click here for pdf

በተፈጥሮ ካልተገኙና ሰው ልጅ ከፈጠራቸው ከማይንቀሳቀሱ የሥልጣኔ ውጤቶች አንዱ ከተማ ነው፡፡ ከተማ የአንድ ሕዝብ ሥልጣኔ የሚታይበትና የሚቀላጠፍበት ማዕከል ነው፡፡ በዚህም የተነሣ የሰው ልጅን ታሪካዊ ሂደት በመመዝገብና የደረሰበትንም ሥልጣኔ በማሳየት ረገድ የከተማን ያህል የተሻለ ቦታ የለም፡፡ የጥንታዊ ሰዎችን ሥልጣኔና ታሪክ የሚያጠኑ ባለሞያዎች የጉዞውን ሂደት የሚገልጡ መረጃዎችን የሚያገኙት በቁፋሮ ከሚገኙ ጥንታውያን ከተሞች ነው፡፡ በእነዚህ ጥንታውያን ከተሞች የሰው አነዋወር፣ ታሪክ፣ የመንግሥት አሠራር፣ የንግድና የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ ወግና ሥርዓት፣ እምነትና ባሕል በተሰናሰለና ሥርዓት በጠበቀ መንገድ ይገኝባቸዋል፡፡
በአብዛኛው የገጠሩ ማኅበረሰብ ባልተሰባሰበ፣ አንድ ወገን በሆነ፣ ግልጽ የአኗኗር መርሕ፣ አስተዳደራዊ መዋቅር እምብዛም ባልተዘረጋበት መንገድ የሚኖር ነው፡፡ የከተማ ማኅበረሰብ ግን በተወሰነ ቦታ፣ ከተለያየ ማኅበረሰብ ተውጣጥቶ፣ በአንድ ውሱን ሕግ እየተዳደረ፣ ለክዋኔዎች ቦታ ወስኖ(ለንግድ፣ ለአምልኮ፣ ለመንግሥት አስተዳደር፣ ለመኖሪያ፣ ወዘተ) የሚኖር በመሆኑ የሥልጣኔ መገለጫዎች በከተሞች የሚገኙትን ያህል በገጠር አናገኛቸውም፡፡ ሐውልቶች፣ አደባባዮች፣ አብያተ መንግሥት፣ ሳንቲሞች፣ የኪነ ጥበብ ሕንጻዎች፣ የተደራጁ ገበያዎች፣ የውኃ መሥመሮች፣ የከተማ መከለያ ግንቦች፣ የእምነት ማዕከሎች በከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ ተሠርተው የምናገኛቸው በከተሞች አካባቢ ነው፡፡

በሀገራችንም የታሪክና ቅርስ ማዕከል የሆኑትን አኩስምን፣ ሮሐን፣ ሐረርን፣ ጎንደርን፣ አንኮበርን፣ አዲስ አበባን፣ ሌሎችንም ብንመለከተ የመንግሥት፣ የኢኮኖሚና፣ የእምነት መናኸሪያ ከተሞች የነበሩና የሆኑ ናቸው፡፡ በእነዚህ ቦታዎች የምናገኛቸውን እርስ በርስ የተግባቡ፣ የተሠናሠሉና የተመጋገቡ የሥልጣኔ መገለጫዎችን ያህል በሌሎች ቦታዎች አናገኝም፡፡ በሌሎች ቦታዎች የምናገኛቸው በተናጠል የተቀመጡ የሥልጣኔ መገለጫዎችን ነው፡፡
የሰው ልጅ በተፈጥሮው ምክንያት ትናንትን ይጠይቃል፡፡ እንዲሁ ዛሬን ብቻ ዝም ብሎ አይቀበልም፡፡ እንደ ሥነ ፍጥረት ሊቃውንት ይህንን የሚጠይቁት መላእክትና ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ መላእክት በተፈጠሩ ጊዜ ‹‹ከየት ተገኘን? እንዴትስ ልንገኝ ቻልን?›› ብለው የጠየቁት ግእዛን ያላቸው (ማሰብና መመርመር የሚችሉና የሚያስፈልጋቸው) ፍጡራን በመሆናቸው ነው፡፡ የሰው ልጅም በምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ዘመን ጀምሮ በእምነትና በፍልስፍና መስኮች ሲጠይቃቸው ከኖራቸው ጥያቄዎች አንዱ ‹‹ዓለም ከየት መጣች?›› የሚለውን ነው፡፡
ሰው ትናንትን የማወቅ፣ ከትናንቱም የመማር፣ ከትናንት ተምሮም ወደፊት የመንደርደር ዕምቅ ፍላጎትና ችሎታ ስላለው መሬት እየጎረጎረ፣ ዋሻ እየበረበረ፣ ዐለት እየፈለጠ፣ ተራራ እየገለበጠ የጥንት ሰዎችን አድራሻ፣ ማንነትና ሥራ ሲመረምር ይኖራል፡፡
ሰው እንደ እንስሳ የዛሬን ብቻ ኑር ሊባል አይችልም፡፡ እንስሳ ትናንትም ነገም የለውም፡፡ ሰው ግን የሦስት ነገሮች ውጤት ነው፡፤ የትናንት አሻራ፣ የዛሬ ሥራ፣ የነገ ራእይ፡፡ ሰው ነገን ያለ ትናንት ማሰብ አይችልም፡፡ ተፈጥሮ አንድን ነገር ለብቻው በንጣሌ እንድንረዳው አልተወችንምና፡፡ ተፈጥሮ ራሷ የትይይዝ ውጤት ናት፡፡ ሊቃውንት ይህንን ለማስረዳት እንደ ቀላል ማሳያ የሚሰጡን ቀለማትን ነው፡፡ አንዱ ቀለም ከሌላ የሚግባባው ቀለም ጋር ስምምነት ፈጥሮ(harmony) ነው የሚኖረው፡፡ ይህንን የቀለማት ተግባቦት የሰዎች አለባበስ፣ የቤት አሠራር፣ የፀጉርና የሰውነት ቀለም፣ የሚተከሉ ዛፎችና እንዲፈጥሩት ይደረጋል፡፡ ምንም እንኳን እነዚህን ቀለማት አስበን ባንመርጣቸውም ተፈጥሮ ተግባቦትንና ስምምነትን ስለምትፈልግ ደመ ነፍሳዊ በሆነ መንገድ እናከናውነዋለን፡፡ 
በአንዲት ከተማ ሕይወት ውስጥም እንደ ቀለማቱ ተግባቦት ሁሉ ትናንት፣ ዛሬና ነገ ተግባብተው መገኘት አለባቸው፡፡ እንኳን እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከመቶ ዓመታት የዘለለ ታሪክ ያላቸው ከተሞች ቀርተው የቅርብ ዘመን የምሥረታ ታሪክ ያላቸው እነ ዱባይ እንኳን አንዳች ከጥንታዊነት ጋር የሚያያዝ ታሪክ ፍለጋ ሲኳትኑ፣ ያንንም ለማሳየትና የከተማቸው የሕይወት አካል ለማድረግ ሲጥሩ እናያቸዋለን፡፡
በአንድ ከተማ ሕይወት ውስጥ በሳል ነቢብ(ቲወሪ)፣ አመራርና አሠራር ከሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አንዱ ትናንትን፣ ዛሬንና ነገን ከከተማዋ ዕድገት፣ ሥልጣኔና የአነዋወር ዘይቤ ጋር አጣጥሞ የመሄድ ብልሃት ነው፡፡ የከተማዋ ጥንታዊነት የዛሬ ዕድገቷንና የነገ ተስፋዋን እንዳይገታው፤ የከተማዋ የዛሬ መስፋፋት፣ ዕድገትና ሥልጣኔ የትናንት አሻራዋን እንዳያጠፋው፤ የከተማዋ የትናንት ታሪክና የዛሬ ዘይቤም የነገውን ትውልድ ድርሻና ዕጣ ፋንታ እንዳያቀጭጨው – በሳል የሆነ ነቢብ፣ አመራርና አሠራር ይጠይቃል፡፡
የአንዲት ከተማ መልክዐ ጠባይ፣ ሕይወትና እሴት የሚገነባው ከዚህ መሰሉ ነቢብ፣ አመራርና አሠራር ነው፡፡ የከተማዋ ሕንጻዎች፣ መኖሪያዎች፣ መንገዶች፣ የሕዝብ ቦታዎች፣ ገበያዎች፣ የእምነት ቦታዎች፣ ማኅበራዊ ተቋማት፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳትና ውበት፣ ከዚህ ነቢብ፣ አመራርና አሠራር ይወለዳሉ፡፡ የሚፈቀዱና የሚከለከሉ ነገሮች ከዚህ ይመነጫሉ፤ የሚጠበቁና ለሕዝብ ክፍት የሚሆኑ ነገሮች ከዚህ ይመሠረታሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ቁልፍ ችግሯ ትናንት፣ ዛሬና ነገን የምታግባባበት የራስዋ የሆነ፣ በዘመናት የዳበረ፣ የተፈተነና ውጤታማነቱ የተመሰከረለት ‹ነቢብ፣ አመራርና አሠራር› ማጣት ይመስለኛል፡፡ በአንድ የውይይት መድረክ አንድ የከተማ ዐቅድ ባለሞያ እንደገለጡት ‹‹አዲስ አበባ እያንዳንዱ መንግሥት የየራሱን ርዕዮተ ዓለም ያነባበረባት ከተማ ናት – The layer of different Ideologies ፡፡ ያ ነው ከተማዋን ሲምታታባት እንዲኖር ያደረገው››
አዲስ አበባ አሁን ዐሥረኛውን የከተማ መሪ ዕቅድ እያዘጋጀች ነው፡፡ እነዚህ መሪ ዕቅዶች ምንም እንኳን ሳይንሳዊ አሠራርን የተከተሉ ሞያዊ ሥራዎች ቢሆኑም የሚዘወሩት ግን በየዘመናቱ ሀገሪቱ በምትመራባቸው ርእዮተ ዓለሞች ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ አዲስ አበባ ‹ወጥ፣ ለዘመናት የዳበረ፣ የተፈተነና የተመሰከረለት የከተማ ዘይቤ› እንዳይኖራት አድርጓታል፡፡
ባለፈው መንግሥት ጊዜ የቁጠባ ቤቶች የአዲስ አበባ የቤቶች መልክዕ ሆኖ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ኮንዶሚኒየምና ሪል እስቴት የአዲስ አበባ የቤት መልክዕ ሆነዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከንቲባነት ለረዥም ዓመታት በማገልገል የሚታወቁት ከንቲባ ዘውዴ እንደሚሉት በአዲስ አበባ ቀበሌ ሲቋቋም ከ2500 – 4000 የሚደርስ ሕዝብ የሚይዝ አንዳች የጉርብትና ማዕከል ለመፍጠር ነበር፡፡ ጉርብትናን ዘመናዊ ለማድረግ፡፡ ‹ከተማ ማለት የጉርብትና ሥርዓት ነውና›፡፡ ርእዮተ ዓለሙ ሲቀየር ግን ቀበሌዎች የጉርብትና ማዕከላት መሆናቸው ቀርቶ የቀይ ሽብርና የነጭ ሽብር ማዕከላት ሆኑ፡፡ ቀበሌ ማለትም የአብዮት ማራመጃ ማዕከል ሆነ፡፡ በሀገራችን መንግሥታት የሚቀያየሩት በመፍረስ በመሆኑ በመንግሥታት መካከል ርክክብ አልተደረገም፡፡
ይህንን መሰሉ በየጊዜው የሚለዋወጡ ነቢቦች፣ አመራሮችና አሠራሮች አንዳቸው ከሌላቸው ጋር ተግባብተው የሚመሠረቱ ባለመሆናቸው አዲስ አበባ ስትፈርስ ስትሠራ የምትኖር መሞከሪያ ከተማ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ እንኳንስ በተለያዩ መንግሥታት ርእዮተ ዓለሞች መካከል ቀርቶ በአንድ መንግሥት ዘመናት እንኳን ሲያፈርሱ ሲሠሩ መኖር እየተለመደ መጥቷል፡፡ ከሸራተን አካባቢ የተነሡ ነዋሪዎች ለድጋሚ ተነሺነት የተጋለጡት በዚህ ያልተግባባ አሠራር ጭምር ነው፡፡ አዳዲስ ቤቶች እንደገና ለመንገድና ለሌሎች ግንባታዎች ተብለው የተሠሩበት ሲሚንቶ ሳይደርቅ እንዲፈርሱ የሚደረጉት በዚህ ወጥነት በሌለው የከተማዋ ነቢብ፣ አመራርና አሠራር የተነሣ ነው፡፡ በተሠሩ በጥቂት ዓመታት ለባቡር ተብለው የፈረሱትንና 900 ሚሊዮን ብር የፈጁትን የአዲስ አበባ መንገዶችን በዚህ በበሰለ ነቢብ፣ አመራርና አሠራር ብቻ ነበር ማትረፍ ይቻል የነበረው፡፡ አንድም ቀድሞ በማሰብ፣ አለያም አጣጥሞ በመሥራት፡፡ 
አዲስ አበባ ዕድገቷንና ታሪኳን የማጣጣም ፈተና ገጥሟታል፡፡ ለመሆኑ ያለፉ ነገሮቿን ሁሉ እንዳሉ ይዛ መቀጠል አለባት? ያለፉ ነገሮቿንስ ሙሉ በሙሉ አፈራርሳስ መቀጠል አለባት? ለመሆኑ ታሪክና ዕድገት፣ ቅርስና ሥልጣኔ እንዴት ነው የሚጣጣሙት? ከተማዋ እነዚህን በትክክል ካልመለሰች ከተማ ሳይሆን ዘመናዊ የሰው ልጅ ማጎሪያ ትሆናለች፡፡ ዛሬ የሚሠሩት ታላላቅ ግንባታዎቻችንስ የነገውን ትውልድ ሥልጣኔ፣ አነዋወርና ፍልስፍና ከግምት ውስጥ እያስገቡ ናቸው? የዛሬ አምስት ዓመት የገነባናቸውንና ስናስመርቃቸው ጉሮ ወሸባ ያረገድንባቸውን እንዲህ በፍጥነት የምናፈርስ ከሆነ ሌሎቹን እንድንጠራጠር ያደርገናል፡፡
አሁን አሁን አዲስ አበባ ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬንም ከነገ የሚያጣጥም ነቢብ፣ አመራርና አሠራር በማጠቷ ምክንያት የአዲስ አበባ ከተማን ጥንታዊነት የሚያሳዩ ቅርሶች እንደ ነፍጠኛና ፊውዳል መገለጫዎች እየተቆጠሩ፣ ቀጥታና ቀጥታ ያልሆነ ሞት እየተፈረደባቸው ነው፡፡ ቀጥተኛ የሆነ ሞት የሚባለው ለዕድገት ፀር፣ለግንባታ ዕንቅፋት፣ ለመስፋፋት እንከን አድርጎ በማየት የማፍረስ ርምጃ መውሰድ ነው፡፡ በዚህ ፍርድ ምክንያት ጥንታውያን መንደሮች፣ ቤቶች፣ ድልድዮች፣ ሐውልቶች፣ አደባባዮች፣ የንግድ ማዕከላት፣ እንዲፈርሱ ተደርገዋል፡፡
ሁለተኛውና ቀጥታ ያልሆነ ሞት የምንለው ደግሞ እነዚህን ጥንታውያን ሀብቶች የመከባከብ ኃላፊነት ያለበት አካል ክብካቤ በመንፈግና ቀስ በቀስ እንዲፈርሱ ሆን ብሎ በመተው የሚደረግ ግድያ ነው፡፡ ይህ ፍርድ የተፈረደባቸው ቅርሶች በአካባቢያቸው ለእነርሱ ሕልውና አሥጊ የሆነ ሥራ ሲከናወን የሚያስጥላቸው የለም፤ የቆሻሻ መጣያ ሲሆኑ በዝምታ ይታለፋሉ፤ ሲፈርሱና ሲበላሹ በዝምታ ይታያሉ፤ ሲዘረፉና ሲወሰዱ የሚያስጥል አያገኙም፤ ጥበቃ አይደረግላቸውም፤ ሞያ በሌላቸው አካላት እንዲጠገኑ ይደረጋል፤ ታጥረውና ተከልለው እንዲቀመጡ ይደረጋል፤ በውስጡ ነዋሪዎች ሲቀመጡባቸውና ግንባታ ሲያከናውኑባቸው ተከታታይ አይኖርም፤ በጢስና እሳት እንዲበላሹ ይተዋሉ፡፡
በአንድ በኩል ያለፈው ነገር ሁሉ መነካት የለበትም የሚሉ የታሪክና ቅርስ ወግ አጥባቂዎች (ወግ አጥባቂነት አዎንታዊ ነው) አሉ፡፡ እንደ እነርሱ ከሆነ የአዲስ አበባ ነባር ነገሮች ሁሉ ተጠብቀውና ተከብረው መኖር አለባቸው፡፡ እነርሱ የከተማዋን፣ ብሎም የሀገሪቱን ጥንት የሚመሰክሩ ናቸውና፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በቦታው ላይ የሚሠራ ሌላ ነገር እስካለ ድረስ የጥንቱ መፍረስ አለበት፡፡ የጥንቱ ጥንት አገልግሏል፡፡ አሁን ዘመኑ የዛሬ ነው፡፡ ጥንቱ ለዛሬ ዕንቅፋት ከሆነ ያለው ዕድል መፍረስ ብቻ ነው ይላሉ፡፡
እነዚህ ሁለቱም ለእኔ ጽንፎች ናቸው፡፡ ሁሉም የጥንት ነገር እንዳለ ሊቀመጥ አይችልም፡፡ በሦስት ምክንያት፡፡ አንድ ሁሉም የጥንት ነገሮች እኩል የሆነ ታሪካዊ፣ ቅርሳዊና ባሕላዊ ዋጋ የላቸውም፤ ሁለተኛ ደግሞ ሁሉም የጥንት ነገሮች ይቀመጡ ካልን ለአዳዲስ ነገሮች ቦታ ላይገኝ ይችላል፤ በመጨረሻም ሁሉንም የጥንት ነገሮች ለማቆየት፣ ለመጠበቅና ለመከባከብ ዐቅም ያስፈልጋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ለአዳዲስና ለዘመናዊ ነገሮችና ሐሳቦች ሲባል ሁሉንም የጥንት ነገሮችን በግዴለሽነት ማፈራረስ ሦስት ጉዳቶች ያስከትላል፡፡ የሰው ልጅን የጥበብ፣ የባሕል፣ የሥልጣኔና የክሂሎት አሻራ ያጠፋል፤ አንድን ነገር ምንጊዜም እንደገና እንድንጀምረው በማድረግ ተያያዥና ተደጋጋፊ ነገርን ያሳጣል፤ በመጨረሻም የከተማዋን የቱሪዝም ገቢ ያመክናል፡፡ 
እነዚህን ሁለት ጽንፎች ለማስታረቅ የሁለቱንም አዎንታዊነት የያዘ አንድ ሌላ መንገድ ያስፈልጋል፡፡ እርሱም አዳዲስ ነገሮችን ከጥንታውያን፣ ዘመናዊነትን ከነባርነት፣ ታሪክን ከዕድገት፣ ቅርስን ከሥልጣኔ ጋር አስማምቶ፣ አደጋግፎና አመጋግቦ መምራት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ወጥነት ያለው፣ በየዘመናቱ የሚዳብር በሳል ሀገራዊ ፍልስፍና ያስፈልጋል፡፡
ይህንን መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ የሚከተሉት አካሄዶች ያስፈልጋሉ
  1. የከተማዋን ታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶች የመለያ መመዘኛ ማስቀመጥ
  2. በመመዘኛው መሠረት የከተማዋን ታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶች በዝርዝር መለየት
  3. እነዚህ የከተማዋ ቅርሶች በልዩ ልዩ መንገድ ለትውልድ የሚተላለፉበትን መሥፈርት ማውጣት
  • እንዳሉ ባሉበት ሁኔታ ለሌላ አገልግሎት ሳይውሉ ለትውልድ መተላለፍ ያለባቸው
  • መጠናቸው ተቀንሶ ናሙናቸው መተላለፍ ያለባቸው( ለምሳሌ አንድን መንደር ሙሉውን ቅርስ አድርጎ ማቆየት ከባድ ቢሆን እንኳን ያ መንደር ምን ይመስል እንደነበር የሚያሳይ አንድ ናሙና ቦታ ለይቶ ማቆየት ይቻላል)
  • በልዩ ልዩ የመቀረሻ መሣሪያዎች(ፎቶ፣ ሥዕል፣ ቪዲዮ፣ ወዘተ) ተመዝግበው መተላለፍ ያለባቸው(አንዳንድ ሠፈሮች የቀድሞ መልካቸውና አሠራራቸው በልዩ ልዩ መቀረሻ መንገዶች ቀርጸ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል)
  • ወደ ሙዝየም ገብተው መተላለፍ ያለባቸው
  • ቅርስነታቸውንና ይዞታቸውን በማይጎዳ መንገድ ለሌላ የማይጣረስ አገልግሎት ተላልፈው ግን ተጠብቀው መተላለፍ ያለባቸው(ጣይቱ ሆቴል እንደተደረገው)
  • ቦታቸውን ቀይረው በቅርስነት መጠበቅ ያለባቸው
  • ማናቸውም ከተማዊ እንቅስቃሴዎች ከእነዚህ የተመዘገቡ ቅርሶች ጋር ያላቸውን ተግባቦት በቅርብ መከታተል፣ ለክትትሉም እንዲያመች የሚመለከተው አካል ከማናቸውም ግንባታ በፊት አካባቢው ከቅርስ ነጻ መሆኑን ምስክርነት እንዲሰጥ ማድረግ
  • የከተማዋ መሪ ዕቅድ ሲዘጋጅም እነዚህን ታሪካዊ ቦታዎችና ቅርሶችን በሚገባ የለየና የእነርሱን የሕልውና መብት የጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ
  • በታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶች አካባቢ ይፋዊ መለያ መለጠፍ፤ ይህ ምልክት የተለየ ቀለም ወይም ዐርማ እንዲኖረው በማድረግ ማንኛውም ሰው እንዲለየው ማስቻል
  • የፌዴራል ቅርስ አዋጅ ቁጥር 209/92 ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች ምንም ዓይነት ሥልጣን ስለማይሰጥ ይህንን ማስተካከል
  • የታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶች አካባቢዎች የተዛማጅ ልማቶች ማዕከል (የሆቴል፣ የጥበበ ዕድ መሸጫ፣  የዐውደ ርእይ ማሳያ፣ የባሕላዊ ገበያዎች) መጠቀም
  • በተማሪዎች፣ በአካባቢው ነዋሪዎችና በቱሪስቶች እንዲጎበኙ መርሐ ግብሮችን ማመቻቸት

  • እነዚህንና የመሰሉትን ተግባራት በጊዜ ማከናወን ካልቻልን አዲስ አበባ ‹ትናንት የሌላት ከተማ› ትሆናለች፡፡ ያውም በታሪክ አጋጣሚ ሳይሆን ሳያስቡ የሚሠሩ አመራሮችና ነዋሪዎች ስላሏት ብቻ፡፡ ከተማ እንደ ፈጣን ምግብ(fast food) ለዕለት ሆድ መሙያ የምትሠራ አይደለችም፡፡ እንደ ገጠር ጠላ ለነገም ጭምር የምትጠነሰስ ናት፡፡ ከተማዋን ለሰዎች መኖሪያነት ምቹና ተመራጭ ለማድረግ መንገድ፣ ሆቴል፣ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ፣ ባቡር፣ ሱፐር ማርኬት፣ የገበያ ማዕከል፣ የግል ኮሌጅ፣ ዓለም ዐቀፍ ተቋማትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ብቻቸውን በቂ አይደሉም፡፡ ጥንታዊ፣ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ፣ መንፈሳዊና ሞራላዊ እሴቶች፣ ቅርሶችና ቦታዎችም ያስፈልጓታል፡፡ እነዚህ ራሳቸው ነገ ታሪክና ቅርስ ስለሚሆኑ፡፡ ከተማ እንደ ላም ዱካ የሚተው እንጂ እንደ አዞ በጅራታቸው ዱካ የሚያጠፉ አመራሮች አያስፈልጓትም፡፡

     © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

    በተለምዶ ሲኤም ሲ በሚባለው ሰፈር፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ሥር ካለው ክልል ወደ የካ ከተማ ክልል ለባቡር የተሠራውን መንገድ እንደ ጦጣ እየዘለልኩ በማቋረጥ ላይ ነበርኩ፡፡ ከእኔ ፊት ፊት ሁለት ሽማግሌዎች በምርኩዛቸው እየተረዱ እንደ ሽሪ ሚሪ የተከረተፈውን የባቡር መንገድ በጥንቃቄ ይሻገራሉ፡፡ ሽሪ ሚሪውን ተሻግረው የተነጠፈው ሐዲድ ላይ ሲደርሱ ልባቸው መለስ አለላቸው መሰል የአኩስም ጋቢ የመሰለ ፀጉር የለበሱት አንደኛው ሽማግሌ ‹‹እንዴው በቃ ይህንን ባቡር የሐበሻ መድኃኒት አደረጉት ማለት ነው?›› ብለው ጓደኛቸውን ጠየቁ፡፡

    ‹‹እንዴት እንዴት በል?›› አሉ ሪዛቸው እንደ ዝቋላ ጥድ ወደታች የወረደላቸው ሌላው አረጋዊ፣ በከዘራቸው የባቡሩን ሐዲድ ነካ ነካ እያደረጉ፡፡

    ‹‹ቆይ ይኼ ባቡር ምንድን ነው የሚመስለው? ባቡሩ ሲያልቅስ ይኼ መንደራችን ምን ይመስላል? መሳፈሪያው እንዴት ነው?በዚህ በመገናኛስ በዋሻ ያልፋል የሚባለው እንዴት እንዴት ሆኖ ነው? እንዴት የሁላችንን ሕይወት ዋጋ ያስከፈለ፤ ስንት ቤቶችን ያስነሣ፣ ስንት ሠራተኞችን ያስረፈደ፣ ስንት ሚሊዮን ብር የፈጀ፣ ለሀገራችንም እንግዳ የሆነ ነገር ሲሠራ፣ እንዴት አንድ ቦታ እንኳን ሥዕሉ አይለጠፍም? ቆይ ይህንን ሁሉ መሥዋዕትነት ከፍለን፣ ጠዋት አርፍደን፣ ማታ ተሠልፈን፣ የሃያ ሁለትና የዑራኤል ሆቴሎች ቀዝቅዘው፣ እኛም መሻገሪያ አጥተን በስተርጅና እንደ ጉሬዛ እየዘለልን የሚሠራው ባቡር ምንድን ነው የሚመስለው? ለመሆኑ ታውቃለህ?››

    ‹‹ይኼው የሀብታሙ ሁሉ ሕንጻ ሲሠራ ከፊት ለፊቱ ሥዕሉ በትልቁ ይሰቀል የለም እንዴ? እኛም ዐቅምና ዕድል ኖሮን ባንሠራም ቆመን ሥዕሉን አይተን እናደንቃለን፡፡ ሕንጻው ሲያልቅ ሠፈሩ ምን እንደሚመስልም እንገምታለን፤ እንደ ሽምግልናችንም ‹አልቆ ለማየት ያብቃን› ብለን እንመርቃለን፡፡ የከተማው ባቡርማ ለምርቃትም ለጸሎትም አስቸጋሪ ሆነኮ፡፡ እኛ የከተማ ባቡር አይተን አናውቅ፣ ምናለ በየሠፈሩ ሥዕሉን ቢለጥፉልን፤ ብናደንቅ፣ ሠሪዎችንም ብንመርቅ፣ እንዲያስፈጽመውም ብንጸልይ፡፡››

    ሽማግሌዎቹ የባቡሩን መንገድ አቋርጠው ወደ ሲ ኤም ሲ ሚካኤል አቅጣጫ ተጓዙ፡፡ መንገዴን ትቼ ወጋቸውን ሽቼ ተከተልኳቸው፡፡
    ‹‹አይህ ወዳጄ እነዚህ የሃይማኖት ሰዎች ‹መንግሥተ ሰማያት ይህንን ትመስላለች› የሚሉትኮ ያለምክንያት እንዳይመስልህ፡፡ የሚደርስብህን ሁሉ መከራ የምትቋቋመው የምታገኘውን አስረግጠህ ካወቅከው ብቻ ነው ብለው ነው፡፡ መንግሥተ ሰማያትን ይስሉብህና ‹ለዚህች ልዩ ሀገር ስትል ዋጋ ክፈል፣ መከራውን በጸጋ ተቀበል፤ እስከ ጊዜው ነው ቻለው› ይሉሃል፡፡ ምነው እነዚህ ባቡር የሚሠሩ ሰዎች ከእነርሱ ቢማሩ፡፡ ለመሆኑ ይኼ ሁሉ ጉድጓድ ተቆፍሮ፣ መንገድ ተከልክሎ፣ ሠፈር ፈርሶ፣ ሐውልት ተነቅሎ፣ ማቋረጫ ጠፍቶ፣ መንገድ ተዘጋግቶ፣ ንግዱ ተቀዛቅዞ የምናገኘው ነገር ምንድን ነው? ምን ይመስላል? አሁን እኛ መሥዋዕትነት እየተቀበልን ያለነው ምን ለማግኘት ነው? ማንም አያውቅም፡፡ ምነው ግን ይህንን ባቡር የሐበሻ መድኃኒት አደረጉትሳ››

    ‹‹እኔም ሁልጊዜ የሚገርመኝ እርሱ ነው፡፡ መገናኛ ሄድኩ፣ ዑራኤል ሄድኩ፣ መስቀል አደባባይ ሄድኩ፣ ሜክሲኮ ሄድኩ፣ በቀደምም መርካቶ ሄድኩ፤ ሕዝቡ የመሰለውን ብቻ ነው የሚያወራው፡፡ አንዱ ኤሌክትሪኩ ከላይ ነው ይላል፣ ሌላው መሬት ውስጥ ተቀብሯል ይላል፤ አንዱ ማውረጃው ከላይ ነው ይላል፣ ሌላው መሬት ውስጥ ነው ይላል፤ አንዱ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት አይመለስም፣ ቦታ የለውም ይላል፤ ሌላው ይመለሳል፣ ግን ከድሮው ሬዲዮ ጣቢያ አጠገብ ይተከላል ይላል፡፡ ይህንን ሁሉ ምን አመጣው? አንተ እንዳልከው የሐበሻ መድኃኒት ይመስል ምሥጢር ስላደረጉት ነው፡፡ እንጂማ ሲሆን እኛ ሽግሌዎቹም እንድናይ ከፍ ከፍ አድርገው፣ ካልሆነም ባቅም ባቅሙ ሥዕሉን መለጠፍ ነበረባቸው፡፡››

    አሁን ሽማግሌዎቹ ወደ ሲኤም ሲ ሚካኤል እየገቡ ነው፡፡ ባርኔጣቸውን ሊያወልቁና እጅ ሊነሡ በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡

    ‹‹በቀደም አያ ተሰማ ምን አለኝ መሰለህ››

    ‹‹ምን አለህ ደግሞ፤ መቼም እርሱ ወግ አያልቅበትም፡፡››

    ‹‹የካና ቦሌ አሁን ነው ትክክለኛ ድንበር ያገኙት፡፡ ይኼው የባቡሩ መንገድ የማያገናኝ ድንበር አበጅቶላቸዋል፡፡ ካሁን በኋላ የምንገናኘው በሞባይል ብቻ ነው፡፡ ከመንገድ ማዶና ማዶ ሆነህ በስልክ እያወራህ በእጅ ሰላምታ መለዋወጥ ብቻ ነው›› አለኝ፡፡

    ‹‹እንዴ መሻገሪያ አያደርጉልንም እንዴ? እኛ ወዲያ ተሻግረን ሚካኤልን ላንሳለም፣ ሙስሊሞችም ወዲህ መጥተው ላይሰግዱ ነው ማለት ነው? ይህማ ደግ አይደለም››

    ‹‹ቢለጥፉትኮ ይኼ ጥያቄ ይመለስልን ነበር፡፡ ግን የሐበሻ መድኃኒት ነው፡፡ ያውም የወፍ መድኃኒት፡፡ ፌርማታው የት ጋ ነው? መንገዱንስ እንዴት አቋርጠን ነው የምንሳፈረው? ሰው ዘሎ ቢገባስ? እንዴው ተጨነቁ ብሎን የሚመስለንን ስንገምት እንውላለን፡፡ ቤት ስትሠራ እንኳን መሐንዲሱ የቤቱን መልክ በወረቀት ስሎ ይሰጥሃል፤ አንተም አይተህ ደስ ሲልህ ይህንንስ ወገቤን አሥሬ እሠራዋለሁ ትላለህ፤ ሰው ዛሬ ወደፊት የሚቀበርበትን ቦታ እንኳን ለማወቅ ፈልጎ በቁሙ መቃብር ያሠራል፤ ልብስ ሰፊ እንኳን ዋናው ልብስ እስኪደርስ በቾክ ጨርቁ ላይ ስሎየልብሱን መልክ ያሳይሃል፤ ደጋሽም ድግሱ እስኪደርስ ቅምሻ ብሎ ይጠራሃል፤ የሞሰቡን እንጀራም በእንጎቻው ትገምተዋለህ፤ ባቡሩን ግን እንዴት እንገምተው? ለመሆኑ ምን መልክ ይኖረዋል? እንዴት ነው የምንሳፈረው? ወጭውስ በኛ ዐቅም ይቻላል? እንደ ሰርዲን ታጭቀን ነው ወይስ ወንበር አለው? ለመሆኑ እንደ አውቶቡስ ቁጥር አለው? ሲሆን አንድ ቦታ ላይ ሠርተው እንደ ኤግዚቢሽን ቢያሳዩን፤ ‹አሃ ለካ እንደዚህ ነው› ብንል አእምሯችን ለምዶት ቢቆይ መልካም ነበር፡፡ ካልሆነም ሥዕሉን በየሠፈራችን ቢያኖሩት››

    ‹‹በቀደም ታናሿ ልጄ የምወልደውኮ ሴት ልጅ ነው አለችኝ››

    ‹‹ያቺ ነፍሰ ጡሯ››

    ‹‹አዎ፤ በምን ዐወቅሽው፣ የዛሬ ልጆች መጠንቆል ጀመራችሁ ወይ አልኳት››

    ‹‹ሐኪሙ አሳየኝ – አለችኝ››

    ‹‹ሆድሽን ከፍቶ አሳየሽ – ብዬ ቀለድኩባት››

    ‹‹አይደለም በመሣሪያ ማየት ይቻላልኮ – አለችኝ፡፡ ዛሬ ያልተወለደን ልጅ ወንድ ይሁን ሴት ማወቅ እየተቻለ እንዴት ነው እንዲህ ሠፈሩን ሁሉ አቋርጦ የሚሄደውን ባቡር መልክ ቀድሞ ማየት ያልተቻለው፡፡ ሲቆፍሩ፣ ሲገነቡ፣ ሲሚንቶ ሲሞሉ፣ አቧራ ሲያቦኑ ብቻ ነው የምናያቸው፤ የሐበሻ መድኃኒት አደረጉት አልክ፣ እውነትክን ነው፡፡››

    አረጋውያኑ ወደ ሚካኤል ግቢ ዘልቀው ተሳለሙና አጥሩ ጥግ ዛፎቹ ሥር ዐረፍ አሉ፡፡

    ‹‹እኔ ግን ምን እንደሚመስለኝ ታውቃለህ?›› አሉ ሽበት ያጀባቸው ሽማግሌ

    ‹‹ምን ይመስልሃል?›› አሏቸው ሪዛሙ አረጋዊ

    ‹‹እኛ ብቻ ሳንሆን እነርሱም አሟልተው ያወቁት አይመስለኝም››

    ‹‹መጠርጠር እርሱን ነው›› አሉና መዳፋቸውን በመዳፋቸው መቱት፡፡

    © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

    ኦሎምፒያ አካባቢ የሚገኘውን የቀለም ባለሞያውን የጌታሁን ሄራሞን ቢሮ በጎበኘሁ ቁጥር በሁለት ነገሮች እደሰታለሁ፡፡ በአንድ በኩል ስለ ቀለማት በሚሰጠው ሕይወት ያለው ትንታኔ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ባከማቻቸው የኢትዮጵያውያን ሰዓሊዎች ሥራዎች፡፡ የእርሱ ወንበርና ጠረጲዛው የቢሮውን አንድ ሦስተኛ ብቻ ነው የያዘው፡፡ ቀሪውን የቢሮውን ክፍል ዋናው ባለ አክስዮን ስብስብ ሥዕሎቹ ይዘውታል፡፡ መቼም ሰው ሥራውን ለምንዳዕ ብቻ ሳይሆን በፍቅርም ሲሠራው ሕይወትን በሌሎች ላይ የመዝራት ዐቅም ይኖረዋል፡፡

    እዚያ ከተሰበሰቡት ሥዕሎች ውስጥ በመጀመሪያው ክፍል ከጠረጲዛው ከፍ ብሎ ግድግዳው ላይ የተሰቀለው ካንቫስ የፈጠራ ሃሳብ ያስደንቀኛል፡፡ በመስተዋቱ ውስጥ ሁለት ጥቋቁር ካልሲዎች በጫማ አቀማመጥ ቅርጽ ተለጥፈዋል፡፡ አንደኛው ምንም ያልነካው ‹አዲስ› ካልሲ ነው፡፡ ሁለተኛው ግን ተረከዙ ላይ ተቀድዷል፡፡

    የጥበቡ ርእስ ‹ጥንድ የመሆን ፈተና› ይላል፡፡ ምን ማለት ነው? ደጋግሜ አየሁት፡፡ ‹‹ወፍ ስትበር የሚያሳይ ሥዕል ሳሉ›› ተብለን በሥዕል ትምህርት ቀልደን ላደግን ሰዎች የሥዕልን ጥበብ ዘልቆ ምሥጢሩን መረዳት እንደ ዋድላ ቅኔ ከባድ ምርምርን ይጠይቃል፡፡ ለረዥም ሰዓት ነው አፍጥጬ ያየሁት፡፡ እንዲያውም በመሐሉ የሥዕሉን ምሥጢር ከመመርመር ወጥቼ እኛ ቤት የነበረች አንዲት የቤት ሠራተኛችን ትዝ አለችኝ፡፡ የምገዛቸው ካልሲዎቼ ሁሉ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከትዳር ተፋትተው ላጤ ሆነው ነበር የማገኛቸው፡፡ ‹‹ምንድን ነው?›› ስላት ‹አይጦቹ ናቸው›› ትለኛለች፡፡

    ግርም ይለኝ የነበረው የነዚህ የስምንተኛው ሺ አይጦች ጠባይ ነበር፡፡ የሀብታም ትምህርት ቤት እንደገባ ልጅ ‹ለአንድ ቀን አንድ ዓይነት› የሚል መርሕ ሳይኖራቸው አይቀርም፡፡ ቢሞቱ ሁለቱንም ካልሲዎች አይበሏቸውም፡፡ ከሁለቱ አንዱን ብቻ ነው የሚመገቡት፡፡ አንዳንዱን ካልሲ ወስደው ለሆቴላቸው በያይነቱ ያዘጋጁበትም እንደሁ እንጃ፡፡ አንዱ ጓደኛዬ ደግሞ የለም ልጂቱ ባለ አንድ እግር ወዳጅ ሳይኖራት አይቀርም ይለኛል፡፡ ከሁለቱ አንዱ ነው፤ ወይም ሌላም ሊሆን ይችላል፡፡

    አሁን እዚህ ደግሞ ካልሲ ጥበብ ሆኖ በፍሬም ተሰቅሎ ሳየው ገረመኝ፡፡

    ‹‹ጥንድ የመሆን ፈተና››

    በኋላ ጌታሁን አንድም እያለ ተረጎመልኝ፡፡ ‹‹እስኪ እየው፤ ይኼኛው ካልሲ ደህነኛ ነው፡፡ እንዲያውም ቅድም እንዳልከው አዲስ ይመስላል፡፡ ተጣማሪው ግን ተቀድዷል፡፡ ካልሲ ሊደረግ የሚችለው በጥንድ ብቻ ነው፡፡ በዚህ በተቀደደው ምክንያት ያልተቀደደው ካልሲም ከጥቅም ውጭ ሆኗል፡፡ ቤቴ ውስጥ በተደጋጋሚ ሲያጋጥመኝ ጊዜ ይህንን ሃሳብ አሰብኩት፡፡ የዚህ የደህነኛው ካልሲ ጥፋቱ ምንድነ ነው?አልኩ፡፡ ሳስበው ጥፋቱ አንድ ብቻ ነው፡፡ የቀዳዳው ካልሲ ተጣማሪ መሆኑ፡፡ በቃ ተጣማሪው ስለ ተቀደደ እርሱም ይጣላል፤ ያለበለዚያም ለልጆች ኳስ መሥሪያነት ይውላል፡፡ ጥንድ የመሆን ፈተና ይኼ አይደለም ታድያ?›› አለኝ፡፡

    እርሱ ይሄንን ሲነግረኝ ባለትዳሮች፣ ጓደኛሞች፣ የንግድ ሸሪኮች፣ የጥበብ ወዳጆች፣ የሥራ አጋሮች፤ እንዲቀያየር ሆኖ እንደተጫነ የኮምፒውተር ስክሪን ሴቨር በዓይነ ኅሊናዬ ቦግ እልም እያሉ አለፉ፡፡ ምርጥ ባል፤ የባሎች ሁሉ መለኪያ ሊሆን የሚችል፤ አባትም ባልም ተብሎ የሚነገርለት ተጣማሪው ተበላሽታ ሲበጠበጥ፣ ሲታመስ፣ ሲመሳቀል፣ ዐቅሙ ሲደክም፣ ሥራው ሲበላሽ፣ አእምሮው ሲናወጥ፣ ይኖራል፡፡ አይቆርጠው አካል፣ አይተወው ሕመም ሆኖበት፤ አይናገር ምሥጢር፣ ዝም አይል ብሶት ሆኖበት፤ ከዕረፍት እንደተመለሰ እሥረኛ ቤቱ እያስጠላው፣ ጥንድ መሆን ፈተና ላይ ጥሎት ይኖራል፡፡

    ምን የመሰለች ሚስት፣ ዐፄ ቴዎድሮስ ‹ሚስት ናት ገረድ› ያሏት ዓይነት፣ ልጆቿን አፍቃሪ፣ ባሏን አክባሪ፣ ትዳርዋን አሥማሪ የሆነች ሚስት፣ ባሏ ተበላሽቶባት፣ ይኼው

    ትዳር ምን ዕዳ ነው፣ ጎጆ ምን ዕዳ ነው

    ከገነት ተባርሮ ገሐነም መኖር ነው

    እያለች ታንጎራጉራለች፡፡ ሥራዋ፣ ሀብቷ፣ መልኳ፣ ዕውቀቷ፣ ጠባይዋ፣ ሥልጣኗ፣ ክብሯ፣ ዝናዋ ከሰው በላይ ሆኖ የትዳር አጋሯ ግን የተቀደደ ጣራ፣ የፈረሰ ግድግዳ፣ የማይዘጋ በር፣ የሚዋጋ ጫማ፣ የሚኮሰኩስ ልብስ፣ የሚያቃጥል ወጥ፣ የሚኮመጥጥ እንጀራ ሆኖባታል፡፡ አትተወው ትዳር፣ አትኖረው ሲኦል ሆኖባት፤ ስንት ውስብስብ ችግር  በቢሮዋ የፈታች ሊቅ፣ የአጋርን ችግር መፍታት ቸግሯት ተጣማሪ ካልሲ ሆናለች፡፡

    በአምስት ጣት የሚበላ ሰው መቼም አብሮ መሥራትን አይጠላም፡፡ ‹ድር ቢያብር አንበሳ ያሥር›፣ ‹ለአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ›፣‹ለአንድ ጉርሻ ሠላሳ ሁለት ጥርስ› እያለ የሚተርት መቼም አብሮ ተባብሮ መሥራትን አይጠላም፡፡ ማበር የሚያስጠላው፣ ሽርክና የሚያስመርረው፤ ኅብረት፣ አንድነት፣ ማኅበር፣ ቡድን፣ ኮሚቴ፣ የሚያቅለሸልሸው እንደ ካልሲው ከተጣማጆቹ የሚቀዳደድ ካለ ነው፡፡ አብሮ ለመሥራት፣ አብሮ ለማደግ፣ አብሮ ለመልፋት፣ አብሮ ለመትጋት ወስነው አጋና ከመቱ በኋላ አንዱ ወገን እንደ ካልሲው የተቀደደ ከሆነ፣ የቀዳዳው ዕድል ፈንታ በደህናው መወሰን ሲኖርበት፣ የደህናው ዕድል በቀዳዳው መወሰን ከጀመረ፣ ያኔ ነው አብሮ መሥራት እሴት ከመሆን ይልቅ ዕዳ የሚሆነው፡፡

    ይህንን ካልሲ ሳይ መኪና ታወሰኝ፡፡ አራት እግር ያለው መኪና አንዱ ጎማ ሲተነፍስ የሚቆመው ለምንድን ነው? ጥንድ የመሆን ፈተና ገጥሞት አይደል፡፡ ያልተነፈሱት ሦስት ጎማዎች በተነፈሰው አንድ ጎማ ምክንያት መቆማቸው የግድ ነው፡፡ ስንት የተጣመሩ ፓርቲዎች ከመካከላቸው እንደ ካልሲው የተቀደደ፣ እንደ ጎማው የተነፈሰ ሲያጋጥማቸው አይደል ቆመው ወይም ፈርሰው የቀሩት፡፡

    አንዳንዴ ምንም ያህል ብንፈልገው ብቻችንን ልንሆነው የማንችለው ነገር አለ፡፡ ብቻችንን ብንሠራው እንኳን ከማናውቅ አካል ጋር የምንጣመርበት ጉዳይም አለ፡፡ ‹አይ የታክሲ ሾፌር፣ አይ አስተናጋጅ፣ አይ ነጋዴ፣ አይ ቀበሌ፣ አይ ተቃዋሚ፣ አይ ደጋፊ፣ አይ ጋዜጠኛ፣ አይ ፖሊስ› እየተባልን በምናውቀውም በማናውቀውም፤ ባደረግነውም፣ ባላደረግነውም የምንወቀሰውኮ ‹ጥንድ በመሆን ፈተና› ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ ብቻችንን መልካም ብንሠራ፣ ንጹሕና ጻድቅ ብንሆን እንኳን፣ የሆነ ቦታ በሚገኙ ሳናውቅና ሳንፈቅድ በተጣመርናቸው የሞያ አጋሮቻችን ጥፋት መወቀሳችንና ሕዝባዊ አመኔታ ማጣታችን አይቀሬ ነው፡፡

    ጥቂት የዚያ ብሔረሰብ ሰዎች፣ የተወሰኑ የዚያ ቡድን አባላት፣ እፍኝ የማይሞሉ የዚያ ሀገር ዜጎች፣ በጣት የሚቆጠሩ የዚያ ሃይማኖት አማኞች፣ ውክልና የሌላቸው የዚያ ማኅበር አባላት፣ ለራሳቸው ብቻ ሲሉ ወጥ በረገጡ የዚያ ሞያ ባለቤቶች፣ ከሁለት ወንበር በማይበልጡ የዚያ መሥሪያ ቤት ባልደረቦች ጥፋት ‹እንደ አህያ ጆሮ እንደ ጦር ጉሮሮ‹ ሁሉንም አንድ አድርጎ የመኮነን አባዜ የመጣው ጥንድ ከመሆን ፈተና ነው፡፡ በተቀዳደዱ ካልሲዎች ምክንያት የሚያገለግሉትም አብረው እንደሚጣሉት፡፡

    ምርጥ የባለሞያ ወጥ፣ በስሕተት በበዛ ጨው ምክንያት ተመጋቢ የሚያጣው ጥንድ የመሆን ፈተና ገጥሞት ነው፡፡ ‹በጨው ደንደስ በርበሬ እንደሚወደሰው› ሁሉ በጨው ጥፋትም በርበሬ ከጥቅም ውጭ ሊሆን ይችላል፡፡

    ዘመናዊ ኑሮ የጉርብትና ሥርዓት ነው፡፡ ዐውቀነውም ይሁን ሳናውቀው ከብዙ ነገሮች ጋር ተጣምረንና ኅብረት መሥርተን ነው የምንኖረው፡፡ ሰው ብቻውን መጥፎ፣ ብቻውንም ጥሩ መሆን አይችልም፡፡ ብቻውን ንጹሕ፣ ብቻውንም ቆሻሻ ለመሆን አይችልም፡፡ እኛ ቤት የምትመጣው ዝንብ ከየት መነሣት እንዳለባት ልንወስንላት አንችልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በአንድ መንደር መብራት፣ ውኃና መንገድን ለማስገባት፤ ጸጥታ፣ ንጽሕናና ውበትን ለመጠበቅ መንደሩ ሁሉ ይስማማና ጥቂት ጎረቤቶች ግን እምቢ ይላሉ፡፡ አልከፍልም፣ አልሠራም፣ አልሰበሰብም፣ አልተባበርም፣ አያገባኝም ይላሉ፡፡ የስንት ጎበዞችን ዕቅድ የጥቂት ቀዳዳ ካልሲዎች ችግር ከጥቅም ውጭ ያደርገዋል፡፡

    ጥንድነት የማይቀር የኑሮ ሥርዓት ከሆነ ከባዱ ነገር ጥንድ የመሆንን ፈተና እንዴት እንለፈው ነው፡፡

    ‹‹ትንሽ በር በሬ ብደቁሰው፣ ብደቁሰው

    ሀገሩን ሁሉ አስነጠሰው፣ አስነጠሰው››

    የተባለው ይህንን ይነግረናል፡፡ ለማስነጠስ በርበሬ መደቆስ አያስፈልገንም፡፡ የሌላው ጎረቤት በርበሬ በቂ ነው፡፡ በቢሯችን ውስጥ መልካም ሽቱ የተቀባ ሰው ካለ ለሁላችን መዓዛው እንደሚተርፈው ሁሉ፣ የጫማውን ጠረን ማስወገድ ያልቻለውም የቢሯችን ባልደረባም በተቃራኒው እንዲያ ነው፡፡

    ጥንድነት የሚያመጣውን ፈተና ለመወጣት አንድም የዳበረ የኑሮ ጥበብ ያሻል፣ አንድም የታሰበበትና ተገቢ የሆነ የጥንድነት ልማድና ሕግ ያስፈልጋል፤ አንድም ደግሞ ከፈተናው የመውጫ ውጤታማ የአደጋ ጊዜ በር ሊሠራ ይገባል፡፡ ጥንድነት የሚያመጣውን ፈተና ለመከላከል፣ ካልሆነም ለመፍታት የሚያስችል ከማኅበረሰቡ ጋር የተዋሐደ የኑሮ ጥበብ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን የኑሮ ጥበብ ለመገንባት ደግሞ የሃይማኖት ትምህርቶች፣ ሥነ ቃል፣ ሚዲያና ዘመናዊ የኑሮ ዘዴ ትምህርቶች ታላቅ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ፡፡

    አብሮነት የሚያስከትላቸውን ፈተናዎች ማራቂያ፣ ሲመጡም የከፋ ጉዳት ሳያደርሱና እንደ ቀዳዳው ካልሲ ለመጣል ሳያበቁ፣ ማስወገጃ የዳበረ ሀገራዊ ልማድና ሕግም ወሳኘው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፈተናውን አምቀን ብቻ እንድንይዘው፣ ያለ መውጫ እንድናስበው፣ የዐርባ ቀን ዕድል አድርገን እንድንቆጥረው፣ መፍትሔው አብሮ መውደቅ ብቻ አድርገን እንድናየው የሚያደርግ ሀገራዊ ልማድና ሕግ ካለ ጥንድነት እሴት ሳይሆን ዕዳ ብቻ ይሆናል፡፡

    ፍየል ቀንዷ ለምን ወደ ኋላ ዞረ? ሲባል፤ ስትገባ መውጫ መውጫውን ለማየት ነው አሉ፡፡ የምንገባበት ነገር ሁሉ አንዳች የመውጫ የአደጋ ጊዜ በር ሊኖረው ይገባል፡፡ የአደጋ ጊዜ በር በማናቸውም ጊዜ፣ በፈለገው ሰው፣ ለማናቸውም ዓይነት ምክንያት አይከፈትም፡፡ የሚከፈትበት ምክንያት፣ ጊዜ፣የመክፈት ሥልጣን ያለው አካል አለ፡፡ በጥንድነት ፈተናም እንዲሁ ነው፡፡ እንደ መግቢያው በር ሁሉ የመውጫ የአደጋ ጊዜም በር ያስፈልጋል፡፡ መግቢያ ብቻ ያለው ባለ አንድ በር ቤት ለጥንድነት አይመከርም፡፡ ዐውቀን የዘጋነው፤ በአደጋ ጊዜ ግን ልንከፍተው የምንችለው፣ የመጨረሻው አማራጫችን እርሱ ሲሆን ዘለን የምንወጣበት የአደጋ ጊዜ በር ያስፈልጋል፡፡ ‹እኔ በዚህ አልስማማም፣ የእኔ ሃሳብ የተለየ ነው፣ እኔ በዚህ መኪና ተሳፍሬ እስክገለበጥ ድረስ አልጓዝም› ብለን ልንናገርበት የምንችለው በር፡፡ ጥንድነት ዕድልና መብት እንጂ ዕዳና ግዴታ እንዳይሆን፡፡

    ከአዲስ አበባ ወደ ፍራንክፈርት፣ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ

    አንድ ወዳጅ አለኝ፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያብሰከስከው፡፡ ሯጮቻችን ሲያሸንፉ፣ ተጨዋቾቻችን ድል ሲያደርጉ፣ ስለ ኢትዮጵያ መልካም ነገር ሲሰማና ሲነገር፣ በሀገሩ ላይ ልማትና ዕድገት ሲታይ፣ አንዳች የሆነ ሀገራዊ ለውጥ ሲታይ፣ ይፈነድቃል፤ መልክዐ ገጹ ይፈካል፤ ደስታው ከልክ አልፎ ጣራ ይነካል፡፡ የሚያሳዝን፣ አንገት የሚያስደፋ፣ የሀገርን ስም የሚሰብር፣ ገጽዋን የሚያበላሽ ነገር ሲሰማና ሲያይ ደግሞ ከሥራ እንደተባረረ ሠራተኛ አንገቱን ይደፋል፤ የእናቱን መርዶ እንደ ሰማ ልጅ ዓይኑ ዕንባ ይሞላል፤ ከጨለማ እሥር ቤት እንደ ገባ እሥረኛ ፊቱ ከል ይለብሳል፤ ሲብሰከሰክ ሲብከነከን ውሎ ያድራል፡፡
    አንድ ቀን ‹‹ለአንተ ግን ሀገር ማለት ምንድን ናት? ወይስ ያንተ ሀገር የተለየች ናት? ምን እንደዚህ ያብከነክንሃል?›› አልኩት፡፡

    ‹‹ታውቃለህ›› አለኝ ፊቱን በቀኝ መዳፉ እየሞዠለጠ፡፡ የጎፈረ ፀጉሩን ደግሞ በግራ ጣቶቹ ይልጋቸዋል፡፡ አጭርና ድንቡሼ ነው፡፡ ወግ ሲጀምር ‹ታውቃለህ› ማለት ይቀናዋል፡፡

    ‹‹ታውቃለህ፤ ሀገር ማለት ‹ሕመሜ› ማለት ናት›› አለኝ፡፡ ከንፈርና አፍንጫዬን አገናኚቼ በጆሮዬ በኩል ወሬውን ዋጥኩና ወደ ኋላዬ ለጠጥ አልኩ፡፡ ሰምቼው የማላውቀው ትርጓሜ ነው፡፡ ‹‹ሀገር ማለት ሕመሜ ነው››፡፡ ይህንን ሳሰላስል ‹‹ሕመም ያልኩህ እንዳይመስልህ፣ ‹ሕመሜ› ነው ያልኩህ›› አለኝ፡፡

    ‹‹ሕመምና ሕመሜ፣ ምን ልዩነት አላቸው››

    ‹‹ዘፋኞችና አንጎራጓሪዎች በጣም የሚወዱትን ሰው ‹ሕመሜ› እያሉ ሲዘፍኑለት ሰምተህ አታውቅም››

    ‹‹ዐውቃለሁ፡፡ ታድያ ሀገርና ያ ምን ና ምን ናቸው››

    ‹‹የጆሮ ጉትቻ ያንገት ሐብል ናቸው – አልልህም መቼም›› አለኝ፡፡

    ‹‹ሕመሜ እያሉ የሚዘፍኑትኮ ስለሚወዱት ነገር ነው፡፡ እያለቀሱ አይምሰልህ፤ ሙሾ እያወረዱም አይደለም፤ የኀዘን እንጉርጉሮ እያዘነቡም አይደለም፡፡ ደስ ብሏቸው እየዘፈኑ ነው፡፡ እስክስታ እየወረዱ የሚዘፍኑት ግን ‹ሕመሜ› እያሉ ነው፡፡ የሚወዱትን፣ ሊያገኙት የሚፈልጉትን፣ እንዲያጡት የማይሹትን፣ መልካሙን ነገር ሁሉ የሚመኙለትን፤ ልቤ፣ አንጀቴ፣ ኩላሊቴ፣ ዓይኔ፣ ሆዴ፣ ነፍሴ የሚሉትን፤ ሞትም አይለየንም፣ ካንተ ውጭ ሌላ አልሻም፣ ሌላው ሁሉ ሰው አይመስለኝም፣ የሚሉለትን ፍቅረኛቸውን ‹ሕመሜ› እያሉ ይዘፍኑለታል፡፡

    ‹‹ አየህ ይህ ፍቅራቸው ሕመም ያለው ፍቅር ነው፡፡ ፍቅር ብቻ አይደለም፡፡ ሰናፍጭ ነው ያድናል፣ ግን ይሰነፍጣል፤ ሚጥሚጣ ነው ደስ ይላል፣ ግን ያቃጥላል፤ መርፌ ነው ይፈውሳል፣ ግን ያማል፤ ፈረስ ነው ይጋልባል፣ ግን ይገለብጣል፤ የሱፍ አበባ ነው ይመስጣል፣ ግን በእሾህ ተከብቧል፡፡ ውስጡ ደስ የሚል ሕመም አለበት፡፡ ደስታ ነው ብለህ እፎይ እንዳትል ሕመሙ እንደ ፍልስጣ ጎን ጎንህን ይወጋሃል፤ ሕመም ነው ብለህ እንዳትተወው ደስታው እንደ ወይን ጠጅ ‹እስኩ ድግሙ ድግሙ› ያሰኝሃል፡፡ ለዚህ ነው ‹ሕመሜ› እያልክ የምትዘፍንለት፡፡ የሚዘፈንለት ሕመም አይተህ ታውቃለህ? ሕመምን ይታከሙታል እንጂ ይዘፍኑለታል እንዴ? ሕመምን ያስታግሡታል እንጂ ያዜሙለታል እንዴ? እንዲያ ነው የምልህ፡፡

    ‹‹እና ሀገር እንዴት ነው ‹ሕመሜ› የምትሆነው?›› አልኩት ፍልስፍናው ደስ ብሎኝ፡፡ በጎድጓዳ መንገድ እንደሚሄድ ገልባጭ መኪና ወደ ግራና ወደ ቀኝ ወዝወዝ ብዬ ተስተካከልኩ፡፡

    ‹‹ሀገርማ ደንበኛዋ ‹ሕመሜ› ናት፡፡ ሀገር ብለህ ስታስብ ጤናና ሕመም ነው የሚሰማህ፡፡ የምትኮራበት፣ ምነው በዚያ ዘመን በኖርኩ ብለህ የምትመኝበት፣ ስታየውና ስትሰማው ደምህ የሚሞቅበት፣ ስታስበውና ስትናገረው ኩራትህ የሚጨምርበት ነገር አላት ሀገር፡፡ ምን እንደሆነ የማታውቀው እንዲሁ ፍቅር የምታስይዝህ ነገር አላት ሀገር፡፡ ታስጨፍርሃለች፣ ታስቦርቅሃለች፣ ታስዘልልሃለች ሀገር፡፡ የትም ቦታ ሆነህ ስሟን ስትሰማው ልብህን ቀጥ የሚያደርግ ነገር አላት ሀገር፡፡ ሙትልኝ ሙትልኝ፣ ድማልኝ ድመልኝ፣ ተሠዋ፣ተሠዋ የሚያሰኝ ኃይል አላት ሀገር፡፡ ምንም ጥቅም ሳታገኝ፣ ምንም ነገር ላንተ ሳይደርስህ፣ የሞተላት ቀርቶ የገደላት እየበላ እንኳን ቢሆን፤ ሞኝ ነሽ ተላላ እያል እየዘፈንክላትም ቢሆን፣ ላንዱ በጭልፋ ላንዱ በአካፋ እየሰጠች እንኳን ቢሆን፤ አንዱ እንገሯን አንዱ አሬራዋን እየጠጣም ቢሆን፤ ላንዱ ቅቤ ላንዱ ዝቃቅቤ እየሰጠችውም ቢሆን – ግን በፍቅር እንድትሞትላት የሚያደርግ ኃይል አላት ሀገር፡፡ እንዳትቀየማት፣ ቂም እንዳትይዝባት፣ እንዲሁ ይቅር እንድትላት የሚያደርግ ኃይል አላት ሀገር፡፡

    ‹‹ደግሞ ገልብጠህ ስታያት ሀገር ሕመም ናት፡፡ ቀዶ ጥገና አድርገህ የማታወጣት፣ ቆርጠህ የማትገላገላት፤ ታክመህ የማትድናት፤ በአበሻ መድኃኒት ነቅለህ የማትጥላት፤ ኮሶ ወስደህ የማታሽራት፤ ሕመምህ ናት ሀገር፡፡ ምነው እዚህ ሀገር ባልተደረገ የምትለው ስንት ታሪክ አላት፤ ምነው በዜጋሽ ላይ እንዲህ ታደርጊያለሽ ብለህ የምታዝንባት ስንት ግፍ አለባት ሀገር፤ ምነው እንደ እንጀራ እናት ታዳያለሽ ብለህ አንጀትህ እርር የሚልባት ስንት አድሎ አላት ሀገር፤ አንዱ

    ሀገሬ ኢትዮጵያ ምድራዊት ገነት

    አደላድለሽኛል በሥልጣንና በሀብት፣

    ብሎ ሲያወድሳት፣ አንተ ግን –

    ሀገሬ ኢትዮጵያ ምድራዊት ገነት

    እስኪ ፈልጊልኝ የሚከራይ ቤት፣

     ትላታለህ፤

    ለሚያሥረው ሀገር ናት፣ ለታሣሪው ሀገር፤ ለገዳይ ሀገር ናት ለሟቹም ሰው ሀገር፤ ለአሳዳጅ ሀገር ናት ለተሰዳጅ ሀገር፡፡

    ‹‹ ‹ሌቦ› እያሉ እንደመዝፈን ያለ፡፡ አሁን ለሌባ ምን ይዘፈንለታል፡፡ ሀገርህ ሰጭ፣ ለጋስ፣ ቸር፣ ደግ፣ ብቻ አይደለችም፡፡ ሀገርህ ሌቦም ናት፡፡ የስንቱን ሕጻን፣ ወጣት፣ ሽማግሌ፣ ልጃገረድ፣ እናት፣ ባልቴት ሕይወት ቀጥፋ ነው እዚህ የደረሰችው፡፡ ግን ሌባ አይደለችም ‹‹ሌቦ›› ናት፡፡ የሚዘፈንላት ሌባ ማለት ነው፡፡ ‹‹ያዛት፣ ያዛት፣ በላት፣ በላት፣ ኡኡኡ›› ብለህ በፖሊስ የምታስይዛት፣ በጎረምሳ የምታስደበድባት ሌባ አይደለችም፡፡የምትዘፍንላት ‹ሌቦ››፡፡

    አሣሪ ሆነህ እንደወድካት ሁሉ ታሣሪም ሆነህ ትወዳታለህ፣ አሳዳጅ ሆነህ እንደወደድካት ሁሉ ተሳዳጅ ሆነህም ትወዳታለህ፤ ቀማኛ ሆነህ እንደወደድካት ሁሉ ተቀምተህም ትወዳታለህ፤ተምረህ እንደወደድካት ሁሉ ደንቁረህም ትወዳታልህ፡፡ ሀገር ማለት ይህቺ ናት፡፡ ሀገር ‹‹ሕመሜ›› ናት፡፡ ሀገር አደዋ አላት፤ ሀገር ማይጨው አላት፡፡ የአኩስም ሐውልት አላት፣ የቆሻሻ ክምርም አላት፤ መንገድ ሠሪም አላት፣ መንገድ ላይ የሚሸናም አላት፤ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የስልክ ታሪክ አላት፣ ከአፍሪካ መጨረሻ የሆነ የስልክ ኔትወርክም አላት፤ ታሪክ ትሠራለች፣ ታሪክም ታፈርሳለች፤ ቅርስ ትሠራለች፣ ቅርስም ታፈርሳለች፡፡ ሀገርህ ይህቺ ናት፡፡

    ‹‹ርግፍ አድርጌ ልተዋት ብትል እሺ አትልህም፡፡ ለቅቀሃት በመሄድ፣ ጥለሃት በመጥፋት፣ ዜግነት ቀይረህ፣ ቋንቋህን ለውጠህ እንኳን እሺ ብላ አትተውህም፡፡ ሞተህ እንኳን አትለቅህም፣ አስከሬን ታስጭንሃለች፡፡ ደግሞ በዚያ ወገን ዝም ብዬ ብቻ ልውደድሽ፤ ዝም ብዬ ብቻ ላድንቅሽ ስትላት ደግሞ እሺ አትልህም፡፡ አንዳች ሕመም ነገር አላት፡፡ ያለህ አማራጭ ‹‹ሕመሜ›› እያልክ መዝፈን ነው፡፡ በሳቅህ ውስጥ ልቅሶ፣ በልቅሶም ውስጥ ሳቅ ትቀላቅልብሃለች፡፡ የጠቦቱን ሥጋ ከመራራ ቅጠል ጋር ታበላሃለች፡፡

    ‹‹ለእኔ ሀገር ማለት ይህቺ ነች፡፡ ‹‹ሕመሜ›› ››

    ዝም ብዬ አየሁት፡፡

     © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

    በአንድ ጫካ ውስጥ አንድ ከሺ ዓመታት በላይ እድሜ የጠገበ ዋርካ ነበረ፡፡ ዋርካው እጅግ ሰፊ፣ ውስብስብና ታላቅ ነው፡፡ በላዩ ላይ አዕዋፍ፣ በሥሩም እንስሳት ይጠለሉ ነበር፡፡ ከፊሉ ፍሬውን ከፊሉም ቅጠሉን ይመገባሉ፡፡ ሌሎቹም ግንዱንና ሥሩን ፍቀው ይበላሉ፡፡ አንዳቸው ለሌላቸው እንስሳትና አዕዋፍ የጠቀሙበት፣ አንዳቸውም አንዳቸውን የበሉበት ዘመን ነበር፡፡ አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር የሚጋቡበት፣ አንዳቸውም ከሌላቸው ጋር የሚዋጉበት ዘመን አለ፡፡ ፈረስና አሞራ ተጋብቶ ክንፍ ያለው ፈረስ ተወልዶ ነበር አሉ፡፡ ታላላቆቹ እንስሳት በልተዋቸው ዘራቸው የጠፉ እንስሳትም አሉ፡፡

    እነዚህ እንስሳት አለመግባባታቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ አንዳንዶቹ ወፍነት፣ አንበሳነት፣ ዝሆንነት፣ ድመትነት የሚባል ማንነት እንጂ እንስሳነት የሚባል ማንነት የለም ይላሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ እንስሳነት የሚባል ማንነት እንጂ ወፍነት ወይም በግነት፣ ፍየልነት ወይም ጦጣነት የሚባል ማንነት የለም ብለዋል፡፡ ከዚህ የተረፉት ደግሞ ሁለቱም አለ ይላሉ፡፤ እስካሁን ግን በአንዱም አልተስማሙም፡፡

    ከዋርካው ሥር የሚያርፉት እንስሳት የዋርካው ቅርንጫፎች መቆረጥ አለባቸው የሚል አቋም ይዘዋል፡፡ ለምን? ሲባሉ እነዚህ ጨቋኝ አዕዋፍ በኛ ላይ ሲዘባነኑ፣ ኩሳቸውን ሲጥሉ፣ ከዚያም አልፈው ከላይ ሆነው እኛን ሲረግጡ የነበረው በቅርንጫፉ ላይ ሆነው ነው፤ የቅርንጫፉ መኖር ግፍና መከራውን፣ ጭቆናና ስቃዩን ስለሚያስታውሰን መቆረጥ አለበት ባይ ናቸው፡፡

    ሌሎቹ ደግሞ በዋርካው ሥር ላይ ቂምና ትችት አላቸው፡፡ ይኼ ዋርካ አንድ ቦታ ተተክሎ የቀረው፣ ከመስፋትና ከመደርጀት አልፎ ተራማጅ ያልሆነው፣ ሥሩ ከምድር ጋር ተክሎ ስለተያያዘ ነው፡፡ ሥሩ ባይዘው ኖሮ ስንፈልግ አውሮፓ ወስደን የበረዶ ዛፍ፣ ስንፈልግ ካልሃሪ ወስደን የበረሃ ዛፍ ማድረግ እንችል ነበር፡፡ ሥሩ ቸክሎታል፡፡ ስለዚህ ሥሩ መነቀል አለበት ይላሉ፡፡

    ሦስተኛዎቹ ወገኖችም እኛ ስለቅጠሉ እንጂ ስለ ፍሬው የሚያገባን ነገር የለም ብለዋል፡፡ እነዚህ ቅጠል በል የሆኑት እንስሳት በዋርካው ላይ ብቅ የሚሉትን ቅጠሎች ሁሉ እየቀነጠቡ ለመጨረስ በሩጫ ላይ ናቸው፡፡ እነዚህን ወገኖች ፍሬ በል የሆኑ እንስሳት ተቃውመዋቸዋል፡፡ ቅጠሉ ከሌለ ፍሬው አይገኝም፡፡ ዋካው እንዲያፈራ ቅጠሉን ተውለት የሚል ክርክር አላቸው፡፡ እነዚያኞቹ ግን ስለ እናንተ የማሰብ ግዴታ የለብንም፡፡ እኛ ማሰብ የሚጠበቅብን ስለ ቅጠሉ ብቻ ነው ብለው ዘግተዋል፡፡

    እነዚህ ቅጠል በል እንስሳት ስለ ሌላው የዋርካው ክፍል አይመለከተንም ባይ ናቸው፡፡ ለእኛ ጉዳዩ የቅጠል ጉዳይ እንጂ የዋርካ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህንን ብለው ቅጠሎችን በሚያማምሩ ባለ ቀለም ላስቲኮች ሸፈኗቸው፡፡       ይህ ጉዳይ ደግሞ የዋርካውን ሕይወት ማሳጠር ብቻ ሳይሆን የሌሎችን እንስሳት የመኖር ሕልውናም አደጋ ላይ ጣለው፡፡ ቅጠሉ ከተሸፈነ ይወይባል፣ አየርና ፀሐይ ወስዶ ለዋርካው ምግብ የሚሠራም አይኖርም፡፡ ዋርካውም ሕይወቱ በጭንቅ ሆነ፡፡ ቅጠል በሎቹ ለቅጠሎች የሠሩት ጌጥ እንደ መቃብር ላይ ጌጥ ሆነ፡፡

    ሌሎች ደግሞ መጡ፡፡ ይህንን ዛፍ ዋርካ ብለን መጥራት፣ ግንዱንም፣ ቅርንጫፉንም፣ ቅርፊቱንም፣ ቅጠሉንም፣ ፍሬውንም በአንድ ዋርካ ስም መጥራት የለብንም አሉ፡፡ የዚህ ዋርካ ታሪክ የመቶ ዓመት ታሪክ ነው፡፡ ለምሳሌ ከተወሰኑ ዘመናት በፊት ቅርንጫፎቹ እንደዚህ አልበዙም ነበር፣ ከመቶ ዓመታት በፊት እነዚህን ሥሮች አልሰደደም ነበር፣ ከሺ ዓመት በፊት ደግሞ በዚህ ውፍረት መጠን አልነበረም፡፡ አሁን በዚህ መጠን ስናገኘው ዋርካ አልነው እንጂ በየጊዜው ሌላ ስም ነበረው፡፡ ችግኝ ነበረ፣ ቁጥቋጦ ነበረ፣ ዛፍ ነበር፣ ሌላም ነበረ፡፡ ይህንን ሁሉ ታሪክ ዋርካ ብለን መጥራት የለብንም ይላሉ፡፡ ዋርካው ችግኝ እያለ፣ ቁጥቋጦ እያለ፣ ዛፍ እያለ የሠራው ነገር አይመለከተንም ባይ ናቸው፡፡

    ክርክሩ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ ሀብት ማለት ጥቅም ነው፡፡ አንዳች ግላዊ ጥቅም የማታገኝበት ሀብት ያንተ አይደለም ማለት ነው የሚሉ ደግሞ ተነሡ፡፡ እነዚህ ዋርካው በዝቷል፣ ሰፍቷል፤ ስለዚህ ከቅርንጫፉም፣ ከጎንና ጎኑም እየፈለጥን በመሸጥ መጠቀም አለብን ይላሉ፡፡ ዋርካው በሥሮቹ አማካኝነት የሚስበውን ውኃና አፈር ለጎረቤት ዛፎች እየሸጥን መጠቀም አለብን የሚል ሃሳብ አላቸው፡፡ የዚህ ተቃዋሚዎች ደግሞ ዛፉ የሚስበው ውኃና አፈር ለቅርንጫፎቹ አልበቃ ብሎ ቅጠሎቹ ደርቀው፣ እንጨቶቹ ጠውልገው እየታዩ እንዴት ለሌላ እንሰጣለን፡፡ የራሳችን እያረረብን እንዴት የሰው እናማስላለን፣ ራሷ ሳትጠና ልታቋቁም ሄደች የተባለው ሊደርስብን አይደለም ወይ ይላሉ፡፡

    የዋርካው ግንድ ተገቢ ቦታ አልተሰጠውም የሚሉም አሉ፡፡ ሥሩንና ቅርንጫፉን የሚያገናኘው፣ ዋርካውንም የተሸከመው ግንዱ ሆኖ እያለ የሚደነቀውና የሚመሰገነው ግን ቅርንጫፉ ነው፡፡ አበባ የሚያወጣውና የሚለመልመው ቅርንጫፉ ነው፡፡ የሚንዠረገገውና ግራ ቀኝ የሚሰፋው ቅርንጫፉ ነው፤ ለምን? ብለው ይጠይቃሉ፡፡

    አንዳንዶቹ በዛፉ ሥር የተጠለሉ እንስሳት የወፎቹን ድምጽ መስማት እንፈልግም እያሉ ነው፡፡ ሌሊት ሌሊት ተነሥተው ከዕንቅልፍ ለምን ይቀሰቅሱናል፡፡ ለምን አንተኛበትም? ደግሞም ዜማቸው ከጥንት እስካሁን ተመሳሳይ ነው፡፡ አዲስ የወፍ ዜማ አልመጣም፤ በቃ፤ ወይ ድምጻቸውን ይቀንሱ አለበለዚያም የጠዋት ዝማሬያቸውን ያቁሙ እያሉ ነው፡፡ ወፎቹም በበኩላቸው እነዚህ አራዊት ምድርና ሰማዩን እያደባለቁ የሚለቁትን ግሳት ወይ ይቀንሱ ወይም ያቁሙ ብለው ይከራከራሉ፡፡

    ሁሉም በየራሱ ብቻ ነው የሚሰባሰበው፡፡ ግንዱን የሚመገቡት ‹የግንድ ሰንበቴ› አላቸው፣ ቅርንጫፉን የሚበሉት ‹የቅርንጫፍ ማኅበር› መሥርተዋል፤ ሥሩ ላይ ያሉት ‹ሥር ጽዋ› አቋቁመዋል፣ አሁን ግራ የገባቸው እንደ ዝንጀሮና ጦጣ ከላይም ከታችም የሚሆኑት እንስሳት ናቸው፡፡ እነዚህ ቅርንጫፉም ላይ መሬቱም ላይ የሚኖሩ እንስሳት ምን ዓይነት ማኅበር ማቋቋም እንዳለባቸው ተቸግረዋል፡፡

    በአንድ ወቅት አንድ ዘንዶ መጥቶ በዋርካው ሥርና ቅርንጫፍ ላይ በነበሩት እንስሳት ላይ አደጋ አድርሶ ነበር፡፡ በዚያ አደጋ ምክንያትም ብዙ እንስሳት ተሰድደው ወደ ሌሎች ዋርካዎች ሄደዋል፡፡ እነዚህ የተሰደዱ የዋርካው እንስሳት በዋርካው ዙሪያ ካሉት እንስሳት ጋር አንዳንድ ጊዜ አይስማሙም፡፡ የዋርካው እንስሳት እዚያ ማዶ ሆኖ ከመጮህ ጎበዝ ከሆናችሁ እዚህ አትመጡም? ይሏቸዋል፡፡ የተሰደዱት እንስሳትም ‹‹ወኔ የሌላችሁ፣ ድፍረት ያጣችሁ፣ ፈሪዎች›› ብለው ይመልሳሉ፡፡

    ዋርካው አሁንም አለ፡፡ እየተፈለጠም እየተቆረጠም ቀጥሏል፡፡ በላዩና በታቹ ያሉት እንስሳት ግን የሚያስማማቸው ነገር አላገኙም፡፡ እስካሁን የተስማሙበት ነገር ቢኖር በዛፉ ላይ በመኖራቸው ብቻ ነው፡፡ ሚዲያ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደቀረበ ሰው፣ ሁሉም የራሱን ድምፅ ብቻ ነው መስማት የሚወደው፡፡ የሚፈልጥ ሊፈልጥ፣ የሚቆርጥ ሊቆርጥ፣ የሚልጥ ሊልጥ፣ የሚከልል ሊከልል፣ የሚለቅም ሊለቅም፣ የሚንጥ ሊንጥ፣ የሚቀነጥስ ሊቀነጥስ፣ የሚነቅል ሊነቅል፣ ሁሉም በየወገኑ ተዘጋጅቷል፡፡ ዋርካው ዋርካ ሆኖ እንዳለ እንዲቀጥል ማን ያትርፈው?

    © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

    ትናንት ማታ የሴቶች፣ ሕጻናትና የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዘነቡ በትዊተር ገጻቸው ላይ ግብረ ሰዶምን በተመለከተ የጻፉትን ነገር ከምመለከት ወይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባይኖር ወይ እርሳቸው ሚኒስትር ባይሆኑ እመርጥ ነበር፡፡ የሴቶችና የወጣቶች፣ የሕጻናት ሚኒስትር ሆነው ግብረ ሰዶምን በመደገፍና የዑጋንዳን አዲሱን ሕግ በመቃወም መጻፋቸው ‹‹ይህቺ ሀገር ወዴት እየሄደች ነው›› ብዬ እንድጠይቅ አድርጎኛል፡፡ ከተወሰኑ ጊዜያት በፊት በአዲስ አበባ የተሾሙ የአሜሪካ አምባሳደር በኢትዮጵያ የግብረ ሰዶማውያን መብት እንዲጠበቅ እሠራለሁ ያሉትን አስታውሼ እኒህ ዲፕሎማት እውነትም ሠርተዋል ማለት ነው አልኩ፡፡

    ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የኤች አይ ቪ ኤድስ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሲደረግ የእምነት ተቋማት መሪዎች ግብረ ሰዶምን በመቃወም መግለጫ ለመስጠት ተዘጋጅተው ወዲያው ነበር የተሠረዘው፡፡ ግብረ ሰዶማውያንን ተዋቸው ተብለው መግለጫቸው መሠረዙ፣ እነርሱም ያንን በዝምታ ማለፋቸው በሀገራችን ከተከናወኑ አሳዛኝ ተግባራት አንዱ ሆኖ እንዲመዘገብ አድርጎታል፡፡

    ዑጋንዳ ሕጉን ያወጣችው የግብረ ሰዶማውያንን ተግባር ለመከታተል፣ ለመቆጣጠርና ሕጋዊ ርምጃ ለመውሰድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕግም ግብረ ሰዶም ወንጀል መሆኑን ከዑጋንዳ ቀድሞ የደነገገ ነው፡፡ ምነው ሚኒስትራችን የግብረ ሰዶም ደጋፊ ሆነው ብቅ አሉ፡፡ ይህ ሕግኮ እርሳቸውንም የሚመለከት ነው፡፡ ግብረ ሰዶም በሀገሪቱ በድብቅ እየተድፋፋ ሕጻናትና ወጣቶችን እየቀጠፈ፣ ማኅበረሰባዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችንን እያፈረሰ ነው፡፡ ሰውን ከተፈጠረበት ዓላማና ግብር ውጭ የሚያደርግ ነው ግብረ ሰዶም፡፡ እንስሳት እንኳን የማይፈጽሙትን የሚያስደርግ ነው ግብረ ሰዶም፡፡

    ምዕራባውያን በራሳቸው ምክንያት የተነሣ የዚህ ሐሳብ ደጋፊም አቀንቃኝም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነርሱ የደገፉትን ሁሉ የመደገፍ ግዴታ ግን የለብንም፡፡ የእነርሱ ማኅበረሰባዊ ሥሪትና የእኛ ሥሪት ፈጽሞ አይገናኝም፡፡ በርግጥ ይህንን መሰል ርካሽ ነገሮችን መደገፍና ማቀንቀን ዓለም ዐቀፍ ተቀባይነትን ለማግኘት አቋራጭ መንገድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እኛ ግን ሚኒስትራችን የምንፈልጋቸው ለአሜሪካ ጉዳዮች አይደለም፤ ለኢትዮጵያ ጉዳዮች እንጂ፡፡

    እርስዎ የተሾሙላቸው ሕጻናት፣ ሴቶችና ወጣቶች ሥራ፣ ንጹሕ ውኃ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የጤና ተቋማት፣ ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶች ቸግሯቸው እንጂ ግብረ ሰዶምነት አልቸገራቸውም፡፡ ግብረ ሰዶምነት የእነርሱ ማጥቂያ መሣሪያ እንጂ ክብርት ሚኒስትሯ የሚቀኙለትና የሚሟገቱለት አይደለም፡፡

    ለሕጻናት፣ ለወጣቶችና ለሴቶች ያልተሠራ ብዙ አጀንዳ ባላት ሀገር፣ በዐቅም እጥረት በጤና ተቋማቱ የማይወልዱ እናቶች፣ በየጉራንጉሩ የሚወለዱ ሕጻናት፣ በየጫት ቤቱ ሥራ ፈትተው የሚባዝኑ ወጣቶች ያሏት ሀገር ግብረ ሰዶምን ጉዳዬ ብላ ማቀንቀኗ በዜጋ ላይ የሚፈጸም ስላቅ ነው የሚሆነው፡፡

    እኔ ይህ መልእክት አሁንም የእርሳቸው ባይሆን እመርጣለሁ፡፡ ማብራሪያ እንደሚሰጡበትም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

    በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የንጉሡ አሽከሮች፣ ወዳጆችና፣ አድናቂዎች ‹‹የጠቅል አሽከር›› ብለው ይፎክሩ ነበር፡፡ ‹‹ጠቅል›› የዐፄ ኃይለ ሥላሴ የፈረስ ስም ነው፡፡ የጠቅል አሽከር -ማለትም የዐፄ ኃይለ ሥላሴ አሽከር ብሎ እንደ መኩራራት ነው፡፡ ያ ዘመን አለፈ፡፡ ጠቅልም አሟሟታቸው በቅጡ ሳይታወቅ በደርግ ተገደሉ፡፡ የጠቅል አሽከሮች ግን መልካቸውን ቀይረው ዛሬም አሉ፡፡

    ዛሬ ያሉት የጠቅል አሽከሮች ‹‹የጠቅል አሽከር›› ብለው የሚፎክሩ አይደሉም፡፡ እንዴው ዝም ብለው የሚጠቀልሉ ናቸው፡፡ አንድን ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ፣ አንድን ሀገር፣ ክልል ወይም አካባቢ እንዴው ጠቅልሎ ‹‹እንዲህ ነው እንዲያ ነው›› ብለው የሚፈርጁ ናቸው፡፡ ኦሮሞ እንዲህ ነው፣ አማራ እንዲህ ነው፣ ትግሬ እንዲህ ነው፣ ሶማሌ እንዲህ ነው፣ ሲዳማ እንዲህ ነው፣ አፋር እንዲህ ነው ብለው የሚደመድሙ ናቸው የጠቅል አሽከሮች፡፡

    አንድ ሕዝብ፣ ብሔር ወይም ብሔረሰብ በውስጡ ሚሊዮን ሰዎች፣ የተለያዩ አስተሳሰቦች፣ የተለያዩ ፍላጎቶች፣ ዕውቀቶችና ለብዙ ዘመናት የተከናወኑ ለውጦች፣ የሚገኙበት የማኅበረሰብ ክፍል ነው፡፡ በርግጥ ያንን ሕዝብ አንድ ሕዝብ የሚያደርጉት የጋራ ባሕል፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ የአነዋወር ዘይቤ ይኖረዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉም የዚያ ብሔር ወይም ብሔረሰብ አባል ያንን ተቀብሎ፣ አምኖና ተግብሮ ይኖራል ማለት አይደለም፡፡ ከዚያ ማኅበረሰብ አንዱን ወይም ሁለቱን የጋራ እሴት ብቻ ወስዶ ሌላውን ከሌላው ብሔረሰብና አካባቢ፣ አልፎ ተርፎም ከሌላ ሀገር ሕዝብ የሚወስድ፤ ጭራሽም በትውልድ የዚያ ማኅበረሰብ አባል ከመሆኑ በቀር በቋንቋ፣ በእምነት፣ በባሕል ወይም በአነዋወር ዘይቤ የማይመሳሰል ሰውም አለ፡፡

    በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚወደድ፣ የሚደነቅ፣ የሚኮራበት ባሕል፣ አስተሳሰብና አነዋወር እንዳለ ሁሉ፤ የማይፈለግ፣ የሚነወርና የሚጎዳም አለ፡፡ ከማኅበረሰቡ አንዳንዱ የማይፈለገውን፣ የሚነወረውንና የሚጎዳውን ለማስቀረት ሲታገል፣ ሌላው ደግሞ ለምን ትነካብኛለህ? ብሎ የሚታገል አለ፡፡

    አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በታሪክ አጋጣሚ ልዩ ልዩ ማኅበረሰቦች ተዋሕደውና ተዋውጠው ሌላ ዓይነት ማኅረሰብ ይፈጥሩና ያ የተፈጠረው ማኅረሰብ የብዙ ባሕሎች፣ አመለካከቶች፣ ቋንቋዎችና አነዋወሮች ቅይጥ የሚሆንበትም ጊዜ አለ፡፡  

    እንዲህ ያለውን እውነታ ድጦና ደፍጥጦ አንድን ሕዝብ ‹‹እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው›› ብሎ ደምድሞ መናገር የጠቅል አሽከር መሆን ነው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሚናገሩ አንዳንድ እናውቃለን ባዮች ‹‹ይሄኛው ትምክህተኛ፣ ያኛው ጠባብ፣ ይኼኛው ደግሞ ገዥ፣ ያኛው ጎሰኛ፣ ይኼ ደግሞ ተገንጣይ ነው›› ብለው በድምዳሜ ይናገራሉ፡፡ ያ ማኅበረሰብ ተነጋግሮና ተስማምቶ እኔ እንዲህ ነኝ፣ ይህንን እቀበላለሁ ባላለበት ሁኔታ አንተ እንዲህ ነህ ብሎ ደምድሞ መናገር እንዴት ይቻላል? የጠቅል አሽከር ካልሆኑ በቀር፡፡

    ይህ የጠቅል አሽከርነት በዕለት ተዕለት ኑሯችንም ላይ ይታያል፡፡ አበሻ ምቀኛ ነው፣ አበሻ ቀጠሮ አያከብርም፣ አበሻ ወሬኛ ነው እያሉ መደምደም ነው የጠቅል አሽከሮች አሉ፡፡ የተወሰኑ፣ የምናውቃቸው፣ ያጋጠሙን ሰዎች ምቀኛ፣ ሸረኛ፣ ቀጠሮ የማያከብሩ፣ ወሬኞች ለሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚያ ሰዎች ግን 80 ሚሊዮን ሕዝብን ወክለው ‹አበሻ› የሚያሰኙ አይደሉም፡፡ አበሾችም እነርሱ ብቻ አይደሉም፡፡ አንዳንድ ሰዎችማ አንድ የሚያበሳጭ፣ የሚያስቆጣ ወይም ያልተገባ ሥራ የሚሠራ ሰው ሲያጋጥማቸው ‹አይ አበሻ› ‹ድሮስ አበሻ›› ማለት ይቀናቸዋል፡፡ ‹‹ደግሞ ለአበሻ›› ብላ ንቀውን ተጸይፈውን የደመደሙ የጠቅል አሽከሮችም ሞልተውናል፡፡ በተቃራኒውም እንዲሁ በጎ በጎ ነገሮችን ሁሉ ጠቅልለው ለፈረንጅ የሚሰጡ የጠቅል አሽከሮችም አሉ፡፡ ‹አይ ፈረንጅ› ብለው የሚፎክሩ፡፡  የፈረንጅ ምቀኛ፣ ተንኮለኛ፣ ሸረኛ፣ ጎጠኛ፣ ወሬኛ የሌለ የሚመስላቸው፡፡ ያውምኮ በቢሊዮን ከሚቆጠር ፈረንጅ ሃያ ሠላሳውን ይሆናል የሚያውቁት፡፡ ለእነርሱ ሂትለርና ሞሶሎኒ፣ ኢያጎና ሻይሎክ አበሾች ናቸው፡፡

    ‹አይ የዛሬ ሴት›፣ ‹አይ የዛሬ ወንድ› የሚሉ የጠቅል አሽከሮችስ አልሰማችሁም? ሁለት ሴቶች፣ አራት ወንዶች ባደረጉት ነገር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ወንዶችንና ሴቶችን የሚጠቀልሉ፡፡ አይ ነጋዴ፣ አይ ጋዜጠኛ፣ አይ ቀበሌ፣ አይ ወረዳ፣ አይ ሐኪም፣ አይ  ታክሲ፣ አይ ወያላ፣ አይ የዛሬ ተማሪ፣ አይ ሆስተስ፣ እያሉ የሚጠቀልሉስ፡፡ ምንም ያህል አብዛኞቹ በችግር ውስጥ ቢነከሩ፣ በሥነ ምግባር ድቀት ቢዳክሩ፣ በግል ጥቅም ቢታወሩ፤ አንዳንዶች ደግሞ ለዘር የሚተርፉ አሉ፡፡ የጠቅል አሽከርነት ግን ለእነዚህ ለትሩፋን ቦታ የለውም፡፡ የጠቅል አሽከርነት ካልጠቀለለ ነጥሎም አንጥሮም ማየት አይቻለውም፡፡  

    ያለፈው ታሪካችን ሁሉ አስከፊ፣ አስጸያፊ፣ አንገት አስደፊ ነው ብለው የሚደመድሙ፤ የቆየ ነገር ሁሉ ኋላ ቀር፣ ጎታችና ለዕድገት ፀር የሚመስላቸው፤ የእነርሱ አያቶች ሲዋጉና ሲራቡ ብቻ የኖሩ አድርገው የሚገምቱ የጠቅል አሽከሮች እንዳሉት ሁሉ የቀድሞው ነገር ሁሉ ምርጥ፣ ልዩ፣ ሊነካ የማይገባው፣ እንዳለ መጠበቅ የሚገባው፣ እንከን የማይወጣለት አድርገው የሚፎክሩ የጠቅል አሽከሮችም አሉ፡፡

    ለእነዚህ የጠቅል አሽከሮች በንጉሡ ዘመንና በደርግ ዘመን ምንም ዓይነት በጎ ሥራ አልተሠራም፡፡ ለእነርሱ ዋናው ጉዳይ ሥራው ሳይሆን የተሠራበት ዘመን ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት ሥርዓቶች ሰው ሲገደል፣ ሲጨቆን፣ ሲራብ፣ ሲገፋ፣ ሲሰደድ፣ ብቻ ነው የነበረው፡፡ ሌላ ነገር አልነበረም፤ ሌላ ነገር አልተሠራም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አሁን ባለንበት ዘመን ምንም ዓይነት መጥፎ ነገር የለም፤ ሁሉ ሙሉ ሁሉ ዝግጁ ነው፡፡ ዛሬ ሁሉ ደልቶት፣ ሁሉ ተመችቶት ነው የሚኖረው፡፡ ለዚያኛው ሙሉ ጥላቻ፣ ለዚህኛውም ሙሉ ፍቅር አላቸው፡፡ ያኛው ፍጹም ሰይጣን፣ ይኼኛውም ፍጹም መልአክ ነው፡፡

    በአንድ በኩል የፕላቶ የአሪስቶትልና የሶቅራጥስና የስክንድስ ፍልስፍና፣ የእስክንድር ታሪክ፣ የበርለዓም የሕንድ መጽሐፍ፣ የዮሐንስ መደብር የዓለም ታሪክ፣ ፈውስ ሥጋዊን የመሰለ የሕክምና መጽሐፍ መኖራቸውን ዘንግተው በግእዝ የተጻፈው ሁሉ ሃይማኖታዊ፣ ቅዱስና ለጽድቅ ብቻ የተጻፈ የሚመስላቸው የጠቅል አሽከሮች እንዳሉት ሁሉ፤ እንድ እና ሁለት መጻሕፍትን ብቻ ተመልክተው በግእዝ የተጻፉትን ነገሮች ሁሉ ከሃይማኖት ያለፈ ፋይዳ የሌላቸው አድርገው የሚደመድሙ የጠቅል አሽከሮችም ሞልተዋል፡፡

    የአማርኛ መጽሐፍ አላነብም፣ የአማርኛ ፊልም አላይም፣ የአማርኛ ዜና አልሰማም የሚሉ የጠቅል አሽከሮች፡፡ በእንግሊዝኛ የተጻፈ ሁሉ ዕውቀትና ብልሃት የሚመስላቸው፡፡ የዚህ ሀገር ልብስ፣ የዚህ ሀገር ጫማ፣ የዚህ ሀገር ቦርሳ፣ የዚህ ሀገር ዕቃ፣ የዚህ ሀገር ሁሉ ቀሽም ነው ብለው የደመደሙ የጠቅል አሽከሮች – እዚህ፣ እዚያ እዚያ ማዶም አሉ፡፡

    መጠቅለል ልዩ ነገርን እንዳናይ ይጋርዳል፡፡ ከመቶዎች ውስጥ ልዩ ለሆነው አንድ ሰው ዕድል እንዳያገኝ ያግዳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለመታየትና ለመሰማት ዕድል ባላቸው ጥቂት አካላት ምክንያትም የመጡበትን አካባቢ፣ ማኅበረሰብና ሙያ ደምድመን እንድንናገርም ያደርገናል፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ የተለየ ነገር መሥራት፣ የተለየ ጠባይ መላበስ፣ የተለየ አመለካከት መያዝ፣ የተለየ አነዋወር መኖር የሚፈልግ ሰው ከተጠቀለሉት ነጥሎ የሚቀበለው ስለማይኖር በጠቅል አሽከሮች ተደፍቆ ይቀራል፡፡ ብዙ ሰው የተናገረለት ነገር ደግሞ ሰነባብቶ እማሬ ይሆናል፡፡ ከዚያም ያንን ማስተባበል ይከብዳል፡፡አንድ እግረኛ ያወራውን ሃምሳ ፈረሰኛ አይመልሰውም ይባላልና፡፡ እኛ ግን ለራሳችን  እንዲህ እንበል ‹የጠቅል አሽከር አይደለሁም››፡፡ እነዚህንም  ያለ መረጃና፣ ያለ ማስረጃ፣ ያለ ዳታና ያለ ይሉኝታ እየጠቀለሉ የሚናገሩትን ‹‹የጠቅል አሽከር›› እንበላቸው፡፡ እንዴው ቢታረሙ፡፡

    © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው

    እኔ እንግዲህ የሚቻለኝን ደክሜያለሁ፤ ከዚህ በላይ ለማድረግ ዐቅሙም ዕውቀቱም የለኝም፡፡ ይህን ጉባኤ ቤት ደርቡሽ ፈተነው፣ መንግሥት ፈተነው፣ እሳት ፈተነው፣ ረሃብ ፈተነው፤ ይህንን ሁሉ ተቋቋመ፡፡ አሁን ግን እኔም አልፋለሁ፡፡ ትምህርት ቤቱም ይዘጋል፡፡ ሁላችንም ታሪክ ሆነን እንቀራለን››

    click here for pdf

    ጎንደር ከተማ በሄድኩ ጊዜ ሠለስቱ ምእት እየተባለ ወደሚጠራው አካባቢ ተጉዤ ነበረ፡፡ በዐፄ ቴዎፍሎስ (1700-1704 ዓም) ተሠርቶ በ1880 እና በ1881 ዓም በተደጋጋሚ በደርቡሽ ተቃጥሎ የጠፋውን የሠለስቱ ምእት ቤተ ክርስቲያን ፍራሽ ለማየት፡፡ ይህ በአንድ ወቅት እንደ ኒቂያ 318 ሊቃውንት ተሰባስበው ይመክሩበት ነበር የሚባለው ዋናው የጉባኤ ቦታ ደርቡሽ ካፈረሰው በኋላ እንደገና ሳይሠሩ ከቀሩት የጎንደር አድባራት አንዱ ነው፡፡

    ከዚሁ ፈርሶ ከቀረውና ዛሬ መጸዳጃ ቤት ከሆነው የሠለስቱ ምእት ቤተ ክርስቲያን ፍራሽ አጠገብ በቆርቆሮ የታጠረ አንድ ግቢ አለ፡፡ ወደ ውስጥ ስትዘልቁ ዳዋ የለበሰ ግቢና በጭቃና ቆርቆሮ የተሠሩ ሦስት አነስተኛ ክፍሎችን ታገኛላችሁ፡፡



    እኔ በጥግ ወዳለው ክፍል ዘለቅኩ፡፡ አንድ ዓይነ ሥውር አረጋዊ አባት አልጋ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ቤቷ ጠባብና በዕቃዎች የተሞላች ናት፡፡ የመጽሐፈ መነኮሳቱ መምህር መጋቤ ምሥጢር ተሾመ ታደሰ ናቸው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ መጀመሪያ ረዳት መምህር ሆነው ከ1987 ዓም ጀምሮ አገልግለዋል፡፡ በ1991 ዓም ደግሞ ሙሉ መምህር ሆነው ጉባኤ ቤቱን ተረክበዋል፡፡

    የ66 ዓመቱ መምህር የሚያስጨንቃቸው የሚበሉት ምግብና የደመወዛቸው ሁኔታ አይደለም፡፡ የመጽሐፈ መነኮሳቱ ጉባኤ ቤት እየጠፋ መምጣት ነው፡፡ በሀገራችን በመጥፋት ላይ ከሚገኙት ጥንታውያን ትምህርቶች አንዱ የመጽሐፈ መነኮሳት የትርጓሜ ትምህርት ነው፡፡ በዋናነት መነኮሳት እንዲመከሩበት የተጻፈውና የተተረጎመው፣ በሦስት ክፍል (ማር ይስሐቅ፣ አረጋዊ መንፈሳዊና ፊልክስዩስ) ይህ መጽሐፍ  በጉባኤ ቤት የሚማረው እየጠፋ መጥቷል፡፡ በሀገራችን ለምንኩስና ሥነ ምግባር መበላሸት አንዱ ምክንያትም ይህንን የትምህርተ ሃይማኖት፣ የሥነ ምግባርና የእምነት መጽሐፍ ያልተማሩ፣ የስም መነኮሳት መብዛት መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡


    ይህን ትምህርት ቤት ታላቁ ሊቅ አለቃ አየለ (ዶክተር) በ1948 ዓም እንደገና እንዲያንሠራራ አድርገውት ለብዙ ዘመናት ቆይቶ ነበር፡፡ ቦታውን በተመለከተ የአካባቢው መስተዳድርና መምህራኑ እየተወዛገቡበት፣ ጉባኤው ግን ሳይታጠፍ ኖሯል፡፡ በ1988 ዓም ኅዳር 30 ቀን የአካባቢው መስተዳድር ቦታውን ለትምህርት ቤቱ ሰጠ፡፡ መምህሩና ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ሲደሰቱ ግን ጉባኤ ቤቱ በ2004 ዓም የካቲት 7 ቀን በተነሣ እሳት ወደመ፡፡ በዚህ ቃጠሎ በ1714 ዓም የተጻፈ መጽሐፈ መነኮሳትን ጨምሮ አያሌ ቅርሶችና መጻሕፍት ወድመዋል፡፡

    ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ትምህርት ቤቱ ችግር ላይ ወደቀ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በጭቃ እና በቆርቆሮ እነዚህን ሦስት ክፍሎች ሠሩ፡፡ ግቢውንም ዳዋ ዋጠው፡፡ ተማሪዎቹም ከምግብና ልብስ ችግራቸው ላይ የመጠለያ እጦትም ተጨመረበት፡፡ ውኃውን የማራኪ ግቢ ጉባኤ ልጆች አስገብተውላቸዋል፡፡ መብራት ግን የለም፡፡ አሁን አሥር ተማሪዎች ዳዋ ተንተርሰው እየኖሩ ጉባኤው እንዳይታጠፍ ይተጋሉ፡፡


    መምህሩም እንዲህ አሉኝ ‹‹እኔ እንግዲህ የሚቻለኝን ደክሜያለሁ፤ ከዚህ በላይ ለማድረግ ዐቅሙም ዕውቀቱም የለኝም፡፡ ይህን ጉባኤ ቤት ደርቡሽ ፈተነው፣ መንግሥት ፈተነው፣ እሳት ፈተነው፣ ረሃብ ፈተነው፤ ይህንን ሁሉ ተቋቋመ፡፡ አሁን ግን እኔም አልፋለሁ፡፡ ትምህርት ቤቱም ይዘጋል፡፡ ሁላችንም ታሪክ ሆነን እንቀራለን››

    እንዲህ ያሉት ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ ብዙ ሀገራዊ ጉዳት አላቸው፡፡ ከዘመን ዘመን የተጠራቀመ ዕውቀት፣ ታሪክ፣ ትውፊትና መረጃ ይጠፋል፡፡ ከሀገራዊ ማዕድ ውስጥም አንድ ዓይነት ይጎድላል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ የምንኩስና ሕይወትም ያለ ዕውቀት ይቀራል፡፡ የኔ ቢጤው ደግሞ በሰማይም በምድርም አይተህና ሰምተህ ታድያ ምን አደረግክ? ተብሎ ይወቀሳል፡፡

    ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ቢፈርስ ያመኑና ያወቁ አበውና ምእመናን ተባብረው አስበልጠው ያሠሩታል፡፡ ትምህርት ቤት ፈርሶ ትምህርቱና ሊቃውንቱ ከጠፉ ግን እንደገና መመለስ ከባድ ነው፡፡ እስኪ በየቦታው የተመሠረታችሁ በጎ አድራጊ ማኅበራትና ግለሰቦች የልባችሁ አጀንዳ አድርጉት፡፡

    ማኅበረ ቅዱሳን ለሦስተኛ ጊዜ ያዘጋጀው የአብነት መምህራን ጉባኤ መታገዱን መግለጫዎችና ዜናዎች እያሳወቁን ነው፡፡ የአብነት መምህራን በቤተ ክህነቱ ‹ለአበል የተረሱ፣ ለሹመት የሚታወሱ› ሆነዋል፡፡ ስብሰባ፣ ዐውደ ጥናት፣ ሥልጠና፣ ጉዞ፣ ሲሆን እነርሱን የሚያስታውስ የለም፡፡ የጵጵስና ሹመት ሲመጣ ግን ‹ከእገሌ ይህንን ከእገሌም ያንን ተማርኩ› የሚለው ይበዛል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነ የሀገሪቱ ሀገራዊ ዕውቀት ማዕከል መሆናቸው ተረስቶ ይህንን ያህል ዘመን ሲኖሩ ‹ቤት ልሥራላቸው፣ ዘር ልዝራላቸው› ያለ ቤተ ክህነት አልገጠመንም፡፡ እንዲያውም እነ መምሬ በዕውቀቱን እነ አያ ብሩ እየቀደሟቸው ቦታ ቦታውን ይዘውታል፡፡
    ማኅበረ ቅዱሳን ለውጥ አምጭ ሥራ ከሠራባቸው ዘርፎች አንዱ የአብነት ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን እስላም ከክርስቲያኑ የሚመሰክረው ነው፡፡ ለአብነት መምህራን ደመወዝ ከመክፈል ቤት እስከ መሥራት፣ ትምህርት ቤቶቻቸውን ከመገንባት ለተማሪዎቹ ቁሳቁስ እስከ ማቅረብ፣ የጤና መርሐ ግብሮችን ከማከናወን እስከ ካሪኩለም ቀረጻ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

    ለአንድ ሊቅ ከቁሳዊ ነገር በላይ መንፈሳዊ ነገሩ ይበልጥበታል፡፡ ጽድቁ፣ ክብሩ፣ ስሙ፣ መዓርጉ፣ ታሪኩ ታላቅ ነገሮች ናቸው፡፡ ከቁሳዊው ድጋፍም ሞራላዊው ድጋፍ ታላቅ ነው፡፡ እነዚህ የአብነት መምህራን ቦታና ዐቅም ወስኗቸው፣ እድሜና አሠራር ገድቧቸው እንዳይቀሩ፤ እርስ በርስ ተገናኝተው እንዲመክሩ፤ አሠራራቸውን እንዲያዘምኑ፣ ዕውቀት እንዲከፋፈሉ፣ ልምድ እንዲለዋወጡ፣ ህልውናቸውን እንዲተዋወቁ፣ ወጥ አሠራር እንዲዘረጉ መደረጉ የሚያስመርቅ እንጂ የሚያስረግም አልነበረም፡፡

    በርግጥ ይህንን መሰል ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ሥራዎች ለመሥራት ተገቢ የሆኑ ቢሮክራሲያዊ መንገዶችን አሟጦ መጓዝ፤ ማወቅ ያለበት እንዲያውቅ፣ መስማት ያለበትም እንዲሰማ ማደረግ፣ ማሳመንና ማግባባት፣ በአሠራሩና በዓላማው ላይ ቀደም ብሎ ከሚመለከታቸው ጋር መወያየት ያስፈልጋል፡፡ አንድን ታላቅ መኪና የአንዲት ብሎን መላላትና መውለቅ እንደምታስቆመው ሁሉ የጥቂት ቤተ ክህነታዊ አሠራሮች አለመጠበቅ ታላቁን ዓላማ ሊያደናቅፈው እንደሚችል ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ትናንት እንዲህ ስለሠራን ነው ማለቱ ብዙም አያዋጣም፡፡ ሁልጊዜ ፋሲካ የለምና፡፡

    በዚያም ሆነ በዚህ ግን የአብነት መምህራኑ መሰባሰብና በሞያቸውና አገልግሎታቸው ዙሪያ መምከር የሚጠቅመው ማንን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሲሆን ቤተ ክህነቱ ራሱ አስቦ መሥራት ነበረበት፤ ካልሆነም ደግሞ የሚሠሩትን ማትጋትና ማገዝ ይገባው ነበር፡፡ ሁለቱም ግን አልሆኑም፡፡ ማኅበሩ በቤተ ክህነቱ አሠራር ያላከናወናቸው ነገሮች አሉ ከተባለ እንዲያከናውን ማድረግ እንጂ አገር አቋርጠው ወንበር አጥፈው የመጡትን ሊቃውንት ማንገላታት የሚገባ አልነበረም፡፡ ጉባኤው ተስተካክሎ በመካሄዱ የምትጠቀመው ቤተ ክርስቲያን ናት ባለ መደረጉ ግን ከሰይጣን በቀር ተጠቃሚው ማነው

    በሌላ በኩልም ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና የፓትርያርኩ ጽ/ቤት በጉዳዩ አፈታት ላይ የሄዱበት መንገድም አስገራሚ፣ አስተዛዛቢም ነው፡፡ የማኅበሩ ጽ/ቤት ከቤተ ክህነቱ በ50 ሜትር ርቀት ላይ መኖሩ እየታወቀ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁም ሆኑ ፓትርያርኩ ያንን ሁሉ የደብዳቤ ውርጅብኝ ማዝነብ ለምን አስፈለጋቸው? ደግሞስ ጉዳዩ የውስጥ ጉዳይ ነው፤ ለእነዚያ ሁሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የመጻፉ ዓላማው ምንድን ነው? አስፈላጊ ከሆነ ልጆቹን ጠርቶ ‹ጉባኤውን አቁሙ› ማለት ይቻል የለም እንዴ? ደግሞስ መጀመሪያውኑ ሳያጣሩ መጻፍ፣ ከዚያ ደግሞ የመሻሪያ ደብዳቤ መጻፍ፣ አከታትሎ ደግሞ የመሻሪያ መሻሪያ መጻፍ የቤተ ክህነቱን ተቋማዊ ኪሣራ ከማሳየት በቀር ሌላ ምን ያሳያል?

    የዛሬን አያድርገውና የፓትርያርክ ደብዳቤኮ የእምነት መግለጫ፣ የሚጠቀስ፣ በክብር የሚቀመጥ፣ በሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ላይ የሚሠፍር ነበር፡፡ እንዲህ ጊዜ በሰጠ ቁጥር መዥለጥ እየተደረገ የሚጻፍ አልነበረም፡፡ ደግሞስ አንድ አባት ልጆቹን ጠርቶ መምከር እየቻለ ‹‹ልጆቼ እንዲህ ያሉ ናቸው›› ብሎ ለዓለም መንገር ከየት ያመጣነው ሥርዓት ነው? ዓለም ችግሯን ለቤተ ክርስቲያን ታቀርባለች እንጂ ቤተ ክርስቲያን ችግሯን እንዴት ለዓለም አቤት ትላለች?

    የሊቃውንቱ መሰባሰብና መወያየት ለቤተ ክርስቲያኒቱ የወንጌል ሥምሪት ወሳኝ ነው፡፡ እንዲያውም ከሲኖዶሱ ጉባኤ በፊት ሊደረግ የሚገባው ነገር ቢኖር የሊቃውንቱ ጉባኤ ነበር፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ የትምህርተ ሃይማኖት፣ የሥርዓትና የትውፊት ጉዳዮች ላይ መክረው የውሳኔ ሃሳቦችን ማቅረብ የነበረባቸው ሊቃውንቱ ናቸው፡፡ ይህ ባለመሆኑም ይመስላል የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አጀንዳዎች ሃይማኖታዊ ከመሆን ይልቅ አስተዳደራዊና ቢሮክራሲያዊ የሆኑት፡፡ ስንትና ስንት የምእመናን ጥያቄዎች እያሉ የሹመትና የበጀት ጥያቄዎች ዋነኛ መነጋገሪያዎች የሚሆኑት፡፡

    የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንኮ የራስዋን ጳጳሳት እንድትሾም የተሟገቱት ከመላዋ ሀገሪቱ የተሰባሰቡ ሊቃውንት ነበሩ፡፡ ምነው መሠረቱ ተዘነጋ፡፡

    አሁንም ሊቃውንቱን ተዋቸው፣ ቤተ ክርስቲያን እንደነርሱ ላሉት ናትና፡፡ በጉባኤያቸው ተገኝቶ መወያየት፣ የጉባኤውን አጀንዳ አብሮ መቅረጽ፣ ጉባኤውን መምራት፣ አሠራሩን ማሳየት ይገባል፣ የአባትም ነው፡፡ የገዛ ሊቃውንቶቻችንን ግን አትሰብሰቡ፣ አትመካከሩ፣ አትወያዩ፣ ችግር አትፍቱ ብሎ ማገድ፣ እምቢ ካላችሁ  ‹ለመንግሥት እነግርባችኋለሁ›› ብሎ መንግሥትን ማስፈራሪያ ማድረግ ሃይማኖታዊ አይደለም፡፡ ምነው በጎንደሩ የጥምቀት ኤግዚቢሽ የመንግሥት አካላት ሊቃውንቱን ሲያከብሩ ባየን፤

    አሁንም እጠይቃለሁ፤ የሊቃውንቱን ጉባኤ ማገድ ጥቅሙ ለማን ነው? ባሏን ጎዳሁ ብላ … እንደተባለው ካልሆነ በቀር፡፡ ሊቃውንቱንም አስተምረው ለወግ ለመዓርግ ባበቋቸው ልጆቻቸው ሲታገዱ ማየት የስምንተኛውን ሺ መግባት ከማሳየት በቀር ሌላ ምን ያሳያል፡፡

    (ለ1966ቱ አብዮት 40ኛ ዓመት ማስተዋሻ)
    በአብዮቱ ዘመን አንድ ጓድ ከዚህ ቀጥሎ የተጠቀሰውን ቃለ መጠይቅ በመስጠቱ ለ17 ዓመታት ወኅኒ ተወርውሮ ነበር፡፡ በ1983 ዓም ከወኅኒ ሲወጣ ሰውዬው አርጅቷል፡፡ ከዘራውን ተደግፎ ቤቱ በረንዳ ላይ ይቀመጥና ቃለ መጠይቁ የታተመበትን ጋዜጣ እያየ ‹‹ይህን ቃለ መጠይቅ የሰጠሁት ዛሬ ቢሆን ኖሮስ?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ ለሰውዬው መልስ ለመስጠት ቃለ መጠይቁን አንብቡት፡፡

    ጋዜጠኛ፡- ለእርስዎ ሀብት ክፍፍልን በተመለከተ በካፒታሊዝምና በሶሻሊዝም መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

    ጓድ፡- በካፒታሊዝም እኩል ያልሆነ የሀብት ክፍፍል ሲኖር፣ በሶሻሊዝም ደግሞ እኩል የሆነ የድኽነት ክፍፍል አለ

    ጋዜጠኛ፡- ጭቆናን በተመለከተ በካፒታሊዝምና በሶሻሊዝም መካከል ልዩነቱ ምንድንነው?

    ጓድ፡- በካፒታሊዝም ሰው ሰውን ይጨቁናል፣ በሶሻሊዝም ግን ፓርቲ ሰውን ይጨቁናል

    ጋዜጠኛ፡- ለምሳሌ በሰሐራ በረሃ ውስጥ ሶሻሊስት ሪፐብሊክ ቢመሠረት ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብለው ያስባሉ?

    ጓድ፡- ከሦስት ዓመታት በኋላ ሀገሪቱ አሸዋ ከውጭ ማስመጣት ትጀምራለች

    ጋዜጠኛ፡- በሶሻሊዝም አስተሳሰብ ደመወዝና ሠራተኛን እንዴት ይገልጧቸዋል?

    ጓድ፡- በሶሻሊዝም ሠራተኛም በሚገባ የሠራ ለመምሰል ጥረት ያደርጋል፣ መንግሥትም ተገቢውን ደመወዝ የከፈለ ለመምሰል ጥረት ያደርጋል

    ጋዜጠኛ፡- ገበያ የሚመራው በአቅርቦትና ፍላጎት ነው ይባላል፡፡ ይህንን ሃሳብ በሶሻሊዝም እንዴት ይገልጡታል?

    ጓድ፡- በሶሻሊዝም የፈለግከውን ነገር መርጠህ አትገዛም፤ ነገር ግን የቀረበልህን ነገር ትገዛና፣ ከገዛህ በኋላ እንድትፈልገው ይደረጋል፡፡

    ጋዜጠኛ፡- አንዳንድ ሰዎች የሶሻሊስት ፓርቲው ጋዜጣ በጣም ትልቅ ነው ይላሉ፤ ለምንድን ነው ትልቅ የሆነው?

    ጓድ፡- ምክንያቱም ሰው እርሱን መያዝ ስለሚያፍር፣ የጋዜጣው ስፋት ስታነበው ፊትህን ለመሸፈን የሚበቃ መሆን አለበት

    ጋዜጠኛ፡- በዓለም ላይ ሰባቱ አስደናቂ ነገሮች የሚባሉ አሉ፡፡ በሶሻሊዝም አስተሳሰብ ሰባቱ የዓለም አስደናቂ ነገሮች ምን ምን ናቸው ብለው ያስባሉ?

    1.         ሁሉም ሰው ሥራ አግኝቷል

    2.       ሁሉም ሰው ሥራ ቢያገኝም ቅሉ ማንም ሰው ግን ሥራ እየሠራ አይደለም(ስብሰባ፣ ግምገማ፣ የፓርቲ ሥራ፣ የአካባቢ ልማት ማኅበር ሥራ አለበት)

    3.       ማንም ሰው ሥራ እየሠራ ባይሆንም እንኳን ሁሉም ሰው ግን ሀገሪቱ ያወጣችውን የዕድገት ዕቅድ ግቡን እንዲመታ አድርጓል

    4.       ምንም እንኳን ሁሉም ሰው ዕቅዱን ተግባራዊ ቢያደርገው፣ ነገር ግን ምንም ዓይነት ውጤት አልተገኘም

    5.       ምንም እንኳን ምንም ዓይነት ውጤት ባይገኝ፣ ነገር ግን ሁሉም ሰው የፈለገው ነገር ሁሉ እንዲኖረው ተደርጓል

    6.       ምንም እንኳን ሁሉም ሰው የፈለገው ነገር ሁሉ ቢኖረው፣ ሁሉም ሰው ግን በሆነው ነገር ርካታ የለውም

    7.       ምንም እንኳን ሁሉም ሰው በሆነው ነገር ሁሉ ርካታ ባይኖረው፣ ፓርቲው ግን የሕዝቡን 100%ድጋፍ አለው፡፡

    እነዚህ ናቸው ሰባቱ አስደና ቂነገሮች፡፡

    ጋዜጠኛ፡- ፓርቲው የሚመራባቸው ሦስቱ መሠረታውያን ሕግጋት ምንድን ናቸው?

    ጓድ፡- ሶሻሊዝም ሩጫ ነው፤ በዚህ ሩጫ ውስጥ የፓርቲው መርሖዎች ሦስት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ሩጫው እንደተጀመረ ሯጮቹን ሁሉ ማሰናከልና የመሪነቱን ቦታ መያዝ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የሩጫውን ፍጥነት መቆጣጠር መቻል ነው፡፡ የመጨረሻውም በተቻለ መጠን ሩጫውን ሳያጠናቅቁ የመሮጫው ትራክ ላይ ረዥም ጊዜ ለመቆየት መቻልነው፡፡

    ጋዜጠኛ፡- አንድ የእርስዎ ጓድ በአብዮታዊው ጦር ተይዘው በቀደም ወደ ወኅኒ ቤት ገብተዋል፡፡ ምን ጎድሎባቸው ነው ፀረ አብዮት የሆኑት፤ አብዮቱ ሁሉን ነገር አሟልቶላቸው ነበር?

    ጓድ፡- ጓዱን የያዙት ሰዎችም ይህንን ነበር የጠየቁት፡፡ እርሱ ወደ አሜሪካ ለመሄድ በዝግጅት ላይ ነበር፡፡ ዝግጅቱን ሲያጠናቅቅ የመውጫ ቪዛ እንዲሰጠው አመለከተ፡፡ ይህንን የሰሙ ወታደሮች ከሌሊቱ በስምንት ሰዓት ወደ ቤቱ መጡ፡፡ በሩን ሰብረው ገቡና ‹‹አብዮቱ ቤት ሰጥቶሃል፣ መኪና ሰጥቶሃል፣ መሬት ሰጥቶሃል፣ የንግድ ድርጅት ሰጥቶሃል፣ሥልጣን ሰጥቶሃል፣ ከውጭ ዕቃ ያለ ቀረጥ እንድታስገባ ዕድል ሰጥቶሃል፤ ለምንድን ነው ወደ አሜሪካ መሄድ የፈለግከው›› ሲሉ ጠየቁት፡፡ እርሱም ተናድዶ ‹‹እንዲህ ከሌሊቱ በ8 ሰዓት እኔ ሳልፈቅድላችሁ በሬን ሰብራችሁ በመግባት እንዳትረብሹኝ ስለምፈልግ ነው አገር ጥዬ የምሄደው›› ብሎ መለሰላቸው፡፡ ለዚህ ነው ያሠሩት፡፡

    ጋዜጠኛ፡- የእርስዎ ጓድ ብቻ ሳይሆኑ የጎረቤትዎ ልጅም መታሠሩን ሰምተናል፤ ልጁ በጣም ትንሽ ልጅ ነው፡፡ ደግሞም በጣም የታወቀ ዋናተኛ ነው፡፡ የታሠረውም ባለፈው ግዮን ሆቴል ዋና ተለማምዶ ሲመለስ ነው ይባላል፡፡ ምክንያቱን ሊነግሩን ይችላሉ?

    ጓድ፡- እንደ ሰማሁት ከሆነ ልጁ የታወቀ ዋናተኛ ነው፡፡ አባቱ በሌለው ገንዘብ ከፍሎለት ግዮን ሆቴል ዋና ይለማመዳል፡፡ የፓርቲያችን ሊቀ መንበር በዚያ ቀን ዋና ለመዋኘት ግዮን ሄደው ነበር፡፡ በአጋጣሚ ዋና እየተለማመዱ ሳለ ወደ መካከል ሄደው ሊሰምጡ ደረሱ፡፡ አጃቢዎቻቸው ዋና የሚችሉ አልነበሩም፡፡ ልጆች ናቸው ተብለው በአካባቢው እንዲንቀሳቀሱ የተፈቀደላቸው የታሠረው ልጅና ሁለት ጓደኞቹ ብቻ ነበሩ፡፡ ሮጠው ገቡና ሊቀ መንበሩን ከመስመጥ አዳኗቸው፡፡ ጓድ ሊቀ መንበርም ለዚህ ውለታቸው አንዳች ሽልማት ሊሰጧቸው ፈለጉና ልጆቹን ጠየቋቸው፡፡ አንደኛው ልጅ ብስክሌት መረጠ፤ ሁለተኛው ልጅ ደግሞ የመጨዋቻ መኪና ጠየቀ፤ ይኼ የጎረቤቴ ልጅ ግን የአካል ጉዳተኞች መሄጃ ጋሪ መረጠ፡፡ ጓድ ሊቀ መንበርም በጣም ተገረሙና ‹‹ምን ያደርግልሃል፤ አንተ ሙሉ ጤነኛ ነህ›› አሉት፡፡ ልጁም ‹‹አባቴ እርስዎን ከሞት ማዳኔን ከሰማ እግሬን ይሰባብረዋል፤ ለዚያ ብዬ ነው›› አላቸው፡፡ በዚህ ተናደው ነው ያሳሠሩት፡፡

    ጋዜጠኛ፡- ባለፈው ሰሞን ለሥራ ጉብኝት ወደ ቻይና ተጉዘው ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ በአንድ ቻይናዊ፣ ኢትዮጵያዊና ዴንማርካዊ የፓርቲ ሰዎች መካከል የተፈጠረ ነገር እንደነበር ሰምተናል፡፡ ሊነግሩን ይችላሉ?

    ጓድ፡- አዎ፤ አራታችን በአንድ ወንዝ ዳር ቆመን ስንዝናና አንድ ጋዜጠኛ መጣና ‹‹ሥጋ ለማግኘት ሲባል ሰልፍ ስለመያዝ ምን ታስባላችሁ?›› ሲል ጠየቀን፡፡ ዴንማርካዊው ‹‹ሰልፍ ማለት ምንድን ነው?›› ሲል መልሶ ጠየቀ፤ ቻይናዊውም ቀጠል አደረገና ‹‹ሥጋ ምንድን ነው?›› ሲል አከለበት፡፡ የኛው ፖለቲከኛ ደግሞ ‹‹ማሰብ ማለት ምንድን ነው?›› ብለው ጋዜጠኛውን መልሰው ጠየቁት፡፡ ይኼ ነው ታሪኩ፡፡

    ጋዜጠኛ፡- በዚሁ አጋጣሚ አብዮታዊ መሪያችን በቻይና ለነበሩ ጋዜጠኞች የሃሳብ ነጻነትን አስመልክቶ አስደናቂ ነገር ተናግረዋል ይባላል፤  ምን ነበር?

    ጓድ፡- ጋዜጠኛው የሃሳብ ነጻነት እያሉ ምዕራባውያን ሶሻሊስት ሀገሮችን ለመበጥበጥ ይሞክራሉ፤ እናንተ ይህንን ችግር እንዴት ፈታችሁት? ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እርሳቸውም ‹እኛ መጀመሪያውኑ ሃሳቡ እንዳይኖር ስላደረግነው ነጻነት መስጠት አይጠበቅብንም› ብለው መልሰውለት በጣም ተደንቆ ነበር፡፡ ?

    ጋዜጠኛ፡ – እኛ ራሳችን ስሕተታችንን ገምግመን ማሻሻል ባለመቻላችን ሌሎች ስሕተቶቻችንን ዐውቀው እየተጠቀሙበት ነው የሚል ትችት ሰንዝረው ነበር፡፡ አንድ ማሳያ እንኳን ሊነግሩንይችላሉ፡፡

    መልስ፡- ይህንን ድክመት እንኳን ነጻ ሆኖ የሚከታተለን ሕዝብ ይቅርና ፀረ አብዮት ናቸው ብለን ያሠርናቸው እንኳን በሚገባ ዐውቀውታል፡፡ አንድ ቀላል አስቂኝ ነገር ልንገርሽ፡፡ አንድ ባልዋ ፀረ አብዮት ሆኖ የታሠረባት ሴትዮ አለች፡፡ ሴትዮዋ ድኽነቱ ሲመራት በቤቷ ጓሮ ድንች ተክላ መሸጥ ፈለገች፡፡ ግን ጉልበት ከየት ይምጣ፡፡ ሰው እንዳትቀጥር፣ ገንዘብ ከየት ይገኝ፡፡ በመጨረሻ ለባልዋ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጽፋ በወኅኒ ቤቱ በኩል ላከችለት ‹‹በጓሯችን ድንች ልተክል ነበር፡፡ ነገር ግን ማን ይቆፍርልኛል፤ አንተ እንዳታግዘኝም ገና ሁለት ዓመት ይቀርሃል›› ባልዋም ‹‹ጓሮውን ስትቆፍሪ ተጠንቀቂ፤ እጅግ ውድ የሆኑ ነገሮችን ደብቄበታለሁ›› ብሎ መልሶ ላከላት፡፡ ደብዳቤው በደረሳት ሌሊት ፖሊሶች መጥተው የተደበቀውን ነገር ፍለጋ የቤቷን ጓሮ ከጥግ እስከ ጥግ ቆፋፈሩት፡፡ እርሷም በድንጋጤ ከረመችና ‹‹ስድስት ፖሊሶች መጥተው የሆነ ነገር ፍለጋ ጓሮውን በቁፋሮ እንዳልነበረ አደረጉት፤ ያልቆፈሩት መሬት የለም፤ ምን ባደርግ ይሻለኛል?›› ስትል ጻፈችለት፡፡ ባሏም ‹‹አሁንማ ቆፍረውልሻል ድንችሽን ትከይ›› ብሎ መለሰላት፡፡

    ጥያቄ፡- ይኼ የመጨረሻ ጥያቄያችን ነው፡፡ ባለፈው ጊዜ በአውሮፕላን ሲጓዙ አንድ ያልታወቀ ፍጡር አውሮፕላኑን እየተከተለ አስቸግሮ ነበር ይባላል፡፡ ፓይለቱና አስተናጋጆቹ ሊያባርሩት አልቻሉም፡፡ በአውሮፕላኑ የነበሩት የሃይማኖት አባቶችም ከዐቅማቸው በላይ ሆኖ ነበር፡፡ እርስዎ ግን የሆነ ነገር ሲያሳዩት እንደ ጢስ በኖ እንደ ጉም ተኖ ጠፋ ይባላል፡፡ ምን እንዳሳዩት ሊነግሩን ይችላሉ?

    መልስ፡- እነርሱ ይህንን ያህል ገንዘብ እንሰጥሃለን አሉት፤ አልሄደም፤ የሃይማኖት አባቶችንም አልፈራም፡፡ ወደ እኔ ቀረብ ሲል ‹‹የወጣት ሊግ አባል ነው የማደርግህ›› ስለው በድንጋጤ ጥሎ ጠፋ፡፡

    አመሰግናሉ፤ ስለ ቃለ መጠይቁ

    አደራ ይኼ ቃለ መጠይቅ ከታተመ የሆነ ቦታ አንድ ቅጅ እንዲቀመጥ፡፡ ምናልባት ከሃያ ዓመት በኋላ እንዳገኘው

    (መነሻ ሃሳብ Jokes of the Velvet Revolution)

    ኳታር፣ ዶሃ

    © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው

    እንዳለ ጌታ ከበደ

    (የ2005 ዓም የ‹በጎ ሰው› ሽልማት ተሸላሚ)

    በልቦለድ መጻሕፍቱና በፕሬስ ውጤቶች ላይ በሚያወጣቸው መጣጥፎች የምናውቀው እንዳለ ጌታ ከበደ ‹‹ማዕቀብ›. የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ እያስነበበን ነው፡፡ መጽሐፉ ስለሳንሱር፣ ስለ ደራስያንና  ስለ አሮጌ መጻሕፍት አከፋፋዮች የሚተርክ ነው፡፡

    የእንዳለ ጌታ ‹ማዕቀብ›› ለየት ያሉ ነገሮችን ያሳየናል፡፡ ሳንሱር በንጉሡ፣ በደርግና በኢሕአዴግ ዘመን ምን ጠባይ እንደነበረው፣ እነማን በሳንሱር እንደታረዱ፣ እንደተደረቱና እንደተቦጨቁ ይተርካል፡፡ ትረካው ሳንሱር ያሳቀቃቸውን ደራስያን ብቻ ሳይሆን በሳንሱር መሥሪያ ቤቱ ተቀምጠው ሳንሱር ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎችንም ትረካ ያካተተ ነው፡፡

    የሳንሱር ስም ሲጠራ እንደ ሰይጣን ስም ቆጥረውት ‹በስመ አብ› የሚሉ ደራስያን ያሉትን ያህል ‹‹ሳንሱር መኖር ነበረበት፣አሁንም መኖር አለበት›› ብለው የሚያስቡ የሳንሱር ባለሞያዎችንም አስተያየትና ሙግት ታነቡበታላችሁ፡፡ በዚህ የሳንሱር ትረካ ከዚህ በፊት ያልሰማናቸው፣ ብንሰማቸውም በተሟላ ሁኔታ ያልሰማናቸውን የሀገራችንን የደራስያን መከራዎችና ተጋድሎዎች ታነባላችሁ፡፡ ኢትዮጵያ እንዴት ታላላቅ የሃሳብና የድርሰት ሰዎቿን እንዳጣች ታያላችሁ፤ ማስፈራራት፣ ግርፋት፣ እሥር፣ አካላዊ ጥቃት፣ ስደትና ግድያ ስለተፈጸመባቸው ደራስያን እያስነበበ ወደኋላ ይዟችሁ ይነጉዳል፡፡

    ያውም የሚያወራችሁ እንዳለ ጌታ አይደለም፡፡ የሚያቀርብላችሁም ደረቅ የጥናት ጽሑፍ አይደለም፤ ራሱ ሳንሱር ነው በሰውኛ የራሱን ታሪክ የሚተርክላችሁ፡፡

    ሳንሱርን ስትሻገሩ ደግሞ የኢትዮጵያን ደራስያንን የሕይወት ገጠመኝ ይጋብዛችኋል፡፡ ከልደት እስከ ሞት በሚተርክ የሕይወት ታሪክ አጻጻፍ መንገድ አይደለም፡፡ ከታሪካቸው አንድን ሳቢ ጉዳይ መርጦ፣ አንዳንዱን ራሱ ያየውን፣ አንዳንዱን የሰማውን፣ አንዳንዱን ደግሞ ያነበበውን፡፡ አንዳንዱ አስገራሚ፣ አንዳንዱ አሳዛኝ ሌላው ደግሞ አናዳጅ ታሪክ ነው፡፡ እንዳለ ጨዋነት በተሞላበት መንገድ የደራስያኑን ክፉና ደግ ገጽታ ያሳየናል፡፡ ሱስና መጠጥ እንዴት አድርጎ የብዙዎችን ታላላቅ ደራስያን ሕይወት እንደቀጠፈ በኀዘን እናያለን፡፡ በሕይወታቸው ዘመን ታዋቂ የነበሩት ደራስያን የነበራቸውን የድህነት ሕይወት እንታዘባለን፡፡ አንዳንዶቹ በቅዱሳን ገድል ላይ የምነባቸውን የደግነት ሥራዎች  ሳናውቃቸው እንዴት ይሠሩ እንደነበር አይታችሁ ትደነቃላችሁ፡፡

    በመጨረሻው ክፍል በሀገራችን ታሪክ ታላቅ ቦታ ካላቸው ነገር ግን ምንም ቦታ ካልተሰጣቸው ወገኖች አንዱ የሆኑትን የአሮጌ መጻሕፍት አከፋፋዮች ታሪክ የያዘውን ክፍል ታገኛላችሁ፡፡ እጅግ መሳጭ ታሪክ፣ ብዙ የማናውቃቸው የሀገራችን ጉዶች፡፡

     የራስዋ የሆነ ፊደል ባላት ሀገር መጻሕፍት ፀረ አብዮት ሆነው እንዴት እንደተቃጠሉ፤ እንዴት የታሪክ መዛግብት በኪሎ እንደተሸጡ፣ ዛሬ የምንኮራባቸው የድርሰት ሀብቶቻችን እንዴት ተወግዘው ከመደርደሪያ እንደተባረሩ ይተርክልናል፡፡ ተራኪው እንዳለ አይደለም፡፡ እየዞረ ያነጋገራቸው ከአርባ ዓመት እስከ ሃያ ዓመት በአሮጌ መጻሕፍት ሽያጭ የተሠማሩ ክቡራን ናቸው፡፡

    እነማን ነበሩ እዚያ የሚመጡት? እነማንን ያደንቃሉ? ማን ምን ዓይነት መጽሐፍ ይገዛ ነበር? እነማን አንባቢ ናቸው? እነማን ደግሞ የንባብ ፀር፣ ጉዳችንን ይዘረግፉላችኋል፡፡ የታላላቅ ሰዎችን መጽሐፍ ልጆቻቸው አውጥተው የሸጡበት ታሪክ፣ በልጆቻቸው የተሸጠባቸውን መጽሐፍ አባቶች መልሰው የገዙበት ገጠመኝ፤ የታላላቅ ሰዎች ፊርማ ያረፈባቸው መጻሕፍት እንዴት ወደ አሮጌ ተራ እንደሚመጡ ያወጓችኋል፡፡ ዕውቀትን ለሕዝብ ለማከፋፈል ሲሉ አሮጌ መጻሕፍት ሻጮች የተቀበሉትን ስቃይና መከራ ይተርኩላችኋል፡፡

    እኔ እንዲያውም በአዲስ አበባ ከተማ የሚሠሩ አደባባዮች በማናውቃቸው የውጭ ኩባንያዎች ስም ከሚጠሩ ምናለ አንዱን እንኳን ‹የአሮጌ መጻሕፍት ሻጮች አደባባይ›› ብንለው ብዬ አስቤያለሁ፡፡ እነርሱ ነበሩ የመረጃ መቀባበያዎቻችን፣ እነርሱ ነበሩ የታሪክ ምንጮቻችን፣ እነርሱ ነበሩ አያሌ መጻሕፍትን ከመቃጠል አድነው ለዘመናችን ያደረሷቸው፡፡

    ዋጋው 60 ብር ብቻ ነው፡፡ ከጀመራችሁት ደግሞ ሳትጨርሱ አታቆሙትም፡፡ አንቡትና ተደሰቱ፡፡

    መልካም ንባብ

    በቤኒን በጋናና በቶጎ የሚገኙ ኢወ- ሚና(Ewe-mina) የሚባሉ ማኅበረሰቦች አሉ፡፡ በተረቶቻቸው፣ በአባባሎቻቸውና በምሳሌዎቻቸው እጅግ የታወቁ ናቸው፡፡ ከሚታወቁባቸው አባባሎች አንዱ አዳኝና አንበሳን አስመልክተው የተናገሩት አባባል ነው፡፡ ምንም እንኳን ይህ አባባል በናይጄሪያ፣ በታንዛንያና በኬንያ ማኅረሰቦችም ጭምር የሚነገር የታወቀ አፍሪካዊ ታላቅ ፍልስፍና ቢሆንም ምንጩ የኢወ ሚና ማኅረሰብ ሊሆኑ እንደሚችል ብዙዎች ገምተዋል፡፡
    ኢወ- ሚናዎች የታሪክ አጻጻፍንና የታሪክ አነጋገርን ያኄሱበት፣ እንደ ቼኑዋ አቼቤ ያሉ ታላላቅ አፍሪካውያን ደራስያንም ነጮች በአፍሪካ ታሪክ ስነዳ ላይ ያደረሱትን በደል ለመግለጥ የተጠቀሙበት ታላቁ አባባላቸው ‹‹አንበሶች የራሳቸው ታሪክ ነጋሪ እስኪኖራቸው ድረስ፣ የአደን ታሪክ ምንጊዜም አዳኙን ከፍ ከፍ እንዳደረገ ይኖራል(Until Lions have their own historians, tales of the hunt shall always glorify the Hunter) የሚለው ነው፡፡

    በኢወ- ሚና ማኅበረሰብ አደን እጅግ የሚያስመሰግን የጀግና ሥራ ነው፡፡ አዳኞች ለብዙ ቀናት ከአካባቢያቸው ርቀው ‹ታግለውና አሸምቀው› በማደን ታላላቅ አራዊትን ተሸክመው ወደ አካባቢያቸው ሲመጡ ሠፈርተኛው በእልልታና በሆታ ይቀበላቸዋል፡፡ እነርሱም አንበሳውን ወይም ዝሆኑን እንዴት እንደገደሉት፣ ያደረጉትን ትግልና የተጠቀሙበትን ድንቅ ዘዴ፣ ተአምራዊ በሆነ መልኩ እንዴት ከሞት እንዳመለጡና ያንን አንበሳ እንዴት ድል እንደነሡት ለሀገሬው ሕዝብ በኩራት ይተርካሉ፡፡
    ከአዳኙ ትረካ፣ ከያዘውም ግዳይ የተነሣ አንዳንድ ጊዜ አዳኙ ልክ አማልክታዊ ኃይል ያለው አካል መስሎ እስከመታየት ይደርስ ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ አዳኞችን የተመለከቱ ዘፈኖች፣ ግጥሞችና ተረቶች ሁሉ በአዳኞቹ ድንቅና ገናና ድርጊቶች የተሞሉ፣ ታዳኙን ንቀው አዳኙን የሚያንቆለጳጵሱ፣ የአዳኙን ግርማና ሞገስ አወድሰው ታዳኙን የሚያንኳስሱ ሆነዋል፡፡ 
    ኢወ ሚናዎች ምንም እንኳን አዳኞቹን ቢያሞግሱ፣ ቢያወድሱና በአዳኞቻቸው ገድልም ቢኮሩ፣ ምንም እንኳን አዳኞቹን ቢሸልሙና የከበሬታ ሥፍራ ቢሰጡ ነገር ግን አዳኙና ታዳኙ በጫካ ውስጥ ብቻቸውን ፊት ለፊት በተፋጠጡ ጊዜ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ በአዳኙና በታዳኙ መካከልም የተከናወነውን ነገር ሁሉ፣ አዳኙ ያደረገውን፣ የደረሰበትንና ታዳኙ የፈጸመውን ሁሉ እንዳልሰሙት ዐውቀዋል፡፡ አንበሳው የተገደለው በተኛበት ቢሆንስ? አንበሳው የታመመ አንበሳ ቢሆንስ? አዳኙ አንበሳን የገደለው በአጋጣሚ ቢሆንስ?  አንበሳው በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ከባድ ተጋድሎ አድርጎ ከሆነስ? የሚለውን ጥያቄም ጠይቀዋል፡፡
    አሁን ታዳኙ አንበሳ የለም፤ ያለው አዳኙ ብቻ ነው፡፡ የአንበሳን ወገን ገድል የሚዘክርለት የለም፡፡ እርሱ ታሪኩን የሚያወራለት፣ ተጋድሎውን የሚመሰክርለት፣ አሟሟቱ የክብርና የጀግንነት ሞት ቢሆን እንኳን ያን የሚተርክለት የለም፡፡ አሁን ታሪኩን የሚተርከው፣ ስለ አንበሳውም የሚናገረው፣ ራሱን ጀግና አንበሳውንም ፈሪ አድርጎ የሚያወራው አዳኙ ብቻ ነው፡፡ አዳኙ ስለራሱም ይናገራል፣ ስለ አንበሳውም ይናገራል፡፡ምስኪኑ አንበሳ ሁለት ጊዜ ነው የሞተው፡፡ በአካልና በታሪክ፡፡ ዘፈኑም፣ ቀረርቶውም፣ ፉከራም፣ ተረቱም፣ አዳኙን እንዲያሞግስ ያደረገው ታሪክ ነጋሪው አዳኙ ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ኢወ- ሚናዎች ታሪኩ የተሟላ የሚሆነው አዳኙም ታዳኙም ታሪካቸውን የመናገር እድል ሲኖራቸው መሆኑን ዐውቀዋል፡፡ ለዚህም ነው ‹‹አንበሶች የራሳቸው ታሪክ ነጋሪ እስኪኖራቸው ድረስ፣ የአደን ታሪክ ምንጊዜም አዳኙን ከፍ ከፍ እንዳደረገ ይኖራል›› በማለት የተናገሩት፡፡
    የአንድን ማኅበረሰብ ልዕልና ከሚያስጠብቁት፣ ነጻነቱን ከሚያስከብሩለት፣ ርእዮቱን ከሚቀርጹለት ነገሮች አንዱ የታሪክ ንግርቱ ነው፡፡ የታሪክ ንግርት የአንድን ማኅበረሰብ ሞራል ለመግደልም ሆነ ለማዳን፣ ተገዥ ሆኖ እንዲኖርም ሆነ ነጻ እንዲወጣ፣ ክብር ወይም ውርደት እንዲሰማው፣ ለራሱ የሚሰጠው ዋጋ እንዲወርድ ወይም እንዲጨምር ያደርገዋል፡፡ 
    ስምኦን ሜሳን የተባሉ በአሜሪካ ኒው ጀርሲ የሚኖሩ አፍሪካዊ ጸሐፊ ለዚህ አባባል በምሳሌነት የሚያነሡት በግብጽ የነበሩ እሥራኤላውያንን ታሪክ ነው፡፡ እሥራኤላውያን ግብጽ ውስጥ ለ400 ዓመታት ያህል ሲኖሩ ግብጻውያን በተደጋጋሚ የሚነግሯቸው ሦስት ዘውጎች ያሉት የታሪክ ትርክት ነበሯቸው፡፡ ‹‹እናንተ ሀገር አልባ የግብጽ ስደተኞች ናችሁ፣ እናንተ ነጻ አውጭ የሌላችሁ ባሪያዎች ናችሁ፣ እናንተ የከበሬታ ሥፍራ የማይገባችሁ ወራዶች ናችሁ››፡፡ እነዚህ ነገሮች የተፈጠሩት በግብጻውያን ነው፡፡ ግብጻውያኑ የአዳኙን ቦታ ይዘው ነበርና ሥልጣናቸውን ተጠቅመው የታሪክ ትርክቱን ይቆጣጠሩት ነበር፡፡ ደጋግመው የመናገር መብትም ስለነበራቸው ራሳቸውን እሥራኤላውያኑን እንኳን አሳምነዋቸው ነበር፡፡ 
    የሙሴ መነሣት በእሥራኤል ሕይወት ላይ ለውጥ ያመጣው የራሳቸው ታሪክ ነጋሪ በማግኘታቸው ነበር፡፡ እስከዛሬ ከገዥዎቻቸው፣ ከጨቋኞቻቸውና ከአስገባሪዎቻቸው ግብጻውያን ሲሰሙት ከነበረው የማንነታቸው ትርክት የተለየ፣ ለእነርሱም ሌላ ማንነትን ሊፈጥርላቸው የሚችል፣ ስላበት ሁኔታ አዲስ ግንዛቤን የሚያስጨብጥ ታሪክ ነጋሪ ተገኘ፡፡ አንድ ማኅበረሰብ እንደ ሙሴ ዓይነት ሰዎችን ሲያጣ የሚጎዳም ለዚህ ነው፡፡ ብዙ ጊዜም ገዥዎችና ጨቋኞች እንደ ሙሴ ዓይነት የታዳኙን ታሪክ ሊነግሩ የሚችሉ ሰዎች እንዳይነሡ፣ ከተነሡም እንዳይቀጥሉ የሚያደርጉትም ይህንን ስለሚያውቁ ነው፡፡ 
    የእሥራኤላውያን የማንነት ግንዛቤ ሙሴ ወደነርሱ ሲመጣ ተለወጠ፡፡ የሙሴ መምጣት የመጀመሪያወን ለውጥ ያመጣው በእሥራኤል የኑሮ ሁኔታ ላይ አይደለም፡፡ በታሪክ ንግርታቸው ላይ ነው፡፡ ሙሴ አዲስ ታሪክ ነጋሪ ሆኖ ብቅ አለ፡፡ አሁን የአዳኙን ብቻ ሳይሆን የአንበሳውን ገድል የሚተርክ የታሪክ ንግርት መጣ፡፡ ሙሴ መጀመሪያ የቀየረው ሦስቱን የትርክቱን ዘውጎች ነበር፡፡ ‹‹እናንተ ሀገር አልባዎች ስደተኞች ናችሁ፡፡›› ይሏቸው ነበር፡፡ ሙሴም ‹‹ስደተኞች አይደለንም፤ ነገር ግን በበደላችን ምክንያት የተቀጣን ነን፤ አሁን ፈጣሪ ይቅር ብሎናል፣ ከነዓን የምትባል ሀገርም ተዘጋጅታልናለች፣ ከዚህ ወጥተንም እንገባባታለን›› ብሎ ነገራቸው፡፡ የተስፋ ሀገርም ሰጣቸው፡፡ የሚጓጉላት፣ የሚሞቱላት፣ ሀገር፡፡ በአንድ ወቅት እስራኤላዊው ነጻ አውጭ ቴዎዶር ኸርዝል ‹‹እኔን የሚቆጨኝ የምኖርባት ሀገር ስለሌለኝ አይደለም፣ የምሞትላት ሀገር ስለሌለኝ እንጂ›› እንዳለው፡፡
    ‹‹እናንተ ባሪያዎች ናችሁ›› ሲሏቸው ሙሴ ግን ‹‹እናንተ የተጨቆናችሁ ጭቁኖች ናችሁ፣ ባሪያዎች አይደላችሁም፡፡ ጭቁኖች ናችሁና ከጭቆና ነጻ ትወጣላችሁ›› አላቸው፡፡ ግብጻውያኑ ‹‹እናንተ ዝቅተኛ ማኅበረሰቦች ናችሁ›› ሲሏቸው ሙሴ ግን ‹‹እናንተ የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝቦች ናችሁ፣ ራሱ እግዚአብሔርም ነጻ ያወጣችኋል›› ብሎ ነገራቸው፡፡ ሙሴ እሥራኤል የነበሩበትን ሁኔታ አይደለም የቀየረው፡፡ በግብጽ ነበሩ፣ እንደ ባሪያ ይገዙ ነበር፣ ዝቅተኛ ማኅበረሰቦችም ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሙሴ የታሪክ ትርክቱን ነው የቀየረው፡፡ ማንነታቸውን የሚያዩበትን ዓይን ነው የቀየረው፡፡ ይህንን ለመቀየር የተቻለው ታሪክ ነጋሪው ሙሴ በመሆኑ ነበር፡፡ 
    ለአንደ ማኅበረሰብ የራሱ ታሪኮች፣ ተረቶች፣ አባባሎች፣ አፋዊ ታሪኮችና ሌሎችም የሚያስፈልጉት በራሱ መንገድ የራሱን  የዓለም የሚያነጽርባቸው መሣሪያዎች ስለሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በጣልያን ድል ተደርገው የአምስት ዓመቱ የፋሺስት አገዛዝ ሲመጣ የፋሺስቶች የታሪክ ትርክትና የኢትዮጵያውያን የታሪክ ትርክት መለያየት ነው የአርበኝነት ትግሉን ያስጀመረው፡፡ ኢትጵያውያን ሽንፈቱን እንዴት ነበር ያዩት፣ አዝማሪዎቹ፣ ፎካሪዎቹ፣ የእምነት መምህሮቹ፣ ትንቢት ተናጋሪዎቹ፣ ምንድን ነበር ትርክታቸው? ይህ ሁሉ ለምን መጣብን? ለሚለው ጥያቄ የሰጡት መልስ ምን ነበር?
    ገለል በሉና ገለል አርጓቸው
    ወደመጡበት ወዳገራቸው
    ለነዚህ ጣልያኖች መድኃኒት ስጧቸው
    የሚያስቀምጥ ሳይሆን የሚያስመልሳቸው
    አርኩም ይሄድና ሶልዲውም ያልቅና
     ያስተዛዝበናል ይኼ ቀን ያልፍና
    የሚሉትና ሌሎችም የሕዝቡ ትርክቶች የጣልያንን መመለስ፣ በኢትዮጵያ ምድር ለዘለዓለም ለመቆየት እንደ ማይችል የሚገልጡ ነበሩ፡፡ ይኼ ትርክት ‹ነጭን ማሸነፍ አይቻልም፣ አሜን ብላችሁ ለጣልያን ተገዙ› እያሉ ይለፍፉ በነበሩት የጣልያን ፕሮፓጋንዲስቶች ሕዝቡ እንዳይዋጥ አድርጎታል፡፡ ምንም እንኳን የእነዚህ ታሪክ ነጋሪዎች ትርክት በወቅቲ ነባራዊውን ሁኔታ ባይቀይረውም፣ ነባራዊውን ሁኔታ ለመቀየር እንዲቻል ግን የአርበኞችን የመመልከቻ መነጽር ቀይሮታል፡፡ ታሪክ ነጋሪዎቹ ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ክፉ ዘመናት እያነሡ፣ እነዚህን ክፉ ዘመናት እንዴት እንደተሻገረች እየተረኩ፣ ይህም ሊያልፍ የሚችል እንጂ ነዋሪ አለመሆኑን ይገልጡ ነበር፡፡ ኢጣልያ በየቦታው ያደረገችውን ጦርነት በራስዋ ሚዲያና ፕሮፓጋንዲስቶች በኩል በመለፈፍ የሕዝቡን ቅስም ለመስበርና ሁሉም ነገር አልቋል ብሎ እንዲቀመጥ ለማድረግ ሞክራ ነበር፡፡ ታሪኩ የአዳኞችን ብቻ እንዲገልጥ ጥረት አድርጋም ነበር፡፡ አንዳንድ አርበኞች ሲያዙ፣ በአደባባይ ሲገደሉ፣ አንዳንድ ባንዶች እጃቸውን ሲሰጡ፣ ስለ ጣልያን ታላቅነትና ደግነትም ሲመሰክሩ ሕዝቡ የአዳኞቹን ብቻ ገድል እንዲሰማ ተሞክሮ ነበር፡፡
    ነገር ግን አልሆነም፡፡ በወሬውም፣ በተረቱም፣ በዘፈኑም፣ በቀረርቶውም፣ በፉከራም፣ በባሕታውያኑም፣ በልቅሶ ሙሾም፣ በወፍጮ ፈጭውም፣ በውኃ ወራጁም ግጥም ውስጥ የጀግኖቹ ስምና ዝና፣ ገድልና ታሪክ እየተነሣ ከሀገር ሀገር ተዛመተ፡፡ የታሪክ ትርክቱ በሕዝቡ እጅ መሆን፣ የተማረኩትንና የተገደሉትንም ቢሆን እንደ ተሸናፊ፣ እንደ ድል ተነሺ ሳይሆን እንደ ሰማዕታትና እንደ ጀግና እንዲታዩ አደረጋቸው፡፡
    ዐፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ በእንግሊዞች ተከብበው፣ በመጨረሻ ራሳቸውን በሽጉጣቸው አጠፉ፡፡ እንግሊዞች ድል አድራጊዎችና ማራኪዎች ሆነው፣ ዐፄ ቴዎድሮሰ ድል ተነሺና ተማራኪ ሆነው ነገሩ ተጠናቀቀ፡፡ ይህንን ነገር ኢትዮጵያውያን እንዴት ነው የተረኩት? ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ታሪክ የማንጽፍ፣ የራሳችንን ታሪክም የማንተርክ ቢሆን ኖሮ አሁን የምናውቃቸውንንና የጀግና ምሳሌ ያደረግናቸውን ዐፄ ቴዎድሮስን ልናገኛቸው ባልቻልን ነበር፡፡ አንዳንድ የታሪክ ሰዎች እንዲያውም ‹‹ሕዝቡ የሚያውቃቸው ቴዎድሮስና ታሪካዊው ቴዎድሮስ ይለያያሉ››  እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ሕዝቡ የአዳኞችን ትረካ እንደማይስማማበት የገለጠው ወዲያው በጦርነቱ ጊዜ መሆኑን የምንረዳው
    ገደልንም እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው
    ማረክንም እንዳይሉ ሰው የለም በጃቸው
    ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው
    ለወሬ አይመቹም ተንኮለኞች ናቸው
    በማለት መግጠሙን ስናይ ነው፡፡

     

    የዐድዋ ጦርነት በኢትዮጵያውያን አሸናፊነት በተጠናቀቀ ጊዜ በአፍሪካ በቅኝ ገዥነት የተሠማሩት አውሮፓውያን ትልቁ ሩጫቸው ዜናው በኢትዮጵያውያን መንፈስ እንዳይሰማ ማድረግ ነበር፡፡ ቢቻል ፈጽሞ ዜናው እንዳይደርስ፣ ካልሆነም ደግሞ የኢትዮጵያውያንን የአሸናፊነት መንፈስ በጠበቀ መንገድ እንዳይሰማ፣ እንዲሁ ተራና መናኛ ዜና ሆኖ እንዲቀር ማድረግ፡፡ የዐድዋ ጦርነት ቅኝ ገዥዎች ለአፍሪካውያን ሲተርኳቸው የኖሩትን ሦስት ትርክቶች ያፈረሰ ጦርነት ነበር፡፡ ‹‹ነጭን ጥቁር አያሸንፍም፣ አሸንፎም አያውቅም፡፡ ጥቁሮች እንዲገዙ፣ ነጮች እንዲገዙ የአምላክ ትእዛዝ ነው፤ አፍሪካ ታሪክ የላትም፣ ታሪኳ የቅኝ ግዛት ታሪክ ነው›› ፡፡
    የዐድዋ ጦርነት እነዚህ ሦስቱን መሠረታውያን የቅኝ ግዛት ትርክቶች አፈረሰ፡፡ ነጭን ጥቁር ሕዝብ አሸነፈ፡፡ በአስደናቂ ሁኔታ በአንድ ቀን ጦርነት አሸነፈ፤ ነጮች ተማረኩ፡፡ ነጮች ጥቁሮችን እንዲገዙ ከእግዚአብሔር የተፈቀደ ነው፤ ለነጮች አለመገዛት የፈጣሪን ትእዛዝ አለማክበር ነው ይባሉ ነበር፡፡ አሁን ግን ኢትዮጵያውያን ታቦት ይዘው ወጥተው፣ ስመ እግዚአብሔር ጠርተው፣ ያውም በዕለተ ጊዮርጊስ፣ ቀሳውስቱና ደባትሩም አብረው ዘምተው ጣልያንን ድል አደረጉ፤ የኢትዮጵያ አምላክ ለነጭ ታዘዙ የሚል አምላክ አለመሆኑን አሳዩ፤ ኢትዮጵያውያን ነጭ ቅኝ ገዥዎችን ድል ሲያደርጉ የተቆጣ፣ የቀሰፈ አምላክ አልታየም፡፡እንዲያውም አብሮ ተዋጋ፡፡ የራስዋ ታሪክ ያላት፣ ሉዓላዊነቷን ጠብቃ የኖረች፣ ለማንም ያልተንበረከከች አንዲት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር መኖሯም ታወቀ፡፡ ጥቁርም ታሪክ አለው፡፡ ከቅኝ ገዥዎችም በፊት ታሪክ ነበር የሚለው ታወቀ፡፡
    የዐድዋ ጦርነት እነዚህን ሦስት ትርክቶች ሻረ፡፡ ይህን ነው ቅኝ ገዥዎች ከአፍሪካውያን ሊሠውሩት የሞከሩት፡፡ ይህ የአድዋ ጦርነት በአፍሪካውያን ዘንድ ሲሰማ የፀረ ቅኝ ግዛት ስሜትን ቀስቅሶ ነበር፣ እኛ የምናምነው በኢትዮጵያ አምላክ ነው የሚሉ ኃይሎችን አስነሥቶ ነበር፡፡ 
    የአንድን ሕዝብ ማንነት፣ መንገድና መዳረሻ ለመወሰን ዋነኛው መሣሪያ የዚያን ሕዝብ ትርክት መቀየር ነው፡፡ ስለራሱ፣ ስለ ማንነቱ፣ ስለ ታሪኩ፣ ስለ ጀግኖቹ፣ ስለ እሴቶቹ፣ ስለ ክብሩና ዝናው፣ ስለ ጀብዱውና የት መጣው የሚተርከውን ነገር መቀየር፡፡ የአንድ ማኅበረሰብ ማነነት፣ እምነት፣ አቋምና ስለ ነገሮች የሚኖረው ምላሽ ከትርክቶቹ የሚሠራ ነው፡፡ እኛ የታሪክ፣ የተረት፣ የአባባል፣ የአፈ ታሪክ፣ የእምነት ትምህርት፣ የቀረርቶ፣ የሽለላ፣ የሙሾ፣ የዘፈን ትርክቶች ውጤቶች ነን፡፡ ከምግብ ንጥረ ነገሮች በላይ በእነዚህ ንጥረ ነገሮች ተገንብተናል፡፡ እነዚህን በቀየርን ቁጥር አብሮ ሰብእናም ይቀየራል፡፡
    ጣልያኖች አዲስ አበባ እንደገቡ ታዋቂ አዝማሪዎችን ካዛንቺስ መሸታ ቤት እየጠሩ፣ ራቁቷን ያለች ሴት ሥዕል አቁመው ለፀጉሯ፣ ለዓይኗ፣ ለጥርሷ፣ ለአንገቷ፣ ለደረቷ፣ ለወገቧ፣ ለሽንጧ፣ ለዳሌዋ፣ ለባቷ ፣ እንዲዘፍኑ ያደርጓቸው ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ስለ ሴት ልጅ ውበት የሚገልጡበት የራሳቸው ነባር ትርክት ጠፍቶ አውሮፓዊ በሆነውና ውጫዊ አካልን ብቻ በሚያሞግሰው ሌላ ትርክት እንዲተካ አደረጉት፡፡ ከዚያም የዘፈኖቻችንን ባህል፣ እኛም ስለ ሴቶቻችን የሚኖረንን እሳቤ አውሮፓዊ ርእዮት ሰጡት፡፡
    የዘመናችን ሚዲያዎችና የፕሮፓጋንዳ መሣሪያዎች ትልቁ ሚናቸው የተራኪነቱን ሚና መውሰድ ነው፡፡ ተራኪነቱን የወሰደ ታሪኩን ይወስነዋል፡፡ ማን ጀግና እንደሆነ፣ ማን ድል እንዳደረገ፣ ማን ታሪክ እንደሠራ፣ ማን እንዳደገ፣ ማን እንደታገለ፣ ማን ታላቅ እንደሆነ፣ ማን እንደሠለጠነ፣ ማን ነጻ እንዳወጣ፣ የሚወስነው ታሪክ ነጋሪው ነው፡፡ የአደን ታሪክ ምን ጊዜም አዳኙን ይከተላልና፡፡ ማንዴላ ለአፓርታይድ ነጮች አሸባሪ፣ ወንጀለኛ፣ ሀገሩን የካደ፣ የዕድሜ ልክ እሥራት የሚገባው አረመኔ ነው፡፡ ማንዴላ ለጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ነጻ አውጭ፣ ታጋይ፣ ጀግና፣ ለሀገሩ የሚሞት፣ የነጻት አባት፣ ቆራጥ፣ ደቡብ አፍሪካዊ ነው፡፡ የሁለቱም ሰው ግን ማንዴላ ነው፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ለፋሺስቶች ወንበዴና ሞት የሚገባቸው ወንጀለኛ ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ቆራጥ፣ የጀግኖች ኮከብ፣ የጽናት ተምሳሌት፣ የእምነት አባቶች አርአያ የሆኑ ጀግና ናቸው፡፡ ታሪኩ የተወሰደበት – ጀግናውን ያጣል፣ አርአያውን ይነጠቃል፣ አይከኑ ይሰበርበታል፣ ኩራቱ ይወሰድበታል፤ ሌላ ማንነትም ይሰጠዋል፡፡ እርሱ ከብት ቢኖረውም አፍ ያለው ከብቱን ይወስንለታል፡፡ ታሪክም አንበሳውን ትቶ አዳኙን ብቻ እንዳገነነ ይቀጥላል፡፡ አንበሳው ነጋሪ የለውምና፡፡
    ኳታር    

    © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ወጥቶ ነበር

    አንዳንዱን ሰው ለምስክርነት ይፈጥረዋል፡: ደግ ሰው ጠፋ እንዳይባል፡: እርሱን የለህም እንዳንለው፣ ዓለምም ‹ጨልጦ ገርኝቶ› እንዳይጠፋ፡፡ እንዲህ ያለውም ሰው እንደ ሄሊኮሜት በዘመናት አንድ ጊዜ ብቻ ይገለጣል መሰል፡፡ መገለጡንም ብዙዎች ሳያውቁት ያልፍባቸዋል፡፡ ያወቁ ደግሞ ይጠቀማሉ፡፡
    በዚህ በኛ ዘመን እንዲህ ያሉ ሰዎች ተገልጠው ነበረ ቢባል ለአብነት ከምንጠራቸው አንዷ እማሆይ ባቄላ ናቸው፡፡ ስማቸውን ማንም አያውቀውም፡፡ ግብራቸው ግን ሌላ ስም አምጥቶላቸዋል፡፡‹ እስመ ስሙ ይምርሖ ኀበ ግብሩ› ነበር የሚለው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ‹እስመ ግብሩ ይመርሖ ኀበ ስሙ› እንዲል የሚያደርጉት ሰዎችም አሉ፡፡ እንደ እማሆይ ባቄላ፡፡ 

    ትግራይ ከሰላ አካባቢ መወለዳቸው የሚነገርላቸው እማሆይ ባቄላ ደሴ ከተማ የገቡት በ1963 ዓም አካባቢ መሆኑ ይነገራል፡፡ ከዚህ ያለፈ ታሪካቸውን የሚያውቅ የለም፡፡ ለእርሳቸው መልካም ሥራ እንጂ ትውልድና ዘር ትርጉም አልነበራቸውምና፡፡ የእናታቸው ስም አመተ እግዚእ፣ የአባታቸውም ስም ገብረ ትንሣኤ መሆኑ የታወቀው እንኳን በየወሩ በ29 ቀን የወላጆቻቸውን ስም በደሴ መድኃኔዓለም በጸሎት እንዲታሰብ ያደርጉ ስለነበር፣ ይህንንም ደጉ ካህን መጋ ብሉይ አባ ዮሴፍ ስላስታወሱት ነው፡፡
    ደግሞም መሥራት እንጂ ማውራት አይችሉበትም፡፡ በአንድ ወቅት የቤተ ክህነቱ ነቅዐ ጥበብ መጽሔት ጋዜጠኛ ታሪካቸውን እንዲያወጉት ቢጠይቃቸው ‹‹እኔ ለአርአያነት የሚያበቃ ሥራ የለኝም፤ ለምነሽ እንጂ ተናግረሽ ኑሪ አልተባልኩም›› ነበር ያሉት፡፡
    አባ ዮሴፍ እንደሚተርኩት እማሆይ በልጅነታቸው ለአንድ የአካባቢው ባላባት ይዳራሉ፡፡ እርሳቸው ግን ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ፈጣሪን አክባሪና የእምነት ሰው ነበሩና ‹‹እኔ ወደምመራሽ ቦታ ሂጂ› የሚል ቃል ከሰማይ ይመጣላቸዋል፡፡ እማሆይም ቃሉን አክብረው እንደ ገብረ ክርስቶስ ከትውልድ ቀያቸው ይጠፋሉ፡፡ ከዚያም መቀሌ አቡነ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ገብተው አገልግሎታቸውን ይጀምራሉ፡፡
     
    እን ስምዖን ጫማ ሰፊው ያደርጉት እንደነበረው ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን፣ አስታማሚ ያጡትን፣ በችግር የተቆራመዱትን፣ በመንገድ የደከሙትን ለምኖ መርዳት ሆነ ሥራቸው፡፡ እነርሱን ለመርዳት ሲሉ ዞረው ይለምናሉ፤ የለመኑትንም ለራሳቸው አንዳች ሳያስቀሩ እየዞሩ በየድኾቹ ቤት ያከፋፍላሉ፡፡ አረጋውያንን ይጦራሉ፤ ሕሙማንንም ያስታምማሉ፡፡ ይህን እያገለገሉ ነበር መቀሌ ላይ የተቀመጡት፡፡ 
     
    በዚህ አገልግሎት ላይ እያሉ ፊታቸውን ወደ ግሼን ማርያም እንዲያዞሩ መንፈስ አነሣሣቸው፡፡ ተነሥተውም ግሼንን ሊሳለሙ መጡ፡፡ ከዚያም በሰኔ 1963 ዓም ወደ ደሴ ገብተው ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተቀመጡ፡፡ ከደሴ መድኃኔዓለም የለያቸው የሥጋ ሞት ብቻ ነው፡፡ 
     
    እማሆይ ደሴ ላይ የመቀሌውን በጎ ምግባር ቀጠሉበት፡፡ ችግረኞችን ይሰበስባሉ፣ መታከሚያ ያጡትን ለምነው ያሳክማሉ፤ በየቤታቸው ወድቀው ሰው አላያቸው ያሉትን ለምነው ያለብሳሉ፣ ያጎርሳሉ፤ የወደቁትን አንሥተው ለክብር ያበቃሉ፤ መንገደኞችን አሳድረው ይሸኛሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ አልፈው ደግሞ ባቄላ ቀቅለው ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም በር ላይ ቆመው ‹ስለ መድኃኔዓለም‹ እያሉ ያድላሉ፡፡ ለዚህም ነበር ሕዝቡ ‹እማሆይ ባቄላ› ያላቸው፡፡
    በ1977 ዓም በተከሰተው ረሃብ ጊዜ  ባቄላ ለምነው በመቀቀል፣ እህል ለምነው ጠላ በመጥመቅ  አያሌ ረሃብተኞችን ታድገዋቸዋል፡፡ ያን ጊዜ እንኳን ረሃብተኞቹ ምግብ ያልጠፋባቸው ሳይቀሩ የእርሳቸውን በረከት እንካፈል እያሉ ተሰልፈው ንፍሮ ይቀበሉ ነበር ይባላል፡፡ እማሆይ እንዲህ ሀገር ያወቀውን ችግር ቀርቶ ሰው ያልደረሰለትንም ቀድመው የሚደርሱ ነበሩ፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ሰው ከግሼን ሲመለስ ከመኪና ወድቆ አደጋ ይደርስበትና ሰውነቱ ይበላሻል፤ እዳሪውንም መቆጣጠር ያቅተዋል፡፡ ሰው ሁሉም ይጸየፈዋል፡፡ እማሆይ ግን አልተጸየፉትም፡፡ ቤታቸው ወስደው፣ ሰውነቱን እያጠቡ፣ አልጋ ላይ ሲጸዳዳ እየጠረጉ፣ ልብሱን በየቀኑ እያጠቡ፣ ሰው ለምነው አብልተው፣ አምላክን ለምነው አዳኑት፡፡ ሰውየውም ድኖ መርቋቸው ሄደ ይባላል፡፡ 
     
    በሌላ ጊዘ ደግሞ አንድ ሰው ገደል ወድቆ ሰውነቱ ከጥቅም ውጭ ይሆናል፡፤ ሆስፒታል ተኝቶ ታክሞም መዳን ይሳነዋል፡፡ የሕክምናው ወጭም ከባድ ይሆንበታል፡፡ ከሐኪም ቤት ሲወጣም መውደቂያ ያጣል፡፡ እማሆይ ይሄንን ሰው ቤታቸው ወሰዱት፡፡ እናት ለልጇ፣ ባልም ለሚስቱ ከሚያደርገው በላይ አድርገው አስታመሙት፡፡ ሰውዬው ከዐሥር ዓመት በላይ እማሆይ ቤት ተኛ፡፡ እርሳቸውም ሳይጸየፉና ሳይመረሩ አስታመሙት፡፡ በመጨረሻ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ በወግ በመዓርግ እንዲቀበር አደረጉት፡፡
     
    አባ ዮሴፍ እማሆይ ባቄላን በተመለከተ በዓይናቸው ያዩት በጆሯቸው የሰሙት ብዙ ታሪክ አላቸው፡፡ እማሆይ ለአገልግሎት ሌትና ቀንን አይመርጡም፡፡ ሌሊት ጅቦች እንደ ሠራዊት አጅበዋቸው ሲንቀሳቀሱ አውቃለሁ ይላሉ፡፡ ይህንን ጸጋቸውን የተረዳው የደሴ ሕዝብም እጁን ያለ ማመንታት ይዘረጋላቸዋል፡፡ ‹ስለ መድኅኑ›› እያሉት እንኳን ክርስቲያኑ ሌላው አያልፋቸውም፡፡ 
     
    እርሳቸው አስቦ የማይሰጠውን ደካማ ለምነው ተቀብለው ለማጽደቅ የመጡ ናቸው፡፡ ግዴታቸውን ያልተወጡትን ግዴታቸውን ይወጡ ዘንድ ለማሳሰብ የተሰጡ ናቸው፡፡ ለምነው ድኻ ይረዳሉ፣ ሕሙማንን ያስታምማሉ፣ ለምነው ባቄላ ቀቅለው ያበላሉ፤ ለምነው የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን ያሠራሉ፡፡ ለምነው የግሼን፣ የላሊበላና የአኩስም መንገደኛን ያስተናግዳሉ፣ ይሸኛሉ፡፡ ደላንታ ውስጥ ለተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት ከ60ሺ ብር በላይ ለምነው ሰጥተዋል፡፡ ደሴ የሚገኘውን ደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴን ቤተ ክርስቲያን ከቤተልሔሙ እስከ ቤተ ክርስቲያኑ የግቢ በር ያለውን ንጣፍ አስነጥፈዋል፡፡
     
    እማሆይ ለምነው መርዳት፣ ለምነው ማልበስ፣ ለምነውም ማስታመም ጸጋቸው ነበርና ይህንን አገልግሎት ያለመታከትና ያለማጉረምረም ይፈጽሙት ነበር፡፡ 
     
    አንድ ቀን ግን እንዲህ ሆነ፡፡
    አንድ የሚያውቁት ሰው መኪና እያሽከረከረ ያዩታል፡፡ ይህ ሰው ቢሰጣቸው የሚረዷቸውን ድኾች፣ የሚያስታምሟቸውን በሽተኞች፣ የሚያለብሷቸውን ዕሩቃን፣ የሚመግቧቸውን ርኁባን እያስታወሱ ወደ ሰውዬው በፍጥነት ገሠገሡ፡፡ እርሱ ግን አላያቸውም፡፡ መኪናውን ዘወር ሲያደርግ እማሆይን ገጫቸው፡፡ እማሆይ መሬት ላይ ተዘረሩ፡፡ በየትኛው ዐቅም ያንን ግጭት ይቋቋሙታል፡፡ ሕዝብ ደነገጠ፡፡ ማንም ልቡ አልቀረለትም፡፡ ወደ ልቡ የተመለሰው ይዟቸው ወደ ሆስፒታል ሮጠ፡፡ 

    እኒያ ለማገልገል ሮጠው የማይሰለቹት እናት አልጋ ላይ ዋሉ፡፡ ‹‹የእኔ ጸሎት ጥሬና ብስል ነው›› ቢሉም ተኝተውም ለሀገራቸውና ለወገናቸው መጸለይን ለአፍታ እንኳን አላቆሙም ነበር፡፡ በዚህ ሕይወትም እያሉ ታኅሣሥ 21 ለ22 አጥቢያ በ2000 ዓም ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች፡፡ ሲገንዟቸው ሰውነታቸው በመስቀል የተከበበ እንደነበር፤ በደረታቸው ላይም ትልቅ መስቀል ማግኘታቸውን አባ ዮሴፍ ይናገራሉ፡፡ 
     
    ደሴም በዘመናችን ብቅ ካሉት ቅዱሳን አንዷን በልቅሶና በጸሎት ሸኘች፡፡ በየአካባቢያችን ግን ለዓይነት አይጠፉም፡፡ እርሱ ሀገርን ያለ አንድ ጻድቅ አይተዋትምና፡፡ 
         
    ምንጭ
    የዓይን ምስክሮችና መዘክር(ለደሴ መድኃኔዓለም 100ኛ ዓመት የተዘጋጀ) መጽሔት


    የአምናው ተሸላሚ የመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ድርጅት መሥራች አቶ ብንያም

    የዓመቱ በጎ ሰዎችን እንድንጠቁም በወጣው ማስታወቂያ መሠረት እስካሁን 43 በጎ ሰዎች ተጠቁመዋል፤ አሁንም ጊዜ አለን፡፡ እንጠቁም፣ መልካም ሰዎችን መሸለም ክፉዎችን ማስተማር ነው፤ መልካም ሰዎችን መሸለም ጀግኖችን መፍጠር ነው፤ መልካም ሰዎችን መሸለም ለልጆቻችን አርአያ መፍጠር ነው፡፡

    ለሀገራቸው፣ ለወገናቸው፣ ለአካባቢያቸው መልካም ሠርተዋል፣ ዕውቅና ልንሰጣቸው፣ ልናከብራቸውና ልናበረታታቸው ይገባል የምትሏቸውን  በሚከተለው መመዘኛ መሠረት በተጠቀሰው የኢሜይል አድራሻ ይጠቁሙ፡፡

    መመዘኛውን እዚህ ያንብቡ(click here
    )
    የመጠቆሚያ አድራሻ

    በድምጽና ምስል ለመከታተል እዚህ ይጫኑ

    አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር በዋናው በር በኩል ወደ አውራ ጎዳናው ይወጣል፡፡ ጥቂት እንደተጓዘ ደግሞ እዚያ አካባቢ ቆመው አላፊ አግዳሚውን ከሚላከፉ ጎረምሶች ጋር ይጨቃጨቃል፡፡ ጭቅጭቁ በምን እንደተጀመረ ማናችንም አላወቅንም፡፡ እነዚያ ጎረምሶች ግን በመምህሩ ላይ ‹ሙድ› ይዘውበታል፡፡ ‹እሺ – – ሊቁ› እያሉ በስድብ ጠረባ ይረፈርፉታል፡፡ እርሱ ደግሞ ስድቡን አልቻለበትም፡፡ ‹‹ያልተማራችሁ፣ ማይሞች፣ ከስድብ በቀር ሌላ የማታውቁ፣ ደደቦች›› ይላል ሥሩ እስኪገታተር ድረስ በቁጣ፡፡ በትከሻው ያንጠለጠለው ቦርሳ ይወዘወዛል፣ መነጽሩም ልውደቅ ልውደቅ ይላል፡፡
    ‹‹እሺ ሊቁ፣ ለምን ላፕቶፕሺን ከፍተሺ ዕውቀት አትጭኝብንም›› እያሉ ጎረምሶቹ ይሳሳቁበታል፡፡እርሱ ይበግናል፡፡ ‹ኤፍ ብቻ ነው እንዴ ቦርሳሽ ውስጥ የያዝሺው፤ በናትሺ አንድ አምስት ኤ የለሽም›› ይሉታል፡፡ እርሱ ይንዘፈዘፋል፡፡ ‹‹አንድ ሁለት ኤ ብትሰጭን ቸብ አርገን በርጫ እንገዛበት ነበር›› ይሉታል፡፡ ሰው እየተሰበሰበ፣ እየከበበው ይሄድና የጎረምሶቹን ስድብ እንደመዝናኛ ቆጥሮት አብሯቸው ይሳሳቃል፡፡ እርሱን ኮሜዲ ፊልም እንደሚሠራ ተዋናይ ቆጥረውት በነጻ ይኮመኩማሉ፡፡ ጎረምሶቹ አንድ ተረብ በወረወሩ ቁጥር ከብቦ የተሰበሰበው ‹አስገቡለት› እያለ እንደ ጎጃም ልቅሶ ያጅባቸዋል፡፡ 

     እየቆየ ከበባው እየሰፋ፣ ሳቁ እየደራ፣ የመምህሩ ንዴት ወደ እሳተ ገሞራነት እየተቀየረ ሄደ፡፡ መምህሩ ከዚያ ከበባ ልውጣ ቢል እንኳን ሰው በጎረምሶቹ ተረብ ስለተዝናና በቀላሉ የሚያስወጡት አይመስልም፡፡ የተከፈለው አዝማሪ መስሏል፡፡ የሚያውቃቸው ስድቦች አልቀውበት አሁን ጣቱን ማውጣትና ‹‹አሳይሃለሁ›› እያለ መዛት ጀምሯል፡፡ የአንዳንድ የእንግሊዝኛ ስድቦችን ሲሳደብም
    የኛ ሙሽራ ኩሪባቸው
    በእንግሊዝ አናግሪያቸው›› ብለው ሳቁበት፡፡ በልቡ አንዳች የፖሊስ ኃይል መጥቶ እንዲገላግለው እየተመኘ ነበር፡፡ ወደ ስድቡ ሜዳ አስቦ ስላልገባ አስቦ ሊወጣ አልቻለም፡፡
    በዚህ መካከል በግራ እጃቸው ጋዜጣ አጣጥፈው የያዙ አንድ አዛውንት ሁላችንንም እየገፈተሩ፣ እንደ ሙሴ የሕዝቡን ባሕር ለሁለት እየከፈሉ ወደ መካከል መጡና ያንን መምህር እጁን ይዘው በዝምታ ጎትተው ከከበባው አወጡት፤ ጎረምሶቹም ‹ሼባው ልቀቀው እንጂ›› እያሉ ተረቧቸው፡፡ እርሳቸው ቀናም አላሉ፣ መልስም አልሰጡ፡፡ እየሰነጠቁ እንደገቡ፣ እየሰነጠቁ ወጡ፡፡
    ከዚያም ወደ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን መታጠፊያ ዘወር አደረጉትና ‹‹ለምን ልጄ፣ ለምን?›› አሉት፡፡
    ‹‹ከዩኒቨርሲቲ ስወጣ ለከፉኝ፣ እኔም መልስ ሰጠኋቸው››
    ‹‹ተማሪ ነህ?››
    ‹‹የዩኒቨርሲቲ መምህር ነኝ››
    ‹‹እና መምህር ሆነህ ነው ከእነርሱ ጋር ስድብ የገጠምከው፤ ጥፋተኛው አንተ ነህ›› አሉት፡፡ እኛ ትንሽ ራቅ ብለን የሚሉትን መስማት ጀመርን፡፡
    ‹‹ተመልከት እዚያ›› አሉት በአመልካች ጣታቸው ወደ አንበሳ ግቢ አቅጣጫ እያመለከቱ፡፡ ‹‹እዚያ ግቢ ውስጥ ምን አለ?›› አሉና ጠየቁት፡፡
    ‹‹አንበሳ ነዋ››
    ‹‹አንበሳ ግን መኖሪያው ግቢ ውስጥ ነው እንዴ?››
    ‹‹አንበሳማ የዱር እንስሳኮ ነው፤ ምን ዓይነት ጥያቄ ነው የሚጠይቁኝ፤ የዩኒቨርሲቲ መምህር ነኝ እያልኩዎ›› መምህሩ ተናደደና ጥሏቸው ሊሄድ ከጀለ፡፡ እርሳቸውም ከእናቱ ጋር መንገድ እንደሚሻገር ሕጻን እጁን አጥብቀው ያዙት፡፡ ‹‹ወዳጂ፣ ሰው በሁሉም ነገር ሊቅ አይሆንም፡፡ በአንዱ ሊቅ ሲሆን በሌላው ማይም ነው፤ በአንዱ መምህር ሲሆን በሌላው ተማሪ ነው፤ በአንዱ ጎበዝ የሆነ ለሌላው ሰነፍ ነው›› አሉት፡፡ ትንሽ ቀዝቀዝ አለ፡፡
    ‹‹አንበሳው በገዛ ጫካው ውስጥ ቢሆን ኖሮ ማን ይደፍረው ነበር? ማን ጀግና ነበር ሃምሳ ሳንቲም ከፍሎ በሃምሳ ሜትር ርቀት የሚያየው? ማን ጀግና ነበር ቀርቦ ፎቶ የሚያነሣው? ማን ጀግና ነበር ከአንበሳው ጋር ፎቶ ሲነሣ የሚውለው? ጫካው የእርሱ ክልል ነው፤ የእርሱ ሠገነት ነው፡፡ እዚያ የቀለበቱ ጌታ (Lord of the Ring) እርሱ ነው፡፡ ከተማው ግን የአንበሳ መደብ አይደለም፣ እርሱ ለከተማ አልተፈጠረም፣ ከተማውን አይችልበትም፤ በግቢ ውስጥ መኖር፣ በአጥር መከለል፣ ከአንበሳው ተፈጥሮ ውጭ ነው፡፡ ስለዚህ ከሚያውቀው ወደማያውቀው፣ ከሠገነቱ ወደ ባርነቱ፣ ከሚያሸንፍበት ወደሚሸነፍበት፣ ከሚችልበት ወደማይችልበት፣ አወደርነውና፤ በከተማ፣ ግቢ ውስጥ አሥረን እንደልባቸውን እንጫወትበታለን፡፡ አሁን የሚፈልገውን አድኖ ሳይሆን የምንሰጠውን ይበላል፣ በፈለገው ሰዓት ሳይሆን በሰጠነው ሰዓት ይመገባል፣ ወደፈለገው ቦታ ሳይሆን ወደፈለግነው ቦታ ይሄዳል፣ የፈለገውን ሳይሆን የፈቀድንለትን ብቻ ያያል፡፡ ለምን? ወደኛ ሜዳ አውርደንዋላ፣ ሜዳውን ትቶ መጥቷላ፤››
    ዝም አሉና ቀና ብለው አዩት፡፡ ቦርሳውን ወደ ላይ ገፋ ገፋ እያደረገ ይመለከታቸዋል፡፡ እኛም መጨረሻውን ለማወቅ ጓጉተን አፍጠን እናያቸዋለን፡፡ ስድብና ድብድብ ለማየት ተሰብስቦ የነበረው ሰውም ነገሩ ዕውቀትና ቁም ነገር ሲሆንበት ጊዜ ቀስ በቀስ ‹‹ሼባው ነገሩን ትምሮ አደረጉት›› እያለ ከአካባቢው ሸሸ፡፡ ‹‹የሚቧቀሱ መስሎኝ ነበር፤ ሼባው አበላሸው፡፡ ስድድቡ ተመችቶኝ ነበር ›› እያሉ በቁጭት ጥለዋቸው ሄዱ፡፡
    ‹‹አንተም እንደ አንበሳው ሆንክ›› አሉ ሽማግሌው፡፡ ወረድክ ከመደብህ፣ ከምትችለው የዕውቀት ክርክር ሜዳ፣ ከምታሸንፍበት የሃሳብ ክርክር ሜዳ፣ ከለመድከው የጥናት ክርክር ሜዳ፣ ወረድክላቸው፡፡ ጎበዞች ናቸው ደግሞ አድንቃቸው፡፡ አወረዱህና በሚችሉት ሜዳ ላይ በደንብ አድርገው ቀጠቀጡህ፡፡ አንተም ሞኝ ነህ በማታውቀው ሜዳ ላይ ትግል ገጠምክ፡፡
    ‹‹ሶምሶን ከፍልስጤማውያን ዐቅም በላይ ሲሆንባቸው፡፡ ፍልስጤማውያን ምን አደረጉ? በደሊላ በኩል ሶምሶን ወደማይችለው እነርሱ ግን ወደሚችሉት ሜዳ አወረዱት፡፡ በሚችሉት ሜዳ አውርደው ደኅና አድርገው ቀጥቅጠው ያንን ኃያል ሰው ወፍጮ ፈጭ አደረጉት፡፡
    ‹‹ብልጥ ከሆንክ አትውረድ፣ ጀግና ከሆንክ የወረዱትን አውጣቸው፡፡አሁን አሁን ብዙ ሰው በዚህ እየተሸነፈብን ነው፡፡ እስኪ ጋዜጣውን፣ መጽሔቱን፣ ፌስ ቡኩን፣ ሰልፉን፣ የፖለቲካ ክርክሩንም ተመልከተው፡፡ ብዙዎቹ ከሜዳቸው ወርደዋል፡፡ ብልጦቹ ከፍ ወዳለው ሃሳብ፣ ዕውቀት ወደሚጠይቀው ክርክር፣ በመረጃና በማስረጃ ወደሚደረገው ውይይት፣ ላቅ ወዳለ ትግል፣ ወደ ልዕልናና ወደ ሠለጠነ አስተሳሰብ ማደግ እንደማይችሉ ያውቁታል፡፡ በዕውቀትና በሃሳብ ክርክር፣ በሠለጠነና ደርዝ ባለው ትግል፤ ማንበብን፣ ማወቅን፣ መመራመርን፣ በሚጠይቅ መሥመር መጓዝ፣ ተጉዘውም ማሸነፍ እንደማይችሉ ያውቁታል፡፡ ስለዚህ አንተን መሰል ሰዎችን ወደ ሜዳቸው ‹ውረድ እንውረድ› ብለው ያወርዷችኋል፡፡ በእነርሱ አጀንዳ፣ በእነርሱ ዐቅም፣ በእነርሱ ተራ ነገር፣ በእነርሱ አሉባልታ፣ በእነርሱ ስድድብ፣ በእነርሱ ጠባብነትና ጎጠኝነት፣ በእነርሱ ወንዘኛነትና መንደርተኛነት፣ በእነርሱ ተረብ ይገጥሟችኋል፡፡ ከዚያም ያሸንፏችኋል፡፡ አሁንማኮ ሁላችንንም አወረዱን፣ እንደነርሱ እንድናስብ፣ እንደነርሱ እንድንጽፍ፣ እንደነርሱ እንድንደራጅ፣ እንደነርሱ እንድንናገር፣ እንደነርሱ እንድንዘፍን፣ እንደነርሱ እንድናምን፣ እንደነርሱ እንድንለብስ አደረጉንኮ፡፡
    አትውረድ ልጄ፣ ዕውቀት ዋጋ ወደማታገኝበት፣ ሃሳብ ልዕልት ወደማትሆንበት፣ ችሎታ ወደሚያስቀጣበት አለማወቅ ወደሚያስከብርበት፣ ማይም አለቃ ወደሆነበት፣ ክርክር ተረብ ወደሆነበት፣ ውይይት እንደ ኮካ ኮላ ጠርሙስ አንድ ዓይነት ወደሆነበት፣ አላዋቂዎች ወደሠለጠኑበት፣ ከብት ካለው ይልቅ አፍ ያለው ወደተሾመበት ሜዳ አትውረድ፡፡ ከወረድክ ግን በማታውቀው ሜዳ፣ በማታውቀው ስልት፣ በወረደ ትግል ይደበድቡሃል፡፡ አትውረድ ልጄ፡፡ አትውረድ፡፡
    © ይህ ጽሑፍ በራስ ሆቴል ግጥም በጃዝ መድረክ ላይ ቀርቦ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ታትሞ የነበረ ነው

    በመካከለኛው ምሥራቅ ከእሥራኤል ቀጥሎ ሁለተኛዋ፣ በዐረቡ ምድር ደግሞ የመጀመሪያዋ የምትሆነው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በኳታር ምድር ልትታነጽ ነው፡፡ 
    በኳታር ምድር የዛሬ አሥር ዓመት ለጸሎትና ለትምህርት መሰባሰብ በጀመሩ ወንድሞችና እኅቶች የተጀመረችው የኳታር ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ወደ አካባቢው ለሥራ የሚጓዙ ምእመናንን በማሰባሰብና በማገናኘት፣ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋትና ክርስቲያናዊ ማኅበራዊ ኑሮን በማጠናከር የምትታወቅ ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያንዋ አገልግሎቷን የምትፈጽመው በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲሆን በዓረቡ ዓለም እንደተለመደውም ዘወትር ዓርብ ከሰዓት በኋላ የቅዳሴና የትምህርት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የኳታር ቅድስት ሥላሴ ምእመናን የሥራ ጫናውን ሁሉ ተቋቁመው ተግተው በማገልገል ብቻ ሳይሆን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀው በማስጠበቅም የሚታወቁ ናቸው፡፡

    በአብዛኞቹ የዓረበ ሀገሮች እንዳሉት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በኳታር ለነበረችው ቤተ ክርስቲያንም ዋና ፈተና የነበረው የራስዋ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አለመኖር ነው፡፡ ይህም አገልግሎቷን በሳምንት ወደ ተወሰኑ ቀናትና ሰዓታት ከማሳነሡም በላይ፣ ምእመናን የሚፈልጓቸውን ሁሉን አገልግሎቶች ለመስጠት እንዳትችል አድርጓት ነበር፡፡ ለቤተ ክርስቲያንዋ የራስዋ ሕንጻ መሥሪያ ቦታ በመፈለግ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ የነበረው የሰበካ ጉባኤ ባሳለፍነው ሳምንት በዐረቡ ዓለም የመጀመሪያ የምትሆነውን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት የሚያስችል መሬት ተረክቧል፡፡
    እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየመን፣ በዓረብ ኤምሬትስ፣ በባሕሬን፣ በኩዌት፣ በሊባኖስና በግብጽ የራስዋ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሯትም በራስዋ ገንዘብ የተሠራና ንብረትነቷ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሆነ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ግን አልነበራትም፡፡ የኳታር ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ከተሠራ ከእሥራኤል ቀጥሎ በመካከለኛው ምሥራቅ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ‹ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን› ይሆናል፡፡
    በኳታር ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ መሠራት ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ በአንድ በኩል የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑን አገልግሎት ከሳምንት እስከ ሳምንት የማያቋርጥ እንዲሆን ሲያደርገው በሌላ በኩል ደግሞ በአካባቢው ላሉት ሌሎች አጥቢያዎችም አርአያነት ይኖረዋል፡፡ ከኳታር በፊት እንቅስቃሴ የጀመሩት እንደ አቡዳቢ መድኃኔዓለም ያሉትን አጥቢያዎች የጀመሩትን በርትተው እንዲፈጽሙ ያነሣሣቸዋል፡፡
    በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያነት ታሪክ በዐረቢያ ፔኒዙኤላ የነበረው ቤተ ክርስቲያን ከ1400 ዓመታት በፊት በየመን ናግራን ታንጾ የነበረው የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ እርሱ ከጠፋ ከ1600 ዓመታት በኋላ በዓረቢያ ፔኑዚኤላ ሁለተኛው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በቅድስት ሥላሴ ስም እንደገና በኳታር መታነጹ የታሪኩ ተገጣጣሚነት የሚያስደንቅ ነው፡፡
     
    ይህ ቤተ ክርስቲያን በአንድ በኩል ታሪካዊ፣ በሌላ በኩል የቤተ ክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ወደ አንድ ምዕራፍ የሚያሸጋግር፣ ሲሠልስም ለሌሎች አርአያነት ያለው በመሆኑ ሥራ በኳታር ለሚገኙ ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ ግብጻውያን እንደዚህ ባሉ አካባቢዎች የሚታነጹ የተለየ ታሪክና ጠቀሜታ ያላቸውን አብያተ ክርስቲያናት በመተጋገዝ እንደሚገነቧቸው ሁሉ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም እያንዳንዷን የሕንጻዋን ብሎኬት ተካፍለው በመገንባት በታሪክ ምዕራፍ ላይ አሻራቸውን ማስቀመጥና በረከት ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡

     በሀገር ቤት፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በአውስትራልያ የሚገኙ ምእመናን በአካባቢያቸው ቤተ ክርስቲያን ባይኖር ነድተውም ሆነ ተሳፍረው ወደ ሌላ አካባቢ በመሄድ ቤተ ክርስቲያን መገልገል ይችላ፤ በዐረቡ ዓለም ግን በአንድ አካባቢ አንድ አጥቢያ ብቻ ስለሚገኝ ወጣ ብሎ በሌላ አጥቢያ መገልገል አይቻልም፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ ኳታር ባሉ ሀገሮች ያለው ቤተ ክርስቲያን አንድ ነው፡፡ ይህን ቤተ ክርስቲያን ማነጽና አገልግሎቱን ማጠናከር፣ በዐረቡ ዓለም የሚገኙ ወገኖቻችን በመንፈሳ ሕይወታቸው በርትተው፣ ከመንፈስ ጭንቀት ተላቅቀው፣ የሚደርስባቸውን ፈተናም አሸንፈው ለሀገራቸውና ለወገኖቻቸው የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው፡፡ በመሆኑም በመላው ዓለም የተሠማሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚታነጸው የራሳቸው አጥቢያ መሆኑን አስታውሰው ልባቸው ኳታር ሊሆን ይገባል፡፡
    የገባው ክርስቲያን እግዚአብሔር ሲሠራ አብሮ ይሠራል፡፡

    click here for pdf

    ልጁ አባቱን ሊጠይቅ ነበር የመጣው፡፡ ሐኪም ነው፡፡ ሐኪም ደግሞ በመንደሩ የተከበረ ነው፡፡ እርሱ መጣ ሲባል በመንደሩ የነበሩ ሕሙማን ሁሉ የአባቱን ቤት ሞሉት፡፡ ብዙዎቹ እንዲሁ አይቶ በሽታቸውን የሚያውቅላቸው ስለሚመስላቸው ‹‹ምንዎትን ነው ያመመዎት›› የሚለው ጥያቄ ግራ አጋብቷቸዋል፡፡ ‹‹ያመመኝን ካወቅኩትማ ምን ችግር ነበረበት፤ በሽታዬን ሊነግረኝ አዶለም እንዴ ሐኪም የሆነው›› ይሉታል ከቤት ከወጡ በኋላ፡፡
    አባቱ አንድ ቀን እንዲህ አሉት ‹‹ድሮ ትዕግሥተኛ ነበርክ፤ አሁንኮ በረባ ባልረባው ትነጫነጫለህ፤ ያሳደጉህን ሠፈርተኞችህን ሁሉ ትሰድባቸዋለህ፡፡ ደግሞ አንዳንዱ በሽታ አዲስ ሆኖብሃል፡፡ ድሮኮ ‹እጁ መድኃኒት ነው›› ትባል ነበር፡፡ ቀንና ሌሊት ሠርተህ አይደክምህም ነበር፡፡ እንግዳ ነገር እንኳን ሲገጥምህ ጓደኞችህን ለመጠየቅ በስልክ ስታጨናንቃቸው ነበር የምታመሸው፡፡ አሁን ምነው ያለ ጊዜህ አረጀህ ልጄ›› አሉት፡፡

    የአባቱ ትዝብት ያልጠበቀው ነው፡፡ ግን በትክክል ነው የገለጡት፡፡ አሁን በቀላሉ ይታክተዋል፡፡ እንዲያውም ያሳደጉት የሠፈሩ ሰዎች ሆነውበት እንጂ ዞር ብሎ ባያያቸው በወደደ፡፡ ለነገሩ በመሥሪያ ቤቱም አካባቢ እንዲሁ ነው የሚሉት፡፡ ‹ሆስፒታሉን ትቶ ኤን ጅኦ ከገባ በኋላ ነገር ዓለሙን ትቶታል› የሚሉት ብዙዎች ናቸው፡፡ ‹አሁንማ አለቃ እንጂ ሐኪም አይደለም፤ ባለ ገንዘብ እንጂ ባለ ዕውቀት መሆኑ ቀርቷል፤ በድሮው ስሙ ነው ያለው›› ይሉታል፡፡

    አሁን አዲስ ነገር የሆነበት አባቱም ተመሳሳይ ነገር መናገራቸው ነው፡፡ ለወትሮው ‹ዓይኔ ብርሃኔ› እያሉ ለመጣ ለሄደው ስለ እርሱ እየተረኩ ሰው የሚያሰለቹት አባቱ ዛሬ ለራሱ ቅሬታቸውን መንገራቸው አዲስ ታሪክ ሆኖበታል፡፡ መንደርተኞቹን ካከመ በኋላ በቤት ውስጥ ቡና ተፈልቶ ምርቃትና ምስጋና ይዥጎደጎድ እንዳልነበረ፣ ዛሬ ‹‹ምነው ልጄ›› የሚል ስሞታ መጣበት፡፡
    ለአባቱ አልመለሰላቸውም፡፡ ለተወሰነ ጊዜ እርሳቸውን ካዳመጣቸው በኋላ ቀጥሎ ውስጡን ነበር የሚያዳምጠው፡፡ ሥራ እንጨት እንጨት ብሎታል፡፡ ሞያው ሐኪም መሆኑ ትዝ የሚለው ሰዎች ‹ዶክተር› ብለው ሲጠሩት ነው፡፡ ስብሰባው፣ ሴሚናሩ፣ ደብዳቤው፣ ንግግሩ ሁሉ የቢሮክራሲ እንጂ የሞያ አይደለም፡፡ የሚያደንዝ እንጂ የሚስል አልሆነም፡፡ የሚያስረሳ እንጂ የሚያነቃ አልሆነም፡፡
    ‹‹ልጄ›› አሉት አባቱ ከረዥም ዝምታ በኋላ፡፡
    ‹‹አቤት›› አላቸው ከተጓዘበት በፍጥነት ተመልሶ፡፡
    ‹‹ለመሆኑ ሞያህን ለማሳደግ ልምምድ ታደርጋለህ? ከወዳጆችህ ጋር ትወያያለህ? ሌላ ቦታ ሄደህ ልምድ ትቀስማህ? ታነባለህ? እንደገናስ ትማራለህ?በጎንደር መምህር ኤስድሮስ የሚባሉ መምህር ነበሩ አሉ፡፡ መጻሕፍቱን ሁሉ መርምረው ትርጓሜ አቅንተው ሲያስተምሩ ኖሩና ‹ምናልባት ያልደረስንበት አዲስ ነገር ቢኖርስ› ብለው በዚያ በጣና ገዳማት ውስጥ ገብተው መጻሕፍቱን ሁሉ ሲያገላብጡ ኖሩ አሉ፡፡ እውነትም ያልደረሱበት ብዙ ነገር ቢያገኙ ተማሪዎቻቸውን እንደገና ጠርተው ‹እኔም ያላወቅኩት እናንተም ያልተማራችሁት አዲስ ነገር አግኝቻለሁና ኑ እንደገና እንማር› ብለው ሰበሰቧቸው፡፡ እሺ ብለው ለአዲስ ዕውቀት የመጡ አሉ፡፡ እምቢ ብለው በቀድሞው ብቻ የቀሩ አሉ፡፡ እሺ ብለው የመጡት የሄዱበት መንገድ ‹የታች ቤት ትርጓሜ› ተባለ፡፡ እምቢ ብለው የቀሩት የሄዱበት መንገድ ደግሞ ‹የላይ ቤት ትርጓሜ› ተባለ፡፡ ለመሆኑ አንተስ ምናልባት ያልደረስኩበት ነገር ቢኖር፤ አዲስ የመጣ ነገር ቢኖር፤ ማወቅ ሲገባኝ ሳላውቀው የቀረሁት ነገር ቢኖር ብለህ አስበህ ታውቃለህ? ዕውቀትኮ ካልጨመሩበት አንድም እየዛገ አንድም እየጠፋ ይሄዳል፡፡ ትዶለዱማለህ ልጄ፡፡ አንድ ምሳሌ ልንገርህ ፡-
    ‹ሰውዬው ሥራ ፍለጋ ሲንከራተት ወደ አንድ የጣውላ ፋብሪካ ይደርስና ይጠይቃል፤ ሰውነቱ ግዙፍና ጠንካራ መምሰሉን ይመለከትና ባለቤቱ እንዲገባ ይጋብዘዋል፡፡ ያላቸው የሥራ መስክ እንጨት ቆራጭነት መሆኑን ይነግሩታል፡፡ ሰውዬውም ያገኘውን ሁሉ ለመሥራት ታጥቆ የተነሣ ነበርና ተቀበለ፡፡ የተወሰነ ሰዓት በመጥረቢያ እንዴት ዛፍ እንደሚቆረጥ አሠለጠኑትና ወደ ሥራው ተሠማራ፡፡ ክፍያው በቆረጠው ዛፍ ልክ ነበር፡፡
    በመጀመሪያው ቀን ሃያ ዛፍ ቆረጠና ጥሩ ክፍያ አገኘ፡፡ በዚህ ደስ ብሎት በማግሥቱ ተነሥቶ ወደ ሥራው ገባ፡፡ በዚያ ቀንም ዘጠኝ ዛፍ ቆረጠ፡፡ በሦስተኛው ቀን ሰባት፣ በአራተኛው ቀን ስድስት፣ በአምስተኛው ቀን አምስት፣ በስድስተኛው ቀን አራት ቆረጠ፡፡ ድካሙ ያው ነው፡፡ የሚቆርጠው ዛፍ ግን እያነሰ ሄደ፡፡ ዛፉ ሲያንስም ክፍያው አነሰው፡፡ ለዕለት ምግቡ እንኳን አልበቃው አለ፡፡ በመጨረሻም ተስፋ ቆረጠ፡፡
    ወደቀጠረው ሰው ዘንድ ሄደና ሥራን ለማቆም እንደሚፈልግ ነገረው፡፡ ‹‹ለምን ታቆማለህ፤ ክፍያው አልተስማማህም?›› አለው፡፡ ‹‹ሂሳቡ በቂ ነው፤ ነገር ግን ብዙ ዛፍ በአንድ ቀን ለመቁረጥ አልቻልኩም፡፡ ካደር አደር እየቀነስኩ መጣሁ፡፡ በዚያውም ልክ የሚከፈለኝ ገንዘብ እየቀነሰ ሄደ፡፡ አሁን ችግር ውስጥ ከመውደቄ በፊት ሥራውን ለማቆም ወሰንኩ›› አለው፡፡
    አሠሪውም ‹በመጀመሪያ ስንት ዛፍ ነበር የቆረጥከው?›› አለው፡፡
    ‹‹አሥር››
    ‹‹በመጨረሻስ?››
    ‹‹አራት››
    ‹‹ለመሆኑ መጥረቢያውን ስለህው ታውቃለህ?›› አለው፡፡
    ‹‹ኧረ በጭራሽ›› አለ ቆራጩ፡፡
    ‹‹ታድያ ምን አድርግ ነው የምትለው፡፡ በመጀመሪያ ቀን የተሳለ መጥረቢያ ሰጥተንህ ስለነበር አሥር ቆረጥክበት፡፡ በየቀኑ በሠራህበት ቁጥር እየዶለዶመ ስለሚሄድ በመጨረሻ አራት ላይ ደረስክ፡፡ ብትቀጥል ደግሞ አንድ ዛፍ መቁረጥ የማትችልበት ደረጃ ላይ ትደርስ ነበር፡፡ በሠራህ ቁጥር መጥረቢያውን እንደገና መሳል አለብህ፡፡ ሁልጊዜም አዲስ ሆኖ ሌላ ዛፍ ለመቁረጥ እንዲችል በየጊዜው መሳል አለብህ፡፡ አሁንም ሂድና እንደዚያ አድርግ›› ብሎ አሰናበተው፡፡
    ‹‹አየህ ልጄ አእምሮም እንደዚያው ነው፡፡ በየጊዜው መሳል ይፈልጋል፡፡ እንደገና መማር፣ እንደገና ማንበብ፣ እንደገና መሠልጠን፣ እንደገና ሞያ መለማመድ ይፈልጋል፡፡ ያለበለዚያማ የዛሬ ስንት ዓመት በተማርከው ከተቀመጥክ ትዶለዱማለህ፤ መጥረቢያውኮ አልጠፋም፡፡ አልተለወጠም፡፡ አሁንም መጥረቢያ ነው፡፡ ግን ስለቱ ቀነሰና አገልግሎቱ ደከመ፡፡ አንተምኮ አሁንም ሐኪም ነህ፤ አልተለወጥክም፡፡ ግን ትዶለዱምና ውጤታማነትህ ይቀንሳል፡፡
    ስለዚህ ልጄ ሂድና ተሳል፤ በየጊዜውም ተሳል፤ በሠራሀ ቁጥር ተሳል፤ አዲስ ዛፍ ለመቁረጥ መጥረቢያው መሳል እንዳለበት ሁሉ፤ አዲስ ችግር ለመፍታት፣ አዲስ ሃሳብ ለማመንጨት፣ አዲስ መንገድ ለማግኘት፣ አዲስ ሕመም ለመፈወስ እንድትችል ሂድና አንተም ተሳል›› አሉት፡፡
    ጉልበታቸውን ስሞ ቀና ሲል ግንባሩን ሳሙት፡፡
    © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው

    ሁለተኛው ‹‹የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት›› ዘንድሮ በመጋቢት ወር መጨረሻ ይከናወናል፡፡ ለሀገሪቱ በጎ ሠርተዋል የሚሏቸውን ሰዎች ይጠቁሙ፡፡ ለጥቆማ የሚረዷችሁ ነጥቦች

    1. ለሀገር ሰላም፣ ለሕዝቦች መቀራረብና መደጋገፍ፣ ለውጥ አምጭ አስተዋጽዖ ያደረጉ፣

    2. በበጎ አድራጎትና ሰብአዊ ተግባራት ተሠማርተው የሰው ልጅን ሕይወት የለወጡ፣

    3. በሥነ ጽሑፍ፣ በኪነ ሕንጻ፣ በሥነ ጥበብና በመሳሰሉት መስኮች ለኢትዮጵያውያን የሚጠቅሙ፣ የኢትዮጵያን ስም ከፍ የሚያደርጉ፣ የሀገሪቱን ሥነ ጥበብ ወደ አንድ የላቀ ደረጃ የሚያደርሱ ሥራዎች የሠሩ፣

    4. በግብርና፣ በቢዝነስ፣ በኢንዱስትሪና በመሳሰሉት መስኮች አዲስ፣ የራሱ ወጥነት ያለውና ያልተደፈረ የሚመስለውን ሥራ ያከናወኑ፣ ለሀገሪቱ ዕድገትና ሥልጣኔም ለውጥ አምጭ አስተዋጽዖ ያደረጉ፣

    5. በጋዜጠኛነት መስክ ተሠማርተው ሙያውን የጠበቀ፣ ለሌሎች አርአያ የሚሆን፣ የሕዝቡን ኑሮ የሚለውጥ ሥራ ያከናወኑ፣

    6. በዲፕሎማሲው መስክ የሀገሪቱን ክብርና ደረጃ ያስጠበቁ፣ የሀገሪቱንም መብት ያስከበሩ፣

    7. በመንግሥትና በሥራ ተቋሞቻቸው የተሰጧቸውን የተለያዩ ሀገራዊ ግዳጆችን በብቃት የተወጡ፣ መሥዋዕትነት የሚጠይቁ ተልዕኮዎችን ያከናወኑ፣ ለትውልድ አርአያ የሚሆኑ ብቁ አመራሮችን የሰጡ፣ በአመራሮቻቸውም ድርጅታቸውንና መሥሪያ ቤቶቻቸውን የለወጡ፣

    8. ሀገራዊ ዕውቀቶችን በማስተማር፣ ቅርሶችንና ባህልን በማስጠበቅና በመከባከብ ለውጥ አምጭ ተግባር ያከናወኑ፣

    9. በጥናትና ምርምር መስክ ተሠማርተው ችግር ፈች የሆኑ ውጤቶችን ያስመዘገቡ፣

    10. በማስታረቅ፣ ግጭቶችን በመፍታት፣ ሀገራዊ የሽምግልና ሥራ የሠሩ፣

    11. በሌሎችም መስኮች የሚጠቀስ፣ ለሀገር የሚጠቅም፣ ለትውልድ አርአያነት ያለው፣ የሀገርን ክብር የሚጨምር፣ ታሪክና ማንነትን የሚያጎላ ተግባር ያከናወኑ ሌሎችንም ኢትዮጵያዊ ዜጎችን ይጠቁሙ፤

     ማስተዋሻ
      • የሚጠቁሟቸው ኢትዮጵያውያን በተቻለ መጠን ከዚህ በፊት ያልታወቁና ይህን መሰል ዕድል ያላገኙ ቢሆኑ ይመረጣል፣

      • በተቻለ መጠን ከአዲስ አበባ ወጣ ባሉ ቦታዎች ሰው ሳውቃቸው ለሀገራቸው አስተዋጽዖ የሚያደርጉ ዜጎችን በመጠቆም ይተባበሩ፣

      • ሲጠቁሙ የጠቆሙትን ሰው ስም፣ ያለበትን ቦታ፣ የሠሩትን በጎ ሥራ ዘርዘር አድርገው ይግለጹ፣ ከቻሉም ስልካቸውን ወይም ኢሜይላቸውን ይላኩልን፣

      • ጥቆማውን እስከ የካቲት 15 ቀን 2006 ዓም ያድርጉልን

      • ከሀገር ውጭ ሆነው ሀገራዊ ሥራዎችን የሚሠሩና ሀገራቸውንንና ሕዝባቸውን የሚጠቅሙትን በጎ ዜጎች እንጠቁም

      • ከጥቆማው በኋላ የተቋቋመው ኮሚቴ ሃያ አምስት ዕጩዎችን ይጠቁማል፤ በእነዚህ ዕጩዎችም ላይ ከተለያየ ሙያ፣ መስክ፣ ዕድሜ፣ እምነት፣ አካባቢ፣ የዕውቀት መስክ የተወጣጡ ነገር ግን እርስ በርሳቸው የማይተዋወቁ 100 ሰዎች ድምጽ ይሰጧቸዋል፡፡ በእነዚህ ሰዎች ድምጽም የመጨረሻዎቹ አምስት ሰዎች ይመረጣሉ፣

      ለመጠቆም ይህንን የኢሜይል አድራሻ ይጠቀሙ  [email protected]

      ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው የሠሩትን ዜጎቻችንን እናበረታታ፣ እንሸልም፣ ዕውቅና እንስጥ

      ሰሞኑን ኤፍሬም ሥዩም ያዘጋጀውን ‹ተዋነይ -ብሉይ የግእዝ ቅኔያት ፍልስፍና› የተሰኘ መጽሐፍ እያነበብኩ ነበር፡፡ አንዳንድ ‹ጻፍን› ብለው የሚያስቡ የኔ ብጤዎች የጥንቱን ሁሉ እንደ አሮጌ በሚያዩበት ዘመን ኤፍሬምን የመሰለ አስተዋሽ ማግኘት መታደል ነው፡፡ ባለማወቃችን ምክንያት የለንም ልንል ስንነሣ፣ እንዲህ የሚያስታውሱን አይጥፉ፡፡

      ቀደምት ኢትዮጵያውያን ፈላስፎች ሃሳቦቻቸውን የገለጡባቸውን የግእዝ ቅኔያት በግጥም መልኩ እየተረጎመ ግራና ቀኝ አድርጎ አቅርቦልናል፡፡ ኤፍሬም የግእዝ ቅኔያቱን የሰበሰበበት መመዘኛው ፍልስፍና ነክነት ይመስለኛል፡፡ ሊቃውንቱ ከምድር እስከ ሰማይ ያሉ ፍጡራንንና ኃያላንን የሞገቱበትንና የመረመሩበትን መንገድና ምጥቀት እናያለን፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ 83 የግእዝ ‹ቅኔዎች› ቀርበዋል፡፡ አንዳንዶቹን አንብባችሁ ስትገረሙ ልትውሉ ትችላላችሁ፡፡

      ለምሳሌ እንዲህ ያለውን የአለቃ ገብረ ሐና ቅኔ ስታዩ፡-

      ኮንኖ ኃጥኣን ክርስቶስ ኢይደልወከ ምንተ

      አፍቅሩ ጸላዕተክሙ እስመ ትብል አንተ

      አንዳንዶቹን አንብባችሁ ደግሞ ስትመሰጡ ታነጋላችሁ፤

      እንዲህ የሚሉትን ስታነቡ፡-

      ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ፣

      ወፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ፤

      አንዳንዶቹ እንደገና እንደገና እንድትመራመሩ ያደርጓችኋል፤

      ባሕቲቶ ነቢረ እግዚአብሔር ፈርሀ

      እም ኢሀልዎ ንዋም እስመ ዓለመ አንቀሐ

      አንዳንዶቹም ብቻችሁን እያወራችሁ እንድትሄዱ ያደርጓችኋል፡-

      እመ ተናገርኩ ጽድቀ ሰብአ ዛቲ ዓለም ይጸልዑኒ፣

      ወከመ ኢይንብብ ሐሰተ ኩነኔ ዚአከ ያፈርሀኒ፣

      እም ኩሉሰ አርምሞ ይኄይስ ወይሤኒ

      በውጭው ዓለም አንድን ዕውቀት ለመረዳት ይቻል ዘንድ በየፈርጁ እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ የኤዞፕ ተረቶች አንድ ዓይነት ቢሆኑም በልዩ ልዩ ዘርፎች እየተዋቀሩ እንደገና እስካሁን ይቀርባሉ፡፡ ኤፍሬም ለግእዝ ቅኔያት ይህንን መንገድ አመላክቷል፡፡ ፍልስፍናውያን፣ ታሪካውያን፣ መንፈሳውያን፣ ትርጓሜያውያን፣ ዶግማውያን፣ ወዘተ እያልን በየዘርፉ ልናያቸውና በሚገባ ልናውቃቸው እንደምንችል አመላክቷል፡፡

      ባይሆን ኤፍሬም ለወደፊቱ የቅኔዎቹን ታሪካዊ ዳራ በግርጌ ማስተዋሻ በኩል ጣል ቢያደርግልን የኔ ብጤዎች በሚገባ ለመረዳት በር ይከፍትልናል፡፡ በመጽሐፉ መጀመሪያ ሊቀ ኅሩያን በላይ እና ራሱ ኤፍሬም የጻፏቸው መቅድሞችም የቅኔዎቹን ያህል ተወደውና ልብ ገዝተው የሚነበቡ ናቸው፡፡

      ይህንን በ190 ገጽ የተጠቃለለ፣ በ100 ብር የሚሸጥ፣ በሻማ ቡክስ የታተመ መጽሐፍ ታነቡት ዘንድ እየጋበዝኩ እስኪ ይኼን ቅኔ ፍቱ

      ድንግል ወለት ትመስለነ ዕቤርተ

      አኮኑ ትውዕል እንዘ ተሐቅፍ እሳተ

      መልካም ንባብ፡፡ 

      ሁለት የጎዳና ልጆች የገና ዋዜማ አመሻሽ ላይ፣ ጎዳና ዳር ቁጭ ብለው አላፊ አግዳሚው ለዓመት በዓሉ ሲራወጥ ያያሉ፡፡ ዶሮ ያንጠለጠለ፣ በግ የሚጎትት፣ ቄጤማ የቋጠረ፣ በሬ የሚነዳ፣ እህል ያሸከመ፣ ‹የገና ዛፍ› የተሸከመ፣ አብረቅራቂ መብራት የጠቀለለ፣ ዋዜማ ሊቆም ወደ ቤተ ክርስቲያን ነጭ ለብሶ የሚጓዝ፣ ምሽቱን በዳንስ ሊያሳልፍ ሽክ ብሎ ወደ ጭፈራ ቤት የሚጣደፍ፣ ብቻ ምኑ ቅጡ፣ ከተማዋ ቀውጢ ሆናለች፡፡

      እነርሱ ደግሞ የተበጫጨቀች ልብስ ለብሰው፣ የደረቀ ዳቦ ይዘው፣ በቢል ቦርድ ላይ የተለጠፈውን የጥሬ ሥጋ ሥዕል እያዩ፣ መጣሁ መጣሁ የሚለው የገና ብርድ እያቆራመዳቸው፣ የቆሸሸ ሰውነታቸውን እየፎከቱ፣ የቀመለ ፀጉራቸውን እያከኩ፣ በታኅሣሥ 15ና በታኅሥ 29 መካከል ያለው ልዩነት ጠፍቷቸው፣ የበግ ድምጽ እንጂ ሥጋው ርቋቸው፣ የበሬው ፎቶ እንጂ ሥጋው ጠፍቶባቸው፣ ያገኙትን ወረቀት እያነደዱ ጎዳናው ዳር ተቀምጠዋል፡፡

      ‹‹ቆይ ግን ገና ምንድን ነው?›› አለ አንደኛው ሰውነቱን እየፎከተ፡፡

      ‹‹የክርስቶስ ልደት ነዋ፤ በማይክራፎን ሲሰብኩ የሰማሁት እንደዚያ ነው››

      ‹‹የት፣ መቼ፣ ለምን ተወለደ?››

      ‹‹እነርሱ የሚሉት ቤተልሔም በምትባል ከተማ፣ በእኩለ ሌሊት፣ በብርድ ወቅት፣ ራቁቱን፣ እናቱ በከተማዋ ማደሪያ የሚሰጣት አጥታ፣ በተናቀው ቦታ በከብቶች በረት ውስጥ ተወለደ፡፡ በጣም ስለበረደውና ራቁቱን ስለነበር ከብቶቹ በትንፋሻቸው አሞቁት፤ ሌላ ሰው ስላልነበረ እረኞቹ መጥተው ዘመሩለት፡፡ እንዲህ ነው የሰማሁት፡፡››

      ‹‹እኛምኮ እንደርሱ የሚያስጠጋን አጥተን ነው ጎዳና የወደቅነው፡፡ እንደርሱ ራቁታችንን ነን፤ እንደርሱ የሚበላ የለንም፤ እንደርሱ እኛንም የሚያሞቁን እነዚህ ውሾች ናቸው፤ እንደርሱ እንደርሱ እኛም በተናቀው ቦታ ላይ ነን›› አለ ሁለተኛው ልጅ ውሻውን እየደባበሰ፡፡

      ‹‹የሚገርምህ ነገር ጌታ የተወለደው በከብቶች በረት ዋሻ ውስጥ ነው፡፡ ያኔ ጥድ የለም፤ በረት እንጂ፡፡ ጌታኮ ጫካ ውስጥ አልተወለደም፡፡ ያኔ ከረሜላ የለም፤ ያኔ ጥጥ የለም፣ ያኔ ፖስት ካርድ የለም፣ የሰብአ ሰገል ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ እንጂ፡፡ አሁን ይኼን ሁሉ ከየት እንዳመጡት እንጃ፡፡ ይልቅስ ራቁታችንን ሆነን፣ የሚበላ ናፍቆን፣ በእንግዶች ማረፊያ ሥፍራ የሚሰጠን አጥተን፣ ከእንስሳት ጋር ተኝተን እኛ አለንላቸው፡፡ ገናኮ መከበር የሚገባው ከእኛ ጋር ነበር፡፡ ገና የሀብታሞች ሳይሆን የድኾች፣ የተከበሩ ሳይሆን የተዋረዱ፣ ቤት ላላቸው ሳይሆን ማደርያ ያጡ፣ ዘመድ ያላቸው ሳይሆን ወገን ያጡ ሰዎች በዓል ነው፡፡ ገና የሚወርዱበት እንጂ የሚወጡበት በዓል አልነበረም፡፡››

      ‹‹እኔም እሱን እያሰብኩ ነበር፡፡ ተመልከት ያኔ የዘመሩትን እረኞች አሁን ማንም አያስታውሳቸውም፡፡ ያኔ የቤተልሔም ሰዎች በጥጋብና በዕንቅልፍ ተወስደው አላስጠጋው ሲሉ በረታቸውን የሰጡት ከብቶች ነበሩ፡፡ አሁን የእነርሱ ዋጋ መታረድ ሆነ፡፡ በዓሉኮ የከብቶች በዓል ነበረ፡፡ እኔ ከብቶች ውለታ በዋሉበት፣ ከሰው የሚበልጥ ሥራ በሠሩበት በገና ቀን መታረዳቸው ይገርመኛል፡፡››

      ‹‹አይግረምህ፤ በሰው ልጅ ታሪክ ሁሉ እንደዚህ ነው፡፡ ታሪክ የሠሩትና መሥዋዕትነት የከፈሉት ምንጊዜም መሥዋዕት እንደሆኑ ናቸው፡፡ በኋላ የሚጠቀመው ታሪክ ሠሪው አይደለም፤ ታሪክ ተራኪው ነው፡፡ ‹የበሬን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ› የተባለው ዝም ብሎ እንዳይመስልህ፡፡ አንተ በሠራኽው ታሪክ አንተን አርደው ያንተን በዓል የሚያከብሩ ሞልተዋል፡፡››

      ‹‹እርሱማ አታይም እንዴ፤ በኛ በድኾች ስም ይለመናል፤ ብር ይሰበሰባል፤ እኛ በፊልም እየተቀረጽን ታሪኩን እንሠራዋለን፤ በኋላ ግን እኛው ራሳችን በድህነት ቢላዋ እንታረድና የኛን በዓል ሌሎች ያከብሩልናል፡፡ ታሪኩን የሚሠሩት እረኞች፣ አበሉንና ደመወዙን የሚበሉት ግን የቤተልሔም ሰዎች፡፡ አንተ ፖስት ካርድ ብቻ ሆነህ ትቀራለህ፡፡ እስኪ የገናን በዓል ተመልከት፡፡ እረኞቹ የታሉ፤ በረቱ የታለ፤ ከብቶቹ የታሉ፤ ከሩቅ ሀገር የመጡት የጥበብ ሰዎች የታሉ፤ ጌታ የተኛበት የእንጨት ርብራብ የታለ፡፡ ሁሉም የሉምኮ፡፡ የእረኞቹን ቦታ ተኝተው የነበሩት የቤተልሔም ሰዎች ወስደውታል፤ የበረቱን ቦታ የገና ዛፍ ወስዶታል፤ የጥበብ ሰዎችን ቦታ የገና አባት ተረክቦታል፤ የከብቶቹን ታሪክ ሰባኪዎቹና ዘማሪዎቹ፣ ፓስተሮቹና ቄሶቹ ወስደውታል፤ የመላእክቱ ዝማሬ በጭፈራ ቤቶቹ ዘፈን ተተክቷል፡፡ ከብቶቹንም፣ እረኞቹንም፣ ሰብአ ሰገልንም፣ በረቱንም፣ መላእክቱንም፣ የምታገኛቸው ፖስት ካርድ ላይ ብቻ ነው፡፡››

      ‹‹የሚገርመኝ ምን እንደሆነ ታውቃለህ፤ በዚህ መንገድ ዳር በተሰቀለ ትልቅ ቴሌቭዥን ላይ ሳይ፣ የሃይማኖት አባቶች ‹በዓሉን ከተቸገሩት ጋር በማክበር አሳልፉት› ሲሉ እሰማለሁ፡፡ አንዳቸውም ግን ከመናገር ባለፈ ከተከበረ መንበራቸው ወርደው ከእኛ ጋር ሲያሳልፉ አይታዩም፡፡ ‹ክርስቶስ ከሰማያት ወረደ› ማለት እንጂ መውረድ ለካስ ከባድ ነው፡፡››

      ‹ካመጣኸውማ ገናኮ የመውረድ በዓል ነበር፡፡ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወረደ የሚባልበት በዓል ነበር፡፡ አሁን ግን የሚወጣ እንጂ የሚወርድ የለም፡፡ ወደ እኛ የሚወርድ የለም፡፡ ሰው አምላክ መሆን ቢያቅተው አምላክ ሰው ሆነ ይላሉ፡፡ እኛ እንደነርሱ መሆን አቅቶናል፤ ታድያ ምናለ እነርሱ እንደኛ ቢሆኑ፡፡ በጣም የሚገርመው ሰብአ ሰገል ስጦታ የሰጡት ራቁቱን ለነበረው፣ ቤት ላጣው፣ የቤተልሔም ሰዎች አላስጠጋ ላሉት፣ ከሰው ወገን ጠያቂ ላልነበረው ለክርስቶስ ነበረ እንጂ ሁሉ በእጃቸው፣ ሁሉ በደጃቸው ለሆኑት ለቤተልሔም ሰዎች አልነበረም፡፡ ዛሬ ግን ስጦታው ለቤተ ልሔም ሰዎች ሆነ፡፡››

      ‹አንድ ቀን አንድ ሰው ሲያስተምር ምን ሰማሁ መሰለህ፡፡ ክርስቶስ ‹ተርቤ አላበላችሁኝም፣ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም› ይላል፡፡ የሰሙት ሰዎች ‹የት አግኝተን እናብላህ እናጠጣህ› ቢሉት ‹ለታናናሾቹ ካላደረጋችሁ ለእኔ አላደረጋችሁትም፣ ለታናናሾቹ ካደረጋችሁ ለእኔ አድርጋችሁታል› አላቸው አሉ፡፡ ታድያ ከኛ የባሰ ታናሽ ማን አለ? ያኔምኮ ክርስቶስ ተራ፣ ድኻ፣ እዚህ ግባ የማይባልና የተናቀ መስሎ ስለመጣ ነው የቤተልሔም ሰዎች ያላስጠጉት፡፡ ዛሬስ ድንገት ከእኛ መካከል ቢኖርስ፣ እዚህ ጎዳና ዳር ከውሾቹ ጋር ተኝቶ ቢሆንስ፤ በገዛ የልደቱ ቀን ሰዎች እርሱን ንቀው እያለፉ፣ ተጸይፈው እያለፉ፣ በጽድና በከረሜላ፣ በበግና በዶሮ፣ በጠላና በጠጅ፣ በፖስት ካርድና በስጦታ የራሱን በዓል እያከበሩለት ቢሆንስ፤ ››

      ‹ማን ያውቃል ወዳጄ፤ ሰው እንደሆነ በዓሉን እንጂ ራሱን ክርስቶስን የሚፈልገው አልመሰለኝም፡፡ ቢፈልጉት ኖሮማ አንድ ጥድ የሚገዙበት እኛን አልብሶ ‹ታርዤ አላለበሳችሁኝም› ከሚለው ያወጣቸው ነበር፤ የአንድ ፖስት ካርድ ዋጋ ለኛ የወር የቤት ኪራያችን ነበር፤ በጉን በልተው እንኳን ቆዳውን ቢሰጡን ለኛ የዓመት ቀለብ ነበር፤ ለከረሜላው የሚወጣው ገንዘብ የኛን የዓመት ጤና ይጠብቅ ነበር፡፡ አሁንማ የበዓሉ ምክንያት ተረስቶ በዓሉ ብቻ ቀርቷል፡፡››

      ‹‹እና አሁን ገና እየተከበረ ይመስልሃል››

      ‹‹ምን እየተከበረ ነው፤ እየተቀበረ ነው እንጂ››

      © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው

      click here for pdf

      ሰንደባ ኢየሱስ – ከሩቁ

      ከባሕርዳር ወደ ጎንደር ስትጓዙ አርኖ የምትባል አነስተኛ ከተማ ታገኛላችሁ፡፡ የከተማዋና የወንዟ ስም አንድ ነው፡፡ አርኖ ላይ ወርዳችሁ ወደ ቀኝ ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል በእግራችሁ ስትጓዙ ሜዳውን ትጨርሱና ገደሉን ፊት ለፊት ትጋፈጡታላችሁ፡፡ በገደሉ መካከል እንደ ሞሰበ ወርቅ በተሸለመች ተራራ አናት ላይ የሰንደባ ኢየሱስ ወተክለ ሃይማኖትን ጥንታዊ ደብር ታገኙታላችሁ፡፡
      የደብሩ ካህናት የቤተ ክርስቲያኑ ታሪክ ከአንድ ሺ ዓመት በላይ እንዳለፈው ይናገራሉ፡፡ በአካባቢው የምናገኛቸው የሥነ ሕንጻና አካባቢያዊ ማስረጃዎች ደግሞ ታሪኩ ቢያንስ ሰባት መቶ ዓመት ሊሆነው እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡
      የሰንደባ ኢየሱስ ወተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ሥነ ሕንጻው ከዛግዌ ዘመን፣ አካባቢያዊ መረጃዎቹ ደግሞ ከ13ኛውና 14ኛው ዘመን ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡

      ቤተ ክርስቲያኑ ክብ ሆኖ ውጩ በጭቃ የተገረፈ ነው፡፡ የጭቃ ግርፉ በቤተ ክርስቲያኑ ላይ የደረሰውን የመፍረስ አደጋ ለመታደግ በአካባቢው ባለሞያዎች የተገነባ ነው፡፡ ወደ ውስጡ ሲዘልቁ ግን ሁለት ጥንታዊ ክፍሎችን ያገኛሉ፡፡

      ሰንደባ ኢየሱስ – ከቅርብ ሲታይ

      የደብሩ መስኮቶች እንደ ይምርሐነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ወጥ እንጨት የተሠሩ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ መስኮት ያራሱ ቅርጽ ያለው ሲሆን፣ አንደኛው ከሌላኛው የተለየ ዲዛይን አለው፡፡ ብዙዎቹ መስኮቶች ለውበት የተሠሩ እንጂ የሚከፈቱ  አይደሉም፡፡ የመስኮቶቹ መቃኖች ከአንድ ወጥ እንጨት ወጣ ብለው የተሠሩ፣ በአራቱም መዓዝን ወጣ ወጣ ያሉ ጌጦች ያሏቸው ናቸው፡፡ ይህ አሠራራቸው ከይምርሐነ ክርስቶስ አሠራር ጋር ያዛምዳቸዋል፡፡
                     
      ሰንደባ ኢየሱስ ወተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያንን ከይምርሐነ ክርስቶስ ጋር የሚያዛምዳቸው መስኮታቸው ብቻ አይደሉም፡፡ የመቅደሱ ግድግዳ አሠራርም ተመሳሳይ ነው፡፡ ግድግዳው በቀጫጭን ጠፍጣፋ ድንጋዮች እየተሰካካ፣ በኖራ መሰል ነገር እየተያያዘ ቀጥ ብሎ የተሠራ ነው፡፡ እጅግ የሚገርመው ግን ድንጋዮች የተያያዙበት ኖራ መሰል ነገር የተለሰነበት መንገድ ነው፡፡ የደብሩ ሊቃውንት ኖራ ከተነከረ ቆዳ ጋር እየተያያዘ እንደተሠራ ይናገራሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ከውጭ ክብ ቢሆንም ሁለቱ የውስጥ ክፍሎቹ ግን አራት መዓዝን ናቸው፡፡ መዓዝኖቹ በርግጠኝነት 90 ዲግሪ ናቸው፡፡ ወደ ላይም በቱምቢ ሲለካ ቀጥ ብሎ የወጣ ወጣ ገባ የሌለው ነው፡፡

      በተሰካኩ ድንጋዮች የተሠራው ግድግዳ

      በግድግዳው አማካይ በሐረግ የተጌጠ ነው፡፡ ጌጡ ከጥግ እስከ ጥግ በሁለት ወይም በሦስት መሥመር እየተዘረጋ ተገጥግጧል፡፡ ከመስኮቶቹ በላይ ደግሞ ሌላ ጌጥ አለ፡፡ በመስኮቶቹ መቃን ርዝመት ልክ ከአንድ ወጥ እንጨት የተሠራ ሐረግ፡፡ ይህ ሐረግ በመስኮቱ ላይ በቻ ሳይሆን ከበሩ በላይም እንዲሁ በየመዓዝናቱ ተሰክቶ ይታያል፡፡

      የተጌጠው መስኮት

      አራት መዓዝኑ የመቅደሱ ግንብ ለስድስት ሜትር ያህል ወደ ላይ ከወጣ በኋላ መቅደሱን ከጣራው ጋር በክብ ግድግዳ ያያይዘዋል፡፡ ወደ ቅድስቱ መግቢያው በር የጥንቱን ይዘት አልለቀቀም፡፡ በአራት ደረጃ የተሠራው መቃን በሥዕል የተሞላ ነው፡፡ በመጨረሻው መቃን ላይ ደግሞ የአሥራ አምስቱ ነቢያት ሥዕል በትንንሹ ተሥሎ ይታያል፡፡

      የአሥራ አምስቱ ነቢያት ሥዕል- የበሩ ላይኛው መቃን
      ከበሩ በላይ ሌላ ጌጠኛ መስኮት አለ፡፡ መስኮቱ ባለ ሦስት መቃን ሲሆን ሦስቱም በሥዕል ያጌጡ ናቸው፡፡ የሚገርመው ግን መስኮቱ ለውበት የተሠራ እንጂ የሚከፈት መስኮት አይደለም፡፡ ከአንድ ወጥ እንጨት የተቀረጸው መስኮት የመስኮቱ ውስጣዊ አካል ራሱ በቀለም ያሸበረቀ ነው፡፡ የመስኮቱ ውስጣዊ አካል ደግሞ እርስ በርሳቸው በተያያዙ ክቦች ቅርጽ የተሠራ ነው፡፡ እያንዳንዱ ክበብም የየራሱ ቀለም ተቀብቷል፡፡

      ዋናው በር በበሩ ላይ የቅዱሳን መላእክት ሥዕል በትልቁ ተሥሎበታል፡፡ ሥዕሉ እንዳይበላሽ በመጋረጃ የተጋረደ ሲሆን ሥዕሉን ባለ ሦስት ደረጃ መቃን አጅቦታል፡፡ ወደ በሩ የመግቢያው ደረጃ ከእንጨት የተሠራ ባለ ሰባት እርከን ነው፡፡ ሊቃውንቱ የሰባቱ መዓርጋት፣ የሰባቱ ሰማያትም ቢሉ ምሳሌ ነው ይላሉ፡፡ ከበሩ ግራና ቀኝ ቢያንስ አራት መቶ ዓመታትን የዘለቁ፣ የሥዕል አጣጣላቸው ከጎንደር ዘመን ቀደም ያሉ ዓመታትንና የጎንደርን ዘመን አሻራ ያዙ ሥዕሎች አሉ፡፡

      ባለ ሰባት ደረጃው በር

      በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ መንበር የሚመስሉና የቤተ ክርስቲያኑን ቅርጽ የያዙ ወጥ ከሆነ እንጨት የተቀረጹ ሳጥኖች አሉ፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት ቅዱስ ላሊበላ ሕንጻዎቹን ከመውቀሩ በፊት ዲዛይኑን በእንጨቶቹ ላይ ማስቀመጡን ይናገራሉ፡፡ በሰንደባ ኢየሱስ ወተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያንም የመቅደሱን ቅርጽና የመቅደሱን ሐረጎችና በሮች ቅርጽ ያዘ አነስተኛ መንበር መሰል ነገር አለ፡፡ እንደ እኔ ግምት ቤተ ክርስቲያኑ ሲታነጽ የቤተ ክርስቲያኑ ቅርጽ አራት መዓዝን የነበረ ይመስላል፡፡ በኋላ ሲፈርስ ለማደስ ሳይሆን አይቀርም ውጩ ክብ የሆነው፡፡

      የቤተ ክርስቲያኑን ቅርጽ የያዘው ጥንታዊው አንድ ወጥ ‹መንበር›

      የመቅደሱ ታችኛው ግድግዳ በዕውቅ ጠራቢ ተስተካክለውና አምረው በተጠረቡ ግዙፍና አራት መዓዝን በሆኑ ዐለቶች የተገነባ ነው፡፡ የዚህ ግድግዳ አሠራሩ በአኩስም ከተገኙ የጥንት መቃብሮች አሠራር ጋር የተዛመደ ነው፡፡ ዐለቶቹ እርስ በርስ የተገጣጠሙበት መንገድ ትኩረት ቢደረግበት ለዛሬውም የግንባታ ችግሮቻችን መፍትሔ የሚሰጡ ናቸው፡፡

      በግዙፍ ጥርብ ድንጋዮች የተገነባው ግድግዳ

      የሰንደባ ኢየሱስ አስደናቂ ታሪክ የሚጀምረው አሁን ቅድስት የሆነውን ክፍል ሲገልጡት ነው፡፡ ቅድስቱ ሁለት ክፍል ያለው እጅግ ሰፊ ክፍል ነው፡፡ ምናልባትም በጥንቱ አሠራሩ ይኼ መቅደሱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በቅድስቱ ውስጥ ያለው ውስጠኛው ክፍል ባለ ሦስት በር ሲሆን የግራና ቀኙ በር ቅስት መልክ ሲኖረው፣ የመካከለኛው በር ግን የከፊል ክብ መልክ ያለው ነው፡፡ ግድግዳው ከጥርብ ድንጋይ የተሠራ፣ በዓምዱ መጨረሻ ላይ ዓምዱን ከቅስቱ የሚያያይዙ መከዳዎች የተሠሩለት ጌጠኛ ግድግዳ ነው፡፡


      በውስጠኛው ክፍል ውስጥ የሚገኙት ሦስት መናብር ለየት ያሉ ናቸው፡፡ መካከለኛው መንበር እጅግ ግዙፍ ከመሆኑም በላይ አሠራሩ የላሊበላን መናብርት የመሰለ ነው፡፡ በግራና በቀኝ ያሉት መናብርት እስካሁን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ካየኋቸው መናብርት ለየት ያሉ ናቸው፡፡ ቅርጻቸውም የኦሪቱን መንበረ ታቦት የሚመስሉ ሲሆኑ ካህናቱ መሥዋዕተ ኦሪት ሲሠዋባቸው የነበሩ ናቸው በማለት ይገልጣሉ፡፡ በላያቸው ያለውን ጌጥና ቅርጽም ጊዜ ወስዶ ማጥናት ይጠይቃል፡፡

      አስደናቂው ቅድስት

      በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ጥንታዊ ሚዛን፣ ከድንጋይ የተሠራ አገልግል፣ ከአንድ ወጥ እንጨት የታነጸ የመብራት ማብሪያ፣ ከአንድ ወጥ እንጨት የተሠራች አገልግል፣ የኦሪቱን የመሰለ የዘይት ማብሪያ ይገኛል፡፡ አሁን አገልግሎት የማይሰጥ ‹ተሰማ ጎንደር› የሚባል ከበሮም ነበራቸው፡፡ ይህ ከበሮ በማኅሌት ጊዜ ሲመታ እስከ ጎንደር ከተማ ይሰማ ስለነበር ‹ተሰማ ጎንደር› ተብሎ መሰየሙ ይነገራል፡፡
      ሰንደባ ኢየሱስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ብቻ ሳይሆን አካባቢውም ከመካከለኛው ዘመን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በአካባቢው አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ የሚነገረው ታሪክ፣ የአሥራ ሁለቱ ንቡራነ እድ ቦታዎች ናቸው ተብለው የሚነገሩት ቦታዎች፣  ደብሩ ከአቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ ጋር ተያይዞ የሚነገርለት ታሪክ፣ ጠለቅ ብለው ቢጠኑ በሀገራችን የሕዝቦች መስተጋብርና በቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን አገልግሎት ላይ ተጨማሪ ዕውቀት የሚሰጡን መረጃዎችን ልናገኝ እንደምንችል መገመት ይቻላል፡፡ የአካባቢው ሽማግሌዎችና የየደብሩ ታሪክ

      ከአንድ ወጥ እንጨት የተሠራው አገልግል
      ሰንደባ(ታዴዎስ)፣ ጉርሐች(ኤልሳዕ)፣ ቀልቀል (ገብረ ዮሐንስ)፣ ምጓዕ(በርሶማ)፣ ጥቃራ(መርሐ ክርስቶስ)፣ ደብረ ቅድስት(ጳውሎስ)፣ ዳንጉሬ(ቀሌምንጦስ)፣ ሰውበዳ(ዮሐንስ ከማ)፣ ዋሻ(እንድርያስ)፣ ገረገራ(አኖሬዎስ)፣ አግድ(እጬ ፊልጶስ)፣ ውሻ ጥርስ(እጬ ፊልሞና) ቦታቸው መሆኑን ይገልጣል፡፡ የሰንደባ ኢየሱስ መጽሐፍ ‹ቡራኬ ዘሰንደባ ታዴዎስ፣ ሲመት ዘኤልሳዕ፣ ወመጽዑ ፲ወ፪ ንቡራነ ዕድ ዘሀገረ ሴዋ ዘደብረ ሊባኖስ – ቡራኬ የሰንደባ ታዴዎስ፣ ሹመት የኤልሳዕ ነው፤ አሥራ ሁለቱ ንቡራነ ዕድ በሀገረ ሸዋ ከምትገኘው ደብረ ሊባኖስ መጡ› ይላል፡፡

      ‹ከኦሪት ዘመን ጀምሮ‹ አገልግሎት ላይ የነበረው የመብራት ማብሪያ
      እጅግ አስደናቂው ነገር አዲስ የሆነ የንቡራነ ዕድ ዝርዘር እዚህ ማግኘታችን፣ ከንቡራነ ዕዱ መካከልም ታዴዎስ፣ ኤልሳዕ፣ አኖሬዎስ፣ ፊልጶስ በሌሎች መጻሕፍት ከሚገኙት ዝርዝሮች ጋር ተመሳሳይ ሲሆኑ – ገብረ ዮሐንስ፣ መርሐ ክርስቶስ፣ ጳውሎስ፣ ቀሌምንጦስ፣ ዮሐንስ ከማ፣ እንድርያስ፣ እጬ ፊልሞና በንቡራነ ዕድ ዝርዝር የምናገኛቸው አዳዲስ ስሞች ናቸው፡፡ እነዚህን አድባራት በእነዚህ ቅዱሳን ርስትነት ቢጠሩም የየደብሩ ታቦታት ግን በሌሎች ቅዱሳን ስም የሚጠሩ ናቸው፡፡

      ከአንድ ወጥ ድንጋይ የተቀረጸው አገልግል
      ይህ ጉዳይ ሁለት ነገሮችን እንድንገምት ያደርጋል፡፡ በዛሬው ወሎና ኤርትራ እንደነበረው የአሥራ ሁለት አበው ሥምሪት በጎንደር አካባቢም ነበር ማለት ነው? ይህ ከሆነ ደግሞ የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ሥምሪት የሚያጠናክርልን ተጨማሪ ነገር አገኘን ማለት ነው፡፡ ወይስ ደግሞ የአካባቢው ቃላዊና ጽሑፋዊ መረጃ እንደሚገልጠው ከደብረ ሊባኖስ የተነሡ አሥራ ሁለት ንቡራነ ዕድ ወደዚህ አካባቢ መጥተው ነበርን? ያ ከሆነ ደግሞ በዚህ ዝርዝር ያገኘናቸውን አዳዲስ ንቡራነ ዕድ ታሪካቸውን መፈለግ የግድ ይለናል ማለት ነው፡፡

      ሁሉም ተጨማሪ ጥናት የሚጠይቁ ፍንጮች ናቸው፡፡ ፍላጎትና ዕውቀት ያለው ሰው አጥንቶ ቢነግረን እንመርቀዋለን፡፡

      በአውሮፓ ክርስቲያኖች ዘንድ የታወቀ አንድ የአራተኛው መክዘ ታሪክ አለ፡፡ ድኾችን እጅግ የሚወድ፣ የተቸገሩትን ለመርዳት ምንም ነገር የማያግደው፤ ከእራሱም አብልጦ ለሌሎችን የሚሞት አንድ ሰው ነበረ፡፡ ይህ ሰው በበጎ ምግባሩ የተነሣ ስሙ ተረስቶ ‹እኁ ቅዱስ- ቅዱሱ ወንድም› እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ በታሪክ ድርሳናትም የተመዘገበው በዚሁ ስም ነው፡፡ ሠርቶ የሚያገኘውን ምንም ለሌላቸውና ለምነው እንኳን ለማግኘት ዐቅም ላነሣቸው በመስጠት የታወቀ ነበር፡፡
      አንድ ጊዜ የሚሰጠው ነገር አጣ፡፡ ብዙ ችግረኞች ደግሞ መልካም ዜናውን ሰምተው ጥቂት ነገር ለማግኘት ወደ እርሱ ዘንድ መጡ፡፡ ምን ይስጣቸው፡፡ የሚያያቸው አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ሌላ አማራጭ የላቸውም፡፡ ብዙዎቹ ገንዘቡን ከጨረሰ በኋላ ከሩቅ ሀገር ሳይቀር በመምጣታቸው አዘኑ፡፡ መመለሻ እንኳን የላቸውም ነበር፡፡ በመጨረሻ እኁ ቅዱስ አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡ ‹‹እኔን ሽጡኝና ተካፈሉ› አላቸው፡፡ እነዚያ ችግረኞችም ምን አማራጭ ስላልነበራቸው እርሱን በባርነት ሸጡትና ገንዘቡን ተካፈሉ፡፡

      ይህ ታሪክ በታሪክነቱ ሲወሳ የኖረ ነው፡፡ አንዳንዴ ግን ታሪክ ራሱን ይደግማልና አንድን ታሪክ የሚካፈሉ ሁለት ሰዎች በሺ ዘመናት ልዩነት ውስጥ ሳይቀር ይፈጠራሉ፡፡ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥም እንደ ‹እኁ ቅዱስ› የተሸጡ ሰው አሉ፡፡ እዚያ ደቡብ – ወሎ ደሴ፡፡

      ደሴ የምትታወቀው በፍቅር ከተማነቷ፣ የኢትዮጵያ ባሕላዊ ዜማዎች አምባ በመሆኗ፣ በንጉሥ ሚካኤል ታሪክና በአይጠየፍ አዳራሽ፣ በዘመናዊው የኢትዮጵያ የመንግሥት ታሪክ ውስጥም በያዘችው ቦታ ብቻ አይደለም፡፡ ብዙ ያልተነገረላቸው ፣ በደሴ ተራሮች ላይ የሚያበሩ፣ የሚንቀሳቀሱ፣ የሚተነፍሱና ሕይወት ያላቸው የደሴ ውድ ቅርስም አሉ፡፡

      እኒህ ሰው የትውልድ ቦታቸው ወሎ እንዳልሆነ በቅርበት የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡ ምናልባት ወደ ሰሜን ሸዋ አካባቢ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ እስካሁን ግን የተወለዱበትን ቦታና ዘመን በርግጠኝነት የሚያውቅ የለም፡፡ እርሳቸውም ሃይማኖታቸውንና ምግባራቸውን እንጂ ሰው ትውልዳቸውንና ጎሳቸውን እንዲጠይቃቸውም እንዲያውቅላቸውም አይፈልጉም፡፡ ከጥንት ጀምሮ የሚያውቋቸው የደሴ ከተማ ሽማግሌዎች ግን እርሳቸውን ያወቁበትን ጊዜና በዚያ ጊዜ የስንት ዓመት ሰው ሊሆኑ እንደሚችሉ በመገመት እድሜያቸውን በሰባና ሰማንያ መካከል ይገምቱታል፡፡ ወደ ጎንደር ለትምህርት ሲሄዱ ደሴ ደረሱ አሉ፡፡ እዚያ የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናትና የተጎዱ ሰዎችን አዩ፡፡ እዚህ በተግባር የሚሠራ ሥራ እያለ እዚያ የቃል ትምህርት ለመማር ምን ወሰደኝ ብለው እዚያው ደሴ ቀሩ አሉ፡፡

      እኒህ ሰው የሚታወቁት በሥራና በፍቅር ነው፡፡ በደሴ ከተማ የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናት በማሳነጽ፣ ታሪክ ሲዘክረው የሚኖር አሻራ አኑረዋል፡፡ እንዲያውም እርሳቸው ካልገቡበት የሚሳካ አይሆንም ብለው ደሴዎች እስኪገምቱ ድረስም ደርሰዋል፡፡ እርሳቸው ካዘዙ ምደርም ትታዘዛለች እንኳን ሰው ይባላል፡፡ የርሳቸው በጎ ሥራ ግን በዚህ የሚያቆም አይደለም፡፡ የተቸገረና የተጨነቀ ሰው ካገኙ ግንባር ቀደም ደራሽ ናቸው፡፡ ለርሳቸው ዘርና ሃይማኖት ሰውን ለመርዳት መመዘኛዎች አይደሉም፡፡ ሰውነት ብቻ ይበቃቸዋል፡፡ ይህ ርዳታቸው ከመከራ ያወጣቸው፣ ከችግር የታደጋቸውና ሕይወታቸውን ያቀናላቸው ሰዎች ስለ እኒህ አባት ሲያወሩ ከማያቋርጥ ዕንባ ጋር ነው፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ከንግግር ይልቅ እርሳቸውን እያሰቡ ዝም ብለው በማልቀስ ይገልጧቸዋል፡፡

      መቼም ለአንዳንዱ አብዝቶ አይደል የሚሰጠው፡፡ እርሳቸው የአካባቢ ጥበቃ አርበኛም ናቸው፡፡ በዚህ የእርግና እድሜያቸው እንኳን መኮትኮቻና መቆፈሪያ፣ አካፋና ባሬላ ይዘው በደሴ ተራሮች ላይ ዛፍ ሲተክሉ ይውላሉ፡፡ ደሴን በአራቱ መዓዝን ስታዩዋት አረንጓዴ ብትሆንባችሁ አትገረሙ፤ እርሳቸው ከአርባ ዓመት በላይ ለፍተውላት ነው፡፡ ለእርሳቸው ዛፍ የሚቆርጥ ቀርቶ ቅጠል የሚበጥስም የማርያም ጠላት ነው፡፡ አይከፈላቸውም፤ አልተመደቡም፤ ደብዳቤ የሰጣቸው የለም፤ እርሳቸው ግን የሀገሬ መራቆት የኔ መራቆት ነው ብለው ደን ሲተክሉና ሲከባከቡ ይኖራሉ፡፡

      የእኒህን አባት ስም የሚያውቀው የለም፡፡ ስማቸው ተረስቷል፡፡ ስማቸው የተረሳው ሕዝብ ሌላ የፍቅር ስም ስላወጣላቸው ነው፡፡ ሕዝብ የንቀት ስም፣ የውርደት ስም፣ የሃፍረት ስም ይሰጣል – ለጠላው፡፡ ሕዝብ የፍቅር ስም፣ የክብር ስም፣ የቁልምጫ ስም ይሰጣል – ላፈቀረው፡፡ ለእርሳቸውም ወላጆቻቸው ያወጡላቸውን ስም የሚያስረሳ ስም ሰጥቷቸዋል፡፡ መፍቀሬ ሰብእ (ሰውን የሚወድድ፣ ሰውም የሚወደው) የሚል ስም፡፡ አባ መፍቀሬ ሰብእ ይባላሉ፡፡

      ድፍን ደሴ ይታዘዛቸዋል፡፡ ንጽሕናቸውንና ሰው ወዳጅ መሆናቸውን ይመሰክርላቸዋል፡፡ ሙስሊሙም ክርስቲያኑም እኩል ልጃቸው ነው፡፡ የግሼንን መንገድ ሲያሠሩ በደሴ ከተማ የታወቁት የሙስሊም ባለሀብት ‹ሃምሳ ሺ ብር ሰጡኝ› ብለው ነግረውኛል፡፡ ቤታቸው ብትገቡ ትደነቃላችሁ፡፡ ወንበርና አልጋ ነው ያላቸው፡፡ አልጋው ላይ መጻሕፍት በክብር ተደርድረዋል፡፡ ‹‹አልጋ ለንጉሥ ነው፤ ነገሥታቱ ደግሞ መጻሕፍቱ ናቸው፡፡ አልጋው ላይ የሚኖሩት እነርሱ ናቸው›› ይላሉ፡፡ ሰው ለሀገሩና ለወገኑ መልካም ሲሠራ ካዩ የለበሱትንም ካባ ቢሆን አውልቀው ይሸልማሉ፡፡ ስለ እርሳቸው ሲነገር አይወዱም እንጂ ስለ መልካም ሰዎች ተናግረው አይጠግቡም፡፡

      አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፡፡

      የደሴ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተጀመረና ለመጨረስ ገንዘብ አጠረ፡፡ ወዲህ ቢባል ወዲያ ገንዘብ ከየት ይምጣ፡፡ የደብሩ አስተዳዳሪ አውጥተው አውርደው አንድ ሃሳብ አመጡ፡፡ አባ መፍቀሬ ሰብእ እንደ እኁ ቅዱስ መሸጥ አለባቸው፡፡ ሄዱና አማከሯቸው፡፡ ‹‹አባ እርስዎን ሸጠን የገብርኤልን ቤተ ክርስቲያን ልንጨርስ ነው›› አሏቸው፡፡ ‹‹እኔ ምን አወጣላችኋለሁ›› አሉ ገርሟቸው፡፡ ‹‹በደንብ ያወጣሉ፡፡ ብቻ ለመሸጥ ይስማሙልን›› አሏቸው፡፡ ‹‹ካወጣሁ እንኳን እንድ ጊዜ ዐሥር ጊዜ ልሸጥ›› አሉ አባ መፍቀሬ ሰብእ፡፡

      በእርሳቸው ስም የርሳቸው ፎቶና ስም ያለበት ቶምቦላ ተዘጋጀ፡፡ ድፍን ደሴ – ሙስሊም ከክርስቲያኑ ተሻምቶ ገዛው፡፡ መፍቀሬ ሰብእ አይደሉ፡፡ ያልተሰበሰበውን ጨምሮ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ተሸጡ – አባ መፍቀሬ ሰብእ፡፡ ሌሎቹ የሀገር ሀብት፣ ቅርስና ታሪክ በሚሸጡበት ዘመን አባ መፍቀሬ ራሳቸውን ለሀገርና ለወገን፣ ለእምነታቸውና ለዓላማቸው ሸጡ፡፡ ሌሎች በቤተ እምነቶች ውስጥ ተደብቀው ለጥቅማቸው ሲሉ የምእመናንን ገንዘብ በሚበሉበት ዘመን፤ ለምእመናን ሲሉ አባ መፍቀሬ ሰብእ ተሸጡ፡፡ ሌሎች በጎቻቸውን ለራሳቸው ሲሸጡ፤ አባ መፍቀሬ ግን ለበጎች ሲሉ ራሳቸውን ሸጡ፡፡ እልም ባለ በረሃ ውስጥ የምትገኝ ቀዝቃዛ ምንጭ ተስፋ የቆረጠውን ሁሉ እንድታረካ፤ ታማኝነትና ሕዝብን መውደድ፣ በዓላማ መኖርና ለዓላማ መሠዋት እየጠፋ ባለበት ዘመን፣ እርሳቸውን ማየት እንደዚያ ነው፡፡

      © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

       
      ጌታቸው ኃይሌ

      ኮሌጅቪል፤ ታኅሣሥ 12 ቀን፤ 2006 (12/21/2013)
      ፕሮፌሰር አምሳሉ አክሊሉና እኔ አብሮአደግ አብሮጎልመስ፥አብሮአረግ ነን። 1947 . . የእንግሊዝ ፊደል አብረን ከቆጠርንበት ጊዜ አንሥቶ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ አንድ ዓይነት ትምህርት ለማስተማር እስከተቀጠርንበት ጊዜ ድረስ በቦታ እንኳን ሳንለያይ አብረን ነበርን። በዚህ አምላክ በመረቀልን ረጅም ጊዜ አንድ ቀንም አንዳችን ሌላውን ቅር የሚያሰኝ ቃል ከአፋችን መውጣቱ ትዝ አይለኝም። የተለያየ ጠባይ ያላቸው ሰዎች መፋቀር፥ መተሳሰብ፥ መረዳዳት፥ እንደሚችሉ የአምሳሉና የእኔ ወዳጅነት ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ለጻፍኩት የሕይወት ታሪኬ ርእሱን የአምሳሉና የጌታቸው ታርክ ብለው የተገባ መሆኑን ያነበበው ሁሉ ሊገምት ይችላል። ረጅሙን በወንድማማችነት አብሮ የመኖር ሕይወታችንን ለማስቀረት ደርግና ሞት ሸመቁበት።

      አምሳሉን በዚህ ረጅም ዘመን እንደማውቀው፥ ሞት ቀርቶ ሕመም ይደፍረዋል ብየ አልገመትኩም፤ እሱም አይገምትም ነበር። ሙሉ ጤነኛ ነበር፤ እኔ ሐኪም ቤት ስመላለስ፥ እሱ ሐኪም ቤቱን የሚያውቀው እንደኔ ያሉ ሕመምተኞችን ለመጠየቅ ሲሄድ ነበር።አምሳሉ ጤነኛ ብቻ ሳይሆን ሕይወቱ በተግባር የተመላ ነበር። ሥራ ሲወጥን፥ ሥራ  ሲያጣድፍ፥ ሥራሲፈጽም፥ እንቅልፍ አልነበረውም። ሲጫወት፥ ሲያጫውት ሁሉን ያስደስት ነበረ። በዚህ ሁሉ ምክንያት መቶ ዓመት ሳይሞላው ሊሞት ቀርቶሆዴን ጎረበጠኝየሚል እንኳን አይመስለኝም ነበር። ግን በኢሳይያስ አፍ፥እስመ፡ ኢኮነ፡ ምክርየ፡ ከመ፡ ምክርክሙ፤ ወኢኮነ፡ ፍኖትየ፡ ከመ፡ ፍኖትክሙ።” (ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ አይደለም፤ መንገዴም እንደመንገዳችሁ አይደለም።) የሚለው አምላክ ወንድሜን አምሳሉን፥ እሱ ባሰበው፥ እኛ ባላሰብንበት ዕለት ወሰደው። ሳንሰነባበት ተለያየን። ጽሎቴ ዕለተ ዕረፍቱን የመረጠለት አምላክ ለነፍሱ ከወዳጆቹ ማህል የተደላደለ ቦታ እንዲመርጥላት ነው።
      አምሳሉ ሥራ የሚፈጸምለት ታታሪ ሠራተኛ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ብልህና አስተዋይ በመሆኑ ጭምር ነው። በብልህነቱ፥ በዐዋቂነቱ እቀናበት እንደነበረ ከእሱ በቀር ማንም አያውቅም። ሊሠሩ የሚገባቸውን ሥራዎች ማንም ሳያያቸው እሱ ቀድሞ ያያቸዋል። አምሳሉ በዘመኑ ሥልጣኔ በተራመዱት አገሮች በአንዱ ተወልዶ ቢሆን ኖሮ፥ በሀብትም ሆነ በሙያ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ ታዋቂዎች አንዱ ይሆን ነበር። ሲዘፍን፥ ቲያትር ሲሠራ፥ ያፈዝ ነበረ።
      አምሳሉ ቀለመወርቅን በማግኘቱ ዕድለኛ የኖነውን ያህል እሷም አምሳሉን የመሰለ አጫዋችና አፍቃሪ የሕይወት ጓደኛ በማግኘቷ ዕድለኛ ነች። በአካል ቢለያዩም ትዝታውንና ጨዋታውን እያስታወሰች እንዳዲስ ስትስቅ እንደምትኖር እርግጠኛ ነኝ።  
      አምሳሉ ቀለመወርቅን ለማግኘት ወዲያ ወዲህ ሲል እኔም ትንሽ ሚና ተጫውቻለሁ፤ ከመልካም ቤተሰብ የተወለደችና ጎልማሳ የምታፈዝ ቆንጆ ልጃገረድ ስለነበረች ለትዳር የሚመኟትና የሚፈልጓት ጥቂቶች አልነበሩም። አንዱ በተለየ ጓደኞቹን አስሰልፎ  ሊያስፈራራሲመጣ አጭር ብትፈልግ አጭር፥ ረጅም ብትፈልግ ረጅም ሆነን መጥተንብሃልና የምትፈልገውን አሳየንና እናሳይ አልነው። ማን እንዳሸነፈ የአምሳሉና የቀለመወርው ልጆች ምስክር ናቸው።
      እኔም እንደቀለመወርቅ በጨዋታው ሳስታውሰው እኖራለሁ። በትምህርት ገበታ ላይ ብቻ ሳይሆን አገር ለመጎብኘትም አብረን ብዙ ነገር አይተናል። ኪሳችን የተማሪ ኪስ ስለነበረ፥ አገር የምናየው መንገድ ላይ እየቆምን ባለመኪና ሲመጣ እየለመንን ነበር። የለማኝ መራጭ ስለሌለው፥ የቆመልን ሁሉ ይወስደናል። አንዳንድ ጊዜ ባለመኪናዎቹ ሁለት ሰው ስለማይወስዱ አውላላ ሜዳ ላይ እንለያያለን። ቀጠሯችን ባቡር ጣቢያ ነው። አንድ ቀን ባቡር ጣቢያ ስንገናኝ፥አምሳሉ፤ የዛሬው ጉዞህ እንዴት ነበር?” አልኩት።
      እረ እባክህ ተወኝአለ።ምነው?” ብለው፥አንዲት ሴትዮ በዶቅዶቂት አሳፈረችኝአለኝ።ታዲያ ምኑ ነው፥ እረ እባክህ ተወኝ የሚያሰኘው?” ብለው።እንዳልወድቅ ትከሻዋን ነበር የያዝኩት፤ እንደሱ አይደለም፤ ወገቤን ያዝአለችኝ። ልንሄድበት ስንደርስ ልቀቀኝ ባትለኝ እዚያው ተጣብቄ ልቀር ነበርአለኝ።
      አይ አምሳሉ፤ ለካ አንተም እንደሌላው ነህ!! ግን የምንጽናናባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉን። በጤና ኖረሃል። መልካም ባለቤት፥ መልካም አባት፥ ታማኝ ወዳጅ ሆነሃል። የልጅ ልጅ ስመሃል። በዕውቀትህ የአገርህን ልጆች አገልግለሃል። ለስምህ ሐውልት ተክለሃል። የፈለከውን ለማድረግ አምላክ ዕድል ሰጥቶሃል። ክብሩ ይስፋ። ለዘላለሙ ሕይወት በሚኬድበት መንገድ የሄድከው የማይቀር ቢሆን ነው። ቤተሰብህን፥ ዘመዶችህን፥ ወዳጆችህን እግዚአብሔር ያጽናቸው። እንደኔ ምስጢረኛ አያሳጣቸው።
      ምንጊዜም የማይረሳህ ወንድምህ
      ጌታቸው ኃይሌ

      አብዛኞቻችን የመዝገበ ቃላትን አጠቃቀም የተማርንበትንእንግሊዝኛአማርኛ መዝገበ ቃላት›› ያዘጋጁት ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ 83 ዓመታቸው ታኅሣሥ 11 ቀን 2006 ዓም ዛሬ ዐረፉ፡፡ ዶክተር አምሳሉ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ከሚባልበት ዘመን ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያስተማሩ መምህር ነበሩ፡፡ 

      ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን፡፡

      በየዓይነቱ የሚባል ምግብ መቼም ታውቃላችሁ፡፡ በጾም ጊዜ የሚዘወተር የሀገራችን ምግብ ነው፡፡ አንዳንድ ቦታ ሦስት ዓይነት ሲኖረው አንዳንድ ቦታ ደግሞ ሠላሳ ዓይነት አለው፡፡ ‹በየዓይነቱ› የሚለውን የምግብ ቤቶች መዝገበ ቃላት ሲተረጉመው ‹‹አንድ ቀይ የምሥር ወይም የሽሮ ወጥ በእንጀራው መካከል ጎላ ብሎ ይቀመጥና እነ አልጫ ሽሮ፣ እነ አልጫ ምስር፣ እነ ምጣድ ሽሮ፣ እነ ቃሪያ፣ እነ ስልጆ፣ እነ ቲማቲም ፍትፍት፣ እነ አበሻ ጎመን፣ እነ የፈረንጅ ጎመን፣ እነ ሩዝ፣ እነ ሱፍ ፍትፍት፣ እነ ቀይ ሥር፣ እነ ድንች ወጥ፣ እነ ተልባ ፍትፍት በዙሪያው አጅበው ይሰለፋሉ›› ማለት ነው ይላል፡፡

      በያይነቱ ሕግም አለው፡፡ ባይጻፍም እኛ ‹የበያይነቱ ሕግ› ብለነዋል፡፡ በበያይነቱ ሕግ መሠረት በመካከል የሚቀመጠው ዋናው ወጥ በቀላሉ የሚገኝና የሚሠራ መሆን አለበት፡፡ ለዚህም ነው ወይ ምስር ወይም ሽሮ የሚሆነው፡፡ ርካሽነቱ የጥሬ ዕቃው ብቻ ሳይሆን በአንድ ትልቅ ድስት ውስጥ በቀላሉ በብዛት ሊሠራ የሚችል ማለትም ነው፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ምሥርና ሽሮ ወጥ፣ በልቅሶ ቤትም ዕድሮች በብዛት ይዘዋቸው የሚመጡት፡፡  አንድ ድንኳን ሙሉ ለቀስተኛና ዕድርተኛ ለማብላት እንደ ቀይ ምስርና ሽሮ ወጥ የሚበቃ አይገኝም፡፡

      ሁለተኛው የበያይነቱ የሕግ ዐንቀጽ ደግሞ በወጥ ጭማሪ ጥያቄ ጊዜ ሊጨመር የሚችለው ዋናው ወጥ (ቀይ ሽሮው ወይም ምሥር ወጡ) ነው ይላል፡፡ እንጀራ ሲተርፍ ወይም እንጀራ ሲጨመር የወጥ ጭማሪ ቢጠየቅ ዋናውን ወጥ ማስጨመር ይቻላል፡፡

      ሦስተኛው የበያይነቱ ሕግ በዋናው ወጥ ዙሪያ ለሚመጡት ዓይነቶች የቁጥር መጠን እንደሌላቸው ይደነግጋል፡፡ ሦስትም ሆኑ አሥራ ሦስት ችግር የለውም፡፡ ቁም ነገሩ ዋናውን ወጥ አጅበው በዙሪያው መኮልኮላቸው ነው፡፡ አራተኛውና እነዚህን በዙሪያው ያሉ ወጦችን የሚመለከተው ሕግ ደግሞ እነዚህ ወጦች ካለቁ አለቁ ነው ይላል፡፡ ዓይነት አይጨመርም፡፡ ዓይነት አለመጨመሩ ብቻ ሳይሆን በበያይነቱ ሕግ ዐንቀጽ አራት ንዑስ ዐንቀጽ አንድ መሠረት በምግብ ቤቱ ውስጥ ዋናው ወጥ አያልቅም እንጂ ዓይነት ሆነው የሚቀርቡት ወጦች ግን ሊያልቁ እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡ እንዲያውም በንዑስ ንዑስ ዐንቀጹ ላይ የዓይነቶቹ መጠን የምግቡ ሰዓት ሲጀመርና ሲያልቅ ሊለያይ እንደሚችልም ያስቀምጣል፡፡ ዋናው ወጥ ግን በብዛት ስለሚሠራ አያልቅም፡፡

      አምስተኛው የበያይነቱ ሕግ ዐንቀጽ ዋናውን ወጥ አጅበው የሚቀርቡት ዓይነት ወጦች ‹ወጥ› ወይም ‹ዓይነት› የሚለውን ስም እስከያዙ ድረስ የፈለጉትን ዓይነት፣ መጠን፣ ቅርጽና ጣዕም ሊኖራቸው እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ለምሳሌ ክክ ወጥ፣ ምጣድ ሽሮ፣ አልጫ ሽሮና አተር ፍትፍት በቅርጽና በስም ካልሆነ በቀር አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ ያው ሽሮ ነው፡፡ ነገር ግን በየራሳቸው ስምና ቅርጽ ይዘው ‹ዓይነት› ሆነው መቅረብ እንደሚችሉ ‹የበያይነቱ ሕግ ይፈቅድላቸዋል፡፡

      በበያይነቱ ሕግ ዐንቀጽ ስድስት መሠረት አንድ ምግብ ‹ዓይነት› ሆኖ የሚቀርበው በዋናነት ለመልኩና ቅርጹ እንጂ በውስጡ ላለው ይዘት እንዳልሆነ ይደነግጋል፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም እነ አበሻ ጎመን፣ እነ ጥቅል ጎመንና እነ ኪያር እሳት ካደበናቸው የምግብ ይዘታቸው በሙሉ እንደሚጠፋ ቢታወቅም ቅሉ፣ ድብን ብለው በስለው ‹ዓይነት› ሆነው ለመቅረብ የቻሉት፡፡

      በበያይነቱ ሕግ ዐንቀጽ ስድስት ንዑስ ዐንቀጽ ሦስት መሠረት ሁለት የበያይነቱ ወጦች የይዘትም ሆነ የቅርጽ ልዩነት ባይኖራቸውም ስማቸው ከተለያየ እንደ አንድ ወጥ ተመዝግበው መንቀሳቀስ ይችላሉ ይላል፡፡ አልጫ ምስርና ቀይ ምስር፣ አልጫ ድንችና ቀይ ድንች ቅርጻቸውም ሆነ ይዘታቸው አንድ ቢሆንም የስም ልዩነት ስላላቸው ግን ይኼው በዓይነትነት ተመዝግበው ቀጥለዋል፡፡

      በበያይነቱ ውስጥ እንደ ቃሪያ የሚያቃጥሉ፣ እንደ ምስር የሚጎረብጡ፣ እንደ ተልባ ፍትፍት የሚለሰልሱ፣ እንደ ሩዝ የአበሻ ምግብ ውስጥ ለምን እንደመጡ የማይታወቁ፣ እንደ ቲማቲም ፍትፍት የንጽሕናቸው ጉዳይ ሆድ ሲያጮኽ የሚውል፣ እንደ ስልጆና እንደ አተር ፍትፍት በአንድ ጉርሻ የሚያልቁ ምግቦችም እንዲካተቱ ሕጉ ይፈቅድላቸዋል፡፡

      በበያይነቱ ሕግ ዐንቀጽ ዐሥር መሠረት ዛሬ አንድ ዓይነት ሆኖ የቀረበ ወጥ ነገ ተለያይቶ ሁለት፣ ሁለት ሆኖ የነበረም እንድ ሆኖ ለመቅረብ እንደሚችል ይፈቅዳል፡፡ ለየብቻቸው ሲቀርቡ የነበሩት ቀሪያ፣ ቲማቲምና እንጀራ ከቅርብ ዘመናት ወዲህ የቲማቲም ፍትፍት ተብለው ኅብረት መሥርተው መጥተዋል፡፡ ‹ሽሮ ወጥ› ተብለው አንድ ላይ የነበሩት ‹ሽሮ ፈሰስ›ና ‹ሽሮ ተጋቢኖ› ሆነው በየራሳቸው መጥተዋል፡፡

      ይህን የበያይነቱን ሕግ አይተን እስኪ የሀገራችን የፖለቲካ ሕግና ባህል እንገምግመው፡፡ ፖለቲካችን ከበያይነቷችን ወይም በያይነቷችን ከፖለቲካችን ተወስዶ ሊሆን ከቻለስ?

      በበያይነቱ ሕግ አንድ ዋና ወጥ እንዳለው ሁሉ በሀገራችንም አንድ አውራ ፓርቲ አለ፡፡ ሌሎቹ በመጠናቸው አነስ አነስ ያሉ ወጦች ዋናውን ወጥ አጅበው እንደሚቀመጡ ሁሉ በሀገራችን ያሉት ከብሔረሰቦች ቁጥር የበለጡት ፓርቲዎችም ይህን አውራ ፓርቲ አጅበው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ይህ በበያይነቱ የሚገኝ ዋናው ወጥ ይኼው በያይነቱ ከተፈጠረ ጀምሮ ምስር ዋና ሆኖ የመካከሉን ዋና ቦታ እንደያዘው አለ፤ አንድም ዓይነት ሆኖ የገባ ወጥ ቦታውን እንዳልወሰደው ሁሉ በሀገራችንም ይኼው ዋናውም ወጥ ሆነ ዓይነቶቹ ዛሬም በዚያው ቦታቸው ናቸው፡፡

      በበያይነቱ ሕግ ዋናው ወጥ ይጨመራል እንጂ ዓይነት አይጨመርም፡፡ በሀገራችን ፖለቲካም አውራው እየጨመረም እየተጨመረም ይኼዳል እንጂ ዓይነቶቹ ካለቁ አለቁ ነው፡፡ ስንት ፓርቲ ዓይነት ሆኖ በሆነ የምርጫ ዘመን ከመጣ በኋላ በሌላ ጊዜ ‹ጨምሩ› ስንል ‹አልቋል፤ ከፈለጋችሁ ምስር ጨምሩ› ተብለናል፡፡  በበያይነቱ ወጥ ዋናው ወጥ በትልቁ ሰታቴ ነው የሚሠራው፤ እንዳያልቅ፡፡ በሀገራችንም ዋናው ፓርቲ በትልቁ ነው የተሠራው፡፡ ወደ ዋናው ወጥ ሰታቴ የማይገባ እህል፣ የማይጨመር ውኃ፣ የማይደረግ ቅመም የለም፡፡ ችግሩ አንዳንዱ በሚገባ ያልተቀመመ፣ አንዳንዱ ‹ኤክስፓየር› ያደረገ፣ አንዳንዱ ምን ሳይጠቅም እንዲሁ የገባ፣ አንዳንዱ እንደ ሽንኩርቱ ያረረ፣ እየሆነ ነው ችግሩ፡፡ ወጥ ሠሪዎቹም ዋናው ዓላማቸው ወጡ እንዲሰፋ፣ እንዲበዛ፤ ከዚያም አልፎ ሌሎቹ ዓይነቶች ሲያልቁ ዋናው ወጥ እንዳያልቅ ማድረግ ነውና ያገኙትን የእህል ዓይነት ሁሉ እያስገቡበት ተቸገርን፡፡

      በልቅሶ ቤትም፣ በግብዣም፣ በድግስም፣ በቤታችንም፣ በየመሥሪያ ቤቱ ካፍቴሪያዎችም፣ በብዛትና በስፋት የምናገኘው ይኼንኑ ዋናውን ወጥ ሆነ፡፡ አንዳንዶች ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት ይህንን ዋናውን ወጥ መሥራት ቀላል፣ ብዙም ችሎታ የማይጠይቅ፣ ርካሽና በትልቅ ዕቃ የሚሠራ፣ ብዙም መሥዋዕትነት የማይጠይቅ ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡

      እንደ በያይነቱ ሁሉ የሀገራችን ፓርቲዎች የቁጥር መጠን የላቸውም፤ በብሔረሰቦች ቁጥር መጠን መስሎን ነበር፤ አሁንማ ከዚያም ቁጥር አለፈ፡፡ አንዳንዶቹ የበያይነቱ ወጦች በማንኪያ ተመጥነው የሚቀርቡት ከአንድ ጉራሽ እንደማያልፉ ሁሉ፣ አንዳንዶቹ ፓርቲዎች በዐሥር ሰው ይመሠረቱና ከአንድ ምርጫ ወይም ከአንድ ስብሰባ፣ አለፍ ካለም ከአንድ ሰላማዊ ሰልፍ አያልፉም፡፡ ቀይ ሽሮ፣ አልጫ ሽሮ፣ ሽሮ ፍትፍት፣ ክክ ወጥ፣ አተር ፍትፍት እየተባለ አንዱን ባቄላ ወይም አተር በዐሥር ዓይነት እንደሚያመጡት ሁሉ ከስማቸው በቀር የፕሮግራም፣ የግብ፣ የአደረጃጀትና የአካሄድ ልዩነት የሌላቸው ፓርቲዎች ሞልተውናል፡፡ ልዩነታቸው አንዱ አበበን ነጻ ሲያወጣ ሌላኛው ጫልቱን፣ ሌላኛው ደግሞ ኪሮስን የቀረውም ደንቦባን ነጻ ማውጣቱ ነው፡፡

      በበያይነቱ ውስጥ እንደሆነው ሁሉ እንደ ቃሪያ አሠራራቸው የሚያቃጥል፣ እንደ ስልጆ የሚሰነፍጥ፣ እንደ ቀይ ሥር መልክ እንጂ  ይዘት የሌላቸው፣ እንደ ሩዝ እንዴት ፓርቲ ሊሆኑ እንደቻሉ ግራ የሚያጋቡ፣ እንደ ቲማቲም ፍትፍት ሆድ ማስጮህ እንጂ አእምሮ መገንባት የማይችሉ ፓርቲዎችም አሉን፡፡

      በበያይነቱ ወጥ ውስጥ እንዳሉት የሐበሻ ጎመንና ጥቅል ጎመን፤ በፖለቲካው እሳት በመንተክተካቸው የተነሣ የምግብ ይዘታቸው የጠፋ፡፡ ቢበሏቸው የማይጠቅሙ፣ ቢተዋቸው የማይጎዱ ዓይነት ፓርቲዎችም አሉን፡፡ እንደ ቃሪያና ቲማቲም ለየብቻ ጀምረው እንደ ‹ቲማቲም ፍትፍት› አንድ ሆነው የመጡ፣ እንደ ‹ሽሮ ወጥ› እንደ ሆነው ጀምረው እንደ ሽሮ ፈስስና ሽሮ ተጋቢኖ ተለያይተው የቀጠሉ ፓርቲዎችም አሉን፡፡

      በበያይነቱ ምግብ የምግብ ሰዓት ሲጀመር የነበሩት ዓይነቶች እያለቁ ሄደው በስተ መጨረሻ በያይነቱ ራሱ አልቆ ‹ምስር ወይም ሽሮ ነው ያለን› እንደሚባለው ሁሉ በሀገራችን ከሃያ ዓመት በፊት ምርጫና ዘመቻ ሲጀመር እንደ አሸን ፈልተው የነበሩት ‹በዴሕ› ና በ‹ዴድ› የሚጠሩ ፓርቲዎች አሁን የት እንደደረሱ የሚያውቅ የለም፡፡ ሁሉም ዓይነቶች አልቀው ዋናው ወጥ ብቻ ቀረ፡፡

      እንግዲህ የኛ የፖለቲካ ሥርዓት በያይነቱ ምግባችንን ሳይመስል አይቀርም፡፡ ምናልባት ምግቡ ከፖለቲካው ይቀድማልና ፖለቲካው ከምግቡ አሠራሩን ቀድቶት እንደሆነ እስኪ እንመርምረው፡፡ ምናልባት በያይነቱን ብናስተካክለው ፖለቲካው ይስተካከል ይሆን?

      ቸር ይግጠመን፡፡

      © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽት ላይ የወጣ ነው

      የዛሬ 600 ዓመት አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ የተባለ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ‹አርጋኖን› የተሰኘ መጽሐፍ ይደርሳል፡፡ ይህንን መጽሐፍ የተመለከቱ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንትም እጅግ ያደንቁና ለንጉሡ ለዐፄ ዳዊት ያቀርባሉ፡፡ ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም መጽሐፉን ተመልክተው በማድነቅ በወርቅ ቀለም እንዲጻፍ አዘዙ፡፡ አባ ጊዮርጊስንም ሸለሙ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላም አባ ጊዮርጊስ ‹መጽሐፈ ምሥጢር› የተባለ መጽሐፍ ደረሰ፡፡ ይህንን የተመለከቱ ሊቃውንትም አድናቆታቸውን ‹‹ቄርሎስና ዮሐንስ አፈወርቅ በሀገራችን ተገኙ፤ ኢትዮጵያም እንደ ሮምና ቁስጥንጥንያ፣ እንደ እስክንድርያም ሆነች› ብለው በማሸብሸብ ነበር የገለጡት፡፡

      ከስድስት መቶ ዓመታት በኋላ ያለችው ኢትዮጵያ ግን ለደራሲዎቿ ቦታ የሌላት፣ ማንበብና መጻፍም ብርቅ የሆነባት፣ ድራፍት ቤት እንጂ መጻሕፍት ቤት፣ ጫት ቤት እንጂ የመጻሕፍት ማከፋፈያ ቤት የማይበረታታባት ሀገር ሆናለች፡፡ ክልል ያላት በክልል ደረጃ የሚጠቀስ ቤተ መጻሕፍት የሌላት፣ መንግሥት ያላት፣ ነገር ግን መንግሥት ዕውቅና የሚሰጠው ድርሰትና ደራሲ የሌላት ሀገር ሆናለች፡፡ ለጀማሪ አቀንቃኞች የሰጠችውን አይዶል እንኳን ያህል ለበካር ደራስያን ለመስጠት ያልፈቀደች ሀገር ሆናለች፡፡ ለአርተር ራምቦ እንጂ ለጸጋዬ ገብረ መድኅን ቦታ የሌላት ሀገር ሆናለች፡፡ ለፑሽኪን እንጂ ለሐዲስ ዓለማየሁ አደባባይ የሌላት ምድር ሆናለች፡፡ ደራሲዎቿ ሲኖሩ ሳይሆን ሲሞቱ ዜና የምትሠራ ሀገር ሆናች፡፡

      ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ መጽሐፈ ብርሃን በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ‹‹እስመ ጽሙዐን ለትምህርት ብሔረ ኢትዮጵያ ኄራን – ምርጦቹ የኢትዮጵያ ሰዎች ትምህርትን የተጠሙ ናቸው›› ይላል፡፡ በዚህ ጥማታቸውም የተነሣ ሕንድ ተሻግረው እነ መጽሐፈ በርለዓምን፣ ግሪክ ገብተው እነ ዜና እስክንድርን፣ አምጥተው ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ንግሥተ ሳባ እንኳን ወደ ሰሎሞን የሄደችው ‹ጥበብን ፍለጋ› መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡ እዚህች ሀገር ውስጥ ቆዳ ለጫማ ከመዋሉ በፊት ለመጽሐፍ ነበር የዋለው፤ ብርዕ ለማገዶ ከመዋሉ በፊት ለጽሕፈት ነበር የዋለው፤ ቀለም ለግድግዳ ከመዋሉ በፊት ለፊደል ነበር የዋለው፡፡

      በዚህች ሀገር ጥንታዊ ታሪክ መጻሕፍትን መጻፍ ብቻ ሳይሆን፤ ማንበብ፣ ማስነበብ፣ ማስጻፍ፣ ሲነበቡ መስማት ጭምር እጅግ የተከበረ ነገር ነበር፡፡ የተከበረ ብቻም ሳይሆን የቅድስናም ምንጭ ነበር፡፡ በየገድላቱና ድርሳናቱም ‹የጻፈ ያስጻፈ፣ ያነበበ የተረጎመ፣ የሰማ ያሰማ› የሚሉት ቃል ኪዳኖች መጻፍን ብቻ ሳይሆን የተጻፈውን ማንበብ፣ ማንበብ ለማይችሉትም ድምጽን ከፍ አድርጎ እያነበቡ ማሰማት፣ ሲነበብም በጽሞና መስማት ጭምር ዋጋ እንዲኖራቸው ያደረጉ ነበሩ፡፡ የደራስያኑ መጻሕፍት እንዳሁኑ በማተሚያ ማሽን በብዛት አይባዙም ነበርና ለጸሐፊዎች ከፍሎ ማስጻፍ፣ ዋጋ ተቀብሎ በሚገባ መጻፍ የሚያስመሰግን የሚያጸድቅም ነገር መሆኑን ኢትዮጵያውያን ያምኑ ነበር፡፡

      ለዚህም ነው በዚያ ሁሉ የእርስ በርስ ጦርነቶች ውስጥ አልፋ፣ አንዳንድ ጊዜም ሀገሪቱ ራስዋ ከጥፋት በተአምራት የተረፈችባቸውን ታሪኮች አስመዝግባ፣ ነገር ግን አያሌ የብራና መጻሕፍትን እስከ ዛሬ ድረስ ጠብቃ ለማቆየት የቻለችው፡፡ በመከራም ጊዜ ከከብቶቿና ከበጎቿ፣ ከእህሏና ከማሯ፣ ከወርቋና ከብሯ ይልቅ መጻሕፍቷን ለማቆየት ነበር ሩጫዋ፡፡ በገድለ ዜና ማርቆስ ላይ በ15ኛው መክዘ መጨረሻ ላይ የተፈጠረውን የእርስ በርስ ጦርነት በመሸሽ የገዳሙ መነኮሳት ከሸዋ ወደ ደቡብ ጎንደር ሲሰደዱ ከአንድ ሺ የሚበልጡ መጻሕፍትን በሦስት ቦታ ዋሻ ውስጥ ደብቀው ማስቀመጣቸውን ይነግረናል፡፡

      የደራስያኑ የድርሰት ሥራ የተወደደ፣ ባለቤትነቱም የተከበረ በመሆኑ በቃል የሚፈስሰው ቅኔ እንኳን ‹የእገሌ ቅኔ; እየተባለ ይጠቀስ ነበር እንጂ የባለቤትነት መብቱን የሚያስከብርለት ሕግና ሕግ አስከባሪ አካል የለም ተብሎ አይደፈርም ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ጎጃም ከመምህሩ የሰማውን ቅኔ ትግራይ ሄዶ እንደራሱ አድርጎ ሲቀኝ የተሰማ ተማሪ ቅኔውን ሲጨርስ ‹ቅኔያቸውስ ደረሰን፣ ለመሆኑ የኔታ ደኅና ናቸው?› የሚል ውርደት የገጠመው ለደራስያኑ የባለቤትነት መብት ጠበቃ የሆነ ማኅበረሰብ ስለነበረን ነው፡፡ የጎንደሩ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ለሸዋው ደብረ ብርሃን ሥላሴ 2000 መክሊት ወርቅ  ‹ደብረ ብርሃን› የሚለውን ስም ለመጠቀም የከፈለውኮ ለባለቤትነት መብት ክብር የነበረው ሕዝብ ስለነበረን ነው፡፡

      ዛሬ ግን በዚህች ታሪካዊት ምድር፤ በዚህች ሥነ ጽሑፍ ተፈጥሮ፣ አድጎ፣ ዳብሮ፣ ሠልጥኖ ለወግ ለማዕረግ ደርሶባት በነበረች ሀገር፤ ደራስያንና ድርሰት የተረሱ ዕቃዎች ሆነዋል፡፡ እነርሱን የሚያበረታታ፣ የሚሸልም፣ ዕውቅና የሚሰጥ፣ ማዕረግ የሚሰጥ፣ በዝተውና መልተው ምድርን እንዲሞሏት የሚያደርግ ማኅበረሰብም፣ ተቋምም መንግሥትም አጥታለች፡፡

      በታደሉት ሀገሮች የዓመቱ ምርጥ ደራሲ፣ የዓመቱ ምርጥ መጽሐፍ፣ በዓመቱ በብዙ ቅጅ የተሸጠ መጽሐፍ እየተባለ ደራስያንንና ድርሰትን የሚያበረታታ፣ እንደ ጻፉበት ጉዳይም በየዘርፋቸው የሚሸልም ተቋምና መንግሥት አለ፡፡ በስማቸው መንገዶችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ አደባባዮችን፣ ፓርኮችን፣ ሙዝየሞችን የሚሰይም መንግሥትና ሕዝብ አላቸው፡፡ ሥራዎቻቸው ብቻ ሳይሆን የሠሩባቸው ቤቶችና የተጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች ሳይቀር የሀገሪቱ ታሪክና ቅርስ ሆነው ይጎበኛሉ፡፡

      ለመሆኑ የገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ የብላታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል፣ የአለቃ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ የአቤ ጉበኛ፣ የበዓሉ ግርማ፣ ቤታቸው የት ነው? የት ነበር የጻፉት? ረቂቃቸው አለን? የጻፉበት ብዕር አለን? ምን ሰየምንላቸው? በምን እናስታውሳቸዋለን? ለመሆኑ የኢትዮጵያን የድርሰት ጉዞ የሚያሳይ አንድ ሙዝየም እንኳን አለን? የሺ ዓመታት የሥነ ጽሑፍ ታሪክ የምንደሰኩር ጀግኖች ሥነ ጽሑፋችን ከየት ተነሥቶ የት ደረሰ? የድርሰት ጉዟችን ከየት መጥቶ የት ጋ ደረሰ? የዕውቀት አባቶቻችንና እናቶቻችን እነማን ነበሩ? እስካሁን ምን ያህል ደራስያንን አፍርተናል? እነማን መቼ ተነሡ? እነማንስ ምን ሠሩ? የመጀመሪያው ገጣሚ፣ የመጀመሪያው የልቦለድ ደራሲ፣ የመጀመሪያው የወግ ጸሐፊ፣ የመጀመሪያው የቴአትር ደራሲ፣ የመጀመሪያው ሃይማኖታዊ መጽሐፍ ደራሲ፣ የመጀመሪያው የጋዜጣ ጽሑፍ ጸሐፊ፣ የመጀመሪያው የፊልም ጽሑፍ ጸሐፊ፣ የመጀመሪያው የጉዞ ማስተዋሻ ጸሐፊ ማነው? ብንባል አንዳች ስምምነት አለን? የምናሳየውስ ነገር አለን? የትስ ነው መረጃው ያለው? ለተተኪው ትውልድስ የት ወስደን ነው የምናሳየው?

      የሀገር የሥልጣኔ ሕዳሴ የሚጀምረው ከዕውቀትና ከኪነ ጥበብ ሕዳሴ ነው፡፡ የአውሮፓንም ሆነ የእስያን የሕዳሴ ታሪክ ብንመለከት ዕውቀት ያልመራው ኪነጥበብ ያላቀጣጠለው ሕዳሴ አናገኝም፡፡ የኢኮኖሚውንም፣ የባሕሉንም፣ የፖለቲካውንም ሕዳሴ ዕውቀት ሊመራ ኪነ ጥበብም ሊያቀጣጥለው ይገባዋል፡፡ ኪነ ጥበቡ ደግሞ ፖለቲካ መር፣ ብሔር መር፣ ገንዘብ መር ሳይሆነ ዕውቀት መር መሆን አለበት፡፡ ሕዳሴ የተሳካና የጸና እንዲሆን የዕውቀት አባቶችና እናቶች ያስፈልጉታል፡፡ የሚታወቁ ሳይሆን የሚያውቁ፣ የሚናገሩ ሳይሆን የሚነገርላቸው፣ ‹አለን አለን› የሚሉ ሳይሆን ‹አሉ አሉ› የሚባልላቸው የዕውቀት ምንጮች ያስፈልጋሉ፡፡

      እነዚህ የዕውቀት ምንጮች ዕውቀታቸውን እንደ ጉንፋን ማጋባት እንዲችሉ መጻፍ አለባቸው፡፡ ጊዜ ወስደው፣ ዐቅም ሰብስበው፣ መረጃ አስሰው፣ ሰርዘው ደልዘው፣ ቀምረው ሰድረው መጻፍ አለባቸው፡፡ የምንጠቅሰው፣ የምንመራበት፣ ብርሃን የምናይበት፣ ዓይነ ልቡናችንን የምናበራበት የዕውቀት ማዕድ ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ ይኼ ደግሞ የደራሲው የጸሐፊው ድርሻ ብቻ አይደለም፡፡ የጥንት እናቶቻችንና አባቶቻችን ቀለም ገዝተው፣ ብራና አስፍቀው፣ ለጸሐፊው ድርጎ ሰጥተው፣ ርስት ከፍለው፣ ዋጋ ቆርጠው፣ ሲጨርስም ሸልመው ያስጽፉ እንደነበረው ሁሉ ደራስያኑን የሚያበረታታ፣ የድካማቸውን ዋጋ እንዲያገኙ የሚያደርግ፣ ለውጥ የሚያመጣ ዓይነተኛ ሥራ ሠርተው ሲገኙም የሚሸልም መንግሥትና ሕዝብ ያስፈልጋል፡፡ ከወረቀትና ከማተሚያ ዋጋ እስከ ሥራ ግብር፣ ከማከፋፈያ ችግር እስከ መብት ማስከበር፤ ከትምህርት ቤት የንባብ ባህል እስከ ሀገራዊ የጽሕፈትና የንባብ አብዮት፣ ከዓመታዊ ሽልማት እስከ የማዕረግ ስሞች፣ የሚሰጥ ተቋማዊ አሠራርና ባህል ያስፈልገናል፡፡ የሀገር ሥልጣኔ ከድርሰት ሥልጣኔ እንደሚጀምረው ሁሉ የሀገር ሞትም ከድርሰት ሞት ይጀምራልና፡፡ 

      © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው


         ጎንደር ላይ በታኅሣሥ 20 ለሚኖረን የ‹‹አራቱ ኃያላን›› መጽሐፍ መርሐ ግብር የተመረጠው 
      ታየ በላይ ሆቴል አዳራሽ ነበር፡፡ 
      ነገር ግን ከጎንደር ከተማና አካባቢው (ከደብረ ማርቆስ፣ ባሕርዳር፣ ደብረ ታቦር፣ አዲስ ዘመን፣ እስቴና ሌሎችም) በመርሐ ግሩ ላይ ለመሳተፍ የተመዘገቡት ታዳሚዎች ቁጥር ከአዳራሹ ዐቅም በላይ በመሆኑ አዳራሽ ለመቀየር ተገደናል፡፡
      በዚህም መሠረት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ባደረገልን ድጋፍ መርሐ ግብሩ የሚካሄደው በጎንደር ከተማ ሲኒማ ቤት መሆኑን እንገልጣለን፡፡ በዚሁ አጋጣሚም አስቀድሞ ትብብሩን ላደረገልን ታየ በላይ ሆቴል ላቅ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡

      ጎንደር ላይ እንገናኝ፡፡

      መምህሩ ናቸው፤ የእነዚህን ባለሀብቶች የሕይወት ታሪክ ሥሩ ብለው የሰጡን፡፡ ስምንት ባለ ሀብቶች፡፡ እነዚህን ሰዎች የምናውቃቸው በቴሌቭዥን እየቀረቡ ስለ ልማት ሲናገሩ ነው፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም ተሸልመዋል፡፡ እኛ መምህራችንን ጠየቅናቸው፡፡ እነዚህን ለምን መረጧቸው? ስንል፡፡ እርሳቸውም ‹‹እነዚህን በሦስት መመዘኛ መረጥኳቸው›› አሉ፡፡ ‹‹አንደኛ ልማታውያን ናቸው፣ ሁለተኛ ተሸላሚ ናቸው፣ ሦስተኛ ደግሞ ዛሬ ቢጠሯቸው የማይሰሙ የናጠጡ ባለጠጎች ናቸው፡፡›› አሉ መምህራችን፡፡ ‹‹ስለዚህም ወጣቱ ትውልድ ከእነርሱ ትምህርት መቅሰም አለበት፡፡ ሀብት እንዲሁ አይገኝም፡፡ ተለፍቶ ነው፤ ተደክሞ ነው፡፡ ደም ተተፍቶ ነው፡፡ ‹ፐ› ላይ ለመድረስ ከ‹ሀ› መጀመር ያስፈልጋል፡፡ ከዕንቁላል ንግድ ተነሥተው ሚሊየነር የሆኑ አሉ፡፡ ከሱቅ በደረቴ ተነሥተው ሚሊየነር የሆኑ አሉ፡፡ ከአንዲት ሱቅ ተነሥተው ሚሊየነር የሆኑ አሉ፡፡ ከጉልት ተነሥተው ሚሊየነር የሆኑ አሉ፡፡ እነዚህ ለትውልዱ አርአያ ናቸው›› አሉን መምህሩ፡፡

      ስምንት ቡድን ተቋቋመ፡፡ ስምንቱ ቡድኖች አንዳንድ ሚሊየነር ያዙ፡፡ ታሪካቸውን የምንሠራበት ቅጽ ተሰጠን፡፡ የመጀመሪያዋን ብር እንዴት አገኟት?ወደ ሚሊየነርነት በየት መንገድ ተጓዙ? ምን ዓይነት ውጣ ውረዶችን አለፉ? እያንዳንዷን ሀብት እንዴት አጠራቀሟት? የሚሉ ጥያቄዎች ተሰጡን፡፡ እኛም የደረሱንን ባለሀብቶች እያነሣን ‹የኛ ባለሀብት ምርጥ ታሪክ ሳይኖራቸው አይቀርም፡፡ እንዲህ እና እንዲያ ሰምተናል እያልን እንፎካከር ጀመር፡፡ በቡድን የተሰጠኑንን ባለሀብቶች ታሪክ ሠርተን ከሁለት ሳምንት በኋላ ለመገናኘትና የደረስንበትን ለመወያየት ተቀጣጥረን ተለያየን፡፡

      ከሁለት ሳምንት በኋላ በመወያያ ክፍላችን ስንገናኝ ሁላችንም ፈገግታችንን ለባለሀብቶቹ ሽጠንላቸው የመጣን ይመስል እንዳኮረፍን ነበርን፡፡ ሁሉም እንደ ነፋስ አቅጣጫ መጠቆሚያ ራሱን ይወዘውዛል፡፡ መምህራችን እስኪመጡ ድረስ የረባሽ ስም ይጻፋል የተባልን ይመስል ዝም እንዳልን ነበር፡፡

      መምህሩ መጡና ‹በሉ የደረሳችሁበትን አቅርቡ› አሉን፡፡ ሁሉም ዝም አለ፡፡ ‹‹የቤት ሥራችሁን አልሠራችሁም ማለት ነው?›› አሉን፡፡ ዝም፡፡

      የመጀመሪያውን ቡድን ጠሩ፡፡ ልጀቹ ወጡ፡፡

      ‹‹እኛ ያገኘናቸው ባለሀብት ምንም ነገር አልነበራቸውም፡፡ የሀብት ማግኛ መንገዳቸውም ‹ማመቻቸት› ይባላል፡፡ድንገት አንድ ዘመዳቸው ከአንድ ድርጅት በርካሽ የግንባታ ማሽነሪዎችን እንዲገዙ አመቻቸላቸው፡፡ ማሽነሪዎቹንም ለመግዛት ከባንክ ብድር ተመቻቸላቸው፡፡ ብድሩንም ለመውሰድ ኳላተራል ተመቻቸላቸው፡፡ በዚህም የተነሣ በአንድ ጊዜ በሁለት እጅ የማይነሡ ባለሀብት ሆኑ፡፡››

      ‹‹እሺ ከድህነት እንዴት ነው ወደ ባለሀብትነት የተለወጡት፣ ሂደቱ ምን ይመስል ነበር››

      ‹‹ምንም ሂደት የላቸውም፡፡ በድንገት ተነሡ፤ በድንገት አደጉ፤ በድንገት ተመነደጉ››

      እሺ እናንተስ› አሉ ወደ ሁለተኛው ቡድን ዞረው፡፡ ልጆቹ ተነሡ፡፡

      ‹‹የኛ ባለሀብት ምንም ነበሩ፡፡ የሀብት መንገዳቸውም ‹ማስገባት› ይባላል፡፡ ድንገት አንድ ባለ ዘጠኝ ፎቅ ሕንጻ ሲሠሩ ታዩ፡፡ ምንድነው ተብሎ ሲጣራ ሚስታቸው የእነ እንትና ዘመድ ናቸው አሉ፡፡ እንዴው አንድ ቀን ነው አሉ፡፡ መኪና ሙሉ ሞባይል ጭነው ከሐርቲሼክ አዲስ አበባ የገቡት፡፡ ፈታሾቹም ምን አፍዝ አደንግዝ እንደተደገመባቸው አይታወቅም እንደ ኤድስ ማስታወቂያ አላየንም አልሰማንም ብለው አሳለፏቸው፡፡ ይሄው ሚሊየነር ሆኑ››

      ‹እናንተስ›› አሉ ገርሟቸው ሦስተኛዎቹን ቡድኖች

      ‹‹የኛ ባለሀብት ደግሞ ንክኪ ናቸው ይባላል፡፡ ሳይነካኩ በፊት ግንበኛ ነበሩ፡፡ ከተነካኩ በኋላ ግን በሞቱ ሰዎች ስም ሳይቀር መሬት እየወሰዱ ቸበቸቡት፡፡ አሁን ስለ መሬት ፍትሐዊ አጠቃቀም ትምህርት የሚሰጡ የሪል ስቴት ባለሀብት ሆነዋል፡፡ ከቀበሌ ቤት ወጥተው ቀበሌ የሚያህል መሬት ወስደው ለቀበሌ ደንብ ማስከበር የሚያስቸግር የሀብታም ቀበሌ የሚሆን ሪል ስቴት እየገነቡ ነው፡፡ ይኼው ነው›› አለ የቡድኑ መሪ፡፡

      አራተኛው ቡድን ተነሣ፡፡

      ‹‹የኛው ለየት ይላሉ፡፡ የሀብት ማግኛ መንገዳቸውም ‹መጠጋት› ይባላል፡፡ ከአንድ ሀብታም ሰው ጋር አንድ ወዳጃቸው ያገናኛቸዋል፡፡ የእርሳቸው ሥራ ሀብታሙ ሲያዝን እርሳቸው ማልቀስ፣ ሀብታሙ ሲስቅ እርሳቸው መንከትከት፣ ሀብታሙ ሲያመው እርሳቸው መርፌ መወጋት፣ ሀብታሙ ሲሸተው እርሳቸው ማነጠስ፣ ሀብታሙ ሲናደድ እርሳቸው መደባደብ ብቻ ሆነ፡፡ ከዚያም እርሳቸውም ሳያስቡት፣ ኧረ እንዲያውም ሳያውቁት ሚሊየነር ሆነው ተገኙ፡፡

      አምስተኛው ቡድን ቀጠለ፡፡

      ‹‹እኒህኛው ባለሀብት ‹መሰጠት› በተባለው መንገድ ነው ሀብት ያገኙት፡፡ ምን ነገር አልነበራቸውም፡፡ ነገር ግን በአንድ ባለ ሥልጣን አማካኝነት እኔ ነኝ ያሉ ፕሮጀክቶች ሁሉ ይሰጧቸው ጀመር፡፡ ቢወዳደሩም ያልፋሉ፤ ባይወዳደሩም ያልፋሉ፡፡ እንኳን የመንግሥት የኤን ጂ ኦ ፕሮጀክቶችም ይሰጧቸዋል፡፡ እነሆ በዚህ መንገድ ዛሬ የሀገሪቱ ወሳኝ ባለሀብት ሆነዋል››

      ስድስተኛው ቡድን ተከተለ፡፡

      ‹‹የኛ ባለሀብት የሀብት መንገድ ‹ብቻ› ይባላል፡፡ አንድን ዕቃ ለማስገባት የሚፈቀድላቸው ‹እነ እገሌ ብቻ› ናቸው፡፡ ስለዚህም በፈለጉት መንገድ የፈለጉትን ዓይነት ዕቃ ያስገባሉ፡፡ በፈለጉት ዋጋም ይሸጣሉ፡፡ መመሪያቸው ብትፈልግ ግዛ ባትፈልግ ተወው ነው፡፡ እኒህ ባለ ሀብት ከዐሥር ዓመታ በፊት አንዲት የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ብቻ ነበረቻቸው፡፡ በአንድ እርሳቸውም በማያስታውሱት ቀን ግን የሆነ ዕቃ ‹ብቸኛ አስመጭ› እንዲሆኑ ተሾሙ፡፡ ተሾመውም አልቀሩ ይኼው ሚሊየነር ሆኑ፡፡

      ‹ሰባተኛውስ ቡድን› አሉ መምህሩ

      ‹‹የኛው ሰው የሀብት መንገድ ‹ትብብር› ይባላል፡፡ እርሳቸው መርካቶ ሱቅ ከፍተው ከዱባይ ዕቃ ያመጡ ነበር፡፡ እንድ ባለ ሥልጣን ግን ‹ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ ረዳት እንፍጠርልዎ› አላቸው፡፡ እርሳቸውም ተስማሙ፡፡ ረዳት የመንግሥት ባለ ሥልጣንም ተፈጠረላቸው፡፡ ከእርሱም ጋር ሸሪክ ሆኑ፡፡ እነሆም መንገዱን እርሱ ሲጠርግ ሥራውን እርሳቸው እየሠሩ ባለሀብት ተባሉ፡፡

      ጉድ ነው ዘንድሮ አሉ መምህሩ፡፡ ስምንተኛው ቡድን ቀጠለ፡፡

      ‹‹የዚህኛው መንገድ ‹ቀንዶ› ይባላል፡፡ ባለ ሀብቱ ከብት እያረዱ በመሸጥ ይታወቃሉ፡፡ አንድ ሰው ግን ከብት እዚህ ከምትሸጥ ለምን ድንበር ሄደህ አትሸጥም አላቸውና፡፡ ወሰዳቸው፡፡ የሀገሪቱንም የቀንድ ከብቶች ድንበር እያሻገሩ ሶማሌና ሱዳን መላክ ጀመሩ፡፡ ሰውም ቀንዶ ይላቸዋል፡፡ እርሳቸውም ቀንዳም ባለሀብት ሆነዋል፡፡

      መምህሩ ተነሡና አፈጠጡብን፡፡

      ‹እና ታሪካቸው ይኼ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ አልፈው፣ እንዲህ ሆነው፣ ይህን ተፈትነው፣ ይህንን ውጣ ውረድ አልፈው፣ ይህን ልምድ ቀስመው የሚባል ታሪክ የላቸውም ማለት ነው?›› አሉ መምህሩ፡፡

      አንዱ ጓደኛችን ተነሣና ‹‹አዎ፤ ሀብት እንጂ ታሪክ የላቸውም፡፡ ሀብታቸው ድንገቴ ነው፡፡ በቃ ድንገት ተነሥተው እንደ ሮኬት ተተኮሱ፡፡ በቃ፡፡ ከአንድ ቀጥለው ሚሊየን ነው የቆጠሩት፡፡››

      ‹‹ታድያ እንዴት ነው ለእናንተ አርአያ የሚሆኑት›› አሉ መምህሩም ተናደው፡፡

      ‹‹አርአያ ባለ መሆን ነዋ› አልናቸው፡፡

      © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው 

       አራቱ ኃያላን መጽሐፍን በተመለከተ በኢትዮጵያ የመካከለኛው ዘመን ታሪክና በጽንዐት በሚታወቁት አባቶች ታሪክና አስተዋጽዖ ዙሪያ ጎንደር ከተማ ላይ ልዩ መርሐ ግብር ይኖረናል፡፡ በጎንደር ዙሪያ፣ በባሕርዳር፣ በደብረ ታቦርና አካባቢው ያላችሁ ሁሉ ተጋብዛችኋል፡፡
      በመርሐ ግብሩ ላይ

      ·   ዶክተር ውዱ ጣፈጠ

      ·   ዶክተር አምሳሉ ተፈራ

      ·   አቶ ባንተ ዓለም ታደሰ – ጥናት ያቀርባሉ

      ቀን ፡- ታኅሣሥ 20 ቀን 2006 ዓም

      ሰዓት ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ

      ቦታ ፡- ጎንደር ታየ በላይ ሆቴል

      የመግቢያውን ካርድ ለማግኘት የሚከተሉትን ስልክ ቁጥሮች ይጠቀሙ

      0918190868 / 0913788769


      ይህ አዲስ አበባ ውስጥ በአንድ የሰባተኛ/ስምንተኛ ክፍል መማሪያ ውስጥ የተገኘ 
      የባዮሎጂ ትምህርት ማስተዋሻ (ኖት) ነው፡፡

      ወይ ባል አላገባሽ ወይ አልመኮስሽ
      እንዴው ልጅ አገረድ ይባላል ስምሽ

      እንደሚባለው ወይ በአማርኛ(በራሳችን ቋንቋ) በሚገባ ተምረን አልተግባባን፤ ወይ በፈረንጅ ቋንቋ በሚገባ ተምረን አልተግባባን፡፡ እንዴው ምን ይሻላል?
      ድሮ ድጎማ የሚባል መምህር ነበር አሉ፡፡ መቶ ብር በማይሞላ ደሞዝ ነበር አሉ የሚቀጠሩት፡፡ ክፍል ውስጥ ክኖው፣ ዲጂቡቲ፣ ክናይፍ know, Djibouti, knife, እያለ ያስተምራል፡፡ ተቆጣጣሪው (ሱፐርቫይዘሩ) እንዴት እንዲህ ታስተምራለህ? ኖው፣ ጂቡቲ፣ ናይፍ በል ይለዋል፡፡ መምህሩም ‹‹በድጎማ ደሞዝማ እንዲያ ብዬ አላስተምርም›› አለ ይባላል፡፡

      በባሕላዊው የጥንት ትምህርታችን ንባብ ወሳኙና የመጀመሪያው ትምህት ነበር፡፡ የፊደል ዘር መለየት ብቻ ሳይሆን አነባበብም ጭምር፤ በየሠፈራችን የነበሩትን የቄስ ትምህርት ቤቶች እናስታውሳቸው፡፡ ፊደሎቹን ከነዜማቸው እስክንሸመድድ ድረስ አንገት ላንገት ተቃቅፈን የምንናጥባቸውን ትምህርት ቤቶች አስታውሱ፡፡
      ማንበብ የዕድገት ቁልፍ ነው፡፡ ለዚህም ነው በጥንት ሥልጣኔ የምናውቃቸው ሀገሮች ሁሉ የራሳቸውን ፊደል ለመፍጠር የተሳካላቸው ሀገሮች የነበሩት፡፡ በሥልጣኔ መጥቆ ፊደልና ጽሕፈት የሌለው ሀገር አናገኝም፡፡ የማያነብብና የማይጽፍ ትውልድ መፍጠር ከዕውቀት የተቆራረጠ ትውልድ መፍጠር ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በዐረብ ሀገሮች በሚገኙ ዜጎቻችን ዘንድ አንዱ ፈተና ‹ማኑዋል አንብቦ› መሣሪያዎችን ለመጠቀም አለመቻል ነው፡፡

      ወላጆች፣ የእምነት ተቋማት፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ሚዲያዎችና የሚመለከተን ሁሉ ልናስብበት የሚገባ ቁልፍ ችግር – ማንበብ የማይወድ ሳይሆን ማንበብ የማይችል ትውልድ በየክልሉ እየተፈጠረ ነው፡፡ ፊደልና አጻጻፍ መለየት የእንግሊዝኛም የሀገራዊ ቋንቋዎችም ችግር እየሆነ ነው፡፡

      እናም፣ የፊደልን ዘር መለየት፣ አጻጻፍን ማወቅና አነባበብን ማርታትን ከነባሩ የትምህርት ሥርዓታችን በሚገባ ቀስመን ወደ ዘመናዊ ትምህርት በጊዜ ካላስገባነው – ትውልድ አደጋ ላይ ነው፡፡

         ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ 
      (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል)

      ርእስአራቱ ኃያላን፦አቡነ በጸሎተ ሚካኤል፣ አቡነ ፊልጶስ፣አቡነ አኖሬዎስ፣ አቡነ አሮን

      አዘጋጅ/ዳንኤል ክብረት

      የገጽ ብዛት – 460 (መግቢያውን፣ዋቤ መጻሕፍትን እና መዘርዝሩንጨምሮ)

      አሳታሚአግዮስኅትመትና ጠቅላላ ንግድ ሥራኃላ. የተ. የግልማኅበር

      ማተሚያ ቤትአማኑኤል/ቤት

      • ምረቃው የተካሄደበት ቦታመንበረፀባዖት /ሥላሴካቴድራል ሁለገብ አዳራሽ

      ቀንኅዳር 15/2006 ..

      አስተያየት ሰጪአምሳሉተፈራ

      የመጽሐፉ ሥነ ድርሳናዊ (ፊሎሎጂካል(1)ጠቀሜታ

      . መግቢያ

      መጽሐፉበጣም ብዙ እናአዳዲስ ነገሮችን ይዟል። ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ የዓላማ ጽናት፣ በዘመኑ የነበረው ቅጣትና ፍርድ አሰጣጥወዘተ2 ከያዛቸው ውስጥ ዋናዋናዎቹ ናቸው። የታሪክ አሰናሰሉ፣ የቋንቋ አጠቃቀሙ፣ የማስረጃዎቹ ተአማኒነት (ባብዛኛው ጥሬ መረጃዎችንናየመጀመሪያ ምንጮችን ማቅረቡ) ወዘተለየትያደርገዋል።

      ይህደግሞ እስካሁን ድረስ ያልተሟላውንየሀገራችንን መካከለኛ ዘመን ታሪክእንዲሟላ ብዙ ድርሻንይወስዳል። በዋናነት ደግሞ የቤክርስቲያን ታሪካችንን የዚያን ዘመን ገጽታናየአበው ቅዱሳንን ታሪክ በስፋትስለሚያሳይ ፋይዳው የጎላ ነው(2)

      ገድላቸውተተርጉሞ የቀረበው አራቱም አባቶችአቡነ በጸሎተሚካኤል፣ አቡነ ፊልጶስ፣አቡነ አኖሬዎስ፣ አቡነ አሮንበተመሳሳይ ዘመን የኖሩስለነበር በአንዱ ገድል ውስጥየሌላውንም ታሪክ እናገኛለን።ይህም ታሪኩን ይበልጥ ተአማኒና ተያያዥ ያደርገዋል። ገድላቱ የቅዱሳኑን የተጋድሎ ዜና፣ ሐዋርያዊአገልግሎትና ያደረጓቸውን ተአምራት አካተዋል። እነዚህን ገድላት ለመጀመሪያ ጊዜ ያጠኗቸው100 ዓመት በፊትየውጭ አገር ሊቃውንትሲሆኑ፤ አራቱንም ገድላት በግእዝ አትመው ወደ አውሮፓቋንቋዎች ተርጉመዋቸዋል(3)3 እኔእስከማውቀው አራቱም ገድላት እስካሁን በአማርኛ ያልተተረጎሙ ሲሆን የአባበጸሎተ ሚካኤል ገድል4 ግንበቅርቡ (2004 ..) ተተርጉሞ(4)ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገድል ጋር በአንድ ላይ በማኅበረቅዱሳን ታትሟል(5)5 ስለዚህ ይህ የዲ/ ዳንኤል ዝግጅት በተፈላጊው ሰዓት የቀረበናተፈላጊነቱም እጅግ የጎላነው የሚል እምነትአለኝ።

      የኢትዮጵያኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንየምትቀበላቸውንና የምትገለገልባቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ድርሳናት፣ ገድላት እንዲሁም ልዩ ልዩመጻሕፍትን ስናጠና ምንጫቸውን በተመለከተ 2 እንከፍላቸዋለን።


      የመጀመሪያዎቹ መሠረታቸውየውጭ ቋንቋ ሆኖበኋላ ወደ ኢትዮጵያቋንቋ (ግዕዝ) የተመለሱእና ሁለተኛዎቹ ደግሞ ሀገር በቀልሆነው ከመጀመሪያው በግዕዝ የተጻፉ ናቸው። በውጭ ቋንቋማለትም በግሪክ፣ በሱርስት፣ በዐረብኛ ተጽፈው ወደግዕዝ የተተረጎሙ በርካታ ናቸው። አንዳንድ አጥኚዎች ይህን ዘመንከአክሱም (በተለይም ከ5ኛው ...) እስከ15ኛው ... ያደርሱታል። በሌላ በኩልደግሞ ሀገርኛ ሥራዎች ይበልጥ የተስፋፉት ከ15ኛው ... በኋላሲሆን ከዚያ በፊትምግን እንደነበሩ ለአብነት ያህልም የቅዱስ ያሬድን ድርሰቶች መጥቀስ እንደሚቻል ባማስረዳት የሚሞግቱ ብዙዎች ናቸው።

      ተጋድሏቸውናትምህርታቸው እንዲሁም ታሪካቸው ተተርጉሞ የቀረበው እና አዘጋጁአራቱ ኃያላን ብሎ የሠየማቸው

      አበውገድላቸው ሀገር በቀል፣ምንጩም ግዕዝ ነው።ወደ አማርኛ ቋንቋ መመለሱምየአንባቢውን ቁጥር በእጅጉ እንዲጨምርና ቅዱሳኑምየተጋደሉለትን ዓላማ ሁሉምበውል እንዲረዳው በእጅጉ ያግዛል። ከዚህም ጋር እያንዳንዱ ለብቻ ቢዘጋጅ4 ታላላቅ መጻሕፍት ሊወጣው የሚችለውን እና እንደመቅድም የቀረበው ታሪካዊ ትንታኔ ደግሞ ራሱን የቻለ 5 መጽሐፍ ሆኖ ሊወሰድየሚገባው ሲሆን ሁሉንምበአንድ ላይ በማቅረቡ/ዳንኤል ለአንባቢ አሳቢነቱን ያሳያል የሚል እምነትአለኝ።

      . መጽሐፉ ከሥነ ድርሣናዊ ሙያ አንጻር ሲታይ

      ረጅምዘመን ባስቆጠረው የጥንታዊ ጽሑፎች ጥናት መስክየጥናቱ ማዕከል ሆነው የሚወሰዱትጥንታዊ፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውየብራና ጽሑፎች፣ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች፣ልዩ ልዩ መዛግብት፣ደብዳቤዎችና በመጽሐፍ መልክምይሁን በጥቅልል መልክ የተዘጋጁሠነዶች ናቸው። ከዘመን አንጻርም ስናያቸው ከዘመነ አክሱም (አንዳንዴም ከዚያ የሚቀድሙ ተገኝተዋል) እስከ መካከለኛውዘመን ገፋ ካለምእስከ ቅድመ ዘመናዊየኢትዮጵያ ታሪክ (19ኛው መ...) ያሉትናቸው። የጥንታዊ ሰነዶቹ ቋንቋ ባብዛኛውግዕዝ ሲሆን የድንጋይላይ ጽሑፎቹን ቋንቋ ስንመለከት የሳባ ቋንቋ፣አናባቢ የሌለው ግዕዝ እናግሪክኛም ይገኝበታል። ከዚህም በተጨማሪ በጥንታዊ አማርኛና ሐረሪ(6)  ቋንቋ፣ እንዲሁም በክርስቲያናዊ ዐረብኛ የተጻፉ ሰነዶች በኢትዮጵያ ተገኝተዋል። እነዚህ ሁሉ በወጉሊጠኑ፣ ሊተረጎሙ እና የያዙት መልእክትም ለሕዝብ ሊዳረስ ይገባዋል። ከዚህም ባሻገር የተለያየ ቅጅ ካላቸውአፈላልጎ ማስተያየትና የጎደለውን ማቃናት ተገቢ ነው።

      ከነዚህእውነታዎች አንጻር በዛሬው ዕለት እየመረቅነውየሚገኘውን የዲ/ዳንኤልመጽሐፍ ስንቃኘው:-

      1. ከቋንቋው አንጻር ከግዕዝ ወደአማርኛ መተርጎሙ፣ ከዘመን አንጻር የሀገራችንን መካከለኛ ዘመን ታሪክ በተለይም በዓምደጽዮን እና ንጉሥሰይፈ አርዕድ የነበረውን ታሪክ በስፋትበመያዙ ፍይዳው ብዙ ነው።

      2. የተለያዩ ቅጂዎች ይኖሩ እንደሁብሎ ማሰቡና ይህንንም ለማሳካት የተለያዩ ገዳማትና አድባራትን፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገርየሚገኙ አብያተ መጻሕፍትንና መዘክሮችን ማሰሱ፣ እንዲሁም በአንዳንድ ግለሰቦች ይዞታ ሊገኙ የሚችሉመረጃዎችን ማፈላለጉ፣ ይህንንም ባብዛኛው ማሳካቱ /ዳንኤልንያስመሰግነዋል።

      3. ተጨማሪየገድል ቅጂዎችን ማግኘቱ እና መጠቆሙበጣም ጠቃሚ ነው።ለምሳሌ ያህልም፥

      እስካሁን ከሚታወቀው የዳጋ እስጥፋኖስገድለ አባ በጸሎተሚካኤል (ኮንቲሮሲኒ 1905 ያሳተመው) በተጨማሪ በተንቤን እንዳ እጨጌኪዳነ ምሕረት ሌላ ገድልመኖሩን መጠቆሙ ለሌላ አጥኚ ጥሩመረጃ ነው።

      ገድለ ፊልጶስን በተመለከተ ቱራኤቭ 1905 ካሳተመውውጭ ሌሎች 6 መኖራቸውንከነዚህም መካከል የአምሐራ ሳይንቱ አዲስና እርሱ ያገኘውእንደሆነ መጠቆሙ በጣም ጠቃሚነው።

      ገድለ አኖሬዎስን አስመልክቶ ኮንቲሮሲኒ 1905 ካሳተመውበተጨማሪ 10 ቅጂዎችን ማግኘቱ የሚደነቅ ነው።

      ገድለ አቡነ አሮንንቱራኤቭ 1905 አሳትሞትነበር። /ዳንኤልይህን እትም ከመቄቱገድለ አሮን ጋር አስተያይቶ ነው ወደአማርኛ የመለሰው። ከዚህ ሌላግን በብሪቲሽ ሙዚየም የሚገኝ አንድ ገድልና በትግራይ ተንቤን ሌላ ቅጅሊኖር እንደሚችል እርሱ ግንሊያገኘው እንዳልቻለ መጠቆሙ መልካም ጥረት ነው።

      4. የትርጉም ሥራው የግርጌማስታዎሻ ጠቀሜታ/ዳንኤልአራቱንም ገድላት ከመገኛቸው ቋንቋ ከግዕዝ ወደአማርኛ መልሷል። አይግለጸው እንጅ ትርጉሙየቃል በቃል ቀጥታትርጉም ይመስላል። ከዚህ በላይ ግንማብራሪያ የሚያስፈልጋቸውንና እርሱ ያገኛቸውንአዳዲስ መረጃዎች ቁጥር በመስጠትአብራርቷል፣ ተንትኗል። በጥቅሉ በገድለ በጸሎተ ሚካኤል ላይ 251 በገድለ ፊልጶስ ላይ 378 በገድለ አኖሬዎስ ላይ 156 በገድለ አሮን ላይ181 ማብራሪያዎችን በግርጌ ማስታዎሻ አስቀምጧል። ይህም ለሥራውምን ያህል እንደተጨነቀ የሚያሳይ ሲሆን እስካሁንከተለመደው የገድላት የአማርኛ ትርጉም የእርሱን የተለየ ያደርገዋል። ከዚህም በላይ የሚተነትናቸው ጉዳዮችአዳዲስና ተዛማጅ ጉዳዮች ስለሆኑ መጽሐፉን የበለጠ ተመራጭ ያደርገዋል።

      5. በአንዳንድ ነጥቦች ላይ እስካሁንየተሰሩ ሥራዎችን ከዳሰሰ በኋላ መረጃዎችተስተካክለው እንዲቀመጡ ማድረጉ ሌላው ጠቀሜታውነው። ለምሳሌ ቱራኤቭ ያሳተመው ገድለ ፊልጶስዘመኑ 14ኛው... ሳይሆን 18ኛው... የተገለበጠ መሆኑን ማሳየቱ፤ ገድለ አቡነአሮን 15ኛው... ሥራ ሊሆን እንደሚችል ለማሳያነትም ገድሉ የደብረሊባኖስን እጨጌዎች ሲዘረዝር የሚያቆመው አቡነ መርሐክርስቶስ7 (1455-1489) ላይ መሆኑንመጥቀሱ(7) ወዘተጥንታዊሰነዶች/መዛግብት ሲጠኑ እንዲህእየተገናዘቡ መሆን እንደሚገባው የሚያስረዳ ነው።

      . አስተያየት

      ከላይባጭሩ እንዳየነው ይህ ሥራበጣም ማለፊያ ነው። ሆኖምእጅግ የተወጣለት ለማድረግ እና ምናልባትጊዜ ቢፈቅድለት /ዳንኤልይህን ሥራ በድጋሚቢያሳትመው ወይም ተመሳሳይሥራዎችን ለወደፊቱ ሲሰራ ቢጠቀምባቸው ብየ የምጠቁመውሁለት አስተያየቶች፣

      የሚያገኛቸውን የገድል ቅጂዎች ሁሉንም እያመሳከረ ልዩነታቸውን እየነቀሰ አንድ ወጥና የተመሳከረ ከሁሉምቅጂዎች የተውጣጣ እትም (8) ቢሰራ፣ቢተረጉም።

      የውጭ ሊቃውንት ያጠኗቸውን ከሚተረጉም ይልቅ እርሱያገኛቸውን አዳዲስ ገድላት ቢተረጉም ወይም በፊት ከተሰሩትጋር እያነጻጸረ ቢሠራ የርሱሥራ ሚናው የጎላሊሆን እንደሚችል ይታየኛል፤ በማለት ሃሣቤን እዚህ ላይእደመድማለሁ።

      በመጨረሻምውድ ወንድሜ /ዳንኤልእግዚአብሔር ኃይልና ብርታቱን ሰጥቶ እንኳንይህን ጠቃሚ ሥራ አስፈጸመህ፤ እንኳንምደስ አለህ፤ ለወደፊቱም የበለጠ ያትጋህ በማለት መልካም ምኞቴን በመግለጽ አስተያየቴን እደመድማለሁ።

      ስላደመጣችሁኝ ሁላችሁንም እግዚአብሔር ያክብርልኝ !!!!

                                               

      1 ፊሎሎጂ የተሰኘውን ጥናት ስያሜወደ አማርኛ በቀጥታአቻ ትርጉም ለመስጠትለጊዜው አልተቻለም። በዚህ አቀራረብግንሥነ ድርሳንወይምጥንታዊ  የጽሑፎች ጥናትብለንልንወስደው እንችላለን።

      2 ከዚህ መካከል እኔ የማቀርበው ፊሎሎጂያዊ ጠቀሜታውን ነው።

      3 የአቡነ አሮንና አቡነፊልጶስ ገድላት በራሺያዊውሊቅ በቱራኤቭ (Boris Turaev, 1905, Acta S. Aaron et S. Philippi,

      Corpus Scriptorum Christianorum Orientalium, Scri. Aeth., ser xx) የበጸሎተሚካኤል እና የአኖሬዎስገድላት

      በጣሊያናዊው ምሁር በካርሎኮንቲሮሲኒ (K. Conti Rossini, 1905, Acta S. Basalota Mikael et S. Anorewos , in

      Corpus Scriptorum Christianorum Orientalium, vol. 28-29, Scri. Aeth., 11-12) ታትመዋል።

      4 የጋስጫው ቅጅ

      5 ገድለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እና ገድለ አቡነ በጸሎተሚካኤልግእዝ እና አማርኛአሳታሚ ማኅበረቅዱሳን፤ ታኅሣሥ ፳፻፬..

      6 በሐረሪ ቋንቋቀድመው ከተጻፉት የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መካከል በቀዳሚነቱየሚጠቀሰው 16ኛው // እንደተጻፈ የሚገመተው ስለ ሐረር 4 ከሊፋዎች ታሪክ የሚናገረውነው።

      7 በእርግጥ የእርሱ ትርጉምኁልቈ ተዝካሮሙ ለአቡነ አሮንወዘደቂቁብሎ በገጽ435 ላይ የደብረ ዳሬቶቹንአበው ብቻ ይዟልእንጅ የደብረ ሊባኖስ እጨጌዎችንአይዘረዝርም።

      8 በሙያው አጠራርCritical Edition የሚባለውሲሆን የበለጡቱ የቅጂ ቤተሰቦችየተስማሙበት ዘር በንባቡ(text) ውስጥ ሲካተት ልዩነቶቹ (Variants) ደግሞ ለንጽጽርበግርጌ ይቀመጣሉ። ይህም Critical Apparatus የሚባለው ነው።

      ውዱ ጣፈጠ (ዶ/ር)

      ታሪክ ትም/ ክፍል

      አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ

      በሀገራችን ውስጥ ለኦርቶዶክስ ክርስትና መስፋፋትና መደርጀት ትልቁን ሚና የተጫወቱት ሀገራዊ ቅዱሳን ካህናትና የሃይማኖት መሪዎች ናቸው፡፡ በተለይም በመካከለኛው ዘመን መንግሥትና ቤተ ክርስቲያን በአንድነት ሁነው አብረው ሰርተዋል፡፡ ነገሥታቱና ካህናቱ አብረው የሰሩትን ያህል በመካከላቸውም አንዳንድ ከሃይማኖት ጋር የሚጋጩ ነገሮች እየተከሰቱ ሲያጋጩዋቸውና ሲያጣሉዋቸው ኑረዋል፡፡ በመካከሉም እርቅ እተፈጠረ የተለመደ ስራቸውን ሰርተዋል፡፡ ያለ ውህደታቸውም የመንግሥትና የቤተ-ክርስቲያኗ  መስፋፋት በጥንካሬ ሊቀጥል አይችልም ነበር፡፡

      ኢትዮጵያውያን ካህናት ከዛጉዌ ስርወ-መንግሥት ጀምሮ የሃይማኖት መÍህፍትን ከቅብጥ፤ ከአረብኛ፤ ከጽርእ በመተርጎም ለሃይማኖት ስራ እንዲዉሉ አድርገዋል፡፡ በጊዜውም የግእዝ kk ትልቅ የሥነ ጽሑፍ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ጥረዋል፡፡ የገድል መÍሕፍት በብዛት ተጽፈዋል፡፡ የሀገራቸውን ቤተ ክርስቲያን አሰራር የተመቸ ለማድረግ አዳዲስ ነገሮች እንዲለመዱና እንዲaaሉ ለውጥም እንዲመጣ ጥረዋል፡፡ በጣት ከሚቆጠሩ አንዳንድ የቤተ-ክርስቲያኗ የቅብጥ (ግብፅ) ጳጳሳት በስተቀር ለቤተ-ክርስቲያኗ ለውጥ እዲጀመር ጥረት ያደረጉ የቅብጥ ጳጳሳት የሉም፡፡

      ኢትዮÉያውያን ቅዱሳንን ከዘመኑ ነገስታት ጋር ሲያጋጭ የኖረው ነገስታቱ ለውጥንና አንዳንድ Bይማኖታዊ ትችቶችን ለመቀበል ባለመፈለጋቸው ነበር፡፡ ቅዱሳኑና  ነገRታቱ መጋጨት የጀመሩት በመካከለኛው ዘመን የኢትዮÉያ ታሪክ ዘመን ነግሶ ከነበረው ከአÑðአምደ Òዮን ዘመነ መንግRት ጀምሮ ነበር፡፡

            ዛሬ የሚመረቀው የዲያቆን ዳንኤል ክብረት የገድላት የአማርኛ ትርጉም መÎÙ ግልÎየሚያደርገው እነዚህ የመካከለኛው ዘመን ቅዱሳን ለBይማኖታቸውና ለሀገራቸው የሰሩትን kሚ ስራ፤ Bይማኖታዊ ተጋድሎና መንፈሳዊ Òናት ቆልጭ አድርጎ የሚያሳየን ነው፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን ገድላትን፤ ታሪከ-ነገስታትን እንዲሁም ሌሎች የታሪክ ድርሳናትን ወደ አማርኛም ይሁን ወደ ሌላ ሀገራዊ kk ተርጎሞ ለማቅረብ ራእይ ያለው ጠንካራ የስራ ሰው ለማየት ብርቅ በሆነበት ጊዜ እነዚህ ድንቅ Bይማኖታዊ  ገድላት በዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወደ አማርኛ ተተርጉመው መቅረባቸው ይበል፤ እጅ ይባርክ፤ በለመደ ጣትህም ሌሎቹን ለመተርጎም እንድትበቃ እግዚአብሄር ይርዳህ ከሚል ማበረታቻ ቃላት ጋር መሆን አለበት፡፡

      ባለፉት ጥቂት አመታት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ከግእዝ ወደ አማርኛ የተረጎሙት የደቂቀ እስጢፋኖስ በህግ አምላክ የሚልና የአባ ባሕርይ ድርሰቶችን አስነብበውናል፡፡ አቶ አለሙ ኃይሌ የአፄ ገላውዴወስን፤ የአፄ ሰርፀ ድንግልንና የአፄ ሱስንዮስን ታሪከ ነገሥታት አሳትመው ለአንባቢ አቅርበዋል፡፡

              ይህንን አራቱ yያላን የሚለውን ደጎስ ያለ መÎÙ (ከመታተሙ በፊት እንዳነብለት ጠይቆኝ ሳነበው በሶስት ቅÎ የተዘጋጀ ነበር) ተመልክቸ አስተያት እንድሰጠው በጠየቀኝ ጊዜ ስው መቸም ብርቱ ነው በሚል የግርምት ህሳቤ ነበር የተቀበልኩት፡፡ ወቅቱ የአመቱ የትምህርት ማጠቃለያ ስለነበርና ሌሎች አጣዳፊ ነገሮች ስለነበሩብኝ፡፡ ቀስ እያልኩ ማንበብ ስጀምር ግን እንዳነብ ስለ ሰጠኝ እድል እያመሰገንኩት ጭምር፡፡

      ይህ አራቱ yያላንበሚል ርእስ ወደ አማርኛ የተተረጎመው መÎÙ የአቡነ  በÐሎተ-ሚካኤል፤ አቡነ ፊልÊስ፤ አቡነ አኖሪዎስና አቡነ አሮን ገድል ነው፡፡ እነዚህ አራቱ yያላን ለBይማኖታቸው መስፋፋት ወደር የማይገኝለት ታሪክ የሠሩ፤ Bይማኖትን ያስፋፉ፤ ብዙ ደቀ መዛሙርት ያስተማሩና ያፈሩ፤ ገዳማትን የመሠረቱ፤ Bይማኖታዊ ክርክር አንሥተው በጊዜው ከነበሩ ነገሥታት ጋር ፊት ለፊት የተፋለሙ፤ የደረሰባቸውን ቁጣ፤ ግርፋት፤ እንግልት፤ ስቃይና መከራ፤ እንዲሁም ስደትና ግዞት ለBይማኖታቸው  በጸጋየተቀበሉና ማንኛውንም መስዋእትነት በBይማኖታቸው በጽናት የተወጡ ናቸው፡፡

            ሌሎች የታሪክ መÑህፍትም እንደሚያስነብቡን ክርክሩ የተጀመረው በአÑððአምደ Òዮን ዘመነ መንግስት ጊዜ ነው፡፡ እነዚህ ቅዱሳንና ሌሎች የBይማኖት ወንድሞቻቸው ወደ መንግስቱ መቀመጫ ተጉዘው Bይማኖታችን የሚያዘውን ነገር አልፈÐምክም በማለት ለምመከርና ለመመለስ በሄዱበት ወቅት ነበር፡፡ የነገሩ ጭብጥ “ለምንት አውሰብከ ብእሲተ አቡከ – ለምን የአባትህን ሚስት አገባህ” የሚል ነበር፡፡ የክሱ ጨብጥ  Bይማኖታዊ ህግን ጥሰሀል የሚል ነበር፡፡ በጊዜው ንጉሱ ይህንን ተቃውሟል፡፡ የምትጠቅሱት አባቴ አይደለም በሚል፡፡ ንጉሱን በአደባባይ እንደወቀሱት በትእግስት ሊያሰናብታቸው አልፈለገም፡፡ በአደባባይ እንዲገረፉ ከዚያም በግዞት ወደ ትግራይ እንዲሄዱ ተደረገ፡፡

            ከጥቂት አመታት በ|ላ ተመልሰው በመምጣት ሌላ ጥያቄ አነሱ፡፡ በገዳም ውስጥ በአንድነት የሚኖሩ ወንድና ሴት መነኮሳት መቀመጫ ተለይቶ እዲወሰን ጠየቁ፡፡ በጊዜው ወንድና ሴት መነኮሳት በአንድነት ይኖሩ ነበር፡፡ ቀደም ብሎ በትግራይ ውስጥ የመነኮሳት መኖሪያ የተለያ ቦታ ነበርና ይህ ጥያቄ ወዲያውኑ ተቀባይነትን አገኘ፡፡ ከዚያም በሸዋና በሌሎች አካባቢዎች ተግባራዊ እንዲሆን ተደረገ፡፡

            በሶስተኛ ደረጃ የቅብጡ ሊቀ-ጳጳስ የቅስናና የዲቁና ማዕረግ ለመስጠት ገንዘብ ይቀበላል (simony) የሚል ክስ አቀረቡ፡፡ ምክንያቱም እነዚህን የክህነት ማዕረጋት ለመስጠት ገንዘብ ማስከፈል በሐዋርያት የተወገዘ ነበርና፡፡ ንጉሱ  ይህንን ክስ አልተቀበለውም፡፡ የቅብጡ ጳጳስም ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው ሁሉ እኔም ተቀብያለሁ ስህተት የለበትም በሚል ክሱን በማጣጣል ካህናቱን አወገዘ፡፡ እነዚህ ካህናትም በግዞት ወደ ዝዋይ ሀይቅ እንዲጋዙ ተደረገ፡፡ በሀካባቢው የእስልምና የመስፋፋት ችግር ስለነበር በዚያ በኩል ለመኖር አይችሉም ይቀጣሉ በሚል እሳቤ፡፡ ነገር ግን ለጥቂት አመታት በዝዋይ አካባቢ ከኖሩ በ|ላ የአባይን ወንዝ እየተሻገሩ ክርስትናን ለማስፋፋት ወደ ጎጃምና ወደ ጣና ሀይቅ አካባቢ አገሮች በስደት ራቅ ብለው ሄዱ፡፡

            ይህ ክርክር በአÑðð አምደ Òዮን ዘመነ መንግስትና በልጁና በወራሹ በአÑððሰይፈ አርእድ ዘመነ መንግስታት ጊዜ ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ሰይፈ አርእድ ወደ ስልጣን በመጣ ጊዜ በአንዲት ሚስት ተወስኖ ለመኖር አስቀድሞ ቃል የገባ ቢሆንም ቃሉን አክብሮ አልኖረም፡፡ በዘመኑም እነዚህ ቅዱሳን ወደ መቀማጫ ከተማው እየመጡ ከስህተቱ ለመመለስ ሞከሩ፡፡ ነገር ግን አልተሳካላቸውም፡፡ እንዲያውም እንግልቱ፤ ቅጣቱና መጋዙ እተባባሰ ሄደ፡፡ ከዚያም እነዚህ አበው ቅዱሳን ወደ ሩቅ ሀገር፤ በጣም ሞቃታማና ቆላማ ወደ ሆነ ሀገር ተጋዙ፡፡ በረሀብና በጥም እንደዚሁም በስቃይ ሲጠበሱ ከእንደዚህ አይነት ድርጊታቸው ይቆጠባሉ በሚል፡፡

            በመÒኃፉ ውስጥ እንደምታነቡት አበው ቅዱሳኑ የደረሰባቸው ቅጣት፤ ግርፋትና እንግልት በዘመናችን ካየነው የደርግ ዘመን ተመሳሳይና በጣም ኢሰብአዊ የሆነ ድርጊት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አንዱ በሃይማኖት ሌላው በፖለቲካ ሰበብ የተፈፀመ፡፡ እንዲያው ለቅንጣት ምሳሌ ያክል ክብራቸውን ለማዋረድና መሳለቂያ ለማድረግ በንጉሱ መቀማጫ ከተማ በአደባባይ ልብሳቸውን አውልቀው እርቃናቸውን እንዲዘዋወሩ ተደረገ፡፡ ረ ስንቱ ይነሳል፡፡ እነርሱ ግን በአቋማቸው Ðንተው የሀይማኖታቸውን ስነ-ምግባር አጥብቀው ያዙ፡፡ ባላቸው ሀይማኖታዊ Òናት ግፉና መከራውን እንዲሁም ግርፋቱንና ስቃዩን በፍስሀ ተቀበሉት፡፡ ስደቱንና ግዞቱን እንደ ቀላል ችግር ተጋፈጡት፡፡ በደረሰው አለማዊና ዘግናኝ ቅጣት የወደቁትንና መስዋዕት የሆኑትን ብዙሀኑን የሀይማኖት ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን አርማ ተሸክመው እስከመጨረሻው ድረስ Ðንተው መንከራተቱንና ስቃዩን በአምላክ ስም አሸነፉ፡፡

            በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የምናገኘው ነገር አቡነ ያእቆብ በተባሉ የቅብጥ ሊቀ-ጳጳስ ዘመነ ፕትረክና ሀይማኖትን ለማስፋፋት ሲባል ኢትዮጵያ በአስራ ሁለት አገረ ስብከታት መከፋፈሉዋንና መምህራን መመደባቸውን ነው፡፡ ይህ ሊቀ ጳጳስ የአቡነ ተክለ-ኃይማኖትን አስራ ሁለት ደቀ መዝሙራትንና የደብረ ሊባኖስ ገዳም ምሩቃንን በመመደብ አገሪቱን ከፋፍሎ እንዲስተምሩ አሰማራቸው፡፡ በዚህ የለውጥ እንቅስቃሴና ቅዱሳኑ በተደረገባቸው መጋዝ ቤተ ክርስቲያንዋ ተስፋፋች፡፡ የሀገረ-ስብከት መከፋፈልም መሰረት ተጣለ፡፡ በቅብጡ ሊቀ ጳጳስ የተፈለመው ብቸኛ የለውጥ መንፈስ ከቅብጥ ከሊቀ ጳጳሳት መካከል ይህ ሊቀ ጳጳስ ብቻ ስሙ በበጎ ሲዘከር የሚኖር ነው፡፡

            በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከምናገኛቸው አያሌ ቁም ነገራት መካካል በጣም ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ የሀገራችን ገድላት፤ ታሪከ ነገስታትና ሌሎች ጥንታዊ Òሁፎች በግእዝ የተÑፉትን ወጣቱ ትውልድ ምን እንደተሰራ ለማወቅ ይቸግረዋል፡፡ የሀይማኖት ታሪክን፤ ድርሳናትን፡ ገድላትንና አለማዊ የጥንት ታሪከ ነገስታትን የማንበብና የመመርመር ፍላጎት በአእምሮው ካልሰረÐ በስተቀር፡፡ በቅርቡ ልናገኛቸው የምንችላቸው ገድላት፤ ወይንም በሌላ የውጭ kk ተተርጉመው የሚገኙና እኛ ግን በቅርብ የማናገኛቸው፤ እንዲሁም የት እንደሚገኙ ለማናውቅ ሁሉ ዘለግ ያለ እድሜና ብርታት ለዲያቆን ዳንኤል ክብረት ይድረሰውና እነሆ ይህንን መÒኃፍ በእጃችን መዳፍ ውስጥ  አስገባልን፡፡ ለመንፈሳዊ ተማሪዎች፤ ለሃይማኖትና ለታሪክ፤ በተጨማሪም ለሌሎች ምሁራን፤ እንዲሁም አግባብነት ላላቸው ሌሎች የትምህርት ዘርፎች የሚረዱ ዋቢ መጻሕፍት ያልተተረጎሙትንና በእጃችን ያልገቡትን ስራዎች የሚችሉ ሁሉ ተርጉመው እንዲያቀርቡልን ይህ ስራ ያበረታታል፡፡                      

            ባለፉት ክፍለ ዘመናት በሀገራችን በደረሰው የፖለቲካ ምስቅልቅል፤ ጦርነትና የህዝብ ፍልሰት በመካከለኛው ዘመን የጥንት የቦታ ስያሜዎች አንድም ተረስተዋል፤ ጠፍተዋል ወይንም በሌላ አዲስ ስም ተተክተዋል፡፡ የጥንቱን ዋና የመረጃ መጻሕፍትን ለሚያነብ ተመራማሪ እነዚህን የጥንት ስያሜዎች የት አካባቢ እንደነበሩ ለማወቅ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ትልቅ የራስ ምታትም ነው፡፡ እነሆ በዚህ መፅሀፍ ዲያቆን ዳንኤል ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል የጥንቱን ስያሜ ይዞ ታሪኩ ተፈፅሞባቸዋል በሚባሉት አካባቢዎች ተዘዋውሮ የአብዛኞቹን ቦታዎች የጥንት አካባቢ ሊደርስባቸው ችሏል፡፡ አብዛኞቹም ስማቸው ተቀይሮ በሌላ ተተክቷል፡፡ አንዳንዶቹም ትንሸ ለወጥ ብሎ ሙሉ ለሙሉ ሳይጠፉ ተገኝተዋል፡፡ ይህን ለማድረግ ለብዙ ቀናት ሳይሰለች አቀበትና ቁልቁለት፤ ሸለቆና ወንዝ ሳይበግረው የጥንቱን አካባቢ ሊለይ በመቻሉ አድናቆት ይገባዋል፡፡ በግርጌ ማስታዎሻ ሰፋ ካለ ማብራሪያ ጋር አቅርቦልናል፡፡ ስሞቹ የተገኙበትን ሌሎች መረጃዎችንም አካቶልናል፡፡ በአገራችን ጥናቱ ስለተደረገበት ዘመንና ለሌላም ነገር የፖለቲካ ካርታ የሌለ ቢሆንም ይህንን ስራ ይዘው ለመቀጠል ለሚፈልጉ ጎዳናውን አስቀድሞ ጠርጎ መንገዱን አመቻችቶላቸዋል፡፡

            እነዚህ አበው ቅዱሳን የደረሰባቸው ስቃይና እንግልት፤ እስራትና ግዞት ምን ያህል ስር የሰደደ እንደነበር በግልፅ ያስተምረናል፡፡ ለመሆኑ የእግዚአብሄርን ስም አንግበው የሃይማኖት ስራ ሲሰሩ ህይወታቸውን ሁሉ ለተንገላቱ አበው ቅዱሳን በክርስቲያኑ መንግስት ይህ ስቃይ ይገባቸው ነበርን ብለን ታሪኩን በጥልቀት እንድንመረምር ይረዳናል፡፡ አሁን በቅርቡ በተለያዩ ሀገራት የእኛንም ጨምር በፖለቲካ ጉዳዮች ዜጎች የደረሰባቸውን መጎሳቆልና መንገላታት ስናጤን አበው ቅዱሳን አባቶቻችን ያለፉበትን የስቃይ ዘመን እንድንገመግም እንገደዳለን፡፡ ሌላው ቀርቶ አሁን በቅርቡ በደርግ መንግስት ያለቁትን የቀይና የነጭ ሽብር ሰለባዎችን ስናስብ ወጣቱ ትውልድ በስንት አይነት ጣእርና ስቃይ ተለብልበው እንዳለቁ ለመገንዘብ ይረዳናል፡

            ሌሎች ተመራማሪዎች አዲስ መረጃ በማግኘታቸው ሰፊና ጥልቅ ምርምር አካሂደው ታሪኩን አገናዝበው እንደሚያስነብቡን አልጠራጠርም፡፡ በዚህ አጋጣሚ የደቂቀ እስጢፋኖስ ተከታዮች የደረሰባቸውን እልቂትና ጭፍጨፋ ከጥቂት አመታት በፊት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ከግእዝ ተርጉመው ያቀረቡልንን መፅኃፍ ያነበባችሁት ስለሆነ ነገሬን እዚሁ ልkጭ፡፡

            ዲያቆን ዳንኤልን ሊያስመሰግነው ከሚገባው ስራ መካከልም በብዙ ድካም የግርጌ ማስተወሻውን ፅፎ ማካተቱ ነው፡፡ በግርጌ ማስታወሻ የተዘረዘሩት ማብራሪያና መግለጫ እጅግ አድካሚ ስራ ነው፡፡ ይሁንና ስራውን ምን ያህል አድቅቆ እንደሰለቀው ግልፅ ያደርግልናል፡፡ በተጨማሪም ተካቶ የቀረበው የቦታና የሰው ስም መዘርዝር እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ይህም አታካችና አድካሚ ሲሆን በምንም ሁኔታ ሰሞች እንዳይረሱ ሳይፃፉ እንዳይቀሩ ለማድረግ በተደጋጋሚ የተደረገውን የአርትኦት ትኩረት ነው፡፡ ሰለ አንድ ነገር ለማወቅ የሚፈልግ ሰው መፅሀፉን ገፅ በገፅ አንብቦ የሚፈልገውን ስም በቶሎ ለማግኘት የሚረዳ በመሆኑ ስራን ያቃልላል፡፡ የህትመት ስራ የናረ ባይሆን ኖሮ የግእዙ ፅሁፍ ቢካተት ጥሩ ነበር፡፡

            ይህ ጥልቅ ስራ ሌሎች ተመራማሪዎች የርሱን አርአያነት ተከትለው እንዲህ አይነቱን የትርጉም ስራ ለመስራት ያነሳሳቸዋል፡፡ በሀገራችን የተደረሱ ብዙ ስራዎች እንዲሁም ከተለያዩ የውጭ kk ወደ ግእዝ የተተረጎሙ የብዙ መጻሕፍት ትርጉም ስራ ገና አልተነካም፡፡ ይህ የማንቂያ ደወል በብዙ ሰዎች ጆሮ ላይ ሊደውል ይገባል፡፡ በተለይም የቤተ-ክርስቲያናችን ካህናትና ምሁራን – ከሊቅ እስከ ደቂቅ – ይህንን የትርጉም ስራ ስራየ ብለው እንዲጀምሩት ይሞግታቸዋል ያበራታታቸዋልም ብየ እገምታለሁ፡፡ በተለይም ጠቅላይ ቤተ-ክህነትም ሆነ የባህል ሚኒስቴር ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ምንም እንኳ የተጠናከረ ድርጅትና የስራ ተነሳሽነት የሚያስፈልገው ቢሆንም በተለይ ጠቅላይ ቤተ-ክህነት እኔ አለሁ ብሎ ብእሩን ሊያነሳ ይገባል፡፡

            ስራው መበረታታት ያለበት ከግእዝ ወደ አማርኛ kk በመተርጎሙ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ወደ ሌሎች የብሄረሰብ kkዎች ቀስ በቀስና በጊዜ ሂደት ስራው መጀመር ያለበት መሆኑ ጭምር ነው፡፡ በጊዜ ሂደት ከታሰበው መድረስ ስለሚቻል አቢይ ቁም ነገሩ ለመጀመር ቆርጦ መነሳሳቱ ላይ ነው፡፡

            ለማጠቃለል ያህል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ስለ ሰራኸው ስራ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ የድካምህን ዋጋ ባለቤቱ ይክፈልህ፡፡ ሌሎች ሰራዎችህንም አሁን የተወጠኑት ጨምሮ በተከታታይ እድታስነብበን በትህትና እመኛለሁ፡፡ ቅዱሳን አበውን የባረከ አምላክ አንተንና ቤተሰብህን ይባርክ፡፡

      አመሰግናለሁ፡፡           

                            

      ባለፈው አንድ ዩኒቨርሲቲ ሄጄ አንድ ጓደኛዬ የነገረኝ አሳዛኝ ነገር ነበር፡፡ የአማርኛ መምህር ለመቅጠር የተሰጠው ፈተና ዩ፣ ዪ፣ ዬ እና ዮ ን መጻፍ ነበር፡፡ በጣም የሚገርመው ግን ከተፈተኑት አምስት የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው መምህራን አንዱ ብቻ አሟልቶ ጽፏቸዋል፡፡ ወደፊት አማርኛን ማንበብና መጻፍ የሚችል ሰው ለማግኘት ሥዕለት ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ እስኪ ይኼንን ማስታወቂያ ተመልከቱት ‹ይከላከላል› ወይስ ‹ይከሳከሳል› – ተከላካይ ነው ቦክሰኛ?

      እሥራኤልን ዐርባ ዓመት በበረሃ የመራ፣ ፈርዖንን ድል የነሣ፣ የኤርትራ ባሕርንም ለሁለት እንደ ድንጋይ የከፈለ ሰው ነው ሙሴ፡፡ እርሱን በተመለከተ አያሌ መጻሕፍትን ጽፈዋል፣ ፊልሞችን ደርሰዋል፣ ብዙዎችም በእርሱ ስም ተጠርተዋል፡፡ ሕዝብን ከባርነት የማውጣት፣ ለሕዝብ ብሎ የመከራከር፣ ለሕዝብ ብሎ ራስን የመሠዋት፣ ሕዝብን ከራሱ በፊት የማስቀደም፣ ሕዝብን በትዕግሥትና በጥበብ የመምራት፣ ለሕዝብ ብሎ ተከራክሮ ድል የማድረግ ተምሳሌት ነው – ሙሴ፡፡
      ሙሴ ከወገኖቹ ጋር የኖረው ከተወለደ እስከ ሦስት ወር እድሜው ብቻ ነው፡፡ ያ ጊዜም ቢሆን ወገኖቹ በግብጻውያን እጅ ከባርነት በከፋ ስቃይ ውስጥ ገብተው የሚንገበገቡበት ጊዜ ነው፡፡ እንኳን ሌላውን ዓይነት ነጻነት ቀርቶ ልጅ ወልዶ የማሳደግ መብት እንኳን አልነበራቸውም፡፡ በተለይም ልጁ ወንድ ከሆነ፡፡ በምድርም ላይ እነርሱን ሊመለከት፣ ሊታደግና ሊራዳ የሚችል አንዳችም ኃይል አልነበረም፡፡ ዓለም እንደ ወስከንቢያ በላያቸው ላይ ተደፍታባቸው ነበር፡፡

      ሙሴ ለዐርባ ዓመታት ያህል የኖረው በፈርዖን ቤተ መንግሥት ውስጥ የፈርዖን ልጅ ተብሎ፣ ግብጻዊነቱ እየተነገረው ነው፡፡ የተማረው የግብጽን ጥበብ፣ የበላው የግብጽን ምግብ፣ የሚያውቀው የግብጽን ቋንቋ፣ የኖረው ከግብጻውያን መኳንንትና መሳፍንት ጋር፣ የሚያየው የግብጻውያንን አማልክት፣ የተወዳጀው ከግብጻውያን ጠንቋዮችና አስማተኞች ጋር ነበር፡፡

      ሙሴ የኖረበት የኑሮ ደረጃ ወገኖቹ ከነበሩበት የኑሮ ደረጃ እጅግ ከፍ ያለ ነበር፡፡ እርሱ በመኳንንት ወግ፣ በቤተ መንግሥት፣ ችግር የሚባል ነገር ሳይነካው፣ ግፍ የሚባል ነገር ሳይደርስበት፣ መብቱ በሚገባ ተጠብቆ፣ ከቅንጦትና ከድሎት አንዳች ሳይጎድልበት፣ የፈርዖን የልጅ ልጅ እየተባለ የኖረ ሰው ነበር፡፡ በተቃራኒው ወገኖቹ ደግሞ ሰው ሊደርስበት የሚችለውን የመጨረሻ መከራ እየተቀበሉ፤ ካሉት በታች ከሞቱት በላይ ሆነው ነበር የሚኖሩት፡፡ ህልውናቸው በሌሎች ፈቃድ እየተወሰነ፣ ፈንግል እንደያዘው ዶሮ ሞታቸው የሰዓታት ጉዳይ እየሆነ፣ መኖር ራሱ ቅጣት ሆኖባቸው ነበር የሚንገፈገፉት፡፡

      ሙሴ እንዲህ በምቾትና በቅንጦት፣ ችግርን በጆሮው እንኳን ሳይሰማት አድጎ፣ የቤተ መንግሥቱን ቅምጥል አጣጥሞ፣ በፈርዖን ዕቅፍ ተቀምጦ – በዐርባ ዓመቱ ግን የወገኖቹ ነገር ያንገበግበው፣ ግፋቸው ይሰማው፣ መከራቸው ያመው፣ ስቃያቸው ያቃዠው፣ ሕመማቸው ያንቀጠቅጠው፣ ሞታቸው ዕረፍት ይነሣው ጀመር፡፡ እርሱ በቤተ መንግሥት ቢቀመጥም ልቡ ግን ከቤተ መንግሥቱ ወጥቶ ግፍ ከሚደርስባቸው ወገኖቹ ጋር ግፍ ይቀበል ጀመር፤ እርሱ ከፈርዖን ማዕድ ቢሰለፍም፣ ልቡ ግን ከወገኖቹ ጋር ይራብ ጀመር፡፡ እርሱ በሐር ልብስ ቢሞቀውም፣ ኅሊናው ግን ከወገኖቹ ጋር ተራቁቶ ይበርደው ነበር፤ እርሱ በሥልጣን ላይ ቢቀመጥም፤ ኅሊናው ግን ከወገኖቹ ጋር ለባርነት ተላልፎ ተሰጥቶ ይገረፍና ይታሠር ነበር፡፡ እርሱ ንጉሣዊ ሕይወትን ቢያጣጥምም፣ ልቡ ግን ከወገኖቹ ጋር ይሞት ነበር፡፡

      ለዚህም ነበር አንድ ቀን ወደ ወገኖቹ ሲወጣ አጋዥ አልባ መሆናቸውን ያየ፣ ለግፍ ተላልፈው የተሰጡ መሆናቸውን ያጠና፣ የእነርሱ ሕይወት እንደ ጢንዚዛ ሕይወት ባለቤት የለውም ብሎ ያሰበ ግብጻዊ አንዱን ዕብራዊ ሲመታው ያየው፡፡ ለተመታው ዕብራዊ እርሱ አመመው፡፡ እርሱ የዚህ ግፍ የሚፈጸምበት ማኅበረሰብ አካል መሆኑን አመነ፡፡ ስለዚህም ታዳጊ ለሌለው ታዳጊ ለመሆን ወሰነና በራሱ ላይ ሞት ፈርዶ ያንን ግብጻዊ መታው፡፡ ልቡ ዐርባ ዓመት ከኖረበት ቤተ መንግሥት ሸፍቶ ሦስት ወር ወደኖረበት የእሥራኤላውያን የድህነት መንደር ገባ፡፡

      እንዴት? ነው ጥያቄው፡፡ እንዴት?

      ሙሴን ማን ነው ያስሸፈተው? ማንነቱን ሳይረሳ ዐርባ ዓመት በፈርዖን ቤተ መንግሥት ያኖረው ማነው? ከድሎቱ ይልቅ የወገኖቹን ስቃይ እንዲመርጥ ያደረገው ማነው? ሰዎች ለአንድ ዓመትና ለሁለት ዓመት ከሀገርና ከወገን ርቀው ባህላቸውንና ቋንቋቸውን ይረሳሉ፣ ማንነታቸውንም ይጥላሉ፡፡ እርሱ ግን ዐርባ ዓመት በፈርዖን ቤተ መንግሥት ሲኖር ለምን ማንነቱን ጠብቆ ኖረ? አንዳንድ ሰዎች ምቾትና ድሎትን ካገኙ፣ ከከበሩና ከተሾሙ ሀገራቸውን፣ ሕዝባቸውንና ወገናቸውን አሳልፈው ለመስጠት ዝግጁ ናቸው፡፡ ሙሴ ግን እምቢ አለ፡፡ እነርሱ ከበሉ ሕዝባቸው የበላ፣ እነርሱ ሲሾሙ ሕዝባቸው የተሾመ፣ እነርሱ ሲያገኙ ሕዝባቸው ያገኘ የሚመስላቸው ባለ ሥልጣናት ብዙ ናቸው፡፡ ሙሴ ግን ከወገኑ ተለይቶ ያገኘው ክብርና ምቾት፣ ሥልጣንና ሀብት ቆረቆረው እንጂ አልተስማማውም፤ ከእርሱ ድሎት ይልቅ የወገኑን መከራ መረጠ፡፡

      መንግሥቱ ለማ፡-

      የተለመደ ነው የመጣ ከጥንት

      ከተጠቂው መራቅ አጥቂን መጠጋት

      እንዳሉት የሀብታም፣ የባለ ሥልጣን፣ የታዋቂ ሰው፣ የባለ ጊዜ፣ የከበረ ወገን፣ የሚፈራና የሚከበር ሕዝብ ወገን ነኝ፣ ዘመድ ነኝ፣ አባል ነኝ ማለት ከጥንትም የነበረ ነው፡፡ የአጥቂው ወገን ሆኖ ከተጠቂው ጋር መቆም፣ የጨቋኝ ወገን ሆኖ ከተጨቋኝ ወገን መቆም፣ የክቡራን ወገን ሆኖ ከተዋረዱ ጋር መሰለፍ፣ የገፊዎች ዘመድ ሆኖ ከተገፊዎች ጋር መወገን፣ የሀብታሞች አካል ሆኖ ከድኆች ጋር መሰለፍ፤ የሹመኞች ቤት ሆኖ ለተራው ሕዝብ ዘብ መቆም ግን ብዙም የማይገኝ እንደ አልማዝ ብርቅ የሆነ ነገር ነው፡፡ ታድያ ሙሴ ይህንን ከየት አገኘው?

      የሙሴ እናት ሙሴን በቤቷ ለመደበቅ የቻለችው ለሦስት ወራት ብቻ ነው፡፡ በዚያ ዘመን ሲወለድ ወንድ መሆኑ የታወቀ ዕብራዊ ሁሉ እንዲገደል በፈርዖን ዐዋጅ ወጥቶ ነበርና፡፡ የጨነቃት እናት መላ አታጣምና ዓባይ ወንዝ ወስዳ በሳጥን አድርጋ ጣለችው፡፡ የጣለችበት ቦታ የፈርዖን ሴት ልጅ ገላዋን የምትታጠብበት ቦታ ነበርና የፈርዖን ልጅ ሳጥኑን አየችው፡፡ ስትከፍተው የሚያምር ወንዝ ልጅ አገኘች፡፡ አምላክ የሰጠኝ ነው ብላ ወሰደችው፡፡ የሙሴ እናት ብልሃትና ጀግንነት ከዚህ ይጀምራል፡፡ እርሷ ባትኖር ኖሮ ሙሴ ከእነዚያ ሁሉ ሟች ሕጻናት ተለይቶ ባልተረፈ – በኋላም ታሪክ ባልሠራ ነበር፡፡

      እናቱ ሙሴን ዓባይ ወንዝ ላይ ሰትጥለው እኅቱ መጨረሻውን እንድታይ ልካት ነበር፡፡ የፈርዖን ልጅ ሙሴን ከባሕር አውጥታ(‹ሙሴ› ማለት ከባሕር የወጣ ማለት ነው) ሞግዚት ስትፈልግ የሙሴ እኅት እናቱን ሞግዚት አድርጋ አመጣችላት፡፡ እናቱም ሞግዚት ሆና ሙሴን አሳደገችው፡፡ በፈርኦን ቤተ መንግሥት ውስጥ በእናቱ ሞግዚትነት ነበር ያደገው፡፡ ሁለተኛው ብልሃቷ ይሄ ነው፡፡ ሙሴ ሲያድግ እናቱ እውነቱን እየነገረችው ነው ያደገው፡፡ ‹‹አንተ በፈርዖን ቤተ መንግሥት ብትኖርም ግብጻዊ ግን አይደለህም፤ አንተ በምቾት ብትኖርም፣ የሚሰቃዩት የእሥራኤላውያን ወገን ነህ፤ አንተ የግብጽን ቋንቋ ብታጠናም ቋንቋህ ግን ዕብራይስጥ ነው፡፡ እዚህ ያገኘኸውን ልምድና ዕውቀት፣ሥልጣንና ክብር፣ ከሞት የመትረፍ ዕድል ወገኖችህን ነጻ ለማውጣት ተጠቀምበት፡፡ ይህ የምታየው ሕዝብ እንዲህ አልነበረም፡፡ ታላቅ ሕዝብ ነበር፣ ታላቅ ሕዝብም ነው፡፡ የአሁኑን መደኽየት፣ የአሁኑን መዋረድ፣ የአሁኑን መገፋት፣ የአሁኑን መጨቆን አትይ፡፡ ነገ ታሪክ ይለወጣል፡፡ አንተ ዛሬ ይህችን ክብርና ሥልጣን፣ ምቾትና ድሎት አገኘሁ ብለህ ከወገንህ ብትርቅ ታሪክ የተለወጠ ዕለት አንተም ስትረገም፣ ስትዋረድና ስትወቀስ ትኖራለህ፡፡ አንት ባታየው ዐጽምህ ይዋረዳል፡፡ ዛሬ ግን ከተገፉትና ከተዋረዱት ወገን ሆነህ ታሪክ ሲለውጥ አብረህ ብትሠራ ስምህ በወርቅ ቀለም ይጻፋል› – እያለች አስተማረችው፡፡

      ሙሴ የእናቱ ውጤት ነው፡፡ ሰውነቱን ፈርዖን ሲያሳድገው ልቡን እናቱ ናት ያሳደገችው፤ ምግቡን ፈርዖን ሲሰጠው ጥበቡን እናቱ ናት የሰጠችው፡፡ አካን ቤተ መንግሥቱ ሲቀርጸው የሀገርና የወገን ፍቅር፣ ጽናትንና ብርታትን፣ ለወገን ሲሉ መሥዋዕት መሆንን የተማረው ከእናቱ ነው፡፡ የጥንቱን ታሪክ እየነገረች ልቡ በወገኑ ፍቅር እንዲቃጠል ያደረገችው እናቱ ናት፡፡ ያንን ታሪክ የመመለስ፣ ይህንን ሕዝብም ታላቅ የማድረግ ድርሻ ያንተ ነው ያለችው እናቱ ናት፡፡ ሙሴን ነጻ አውጭ እንዲሆን አድርጋ የሠራችው እናቱ ናት፡፡ በሙሴ ውስጥ ያለችው፣ ከፈርዖን ጋር የተከራከረችው፣ ቤተ መንግሥቱን ጥሎ ለወገኑ ሲል በረሃ እንዲንከራተት ያደረገችው፣ ባሕር እንዲክፍል ያበቃችው፣ የሕዝቡን ስድብ፣ ማጉረምረም፣ ሐሜትና ዐመጽ ችሎ ሕዝቡን እንዲመራ ያደረገችው እናቱ ናት፡፡ ‹ሕዝቤ ከሚጠፋ እኔን ከሕይወት መጽሐፍ ደምስሰኝ› ያሰኘችው እናቱ ነች፡፡

      እንዲህ ያለች እናት በሌለችበት፣ እንዲህ ያለ ሙሴ መፈለግ ጉም መዝገን ይሆናል፡፡ እኛ የምንለፋው ሙሴን ለማግኘት ነው፡፡ የሚበጀን ግን ጀግናዋን የሙሴን እናት ማግኘት ነው፡፡

      የሙሴ እናት የት ነው ያለሽው?

      © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

      እጨጌ ዕንባቆም የመናዊ
      ልዩ መርሐ ግብር በደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት(መርካቶ) አዳራሽ

                                       ቀን –  ኅዳር 22 ቀን 2006 ዓም

                                       ሰዓት-  ከቀኑ በ8 ሰዓት


                                     የመግቢያ ካርዱን ይውሰዱ


      • ከየመን በ16ኛው መክዘ መጥቶ የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት ስለሆነውና አያሌ መጻሕፍትን ስለደረሰውና ስለተረጎመው እጨጌ ዕንባቆም የመናዊ ልዩ ዝግጅት በተለያዩ ሊቃውንትና ምሁራን ይቀርባል

      • በመርሐ ግብሩ ላይ ለመሳተፍ የመግቢያ ካርዱን 
      • ለም ሆቴል ማትያስ ሕንጻ ከሚገኘው አግዮስ መጻሕፍት መደብር፣ 
      • ከደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት(መርካቶ) ሰንበት ትምህርት ቤት ጽ/ቤት እና 
      • ከማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት ፊት ለፊት ከሚገኙ የመጻሕፍት ማከፋፈያ ሱቆች(የአርከበ ሱቆች) ማግኘት ይችላሉ፡፡
      • አስቀድመው የመግቢያ ካርዱን በመውሰድ አብረን ሊቃውንቱን እናስብ
      አዘጋጆች

      • ምክሐ ደናግል ሰንበት ትምህርት ቤትና ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

      የወረዳው ሊቀ መንበር ለስብሰባው በሚገባ መዘጋጀታቸው ሲወራ ነው የሰነበተው፡፡ ሕዝቡን ለፀረ ሽብርተኛት ዘመቻ በሚገባ ማንቀሳቀስ አለብኝ ብለዋል አሉ፡፡ አንድም ሰው ከዚህ ስብሰባ መቅረት እንደሌለበት በየሰፈሩ ሲወራ ነበር፡፡

      የስብሰባው ቀን ሕዝቡ እግር ኳስ የሚያይ መስሎ አዳራሹን ሞላው፡፡ ቦታ የጠበባቸውም በመስኮት በኩል ጉርድ ፎቶ የሚነሡ ይመስል አንገታቸውን ብቻ አስግገው ያጮልቃሉ፡፡ እስካሁን ማንም ሊቀ መንበር ያልተናገረውን ንግግር ሊያደርጉ ነው ስለተባለ ሰው ምን እንደሚናገሩ ለመስማት ጓጉቷል፡፡ በተለይ አንዳንዱ የወረዳው ነዋሪ እንደ ክትባት ለሁሉ የታዘዘ የሚመስል ተመሳሳይ ንግግር መስማት ሰልችቶታል፡፡ ተናጋሪዎች እንደ ኮካኮላ ጠርሙስ አንድ ዓይነት ሆነው  እንደ ተመረቱ ሁሉ እንኳን ቃሎቻቸው ሳሎቻቸው እንኳን ስለሚመሳሰሉ አንዳንዱ ‹ይህንን ንግግር የት ነበር የሰማሁት›› እስከማለት ደርሷል፡፡ አሁን የኛ ወረዳ ሊቀ መንበር ይህንን እንደ ኮንዶሚንየም መልክ የተመሳሰለ ንግግር ሰብረው ሪኮርድ ሊያስመዘግቡ መሆኑን ስንሰማ ተገልብጠን መጣን፡፡

      አንድ በስብሰባው ውስጥ ያገኘሁት ሰው ‹‹እነዚህ ባለ ሥልጣናት ግን አንድ ዓይነት ቃላት ከየት ነው የሚያገኙት?›› ብዬ ስጠይቀው ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ ‹‹የባለ ሥልጣናት መዝገበ ቃላት›› የሚባል ያልታተመ መጽሐፍ አለ፡፡ከዚያ ብቻ ነው ቃላት መምረጥ የሚችሉት፡፡ እዚያ ውስጥ የንግግር ቅጽ አላቸው፡፡ ወረዳውን፣ ቀኑን፣ የተሰብሳቢዎቹን ዓይነትና የበዓሉን ስም ብቻ ትቀይርና ንግግሩን ትወስዳለህ›› ብሎ ቀለደብኝ፡፡

      አሁን ሊቀ መንበሩ እየገቡ ነው፡፡ ሕዝቡ አጨበጨበ፡፡ ፕሮግራሙን የሚመራው ሰው ማይክራፎኑን ያዘና ‹አሁን ስብሰባችንን የምናከናውንበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡›› ሲል ሕዝቡ አጉረመረመ፡፡ ግራ ገባው፡፡ ‹ይህ ሕዝብ ባይገባው ነው›› ብሎ አዘነልን፡፡ ‹‹ወረዳችን በዕድገት እመርታ ላይ መሆኗን ታውቃላችሁ፡፡ ልዩ ልዩ ጽሕፈት ቤቶችና አጋር አካላት ተሳልጠው በመሥራታቸውና ሙስናንና ብልሹ አሠራን አስወግደን ልማታዊ አስተሳሰብን በማምጣታችን …›› ሕዝቡ ትዕግሥት አጣ፤ አንድ ጎረምሳ እንዲያውም ‹‹ይህንነን ንግግር የዛሬ ሦስት ዓመት ሰምተነው ነበር፡፡›› ሲል ተሰብሳቢው ሳቀ፡፡

      አንደኛዋ ወይዘሮማ ‹‹ምነው መንግሥት በየቦታው ተዋንያኑን ብቻ ነው እንዴ የሚቀይራቸው? የፊልሙን ስክሪፕትስ ለምን አይቀይረውም፡፡ ያ ይሄዳል ይሄ ይመጣል፤ ፊልሙ ያው ነው፡፡›› ሳቅና ጭብጨባ አጀባቸው፡፡ ሰውዬው ግራ እንደገባው ነው፡፡ ‹‹ይህ ንግግር ከራሴ የወጣ ነው፡፡ ይህንን ማን ተናግሮት ነው የዛሬ ሦስት ዓመት የሰሙት›› አለ ተገርሞ፡፡ ‹‹ባክህ ሃርድ ዌሩ ነው እንጂ ሶፍት ዌሩ ያው ነው፡፡ ወይ አብዴት አድርጉት ወይ ቀይሩት››  ወጣቱ ሲናገር በዐዋቂነቱ ተጨበጨበለት፡፡

      የወረዳችን ሊቀ መንበር አዝማሚያው ስለገባቸው ማይክራፎኑን ከፕሮግራም መሪው ተቀበሉት፡፡ ‹‹ወደ መጣንበት ጉዳይ ብንገባ ይሻላል፡፡›› ሲሉ አንድ ካህን ድምጻቸውን ከፍ አደረጉና ‹‹ልክ ነው ከተአምሩ መቅድሙ ረዘመብንኮ›› አሏቸው፡፡ ሊቀ መንበሩ ፈገግ ብለው ወረቀታቸውን ከቦርሳቸው አወጡ፡፡ አሁን ስፒል ቢወድቅ የሚሰማበት ዝምታ ተፈጠረ፡፡ የሰው ጆሮ እንደ ዲሽ ተዘረጋ፡፡

      ሊቀ መንበሩ ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡ ‹ፈጣሪ በቸርነቱ እስካሁን ሀገር አስፍቶ ጠላት አጥፍቶ አኑሮናል› ብለው ሲጀምሩ ሕዝቡ ቀጣዩን እንኳን ሳይሰማ አጨበጨበ፡፡ የተከበራችሁ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት፣ የክፍለ ከተማ አመራሮች፣ የድርጅት ኃላፊዎች፣ የሥራ አስፈጻሚ አባላት፣ የወጣት ሊግ አመራሮች፣ የሴቶች ሊግ አመራሮች፣ የአነስተኛና ጥቃቅን አመራሮችና አባላት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅት ኃላፊዎች፣ የአደረጃጀቶች ኃላፊዎች….. እያሉ እንደ ስም ጠሪ መምህር ወይም እንደ ሙሾ አውራጅ ሲዘረዝሩ ሊውሉ ነው ተብሎ ነበር የተጠበቀው፡፡

      ‹‹ድርጅታችንም እስካሁን በፈጣሪ ቸርነት፣ በታጋዮች መሥዋዕትነት፣ በአመራሩ ብስለትና በሕዝቡም ይሁንታ ይህንን ሀገር እየመራ መጥቷል፡፡›› ሲሉ ከጎኔ የነበሩት አንድ ሽማግሌ ‹‹ይኼ ነገር የሆነ የሆነ ነገር ሸተተኝ›› አሉኝ፡፡ በዚህ እድሜያቸው የሆነ ነገር ለማሽተት መቻላቸውን አደነቅኩና ‹‹ምን ሸተተዎት›› አልኳቸው፡፡ ‹‹ቆይ እስኪ ቀጣዩን እንስማው›› አሉ፡፡ እንደ ሬዲዮ አንቴና አንገታቸውን ወደ ላይ መዝዘው፡፡

      ሊቀመንበራችን እንደ ቀጠሉ ናቸው ‹‹ደግሞም ሕዝባችን እስካሁን አሳፍሮን አያውቅም፤ ከእንግዲህም ያሳፍረናል ብለን አናምንም›› ሲሉ ጭብጨባው ቀለጠ፡፡ እኒያ ሽማግሌ ግን ወደ ላይ የዘረጉትን የአንገታቸውን አንቴና ወደ ውስጥ ሰበሰቡት፡፡ ከዚያም ራሳቸውን ወደ ቀኝና ግራ ወዘወዙ፡፡ ‹‹ይኼ የተከተፈ ንግግር ነው›› አሉ፡፡ በግራ በቀኝ፣ በፊት በኋላ የተቀመጡት ተሰብሳቢዎች ዘወር ዘወር እያሉ አዩዋቸው፡፡ ሊቀ መንበራችን ግን ቀጠሉ፡፡ ‹‹አሁን ግን አገር የሚያጠፋ፣ ገጽታ የሚለውጥ፣ ዕድገት የሚገታ፣ የሕዝብን ሰላም የሚያናጋ ጠላት መጥቶብናል›› ሽማግሌው አንገታቸውን አውልቀው መጣል ይፈልጋሉ መሰል ከአመድ እንደተነሣች አህያ ያርገፈግፉታል፡፡

      ‹‹እኛም ብሔር ብሔረሰቦች ፊታቸውን ወደ ልማት ማዞራቸውን፣ ሀገራችንም በአንጻራዊ ሰላም ላይ መሆኗን ተመልክተን፤ ዐቅማችንንም ለልማት እንጂ ለሌላ ነገር ማዋል የለብንም ብለን ዝም ብንለው፤ ደግሞ እያለፈ እንደ ዘንዶ አደጋ ማድረስ ጀመረ››፡፡ ሽማግሌው የአንገታቸው አልበቃ ብሏቸው በጫማቸው መሬቱን ይፎግሱ ጀመር፡፡ ‹‹አሁን ግን ሕዝባችንን አጋዥ አድርገን ሀገራችንን አሳልፈን አንሰጥም በማለት ተነሥተናል፡፡ ሕዝባችን ሆይ እስካሁን የበደልንህ አይመስለንም፡፡ አንተም አልበደልከንም፡፡ ዐቅም ያለህ በዐቅምህ እርዳን፤ ዐቅም የሌለህ ለሚስትህ/ለባልሽ፣ ለእምነትህ ስትል መረጃ በመጠቆም እርዳን፡፡›› አሁን ሽማግሌው እጃቸውን ከእጃቸው ጋር ማፋተግ ጀመሩ፡፡ ሊልጡት ነው እንዴ፡፡ ‹‹ወስልቶ ከዚህ ዘመቻ የቀረ ካለ ግን ይጣላናል፡፡ አንተወውም፤ ድርጅታችንን፤ እንምረውም››

      ‹‹ኦህ›› አሉ ሽማግሌው፡፡

      ‹ለዚህ አማላጅ የለንም፡፡ ፀረ ሽብር ዘመቻችን ተጀምሯልና የሀገራችን ሰው በዚሁ ወቅት በየራስህ ከትተህ እናግኝህ፡፡››

      ሕዝቡ አጨበጨበ፡፡ ጭብጨባውም ረዘመ፡፡

      ሽማግሌው ማንም ሳይቀድማቸው ተሥፈንጥረው ተነሡ፡፡

      ‹‹እሽ አባቴ›. አሉ ሊቀመንበሩ፡፡ ሽማግሌው ወኔ ይዟቸው የተነሡ መስሏቸው፡፡

      ‹‹ይህ ንግግር የማን ነው?›› አሉ፡፡ እየተንቀጠቀጡ፡፡ ሰው አጉረመረመ፡፡

      ‹‹እንዴት ማለት›› አሉ ሊቀ መንበሩ፡፡

      ‹‹ይህ ንግግር ዐፄ ምኒሊክ ለዐድዋ ዘመቻ ከተናገሩት ንግግር የተወሰደ አይደለም?›› አሉ ሽማግሌው፡፡

      ‹‹ነው›፡፡ ግን ሬሚክስ አድርጌ በአዲስ አቀራረብ ነው ያመጣሁት፡››

      ‹‹ምኑን ነው ሬሚክስ ያደረጉት››

      ‹‹ከዓላማዬ ልጀምርልዎት፡፡ የቀድሞ መሪዎችን ንግግር እንዲህ ሬሚክስ እያደረግን ካላቀረብነው ይረሳሉ፡፡ ትውልዱ አያስታውሳቸውም፡፡ ይህንን ያደረግኩት ለምኒሊክ ክብር ብዬ ነው፡፡ አላዩም ዘፋኞቻችንን፤ የቀድሞ ዘፋኞችን ዘፈን ሬሚክስ እያደረጉ በአዲስ አቀራረብ ሲያቀርቡ፡፡ እኔም እንደዚያው ነው ያደረግኩት፡፡ ሬሚክስ ያደረግኩት ደግሞ የምኒሊክን ባላባታዊ አስተሳሰብ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ጋር ነው፡፡ በአዲስ አቀራረብ ያልኩት ንግግሩን ልማታዊ፣ ሕዝባዊ፣ ፌዴራላዊ፣ ብዝኃነትን የያዘ አድርጌ ነው ያቀረብኩት፡፡›› አሉ ሊቀ መንበሩ፡፡

      ‹‹እና ዐፄ ምኒሊክን በአዲስ አቀራረብ አቀረቧቸው ማለት ነው›› አሉ ሽማግሌው፡፡

      ‹‹አዩ አባቴ ማዘመን ማለት ይኼ ነው፡፡ ታሪክን ማረም ይገባል፡፡ አዲስ መፍጠር ካልተቻለ የነበረውን ሬሚክስ እያደረጉ በአዲስ አቀራረብ ማቅረብ ነው፡፡ ሕዝቡም የሚወደው ይኼንን ነው›› አሉና ወደ ሕዝቡ ሲመለከቱ ጎረምሶቹ ‹‹ሼባው አቦ ተወና፣ እኛ ተመችቶናል›› አሏቸው ሽማግሌውን፡፡

      ሽማግሌውም ‹‹በጦርነት ያልጠፋች ሀገር በሬሚክስ መጥፋቷ ነው በሉኛ›. ብለው ተቀመጡ፡፡ በአዲስ አቀራረብ በሬሚክስ ላስደሰቱን ለሊቀ መንበራችን ግን ጭብጨባው ቀለጠላቸው፡፡

      © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው

      አንዳንዶች በድሎትና በምቾት ላይ ያገኙትን የሰላም ዘመን ምንም ሳይጠቀሙበት ‹ተወለዱ- ሞቱ› ተብለው ያልፋሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ስደታቸውን፣ እሥራቸውንና ግዞታቸውን፣ መከራቸውንና ሕመማቸውን የሀገርንና የወገንን ታሪክ ለመለወጥ፣ በሰው ልጅ ታሪክም ውስጥ ጉልሕ ቦታ ለመያዝ ሲጠቀሙበት ይታያሉ፡፡ እኛ ‹የመከራ በረከት› ፈረንጆች ‹blessing in disguise› የሚሉት ማለት ነው፡፡ ሰውን የሚጎዳው የደረሰበት ችግርና መከራ አይደለም፡፡ በዚያ ችግና መከራ ውስጥ ሆኖ የሚያየው ነገር ነው፡፡ ገነት ውስጥ ሆነው ሲዖልን ከሚያዩ ሰዎች ይልቅ ሲዖል ውስጥ ሆነው ገነትን የሚያዩ ሰዎች ይበልጣሉ፡፡ አንዳንዶች በመታመማቸው ምክንያት ታሪክ ሠርተዋል፡፡ አንዳንዶች በመታሠራቸው ምክንያት ታሪክ ሠርተዋል፤ አንዳንዶች በመሰደዳቸው ምክንያት ታሪክ ሠርተዋል፤ አንዳንዶችም በመቸገራቸው ምክንያት ታሪክ ሠርተዋል፡፡
      ችግር ሁለት ነገሮችን ትወልዳለች፡፡ ጠቢባን ሲያዋልዷት ብልሃትን፣ ሞኞች ሲያዋልዷት ድህነትን፡፡

      ችግርን ቀምሰዋት፣ በጥበብም አዋልደዋት ብልሃትን እንድትወልድ ካደረጓት የሀገራችን ሰዎች አንዱ ደጃዝማች ኃይሉ እሸቴ ናቸው፡፡ ዘመነ መሳፍንት ተብሎ በሚጠራው የሀገራችን ዘመን አብዛኛውን ዘመናቸውን ያሳለፉት የአስተዳደር፣ የጦርና የቀለም ሰው ደጃዝማች ኃይሉ እሸቴ የተወለዱት በ1746 ዓም አካባቢ ጥር 12 ቀን ነው፡፡ አባታቸው ደጃዝማች እሸቴ እናታቸውም ወ/ሮ ወለተ ራጉኤል ይባላሉ፡፡

      ደጃዝማች ኃይሉ በዘመኑ እንደነበሩት የኢትዮጵያ የመኳንንት ልጆች ፈረስ ግልቢያውንና አደኑን እየተማሩ፣ የቀለም ትምህርቱንም ጎን ለጎን እያስኬዱ አደጉ፡፡ በዚህ መካከል ግን መጋቢት 11 ቀን 1760 ዓም አባታቸው ደጃዝማች እሸቴ በጦርነት ላይ ሞቱባቸው፡፡ ያኔም እድሜያቸው ወደ አሥራ አራት ዓመት ያህል ሆኗቸው ነበር፡፡ ወላጅ እናታቸው በ1755 ዓም የሞቱባቸው ኃይሉ እንደገና የአባታቸው በልጅነታቸው መሞት ኀዘኑን አጸናባቸው፡፡

      ዘመነ መሳፍንት ግም ግም ሲልና ከትግራይ የመጡት ራስ ሚካኤል ስሑል መንግሥቱን እየጠቀለሉት ሲመጡ፤ በጎንደር ከተማም በቋረኞቹና በኦሮሞዎቹ መካከል ንጉሡን ኢዮአስን ይዘው መንግሥቱን ለመቆናጠጥ የፖለቲካው ትግል ሲያይል፣ ኃይሉ እሸቴ የራስ ሚካኤል ስሑልን ልጅ ወለተ ተክለ ሃይማኖትን አግብተው የራስ ሚካኤልና የቋረኞቹ ደጋፊ መሆናቸውን አሳዩ፡፡ ራስ ሚካኤል ስሑል በጎንደር ቋረኞችን ይዘው ሥልጣን ሲያደላድሉ፣ ደጃች ልቦ እና ደጃች ፋሲል ከተባበሯቸው ከይልማና ዴንሳ፣ ከሜጫ፣ ከዳሞትና ከወሎ ተወላጆች ጋር ሆነው ሸፈቱ፡፡ የተወሰኑት ቋረኞችም ተከተሏቸው፡፡ ራስ ሚካኤልም አስገብራለሁ ብለው፣ ደጃዝማች ኃይሉም የአባታቸውን ሞት ለመበቀል አብረዋቸው ዘመቱ፡፡ የመጀመሪያውን የታወቀ ጀብዷቸውንም በዚህ ጦርነት ላይ አሳዩ፡፡ የዘመኑ ገጣሚም

      ጎራዴማ ወትሮ እንዲመታ ዐውቃለሁ፣

      እኔ ኃይሉን እንጂ አመሰግናለሁ፤

      ብሎ ገጠመላቸው፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ደጃዝማች ኃይሉ ተፈሪነታቸውና ተሰሚነታቸው እየጨመረ፤ በግዛትም ላይ ግዛት እየተሾሙ ኖሩ፡፡ በተደጋጋሚ በየጦርነቱ ባሳዩት ጀብዱ እየተገጠመላቸው፣ ግዛትም እየተጨመረላቸው፤ የራስ ሚካኤል ስሑል ዘመን ሲያልፍም ከመጭዎቹ ኃያላን ጋር እየተስማሙ እስከ ዐፄ ተክለ ጊዮርጊስ ዘመን እየተወደዱና እየተሞገሱ ቀጥለው ነበር – ደጃዝማች ኃይሉ፡፡

      በአንድ በኩል የዐፄ ተክለ ጊዮርጊስ ዘመን በ1771 ዓም ሲጀምር የደጃዝማች ኃይሉ የተወዳጅነትና የተከባሪነት ዘመን በሌላ በኩል ማዘቅዘቅ ጀመረ፡፡ በተክለ ጊዮርጊስና በሰሎሞን መካከል በቤተ መንግሥት የሥልጣን ሽኩቻ ተፈጠረ፡፡ በመጨረሻም ደጃች ክንፉ የሰሎሞንን ዋና ደጋፊ ራስ ኃይሉን ወግተው ንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስን አነገሡ፡፡ በዚህ ጊዜ ደጃዝማች ኃይሉ የዘመነ መሳፍንት ሁከትና ውጊያ ሲሰለቻቸው ካልመጡብኝ አልሄድም ብለው ዐርፈው ተቀምጠው ነበር፡፡ ደጃች ክንፉ ራስ ኃይሉን ለመውጋት ሲዘምቱ ደጃዝማች ኃይሉ አብረዋቸው እንዲዘምቱ ልከውባቸው ነበር፡፡ ደጃዝማች ኃይሉ ግን ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ይህም በአሸናፊዎቹ በእነ ደጃች ክንፉ ዘንድ ጥርስ አስነከሰባቸው፡፡

      ከጦርነቱ በኋላ በንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስና በደጃች ክንፉ ታዝዘው ደጃዝማች ኃይሉ ወደ ጎንደር መጡ፡፡ የጠበቃቸው ግን ጎጃም ቡሬ ላይ በቁም እሥር መቀመጥ ሆነ፡፡ እርሳቸውም ቡሬ ላይ ጥቂት ከቆዩ በኋላ ጠፍተው ሲሄዱ ደጃች ክንፉ ፈረሰኛ ልከው አቸፈር ላይ አስያዟቸውና በሠንሠለት ታሥረው ጎንደር ገቡ፡፡ እርሳቸው ታሥረው ጎንደር ሲገቡ የጎንደር ሕዝብ በእጅጉ ማዘኑን ታሪከ ነገሥቱ ይነግረናል፡፡ የዋልድባ መነኮሳትም ኃይሉን ለማስፈታት ምልጃ ገብተው ነበር፡፡ ንጉሡም ከዛሬ ነገ እፈታለሁ እያሉ ዝም ብለው አስቀመጧቸው፡፡

      የጎንደሩ የቁም እሥር ያልተመቻቸው ደጃዝማች ኃይሉ በሌሊት ጠፍተው ማኅደረ ማርያም ገቡና የተማጽኖ ደወል መቱ፡፡ ኃይሉ በደኅናው ዘመን ከታላላቅ ገዳማትና አድባራት አባቶች ጋር በጎ ግንኙነት ነበራቸው፡፡ እርሳቸውም የዘመኑን ትምህርት የተማሩ ነበሩና በእነዚህ ታላላቅ አባቶች ዘንድ ተሰሚነት ነበራቸው፡፡ ደጃዝማች ኃይሉ በእቴጌ ማርያም ሥና በተደበረችው ማኅደረ ማርያም ለአራት ዓመት ከሦስት ወር ነበር በግዞት የተቀመጡት፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በሰላሙ ዘመናቸው በጦርነትና በአስተዳደር ካበረከቱት አስተዋጽዖ ይልቅ ኃይሉን ሲያስጠራቸው የሚኖረው በዚህ በግዞትና በመከራ ዘመናቸው ለሀገራቸው የሠሩት ተመን የማይገኝለት ሥራቸው ነበር፡፡

      ራስ ኃይሉ በማኅደረ ማርያም ሲቀመጡ ከሁካታውም ከጦርነቱም ጋብ አሉ፡፡ ሀገር ለሀገር ከመዞር ዐርፈው ወደ ልባቸው ተመለሱ፡፡ በደብሩ የሚከናወነው ጸሎትና ትምህርትም ጽሞናን ሰጣቸው፡፡ በዚያ ዘመን ማንም ሊታየው ያልቻለውን ዘመን ተሻጋሪ ራእይም አዩ፡፡ ሀገሪቱ በግራኝ አሕመድ ጊዜ ከገጠማት የርስ በርስ ጦርነት ወጥታ ወደ ሌላ የርስ በርስ ጦርነት ገብታለች፡፡ በጎንደር ከተማ የሚደረገው የሥልጣን ትግል ከምንም በላይ የጎዳው ሕዝቡንና የሕዝቡን ታሪክ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ለብዙ ዘመናት በየቤተ መንግሥቱ፣ በየገዳማቱና አድባራቱ የተከማቹ መዛግብት በጦርነቱ ምክንያት ይቃጠላሉ፤ ይቆነጻጸላሉ፡፡ ኃይሉ በንሥር ዓይናቸው ይህንን ነበር ያዩት፡፡

      ‹በሰንበት ላይ ደብረ ዘይት፣ በእራት ላይ ዳረጎት› እንዲሉ ኃይሉ ይህንን ሲያስቡ የሸዋው ተወላጅ ጽሕፈት ዐዋቂው አቤቶ አበጋዝ ወደ ማኅደረ ማርያም መጣ፡፡ ደጃዝማች ኃይሉ እሥርና ግዞቱን ወደ ታላቅ የጥናትና ምርምር ተቋምነት ቀየሩት፡፡ ከየገዳማቱና ከየሊቃውንቱ እየተላላኩ የታሪክ መዛግብትን እያስመጡ፣ እያመሳከሩና እየጠየቁ ስማቸውን እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚያስጠራውን፣ ዛሬ በፓሪስ ቤተ መጻሕፍት በቁጥር 143 ተመዝግቦ የሚገኘውን፣ በአራት አዕማድ ተጽፎ፣ በ370 ገጽ በብራና የተዘጋጀውን ‹ታሪከ ነገሥት ዘደጃዝማች ኃይሉ እሸቴ› የተባለውን የኢትዮጵያ የታሪክ መጽሐፍ አዘጋጁ፡፡ ለሦስት ዓመታት ያህል መረጃዎችን ሲያሰባስቡ፣ መጻሕፍቱን ሲያመሳክሩ ቆይተው፣ ለአንድ ዓመት ያህል ተጽፎ በ1778 ዓም መስከረም ሰባት ቀን ተጠናቀቀ፡፡

      ደጃዝማች ኃይሉ ከማኅደረ ማርያም ግዞት በኋላ እንደ ጥንቱ ባይሆንም እየተሾሙ ለጥቂት ጊዜ ቆይተዋል፡፡ በተለይ በራስ ዓሊ ጊዜ  ስሜንንና በጌምድን እየተሾሙ በደስታ ኖረዋል፡፡ ራስ ዓሊ ሲሞቱ ግን ከቀጣዩ ባለ ሥልጣን ከራስ ወልደ ገብርኤል ጋር መስማማት ባለመቻላቸው በስደት ወደ ጎጃም ወደ ራስ መርእድ ዘንድ ሄዱ፡፡ በዚያ ሆነው ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን ዘመን ሲናፍቁ መርዕድና ወልደ ገብርኤል ሐምሌ 15 ቀን 1791 ዓም ባደረጉት ውጊያ ሁለቱም ራሶች ሲወድቁ የድሉ ሚዛን ወደ ራስ ወልደ ገብርኤል ሰዎች ዞረ፡፡ደጃዝማች ኃይሉም ወደ ርስቴ እመለሳለሁ የሚለው ተስፋቸው ተቆረጠ፡፡

      ደጃዝማች ኃይሉ የሕይወታቸውን ፍጻሜ ያሳለፉት ጎጃም ሞጣ ነው፡፡ እዚያ ምናልባት እስከ 1810 ዓም አካባቢ የቆዩ ይመስላል፡፡ ሞጣ እያሉ ታላቁ የውጊያና የታሪክ ሰው ታምመው ሞቱ፡፡ ወገኖቻቸውም ሬሳቸውን ይዘው ራሳቸው ወዳሠሩት ወደ እስቴ መካነ ኢየሱስ ለመቅበር መጡ፡፡ ዘመነኞቹ የራስ ጉግሣ ሰዎች ግን ሬሳውን አናሳልፍም ብለው እምቢ አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ልጃቸው ወ/ሮ ምርጪት ፡-

      እግዚኦ አቤት አቤት

      እግዚኦ አቤት አቤት

      አፈር ይለምናል የሀገሩ ባለቤት፤

      ብለው ወደ ራስ ጉግሣ ደብዳቤ ጻፉ፡፡ ራስ ጉግሣም ነግ በእኔ ብለው ፈቅደው የታላቁ የውጊያና የታሪክ ሰው የደጃዝማች ኃይሉ መጨረሻ በእስቴ መካነ ኢየሱስ ተፈጸመ፡፡ በክፉ ዘመን ሰብስበው በማጻፍ ለዘመናችን ያበረከቱልን ታሪከ ነገሥት ግን ዘመንን እየተሻገረ እስከ ዘመናችን ዘልቋል፡፡ ለነገም ይኖራል፡፡ በችግራቸው የሚቆዝሙ፣ በመከራቸው የሚተክዙ፤ ከግንብ ባሻገር ብርሃንን ለማየት ያልታደሉ ሰዎችንም ይወቅሳል፡፡ እኛም ዜናውን ከታሪከ ነገሥታቸውና ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ከጻፉላቸው አጭር ታሪክ አግኝተነዋል፡፡

      © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

      ከዲያቆን ዓባይነህ ካሤ


      ኢትዮጵያውያን ደማቸው የዐረብን አስፋልት አቀለመው፡፡ ባንዲራውን በራሱ ላይ ሸብ ያደረገው የእማማዬ ልጅ የእኔ ጀግና ማንነቱን እየተናገረ በአናቱ ላይ የወረደውን የድንጋዩን ናዳ በሀገሩ ፍቅር ተቋቁሞ በክብር አሸለበ፡፡ ለእርሱ ከዚህ በላይ ሌላ ድል አልነበረምና፡፡ ድንጋዩስ እርሱን አሳርፎታል፡፡ ነፍሱን ይማርልን እንጂ! ባንዲራችን ግን እንደተመታች እንደታመመች ናት፡፡ እውን ይኽ የሆነው በእኛ ላይ ነው? 


      ይህቺ ባንዲራ እኮ ጨርቅ አይደለችም፡፡ ያ በሳኡዲ መሬት ተወግሮ የሞተው ወንድሜ የኮራባት በሞቱ ጊዜ የለበሳት የክብሩ፣ የማንነቱ መገለጫ እንጂ፡፡ ማንም ባይደርስለት ባንዲራው ነበረችለት፡፡ በእርሷ ተጽናና፡፡ ሞተ አልለውም መሰከረ እንጂ፡፡ ባንዲራ ለብሶ መከራን መጋፈጥ የሰማእታት ወግ ነው፡፡ 

      ዳግማዊ ሆሎኮስት በኢትዮጵያውያን ላይ? እንዴት እንዴት? ደግሞ በ ፳፩ኛው ክፍለ ዘመን፡፡ የሰውን ሕይወት የሚያስገብር ምን ጥፋት ተገኝቶ ነው ወይስ የሟርት መስዋእታቸው እኛ ነን፡፡ “ከሕግ አስከባሪው ፖሊስ” እስከ ዱርየው የእኅቶቻችን ክቡር ሰውነት እንደ ውሻ ሲጎተት ከማየት የሚዘገንን አረመኔነት ምን አለ? ይህ እኮ ንቀት ነው፡፡ ይህ እኮ ድፍረት ነው፡፡ ይህ እኮ የሀገርን ሉዐላዊነት መድፈር ነው፡፡ 


      ምንም ዓይነት ወንጀል የሠራ ሰው የሚዳኝበት ሥርዓት አለው፡፡ ስንቶች አእምሯቸውን ስተው ተመለሱ…ዝም አልን፡፡ ስንቶች እንደ ከብት ከግመሎቻቸው እጅግ በተዋረደ ሁኔታ እንደ ሸቀጥ ተጠፍረው ተላኩልን…ያኔም ዝም አልን፡፡ ስንቶች ከፎቅ ራሳቸውን እየወረወሩ ተፈጠፈጡ… አሁንም ዝም አልን፡፡ ዛሬ ደግሞ በዚህ መጡ…ዝም እንዳልን እንቀጥል ይሆን? ስጋቴ ይህ ነው፡፡ አስኪ በማነህ ማነህ የተረፉትን እንድረስላቸው፡፡

      ለመጽሓፋቸው (ኢትዮጵያን አትንኩ ለሚለው) ያልተገዙ በቀላሉ ይተውናል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እኮ ወንዝ እና ተራራዋን ማለት አይደለም፡፡ ከምንም በላይ ሕዝቧ እንጂ…ቀጥሎ ወንዝ እና ተራራዋ ሜዳ እና ሸለቆዋ…ወዘተ ይከተላሉ፡፡ ስለሆነም የሚከተሉትን ለማድረግ ብንተጋ፤

      ፩. በየቤቱ የተዘጋባቸውን እና በእንግልት ብዛት የሚቃስቱትን ፈልጎ ማግኘት እና አሰቸኳይ እርዳታ ማድረግ፣ መመለሻቸውን ማበጃጀት፣

      ፪. በየፖሊስ ጣቢያው ወይንም ወኅኒው የታሰሩትን ፈልጎ ማግኘት እና ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ከሚመለከታቸው ጋር መነጋገር፣

      ፫. የተቃውሞ ድምጻችንን በሕጋዊ መንገድ በያለንበት ማሰማት፣

      ፬. ችግር የደረሰባቸው፣ ሰብአዊ መብቶቻቸው የተጣሱባቸው ወገኖቻችን ከሳኡዲ ሁሉ ካሣ የሚያገኙበትን ማፈላለግ፣

      ፭. ከተመለሱም በኋላ የሚያገግሙበትን እና መደበኛ ኑሮ የሚገፉበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት፡፡

      ፮. እነዚህን እና ሌሎችንም ጉዳዮች የሚፈጽም ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋም፡፡

      ለዚህ አልተፈጠርንምና፡፡

      በኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት ታላቅ ቦታ ያላቸውን ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራትንና ፕሮፌሰር ዶናልድ ክራሚን ለማሰብ ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኮንን አዳራሽ መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በወቅቱ የሁለቱም ደቀ መዝሙር የነበረው ዶ/ር ውዱ ጣፈጠ ያቀረበውን ማስታወሻ እንብቡት፡፡


      ዝክረ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራትና ፕሮፌሰር ዶናልድ ክራሚ

      ዉዱ ጣፈጠ( ዶ/ር)

      ከተማሪዎቻቸው አንዱ

      ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራትና ፕሮፌሰር ዶናልድ ክራሚ ሁለቱ በዩነቨርስቲ የትምህርት ቆይታዬና ብሎም በህይወቴ ላይ ቀና ተፅእኖ ያሳደሩ ታላቅ መምህሮቼ ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የቅድመ-ምረቃ የታሪክ የአራተኛ ዓመት ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ከፕሮፌሰር ታደሰ ጋር የመጀመሪያን ትውውቅ አደረግን፡፡ ለቅድመ ምረቃ (ለቢ.ኤ.) ዲግሪ ማóóያ የምረቃ Òሁፍ ምርምር ለማድረግና ውጤቱንም ለመፃፍ እንድችል እርሳቸው አማካሪዬ ሁነው ተመድበው ነበር፡፡ በወቅቱ እርሳቸው የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ስለነበሩ እርሳቸውን አግኝቶ ለማነጋገር ትንሸ ችግር ፈጥሮብኝ ነበር፡፡ ከትንሸ መመላለስ በኋላ አግኝቸ ራሴን ሳስተዋውቅ ትኩር ብለው እየተመለከቱ በርጋታ አዳመጡኝ፡፡ ከዚያም እስኪ ወደ ሌላ ነገር ከመግባታችን በፊት የራስህን ታሪክ፤ የቤተሰብህን፤የአስተዳደግህንና የትምህርትህን ነገር ግለፅኝ ብለው ጠየቁኝ፡፡ በጊዜው ይህ ሁሉ ምን ያደርጋል ብየ በየዋህነት ራሴን ጠይቄ ነበር፡፡ የርሳቸው አካሄድ የገባኝ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነበር፡፡

        ለቅድመ ምረቃ የምርምር ስራ የሰራሁበት ርእስ ስለ ራጉኤል አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ነበር – እንጦጦና አዲስ አበባ መርካቶ ስለሚገኙት መንትያ አብያተ ክርስቲያናት፡፡ ፕሮፌሰር ታደሰ  በጣም ረጋ ያሉ፤ በተመስጦ የሚያዳምጡ፤ ቀስ ብለው የሚናገሩና እንዲህ አይነቶቹን ዋና ዋና ፍሬ ነገሮች አስተውለሀዋል ብለው በማስታወሰ መንገድ የሚያሳዩ ነበሩ፡፡ በዜያ ጊዜ እኔን ለመሰለው ገና ጀማሪ በማበረታታትና በሚቀጥለው ጊዜ ስንገናኝ አዲስ መረጃ እንደምታመጣ ተስፋ አለኝ ብለው የሚሸኙ ነበሩ፡፡ የሚያውቁትን መረጃ ጠቅሰው ፈልግ የሚሉ፤ መረጃ ሊሰጡ የሚችሉና ያውቃሉ ብለው የሚገምቷቸውን ሰዎችን ስም የሚነግሩና ሲቻልም የሚያስተዋውቁ ነበሩ፡፡

         በዚያ ጊዜ እጅግ ያስቸገረኝ ነገር ቢኖር ጽሕፈታቸውን ማንበቡ ነበር፡፡ ይህም ቢሆን ዲኑ ቢሮ ትሰራ የነበረች ወ/ሮ እልፍነሽ እንዳለ ተረር አድርጋ እያነበበች ችግሬን ታቃልልኝ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ አብራቸው ስለሰራች ጽህፈታቸውን ያለችግር ማንበብ ችላ ነበርና፡፡

          አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመቀጠር እድል ባጋጠመኝ ወቅት ሁል ጊዜ ያለማቋረጥ ድጋፋቸውንና አበረታች ቃላቸውን ያለ ምንም ስስት ይነግሩኝ ነበር፡፡ ይህም የታሪክ ትምህርት ክፍል በርሳቸው ስር ሆኘ ምክራቸውን እጠየቅሁ እንዳነብና ልምድ እንዳገኝ መድቦኝ ነበርና፡፡ የመካከለኛውን ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ለማጥናት የሚረዳኝን የግእዝ ቋንቋ ትምህርት ሁለት ኮርስ እንድወስድ አበረታቱኝ፡፡ በጊዜው ኮርሱን ይሰጡ ለነበሩት ለዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ አስተዋወቁኝ፡፡ ብዙ አልገፋሁበትም እንጅ የፈረንሳይኛና የጣሊያንኛ  ቋንቋ ትምህርት እንድማር አበረታተውኝ ነበር፡፡

         ቀጥሎም ታሪክ የማስትሬት ትምህርት በምማርበት ጊዜ ትልቅ ድጋፍ በማድረግ የተለመደ የማማከር ሀላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡ ለዚህ ዲግሪ ማóóያ   የምርምር ጥናቴ ርእስ የነበረው የዋግና የላስታ ታሪክ የሚል ነበር፡፡ እርሳቸው እንደነገሩኝም የላስታ መሪዎች የዛጉዌን ታሪክ ለመፃፍ እቅዳቸው እንደነበርና ይህንን ታሪክ ለመፃፍ በማሰቤ፤ የትምህርት ክፍሉም ሆነ እርሳቸው ሰለገፋፉኝ፤ በመቀበሌ ደስ እንዳላቸው ገልፀውልኛል፡፡

      የምሰራበት የታሪክ ዘመን ራቅ ያለ በመሆኑና ታሪኩን ለማያያዝና መስመር የያዘ የታሪክ ዳራ እንዲኖረው ለማድረግ ያለ መሰልቸት ይመክሩኝ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ስራየ ደከም ያለ ሲመስላቸው በራሳቸው ፅፈው ይህንን ጨምረው እያሉ ታሪኩ ወጥነት ኖሮት እንዲተረክ እጅግ ለፍተዋል፡፡ በምሳ ሰአት ጭምር ቁጭ ብለው እያረሙና እያስተካከሉ ይህ ነው ተብሎ የማይገለጽ ድካም አሳልፈዋል፡፡ በዚያ ጊዜ የማስተርስ ድግሪ ትምህርት አራት አመት ይወስድ ስለነበር የማስረከብያ ጊዜው እንዳያልፍብኝ ብለው አሜሪካን አገር ትኖር የነበረች የልጃቸውን ቀለበት ቀን በኔ ምክንያት ሳይሳተፉ ቀርተዋል፡፡ ችግር የለም አንተም ልጄ ነህ እንዳሉኝ” አስታውሳለሁ፡፡ በ|ላም በአሉ እዚህም ተከበረ፡፡

         በተለይም ደግሞ የታሪክ የዶክተሬት ትምህርት እንድማር በማሰብ፤ ለሌሎች እንዳደረጉት ሁሉ፤ እኔንም ከÝሮፌሰር ክራሚ ጋር አስተዋወቁኝ፡፡ በ1991 .ም. ወደ ኢሊኖይ ዩኒßርስቲ – ኧúርባና aምፔይን – በሄድኩ ጊዜ Ýሮፌሰር ክራሚ እንደ Ýሮፌሰር ታደሰ ሁሉ አገሩን በማስተዋወቅ፤ በማበረታታት፤ የሚቸግረኝን ነገር ሁሉ በማደረግ ትልቅ ድጋፍ አድርጎልኛል፡፡ እኔ በሄድኩበት አመት ከኬንያ የመጣውን ሌላ ተማሪ አይሮፕላን ጣቢያ ድረስ በመሄድ ተቀበለው፡፡ እኔንም እንደዚሁ፡፡ ሁለታችንም እቤቱ ወስዶ አሳረፈን፤ አስተናገደን፡፡ ቤት ተከራይተን ራሳችንን እስክንችል ድረስ ለሳምንት ያክል እቤቱ ተቀመጥን፡፡ እንግድነት በጣም ሳይሰማንና ተሳቀንም በችኮላ ቤት እድንከራይ ሳንሆን፡፡ አሜሪካ በደረስኩበት ጊዜ ምንም ገንዘብ አልነበረኝምና ገንዘብ እስካገኝ ድረስ ቤቱ እንድቀመጥ ጋብዞኝ ነበር፡፡ በተለይም ባለቤቱ ሚስ ሎሬይን ክራሚን እንደ እናት ነበር የምንመለከታት፡፡

        አገርን ለቅቆ፤ ባህርን ተaግሮ በሌላ አገር መኖር የሀገርና የወገን ናፍቆት አስቸጋሪ ቢሆንም በአመት በአል ቀናት ማለትም የአሜሪካን የምስጋና ቀን፤ ገናና፤ ፋሲካ በደረሰ ቁጥር Ýሮፌሰር ክራሚ ቤት እየተጋበዝን በአላቸውን በአል አድርገን ውለናል፡፡ ምናልባት በአጋጣሚ በከተማው ካልኖሩ በስተቀር፡፡ በእነዚህ በአላት ሌላ ከተማ የሚኖሩ ልጆቹና ¹ደኞቹ ስለሚሰባሰቡ በአላቸውን ደመቅ አድርገን ተደስተን አብረን አሳልፈናል፡፡ የኢትዮÉያ ቡና ተፈልቶ፤ የኢትዮÉያ ቱሪስት አስጎብኚ ድርጅት በሰራቸው የንግስተ ሳባ ስእል ባላቸውና በሚያማምሩት የቡና ስኒዎች አገራችን ያለን እስኪመስለን ድረስ ተጋብዘናል፡፡ ቢራና ወይንም ተጎንጭተናል፡፡

        በዩኒቨርስቲው የትምህርት መርሀ ግብርና ሌሎች ችግሮች በተከሰቱ ቁጥር እንደ አባታችንና እናታችን ቤት ሳንሳቀቅና ሳንፈራ ቢሮው ሄደን የገጠመንን ችግር አማክረን መፍትሄ አግኝተናል፡፡ በተቻለው ጊዜ ሁሉ እኛን ለማረጋጋትና ችግራችንን ለማቃለል ከልቡ ጥ[ል፡፡ አንዳንዴም ንዴታችንን ለማስረሳት ቢራ እየጋበዘ፡፡ ያውም ከሚያውቃቸው አንዳንድ ቀልዶች ጋር እያዋዛ፡፡ “ባርባ አራቱ የጎንደር ታቦታት’ እና ‘ነው እንዴ” ከሚሉ ሀገርኛ ቀልዶች ጋር፡፡

        በዚሁ የአሜሪካ ቆይታየም Ýሮፌሰር ታደሰም እዚያው ስለነበሩ የሁለቱ አማካሪዎቼና መምህሮቼ በአንድ ከተማ መገኘት ለአኔ ጥሩ አጋጣሚ ነበር፡፡ የዶክተሬት ዲግሪ ማóóያ የጥናት ሰራየ በኢትዮÉያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ላይ ስለነበር በቂ የሆነ ድጋፍና ምክር ለማግኘት ችያለሁ፡፡ ቀደም ብሎ ሁለቱ መምህሮቼና Ýሮፌሰር ሁሴን በኢትዮÉያ የሀይማኖት ጉዳዮች ላይ ምርምር ለማደረግ እቅድ ስለነበራቸው፤ እኔም በዚሁ እቅድ ውስጥ ተካትቸ ስለነበርና፤ የጥናት ርእሴም የዚሁ አካል ስለነበር የሁለቱ መምህሮቼ ድጋፍ አልተለየኝም ነበር፡፡

       ከሁለቱ መምህሮቼ ጋር የነበረኝ ቅርርብ በምርምር ስራ ላይ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ቤተሰባዊ ጭምር እንጅ፡፡ የÝሮፌሰር ታደሰ ሁለት ሴት ልጆች – ህይወቴና ህሊና ታደሰ – የቀለበት ስነ-ስርአታቸውን በተለያየ ወቅት ባደረጉ ጊዜ መጋበዝ ብuሳይሆን እኔም ሆንኩ የታሪክ ትምህርት ክፍል አባሎች እንደ ቤተሰብ አባል ንቁ ተሳታፊ ነበርን፡፡ ምንም ጊዜ የማይረሳኝና ምን ያህል Ýሮፌሰር ታደሰ እንደሚያቀርቡኝ የተረዳሁት በጊዜው ¹ደኛየ ነበረችውን ያሁኗን ባለቤቴን ይŸት እንድገኝ በጋበዙኝ ጊዜ ነበር፡፡ እርን በአካል አያውkትም ነበር፡፡ ነገር ግን መጠየቅ ይወዳሉና በማስተርስ ዲግሪ ማóóÎሁፌ ውስጥ ስማóን አይተው ጠይቀውኝ ነበርና አስረዳሁዋቸው፡፡ ታዲያ የግብŸ ጥሪ ወረቀት ሲሰጡኝ “¹ደኛህን ትተሀት እዳትመጣ፡፡ ልብ በል እርካልመጣች እዳትመጣ” ያሉኝ ነበር፡፡ የቀለበቱን ስነ-ስርአት አንስተን ባወራንቁጥር እኔና ዶ/ር አበበ ፍስሀ የተጫወታችሁት አይረሳኝም ይሉ ነበር፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ጊዜያት ከውጭ ለመጡ ቀደምት ¹ደኞቻቸው ግብŸ ባደረጉ ጊዜ እኔና የአሁኗ ባለቤቴ ተጋብዘን የባለቤታቸውን የወ/ሮ አልማዝን የተዋጣ የባልትና ሞያ ተkድሰናል፡፡

        Ýሮፌሰር ክራሚ የ60ኛ አመት የልደት በአሉን ባከበረበት ጊዜ በወዳጅነት ተጠርተን ተጋብዘን ነበር፡፡ ከባለቤቴ ጋር ምን እንስጠው ተባብለን ተመካከርንና ወይን እንግዛለት ተባባልን፡፡ መቸም የተማሪ አቅም ነው ብለን አነስ ያለች የጣሊያን ወይን ወሰድንለት፡፡ ከጥቂት ቀናት በ|ላ በÑፈልኝ ማስታወሻ ሌሎች ለልደቴ ከላኩልኝ ነገር ሁሉ እንደናንተ የሚጥም ወይን ያመጣልኝ የለም የሚል ቃል ነበረው፡፡


        Ýሮፌሰር ክራሚ ጋር ለመስክ ስራ አብረን አልተ¹ዝንም፡፡ ነግር ግን በአንድ አጋጣሚ ወሎ ላይ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የምርምር ስራ ሲያካሂድ ባቲ ከተማ አጠገብ አንድ ቀን አብሬው ውየ ነበር፡፡ ሰዎችን ሲያነጋግር የጥያቄውን አሰነዛዘርና በጥሞና ማዳመጡን መገንዘብ ችያለሁ፡፡  የማስተርስ ተማሪ በነበርኩ ጊዜ ከÝሮፌሰር ታደሰ ጋር በ1994 .ም. ከሌሎች ዘጠኝ ተማሪዎች ጋር ወደ ሰሜን ሸዋ ለሦስት ሳምንታት የመስክ ስራ አብረን ሄደን ነበር፡፡ ቡልጋን፤ በከፊል መርሀቤቴን፤መንዝን፤ ሸንኮራንና፤ ምንጃርን ጎበኘን፡፡ የማይረሳኝ ጉብኝት ነበር፡፡ በምግብ ሰአት ሁላችንም፤ እርሳቸውን ጨምሮ፤ በአንድ ተካፍለን እንበላለን፡፡ ሰዎችን እንዴት እንደምናነጋግር፤ መረጃ እንዴት መሰብሰብ እንዳለብን፤ እንዴት እንደምናቀነባብር በደንብ የተማርንበት ነበር፡፡ ማታ ማታ የቀኑን ስራችንን እንገመግማለን፤ የሚቀጥለውን ቀን ስራ እናቅዳለን፡፤ እንዲሁም በጠዋት ተነስተን ጉዞአችንን እነቀጥላለን፡፡
       በጉዞ ላይ ምንጊዜም መምህራችን ከማለዳ ጅምረው እያጫወቱን እን¹ዘለን፡፡ በማንኛውም ጉዳይ ላይ በርከት ያሉ ቀልዶችና ወጣቶች የሚያወሩትን ወሬ ሁሉ እያወጉ ያስቁናል፡፡ ከአራት ሰአት በ|ላ “እንግዲህ የኔን ጨረስኩ፤ በሉ አሁን ደግሞ የናንተን አምጡ” ይሉንና ከዚያ በ|ላ ተራቸውን አድማጭ ይሆናሉ፡፡ እኛም ምንም ሳንፈራ ማንኛውንም ነገር እናወራለን፡፡ ሀብታይ ዘራይ የተባለ ወፈር ያለ ተማሪ ከ|ላቸው ይቀመጥ ነበርና አጫጭሮቹን አላሳይ ብሎ ሲከልላቸው ጊዜ “መገዘዝ ዘወር በል አጫጭሮቹን ልይበት” እያሉ ያስቁን ነበር፡፡ መገዘዝ ቡልጋ ውስጥ የሚገኝ ግዙፍ ተራራ ነው፡፡ ከወራት በ|ላ የማጠቃለያ ስራየን ጽፌ ስሰጣቸው በአጋጣሚ ቡልጋን መÍፍ ረሳሁት፡፡ ቡልጋ ደግሞ የርሳቸው አገር ነው፡፡ ቁም ነገር መርሳቴን ለመግለጽ ‘poor Bulga ምስኪኗ ቡልጋ’ ብለው ስህተቴን በቀልድ አዋዝተው አስገረሙኝ፡፡ 
        ከቀን ጉዞአችን በ|ላ ማታ ወደ ማደሪያችን ስንመለስ ሁልጊዜም ቅድሚያ የሚሰጡት ስልክ ደውለው ባለቤታቸውን ማነጋግር ነበር፡፡ ይህ ምንም ቢሆን የማይቀር፤ስልክ አይሰራም ካልተባለ፤ በቀር የምይዘነጋ የእለቱ ስራ ነበር፡፡ እውነትም Ýሮፌሰር ሽፈራውእንዳለው “ምሳሌ ሊሆኑ የሚገባቸው አፍቃሪ ባል” ነበሩ፡፡ በ1990 .ም. ለ13ኛው የኢትዮጵያ ጥናት ጉበኤ ወደ ቶክዮ፤ ጃፓን፤ በሄድንበት ጊዜ Ýሮፌሰር ባህሩ የጋበዘንን ውስኪ አንድ ምሽት እየጠጣን እንዴት የትዳር ¹ደኛችሁን እንደተዋወቃችሁ አውሩ ተባለ፡፡ መጀመሪያ በእድሜ የምናንሰው አወራንና ቀጥሎ ደግሞ ትላልቆቹ አጫወቱን፡፡ በመጨረሻም Ýሮፌሰር ታደሰ ከባለቤታቸው ጋር እንዴት እንደተዋወቁ ሲያወሩን ፍቅር እስከ መቃብርን የሚወዳደር የፍቅር ጥምረት፤ እውነተኛና አስገራሚ ታሪክ ነበር፡፡ Ýሮፌሰር ታደሰና ወ/ሮ አልማዝ ፍቅራቸው እንደÐናና እንደ ደመቀ አብረው በፍቅር ኖረው አንድ አመት ባልሞላ የጊዜ ርቀት በሞት ተከታትለው አረፉ፡፡
        ዶ/ር ተካልኝ እንደሚያጫውተን Ýሮፌሰር ታደሰ ተማሪዎቻቸውን ይዘው ወደ መስክ የምርምር ስራ በየአመቱ ሲወጡ በጣም የሚያቀርቡአቸው ተማሪዎች አሉአቸው፡፡ ቦርሳቸውን የሚይዝላቸው፡፡ እነዚህን ተማሪዎች ‘ዳዊት’ የሚል ስም ተማሪዎቹ ያወጡላቸዋል፡፡ የመንፈሳዊ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የመምህራቸውን ዳዊት ተሸክመው እንደሚከተሉ ሁሉ፡፡ ታዲያ ዶ/ር ተካልኝ አንድ ጊዜ ይህንን ለÝሮፌሰር ታደሰ ሲያጫውታቸው “ለዚህ ነበር እንዴ ጉሉማን ዳዊት ትሉት የነበር፤ እኔ እኮ እስካሁን አላወቅሁም ነበር” ብለው ሳቁና አሳቁን፡፡ ዶ/ር ጉልማ አሁን የሚኖረው አሜሪካን አገር ነው፡፡ እኔም በወቅቱ ዳዊት መባሌን አልሰማሁም እንጅ የአመቱ ዳዊት ነበርኩ ማለት ነው፡፡
       Ýሮፌሰር ታደሰና Ýሮፌሰር ክራሚ ብዛት ያላቸውን የቅድመ ምረቃ፤ ማስተሬትና ዶክተሬት ተማሪዎች አማክረው አስመርቀዋል፡፡ ከድሮ ተማሪዎቻቸውም ጋር እንደ ስራ ባልደረባና እንደ ¹ደኛ ሁነው ብዙ ዘመናትን አሳልፈዋል፡፡ ተማሪዎቻቸውም እነዚህን የእወቀት አባቶቻቸውን አክብረው ኖረዋል፡፡ ሁለቱም ለንደን የዶክተሬት ድግሪ ተማሪ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ በፍቅርና በመግባባት አብረው ሰርተዋል፤ ኖረዋልም፡፡ በሞትም ቢሆን ሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ በሞት ተከታትለው አልፈዋል፡፡ Ýሮፌሰር ታደሰ በግንቦት እንዲሁም Ýሮፌሰር ክራሜ በነሀሴ 2005 .ም.፡፡ ሞት አይቀሬ ነውና ሞት አለያይቶአቸዋል፡፡ እግዚአብሄር ነፍሳቸውን በአብርሀምና በያ˜ቆብ ቦታ እንዲያሳርፍ እንመኛለን፡፡ ለቤተሰባቸውም መÒናናትን ይስጣቸው፡፡  

      ሰኞ፤ ጥቅምት 18/2006 .ም.

      ኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ሲዘመር ከሚያነሣቸው ነጥቦች መካከል ‹የዜግነት ክብር› የሚለው የተለየ ስሜት ይሰጠኛል፡፡ ለአንዲት ሀገር ሰው ትልቁ ዋጋው ‹የዜግነት ክብር› ነው፡፡ ሀገር አለኝ ብሎ ማሰብ፤ የሚያስብልኝ፣ የሚጮህልኝ መንግሥት አለኝ ብሎ ማመን፤ የእኔ ጉዳይ ጉዳዩ የሆነ አካል አለ ብሎ መመካት፡፡

      እንዲህ እንደ ሰሞኑ ያለ፣ በሳዑዲ እየተፈጸመ እንዳለው ነገር ያለ ስናይና ስንሰማ ደግሞ ‹የዜግነት ክብር› መዝሙር ብቻ ይሆንብናል፡፡ ‹ኢትዮጵያዊ ማለት› ብለን ልንተረጉም ይቸግረናል፡፡ ማንም  የአራዊት ጠባይ ያለው ሁሉ ተነሥቶ መንገድ ላይ ደሙን የሚያፈሰው፣ እግሩን የሚቆርጠው፣ የሚደበድበውና በፈለገበት ቦታ የሚያሥረው ከሆነ፣ ይህማ እንኳን የዜግነት ክብር የስደተኛነት ክብርም አላገኘም ማለት ነው፡፡ ሀገር አልባ ጂፕሲዎች ከሚደርስባቸው ግፍ በላይ ባለሀገሩ ኢትዮጵያዊ ከደረሰበትማ ‹የዜግነት ክብር› የቱ ላይ ነው፡፡ ደግሞስ በአንድ ኢትዮጵያዊ ላይ ሰው መሆኑን የሚያጠራጥር ከዚህ በላይ ምን ሊደርስበት ይችላል፡፡

      ይህ ነገር ሁለት ነገሮችን እንድናስብ ማድረግ አለበት፡፡

      1.   የመንግሥት አካላት በየሀገሩ ያሉትን ዜጎቻችንን ለማወቅ፣ ለመከታተልና መብታቸውን ለማስከበር ያላቸውን ብቃት

      2.እንዲህ ዓይነት ነገር በሌላ ጊዜና በሌላ ሀገር እንዳይደገም ልናደርገው የሚገባንን ዘላቂ መፍትሔ

      የዜግነት ክብር የሚኖረው አንድ ዜጋ የትም ቦታ ቢኖር የዜግነት መብቱ እንዲከበርለት፣ በዜግነቱ እንዲኮራና የዜግነቱንም ግዴታ እንዲወጣ ሲደረግ ነው፡፡

      ይህ የዜግነት ክብር እንዲጠበቅ መንግሥት፣ የዲፕሎማቲክ ሚሽኖች፣ የዲያስጶራ ማኅበረሰቦችና ጠቅላላው ሕዝብ ከዚህ ጊዜ የተሻለ የመንቂያ ጊዜ አያገኙም፡፡ ይህንን ለማሰብ እስከዛሬ የፈሰሰው ደም በቂ ካልሆን፤ የሚያስፈልገን የስንት ሰው ደም ይሆን?

      click here for pdf

      በይምርሐነ ክርስቶስ ጣራ ላይ የሚገኘው የዳዊት ኮከብ
      ባለፈው ሳምንት ተስፋዬ ገብረ አብ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ያነሣቸውን ነጥቦች ማየት ጀምረን ‹የሦስቱን ተክለ ሃይማኖቶች› ጉዳይ ለዛሬ አቆይተነው ነበር፡፡ እንቀጥል፡፡

      1)        የሰባተኛው መክዘ ተክለ ሃይማኖት

      ተስፋዬ የጠቀሳቸው የሰባተኛው መክዘ ተክለ ሃይማኖት የሉም፡፡ እስካሁንም እንደርሱ ፈጠራቸውን የሚናገሩ እንጂ ማስረጃ ያመጡ አልተገኙም፡፡ ይህንን ነገር መጀመሪያ ያነሣው የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ገድለ ተክለ ሃይማኖትም ስለ ጽላልሽ (ኢቲሳ) ተክለ ሃይማኖት እንጂ ስለ ሰባተኛው መክዘ ሌላ ተክለ ሃይማኖት አይናገርም፡፡ ገድለ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ልዩ ልዩ ቅጅዎች ቢገኙም ሁሉም ግን በተወለዱበት ቦታ፣ በተወለዱበት ዘመን፣ በወላጆቻቸው ስም፣ በሠሯቸው ሥራዎችና በገዳማቸው ላይ የሚተርኩት ታሪክ ተመሳሳይ ነው(Encyclopedia Aethiopica, Vol., IV,.P.833) በአንድ ወቅት ታላቁን የታሪክና የኢትዮጵያ ጥንታውያን መዛግብት ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን ስለዚህ ጉዳይ ስጠይቃቸው ‹አለኝ ያለ ማስረጃውን ያምጣ፣ የለም የምንለው ፈልገን ልናመጣ አንገደድም›› እንዳሉት አለን የሚሉት እስኪያመጡ ድረስ የምናውቀውን ይዘን እንቀጥላለን፡፡

      2) መራ ተክለ ሃይማኖት የሚባል ንጉሥ ነበረ፡፡ እንደ ደብረ ሊባኖስ ዘሺምዛና(ኤርትራ) እና ደብረ ሐይቅ መዛግብት ከሆነ መራ ተክለ ሃይማኖት የዛግዌ ሥርወ መንግሥት መሥራች ንጉሥ እንጂ ‹ቄስ› አልነበረም፡፡ የዛግዌን ዘመን በተመለከተ የተጻፉ የዛግዌ ቅዱሳን ገድሎች(ፔሩሾ የጻፈውን የገድለ ላሊበላ መቅድም መመልከት) ይህንን አይነግሩንም፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የዛግዌን ታሪክ ያጠኑት ሊቃውንት(ለምሳሌ E. A. Wallis Budge, A History of Ethiopia, London, 1928; Sergew Hable Sellassie, Ancient and Medieval Ethiopian History) መራ ተክለ ሃይማኖት ቄስ ነበረ አይሉንም፡፡ የላስታ ትውፊትም ይህን አይናገርም፡፡ በላስታ አድባራትና ገዳማት የሚሳሉት ቅዱሳን አራቱ ነገሥታት ናቸው (ቅዱስ ላሊበላ፣ ቅዱስ ሐርቤ(ገብረ ማርያም)፣ ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስና ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ)፡፡ ከእነዚህም ክህነትና ንግሥናን እንደያዘ የሚነገረው ይምርሐነ ክርስቶስ ነው፡፡ ተስፋዬ እንዲሆን የሚፈልገውን ብቻ ነው የነገረን፡፡ 

      ስለዚህም በገድለ ተክለ ሃይማኖት የሦስት ሰዎች ገድል ተቀላቅሏል የሚለን ማስረጃ አልባ ሕልም ነው፡፡ 

      ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተጻፈው በገድላቸው ብቻ አይደለም፡፡ በብዙ ጥንታውያን መዛግብትም ጭምር እንጂ፡፡ በገድለ አቡነ ኢየሱስ ሞአ(ወሎ)፣ በገድለ አቡነ ፊልጶስ፣ በገድለ አቡነ አኖሬዎስ(ባሌ)፣ በገድለ አቡነ እንድርያስ(ደቡብ ጎንደር) በገድለ አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ቢዘን (ኤርትራ፣ እንዲያውም በ ደብረ ቢዘኑ(ኤርትራ) ገድለ አቡነ ፊልጶስ ወአቡነ ዮሐንስ ላይ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት አልፎ የእርሳቸውን ደቀ መዛሙርት ዝርዝር በሚገባ ይነግረናል፡፡ C. Conti Rossini, Gadla Filipos e il Gadla Yohannes,1901, P.156)፣ በገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ(ሰሜን ሸዋ)፣ በገድለ አቡነ ቀውስጦስ፣ በገድለ አቡነ ዕንባቆም(ወለጋና ምዕራብ ሸዋ)፣ በገድለ አቡነ ተክለ ሐዋርያት(ምዕራብ ሸዋ)፣ በገድለ አቡነ ተክለ አልፋ(ምሥራቅ ጎጃም)፣ በገድለ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ(ትግራይ)፣ በገድለ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ(ኤርትራ)፣ በገድለ አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ(ምዕራብ ሐረርጌ)፣ ተጽፎ ይገኛል፡፡ እነዚህ በተለያዩ ዘመናት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተጻፉ ገድሎች በደብረ ሊባኖስ በ12ኛው መክዘ መጨረሻና በ13ኛው መክዘ መጀመሪያ ላይ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚባሉ አባት ተነሥተው እንደነበረ ታሪካቸውን በአጭርም ሆነ በስፋት ይነግሩናል፡፡ ከኢትዮጵያውያንም ውጭ በ16ና17ኛው መክዘ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት እነ ኢማኑኤል አልሜዳና ፓድሮ ፓኤዝ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ ያገኙትን ነገር መነሻ ስለ ደብረ አስቦው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጽፈዋል፡፡ ሌላ ተክለ ሃይማኖት ስለመኖሩ ግን ያነሡት ነገር የለም፡፡

      በርግጥ አልሜዳ ተክለ ሃይማኖትን በሰባተኛው ወይም በስምንተኛው መክዘ የተነሡ ናቸው ብሎ ገምቷል፡፡ ወደዚህ ግምት የወሰደው የኢትዮጵያውያንን ገድላት አጻጻፍ ባለቁ ነበር፡፡ ኮንቲ ሮሲኒ ‹‹ወደ ኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት ይበልጥ ራሴን ባስገባሁ ቁጥር ሀገራዊውን ትውፊት ማወቅ እንዳለብኝ ይበልጥ እየተረዳሁ መጥቻለሁ፡፡ ይህንን ሀገራዊ ትውፊት፣ ከሕዝቦችን ንቅናቄ ታሪክና ከተከታታይ መሪዎቹ ታሪክ ጋር(ምንም እንኳን አንዳንዴ አፈ ታሪክም ቢሆን) እያወቅን በመጣን ቁጥር ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ርግጠኛ የሆነ ግንዛቤ ይኖረናል›› እንዳለው(C. Conti Rossini, “Note di agiografia etiopica (Abiya- Egzi, Arkaledes e Gabra Iyesus),” Rassegna di studi orientali, 17(1938), 409-10. ) የኢትዮጵያን ባህል ና ትውፊት ካላወቁ የሚፈጠረውን ስሕተት ነው አልሜዳ የፈጠረው፡፡ ለምሳሌ አልሜዳ እንደ አንድ ማሳያ ያነሣው ‹በገድለ ተክለ ሃይማኖት ውስጥ ስለ ሙስሊሞች አልተገለጠም› የሚል ነው፡፡ የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ገድሎች ግን ከክርስትና ውጭ ያሉትን ሕዝቦች ‹ተንባላት› እያሉ ነው የሚጠሯቸው፡፡ ሙስሊም ወይም እስላም የሚለውን ስም በሚገባ የምናገኘው የክርስቲያን ሙስሊም ግንኙነት እየሻከረ በመጣባቸው የመካከለኛው ዘመን የመጨረሻዎቹ ዓመታትና ከግራኝ አሕመድ ጦርነት በኋላ ነው፡፡ በገድለ አኖሬዎስ፣ በገድለ አቡነ አሮን፣ በገድለ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልና በገድለ አቡነ ፊልጶስም በተመሳሳይ ሁኔታ ነው የሚገኘው፡፡

      አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ከፖለቲካ ጋር የማያያዝ ነገር በተስፋዬ አልተጀመረም፡፡ ሌሎች አካላትም ሲያራምዱት የኖሩና የሚራምዱትም ነገር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ያልተጠኑ ሦስት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው የሰሎሞናዊ መንግሥት ምለሳ (Restoration) የሚባለው ነገር፡፡ ሁለተኛው በዚህ ምለሳ ላይ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ነበራቸው የሚባለው ሚና እና የታሪኩ ምጮች ናቸው፡፡

      የንጉሥ ሐርቤ የዳዊት ኮከብ ያለበት ማኅተም

      እንደ እውነቱ ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ በአኩስም ዘመን የነበሩ ነገሥታት ራሳቸውን ሰሎሞናውያን ብለው የጠሩበት መረጃ የለንም፡፡ ለኢትዮጵያ ነገሥታት ግን ራሳቸውን ከኢየሩሳሌምና ከቅድስት ሀገር ጋር ማያያዝ የተለመደ ነው፡፡ በዚህ ረገድም የዛግዌ ነገሥታት ሰሎሞናውያን የማይሆኑበት ምክንያትም የለም፡፡ እንዲያውም ለሰሎሞናዊነቱ ከኋለኞቹ ነገሥታት ይልቅ የዛግዌ ነገሥታት ይቀርባሉ፡፡በውቅር ቤተ ክርስቲያኖቻቸውም ሆነ በማኅተሞቻቸው ላይ የዳዊትን ኮከብ በብዛት እናየዋለን፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድም የዛግዌ ነገሥታት ይበልጣሉ፡፡ ቅዱስ ላሊበላም የሮሐን አብያተ ክርስቲያናት ሲያንጽ ኢየሩሳሌምን እያስታወሰ ነው፡፡ በኋላ ዘመን ‹ሰሎሞናውያን› ከተባት የይኩኖ አምላክ ዘሮች ነገሥታት ወገን እንድም ንጉሥ ኢየሩሳሌም ሄደ ተብሎ አልተጻፈለትም፣ አልተነገረለትምም፡፡ የዛግዌ ነገሥታትን ግን ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ የሚተካከላቸው የለም፡፡

      የአኩስምን ነገሥታት (በተለይ ዐፄ ካሌብና ዐፄ ገብረ መስቀል በወሎ አካባቢ አያሌ አብያተ ክርስቲያናትን ተክለዋል፡፡ የዛግዌ ነገሥታትም (በደብረ ሊባኖስ ዘሺምዛና ወንጌል እንደ ተገለጠው) ለኤርትራና ትግራይ ገዳማት ርስት ሰጥተዋል፡፡ የሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት መላሽ የሚባለው ይኩኖ አምላክም ቢሆን በእናቱ የቡግና ተወላጅ ነው፡፡ ውትድርና ተቀጥሮ የኖረውም ቡግና ነው፡፡ የተማረውም ወሎ ሐይቅ እስጢፋኖስ ነው፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞአ ትውልዳቸው ቡግና ስለሆነ ነው ይኩኖ አምላክ ወደ ሐይቅ ለትምህርት የሄደው፡፡ እርሱ ሲነግሥም መጀመሪያ ያሳነጸው የወሎዋን ገነተ ማርያምን ነው፡፡ አጽሙም የሚገኘው በወሎዋ አትሮንሰ ማርያም ነው፡፡ ይኩኖ አምላክ በሸዋ ውስጥ ስሙ እንጂ ቅርሱ ያለ አይመስልም፡፡

      ይኩኖ አምላክ ወደ ሸዋ የወረደው እርሱ ሸዬ ስለሆነ አይመስልም፡፡ የዛግዌ ነገሥታት የበረታ ኃይል ከሚገኝበት ከወሎ አካባቢ ለመሸሽና የደቡቡን ኃይል ለማሰባሰብ እንጂ፡፡ ኮንቲ ሮሲኒ ከኤርትራ አግኝቶ ባሳተመው እንድ ጥንታዊ የብራና ጽሑፍ ላይ  ‹‹(የይኩኖ አምላክ ሠራዊት) ሰባቱ ጉደም ናቸው፡፡ እነርሱም ወግዳ – መለዛይ፣ ዲንቢ – ዳባራይ፣ ሙገር – እንደ ዛቢ፣ ወጅ – እነጋሪ፣ ወረብ – እነካፌ፣ ጽላላሽ እነ ጋፌ እና ሙዋይ – አውዣዣይ ናቸው፡፡ የእነርሱም አለቃ መለዛይ ከንጉሡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ ተዋግቶም ጠላቶቹን ድል ነሣ›› ይላል (Taddesse Tamrat, Ethnic Interaction and Integration In Ethiopian History: The case of The Gafat, JES, Vol. XXI,1988, P. 125)

      ይኩኖ አምላክ የዛግዌ ነገሥታትን ሊያሸንፍ የቻለው በዚያ ዘመን በጥበበ ዕድ አንድነት በፈጠሩት(ሰባት ጉዳም) ጋፋቶች ርዳታ ነው፡፡ ምንጊዜም የመሣሪያ ኃይል ያለው ያሸንፋልና፡፡ ይኩኖ አምላክ ወደ ሸዋ ባደረገው መስፋፋት ወደ ክርስትና ተመልሶ ከደጋው ሸዋ ክፍል ጋር የነበረውን ጠላትነት ያጠፋውን የዳሞትን መንግሥት ኢኮኖሚያዊ ዐቅም ተጠቅሞበታል፡፡ ልክ በኋላ ዘመን ዐፄ ምኒሊክ የደቡቡን ኃይልና ዐቅም በመጠቀም ገንነው እንደወጡት ማለት ነው፡፡ ይኩኖ አምላክ ወደ ሸዋ በመምጣት ኃይሉን በማደራጀቱ ሸዬ ሆኖ ቀረ፡፡ ልክ በኋላ የሸዋ ነገሥታት ወደ ጎንደር ሄደው ጎንደሬ ሆነው እንደቀሩት ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ‹ሰሎሞናዊ› የሚባል የተለየ መንግሥት አልነበረንም፡፡ ነገሥታቶቻችን ሁሉ ራሳቸውን ከኢየሩሳሌም ጋር ያያይዙ ነበር፡፡ ዐፄ ካሌብም ከናግራን ዘመቻ መልስ ዘውዳቸውን ኢየሩሳሌም ነው የላኩት፡፡ የዐፄ ገብረ መስቀል ልጅ ሙሴም መጀመሪያ ወደ ኢየሩሳሌም፣ በኋላም ወደ ሶርያ በመጓዝ በዚያ ገመንነው ገዳም መሥርተዋል፡፡ ገዳማቸውም ‹ሙሴ አል ሐበሽ ገዳም› ይባላል፡፡

      የዛግዌ ነገሥታትም ሰሎሞናውያን የማይሆኑበት ምክንያት የላቸውም፡፡ በገድሎቻቸው ላይ ኢየሩሳሌምን አብዝተው የሚያነሡ፣ ማኅተሞቻቸው ሁሉ የዳዊት ኮከብ የሆኑ፣ በውቅር ቤተ ክርስቲያኖቻቸው የዳዊትን ኮከብ የቀረጹ የዛግዌ ነገሥታት እንዴት ሰሎሞናውያን አይሆኑም፡፡

      የኢትዮጵያዊው የቅዱስ ሙሴ(የዐፄ ገብረ መስቀል ልጅ) ገዳም በሶርያ
      በመሆኑም የጠፋና የተመለሰ የሰሎሞን መንግሥት አለ ብሎ ለመናገር ያስቸግራል፡፡ ሥርወ መንግሥታቱንም ‹የአኩስም፣ የላስታ፣ የሸዋ፣ የጎንደርና የሸዋ 2ኛ› ብሎ መክፈሉ የተሻለ ነው፡፡

      ሲባል እንደኖረው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲሦ መንግሥት ቢቀበሉ ኖሮ በገድለ አቡነ አኖሬዎስና በገድለ አቡነ ፊልጶስ ላይ እንደምናነበው እነዚህ ሁለት ቅዱሳን ወደ ደብረ አስቦ(የአሁኑ ደብረ ሊባኖስ) ሲመጡ ግንባር በምታክል መሬት ላይ አተር ዘርተው ሲሰበስቡ ባላገኟቸው ነበር፡፡ ደብረ ሊባኖስ ይበልጥ እየታወቀና በማዕከላዊ መንግሥት ቦታ እያገኘ የሄደው ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በኋላ ነው(ምናልባት ኤርትራ ይገኝ ከነበረው ከደብረ ሊባኖስ ዘሺምዛና ጋር ያለው ግንኙነት እየተዳከመ ሲመጣ)፡፡ ደብረ ሊባኖስ የሚለውን ስም ያገኘውም ያኔ ነው፡፡(Les chroniques de Zara Ya’eqob.,P. 91) አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከነገሥታቱ ጋር የተለየ ቀረቤታ ቢኖራቸው ኖሮ በዓለ ዕረፍታቸው ነገሥታቱና መኳንንቱ በተገኙ ነበር፡፡ ነገሥታቱ በደብረ ሊባኖስ መገኘት የጀመሩት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ካረፉ ከ100 ዓመታት ቆይተው ከዐፄ ይስሐቅ ዘመን (1406-1421 ዓም) በኋላ ነው፡፡ እንዲያውም የደብረ ሊባኖስ አባቶች በነበራቸው ጽኑዕ አቋም የተነሣ ከነገሥታቱ ጋር ባለ መስማማት ነው የሚታወቁት፡፡ 3ኛውን እጨጌ አቡነ ፊልጶስን፣ አሥራ አንዱን ንቡራነ ዕድና እጨጌ እንድርያስን ማስታወሱ ይበቃል፡፡

      ከላስታ ወደ ሸዋ የመንግሥት ዝውውር ሲደረግ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሐይቅ እስጢፋኖስ በትምህርት ላይ ነበሩ(የሚጣቅ ዐማኑኤሉ ገድለ ተክለ ሃይማትና ገድለ ኢየሱስ ሞአ በዝርዝር እንደሚተርከው)፡፡ በዚህ የሥልጣን ዝውውር ላይ ይበልጥ ተሳታፊ የነበሩት አቡነ ኢየሱስ ሞአ ዘሐይቅ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ሐይቅ የዐቃቤ ሰዓትነት ሥልጣን ነበረው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲሦ መንግሥት አግኝተዋል የሚለው ትረካ መንግሥት ወደ ጎንደር ከተቀየረ በኋላ(17ኛው መክዘ) በተጻፈው በብዕለ ነገሥት ላይ የተገለጠ ነው፡፡ ብዕለ ነገሥት የነገሥታትን ሀብት ለማሳየት የተጻፈ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ነው ከይኩኖ አምላክ ጋር ቃል ኪዳን ገብተዋል ተብሎ የተጻፈው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ መንግሥት ወደ ጎንደር ሲዞር ደብረ ሊባኖስ ከማዕከላዊው መንግሥት ራቀ፡፡ በአካባቢውም ክርስቲያን ባልሆኑ ሕዝቦች ተከበበ፡፡ የጎንደር ነገሥታት ገዳሙን እንዳይረሱትም በብዕለ ነገሥት የአባታቸውን ይኩኖ አምላክን ቃል ኪዳን እንዲያስታውሱ የሚያደርግ ነገር ተጻፈ፡፡

      እናም ተስፋዬም ሆነ ሌሎች እንደሚሉት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከቅድስና ሥራ በቀር የገቡበት ፖለቲካ የለም፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ፈጽመው ወደ ደብረ አስቦ ሲገቡ ይኩኖ አምላክ በመንበሩ ላይ ነበር፡፡ ነገር ግን የጠበቃቸው ዘንዶ ይመለክበት የነበረ ዋሻ እንጂ ከሲሦ መንግሥት የተገኘ ግብር አልነበረም፡፡ ያንን ዋሻም ያገኙት ከጣዖት አምላኪዎች አስለቅቀው ነው፡፡ 28 ዓመት በደብረ አስቦ ሲቀመጡም የጎበኛቸው ንጉሥ አልነበረም፡፡ ደቀ መዝሙሮቻቸውም ከዝንጀሮ ጋር እየተሻሙ እህል ዘርተው ከማብቀል ውጭ የተለየ ርስት አልነበራቸውም፡፡ ደብረ ሊባኖስ ሲተከልም የአካባቢውን ሕዝቦች በማሳመን እንጂ በነገሥታቱ ድጋፍ አልነበረውም፡፡ ከይኩኖ አምላክ በኋላ የመጣው ያግብዐ ጽዮንና አምስቱ የያግብዐ ጽን ልጆች ለአቡነ ተክለ ሃይማትም ሆነ ለደብረ አስቦ ያደረጉት ነገር አልነበረም፡፡ ዐፄ ዐምደ ጽዮንና ዐፄ ሰይፈ አርእድም ከደብረ ሊባኖስ እጨጌዎች ጋር በሰላም አልኖሩም፡፡

      አቡነ ፊልጶስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሲመጣ የአካባቢው ሰዎች ‹የገዳሙ መነኮሳት ሰው ይበላሉ›› ብለው ነው የነገሩት፡፡ ይህም ደብረ አስቦ በዚያ ዘመን የመነኮሳት ማኅደር እንጂ እንኳን ነገሥታቱ የአካባቢው ሰዎችም በቅጡ እንዳልቀረቡት ያሳየናል፡፡ የደብረ ሊባኖስ የመጀመሪያዎቹ አባቶችም በራሳቸው ጥረት በደብረ አስቦ ዋሻ ውስጥ ገዳም የተከሉ እንጂ በነገሥታቱ ድጋፍ ሲሦ መሬት የያዙ እንዳልነበሩ ያሳየናል፡፡ 

      ከዐሥረኛው መክዘ ጀምሮ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በሰሜኑና በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ምክንያት የነበረው ግንኙነት ተቋርጦ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት እንደሚገልጡትም የሰዎች ፍልሰት ከሰሜኑ የሀራችን ክፍል አሁን ሸዋ ወደሚባለው አካባቢ በየተወሰነ መጠን ብቻ ይከናወን ነበር፡፡ ይህንን ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ ለሆነ ዘመን የተለያየ ሕዝብ እንደገና ያዋሐዱት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዳሞትን ከሸዋ ጋር ካገናኙ በኋላ ወደ ወሎ በመሄድ ሐይቅ ቆዩ፤ ቀጥለውም ወደ ትግራይ በመጓዝ ደብረ ዳሞ ገቡ፡፡ ለሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የምንኩስና ሕይወት ማንሠራራት አንዱ ምክንያት የሆኑትን አቡነ መድኃኒነ እግዚእን አመነኮሱ፡፡ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ደግሞ አምስቱን ከዋክብት(አቡነ አሮን ዘክቱር፣ አቡነ መርቆሬዎስ ዘዶባ፣ አቡነ ዘካርያስ ዘኬፋ፣ አቡነ ገብረ ክርስቶስ ዘዳኅና፣ አቡነ ዳንኤል ዘጸዐዳ)ና ሰባቱን ከዋክብት በማመንኮስ(R. Basset, Etudes sur I historie d Ethiopie,.p 10) የሰሜኑን ገዳማዊ ሕይወት እንደገና ነፍስ ዘርተውበታል፡፡ በዚህም ምክንያት የሰሜኖቹ ወደ ደቡብ በመምጣት፣ የደቡቦችም ወደ ሰሜን በመሄድ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲያንሠራራ አድርገውታል፡፡

      ተስፋዬም ሆነ መሰሎቹ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ላይ የሚዘምቱት የእምነትም ሆነ የታሪክ ክርክር ስላላቸው አይደለም፡፡ ሀገሪቱ የቆመችባቸውን ተራዳዎች የመናድና እሴት አልባ የማድረግ ተልዕኮ ስላላቸው እንጂ፡፡ ይህ ተልዕኮ ደግሞ በዚህች በብዙ ቅዱሳን ጸሎት በታጠረች ሀገር ላይ ፈጽሞ የሚሳካ አይደለም፡፡ የሌለን ነገር የሚፈልግ አያገኝምና፡፡  

      ©ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው


      ማስተዋሻ

      አቡነ ተክለ ሃይማኖትን የተመለከተ አንድ መጽሐፍ በማዘጋጀት ላይ ነኝ፡፡ ጻድቁ በጸሎታቸው ቢረዱኝ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ይወጣ ይሆናል፡፡ እናንተም ጸልዩበት፡፡


      ብዙዎቻችሁ ከኢትዮጵያ ውጭ ምትኖሩ አንባብያን አዲሱን መጽሐፍ ባላችሁበት ለማግኘት ጠይቃችኋል፡፡ ያለው አማራጭ በ [email protected] ኢሜይል ላኩልን፡፡ በኢሜይላችሁ ያላችሁበትን አድራሻ አብራችሁ ላኩልን፡፡ የመላኪያውን ዋጋ ጠይቀን እንነግራችኋን፡፡ ከዚያም የመጽሐፉንና የመላኪያውን ዋጋ በባንክ በኩል ከላካችሁ መጽሐፉን በነጠላም ሆነ በብዛት እንልክላችኋለን፡፡ አስቀድመን በመላክም ከሀገር ቤቱ አንባቢ እኩል እንድታነቡ እናደርጋለን፡፡
      መልካም ንባብ፡፡ 

      click here for pdf
      በቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀትና በቤተ ክርስቲያን ትምህርት የበሰሉ፣
      ዘረኝነትንና ጠባብነትን እስከ መጨረሻው የተዋጉ፣
      የፍቅር መሥፈርታቸው ሰው መሆን ብቻ የሆነ፣
      ቤተ ክርስቲያን የቤተ መንግሥቱ ጥገኛና ተቀጽላ እንዳትሆን በብርቱ የተጋደሉ፣
      ለእምነታቸውና ለአቋማቸው ሲሉ ከነገሥታቱ ጋር ፊት ለፊት የተገዳደሩ፣
      ከእሳት፣ ከግርፋት፣ ከአራዊት፣ ከዘንዶ፣ ከግዞት፣ ከስደት ጋር ተጋፍጠው እምነታቸውን ያስከበሩ፣
      ነገሥታቱ በተሳሳተ መንገድ ሲሄዱ እንደ ዮሐንስ መጥምቅ ያለ ፍርሃት የገሰጹ፣
      በመላዋ ኢትዮጵያ ለስብከተ ወንጌል የተሠማሩ፣
      ቤተ መንግሥትን ለሥልጣንና ለጥቅም ሲሉ ከተጠጉ ሥጋውያን ካህናት ጋር በእምነትና በጽናት ያደረጉት ትግል፤
      ምንኩስና መንኖ ጥሪት(ሀብት ንብረትን መተው) ነው ብለው የተሰጣቸውን የማባበያ ገንዘብ፣ ወርቅና ርስት ላለመቀበልና       ሃይማኖታዊ ነጻነታቸውን ለመጠበቅ ያደረጉት ተጋድሎ፣

      የአራት የእምነት ኃያላን አበው

                                   (አቡነ በጸሎተ ሚካኤል፣ አቡነ ፊልጶስ፣ አቡነ አሮን፣ አቡነ አኖሬዎስ) ታሪክ
      ከበቂ ታሪካዊ ማብራሪያ፣ የፎቶ ግራፍና የሥዕል ማስረጃዎች፣ የቦታና የሰዎች ስሞች መዘርዝሮች ጋር፣

      የመካከለኛው ዘመን ኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ባሕላዊ ታሪክ በሰፊው የተዳሰሰበት፣
              ጠፍተው የነበሩ ቦታዎችን በአሠሣ በመፈለግ፣ የጠፉ መረጃዎችን ከየገዳማቱና አድባራቱ በማፈላለግ፣ በቀደምት ሊቃውንት            የተጻፉትን በማጣቀስ፣ የተዘጋጀ የጥናት መጽሐፍ፣

      በመጽሐፉ ውስጥ

      • የአቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ የአቡነ ኤዎስጣቴዎስ፣ የአቡነ ዜና ማርቆስ፣ የአቡነ ኢየሱስ ሞአ፣ የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ፣
      • በአሥራ ሁለት አህጉረ ስብከት ለስብከተ ወንጌል የተሠማሩት የአሥራ ሁለቱ ንቡራነ ዕድ ታሪክና የሥምሪት ሀገረ ስብከት            በስፋት ቀርቧል፤
      • በመካከለኛው ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሰፊ ቦታ ያላቸው ግብጻውያን ጳጳሳት – የአቡነ ዮሐንስ፣           የአቡነ ያዕቆብ፣ የአቡነ ሰላማ መተርጉምና የአቡነ በርተሎሜዎስ ታሪክ ቀርቧል፤
      • በደቡብ ኢትዮጵያና በኦሮሚያ ጥንት የነበሩትን የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴዎች ያሳያል፤
      • አቡነ ፊልጶስ ዛሬ ስላለችው ቤተ ክርስቲያን ከ600 ዓመታት በፊት የተነበየውን ትንቢት ያዩበታል

      ነገሥታቱና መኳንንቱ ሲያሳድዷቸውና መከራ ሲያበዙባቸው፤ ከነገሥታቱ ጋር የተጠጉ የቤተ መንግሥት ካህናትና መነኮሳት ሲያሳብቁባቸውና ተንኮል ሲሠሩባቸው፤ እግዚአብሔር ደግሞ ቅድስናቸውንና እምነታቸውን በተአምራት ሲገልጥላቸው ያያሉ፡፡

                                  አራቱ ኃያላን – ከአሥራ አምስት ቀን በኋላ በገበያ ላይ ይውላል

      አቡነ ተክለ ሃይማኖትና አቡነ ኤዎስጣቴዎስ( ጎርጎራ፣ ደብረ ሲና ማርያም)

      ተስፋየ ገብረ አብ ‹የስደተኛው ማስተዋሻ› የተሰኘ መጽሐፍ ማውጣቱንና ባነበው መልካም እንደሆነ ገልጦ አንድ ወዳጄ ‹ስስ ቅጅውን› ከሀገረ አሜሪካ ላከልኝ፡፡ ከዚህ በፊት ሌሎች መጻሕፍቱን አንብቤያቸዋለሁ፤ በአጻጻፍ ችሎታው የምደሰተውን ያህል እንደ አበሻ መድኃኒት ነገሩን ሁሉ እርሱ ብቻ የሚያውቀው ምስጢር ስለሚያደርገው፤ በአንዳንድ ጉዳዮችም ሆን ብሎም ሊያናጋቸው የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ እሴቶች ያሉ ስለሚመስለኝ፤ ተስፋዬ ለምን እንደዚህ ይጽፋል? እያልኩ የምጠይቃቸው ነገሮች ነበሩ፡፡
      በዚህ መጽሐፉ ውስጥም ያንን ጥርጣሬየን አጉልቶ ሥጋ ነሥቶ እንዳየው የሚያደርገኝ ነገር ገጠመኝ፡፡ ተስፋየ በገጽ 306 ላይ ‹‹የፍስሐ ጽዮን ፖለቲካ› በሚል ርእስ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የማያውቀውን ነገር ጽፏል፡፡ ስለማያውቀው ነገር የጻፈው ባለማወቁ ብቻ አይመስለኝም፡፡ አንድም ለማወቅ ባለመፈለጉ፣ አለያም ሆን ብሎ የማፍረስ ዓላማ ይዞ ይመስለኛል፡፡

      ይህን የምለው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ ተስፋዬ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለመጻፍ ሲፈልግ ሊያነባቸው የሚችላቸው መጻሕፍት በምድረ አውሮፓ እንደ ማክዶናልድ በዝተው ሞልተው ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ባልሆኑ ሰዎች የተጻፉ ናቸው፡፡ ሌላው ቢቀር ኤንሪኮ ቼሩሊ የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔቶች ታሪክ(Gli Abbati di Dabra Libanos, 1945)፣ ኮንቲ ሮሲኒ ከሐተታ ጋር ያሳተመውን ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣በዋልድባ ቅጅ (Il Gadla Takla Haimanot secondo la redazione Waldebbana, 1896)፣ የዊልያም በጅን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕይወትና ተአምር (The Life and Miracles of Takla Haymanot, 1906)፡፡ ከኢትዮጵያውያን ጸሐፍትም ውስጥ የታደሰ ታምራትን Church and State in Ethiopia, ማንበብ በተገባው ነበር፡፡

      ከዚህም ዘልሎ ጥልቅ ጥናት አድርጌ ደረቴን ነፍቼ እናገራለሁ ለሚል ደግሞ እንግሊዝ ምቹ ናትና ሎንዶን ወደሚገኘው ብሪቲሽ ሙዝየም ሄዶ በማይክሮ ፊልም የተነሡትንም ሆነ በአካል ያሉትን ብራናዎች ማየት ነው፡፡ እዚያም የማያደርሰው ከሆነ በዋና ከተማው በሆላንድ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙትን የጌታቸው ኃይሌን THE MONASTIC GENEALOGY OF THE LINE OF TÄKLÄ HAYMANOT OF SHOA, (Rassegna di Studi Etiopici, Vol. 29 (1982-1983), pp. 7-38)፤የተስፋዬ ገብረ ማርያምን A Structural Analysis of Gädlä Täklä Haymanot(African Languages and Cultures, Vol. 10, No. 2 (1997), pp. 181-198)፤ የሐንቲንግ ፎርድን (G.W.B. Huntingford, “The Lives of Saint Takla Haymanot,” Journal of Ethiopian Studies, 4(1966), 34-35.) የአሉላ ፓንክረስትን Dabra Libanos Pilgrimage Past and Present, The Mytery of the Bones and the Legend of Saint Takla Haymanot,(the sociology ethnology Bulletin) 1,3 (1994), P. 14-26 ጥናቶችን ማየት ይቻል ነበር፡፡ ያም ካልሆነ ወደ ቤልጅየም ሄዶ ፒተርስ አሳታሚ ከጥልቅ ጥናት ጋር የሚያሳትማቸውን የኢትዮጵያ ጥንታዊ መዛግብት ኅትመቶች ማገለባጥ ይቻል ነበር፡፡

      የገረመኝ ገድለ ተክለ ሃይማኖትን ያህል በኢትዮጵያ ታሪክ (History)ና የታሪክ አጻጻፍ(Historiography) ታላቅ ቦታ ያለው፣ በኢትዮጵያ ገድላት ጥናት(Hagiography) ቀዳሚ የሆነና በብዙ አጥኝዎች የተጠና ጉዳይ ያለ ምንም በቂ ማስረጃ አፈርሳለሁ ብሎ መነሣቱ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ከማይወጣበት የክርክር አዘቅት ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል፡፡

      የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥዕል( እስክንድርያ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን – ግብጽ)
      ተስፋዬ ጽሑፉን የጀመረው በስድብ ነው፡፡ ኤርትራዊት እናቱ ‹ይዘምሩት ነበር‹ ብሎ ያቀረበው ጽሑፍ የራሱን ስድብ በእና ያሳበበበት ነው፡፡ የኤርትራን ቤተ ክርስቲያንና ኤርትራውያን ክርስቲያን እናቶችን ከእርሱ በላይ አውቃቸዋለሁ፡፡ ተሰድደው በየሀገሩ ከተበተኑት ጋር አብረን ቋንቋና ድንበር ሳያግደን አገልግለናል፡፡ አሥመራ ከተማ ከሚገኙት ታላላቅ አድባራት አንዱም የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በምንም መልኩ አንዲት ኤርትራዊት እናት ተስፋዬ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ላይ የተሳለቀውን ‹መዝሙር› አትዘምርም፤ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ደማቸው የፈሰሰው ሰባት ዓመት ሙሉ ለጸሎት የቆሙበት እግራቸው በጸሎት ብዛት በመቆረጡ እንጂ ሰይጣን ‹ፈንግሏቸው› አለመሆኑን ኤርትራውያን እናቶች በሚገባ ያውቁታል፡፡ የሚገርመው ነገር ተስፋዬ በጆሮ ጠገብ የሆነ ቦታ የሰማውን መዝሙር አጣምሞት እንጂ መዝሙሩ እንዲህ አይደለም፡፡

      ተክለ ሃይማኖት የዓለም ብርሃን ናቸው

      ይኼው ለዘላለም ያበራል ገድላቸው

      ነው የሚለው፡፡

      ተስፋዬ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ አነበብኳቸው የሚለን አምስት መጻሕፍትን ነው፡፡ የአባ ዮሐንስ ከማ፣ የኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ የጽጌ ስጦታው፣ የዳኛቸው ወርቁና የኢረይን ሙራይ፡፡ አባ ዮሐንስ ከማን እንደማያውቃቸው፣ የጻፉትንም ገድል እንዳላነበበ የሚያሳብቅበት ‹ደብተራ› ሲላቸው ነው፡፡ አባ ዮሐንስ ከማ ሰባተኛው የደብረ ሊባኖስ እጨጌ እንጂ ደብተራ አልነበሩም፡፡ በዚያ ዘመን ‹ደብተራ› ማለት የንጉሡን ደብር(ድንኳን) የሚያገለግሉት ካህናት ናቸው፡፡ አባ ዮሐንስ ከማ በዐፄ ይስሐቅ(1407-1423)ዘመንና በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ(1437-1461)የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የነበሩ ደብረ ሊባኖስን እንደገና ያሳነጹ ገድለ ተክለ ሃይማኖትንም ያስጻፉ አባት ናቸው፡፡ ተስፋዬ አባ ዮሐንስ ከማ ከ200 ዓመታት ቆይታ በኋላ ስለ ጻፉ ተሳስተዋል ይላል፡፡ ባታውቀው ነው እንጂ ሙሴ ኦሪትን የጻፈው ዓለም ከተፈጠረ ከሺዎች ዓመታት በኋላ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ገድሎች ዘግይተው የሚጻፉት የአንድን ቅዱስ ቅድስና ለመመስከር ካረፈ ቢያንስ ግማሽ ምእተ ዓመት ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ በመቃብሩ ላይ የሚሠሩት ተአምራት፣ በአማላጅነቱ የሚሠራቸው ተአምራትና ሌሎችም መታየት አለባቸው፡፡ 

      ተስፋዬ አላዋቂነቱን እንደ ዕውቀት ስለወሰደው እንጂ የአቡነ ዮሐንስ ከማ ገድል የመጀመሪያው የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድል አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አራት ቀደምት ሰዎች ጽፈዋል፡፡ 1)በስንክሳር ተጽፎ የሚገኘው(በተለይም በፓሪሱ ስንክሳር) አጭር የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ፣ 2) የትግራይ ተወላጅ በሆነው በተክለ ጽዮን የተጻፈው የዋልድባው ገድለ ተክለ ሃይማኖት [አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት (በቆብ) የልጅ ልጅ ናቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አቡነ መድኃኒነ እግዚእን ሲያመነኩሱ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ደግሞ ሰባቱ ከዋክብት የተባሉትንና በጣና ዙሪያ የሰበኩትን (አቡነ ዮሐንስ ዘቁየጻ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘጣሬጣ፣ አቡነ ያሳይ ዘማንዳባ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አቡነ ዮሐንስ ዘጉራንቋ፣ አቡነ ታዴዎስ ዘባልተዋርና አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን) ሲያመነኩሱ ነው ምንኩስናን ተቀብለው ለተልዕኮ የተሰማሩት፡፡ ለዚህም ነው የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ገድል ዋልድባዎች የጻፉት፡፡] 3)ያልታወቀ ጸሐፊ አጭሩንና የሐይቅ እስጢፋኖስ ቅጅ የሚባለውን ጽፏል፡፡ ይኼኛው ገድል ቀዳሚ ሳይሆን አይቀርም፤ አንደኛ የተጻፈው ከሌሎች ቅዱሳን ገድሎች ጋር እስትግቡእ ሆኖ በስንክሳር መልክ ነው፡፡ ሁለተኛ የተጠቀማቸው አማርኛዎች በአሁኑ ጊዜ ጥቅም ላይ የሌሉ ዓይነት ናቸው፣ 4)አቡነ ዮሐንስ ከማ የጻፈው የደብረ ሊባኖስ ቅጅ ናቸው፡፡

      ይህ የአቡነ ዮሐንስ ከማ ገድል ምናልባት ከ1418-19 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ በዐፄ ይስሐቅ ዘመን የተጻፈ መሆኑ ይገመታል(Encyclopedia Aethiopica, Vol. IV, P. 832) በግብጽ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው ዐረብኛው ገድል በዐፄ ገላውዴዎስ ዘመን(1533-1551) የተጻፈ ይመስላል(Encyclopedia Aethiopica,Vol.IV, P.832)፡፡ ያልተመዘገቡ አያሌ ገድላት በየገዳማቱ መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ 22 የብራና ገድሎች በአውሮፓ፣ 20 በኢትዮጵያ የማኑስክሪፕት ቤተ መጻፍት(EMML)፣ 3 በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት፣ 5 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድሎች ይገኛሉ፡፡ በአንድ ቅዱስ ላይ የተለያዩ ቅጅዎች መገኘታቸው መረጃዎችን ያሰፋቸዋል እንጂ ጉዳት የለውም፡፡ ስለ አንድ ክርስቶስ አራት ዓይነት ወንጌሎች መጻፋቸውን ማስታወስ ይበቃል፡፡

      አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በብዙ ሥራዎቻቸው የተከበሩና የተመሰገኑ ሊቅ ናቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ላነሡት ሃሳብ ግን ያቀረቡት ማስረጃ የላቸውም፡፡ ከኢትዮጵያ ገድሎች ሁሉ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ገድል ያህል የሚታወቅና የተጠና የለም፡፡ ከሌሎች ጋር እየተነጻጸረም ሆነ በራሱ(Textual analysis) ገድለ ተክለ ሃይማኖት በአውሮፓውያንም ሆነ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ተጠንቷል፡፡ እስካሁን ግን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም ሆኑ ሌሎች የሚሉት ‹ሌላ ገድል› አልተገኘም፡፡ አለቃም ያነበቡት ከሆነ ያነበቡትን፣ ያገኙት ከሆነም ያገኙበትን አልነገሩንም፡፡ ምንጭ የላቸውምና ለታሪክ ክርክር ሊጠቀሱ አይችሉም፡፡

      ጽጌ ስጦታውም ቢሆን ምናቡንና አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን ጠቀሰ እንጂ አለ የሚለውን ‹የዚያኛውን ተክለ ሃይማኖት› ገድል ሊያመጣልን አልቻለም፡፡ ዳኛቸው ወርቁ የጻፈው ልቦለድ እንጂ ታሪካዊ ዋጋ ያለው ነገር ስላልሆነ ለክርክር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ይባስ ብሎ ተስፋዬ ኢለይን ሙራይ ለልጆች ብላ የጻፈችውን ተረት ጠቅሶልናል፡፡ ይህ ነገር የቦሩ ሜዳን ክርክር ነው ያስታወሰኝ፡፡

       በቦሩ ሜዳ ክርክር ‹ለኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ልደት አለው› የሚሉና ‹ሦስት ልደት አለው› የሚሉ ሊቃውንት ተከራክረው ነበር፡፡ በዚህ ክርክር የሁለት ልደትን ወክለው ከተከራከሩት መካከል የነበሩት መልከአ ብርሃን ወልደ ዮሐንስ ‹ነአምን ክልኤተ ልደታተ› የሚል ንባብ ከሊቃውንት መጽሐፍ ጠቅሰው ተከራከሩ፡፡ ዐፄ ዮሐንስም የሦስት ልደቶችን ተከራካሪ አለቃ ሥነ ጊዮርጊስን ‹በል አንተም እንደ እርሱ ከሊቃውንት መጽሐፍ ሦስት ልደት የሚል ንባብ አምጣ› አሉት በዚህ ጊዜ አለቃ ሥነ ጊዮርጊስ ‹በደብረ ብርሃን ተአምረ ማርያም ይገኛል› አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሡ ‹ከምታስተምረው ከአራቱ ጉባኤ አጣህና ነው ከተአምረ ማርያም ትጠቅሳለህ›› ቢሏቸው ‹ ከጉባኤው መጽሐፍስ የለም››  አሉ ይባላል፡፡

      የተስፋዬ አጠቃቀስ ከዚህም የወረደ ነው፡፡ አለቃ ሥነ ጊዮርጊስ የተወቀሱት ለእምነት ክርክር የማይጠቀስ የተአምር መጽሐፍ በመጥቀሳቸው ነው፡፡ ተስፋዬም ከዚያ ወርዶ ወርዶ ለታሪክ ክርክር የማይጠቀስ የተረትና የልቦለድ መጽሐፍ ሲጠቅስ ይገኛል፡፡

      ተስፋዬ ወግዳ የተሸሸገ ለሕዝብ የማይቀርብ ገድለ ተክለ ሃይማኖት አለ ይላል፡፡ በሀገራችን ጠንቋይ እንዳይጋለጥ ሲፈልግ የሌለ ነገር ያዝዛል ይባላል፡፡ ተስፋዬም ወግዳ የተደበቀ ገድል አለ አለ፡፡ ወግዳ በሰሜን ሸዋ በደብረ ብርሃን ዙሪያ ወረዳ ሥር የሚገኝ ቦታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍት በ1964 ዓም ማይክሮ ፊልም መነሣት ሲጀምሩ ከሰሜን ሸዋ ነበር የተጀመረው፡፡ እነ ሥርግው ሐብለ ሥላሴ(አጥንታቸውን ያለምልመው እንጂ) እያንዳንዷን ወረዳ ለቅመው አንሥተውታል፡፡ እንኳን በገዳማት አድባራት የሚገኙት በግለሰቦች እጅ የሚገኙትም አልቀሯቸውም፡፡ እንኳን የቤተ ክርስቲያኒቱ መጽሐፍ የሕንድ፣ የግሪክ መጻሕፍት አልቀራቸውም፤ እንኳን ገድልና ተአምር የቤተ ክርስቲያንን እምነት የሚቃረኑ መጻሕፍት በክብር ተጠብቀው ነው የተገኙት፡፡ ተስፋዬ ወግዳ የማይደረስበት መስሎት መደበቂያ ዋሻ አለ ይላል፡፡ ወግዳኮ ከአዲስ አበባ የ120 ኪሎ ሜትር ጉዳይ ነው፡፡

      በማይክሮ ፊልም ቀረጻው ወቅት በሥራ ላይ የተሠማሩት የሀገሬው ተወላጆች ነበሩና ያስቸገራቸው ነገር አልነበረም፡፡ በዚህ ጉዞ ውስጥ ይህ ‹የወግዳ ገድል› ይገኝ ነበር፡፡ ግን የለምና አልተገኘም፡፡ ይህ ዓይነት ፕሮፓጋንዳ ዛሬ አልተጀመረም፡፡ በትግራይ፣ በወሎ፣ በጎጃም በተክለ ሃይማኖት ስም ስለሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን የተጻፉ ገድሎች አሉ እየተባለ እንዲሁ በአፍ ታሪክ ይነገራል፡፡ እስካሁን ግን ማስረጃ አምጥቶ ያረጋገጠ አልተገኘም፡፡ የትግራይ ገዳማት የብራና መጻሕፍት በቅርቡ ዲጂታላይዝ ተደርገዋል፡፡ ግን የተባለው አልተገኘም፡፡ በመካከለኛው ዘመን ሌላው ቀርቶ ከማዕከላዊው መንግሥት ተጋጭተው ርቀው በነበሩት የደቂቀ እስጢፋኖሳውያን ገዳም በጉንዳ ጉንዲ እንኳን የደብረ ሊባኖሱን ገድል የመሰለ ቅጅ ነው የተገኘው፡፡

      ማንኛውም ክርክር ሲቀርብ ለክርክሩ ብቁ የሆነ ማስረጃ መቅረብ አለበት፡፡ ልቦለዱንም፣ ቀልዱንም ለታሪክ ማስረጃ መጥቀስ ቧልት እንጂ ቁም ነገር አይሆንም፡፡

      ተስፋዬ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚባለውን የታወቀ ታሪክ (official history) ለመቀበል አልፈለገም፡፡ ያ በራሱ ችግር አይደለም፡፡ አዲስ ማስረጃ አምጥቶ ወይም ነባሩን ማስረጃ በክርክር አፍርሶ ያላየነውን ካሳየን እናመሰግነው ነበር፡፡ እርሱ ግን ወይ የታወቀውን አልተቀበለ፣ አለያም አዲስ ማስረጃ አላመጣ፣ ከሁለት የወጣ ጎመን ሆነብን፡፡

      ሮማውያን የሕግ ሊቃውንት Argumentum ad Contrario የሚል መርሕ ነበራቸው፡፡ ‹አንድን ነገር የታመነውንና የታወቀውን ትተህ በተቃራኒው ያለውን አረጋግጥ› ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ የሚባለውንና የሚታመነውን ተወውና ተቃራኒውን በማስረጃ፣ በተጠየቅና በትንታኔ አረጋግጥ ማለት ነው፡፡ ተስፋዬ ይህንን ለማረጋገጥ ዐቅም አላገኘም፡፡ እንዲሁ ቧልቱን ብቻ ነገረን፡፡

      ተስፋዬ የታሪክ ስሕተቱን የሚጀምረው በሰባተኛው መክዘ ዐፄ ዳዊት የሚባሉ ንጉሥ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበሩ ሲለን ነው፡፡ ተስፋዬ በቀላሉ የሚገኘውን የሬኔ ባሴን ታሪከ ነገሥት፣ የሥርግው ሐብለ ሥላሴን የነገሥታት ዝርዝር፣ የተክለ ጻድቅ መኩሪያን መጻሕፍት አለያም የብላቴን ጌታ ኅሩይን ‹ዋዜማ›፣ የጌታቸው ኃይሌን ባሕረ ሐሳብ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1975 አሳትሞት የነበረውን The Dictionary of Ethiopian Biography, ብታይኮ እንዲህ ካለ ስሕተት ውስጥ አትወድቅም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ዳዊት በሚል ንጉሥ መጀመሪያ የነገሠው ዐፄ ዳዊት አንደኛ ከ1374-1406 ዓም ነው፡፡ ከየት አምጥተህ ነው በሰባተኛው መክዘ ያደረግከው፡፡

      እጂግ የሚገርመው ነገር የሀገራችን ሊቃውንት ‹ጨዋ ደፋር ነው› እንደሚሉት ተስፋዬም ያለ ምን ጥናት፣ ያለ ምንም ማስረጃ እርሱ ራሱም እንደሚለን ‹ኢትዮጵያ ሳለ የሰማቸውን አፈ ታሪኮች ሰብስቦ›(እኔ ግን አይመስለኝም፣ አሜሪካ ሆኖ ፈጥሮ እንጂ) በድፍረት ‹ሦስት ተክለ ሃይማኖቶች አሉ ይላል፡፡ ቢያንስ ለዕውቀት ክብር ሰጥቶ ‹ያሉ ይመስለኛል› ቢል እንኳን ምን አለበት፡፡ ለካስ እስከዛሬም በሌሎች መጻሕፍቱ ሲነግረን የነበሩት ‹የመንግሥት ምሥጢሮች› እንዲህ የተሰበሰቡ አፈ ታሪኮች ነበሩ ማለት ነው?

      ለመሆኑ ተስፋዬ እናዳለው ሦስት ተክለ ሃይማኖቶች  አሉን? ሦስቱስ በገድለ ተክለ ሃይማኖት ተቀላቅለዋልን? ሳምንት እንመለሳለን፡፡

      © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ ላይ የወጣ ነው

      ዕቃ ለማውጣት ቦሌ ወደሚገኘው የካርጎ ተርሚናል ሄጃለሁ፡፡ መቼም ዘመድ ውጭ ሀገር ያለው ሰው ደጋግሞ የሚሄደው አንድም ለወዳጁ እድሜ ከጤና ለመለመን ቤተ ክርስቲያን፣ አንድም የተላከለትን ዕቃ ለመውሰድ ካርጎ ተርሚናል፣ አንድም የዓመት በዓል ብር ለመቀበል ባንክ ቤት ነው፡፡

      ወረፋውን ጠብቄ መስኮቱ ጋ ደረስኩና ስሜን አስመዘገብኩ፡፡ እስክትጠራ ጠብቅ ተብዬም ወንበር ፈልጌ ተቀመጥኩ፡፡ ከጎኔ አንድ ጎልማሳ ተቀምጦ ይቁነጠነጣል፡፡ አንዴ ፀጉሩን አንዴ ዓይኑን ያሻል፡፡ ኩኩሉ እንደሚል አውራ ዶሮ አንገቱን ከወዘወዘ በኋላ ወደ እኔ ዞር አለና ‹‹ስምህ ናፍቆህ ያውቃል›› አለኝ፡፡

      ገረመኝና ‹‹ስሜማ አብሮኝ ነው የሚኖረው፤ ምን ብሎ ይናፍቀኛል›› አልኩት፡፡

      ‹‹ስምህን ሰጥተህ አታውቅም፤ አሁን ስምህን አልሰጠህም እንዴ›› አለኝ፡፡

      ይበልጥ ግራ ገባኝና ‹‹እና ወሰዱት ማለት ነው›› አልኩት ሳቅ እያፈነኝ፡፡

      ‹‹ታድያስ፤ አሁንኮ ወሳኙ እነርሱ ጋር ያስመዘገብከው ስምህ እንጂ አንተ ጋ ያለው ስምህ አይደለም፡፡ አንተ እገሌ መሆንህ ቁም ነገር የለውም፡፡ እነርሱ ‹እ-ገ-ሌ› ብለው ሲጠሩህ ነው ሕይወትህ የሚንቀሳቀሰው፡፡ እኔ አሁን ስሜ ናፍቆኛል፡፡ ስሜ ሲጠራ መስማት፣ ስሜ ሲጠራ አቤት ማለት ናፈቀኝ፡፡››

      የእርሱን ስሰማ እኔም ስሜ ይናፍቀኝ ጀመር፡፡ ‹‹ትጠራላችሁ›› አይደል ያሉን፤ እውነትም ስማችንን ወስደውታል ማለትኮ ነው፡፡ ካልጠሩን ቁጭ ብለን መቅረታችን ነው፡፡ የተጠሩት ደግሞ እየተፍነከነኩ ወደ መስኮቱ እየተጠጉ ነው፡፡ ሰልፉ ሲረዝም፣ ጊዜው ሲሄድ፣ መቀመጥም ሲሰለቻችሁ ደግሞ ስማችሁ ይበልጥ ይናፍቃችኋል፡፡

      ‹‹እዚህ ብቻ ነው ወይስ ሌላውም ቦታ ወረፋ አለው›› አልኩት፡፡

      ‹‹ምን እዚህ ብቻ ኑሮህኮ እንደዚሁ ነው፡፡ ስም ትሰጣለህ፣ ትጠብቃለህ፣ ስምህን ትናፍቃለህ፣ እድለኛ ከሆንክ ትጠራለህ፣ አቤት ትላለህ፣ ወደ ሌላው ምእራፍ ትሻገራለህ፡፡ እዚያም ስም ትሰጣለህ፣ ስም ትናፍቃለህ፣ ትጠራለህ፣ አቤት ትላለህ፣ እንዲህ እያልክ ትኖራለህ፡፡ አቤት ካላልክ ደግሞ ችግር ነው፡፡ ያልፍሃል፡፡ አሁን ያ ሰውዬ ስልክ እያወራ አለፈው፡፡ ‹አቤት› ማለት ነበረበት፡፡ አሁን እንደገና ስሙ እየናፈቀው ነው፡፡ ያኛው ደግሞ ስሙ ቢናፍቀው፣ ቢናፍቀው የሚጠራው አጥቷል፡፡እየደጋገመ ‹ጥሩኝ እንጂ› ይላል፡፡‹ቆይ እንጠራሃለን› ይሉታል፡፡ አሁን አንተን በስልክ ጠርተውህ ነው አይደል የመጣኸው? አሁን ይኼ ጋቢ ነገር የለበሰው ሰው ለምን አትጠሩኝም ብሎ ነው ከክፍለ ሀገር የመጣው፡፡ ስሙ ናፍቆት፡፡ ልጁ ደውላ ዕቃ ልኬልሃለሁ አለቺው፡፡ እርሱ ካሁን አሁን ስሜ በስልክ ይጠራል ብሎ ቢጠብቅ ቀረበት፡፡ ስሙ ሲናፍቀው መጣና ‹እባካችሁ ጥሩኝ› አለ፡፡ እነርሱ ደግሞ ‹ሀገርህ ተመለስና ስንጠራህ ትመጣለህ› ይሉታል፡፡ ስሙ የናፈቀው ሰው መች እንዲህ በቀላሉ ይመለሳል፡፡››

      ‹‹እውነትምኮ ስም የሚያስናፍቁ አሠራሮች ሞልተዋል›› አልኩት ለመጎትጎት

      ‹‹ቤት ለማግኘት ትመዘገባለህ፣ ስምህ ይናፍቅሃል፡፡ ጋዜጣ ላይ ወጣ፣ ተለጠፈ፣ በሬዲዮ ተነገረ በተባለ ቁጥር ስምህን ማየት ትናፍቃለህ፡፡ እዚያ ዝርዝር ውስጥ ስታጣው ቅር ይልሃል፡፡ ስኳር ለማግኘት ትመዘገባለህ፣ ከሻሂው ሱስ ይልቅ ስምህን የመስማት ሱስ ይይዝሃል፡፡ ሥራ ለማግኘት ትመዘገባለህ፣ እንጠራሃለን ስትባል ትጠብቃለህ፤ ከዚያ ስልክ ባቃጨለ ቁጥር እመር ብለህ ትነሣለህ፤ የሆነ ሰው ስምህን ሲጠራው፣ አንተም አቤት ስትል ለመስማት ትናፍቃለህ፡፡ ጓደኛህ ደውሎ በቅጽል ስምህ ከጠራህ ትናደዳለህ፡፡ አንተ የምትጠብቀው ‹አቶ እንትና ነዎት› ተብሎ ሲጠራ መስማት ነዋ፡፡ ››

      ‹‹ቆይ ግን ለምን ይመስልሃል ስማችን እስኪናፍቀን የምንደርሰው››

      ‹‹አንደኛ ለምዶብናል፡፡ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ስም ጠሪ መምህር ተመድቦ ስም መጥራት ተለምዷል፡፡ ዕድር ላይ ይጠራል፤ ፍታት ላይ ይጠራል፤ ዕቁብ ላይ ይጠራል፤ ቡና ለመጠጣት ይጠራል፤ እሥረኛ ለመጠየቅ ይጠራል፤ ቪዛ ለመጠየቅ ይጠራል፤ ስም መጥራት ባህላችን ሆኗል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ስማቸው የሚጠራና የማይጠራ ስላሉ ነው፡፡ ስማቸው ሊጠራ የሚችል፣ ስማቸው የማይጠራና ስማቸው ሳይጠራ እንደተጠራ የሚቆጠሩ አሉ፡፡ ስማቸው ሊጠራ የሚችለው እንደ እኔና አንተ ያሉት ናቸው፡፡ ዕድል ካለህ ስምህ ይጠራል፡፡ ስማቸው የማይጠራው ደግሞ አንዳች ምክንያት የሚኖራቸው ናቸው፡፡ ስማቸው መጠራት የማያስፈልጋቸው ደግሞ ጉዳያቸው በውስጥ የሚያልቅላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ስማቸው የወርቅ ቁልፍ ነው፤ ብዙ ቢሮዎችን ይከፍታል፤ ወይም ደግሞ የወርቅ ቁልፍ ያንጠለጠለ ስም የሚያውቁ ናቸው፡፡ አንዳንዴኮ ስምን መናፈቅ ይሻላል፡፡ ጭራሽ ስምህ ይጠፋልኮ››

      ‹‹አንተ ዋናው ክፉ አትሥራ እንጂ ስምህ ቢጠፋ ምን ችግር አለው? ከባሰ በሕግ መጠየቅ ነው››

      ‹‹ኖ ኖ ኖ ኖ ኖ እንደዚያ አይደለም፤ ስምህ ከነ ጭራሹ ከመዝገብ ላይ ይጠፋል እንጂ፤ ስምህ አልተመዘገበም፤ ‹ዳታ› ውስጥ የለም፡፡ ኮምፒውተር ውስጥ አልገባም፤ መዝገብ ላይ አልተገኘም፤ ፋይሉ ጠፍቷል፤ ትባላለህ፡፡ አንዳንዱ ስምማ ይገርምሃል እንደ ቁልፍ ማንጠልጠያ ወልቆ የሚጠፋ ነውኮ የሚመስለው፤ በተመዘገበበት ቦታ አታገኘውም፡፡ አሁን የእኔ ስም ዕድር ልከፍል ከሄድኩ አንደኛ ነው የሚጠራው፤ ስኳር ልወስድ ከሄድኩ ግን ጭራሽ ሳይጠራ ሊቀር ይችላል፡፡ ለክፍያና ለመዋጮ ብቻ የታደሉ ስሞች አሉ፡፡ ለመቀበል ብቻ የታደሉ ስሞችም አሉ፡፡ ሁለቱንም ስሞች በየመዝገባቸው ነው የምታገኛቸው፡፡ አንተ አንዴ እንኳን ስምህ አልጠራ ብሎህ እየናፈቀህ አንዳንድ ሰዎች ሁለትና ሦስት ጊዜ ስማቸው ሲጠራ ስታይ፣ ስም የሌለህ ሁሉ ይመስልሃል፡፡››

      ‹‹ግን ለሥራና ለስም የታደሉ ሰዎች የሉም››

      ‹‹ሞልተው፤ አሁን እኛ ሀገር ሊቅ፣ ሳይንቲስት፣ እውነተኛ ነጋዴ፣ ባለሞያ፣ ሥራ ፈጣሪ፣ ገበሬ፣ ምናምን ለስም ያልታደሉ ናቸው፡፡ ስማቸውን የደመወዝ መክፈያና ግብር ሰብሳቢ ብቻ የሚያውቀው፤ አርቲስት፣ ዘፋኝ፣ ቀልደኛ፣ ደግሞ ለስም የታደሉ፡፡ እስኪ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የአንድ ሳይንቲስት ቤት ዓመት በዓል ሲያከብር አይተህ ታውቃለህ? የአንድ የረዥም ርቀት አሽከርካሪ ቤት ገብቶ ኑሮውን ሲያስቃኝ አይተህ ታውቃለህ? እነዚህ ለስም ያልታደሉ ናቸው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ሥራውን የሠሩት፣ የደከሙት፣ የለፉት ስማቸው ሳይጠራ መጨረሻ ላይ የሚጨመሩ ቅመሞች ስማቸው ሲጠራ ትሰማለህ፡፡›› 

      ይህንን እያወራልኝ በድምጽ ማጉያ ስም መጥራት ተጀመረ፡፡ አምስት ሰዎች ተጠሩ፡፡ አብሮኝ የነበረው ሰው ግን አልተጠራም፡፡ በድምጽ ማጉያው ‹መሐሪ ተሾመ› የሚል ስም ሲጠራ ከእኛ ፊት ለፊት ባለው ወንበር ላይ የተቀመጠው ሰው ‹ወንድ ከሆንሽ መሐሪ አስቻለው ብለሽ አትጣሪም›› አለ፡፡

      ‹‹መሐሪ አስቻለው ብሎ መጣራት የወንድነት መለኪያ ሆነ እንዴ›› አልኩት

      ‹‹መሐሪ አስቻለው እኔ ነኛ››

      © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው

      የመንበረ ፓትርያርክ 32ኛው ጉባኤ የረቡዕ ዕለት ከሰዓት ውሎ ካለፉት የተለየ ነበር፡፡ ዋና አጀንዳው ‹መቻቻልን› የተመለከተ ሲሆን አቅራቢዎቹም ከፌዴራል ጉዳዮች የተወከሉ አካላት መሆናቸውን በዕለቱ የመርሐ ግብር ዝርዝር ላይ ተገልጧል፡፡ ከሰኞ ጀምሮ ይቀርብ በነበረው የአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች ላይ የመብት ጥሰትና ሥልጣንን ለግል ሃይማኖት ማስፋፊያ የመጠቀም አዝማሚያዎች መኖራቸውን፣ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠው እምነትን የመያዝ፣ የማስፋፋትና የአምልኮ ቦታ የማግኘት መብት እየተጣሰ መሆኑን የሚገልጡ ዘገባዎች ይሰሙ ነበር፡፡

      በትናንትናው የከሰዓት ውሎ ስለ መቻቻል ገለጣ ከተሰጠ በኋላ ብጹዐን ሊቃነ ጳጳሳትና የጉባኤው ተሰብሳቢዎች የየአካባቢያቸውን ችግሮች በዝርዝር ነበር ያነሷቸው፡፡ ‹‹መቻቻል እስከ ምን ድረስ ነው›› ብለው ነበር ብጹዕ አቡነ ቄርሎስ የጠየቁት፡፡ ‹‹አሁን በምዕራብ ወለጋ ያለው ሁኔታ መንግሥት በአገሩ ያለ ይመስላል ወይ? ሰው እግሩን እሳት እየበላው ቻል ይባላል እንዴእንድንቻቻል አድርጉን፣ እንችላለን›› ነበር ያሉት፡፡

      የምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሄኖክ ‹በነጆ ወረዳ በሕጋዊ መንገድ ተሠርቶ የነበረው ቤተ ክርስቲያን በአካባቢው ባለ ሥልጣናት ተጽዕኖ እንዲፈርስ መደረጉን፣ ለምን ታፈርሳላችሁ ብለው ድርጊቱን የተቃወሙ ስድሳ ምእመናን መታሠራቸውን›› በኀዘን ነበር የገለጡት፡፡ አያይዘውም ‹‹በባኮ ወረዳ የተመደቡ አንድ ካህን እያረሱ እያሉ የአካባቢው ባለ ሥልጣናት መጡ፤ ካህኑን በሰደፍ እየደበደቡ ‹ከዚህ ሀገር ልቀቁ፣ ይህ የነፍጠኛ መኖሪያ አይደለም› እያሉ አሰቃዩዋቸው፡፡ ካህኑን ሲደበድቧቸው አንበርክከው፣ ለ15 ደቂቃ አተኩረው ፀሐይዋን እንዲያዩ እያስገደዱ ነበር፡፡ ድብደባውን ሰምተው የወጡት ባለቤታቸው በድንጋጤ ታመው ከጥቂት ቀናት በኋላ ሕይወታቸው አለፈ››

      ‹‹በሰንበትና በቅዱስ ሚካኤል ቀን ምእመናን ሊያስቀድሱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ ‹ለቅዳሴ ካህናቱ ይበቃሉ፤ እናንተ ውጡ›› እየተባሉ እንዳያስቀድሱ ይደረጋሉ፡፡ ከእኛ ቤተ ክርስቲያን 70 ሜትር ርቀት ላይ ሆን ተብሎ እርስ በርስ ለማጋጨት ለፕሮቴስታንቶች የጸሎት ቦታ ተሰጠ፡፡ ለምን ታጨቃጭቁናላችሁ፤ ይህ ቦታ ለእነርሱ አይሆንም ብሎ በመከራከሩ አንድ ዲያቆን ተደብድቦ ሞተ፡፡ የሕክምና ውጤቱም ሆን ተብሎ በወባ በሽታ ሞተ ተብሎ ተሠራ፡፡ ለሁለት ዓመት ያህል ተከራክረን አሁን ቦታው ለእኛ ተወሰነ፡፡

      ጊምቢና መንዲ ላይ የምእመናን ልጆች ትምህርት ቤት ውስጥ በፖሊስ ማተባችሁን በጥሱ እየተባሉ ነው፡፡ ለምን ስንላቸው ከላይ የወረደ መመሪያ አለ ይሉናል፡፡››

      ቀጥለው የሀገረ ስብከታቸውን ችግር ያቀረቡት የጋሞጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤልያስ ነበሩ፡፡ ‹‹በጋሞ ጎፋ መቱ ወረዳ፣ ዋጁ ኡቆ ላይ የመስቀል ማክበሪያ ቦታችን ለሱቅ መሥሪያ ቦታ ተሰጠ፡፡ አቤት ብንል የሚሰማን በማጣታችን ዘንድሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መስቀል ሳናከብር ዋልን፡፡ ሀገሪቱ በችግር ላይ በነበረች ጊዜ እንኳን መስቀል ሳይከበር ቀርቶ አያውቅም ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያን የይዞታ ቦታ ለመንግሥት እየተሰጠ ነው፡፡ በአቡነ ጳውሎስ ዘመን በቅዱስነታቸው በኩል ለክልሉ ደብዳቤ ጻፍን፡፡ ክልሉ ወሰነልን፡፡ ነገር ግን እስካሁን አልተረከብንም፡፡››

      ቀጥለው ሃሳባቸውን የሰጡት የባሰ ካልመጣ በቀር ድምጻቸው ማይሰማው ብጹዕ አቡነ ያሬድ የሶማሌ ክልል ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነበሩ፡፡ ‹‹በሶማሌ ክልል አምስት አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ናቸው ያሉን፡፡ ምእመናኑ ብዙ ናቸው፡፡ ሲወልዱ የሚያስጠምቁበት፣ ሲያርፉ የሚቀበሩበት ቤተ ክርስቲያን እንትከል ብንል የሚሰማን አጥተናል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የሚረዱ ምእመናን በግላቸው ጥቃት እየደረሰባቸው ነው፡፡ ለዚህ መልሳችሁ ምንድን ነው›› ብለዋል፡፡

      በገለጻው ላይ ኢትዮጵያ ክርስትናን የተቀበለችው በ4ኛው መክዘ ነው የሚለውን የተቃወሙት ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ‹‹ታሪክ ክፉም ሆነ በጎ እንደ ታሪክነቱ መተረክ አለበት፤ አቅራቢው ወንድማችን በ4ኛው መክዘ ክርስትና ገባ ያልከው ተሳስተሃል፡፡ ለመሆኑ ይህንን ለማለት ‹ላይሰንስ አለህ?› አባቱን የሚኮንን ልጅ ምን ያደርጋል? ነገሥታቱን ወቀሳችሁ፣ ቤተ ክርስቲያንን ነቀፋችሁ፤ ለመሆኑ ከማን ነው ይህቺን ሀገር የተረከባችሁት? ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው ጌታ ባረገ ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 ላይ አለ፡፡ ይህንን ዛሬ ‹ግራጁዌት አድርገው›፤ ልዑካኑ ስትመጡ ስለምትናገሩት ነገር ዕወቁ፤››

      የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ እንድርያስም ‹‹በቤተ መንግሥት የወርቅ ዕቃ ብቻ አይኖርም፣ የእንጨትም፣ የድንጋይም ዕቃ አለ፡፡ በቤተ ክርስቲያንም ሁሉም ጥሩ አይሆንም፣ መጥፎም ይኖራል፡፡ ነገር ግን እስከ መጨረሻው የጸና ይድናል ብሏል፡፡ በእኔ ሀገረ ስብከት ስድስት አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፡፡ ሦስቱ በአንድ አካባቢ፣ ሦስቱ በሌላ ቦታ፡፡ ይህንን ለክልሉ መንግሥት ብናሳውቅ አልረዱንም፡፡ የተበደለ ሰው ይጮኻል፤ ሲጮህ ደግሞ ፖለቲካ ነው ይባላል፡፡ ድሮ ያስቸገረን የንዋያተ ቅድሳት ዘረፋ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ወደ ማቃጠል ተዛውሯል፡፡ አንዱ ባለ ሥልጣን እንዲያውም ችግሩን ሳቀርብለት ተቆጣኝ፤ ብዙ ብናገር ነፋስ ስለሚወስደው እዚህ ላይ ይብቃ››

      ከብጹዐን ሊቃነ ጳጳሳት ቀጥሎ የተናገሩት የወላይታ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ‹‹በበዴሳ ወረዳ ያለ አንድ የሌላ እመነት ተከታይ የሆነ ዳኛ ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጋር ቄራ አንካፈልም፤ በመኪና አብረን አንሄድም› ብሎ ዐወጀ፡፡ በጋራ በመቻቻል የኖርንበትን ዕድር ሁሉ ለዩ ብሏል፡፡ ታድያ እንዴት መቻቻል ሊመጣ ይችላል፡፡››

      ከጉባኤው የቀረበውን ቅሬታና ሃሳብ ያዳመጡት የፌዴራል ጉዳዮች የሥራ ኃላፊዎች የቀረቡት ቅሬታዎች በሰነድ ተደግፈው ቢደርሷቸው እነርሱም በመፍትሔው ላይ መሥራት እንደሚችሉ፤ ኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ጉባኤም ጉዳዩ በየደረጃው ቢቀርብለት መፍታት እንደሚችል፡፡ ቅሬታዎችን እንደዚህ ባለ መድረክ ከሚሆን በየጊዜው እየተገናኙ መፍታት ቢቻል›. የሚሉ ሃሳቦችን ሠንዝረዋል፡፡

      የዘንድሮው የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ በአደረጃጀቱ ውበት፣ በተሳታፊዎቹ ብዛት፣ በአህጉረ ስብከቶች ቁጥር(50 ደርሰዋል)፣ በስብሰባው ቁም ነገረኛነት ካለፉት የተለየ ነበር፡፡ እነ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ የሰበካ ጉባኤ ስብሰባ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን በብርቱ እንደ ደከሙበት ያሳያል፡፡ በየዘገባዎቹ የተሰሙትን የመብት ጥሰቶች፣ ሥልጣንን ተገን በማድረግ የሚፈጸሙ ጫናዎች፣ የአምልኮ ቦታ እጥረቶች፣ በካህናቱ ላይ የሚፈጸሙትን ግፎችና፣ የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ የመንጠቅ ርምጃዎች ግን ሊገቱ ይገባቸዋል፡፡ ከአንዳንድ ክልሎች በቀር በብዙዎቹ የዞንና የክልል ባለ ሥልጣናት ችግሩን ተረድተው ለመፍታት እንደሚጥሩ ተገልጧል፡፡ በወረዳ ደረጃ የሚገኙት ግን ሥልጣንን ተገን በማድረግ የግል እምነታቸውን እያስፋፉ መሆኑን ያሳያል፡፡ በደቡብ ጎንደርና በምሥራቅ ጎጃም የተፈጸሙት የአብያተ ክርስቲያናትን የማቃጠል ርምጃዎች በጊዜው ተጣርተው መፍትሔ ካልተሰጣቸው ፍጻሜያቸው አያምርም፡፡

      በየአካባቢው በሚገኙ ባለ ሥልጣናት የሚፈጸሙ ትንኮሳዎችም መቆም አለባቸው፡፡ ብጹዐን ሊቃነ ጳጳሳቱ ‹አታስቆጡን› እያሉ ደጋግመው የተናገሩት ነገር የዋዛ አይደለም፡፡ ኃላፊነት የማይሰማቸው አካላት የሚፈጽሙት ገደብ አልባ ትንኮሳና ጫና ወዴት እያመራ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

      ቤተ ክርስቲያኒቱም አደረጃጀቷንና አሠራርዋን ይበልጥ የምትፈትሽበት፣ አሁን ለገጠማት ተግዳሮት ብቁ የሚሆን አሠራና አወቃቀር የምትይዝበት፣ ችግሮችን በስብሰባ ብቻ ሳይሆን በአካባቢያዊ ውይይት፣ በሕግ መሥመርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት የምትፈታበት መንገድ ሊኖር ይገባል፡፡  

      ያለበለዚያ መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል የተረተው ተረት መድረሱ የማይቀር ነው፡፡

      በጣልያን ጊዜ ነው አሉ፡፡ ጎንደር ላይ ጣልያን በድማሚት አንዱን ተራራ ያናውጠዋል፡፡ ተራራው ‹እድም› እያለ ይፈርሳል፡፡ አንዲት የከብት እረኛ ልጅ ፈርታ ወደ እናቷ ሄደችና ‹እማዬ ኧረ ጣልያን ተራራውን እያፈረሰው ነው›› አለቻት፡፡ እናቷም ‹‹እነ ደጃዝማች እገሌ፣ እነ ፊታውራሪ እገሌ፣ እነ ራስ እገሌ እጅ አንሰጥም ብለው እየተጋደሉ ዐለፉ፡፡ ተራራውንስ ተይው ያፍርሰው፤ እርሱም መቀመጡን አብዝቶት ነበረ፡፡›› አለቻት አሉ፡፡ 

      ‹ይህቺ ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር የሚጠብቅና የሚታደግ አንዳች ኃይል አለ› የሚባለውን ነገር እንድናምን የሚያደርጉ ብዙ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ሕዝቧ ብትን፣ ቅዝቅዝ፣ ድብዝዝ ሲል ከየት እንደሚመጣ ሳይታወቅ ብቅ የሚል፣ እንደ አውሎ አጥለቅልቋት፣ እንደ እቶን አንድዷት፣ እንደ ሐረግ አስተሣስሯት፣ እንደ ደመና ከልሏት፣ እንደ አደይ አበባ አስውቧት፤ እንደ ቀስተ ደመና ቃል ኪዳኗን አድሶ፣ እንደ ጠል አረስርሶ፣ እንደ ሸማ ፍቅር አላብሶ፣ እንደ ደመራ የሀገር ፍቀር ስሜት ለኩሶ፣ እንደ ጨረቃ አድምቆ፣ እንደ ፀሐይ አሙቆ፣ እንደ ሰም አጣብቆ፣ የሚጎበኝ መንፈስ አላት፡፡

      እውን ኳስ ነው ያስለቀሰን? እውን ግብ ነው የናፈቀን? እውን የጨዋታ ጥበብ ነው የጠማን? እውን ለዓለም ዋንጫ መድረሳችን ነው እንዲያ ፍቅርን እንደ ሸማ ያላበሰን? እኔ ግን ያየሁት ከዚህ ሁሉ በላይ የሆነውን ነው፡፡ አንዳች ያጣነው ነገር፣ አንዳች የጠማን ነገር፣ አንዳች የተነጠቅነው ነገር፣ አንዳች ቁጭት ውስጥ የከተተን ነገር፣ አንዳች እንደ ዋልታ የሚይዘን፣ እንደ ማገር የሚያስተሣስረን፣ እንደ ተራዳ የሚደግፈን፣ እንደ ደመራ የሚሰበስበን፣ እንደ ችቦ አንድ የሚያደርገን፣ አንዳች ነገር የጠማን ይመስለኛል፡፡

      ትናንት የኳስ ደጋፊዎችን አልነበረም ያየሁት፣ የኢትዮጵያን ደጋፊዎች እንጂ፡፡ አንድነቷን፣ ኅብሯን፣ ልዕልናዋን፣ ታላቅነቷን የሚደግፉ፤ መለያየትን፣ መከፋፈልን፣ መገፋፋትን፣ መጠፋፋትን፣ የሚቃወሙ ኢትዮጵያውያንን ነው ያየሁት፡፡ ሰንደቋን ከንሥር በላይ ከፍ ያደረጉት፣ መዝሙሯን በባዶ ሆዳቸው ሰማይ እስኪገረም ድረስ የዘመሩት፣ ከተማዋን በአረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ያጥለቀለቁት ለኳሱ ብቻ አይመስለኝም፡፡ ዓላማቸው ከኳስ በላይ ነበር፡፡ ፍላጎታቸው የኳስ ቡድኑ ሦስት ነጥብ እንዲያመጣ ብቻ አልነበረም፡፡ ፍላጎታቸው አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ ሕዝባዊነት፣ ጀግንነት፣ ኢትዮጵያዊነት ሦስት ነጥብ እንዲያመጣ ነበር – አምጣቷልም፡፡

      ትናንት ናይጄርያ ቡድናችንን፣ እኛ ታሪካችንን አሸንፈናል፡፡

      የሰሜኑ ዋልያ ከወጣበት የዳሽን ተራራ ይልቅ፣ ዋልያዎቹ የወጡበት የኢትዮጵያዊነት ተራራ ይበልጥ ነበር፡፡ ከዋልያው ብርቅዬነት የዋልያዎቹ ብርቅዬነት በልጧል፤ እንዲህ አንድ አድርጎ የሚያስደስተን፣ አንድ አድርጎ የሚያስለብሰን፣ አንድ አድርጎ በቁጭት የሚያስለቅሰን አጥተን ነበር፡፡ ልቅሷችን የበደል፣ ደስታችን የግላዊ ጥቅም፣ መሰባሰቢያችን ብሔረሰብ፣ መገናኛችን የወንዝ ቋንቋ፣ መነጋገሪያችን አካባቢያዊ ጉዳይ፣ ንግግራችን ጨቋኝና ተጨቋኝ ሆኖብን ነበር፡፡ ዋልያዎች ሆይ ክብር ይስጣችሁና ከዚያ ከፍ አድርጋችሁናል፡፡ አልተሸነፋችሁም አሸንፋችኋል፡፡ መለያየትን፣ መከፋፈልን፣ መገፋፋትን፣ ወንዝ ለወንዝ መሄድን፣ በሰፋ ግብ አሸንፋችኋል፡፡ ባንዲራ አስለብሳችሁ፣ ለባንዲራ አስዘምራችሁ፣ ለባንዲራ አስለቅሳችሁናል፡፡

      ልጆቻችን አንድ፣ ከፍ ያለ፣ አድማስ ላይ ብቻ የሚታይ፣ ከሁላችንም ድምር በላይ የሆነ ሀገራዊ ስሜት እንዲሰማቸው አድርጋችኋል፡፡ በየተወሰነ ዘመን ራሱን እንደሚያድሰው የከራድዮን ወፍ የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ እንደገና አደሳችሁት፡፡ በየትኛው ሕግና መመሪያ፣ በየትኛው አሠራርና ቅጣት፣ በየትኛው መዋቅርና አደረጃጀት ይህንን የሰንደቅ ዓላማ ፍቅርና ክብር፣ ይህን የሀገር ፍቅርና ክብር፣ ይህን የአንድነት ስሜትና መንፈስ ልናመጣው እንችል ነበር? እንኳን ኖራችሁ፡፡

      እናንተ አላዘዛችሁንም፣ ግን አደረግነው፤ አልነገራችሁንም፣ ግን ፈጸምነው፤ ዐዋጅ አላወጣችሁም፣ ግን ተገበርነው፤ መዋቅር አልዘረጋችሁም፣ ግን ልባችን ውስጥ ገባችሁ፤ አልቀጣችሁም፣ ግን ታዘዝናችሁ፤ ጥሪ አላስተላለፋችሁም፣ ግን ሆ ብለን ወጣን፤ አልመዘገባችሁንም፣ ግን አባላችሁ ሆንን፤ ደወል አልደወላችሁም፣ ግን ሌሊት በስታድዮም ሰዓታት አደርን፤ አበል አልከፈላችሁንም፣ ግን ሳይደክመን ተሰለፍን፤ ወደ ከፍታው መራችሁን፣ እኛም  በደስታ ተከተልናችሁ፡፡

      በኳስ ሜዳማ ብራዚልም ይሸነፋል፤ ስፔንም ይሸነፋል፤ የኳስ ወላጅ እናቱ እንግሊዝም ትሸነፋለች፡፡ የአኩስምና የላሊበላ፣ የጀጎልና የጎንደር ግንብ ጥበብ የተሞላበት ያንን የመሰለ ኳስ፣ የጠጅ አጣጣላችን፣ የጠላ አጠማመቃችን፣ የቅመም አቀማመማችን፣ የወጥ አሠራራችን፣ የክትፎና የቆጮ፣ የገንፎና የአምባሻ ጥበባችን በእናንተ ጨዋታ ታየ፡፡ ኳስን ገረማት፡፡ እንግሊዝ አፍ ያዘች፣ ስፔንን ገረማት፣ ብራዚል ልትቀሩ ነው ብላ ቅር አላት፣ ፈረንሳይ አጀብ አለች፣ ጀርመን ተደነቀች፤ ጣልያን ተደመመች፡፡

      አሁን ስለ እናንተ ስንናገር በኩራት ነው፤ አሁን ልጆቻችን የሚጨዋወቱት በቁጭት ነው፡፡ ‹ዋልያው ንሥሩን ጋልቦታል› እንላለን፡፡ ይህንን ድሮ በ ‹ዜና እስክንድር› ብቻ ነበር የምንሰማው፡፡ እስክንድር ጠቢቡ ወደ ገነት ለመሄድ ብሎ ንሥሩን ከፈረስ ጋር አዳቅሎ ጋለበው አሉ፡፡ እናንተም እንዲሁ ንሥሩን ጋልባችሁ ወደ ልዕልናው ገነት፣ ወደ ኢትዮጵያዊነት ገነት፣ ወደ አንድነት ኤደን ወሰዳችሁን፡፡

      ይህቺን ቀን እንደ አድዋ ድል፣ እንደ ዶጋሊ ድል፣ እንደ ሚያዝያ ሃያ ሰባት፣ ስናከብራት ትኖራለች፡፡ የድል ቀን ናትና፡፡ አንድነት መለያየትን፣ ኅብረ ብሔርነት ጠባብነትን፣ ኢትዮጵያዊነት ጎጠኛነትን፣ ሉዓላዊነት ተዋራጅነትን ድል ያደረጉበት ቀን ናት፡፡ 

      ‹ዛሬ በናትሽ ዳጎስ ያለ ሰነድ ወይም መጽሐፍ ወይም ዶሴ መብላት አማረኝ›› አለች አንዲት ነጭ አይጥ ለጓደኛዋ፡፡
      ‹‹ለምን አንዱ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት አልወስድሽም›› አለቻት ጥቁሯ አይጥ፡፡

      ‹‹እኔን ለማስደብደብ ነው እንዴ ፍላጎትሽ›› አለቻት ነጯ

      ‹‹ማነው ደግሞ የሚደበድብሽ››

      ‹‹ሠራተኞቹ ናቸዋ››

      ‹‹ስለ ሕዝብ ቤተ መጻሕፍት አታውቂም ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥኮ አንድ ነገር የሕዝብ ነው ከተባለ ሁለት ነገር ነው ማለት ነው፡፡ ወይ የማንም አይደለም፤ ወይም የጥቂቶች ብቻ ነው፡፡ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ማለት የማንም ያልሆነ ቤተ መጻሕፍት ማለት ነው፡፡ በጀት የለው፤ ተቆጣጣሪ የለው፤ ባለቤት የለው፡፡ ማዘጋጃ ቤት የባህል ቢሮ ነው ይለዋል፤ የባህል ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ነው ይለዋል፤ ኮሙኒኬሽን ጽ/ ቤት የወጣቶች ሊግ ነው ይለዋል፤ የወጣቶች ሊግ የሕዝብ ነው ይለዋል፡፡ ስንትና ስንት የጥንት መጽሐፍ ባለቤት ስላጣ ማንም ዘወር ብሎ አያየውም፡፡ ይልቅ ተነሽ እንሂድ››

      ተያይዘው ሄዱ፡፡ ገቡ፡፡ አንድ አስነባቢ ገቢያቸውን ለብሰው ጠረጲዛ ላይ ክንዳቸውን ተንተርሰው ሸለብ አድርገዋል፡፡ አይጦቹ በበሩ ሲገቡ እንኳን አላዩዋቸውም፡፡

      ‹‹ያንን መጽሐፍ አውርጂው›› አለቻት ጥቁሯ፡፡ ነጯ አይጥ ሄደችና አወረደችው፡፡ ዳስ ካፒታል የሚለው የማርክስ መጽሐፍ ነው፡፡ ‹‹ለእኔ ደግሞ እዚያ ማዶ ያለውን አምጭልኝ›› አለቻት፡፡ ኦክስፎርድ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ነው፡፡ ሁለቱም ተቀምጠው መቆርጠም ጀመሩ፡፡

      አስነባቢው የሆነ ድምጽ ስለሰሙ ቀና አሉና መልሰው ተኙ፡፡

      ‹‹እንዴ በሙሉ የድሮ መጽሐፍ ብቻ ነው እንዴ›› አለች ነጯ አይጥ፡፡

      ‹‹እዚህ ከተማ ለስብሰባ፣ ለድግስ፣ ለቲሸርት፣ ለኮፍያ፣ ለቢል ቦርድ፣ ለሲምፖዝየም፣ ለምናምን መታሰቢያ ቀን፣ ለምናም መመሥረቻ ቀን የሚሆን በጀት እንጂ ለዕውቀት የሚሆን በጀት የለም፡፡ አታይም ሠላሳ ሺ ሕዝብ የሚይዝ ኮንዶሚንየም ሲገነባ በግ ማረጃ እንጂ ቤተ መጻሕፍት ተገንብቷል? ለመጠጥ ቤት፣ ለጫት ቤት፣ የሚሆን ቦታ ግን ሕንጻዎቹ ሥር ተሠርቷል፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቹ በየቢሮው ያሉት ከዕውቀት የጸዱ፣ ከሆድ የተዛመዱ ናቸዋ፡፡ ያለ አእምሮ ልማት ቁሳዊ ልማት ከየት ይመጣል፡፡ መገንባት ብቻውን አያለማምኮ፡፡ የገነባሽውን በሚገባ የሚጠቀም፣ የሚከባከብ፣ እድሜውን የሚያረዝም፣ እሴት የሚጨምርም ዜጋ ያስፈልጋል፡፡ በጎጆ አስተሳሰብ ዘጠኝ ፎቅ ላይ መኖር ትርፉ በረንዳ ላይ በግ ማረድ ነው፡፡ ከወረቀት ግብር የቢራ ግብር በሚቀንስባት ሀገር፤  ኪነ ጥበብ ከማይበረታቱ ኢንዱስትሪዎች መደብ በተመደበባት ሀገር ምን ትጠብቂያለሽ›› አለች ጥቁሯ፡፡

      ‹‹ባለፈው አንዲት ጓደኛዬን ለአዲስ ዓመት ወጣ ብለን እንዝናና ስላት የት እንደወሰደችኝ ታውቂያለሽ››

      ‹‹ዱከም ወስዳ ሥጋ ጋበዘችሽ››

      ‹‹ኧረ አይደለም፤ አቃቂ››

      ‹‹አቃቂ ደግሞ ምን አለ?››

      ‹‹ድሮ በደርግ ጊዜ ኩራዝ አሳታሚ እያለ ሊታተሙ የተሰበሰቡ ረቂቆች አሉ ብላ ይዛኝ ሄደች፡፡ አንድ ትልቅ የቆርቆሮ መጋዘን ውስጥ ተከምረውልሻል፡፡ እዚያ ይዛኝ ገባች፡፡ እዚህ ሀገር የታወቁ ደራስያንን ሥራ ስንከሰክስ ስንከሰክስ ዋልንልሽ፡፡ አንዳንዱ ታርሟል፤ አንዳንዱ አልፏል የሚል ተጽፎበታል፡፡ አንዳንዱ ማኅተም አለው፡፡

      ‹‹ዝም አሏችሁ››

      ‹‹ማንም ዝር አይልም ከአይጥ በቀር አሉ የለመዱትማ ሲነግሩን››

      ‹‹ወይ ይህቺ ሀገር፣ ከገዛ ታሪኳና ቅርሷ፣ ከገዛ መዛግብቷና ሰነዶቿ ጋር የምትጣላ ሀገር፡፡ ባለፈው የባድሜ  ጉዳይ በዓለም ፍርድ ቤት ሲዳኝ አንዱ የተጠየቅነው ሰነድ ነበር አሉ፡፡ የተቆረጠ ደረሰኝ፣ የተሰጠ ሹመት፣ ከዚያ አካባቢ የተጻፈ ነገር፣ የሐኪም ቤት ካርድ፣ ያ ቦታ የኢትዮጵያን እንደነበረ የሚያሳይ ዶሴ አምጡ ተብሎ ነበር አሉ፡፡ እዚህ ሀገርኮ ስንቱ ፋይል፣ ስንቱ ዶክመንት፣ ስንቱ ደብዳቤ፣ ስንቱ መረጃ አሮጌ ነው እየተባለ ተጥሎ በየቆርቆሮው ቤት ታሽጎበታል መሰለሽ፡፡ ለኛማ ሠርግና ምላሽ ነው፡፡ እርሱን እየበላን እንኖራለን፡፡ ሀገሪቱ ግን ታሳዝናለች፡፡››

      ‹‹ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት የሚባል ድርጅት አለ አይደል እንዴ››

      ‹‹አንድ ለእናቱ የሆነውን ነው የምትይኝ? ይኼው ሰማንያ ዓመት ሆኖታል አንድ ለእናቱ ነው፡፡ እስኪ ክልል ውረጅ አንድ የመዛግብት ማዕከል ታገኛለሽ? በተለይማ ባለፉት ሥርዓቶች የነበሩ መዛግብት የጠላት ገንዘብ ተደርገው የማንም መጫወቻ ሆነዋል፡፡ ወይ ቆርቆሮ ቤት ገብተዋል፤ ወይ ተቃጥለዋል፤ ያለበለዚያም በኪሎ ተሸጠዋል፡፡››

      ‹‹ይበላቸው እባክሽ፤ እነርሱ በዘመናቸው እኛ ድርሽ እንዳንል ድመት ለሚያረባ ሰው የድመት መሬት እየሰጡ አሳድደውናል፡፡ይኼው ዛሬ የሀብታም መሬት እንጂ የድመት መሬት የለ፡፡እንደልባችን ታሪክ ስንበላ እንውላለን፡፡››

      ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ በሽታ መቼ ተከሰተ፣ የት የት ቦታ ተከሰተ፣ ምን ያህል ሕዝብ ተያዘ፣ ምን ተደረገ፣ መቼ ጠፋ? ብለሽ ብትጠይቂ መልሱ ያለው የት እንደሆነ ታውቂያለሽ?››

      ‹‹ጤና ጥበቃ ነዋ››

      ‹‹ተሳስተሻል፡፡ እኛ ሆድ ውስጥ ነው፡፡ የሆስፒታል የድሮ ካርዶችኮ እንድንበላቸው ተፈቅደውልን የተከፋፈተ መጋዘን ውስጥ ተጥለዋል፡፡ እንደ ጓያ ነቃይ የዛሬን እንጂ የነገን የሚያስብ የለም፡፡ አሁንኮ ሀገሪቱ ስላደገች የወዳደቀ ትራፊ ሳይሆን አልፎልን ታሪክና መረጃ ነው የምንበላው፡፡ አንዳንድ መረጃዎችን ወደ እናንተ እናደርሳለን አሉ ጋዜጠኞች፡፡ የሚደርሰውኮ ወደኛ ነው፡፡›› 

      ‹‹አንድ ነገር አስታወስሽኝ፡፡ ከሆነ ዓመት በፊት አንድ ትልቅ ባለ ሥልጣን የተናገረው ነገር፡፡ ኢሕአዴግ ባሕርዳር ሲገባ እነርሱ የኢሠፓ ጽ/ቤት ነበር ያደሩት፡፡ ብርድ ስለነበር ሌሊቱን ፋይል እያነደዱ ሲሞቁ፡፡ በመካከል የአንድ ደራሲን ልቦለድ አግኝቶ እንዳነበበውና አዲስ አበባ ፈልጎ እንደሰጠው ሲናገር ነበር፡፡ አሁን ሰነድ ማቃጠል፣ ፋይል ማንደድ በቴሌቭዥን በኩራት የሚቀርብ ገድል ነው?ሰዎቹ ናቸው እንጂ ኢሠፓ ፋይሉኮ ኢሠፓ አይደለም፡፡ ፋይሉማ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው፡፡››

      ‹‹የኢትዮጵያን ዕቃ ገዥ ከሌላው ዓለም ገዥ የሚለየው አንዱ ነገር ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ?››

      ‹‹አላውቅም››

      ‹‹ሌላው በተራ ወረቀትና ፌስታል ዕቃውን ይጠቀልላል፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን በታሪካቸው ስለሚኮሩ በታሪካዊ መዛግብትና ሰነዶች፣ በታሪካዊ ደብዳቤዎችና ፋይሎች ዕቃቸውን ይጠቀልላሉ፡፡ በየሱቁ ከምትገዥው ስኳር በላይ ባለ ሱቁ የጠቀለለበት ፋይል ዋጋው ውድ ነው፡፡

      ‹‹ባክሽ አሁን ወሬውን ትተን እነርሱ ሙስናቸውን እኛ ታሪካችንን እንብላ፡፡››

      ቆርጠም ቆርጠም ሲል አስነባቢው ቀና አሉ፡፡ እንዳጋጣሚ አንድ አንባቢ ገብቷል፡፡

      ‹‹አባት፣ አይጥ ሳይሆን አይቀርም›› አላቸው፡፡

      ‹‹ባክህ በጨረሱትና እኔም ወደሌላ ቦታ በተዛወርኩ ይሻለኝ ነበር›› አሉት፡፡

      ቆርጠም፤ ቆርጠም፤ ቆርጠም

      ታሪክ እንበላለን፡፡

      © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው