የወፏ ዝማሬ – 2

በዓባይ ዳር በሚገኝ መንደር የምትኖር አንዲት ወፍ ነበረች፡፡ በዚያ ወንዝ ለሚዋኙም ሆነ ለሚሻገሩ ደምፅዋን አሠማምራ ትዘምር ነበረች፡፡ ደግሞ ላባዎቿ በኅብር ቀለማት የተሞሉ ነበሩ፡፡ እርሷ ላይ የሌሉ የአዕዋፍ ቀለማት አልነበሩም፡፡ ዝማሬና ዜማዋ ከቶ አይቀየሩም፡፡ በዚህም የተነሣ ዝማዋን ለምደውት አብረዋት የሚያዜሙ ብዙዎች ነበሩ፡፡ በዙሪያዋ ያሉ አዕዋፍ፣ ከወንዙ ለመጠጣት የሚመጡ አራዊት፣ በወንዙ ውስጥ የሚገኙ ዐሣት አብረዋት ያቀነቅናሉ፡፡ እንኳንና በነፍስ የሚኖሩ ሰዎችና በደመ ነፍስ የሚንቀሳቀሱ እንስሳት ቀርተው ዕጽዋት እንኳን እንደ ቅኔ ማኅሌት እንደ ገባ ደብተራ አብረዋት ያሸበሽባሉ፡፡ የእርሷ ዝማሬ ምንም የማይመስላቸው በወንዙ ዳር የተጎለቱት ድንጋዮች ብቻ ናቸው፡፡
እንዲህ እያለች ስትኖር ለዐቅመ ዕንቁላል ደረሰች፡፡ ጎጆ ልትቀልስም አሰበች፡፡ እንጨትና ሣር ሰብስባ ቤቷን የአንድ ጎጆ ባጥ ሥር መቀለስ ጀመረች፡፡ እንጨትና ሣር ደልድላ ጭድ በመካከሉ ልታስቀምጥ ስትል የሠፈሩ ልጆች መጡና በድንጋይና በእንጨት ፍርስርሱን አወጡባት፡፡ እርሷ ለመሥራት አንድ ወር የፈጀባትን እነርሱ ለማፍረስ አፍታም አልወሰደባቸው፡፡ ልጆቹ ጎጆዋን አፍርሰው የጀግንነት ስሜት ተሰምቷቸው እየሳቁና እየተደሰቱ ሄዱ፡፡ እርሷ ግን መከራዋን ታቅፋ ቀረች፡፡ መገንባት እንደ ማፍረስ መች ቀላል ነውና፡፡

መቼም ያለ ጎጆ አይኖር፤ ያለ ጎጆም ዕንቁላል አይጣል፡፡ ያለ ጎጆም ጫጩት አይፈለፈል፡፡ አማራጭ አልነበራትምና ዛፍ ላይ ሣርና እንጨቱን መሰብሰብ ቀጠለች፡፡ ልጆቹ ዐውቀው እንዳያፈርሱባትም በቅጠል ሸፈንፈን አደረገችው፡፡ ዕንቁላሉ መደላድል እንዲያገኝም ጭድ በመካከሉ ረበረበችበት፡፡ ነፋስ ወዝውዞ እንዳይጥለው በልጥ ከግንዱ ጋር ጠለፈችው፡፡ የፀሐይ ብርሃን እንዲያገኝም በስተ ምሥራቅ በኩል በር ሠራችለት፡፡ ከሥራዋ እፎይ ብላ ዕንቁላሏን ልትጥል ስትደላደል ግን እንደ አውሎ ነፋስ የሚያስገመግም ድምፅ ከወደ ዛፉ አካባቢ ሰማች፡፡ ድምፁም ወደ እርሷ ጎጆ እየቀረበ መጣ፡፡
ጎጆዋ ተነቃነቀ፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ የመጣ መሰለ፡፡ ቱር ብላ ወጣችና ዙሪያዋን እያንዣበበች ተመለካከተች፡፡ የሰማይ ስባሪ የሚያህል አሞራ እርሷ ጎጆ የሠራችበት ዛፍ፣ ያውም ጎጆው ከተንጠለጠለበት ግንድ ላይ ክንፉን እያማታ ቆሟል፡፡ አንዳች የሚበላ አጥንት በምንቃሩ ወሽቆ ከሥጋው ጋር ይታገላል፡፡ እርሱ ከሥጋው ጋር በታገለ ቁጥር የእርሷ ጎጆ ይነቃነቃል፡፡ ክንፉን ግራና ቀኝ ባማታው ቁጥር ኃይለኛ ነውጥ ይፈጥራል፡፡ ነውጡ በተፈጠረ ቁጥርም የእርሷ ጎጆ ይፈርሳል፡፡ አሞራው ጎጆዋን በግማሽ አፍርሶት ሄደ፡፡ እርሷም በዚያ አሳዛኝ ዝማሬዋ ታስተዛዝል ጀመር፡፡
እያስተዛዘለች እያለ አሞራው አሁንም እንደገና ከእርሱ ቁመት የማይተናነስ ሙዳ ሥጋ ይዞ መጣ፡፡ ለክፋቱ ደግሞ እዚያው ግንድ ላይ ቆሞ ቀሪውን የወፍ ጎጆ ይነቀንቀው ጀመር፡፡ አሞራው አራተኛ ጉርሻ ላይ ሲደርስ ጎጆው ሙሉ በሙሉ ፈረሰ፡፡ የወፏም ዝማሬ ወደ እንጉርጉሮ ተለወጠ፡፡የት ትሂድ? የትስ መሄጃ አላት? ወፍ ባትሆን ተመኘች፡፡ ግን ወፍ ናት፡፡ አሞራው ለመብላት ሲል ጎጆዋን ያፈርሳል፡፡ እርሷ ግን ጎጆዋን እሠራ ብላ የአንዲት ፍሬ ፍርካሽ እንኳን ለመቅመስ ዕድል አልነበራትም፡፡
አዝና አዝና ስትጨርስ የግድ ነውና ጎጆዋን ለመሥራት እንደገና ፈለገች፤ እንደገና አሰበች፡፡ እንደገናም ሣርና እንጨት፣ ቅጠልና ጭድ ፍለጋ መንከራተት ጀመረች፡፡ የነበረው እንዳልነበረ ሆኗልና እንደገና ሀ ብላ ወጠነች፡፡ አሁን ዜማዋ ከፊል እንጎርጉሮ፣ ከፊል ምሬት፣ ከፊል ደግሞ ተስፋ ሆኗል፡፡ ተስፋ ያልቆረጠችው ተስፋ ያለው ነገር አግኝታ አይደለም፡፡ ተስፋ ከመቁረጥ የሚሻል ሆኖ እንጂ፡፡
አሁን ከሰውም ከእንስሳትም ርቃ ዓባይ ዳር በሚገኝ የደንገል ዛፍ ላይ ጎጆዋን መሥራት ጀመረች፡፡ ምናልባት በዓለም ከመኖር ብሕትውናው ይሻል ይሆን ብላ፡፡ ‹‹ወይከውን ከመ ዕጽ እንተ ትክልት ኀበ ሙሐዘ ማይ – በወንዝ ዳር እንደተተከለች ተክል ይሆናል፤ እንተ ትሁብ ፍሬሃ በበጊዜሃ – ፍሬዋን በየጊዜው እንደምትሰጥ፤ ወቆጽላኒ ኢይነግፍ – ፍሬዋም እንደማይደርቅ›› የሚለውን አስባ፡፡
እንደ ገና ድካም እንደገና ልፋት፡፡ ጎጆዋን ልትቀልስ፣ ዕንቁላሏን ልትጥል፤ ጫጩት ልትፈለፍል፡፡ ከመጀመሪያው ቤት ሁለተኛው፣ ከሁለተኛውም ሦስተኛው ከበዳት፡፡ እንጨቱ እየተማገደ፣ ሣሩ እየተመደመደ፣ ጭዱም እየተወሰደ አልቋል፡፡ ለምለሙ ጊዜ አልፎ የበጋው ደረቅ ወቅት መጥቷል፡፡ በቅርብ ይገኝ የነበረው ነገር ሁሉ ርቋል፡፡ ግን ምን ይደረጋል፡፡  
ክንፏን እስከሚያማት ድረስ ባክና በሰበሰበችው እንጨት፣ ሣርና ጭድ ጎጆዋን ለሦስተኛ ጊዜ ቀለሰች፡፡ አንድ ሦስት ቀን የቀደመው መዓት ይመጣል ብላ ብትጠብቅ ምን የለም፡፡ እንዲህ ከሰውም ከእንስሳም መራቁ ይሻላል ብላ በምርጫዋ ተደሰተች፡፡ አንድ አንድ እያለችም ዕንቁላሏን መጣል ጀመረች፡፡ ችግሩ ግን ያን ጊዜ መጣ፡፡ እርሷ ዕንቁላሏን ጥላ ምግብ ፍለጋ ሄዳ ስትመለስ ዕንቁላሏን አታገኘውም፡፡ ሁለት ሦስት ቀን ወድቆ ይሆናል ብላ አሰበች፤ ጥፋቱም የእርሷ እንደሆነ አመነች፡፡ እንዳይወድቅ ለማድረግም ጎጆዋን እንደገና አጠባበቀች፡፡ በአራተኛው ቀን ግን አሁንም ዕንቁላሏን አላገኘችውም፡፡ ፈለገችው፡፡ እንዳች ስባሪ በአካባቢው አላገኘችም፡፡ በአምስተኛው ቀን ዕንቁላሏን ጥላ ከጎጆዋ ወጣችና እልፍ ብላ በሌላ ዛፍ ላይ ተቀምጣ የሚሆነውን ማየት ጀመረች፡፡
እነሆ ጉዱ፡፡
እርሷ ወጣ ከማለቷ አንድ ዕባብ በግንዱ ላይ እየተሳበ መጣ፡፡ ዕባቡ የመጣው ከወንዙ ዳር ነው፡፡ አስጠሊታ ራሱን ወደ ጎጆዋ አዝልቆ ዕንቁላሏን ሰለቀጠው፡፡ ነፍስ አልነበራትም እንጂ ድንጋጤው ነፍሷን ያወጣው ነበር፡፡ አሁን የከፋ አደጋ መጣ፡፡ ቤቷ አይደለም የፈረሰው፤ ዕንቁላሏ ነው የሚበላው፡፡ ምትኳ፣ ዘሯ፣ ተስፋዋ፣ ሀልወቷ፣ ኑባሬዋ ነው የሚበላው፡፡ ዕንቁላል እንዳትጥል አልተከለከለችም፤ የምትጥለው ግን ለሌላ ሆነ፡፡ እርሷ አንድ ቀን ዕንቁላል መጣል ታቆማለች፡፡ ያን ጊዜ ህ ዕንቁላል የለመደ ዕባብ እርሷን መብላት ይጀምራል፡፡ ከሁሉም ተገላገልኩ ብላ የመጣችበት ቦታ ከሁሉም የባሰ ሆነ፡፡
በረረረች፣ ከነፈች፣ ወጣች፣ ወረደች፣ ከነፋሱም ጋር ሄደች፣ ከነፋሱም በተቃራኒም ነጎደች፡፡ መሬት ወረደች፣ ወንዝ ውስጥ ገባች፡፡ በመጨረሻ ደከማት፡፡ ሲደክማት አንድ ዛፍ ላይ ቆማ እንዲህ እያለች ታንጎራጉር ጀመር፡፡
ኦ እለሎ፣ ኦ እለሎ
ኦ እለሎ፣ ኦ እለሎ
ወዴት ሄጄ ልኑር
ወዴት ሄጄ ልሥራ፤
ባጡ ሥር ስሠራ
ልጆቹ መከራ፣
ዛፉ ላይ ስሠራ
አሞራው መከራ፣
ወንዙ ዳር ስሠራ
ዕባቡ መከራ፡፡
ወዴት ሄጄ ልኑር፣
የት ሄጄ የት ልሥራ፤
የት ውዬ የት ልደር፤
 © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው