤተ ክርስቲያንዋን በተለይ ለምዕራቡ ዓለም ያስተዋወቋት የኢየሩሳሌም(በተለይም የዴር ሡልጣን) ገዳማት አባቶች ነበሩ፡፡

ሦስተኛ ደግሞ ለገዳሙ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ይሆናል፡፡ የዓመቱን ፋሲካ ጠብቆ ጧፍ ከመሸጥ ይልቅ ራቅ አድርጎ አስቦ ታሪካችንን የሚያሳዩ ፖስት ካርዶችን፣ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱና ስለ ኢየሩሳሌም ገዳማት የተጻፉ መጻሕፍትን፣ የጎብኝዎች መመሪያዎችን(Tourist Guide)፣ ኢትዮጵያዊ ትውፊት ያላቸው ቅዱሳት ሥዕላትን፣ የላንቲካ ዕቃዎችን(የሀገሪቱን ባሕል፣ የእምነት ሥርትዓቷንና ታሪኳን የሚያሳዩ ሰሐኖች፣ ቲሸርቶች፣ ኩባያዎች፣ የወግ ዕቃዎች፣  ጌጣ ጌጦች) ለቱሪስቶች በመሸጥ ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት ያስችላል፡፡

እስካሁን በታየው ልማዳችን ዕቃ ቤት እንጂ ሙዝየም በብዛት የለንም፡፡ በሀገር ቤት እንኳን ያሉን ሙዝየሞች ከታሪካችንና ከቅርሳችን ጋር ሲወዳደሩ ዓባይን በጭልፋ የሚያስብሉ ዓይነት ናቸው፡፡ በኢየሩሳሌም የሚገኙ አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ሙዝየም ብቻ ሳይሆን የጥናትና ምርምር ተቋማት ጭምር እንዳሏቸው የኢየሩሳሌም የቱሪዝም መሥሪያ ቤት የሚያሳትማቸው የቱሪስት መርጃ መጻሕፍት ያሳያሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ የቅርብ ዘመን ታሪክ ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት እንኳን ቱሪስት እንደ ጎርፍ የሚፈስበት ሙዝየም አላቸው፡፡ ለተመራማሪዎችም ኢየሩሳሌምን የተመለከቱ መረጃዎችን በመሸጥ ገቢ ያገኛሉ፡፡

የአርመን ሙዝየም ሕንጻ
ወደ ኢየሩሳሌም ምእመናንን የሚያጓጉዙ ተቋማት ከገዳማቱ አስተዳደር ጋር በመመካከር ሊያከናውኗቸው ከሚገቡ ነገሮች አንዱ የሙዝየሙ ጉዳይ ነው፡፡ ‹ታሪክ እንደ ነጋሪው ነው› በሚል ያረጀ ብሂል ስለ ራሳችን ታሪክ ለእኛ እንኳን የሚገርመንን ዓይነት ያልነበረ ታሪክ እንደነበረ እየተደረገ፣ የነበረውም እየተዘነጋ እየቀረበልን መሆኑን ካየን ለቱሪስቶችማ ምን ሊነገር እንደሚችል መገመት ነው፡፡

ይህንን ሙዝየም እንዴት ባለ መንገድ ልናቋቁመው፣ ልናካሂደው ምን ምን እንዲሠራ ልናደርገው እንደምንችል በሚገባ በዓይን ዓይቶ ለመረዳት በግሪክ ፍጥሞ ደሴት የሚገኘውን የቅዱስ ዮሐንስ ገዳም መጎብኘቱ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ያም ካልተቻለ በኢየሩሳሌም አሮጌው ከተማ የሚገኙትን የአርመንንና የግሪክን ፓትርያሪኬት ሙዝየሞች ማየቱ በቂ ሊሆን ይችላል፡፡

6. ሴሚናሪ

ምንም እንኳን የገዳማቱ መነኮሳት የቀድሞ አባቶች ገዳሙን የጠበቁት ተምረው አይደለም ቢሉም አባባሉም ስሕተት ነው፣ ትምህርትም የግድ ነው፡፡ የቀድሞ አባቶች አልተማሩም የሚለው ብሂል ከሁለት ነገሮች የሚመነጭ ነው፡፡ አንድ ካለማወቅ ሁለትም ከንቀት፡፡ የቀድሞ አባቶች ለትምህርት ታላቅ ቦታ እንደነበራቸው ባከማቿቸው መጻሕፍት ብቻ እንኳን ማወቅ ይቻላል፡፡ እንኳን የክርስትና መጻሕፍት የአይሁድ፣ የግሪክ፣ የሂንዱስታንና የእስልምና መጻሕፍትን ሳይቀር ወደ ግእዝ እየተረጎሙ አስቀምጠውልናል፡፡ ተተኪዎቻቸው እንደነ እርሱ ዕውቀት ወዳጆች መስለዋቸው፡፡ ታላቁ ንጉሥና የዴር ሡልጣን ገዳም ባለ ውለታ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ‹‹መጽሐፈ ብርሃን›› በተሰኘው መጽሐፉ ‹‹እስመ ጽሙዐን ለትምህርት ብሔረ ኢትዮጵያ ኄራን – ምርጦቹ የኢትዮጵያ ሰዎች ትምህርትን የተጠሙ ናቸው›› እንዳለው ኢትዮጵያውያን ትምህርትን የተጠሙና ለዕውቀት ማንኛውንም ዓይነት ዋጋ የሚከፍሉ ነበሩ፡፡

ዛሬ ባለው ዓለም ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ቅኔ፣ ቅዳሴ፣ ዝማሬ፣ ትርጓሜና አቋቋም እጅግ አስፈላጊዎች ቢሆኑም ብቻቸውን ግን ወንዝ ሊያሻግሩን አይችሉም፡፡ ዛሬ በልዩ ልዩ የሀገራችንና የዓለም ቋንቋዎች ማስተማርና መጻፍ የሚያስፈልግበት፣ ጥንታዊ ሀብታችንን በዘመናዊ መንገድ ማቅረብ የሚጠየቅበት፣ ሕዝቡን ለመድረስ ልዩ ልዩ ሚዲያዎችን መጠቀም የግድ የሚልበት፣ ከትውልዱ ጋር ለመግባባትና የትውልዱን ጥያቄ ለመመለስ ሁለገብ ዕውቀት የሚያሻበት፣ ዘመን ነው፡፡

የኢየሩሳሌም ገዳማት አባቶችና እናቶች ከላይ በተጠቀሱት ነገሮች የሠለጠኑ፣ በሚገባ የታጠቁና በሁለት በኩል የተሳሉ ሰይፎች እንዲሆኑ ግድ ይላቸዋል፡፡ አንድም ‹‹መልክ ከእግዚአብሔር ሞያ ከጎረቤት›› ነውና ከጎረቤቶቻቸው ልምድ ለመቅሰም ስለሚችሉ፤ አንድም የትምህርት መርጃዎችን ከልዩ ልዩ ተቋማት ለማግኘት ቀላል ስለሆነ፤ አንድም በአንድ አካባቢ መኖራቸው በፈረቃ ለመማር ስለሚያስችላቸው፤ አንድም ልዩ ልዩ ቋንቋዎችን ለመማር ኢየሩሳሌም አመቺ በመሆኗ፡፡ ሌላው ቀርቶ በሀገር ቤት የሚገኙ መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶቻችንንም ከኢየሩሳሌም ትምህርት ቤት ጋር በማቀናጀት የተሻሉ ለሚባሉ ተማሪዎች ስኮላርሺፕ መስጠት ይቻላል፡፡

ዛሬ ዛሬ ከፍ አድርጎ ማሰብ እየጠፋ ነው መሰል የአባቶቻችን ሃሳብ አሜሪካና አውሮፓ መሄድ፣ ከግሪክ ንዋያተ ቅድሳት ማምጣት፣ ቤት መሥራት፣ ዘር መዝራት እየሆነ ነው፡፡ ነገ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትፈልገኛለች፣ ነገ ወደ ኢትዮጵያ ኮሌጆች ሄጄ አስተምራለሁ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን እተረጉማለሁ፣ ሕዝቡን በወንጌል እደርሳለሁ፤ የመነኮስኩበትን ገዳም ኑሮና አሠራር አሻሽላለሁ፣ ቤተ ክርስቲያኔን በዓለም መድረክ አስጠራለሁ፣ ብሎ ከፍ አድርጎ የሚያስብ እያጣን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያናችን ጉዳት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የኢየሩሳሌም መነኮሳት የነበራቸውን ቦታ ባለፈው ጊዜ በመጠኑ ጠቅሰነዋል፡፡ የኢትተጵያ ታላላቅ ገዳማት አባቶች አብዛኞቹ ኢየሩሳሌም መጥተዋል፡፡ እዚህ ያዩትንና የሰሙትን ይዘው በሀገራቸው ተግብረውታል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትንና ንዋያተ ቅድሳትን ወደ ሀገር አምጥተዋል፡፡ ሌላው ቢቀር አፈሩንና የዮርዳኖስን ጠበል እየያዙ በመምጣት ከገዳሞቻቸው አፈርና ጠበል ጋር አዋሕደውታል፡፡ እንደ ቅዱስ ላሊበላ ያሉትም ምድራዊትና ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን ከተመለከቱ በኋላ ‹ከመዝ ግበር› በተባሉት መሠረት የኢየሩሳሌምን አምሳል በሀገራቸው ሠርተዋል፡፡

ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ከኢየሩሳሌም መነኮሳትና መነኮሳዪያት ብዙ ትጠብቃለች፡፡ በዕውቀት የበሰሉ፣ በቋንቋ የተካኑ፣ ዓለም ዐቀፋዊ ልምድ ያላቸው፣ በሁለት በኩል የተሳሉ ሆነው እንዲያገለግሏት፡፡ ለዚህ ደግሞ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሴሚናሪ ያስፈልጋል፡፡ የተቋሙን አመሠራረትና አሠራር ለመረዳት ከሌሎቹ ልምድ መቅሰም ነው፡፡ ወጭውን ለመሸፈን ደግሞ ምእመናን አንድም ሁለትም ተማሪ ስኮላርሺፕ እንዲሰጡ ማስረዳት ነው፡፡ ዛሬ ሰው ያጣንበት ዘመን ስለሆነ ሰው ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለመርዳት ምእመናን ዝግጁ ናቸው፡፡ ብቻ የቆረጠ፣ የገባውና፣ ዓላማ ያለው ሰው ይኑረን እንጂ፡፡

አሁን አሁን በዓለም ዐቀፍ መድረኮች ቤተ ክርስቲያንን ወክሎ በብቃት ሊሳተፍ የሚችል ሰው እያጣን ነው፡፡ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል የእምነት ውይይት (Inter – church dialogue) ይደረጋል፤ በልዩ ልዩ እምነቶች መካከልም ውይይት ይደረጋል(Inter – faith dialogue)፣ የአፍሪካና የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ይደረጋል፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጉባኤ ይደረጋል፤ በሌሎች የዓለም መድረኮችም የሃይማኖት አባቶች ይጋበዛሉ፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመተርጎም ሥራም ከግሪክ፣ ከዕብራይስጥ፣ ከላቲንና ዐረብ ጋር ማነጻጸር ይጠይቃል፤ ለዚህ ሁሉ ትምህርትና ሥልጠና ወሳኝ ነው፡፡ ለዚህ ነው ኢየሩሳሌም ላይ አንድ ደረጃውን የጠበቀ፣ ሰው ሊያፈራ የሚችል፣ ሴሚናሪ ይኑረን የምለው፡፡

(ይቀጥላል) 

ኢየሩሳሌም

ከመቶ ዓመታት በፊት ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ አባቶች

click here for pdf

ከዚህ በፊት ለኢየሩሳሌም ገዳማችን ሊደረጉ የሚገቡ ዐሥር ነገሮችን አቀርባለሁ ባልኩት መሠረት ሦስቱን አቅርቤያለሁ፡፤ አራተኛውን እነሆ

4. ጠንካራ የምልመላ መሥፈርት ይኑር

አባቶቻችን ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ ሲያደርጉ ሁለት ሺ ዓመት አልፏቸዋል፡፡ በየዘመናቱ ከአውሮፓና ከእስያ የመጡ ተጓዦችና ታሪክ ጸሐፊዎች የኢትዮጵያውያን መነኮሳትን የፈቃድ ድህነት፣ የጸሎት ትጋት፣ ተአምር አድራጊነት፣ ሊቅነት፣ መንፈሳዊነትና ፍጹማዊ ምናኔ በአድናቆት ጽፈውታል፡፡ እነዚያ መነኮሳት ወደ ቅድስት ሀገር የመጡት ለአራት ዓላማዎች ነበር፡፡

  1. ከቅዱሳን ቦታዎች በረከት ለማግኘት፣

  2.  ፍጹም የሆነ ምናኔን ለመኖር፣

  3. ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ዕውቀትን ለመገብየትና

  4. የኢትዮጵያውያንን ቅዱሳት መካናት ለመጠበቅ፡፡

ያኔ የዐረብ ሀገሮችን፣ የሱዳንንና የሳዑዲን በረሃዎች፣ የዐረቦችንና የቱርኮችን አገዛዝ፣ ውኃ ጥሙንና መከራውን አልፎ ለመምጣት መንፈሳዊ ጽናትና የጸና እምነት ያስፈልግ ስለነበር ለክፉ የሚሰጥ ሰው ይህንን ሁሉ ችሎ ወደ ኢትዮጵያውያን ገዳማት አይመጣም ነበር፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በመነኮሳቱ መካከል መለያየትና መከፋፈል እንደነበረ እቴጌ ጣይቱ መነኮሳቱን ‹‹እባካችሁ አትጣሉ፣ አንድ ሁኑ›› እያሉ የጻፉት ደብዳቤ ይነግረናል፡፡ ለገዳሙ በጎ የሠሩ አንዳንድ አባቶችም ዕጣ ፈንታቸው መሰደድ፣ መገፋትና መባረር እንደነበረ የነ አባ ወልደ ሰማዕት ታሪክ ይነግረናል( በነገራችን ላይ የአባ ወልደ ሰማዕትን አስደናቂ ታሪክና በገዳሙ መነኮሳት የደረሰባቸውን ግፍ በቀጣይ ሳምንት እመለስበታለሁ፡፡ በዘመናቸው የዓይን ምስክሮች የነበሩ ሁለት ሰዎች የጻፉትን፣ ሁለት ሌሎች ሰዎች ደግሞ ከእርሳቸው ሰምተው ለትውልድ ያስቀመጡትን ታሪክ አግኝቻለሁ)

ዛሬ መነኮሳትን ለኢየሩሳሌም ገዳማት የሚመድበው ጠቅላይ ቤተ ክህነት ነው፡፡ ስለዚህም በመንገድ የሚደርስ ፈተና፣ በኑሮ የሚደርስ ችግር፣ ረሃብና እርዛት የለም፡፡ መከራ የሚያጠራው ሰውም የለም፡፡ ለዚህም ነው ወደ ኢየሩሳሌም ገዳማት ለሚመደቡ አባቶችና እናቶች ጠንካራ የምልመላ መሥፈርት ያስፈልጋል የምንለው፡፡ መንፈሳዊነታቸው፣ ለጸሎት ያላቸው ትጋት፣ ዐቅመ ደካሞችን ለመርዳት ያላቸው ፍላጎትና ብርታት፣ ለመማርና ዕውቀት ለመሸመት ያላቸው ጉጉትና ዐቅም፣ በዓላማቸው ለመጽናትና የመጡበትን ግዳጅ ለመፈጸም ያላቸው ዝግጁነት መታየት አለበት፡፡

ከዘረኛነት የነጹ፣ ነጋ ለኪዳን መሸ ለቁርባን የሚሉ፣ ቅዳሴና ሰዓታት የማይሰለቻቸው፣ በሕይወት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆኑ፣ ንጽሕናቸውንና ቅድስናቸውን ጠብቀው በመኖር ነገ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለምትፈልጋቸው መዓርግ ዝግጁ የሆኑ፣ አፍቅሮ ነዋይ የራቀላቸው፣ ቤት ልሥራ ዘር ልዝራ የማይሉ እንዲሆኑ ጠንካራ የመመልመያ መሥፈርት ያስፈልጋል፡፡

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የኢየሩሳሌም መነኮሳት የሠሯቸው ሥራዎች የሚያስደንቁ፣ የሚያኮሩና እንኳን እኛ ልጆቻቸውን ሌሎችንም ያስገረሙ ነበሩ፡፡ ዛሬ አንዳንድ መነኮሳት ‹‹እኛ ለጸሎት እንጂ ዕውቀት ለመሸመት ወይም ተግባረ ዕድ ለመሥራት ኢየሩሳሌም አልመጣንም›› ቢሉም በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ግን ዕውቀትና ገዳማዊ ሕይወት ተለያይተው አያውቁም፡፡ ሌላው ቀርቶ በ13ኛው መክዘ ምርጦቹ ስምንት መቶ መነኮሳት በመንፈሳዊ ሕይወት በስለው፣ በምንኩስና ተክነው፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀት ተራቅቀው የወጡት ከሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም መሆኑን መርሳት አይገባም፡፡ መካከለኛዋን፣ ምዕራብና ምሥራቅን ብሎም ደቡብ ኢትዮጵያን ተካፍለው ያስተማሩት አሥራ ሁለቱ ንቡራነ ዕድ ተምረውና ተቀርጸው የወጡት ከደብረ ሊባኖስ ነበር፡፡ በኤርትራና በትግራይ ያስተማሩት አምስቱ ከዋክብትና ሰባቱ ከዋክብት የሚባሉት ሐዋርያውያን የተገኙት ከደብረ በንኮል ነበር፡፡


ታላላቅ የቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳት መጻሕፍት ከግሪክ፣ ከዐረብኛ፣ ከዕብራይስጥና ከላቲን ወደ ግእዝ የተተረጎሙት በዴር ሡልጣን መነኮሳት ትጋት መሆኑ ተረስቶ ቋንቋ አለማወቅ ዛሬ አንዳንዶቹን ያኮራቸዋል፡፡ በቅዱሳት መጻፍት የአንድምታ ትርጓሜ ላይ የኢየሩሳሌም ገዳማት መነኮሳትን አስተዋጽዖ ለማወቅ የእሥራኤልን ቦታዎች ከጎንደር ቦታዎች አነጻጽረው የተረጎሙበትን ዘይቤ ማየቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ የነበሩት አባቶች ጸሎት ብቻ አልነበረም ተግባራቸው፡፡ ዙሪያ መለስ ነበሩ፡፡ በዐፄ ናዖድ ዘመነ መንግሥት(1487-1500 ዓም) ወደ ኢየሩሳሌም ከመጡት የደብረ ብሥራት ዜና ማርቆስ አሥራ ሁለት አባቶች አንዱ የሆነው አባ በኃይለ ማርያም፣ በተዋሕዶ እምነቱ ምክንያት ለደረሰበት ተዋርዶ ከካቶሊካዊው  ሰው ጋር በኢየሩሳሌም አደባባይ ለመከራከር ሲጠይቅ ዳኛው ‹‹በምን ቋንቋ ትከራከረዋለህ?›› ብሎ ሲጠይቀው ‹‹በዐረብኛ ወይም በዕብራይስጥ›› ሲል መለሰለት፡፡ ዳኛውም ‹‹እንዴት እነዚህን ቋንቋዎች ልታውቅ ቻልክ›› ብሎ በአድናቆት ሲጠይቀው ‹‹ወአነ አአምር በልሳነ ዓረብ ወዕብራይስጥ ፍካሬሆን ለመጻሕፍተ ሕግ ወነቢያት እስመ ተምህርኩ እም ኀበ መምህር ዐቢይ ኢሳይያስ በትእዛዘ ንጉሥ ናዖድ ፈራሄ እግዚአብሔር ዘምስለ ዕንባቆም እኅወ መምህር ዐቢይ ዘስሙ እንድርያስ – እኔም የሕግና የነቢያት መጻሕፍትን ትርጓሜያቸውን በዐረብና በዕብራይስጥ ቋንቋ ዐውቃለሁ፡፡ እግዚአብሔርን በሚፈራ ንጉሥ በናዖድ ትእዛዝ ከታላቁ መምህር ከኢሳይያስ ዘንድ የእንድርያስ ወንድሙ ከሚሆን ከዕንባቆም ጋር ተምሬያለሁና፡፡›› አለው ይላል ገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከመካከለኛው ዘመን በኋላ የዕብራይስጥና የዐረብኛ ቋንቋ በሦስት ቦታዎች ይሰጡ ነበር፡፡ ደብረ ሊባኖስ(ሸዋ)፣ ደብረ ማርያም(ጎንደር) እና ማኅበረ ሥላሴ(ጎንደር)፡፡ ብዙዎቹ መነኮሳት በእነዚህ ቦታዎች ገብተው ቋንቋውን አጥንተው ነበር ወደ ኢየሩሳሌም የሚመጡት፡፡ የደብረ ማርያሙን የዕብራይስጥ መጽሐፍ እኔም አይቼዋለሁ፡፡


ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ እንደ ጻፉትና ዛሬም በቫቲካን ቤተ መዛግብት እንደምናገኘው ታሪክ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን የዴር ሡልጣን መነኮሳት በፍሎሬንስ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ተካፍለው ነበር፡፡ ጉባኤው የተካሄደው በላቲን ቋንቋ ነበር፡፡ ኢትጵያውያን መነኮሳትም ጉባኤውን የተሳተፉት በላቲን ቋንቋ ነበረ፡፡ በነገራችን ላይ አርመኖች የራሳቸውን ፊደል እንዲፈጥሩ የረዷቸው በዴር ሡልጣን የነበሩ ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ናቸው፡፡ የአርመንን ፊደል የፈጠረው መነኩሴ የኖረው በዴር ሡልጣን ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን ወደ አርመንኛ ሲተረጉምም የረዱት ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት የግእዝ ፊደልን የሚመስሉ ፊደሎችና የግእዝ ቃላት በአርመንኛ ቋንቋ ውስጥ በብዛት ይገኛል፡፡

‹‹ቄሱ ዮሐንስ – ፐሪስተር ጆን›› በሚል ስያሜ ኢትዮጵያን ሲፈልጉ የኖሩት የ14ኛው፣ 15ኛውና 16ኛው የአውሮፓ አሳሾች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ መረጃ ያገኙት ከኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት መነኮሳት ነበር፡፡


ይህንን ሁሉ የማነሣው ቀደምት አባቶቻችን እንዴው ሲጸልዩና ርስት ሲጠብቁ ብቻ እንደኖሩ አድርጎ የመመልከት ደካማ አስተሳሰብ በኢየሩሳሌማውያን ላይ ስለሚታይ ነው፡፡ አባቶቻችንና አባቶቻችሁ እንዲያ ብቻ አልነበሩም፡፡ ሌላው ቀርቶ ከራሳቸው አልፈው የሌሎች መመኪያ ለመሆን የበቁና በሌሎች ሀገሮች ገዳማትን የመሠረቱ አባቶችም ነበሩ፡፡ ሶርያውያን ‹‹ሞሰስ – አል – ሐበሽ – ኢትዮጵያዊው ሙሴ›› ብለው የሚጠሩት በ6ኛው መክዘ የነበረው የዴር ሡልጣን መነኮስ በሶርያ ከታወቁት የገዳማት መሥራቾች አንዱ ነው፡፡ ታሪኩ የንጉሥ ልጅ እንደነበር ይገልጣል፡፡ የአርመን ቤተ ክርስቲያን የምታከብራቸው አቡነ ኤዎስጣቴዎስም በዴር ሡልጣን ኖረው ነው ወደ አርመን የተጓዙትና በዚያ ያረፉት፡፡


የኢየሩሳሌም መነኮሳት ለሀገራቸው ያበረከቱት መጻሕፍትን ብቻ አልነበረም፡፡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችም ወደ ኢትዮጵያ ይገቡ ከነበሩበት መንገድ አንዱ ከኢየሩሳሌም በሚመጡ መነኮሳት አማካኝነት ነበር፡፡ እነ አቡነ ዕዝራ በ16ኛው መክዘ ኢየሩሳሌም ኖረው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የውኃ ወፍጮ ይዘው በመምጣት ነበር ለገዳማቱ ያስተዋወቁት፡፡የግራኝ ጦርነት ተከታትሎ ተነሥቶ ተክኖሎጂው ባይስፋፋም አባታችን ግን ጥረት አድርገው ነበር፡፡


የእነዚህን አባቶች ብቃት፣ ዕውቀትና ትጋት ስናይ ዛሬ ያለንበትን ደረጃ መመዘን እንችላለን፡፡ ለዚህም ነው በኢየሩሳሌም ገዳማት የሚመደቡ አባቶች የቀደሙትን ደረጃ የሚያስጠብቁ፣ የቤተ ክርስቲያንን መልካም ገጽታ የሚገነቡ፣ የኢትዮጵያን በረከት ለዓለም፣ በሌሎች የሚገኘውን ልምድ ደግሞ ለኢትዮጵያ የሚያስተላልፉ እንዲሆኑ በሚገባ ተመርጠውና ተመዝነው መመደብ አለባቸው የምንለው፡፡ በኢየሩሳሌም የምንወዳደረው ከግብጾች፣ ከአርመኖች፣ ከግሪኮች፣ ከላቲኖች፣ ከሶርያኖች ጋር ነው፡፡ ለመሆኑ ትናንት ከግሪክ ቀጥላ በፕሮቶኮል ደረጃ 2ኛ የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ ስንተኛ ናት? የእሥራኤልን የፕሮቶኮል ዶክመንት ያየ ያውቀዋል፡፡  


እንዴት ነው አሁን ለቅዳሴና ለሰዓታት ያለው ፍላጎት? እንዴት ነው ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመማር ያለው ትጋት?  እንዴት ነው የእጅ ሥራ ሠርቶ ገዳሙን ለመርዳት ያለው ሩጫ? (የገዳማውያን አንዱ ተግባር ተግባረ ዕድ አይደለም እንዴ? ለታላቁ እንጦንስ ቅዱስ ሚካኤል ሰኔል መታታት ለምን አስተማረው) እንዴት ነው በኢትዮጵያ የሚገኙ ገዳማትን ለመርዳት ያለው ትጋት? ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ያለው ጽናት?መንኖ ጥሪት ሆኖ ለመኖር ያለው ተጋድሎ? እውነት ሙሉ በሙሉ በቁሪት ነው ገዳሙ የሚተዳደረው?ለወር ጉርስ ለዓመት ልብስ በዶላር የሚከፈላቸው ባለ ቁሪቶች በኢትዮጵያ ገዳማት አሉ?እነ መምህር ወልደ ሰማዕት በኢየሩሳሌም ከተማ ለገዳማቱ ነበር ቤት የሠሩት፣ ዛሬስ የት ነው ቤቱ እየተሠራ ያለው?የዚህ ሁሉ አንዱ ችግር ከመምረጫ መመዘኛው ነውና እንደገና ቢታይ፡፡


ለመሆኑ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ጋብቻ የሚከናወነው በተክሊል ነው? ለመሆኑ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ከቅዳሴ በኋላ ጋብቻ በቢሮ ውስጥ እንዲደረግ ይፈቅዳል? ቤተ ክርስቲያንስ የኦርቶዶክስ አማኝ ያልሆኑትን ለማጋባት ሥርዓቷ ይፈቅድላታል?የእሥራኤልስ ሕግ ይፈቅዳል? ቤተ ክርስቲያን የማዘጋጃ ቤትን ሥራ መሥራት ትችላለች?ይኼ ሁሉ ለምን መጣ? ለእምነት ሳይሆን፣ ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን ለሌሎች ነገሮች ትኩረት ከመስጠት፡፡ ‹‹ሕግ ይወጽዕ እም ጽዮን›› ነበር፡፡ አሁን ግን በጽዮን ሕግ እየጠፋ ነው፡፡ ለዚህ ነው ወደ ኢየሩሳሌም የሚመጡ አባቶችን የመላኪያ መሥፈርቱ ይጥበቅ፣ ቅድሚያ ለሃይማኖት፣ ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ለጽድቅ የሚሰጡ አባቶችና እናቶች ይምጡ የምንለው፡፡


(ይቀጥላል)


ኢየሩሳሌም

ከዚህ ቀደም ባለው ጽሑፍ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የሚገኘውን ገዳማችንን በተመለከተ ዐሥር ነጥቦች እንደማነሣ ቀጠሮ ሰጥቼ ነበር ያቆምኩት፡፡ ዛሬ ሦስቱን አነሣለሁ፡፡

  1. ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋም

የዴር ሡልጣን ገዳማችን ሁለት ዓይነት ችግሮች ተደቅነውበት ይገኛሉ፡፡ የመጀመሪያው የይዞታ ባለቤትነት ያልተፈታ ችግር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ገዳሙ ላለፉት ሁለት መቶ ዓመታት ምንም ዓይነት ጥገና ባለማግኘቱ የተደቀነበት የመፍረስ አደጋ ነው፡፡ የሁለቱም ችግሮች መነሻው ግብጾች በገዳሙ ላይ የሚያቀርቡት የይገባናል ጥያቄና እርሱንም ተከትሎ በመተግበር ላይ የሚገኘው ይርጋ ሕግ(states co)ነው፡፡

ይህንን የገዳማችንን ችግር ለመፍታት በዘላቂነት፣ በተጠናና ዓለም ዐቀፍ ደረጃ ባለው መልክ የሚሠራ ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋም ያስፈልገናል፡፡ ይህ ኮሚቴ የሃይማኖት፣ የሕግ፣ የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ መንገዶችን ሁሉ በመጠቀም የዴር ሡልጣንን ገዳም ባለቤትነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚፈታ፣ ገዳሙም ጥንታዊነቱንና ደረጃውን ጠብቆ እንዲጠገንና እንዲገነባ የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡

ዛሬ ዓለም በኑሮ ደረጃ የትና የት በደረሰበት ዘመን መብራት፣ ውኃና መጸዳጃ ማግኘት ለዴር ሡልጣን መነኮሳት ፈተና መሆን የለበትም፡፡ በእሥራኤል ሀገር እንስሳ እንኳን በማይኖርበት መልኩ እንዲኖሩ ያስገደዳቸውን የይርጋ ሕግ አስቀርቶ ለደረጃቸውና ለሰብአዊነታቸው የሚመጥን የመኖሪያ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረግ አለበት፡፡ በአካባቢው የሚገኙ፣ ቦታንም ከእኛ የወሰዱ አብያተ ክርስቲያናት ሰማይ ጠቀስ ፎቅና ቤተ ክርስቲያን እየሠሩ፣  እነርሱ ግን በጎልጎታ ፍርስራሽ በተሠሩ በኣቶች እንዲኖሩ መገደድ የለባቸውም፡፡ የተቆረጠ ገመድ ለመቀጠል፣ የተሠበረ ቧንቧ ለመሥራት፣ የተበላሸ መጸዳጃ ለማስተካከል፣ የተጣመመ ሚስማር ለማቃናት ሌሎችን ደጅ መጥናት የለባቸውም፡፡

ይህ ነገር ሊፈታ የሚችለው ነገሩን የምር አድርገን ስንይዘው ብቻ ነው፡፡ በየዓመቱ በሚመጡ ተሳላሚዎች ብቻ የሚሠራ አይደለም፡፡ በቀን 24 ሰዓት፣ በሳምንት ሰባት ቀን፣ በወር ሠላሳ ቀናት፣ በዓመት አሥራ ሦስት ወራት የሚሠራ ሥራ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ ከአስጎብኝ ድርጅቶች፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከታዋቂ ሰዎች፣ ከምሁራን፣ በውጭ ሀገር ከመኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ከቤተ እሥራኤላውያን፣ ወዘተ የተውጣጣ አንድ ጠንካራ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋም አለበት፡፡ ይህንን ኮሚቴ ለማቋቋም የአስጎብኝ ድርጅቶች ኃላፊዎች ተነሣሽነቱን በመውሰድ፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር መሥራች ጉባኤ መጥራት ይቻላል፡፡

ይህ ብሔራዊ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ዋና ጽ/ቤቱን በማድረግ በእሥራኤልና በሌሎች ሀገሮች ቅርንጫፎችን በመክፈት ኢትዮጵያውያንንና የኢትዮጵያን ወዳጆች ማስተባበር ይችላል፡፡ ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጋር ጉዳዩን የተመለከተ ውይይት እንዲካሄድ ማስቻል፣ ከእሥራኤል መንግሥት ጋር የዲፕሎማሲ ውይይት መጀመር፣ ተጽዕኖ አድራጊ ተቋማትንና ግለሰቦችን በመፈለግ ተጽዕኖ አድራጊነታቸውን መጠቀም፣ ሚዲያዎች ጉዳዩን የተመለከቱ ዘገባዎችን እንዲሠሩ ማስቻል፣ ሕዝቡንም በማስገንዘብ ሀገራዊ ንቅናቄ መፍጠር፣ ደረጃ በደረጃ ሊፈቱ የሚገባቸውን ችግሮች በመለየት ደረጃ በደረጃ መፍታት፣ ሲፈቀድ የጥገናውንና የግንባታውን ሥራ ማከናወን፡፡

ይህንን ጉዳይ አሁኑኑ ማቋቋምና ሥራ መሥራት ካልቻልን ከገዳሙ በላይ በሚደረገው የጥገና ሥራ የድንጋይ መዓት እየዘነበበት የሚገኘው ገዳም፣ የእግዚአብሔር ቸርነት ካልጠበቀው በቀር የመናድ አደጋ ተደቅኖበታል፡፡ ወደፊትም የመፍረስ አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ አስቀድመን የሕግና የዲፕሎማሲውን ሥራ ካልጀመርነው፣ የፈረሰ ጊዜ ‹‹መልሳችሁ ልትሠሩ አትችሉም›› የሚል ክርክር ያጋጥመንና ፍርስራሽ ታቅፈን መቅረታችን የማይቀር ነገር ነው፡፡ ነገን መቅደም ያለብን ዛሬ ነው፡፡ በተለይ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጡት አስጎብኝዎች ይህንን ነገር ፈጥኖ በመከወን ረገድ ሃይማኖታዊም፣ ታሪካዊም፣ ዜግነታዊም ኃላፊነት አለባቸው፡፡


  1. የጋራ የጉዞ ከሚቴ

ወደ ኢየሩሳሌም ለትንሣኤ በዓል፣ ለዳግም ትንሣኤ በዓልና ለገና የሚደረገው የኢትዮጵያውያን ተሳላሚዎች ጉዞ ተጠናክሯል፡፡ የተጓዡም ቁጥር ጨምሯል፡፡ ነገር ግን ይህንን ዕድል በሚገባ አልተጠቀምንበትም፡፡ ተሳላሚዎቹ የሚገናኙበትን፣ ስለ ገዳማቸው የሚመክሩበትን፣ ገዳማቸውን ዘላቂ በመሆነ መንገድ የሚረዱበትን መንገድ አልፈጠርንም፡፡ እንዲያውም በአንዳንዶቹ አስጎብኝዎች መካከል የማይታረቅ የሚመስል ቅራኔ አለ፡፡ በአስጎብኝዋቻቸው ምክንያት ሰላምታ ለመለዋወጥ እንኳን የማይፈላለጉ ተሳላሚዎች አሉ፡፡ ሁሉም በየሆቴሉ ከርሞ፣ በየመኪናው ተጓጓጉዞ፣ በየራሱ ፋሲካን አክብሮ ወደነበረበት ይመለሳል፡፡ ሰማይና ምድር፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ሰውና መላእክት አንድ በሆኑበት ቅዱስ ቦታ ተለያይተን እንመለሳለን፡፡

የኢየሩሳሌም ጉዞ ከመላው ዓለም የሚመጡ ኢትዮጵያውያን የሚገናኙበት፣ የሚተዋወቁበት፣ በአንድ ሊመክሩ የሚችሉበት፣ ፍቅርና ሰላም የሚመሠርቱበት፣ የፖለቲካና የዜግነትን ድንበር ተሻግረው የእምነት አንድነት የሚያሳዩበት መሆን ነበረበት፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ትንሣኤን እንኳን በአንድ አዳራሽ ማክበር፣ በአንድነት መመገብ አልቻልንም፡፡ አንድ ቀን ሰጥተን እንኳን መማማር፣ መመካከርና የገዳማችንን ነገር ከገዳማውያኑ ጋር መወያት አልቻልንም፡፡

ይህን ችግር ለመፍታት አስጎብኝዎች የጋራ ኮሚቴ ሊኖራቸው፣ ችግራቸውን በሰከነ፣ በሠለጠነና መንፈሳዊ በሆነ መንገድ ሊፈቱ፣ አንዳንዱንም ችግር ይቅር ተባብለው ተሻግረውት ሊያልፉ ይገባል፡፡ ከችግራችን በላይ የሆነ ጊዜ የማይሰጥ ሌላ አደጋ ከፊታችን ስላለ፣ለባሰው ችግር ሲባል የኛን መለስተኛ ችግር መፍታት አለብን፡፡‹‹ለምጣዱ ሲባል አይጧን ማሳለፍ›› ይገባል፡፡ በጋራ የጉዞ መርሐ ግብራችን ማጣጣም፣ በኢየሩሳሌም ከተማ አንድ ቀን የኢትዮጵያውያንን ቀን ማክበር፣ የጋራ መንፈሳዊ ጉባኤ በማድረግ መማማር፣ ኅብረታችንን በመጠቀም የመጓጓዣ፣ የመኝታና ሌሎች ወጭዎችን እንዲቀንሱልን ማድረግ፣ ለተሳላሚዎቹ ተመሳሳይ መረጃ እንዲሰጣቸው ማድረግ፣ በመካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንም በጋራ መፍታት ያስፈልጋል፡፡

  1. የጋራ የመታሰቢያ ቀን

በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌምና በአካባቢዋ የሚገኙት ገዳሞቻችን በመሥዋዕትነት ተተክለው በመሥዋዕትነት የጸኑ ናቸው፡፡ እነዚህን ገዳማት ለማቅናትና ለመጠበቅ ሕይወታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ዕውቀታቸውን የሠው አያሌ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ከዘመናት በፊት መጭው ጊዜ ታይቷቸው ቋሚ ቅርስና ታሪካዊ ሥራ የሠሩ ጠንካራ ቀደምቶቻችን ነበሩ፡፡ እነዚህ ማስታወስ ይገባል፡፡

ብጹዕ አቡነ ማቴዎስ (በረከታቸው ይደርብንና) የነገሥታቱና ንግሥታቱ መታሰቢያ ታኅሣሥ 3 ቀን፣ የሌሎች መኳንንታና መሳፍንት ደግሞ ግንቦት አንድ ቀን በጸሎትና በቅዳሴ እንዲታሰብ በማኅበር አስወስነው ሲሠራበት ይኖራል፡፡ እኛም ተጓዦች ደግሞ በየዘመናቱ ሲጓዙ የኖሩትን፣ ሳይደርሱ በረሃ የቀሩትን፣ በባርነት ተሽጠው የጠፉትን፣ ከመጡ በኋላም በጽናት ያገለገሉትን አባቶችና እናቶች ታሪክ የምንሰማበት፣ በጸሎት የምንዘክርበት፣ ታሪካቸውንም ለትውልድ የምናስተላልፍበት፣ ዛሬም አገልግለው በአረጋዊነት ለሚጦሩ አባቶችና እናቶች አስፈላጊውን ሁሉ የምናደርግበት አንድ ራሱን የቻለ የቀደምቶቻችን መታሰቢያ ቀን ያስፈልገናል፡፡

ቀደም ብሎ የጋራ የጉዞ ኮሚቴ ይኑረን ያልኩትም ይህንን የመሰለውን ለማቀናጀት ነው፡፡ አስጎብኝዎች ተመካክረው አንዱን ቀን በመስጠት፣ ጠዋት የኢትዮጵያ ቀን በኢየሩሳሌም ብለን የገዳማቱን ሁኔታ፣ በብሔራዊ ኮሚቴው የተደረገው ጥረት የደረሰበትን ደረጃ፣ ከእኛ ምን እንደሚጠበቅ፣ ለገዳማቱ በጊዜያዊነትና በዘላቂ ስለሚያስፈልገውን ነገር የምንመክርበት ቢሆን፡፡ ምሳ በአንድነት ከተመገብን በኋላ ደግሞ ‹‹የአባቶቻችን መታሰቢያ ቀን›› ብለን ታሪካቸውን በማስታወስ፣ የመታሰቢያ ሥራ በመሥራት፣ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ገዳማትም ርዳታ በመሰብሰብ በትምህርትና በመዝሙር የምናሳልፈው ጊዜ ቢሆን፡፡


የትናንቱ በተረሳ ቁጥር ለዛሬው የምንሰጠው ዋጋ ይቀንሳል፤ ያገኘነው ነገር እንዲሁ የተገኘ ይመስለንና እንዲሁ እናጣዋለን፤ ዛሬ እንደ እነርሱ የሚነሣ ብርቱ ጀግናም እናጣለን፣ ምሳሌ የለውምና፡፡ በተደጋጋሚ የሌሎችን በመስማት ብዛትም የራሳችንን እስከመካድ ልንደርስ እንበቃለን፡፡ በቁጭት ተነሣሥተን ለሃይማኖታችንና ለታሪካችን በጽኑ እንዳንቆምም ማበርቻ እናጣለን፡፡

በቅድስት ሀገር የጉብኝት መርሐ ግብር ውስጥ ለገዳሞቻችን የምንሰጠው ቦታ ውሱን ነው፡፡ የጉዞው መብዛትና የዐቅምም ጉዳይ ገድቦብናል፡፡ ቢያንስ አንዱን ቀን በመሠዋት እና መርሐ ግብራችንን በማሸጋሸግ ግን የቀደሙትን ውለታ መክፈል ባንችል እንኳን ‹‹ዋኖቻችሁን አትርሱ›› የሚለውን ቃል መፈጸም እንችላለን፡፡

(ይቀጥላል)

ጥብርያዶስ፣ እሥራኤል

ከ ሁለት ሺ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የተገለጠው ኢየሩሳሌምን ለመሳለም የሚደረገው ጉዞ ዛሬ የሺዎች ጉዞ ሆኗል፡፡ በእግር ተጉዘው ኢየሩሳሌም ለመድረስ ሱዳንን፣ ግብጽና የሲና በረሃን ያቋርጡ የነበሩት፤ ያለበለዚያም በመካ በኩል ተሻግረው በዮርዳኖስ በኩል ይገቡ የነበሩት አባቶቻችን ክብር ይግባቸውና፣ በኢየሩሳሌም ያቆዩትን ቦታ ለመሳለምና የትንሣኤ በዓልንም በትንሣኤው ቦታ ለማክበር ኢትዮጵያውያን ከሰባ ሺ ብር በላይ እየከፈሉ ይጓዛሉ፡፡

ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት የኢትዮጵያውያን ምእመናን የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት በአዲስ መልክ የኢየሩሳሌምን ጉዞ ሲጀምር በአንድ ድርጅት ብቻ ይከናወን የነበረው ጉዞ፣ ዛሬ ከሃያ በላይ በሚሆኑ አጓጓዦች በኩል ከመላው ዓለም ኢትዮጵያውያን ይሰባሰባሉ፡፡ ከሃምሳ ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ በሚመጡ ተሳላሚዎች የተጀመረው ጉዞ ዘንድሮ ከ27 ሀገሮች በመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደሚከናወንበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ከዓመታት በፊት በአብዛኛው በሽማግሌዎችና በእናቶች ብቻ ይደረግ የነበረው ጉዞ ዛሬ ከሦስት ወር ጽንስ እስከ 94 ዓመት አዛውንት ተካትተውበት የሚደረግ ሆኗል፡፡

ከዐሥር ዓመታት በፊት የትንሣኤ በዓል በዴር ሡልጣን ሲከበር በአንደኛው የገዳሙ አጥር ጥግ ተሰባስበው ይታዩ የነበሩት ተሳላሚዎች ዛሬ ግቢው ጠቧቸው፣ መንገዶችን አጨናንቀው፣ ጠጠር መጣያ እስከ ማሳጣት ደርሰዋል፡፡ ወይም አንድ የእሥራኤል ጋዜጠኛ እንዳለው ‹‹ነጭ ጎርፍ በፍኖተ መስቀል በኩል ሲፈስ የሚታይበት ተአምር›› ላይ ደርሰዋል፡፡ ድንበር የለያያቸው ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ዜግነት ሳያግዳቸው፣ ሃይማኖት አገናኝቷቸው በአንድ የሚያመልኩበት፣ አንድ ማዕድ የሚቆርሱበት፣ የዘመድ ወግ የሚያወጉበት ሥፍራ ሆኗል፡፡

ይህ ሁሉ እግዚአብሔር የሰጠን ዕድል ቢሆንም ከተጠቀምንበት ነገር ያልተጠቀምንበት ይበልጣል፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ አስተሳሰባችን ከጠላት ተኮር ሥነ ልቡና ባለመላቀቁ ነው፡፡ ልክ ነው ግብጻውያን አሁንም በዴር ሡልጣን ገዳማችን ላይ ግፍ ይፈጽማሉ፡፡ አሁንም ችግር ይፈጥራሉ፤ አሁንም ገዳሙ እንዳይጠገን ይከላከላሉ፤ ህልውናችን ያበሳጫቸዋል፤ ብዛታችን ያንገበግባቸዋል፡፡ በግብጻውያን ምክንያት የተቀበልናቸው ብዙ መከራዎች አሉ፡፡ እንዳንሠራ የታገድናቸው ነገሮች አሉ፡፡ ግን የሁሉም ነገር መነሻና መድረሻ ግብጻውያን ናቸው ብለን መደምደም አንችልም፡፡ አንዳንዴም ‹‹እኛን የጨረሰን የራሳችን ጠማማ ነው›› እንዳሉት ዛፎች ለግብጻውያን ችግር ፈጣሪነት መነሻ እኛው ሆነን እንገኛለን፡፡

ታሪክ እንኳን እንደሚያስተምረን የዴር ሡልጣን ዋናው በር በግብጻውያን እጅ የቀረው ቁልፉ ለኢትዮጵያውያን እንዲሰጥ በተወሰነ ጊዜ በንጉሥ ምኒሊክ ተወካይና በገዳሙ ተወካይ መካከል ‹‹ቁልፉን መረከብ ያለብን እ ኔ ነኝ›› በሚል በተነሣው ውዝግብ ምክንያት ነበር፡፡ ዛሬ በየዓመቱ በስቅለት ቀን መብራት ይዘን እንለፍ አንለፍ የሚለው ውዝግብ የተፈጠረበት አንዱ ምንያት የኛው ጳጳስ በሰጡት ፈቃድ ነው፤ በገዳሙ በር አጠገብ ያሉት የብረት ቅስቶች የተገነቡት የኛው ጳጳስ በሰጧቸው ፈቃድ ነው፡፡

ግብጻውያን ጠንካራ ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁመን የዴር ሡልጣንን ነገር ዓለም ዐቀፋዊ አጀንዳ እንዳናደርገው አላገዱንም፤ ግብጻውያን በየዓመቱ የሚመጡ ምእመናንን በሚገባ እንዳናስገነዝብ አላገዱንም፤ ግብጻውያን እያንዳንዱ አጓጓዥ እንደ አይጥና ድመት እንዲተያይ አላደረጉም፤ ግብጻውያን በኢትዮጵያና በግብጽ ቤተ ክህነት በኩል ድርድር እንዳይጀመር አላደረጉም፤ ግብጻውያን ለሀገሩ የሚመጥኑ አባቶችን እንዳንመድብ አልያዙንም፤ ግብጻውያን ስለ ገዳማችን ተገቢውን መረጃ እንዳናስተላልፍ እጃችንን አልቆለፉንም፤ ግብጻውያን ምእመናን ተሳላሚዎችን አስተባብረን ሥራ እንዳናሠራ አላሳገዱንም፡፡

ጠላት ሁለት ጊዜ ይጎዳሃል፡፡ የመጀመሪያው በጠላትነቱ የሚሠነዝረው ጥቃት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በእርሱ እያመካኘህ ችግርህን ወደ ውስጥ እንዳታይ ማድረጉ ነው፡፡ ከሁለቱም የሚከፋው ሁለተኛው ነው ይባላል፡፡ የሁሉም ነገር ምክንያትና ሰበብ ጠላትህ ይሆናል፡፡ ሰዎችም በቀላሉ ይቀበሉሃል፡፡ አንተም ለማስረዳት ብዙ አትቸገርም፡፡ ለራስህም የችግርህ ሁሉ ምንጭ አድርገህ ትቀበለውና ሌሎች ነገሮችን አትመለከትም፡፡ አመለካከትህ ጠላት ተኮር ይሆናል፡፡


በኢየሩሳሌም ገዳሞቻችንም የሚታየው ይኼው ነው፡፡ ለማንኛውም ነገር ምክንያቶቹ ግብጻውያን ናቸው፡፡ ስለ ራሳችን ድክመት የሚያወራ የለም፡፡ ራሱን የሚወቅስም አልተገኘም፡፡ ብዙ ችግሮቻችን ግን ግብጻውያን ባይኖሩም የሚኖሩ ናቸው፡፡ ከጠባያችን፣ ከአሠራራችንና ከአካሄዳችን የሚመነጩ ናቸው፡፡ የግብጻውያኑ ችግርም መፍትሔ ያላገኘው እኛ ስለያዝነው ይመስለኛል፡፡ ነገሩን ጠበቅ አድርገን በመያዝ ብርቱ ሃይማኖታዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጫና ለማሳረፍ የምናደርገው ጥረት አለመኖሩ፡፡ የዴር ሡልጣን ነገር ትዝ የሚለን ለትንሣኤ በዓል ጊዜ መሆኑ፤ ከዚያ በቀር ይህን ጉዳይ ሥራዬ ብሎ የያዘ አንድም ቤተ ክህነታዊ አካል አለመኖሩ፡፡ ግብጾችኮ ጉዳዩን በፓርላማ ደረጃ በብሔራዊ ኮሚቴ ነው የሚከታተሉት፡፡ እኛኮ እንኳን ፓርላማ ቤተ ክህነት የሚያውቀው ኮሚቴ የለም፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም ቢሆን ከኢየሩሳሌም ገዳማት በሚቀርብ ጥያቄ ይወያያል እንጂ የኢየሩሳሌም ገዳማትን ጉዳይ በዝርዝር አጥንቶ፣ የድርጊት መርሐ ግብር ቀርጾ፣ አካል አቋቁሞ፣ ከሚመለከታቸው ጋር ኅብረት መሥርቶ ዘላቂና ተከታታይነት ያለው ሥራ አይሠራም፡፡ አብዛኛው የኢየሩሳሌም ገዳማትን የሚመለከተው አጀንዳም ‹‹አቡነ እገሌ ይነሡ አይነሡ›› በሚለው ላይ የሚያተኩር ነው፡፡

በፓትርያርኮች ደረጃ በግብጽ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መካከል ውይይት ሲደረግም የኢየሩሳሌም ገዳማችን ጉዳይ አጀንዳ ሆኖ የተነሣበት ጊዜ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ቢያንስ ውይይት ለመጀመር፣ ችግሩን ለመፍታትና አንዳች የስምምነት ደረጃ ላይ በየእርከኑ ለመድረስ የሚያስችል መግባቢያ እንኳን የለም፡፡ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በቅርቡ ወደ ግብጽ ይሄዳሉ፡፡ እስከ አሁን ባለኝ መረጃ ዴር ሡልጣን የአጀንዳቸው አካል የሆነ አይመስለኝም፡፡ ለግብጻውያን ግን ዴር ሡልጣን ከዓባይ ቀጥሎ ከኢትዮጵያን ጋር ላላቸው የዲፕሎማሲ ግንኙነት አንዱ አጀንዳቸው ነው፡፡

ይህንን በዚህ እንተወውና ለመሆኑ ወደ ኢየሩሳሌም ገዳማት የምንመድባቸው አባቶች መመዘኛቸው ምንድን ነው? የሃይማኖት ትምህርት፣ የእምነት ጽናት፣ ለጸሎትና ለአገልግሎት ያላቸው ፍላጎት፣ ለመማር ያላቸው ትጋት፣ ከአካባቢው ጋር ተዛምደው ለመኖር ያላቸው ዝግጁነት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አምባሳደር ለመሆን ያላቸው ችሎታ ይታያል? ከዐሥር ዓመታት በላይ ተቀምጠው ዐረብኛና ዕብራይስጥ የማይችሉ ከሆነ ኢየሩሳሌም መኖር ጥቅሙ ምንድን ነው? አገልግሎቱ ሲሆን ከሀገር ቤት ካልበለጠ ካልሆነም እንደ ሀገር ቤቱ ካልሆነ በኢየሩሳሌም ገዳማት መኖሩ በአሜሪካ ከመኖር ልዩነቱ ምንድን ነው? በኢየሩሳሌም ገዳማችን ደረጃውን የጠበቀ፣ አባቶችን ለዓለም አቀፋዊ አገልግሎት የሚያበቃ ትምህርት ቤት ከሌለን ኢየሩሳሌም መመደብ ከሥጋዊ ዕድል በዘለለ ጥቅሙ ምንድን ነው? የራሳችን የቅብዐ ቅዱስ ማዘጋጅ፣ የዕጣን መቀመሚያ፣ የንዋያተ ቅድሳት ማዘጋጃ፣ የመስቀል መሥሪያ፣ ከሌለን ኢየሩሳሌም መመደብ ጥቅሙ በዶላር ደመወዝ ማግኘት ነው ማለት ነው፡፡

የኢየሩሳሌም ገዳማችን ቤተ ክርስቲያናችን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላትን ግንኙነት የሚያጠናክሩ፣ ከአካባቢው ባለ ሥልጣናት ጋር በሚገባ ተግባብተው የገዳማችንን መብት የሚያስከብሩ፣ በልዩ ልዩ ሞያ ሠልጥነው ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን ተስፋ የሚሆኑ፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ለማወቅ የሚመጡትን ምሁራን በደረጃቸው የሚያናግሩ፣ በማንኛውም መድረክ ተገኝተው ቤተ ክርስቲያንን ሊወክሉ የሚችሉ፣ ልዩ ልዩ የገቢ ምንጭ ፈጥረው የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን የሚረዱ ተቋማትን የማያፈሩ ከሆነ መነኮሳቱ ‹‹አረዳ ጠባቂ›› ከመሆን ያለፈ ለቤተ ክርስቲያን በቁዔታቸው ምንድን ነው? መቼም ይህንን ሁሉ ያላደረግነው በግብጻውያን ምክንያት ነው አንልም፡፡


በዚህ በትንሣኤ ሰሞን ከዐሥር ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ምእመናን በኢየሩሳሌም ተገኝተው ነበር፡፡ ነገር ግን እነርሱን በአንድ ጉባኤ ለማስተባበር፣ ስለ ገዳማቱ ሁኔታ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ፕሮጀክት ቀርጾ ያንን እንዲተገብሩ ለማድረግ፣ ምእመናኑን ለማስተማርና ለማነጽ፣ ጥረት ሲደረግ አላየሁም፡፡ ከዚያ ይልቅ የሀገር ቤቱ አሠራር አልለቀን ብሎ አንዳንድ ቁራጭ ጧፍ ለመሸጥ ነበር መከራ ስናይ የከረምነው፡፡ ውኃ አዙሮ ለመሸጥ ነበር ጥረት ሲደረግ የነበረው፡፡ ምእመናኑን በሚገባ አስረድቶ፣ ዘላቂ ነገር እንዲሠሩ አወያይቶ፣ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ነገር ከመሥራት ይልቅ አንድ ሺ ጧፍ ሽጦ አንድ ሺ ዶላር ለማግኘት መድከሙ በዋናው አልጋ ላይ መተኛት ሲቻል በትራሱ ላይ እንደ መተኛት ነው፡፡

ተሳላሚ ምእመናኑም ራሳቸውን እንደ ቱሪስት ቆጥረው ተሳልሞ ለመጓዝ ከመትጋት ባለፈ የገዳሙን ሁኔታ ለማወቅ፣ ዘላቂና ችግር ፈች ሥራ ለመሥራት፣ አልከፈት ያለውን የቤተ ክህነት በር በሚገባ አንኳኩቶ ለማስከፈት አልቻልንም፡፡ አጓጓዦቹም ምእመናኑ ተገናኝተው፣ ተዋውቀውና ተወያይተው፣ በአንድ ኢትዮጵያዊ መንፈስ አንድ ሥራ እንዲሠሩ ጥረት ሲያደርጉ አይታዩም፡፡ እንዲያውም ተጓዦቻቸው ባለመተዋወቅና በመፈራራት የጎሪጥ እንዲተያዩ ያደርጓቸዋል፡፡

እነዚህን ለምሳሌነት የጠቀስኳቸው በግብጻውያን ብቻ እያመካኘን በመቀመጣችን ያልሠራነው ሥራ ምን ያህል ዋጋ እያስከፈለን መሆኑን ማየት እንድንችል ነው፡፡ ግብጻውያን ርስታችንን ከመንጠቃቸው በላይ በእነርሱ እያመካኘን የኛን ሥራም እንዳንሠራ አድርገውናል፡፡ አሁን ለዴር ሡልጣን መልካም ዘመን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በግብጽ ላይ አንገቷን ቀና አድርጋለች፣ የአካባቢው የፖለቲካ ምሕዳር እየተቀየረ ነው፡፡ ምእናንም በብዛት ወደ ኢየሩሳሌም እየመጡ ነው፡፡ ከመላው ዓለምም ተሳላሚዎች እየበዙ ነው፡፡ ይህንን እግዚአብሔር የሰጠንን ዕድል ካልተጠቀምን እንነጠቃለን፡፡ ስለዚህ በአዲስ አስተሳሰብ፣ በአዲስ መንፈስና በአዲስ መንገድ መነሣት አለብን፡፡

እንዴት? በቀጣይ ዐሥር ነገሮችን እጠቁማሁ፡፡

ዴር ሡልጣን፣ ኢየሩሳሌም

(አማትና ምራት በአንድ ላይ የሚያነቡት)
አንድ ጊዜ አንዲት እናት ይህንን ታሪክ ነግረውኝ ነበር፡፡

እኔና ባለቤቴ የተጋባነው ልጆች ሆነን ነው፡፡ ያኔ እንዳሁኑ ተያይቶ፣ ተጠናንቶ፣ ሰንብቶ፣ ቆያይቶ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ እንዲያውም የኛ ጊዜ ዘመናይ ነው ተብሎ የተወሰነ ጊዜ ትተያይና ወላጆቹ ለወላጆቿ ሽማግሌ ይልኩና፣ በስንት መመላለስ፣ አጥንትህ ጉልጥምትህ ተጠንቶ፣ ሀብት ንብረትህ ታይቶ ነበር የሚፈቀድልህ፡፡ ዛሬማ መንገድ ላይ ተንበርክኮ አንዲት የሃምሳ ብር አበባ ይዞ መለመን ነው አሉ፡፡ በኛ ዘመን በሬ ጎትተህ፣ መኪና አንጋግተህ፣ ጥሎሽ አግተልትለህም ከተሳካልህ ነው፡፡

ታድያ መጋባት አይቀርም ተጋባን፡፡ የእርሱ ወላጆች የሚያከራዩት ቤት ነበራቸው፡፡ አንዱን ቤት ሰጡንና ኑሮ ጀመርን፡፡ መቼም ፍቅርና ትዳር ለየቅል ነው፡፡ ታድያ እኛ ትዳር እንደጀመርን ባለቤቴ የልጅነት ነገር ሆነበትና ከጓደኞቹ እየተማረ ውኃ ቀጠነ ማለት ጀመረ፡፡ ባልነት ማለት መኮሳተር፣ መጎማለል፣ አንቺ እያሉ መጣራት፣ አምሽቶ መምጣት መሰለው፡፡ ይህን ጠባይ እርሱ እንዳላመጣው ዐውቅ ነበር፡፡ ጓደኞቹ ናቸው ያስተማሩት፡፡ በጊዜ ገብቶ አብረን ነበር ስንስቅና ስንጫወት የምናመሸው፡፡ እንዲያውም የኔ ባልኮ ዘመናይ ነው እያልኩ ነበር ለሰው የምናገረው፡፡ ወጥ ስሠራ እንኳን የሚያቀራርብልኝ እርሱ ነበር፡፡ በኋላ ጓደኞቹ ጠምደው ያዙት፡፡ ‹ለምን ቀሚስ አትለብስም› እያሉ መሳቂያ መሳለቂያ አደረጉት፡፡

የእነርሱን ወሬ መቋቋም ሲያቅተው እንደ እነርሱ ሆነ፡፡ ያገባሁትን ባል ወሰዱብኝና ሌላ ባል አጋቡኝ፡፡ አየህ ብዙ ሚስቶችኮ ባሎቻችንን ተነጥቀናል፡፡ እኛ ስናገባ ያገኘናቸውን ባሎች ወይ ጓደኞቻቸው ወይ ወላጆቻቸው ወይም ደግሞ የሥራ ባልደረቦቻቸው ነጥቀውናል፡፡ ያላገባናቸውን ሌሎች ባሎችም አጋብተውናል፡፡ አንዳንዶቻችንኮ ከተፈራረምናቸው ባሎቻችን ውጭ ነው የምንኖረው፡፡ የኔም እንደዚያ ሆነልህ፡፡

ይህንን ሲተርኩልኝ ባልየው እያሳቁ ያዩናል፡፡ አማትዬው ደግሞ ‹‹መቼም አትረሽም አንቺ›› ይላሉ እርጅና እንኳን ብልቀነሰው ጆሯቸው እየሰሙን፡፡ እርሳቸውም ‹‹ሰው የልቡን ሲነግሩት የኮረኮሩት ያህል ይስቃል›› ብለው በባላቸው ተረቱና ቀጠሉ፡፡

ነጋ ጠባ ጭቅጭቅ ሆነ፡፡ አምሽቶ መምጣት፣ ጠጥቶ መምጣት፣ የት እንደሄደ ሳይናገር ሶደሬና ላንጋኖ ጠፍቶ መክረም፤ የት ገባሽ የት ወጣሽ ማለት አመጣ፡፤ በእርሱ ቤት መቀናቱ ነው፡፡ ጓደኞቹ ሲያወሩ የሰማውን ሁሉ እውነት አደረገው፡፡ እኔም እየመረረኝም እየሰለቸኝም መጣ፡፡

የእርሱ እናት እንዴት ጥሩ ሰው መሰሉህ፡፡ ምናለ እንደርሳቸው ያለውን አማት እንደ ካሴት አባዝቶ በየቤቱ ቢያድሉት፡፡ በዚያ ዘመን እንደ አጤ ቴዎድሮስ ቀድመው የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ከቤታችን አይጠፉም፡፡ ምን ጎደለ? ምን ጠፋ? ነው ሐሳባቸው ሁሉ፡፡ በዚያ ዘመን አማት ልጅ ቤት የሚመጣው እንድም ሊያንጓጥጥ አንድም ሊያመናጭቅ ነው፡፡ አማት ሲባሉ ደርሰው መጥተው ሞያህን፣ ቤትህን ይገመግሙና ይዘረጥጡሃል፡፡ እርሳቸው እቴ፡፡ አንድ ቀን ክፉ ቃል ወጥቷቸው አያውቁም፡፡ ኧረ እንዲያውም ክፉ ቃል የሚባለውን ራሱን የሚያውቁት አይመስለኝም፡፡ የሚጨነቁት ለእኔ ነበር፡፡ ቁጭ ብለው ይመክሩኛል፣ ሞያ ያስተምሩኛል፣ ታሪክ ይተርኩልኛል፡፡ አቤት ቀልዳቸው፡፡ የባሌን ችግር የምረሳው በእርሳቸው ቀልድ ነበር፡፡ ከነገሩኝ በኋላ እንኳን ብዙ ጊዜ ብቻዬን እስቅ ነበር፡፡ ታድያ የቤቱን ችግር ነግሬያቸው አላወቅም፡፡ ለምን ይጨነቁ ብዬ፡፡

በኋላ ግን ባሰብኝ፡፡ ‹‹ቡችላው ሲጮህብሽ ዝም ካልሽው ውሻው ይነክስሻል›› ይባላል፡፡ ጭቅጭቁን ስታገሠው ጊዜ ዱላ ጀመረ፡፡ እርሱን ግን መቋቋም አቃተኝ፡፡ ሲብስብኝ ለእማማ ነገርኳቸው፡፡ አረሩ፣ ደበኑ፡፡ ምን አድርገሽው ነው እንኳን አላሉኝም፡፡ እስኪመጣ ድረስ አብረውኝ ቁጭ አሉ፡፡ አጅሬው አገር ሰላም ነው ብሎ ማታ ነበር የመጣው፡፡ እናቱን ይወዳቸዋልም ያከብራቸዋልም፡፡ ለእናት ለአባቱ አንድ ልጅ ነው፡፡ ከአባቱ ይልቅ እናቱን ነበር የሚፈራው፡፡ እርሳቸውን እንኳን ልጃቸው የሠፈር ሰው እንደ ንጉሥ ነው የሚያከብራቸው፡፡

ሲመጣ እሳት ጎርሰው እሳት ልሰው ጠበቁት፡፡ ‹‹አንተ ይህችን ትመስል ልጅ ያጋባንህኮ ተንከባክበህ፣ አክብረህ እንድትይዛት ነው፡፡ እንድትጫወትባት አይደለም፡፡ በእርሷ ላይ ነው ዱላ የምታነሳው፣ በእርሷ ላይ ነው አምሽተህ የምትመጣው፡፡ አየሁህኮ፣ በዓይኔ በብረቱ አየሁህ፡፡ ይህችን ትመስል ልጅ እንድታበላሽ አልፈቅድልህም፡፡ እኔ ጥሩ ሰው መስለህኝ ነበር የዳርኩልህ፡፡ ለካ እንደዚህ ሆነሃል፡፡ በይ ተነሽ፤ እኔ ምን የመሰለ ባል ፈልጌ እድርሻለሁ፡፡ ያዥ ልብስሽን›› አሉና ያን ጊዜ ሞባይል የለም በቤት ስልክ ለባላቸው ደወሉ፡፡ ባላቸው ፔጆ መኪናቸውን ይዘው መጡና ተነሥቼ ወደ አማቴ ቤት፡፡

እዚያ ስደርስ የእንግዳ ክፍል ተከፈተልኝ፤ ልብሴ ተጣጥፎ ተቀመጠልኝ፡፡ ‹‹አይዞሽ የኔ ልጅ፤ እርሱ የእኔ ልጅ አይደለም፡፡ ልጄ አንቺ ነሽ፡፡ እንኳን መምታት ዘወር ብሎ ሊያይሽ አይችልም›› ተባልኩ፡፡ መቼም የእርሳቸውን ነገር አውርቼ አልጠግበውምኮ፡፡ የእኔ እናት እንጂ የእርሱ እናት አይመስሉኝም፡፡ የእኔ እናትና አባትማ ናዝሬት ስለነበሩ እንዲህ በቶሎ መምጣት አይችሉም፡፡ እናቴም ‹‹ምን ከእኔ የበለጠ እናት አግኝተሻል፤ እኔ ምን አደርግልሻለሁ›› ነበር የምትለኝ፡፡

ባለቤቴ ጨነቀው፡፡ ምን ያድርግ፡፡ መብረቅ የቀላቀለ ዝናብ ነው የወረደበት፡፡ እናቱን ያውቃቸዋል፡፡ አይወስኑ እንጂ ከወሰኑ ማንም አይመልሳቸውም፡፡ እንደፎከሩት ለሌላ ቢድሯትስ ብሎ ፈራ፡፡ማን ተከራክሮ ይመልሳቸዋል፡፡ እንደ ዘንድሮ ባልና ሚስት ፍርድ ቤት መሄድ ያኔ አይታወቅ፡፡ ምን ያድርግ? ወስከንቢያው ነው የተደፋበት፡፡ ከአንድ ሳምንት በኋላ የእርሱ ሽማግሌዎች የነበሩት ታላላቅ ሰዎች መጡ፡፡ እማማ እሽ ሊሉ ነው፡፡ ‹‹ልጄን እንዲያበላሽ አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ ጓደኞቹ ካዋጡት ይዳሩት፡፡ እኔ የሚሳደብና የሚደባደብ ልጅ አልወለድኩም፤ አላሳደግኩም፡፡ ይቺን ትመስል ልጅ ብንድርለት በእርሱ ብሶ ሊማታ፡፡ የለም የለም፤ ልጄን እኔ ምን የመሰለ ጠባይ ከመልክ የተሰጠው ፈልጌ እድራታለሁ እንጂ እርሱማ አይጫወትባትም›› ብለው አሻፈረኝ አሉ፡፡ የእኔ እናት እንጂ የእርሱ እናት አይመስሉም ነበር፡፡ ሽማግሌዎቹም ተጠራጠሩ፡፡ እኛ ቤት የመጡ ነበር የመሰላቸው፡፡ እማማኮ ስለ ምራታቸው የሚያወሩ አይመስሉም፡፡

በሁለተኛው ሳምንት አጅሬ ለካ እናቴ ጋር ደውሏል፡፡ ስትሰማ ደነገጠች፡፡ ለአባቴ ነግራው ሲበሩ መጡ፡፡ ከቤት መውጣቴን ሰሙ፡፡ ደግሞ ወጥቼ የገባሁት አማቶቼ ጋ፡፡ ጉድ ተባለ፡፡ አቤት እማማ የሠሩት ሥራ፡፡ የእርሱ እናት እኔን አልሰጥም ብለው የእኔ እናትና አባት ለእርሱ አማላጅ ሆነው መጡ፡፡ ተገላበጠ፡፡ እማማ እንደ ባሕሉ አስተናገዱና ምን ልታዘዝ? አሉ፡፡ ‹‹ልጃችሁ ሽምግልና ልኮን ነው›› አሉ፡፡ እማማ አልሰጥም ብለው እምቢ አሉ፡፡

‹‹ምንም ብትወልዷት አልፈቅድላችሁም›› አሏቸው፡፡ ቀኑን ሙሉ ሲለምኑ ዋሉ፡፡ አባቴ ብልሃተኛ ነው፡፡ ‹‹እንጥራውና እዚሁ ዋስ ጠርቶ ቃል ይግባ›› አለ፡፡ እማማ ተስማሙ፡፡ ተጠርቶ መጣ፡፡ እየተንቀጠቀጠ ነበር የገባው፡፡ ወዳደገበት ቤት የሚገባ አይመስልም ነበር፡፡ ‹‹ሁለተኛ አንዳች ነገር አልናገራትም፣ እጄን አላነሣም፣ አላመሽም፣ አልጠጣም፣ ከቃሏ አልወጣም ብለህ ቃል ግባ›› አሉት እማማ፡፡ ቃል ገባ፡፡ ዋስ ጥራ ተባለ፡፡ ዋስ ማንን ቢጠራ ጥሩ ነው፤ የእኔን አባት፡፡ እዋሰዋለሁ አለ አባቴ፡፡ ‹‹በል ሁላችንምም ጉልበት ሳም›› አሉት እማማ፡፡ ሳመ፡፡ ‹‹አንድ ነገር ቢልሽ ደውይልኝ፤ ልጄን እወስዳታለሁ፡፡›› አሉ እማማ በማሠሪያው፡፡

እኔም ቤቴ ተመለስኩ፡፡ ኩሽ የለ፤ ዱሽ የለ፡፡ ሰላም፡፡ ጠባዩ ለወጥ ሲል ‹‹ለእማማ እደውላለሁ›› ነበር የምለው፡፡ እንዲህ ‹‹ለእማማ እደውላለሁ›› እያልኩ ይኼው ዐርባ ዓመት ኖርን፡፡ ስናስበው እንስቃለን፤ ለእኛ በሰላም መኖር ምክንያቱ እማማ ናቸው፡፡ ብዙ አማቶች ለልጃቸው አግዘው ከምራታቸው ጋር ነው የሚጣሉት፡፡ እንዲህ እንደርሳቸው ከዝምድና በላይ የሚያስብ አይገኝም፡፡ እናቴ ለእኔ በትረዳ ምን ይገርማል፡፡ አማቴ እናት ሲሆኑ ግን እንዲህ ትዳርን ያዘልቃል፡፡ እርሱማ ልጃቸው ነው፡፡ የት ይሄድባቸዋል፡፡ አሁን አሁን ነገሩ ሲነሣ ‹‹እማማ ግን እውነት ለሌላ ሊድሩኝ ነበር›› እላቸዋለሁ፡፡ ‹‹ባክሽ ላስፈራራው ብዬ ነው፡፡ ስቆርጥ ያውቀኝ የለ፡፡ ጉድ ትሠራኛለች ብሎ ነውኮ የፈራው፡፡ እናቱ ሚስቱን ወሰዱበት ቢባል እነዚህ ጓደኞቹ የሚለቁት ይመስልሻል?ጳውሎስ ኞኞ ነበር በጋዜጣ የሚያወጣው›› ይላሉ እየሳቁ፡፡

መከራየት እኒህን አማት ነበር፡፡

© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

 click here for pdf

ሰሞኑን ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ ‹‹ሊያፈርሱት ነው›› የሚል ዜና በኅትመት ሚዲያዎችም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ይታያል፣ ይሰማል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍት ግን አንድ መንፈሳዊ ተቋም ሊፈርስ የሚችለው በውጭ ኃይል ጫናና ዐቅም ሳይሆን በውስጣዊ ምክንያቶች መሆኑን ይነግሩናል፡፡ ኢየሩሳሌምን ናቡከደነፆር ያፈረሳት ናቡከደነፆር ኃያልና ተዋጊ ስለነበረ አይደለም፡፡ የባቢሎኑ ናቡከደነፆር መሣሪያ እንጂ መነሻ አልነበረም፡፡ ኢየሩሳሌም የፈረሰችው እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን አሳልፎ ስለሰጣት ነበር፡፡ ኢየሩሳሌም የቃል ኪዳን ከተማ መሆኗ ቀርቶ ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ የሚቀልዱባት፣ ካህናቱም በአገልግሎታቸው የሚያሾፉባት ከተማ ሆነች፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ ለዚህም ነበር ነቢዩ ዳንኤል በጸለየው ጸሎት ላይ ‹‹ኃጢአትን ሠርተናል፣ በድለንማል፣ ክፋትን አድርገናል፣ ዐምፀናልም፣ ባሪያዎችህንም ነቢያትን አልሰማንም›› በማለት የገለጠው፡፡

አሁንም የሚጠቅመን ነገር እግዚአብሔር ለሌሎች አሳልፎ እንዲሰጠን የሚያደርግ ነገር ሠርተናል ወይስ አልሠራንም? የሚለውን ማየት ነው፡፡ ለመዋጥ የሚያበቃ ምክንያት ከኛ ዘንድ ከሌለ በቀር አንበሳው ስላገሣ ብቻ አይውጠንም፡፡ እኛ ከእግዚአብሔር ጋር መሆናችንን ርግጠኞች እንሁን፡፡ እግዚአብሔር ከኛ ጋር ለመሆኑ ርግጠኞች ነንና፡፡ ውስጣችን ለእግዚአብሔር የተመቸ ለመሆኑ ርግጠኞች እንሁን፣ እግዚአብሔር ለእኛ የተመቸ ነውና፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ዝግጁ እንሁን፡፡ በክርስትና ውስጡ ውጩን ይስበዋል እንጂ፣ ውጩ ውስጡን አይስበውም፡፡ ‹‹ዝናብም ወረደ፣ ጎርፍም መጣ፣ ነፋስም ነፈሰ፣ ያንንም ቤት መታው በዐለት ላይ ስለተመሠረተ ግን አልወደቀም›› ይላልና፡፡ ያልወደቀው ስላልተመታ ሳይሆን መሠረተ ጽኑዕ ስለነበረ ነው፡፡

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ዐርፈው አቡነ ቴዎፍሎስ ዐቃቤ መንበር እያሉ ቤተ ክህነቱ ይታመስ ነበር አሉ፡፡ የቤተ ክህነቱ የዘር አስተሳሰብ እያቆጠቆጠ የመጣበት ዘመን ነበርና ‹‹ቀጣዩ ፓትርያርክ ማን ይሆን?›› ከሚለው ይልቅ ‹‹ቀጣዩ ፓትርያርክ ከነማን ወገን ይሆን?›› የሚለው ብዙዎችን የሚያስጨንቅበት ጊዜ ነበር፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ እንደ ዘመነ ሴዴቅያስ የሐሰት ነቢያትን በሆኑት በመሰል ባሕታውያን በኩል ‹ቀጣዩ ፓትርያርክ እገሌ ነው፣ ራእይ አይቻለሁ›› ያሰኙም ነበር፡፡

በወቅቱ ዐቃቤ መንበር ለነበሩት ለአቡነ ቴዎፍሎስ ብዙ ሰዎች እየሄዱ ‹‹እገሌ ፓትርያርክ ቢሆኑ፣ ሕዝቡ እገሌን እያለ ነው፣ መኳንንቱ እገሌን እያሉ ነው፣ ባሕታውያኑ እገሌ ይሆናሉ ብለው ትንቢት እየተናገሩ ነው፣ ቤተ ክህነቱም እገሌን እያለ ነው›› እያሉ ይነግሯቸው ነበር፡፡ ሁሉንም የሰሙት አቡነ ቴዎፍሎስም ‹‹ባሕታውያኑም፣ ሕዝቡም፣ መኳንንቱም፣ ቤተ ክህነቱም ያሉትን ሰምቻለሁ፡፡ እግዚአብሔርስ ምን አለ?›› ብለው ጠየቁ ይባላል፡፡

አሁንም የሚጠቅመው ከልዩ ልዩ ቦታ በሚነፍሰው ነፋስ መሸበር ሳይሆን እንደ አቡነ ቴዎፍሎስ ‹‹እግዚአብሔርስ ምን አለ?›› ብሎ መጠየቅ ነው፡፡ ሁሉም የየራሱን ሊወስን፣ ሊፎክር፣ ሊነሣ ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ካልወሰነ ግን የሚሆን አንዳች ነገር የለም፡፡ የእግዚአብሔርን ውሳኔ የሚያመጣው ደግሞ የወደረኞቹ ኃይል ሳይሆን የራሳችን ስንፍና ነው፡፡

ታዋቂው ገጣሚ ጸጋዬ ገብረ መድኅን በጻፈው የቴዎድሮስ የመቅደላ ስንብት ላይ ‹‹ከሠራሁት ነገር ይልቅ ያልሠራሁት ነው የሚቆጨኝ›› እንዳሉት፡፡ ያልሠራነው ነገር እንዳይኖር፣ ምክንያት የሆንነው ነገር እንዳይኖር፣ ልንፈጽመው ሲገባን ያልፈጸምነው ነገር እንዳይኖር፣ ልናስበው ሲገባን ያላሰብነው ነገር እንዳይኖር ነው መፍራት፡፡ እንጂ ሊመጣ ያለውን ነገር አይደለም መፍራት፡፡ ክርስቲያን ሞትን አይፈራም አሟሟቱን እንጂ፡፡   

ሰውዬው በሩን በጠንካራ ብረት ዘግቶ ሲጠብቅ ያየው ጎረቤት ‹‹ምነው እንዲህ ታጠብቀዋለህ፤ አላህን አታምንም እንዴ ብሎ ቢጠይቀው ‹‹አላህንም አምናለሁ፣ በሬንም አጠብቃለሁ›› እንዳለው በእግዚአብሔር ያለንን እምነት ማጽናት በራችንንም ማጥበቅ ያስፈልገናል፡፡ የአመራር አቅማችን እንዴት ነው? መደበኛ አገልጋዮቻችንና አባሎቻችን እንዴት ናቸው? በአመራራችን ደስተኞች ናቸው? ማዕከሎቻችን እንዴት ናቸው? ከሊቃነ ጳጳሳትና ከአህጉረ ስብከት ጋር ያላቸው ግንኙነት መልካም ነው? ግቢ ጉባኤያቱ እንዴት ናቸው? ሚዲያዎቻችንስ በቀድሞው ጥንካሬና ብስለት ላይ ናቸው? ሌሎችንም በሮች ማጠባበቁ የሚበጅ ይመስለኛል፡፡

ከዚያ ወዲያ ግን፣ የምንችለውን ሁሉ ካደረግን በኋላ ግን፣ የዐቅማችንን ሁሉ ከፈጸምን በኋላ ግን ‹‹እግዚአብሔር ምን አለ? የሚለው እንጂ እነ እገሌ ምን አሉ›› የሚለው ሊያሳስበን እንጂ ሊያስጨንቀን አይገባም፡፡ ቂጣ ከሆነ ይጠፋል፣ ሺልም ከሆነ ይገፋል፡፡

እንደ ክርስትና ትምህርት ከሆነ ህልውና ከግዘፋዊ ኑባሬ ጋር አይደለም የሚያያዘው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ከሚገኝ ሕይወት እንጂ፡፡ ግዘፋዊ ኑባሬ ማለት እታየ እየተደሳሰሰ፣ አካላዊ ቦታ ይዞ መኖርን ነው፡፡ እያሉ የሌሉ እንዳሉት ሁሉ እንደሌሉ የተቆጠሩ ደግሞ አሉ፡፡ ሰማዕታት በግዘፋዊ ኑባሬ አሁን በዚህ ዓለም የሉም፡፡ ነገር ግን ዘለዓለማዊ ህላዌ አላቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ግዘፋዊ ኑባሬ እያላቸው እየበሉና እየጠጡ፣ እየሠሩና እየተንቀሳቀሱ እንደሌሉ የተቆጠሩም አሉ፡፡ የጠፋው ልጅ ወደ አባቱ ሲመጣ ‹ሞቶ ነበር›› የተባለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

እኛም ህልውናችንን መመዘን ከግዘፋዊ ኑባሬ ጋር ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር ከመኖር አንጻር ነው፡፡ መጨነቅ ያለብንም ያለ ዘለዓለማዊ ህልውና እንዳንቀር እንጂ ግዘፋዊ ኑባሬያችንን እንዳናጣ አይደለም፡፡ ዘለዓለማዊ ህልውና ከእምነታችን፣ ከሠራናቸው ሥራዎችና ካተረፍነው መክሊት የሚመነጭ ነው፡፡

ክርስትና የመሞት እንጂ የመግደል ሃይማኖት አይደለም፡፡በክርስትና በመሞት እንጂ በመግደል አክሊል አይገኝም፡፡ ስንክሳራችንን የሞሉት ቅዱሳን በዓላውያን ተገድለው አክሊል ሰማያዊ ያገኙ ናቸው፡፡ ይህንን ያልተረዱ ሰዎች የሚያወጧቸው ስሞች ሊገርሙን አይገባም፡፡

ባይሆን የጎዱን መስሏቸው ታሪካዊና ሀገራዊ ስሕተት ለሚሠሩት ልናዝንላቸው ይገባል፡፡ አሁን ለሚሠሩት ስሕተት ግማሽ ምዕተ ዓመት እንኳን ሳይሞላ እንደሚፀፀቱበት ልንነግራቸው ይገባል፡፡ አሁን ‹‹ስቅሎ ስቅሎ›› የሚሉት የቤተ ክህነቱን ሰዎችም ይህንን ያስታውሱ፡፡ አይሁድ ጌታን ለሮማውያን አሳልፈው ከሰጡ ከ35 ዓመታት በኋላ ጌታን አሳልፈው የሰጧቸው ሮማውያን በጥጦስ አማካኝነት በእነርሱም ላይ ዘምተው እነርሱንም ከተማቸውንም አጥፍተዋቸዋል፡፡

እነርሱም፣ እነዚያም፣ እኛም ወደ ውጭ እያየን ችግሮቻችንን ከውጭ ከመፈለግ ይልቅ ወደ ውስጦቻችን እንመልከት፡፡ ውስጣችንን በደንብ ካየነው በውስጡ በኩል ውጩ በደንብ ያታየናል፡፡ በውጩ በኩል ግን ውስጡን ማየት አይቻልም፡፡ ቁም ነገሩ ‹ምን አሉን›› አይደለም፤ ምንድን ነን? ነው፡፡  እንዳንሆን እንጂ እንዳይሉን መከላከል አንችልምና፡፡ 

በዓባይ ዳር በሚገኝ መንደር የምትኖር አንዲት ወፍ ነበረች፡፡ በዚያ ወንዝ ለሚዋኙም ሆነ ለሚሻገሩ ደምፅዋን አሠማምራ ትዘምር ነበረች፡፡ ደግሞ ላባዎቿ በኅብር ቀለማት የተሞሉ ነበሩ፡፡ እርሷ ላይ የሌሉ የአዕዋፍ ቀለማት አልነበሩም፡፡ ዝማሬና ዜማዋ ከቶ አይቀየሩም፡፡ በዚህም የተነሣ ዝማዋን ለምደውት አብረዋት የሚያዜሙ ብዙዎች ነበሩ፡፡ በዙሪያዋ ያሉ አዕዋፍ፣ ከወንዙ ለመጠጣት የሚመጡ አራዊት፣ በወንዙ ውስጥ የሚገኙ ዐሣት አብረዋት ያቀነቅናሉ፡፡ እንኳንና በነፍስ የሚኖሩ ሰዎችና በደመ ነፍስ የሚንቀሳቀሱ እንስሳት ቀርተው ዕጽዋት እንኳን እንደ ቅኔ ማኅሌት እንደ ገባ ደብተራ አብረዋት ያሸበሽባሉ፡፡ የእርሷ ዝማሬ ምንም የማይመስላቸው በወንዙ ዳር የተጎለቱት ድንጋዮች ብቻ ናቸው፡፡

እንዲህ እያለች ስትኖር ለዐቅመ ዕንቁላል ደረሰች፡፡ ጎጆ ልትቀልስም አሰበች፡፡ እንጨትና ሣር ሰብስባ ቤቷን የአንድ ጎጆ ባጥ ሥር መቀለስ ጀመረች፡፡ እንጨትና ሣር ደልድላ ጭድ በመካከሉ ልታስቀምጥ ስትል የሠፈሩ ልጆች መጡና በድንጋይና በእንጨት ፍርስርሱን አወጡባት፡፡ እርሷ ለመሥራት አንድ ወር የፈጀባትን እነርሱ ለማፍረስ አፍታም አልወሰደባቸው፡፡ ልጆቹ ጎጆዋን አፍርሰው የጀግንነት ስሜት ተሰምቷቸው እየሳቁና እየተደሰቱ ሄዱ፡፡ እርሷ ግን መከራዋን ታቅፋ ቀረች፡፡ መገንባት እንደ ማፍረስ መች ቀላል ነውና፡፡

መቼም ያለ ጎጆ አይኖር፤ ያለ ጎጆም ዕንቁላል አይጣል፡፡ ያለ ጎጆም ጫጩት አይፈለፈል፡፡ አማራጭ አልነበራትምና ዛፍ ላይ ሣርና እንጨቱን መሰብሰብ ቀጠለች፡፡ ልጆቹ ዐውቀው እንዳያፈርሱባትም በቅጠል ሸፈንፈን አደረገችው፡፡ ዕንቁላሉ መደላድል እንዲያገኝም ጭድ በመካከሉ ረበረበችበት፡፡ ነፋስ ወዝውዞ እንዳይጥለው በልጥ ከግንዱ ጋር ጠለፈችው፡፡ የፀሐይ ብርሃን እንዲያገኝም በስተ ምሥራቅ በኩል በር ሠራችለት፡፡ ከሥራዋ እፎይ ብላ ዕንቁላሏን ልትጥል ስትደላደል ግን እንደ አውሎ ነፋስ የሚያስገመግም ድምፅ ከወደ ዛፉ አካባቢ ሰማች፡፡ ድምፁም ወደ እርሷ ጎጆ እየቀረበ መጣ፡፡

ጎጆዋ ተነቃነቀ፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ የመጣ መሰለ፡፡ ቱር ብላ ወጣችና ዙሪያዋን እያንዣበበች ተመለካከተች፡፡ የሰማይ ስባሪ የሚያህል አሞራ እርሷ ጎጆ የሠራችበት ዛፍ፣ ያውም ጎጆው ከተንጠለጠለበት ግንድ ላይ ክንፉን እያማታ ቆሟል፡፡ አንዳች የሚበላ አጥንት በምንቃሩ ወሽቆ ከሥጋው ጋር ይታገላል፡፡ እርሱ ከሥጋው ጋር በታገለ ቁጥር የእርሷ ጎጆ ይነቃነቃል፡፡ ክንፉን ግራና ቀኝ ባማታው ቁጥር ኃይለኛ ነውጥ ይፈጥራል፡፡ ነውጡ በተፈጠረ ቁጥርም የእርሷ ጎጆ ይፈርሳል፡፡ አሞራው ጎጆዋን በግማሽ አፍርሶት ሄደ፡፡ እርሷም በዚያ አሳዛኝ ዝማሬዋ ታስተዛዝል ጀመር፡፡

እያስተዛዘለች እያለ አሞራው አሁንም እንደገና ከእርሱ ቁመት የማይተናነስ ሙዳ ሥጋ ይዞ መጣ፡፡ ለክፋቱ ደግሞ እዚያው ግንድ ላይ ቆሞ ቀሪውን የወፍ ጎጆ ይነቀንቀው ጀመር፡፡ አሞራው አራተኛ ጉርሻ ላይ ሲደርስ ጎጆው ሙሉ በሙሉ ፈረሰ፡፡ የወፏም ዝማሬ ወደ እንጉርጉሮ ተለወጠ፡፡የት ትሂድ? የትስ መሄጃ አላት? ወፍ ባትሆን ተመኘች፡፡ ግን ወፍ ናት፡፡ አሞራው ለመብላት ሲል ጎጆዋን ያፈርሳል፡፡ እርሷ ግን ጎጆዋን እሠራ ብላ የአንዲት ፍሬ ፍርካሽ እንኳን ለመቅመስ ዕድል አልነበራትም፡፡

አዝና አዝና ስትጨርስ የግድ ነውና ጎጆዋን ለመሥራት እንደገና ፈለገች፤ እንደገና አሰበች፡፡ እንደገናም ሣርና እንጨት፣ ቅጠልና ጭድ ፍለጋ መንከራተት ጀመረች፡፡ የነበረው እንዳልነበረ ሆኗልና እንደገና ሀ ብላ ወጠነች፡፡ አሁን ዜማዋ ከፊል እንጎርጉሮ፣ ከፊል ምሬት፣ ከፊል ደግሞ ተስፋ ሆኗል፡፡ ተስፋ ያልቆረጠችው ተስፋ ያለው ነገር አግኝታ አይደለም፡፡ ተስፋ ከመቁረጥ የሚሻል ሆኖ እንጂ፡፡

አሁን ከሰውም ከእንስሳትም ርቃ ዓባይ ዳር በሚገኝ የደንገል ዛፍ ላይ ጎጆዋን መሥራት ጀመረች፡፡ ምናልባት በዓለም ከመኖር ብሕትውናው ይሻል ይሆን ብላ፡፡ ‹‹ወይከውን ከመ ዕጽ እንተ ትክልት ኀበ ሙሐዘ ማይ – በወንዝ ዳር እንደተተከለች ተክል ይሆናል፤ እንተ ትሁብ ፍሬሃ በበጊዜሃ – ፍሬዋን በየጊዜው እንደምትሰጥ፤ ወቆጽላኒ ኢይነግፍ – ፍሬዋም እንደማይደርቅ›› የሚለውን አስባ፡፡

እንደ ገና ድካም እንደገና ልፋት፡፡ ጎጆዋን ልትቀልስ፣ ዕንቁላሏን ልትጥል፤ ጫጩት ልትፈለፍል፡፡ ከመጀመሪያው ቤት ሁለተኛው፣ ከሁለተኛውም ሦስተኛው ከበዳት፡፡ እንጨቱ እየተማገደ፣ ሣሩ እየተመደመደ፣ ጭዱም እየተወሰደ አልቋል፡፡ ለምለሙ ጊዜ አልፎ የበጋው ደረቅ ወቅት መጥቷል፡፡ በቅርብ ይገኝ የነበረው ነገር ሁሉ ርቋል፡፡ ግን ምን ይደረጋል፡፡  

ክንፏን እስከሚያማት ድረስ ባክና በሰበሰበችው እንጨት፣ ሣርና ጭድ ጎጆዋን ለሦስተኛ ጊዜ ቀለሰች፡፡ አንድ ሦስት ቀን የቀደመው መዓት ይመጣል ብላ ብትጠብቅ ምን የለም፡፡ እንዲህ ከሰውም ከእንስሳም መራቁ ይሻላል ብላ በምርጫዋ ተደሰተች፡፡ አንድ አንድ እያለችም ዕንቁላሏን መጣል ጀመረች፡፡ ችግሩ ግን ያን ጊዜ መጣ፡፡ እርሷ ዕንቁላሏን ጥላ ምግብ ፍለጋ ሄዳ ስትመለስ ዕንቁላሏን አታገኘውም፡፡ ሁለት ሦስት ቀን ወድቆ ይሆናል ብላ አሰበች፤ ጥፋቱም የእርሷ እንደሆነ አመነች፡፡ እንዳይወድቅ ለማድረግም ጎጆዋን እንደገና አጠባበቀች፡፡ በአራተኛው ቀን ግን አሁንም ዕንቁላሏን አላገኘችውም፡፡ ፈለገችው፡፡ እንዳች ስባሪ በአካባቢው አላገኘችም፡፡ በአምስተኛው ቀን ዕንቁላሏን ጥላ ከጎጆዋ ወጣችና እልፍ ብላ በሌላ ዛፍ ላይ ተቀምጣ የሚሆነውን ማየት ጀመረች፡፡

እነሆ ጉዱ፡፡

እርሷ ወጣ ከማለቷ አንድ ዕባብ በግንዱ ላይ እየተሳበ መጣ፡፡ ዕባቡ የመጣው ከወንዙ ዳር ነው፡፡ አስጠሊታ ራሱን ወደ ጎጆዋ አዝልቆ ዕንቁላሏን ሰለቀጠው፡፡ ነፍስ አልነበራትም እንጂ ድንጋጤው ነፍሷን ያወጣው ነበር፡፡ አሁን የከፋ አደጋ መጣ፡፡ ቤቷ አይደለም የፈረሰው፤ ዕንቁላሏ ነው የሚበላው፡፡ ምትኳ፣ ዘሯ፣ ተስፋዋ፣ ሀልወቷ፣ ኑባሬዋ ነው የሚበላው፡፡ ዕንቁላል እንዳትጥል አልተከለከለችም፤ የምትጥለው ግን ለሌላ ሆነ፡፡ እርሷ አንድ ቀን ዕንቁላል መጣል ታቆማለች፡፡ ያን ጊዜ ህ ዕንቁላል የለመደ ዕባብ እርሷን መብላት ይጀምራል፡፡ ከሁሉም ተገላገልኩ ብላ የመጣችበት ቦታ ከሁሉም የባሰ ሆነ፡፡

በረረረች፣ ከነፈች፣ ወጣች፣ ወረደች፣ ከነፋሱም ጋር ሄደች፣ ከነፋሱም በተቃራኒም ነጎደች፡፡ መሬት ወረደች፣ ወንዝ ውስጥ ገባች፡፡ በመጨረሻ ደከማት፡፡ ሲደክማት አንድ ዛፍ ላይ ቆማ እንዲህ እያለች ታንጎራጉር ጀመር፡፡

ኦ እለሎ፣ ኦ እለሎ

ኦ እለሎ፣ ኦ እለሎ

ወዴት ሄጄ ልኑር

ወዴት ሄጄ ልሥራ፤

ባጡ ሥር ስሠራ

ልጆቹ መከራ፣

ዛፉ ላይ ስሠራ

አሞራው መከራ፣

ወንዙ ዳር ስሠራ

ዕባቡ መከራ፡፡

ወዴት ሄጄ ልኑር፣

የት ሄጄ የት ልሥራ፤

የት ውዬ የት ልደር፤

 © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው

ሰውዬው ዛፍ ሥር ቁጭ ብሎ ያዳምጣል፡፡ ወፏን፡፡ የሚመስለው ግን የተመሰጠ በገና ደርዳሪን፣ የተሸለመ መሰንቆ መቺን፣ ከብቶቹ ለምለም ሣር ያገኙለት ባለ ዋሽት እረኛን እንደሚያዳምጥ ነው፡፡ ዐሥር ጊዜ አንገቱን ይነቀንቃል፡፡ የወፏ ዝማሬ ገብቶታል መሰል፡፡ በግጥሙ ቤት፣ በስንኙ አወቃቀር፣ በሐረጉም ቅኔ እንደረካ ሰው ነው ሁኔታው፡፡ ሰምና ወርቁን እንዳገኘ ቅኔ ሰሚ አንገቱን ግራ ቀኝ ይወዘውዛል፡፡ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ወፏ ራሷ ደንግጣ ልትበርር እስክትደርስ ድረስ ለወፏ ዝማሬ የፊልም ቤት ጭብጨባ ያጨበጭባል፡፡

ይኼ ሁሉ ሲሆን አሻግሮ ሌላ ሰው ያየዋል፡፡ ያውም የሰውየውን ጤንነት እየተጠራጠረ፡፡ መጀመሪያ የሆነ ሌላ ነገር እያዳመጠ መስሎት ነበር፡፡ ጠጋ ሲል ምንም ሌላ ነገር አጣ፡፡ የሚያነብም መስሎት ነበር፡፡እጁ ግን ባዶ ነው፡፡ በአካባቢውም አንገቱን አዟዙሮ የሚያወጋው አንዳች ነገር ካለ ብሎ ፈለገ፡፡ ሰውዬው ብቻውን ነው፡፡ የሚገርመው ግን ወፍ አዳማጩ ሰው መንገደኛውን አላየውም፡፡ እርሱ ተመስጦ ላይ ነው፡፡ አንዳች ነገር ልቡን ነክቶት እንገቱን ከላይ ወደ ታች እየነቀነቀ ነው፡፡

መንገደኛው ሰው ጠጋ አለው፡፡ ወፍ አዳማጩ ሰው ቀና አለ፡፡ በእጁ እንዲቀመጥ ጋበዘው፡፡ መንገደኛው እየተገረመ ተቀመጠ፡፡

‹‹አንዳች ነገር መጠየቅ እችላለሁ›› አለ መንገደኛው ሰው፡፡

‹‹ድምጽህን ቀንሰህ እንጂ አዎ›› አለው የሹክሹክታ ያህል››

‹‹እ-ሺ – ምንድን ነው የምታዳምጠው›› አለው በጆሮው የመናገር ያህል ቀስ ብሎ፡፡

‹‹ወፏን››

መንገደኛው በኤሌክትሪክ ወንበር ላይ ያስቀመጡት ያህል ተስፈንጥሮ ተነሣ፡፡ ከሆነ አንድ ጠንቋይ ጋር የተቀመጠ መሰለው፡፡ ወፍ ከሚሰማ ጠንቋይ፡፡ ደግሞስ ወፏ ምን እያለች እንደሆነ ማን ያውቃል፡፡ የምትናገረው ስለ እርሱ ቢሆንስ፡፡ ወፍ አዳማጩ ሰው ግን ግራ እጁን ይዞ ጎተተና እንደገና አስቀመጠው፡፡

‹‹ለምን ደነገጥክ?›› አለው ቀስ ብሎ፡፡

‹‹አይ ታስፈራለህ፡፡ ልሄድ ነው በቃ›› አለ እጁን ለማስለቀቅ እየሞከረ

‹‹ይልቅ ሞኝ አትሁን፤ ተቀመጥና ወፏን አዳምጥ፡፡ ስንት ነገር ታገኛለህ መሰለህ›› አለው፡፡

መንገደኛው ድንጋጤውና ፍርሃቱ ጨመረበት፡፡ ‹‹አልችልም፤ እኔ ወፍ ማዳመጥ አልችልም›› አለው መንገደኛው፡፡

ወፍ አዳማጩ ሰው በቀሰስታ ‹‹እኔ አሳይሃለሁ መንገዱን›› አለው፡፡ መንገደኛው አሁን ጭራሽ ባሰበት፡፡ እርሱንም ጠንቋይ ሊያደርገው ያሰበ መሰለው፡፡ ዘወር ዘወርወር ብሎ አካባቢውን ማተረ፡፡ በሩቁ በሚታየው የማቋረጫ መንገድ በኩል እንደርሱ ያሉ መንገደኞች ሲጓዙ ይታዩታል፡፡ እርሱም እንዳች ማረፊያ ጥላ ፍለጋ ነበር ወደዚህ አሳብሮ የመጣው፡፡ የገጠመው ግን ወፍ የሚያዳምጥ ሰው ነው፡፡ በርግጥ ይህ ዛፍ በመንገድ ለሚደክሙ መንገደኞች አሳብረው የሚያርፉበት ነበር፡፡ እርሱም ብዙ ጊዜ እዚያ ዐርፎ ያውቃል፡፡ እዚያ ሲያርፍም የወፎችን ዝማሬ በአልፎ ሂያጅ ልቡ ሰምቶ ያውቃል፡፡ በአካባቢው ትልቁ ዛፍ ያ ስለሆነ ወፎቹ ይመርጡታል፡፡ ያ ዝማሬያቸው ግን የዚህን ሰውዬ ያህል መስጦትም፣ አስደስቶትም አያውቅም፡፡

‹‹አሁን እንዴው የምርህን ወፍ እያዳመጥክ ነው›› አለው መንገደኛው፡፡

‹‹አንተ ግን ምንም አይሰማህም›› ብሎ መለሰለት አዳማጩ፡፡

‹‹በቃ ያው የወፍ ዜማ፤ በቃ፡፡ የወፍ ዜማ ብርቅ ነው እንዴ››

‹‹ወፏ የምትለውንስ ትሰማለህ››

‹‹ልጅ ሆነን የወፍ ቋንቋ እያልን እንጫወት ነበር፡፡ ያ ግን የወፍ ቋንቋ አይመስለኝም፡፡ ሰውም የወፍ ቋንቋ የሚያውቅ አይመስለኝም››

‹‹የወፍን ቋንቋኮ ማንም ሰው መስማት ይችላል››

‹‹እኔ ለምሳሌ አልችልም›› ጆሮውን በእጆቹ ዳሰሰ፡፡

‹‹ትችላለህ››

‹‹አንተ እኔን ታውቀኛለህ›› በጥንቆላው እንዳያውቀው በመፍራቱ ‹አላውቅህም› እንዲለው ፈለገ፡፡

‹‹ሰው አይደለህም እንዴ››

‹‹ብሆንስ››

‹‹ከሆንክማ ትችላለህ ማለት ነው፡፡ ሰው ሁለት ዓይነት ጆሮ አለው፡፡ የሥጋ ጆሮና የልቡና ጆሮ ወይም እዝነ ሥጋ እና እዝነ ልቡና፡፡ በሥጋ ጆሮው ማዳመጥ የሚችለው የሰው ቋንቋ፣ መስማት የሚችለውም አልፎ ሂያጅ ድምጽ ነው፡፡ በልቡና ጆሮው ግን ወፍንም፣ እንስሳንም፣ ወንዝንም፣ መብረቅንም፣ ተራራንም፣ ዛፍንም መስማት ይችላል›› አለው፡፡ ከበደ ሚካኤል ይህንን ችሎታቸውን ተጠቅመው ነው ደመናና ጽጌረዳ ሲያወሩ የሰሙትን የነገሩን፡፡ ‹ጽጌረዳና ደመና› የሚለውን ግጥማቸውን ታውቀዋለህ?

‹‹እሺ አንተ ከወፏ ምን ሰማህ?›› አለው መንገደኛው፡፡

‹‹ምን የመሰለ ቅኔ፣ ምን የመሰለ ዕውቀት፣ ምን የመሰለ የሕይወት ትርጓሜ››

‹‹እስኪ አንዱን ንገረኝ››

‹‹ወፏ ምን አለች መሰለህ፡፡ ትዘምር የነበረው ስለ ዛፉ ነው፡፡ ዛፍ ሆይ አትመካ፣ እኔን አስጠለልኳት፣ አሳረፍኳት ብለህ አትመካ፡፡ በቅርንጫፍህ አትመካ፡፡ ለእኔ ዋናው ያንተ ቅርንጫፍ አይደለም፡፡ለእኔ ዋናው የራሴ ክንፍ ነው፡፡ ቅርንጫፍህ ሊቀር ይችላል፡፡ አንተም አላስጠልልም ልትል ትችላለህ፡፡ ያ ያንተ መብት ነው፡፡ እኔ ግን የምመካውም የምተማመነውም በገዛ ክንፎቼ ነው፡፡ ክንፎቼ ካሉልኝ የትም እሄዳለሁ፡፡ ሌላ ዛፍ ላይ ዐርፋለሁ፡፡ ሌላ ቤት ላይ እወጣለሁ፡፡ በተራሮች ላይ እቆማለሁ፡፡ በመስኩ ላይ እራመዳለሁ፡፡ ስለዚህ ልሰበር ነው፤ ልወድቅ ነው፤ ልጥልሽ ነው፤ ልወዛወዝ ነው እያልክ አታስፈራራኝ፡፡ ወፍ የተባልኩት ከእኔ ጋር ባሉት ክንፎቼ እንጂ አንተ ጋር ባሉት ቅርንጫፎችህ አይደለም፡፡ ወፍ የሆንኩት እኔ ጋር ባሉት ላባዎቼ እንጂ አንተ ጋር ባሉት ቅጠሎች አይደለም፡፡ ወፍ የተባልኩት በቆምኩበት እግሬ እንጂ በቆምኩበት ግንድ አይደለም፡፡ እኔ ባለኝ እንጂ በምትሰጠኝ አልተማመንም፤ እኔ በያዝኩት እንጂ በተለገስኩት አልመካም፡፡ – ይህንን ነበር የምትዘምረው››

መንገደኛው ተገረመ፡፡ የወፍ አድማጩን ችሎታም አደነቀ፡፡ አብልጦ ደግሞ የወፏን ዝማሬ አደነቀ፡፡ ወፍኛ ቢችል ኖሮ መወድስ ያደርሳት ነበር፡፡

‹‹ቆይ አንተ ይህንን የወፍ ቋንቋ ከየት ተማርከው›› መንገደኛው ጠየቀ፡፡ ቅድም እንዳልፈራ ሁሉ አሁን ለማወቅ ጓጓ፡፡ የማያውቁት ነገር ምንጊዜም ያስፈራል፡፡ መቃብር ለመቃብር ቆፋና ለቀባሪ እኩል አያስፈራም፡፡

‹‹ይህ ነገር የምትማረው አይደለም፡፡ ሰው በመሆንህ የምታገኘው ነው፡፡ ግን ማሳደግ ይፈልጋል፡፡ እዝነ ልቡናህን መጠቀም ይፈልጋል፡፡ ለሕይወት ትርጉም መስጠትን ይፈልጋል፡፡ ዝም ብሎ የተፈጠረ፣ ዝም ብሎም የሚኖር፣ ዝም ብሎ ነገር የለምና፤ ዝም ብለህ የምታልፈው ዝም ብሎ ነገር ሊኖር አይገባም፡፡ ኑሮ ከንቱ አይደለችም፤ ሕይወት ቂላቂል አይደለችም፡፤ ሕይወት ቅኔ ናት፡፡ እየፈታህ የምትማርባትም የምትደመምባትም፡፡ ፍጡራን ሁሉ ልዩ ልዩ ዓይነት ቅኔዎች ናቸው፡፡ ማዳመጥ፣ ማየት፣ መንካት፣ መመርመር፣ መተንተን የሚፈልጉ ቅኔዎች፡፡ አየህ በሥጋ ጆሯችን ብዙ ቸበርቻቻዎች ስንሰማ ስለምንኖር የሕይወትን ዝማሬ የመስማት ዕድላችን ጠብቧል፡፡ አንት ግን እይ፣ ስማ፤ አካባቢውን፣ የዐየሩን ሁኔታ፣ ድምጹን፣ የፍጥረትን እንቅስቃሴ፣ የፍጥረትን የርስበርስ ተግባቦት አድንቅ፤ አድንቅና ፍታው፡፡ ድምጽ ዝማሬ፣ ትርዒትና መልእክት የሌለው ፍጡር የለም፡፡ ዝማሬያቸው ግን የሚሰማው፣ ትርዒታቸው ግን የሚታየው፣ መልእክታቸው ግን የሚረዳው ለሰው ነው፡፡ሰው ነው የሚፈታላቸው፡፡ ፍቺው ግን እንደየዕውቀታችን፣ እንደየኑሯችን፣ እንደየ ዐቅማችን፣ እንደየመረዳታችን፣ እንደየ ባሕላችን ሊለያይ ይችላል፤ የወፏን ዝማሬ እንተ ብትሰማው ሌላ ይሆናል የምትረዳው፡፡ ወፏ እንደዚያ አላለችም፡፡ እኔ ነኝ እንደዚያ የተረዳኋት፡፡ መድኃኒት እንደየበሽታው ነው፡፡

‹‹ያሬድ ያያትን፣ ሰባት ጊዜ እየወደቀች የተነሣችውን ትል አንተ ብታያት ኖሮ ሌላ ነገር ልትረዳ ትችል ይሆናል፡፡ ያሬድ ግን ወድቆ መነሣትን፣ ታግሎ ማሸነፍን፣ ተስፋ አለመቁረጥን፣ አለመታከትን ከእርሷ ተማረ፡፡እርሷ ተጓዘች፡፡ እርሱም ጉዞዋን ተረጎመላት፡፡ ስለ ጳልቃን ጣልቃን፣ ስለ ከራድዮን፣ ስለ ዝሆን (ውርዝው ነጌና ዐቢይ ነጌ)፣ ስለ አንበሳ፣ ስለ ቀበሮ፣ ስለ ቁራ፣ ስለ ርግብ፣ ስለ ጉንዳን የምንሰማቸው ታሪኮች ሁሉ የእነርሱን አነዋወር ተመልክቶና አዳምጦ ለሕይወት የሚበጅ ትርጉም ከመስጠት የመጣ ነው፡፡

‹‹እይ፣ ዝም ብለህ ግን አትይ፤ ስማ፣ ዝም ብለህ ግን አትስማ፡፡ ዓለም መጽሐፍ ናት፡፡ ሚሊዮን ገጾች ያሏት፡፡ ገጹ እያንዳንዱ ገጠመኝህ ነው፡፡ ብልሆች እያንዳንዱን ገጽ ያነቡታል፡፡ ይማሩበታልም፡፡ ሞኞች ግን ገጹን እያጠፉ ብቻ ያልፉታል›› ይሄው ነው ወዳጄ፡፡

አሁን መንገደኛው ራሱ የወፏን ዝማሬ መስማት ጀመረ፡፡ አንገቱንም መነቅነቅ ቀጠለ፡፡ እርሱ የሰማውን ደግሞ ሌላ ደራሲ ይነግረን ይሆናል፡፡

ፍራንክፈርት፣ ጀርመን