የ2006 የበጎ ሰው ሽልማት ደረሰ
ከዚህ በፊት በዚሁ ጦማርና በልዩ ልዩ ሚዲያዎችም በተነገረው መሠረት ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው መልካም ሠርተዋል የተባሉ ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያን ተጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ እጅግ የተሻሉትን ለመምረጥ የመጨረሻው ሂደት እየተከናወነ ነው፡፡
መርሐ ግብሩ የሚካሄደው ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን ከቀኑ በ 8 ሰዓት አዲስ አበባ ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው እሊሌ ሆቴል ሲሆን፣ ተሸላሚዎች፣ ተጋባዥ እንግዶች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎችም በተገኙበት ይከናወናል፡፡ ሽልማቱ የሚከናወነው በሰባት ዘርፎች ነው፡፡
- የሀገራዊ ዕርቅና ሰላም ዘርፍ
- የበጎ አድራጎት(ሰብአዊነት) ዘርፍ
- የኪነ ጥበብ/ ሥነ ጥበብ ዘርፍ
- ግብርናና ኢንዱስትሪ ዘርፍ
- መንግሥታዊ ኃላፊነትን በብቃት የመወጣት ዘርፍ
- ቅርስ ጥበቃ፣ ባሕልና ቱሪዝም ዘርፍ
- ሳይንስና ቴክኖሎጂ/ ጥናትና ምርምር ዘርፍ
በእነዚህ ዘርፎች የተመረጡ ተሸላሚዎች በመጨረሻ መራጮች ድምጽ ከተሰጠባቸው በኋላ ይታወቃሉ፡፡ የሽልማቱ ዋና ዓላማ ገንዘብ አይደለም፡፡ በጎ ሰዎችን በማበረታታት፣ ለበጎ ሰዎችም ዕውቅና በመስጠት ለሀገር ሰው ማትረፍ እንጂ፡፡ ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያ ወዳጆች የሆኑ ጀግኖችን ማሳወቅ ሥራቸውም ለትውልድ አርአያ እንዲሆን ማድረግ እንጂ፡፡ የመመሰጋገንንና የመበረታታትን ባሕልም ማበልጸግ እንጂ፡፡
በዕለቱ መገኘት ለሚፈልጉ በቅርቡ የመግቢያ ካርዱ የሚገኝበትን መንገድ እንጠቁማለን፡፡