የተሰበሰበ ድንች (ካለፈው የቀጠለ)


እኔና ባለቤቴ ልክ እንዳንቺ ሆነን ነበር፡፡ ነገራችን ሁሉ ችኮ ሆኖ፡፡ ያ ድሮ እንደ መልካም ሙዚቃ ጆሮሽን አዘንብለሽ የምትሰሚው የባልሽ ድምጽ ፍሬን እንደያዘ መኪና ድምጽ ሲሆንብሽ ይሰማሻል፡፡ ይናፍቅሽ የነበረው ድምጽ ሲደውል ሐሳብ ውስጥ ይጥልሻል፡፡ ደግሞ ምን ሊል ይሆን? ትያለሽ፡፡ ስልክ ከማንሳት ይልቅ ስልኩን ለመዝጋት ትቸኩያለሽ፡፡ ለመሆኑ ባል ማለት ምንድን ነው? ለእኔ ከባልሽ ጋር ብቻ የምታደርጊያቸው ነገሮች ስላሉ ነው፡፡ ከእርሱ ጋር ብቻ የምትቀልጃቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምታወሪያቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምትሠሪያቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምትወስኛቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምትባልጊያቸው፣ ከእርሱ ጋር ብቻ የምታኮርፊያቸው፡፡

ለአንቺ ብቻ የሚቀጸሉ፣ለአንቺ ብቻ የሚውሉ፣ ለአንቺ ብቻ የሚነገሩ፣ ለአንቺ ብቻ የሚገለጡ፣ ለአንቺ ብቻ የሚደረጉ፣ ለአንቺ ብቻ የሚሰሙ የተለዩ ነገሮች ከሌሉ ምኑን ሚስት ሆንሺው፡፡ ባልሽ ደግ፣ ሩኅሩኅ፣ ትዕግሥተኛ፣ የማይሰክር፣ ገንዘብ የማያባክን፣ ታማኝ፣ መልከ ቀና  ቢሆን እጅግ የታደልሽ ትባያለሽ፡፡ ይኼ ሁሉ ግን መልካም ሰውነቱን እንጂ መልካም ባልነቱን አያሳይም፡፡ ደግ ሰው፣ ቆንጆ ሰው፣ ትጉኅ ሰው፣ ፍጹም ሰው ያሰኘዋል እንጂ ብቻውን መልካም ባል አያሰኘውም፡፡
መልካም ባል ለመሆን በመልካም ሰውነት ላይ ሊጨመሩ የሚገባቸው ሌሎች የባልነት ነገሮች አሉ፡፡ በመልካም ባል ውስጥ ሚስትነት፣ በመልካም ሚስት ውስጥ ደግሞ ባልነት መኖር አለባቸው፡፡ መልካም ባል ማለት ሚስት መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚረዳ፣ ሚስትነት በውስጡ ያለው ባል ማለት ነው፡፡ መልካም ሚስትም እንዲሁ፡፡ መልካም ባል ማለት የሚስትን ስሜት፣ ልብና ኩላሊት ለማወቅ የሚችል ማለት ሳይሆን ሊረዳውና ሊሰማው የሚችል ማለት ነው፡፡
እንዲህ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቼ ሳስበው ለካ እኛ ቤት ውስጥ የነበሩት ባልና ሚስት ጠፍተው አንድ ወንድና አንዲት ሴት ቀርተዋል፡፡ አብረው የሚኖሩ፣ አብረው የሚሠሩ፣ አብረው የሚያድሩ፣ አብረው የሚበሉ፣ አብረው ልጅ የሚያሳድጉ ሁለት ወንድና ሴት፡፡ ባለ ትዳሮቹ ጠፍተው ትዳሩ ቀርቷል፡፡ አንድ ነገር የሚመሠረተው፣ ለመመሥረቱ በሚኖረው ቀዳሚ ምክንያት ነው፡፡ ያ ምክንያት ነው ለዚያ ነገር የህልውናው ሞተር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ምክንያቱ ይጠፋና ነገሩ ብቻውን ይኖራል፡፡ የምክንያቱ ሳይሆን ምክንያቱ የፈጠረው ተቋም ወይም ቡድን አባል ትሆኛለሽ፡፡
ከዚያ በኋላ የምትኖሪው ወይም የምትንቀሳቀሽው ለምክንያቱ ሳይሆን በምክንያቱ የተነሣ ለተፈጠረው ተቋም ወይም ቡድን ይሆናል፡፡ ያ ተቋም የተመሠረተበትን ምክንያት ለመፈጸም ሲል የፈጠራቸው ሕጎች፣ ሥርዓቶች፣ ደንቦች፣ ባሕሎች፣ ልማዶች፣ ወጎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች በሰው ውስጥ ሰርጸው የመኖር ዐቅም ስላላቸው፤ አንቺም ለእነዚህ እየተገዛሽ መኖር ትቀጥያለሽ፡፡ ያን ጊዜ ሕይወት አዙሪት ይሆንብሻል፡፡ ሥራ ስላለሽ ከቤት ትወጫለሽ፣ ቤት ስላለሽ ብቻ ተመልሰሽ ትመጫለሽ፤ ልጆች ስለወለድሽ ለእነርሱ ስትዪ ትዳርሽን ትቀጥዪዋለሽ፣ ባል ስላለሽ ብቻ አብረሽ ትተኛለሽ፤ የጋራ ጉዳይ ስላለሽ ብቻ ተነጋገሪያለሽ፤ እያለ ይቀጥላል፡፡
እኔ እንዳየሁት አንቺ በትዳር ውስጥ ስትሆኚና ትዳሩ አንቺ ውስጥ ሲሆን ይለያያል፡፡ አንቺ በትዳር ውስጥ ስትሆኚ፣ በውስጥሽ ምንም ስሜት ሳይኖርሽ፣ ነፍስሽ ምንም ሳይሰማት እንዴው ማድረግ ስላለብሽ ብቻ ስታደርጊው ነው፡፡ ምግብን ሆድሽ ብቻ ሲበላውና ኅሊናሽ ጭምር ሲበላው አይለያይም? ለመኖር መብላት ስላለብሽ ብቻ ስትበዪና ደስ ብሎሽ፣ ኅሊናሽ ረክቶ፣ ዘና ብለሽ ስትበዪ ማለቴ ነው፡፡ አንቺ በትዳር ውስጥ ስትሆኚ ለመኖር ብቻ ሲባል ምግብ እንደመብላት ነው፡፡ ትዳር በአንቺ ውስጥ ሲሆን ግን ሌላ ነው፡፡ ስትሄጂ፣ ስትሠሪ፣ ስትተኚ፣ ሲደክምሽና ስትበረቺ እንኳን ትዳርሽን ባሰብሽ ቁጥር አንዳች ልዩ የሆነ የደስታና የእርካታ ስሜት ሲሰማሽ፤ ገብተሸ ስትዋኚበት፣ ያወራችሁትን፣ ያደረጋችሁትን፣ የሆናችሁትን፣ ሌላው፤ ቀርቶ የተኳረፋችሁትን እንኳን እንደ ቤት እንስሳ መልሰሽ ስታመነዥኪው እንደ መልካም ጠጅ በኅሊናሽ ኩልል ብሎ ሲንቆረቆር፤ ከቤትሽ ስትወጭ ለመመለስ ስትቸኩዪ፤ ከባልሽ ስትለዪ ለመገናኘት ስትጣደፊ፤ ባልሽን፣ ልጆችሺን፣ ቤትሽን ይዘሺው ስትሄጂ – ያ ነው – ትዳር በአንቺ ውስጥ ሲኖር ማለት፡፡
ትዳር ስንጀምር ትዳር ውስጣችን ገብቶ ነበር፡፡ ስንቆይ ግን እኛ እንገባና እርሱ ይወጣል፡፡ ያኔ ነው ‹መነጋገር› መነጋገር ብቻ የሚሆነው፡፡ መነጋገር የፍቅር መግለጫ፣ በነፍስ የመዛመድ ምልክት፣ በሐሳብ የመገናዘብ ማሳያ መሆኑ ይቀርና መነጋገር መነጋገር ብቻ ይሆናል፡፡ እኔም እንዲህ ሆኖብኝ ብዙ ጊዜ ተቸገርኩ፡፡ ስነጫነጭ፣ ስብሰከሰክ፣ ስማረርና ስቆርጥ ስቀጥል ኖርኩ፡፡ አንድ ቀን እንደ ድንገት ጋብቻን ስለማደስ የተጻፈ መጽሐፍ አገኘሁ፡፡ በፈረንጆቹ ባሕል ጋብቻን ማደስ (marriage renewal) የተለመደ ባሕል ነው፡፡ ለምን ወደ እኛ አንቀይረውም ብዬ አሰብኩ፡፡
በዚያ መጽሐፍ ላይ አንድ ቁም ነገር አየሁ፡፡ ከትዳር ልምድ ያገኘሺውን ነገር ተጠቅመሽ አዲስ የቃል ኪዳን ሰነድ አዘጋጂ ይላል፡፡ ለባለቤቴ ወሰድኩና አሳየሁት፡፡ ሲያነበው ወደደው፡፡ ያ ነገር ምክንያት ሆነንና ስለትዳር ማደስ አወራን፡፡ እኔም የራሴን እርሱም የራሱን ሰነድ አዘጋጀ፡፡ በቃል ኪዳን ሰነዱ ሞዴል ላይ ያለፈውን የትዳር ዘመን፣ ባለፈው ዘመን በክፉም በደጉም ለቆየንባቸው ዘመናት ለፈጣሪ ምስጋና፣ ለፈጠርናቸው ስሕተቶች ይቅርታ፣ ከዚያ ደግሞ ለወደፊቱ በትዳራችን እንድናደርግ የምንፈልገውን ነገር ይዘረዝራል፡፡ እኔ የርሱን እርሱም የእኔን ልናዘጋጅ ተስማማን፡፡ ባሌ ምን ቢሆንልኝ እንደምፈልግ ለብዙ ጊዜ አሰብኩበት፤ እርሱም አስቦበታል፡፡
ያዘጋጀነው ሰነድ ከትዳራችን ምን እንደምንፈልግና፣ ምን እንደማንፈልግ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነበር፡፡ ትዳራችንን የፈተሽንብት መልካም አጋጣሚ ሆነልን፡፡ ሁለታችንም በተዘጋጀልን ሰነድ ላይ መጠነኛ ማሻሻያ ከማድረግ ያለፈ አልተጓዝንም፡፡ አሁን በስለናል፤ ከልምድ ብዙ ነገር አግኝተናል፤ በፊት በትዳር ውስጥ እናስባቸው ያልነበሩ ነገሮችን ማሰብ ጀምረናል፤ ተፈታትነናል፤ ተዋውቀናልም፡፡ አንዳችን የሌላችንን በማዘጋጀታችን የተነሣ ነገሮች በዝርዝር ቀርበው ነበር፡፡ አናደርግም የምንለው፣ እናደርጋለን የምንለው ቁልጭ ብሎ ቀርቧል፡፡
በጣም የሚገርምሽ ነገር ችግር የማይመስሉን ነገሮች ሁሉ በሌላችን ተነቅሰው ሲመጡ ችግር መሆናቸውን ለመረዳት አስችሎናል፡፡ ቀላል የሚመስሉ፣ እንደዋዛ የምንዘላቸው፣ ነገር ግን ሌላችንን የሚያናድዱና የሚያሳዝኑ ነገሮች ሁሉ መጡ፡፡  በፈጣሪ ፊት ቆምንና ሁለታችንም እንደገና ቃል ገባን፡፡ እንደገናም ተጋባን፤ ለትዳራችን አዲስ እሴት ጨመርንለት፣ እንደገና የመኖሪያ ምክንያታችንን አደስነው፤ እርሱ ወደ እኔ፣ እኔም ወደ እርሱ ውስጥ ገባን፡፡ ትዳራችንም ወደ እኛ ገባ፡፡ ያንን ሰነድ በየጊዜው እያየሁ ራሴን አረጋግጥ ነበር፡፡ ቃሌን እየጠበቅኩ ነውን? እል ነበር፡፡ እንደ አዲስ ተጋቢ ነበር የሚሰማኝ፡፡
እንዳየሁት ከሆነ ትዳርና አትክልት በየጊዜው ካልተከታተሉት አረም ይበቅልበታል፡፡ ሲብስም አትክልቱ ይጠፋና አረሙ መታየት ይጀምራል፡፡ ያኔ ነው እንጨት እንጨት የሚለው፡፡ ጎበዝ ሰው ቶሎ ብሎ ያርምና አትክልቱ እንዲያብብ ያደርገዋል፡፡ እንደገና መኮትኮት፣ እንደገና ማዳበሪያ ማድረግ፣ እንደገና አፈር መከለስ፣ እንደገና ውኃ ማጠጣት፣ እንደገና አጥር ማጠር ይጠይቅ ይሆናል፡፡ ድሮ አፈር አድርጌ ነበር፣ ማዳበሪያ ነበረው፣ አጠጥቼው ነበር፣ ኮትኩቼው ነበር አይሠራም ወዳጄ፡፡ አንዳንዴም እርሻው ብቻ ቀርቶ ተክሉ ሊጠፋ ይችላል፡፡
እና እስኪ ቆም ብለሽ ተመልከቺው፤ እንደገና መጋባት፣ ጋብቻውን እንደገና ማደስ፣ ለአዲሱ ሰብእናሽ አዲስ ሐሳብ መፈለግ፣ አሁን ለደረስሽበት ነገር አዲስ ቃል ኪዳን መግባት ያስፈልጋችሁ ይሆናል፡፡ ትዳርሽ አርጅቶ ይሆናል፡፡ ትዳር ይፀነሳል፣ ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ያረጃል፣ ዝም ካሉትም ይሞታል፡፡ ጀግኖች ደግሞ እንዳያረጅና እንዳይሞት እንደ አዲስ ያድሱታል፡፡ አንቺም ትዳርሽ እንደ ንሥር አድሽው፤ ያለበለዚያ መጀመሪያ ያረጃል፤ ከዚያም ከባሰ ይሞታል፡፡ እሳትን እንጨት ላይ እያለ መልሶ ማቀጣጠል መልካም ነው፤በእንጨትነቱ ካልተደረሰም እንጨቱ ከሰል ሲሆን ቶሎ መድረስ ነው፤ ከሰሉ አመድ ከሆነ በኋላ ግን እንደገና ማቀጣጠል አስቸጋሪ ነው፡፡ ›› ነበር ያለቺኝ፡፡
አሁን  ሳስበው እርሷ ያለቺኝ ሳይሻል አይቀርም፡፡
‹እውነትሽ ነው› አለቺ ጓደኛዋ ‹‹ሁላችንም ብንሞክረው ሳይሻል አይቀርም››
ዑራኤል የኤሌክትሪክ ሱቆች ጋር ደርሼ ተለየኋቸው፡፡ እነርሱ ግን ቀጠሉ፡፡
ፍራንክፈርት አውሮፕላን ጣቢያ