ያልሰማኸው ነገር

ይሄ ልጅ ለምን እዚህ እንደመጣ ግልጽ አልሆነላቸውም፡፡ ከሃያ ዓመት በኋላ ነው እንዲህ ቤት ውሎ ቤት ሲያድር ያዩት፡፡ ሥራ አለው፣ በትምህርት ተወጥሯል፤ ንግዱን እያጧጧፈ ነው ሲባል ነበር የሚሰሙት፡፡ በቤቱ ውስጥ የተሻለ የተማረ ሰው እርሱ በመሆኑ ሠርግና ልቅሶ ለምን አልመጣህም ብሎ የሚወቅሰው ቤተ ዘመድ አልነበረም፡፡ አንዳንዶቹም ስሙን ሰምተው እንዲሁ ያደንቁታል እንጂ አይተውት አያውቁም፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ድሮ በልጅነቱ እንዳዩት ናቸው፡፡
አሁን ግን ነገር ዓለሙን ሁሉ ትቶ እዚህ አያቱ ቤት መዋል ማደር ከጀመረ ሰነባበተ፡፡ አያቱ ደግሞ ይሳቀቃል ብለው ለምን መጣህ? ሥራና ትምህርትህንስ የት ተውከው? ብለው መጠየቅ ከብዷቸዋል፡፡ እጅግ በጣም የገረማቸው ደግሞ መቀመጫው ላይ ወስፌ እንደተተከለበት ሁሉ ለአፍታ ቁጭ ማለት የማይችለው ሰውዬ ደርሶ ቀኑን ሙሉ ቤት ውስጥ ተቀምጦ ሲቆዝም መዋሉ ነው፡፡

አንድ ቀን ግን ደፍረው መጠየቅ እንዳለባቸው ወሰኑና ወደ እልፍኛቸው አስጠሩት፡፡ ‹‹ልጄ በደኅህ ነው? እንደዚያ ለምግብ እንኳን ጊዜ የለኝም የምትለው ሰውዬ ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብለህ የምትውለው›› አሉና ጠየቁት፡፡ አንገቱን ደፍቶ መሬቱን በመነጽሩ ጫፍ እየጫረ ዝም አላቸው፡፡ ‹‹የሆንከው ነገር አለ? ምናልባትኮ ለእኔ ቀላል ይሆናል፡፡ መቼም የዛሬ ልጆች ትንሹን ነገር ሁሉ አክብዳችሁ ነው የምታዩት፡፡ ሰውዬው እህል ሊሸከም ተጠርቶ ዋጋ ሲነጋገር ‹ለመሆኑ ሸክሙ ከባድ ነው ቀላል?› ብሎ ቢጠይቅ አሸካሚው ሰው ‹እንደ ተሸካሚው ነው› ብሎ መለሰለት አሉ፡፡ነገር እንዳያያዝህ ነው››
‹‹አያቴ ለአንተ ምንም አያደርግልህም፤ ምናልባትም ደግሞ አያስደስትህም›› አላቸው ጭኑን በመዳፉ እየመታ፡፡
‹‹ሲያደርጉት ነበር እንጂ ይህንን ማሰብ፤ ከሆነ ወዲያ መናገር ምን ያከብዳል››
‹‹ከወንድሜ ጋር ተጣላን› አላቸው ቀለል አድርጎ››
‹‹እና ወንድምና ወንድም መጣላቱ አዲስ ነገር ነው እንዴ››
‹‹ጠቡ ከበድ ያለ ነው››
‹‹ማቃለሉን ትታችሁ ማካበዱን እንዴት ቻላችሁበት››
‹‹መጀመሪያም የከበደ ነበር››
‹‹እንዴት እንዴት ሆኖ››
‹‹አንተኮ ሁሉን ታውቀዋለህ አያቴ፤ ዝም ብለህ ነው የምታስለፈልፈኝ››
‹‹ዕውቀት ብዙ ዓይነት ነው ልጄ፡፡ አሟልተህ የማታውቀው አለ፤ አዛብተህ የምታውቀው አለ፤ ጨርሰህ የማታውቀው አለ፤ የምታውቀውም ነገር አለ፡፡ ለመሆኑ ምንድን ነው ያጣላችሁ?››
‹‹እስከ ዛሬ ማንነቱን አላውቀውም ነበር፤ በእኔ ላይ ሲጫወት የኖረ መሆኑን አላውቅም ነበር፤ ሲጨቁነኝና ሲበድለኝ የኖረ፣ እንዲህ ሆኜ እንድቀር ያደረገኝ መሆኑን ዛሬ ዐወቅኩት›› አላቸው እያንገፈገፈው፡፡
‹‹ሌላስ ያወቅከው ነገር የለህም›› አሉት ጋቢያቸውን ከራሳቸው ወደ ትከሻቸው ወረድ እያደረጉ፡፡
‹‹ታላቅ ነኝ ብሎ ስንት ስቃይ ሲያደርስብኝ ነው የኖረው፡፡ ይደበድበኝ ነበር፤ ይቀማኝ ነበር፣ ይንቀኝ ነበር፣ ጉልበቴን ይበዘብዝ ነበር፤ ምርጥ ምርጡን ለራሱ ብቻ ይወስድ ነበር፤ ስሜን እንኳን በትክክል አይጠራኝም ነበር፤ ለራሱ በሚስማማው የማሾፊያ ስም ነበር የሚጠራኝ ፡፡››
‹‹ይህ ሁሉ ሲሆን ለመሆኑ አንተ ነበርክ››
‹‹የተወሰነው ደርሼበታለሁ፣ ሌላውን አንብቤያለሁ፣ ሌላውን ደግሞ ከሰው ሰምቻለሁ››
‹‹መልካም ይህንን ብቻ ነው የነገሩህ ሌላ ነገር አልነገሩህም፤ ላንተ ያደረገልህን ነገርስ አልነገሩህም፤ አንተ በእርሱ ላይ ያደረግክበትን ነገርስ አልነገሩህም?››
ዝም አለ፡፡
‹‹አየህ የምንሰማውና የምንናገረው የምንፈልገውን ብቻ ከሆነ ችግር ነው፡፡ ወይ ጨርሰን አለመስማት አለማየት ነው፡፡ እንሰማለን እናያለን ካልን ደግሞ ሁሉንም ማየትና መስማት ነው፡፡ የዛሬ ልጆች ችግራችሁ መርጣችሁ ነው የምታዩትና የምትሰሙት፡፡ በከፊል ሰምታችሁ በሙሉ ትፈርዳላችሁ፣ በጥቂት ዐውቃችሁ በብዛት ትደመድማላችሁ፤ መርጣችሁ ሰምታችሁ ሳትመርጡ ታወግዛላችሁ፡፡ ስማ ልንገርህ፤ አንተምኮ ብዙ ነገር አድርገህዋል፡፡ በድንጋይ መተህዋል፤ ደብተሩንና መጽሐፉን ቀዳደህበታል፤ የሚያጠናበትን ክፍል በድንጋይ እየደበደብክ ከሠፈሩ እንዲለቅ አድርገህዋል፡፡ ስንት የለፋበትንና የደከመበትን የሥዕልና የቅርጻ ቅርጽ ሥራውን ድምጥማጡን አጥፍተህበታል፡፡ ይህንንስ አልነገሩህም፡፡ አንተ ምንም ሳታጠፋ ከመላእክት ጋር ነው የኖርከው አሉህ? አንተ ተመታህ እንጂ አልተማታህም፤ ተሰደብክ እንጂ አልተሳደብክም አሉህ?እርሱስ ላንተ ያደረገልህ ነገር የለም? አላስተማረህም? የእናት የአባታችሁን ርስት ለመጠበቅ ደም አልከፈለም? አንተን የሠፈር ጎረምሶች በተተናኮሉህ ቁጥር የግንባር ሥጋ ሆኖ አልመከተልህም? በክፉው ቀን አዝሎህ ለስንት ቀን የተጓዘበትን፣ በረሃብ ቀን አንተን አስቀድሞ ያበላበትን፣ ይህንን አልነገሩህም፣ አልጻፉልህም?››
ዓይኑን ከግራ ቀኝ እያንከባለለ ያያቸው ጀመር፡፡
‹‹ሴትዮዋ ጆሮዬ ታሟል አልሰማም ብለው ከዘመድ ተጠግተው ይኖሩ ነበር አሉ፡፡ አንድ ቀን ታድያ ዘመዶቻቸው ቡና እየጠጡ ያሟቸዋል፡፡ አልሰማም ብለዋልና ምንም ነገሩ ቢያበግናቸው ዝም አሉ፡፡ ሐሜቱ እየቀጠለ ሲሄድ ግን አልቻሉምና ‹‹ምነው እናንተ፣ ሳልሞት በቁሜ ታወራርዱኛላችሁ›› ብለው ተናገሯቸው፡፡ ሰዎቹም ደንግጠው ‹እማማ አልሰማም አላሉም እንዴ?› አሉና ጠየቋቸው፡፡ ሴትዮዋም ‹ክፉ ክፉውንማ እሰማለሁ› አሉ ይባላል፡፡ እናንተም ክፉ ክፉውን ብቻ ነው እንዴ የምትሰሙት፡፡ ዝንጀሮ የራሷ ጠባሳ አይታያትም እንደሚባለው እናንተስ የሠራችሁት ስሕተት የለም?
‹‹ልጄ የተነገረህን ተወው አልልህም፤ እንዴ ሰምተህዋልና፡፡ ነገር ግን ያልተነገረህን ፈልግ፡፡ ያልተነገረህ ብዙ ነገር አለ፡፡ ስለወንድምህ ያልሰማህው ብዙ ነገር አለ፡፡ ደግነቱንና መልካምነቱን የነገረህ የለም፤ ጥፋቱንና ድክመቱን ግንቅመም እየጨመሩ በደንብ አስጨብጠውሃል፡፡ ጎዱህ እንጂ አልጠቀሙህም፡፡ እኛ ድሮ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ሂሳብ ስንሠራ ‹ተንጠልጣይ ሂሳብ› የሚባል ነገር ነበር፡፡ ሳይወራረድ፣ ሳይዘጋ እንዲሁ ከዓመት ዓመት ሲንከባለል የሚኖር ሂሳብ ነው፡፡ የእርሱ መዝጊያ ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ውሳኔ ነው፡፡ በውሳኔ ይዘጋል፡፡ ያለበለዚያማ የርሱ አለመወራረድ አንሶ የቀጣዩን ዓመት ሂሳብም ይበጠብጠዋል፡፡ ያልተዘጋ ቁርሾም እንዲህ ነው፡፡ አልዘጋ ካለ ወስኖ መዝጋት ነው፡፡ ከዚያ ወደፊት መሄድ ነው፡፡ ወደማትቆጣጠረው ትናንት ሄዶ መከራ ከማየት ወደምትቆጣጠረው ነገ መሄድ ይሻልሃል፡፡
‹‹እኔ ልምከርህ፤ የሰማኸውን ብቻ ሰምተህ አትፍረድ፤ ያልሰማኸውን ደግሞ ፈልግ፡፡ አንዳንዴም ከሰማኽው ያልሰማኸው ይበልጣል፡፡ የለም ብለህ አትደምድም፤ ቢኖር ትደነግጣለህ፤ አለ ብለህ ባይኖር ግን ምንም አትሆንም፡፡
‹‹ልገድለው እያሰብኩ ነበር፡፡ መንገድ እየፈለግኩ ነበር፤ ከራሴ ጋር እየተሟገትኩ ነበር፡፡ አተረፍከኝ፡፡ እስኪ እውነትም ያልሰማሁት ነገር ካለ ልፈልገው፡፡ አሁን እንኳን አንተ ብዙ ያልሰማሁትን ነገር ነገርከኝ፡፡ ለካስ ያወቅኩ መስሎኝ ባላወቅኩት ነው ልፈርድ የነበረው››
ያን ምሽት እዚያ ቤት አላደረም፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው፡፡