ራትን ቁርስ ላይ
አፍሪካውያን ቀደምት አያቶቻችን እንዲህ የሚል ትንቢት አዘል አባባል ነበራቸው፡፡ ‹‹የዚህ ትውልድ ትልቁ አደጋ ራታቸውን በቁርስ ሰዓት ለመብላት መፈለጋቸው ነው››፡፡ ሰው እንደ መላእክት አይደለምና በሂደት እየበሰለ፣ በሂደት እየተገነባ፣ በሂደትም የበለጠ እየተማረ የሚሄድ ፍጡር ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የመንፈስ፣ የአካል፣ የስሜትና የአእምሮ ዕድገትና ለውጥን ይጠይቃል፡፡ ሰው ሲወለድ ለማደግና ለመለወጥ ከሚያስችል ዐቅም ጋር ነው፡፡ ይህንን ዐቅም ተጠቅሞ ለማደግና ለመለወጥ ግን ልምድ፣ ትምህርትና የሰውነት ግንባታ ያስፈልጉታል፡፡ ልምድ የሚባለው ከተወለደ ጊዜ ጀምሮ በሕይወት ውጣ ውረድ የሚደርስበት ተሞክሮ ነው፡፡ ይህም የሕይወት ተጋድሎ ይባላል፡፡ ትምህርት ከሰዎች፣ ከትምህርት ቤት፣ ከመጻሕፍት፣ ከአካባቢውና ከሌሎችም የዕውቀት ምንጮች የሚያገኘው ጥበብ ነው፡፡ የሰውነት ግንባታ የሚባለው ደግሞ በምግብና በእንቅስቃሴ የሚያበለጽገውን አካል ነው፡፡
እነዚህ ነገሮች የሚመጡትና የሚከናወኑት በሂደት ውስጥ በመሆኑ ሰዎች ለተለያዩ የኑሮ ደረጃዎች የሚበቁበት ጊዜ ይለያያል፡፡ በልጅነት፣ በወጣትነት፣ በዐዋቂነትና በአረጋዊነት ጊዜ የሚከናወኑት ተግባራት በዚያው በየዘመናቸው እንዲከናወኑ የሚያስገድዱት ሰዎች እነዚህን ነገሮች ለማከናወን የብስለታቸው ደረጃ እንደ ዕድሜያቸውና በዚያ ዕድሜ የተነሣ እንደሚያገኙት ልምድና ዕውቀት ብሎም አካላዊ ዝግጁነት ስለሚለያይ ነው፡፡ የልጆች ጋብቻንና የልጅነት ጊዜ ወሊድን የምንቃወመው፣ ጋብቻም ሆነ ወላጅነት የሚፈልጓቸው የመንፈስ፣ የአካል፣ የስሜትና የአእምሮ የዕድገት ደረጃዎች ስላሉ ነው፡፡
የመንፈስ ዕድገት የምንለው በመንፈሳዊው ዓለም ሰው የሚኖረው ዕድገትና ለውጥ ነው፡፡ በእምነት፣ በአመለካከት፣ በመርሕና በአተያይ የሚኖረው የብስለት ደረጃ፡፡ የስሜት ዕድገት ለነገሮች የሚኖረንን ፍቅርና ጥላቻ፣ ቀረቤታና ርቀት፣ ሙቀትና ቅዝቃዜ፣ ስበትና ግፊት የምንለካበት የዐቅም መጠን ማደግ ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች ለመቆጣጠር፣ ሕጋዊ፣ ሰላማዊ፣ ትክክልና ተገቢ በሆነው መንገድ ለመምራት ያለን ዐቅም ማለት ነው፡፡ የአእምሮ ዕድገት ስንል ደግሞ በዕውቀት ማደግን ነው፡፡
በትምህርት፣በልምድና በሰውነት ግንባታ እያደገና እየተለወጠ የሚሄደው ሰው፣ ሕይወቱ ተከታትለው በሚመጡ ሦስ ነገሮች የሚዘወር ነው፡፡ ዐሉላ ጥላሁን ‹‹የሕይወት ሙሻዙር›› ይለዋል፡፡ እነዚህ ሦስቱ ጉጉት፣ ተጋድሎና ስኬት ይባላሉ፡፡ በሰው ሕይወት ውስጥ የሚያጓጓ፣ ይደረስበታል ተብሎ የሚታሰብ፣ የሚናፈቅና ተስፋ የሚደረግ ነገር ከሌለ ተጋድሎ የሚባለው የሕይወት ዋነኛ አጣፋጭ፣ ሰውንም ወደ ሙሉ ሰውነት የሚያደርሰው ታላቁ ድልድይ ተሰብሯል ማለት ነው፡፡ እርሱ ከተሰበረ ደግሞ ስኬት የሚባለው ነገር አይታሰብም፡፡ በዓለማችን ላይ ከፍተኛ ሥልጣኔ የተመዘገበባቸው ሀገሮችና ዘመናትን ታሪክ ብናጠና እነዚህ ሦስቱ ነገሮች ገንዘባቸው የነበሩ መሪዎችን፣ ሊቃውንትንና ሕዝቦችን እናገኛለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በኋላ ቀርነት ይሰቃዩ የነበሩና አሁንም የሚሰቃዩትን ሕዝቦች ስናይም እነዚህ ነገሮች ሲያጥሯቸው እናስተውላለን፡፡
ሰው ይህንን የሕይወት ሙሻዙር ዘውሮ ሕይወቱን ወደ ልዕልና እንዳያደርሳት የጉጉት፣ ተጋድሎና ስኬትን መሥመር የሚሰብሩ አራት ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ዋናን የሚያጠፋ ርዳታ ነው፡፡ ርዳታ ወይም እገዛ መልካም የሚሆነው ዓሣ ሊያሰግር የወጣውን ሰው በቀላሉ ብዙ ዓሣዎች እንዲያሰግር የሚያስችለውና እርሱም የተሻለ ማስገሪያ እንዲሠራ የሚያበቃው ዓይነት ርዳታ ከሆነ ነው፡፡ ሰውዬው ቁጭ ብሎ ዓሣ እንዲያገኝና ምንም እንዳያስብ የሚያደርገው ርዳታ ግን ርዳታ ሳይሆን ግድያ ነው፡፡ መጀመሪያ ብዙ ዓሣ ለማስገር የነበረውን ጉጉት ይገድልበታል፡፡ ቀጥሎ ያንን ጉጉት ለማሟላት እንዳይጋደል ያሰንፈዋል፡፡ በመጨረሻም ስኬት አይኖረውም፡፡ ስኬት ማለት የጥረት ውጤት ነውና፡፡ ያለ ጥረት በዱብ ዕዳ የተገኘ ነገር ሁሉ ስኬት አይደለም፡፡ ዕድል፣ ዕጣ ወይም ስጦታ ይሆናል እንጂ፡፡ ሰውን ወደ ዕድል፣ ዕጣና ስጦታ ደረጃ ማውረድ ደግሞ ከሰውነት አሳንሶ ‹መትኅተ ሰብእ መልዕልተ እንስሳት› ማድረግ ነው፡፡ ራቱን ቁርሱ ላይ እንዲበላው ማድረግ፡፡ ነገ ልታገኘው የምታስበውና የምትለፋለት አዲስ ነገር ከሌለህ ‹ነገ› ለምን ይምጣ? ‹ነገ› ስ ከአንድ ተጨማሪ ቀን ውጭ ሌላ ምንድን ነው?
ሁለተኛው ሰባሪ አደጋ ደግሞ በወንጀል የተገመደ አቋራጭ መንገድ ነው፡፡ በስርቆት፣ በጉቦ፣ በማስመሰል፣ በሥልጣን በመባለግ፣ የሰዎችን ዕድል በማበላሸት፣ ትውልድን በመግደል፣ ሀገርን በማጥፋት፣ ወዘተ በኩል የሚገኝ አቋራጭ መንገድ፡፡ በቀላሉ ሥልጣን፣ ገንዘብ፣ ክብር፣ ስምና ዝና የሚገኝበት፡፡ ይህ መንድ ምናልባት ገንዘብ፣ ስምና ክብር፣ ሥልጣንና ዝና ያስገኝ ይሆናል፡፡ ውስጣዊ ደስታ ግን አያስገኝም፡፡ ደስታ ከስኬት የሚገኝ ነውና፡፡ ሌሎቹን ነገሮች ማስመሰል ቢቻልም ውስጥን ማስመሰል ግን አይቻለም፡፡ ደስታ ውስጣዊ ስለሆነ ነው አስመስሎ መሥራት የማይቻለው፡፡
እንዲህ ባደረገ ሰው ውስጥ የሚፈጠረው ጦርነት የትም ቦታ የማይፈጠር ነው፡፡ የሕግ መውጣት፣ የሥርዓት መለወጥ፣ የዳኝነት ሥርዓት መጠንከር፣ የሚዲያ ምርመራ መጀመር፣ የሰዎች ዕውቀት መጨመር፣ እርሱ የፈጸማቸውን ነገሮች የሚቃወሙ አሠራሮች መምጣት፣ የዓለም አስተሳሰብ እየተቀየረ መሄድ ያሳስበዋል፡፡ ያስጨንቀዋል፡፡ ለዚህም ነው እውነተኛውን ደስታ የማያገኘው፡፡ ድሮ ‹‹ከዕለታት አንድ ቀን›› የሚለው መግቢያ ለተረት የሚያገለግል ነበረ፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን ለሰዎችም ያገለግል ጀምሯል፡፡ ‹‹ከዕለታት አንድ ቀን እገሌ ድንገት ኢንቨስተር ሆነ፣ ድንገት ባለ ሀብት ሆነ፣ ድንገት ባለ ዘጠኝ ፎቅ ሆነ፣ ድንገት ባለ ሥልጣን ሆነ፣ ድንገት ባለ ኩባንያ ሆነ፣›› ከየት ተነሥቶ፣ በየት በኩል ሄዶ፣ ምንም አድርጎ? መልስ የለም፡፡ ‹‹እንዴው ከዕለታት በአንድ ቀን›› ነው መልሱ፡፡ በዚህ መንድ የሚመጡ ሰዎች ስኬታማ አይደሉምና ደስተኛም አይደሉም፡፡ ደስተኛ ግን ይመስላሉ፡፡ ራታቸውን ቁርሳቸው ላይ ስለበሉት ምንጊዜም የራት ነገር ሲያሳስባቸው ይኖራል፡፡ ራት ያልበላ ሰው የሚተኛውን የረሃብ ዕንቅልፍ ስለሚተኙ፤ አልጋ እንጂ ዕንቅልፍ አይኖራቸውም፡፡ ቅዠት እንጂ ሕልም አይታያቸውም፡፡
ሦስተኛው ሰባሪ አደጋ ዕድል፣ አጋጣሚና የተመቻቸ ሁኔታ የሚፈጥሩት ግሽበት ነው፡፡ የማስተማሪያ ዐቅምና ዕድል ስላገኘን ብቻ ልጃችንን ያለ ዕድሜው ወደ ትምህርት ቤት ብንልከው ልጁ እየተማረረ እንጂ እየተማረ አይመጣም፡፡ በኋላም ከፍ ሲል ትምህርት ጠል ከሚሆንባቸው ምክንያቶች አንዱ ያለ ዕድሜ ወደ ትምህርት ቤት መግባትና መደበኛ ትምህርት መጀመር ናቸው፡፡ ዕድልና አጋጣሚ አገጣጥሞላቸው ያለ ከዕድሜና ከዕውቀት በፊት ገንዘብ ማግኘት ያቻሉ አንዳንድ ሰዎች ገንዘቡ መጥፊያቸው ሲሆን አይተናል፡፡ አካባቢያቸውን ለማስተዳደር መጀመር ባለባቸው ጊዜ አገር ማስተዳደር የሚጀምሩ፣ ቤተሰባቸውን መምራት ከመጀመራቸው በፊት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መምራት የጀመሩ ሰዎች ዕድሉን ለስኬት ከመጠቅም ይልቅ ሀገር ለማጥፋት የሚጠቀሙበት በዚህ ስኬት ሰባሪ አደጋ የተነሣ ነው፡፡ ራታቸውን ቁርስ ላይ በልተውት፡፡
ዛሬ ዛሬ በጋብቻ ውስጥ ብቻ ሊደረጉ የሚገባቸው ነገሮች ከጋብቻ በፊት፣ በበሳል ዕድሜ ሊፈጸሙ የሚገባቸው ጾታዊ ግንኙነቶች በሚዲያ፣ በፊልም፣ በማኅበራዊ ድረ ገጾችና በአንዳንድ አቀንቃኞች ምክንያት በሚፈጠሩ የስሜት መመቻቸቶች የተነሣ በልጅነት ዕድሜ እየተፈጸሙ በመምጣታቸው ሰዎች ራታቸውን ቁርስ ላይ በልተው የሚጓጉለት ነገር እንዳይኖር አድርጓቸዋል፡፡ ልጆች ተምረው ሊያገኙት የሚገባውን ነገር የድመት ፍቅር በያዛቸው ወላጆች ምክንያት ሳይማሩ ስለሚያገኙት ለትምህርት ሊያውሉት የሚያስፈልግ ጉጉትና ጥረት ተሟጥጦባቸዋል፡፡ በምዕራቡ ዓለም ታላላቅ ሰዎች ልጆቻቸውን በኩባንያቸውና በፖለቲካ መሥመራቸው መተካት የቻሉት፣ ልጆቹ መሥመሩን ተከትለው በመጋደል መሥመሩ የሚያስገኝላቸውን እያገኙ እንዲያድጉ በማድረጋቸው ነው፡፡ የአባታቸው ሀብት ስለሆነ ብቻ አያገኙትም፤ ተምረው፣ ሠርተው፣ ከሌሎቹ ጋር ተወዳድረው፣ ከታች እስከ ላይ ያለውን የዕድገት መሰላል በመንፈስ፣ በትምህርት፣ በልምድና በአካላዊ ዕድገት እየዳበሩ አልፈው፣ በተወዳዳሪነትና በአሸናፊነት ተጋድሎ ተፈትነው ሲደርሱ፤ ያን ጊዜ ወላጆቻቸው ‹ተቀመጥ በወንበሬ፣ ተናገር በከንፈሬ› ብለው ያስረክቧቸዋል፡፡ ሳንቲሞች እንዴት እንደመጡ ሳያውቁ ብሮችን አያስነኳቸውም፡፡ ነገ ሊደርሱበት የሚገባውን ራት ዛሬ በቁርስ ሰዓት አያበሏቸውም፡፡ ልጅ ምንም ያህል ቢፈለግ በሦስት ወር ይወለድ አይባልምና፡፡
አራተኛው ሰባሪ አደጋ የሚመጣው በጋሸበ አድናቆትና ግፊት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከሰዎች የሚሰጠንን አስተያየት፣ ድጋፍ፣ ተቃውሞ፣ ክብር፣ ዝና፣ ስምና ታላቅነት ከውስጣችን ዐቅም ጋር መዝነን ካላስተናገድነው አደጋ ያስከትላል፡፡ ሰዎች ትችላላችሁ፣ ያለ እናንተ ሰው የለንም፣ ጀግና ናችሁ፣ ስላሉን ያሉንን ሁሉ አንሆንም፡፡ ጭብጨባውን፣ ሙገሳውን፣ አድናቆቱን ለችሎታ መመዘኛነት ከወሰድነው ከራሳችን ጋር እንጣላለን፡፡ ቀስ በቀስ በዕድገትና በልምድ፣ በትምህርትና በተጋድሎ ልንደርስበት የሚገባንን ገፋፍተው ሲያወጡን ከተቀበልንና ‹ሕዝብ ከመረጠኝ፣ ሕዝብ ካለ፣ ሕዝቡ ከደገፈኝ› ካልን ራታችንን ቁርስ ላይ ያስበሉናል፡፡ እላይ ከወጣን በኋላም የምናደርገው ይጠፋናል፡፡ በውጫዊ ግፊትና አድናቆት ‹ነህ› የሚሉንን ከመቀበል በውስጣዊ ዕውቀት ‹አይደለህም› የሚለንን መቀበሉ ያዋጣናል፡፡ ዛሬ ዓለምን ለበሽታ የዳረጓት ዕንቁላል ሳይሆኑ ዶሮ የሆኑት ናቸው፡፡
ሰው በሂደት የሚሟላ ፍጡር ነው፡፡ የሚያሟሉትም ትምህርት፣ ልምድና የሰውነት ግንባታ ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ የሚፈጸሙት በጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ አንድን ነገር ዕድል ስላገኘን፣ ነገሮች ስለተመቻቹ፣ አቋራጭ መንገድ ስላለው፤ በአድናቆትም ሆነ በተቃውሞ ስለተገፋፋን፣ ጊዜ የሰጠው ቅል ስለሆንን ወይም ደግሞ በምናያቸው ፊልሞች፣ በምናነባቸው ስሜት ቀስቃሽ ጽሑፎች፣ ከጓደኞቻችን በሚፈጠሩብን ግፊቶች ተስበንና ተገፍተን ራታችንን ቁርስ ላይ መብላት የለብንም፡፡ ጉጉት የሌለው ነገ፣ የማይጋደሉበትም ሕይወት ስኬትን አያመጣምና፡፡ ስኬትን የማያጣጥም ሰውነት ደግሞ ምንጊዜም ውስጡ ክፍተት ይኖረዋል፡፡ ያ ክፍተት ነው ተስፋ መቁረጥን፣ ትካዜን፣ ራስን መጥላትን፣ የበታችነትን፣ ወራዳነትንና ራስን መጥፋትን የሚፈጥረው፡፡