እንደገና እንጋባ(የመጨረሻ ደብዳቤ)
ይኼ የመጨረሻዬ ደብዳቤ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ወይ እንደገና እንጋባለን አለበለዚያም እኅትና ወንድም ሆነን እንቀጥላለን፡፡ አሁን ‹እኅትና ወንድም ሆኖ መቀጠል›› ሲባል ቀላል ነገር ይመስላልኮ፡፡ የተለያዩ ባልና ሚስቶች ‹እኅትና ወንድም› ሆነው ለመቀጠል ሦስት ነገሮች ሳያስፈልጋቸው አይቀርም፡፡ ጠላትነትን ማጥፋት፣ ሌላ ዓይነት ወዳጅነትን መቀጠልና በአዲሱ መንገድ የሚመጡትን አስከፊ ነገሮች ሁሉ ለመቀበል መቻል፡፡ አንዳንድ ተጋቢዎች ሲለያዩ በጋብቻ ምትክ ጠላትነትን ተክተው ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ እንኳን ከዚህ በፊት አንድ ሆነው የኖሩና አንድ ሆነው ያደሩ፣ የተዋወቁም አይመስሉ፡፡ አንዱ ሌላውን ሲያስበው ያንገሸግሸዋል፡፡ ‹‹በለው በለው፣ ግደለው ግደለው› የሚለው ስሜት ይመጣበታል፡፡ ከፍቺ በኋላ ለሚፈጠሩ አሰቃቂ ወንጀሎች አንዱ ምክንያትም ይኼው ነው፡፡ ንብረት ክፍፍል ላይ ‹‹ይህንንማ አትገኛትም፣ አያገኛትም›› እየተባባሉ ምርኮ ስብሰባ የሚያስመስሉትም ለዚህ ነው፡፡
‹ሌላ ዓይነት ወዳጅነት› ያልኩሽ ቢያንስ ለመጠያየቅ፣ ተገናኝቶም ቢሆን ሻሂ ለመጠጣት፣ ስለ ልጆች ለመነጋገር፣ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠያየቅ መግባባት ላይ መድረስ ማለት ነው፡፡ በትዳሩ ጉዳይ ለጊዜው ባይግባቡም ሌላ የሚያግባባቸው ነገር አያጡም፡፡ ትዳሩ ቢፈርስ እንኳን ትውውቁና ዝምድናው እንዲቀጥል ለማድረግ መጣር አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ አንዳቸው ስለሌላቸው ክፉ ላለማውራት፣ ምሥጢሮቻቸውንም ጠብቀው ለመኖር መስማማት ኑሮን ሰላማዊ ለማድረግ ሳይጠቅም አይቀርም፡፡ ይኼ ነገር ለሁለቱም ሰላማዊ ኅሊና ይሰጣቸዋል፡፡ ከጠብ ስሜት፣ ከበቀል መንፈስ፣ ያድናቸዋል፡፡ ስለ ሌላ ሰው በክፉ ማሰብ ከሚታሰብለት ሰው በላይ ክፉ አሳቢውን ይጎዳዋል፡፡ ለስንት በጎ ነገር ሊጠቀምበት የሚችለውን የኅሊና ጉልበት ለማይጠቅም ጠብና ሐሜት፣ ጥላቻና ክፋት እንዲጠቀምበት በማድረግ ውሳጣዊ ሰላሙን ያሳጣዋል፡፡ በሌላም በኩል ደግሞ በሰላም ተለያይተው በሰላም የሚኖሩ ተፋቺዎች በጠብ ከተለያዩት ይልቅ እንደገና ለመጋባት የቀና መንገድ ይኖራቸዋል፡፡ ለፍቺ ያበቃቸው ቁስል እንዲድን ዕድል ሰጥተውታልና፡፡ ከፍቺ በኋላ በክፉ በመፈላለግ ቁስሉ ይበልጥ እንዲያመረቅዝ አላደረጉትምና፡፡
በአዲሱ መንገድ የሚመጡትን አስከፊ ነገሮች ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ መሆን ሲባል መለያየቱ የሚያመጣቸውን አሳዛኝና አስከፊ ነገሮችም ለመቀበል ዐቅም ማግኘት ማለት ነው፡፡ ተለያይቶ መኖሩን፣ የሀብት መካፈሉን፣ የአንደኛው ወገን ከሌላ የጾታ ጓደኛ ጋር መታየቱን፣ ከልጆች መለየትን የመሰሉ ነገሮችን ‹አስፈላጊ ሰይጣን› ናቸው ብሎ ለመቀበል መቻል ነው፡፡ ይህንን ለመቀበል ዐቅም ያጡ ተፋቺዎች ትልቁን ትዳር አፍርሰው ለትንሹ ንብረት ሲሟገቱ፤ እንዴት እገሌን ከሌላ ጋር አየዋለሁ፣ እንዴት እገሊትን የእገሌ ሆና አያታለሁ እያሉ ደም ሲለብሱ፤ ቆይተውም ወደ በቀል መንገድ ሲገሠግሡ ይታያሉ፡፡ ለዚህ ነው ‹እኅትና ወንድም ሆነን እንቀጥላለን›› ያልኩሽ፡፡ እርሱም ዛሬ ዛሬ ለብዙዎቻችን እያስቸገረን ነውና፡፡
የመጨረሻው ደብዳቤዬ ነውና ‹ባለቤቴ› ስለሚለው ነገር እነግርሻለሁ ያልኩትን ነግሬሽ ልጨርስ፡፡ በግእዙ ‹በዐለ ቤት› ማለት ‹የቤት ጌታ፣ የቤት አለቃ› ማለት ነው፡፡ ‹ቤት› ደግሞ በምሥራቃውያን ባሕል ብዙ ነገርን የሚይዝ ነው፡፡ ቤት ነገድ ነው ‹ቤተ እሥራኤል እንዲሉ› ቤት ሀገር ነው ‹ቤተ አምሐራ›› ብለው እንዲጠሩ፡፡ ቤት በማኅደሩ አዳሪውን ጠርተው ‹ነዋሪ› ማለት ነው፡፡ ‹‹ቤቶች›› እንዲሉ፡፡ ቤት ‹የቅርብ ዘመድ› ማለት ነው፡፡ ‹ቤተሰብ› እንዲሉ፡፡ ቤት ወገንን ያሳያል ‹ሥራ ቤቶች› ሲል የቤት ውስጥ ሥራ የሚሠረቱትን አንድ አድርጎ እንዲገልጥ፡፡ ባለ ይዞታነትንና ባለሀብትነትንም ይገልጣል፡፡ ‹ባለቤት› ሲል ባለሀብት ማለት እንደሆነው፡፡ ቤት ልብስም ይሆናል ‹ቤተ እግር› ሲል ካልሲ፣ ገምባሌ ማለት ነውና፡፡ ቤተ እድ ሲልም ‹እጀ ጠባብ፣ እጅጌ፣ ቀለበት› ማለት ነው፡፡ የተሸለመ እልፍኝ ማለትም ይሆናል፡፡ ‹ቤተ አንስት› ሲል የተሸለመ የተጌጠ ቤት ማለት ነው፡፡
ባለትዳሮችም ‹ባለቤቴ› ሲባባሉ የቤቴ ጌታ፣ የቤቴ አለቃ፣ ወገኔ፣ ነገዴ፣ አብሮኝ የሚኖር፣ የቅርብ ዘመዴ፣ በአንድ አብረን የምንሠራ፣ የሀብቴ የንብረቴ ባለሀብት ባለይዞታ የሆነ፣ ጌጠየ፣ ሽልማቴ፣ ልብሴ፣ ሞገሴ፣ እልፍኜ› ማለት ነው፡፡ በሌላም በኩል ‹ቤተ› ማለት ‹አደረ፣ ኖረ› ማለት ነው፡፡ ባለቤቴ ማለት ደግሞ አብረን የምናድር አብረን የምንኖር፣ ልቤ መኖሪያዋ፣ ማደሪያዋ ልቧ መኖሪያዬ፣ ማደሪያዬ የሆነ ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ሊቃውንትም ‹ጉዳዩን በቤት በኩል ብቻ ሳይሆን በ‹በዐል› በኩልም ይፈቱታል፡፡ ‹በዐለ› – ከበረ፣ ከፍ ከፍ አለ፡፡ በዐለ – ቻለ፣ ዐወቀ፣ ሠለጠነ፣ ገዛ ማለት› ነው፡፡ ‹በዐለ መድኃኒት› ሲል መድኃኒት ያለው የሚያውቅ ማለት ነው፡፡ ‹በዐለ ሥልጣን› ሲል ሥልጣን ያለው ማለቱ ነው፡፡ ‹በዐለ ቤት› ሲል ‹የቤቱ ሠራዒ መጋቢ› ማለቱ ይሆናል፡፡ ባለቤቴ የሚለው ነገር እኩል ሥልጣንን፣ እኩል ባለሀብትነትን፣ እኩል አለቅነትንና እኩል መብትን ያሳያል፡፡ በእኔ ላይ ሥልጣን ያለው፣ ሥልጣን ያላት፣ እኔን የምታውቅ፣ በእኔ ላይ የሠለጠነ፣ የሠለጠነች፣ ማለት ነው፡፡
ለዚህ ይመስለኛል በባሕላችን ‹ከባለቤትዎ ጋር› እየተባለ ጥሪ የሚተላለፈው፡፡ ሰውየው ለብቻው ሙሉ አይሆንም፣ ሴትዮዋም ለብቻዋ ሙሉ አትሆንምና፣ ሥልጣንም የላትም የለውምና፣ ስጦታ እሰጣለሁ፣ ቃል እገባለሁ፣ ብትልና ቢል አይችልምና ሙሉ አድርገን እንጥራቸው ብለው ነው ‹ከባለቤትዎ ጋር› ብለው የሚጋብዙን፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በአብርሐና አጽብሐ ዘመን ብቻ ነው ይባላል ሁለት ነገሥታት በአንድ መንበር የገዙት፡፡ ከአብርሐ አጽብሐ ወዲህ በትዳር ብቻ ይመስለኛል ሁለት ነገሥታት በአንድ መንበር የሚነግሡት፡፡ ይህንን በአንድ መንበር ሁለት ነገሥታት መንገሣቸውን ነው ‹ባለቤቴ፣ ባለቤቴ› እየተባባልን የምንጠራው፡፡
አንዱ ለሌላው ታዛዥ፣ ተገዥ ሆኖ፤ እርሱም በሌላው ላይ ገዥ፣ አዛዥ ሆኖ፣ የመኖርን ስልት ለማምጣት ነው ‹ባለቤቴ› ማለት፡፡ በፈቃድ መገዛትን፣ በፈቃድም ራስን መስጠትን ለማመልከት ነው ‹ባለቤቴ› ማለት፡፡ አንዱ የኔና ያንቺ ችግር ‹ብቻችንን ባለቤት እንሁን› እያልን ይመስለኛል፡፡ ሥልጣናችንን ስንጠቀመው ሌላውን ባለ ሥልጣን እየረሳን ስለሆነ መሰለኝ ችግራችን፡፡
እና እስኪ ከራስሽ ጋር ብቻ ተወያይና ለእኔም ባትጽፊልኝ ለራስሽ መልስ ስጭ፡፡ እኔ ለአንቺ፣ አንቺም ለእኔ ክፉ ብትሆኚ እንኳን የተሻልን ክፉዎች የምንሆን ይመስለኛል፡፡ ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይባል የለ፡፡
በይ ደኅና ሁኚ፡፡ ምንም ብንለያይ ደኅና መሆንሽ ሁላችንንም ይጠቅማልና፡፡
© ሦስቱም ደብዳቤዎች በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ወጥተዋል