የወፏ ዝማሬ

ሰውዬው ዛፍ ሥር ቁጭ ብሎ ያዳምጣል፡፡ ወፏን፡፡ የሚመስለው ግን የተመሰጠ በገና ደርዳሪን፣ የተሸለመ መሰንቆ መቺን፣ ከብቶቹ ለምለም ሣር ያገኙለት ባለ ዋሽት እረኛን እንደሚያዳምጥ ነው፡፡ ዐሥር ጊዜ አንገቱን ይነቀንቃል፡፡ የወፏ ዝማሬ ገብቶታል መሰል፡፡ በግጥሙ ቤት፣ በስንኙ አወቃቀር፣ በሐረጉም ቅኔ እንደረካ ሰው ነው ሁኔታው፡፡ ሰምና ወርቁን እንዳገኘ ቅኔ ሰሚ አንገቱን ግራ ቀኝ ይወዘውዛል፡፡ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ወፏ ራሷ ደንግጣ ልትበርር እስክትደርስ ድረስ ለወፏ ዝማሬ የፊልም ቤት ጭብጨባ ያጨበጭባል፡፡

ይኼ ሁሉ ሲሆን አሻግሮ ሌላ ሰው ያየዋል፡፡ ያውም የሰውየውን ጤንነት እየተጠራጠረ፡፡ መጀመሪያ የሆነ ሌላ ነገር እያዳመጠ መስሎት ነበር፡፡ ጠጋ ሲል ምንም ሌላ ነገር አጣ፡፡ የሚያነብም መስሎት ነበር፡፡እጁ ግን ባዶ ነው፡፡ በአካባቢውም አንገቱን አዟዙሮ የሚያወጋው አንዳች ነገር ካለ ብሎ ፈለገ፡፡ ሰውዬው ብቻውን ነው፡፡ የሚገርመው ግን ወፍ አዳማጩ ሰው መንገደኛውን አላየውም፡፡ እርሱ ተመስጦ ላይ ነው፡፡ አንዳች ነገር ልቡን ነክቶት እንገቱን ከላይ ወደ ታች እየነቀነቀ ነው፡፡
መንገደኛው ሰው ጠጋ አለው፡፡ ወፍ አዳማጩ ሰው ቀና አለ፡፡ በእጁ እንዲቀመጥ ጋበዘው፡፡ መንገደኛው እየተገረመ ተቀመጠ፡፡
‹‹አንዳች ነገር መጠየቅ እችላለሁ›› አለ መንገደኛው ሰው፡፡
‹‹ድምጽህን ቀንሰህ እንጂ አዎ›› አለው የሹክሹክታ ያህል››
‹‹እ-ሺ – ምንድን ነው የምታዳምጠው›› አለው በጆሮው የመናገር ያህል ቀስ ብሎ፡፡
‹‹ወፏን››
መንገደኛው በኤሌክትሪክ ወንበር ላይ ያስቀመጡት ያህል ተስፈንጥሮ ተነሣ፡፡ ከሆነ አንድ ጠንቋይ ጋር የተቀመጠ መሰለው፡፡ ወፍ ከሚሰማ ጠንቋይ፡፡ ደግሞስ ወፏ ምን እያለች እንደሆነ ማን ያውቃል፡፡ የምትናገረው ስለ እርሱ ቢሆንስ፡፡ ወፍ አዳማጩ ሰው ግን ግራ እጁን ይዞ ጎተተና እንደገና አስቀመጠው፡፡
‹‹ለምን ደነገጥክ?›› አለው ቀስ ብሎ፡፡
‹‹አይ ታስፈራለህ፡፡ ልሄድ ነው በቃ›› አለ እጁን ለማስለቀቅ እየሞከረ
‹‹ይልቅ ሞኝ አትሁን፤ ተቀመጥና ወፏን አዳምጥ፡፡ ስንት ነገር ታገኛለህ መሰለህ›› አለው፡፡
መንገደኛው ድንጋጤውና ፍርሃቱ ጨመረበት፡፡ ‹‹አልችልም፤ እኔ ወፍ ማዳመጥ አልችልም›› አለው መንገደኛው፡፡
ወፍ አዳማጩ ሰው በቀሰስታ ‹‹እኔ አሳይሃለሁ መንገዱን›› አለው፡፡ መንገደኛው አሁን ጭራሽ ባሰበት፡፡ እርሱንም ጠንቋይ ሊያደርገው ያሰበ መሰለው፡፡ ዘወር ዘወርወር ብሎ አካባቢውን ማተረ፡፡ በሩቁ በሚታየው የማቋረጫ መንገድ በኩል እንደርሱ ያሉ መንገደኞች ሲጓዙ ይታዩታል፡፡ እርሱም እንዳች ማረፊያ ጥላ ፍለጋ ነበር ወደዚህ አሳብሮ የመጣው፡፡ የገጠመው ግን ወፍ የሚያዳምጥ ሰው ነው፡፡ በርግጥ ይህ ዛፍ በመንገድ ለሚደክሙ መንገደኞች አሳብረው የሚያርፉበት ነበር፡፡ እርሱም ብዙ ጊዜ እዚያ ዐርፎ ያውቃል፡፡ እዚያ ሲያርፍም የወፎችን ዝማሬ በአልፎ ሂያጅ ልቡ ሰምቶ ያውቃል፡፡ በአካባቢው ትልቁ ዛፍ ያ ስለሆነ ወፎቹ ይመርጡታል፡፡ ያ ዝማሬያቸው ግን የዚህን ሰውዬ ያህል መስጦትም፣ አስደስቶትም አያውቅም፡፡
‹‹አሁን እንዴው የምርህን ወፍ እያዳመጥክ ነው›› አለው መንገደኛው፡፡
‹‹አንተ ግን ምንም አይሰማህም›› ብሎ መለሰለት አዳማጩ፡፡
‹‹በቃ ያው የወፍ ዜማ፤ በቃ፡፡ የወፍ ዜማ ብርቅ ነው እንዴ››
‹‹ወፏ የምትለውንስ ትሰማለህ››
‹‹ልጅ ሆነን የወፍ ቋንቋ እያልን እንጫወት ነበር፡፡ ያ ግን የወፍ ቋንቋ አይመስለኝም፡፡ ሰውም የወፍ ቋንቋ የሚያውቅ አይመስለኝም››
‹‹የወፍን ቋንቋኮ ማንም ሰው መስማት ይችላል››
‹‹እኔ ለምሳሌ አልችልም›› ጆሮውን በእጆቹ ዳሰሰ፡፡
‹‹ትችላለህ››
‹‹አንተ እኔን ታውቀኛለህ›› በጥንቆላው እንዳያውቀው በመፍራቱ ‹አላውቅህም› እንዲለው ፈለገ፡፡
‹‹ሰው አይደለህም እንዴ››
‹‹ብሆንስ››
‹‹ከሆንክማ ትችላለህ ማለት ነው፡፡ ሰው ሁለት ዓይነት ጆሮ አለው፡፡ የሥጋ ጆሮና የልቡና ጆሮ ወይም እዝነ ሥጋ እና እዝነ ልቡና፡፡ በሥጋ ጆሮው ማዳመጥ የሚችለው የሰው ቋንቋ፣ መስማት የሚችለውም አልፎ ሂያጅ ድምጽ ነው፡፡ በልቡና ጆሮው ግን ወፍንም፣ እንስሳንም፣ ወንዝንም፣ መብረቅንም፣ ተራራንም፣ ዛፍንም መስማት ይችላል›› አለው፡፡ ከበደ ሚካኤል ይህንን ችሎታቸውን ተጠቅመው ነው ደመናና ጽጌረዳ ሲያወሩ የሰሙትን የነገሩን፡፡ ‹ጽጌረዳና ደመና› የሚለውን ግጥማቸውን ታውቀዋለህ?
‹‹እሺ አንተ ከወፏ ምን ሰማህ?›› አለው መንገደኛው፡፡
‹‹ምን የመሰለ ቅኔ፣ ምን የመሰለ ዕውቀት፣ ምን የመሰለ የሕይወት ትርጓሜ››
‹‹እስኪ አንዱን ንገረኝ››
‹‹ወፏ ምን አለች መሰለህ፡፡ ትዘምር የነበረው ስለ ዛፉ ነው፡፡ ዛፍ ሆይ አትመካ፣ እኔን አስጠለልኳት፣ አሳረፍኳት ብለህ አትመካ፡፡ በቅርንጫፍህ አትመካ፡፡ ለእኔ ዋናው ያንተ ቅርንጫፍ አይደለም፡፡ለእኔ ዋናው የራሴ ክንፍ ነው፡፡ ቅርንጫፍህ ሊቀር ይችላል፡፡ አንተም አላስጠልልም ልትል ትችላለህ፡፡ ያ ያንተ መብት ነው፡፡ እኔ ግን የምመካውም የምተማመነውም በገዛ ክንፎቼ ነው፡፡ ክንፎቼ ካሉልኝ የትም እሄዳለሁ፡፡ ሌላ ዛፍ ላይ ዐርፋለሁ፡፡ ሌላ ቤት ላይ እወጣለሁ፡፡ በተራሮች ላይ እቆማለሁ፡፡ በመስኩ ላይ እራመዳለሁ፡፡ ስለዚህ ልሰበር ነው፤ ልወድቅ ነው፤ ልጥልሽ ነው፤ ልወዛወዝ ነው እያልክ አታስፈራራኝ፡፡ ወፍ የተባልኩት ከእኔ ጋር ባሉት ክንፎቼ እንጂ አንተ ጋር ባሉት ቅርንጫፎችህ አይደለም፡፡ ወፍ የሆንኩት እኔ ጋር ባሉት ላባዎቼ እንጂ አንተ ጋር ባሉት ቅጠሎች አይደለም፡፡ ወፍ የተባልኩት በቆምኩበት እግሬ እንጂ በቆምኩበት ግንድ አይደለም፡፡ እኔ ባለኝ እንጂ በምትሰጠኝ አልተማመንም፤ እኔ በያዝኩት እንጂ በተለገስኩት አልመካም፡፡ – ይህንን ነበር የምትዘምረው››
መንገደኛው ተገረመ፡፡ የወፍ አድማጩን ችሎታም አደነቀ፡፡ አብልጦ ደግሞ የወፏን ዝማሬ አደነቀ፡፡ ወፍኛ ቢችል ኖሮ መወድስ ያደርሳት ነበር፡፡
‹‹ቆይ አንተ ይህንን የወፍ ቋንቋ ከየት ተማርከው›› መንገደኛው ጠየቀ፡፡ ቅድም እንዳልፈራ ሁሉ አሁን ለማወቅ ጓጓ፡፡ የማያውቁት ነገር ምንጊዜም ያስፈራል፡፡ መቃብር ለመቃብር ቆፋና ለቀባሪ እኩል አያስፈራም፡፡
‹‹ይህ ነገር የምትማረው አይደለም፡፡ ሰው በመሆንህ የምታገኘው ነው፡፡ ግን ማሳደግ ይፈልጋል፡፡ እዝነ ልቡናህን መጠቀም ይፈልጋል፡፡ ለሕይወት ትርጉም መስጠትን ይፈልጋል፡፡ ዝም ብሎ የተፈጠረ፣ ዝም ብሎም የሚኖር፣ ዝም ብሎ ነገር የለምና፤ ዝም ብለህ የምታልፈው ዝም ብሎ ነገር ሊኖር አይገባም፡፡ ኑሮ ከንቱ አይደለችም፤ ሕይወት ቂላቂል አይደለችም፡፤ ሕይወት ቅኔ ናት፡፡ እየፈታህ የምትማርባትም የምትደመምባትም፡፡ ፍጡራን ሁሉ ልዩ ልዩ ዓይነት ቅኔዎች ናቸው፡፡ ማዳመጥ፣ ማየት፣ መንካት፣ መመርመር፣ መተንተን የሚፈልጉ ቅኔዎች፡፡ አየህ በሥጋ ጆሯችን ብዙ ቸበርቻቻዎች ስንሰማ ስለምንኖር የሕይወትን ዝማሬ የመስማት ዕድላችን ጠብቧል፡፡ አንት ግን እይ፣ ስማ፤ አካባቢውን፣ የዐየሩን ሁኔታ፣ ድምጹን፣ የፍጥረትን እንቅስቃሴ፣ የፍጥረትን የርስበርስ ተግባቦት አድንቅ፤ አድንቅና ፍታው፡፡ ድምጽ ዝማሬ፣ ትርዒትና መልእክት የሌለው ፍጡር የለም፡፡ ዝማሬያቸው ግን የሚሰማው፣ ትርዒታቸው ግን የሚታየው፣ መልእክታቸው ግን የሚረዳው ለሰው ነው፡፡ሰው ነው የሚፈታላቸው፡፡ ፍቺው ግን እንደየዕውቀታችን፣ እንደየኑሯችን፣ እንደየ ዐቅማችን፣ እንደየመረዳታችን፣ እንደየ ባሕላችን ሊለያይ ይችላል፤ የወፏን ዝማሬ እንተ ብትሰማው ሌላ ይሆናል የምትረዳው፡፡ ወፏ እንደዚያ አላለችም፡፡ እኔ ነኝ እንደዚያ የተረዳኋት፡፡ መድኃኒት እንደየበሽታው ነው፡፡
‹‹ያሬድ ያያትን፣ ሰባት ጊዜ እየወደቀች የተነሣችውን ትል አንተ ብታያት ኖሮ ሌላ ነገር ልትረዳ ትችል ይሆናል፡፡ ያሬድ ግን ወድቆ መነሣትን፣ ታግሎ ማሸነፍን፣ ተስፋ አለመቁረጥን፣ አለመታከትን ከእርሷ ተማረ፡፡እርሷ ተጓዘች፡፡ እርሱም ጉዞዋን ተረጎመላት፡፡ ስለ ጳልቃን ጣልቃን፣ ስለ ከራድዮን፣ ስለ ዝሆን (ውርዝው ነጌና ዐቢይ ነጌ)፣ ስለ አንበሳ፣ ስለ ቀበሮ፣ ስለ ቁራ፣ ስለ ርግብ፣ ስለ ጉንዳን የምንሰማቸው ታሪኮች ሁሉ የእነርሱን አነዋወር ተመልክቶና አዳምጦ ለሕይወት የሚበጅ ትርጉም ከመስጠት የመጣ ነው፡፡
‹‹እይ፣ ዝም ብለህ ግን አትይ፤ ስማ፣ ዝም ብለህ ግን አትስማ፡፡ ዓለም መጽሐፍ ናት፡፡ ሚሊዮን ገጾች ያሏት፡፡ ገጹ እያንዳንዱ ገጠመኝህ ነው፡፡ ብልሆች እያንዳንዱን ገጽ ያነቡታል፡፡ ይማሩበታልም፡፡ ሞኞች ግን ገጹን እያጠፉ ብቻ ያልፉታል›› ይሄው ነው ወዳጄ፡፡
አሁን መንገደኛው ራሱ የወፏን ዝማሬ መስማት ጀመረ፡፡ አንገቱንም መነቅነቅ ቀጠለ፡፡ እርሱ የሰማውን ደግሞ ሌላ ደራሲ ይነግረን ይሆናል፡፡
ፍራንክፈርት፣ ጀርመን