በቄሮ ምንነት እና “ድርጊቶች” ላይ በርካታ ውዝግቦች እየተነሱ ነው። ውዝግቦቹ የሚነሱት በሁለት ፅንፎች ነው፦ ፩ኛው ፅንፍ ያሉት ሰዎች “ቄሮ ቅዱስ ነው” ሲሉ፣ ፪ኛው ፅንፍ ያሉት  ሰዎች ደግሞ “ቄሮ እርኩስ ነው” ይላሉ። እኔ ደግሞ ቄሮ እኛ ነህ የምንለውን ይሆናል ባይ ነኝ።

እንደኔ እንደኔ የውዝግቡ ሁሉ መንስዔ የቄሮን ምንነት እና የንቅናቄውን ዓይነት፣ እንዲሁም “የትግሉን” ወይም ደግሞ “የድሉን” ባለቤት ካለመረዳት የመጣ ነገር ይሆን ይሆናል በማለት ነው ይህንን ጽሑፍ ለአማራጭ አስረጅነት ያዘጋጀሁት። እግረመንገዴንም ለውዝግቡም ይሁን ለውዝግቡ መንስዔ የሆኑ ተቃርኖዎችን እዳስሳለሁ። ዓላማዬ ከፅንፉ እና ከፅንፉ ወዲህ ዓለም እንዳለ ለማሳየት እንጂ መሞከር ብቻ ሳይሆን ፍረጃችን ተፅዕኖ እንዳለው ማስታወስም ጭምር ነው።

ቄሮ – ሥያሜው ምን ይነግረናል?

‘ቄሮ’ ቃሉ ‘ያላገባ፣ ያልወለደ’ ወጣትን ይወክላል። ነገር ግን ወጣት የሚለውን ቃል የሚተኩ ሌሎች የኦሮምኛ ቃላት አሉ። እነዚህም ‘ደርደሩማ’፣ ‘ደርገጌሳ’ እና ‘ጎሮምሳ’ የሚሉት ቃላት ምሳሌ ይሆናሉ። ቄሮ የሚለው ቃል ምንጩ ‘ቄረንሳ’ ከሚለው እና ነብር የሚል ትርጉም ካለው ቃል የተቀዳ እንደሆነ ይነገራል። ስለዚህ ቄሮ ማለት እንደነብር ያለ ብርቱ ወጣት ማለት ነው፣ ማለት እንችላለን። ይሁን እንጂ አሁን በተለይ በኦሮሞ ፖለቲከኞች ዘንድ ‘ቄሮ የሚለው ቃል ፍቺ ‘አብዮተኛ ወጣት’ የሚል ትርጉም አለው።

“የቄሮ ንቅናቄ” ውልደት እና ዕድገት

ቄሮ የሚለው ቃል የፖለቲካ መድረኩ ውስጥ የገባው እ.ኤ.አ. በ2011 የአረቡ አብዮት በፈነዳበት ወቅት ነበር። መቀመጫውን ዳያስፖራ ያደረገው ንቅናቄ ከዩንቨርስቲ ተማሪዎች ጋር ግንኙነት በመመሥረት ‘ቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ’ የሚባል ኢመደበኛ ማኅበር ፈጠረ። የዚህ ማኅበር አባላት መረጃዎችን በኢሜይል እና በድረገጻቸው እየተለዋወጡ በርካታ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ቀጠሉ። ሥማቸው በይፋ የተነሳው ግን በ2006 የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር  ፕላንን ተከትሎ በተነሳው እና ዩኒቨርስቲዎችን ባዳረሰው የተቃውሞ ሰልፍ ወቅት ነው።

ከዚያ በኋላ የተጋጋለው የተቃውሞ ሰልፍ መላው ኦሮሚያን ሲያዳርስ በየአካባቢው ያሉ ወጣቶች ራሳቸውን ቄሮ ብለው መጥራት ጀመሩ። የመጀመሪያው የቄሮ አደራጅ የነበረው (qeerroo.org የተባለ) ድረአምባም ይሁን የፌስቡክ ገጹ አሁን እምብዛም ተከታታይ የላቸውም። ይልቁንም የወጣቶቹ ኅብረት መሪ ተደርጎ በዘልማድ የሚወሰደው የኦኤምኤን ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃዋር መሐመድ ነው።

ከዚያ በኋላ በኦሮሚያ ክልል፣ በየአካባቢው የሚነሱት ተቃውሞዎች ውስጥ የሚሳተፉ የተደራጁም ይሁኑ ያልተደራጁ ወጣቶች በሙሉ – ራሳቸውን ሲገልጹም ይሁን ሌሎች ሲገልጿቸው – ቄሮ በሚል ሥያሜ ሆነ። ቄሮ በዚህ አካሔድ በማንም ግለሰብ ወይም ቡድን ቁጥጥር ሥር ያልሆነ፣ ነጻ ነገር ግን በኦሮሙማ (ኦሮሞነት) የተሰባሰበ ኢመደበኛ ቡድን ሆነ። ይህ ማለት ግን ወጣቶቹ በፖለቲካ ፍልስፈፍናቸውም ይሁን ብስለታቸው፣ በኢትዮጵያ እና ኦሮሚያ ታሪክም ይሁን ፖለቲካ አረዳዳቸው ወጥ አቋም አላቸው ማለት አይደለም።

ይህ በእንዲህ እያለ በአማራ ክልል የነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ላይ የሚሳተፉትን ወጣቶች ሥም ለመስጠት ተሞከረ። ‘ፋኖ’ የሚለው ሥያሜ ‘ቄሮ’ ከሚለው ጎን ለጎን መጠቀሱ የተለመደ ነገር ሆነ። ያን ጊዜ በቄሮ ሥምም ሆነ በፋኖ ሥም የሚደረገው ነገር በሙሉ፣ ማዕከላዊ መንግሥቱን እስካስጨነቀ ድረስ “ትክክል” ነበር። ይሁን እንጂ መሬት ላይ “ቄሮ ነኝ” የሚሉትን ያክል፥ “ፋኖ ነኝ” የሚሉ ወጣቶች እምብዛም አልነበሩም። እንዲያውም ‘ፋኖ’ የግንቦት ሰባት ፈጠራ ነው የሚሉ የአማራ ብሔርተኞች ገጥመውኛል። ይሁንና የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ አሁን ለምናየው የለውጥ አዝማሚያ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ወጣቶችን ሲጠሩ “ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ…” እያሉ መጥራትን ‘ፕሮቶኮል’ አድርገውታል።

የትግሉ እንዲሁም የድሉ “ባለቤቶች”

የያኔዎቹ ኦሕዴድ እና ብአዴን ተባብሮ ትሕነግ ላይ ማበይ፥ ከወጣቶቹ አመፅ ባልተናነሰ (ወይም በበለጠ መልኩ) ኢሕአዴግን ነቀነቀው። የፓርቲዎቹ ከወጣቶቹ ጋር ያልተጻፈ መግባባት ላይ መድረስ ደግሞ የቀድሞውን ኢሕአዴግን ገድሎ፣ አዲሱን ኢሕአዴግ ወለደ። አሁን ከትሕነግ/ኢሕአዴግ ወደ ኦዴፓ/አዴፓ/ኢሕአዴግ አገዛዝ ተሸጋግረናል። ይሁንና ገና አመፁ አልሰከነም። የትግሉ ባለቤት ተቃዋሚዎች በሙሉ፣ በተለይም አደባባይ የወጡት የኢትዮጵያ ወጣት አመፀኞች ናቸው፤ የድሉ ባለቤቶች ግን የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች፣ በተለይም ኦዴፓ እና አዴፓ ናቸው። ያለእነሱ ከቀድሞ አቋማቸው መቀልበስ፣ እንዲሁም ለማበር መወሰን በኢሕአዴግ ቤት አሁን ያለው ወደ ዴሞክራሲ የመሸጋገር ዕድል ፈፅሞ አይመጣም ነበር ብዬ እገምታለሁ።

ይሁንና ወጣቶቹ የልኂቃን ተቃዋሚዎችን ጥያቄ ከማስተጋባት ባሻገር ለእንዲህ ያለ ነፍስን አሳልፎ እስከመስጠት የሚደርስ ብሶት የዳረጋቸው ሥራ አጥነት እና ‘የሪከግኒሽን’ ጥያቄ መልስ ቢሰጠው ኖሮ፥ ድሉን የጋራ ድል አድርገን መቁጠር የምንችልበት ዕድል ይኖር ነበር።

አሁን ባለው ሁኔታ ብዙኃን ሥራ አጦች በየአደባባዩ በከፈሉት መስዋዕትነት፥ ‘እነዚህ ሥራ ፈቶች ደግሞ መረበሽ ጀመሩ’ እያሉ ይበሳጩባቸው የነበሩ ልኂቃን በአንድ በኩል፣ እንዲሁም በሌላ በኩል ደግሞ ‘እስከመቼ እንዲህ ተዋርዳችሁ ትኖራላችሁ፣ ታግላችሁ ነጻ ውጡ እንጂ’ እያሉ ሲቆሰቁሷቸው የነበሩ ልኂቃን ሥልጣን እየተቆጣጠሩ ሲመጡ ወጣቶቹ ችላ መባላቸው ሐቅ ነው።

ይህ ነገር ምናልባትም የትግሉ “ባለቤቶች” እና የድሉ “ባለቤቶች” ወይም “ተጠቃሚዎች” መካከል መቃቃር ሳያስከትል አይቀርም። ይህ ጉዳይ አዲስ ብሶት የሚወልድ መሆኑም የጊዜ ጉዳይ ነው።

“ጀግኖች” የነበሩ “ፅንፈኞች”
(የውክልና ጦርነት መሣሪያዎች)

በየአካባቢው በሥራ አጥነታቸው ምክንያት ዋጋ አጥተው፣ በአደገኛ ቦዘኔነት ተፈርጀው ከፊሉ ስደት እየበላቸው፣ ከፊሉ ሱስ እየዋጣቸው የነበሩ ወጣቶች ድንገት የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመፅ ማገዶ ነበሩ። ያኔ “ጀግኖች” ተብለዋል። ምክንያቱም ለልኂቃኑ ፖለቲካ ሁነኛ መሣሪያ ነበሩ። ወጣቶቹ ምናልባትም አእምሮ ከሚያላሽቅ የሥራ አጥነት ስሜት ወጥተው፥ ለራሳቸው ያላቸው ዋጋ እና ግምት የጨመረው በዚህ አመፅ ባደረጉት ተሳትፎ ይሆናል። ሕዝባዊ አመፁ ቆሞ ድንገት አገር መረጋጋት ሲጀምር ግን ወደ “መንደር ያሰለቹ አደገኛ ቦዘኔነት” መመለሳቸው ሆነ። ከተሰጣቸው ሥም መውረድ ከባድ ነው። ስለሆነም የአብዮታቸው ጠባቂ ሆኑ – ከሳሽ፣ ፈራጅ እና ቀጪ። የደቦ ፍርድ፤ በዚህ ወቅት ነው በፅንፈኝነት መፈረጅ የጀመሩት።

በዕውቁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የምትመራው ‘ኢትዮጲስ’ ጋዜጣ (በጥቅምት 24, 2011 እትሟ) በርዕሰ አንቀፅዋ ቄሮዎችን ለዘብተኛ እና ፅንፈኛ በሚል ከለያየቻቸው በኋላ ፅንፈኞቹን የማስቆም ሥራ መሠራት እንደሚገባ ጠቁማለች። የኢትዮጲስ ስህተት ምናልባት (አንድም) በአገሪቱ የደቦ ፍርዶች እና ወደ ስርዓት አልበኝነት የሚወስዱ እንቅስቃሴዎችን ለቄሮ ብቻ ለይታ መስጠቷ ነው። መቼም በድንጋይ ወግሮ መግደል እና በእንጨት ላይ ዘቅዝቆ መስቀልን የመሳሰሉ የደቦ ፍርዶች አንዱ ከሌላው የሚሻሉበት መንገድ አለ ተብሎ አይታመንም። በዚህ ረገድ ጉዳዩ ‘ወጣት ፅንፈኞች’ በሚል ሊጠቃለል ይችል ነበር ብዬ አምናለሁ። (ሁለትም) ቄሮ የተጻፈ ፕሮግራም የሌለው፣ አባላቱ በዝርዝር የማይታወቁ፣ አንድ ስትራቴጂ እና ግብ የሌለው የግፉአን ማኅበር መሆኑን ከግምት ውስጥ ያላስገባ መደምደሚያ መሆኑ ስህተት ያደርገዋል። ይህም ማለት ማንም ተነስቶ ቄሮ ነኝ ብሎ ማወጅ እና በዚያ ሥም ወንጀልም ይሁን መልካም ጀብዱ መፈፀም ያስችለዋል ማለት ነው። ብዙኃን መገናኛዎች ግን ቡድኑን ግልጽ ቅርፅ እና መዋቅር እንዳለው እንዲሁም “ተግባሩን” አቅዶ እንደፈፀመ ማኅበር ተመልክቶ “እንዲህ ነው” ወይም “እንዲያ ነው” ማለት የተሳሳተ ትርጉም ይሰጣል። (ሦስትም) የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች – ለምሳሌ የጃዋር “የቄሮ መንግሥት” እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ “ፀጉረ ልውጦችን መቆጣጠር” የመሳሰሉ – ንግግሮች ወጣቶቹን የውክልና ጦርነት ውስጥ እንደከተታቸው ከግንዛቤ ያላስገባ መደምደሚያ መሆኑ ነው።

ፍረጃ እና ተፅዕኖው፤
እስመ ሥሙ ይመርሖ ሀበ ግብሩ
(nomen est omen)

ቄሮንም ይሁን ፋኖን ወይም ሌላ የፖለቲካ ቡድኖችን በተመለከተ ለምናደርጋቸው ፍረጃዎች ማድረግ የሚገባን ጥንቃቄ አለ። ፍረጃ (labeling) በሥነ-ልቦና ግንባታ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንዳለ በርካታ ጥናቶች ያሳያሉ። «እነ እከሌ ይህን አያደርጉም»፣ «እንትን ሆኜ እንዲህ አላደርግም» የሚሉ አባባሎች የሚያስረዱን ቁምነገር ቢኖር የሆኑ ሰዎች ስብስብን የሚገልጽ ማንነትን የምንበይንበት (labeling/defining) መንገድ መልሶ የአባላቱን ድርጊት እንደሚወስን መረዳት እንደሚያሻን ነው። “ቄሮ አብዮተኛ ወጣት ነው” በተባለ ጊዜ አደባባዮችን በተቃውሞ ሰልፎች ንጧል። የለውጥ ጀምበር ሲከፈት “ለውጡን ጠብቁ” ሲባል እንደዚያው ለማድረግ እየሞከረ ነው። ወጣቶቹ በልኂቃኑ የሚሰጣቸውን ሥያሜ ለመመጠን እየተፍጨረጨሩ ነው። “ቄሮ መንግሥት ነው” ብለን ከአቅሙ በላይ ሥራ ከምናሸክመው፣ “ቄሮ የዴሞክራሲ እና የሥልጡን ፖለቲካ ጠበቃ ነው” ብለን በዚህ አቅጣጫ እንዲተጋ ብናደርገው ይመረጣል። “ቄሮ ፅንፈኛ ነው” እያልን ወደዚያ ከምንገፋው “ቄሮ ይህንን አያደርግም” ብለን ብንገስፀው ይሻላል።

ቺርስ ለጥንቃቄ!

ትላንት አንድ የስዊድን ጋዜጠኛ “ሐሳብን ከመግለጽ ነፃነት ይልቅ ደኅንነቴን እመርጣለሁ” የሚል አስተያየት አዲስ አበባ ላይ እንደገጠማት ነገረችኝ። ዛሬ ደግሞ በጥዋቱ አንዲት አሜሪካዊ ጓደኛዬ በዋትሳፕ “ብጥብጥ ካለበት ዴሞክራሲ ይልቅ ሠላማዊ አምባገነንነት ይሻላል” የሚል ክርክር እንደገጠማት ነገረችኝ። በጣም ነው ያዘንኩት፤ ምክንያቱም እዚህ ድምዳሜ ላይ እንድንደርስ የሚፈልጉ የፖለቲካ ቡድኖች እንዳሉ አውቃለሁ።

በመሠረቱ ዛሬ በጉዳዩ ላይ በአጭሩ መሞነጫጨር የፈልግኩት በነዚህ ሰዎች ብቻ አስተያየት ተነሳስቼ አይደለም። “ጭቆና ለምደን ነፃነት መሸከም አቃተን” የሚሉ አስተያየቶችን ደጋግሜ እሰማለሁ። ስህተቱ የሚጀምረው ዴሞክራሲም ይሁን ነፃነት ላይ “ደርሰናል” ከሚለው ድምዳሜ ነው። አሁን ያለንበት ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ ነፃነት ለማዋለድ በምጥ ላይ ነው ቢባል ይሻላል። እንደ አዋላጆቹ ብቃት ፅንሱ (ዴሞክራሲው) ይወለዳል ወይም ይጨናገፋል። አዋላጆቹ ካላወቁበት ደግሞ ፅንሱ እናትየውን ጨምሮ ይዞ ሊሔድ ይችላል። ስለዚህ ድምዳሜያችን ጥንቃቄ የሚያሻውን ጉዳይ ችላ እንድንለው ሊያደርገን ይችላል። ግን ዋነኛው የአረዳድ ችግር የዚህ ጉዳይ ብቻ አይደለም።

ሠላም በአምባገነንነት እና በዴሞክራሲ ውስጥ

አምባገነንነት ሕዝቡ “በቃኝ” ብሎ ቀና እስከሚል ድረስ ረግጦ የመግዛት ስልተ መንግሥት ነው። አምባገነኖች የበቃኝ ነጥብ ከመድረሷ በፊት ሁሉንም ነገር ስለሚያፍኑ ሠላም ያለ ያስመስላሉ። በአምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ ፀጥታ ስላለ ሠላም ያለ ይመስላል። ነገር ግን የታፈነ አመፅ አለ፤ የታፈነ ደም መፋሰስ አለ። ስለ አመፁም ይሁን ስለ ደም መፋሰሱ መነጋገር አይፈቀድም። የመረጃ ምንጮችም ይታፈናሉ። በአምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ የአመፁ መሪ መንግሥት ነው።

በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግን ሰዎች ቅሬታቸውን ሁሉ ያጮኻሉ፣ ትንሿም ብሶት ሳትቀር ትሰማለች። ይህ ራሳቸውን እንደሰጎን አሸዋ ውስጥ ቀብረው የሚኖሩትን ብዙዎች ከምቾት ዞናቸው ስለሚያስወጣቸው ሠላም ደፈረሰ ይላሉ። በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ፀጥታው ይደፈርስ ይሆናል እንጂ እንደ አምባገነናዊ ስርዓት ሠላም አይደፈርስበትም። ግጭቶች በዴሞክራሲያዊ ስርዓትም ውስጥ አሉ። ይሁን እንጂ ንግግር ስለማይታፈን ግጭቶችን በአካል ሳይከሰቱ በድርድር መፍትሔ ይፈለግላቸዋል፤ ከተከሰቱም በኋላ በአጭሩ ለመቅጨት ፈጣን መፍትሔ ለመፈለግ ዴሞክራሲ ያስችላል።

በጣም ስኬታማ የሚባሉት አገሮች ውስጥ ልዩነቶቻቸውን በዴሞክራሲያዊ ስርዓት አቻችለው ኖረዋል፤ እኛም እንችላለን!

ሐሳብ እና አመፅ

“እመፅ ማነሳሳት” እና “የጥላቻ ንግግር” የሚባሉ ችግሮች አሉ። ነገር ግን ብዙዎች ቃላቱን የሚጠቀሙባቸው የማይፈልጉትን ሐሳብ ለማፈን ሲሆን ብቻ ነው። በመሠረቱ ዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች ላይ ሐሳብን የመግለፅ ነፃነት እንዲከበር ቁርጠኛ አቋም የተወሰደበት አንዱ ምክንያት ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት “አመፅ” እና “ለውጥ” መካከል ሚዛን መፍጠር ስለሚችል ነው። ሐሳባቸውን በነፃነት እንዲገልፁ ያልተፈቀደላቸው ሰዎች በአመፅ ያደርጉታል። እንዲናገሩት ሲፈቀድላቸው ግን የሚጋጩ ፍላጎቶቻቸውን ሳይቀር ማስታረቂያ መንገድ በመነጋገር ይፈልጋሉ።

በአገራችን መደራጀትም ይሁን ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ታፍነው መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህ በእንዲህ እያለ የማኅበራዊ ሚድያ መከሰት ተናደው መድረክ ያጡትንም፣ የተስማሙ የሚመስላቸውንም የሚጋጩትንም በአንድ ግንባር አገናኛቸው። በዚህ መሐል ጎራ ለይተው በሐሳብ መቆሳሰላቸው የሚጠበቅ ነው። መሬት ላይ ለመግባባት መነጋገርን፣ የዜግነት መብት እና ግዴታዎችን ማወቅ እና ማክበርን የሚያስተምሩ ሲቪል ማኅበራት ቢያብቡ ኖሮ፥ ሐሳቦች በየጉዳዩ ላይ ዕውቀት ካላቸው ሰዎች አንደበት ተቀብለው የሚያንሸራሽሩ ሚድያዎች ቢያብቡ ኖሮ፥ ዛሬ አላዋቂዎች ባሻቸው ጉዳይ ላይ ደፋር ተንታኝ ሆነው ብዙ ተከታይ እና አድማጭ አያፈሩም ነበር። ለዚህ ያበቃን አምባገነንነት እንጂ ዴሞክራሲ አይደለም።

አሁንም ቢሆን መፍትሔው ማዕቀብ አይደለም፤ ነፃነት ነው። ሁሉም ሰዎች በነፃነት በተነጋገሩ ቁጥር አሸናፊ ሐሳቦች እየተንጓለሉ ይወጣሉ። “እውነት ለሐሰትም ሳይቀር ምስክር ነች” እንደሚባለው፥ የሚዋሹት እውነት በሚናገሩት ይጋለጣሉ፤ ጥላቻ የሚሰብኩት ፍቅር በሚሰብኩት ይሸነፋሉ።

መፍትሔው በሰው ልጅ ማመን ነው

አምባገነናዊነት እና ዴሞክራሲያዊነት በሰው ልጆች ላይ ያለን እምነት መገለጫዎች ናቸው ብዬ አምናለሁ። አምባገነን ስንሆን ሰዎች መጥፎዎች ናቸው። ቁጥጥር፣ እገዳ እና ቅጣት ያስፈልጋቸዋል ብለን እናምናለን። ዴሞክራት ስንሆን ደግሞ በተቃራኒው በሰው ልጆች ቀናነት እምነት ይኖረናል። ሰዎች ሲያጠፉ እንኳን ለክፋት ወይም ክፉ በመሆን ሳይሆን በመሳሳት ነው ያደረጉት ብለን እናምናለን። ስለዚህ ዴሞክራት ስንሆን ለሰዎች ነፃነት፣ ከኃላፊነት እና ተጠያቂነት ጋር እናጎናፅፋለን።

በዴሞክራሲ ተስፋ ቆረጥን ማለት በሰው ልጆች ተስፋ ቆረጥን ማለት ነው።

የኢትዮጵያ ሥርወ መንግሥት መነሻ ማዕከሉ (core state የሚሉት) ሰሜን ላይ ነበር – አክሱም። ቀስ በቀስ ወደ ደቡብ እያፈገፈገ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ላይ ሸዋ ላይ ከትሞ እስከ ዛሬ ዘልቋል። ‘የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ’ በአሁኑ ቅርፅዋ የተሠራችው በ19ኛው ክፍለዘመን ማገባደጃ ነው። ከዛሬዪቱ ኢትዮጵያ በፊት የነበረችው ‘ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ’ ነች። ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ የዓለማችን ጥንታዊ አገራት ሁሉ፣ ድንበር አልነበራትም – የተፅዕኖ አድማስ እንጂ።  የተፅዕኖ አድማሷ ደግሞ እንደ ጊዜው እና እንደ ነጋሹ አቅም ሲሰፋና ሲጠብ ነው የከረመው።


ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ የአማርኛ ተናጋሪዎች እና የትግርኛ ተናጋሪዎች በዋነኝነት የሚዘውሯት ነበረች። በተለይ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ወዲህ ያለችው ኢትዮጵያ በሁለቱ ፉክክር እና ማመቻመች (compromise) ነበር የቆመችው። ዳግማዊ ምኒልክ ደቡቡን እና ምሥራቁን የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ አካል ባደረጉበት ወቅት ግን በቁጥር ከትግርኛ ተናጋሪዎቹ እና ከአማርኛ ተናጋሪዎቹ የሚበልጡ ኦሮሞዎች የአገረ መንግሥቱ አካል በመሆናቸው፥ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በፊት ከነበራቸው ተቀናቃኝነት የበለጠ ኃይል አግኝተዋል። ይህ ክስተት ኢትዮጵያን ሦስተኛ የሥልጣን ተፎካካሪ እንድታገኝ አድርጓታል። (ይህ ማለት ግን ከዚያ በፊት ኦሮሞዎች የአገረ መንግሥቱ አካል አልነበሩም ማለት አይደለም፤ ሸዋ ቀድሞውንም ቅይጥ ከመሆኑም ባሻገር፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ‘ታላቁ የኦሮሞ ፍልሰት’ የኦሮምኛ ተናጋሪዎች ሰሜኑን የኢትዮጵያ ክፍል ተቀላቅለዋል። ይህም የወሎና የጁ ኦሮሞ ፖለቲከኞችን አፍርቷል። በዘመን ወደኋላ በነጎድን ቁጥር ታሪኩ ይለዋወጣል፤ ስለዚህ ርቀን ባንሔድ ጥሩ ነው። የዚህ ጽሑፍ ዓላማም ዛሬን በሚጫኑ የቅርብ ጊዜ ታሪካዊ መቀናቀኖች ላይ ማተኮር ብቻ ነው። እንዲያውም ትግራይን ከተፎካካሪ ሕዝቦች የነጠሉ የታሪክ ኩነቶችን መለየት ነው።)

የኤርትራ (ባሕር ምላሸ) የጣልያን ቅኝ ግዛት መሆን የትግራዋዩን ቁጥር በግማሽ ቢቀንሰውም ትግራይ የመንግሥት መነሻ ማዕከል በመነበሯ ምክንያት የመሐል አገር የሥልጣን ፉክክሩ ውስጥ ተፅዕኖዋ ሳይቀንስ ከርሟል። በዳግማይ ምኒልክ ሰዐት ትልቁ ኃይል እና ሥልጣን ሸዋ ላይ ተከማችቶ የነበረ ቢሆንም፣ ትግራይ እና ደቡቡም በየአካባቢ ንጉሡ የተወሰነ ነጻነት ነበረው። በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (ቀኃሥ) ግዜ ግን የአካባቢ ነገሥታት ሁሉ ከስመው ማዕከላዊነት ሰፈነ። ቀኃሥ የሥልጣን መስህቡን ሁሉ አዲስ አበባ ላይ – በመዳፋቸው ሥር አኖሩት።

ደርግም የቀጠለበት ይህንኑ የቀኃሥ እጅግ የተማከለ መንግሥታዊ ስርዓት ነው። ኢሕአዴግ ሲመጣ ምንም እንኳን በፌዴራል ስርዓት የማዕከላዊ መንግሥቱን ሥልጣን በሕግ (de jure) ለክልሎች ቢያከፋፍልም በተግባር (de facto) ትልቁ ሥልጣን ግን በማዕከላዊ መንግሥቱ ቁጥጥር ሥር ነበር። የኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በእጅ አዙር የሥልጣኑን ቁጥጥር ለኢሕአዴግ ፈላጭ ቆራጮቹ ትሕነግኦች (TPLFs) ስላጎናፀፈ መቐለን ከአራት ኪሎ ያላነሰ ባለ ሥልጣን አድርጓት ነበር።


የትግራይ ፖለቲከኞች የማዕከላዊ ፖለቲካውን ለመቆጣጠር ባደረጉት ትግል፥ የኤርትራ ትግራዋዮች ድጋፍ አስፈልጓቸው ነበር። ይሁን እንጂ የትሕነግ ፖለቲካ ቢያንስ በሕግ ደረጃ ክልሎችን የሚያጠናክር በመሆኑ መልሶ ራሱን በልቶታል። ቀድሞ ያልነበሩ የኦሮምያ እና የአማራ ክልሎች ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት የራሳቸው መንግሥታዊ መዋቅር፣ የራሳቸውን የፀጥታ ኃይል እና አስተዳደራዊ መዋቅሮች ዘርግተው አንድ ትውልድ ሲያሳልፉ የሕዝብ ቁጥራቸውን የሚያክል ጥያቄ ይዘው ተነሱ። የትሕነግ ሰዎች የፌዴራሊዝሙን ፅንሰ ሐሳብ ሲነድፉ ወቅታዊ የበላይነታቸውን እንጂ ዘላቂ ውጤቱን የጠረጠሩ አይመስለኝም። አሁን ወደ ዳር የመገፋታቸውን ውጤት መቀበል ሲያዳግታቸው በማየቴ ይህንን አልኩ እንጂ፥ ምናልባት ሲጀምሩት አግባብ ነው ብለው አምነውበትም ሊሆን ይችላል። የሆነ ሆኖ አሁን በግልጽ እንደምናስተውለው የኦሮሞ እና አማራ ጥምረት የመንግሥትን ሥልጣን ተቆናጥጧል። ይህንን መቀልበስ የሚችል ኃይል በቅርብ ግዜ የሚመጣ አይመስለኝም።

የታሪካዊቷ ኢትዮጵያ ግዛተ ዐፄ ከተመሠረተበት ግዜ ጀምሮ አሸናፊው ተሸናፊውን እየዋጠ እዚህ የደረሰው የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት፥ አሁን አዲስ ምዕራፍ ላይ ነው። በዶናልድ ሌቪን አገላለጽ በአማራው አንብሮ (thesis) እና በኦሮሞው ተፃርሮ (anti-thesis) የተገነባችው ‘ታላቋ ኢትዮጵያ’ (የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ብዬ ነው እኔ የምረዳው) የወትሮ የሥልጣን ተቀናቃኞቹን (የትግርኛ ተናጋሪዎቹን) ከማዕከላዊው መንግሥት ገለል አድርጎ፣ ተረኛ እና ዋነኛ ዘዋሪዎቹ ሁለቱ ድምር ብዙኃን፣ ማለትም የኦሮምኛ እና የአማርኛ ተናጋሪዎችን አንግሧል። ይህ ለጊዜው ቢጨናገፍ እንኳን ለአገራዊ ቀውስ እና አለመረጋጋት ይዳርጋል እንጂ አይፀናም።

የትግራይ ፖለቲካ የዳር አገር ፖለቲካ የሆነው በሚከተሉት ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው፦ አንደኛ የመናገሻ ከተማው ከትግራይ ተነቅሎ ወደ ደቡብ በመጓዝ በመጨረሻ ሸዋ ላይ መፅናቱ ጂኦግራፊያዊ ፋይዳዋን በመቀነሱ፣ ሁለተኛ የኤርትራ ቅኝ መገዛት የትግርኛ ተናጋሪውን ሕዝብ ቁጥር መቀነሱ እና ሦስተኛ በፌዴራሊዝሙ የኦሮምኛ ተናጋሪ እና የአማርኛ ተናጋሪ የተከፋፈሉ ክፍለ አገሮች ተቀላቅለው ብዙ ሕዝብ የያዙ (እና መደራደሪያ የሆናቸው) ክልሎች መፈጠራቸው ናቸው። እዚህ እንደምናየው በትግራይ ወደዳር መገፋት የትሕነግ ፖለቲካ የመጨረሻውን መዋጮ ማድረጉን ነው።

አሁን በሕዝብ ብዛት ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሶማሊዎች ናቸው። እንደምናስተውለው የሶማሊ ፖለቲካ ከጊዜ ወደጊዜ መደ መሐል (mainstream) እየመጣ ነው። በተቃራኒው የትግራይ ፖለቲካ ከመሐል ወደ ዳር (periphery) እያፈገፈገ ነው። ስለዚህ በመጪዎቹ ሁለት እና ሦስት ዐሥርት ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የትግርኛ ተናጋሪዎች የፖለቲካ ተፅዕኖ እየቀነሰ የመሔድ ዕድሉ በጣም ሰፊ ነው፤ ከትግርኛ ተናጋሪዎች ይልቅ ሶማሊኛ ተናጋሪዎች ወደ መሐል ይቀርባሉ። ከዚህ በኋላ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በኢትዮጵያ የሚሰፍን ከሆነ በብዙኃን አመራር (majority rule) መርሕ ትልቁን ሥልጣን የሚቆጣጠሩት የኦሮምኛ ተናጋሪዎች እና የአማርኛ ተናጋሪዎች ጥምረት ነው። ይህ የፌዴራል ስርዓቱ ቅርፅ ቢቀያየርም እንኳን በተለየ መልኩም ቢሆን መቀጠሉ አይቀርም።

በሌላ በኩል፣ የኦሮምኛ እና የአማርኛ ተናጋሪዎቹ አንድ ጥምረት ለመመሥረት መስማማት ቢያቅታቸውም የመጨረሻዎቹ ሁለት ግንባሮች (frontiers) እነርሱ በመሆናቸው የዳር አገር አጋር በማፍራት በፈረቃ ጉልህ (dominant) ድርሻ እየተወጡ ይቀጥላሉ። ከሁለቱ መሐል ያልወጡ ቡድኖች ሥልጣን የሚቆጣጠሩበት እጅግ ጠባብ ዕድል ቢኖርም፥ የሁለቱን ሕዝቦች ፍላጎት እና ጥያቄ በማስተናገድ ይጠመዳሉ። የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ዕጣ ፈንታ ግን የሁለቱ ሕዝቦች ፍላጎት እና ውሳኔ ወዲያ ወዲህ እያላጋው ለረዥም ግዜ መጓዙ አይቀርም።

የእነዚህ ሁለት ክፈለ ዘመናት ፖለቲካዊ ሒደት በአሁኑ የኢትዮጵያ የሽግግር ፖለቲካ ተስተውሏል። የትግራይ ፖለቲከኞች የወታደራዊ አቅማቸውም ይሁን በተለያዩ ማስፈራሪያዎች የሁለቱን ብዙኃን ጥምረት ማሸነፍ አልተቻላቸውም። ለዚህ የትግራይ ፖለቲከኞች ሽንፈት የትሕነግ ራስን በራስ የሚያጠፋ ፖለቲካ የመጨረሻውን በትር አሳርፏል። ይህንን እውነት በመጋፈጥ የትግራይ ፖለቲካኞች ነባሩን የመሐል ፖለቲከኛ አጨዋወታቸውን በመቀየር የዳር አገር ፖለቲካ መጫወት ይኖርባቸዋል።

በዚህ ርዕስ ረዥም መጣጥፍ መጻፍ ከጀመርኩ ረዥም ግዜ ሆነኝ፡፡ እስካሁን አላለቀም፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፤ ጉዳዩ ስሜት የሚነካ እና በስሜት የሚነዳ ስለሆነ ፈርቼው ነው፡፡ የፖለቲካ ተዋስኦዋችንን በተከታተልኩት ቁጥር የተረዳሁት አንድ ነገር ቢኖር “ብሔርተኛ ነኝ” በሚሉ እና “ብሔርተኛ አይደለሁም” በሚሉት ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት ብሔርተኝነትን የማመን እና የመሸሸግ ችሎታ ልዩነት ነው፡፡ ወይም ደግሞ አንዳንዴ ልዩነቱ ግለሰቦቹ የሚያራምዱት ብሔርተኝነት የሚያቅፋቸው ሰዎች ቁጥር የበዛ መሆኑ ‹ብሔርተኝነቱን› የመሸሸግ ዕድል ያገኛል፡፡ በጣም በተሳሳተ መደምደሚያ ላለመጀመር ያክል “ብሔርተኝነት” ደረጃው እና ልኩ ይለያይ ይሆናል እንጂ ሙሉ ለሙሉ ከውስጡ የወጣለት ሰው የማግኘት ዕድላችን ጠባብ ነው ብለን እንስማማ፡፡ የሆነ ሆኖ፣ ‹ብዙኃን ብሔርተኛ ናቸው› የሚል መደምደሚያ ይዤ ነው ይህንን የምር አጭር ያልሆነ መጣጥፍ፣ ረዘመብኝ ካልኳችሁ መጣጥፌ ጨልፌ እና ጨምቄ የማስነብባችሁ፡፡

የመጀመሪያው አንቀፄ እንደሚያመለክተው ‹ብዙኃን ብሔርተኞች ናቸው›፡፡ ‹ብሔርተኝነት ቅዱስ ነው ወይስ እርኩስ?› የሚል ጥያቄ ማንሳት ‹ብዙኃን ቅዱስ ናቸው ወይስ እርኩስ?› የሚል ጥያቄ እንደማንሳት ያስፈራል፡፡ ቢሆንም እንጋፈጠዋለን።

ብሔርተኝነት ሲበየን

ብዙዎቹ ዓለም ዐቀፍ ዩንቨርስቲዎች ውስጥ ያሉ ምሁራን ለብሔርተኝነት ያላቸው ንቀት የትየለሌ ነው፡፡ ንቀቱ አንድም ብሔርተኝነት ‹ማኅበራዊ ፈጠራ› (social fabrication) ነው ከሚል የመነጨ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የሰው ልጅን ያክል ባለ ብሩሕ አእምሮ በአጋጣሚ በበቀለበት ማኅበረሰብ ብቻ መበየን ከእውነታው የራቀ ስለሚሆን ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የብሔርተኝነት የመዝገበ ቃላት ፍቺው “ተመሳሳይ ባሕል ያላቸው ሕዝቦች ፖለቲካዊ ነጻነት መፈለግ” ወይም “በአገር በጣም የመኩራት ስሜት” ነው (P.H. Collin (2014))፡፡

ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ ብሔርተኝነትን የሚበይነው እኔንም በሚያስማማ መልኩ ነው፡- “የአንድ ግለሰብ ታማኝነት እና ቁርጠኝነት ከሌሎች ግለሰቦች እና ቡድኖች ፍላጎት በላይ ለብሔረ-መንግሥቱ (nation state) ማድላት ላይ የተመሠረተ ርዕዮተዓለም ነው”። በዚህ መሠረት ቀጣዮቹን ርዕሰ ጉዳዮች እያነሳን እንጥላለን፡፡

ሰዎች ለምን ብሔርተኛ ይሆናሉ?

ለዚህ ጥያቄ ቀላል መልስ እሰጣለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች ብሔርተኛ የሚሆኑት ፈቅደው እና አቅደው ሳይሆን ባጋጣሚ ነው፡፡ አጋጣሚው የሚጀምረው ‹የት እና ከማን ተወለዱ?› ከሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ሰዎች ብሔርተኝነትን በንባብ እና በውይይት ሊያዳብሩት ይችላሉ እንጂ የሚጀምሩት ግን በውርስ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ብሔርተኝነት ራሳቸውን በአንድ የብሔር አባልነት የሚጠሩ ሰዎች እስኪኖሩ ድረስ አይኖርም፡፡ የሆኑ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ እና የሚያስተሳስራቸው ማኅበራዊ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን በአንድ ማንነት ለይተው መጥራት ሲጀምሩ ወይም በሌሎች በዚያ ማንነት መጠራት ሲጀምሩ ብሔርተኝነት ተጀመረ ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ብሔርተኝነት በስሎ እና ጎርምቶ የሚወጣው እነዚያ ሰዎች ራሳቸውን ከሌሎች የተሻሉ እንደሆኑ ሲያስቡ፣ እና/ወይም በማንነታቸው ሳቢያ በሌሎች እየተጠቁ እንደሆኑ ሲያስቡ ነው፡፡ ብሔርተኝነት የሚጎመራው የጋራ ማንነት ላይ ጥቃት ያደርሳሉ ተብለው የሚታሰቡ የተለየ ማንነት እንዳላቸው የሚታመኑ ጠላቶች ሲኖሩ ነው፡፡

ከዚህ ውጪ ግን ብሔርተኞች በብሔርተኝነታቸው (ምርጫ) ውስጥ ጥቅማቸውን ሳይታወቃቸውም ቢሆን ያሰላሉ፡፡ ብዙ ግዜ ተጠቃሚ ከሚያደርጋቸው ስብስብ ውጪ በሆነ ብሔርተኝነት ውስጥ የታቀፉ ብሔርተኞችን አናገኝም፡፡ በርግጥ በዓለም ዙሪያ ሥር የሰደደ “የብሔርተኞች አምባገነንነት” አለ። የአንድ ዘውግ/ብሔር ብሔርተኞች በሚበዙበት አካባቢ ሌሎች ድምፆች ሁሉ ስለሚደቆሱ ፀጥ ይላሉ። ሆኖም ሰዎች የሚመርጡት የብሔርተኝነት ስብስብ የበለጠ የሚጠቅማቸውን ስብስብ ነው። ስለዚህ ሌላኛው ሰዎች ለምን ብሔርተኛ ይሆናሉ ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሆነው በውስጡ የሚያፈሩት ጥቅም ስላለ ነው ማለት ይቻላል፡፡

‹ብሔርተኝነት› ወ ‹አርበኝነት›

ብሔርተኝነትን የሚጠየፉ ትርክቶች ድምፅ እያገኙ ሲመጡ ራሳቸውን በአርበኝነት የሚገልጹ ሰዎች እየታዩ ነው፡፡ የሜርየም ዌብስተር መዝገበ ቃላት አርበኝነት “ከብሔርተኝነት ጋር እንደ አንድ የሚቆጠር ነገር ግን አንድ ያልሆነ ፅንሰ ሐሳብ ነው” ይላል። ብዙዎቹ የአገር ፍቅር (አርበኝነት) በብሔርተኝነት ሊቆጠር አይገባውም ብለው የሚያስቡ ጸሐፍት ‘አርበኝነት ከትውልድ ቀዬ፣ አካባቢ ወይም ስፍራ፣ ሕዝብ፣ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ፖለቲካ፣ ባሕል እና ወግ ጋር ያለ ስሜታዊ ትስስር የሚፈጥረው ተቆርቋሪ-ተከላካይነት ነው። አርበኝነት የወገኔን ጥቅም አላስነካም ባይነት ነው’ ይላሉ። ‘ብሔርተኝነት ማለት ምናልባትም አርበኝነት ልኩን ሲያልፍ ነው’ የሚሉም አሉ። ሲድኒ ጄ. ሀሪስ የተባለ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ‘Strictly Personal Prijudices’ በተሰኘ መጽሐፉ የተጠቀመው አገላለጽ የብዙዎቹን ንፅፅር ለማጠቃለል ይረዳል፡- “በአርበኝነት እና በብሔርተኝነት መካከል ያለው ልዩነት፣ አርበኛ አገሩ በምታደርገው ነገር ሲኮራ፣ ብሔርተኛ ግን አገሩ ምንም ብታደርግ ምን የሚኮራባት ነው፤ የመጀመሪያው የኃላፊነት ስሜት ሲፈጥር፥ የኋለኛው ግን ወደ ጦርነት የሚነዳ ጭፍን ትዕቢት ነው” ብሏል።

ነገር ግን ብሔርተኝነትን ከአርበኝነት ጋር ለይተው የማይመለከቱትም አሉ። ለምሳሌ ከፈረንሳዩ አብዮት ቀድሞ በጽሑፍ ዓለም አብዮቱን የለኮሰው ቮልቴር: “አንድ ሰው የአንዱ ጥሩ አርበኛ ለመሆን የቀሪው ሰው ዘር በሙሉ ጠላት መሆን ያለበት መሆኑ የሚያሳዝን ነገር ነው” ማለቱ ተጠቅሷል።

‹ኅብረ-ብሔርተኝነት› ወ ‹ዘውጌ-ብሔርተኝነት›

ብሔርተኝነት ብዙ ግዜ ቋንቋ እና/ወይም ሃይማኖትን ነው መሠረት የሚያደርገው፤ በእርግጥ ብዙ ጊዜ አንዱ በሌላው ይሸፈናል፡፡ ሆኖም ሌሎችም ብሔርተኝነቶች አሉ፡፡ ዶ/ር ተሻለ ጥበቡ የብሔርተኝነት ዓይነቶችን በአምስት ይከፍሏቸዋል፤ 1ኛ – የዘውግ (በተለይ ቋንቋን መሠረት ያደረገ) ብሔርተኝነት፣ 2ኛ – የኅብረት ብሔርተኝነት (ለምሳሌ በአፍሪካዊነት፣ በአረብነት…)፣ 3ኛ – የአገረ-መንግሥት ብሔርተኝነት (በአንድ አገር ዜግነት ላይ የተመሠረተ)፣ 4ኛ – የሃይማኖት ብሔርተኝነት (ለምሳሌ የእስልምና፣ የሂንዱ፣ የክርስትና…) እና 5ኛ – የአካባቢ ብሔርተኝነት ናቸው (ለምሳሌ የሸዋ፣ የሐረርጌ ብሔርተኝነት…)፡፡ በነዚህ የተለያዩ ብሔርተኝነቶች ውስጥ ግልጽ መሥመር የለም ስለዚህ አንዱ ከሌሎቹ በግልጽ አይለዩም፡፡ ከዚያም በላይ ሁሉንም ዓይነት ባሕሪ ያላቸው ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ግን በይበልጥ የሚታወቁት ሁለቱ ናቸው – የዘውጌ እና የኅብረት ብሔርተኝነት (pan-ethiopia nationalism፡ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት)፡፡

ኢትዮጵያዊነትነት እንደዘር የሚቆጥሩት ብሔርተኞች አሉ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን እንደዜግነት ብቻ የሚቆጥሩት አሉ – ለነርሱ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት የአገረ-መንግሥት ብሔርተኝነት ብለው ነው የሚቆጥሩት – በዜግነት ብቻ የሚገኝ ብሔርተኝነት አድርገው፡፡ ይህ ግን ለሌሎች ገና መዳረሻ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት የውጭ ጠላቶችን (ግብጽ፣ ቱርክ፣ ጣልያን፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ (ከተገነጠለች በኋላ)…) እና የውስጥ ጠላቶችን (የኤርትራ ብሔርተኝነት (ከመገንጠሏ በፊት)፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነት፣ የኦጋዴን ብሔርተኝነት…) ማሰባሰቢያ መሣሪያ ያደርጋል፡፡ የዘውጌ ብሔርተኝነቶች ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነትን እንደጠላት መዝግበው፣ እንደጨቋኝ ይታገሉታል፡፡ ምክንያቱም የአንዱ መጠንከር የሌላውን ያቀጭጫል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ጎልቶ መውጣት፣ የዘውጌ ብሔርተኝነቶችን ያዳክማል፤ በተቃራኒውም የዘውጌ ብሔርተኝነቶች ጎልቶ መውጣት የኢትዮጵያ ብሔርተኝነቶችን ያዳክማል፡፡ ይህ በዐቃፊው እና ንዑስ ስብስቦቹ አማካይነት የተፈጠሩ ብሔርተኝነቶች መካከል የተፈጠረው ተቀናቃኝነት መንስዔው ዐቃፊው ብሔርተኛ መሠረቱን በዘውጌ ዓይን መመልከቱ ነው። የዘውጌ ብሔርተኞች የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ንዑስ ስብስብ መሆን ሲገባቸወ፥ ፈፅሞ የማይቀላቀሉ (mutually exclusive) ናቸው የሚሉ አሉ።

በርግጥ የዘውጌ ብሔርተኞች እርስበርሳቸውም ይቀናቀናሉ፤ አንዳቸው ሌላኛቸውን በጠላትነት ይመድባሉ፡፡ ለምሳሌ የአማራ ብሔርተኞች እና የትግራይ ብሔርተኞች ዓይንና ናጫ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የኦሮሞ ብሔርተኞች ከሌሎች ዘውጌ ብሔርተኞች ጋር ያላቸው ቅራኔ ከኢትዮጵያ ብሔርተኞች ጋር ያላቸው ቅራኔ አይበልጥም፡፡   

‹ዘር› ወ ‹ዜግነት› ወ ‹ማንነት

‹ዘር› ለሚለው ቃል ብያኔ ለመፈለግ መሞከር በራሱ ‹ዘረኝነት› ነው ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ከዚያም በታች ለመውረድ ስለሚቻል አያስፈራኝም፡፡ የአንድ ዘር ሰዎች በጥቅሉ የቆዳ ቀለም እና የፊት ቅርፅ ተመሳሳይነት ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን እንደ ዘር የሚቆጥሩ ሰዎች የኢትዮጵያ ሶማሊ ከሶማሊ ሪፐብሊክ ሰዎች ጋር፣ የኢትዮጵያ ኑዌሮች ከሱዳን ኑዌሮች፣ የቦረና ኦሮሞዎች ከኬንያ ቦረናዎች፣ የኢትዮጵያ ትግራዋዮች ከኤርትራ ትግራዋዮች ጋር ልዩነት እንደሌላቸው ይዘነጉታል፡፡ ይህንን አልኩኝ እንጂ ሶማሊ ከአማራ ጋር ያለው ልዩነት ራሱ በዓይን የሚለይ አይደለም፡፡ የሆነ ሆኖ ዘር ሰፊ የሰዎች ስብስብ የያዘ ስለሆነ ከኢትዮጵያዊነትም ይሰፋል፡፡

በሌላ በኩል ማንነት ተቀራራቢ ምስስሎች ላይ ተመሥርቶ የሚሰጥ ድልድል ነው፡፡ በቋንቋ (ኦሮሞ፣ ሶማሊ…)፣ በመኖሪያ አካባቢ (ጎጃሜ፣ አዲስ አበቤ…)፣ በሃይማኖት (ሙስሊም፣ ክርስቲያን…)፣ በሙያ (መሐንዲስ፣ ጋዜጠኛ…)፣ እና ወዘተ. አንድ አገር ወይም ዘውግ የእነዚህ ሁሉ ቅይጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ዜግነት የተሻለ አስታራቂ ይሆናል፡፡ ዜግነት በተለየ ድንበር ውስጥ የሚኖሩና በተለየ የሕግ ድንጋጌ የሚተዳደሩ ዜጎችን በሙሉ የሚያሰባስብ ማንነት ነው፡፡ ዜግነት ኢትዮጵያዊነትን ለመበየን ጤናማ መንገድ ነው፡፡  

‹ዘውጌ/ኅብረ-ብሔርተኝነት› ወ ‹የዜግነት ብሔርተኝነት›

ኢትዮጵያን እንደ አንድ ብሔር/ዘር የሚመለከቱ ሰዎች አሉ፡፡ እንደብሔር ስብስቦች የሚያዩ ሰዎችም አሉ፡፡ አሁን የሚበዙት እንደብሔር ስብስብ የሚመለከቷት ሰዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ኅብረ-ብሔራዊ ስብስብ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች የሚመለከቱበት ዓይን ዘውጌ ስለሆነ ኢትዮጵያዊነትን ለመግለጽ ሁሉም ባይቻልም፣ ብዙዎቹ የተሳተፉባቸውን ታሪካዊ ኩነቶች በማጉላት፣ ብዙዎቹን ቋንቋዎችንና ባሕሎችን በመዘርዘር ወዘተ ሲደክሙ ይስተዋላል፡፡ የኮታ ማሟላት እና በየኩነቱ ላይ ያንንም፣ ያቺንም ለመወከል ይፍጨረጨራሉ፤ መቼም ሙሉ ለሙሉ አይሳካላቸውም፡፡ ምክንያቱም አስተሳሰቡ ዘውጌ/ዘር ተኮር ነው፡፡ አመለካከቱ የብሔርተኝነት ነው፡፡

የዜግነት ብሔርተኝነት ከዚህ የተሻለ የሚሆነው ለዜጎች ሁሉ የዕኩል ዕድል እና ውክልና መንገዶችን በሕግ በመደንገግ እና ይህንን ሕጋዊ ድንጋጌ በማስከበር ይበየናል፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ አማርኛ ቋንቋ አንዱ የሥራ ቋንቋ የሆነበት ምክንያት የዜግነት ብሔርተኝታቸው በሕግ የበላይነት ስለተከበረ ነው፡፡ የቋንቋ ልዩነት እና የውክልና ጉዳይ ገና አጀንዳ ከመሆኑ በፊት እንዲቀጭ የሚያደርግ የዕኩል ዕድል እና ውክልና መንገዶች ከተረጋገጡ ከላይ ያየናቸው ፈተናዎች አይመጡም፡፡

ልዩነቱን ለማሳየት ሪቻርድ ሒል የተባሉ የሚቺጋን ስቴት ዩንቨርስቲ ፕሮፌሰር የሁለቱን (የዘውግ እና የዜግነት ብሔርተኝነቶች) ልዩነት እንደሚከተለው ያስቀምጡታል፡- “የዘውግ ብሔርተኝነት መሠረቱ “ደም” ቆጠራ ነው፤ በደም የተቆጠሩት ሕዝቦች አገረ-መንግሥት ይኖራቸዋል፡፡ የዜግነት ብሔርተኝነት ግን መሠረቱ ሕጋዊ ዜግነት ነው፤ አገረ-መንግሥቱ ለዜጎቹ አገር ይሆንላቸዋል፡፡ […] ምንም እንኳን የወል ዘውግ መኖሩ የአንድን ዘውግ ሰዎች በሌሎች ላይ እንዲተባበሩ ቢረዳቸውም፣ ሌሎች የዘውግ፣ የመደብ፣ የሥርዓተ ፆታ፣ እና ሌሎችም ክፍፍሎች ላይ የተመሠረተውን ልዩነታቸውን እንዲያስታርቁ ሊረዳቸው ግን አይችልም፡፡ የዜግነት ብሔርተኝነት የሕግ እና ፖለቲካ ተሳትፎ ዕድሎችን በማመቻቸት ተፎካካሪ ቅሬታዎች/ፍላጎቶችን ለማመጣጠን ይረዳል፡፡ የዘውግ ብሔርተኝነትን ሊፎካከረው የሚችለው ብቸኛው አማራጭ ደግሞ የዜግነት ብሔርተኝነት ነው፡፡ ምክንያቱም የተለያዩ የዘውግ ቡድኖች ጎን ለጎን፣ በሠላም እና በመተማመን ሊኖሩ የሚችሉት ጠንካራ፣ ርትዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውክልና ለሁሉም ማቅረብ የሚችል አገረ-መንግሥት ሲኖር ነው፡፡”

የብሔርተኞች ባሕርያት

ጆርጅ ኦርዌል ሦስት የብሔርተኛ ሰዎችን ፀባይ ለመለየት ሞክሯል፡፡ የአንድን ሰው ወይም ቡድን ብሔርተኛ ስሜት ለመገምገም በእነዚህ ሦስት ፀባዮች ብቻ መለካት በቂ ነው፡፡ 1ኛው – ሌላ ያለማሰብ አባዜ (obsession) ነው፡፡ ብሔርተኞች ከራሳቸው ቡድን የበላይነት ጉዳይ በቀር ሌላ ነገር ማሰብ አይችሉም፡፡ 2ኛው – በአንድ አቋም አለመፅናት (instablility) ነው፡፡ ብሔርተኞች ዛሬ የያዙት አቋም ነገ ላይኖር ይችላል፡፡ ታማኝነታቸው ለብሔርተኝነቱ እንጂ ለርዕዮተዓለሞች አይደለም፡፡ 3ኛው – ለሐቅ አለመጨነቅ (indifference to facts) ነው፡፡ በብሔርተኝነት ዓይን ድርጊቶች የሚገመገሙት ማን አደረጋቸው በሚለው እንጂ ምን ተደረገ በሚለው አይደለም፡፡

እነዚህ እና ከላይ ያየናቸው ነገሮች በሙሉ የሚያሳዩን ምንድን ነው? የብሔርተኝነትን ቅድስና ወይስ ርክሰት?

ቅድስና የጥቂቶች ነው!

ሰዎች ከራሳቸው ዕኩል ሌሎችን ሊወዱ ይችላሉ የሚለው እምብዛም አሳማኝ አይደለም፡፡ ሰዎች የሌሎችን ልጆች ከራሳቸው ልጆች ዕኩል የመቀበላቸው ነገርም እንደዚያው ነው፡፡ ሰዎች የሚከተሉትን እምነት ከሌሎች የተሻለ እና ምናልባትም እውነተኛ ነው ብለው ይገምታሉ፡፡ ብሔርተኝነትም እንደዚያው ነው፡፡ ሰዎች እነርሱ የተወለዱበትን ማኅበረሰብ፣ የሚከተሉትን እምነት እና አስተሳሰብ የሚያራምደውን ቡድን እንደትክክለኛ ሌላውን እንደተሳሳተ መቁጠራቸው የሚወልደው ነገር ነው – ብሔርተኝነት፡፡ ጥቂቶች ግን በዚህ ታጥረው አይቀሩም፡፡ የታሰሩበትን የውርስ ቅርፊት ሰባብረው ውጪውን ዓለም ለማየት የሚችሉ ጥቂቶች ይኖራሉ፡፡ ጥቂቶች እምነቴ የተሳሳተ ነው ብለው ሊቀይሩ የሚችሉትን ያክል ብሔርተኝነታቸውም የተሳሳተ እንደሆነ አምነው ወደ ሌላ ብሔርተኝነት የሚዘሉበት ዕድል አለ፡፡ ሁሉም እምነቶች ስህተት ናቸው ብለው ኢ-አማኒ የሚሆኑትን ያክል ሁሉም ብሔርተኝነቶች የተሳሳቱ ናቸው ብለው የሚያምኑበት ዕድል ይኖራል፡፡ ምናልባት ይህ ከብሔርተኝነት እርክሰት ወጥቶ ወደ ቅድስናው ምኩራብ መዳረሻ ይሆን ይሆናል፡፡ ችግሩ ‹ብዙኃን እዚህ ምኩራብ የሚደርሱት መቼ ነው?› የሚለው ነው፡፡ ምክንያቱም ‹ብዙኃን ይመውዑ› ይባላል – ትክክል ቢሆኑም ባይሆኑም ብዙኃን ይፈርዳሉ፡፡

ነገሮችን አቃልሎ እና ሸንሽኖ ለመረዳት መሞከር ጠቃሚ የሚሆንበት አጋጣሚ ቢኖርም፥ ሁሌም ትክክለኛ ውጤት አያስገኝም። አገርን የሚያክል ትልቅ ፅንሰ-ሐሳብ በግለሰብ ርስት ዓይን  ለመረዳት መሞከርም ከዚህ ዓይነቱ አደገኛ ስህተቶች አንዱ ነው። በኢትዮጵያ ‘እከሌ የተባለው ግዛት የማን ነው?’ እና ‘እከሌ የተባለውን ግዛት ማን ያስተዳድር?’ የሚሉት ጥያቄዎች ዐውድ በጣም አሳፋሪ እና ‘ገና በዚህ ጉዳይ እንኳ መግባባት አልቻልንም እንዴ?’ በሚል ራሳችንን እንድንታዘብ የሚያደርግ የዘወትር ገጠመኝ ነው። 
‘አዲስ አበባ የማነች?’ የሚለውን ጥያቄ ደጋግሞ መስማት አስደናቂ አይደለም። የቡድን ሥም እየጠሩ፣ ታሪክ እየደረደሩ የባለቤትነት ማስረጃ ለማምጣት የሚሞክሩትን ሰዎች መከራከሪያ ማድመጥም የከተማዋን ኅልውና ያክል አዲስ ነገር አይደለም። የዚህ ጽሑፍ መነሻም የምክትል ከንቲባዋን ሹመት ተከትሎ የዚህ ክርክር እንዳዲስ ማገርሸት ነው። አዲስ አበባ የማን ነች? እነማን ናቸው ሊያስተዳድሯት የሚገባቸው? መጀመሪያ ግን ኢትዮጵያ ራሷስ የማነች?
ኢትዮጵያ የማነች?
ቢያንስ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ኢትዮጵያ የምንላት ሕዝቧን፣ ግዛቷን፣ መንግሥቷን እና ሌሎች የዓለም መንግሥታት የሚቀበሉትን ሉዓላዊነቷን ነው። ሉዓላዊነት የአገር ፅንሰ-ሐሳብነት መገለጫ ነው። በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች” ናቸው (አንቀፅ 8)። ይህ ማለት ‘ኢትዮጵያ የኦሮሞ፣ አማራ፣ ሶማሌ፣ ትግራዋይ፣ ወዘተ የጋራ ንብረት ናት’ የሚል ትርጉም ይሰጣል። ከላይ ሲታይ ‘ኢትዮጵያ የሁሉም ናት’ የሚል ጭብጥ ያለው ይመስላል። ነገር ግን በዚህ ብያኔ እያንዳንዱ ዜጋ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለድርሻ መሆን አይችልም። ‘የኢትዮጵያ’ የሚባሉት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች አባል ያልሆነ የኢትዮጵያ ዜጋ የሉዓላዊ ሥልጣኑ ባለቤት መሆን አይችልም።
ነገሩን በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት ያክል፥ ሕገ መንግሥቱ “የውጭ አገር ዜጎች የኢትዮጵያ ዜግነት ሊያገኙ ይችላሉ” ይላል(አንቀፅ 6)። እነዚህ የኢትዮጵያ ዜግነት የተሰጣቸው የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ናቸው ወይስ አይደሉም? ባለቤት እንዲሆኑ አንዱ የኢትዮጵያ ብሔረሰብ አባል ሆነው ዜግነት መቀበል አለባቸው ማለት ነው። ይህ ደግሞ አያስኬድም፤ ምክንያቱም ሰዎች የኢትዮጵያ ዜግነትን ለመቀበል፥ የራሳቸውን የዘውግ ማንነት እንዲክዱ እና አዲስ እንዲቀበሉ ማስገደድ አይቻልም። በጥቅሉ ይህ ድክመቱ የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት ዜጎች ሁሉ የአገር ሉዓላዊ ባለቤትነት ዕኩል ድርሻ የሌላቸው በማድረግ አስገራሚ ገጽታ ያላብሰዋል። ይህ ችግር የተከሰተው ኢትዮጵያዊ ዜግነት የተመሠረተው በዜግነት መብቶች ሳይሆን በቡድን ማንነት መብቶች በመሆኑ ነው። ለዚህ ነው በዜግነት-ብሔርተኝነት (civic nationalism) የሚመራ ‘ኢትዮጵያዊነት’ መመሥረት ያልተቻለው። የሁሉም የተባለ ነገር የእያንዳንዱ የመሆን ዕድሉ አናሳ ነው። የእያንዳንዱ የሆነ ነገር ግን የሁሉም መሆን ይችላል። 
‘ኢትዮጵያ የማናት?’ የሚለው ጥያቄ ‘የእንዳንዱ/ዷ ዜጎቿ’ የሚል መልስ እስከሚያገኝ ድረስ፥ የክልሎች፣ የክፍለ ክልሎች የማንነት ጥያቄም እንዲሁ አጥጋቢ መልስ አያገኝም። ምክንያቱም የአስተሳሰብ ናሙናው አንድ ዓይነት ነው። ችግሩ አንድ አገር ባለቤት ለመሆን የሚገባቸው እና የሚመጥኑ ጥቂት የማሕበረሰብ ክፍሎች ብቻ ናቸው ብሎ ከማሰብ የሚመነጭ ነው። በርግጥ አገራት የተገነቡት በረዥም የፖለቲካ ሒደት፣ በፍጭት እና ማመቻመች ነው። ይሁን እንጂ በተለይ በዚህ ትውልድ ላይ የሚገኙ ሰዎች አገሮቻቸውን በምርጫ አላገኙም፥ በአገረ መንግሥት ግንባታው ላይም አልተሳተፉም (እንደኤርትራ ያሉትን አዳዲስ አገራት ለጊዜው እንዘንጋቸው)። እናም በዓለም የተከፋፈሉት ድንበሮች ለሠላም እና ስርዓት (order) ሲባል ዕውቅና ተሰጥቷቸው ይኖራሉ እንጂ የአንድ አገር ዜግነት ለመሆን ዘር አይመረጥም፤ ይህ በየትኛውም ዓለም ዐቀፍ ሕግ ተቀባይነት የለውም። በሕግ አግባብ ዜጋ የሆኑ ሁሉ ደግሞ የአገር ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው። ይህ በኢትዮጵያ አልተከበረም፤ በሕግም፣ በአስተሳሰብም። ስለዚህ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በተከፋፈሉት አስተዳደራዊ ክልሎች እና ክልላዊ ሕገ መንግሥታትም ተመሳሳይ ችግሮች ይስተዋላሉ። 
የክልል ሕገ መንግሥታት የክልሉ ‘መሥራቾች’ እና ‘ባለቤቶች’ የሚሏቸው ፅንሰ-ሐሳቦች አሏቸው። በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ክልሎቹ ሲመሠረቱ እና ፌዴራል ስርዓቱ ሲዘረጋ ነዋሪ የነበሩ ዜጎች ሳይቀሩ የክልሎቹ ‘መሥራቾች’ ተብለው ባለመቆጠራቸው ምክንያት የዜግነት መብቶቻቸው እንኳን አልተከበሩላቸውም። ይልቁንም ‘መጤ’ በሚል ቃል እና ‘እንግዳ’ በሚል መጠሪያ ማሸማቀቅ እና ማሳደድ እንደሞያ ተይዟል። በየቦታው በርስት እና የተፈጥሮ ሀብት ግጭት የበረከተው ግጭት፣ ዜጎችን በሕጋዊ መንገድ ከሚኖሩበት ቀዬ የማፈናቀል ደዌ የተባባሰው፥ በከፊል ዜጎች የባለቤትነት ስሜት እና በከፊሎቹ የባይተዋርነት ስሜት ነው። አገርን ወይም ክፍለ አገርን የተወሰኑ ዜጎች ርስት አድርጎ የመቁጠር አባዜ ነው፥ እኔ ከእከሌ የበለጠ ባለቤት ነኝ የሚለው አስተሳሰብ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እና በየክልሉ ሕገ መንግሥታት እንዲሁም በየግለሰቡ አእምሮ ውስጥ ተዘርቶ የበቀለው። 
አዲስ አበባን እነማን ያስተዳድሯት? 
አዲሱን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (በሙሉ የከንቲባ ሥልጣን) መሾም ተከትሎ የአዲስ አበባ ባለቤት እና አስተዳዳሪ ጉዳይ የተለመደ ሙግት አገርሽቷል። በሚያሳዝን ሁኔታ ከጥቂት የሕጋዊ አግባብነት እና የቅቡልነት ጥያቄ ካነሱት ተቺዎች በስተቀር፥ ሹመቱን የተቃወሙትም ይሁኑ የደገፉት ከላይ በተጠቀሰው የአስተሳሰብ ደዌ ተነድተው ነው ማለት ይቻላል። በተለይም ደግሞ ምክትል ከንቲባው ‘ኦሮሞ ስለሆኑ ይገባቸዋል’ እና ‘ኦሮሞ ስለሆኑ አይገባቸውም’ የሚሉት ሁለቱም አንድ ዓይነት ስህተት ሠርተዋል። 
በዚህ በኩል የአዲስ አበባን ነዋሪዎች ቁጥር በብሔር ሸንሽነው ‘አማራዎች ብዙ ነን፤ መምራት ያለብንም እኛው ነን’ ይላሉ። በወዲያ በኩል ደግሞ ‘የታሪክ ባለቤትነቱ የኦሮሞ ስለሆነ አስተዳደሩ የእኛ መሆን አለበት’ ይላሉ። እንደገና በዚያ በኩል ደግሞ ‘በታሪክ ከተባለማ ወደኋላ በተጓዝን ቁጥር የእኛ ነበር’ ይላሉ። በወዲያ በኩል ደግሞ ‘በሕገ መንግሥቱ እና በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ የእኛ ባለቤትነት ተረጋግጧል’ የሚል ክርክር ይመጣል። በዚህ ብቻ አይወሰንም፤ ‘አዲስ አበባ ተወልደው ባደጉ ‘ልጆቿ’ መመራት አለበት’ የሚሉ አሉ። በባለቤትነት እና በአስተዳዳሪነት ይገባኛል ሽሚያ ውስጥ ሙያዊ ብቃት፣ የነዋሪው ምርጫ እና ይሁንታ ከቁብ አልተጻፈም፤ ብቸኛው ቁምነገር መወለድ ብቻ ይመስላል።
‘አዲስ አበባን እነማን ያስተዳድሯት?’ በሚለው ጥያቄ ውስጥ ቁም ነገሩ መወለድ ብቻ ተደርጎ መታሰብ ካልቀረ በቀር፥ የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄም ማጨቃጨቁ አይቆምም። አዲስ አበባን የአዲስ አበባ ነዋሪ እስከሆኑ፣ የነዋሪዎቿን ቅቡልነት ባገኘ ምርጫ እስከተመረጡ ድረስ የቻይና ዘር ያለው የኢትዮጵያ ዜጋም ቢሆን፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ወይም ሱማሊ ክልል ተወልዳ ያደገችና በኋላ የአዲስ አበባ ነዋሪም የሆነችም ብትሆን መምራት ትችላለች። በመወለድ የሚገኝ የማስተዳደር መብት የለም። እንዲህ ከሆነ የአዲስ አበባ ግዜያዊ ባለቤቶች በወቅቱ ነዋሪዎቿ ይሆናሉ። 
‘ልዩ ጥቅም’ vs. ‘ባለቤትነት’
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 49/5 «የኦሮምያ ክልል፤ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብትን አጠቃቀምንና የመሳሰሉት ጉዳዮችን በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል» ይላል። ይህንን በተሳሳተ መንገድ የሚረዱት ብዙ ናቸው። 
ልዩ ጥቅሙ አዲስ አበባ በአንድ በኩል የመጠጥ ውኃ እና ሌሎችም ከአጎራባቿ የኦሮምያ ክልል አስተዳደራዊ አካባቢዎች የምታገኝ በመሆኑ፤ በሌላ በኩል ቆሻሻዎቿን የምታራግፍበት እና የበከለችውን ወንዝ የምታስወግድበት እና ሌሎችንም ጫናዎች የምታሳድርበት በመሆኑ ለጥቅሟና ጉዳቷ እንደክፍያ የሚሰጥ ጥቅም ነው እንጂ የልዩ ባለቤትነት ዐዋጅ አይደለም። ይህ ጉዳይ አዲስ አበባ የየትኛውም ክልላዊ አስተዳደር መሐል ብትገኝ ኖሮ ማድረግ የሚገባት ጉዳይ ነው። በርግጥ ልዩ ተጠቃሚዎቹ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉት አካባቢዎች ናቸው መሆን የሚኖርባቸው። የሆነ ሆኖ ያ የሚደረገው በክልሉ አማካይነት ነው። ነገር ግን ኦሮምያ የኢትዮጵያ አካል መሆኗ ቀርቶ ነፃ መንግሥት ብትሆን እንኳን የአዲስ አበባ ጊዜያዊ ባለቤቶች ነዋሪዎቿ፣ አስተዳደሮቿም የነዋሪዎቿ ምርጫዎች ናቸው የሚሆኑት። ከዚያ ውጪ ያለው ሁሉ ሕጋዊ ቅቡልነት የለውም። በሕግ ቢደነገግም ፍትሐዊ ስለማይሆን ተቀባይነት አይኖረውም።

አሁን ያለንበት ሁኔታ “ታስሮ የተፈታ ጥጃ” ሁኔታ ነው። መዝለል እና መቦረቅ – የነፃነታችንን ልክ መፈተን የምንፈልግበት ወቅት ነው። ምክንያቱም ነፃነታችን ከእስር የተፈታው ገና አሁን ነው፣ የዴሞክራሲ ባሕል አልነበረንም፣ በዚያ ላይ ያልተመለሱ እልፍ ጥያቄዎች አሉን። ይሁን እንጂ ሲደክመን እንሰክናለን። መዝለል ስለምንችል ብቻ አንዘልም። መርገጥ ስለምንችል ብቻ አንራገጥም። ያልተመለሱ ጥያቄዎችን በተደራጀ፣ በሕጋዊ እና ሠላማዊ መንገድ ታግለን ማስመለስ እንጀምራለን። ከዚያ በፊት ግን ዝላያችን እና እርግጫችን ለገዢዎቻችን የለውጡን ተስፋ ለመቀልበሻ፣ እኛን መልሶ ለመርገጫ ምክንያት እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
አንዲት ኤርትሪያዊት የትዊተር ተጠቃሚ፣ ‘ሰውያችሁ ባለ ግርማ ሞገስ እና ጥሩ ተናጋሪ በመሆኑ እንዳትሸወዱ፣ የእኛም መሪ እንደዛ በመሆኑ የለውጡን ተቋማዊነትን ሳናረጋግጥ ነው ለዚህ የተዳረግነው’ የሚል መልዕክት ለኢትዮጵያውያን አቻዎቿ አስተላልፋለች። አዎ፣ የዛሬው ታላቁ አምባገነን ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የዛሬ 27 ዓመት ገደማ በኤርትራውያን ዘንድ ታላቅ ሕዝባዊ ይሁንታ ያለው መሪ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከራሳቸው መጠበቅ” በሚለው ጽሑፌ ‘ብዙዎቹ ነጻ አውጪዎች ኋላ አምባገነን ይሆናሉ’ ማለቴን እንደ ጅምላ ድምዳሜ የወሰዱብኝ አስተያየት ሰጪዎች አሉ። እኔ ለማመልከት የፈለግኩት በአንድ ወቅት ‘ነጻ አውጪ’ የነበረ፣ ሌላ ግዜ ‘አምባገነን’ እንደማይሆን አያረጋግጥም ነው። ይህ እንዳይሆን ብቸኛው ዋስትና ‘ቁጥጥርና ሚዛን’ (check and balance) ነው። ትላንት ጓደኞቼ ስለ ኢዲ አሚን ዳዳ አንድ ጽሑፍ እያስነበቡኝ ነበር። ከዓለማችን የምንግዜም አምባገነኖች አንዱ የሆነው ኢዲ አሚን በሥልጣን አፍላው ዘመን በምዕራባውያን ሚዲያዎች ሳይቀር የተንቆለጳጰሰ ሰው ነበር። ሰውን አምባገነን የሚያደርገው ተቋማዊ ነጻነት አለመኖሩ እና የግለሰቦች ሥልጣን አለመገደቡ ነው። 
ኢትዮጵያ ለውጥ ለምን አይዋጣላትም?
ይህንን ጥያቄ ያነሳሁት አሁን ያለንበትን የለውጥ ተስፋ ጥላሸት ለመቀባት ወይም ተቀልብሷል ለማለት አይደለም። ለውጡ ከግለሰቦች በጎ ፈቃድ ወደ ተቋማዊ እውነታነት እንዲሸጋገር ካለኝ ጥልቅ ጉጉት ነው። ሁሉም ሰው የለውጡን አካሔድ በጥንቃቄ እንዲመለከተው ስለምፈልግ ነው።
ኢትዮጵያ እንዲህ የለውጥ ተስፋ ውስጥ የገባችው አሁን ብቻ አይደለም። የንጉሣዊው ስርዓት መደርመስ እና የመሬት ላራሹ መታወጅም ግዙፍ ሕዝባዊ ይሁንታ እና ተስፋ ፈንጥቆ ነበር። የምርጫ 1997 ዋዜማ አገራችን የመጀመሪያውን ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ልታካሒድ ነው በሚል ትልቅ ተስፋ
ፈንጥቆ ነበር። ሌላው ቀርቶ የደርግ መውደቅ እና በሌላ ታጣቂ መተካት ትልቅ የለውጥ ተስፋ ፈንጥቆ ነበር።
ከ’ያ ትውልድ’ ሰዎች አንዱ ገጣሚ ኃይሉ ገ/ዮሐንስ (ገሞራው) ‘ኢትዮጵያ ለውጥ የማይዋጣላት አበውን አጠያይቄ በነገሩኝ መሠረት “ተረግማ ነው”‘ በሚል በ1993 ‘ኢትዮጵ’ መጽሔት ላይ ተከራክሯል። ዐፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ሲያጠፉ፣ ዐፄ ዮሐንስ በደርቡሾች አንገታቸው ሲቀላ፣ ልጅ እያሱ ሲገደሉ፣ አቡነ ጴጥሮስ በጣሊያን ሲረሸኑ፣ ደጃች በላይ ዘለቀ እና ጄነራል መንግሥቱ ነዋይ በአደባባይ ሲሰቀሉ፣ ዐፄ ኃይለሥላሴ ሲገደሉ በአገራቸው አዝነው እና ተማርረው ነው በሚል ገሞራው ተከራክሯል።
እኔ ግን በእርግማን አላምንም። እንመን ቢባል እንኳ በጥቂቶች ጥፋት ብዙዎች የሚቀጡበት ምክንያትም አይኖርም። ለውጥ የማይዋጣልን ለቅድመ ለውጡ የምንከፍለውን መስዋዕትነት ሩቡን እንኳን ለውጡን ለማስጠበቅ ስለማንከፍል ነው። ከዚያም በላይ የከፋው ደግሞ ተረኛ ጨቋኝ እንመርጣለን እንጂ ነፃነትን ብቻ ዒላማ አድርገን ስለማንመርጥ ነው። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ደግመው ደጋግመው እንደተናገሩት ‘ኢትዮጵያውያን ተጨቋኝነትን እንጂ ጭቆናን አንቃወምም’።
ሁለቱ ፅንፎች
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ያለፉትን ሦስት ስርዓቶች ተቃውመዋል በሚል ነው ሥማቸው የሚነሳው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን መምጣት በሙሉ ይሁንታ ከተቀበሉ ሰዎች ሁሉ የእርሳቸውን አስገራሚ የሚያደርገው የተቃዋሚነታቸው ታሪክ ነው። እንደ እርሳቸው ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን ወደ ሥልጣን ያመጣቸው ‘ኢትዮጵያ የተአምር አገር መሆኗ ነው፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እንደማይታዋት ማሳያ ነው’።
በሌላ በኩል፣ ከኢንሳ ኃላፊነታቸው የተነሱት ጄኔራል ተክለብርሃን በትግራይ ቲቪ ቀርበው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ትሕነግን (TPLF) ለማጥፋት ያለሙ ሰው እንደሆኑ አድርገው ገልጠዋቸዋል።  ‘አካሔዳቸው ፕሬዝደንታዊ ዓይነት ነው። ሕግ ይጥሳሉ፣ እስረኛ ይፈታሉ፣ አሸባሪ ይጠራሉ፣ ባድመን ሕግ ተላልፈው ያለ ቅድመ ሁኔታ ሰጥተዋል፣… እየተመራን ያለነው በጁንታ ነው’ ብለዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያ አንድነት ከምንም በላይ የሚያሳስባቸው ሰው ናቸው። የድጋፋቸው እና የደስታቸው ምንጭም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አመጣጥ ኢትዮጵያ ካሁን አሁን ወደ ቀውስ ገባች እየተባለ ባለበት በኢትዮጵያ ሥም እየማሉ የሚገዘቱ መሪ ሁነው፣ አመፁን ሁሉ ፀጥ ማስባል በመቻላቸው ነው። በተቃራኒው የትሕነግ ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና ተቀባይነት ያስገኘላቸውን ለውጥ የሚቃወሙት ቀድሞ የነበራቸውን የበላይነት ስለሚቀማቸው ነው። የበላይ ፈላጭ ቆራጭ ለነበረ ሰው ዕኩልነት አዋጭ አይደለም። የለውጡ ድባብ ግን ከነዚህ ዕኩልነት አያዋጣንም ከሚሉት ውጪ ያሉትን ከሞላ ጎደል አስማሚ ነው። ለአገር ተቆርቋሪ የሆኑትን ከመፍታትም በላይ፣ ተሰደው የከረሙትንም ወደ አገር ቤት የሚመልስ የለውጥ ድባብ ነው ያለው። 
ቀጣዩ ግጭት የሚነሳው በሁለቱ ፅንፎች መካከል ነው ብዬ እሰጋለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩት የለውጥ መንፈስ ደጋፊዎች እና የለውጥ መንፈሱን በሚቃወሙት መካከል። የለውጡ መንፈስ ደጋፊዎች ብዙኃን ቢሆኑም በኢኮኖሚ እና በመዋቅር አልተደራጁም። የለውጡ መንፈስ ተቃዋሚዎች የድርጅት መዋቅሩ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ አቅሙም አላቸው። ለዚህም ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገደምዳሜም ቢሆን ‘ለውጡን ጠብቁ’ የሚል መልዕክት የሚያስተላልፉት። በርግጥ ትሕነግም በመግለጫ ሳይቀር ተቃራኒው እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል። ለውጡን ጠብቁ የሚለው ጥሪ እና ዛቻ ብዙ አብዮቶች እንዲቀለበሱ ሰበብ የሚሰጣቸው “ፀረ አብዮቶችን የመመንጠር ዘመቻ” ጋር ስለሚመሳሰልብኝ ያስደነግጠኛል። ይሁን እንጂ የሚከተለውን ጥያቄ አቀርባለው። 
የትኛውን ለውጥ እንጠብቅ?
እስረኞችን የመፍታት እርምጃው ለውጥ ነው። ይሁን እንጂ ድርጊቱ የተፈፀመው በሕጋዊ አግባብ ሳይሆን በፖለቲካ አመራሮቹ መልካም ፈቃድ ነው። (እርግጥ አሁን ዐዋጁም እየተሻሻለ ስለሆነ በአስቸኳይ መፍትሔ የተስተካከለው በሕግ እየፀና ነው እና ትክክለኛ አካሔድ ነው። ይህንን ግን በሁሉም ረገድ እንዲቀጥል ማድረግ ነው ‘ለውጡን መጠበቅ’ ማለት ሊሆን የሚችለው።) በሕግ ያልተፈቀዱ ባንዲራዎች ያለምንም ስጋት አደባባይ ላይ እንዲውለበለቡ ተፈቅዷል። በእርግጥ ሕጎቹ ፍትሓዊ ባለመሆናቸው ድርጊቱ/ለውጡ መልካም ነው። ነገር ግን በፖለቲካ አመራሮቹ ይሁንታ ብቻ የተደረገ ስለሆነ ሕጋዊ ዋስትና የለውም። የባንዲራን ጉዳይ እንደምሳሌ አነሳሁት እንጂ በሁሉም እርምጃ አካሔዱን ማስተዋል እና መገምገም አለብን። 
የፖለቲካ መሪዎች የመፍቀድ መብት ካላቸው፣ የመከልከልም ይኖራቸዋል። የፖለቲካ መሪዎች ሥልጣን ተለጥጦ በጎ ፈቃዳቸው ለብዙኃኑ ተስማሚ እስከሆነ ድረስ ችግሩ አይስተዋልም። ችግሩ ይህንኑ ሥልጣናቸውን ለብዙኃኑ ተስማሚ ባልሆነ መንገድ የተጠቀሙበት ግዜ ነው የሚመጣው። በርግጥ ቅንነት ከፖለቲካ ምኅዳራችን የተሰወረ ነገር በመሆኑ አሁን መከሰቱ ግሩም ነው። ነገር ግን የብዙኃኑ ተጠቃሚነት በጥቂት ባለሥልጣናት ቅንነት እና በጎ ፈቃድ ላይ ተንጠልጥሎ መቀመጥ የለበትም። ምክንያቱም ደግሞ ባለሥልጣናቱ ዘላለም የማይኖሩ ከመሆኑም ባሻገር ቅንነታቸውም ዘላለም ላይኖር ይችላል።
መፍትሔው የተለያዩ ተቋማት ነጻ እና ገለልተኛ እንዲሆኑ አድርጎ መገንባት ነው። መወገን ካለባቸውም ለሕዝብ እና ሕገ መንግሥቱ መሆን አለበት። ለውጡን ስንደግፍ የምናየው ለውጥ ሕጋዊ ዋስትና እንዲኖረው፣ ተቋማዊ ነጻነት እንዲጠናከር፣ የፍትሓዊ ሕግ የበላይነት እንዲስፋፋ ግፊት በማድረግ መሆን አለበት። አለበለዚያ ይህም ዕድል ያመልጠናልና ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለለትን ለውጥ በዚህ መንገድ እንጠብቅ። 

ከእኛ አገር የማያልቁ ችግሮች መካከል አንዱ የማንነት አረዳድ እና አበያየን ጉዳይ ነው። ማንነት እና ምንነት የፖለቲካ ጫወታችን አስኳል ሆኖ ሳለ፣ የማንነት አበያየናችን ግን ግለሰቦች የራሳቸውን ማንነት የሚበይኑበት ነጻ ዕድል የማይሰጥ ነው። 
የኦነጉ በያን አሶባ ባንድ ወቅት ከኢሳት ቴሌቪዥን “ኦሮሞ ማነው?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። “ኦሮሞ ነኝ ያለ” የሚል ምርጥ መልስ ሰጥተዋል። ነገር ግን ብዙዎች ማንነትን በዘር የሚወረስ እንጂ በማኅበራዊ-ሥሪት (social construction) የሚመጣ ነገር አድርገው አይመለከቱትም። እውነት መሆኑን ከራሷ ማረጋገጥ አልቻልኩም እንጂ ድምፃዊ ሴና ሰለሞን ከአማራ ተወላጆች የተወለደች ኦሮሞ ነች፤ “ኦሮሞ ነኝ” ስላለች። ራሷን የምትገልጸው እንደ ኦሮሞ ሲሆን፣ በዘፈኖቿ የታገለችውም ለኦሮሞ ሕዝብ ነጻነት ነው። የወላጆቿ የማንነት ታሪክ የሐሰት ወሬ ቢሆን እንኳ ነባራዊ ምሳሌ እናጣለን እንጂ፣ ምሳሌው ማንነትን የመምረጥ ግለሰባዊ ነጻነቱን የተሳሳተ አያደርገውም። 
‘ኢትዮጵያዊ ማንነት አለ፣ የለም? ጎጃሜ ማንነት አለ፣ የለም? አዲሳበቤ ማንነት አለ፣ የለም?’ የሚሉት ጉንጭ አልፋ ክርክሮች ምንጫቸው የግለሰቦች ማንነት እኛ ራሳችንን እንዲሁም ሌሎችን ከምንረዳበት መንገድ ውጪ መወሰን የለበትም ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ ነው። በቀላል ቋንቋ ለመግለጽ አባባሉ “እኔ ናችሁ ከምላችሁ ውጪ መሆን አትችሉም” ነው። 
በበኩሌ ሰዎች የራሳቸውን ማንነት ብለው የሚጠሩት ወይ ‘የሚኮሩበትን’ አሊያም ‘የተበደለባቸውን’ [ወይም የተበደለባቸው የሚመስላቸውን] ማንነታቸውን ነው ብዬ ነው የማምነው። ይሁን እንጂ ሁሉም ሰዎች ማኅበራዊ ሥሪታቸው ከብዙ ድርብ፣ ድርብርብ ማንነቶች የተገነባ ነው። ጥቁር ሕዝብ መሐል ላደጉ ኢትዮጵያውያን ጥቁርነት የማንነታቸው መገለጫ መሆኑ ትዝ ብሏቸው አያውቅም። ነገር ግን ከኢትዮጵያዊ ወላጆች ተወልደው ነጮች አገር ያደጉ ኢትዮጵያውያን “ምንድን ነህ/ምንድን ነሽ?” የሚል ጥያቄ ቢቀርብላቸው፣ ጥቁርነታቸው ቀድሞ የሚመጣባቸው መልስ ሊሆን ይችላል? “ምንድን ነህ/ነሽ?” የሚለው ጥያቄ የማንነት ወይም የምንነት ጥያቄ መሆኑ አያጠራጥርም። መልሱ ግን ወጥ አይደለም። እንደ ሁኔታው እና ቦታው ይለያያል። አንዱ “አካውንታንት ነኝ” ብሎ ሙያውን እንደማንነቱ መገለጫ ሊጠቅስ ይችላል፣ ሌላዋ “ሙስሊም ነኝ” ልትል ትችላለች። በሁኔታው፣ በወቅቱ እና በቦታው ሰዎች ስለማንነታቸው የሚሰማቸው ስሜት የተለያየ ሊሆን ይችላል። ይህም የማንነትን ወጥ አለመሆንና ድርብርብነት ያረጋግጣል።
እኔ በማንነቴ ቀረፃ ውስጥ “የድሀ ልጅ” መሆኔን ያክል ተፅዕኖ የፈጠረብኝ ነገር አለ ብዬ አላምንም። የድሀ ልጅ ሆኖ ማደግ ያለንን ነገር ‘ላጣው እችላለሁ’ በሚል ፍርሐት እና የሌለንን ነገር ‘ላገኘው አልችልም’ በሚል ስጋት ውስጥ መኖር ማለት ነው። ይህ ማንነት ነው። በድህነት ውስጥ ላደገ ሰው፣ ዓለም ማለት የመግዛት አቅም ባላቸው እና በሌላቸው ሰዎች የተሞላች ናት። የአዲስ አበባ ድሀ፣ ከብራዚል ድሀ ጋር በሥነ ልቦና የሚያግባባ ማንነት አለው። ነገር ግን “የድሀ ልጅ” የሚባል ማንነት በኛ የፖለቲካ መዝገበ ቃላት የለም። ስለዚህ ከዚህ ውጪ ብዙ ማንነቶች አሉኝ። ለምሳሌ ጦማሪነት። ከዚህ በፊት ስታሰር ስፈታ የነበርኩት ተቺ ጦማሪ ስለሆንኩ ነው። ስለዚህ ምንድን ነህ ስባል ‘ብሎገር ነኝ’ የምልባቸው ግዜያት ብዙ ናቸው። ለምሳሌ እስር ቤት በማንነቴ ነው የታሰርኩት የሚሉ ነበሩ። እነሱ “ኦሮሞ በመሆኔ”፣ “አማራ በመሆኔ” ሲሉ እኔ ደግሞ “ብሎገር በመሆኔ” እል ነበር። ይህም ማንነት ነው። ይህንን ብነፈግ እንኳ በትምህርት ያፈራሁት፣ በተወለድኩበት አካባቢ ያፈራሁት፣ በእምነቴ ወይም ባለማመኔ ያፈራሁት ብዙ ማንነቶች አለኝ። 
ነገር ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ብያኔ መሠረት እነዚህ ሁሉ ማንነቶቼ ዋጋ የላቸውም። “ምንድን ነህ?” ስባል የወላጆቼን የዘውግ ማንነት እንድናገር ይጠበቅብኛል። ወላጆቼ ቅይጥ ቢሆኑ እንኳን የአባቴን [ይህ ካልሆነ ደግሞ የእናቴን] የዘውግ ቡድን ማንነቴ ብዬ እንድናገር ይጠበቅብኛል። እኔ እኔን ይገልጸኛል የምለው ማንነት እንዲኖረኝ ነጻነቱ የለኝም። በዚህ አካሔድ “ኦሮሞ ነኝ” ማለት፣ ወይም “አማራ ነኝ” ማለት፣ ወይም “አዲሳበቤ ነኝ” ማለት ምንም ዋጋ/ጥቅም የለውም። ምክንያቱም በኔ ማንነት ላይ እኔ የመወሰን ነጻነቱ የለኝም። 

ፎቶው ላይ ከግራ ወደቀኝ የሚታዩት፤ የኮንሶ መሪ ካላ ገዛኸኝ እና ወንድማቸው
በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ሕዝባዊ አመፆች በተቀጣጠሉበት ወቅት፣ በሕዝብ ብዛት ትንሿ ኮንሶም ከዐሥር ወራት ላላነሰ ጊዜ ሕዝባዊ ተቃውሞ ታደርግ ነበር። በወቅቱ የመብት ተሟጋቾች አመፁ አገር ዐቀፍ እንደሆነ ለማስረዳት እንደምሳሌ የኮንሶን ጉዳይ ደጋግመው ይጠቅሱት ነበር። በወቅቱ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሠላማዊ ተቃውሞዎችን በኃይል በመበተን፣ ብዙዎችን ወደ እስር ቤት አጉረዋል። ከነዚህ እስረኞች ውስጥ የኮንሶ የጎሳ መሪ የሆኑት ካላ ገዛኸኝ ወልደዳዊት ካዮቴ ይገኙበታል። (‘ካላ’ በጎሳ መሪነት የሚገኝ የጎሳ ሐረግ ማዕረግ ነው።)
ካላ ገዛኸኝ ከመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ በሲቪል ምሕንድስና ተመርቀዋል። የጎሳ መሪነቱን ከአባታቸው የወረሱት በጥቅምት 2006 በባሕላዊው ወግ መሠረት ከአባታቸው ነበር። የጎሳ መሪው በኮንሶ ማኅበረሰብ ልማድ መሠረት ልማዳዊ ዳኝነት፣ ግልግል እና ሌሎችም ማኅበራዊ አስተዳደር ይሰጣል። ይሁን እንጂ የአሁኑ የጎሳ መሪ ካላ ገዛኸኝ ሠላማዊ ሕዝባዊ ጥያቄ በማንሳታቸው ምክንያት ከሌሎች የኮንሶ ብሔረሰብ አባላት ጋር ለእስር ከተዳረጉ እና ከማኅበራዊ ኃላፊነታቸው ከተገለሉ አንድ ዓመት ከ10 ወራት አለፏቸው። ካላ ገዛኸኝ በተከሰሱበት መዝገብ ብቻ 43 ሰዎች ተከስሰዋል። ያነጋገርኳቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደነገሩኝ ግን የጠቅላላ እስረኞቹ ቁጥር 467 ነው። እነዚህ ሕዝባዊ ጥያቄ ያነሱ የኮንሶ ብሔረሰብ አባላት በጊዶሌ ማረሚያ ቤት፣ ኮንሶ ፖሊስ ጣቢያ እና አርባ ምንጭ ማረሚያ ቤት ታስረው ይገኛሉ። ካላ ገዛኸኝ እና ሌሎችም 180 ገደማ ሰዎች የታሰሩት በአርባ ምንጭ ማረሚያ ቤት ነው። 
ከእስር ውጪ ከመንግሥት የሥራ ገበታቸው ተባርረው (እና ከግንቦት 2008 ጀምሮ) ቤተሰባቸው የኅልውና አደጋ ላይ የወደቀባቸው ከ250 በላይ የኮንሶ ብሔረሰብ አባላት እንዳሉ ዝርዝሩን እና አቤቱታ ያቀረቡበትን ደብዳቤ ተመልክቻለሁ። 

የኮንሶ ጥያቄ ምንድን ነው?
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደነገሩኝ ኮንሶ ተጠሪነቷ ለደቡብ ክልላዊ መንግሥት የነበረች ልዩ ወረዳ ነበረች። ይሁን እንጂ ከመጋቢት 2003 ጀምሮ ልዩ ወረዳነቷ ቀርቶ፣ ተጠሪነቷም ለዞን ሆኗል። ነዋሪዎቹ በአሁኑ ወቅት ‘በሰገን አካባቢ ሕዝቦች’ አስተዳደር ሥር ‘እንደተጨፈለቁ’ የነገሩኝ ሲሆን፣ ይህም የራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ከመጣሱም በላይ ከተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶች የመገለል ጦስ እንዳመጣባቸው አጫውተውኛል። ይህንንም በመቃወም በ2008፣ የ81ሺሕ ሰዎች ፊርማ በማሰባሰብ 12 አባላት ያሉት ኮሚቴ በመወከል ጥያቄያቸውን ለክልሉ ምክር ቤት እንዲሁም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርበዋል። ሆኖም ያገኙት መልስ የለም። ይልቁንም የፀጥታ ኃይሎች 12ቱን የኮሚቴ አባላት ሊያስሯቸው ሲሞክሩ ሕዝቡ ሆ ብሎ ወጥቶ በማስቆም፣ የኮሚቴ አባላቱ እንዳይታሰሩ በሚል ውክልናቸውን አንስቷል። 
ኮሚቴዎቹ ቢነሱም ተቃውሞዎቹ ግን የቀጠሉ በመሆኑ በወቅቱ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት አሰፋ አብዩ ተወካዮቻችሁን ላናግር በማለታቸው 23 ሰዎች ተወክለው አነጋግረዋቸዋል። ወትሮም ጥያቄያቸውን ማስተናገድ የነበረበት ሌላ አካል በመሆኑ የፌደራል ፖሊስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ካላ ገዛኸኝን ጨምሮ ሁሉንም ለቃቅሞ ለእስር ዳርጓቸዋል። በእስሩ ወቅት የጎሳ መሪውን እና ልማዱን በሚያዋርድ መልኩ ካልሞተ በቀር ከክንዱ የማይወልቀውን ከዝሆን ጥርስ እና ከአውራሪስ ቀንድ የተሠራ የቃልኪዳን አምባር ፖሊሶች መሰባበራቸውን በምሬት ነግረውኛል።
ክሱ ምን ይላል?
የታሰሩት ሰዎች ከ400 በላይ ቢሆኑም ፍርድ ቤት እየቀረቡ ያሉት ግን የተወሰኑት ብቻ እንደሆኑ ተነግሮኛል። ፍርድ ቤት ከሚቀርቡት ታሳሪዎች መካከል የነካላ ገዛኸኝ መዝገብ (እዚህ ሙሉውን ማየት ይቻላል) ላይ እንደሚነበበው ከሆነ ክሱ የፖለቲካ ነው። “የወረዳው ሕዝብ በመንግሥት ላይ በአመፅና በአድማ ካልተሰለፈ ይህ ጥያቄ በሠላማዊ መንገድ ምላሽ አያገኝም” በማለት ቅስቀሳ አድርገዋል በሚል ታስረው እስካሁን ፍርድ አላገኙም። እንደሌሎች ፖለቲካ እስረኞችም ክሳቸው አልተቋረጠላቸውም። አሁን ቀጣዩ ቀጠሯቸው በመጪው ሰኞ ሰኔ 18/2010 ነው። 
ለምን አልተፈቱም?
የኮንሶ እስረኞች ከኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በተቃውሟቸው ምክንያት ተለቃቅመው እንደታሰሩት ዜጎች ሁሉ የፖለቲካ እስረኞች ናቸው። ይሁን እንጂ ከኮንሶ እስረኞች መካከል እስካሁን አንድም ሰው አልተፈታም። በዚህም “እኛ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ወይ?” የሚል ቁጭት ተሰምቷቸዋል። ከ350 ሺሕ በላይ ነዋሪ ባላቸው 42 የኮንሶ ቀበሌዎች የተውጣጡ ሽማግሌዎች ይህንን አቤት ለማለት ተሰብስበው አኔቱታዎቻቸውን ለክልሉ መንግሥትም፣ ለፌዴራሉ መንግሥትም አቅርበው ነበር። ይሁን እንጂ ማንም መልስ አልሰጣቸውም። ይልቁንም አሁንም በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች እየተዋከቡ ነው። ከሽማግሌዎቹ መካከል አንድ ሰው ባለፈው ሳምንት ሲታሰር ሌሎችም ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው። 
አሁን ዜጎች የፀጥታ ኃይሎች ማዋከብ በመቅረቱ መፍራት ባቆሙበት ሰዐት፣ የኮንሶ ሰዎች ግን አሁንም ከእስር ስጋት ጋር ተፋጥጠዋል። ይህንን እጅግ በጣም አሳጥሬ የጻፍኩትን መረጃ የሰጡኝ ሰዎች ሥማቸውን መጥቀስ ይፈቅዱልኝ እንደሆነ ስጠይቃቸው፣ “እኛ አካባቢ ያለው ሁኔታ እንደ አዲስ አበባ አይደለም። ለኛ ጥሩ አይደለም” ብለውኛል። 
ለኮንሶ ብሔረሰብ ዜጎቻችን የሚደርስላቸው ማን ይሆን? [እባካችሁ ይህንን መረጃ እንዲሰራጭ በማገዝ የሚመለከተው አካል በአስቸኳይ የኮንሶ ዜጎቻችንን ከእስር እንዲፈታ የበኩሎን አስተዋፅዖ ያድርጉ።]

(ከታች ያስቀመጥኳቸው ጥቆማዎች በጥናት ላይ የተመሠረቱ የመፍትሔ ሐሳቦች ሳይሆኑ በግል ትዝብት የተጠቆሙ ናቸው። በምስሉ ላይ የሚታየው (ፎቶ: ቴዎድሮስ አያሌው) በ1977 ድርቅ ወቅት ደርግ ቄለም ወለጋ አስፍሯቸው የነበሩ እና አሁን ተፈናቅለው አላማጣ የሚገኙ ናቸው። በምስሉ እንደሚታየው አብዛኛዎቹ የተወለዱት እዚያው አካባቢ ሲሆን፣ ወላጆቻቸው እና አያቶቻቸው ናቸው ከአላማጣ ነበር ቄለም ወለጋ እንዲሰፍሩ የተደረጉት።)

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ‘የማንነት’ እና ‘የብሔር’ ፖለቲካ ወይም ጥያቄ ተምታተዋል። ብዙ ግዜ ሁሉም ነገር ‘የብሔር ጥያቄ’ ነው፤ መልሱም የሚገኘው ‘በብሔርተኝነት’ ነው የሚባለው ጉዳይ ከማንነት ጋር የተያያዘውን ጥያቄ ያድበሰብሰዋል። እንዲያውም አንዳንዴ ብሔርተኝነት ችግሩን ሊያባብሰው ይችላል። የማንነት ወይም የብሔር ትርጉሙም እንዲሁ የተምታታ ነው። ምክንያቱም ማንነትም ይሁን ብሔር በተለምዶ የሚበየነው በቋንቋ ላይ ተመሥርቶ ነው። ስለዚህም በተምታታ ትርጉም ላይ የተመሠረተ ብሔርተኝነትም ለተሳሳተ ጥያቄ የተሳሳተ መልስ ለመስጠት ይዳርጋል። ማንነት በቋንቋ ሊመሠረት ይችላል፤ ነገር ግን አንድ ቋንቋ እየተናገሩ የተለያየ ማንነት ያላቸው ግለሰቦች ወይም ሕዝቦች አሉ። ማንነት በፆታ ብቻ ሊወሰን ይችላል። ወይም ደግሞ በፆታዊ ግንኙነት ምርጫ ሊወሰን ይችላል። በመልክ ወይም በቆዳ ቀለም። ወዘተ… ለምሳሌ ያክል ቱትሲዎች እና ሁቱዎች አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ሆነው፣ ልዩነታቸው የመልክ (እና የታሪክ ድርሻ) ነው። 
ፌዴራሊዝሞች የአወቃቀር ስርዓታቸው ምንም ቢመስል፣ ዋነኛ ዓላማቸው በብሔርተኝነቶች መካከል ውጥረቶችን ሥልጣን በማከፋፈል እና በማጋራት ማርገብ ነው። የእኛው ግን ውጥረቱን ምናልባትም አባብሶታል አልያም ገሀድ አውጥቶታል። በሕገ መንግሥቱ ባይሰፍርም “የእንትን ክልል፣ ለእነ ‘እንቶኔ'” የሚል ያልተጻፈ ሕግ አለ። ‘እንቶኔነት’ ከወላጆች በደም የሚወረስ መሆኑም እንዲሁ ያልተጻፈ ሕግ ነው። ስለዚህ በእንትን ክልል ያሉ ከእነ እንቶኔ ውጪ ያሉ ነዋሪዎች በሙሉ የመገለል፣ የመጠቃት፣ የመሰደድ ዕድላቸው ሰፊ ነው። በእርግጥ በዚህ መሰሉ ጥቃት እና ስደት በተደጋጋሚ የሚጠቁት ሰዎች በተለይ በብዙ ክልሎች የተበተኑት ብሔረሰብ አባላት ናቸው። ነገር ግን ይሔ ዕጣ ያልገጠመው አለ ለማለት ይከብዳል። ባለፈው ዓመት ከሶማሌ የተፈናቀሉት 600 ሺሕ የኦሮሞ ተወላጆች ጉዳይ ሪከርድ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የአማራ ተወላጆች የመፈናቀል ዜናን መስማትም ለጆሮ እንግዳ አይደለም። የሆነ ሆኖ ዛሬ በኢትዮጵያ ያሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር 1 ሚሊዮን ተኩል ገደማ ነው። በየዘውጉ ተጎራባቾች አንዱ አንዱን በውኃ እና ግጦሽ/እርሻ መሬት ማጥቃት እና ማፈናቀል የነበረ፣ እና የበለጠ ፖለቲካዊ እየሆነ የመጣ ነገር ነው። ማንነትን መሠረት ያደረጉ መፈናቀሎች በተከሰቱ ቁጥር የዘውጉን ቡድን እየቆጠሩ የአንድ ወገን ጉዳይ ብቻ ማስመሰሉ ለብሔተኝነት ፖለቲካ ይበጅ ይሆናል እንጂ ችግሩን ለመቅረፍ እምብዛም አይበጅም። ልብ በሉ፣ የተፈናቀሉት ሰዎች በማንነታቸው እስከሆነ ድረስ የተፈናቃዮቹን ማንነትም ይሁን የአፈናቃዮቹን ማንነት መጥቀሱ ላይ ችግር የለውም። ነገር ግን ለብሔርተኝነት ትርፍ ሲባል ብቻ ነገሩ በሁለት ሕዝቦች መካከል የተደረገ ፍጥጫ ማስመሰል እሳቱ ላይ ነዳጅ ማርከፍከፍ ነው። ከዚያም በላይ ሰዎች ችግሩን በገለልተኛ ዓይን አይተው እንዳይከላከሉት ወይም ጥብቅና እንዳይቆሙለት ይገፋል።
ለምሳሌ፣ በቤንሻንጉል-ጉሙዝ ክልል አንድ ቀበሌ ውስጥ የተፈናቀሉ የአማርኛ ተናጋሪዎች ጉዳይ “የቤንሻንጉል-ጉሙዝ ሕዝብ የአማራን ሕዝብ አፈናቀለ” ብሎ መዘገብ የተሳሳተ ምስል ከመስጠቱም በተጨማሪ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል መቃቃር ይፈጥርና በክልሉ ሌሎች ቀበሌዎች ነዋሪዎች የሆኑ አማርኛ ተናጋሪዎችንም ለበለጠ ጥቃት ሊዳርግ ይችላል። አንዳንዴ መፈናቀሎቹ የሚከሰቱት በቀበሌዎቹ አስተዳደሮች ሆኖ ሳለ፣ የሕዝቡ ሥራ አስመስሎ ማቅረቡም ነዋሪዎቹን ከጎረቤቶቻቸው ጋር ማቀያየም ነው።
ችግሩ እንዴት ይቀረፍ?
በመጀመሪያ ደረጃ የችግሩን ምንጭ በአግባቡ መፈተሽ አስፈላጊ ነው። ዋነኛው ችግር የሚመስለኝ የአስተሳሰብ ነው። 
1ኛ፣ ክልሎች የየትኛውም ክልል ተወላጅ በክልላቸው የመኖር መብት እንዳለው መቀበልና መብቱን ማረጋገጥ አለባቸው።
የትኛውም ክልል የየትኛውም ብሔረሰብ ተወላጅ የግል ንብረት አይደለም። የትኛውም ብሔረሰብ ተወላጆች በየትኛውም ክልል ውስጥ ከየትኛውም ብሔረሰብ ተወላጅ የበለጠ ወይም ያነሰ መብት የላቸውም። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 32/1 “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቷ ውስጥ የሚገኝ የውጭ አገር ዜጋ በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት፣” መብት አለው ይላል። ይህ ደግነቱ ሕገ መንግሥቱ አክብሮታል አንጂ ባያከብረውም የማይሻር የተፈጥሮ ሕግ ነው። በክልሎች ቀርቶ በአገራት ድንበሮች ይህንን መገደብ ከተፈጥሮ ሕግ ያፈነገጠ፣ ነገር ግን ለስርዓት (order) ሲባል የምንታገሰው ሕግ ነው። ይህንን ከልብ መቀበል ያስፈልጋል። በሕግ እና ደንቦች የሚተገበርበት መንገድ ይመቻቻል እንጂ በልዩነት የሚታደልበት/የሚነፈግበት መንገድ ሊኖር አይገባም። 
ፌደራሊዝሙ ያልተማከለ አስተዳደር ፈጥሯል። (በፌዴራሊዝሙ አወዛጋቢው ጉዳይ አከላለሉ ዘውግ-ተኮር መሆኑ ላይ ነው። ይሔ ጽሑፍ መዋቅሩ ሳይለወጥ ችግሩን መቅረፍ ላይ ያተኮረ ስለሆነ ወደዛ ውዝግብ አንገባም።) እነዚህ አስተዳደሮች በእየርከኑ ባሉ የአስተዳደር ክፍሎች ውስጥ የነዋሪዎችን ቁጥር ከግምት ውስጥ ያስገባ የብዙኃን አመራር እና የድሀጣንን መብት የማክበር ግዴታ አለባቸው። ብዙኃኑ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ከሆነ ቋንቋው የክልሉ የሥራ ቋንቋ ባይሆን እንኳ የአስተዳደር ክፍሉ የሥራ ቋንቋ መሆን ይኖርበታል። ይህ ግን ለአስተዳደር ቅልጥፍና እንጂ መብትን ለማከፋፈል አይደለም። ድሀጣኑ ከብዙኃኑ ዕኩል መብቶች እና ዕድሎች ሊኖሯቸው የግድ ነው። በሕጋዊ መንገድ መኖሪያ ቦታ የማግኘት እና የመሥራት መብታቸው ያለቁጥራቸው ወይም ያለማንነታቸው ገደብ ሊከበርላቸው ይገባል። የአካባቢ አስተዳደሮች ይህ አረዳድ እንዲሰርፃቸው ያልተቋረጠ የብዙኃን መገናኛዎች ዘመቻ እና የግንዛቤ ማስበጫ ሥልጠናዎች ሊሰጧቸው ይገባል። (በነገራችን ላይ በብዙ ክልላዊ አስተዳደሮች ውስጥ በርካታ አማርኛ ተናጋሪ ነዋሪዎች ያሉ ቢሆንም፣ ከአማርኛ ተናጋሪዎቹ ቁጥር ያነሰ ተናጋሪ ያላቸው ቋንቋዎች የሥራ ቋንቋ ሳይሆኑ ሌሎቹ የሆኑበት ብዙ ምሳሌ አለ። የአማርኛ ተናጋሪዎቹ ቁጥር እና አሰፋፈር እስከፈቀደ ድረስ ልዩ የአስተዳደር ዞን፣ ወይም ተደራቢ የሥራ ቋንቋ መሆን የማይችልበት ሕጋዊ አግባብ የለም።)
2ኛ፣ ከትውልድ ክልላቸው ውጪ የሚኖሩ ግለሰቦች የሚኖሩበትን ክልል ሕግ እና ደንቦች (ፍትሓዊ ወይም በሁሉም ላይ የተጣሉ እስከሆኑ ድረስ) ማክበር አለባቸው። 
አንዳንድ ከትውልድ ቀዬአቸው ውጪ የሚኖሩ ዜጎች፣ ማኅበረሰቤ ብለው የሚጠሩት የተወለዱበትን እንጂ የሚኖሩበትን ቀዬ አይደለም። ይባስ ብሎ የተወለዱበት፣ ያደጉበትን ቀዬ ሳይሆን የወላጆቻቸውን ደም እና የትውልድ ቀዬ ቆጥረው ቀዬዬ ብለው የሚጠቅሱ አሉ። “የኔ” የሚሉትን ማኅበረሰብ መምረጥ የግል ድርሻቸው ቢሆንም የሚያስከፋው ነገር የሚኖሩበትን ማኅበረሰብ የሚንቁ ሰዎች መኖራቸው ነው። እነዚህኞቹ፣ በሚኖሩበት አካባቢ የአስተዳደር ችግር ሲደርስባቸው ‘አቤት’ የሚሉት ለሚኖሩበት ክልል አስተዳደር የላይኛው ክፍል ሳይሆን፣ ለመጡበት ክልል አስተዳደር ነው። ይህ ያልተማከለ አስተዳደር የሥልጣን ክፍፍልን የሚጋፋ እና በክልሎች መካከል ውጥረት የሚያነግሥ አካሔድ ነው። በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል አንድ ቀበሌ ውስጥ አስተዳደራዊ በደል የደረሰባቸው ዜጎች፣ ከዚያ በላይ ላለው አስተዳደር ወይም ፌዴራል መንግሥቱ ያመለክታሉ እንጂ ለመጡበት/ለሚወለዱበት ክፍል ማመልከት የለባቸውም። 
ዜጎቻችን አገር ለቀው ሲወጡ፣ የሚቀበላቸውን አገር ባሕልና ስርዓት አክብረው እንደሚኖሩ ሁሉ፣ በአገር ውስጥ ከአንዱ ቀዬ ወደሌላው ሲሔዱ፣ አዲስ ለሚኖሩበት አካባቢ ልማድ እና አሠራር (መሠረታዊ መብቶቻቸውን እስካልገፈፉ ድረስ) ተገዢ መሆን ይኖርባቸዋል። የአካባቢውን ደንብና ስርዓት አለማክበር የግጭት እንዲሁም የመፈናቀል መንስዔ ስለሆነ በዚህ መንገድ መከላከልም ይቻላል።
3ኛ፣ ብሔርተኞች ብሔርተኝነት በዘውግ ሳይሆን በክልል ላይ አስተሳሰቡን እንዲወስን ማድረግ አለባቸው። 
ይህ የዘውግ ብሔርተኝነት (ethno-nationalism) ከክልሎቹ ሥያሜ ይጀምራል። አማራ፣ ሶማሊ፣ አፋር፣ ሐራሪ፣ ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልሎች ለምሳሌ በክልሎቹ በሚኖረው አብዛኛው ሰው ዘውግ ሥያሜ ነው ክልሎቹ የሚጠሩት። ከዚህ በተሻለ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ጋምቤላ እና ደቡብ ሕዝቦች ዐቃፊ አገላለጽ አላቸው። ይሁን እንጂ እነርሱም ብሔርተኝነታቸው ክልላዊ (territorial-nationalism) አይደለም። ለምሳሌ በኦሮሚያ ገዢው ፓርቲ ኦሕዴድ (የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት) እንጂ “የኦሮሚያ ሕዝቦች” አልተባለም። በኦሮሚያ የሚኖሩት ግን የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ብቻ ባለመሆናቸው ዐቃፊነት ይጎድለዋል። በዚያው ክልል ተቃዋሚው ኦፌኮ (የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ) ነው። የኦሮሚያ አለመሆኑ ብሔርተኝነቱ በክልሉ ያሉትን ሌሎች ዘውጎች እንዳያቅፍ ከሥሙ ጀምሮ እንቅፋት ይሆናል። የሌላ ዘውግ አባላት ለመብቶቻቸው ለመታገል እነዚህን ድርጅቶች መቀላለቀል አይችሉም ማለት ነው። በብአዴንም ተመሳሳይ ችግር ነው የምንመለከተው። በትግራይ አረና ምንም እንኳን በተግባር ባይሳካለትም በአስተሳሰብ ደረጃ ክልላዊ ፓርቲ ነው። የክልሉ ነዋሪ እስከሆኑ ድረስ ትግራዋይ ያልሆኑ ሰዎችም አረናን መቀላቀል ይችላሉ። 
ብሔርተኝነትን ክልላዊ ማድረግ በክልሉ ውስጥ ከብዙኃኑ ዘውግ ያልተወለዱ ሰዎች በክልሉ ውስጥ ውክልና እንዲኖራቸው ያደርጋል። ብዙዎቹ መፈናቀሎች የሚከሰቱት ሰዎቹን የሌላ ክልል ሰው ናቸው ብሎ ከሚያስብ በመነጨ አስተሳሰብ ነው። ነገር ግን ሰዎች አንድን አካባቢ መርጠው በሕግ አግባብ ነዋሪ እስከሆኑ ድረስ መወከል የሚኖርባቸው በሚኖሩበት አካባቢ እንጂ ጥለውት በመጡት አካባቢ መሆን የለበትም። ብሔርተኝነት ክልላዊ ሲሆን በነዋሪዎቹ መካከል ያለውን የዘውግ ውጥረት ይቀንሳል። ለምሳሌ ያክል በኦሮምያ ክልል ላሉ አማራዎች የአማራ ክልል ብሔርተኝነት ነው ጥብቅና የኦሮሚያ ብሔርተኝነት እንዲሆን ያደርጋል። 
4ኛ፣ የፌዴራል መንግሥቱ ከቀዬ ለመሰደድ እና የአገር ውስጥ ፍልሰት ፖሊሲ መቅረፅ አለበት። 
አዲስ አድማስ ጋዜጣ የጠየቃቸው አንድ ተፈናቃይ ወደትውልድ መንደራቸው ለምን እንደማይሔዱ ሲናገሩ ከትውልድ ቀያቸው የተሰደዱት የእርሻ መሬት አጥተው እንደሆነ ተናግረዋል። በርግጥም የአገር ውስጥ ፍልሰት ዋነኛው መንስዔ የእርሻ መሬት ለልጅ ልጆች ሲተላለፍ እየጠበበ ቤተሰብ ማስተዳደር ባለመቻሉ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ብዙ ግዜ በመታረሱ መሬቱ እየነጠፈ ራሳቸውን ለማስተዳደር ሌላ ቦታ ሔደው ማረስ ስለሚገደዱ ነው። እነዚህ ከቀያቸው በችግር የፈለሱ ዜጎች ሌሎች መንደሮች እየሔዱ ጫካዎችን በመመንጠር፣ የግጦሽ መሬቶችን በመውረር እና በሌሎችም ሕጋዊ በሆኑና ባልሆኑ መንገዶች የሚቀይሱት መንደር ከሔዱበት አካባቢ ሰዎች ጋር ግጭት ውስጥ እየከተታቸው ነው። ስለሆነም ይህ ችግር እየተባባሰ ይሔድ እንደሆነ እንጂ እየቀነሰ የሚሔድ አይመስልም። ሆኖም የፌዴራል መንግሥቱ ይህንን ጉዳይ አቅጣጫ ለማስያዝ የሚያስችል ፖሊሲ የለውም። ችግሩ አንድም ከሕዝብ ብዛት ጋር የሚያያዝ ነው። ይሁን እንጂ ያለፉት ሁለት የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች የሕዝብ ብዛትን በተመለከተም ይሁን የአገር ውስጥ ፍልሰትን በተመለከተ ያስቀመጡት አቅጣጫ የለም። ይህ ለቀውሱ መባባስ ብቻ ሳይሆን አፋጣኝ የእርምት እርምጃ መውሰድ እንኳን እንዳይቻል አድርጓል። 
5ኛ፣ መጠባበቂያ ፈንድ መመደብ።
ምንም እንኳን ዋናው ሥራ መፈናቀልን መከላከል ቢሆንም ከሆነ በኋላም ሰብአዊ እርዳታ ለተፈናቃዮቹ በአስቸኳይ ሊደርስላቸው ይገባል። በበጀት ረገድ ምን እየተሠራ እንደሆነ አላውቅም። የሆነ ሆኖ የዘንድሮን ያክል የከፋ ባይሆንም መፈናቀል በእየዓመቱ እየተከሰተ ነው። በአሁኑ ወቅት ብዙዎቹ ተፈናቃዮች በጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ ናቸው። ግዜያዊ መጠለያዎቹ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለሟሟላት እንኳ አይችሉም። የንፅህና መጠበቂያ እና መፀዳጃ ሥፍራዎች አልተመቻቹላቸውም። ከምግብና መጠጥ እጥረቱ በተጨማሪ መሠረታዊ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት የማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ናቸው። በዚያ ላይ ጊዜያዊ መጠለያዎቹ ውስጥ ሳይገቡ በአካባቢው ሰዎች ተጠግተው የሚኖሩም አሉ። ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር መንግሥት መጠባባቂያ በጀት በዚህ ሥም ማዘጋጀት እና የሰብአዊ እርዳታ ማድረግ እንዲሁም መልሶ ማቋቋም ይኖርበታል። 

ኦሕዴድ እና ብአዴን በሕወሓት የበላይነት ይመራ የነበረውን የኢሕአዴግ ፖለቲካ ከውስጥ መነቅነቅ ሲጀምሩ ተቃዋሚዎች ተደስተው ነበር። ኦሕዴድ በክልሉ አንፃራዊ የተቃውሞ-ነጻነት ሲፈቅድም እንዲሁ ተደስተዋል። ነገር ግን የዐብይ ጠቅላይ ሚኒስትርነት እና የተቃዋሚውን ቋንቋ መነጋገራቸው ድንጋጤ ፈጥሯል። ባጭሩ ተቃዋሚዎች ከኢሕአዴግ ጋር “መደራደር ይገባናል” ሲሏቸው የነበሩት ጉዳዮች – የፖለቲካ እስረኛ ማስፈታት እና አንዳንድ አዋጆችን ማሻሻል፣ በጥቅሉ የፖለቲካ ምኅዳሩን የማስፋት ጥያቄ እና ተቋማትን ከፖለቲካ ጥገኝነት ማላቀቅ – የመሳሰሉትን ነገሮች በራሳቸው በኢሕአዲጉ ሊቀ መንበር ሲቀነቀን፣ ተቃዋሚዎች አጀንዳ አጥተዋል። የድንጋጤያቸው ምንጭም ይኸው ይመስላል። በርግጥ የፖለቲካ ድርጅቶቹ ሲያልፉበት ከነበረው ፈታኝ ሁኔታ አንፃር በመዳከማቸው የፖለቲካ ለውጦችን እያዩ ከወቅቱ ጋር የሚሔድ ፖለቲካ መጫወት ቢያቅታቸው የሚገርም አይደለም። 
የፖለቲካ ድርጅቶቹ “የአኩራፊዎች እና የጡረተኞች መሰብሰበቢያ” እየተባሉ ሲተቹ ከርመዋል። ምንም እንኳን ከላይ ያሉ ቢመስልም ውስጣቸው በብዛት ባዶ ነው። ለኢትዮጵያ (100 ሚሊዮን ሕዝብ) የሚመጥን የመምራት አቅም ያላቸው ሰዎች ስብስብ የላቸውም። በመገናኛ ብዙኃን በሚራገቡ አጀንዳዎች ላይ የመንግሥትን አቋም ካወቁ በኋላ ተቃራኒውን ይዘው ከመሟገት በላይ ርዕዮተ ዓለማዊ አቅጣጫ የሌላቸው ድርጅቶች ቀላል አይደሉም። አንዳንዶቹ ከላይ ያሉትን ታዋቂ ሊቀ መንበሮቻቸውን የሚተኩ አባላት እንኳን አላፈለቁም። ኢትዮጵያን መምራት የሚችሉ በርካቶች ድግሞ ወይ የፖለቲካውን ትኩሳት እየፈሩ አንገታቸውን ደፍተው ‘ዝምተኛ-ብዙኃን’ መሐል ተቀብረዋል፤ አልያም ተሰድደዋል። በዚህም ምክንያት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶቹ የኢሕአዴግ የፖለቲካ አጨዋወት ሲቀየር፣ የራሳቸውን አጨዋወት በመቀየር ፈንታ ድንጋጤ ውስጥ መግባታቸውን የሚያሳብቁ ነገሮች ናቸው አሁን የሚታዩት። “እስረኛ የፈቱት ወደው ሳይሆን ተገደው ነው”፣ “ሰውዬው ኢሕአዴግ ናቸው፣ ኢሕአዴግ ከሚቀየር ግመል በመርፌ ቀዳዳ…”፣ “ጥቂት ሰዎች ተቀየሩ ማለት ነገሮች ተቀየሩ ማለት አይደለም”፣ “ይች ይቺ ተቃውሞ ለማስቆም የተፈጠረች የኢሕአዴግ ሴራ/ድራማ ናት”… እነዚህ ንግግሮች ለቀጣዩ የፖለቲካ ጫወታ ፋይዳቸው ምን እንደሆነ ሊገባኝ አይችልም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእያንዳንዱ ንግግራቸው እና ድርጊታቸው የብዙዎችን ቀልብ እየገዙ እና “አለቀለት” ለተባለው ኢሕአዴግም አዲስ ነፍስ እየዘሩበት ነው። ይህ የገባቸው ተቃዋሚዎች የማጥላላት እና የማጣጣል ትርክት ለመፍጠር እየተፍጨረጨሩ ነው። ይህ ፖለቲካዊ ኪሳራ ሊያስከትል ይችላል።  የሴራ ፖለቲካዊ ትንተና እና ጫወታም መሬት ላይ ጠብ የሚያደርገው እንደሌለ ከበቂ በላይ ታይቷል። የብሽሽቅ ፖለቲካም ጉንጭ ከማልፋት በላይ ትርፍ የለውም። ሕዝብን “ተታልላችኋል” እያሉ መውቀሱም አግባብ አይደለም። ምክንያቱም ሕዝቡ የሚያየውን መዳኘት ይችላል።
ይልቁንም (በፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ ምክንያት የተከተለው እና ሁለተኛው ደረጃ) “የማማረር ፖለቲካ” ተላቅቆ፣ ወደ አንደኛው ደረጃ ፖለቲካ ማለትም አማራጭን የማሳየት እና ሕዝባዊ መሠረት የመጣል ፖለቲካ መጫወት ያስፈልጋል። የፖለቲካ ምኅዳሩ ለይቶለት ሳይዘጋ በፊት ለእስር እና ስደት የተዳረጉት ፖለቲከኞች ጥያቄ ምንድን ነበር? የሕዝቦች ጥያቄ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ደኅንነት እንዴት ነው የሚጠበቀው? ድንቁርና እና ድህነትን እንዲሁም ኢፍትሓዊነትን ለመቀነስ አገራችን ምን ዓይነት የፖለቲካ ስርዓት መከተል አለባት? አሁን ሰዐቱ ይህንን የመመለስ ነው። 
የፖለቲካ ድርጅቶች የሚሠሩት ሥራ በየአደባባዩ ሰልፍ ከመውጣት እና የተቃውሞ መግለጫዎችን ከማውጣት በላይ ነው። አብላጫ የምክር ቤት ወንበር አግኝተው መንግሥት ሲመሠርቱ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አማራጭ በመኖራቸው ብቻ የሚሠሯቸው ሥራዎችም ብዙ ናቸው። በዋነኝነት አማራጭ የአገር አመራር አቅጣጫ ማሥመር አለባቸው። አገሪቱ ወዴት ነው መሔድ ያለባት? እንዴት ነው ወደዚያ መሔድ የምትችለው? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ የማኅበረ–ኢኮኖሚያዊ ፍልስፍናቸውን ለሕዝብ ማስተዋወቅ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ብቁ የሆኑ አመራሮችን መሰብሰብ እንዲሁም እየኮተኮቱ ማሳደግ አለባቸው። አለበለዚያ እንደሥማቸው ተቃዋሚ ብቻ ሆነው ይቀራሉ። 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ “ተፎካካሪ” የሚለውን መጠሪያ እንደአስታራቂ መርጠዋል። እኔ እስካሁን ያለውን ፖለቲካ የገዢ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፖለቲካ ብለው እመርጣለሁ። ምክንያቱም ገዢው ፓርቲ አገር ለመምራት ወይም ሕዝብ ለማገልገል ሳይሆን ፈላጭ ቆራጭ ገዢ ለመሆን ነው ሲተጋ የኖረው። ተቃዋሚዎች ደግሞ የገዢውን አገዛዝ ሲቃወሙ እዚህ ደርሰናል። ኢሕአዴግ መቀ:የር እፈልጋለሁ ብሎ ጭላንጭል ሲያሳይ፣ የነገውን ለነገ ትተው ተቃዋሚቹም መቀየር አለባቸው። እውነተኛ አማራጭነታቸውን ለማሳየት አጋጣሚውን መጠቀም ይኖርባቸዋል። አለበለዚያ ነገ ኢሕአዴግ ስህተት እስኪሠራ ጠብቆ “ይኸው ይሄንኑ ፈርተን ነበር” ማለት አያዋጣም፤ በሥሙ ብዙ ነገር ለሚፈፀመው ሕዝብም የሚያተርፍለት ነገር የለም። ምንም እንኳን ወደፊትም የመሔድ ወይም ወደ ኋላ የመመለስ ዕድሉ ዕኩል ቢሆንም አሁን (በዚህ ቅፅበት) ከሞላ ጎደል ሰፊ የፖለቲካ ምኅዳር አለ። የፖለቲካ ምኅዳሩ ስፋት ወደኋላ እንዳይመለስ ሕጋዊ እና ተቋማዊ መሠረት አፍርቶ ለዘለቄታው ዋስትና እንዲያገኝ ከመሥራት ጎን ለጎን አማራጭ የፖለቲካ መፍትሔን ለሕዝብ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል። ሕዝብ ውስጥ የሰረፀ ፖለቲካዊ የመፍትሔ ሐሳብ ካለ፣ አመንጪዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ባይኖሩም እንኳን የግዜ ጉዳይ ቢሆን ነው እንጂ ግቡን ይመታል።
አማራጭ የፖለቲካ ሐሳብ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ካሉ እኛም “ገዢ” እና “ተቃዋሚ” እያልን ከመፈረጅ እንገላገላለን። “ተፎካካሪ” ከሚለው እና የሥልጣን ሽሚያን ብቻ ከሚጠቁመው ቃልም ይልቅ “አማራጭ” የፖለቲካ ድርጅቶች የሚለውን እንጠቀማለን። አማራጭ የፖለቲካ ድርጅቶች ካሉ፣ የድርጅቶቹን ሥም ስንሰማ የገዢውን ሐሳብ በመቃወማቸው ሳይሆን፣ በአማራጭ ሐሳባቸው እናስታውሳለቸዋለን። ‘ምረጡን’ ብለው ሲመጡም እንደተቃዋሚ “ተቃውሟቸውን” ወይም እንደ ተፎካካሪ “ፉክክራቸውን” ሳይሆን አማራጭ ሐሳባቸውን እንመርጣለን። 
Time to move on, and choose your place in the board. 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ተስፋን-በጥንቃቄ (cautious optimism) ካነገቡት ሰዎች አንዱ ነኝ። የተስፋዬ መሠረቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን የመጡበት መንገድ፣ የገቧቸው ቃልኪዳኖች እና አሁን የታየው መረጋጋት ናቸው። አሁን የታየው መረጋጋት ስል የቄሮዎች የአደባባይ ተቃውሞ መቆሙን ማለቴ አይደለም። ተቃዋሚዎችን እያሳደዱ መከታተል፣ ማዋከብ እና ማሰር ርቀን ሳንሔድ አምና ከነበረው አንፃር እንኳ ልዩነቱ የትየለሌ ነው። ለዚህ የራሴን ስሜት እና ተሞክሮ ነው በምሳሌነት የማቀርበው። በፊትም አሁንም ሐሳቤን በነጻነት እገልጻለሁ። ነገር ግን አምና እና ካቻምና ከያንዳንዱ ጽሑፎቼ/ንግግሮቼ ቀጥሎ እስር ይመጣል እያልኩ እየሰጋሁ ነበር የማደርገው። አሁን ምን ያክል ይዘልቃል የሚለው ቢያሰጋኝም እታሰራለሁ እያልኩ በየደቂቃው አልባትትም። በፊት ሲያስሩ፣ ሲያዋክቡ እና ሲከስሱ ከነበሩት አንዳንድ ኃላፊዎችም ጋር ባጋጣሚዎች አውርቻለሁ። ከላይ ለውጥ ያለ ሲመስል እነርሱም ከታች ይለወጣሉ። አንድ ከፍተኛ የፌዴራል ፖሊስ ኃላፊ የኛን እንቅስቃሴ “የበፊቱ አመራር እንደ ወንጀል ያየው ስለነበር ወንጀል ነበር። አሁን ግን እንደወንጀል አይታይም” ብለውኛል። ይህ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰዎች ላይ የተፈጠረው የ”ለውጥ መጥቷል” ስሜት እና የፍርሐት ማጣት ከተጠቀሙበት ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ትልቅ ዕድል ነው። ሌላው ሌላው ሁሉ ለዘለቄታው ለመቅረፍ ረዥም የፖለቲካ እና የሥራ ባሕል አብዮት የሚፈልግ ፈርጀ ብዙ የሁላችንም ችግር ነው።
አሁን ስጋቴ ከግዜ ጋር የሚደረገው ፉክክር ነው። ጊዜ መጨቆኛ መዋቅሩን ለተቆጣጠሩት ጨቋኞችም፣ ባዶ እጃቸውን ለገጠሟቸው ተጨቋኞችም ዕኩል ነው የሚነጉደው። ማርቲን ሉተር ኪንግ (ትንሹ) “ጊዜ ከደጋጎች ይልቅ ክፉዎቹ የተሻለ የሚጠቀሙበት ይመስለኛል” ብሎ ጽፎ ነበር። ለዚህ ነው ማንም መጣ ሔደ ለመሪዎች ለውጥ ማስኬጃ በሚል ሰበብ አላግባብ ጊዜ መሸለም የማያስፈልገው። እውነተኛው ለውጥ በተቋማት ለውጥ እንጂ በሰዎች ለውጥ አይመጣምና! 
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቁ ተልዕኮ የ2012ቱ የኢትዮጵያ አገር ዐቀፍ ምርጫ ነጻ እና ርትዓዊ እንዲሆን ማድረግ ነው ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን ይህን “ብዙ መጠበቅ” ነው ብለውታል የኢትዮጵያን ጉዳይ በመተንተን የሚታወቁት ፈረንሳዊው ሬኒ ሊኾርት። እሳቸው እንደሚሉት ኢሕአዴግ የውስጥ ልዩነቱን ፈትቶ ሠላም ካላላገኘ፣ አገሪቱም ሠላም አታገኝም። ተረኩ የፓርቲውን መበተን ከኢትዮጵያ መበተን ጋር የሚያስተካክል ነው። የፓርቲው አባላት ሁሉንም ክልላዊ መዋቅሮች በተቆጣጠሩበት እንዲሁም አማራጭ የተደራጁ ኃይሎች በሌሉበት ሁኔታ ይህ አይሆንም የሚባል አይደለም። ነገር ግን ይህ የኢሕአዴግ ውስጣዊ ክፍፍል ተቀርፎ የሥልጣን መደላድል ከመጣ ሁሉም ነገር ወደነበረበት የጭቆና አዙሪት ይመለሳል የሚል ስጋት አለኝ። 
የጠ/ሚኒስትሩ የሥልጣን ምንጭ ምንድን ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በኢሕአዴግ ውስጥ የተቃዋሚውን ቋንቋ በመናገር ነው ለሥልጣን የበቁት። በዝግ ስብሰባቸው ምን እንደተመከረ፣ ምን ዓይነት የማመቻመቻ ድርድር/ቃልኪዳን አድርገው አብላጫ ድምፅ ለማግኘት እንደቻሉ አናውቅም። ዞሮ ዞሮ መርጠው ለዚህ ያበቋቸው የኢሕአዴግ አባላት ናቸው። የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር (ኃይለማርያም ደሳለኝ) ያለግዜያቸው እንዲለቁ፣ እሳቸውም ከኢሕአዴግ ባፈነገጠ አካሔድ የኢሕአዴግን ሥልጣን እንዲቆናጠጡ ያደረጋቸው ሕዝባዊ ተቃውሞ ነው። ስለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ምንጭ ኢሕአዴግ እና ሕዝባዊ ተቃውሞዎች በጣምራ ነው።  ይህ በሥልጣን ዘመናቸው ሊሠሩ የሚችሉትን ማመላከቻ ነው። በርግጠኝነት ኢሕአዴግን ማፍረስ አይፈልጉም፤ ምናልባት ማደስ ግን ይፈልጋሉ። በምን ዓይነት መንገድ? ምናልባትም ሕዝባዊ ጥያቄዎችን በመመለስ። ተቃርኖው የሚጀምረው እዚህ ጋር ነው። 
የኢሕአዴግ (አብዮታዊ ዴሞክራሲ) ትልቁ ችግር ሕዝባዊ ጥያቄዎችን በራሱ አውጥቶ፣ መልሱንም በራሱ መንገድ መስጠት ነው።  ዴሞክራሲ ደግሞ በተቃራኒው ሕዝብ ችግሩን እንዲናገር በመፍቀድ እና ችግሩን በመቀበል፣ መፍትሔው ከሕዝቡ ፍላጎት አኳያ እንዲመለስ ማድረግ ነው። ይህ ሕዝባዊ ቅቡልነት የሚያስገኝ አሠራር ግን የኢሕአዴግን ሕልውና አደጋ ላይ ሊጥልበት ይችላል። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በልባቸው የያዙት፣ በቅንነት የተመራ የለውጥ ፍላጎት ካለ ይህንን ፈተና ለመጋፈጥ መዘጋጀት አለባቸው። የሕዝብ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያለባቸው መልሶቹ ኢሕአዴግን ወደመቃብር የሚልኩት ቢሆንም እንኳን ነው። ይህ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢስማሙባቸው እንኳ በዝግ መክረው ለመረጧቸው የኢሕአዴግ አባላት የሚያስማማቸው ይመስላችኋል? እኔን ያጠራጥረኛል።
በ2012 ነጻ እና ርትዓዊ ምርጫ ለማድረግ ከሚያስፈልጉት ነገሮች ውስጥ ዋነኛው ሜዳውን ለሁሉም ዕኩል ማደላደል እና ሁሉንም አካላት ማሳተፍ ነው። በርግጥ ምርጫ ቦርድ ያለበትን አድሎ ቀርፎ፣ ለማንም ወገንተኛ ባልሆኑና ልምዱና የትምህርት ዝግጅቱ ባላቸው ሰዎች ቢመራ አንድ ነገር ነው። ነገር ግን የፖሊስ እና ደኅንነት አካላት (ከሥልጣን ያዥው ውጪ ያሉት) ተወዳዳሪ ፓርቲዎች እና መራጮችን ማዋከብ ማቆም አለባቸው። የተሰደዱ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ድርጅቶችም ተስፋ አስቆርጦ ያሰደዳቸው እና ነፍጥ ያስነሳቸው መንስዔ ተቀርፎ ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ዋስትና መስጠት የግድ ነው። ይህንን ለማድረግ በአንድ ወገን “ሁሉን ዐቀፍ ድርድር መደረግ አለበት” የሚል ሙግት አለ። የዚህ ሙግት ዋነኛ አራማጅ በቅርቡ ከእስር የተፈታው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ነው። በሌላ በኩል “ድርድሩ የግድ አያስፈልግም” የሚሉም ወገኖች አሉ። ለምሳሌ ፖለቲከኛው ግርማ ሰይፉ ጋር በአንድ ጫወታችን መሐል ‘ተቃዋሚው ከኢሕአዴግ ጋር የግድ መደራደር የለበትም። ኢሕአዴግ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ተወጥቶ ለነጻ ውድድር የምርጫ ሜዳውን በሐቅ ካመቻቸለት ከዚያ በኋላ ያለው የተቃዋሚው ሥራ ነው’። እርግጥ አሁን ከውስጥም ከውጭም ያለው ግፊት ከፊል ፍሬ አፍርቶ፣ “ለውጥ አይመጣም” ከሚል ድፍንፍን ያለ ግዜ “ምን ዓይነት ለውጥ ይመጣ ይሆን?” ወደሚል ጉጉት ተሸጋግረናል። ይህንን የለውጥ ተስፋ ወደ ተግባር እንዲለወጥ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ብዙ ይጠበቃል። 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ባለው የተዝናና ሁኔታ ለቀጣዩ ምርጫ አገሪቷን ቢያዘጋጁ አገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች አፈር ከላሱበት ተነስተው በውስጣዊ ወጀብ የሚሰቃየውን ኢሕአዴግ መፈተናቸው አይቀሬ ነው። ፈተናው ኢሕአዴግን ወደለመደው ጫወታ የመመለስ ዕድሉም እንዲሁ ሰፊ ነው። ምናልባት አቶ ዐብይ አሕመድ፣ አቶ ለማ መገርሳና ጥቂት የለውጥ ፊቶች በምርጫ ክልላቸው በብልጫ ያሸንፉ ይሆናል። ነገር ግን በሌሎቹ የምርጫ ክልሎች ውስጥ ሕዝቡ ላይ ግፍ ሲያደርሱ የነበሩ የኦሕዴድ ካድሬዎች ለሕዝቡ ጥቅም ሲታሰሩ ሲፈቱ የከረሙትን የኦፌኮ አባላትን አያሸንፉም። ከኦሮምያ ውጪም ተመሳሳይ ሁኔታ ይኖራል። ኢሕአዴግ ይህን ፈታኝ ሁኔታ በተለመደው የማዋከብ፣ የማሳደድ እና የማሰር ስልት ለመጋፈጥ የሞከረ ዕለት ደግሞ የተካበው ተስፋ ሁሉ ይናዳል። ጫወታው ፈረሰ፤ ዳቦው ተቆረሰ!
በአንድ ወቅት ከሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ጋር ቃለ ምልልስ ሳደርግ፣ “ኢትዮጵያን የሚያተራምሳት ዴሞክራሲ ማጣት አይደለም፤ የዴሞክራሲ ተስፋ ማጣት ነው” ብሎኝ ነበር። እውነትም የዛሬውን አገራዊ መረጋጋት ስንመለከተው በተስፋ ላይ የቆመ መረጋጋት ነው። የዚህ ተስፋ መፍረስ፣ የሚያፈርሰው ብዙ ነገር ነው። 
በሥልጣን መጫወት፣ በእሳት መጫወት!
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐቀኛ የለውጥ ፍላጎት ካላቸው፣ ‘ይህ በኔ ዘመን አይከሰትም’ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። ይህ ግን የሰውን ራስ ወዳድ ተፈጥሮ እንዲሁም የሥልጣንን አባላጊነት ካለመረዳት የሚመነጭ ነው። ብዙዎቹ የዓለማችን አምባገነኖች በአንድ ወቅት ሐቀኛ የለውጥ አርበኞች ነበሩ። አንዴ የሥልጣን መደላደል ከፈጠሩ በኋላ ግን በምናባቸው በሚፈጥሩት “የለውጡ ጠባቂነት” ሚናቸው ተሸፍነው ከቀዳሚዎቻቸው የበለጠ ጉዳት ያደርሳሉ። ብዙዎቹ የለውጥ አርበኞች የመጣው ለውጥ እንዳይቀለበስ በሚል ሰበብ አስባብ ለረዥም ግዜ ሥልጣን ላይ ይከርማሉ፣ የሚያምኗቸውን ሰዎች ብቻ መርጠው ቁልፍ ቦታ ላይ ይሾማሉ፣ የለውጥ ሒደታቸውን የተቃወሙትን ‘አድኀሪያን’ በፈርጣማ ጡንቻዎቻቸው ይጨፈልቃሉ፣ በመጨረሻም ‘ለውጥ’ የሚሉት የራሳቸውን ሥልጣን ተቆናጦ መቆየት ብቻ እስኪመስል ድረስ ፈላጭ ቆራጭ ይሆናሉ – በአጭሩ አምባገነን ይሆናሉ። ከለውጥ አምጪነት፣ መለወጥ ያለበት አካል ወደ መሆን ይሸጋገራሉ። 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ለውጪያዊ መረጋጋት እና ለውስጣዊ መስማማት ግዜ ባገኙ ቁጥር፣ ሰው ናቸውና በሥልጣን የመበላሸት ዕድላቸውም ሰፊ ነው የሚሆነው። የሥልጣን መደላደል “ከእኔ ወዲያ ላሳር” ወደሚል ትምክህት ይመራቸዋል። ስለዚህ ከላይ “አሁን ያለው የተዝናና ሁኔታ” ያልኩት በእርሳቸው ይሁንታ ብቻ የመጣው መልካም ጊዜ ለፈተና ግዜ አይፀናም። ሹመኞች በጭንቅ ግዜ የማይገቡት ቃል የለም። ዕውቁ ፖለቲከኛ አንዷ-ዓለም አራጌ “we are victims of broken promises” (‘እኛ የተከዱ ቃልኪዳኖች ሰለባ ነን’) ያለው በጭንቅ ግዜ የተገቡ ቃል ኪዳኖች፣ በመረጋጋት ግዜ ስለሚዘነጉ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለገቧቸው ቃልኪዳኖች ማስተማመኛ አስቸኳይ ሕጋዊ ዋስትና ይስጡ። የሚሻሩት ዐዋጆች አሁኑኑ ይሻሩ፣ የሚሻሻሉት ዐዋጆች አሁኑኑ ይሻሻሉ፣ የሚጨመሩት ድንጋጌዎች አሁኑኑ ይጨመሩ… የተቋማት ገለልተኝነት ሥራ መሠረቶች አሁኑኑ ይጣሉ… ለቀጣዩ ምርጫ ያለው መሰናዶ በሕግ እና ተቋማዊ አግባብ በአስቸኳይ ይፈፀሙ። የፖለቲካ ዕርቅ ጥሪዎች በነቢብ ሳይሆን በገቢር ይደረጉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ነገሮች በማለዳ ማድረግ ከቻሉ ብዙዎቹ ለውጥ-ፈላጊ የዓለማችን ሰዎች ከወደቁበት ገደል ይተርፋሉ። ሥማቸውም “ከአብዮት ከዳተኞች” ተርታ ሳይሆን፣ ምናልባትም ከዘመን ባንዴ ብቻ ከተከሰቱት “ከጨቋኞች መሐል የወጡ የነጻነት ፋና ወጊዎች” – ከእነ ፍሬድሪክ ደ ክላርክ ተርታ ይመደባሉ። ምርጫው የእርሳቸው ነው፤ ራስን ከራስ ማዳን ወይም በሥልጣን መጫወት።

(ይህ ጽሑፍ በ1992 ከታተመው “Ethnic Federalism in a Dominant Party State: The Ethiopian Experience 1991-2000” ከሚለው የሎቪስ አለን ጥናት ውስጥ ካለ ንዑስ ርዕስ ተቀንጭቦ የተተረጎመ ነው።)
በሽግግር መንግሥቱ ግዜ የታተሙት ዐዋጆች ሁሉ ክልሎች እና ንዑስ ክፍሎቻቸው የማዕከላዊ መንግሥቱ ምንዝሮች እንደሆኑ ተመልክቷል። የሽግግር ምክርቤቱ ለብሔሮች ‹የራስን ዕድል በራስ መወሰን› የሚል ቃል በስተቀር የክልሎች ሥልጣን የተገደበ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ያልተማከለ፣ አሀዳዊ፣ ወይም ፌዴራላዊ ስለመሆኑ ምንም አይታወቅም ነበር። የ1987ቱ ሕገ መንግሥት ግን ይህንን ግራ መጋባት ቀርፎታል። አሀዳዊውን ስርዓት በመተው ፌዴራላዊውን እንደሚከተል በግልጽ ያስቀምጣል (አንቀፅ1)። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የፌዴራል አወቃቀር ላይ በርካታ እንግዳ እና አሻሚ ነገሮች አሉ። ይህም ከነባር ፌዴሬሽኖች የፌዴራል ኅልዮት እና አተገባበር አንፃር ይገጥማሉ ወይም ይጋጫሉ የሚለውን የመደምደሙን ነገር  ከባድ ያደርገዋል። የመገንጠል መብት፣ ለፌዴሬሽኑ አባል አገረ-መንግሥታት ፈንታ ሉዓላዊነት “ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች”  መሰጠቱ፣ ገለልተኛ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት አለመኖር፣ እና ጠንካራው የሥራ አስፈጻሚ አካል ለዚህ ውስብስብ ባሕሪው ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው።
የክልሎች ሥልጣን ተቃርኖ
በኢትዮጵያ ፌዴራል አወቃቀር ግልጽ የሆነ አያዎ እንዳለ ብዙ ጸሐፊዎች አስፍረዋል። በአንድ በኩል ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የተወሰኑ ሁኔታዎችን አሟልተው የመገንጠል መብት ተሰጥቷቸዋል። ይህ ከሌሎች የፌዴራል ስርዓታት በተለየ የፌዴራሉ አካላትን ነጻነት የተለጠጠ ያደርገዋል። በሌላ በኩል፣ የአባል አገረ-መንግሥታቱ ሥልጣን በአንፃሩ በጣም ውሱን ነው። የክልል መንግሥታቱ ሥራቸውን ለመሥራት በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ጥገኛ ናቸው። በብሬዝኬ እንደተገለጸው፣ ሕገ መንግሥቱ “ጥቂት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቶችን መድኅን” ያቀርብና፣ እስከ መገንጠል በሚለው መካከል ምን እንዳለ ስላልተገለጸ፣ ጠባብ የራስን ዕድል የመወሰን ቅርፅ እና የተገደበ የባሕል ነጻነት ያጎናፅፋል።”
ዱካቼክን ጨምሮ የተወሰኑ የፌዴራሊዝም አጥኚዎች የመገንጠል መብት አንድን አገረ መንግሥት ፌዴራላዊ ለመባል እንዳይበቃ ያደርገዋል በማለት እስከመከራከር ይደርሳሉ። የመገንጠል መብት ዜጎች ለማዕከላዊ መንግሥቱ ያላቸው ታማኝነት ቀስ በቀስ እንዲቀንስ ያደርገዋል። በተጨማሪም፣ ክልሎች ኅብረቱን የመልቀቅ ነጻነቱ ሲኖራቸው፣ በማዕከሉ እና አገረ መንግሥታቱ መካከል ያለው የፖለቲካ መዋቅር ከፌዴሬሽን ይልቅ የላላ ንዑስ ብሔራዊ ቁጥጥር ያለው ኮንፌዴሬሽን ዓይነት ይሆናል። ሉዓላዊነት ለብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መሰጠቱም ቢሆን ብሔረሰቦች ከፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን ከክልሉ አገረ መንግሥታት ሳይቀር እንዲገነጠሉ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ያልተለመደ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓት ከመሆኑም ባሻገር የሚመስለው አንድም የፌዴራል ስርዓት ዛሬ ላይ የለም። የመገንጠል መብት መኖር ኢትዮጵያን ፌዴራላዊ ለመባል አያበቃትም የሚለው እንደ አስተያየት ሰጪው ይወሰናል። ሌሎች የፌዴራል ስርዓቶችን ብንመለከት፣ አንዳንድ የዘውግ ቡድኖችን ወይም ክልሎችን የመገንጠል መብት የሰጡ ስርዓቶች አሉ። ነገር ግን እነዚህኞች ከሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች ውጪ የተሰጡ ናቸው።
እንደስፔንና ካናዳ ያሉ ኅብረብሔራዊ ፌዴሬሽኖች መሰል ፈቃዶችን በዘውግ ለተለዩ ክልሎች ሰጥተዋል። ሆኖም እነዚህ ፈቃዶች ከሕገ መንግሥት ውጪ ነው የተደነገጉት። ይህም መዋቅሩን የበለጠ ተለዋዋጭ አድርጎታል። ይህንንም ማድረግ የተቻለው ቀስ በቀስ የወቅታዊ የፖለቲካ ፍላጎቶችን ለማሟላት ነው። ኩዩቤክ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ከካናዳ ፌዴሬሽን ለመገንጠል እንቅስቃሴ ሲጀምሩ፣ በካናዳ የፖለቲካ ሒደት ውስጥ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ሳያስፈልግ ትልቅ ለውጥ ተደርጓል። የኪዩቤክ ገዢ ፓርቲ በሪፈረንደም ከተሳካለት ሉዓላዊ አገር የመፍጠር መብቱን አረጋግጧል። እኤአ የ1995ቱ የሉዓላዊነት ዐዋጅ የዚያን ዓመት የተካሔደውን ሪፈረንደም ማሸነፍ ቢችሉ ኖሮ ለኪዩቤኮች የመገንጠል ሕጋዊ ዕድል ሰጥቷቸው ነበር። 
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከስፔኑ የ1978 (እኤአ) ሕገ መንግሥት ጋር ሊነፃፀር ይችላል። ልክ እንደ ኢትዮጵያ ስፔን ደም አፋሳሽ የመንገንጠል ንቅናቄ እና ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ታሪክ ችግር ነበረባት። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ፣ የስፔን መንግሥት የሆነ ዓይነት ነጻነት ማስተዋወቅ ፈልጓል። ነገር ግን ክልሎቹን እና የጥያቄ አቅራቢዎቹን ድንበሮች በሕገ መንግሥታዊ አንቀፆች ለመለየት አልሞከረም። በምትኩ፣ “ራስ ገዝ ማኅበረሰቦች” በሚል ቀስ በቀስ የሚያድግ ራስን የማስተዳደር ሥልጣን ተሰጣቸው። ይህም የሆነው በሌሎች የፌዴራል መንግሥታት ከተለመደው በተለየ ሁኔታ በክልል እና ማዕከላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ነበር። ሆኖም፣ ዋናዎቹ የመከላከያ እና የኢኮኖሚ አውታሮች በማዕከላዊው መንግሥት ቁጥጥር ሥር ናቸው። ራስ ገዝ ማኅበረሰቦቹ ሁሉም እንደየ ድርድራቸው የተለየ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ነው የተሰጣቸው። ይህ አለመመጣጠን ከአዲሱ የራሽያ ፌዴሬሽን ጋር አንዳንድ መመሳል አለው። በ1992ቱ (እኤአ) የራሽያ ፌዴሬሽን ስምምነት የተለያዩ የዘውግ ሪፐብሊኮች የመገንጠል መብት ተሰጥቷቸው ነበር። ይህ የሶቪየት ኅብረት ግዜም የነበረ ነው። ሆኖም ስምምነቱ (እኤአ) በ1993 ሲከለስ ተሰርዟል። በፈንታው፣ ማዕከላዊው መንግሥት ከዘውግ ሪፐብሊኮቹ ጋር ሥልጣን የመጋራት የሁለትዮሽ ስምምነቶችን መደራደር የጀመረበት “ድኅረ ሕገ መንግሥታዊ ሒደት” ውስጥ ገብቷል። 
የካናዳ፣ ስፔን እና ራሽያ ሕገ መንግሥቶች የመገንጠል መብትን አላካተቱም። ነገር ግን በተግባር የተለጠጠ “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መድኅኖችን” ለአባላቱ የተለያየ የራስ ገዝ አስተዳደር ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ግን በተቃራኒው መሔድን መርጧል። የመጨረሻውን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ማለትም የመገንጠል መብትን ሰጥቶ የክልሎቹን የለት ጉዳዮች ለመፈፀም የሚያስፈልገውን ሥልጣን ግን ባንፃሩ ይገድበዋል። መሬት እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ለምሳሌ የሚተዳደሩት በፌዴራል ሕግጋት ነው። የክልል መንግሥታቱ የዕለት ተለት ሥራቸውን ለመከወን የአገርዐቀፉን መደብ መከተል አለባቸው። ይህም ማለት በፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚፀድቀው የአምስት ዓመት የኢሕአዴግ ዕቅድ በሁሉም የክልል መንግሥታት፣ በያንዳንዱ የአስተዳደር እርከን ተፈፃሚ መሆን አለበት። የክልል የገቢ ምንጮች ከፌዴራሉ አንፃር ጥቂት እና እዚህ ግባ የማይባሉ ናቸው። ይህም ማለት የክልል መንግሥታት ሥራዎቻቸውን ለመከወን የፌዴራል መንግሥቱ ድጎማ እና ሥጦታ ላይ ጥገኛ መሆን አለባቸው። 
ቁጥጥር አልባው ገዢ ፓርቲ 
በርካታ የፌዴራሊዝም አጥኚዎች እንደሚሉት አንድ ፌዴሬሽን መንግሥት ከሕግ በታች ካልሆነ ሐቀኛ ሊሆን አይችልም፡፡ የፖለቲካ ኃይሎቹ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ካላከበሩ የተሰጡት ዋስትናዎች ዋጋ የላቸውም፡፡ መንግሥት ለሕግ ታዛዥ መሆኑን ለማረጋገጥ የፌዴራል ስርዓቱን አተገባበር እና የፖለቲካ አመራሮችን ሥራዎች መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን የሕግ ማዕቀፉ በራሱ የፌዴራል ስርዓቱ የፌዴራል እና ክልሎች ግንኙነትን በመወሰን ረገድ መዋቅራዊ የቁጥጥር ድንጋጌዎችን መጣል አለበት፡፡ እዚህ ጋር መነሳት ያለበት ጥያቄ ‹የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የፖለቲካ አመራሩ የፌዴራል መርሖችን እንዳይጥስ በቂ የቁጥጥር መንገዶችን አስቀምጧል ወይ?› የሚለው ነው፡፡
እንደ አሜሪካው ዓይነት የፌዴራል ስርዓት ውስጥ፣ የሕግ አውጪው ሁለተኛ ምክር ቤት የሌሎች የፌዴራል ተቋማትን ሥልጣን በመቆጣጠር የሥልጣን ክፍፍልን በተመለከተ መሠረታዊ ሚና ይጫወታል፡፡ እንደ አውስትራሊያ እና ካናዳ ባሉ የፓርላሜንታዊ ፌዴራል ስርዓቶች ውስጥ ደግሞ ሁለተኛው ምክር ቤት የአገርዐቀፉ መንግሥት ሕጋዊ ተግባራት ውስጥ ክልሎቹ መማከራቸውን ያረጋግጣል፡፡ በኢትዮጵያ ሁለተኛው ምክር ቤት፣ ማለትም የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ አንዳቸውንም መሰል ዓይነቶቹን ክፍተቶች አይሞላም፡፡ የኢትዮጵያ ስርዓት በተፈጥሮው ፓርላሜንታዊ ነው፤ ነገር ግን የፕሬዘዳንታዊ ስርዓት ፀባይ አለው፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና በአፅፈፃሚው አካል መካከል ያለው ግንኙነት የሚዳኘው በምክር ቤቱ መርሕ መሆኑ በአሜሪካ ሕገ መንግሥት እንደሚታየው ዓይነት የሥልጣን ክፍፍልን እና የቁጥጥር መንገዶችን ይቀንሳል፡፡ ነገር ግን ከሌሎች የፓርላሜንታዊ ስርዓቶች በተለየ ሠራዊቱ እና የምኒስትሮች ምክር ቤት ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቅ ሥልጣን አለው፡፡ በተጨማሪም፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በሕግ ማውጣት ሒደት ውስጥ የሚቆጣጠርበት መንገድ የለውም፡፡ ይህም ከሌሎች ባለሁለት ምክር ቤት ስርዓቶች አሠራር ጋር ይቃረናል፡፡ ከላይ እንደተገለጸው፣ ሕገ መንግሥቱ አደጋ ላይ በሆነ ግዜ ብቻ ነው የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ጣልቃ ገብቶ ውሳኔ የሚያሳልፈው፡፡ በዚህም ክልሎች በፌዴሬሽን ምክር ቤቱ በኩል ጠቅላላ የፌዴራል ድንጋጌዎችን የመምከር ወይም በፌዴራል ደረጃ ሕግጋትን የመጠቆም ምንም ዕድል የላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ተቋማዊ መዋቅር ለተጠናከረ ማዕከላዊ የሥራ አስፈፃሚ አካል ቦታ የሚሰጥ ሲሆን የፌዴሬሽኑም ይሁን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ማዕከላዊ የሥራ አስፈፃሚውን ለመቆጣጠር የሚያስችለው ተቋማዊ ሁኔታ አናሳ ነው፡፡
በብዙዎቹ የፌዴራል ስርዓቶች ውስጥ፣ ነጻ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ስላለ ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም እና ተለዋዋጭ ኩነቶች ጋር የማስማማት ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ ገለልተኝነቱ የግድ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም የፖለቲካ ኃይሎች እና ሁሉም የአገሪቱ ወገኖች ለማንም እንደማያደላ አውቀው ውሳኔውን እንዲቀበሉ ያደርጋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት  የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ስለሌለው ከሌሎቹ ስርዓቶች ይለያል፡፡ በምትኩ፣ ሕገ መንግሥታዊው ጉዳይ ለፖለቲካው አካል፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ተትቷል (አንቀፅ 62)፡፡ በፍርድ ቤት የሚነሳ ማንኛውም አለመግባባት የሚታየው በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥር በ1988 በተቋቋመው የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ነው፡፡ ጉባዔው የተቋቋመው ከፖለቲካ እና የሕግ አካላት ተውጣጥቶ ነው፡- እነዚህም የፍርድ ቤቱ ፕሬዚደንት እና ምክትላቸው፣ ሦስት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመረጡ ስድስት የሕግ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ጉባዔውም በመጨረሻ ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ጥቆማውን በመላክ ውሳኔ ያስገኝለታል (አንቀጥ 83)፡፡
ይህ የሚያመለክተው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ፈጣሪዎች በክልሎች መሐል የሚነሱ አለመግባባቶች በሕግ አግባብ ይፈታሉ ብለው የማያምኑ መሆኑን፣ ነገር ግን የሆነ ዓይነት ፖለቲካዊ መፍትሔ መኖር አለበት ብለው መገመታቸውን ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተግባር፣ ምንም እንኳን ፍርድ ቤቶች በጥቅሉ ነጻ ቢሆኑም፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ሥራ ሥልጣን በተቆጣጠረው የፖለቲካ ፓርቲ እጅ ነው፡፡ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አባላትን ጨምሮ ዳኞች የሚሾሙት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው (አንቀፅ 81)፡፡ ነጻ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት አለመኖሩ፣ የኢትዮጵያ ስርዓት መንግሥታዊ የሥልጣን ገደቦች ስለሚያጥሩት ለሕገ መንግሥታዊነት መርሖች ቁርጠኝነት እንዳይኖር ማድረጉን እንዲናገሩ ታዛቢዎችን አስገድዷቸዋል፡፡ ነገር ግን፣ ለምሳሌ፣ የኢትዮጵያን ስርዓተ ናሙና ከራሽያ ፌዴሬሽን ጋር ካወዳደርነው የኢትዮጵያ ስርዓት ቁጥጥር ማጣት በአንፃሩ የተሻለ ነው፡፡ የራሽያ ሕገ መንግሥት ለፕሬዚዳንቱ የሕግ ክለሳ እና በክልሎች እና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ያሉ አለመግባባቶችን የመገላገል ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይህም ከፌዴራላዊ መርሖች ያፈነገጠ ነው፤ የማዕከሉ ባለሥልጣናት ለብቻቸው የፌዴራሉ አባላትን ሥልጣን መወሰን የለባቸውም፡፡