እንደገና እንጋባ

ይህንን ደብዳቤ ስጽፍ ፊት ለፊቴ የቤተሰባችንን ፎቶ ግድግዳው ላይ እያየሁ ነው፡፡ ‹‹ይናገራል ፎቶ›› አሉ፡፡ አቤት በፎቶማ እንዴት ያምርብናል፡፡ ፎቶ ላይ ያለው ፈገግታ እንዲሁ ትዳር ውስጥም ቢቀጥል እንዴት ጥሩ ነበር፡፡ ግርም ይላልኮ፡፡ፎቶ አንሺዎች ሁሉ ከአንድ እናት የተወለዱ ይመስል ለምንድን ነው በግድ ‹‹ፈገግ በሉ›› የሚሉት፡፡ በቃ ፎቶ ማለት ደስታን ማሳያ ብቻ ነው እንዴ፡፡ የከፋው ሰው ፎቶ አይነሳም ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ፎቶ አንሺዎችና ቪዲዮ ቀራጮችኮ በገዛ ሠርጋችን ተዋንያን ያደርጉናል፡፡ እንደ ራሳችን ሳይሆን እንደ እነርሱ ፈቃድ ያስኬዱናል፣ ያሳስሙናል፣ ያስተቃቅፉናል፣ ያሰልፉናል፣ ያጣምሙናል፣ ያቃኑናል፡፡ እነርሱ ግን የፊልም ዳይሬክተር ናቸው ወይስ የሠርግ ቪዲዮ ቀራጮች? እኛስ ሙሽሮች ነን ወይስ ተዋንያን?
ከተለያየን ጀምሮ ይህንን ፎቶ ደጋግሜ እያየሁ ደጋግሜ አስባለሁ፡፡ ለብቻ መሆን አንድ የሚጠቅመው ነገር ቢኖር የማሰቢያ ጊዜ መስጠቱ ነው፡፡ ሰው ለመኖር ለካ ከምግብና መጠለያ እኩል የማሰቢያ ጊዜም ያስፈልገዋል፡፡ እንዲሁ ስንዞር፣ እንዲሁ ስንወጣና ስንወርድ፣ እንዲሁ ቀዳዳ ለመሙላት ወዲህ ወዲያ ስንል፣ እንዲሁ ጠዋት ወጥተን ማታ ስንገባ አይደል እንዴ የኖርነው? አሁን ሳስበውኮ የኑሮ ወንዝ ወደወሰደን ፈሰስን እንጂ አስበን አልኖርንም፡፡

እስኪ ልጠይቅሽ ለመሆኑ ለኛ ትዳር ምንድን ነበር? አንድ ቤት መኖር፣ አንድ አልጋ ላይ መተኛት፣ ልጆች መውለድ፣ ወላጆቻችን ቤት አንድ ላይ መሄድ፣ መጎራረስ፣ <ከባለቤትዎ ጋር> ተብሎ መጠራት፣ ምንድን ነው ግን ትዳር? ለመሆኑ ሠርገን ነበር ወይስ ተጋብተን ነበር? ጋብቻ ነበረን ወይስ ትዳር? አቤት ለሠርጋችን እንዴት ነበር የለፋነው፡፡ ‹‹ጋብቻ የትዳር መጀመሪያው ሥነ ሥርዓቱ ነው፤ ሠርግ ማጀቢያው ድግስ ሲሆን፣ ትዳር ደግሞ በዚህ በኩል ተገብቶ የሚኖረው ኑሮ ነው›› የሚል ካነበብኩ በኋላ ይህንን ጥያቄ መጠየቅ ጀምሬያለሁ፡፡ አዳራሽ ለማግኘት፣ መኪና ለማግኘት፣ የሠርግ ልብስ ለመምረጥና ለማሰፋት፣ ድግሱን ለማሣመር፣ የሚጠሩ ሰዎችን ለመምረጥ፣ ሚዜዎቻችንን ለመምረጥ ስንቴ ነበር ያሰብነው፤ ሰሐንና ብርጭቆ እንኳን ሳይቀር አስበንበት፣ ሰው አማክረን፣ ዙረን መርጠን፣ ከሌሎች ልምድ ወስደን ነበር የተከራየነው፡፡
በእኔና ባንቺ ሠርግ ስንት ሰዎች ተሳተፉ፣ ስንቶች ለፉ፣ የስንት ሰዎች ሐሳብ ተዋጣ፣ የስንቶች ልምድ ተቀሰመ፣ የስንቶች ጉልበትስ ፈሰሰ፡፡ በያንዳንዱ ጉዳይ እንወያይ፣ እንከራከር፣ እንጨቃጨቅ፣ እንለያይ ነበር፡፡ በያንዳንዱ ጉዳይ እንደገና እንገናኝ፣ እንግባባ፣ እንስማማና እንታረቅ ነበር፡፡ በብዙ ሰዎች ታግዘን አግብተን ትዳርን ብቻችንን ገጠምነውና አልቻልነውም፡፡ ሠርግ ላይ ያለው እገዛ ትዳር ላይ ቢሆን እንዴት ጥሩ ነበር፡፡
አሁን ሳስበው የለፋነው ለሠርጋችን እንጂ ለትዳራችን አልነበረም፡፡ እስኪ ትዝ ይበልሽ፡፡ ከኛ በፊት የተጋቡ ሙሽሮችን ልምድ የወሰድው ስለ ሙሽራ ልብስ፣ ስለ ቬሎ፣ ስለ ሚዜ፣ ስለ መኪና፣ ስለ ድግስ፣ ስለ አዳራሽ፣ ስለ መጥሪያ ካርድ፣ ስለ ባንድ፣ ስለ ቪዲዮ እንጂ ስለ ኑሯቸው አልነበረም፡፡ እነርሱምኮ ‹ዲል› ባለ ድግስ፣ የሁላችንንም ቀልብ በማረከ ሥነ ሥርዓት ተጋብተው ይሆናል፡፡ ከዚያስ? ነው ጥያቄው፡፡ የኛስ ሠርግ ጉ-ድ የተባለ አልነበረም፡፡ እስካሁን ድረስ የእኔና የአንቺን ሠርግ እንደ ትንግርት የሚያወሩት አሉኮ፡፡ ከሠርጉ በኋላ የሆንነውን ስለማያውቁ፡፡
አንድ ወዳጄ ትዳርና ችግኝ አንድ ነው ብሎኛል፡፡ ሁለቱም ክብካቤ ይፈልጋሉ፡፤ ሁለቱም በየጊዜው መኮትኮትና ማሳደግን ይጠይቃሉ፡፡ ሁለቱም መከርከምና ድንጋይና አረሙን እንዲያስወግዱላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ሁለቱም የዕለት ተዕለት ትኩረት ይሻሉ፡፡ እኛ ግን እንደዚያ ያደረግን አይመስለኝም፡፡ ጉልበታችን ሁሉ ለሠርጉ ፈሰሰና ትዳሩ ላይ አቅም ጠፋ፡፡ ‹‹ዳገት ላይ ሰው ጠፋ›› አሉ ፕሮፌሰር መስፍን፡፡ ድሮ ልጆች ሆነን
ገንዘባችን ሁሉ አለቀ በሻይ
ሚስት ሳናገባ ዓለምን ሳናይ – እንል ነበር፡፡ ከየት የመጣ ግጥም እንደሆነ እንጃ፡፡ የኛም ጉልበታችንና ዐቅማችን ሁሉ ሠርጋችን ላይ ፈሰሰና ‹ዓለምን ሳናይ› ቀረን፡፡ ይገርምሻል፡፡ በቴሌቭዥን ሰሞኑን የችግኝ ተከላ ዜና ሲነገር ትዝ የሚለኝ የእኔና የአንቺ ትዳር ነው፡፡ ድሮ በሠፈራችን በሚገኝ ጋራ ላይ ሰኔ በመጣ ቁጥር በቀበሌ ትእዛዝ እየወጣን የምንተክለው ችግኝ ነበር፡፡ ከተከልነው በኋላ ግን ዞር ብሎ የሚያየው የለም፡፡ ሰኔና ሰኞ የገጠመለት  ችግኝ ይጸድቃል፡፡ ሌላው ግን ደርቆ ይቀራል፡፡ ቀበሌውም ማስተከል እንጂ ማሳደግ አያውቅበትም፡፡ የብዙዎቻችን ትዳር እንደዚያ ይመስለኛል፡፡ ልክ አንድ አገር ሰው ተሰብስቦ ችግኝ እንደሚተክለው ሁሉ አንድ አገር ሰው ተሰብስቦ ትዳር የሚባለውን ችግኝ የሠርግ ቀን ይተክለዋል፡፡ ችግኙን ማንም ዞር ብሎ እንደማያየው ሁሉ ትዳርን የሚከባከበው፣ ውኃ የሚያጠጣው፣ አረም የሚነቅልለት፣ አፈር የሚያደርግለት፣ ፋንድያ የሚደፋለት፣ አውሬ እንዳያበላሸው አጥር የሚቀጥርለት የለም፡፡ ልክ ያደለው ችግኝ በዕድል አድጎ እንደሚገኘው ሁሉ፣ ያደለው ትዳርም አድጎ ተመንድጎ እናየው ይሆናል፡፡ ‹‹አፍራ ያለው ተኝቶም ያፈራል›› ይባል የለ፡፡ ብዙ ትዳሮች ግን እንደ ብዙዎቹ ችግኞች ከስመው ቀርተዋል፡፡
እኔማ አንዳንዴ ‹ለሠርጋችን ከተጨነቅነው ግማሹን እንኳን ለትዳራችን አድርገነው ቢሆን ኖሮ እንደዚህ ባልሆንን ነበር› እላለሁ፡፡ እንዴው ብቻዬን ስለሆንኩ ሰው አያየኝም እንጂ፣ ያበድኩኮ ነው የምመስለው፡፡ ብቻዬን እስቃለሁ፤ ብቻዬንም አወራለሁ፡፡ ባለፉት ዓመታት ያወራናቸውን ሳስባቸው ስለ ቤት ወጭ፣ ስለ ልጆች ትምህርት ቤት፣ ስለ ወላጆቻችን፣ ስለ ጎረቤቶቻችን፣ ስለ ልቅሶና ሠርግ፣ ስለ ርዳታና መዋጮ፣ ስለ መኪናና የቤት ዕቃ፣ ስለ ሥራ ቦታ ችግሮች ሆነው አገኛቸዋለሁ፡፡ እነዚህ ነገሮች ግን ብቻ እንዴት ትዳርን ያሳድጉታል? እንዴትስ ፍሬያማ ያደርጉታል? ስለ እኔና ስለ አንቺ፣ ስለምትወጅውና ስለምትጠይው፣ ስለምንጨምረውና ስለምናርመው፣ አንቺን ይበልጥ ስለማስደሰትና እኔን ይበልጥ ስለማርካት፣ እኔ ላንቺ ማድረግ ስላለብኝና አንቺ ለእኔ ማድረግ ስላለብሽ ነገር ማውራታችንን፣ መወሰናችንንም አላስታውስም፡፡
ደግሞ የሚገርምሽ ነገር፤ ዛሬ ዛሬ ሳስበው ግርም የሚለኝ፣ የምንነጋገረውኮ በሚያጋጥሙን ነገሮች ላይ ብቻ ነው፡፡ አንዳች ነገር ካልገጠመን አንነጋገርም፡፡ ለነገሩማ በዝምታ አድገን እንዴት መነጋገር እንልመድ ብለሽ ነው፡፡ ‹‹ጥፋቱስ አይደለም ካንቺ ወይም  ከእኔ፣
ፍቅር በመሆኑ እንጂ ጽድቅና ኩነኔ፣
አንቺ አንቺን መሆንሽ እኔ እኔን መሆኔ››
አሉ አብዬ መንግሥቱ እውነታቸውን ነው፡፡ እንዴው ጊዜ ወስደን፣ ከሌላው ነገር ወጣ ብለን፣ እየተዝናናንም ቢሉ ወይም ለራሳችን ጊዜ ሰጥተን ስለ ወደፊት ኑሮአችን፣ ስለ እኔና አንቺ ጉዳይ፣ ልናደርገው ስለምንፈልገው ነገር ወይም መሆን ስለምንሻው ጉዳይ አውርተን እናውቃለን ብለሽ ነው? እንዴው ሊመጣልኝ አልቻለም፡፡ አንድ ነገር ይገጥመናል፣ በዚያ ላይ እናወራለን፣ ጉዳዩ ከእኔ ወይንም ካንቺ ጋር ይገናኝና አንዳችን አጥቂ ሌላችን ተከላካይ እንሆናለን፡፡ ከዚያማ ‹‹ጨሰ አቧራው ጨሰ›› ማለት ያኔ ነው፡፡ ግን ለመሆኑ ይህንን ‹‹ጨሰ አቧራው ጨሰ›› የሚል የሠርግ ዘፈን ያመጣው ማነው? መቼም እንደኔ አግብቶ የፈታ ሰው መሆን አለበት፡፡
በተለይማ ልጆች ከመጡ በኋላ ባሰብን፡፡ እኔም ባልሽ መሆኔ ቀርቶ የልጆችሽ አባት ሆንኩ፤ እንቺም ሚስቴ መሆንሽ ቀርቶ የልጆቼ እናት ሆንሽ፡፡ ለመሆኑ ግን ከኛ የሚተርፈንን ጊዜ ነው ለልጆች መስጠት ያለብን ወይስ ከልጆች የሚተርፈውን ጊዜ ነበር እኛ መውሰድ የነበረብን? ለመሆኑ በትዳር ውስጥ ዋናው ጉዳይ ምንድን ነው? ‹ባለቤቴ› የሚለውን ባሕላዊ አጠራር የወደድኩትም ያደነቅኩትም አሁን ነው፡፡ ለምን መሰለሽ? በቀጣዩ ደብዳቤዬ እነግርሻለሁ፡፡
ብንጣላም፣ ብንለያይም፣ ባንግባባም፣ ግን ደኅና ሁኚ፡፡
ያንቺው የቀድሞ ባለቤት
(ሳምንት ይቀጥላል)
 © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው