‹‹እግዚአብሔርስ ምን አለ?››
click here for pdf
ሰሞኑን ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ ‹‹ሊያፈርሱት ነው›› የሚል ዜና በኅትመት ሚዲያዎችም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ይታያል፣ ይሰማል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍት ግን አንድ መንፈሳዊ ተቋም ሊፈርስ የሚችለው በውጭ ኃይል ጫናና ዐቅም ሳይሆን በውስጣዊ ምክንያቶች መሆኑን ይነግሩናል፡፡ ኢየሩሳሌምን ናቡከደነፆር ያፈረሳት ናቡከደነፆር ኃያልና ተዋጊ ስለነበረ አይደለም፡፡ የባቢሎኑ ናቡከደነፆር መሣሪያ እንጂ መነሻ አልነበረም፡፡ ኢየሩሳሌም የፈረሰችው እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን አሳልፎ ስለሰጣት ነበር፡፡ ኢየሩሳሌም የቃል ኪዳን ከተማ መሆኗ ቀርቶ ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ የሚቀልዱባት፣ ካህናቱም በአገልግሎታቸው የሚያሾፉባት ከተማ ሆነች፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ ለዚህም ነበር ነቢዩ ዳንኤል በጸለየው ጸሎት ላይ ‹‹ኃጢአትን ሠርተናል፣ በድለንማል፣ ክፋትን አድርገናል፣ ዐምፀናልም፣ ባሪያዎችህንም ነቢያትን አልሰማንም›› በማለት የገለጠው፡፡
አሁንም የሚጠቅመን ነገር እግዚአብሔር ለሌሎች አሳልፎ እንዲሰጠን የሚያደርግ ነገር ሠርተናል ወይስ አልሠራንም? የሚለውን ማየት ነው፡፡ ለመዋጥ የሚያበቃ ምክንያት ከኛ ዘንድ ከሌለ በቀር አንበሳው ስላገሣ ብቻ አይውጠንም፡፡ እኛ ከእግዚአብሔር ጋር መሆናችንን ርግጠኞች እንሁን፡፡ እግዚአብሔር ከኛ ጋር ለመሆኑ ርግጠኞች ነንና፡፡ ውስጣችን ለእግዚአብሔር የተመቸ ለመሆኑ ርግጠኞች እንሁን፣ እግዚአብሔር ለእኛ የተመቸ ነውና፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ዝግጁ እንሁን፡፡ በክርስትና ውስጡ ውጩን ይስበዋል እንጂ፣ ውጩ ውስጡን አይስበውም፡፡ ‹‹ዝናብም ወረደ፣ ጎርፍም መጣ፣ ነፋስም ነፈሰ፣ ያንንም ቤት መታው በዐለት ላይ ስለተመሠረተ ግን አልወደቀም›› ይላልና፡፡ ያልወደቀው ስላልተመታ ሳይሆን መሠረተ ጽኑዕ ስለነበረ ነው፡፡
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ዐርፈው አቡነ ቴዎፍሎስ ዐቃቤ መንበር እያሉ ቤተ ክህነቱ ይታመስ ነበር አሉ፡፡ የቤተ ክህነቱ የዘር አስተሳሰብ እያቆጠቆጠ የመጣበት ዘመን ነበርና ‹‹ቀጣዩ ፓትርያርክ ማን ይሆን?›› ከሚለው ይልቅ ‹‹ቀጣዩ ፓትርያርክ ከነማን ወገን ይሆን?›› የሚለው ብዙዎችን የሚያስጨንቅበት ጊዜ ነበር፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ እንደ ዘመነ ሴዴቅያስ የሐሰት ነቢያትን በሆኑት በመሰል ባሕታውያን በኩል ‹ቀጣዩ ፓትርያርክ እገሌ ነው፣ ራእይ አይቻለሁ›› ያሰኙም ነበር፡፡
በወቅቱ ዐቃቤ መንበር ለነበሩት ለአቡነ ቴዎፍሎስ ብዙ ሰዎች እየሄዱ ‹‹እገሌ ፓትርያርክ ቢሆኑ፣ ሕዝቡ እገሌን እያለ ነው፣ መኳንንቱ እገሌን እያሉ ነው፣ ባሕታውያኑ እገሌ ይሆናሉ ብለው ትንቢት እየተናገሩ ነው፣ ቤተ ክህነቱም እገሌን እያለ ነው›› እያሉ ይነግሯቸው ነበር፡፡ ሁሉንም የሰሙት አቡነ ቴዎፍሎስም ‹‹ባሕታውያኑም፣ ሕዝቡም፣ መኳንንቱም፣ ቤተ ክህነቱም ያሉትን ሰምቻለሁ፡፡ እግዚአብሔርስ ምን አለ?›› ብለው ጠየቁ ይባላል፡፡
አሁንም የሚጠቅመው ከልዩ ልዩ ቦታ በሚነፍሰው ነፋስ መሸበር ሳይሆን እንደ አቡነ ቴዎፍሎስ ‹‹እግዚአብሔርስ ምን አለ?›› ብሎ መጠየቅ ነው፡፡ ሁሉም የየራሱን ሊወስን፣ ሊፎክር፣ ሊነሣ ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ካልወሰነ ግን የሚሆን አንዳች ነገር የለም፡፡ የእግዚአብሔርን ውሳኔ የሚያመጣው ደግሞ የወደረኞቹ ኃይል ሳይሆን የራሳችን ስንፍና ነው፡፡
ታዋቂው ገጣሚ ጸጋዬ ገብረ መድኅን በጻፈው የቴዎድሮስ የመቅደላ ስንብት ላይ ‹‹ከሠራሁት ነገር ይልቅ ያልሠራሁት ነው የሚቆጨኝ›› እንዳሉት፡፡ ያልሠራነው ነገር እንዳይኖር፣ ምክንያት የሆንነው ነገር እንዳይኖር፣ ልንፈጽመው ሲገባን ያልፈጸምነው ነገር እንዳይኖር፣ ልናስበው ሲገባን ያላሰብነው ነገር እንዳይኖር ነው መፍራት፡፡ እንጂ ሊመጣ ያለውን ነገር አይደለም መፍራት፡፡ ክርስቲያን ሞትን አይፈራም አሟሟቱን እንጂ፡፡
ሰውዬው በሩን በጠንካራ ብረት ዘግቶ ሲጠብቅ ያየው ጎረቤት ‹‹ምነው እንዲህ ታጠብቀዋለህ፤ አላህን አታምንም እንዴ ብሎ ቢጠይቀው ‹‹አላህንም አምናለሁ፣ በሬንም አጠብቃለሁ›› እንዳለው በእግዚአብሔር ያለንን እምነት ማጽናት በራችንንም ማጥበቅ ያስፈልገናል፡፡ የአመራር አቅማችን እንዴት ነው? መደበኛ አገልጋዮቻችንና አባሎቻችን እንዴት ናቸው? በአመራራችን ደስተኞች ናቸው? ማዕከሎቻችን እንዴት ናቸው? ከሊቃነ ጳጳሳትና ከአህጉረ ስብከት ጋር ያላቸው ግንኙነት መልካም ነው? ግቢ ጉባኤያቱ እንዴት ናቸው? ሚዲያዎቻችንስ በቀድሞው ጥንካሬና ብስለት ላይ ናቸው? ሌሎችንም በሮች ማጠባበቁ የሚበጅ ይመስለኛል፡፡
ከዚያ ወዲያ ግን፣ የምንችለውን ሁሉ ካደረግን በኋላ ግን፣ የዐቅማችንን ሁሉ ከፈጸምን በኋላ ግን ‹‹እግዚአብሔር ምን አለ? የሚለው እንጂ እነ እገሌ ምን አሉ›› የሚለው ሊያሳስበን እንጂ ሊያስጨንቀን አይገባም፡፡ ቂጣ ከሆነ ይጠፋል፣ ሺልም ከሆነ ይገፋል፡፡
እንደ ክርስትና ትምህርት ከሆነ ህልውና ከግዘፋዊ ኑባሬ ጋር አይደለም የሚያያዘው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ከሚገኝ ሕይወት እንጂ፡፡ ግዘፋዊ ኑባሬ ማለት እታየ እየተደሳሰሰ፣ አካላዊ ቦታ ይዞ መኖርን ነው፡፡ እያሉ የሌሉ እንዳሉት ሁሉ እንደሌሉ የተቆጠሩ ደግሞ አሉ፡፡ ሰማዕታት በግዘፋዊ ኑባሬ አሁን በዚህ ዓለም የሉም፡፡ ነገር ግን ዘለዓለማዊ ህላዌ አላቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ግዘፋዊ ኑባሬ እያላቸው እየበሉና እየጠጡ፣ እየሠሩና እየተንቀሳቀሱ እንደሌሉ የተቆጠሩም አሉ፡፡ የጠፋው ልጅ ወደ አባቱ ሲመጣ ‹ሞቶ ነበር›› የተባለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
እኛም ህልውናችንን መመዘን ከግዘፋዊ ኑባሬ ጋር ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር ከመኖር አንጻር ነው፡፡ መጨነቅ ያለብንም ያለ ዘለዓለማዊ ህልውና እንዳንቀር እንጂ ግዘፋዊ ኑባሬያችንን እንዳናጣ አይደለም፡፡ ዘለዓለማዊ ህልውና ከእምነታችን፣ ከሠራናቸው ሥራዎችና ካተረፍነው መክሊት የሚመነጭ ነው፡፡
ክርስትና የመሞት እንጂ የመግደል ሃይማኖት አይደለም፡፡በክርስትና በመሞት እንጂ በመግደል አክሊል አይገኝም፡፡ ስንክሳራችንን የሞሉት ቅዱሳን በዓላውያን ተገድለው አክሊል ሰማያዊ ያገኙ ናቸው፡፡ ይህንን ያልተረዱ ሰዎች የሚያወጧቸው ስሞች ሊገርሙን አይገባም፡፡
ባይሆን የጎዱን መስሏቸው ታሪካዊና ሀገራዊ ስሕተት ለሚሠሩት ልናዝንላቸው ይገባል፡፡ አሁን ለሚሠሩት ስሕተት ግማሽ ምዕተ ዓመት እንኳን ሳይሞላ እንደሚፀፀቱበት ልንነግራቸው ይገባል፡፡ አሁን ‹‹ስቅሎ ስቅሎ›› የሚሉት የቤተ ክህነቱን ሰዎችም ይህንን ያስታውሱ፡፡ አይሁድ ጌታን ለሮማውያን አሳልፈው ከሰጡ ከ35 ዓመታት በኋላ ጌታን አሳልፈው የሰጧቸው ሮማውያን በጥጦስ አማካኝነት በእነርሱም ላይ ዘምተው እነርሱንም ከተማቸውንም አጥፍተዋቸዋል፡፡
እነርሱም፣ እነዚያም፣ እኛም ወደ ውጭ እያየን ችግሮቻችንን ከውጭ ከመፈለግ ይልቅ ወደ ውስጦቻችን እንመልከት፡፡ ውስጣችንን በደንብ ካየነው በውስጡ በኩል ውጩ በደንብ ያታየናል፡፡ በውጩ በኩል ግን ውስጡን ማየት አይቻልም፡፡ ቁም ነገሩ ‹ምን አሉን›› አይደለም፤ ምንድን ነን? ነው፡፡ እንዳንሆን እንጂ እንዳይሉን መከላከል አንችልምና፡፡