ኡመተ ፈናን ኡመተ ቀሽቲ ዲሬ ዳዋ

(አርቲስቱና ሽቅርቅሩ የድሬዳዋ ሕዝብ)


ደራሲ፡- አፈንዲ ሙተቂ
የገጽ ብዛት፡-191
ዋጋ፡- 60 ብር
የኅትመት ዘመን፡- 2006 ዓም
አፈንዲ ሙተቂ ያበረከተልንን መጽሐፍ አነበብኩት፡፡ ከአዋሽ ወዲያ ማዶ ያለውን ሀገራችንን ሙልጭ አድርገን ለማወቅ የሚጎድለን ነገር መኖሩን የምንረዳው የእርሱን መጽሐፍ ስናነብ ነው፡፡ እንኳን እንደ እኔ በጎብኝነት የሚያውቀው ቀርቶ ተወልጄበታለሁ አድጌበታለሁ የሚለው ሁሉ የቀበሌ መታወቂያውን እንደገና እንዲያወጣ የሚያደርግ መጽሐፍ ነው፡፡
ሰው የሚያውቀውን ሲጽፍ ወይም የሚጽፈውን ሲያውቅ እንዲህ ያለ መጽሐፍ ይገኛል፡፡ ባሕሉ አልቀረ፣ ትውፊቱ አልቀረ፣ አባባሉ አልቀረ፣ ታሪኩ አልተዘለለ፣ መልክዐ ምድራዊ መረጃው አልተዘነጋ፣ አፈ ታሪኩ ቦታውን አልሳተ፣ ሁሉም በመልክ በመልኩ ተሰድሮ እንደ መልካም የወታደር ሠልፍ የቀረበበት መጽሐፍ ነው፡፡

አፈንዲ ለአካባቢው ወግና ታሪክ ቅርበት ብቻ ሳይሆን ፍቅርም እንዳለው፣ ፍቅር ብቻም ሳይሆን ጥናትም እንዳለው፣ ጥናትም ብቻ ሳይሆን ትኩረትም እንዳለው መጽሐፉ ያሳየናል፡፡ የሕዝቡን ፍቅርና አንድነት፣ መተሳሰብና አብሮነት፣ የቆየውን የመተጋገዝ ልማድና ተግባቦት ያሳየባቸው ወጎቹ የመለያየት ጥላ ላጠላበት ህልውናችን ፈዋሾ ናቸው፡፡
በተለይም የሐረርጌ ኦሮሞን ትውፊትና ባሕል፣ የአስተዳደር ታሪክና ዕምቅ ብቃት ያሳየበት ጹሑፉ እዚያው ሕዝቡ ውስጥ ያለን ያህል እንድንረዳው የሚያደርግ ነው፡፡ አፈንዲ የአካባቢውን ነገር ሲነግረን በአንዳንዶች ዘንድ እንደሚታየው እንድንጠብ አድርጎ ሳይሆን እንድንሰፋ አድርጎ ነው፡፡ ያንን አካባቢ ከእኛ ውጭ አድርገን እንድናየው አድርጎ ሳይሆን ውስጡ እንድንገባበት አድርጎ ነው፡፡
አፈንዲ ሦስት ነገሮች አሉት፡፡ ርትዕ፣ ዕውቀትና የኃላፊነት ስሜት፡፡ ነገሮችን ያየበት መንገድ ርትዕ እንዳለው የሚያሳይ ነው፡፡ በአካባቢው ለተደረጉ ነገሮች ሁሉ ሃይማኖትና ዘርን ሳይለይ ለሁሉም የድርሻውን ሰጥቷል፡፡ የተለያዩ እምነቶች፣ ባሕሎችና ግለሰቦች በአካባቢው የነበራቸውን በጎ ሚና ለማጉላት፣ ክፉውንም በጨዋነት ለማረም ያደረገው ጥንቃቄ የሚያስመሰግነው ነው፡፡
አፈንዲ በተለይ ከአዋሽ ማዶ ስላለው ታሪክ፣ ባሕል፣ ትውፊትና መልክዐ ምድር ለሌላውም ሊተርፍ የሚችል ዕውቀት ስላለው የሚጽፈው የቃላት ስብስብ አይደለም፡፡ በእያንዳንዱ ቃል ላይ ዕውቀት ያዘለ ነገር አለው፡፡ የሚጽፍ ሰው የሚጽፈው ነገር የት እንደሚደርስ አያውቅምና በኃላፊነት ስሜት እንዲጽፍ ይመከራል፡፡ አፈንዲ በዚህ መጽሐፉ በእምነቶች፣ በሕዝቦች፣ በጎሳችና በፖለቲካ መሪዎች መካከል ተግባቦት ይፈጠር ዘንድ፣ መደናነቅና መከባበር እንዲኖር የሚያደርጉ ሐሳቦችን በኃላፊነት መንፈስ ጽፏል፡፡ ‹‹እንዴው ዘራዋ›› የሚል ነገር አላየሁበትም፡፡ ታላቅ ችሎታና ብስለት ነው፡፡
አንቡት፡፡ ታውቃላችሁ፣ ትዝናናላችሁ፣ ትጨምራላችሁ፡፡