የጂቡቲ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ዕቃዎች በዘመናዊ መሣሪያ በመፈተሽ በአንድ ኮንቴይነር ዕቃ፣ ከአሥር እስከ 35 ዶላር ለማስከፈል አዲስ ዕቅድ አወጣ፡፡

የጂቡቲ ወደብ አስተዳደር አዲሱን ክፍያ እ.ኤ.አ. ከጥር 15 ቀን 2016 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርግ፣ ለኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ማሳወቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ይህ አዲስ አሠራር 85 በመቶ የሚሆነውን የወጪና ገቢ ንግድ በጂቡቲ ወደብ በኩል ለምትጠቀመው ኢትዮጵያ ዱብ ዕዳ ሆኗል፡፡ 

ባለፈው ዓርብ ታኅሳስ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ይህ መረጃ ለኢትዮጵያ መንግሥት እንደደረሰ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከጂቡቲ መንግሥት ጋር በጉዳዩ ላይ ለመወያየት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስወደብና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ አምባዬ ባለፈው ዓርብ ምሽት ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ጉዳዩን ከአንድ ሰዓት በፊት መስማታቸውን ገልጸው፤ ከማሪታይም ባለሥልጣን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ማብራሪያ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል፡፡

የማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኰንን አበራ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ አዲሱ ክፍያ የውጭ ዕቃዎችን ይመለከት እንደሆነ የንግድ ሚኒስቴር የኤክስወደብ ፕሮሞሽን ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ አሰፋ ሙሉጌታ ይህንን ጉዳይ እንዳልሰሙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደገለጹት፣ የጂቡቲ ወደብ አስተዳደር የመፈተሽ አቅሙን ለማሳደግ ከዚህ በፊት ከነበረው ልማዳዊ አሠራር (ማንዋል) ወደ ዘመናዊ (ዲጂታል) የፍተሻ ዘዴ ለመሸጋገር ሲሠራ ቆይቷል፡፡ 

በልማዳዊው የቀድሞ አሠራር ለፍተሻ ክፍያ አይጠይቅም ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. ጥር 15 ቀን 2016 በሚጀመረው ዘመናዊ ፍተሻ ግን ክፍያ እንደሚጠይቅ፣ የጂቡቲ ወደብ አስተዳደር ለኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡

የሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ምንጮች እንደተናገሩት፣ ይህ ክፍያ በፍፁም ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም፡፡ ይህ ያልተጠበቀ ክፍያ ከተጀመረ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከመፈተኑ ባሻገር የኑሮ ውድነቱን እጅግ ያባብሳል ይላሉ፡፡

‹‹በኮንቴይነር ክፍያ የፈጸመ ነጋዴ ላወጣው ወጪ ክፍያ የሚጠይቀው ኅብረተሰቡን ነው፤›› በማለት የሚናገሩት የኢንተርፕራይዙ ምንጮች፣ አገሪቱንም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ያስወጣታል በማለት አዲሱ የጂቡቲ መንግሥት ተጨማሪ ክፍያ ጥያቄ፣ አገሪቱን ለውስብስብ ችግር እንደሚዳርግ አበክረው ገልጸዋል፡፡

ጂቡቲ ተጨማሪ ገቢ የሚገኝበትን አዲስ አሠራር ለመጀመር መዘጋጀቷን የሰሙ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ በዚህ ያልተጠበቀ የጂቡቲ መንግሥት ዕርምጃ በመደናገጥ የጂቡቲን መንግሥት ሐሳብ ለማስለወጥ ንግግር ለመጀመር ተዘጋጅተዋል ተብሏል፡፡  

 

 

የሲሚንቶ ገበያ ተቀዛቀዘ

-የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ፈተና መሆኑ ተነገረ

በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እየተፈተነ የሚገኘው የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ የገበያ መቀዛቀዝ አሳየ፡፡ አገር ውስጥ የሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ዓመታዊ የማምረት አቅማቸው 13 ሚሊዮን ኩንታል ቢሆንም፣ ሽያጩ ግን ከሰባት ሚሊዮን ኩንታል ያልበለጠ መሆኑ ታውቋል፡፡ 

 

ከገበያ መቀዛቀዝ ባሻገር የመንግሥት የልማት ድርጅት የሆነው ሙገር ሲሚንቶ፣ ሰሞኑን አንድ ኩንታል ፒፒሲ ሲሚንቶ የሚሸጥበትን ዋጋ ከ210 ብር ወደ 190 ብር አውርዶታል፡፡ 

በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና ከቀትር በኋላ 11፡00 ሰዓት እስከ ምሽት 4፡00 ሰዓት ድረስ ኃይል እንዳይጠቀሙ በመንግሥት ትዕዛዝ በመሰጠቱ የገበያ መቀዛቀዝ መፈጠሩ የተነገረ ሲሆን፣ የተለያዩ ሲሚንቶ ፋብሪካዎችም ሥራ እያቆሙ ነው፡፡ 

ሥራ ካቆሙ ፋብሪካዎች ውስጥ ሲኤች ክሊንከር፣ ሁዎንግሽን ሲሚንቶና ኢስት ሲሚንቶ ይገኙበታል፡፡ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ዘርጋው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ትልቁ ፈተና ሆኗል፡፡ 

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከአንድ ሺሕ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ሙቀት ስለሚፈልጉ፣ ይህ ሙቀት ከተፈጠረ በኋላ ኃይል ሲቋረጥ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ለብልሽት እንደሚዳረጉ፣ እንደገና ኃይል ሲመጣ ደግሞ ፋብሪካዎቹን ወደ ሥራ ለመመለስ አስቸጋሪ እንደሆነ አቶ መኮንን ገልጸዋል፡፡ 

የገበያውን መቀዛቀዝ በተመለከተ ሁሌም በክረምት ወራትና ክረምት ከወጣ በኋላ ለተወሰኑ ወራት የሲሚንቶ ገበያ መቀዛቀዙ የተለመደ እንደሆነና ከመብራት ጋር እንደማይገናኝ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና በዚህ ሐሳብ የማይስማሙ አሉ፡፡ 

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የአንድ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት በአንድ ጊዜ በርካታ ፕሮጀክቶችን ያስጀመረ በመሆኑ፣ ለሚያሠራው ሥራ ክፍያ ለመፈጸም እየተቸገረ ነው፡፡ 

መንግሥት የበጀት እጥረት ስላለበት መንግሥት ክፍያ እየፈጸመ ባለመሆኑ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በመቀዛቀዙ የሲሚንቶ ገበያውም ሊቀዛቀዝ እንደቻለ አመልክተዋል፡፡ ባለፉት በርካታ ዓመታት የዋጋ ንረት ሲያጋጥመው የቆየው የሲሚንቶ ገበያ፣ በአሁኑ ጊዜ መቀዛቀዝ ስለታየበት፣ ሁሉም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከ190 ብር እስከ 210 ብር ድረስ ባለው ዋጋ በመሸጥ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ሲሚንቶ ገበያው ውስጥ በኩንታል እስከ 400 ብር ይሸጥ ነበር፡፡ 

አቶ መኮንን ሙገር የሲሚንቶ ዋጋ ሊቀነስ ከቻለባቸው ምክንያቶች አንዱ ሲጠቀም የቆየውን ጥቁር ናፍጣ ትቶ፣ በድንጋይ ከሰል እንዲጠቀም በመወሰኑ ነው ብለዋል፡፡ 

በ15 ቀናት ውስጥ በድንጋይ ከሰል መጠቀም እንደሚጀምር የተናገሩት አቶ መኮንን፣ ከጥቁር ናፍጣ ይልቅ የድንጋይ ከሰል ርካሽ በመሆኑ ሙገር ዋጋ ለመቀነሱ አንዱ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

 

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅና የግዢና ንብረት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር በአሥር ሚሊዮን ብር ሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታወቀ፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ኤፍሬም ደሳለኝና የግዥና ንብረት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ንጉሤ ታደሰ በቁጥጥር ሥር የዋሉት፣ ኅዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ሲሆን፣ ኅዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ 

ተጠርጣሪዎቹ በድርጅቱ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ተመድበው ሲሠሩ የመንግሥትንና የሕዝብን ጥቅም ማስጠበቅ ሲገባቸው፣ አቶ ገብረ አምላክ በርሄ ከሚባሉ ግለሰብ ጋር በመመሳጠር ግምቱ 8,974,000 ብር የሆነ የመንግሥት ንብረት (ምንነቱ አልተገለጸም) አውጥተው በመሸጥ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን፣ መርማሪ ፖሊስ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በተጨማሪ ያለምንም ስምምነትና ውል ከ1.9 ሚሊዮን ብር በላይ ከድርጅቱ ካዝና በማውጣት ለልኳንዳ ነጋዴዎች እንዲከፈል በማድረጋቸው፣ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመገልገል የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በመሆኑም መርማሪ ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ እንዲፈቀድላቸው ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄም ታልፏል፡፡ 

 

በማረሚያ ቤት አለመኖራቸው በተገለጸው አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ የቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ

በሽብር ድርጊት ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ተመሥርቶባቸው ማረሚያ ቤት በሚገኙት በእነ ዘመኑ ካሴ የክስ መዝገብ በመከላከያ ምስክርነት በተቆጠሩት የግንቦት ሰባት አመራር የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣

በመከላከያ ምስክርነት እንዳይቀርቡ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ የነበረው ይግባኝ ኅዳር 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ውድቅ ተደረገ፡፡

ተከሳሾቹ ከተመሠረተባቸው ክስ አንዱ የግንቦት ሰባት አመራር ከነበሩትና ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ከየመን ወደ አስመራ ሊሄዱ ሲሉ ከሰንዓ አውሮፕላን ማረፊያ ተይዘው ወደ ኢትዮጵያ ተላልፈው ከተሰጡት አቶ አንዳርጋቸው ጋር ተገናኝተው መመርያ መቀበላቸውን የሚመለከት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም አቶ አንዳርጋቸው በፌዴራል ማረሚያ ቤት ስለሚገኙ በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው፣ ክሱን እየመረመረ ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት አመልክተው ፍርድ ቤቱም ተቀብሏቸዋል፡፡

የተከሳሾቹን አቤቱታ በመቃወም ለፍርድ ቤቱ ያመለከተው ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ፣ አቶ አንዳርጋቸው በእነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብና በእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የክስ መዝገብ የዕድሜ ልክና ሞት ፍርደኛ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ምስክርነት ለመስጠት እንደማይችሉና መብታቸው የተገፈፈ መሆኑን አስረድቶ ተቃውሞ ነበር፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን አቶ አንዳርጋቸው መብታቸው የተገፈፈው ስለራሳቸው እንጂ ስለሌሎች ምስክርነት መስጠት ስላልሆነ ሊመሰክሩ እንደሚገባ ገልጾ፣ የዓቃቤ ሕግን ማመልከቻ ውድቅ በማድረግ ቀርበው እንዲሰሙ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

አቶ አንዳርጋቸውን በመከላከያ ምስክርነት እንዲያቀርብ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ታዞ የተለያዩ ምክንያቶችን በመስጠት ሳያቀርባቸው ቢቆይም፣ ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ደብዳቤ ግን ‹‹አቶ አንዳርጋቸው ማረሚያ ቤት የሉም፤›› ብሎ መግለጹ ይታወሳል፡፡

ተከሳሾቹ የማረሚያ ቤቱን ምላሽ በመቃወም አቶ አንዳርጋቸው አገር ውስጥ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉና በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር እንደሚያውቁ በመጠቆም፣ ለእነሱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ተመካክሮ እንደሚያሳውቃቸው ገልጾ በቀጠሮ ላይ እንዳሉ፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ አቶ አንዳርጋቸው በመከላከያ ምስክርነት ሊቀርቡ እንደማይገባ ለሥር ፍርድ ቤት ያመለከተበትን ምክንያት ጠቅሶ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቦ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ መርምሮ በሰጠው ብይን በፍርድ ቤት እንዲቀርብ የታዘዘ ምስክር ‹‹ይቅረብ አይቅረብ›› ተብሎ ይግባኝ ሊባል እንደማይቻል በመግለጽ፣ የዓቃቤ ሕግን ይግባኝ እንዳልተቀበለው አስታውቋል፡፡ 
የጠቅላይ ፍርድ ቤትን ውሳኔ የተቃወመው ዓቃቤ ሕግ፣ መሠረታዊ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን በመጥቀስ ለሰበር ሰሚ ችሎት ማመልከቻ ማቅረቡን ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡  

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች በኤቲኤም ማሽን ገንዘብ ማውጣት ባለመቻላቸው፣ በአጭር የመልዕክት ጽሑፍ ገንዘብ ማውጣታቸውን በሚገልጸው መልዕክት ከፍተኛ መደናገጥ እየተፈጠረባቸው ነው፡፡

ባንኩ በበኩሉ በጊዜያዊ ገንዘብ ዝውውር የኔትወርክ ችግር ያጋጠመ ቢሆንም፣ የገንዘብ ኪሳራ እንደማይገጥማቸው ገልጿል፡፡

በከተማዋ የተለያዩ የባንኩ ቅርንጫፎችና በንግድ ተቋማት አካባቢ በተተከሉ የኤቲኤም ማሽኖች ደንበኞች ገንዘብ ለማውጣት ቢሞክሩም፣ ሙከራቸው አለመሳካቱን ከማሽኑ የመረጃ ሰሌዳ እየተገለጸላቸው መሆኑንም እየገለጹ ነው፡፡ ሪፖርተርም ይኼንኑ ችግር በተለያዩ ቦታዎች ተዟዙሮ አይቷል፡፡ በተለይ ደንበኞች ሙከራው እንዳልተሳካላቸው ዓይተው ከሄዱ በኋላ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሞክረው ያልተሳካላቸውን የገንዘብ መጠን ማውጣታቸውን የሚገልጸው መልዕክት ሲደርሳቸው፣  ድንጋጤና ግራ መጋባት ተፈጥሮባቸዋል፡፡ 

ነገር ግን ከቆይታ በኋላ የተጠቀሰውን የገንዘብ መጠን ወደ አካውንታቸው መመለሱን የሚያሳይ መልዕክት ከባንኩ እንደሚደርሳቸውም ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይኼንን በተመለከተ መገናኛ፣ አራት ኪሎ፣ ካዛንቺስና ቦሌ አካባቢዎች የሚገኙ የባንኩ ቅርንጫፎች ሪፖርት በሚያደርጉ ደንበኞች ተጨናንቀው መሰንበታቸውን ለማየት ተችሏል፡፡ በአንዳንዶቹ ቅርንጫፎች ደንበኞች በምሬት ከባንኩ ሠራተኞች ጋር ሲጨቃጨቁም ተስተውለዋል፡፡

የባንኩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በተወሰኑ ቅርንጫፎች አካባቢ ባሉ ማሽኖች ችግሩ መስተዋሉን አምነው ችግሩ ከኔትወርክ መቆራረጥ ጋር የተያያዘ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ከቴክኖሎጂው ጋር ለመራመድ በሚደረገው ጥረትም ችግሮች እንደሚከሰቱ ጠቁመዋል፡፡

ችግሩ የተከሰተው በዝውውር (Transfer)  አለመሟላት ምክንያት ቢሆንም፣ በማዕከል ቋት አማካይነት የሚተላለፍ በመሆኑና ጥብቅ ክትትል ስለሚደረግበት፣ ደንበኞች ሥጋት ላይ ሊወድቁ እንደማይገባና በፍጥነት ሊስተካከል እንደሚችል አቶ ኤፍሬም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ደንበኞች እንዲህ ዓይነት ችግር በሚገጥማቸው ወቅት በአቅራቢያቸው በሚገኙ ቅርንጫፎች ወይም ኤቲኤም ካርዱን ያወጡበት ቅርንጫፍ በመሄድ ሪፖርት እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የባንኩን ነፃ የስልክ መስመር በሆነው በ950 በመደወል ጥያቄ ሊያቀርቡ ይገባልም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመላው አገሪቱ ከ650 በላይ የኤቲኤም ማሽኖች  አሉት፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ከ250 በላይ መትከሉን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

 

የኃይል ማመንጫዎች ብልሽት በመላ አገሪቱ የኃይል አቅርቦት እያስተጓጎለ ነው

በጣና በለስና በጊቤ አንድ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በደረሰ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያና የኤሌክትሮኒክ መቆጣጠሪያ ብልሽት፣ በመላ አገሪቱ የኃይል አቅርቦ ተስተጓጉሏል፡፡ ቅዳሜ ኅዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በአገሪቱ ትልቁና 460 ሜጋ ዋት

የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ላይ በሚገኘው ጣና በለስ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ  የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መቆጣጠሪያ ተበላሽቷል፡፡

ይህንን ብልሽት ለማስተካከል እየተሞረከ ባለበት ወቅት በነጋታው እሑድ ኅዳር 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ደግሞ በጊቤ አንድ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ ተመሳሳይ ብልሽት አጋጥሟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከጊቤ አንድ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ተነስቶ ከሰኮሩ ከተማ ወደ ጌዶ የተዘረጋው የኃይል መስመር አደጋ ደርሶበታል፡፡

በእነዚህ ምክንያቶች ኅዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀኑ 6፡30 እስከ 10፡30 ሰዓት፣ ኅዳር 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ደግሞ ከ9፡30 ሰዓት ጀምሮ በመላ አገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጧል፡፡ በዚህ የኃይል መቋረጥ ነዋሪዎች በሚያካሂዱት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ፣ ከጥቃቅንና ከአነስተኛ አምራቾች እስከ ግዙፍ ማምረቻ ተቋማት ችግር ገጥሟቸዋል፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ በሁለት አቅጣጫዎች አገልግሎት መስጠት የጀመረው የቀላል ባቡር ትራንስፖርትም መስተጓጎል ገጥሞት ነበር፡፡

የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ባለሥልጣን ባለሙያዎች ወደ ሥፍራው ተንቀሳቅሰው ችግሩን ለመፍታት እየሞከሩ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

460 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ያለው ጣና በለስና 184 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨቅ አቅም ያለው ጊቤ አንድ፣ በብሔራዊ የኃይል ቋት ውስጥ መግባት ባለመቻላቸው በአገሪቱ ችግር ተፈጥሯል፡፡

በዚህ ምክንያት በመላ አገሪቱ ኃይል ከመቋረጡም በላይ፣ ችግሩ እስካሁን ባለመፈታቱም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም የኃይል መቆራረጥ እያጋጠመ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ እነዚህ ችግሮች  በአሁኑ ወቅት የጎላ ደረጃ ይድረሱ እንጂ ችግሮቹ ያልተፈቱባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡

ከእነዚህ ውስጥም የመለዋወጫ ዕቃዎች በወቅቱ አለማዘጋጀት፣ በግድቦች አስተዳደር የባለሙያ እጥረት፣ አሮጌ የማሰራጫና ማስተላለፊያ መስመሮች በአዲስ አለመተካትና አሻጥረኛ ሠራተኞች መኖራቸው ለችግሩ መባባስ እንደ ምክንያት ያስቀምጣሉ፡፡

አሁን በተፈጠረው ችግር ብቻ አዲስ አበባ ከ120 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት መከሰቱን መረጃዎች አመልክተው፣ በአንዳንድ መንደሮች ኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት ቅንጦት እየሆነ ነው፡፡

አሁን ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን፣  በመስኩ ከሚገኙ ባለሙያዎች ጋር ግንኙነት በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ እየተሠራ እንደሆነ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

 

 

 

 

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን ላይ ተቃውሞ አሰሙ

‹‹አረጋግተን እንዴት ትምህርት መጀመር እንዳለባቸው እየተነጋገርን ነው›› የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም፣ ኅዳር 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ሠልፍ ወጡ፡፡ 

ተማሪዎቹ በማስተር ፕላኑ ውስጥ ማንኛውም የኦሮሚያ ቦታ መወሰድ ወይም መካተት እንደሌለበት የሚያንፀባርቁ መፈክሮችን ይዘው ከዩኒቨርሲቲው ግቢ በመውጣት፣ ወደ ሐረማያ ከተማ ለመሄድ ባደረጉት ሙከራ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር መጋጨታቸው ታውቋል፡፡ 

ተማሪዎቹ እንቅስቃሴውን የጀመሩት ኅዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ምሽት ላይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እንቅስቃሴውን በመስማቱ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመራ ለፀጥታ ኃይሎች መረጃው በመድረሱ የዩኒቨርሲቲው ፖሊሶች፣ የክልሉ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስና የፌዴራል ፖሊስ ባደረጉት መከላከል፣ የተማሪዎቹ ሠልፍ በቅጥር ግቢው መገታቱን ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ተማሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ 

የተቀናጀ ማስተር ፕላኑን በሚመለከት ባለፈው ዓመት ተነስቶ በነበረው ተቃውሞ የመንግሥት አካላት ትኩረት በመስጠት በተለይ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ ነዋሪዎችና ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ተፈጥሮ የነበረውን ውጥረት ከማርገባቸውም በተጨማሪ ስምምነት ላይ እንደደረሱ መገለጹ ይታወሳል፡፡ 

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነገሩን እንደ አዲስ እንዴት ሊያነሱት እንደቻሉ ተማሪዎቹ ተጠይቀው እንደገለጹት፣ ኅዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም. የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስብሰባ አዳራሽ ጉባዔ ጠርቶ ነበር፡፡ ከስብሰባው አጀንዳዎች አንዱ የከተማ ማስተር ፕላኖችን ማስተካከል ነው፡፡ በመሆኑም ባለፈው ዓመት ተቃውሞ ተነስቶበት በቂ ማብራሪያ ሳይሰጥበትና ስምምነት ላይ ሳይደረስ በዝምታ ታልፎ፣ አሁን ሊፀድቅ እንደሆነ በመገመት ሳይሆን እንዳልቀረ፣ የተቃውሞውን ምክንያት መገመታቸውን ተማሪዎቹ አስረድተዋል፡፡ 

ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ እየተዟዟሩ መፈክር በማሰማት ላይ እያሉ፣ ለተቃውሞው መነሳት ምክንያት ናቸው የተባሉ ቁጥራቸው የማይታወቁ ተማሪዎች መታሰራቸውንና የተወሰኑ ተማሪዎች ተደብድበው ጉዳት እንደደረሰባቸው ተማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ በወቅቱ ጥይት የተኮሰ ቢሆንም የተጎዳም ሆነ የሞት አደጋ እንዳልደረሰ አክለዋል፡፡ ቁጥራቸው የማይታወቅ ተማሪዎች ሠልፉ ከመደረጉ አስቀድመው ከግቢው በመውጣት ከዘመዶቻቸው ጋር መቀላቀላቸውንና ከተለያዩ ክልሎች የመጡም ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ በተለያዩ ቦታዎች ተደብቀው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ 

ኅዳር 20 እና 21 ቀን 2008 ዓ.ም. (ኅትመት እስከገባንበት ምሽት ድረስ) በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሒደት መቋረጡም ታውቋል፡፡ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ ተማሪዎች ስላነሱት ተቃውሞ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ፣ ተማሪዎቹ ተቃውሞ ማንሳታቸውን አረጋግጠው ‹‹አረጋግተን እንዴት ትምህርት መጀመር እንዳለባቸው እየተመካከርን ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

ተማሪዎቹ ኅዳር 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ ረፋዱ 2፡30 ሰዓት ድረስ፣ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረጋቸውን የተናገሩት ፕሮፌሰሩ የአካባቢው አስተዳደር፣ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስና ፌዴራል ፖሊስ ወደ ውጭ እንዳይወጡ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ 

የተማሪዎቹ ተቃውሞ ከማስተር ፕላኑ ጋር ብቻ የተገናኘ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰሩ፣ እንዴት ስለማስተር ፕላኑ ሊያነሱ እንደቻሉ እሳቸውም እንዳልገባቸው አስረድተዋል፡፡ በሠልፉ ግርግር ትንሽ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች ሕክምና የተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ሦስት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ክሊኒክ እየታከሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ፖሊስ ወደ ሰማይ ከመተኮስ ባለፈ ተማሪዎችን የሚጎዳ ድርጊት አለመፈጸሙን፣ ለረብሻው ምክንያት ናቸው የተባሉ ተማሪዎች ተይዘው በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ከፖሊስ፣ ከዩኒቨርሲቲውና ከተማሪዎች የተውጣጣ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ምርመራ እያደረገባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የተወሰኑ ተማሪዎችም መለቀቃቸውን አክለዋል፡፡ 

ተማሪዎቹ ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ እሳቸውን ጨምሮ መምህራኑ እየመከሩ መሆኑን ፕሮፌሰር ጨመዳ አስታውቀዋል፡፡ ለትምህርት ሚኒስትሩ ለአቶ ሽፈራው ሽጉጤና ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ማሳወቃቸውንም አረጋግጠዋል፡፡ 

 

የምሥራቅና የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ተረጂዎች ቁጥር ከ50 በመቶ በላይ ጨምሯል

ከኤልኒኖ የአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የተከሰተው ድርቅ እያሳረፈ ያለው ተፅዕኖ እየሰፋ መምጣት የተረጂዎችን ቁጥር እንዲጨምር እያደረገ ነው፡፡

ሰሞኑን በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ለመቃኘት የተንቀሳቀሰው የጋዜጠኞች ቡድን ከተመለከታቸው አካባቢዎች መካከል፣ የምዕራብና የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ውስጥ ከወራት በፊት የነበሩት ተረጂዎች ቁጥር ከ50 በመቶ በላይ ጨምሯል፡፡በኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃረን አልዪ እንደገለጹት፣ እስካሁን¬ 549,000 ተረጂዎች ተለይተው ዕርዳታ ሲሰጣቸው ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ድርቁ አሁንም ለውጥ ሳያሳይ በመቀጠሉ የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ብቻ ከ320 ሺሕ በላይ ተጨማሪ ተረጂዎች የመንግሥትን ዕርዳታ የሚሹ በመሆናቸው፣ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ የተረጂዎች ቁጥር 900 ሺሕ ይደርሳል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ለእነዚህ ተረጂዎች የሚሆን ተጨማሪ የምግብ ዕርዳታ የተጠየቀ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በምዕራብ ሐረርጌ ዞንም በተመሳሳይ በድርቅ የተጎዱ ተረጂዎች ቁጥር እንደጨመረ፣ የዞኑ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቶፊቅ አብዱላሂ ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ቶፊቅ ገለጻ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብለው ሲሰጣቸው የነበሩት ከ500 ሺሕ በላይ ተረጂዎች ነበሩ፡፡ በጥር ወር ግን የተረጂዎች ቁጥር ከ720 ሺሕ በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል፡፡ 

የሁለቱም ዞኖች የሥራ ኃላፊዎች የተረጂዎቹ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል፡፡ በሁለቱም ዞኖች እስካሁን ዕርዳታ ሲሰጣቸው የነበሩት የባሰ ችግር የነበረባቸው ናቸው፡፡ ድርቁ እየተራዘመ በመምጣቱ ግን የተሻሉ ናቸው የተባሉትንም ጭምር ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው እየሆኑ መጥተዋል፡፡

በአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳም ባለፈው ዓመት 14,404 የነበሩ ተረጂዎች ቁጥራቸው ከ51 ሺሕ በላይ ሆኗል፡፡

እንደ ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ፣ በ2007 የምርት ዘመን ይገኛል ተብሎ የታቀደው 12 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ነበር፡፡ በቅርቡ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ግን ሊገኝ የሚችለው ከሦስት ሚሊዮን ኩንታል ያነሰ ነው፡፡ በምዕራብ ሐረርጌም የሚጠበቀው ምርት ቀድሞ ከተገመተው በእጅጉ ያነሰ እንደሚሆን ታምኗል፡፡

በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የድርቅ ተጎጂዎች ከሆኑ ወረዳዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የሚደጋ ቶላ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሳርቱ ሙክታር እንደሚሉት፣ መንግሥት ዕርዳታ እየሰጣቸው ቢሆንም ዕርዳታው በቂ አይደለም፡፡ በአንድ ቤተሰብ 15 ኪሎ ስንዴ እየተሰጣቸው መሆኑንና ሦስት ጊዜ መውሰዳቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከስንዴው ጋርም አንድ ሊትር ዘይት ቢሰጣቸውም ይህ ግን በቂ አይደለም ይላሉ፡፡ የውኃ ችግሩ ግን እጅግ የከፋ መሆኑን የሚገልጹት የሚደጋ ቶላ ወረዳ ነዋሪዎች፣ በአጋጣሚ በዘነበው ዝናብ በአንድ ኩሬ ላይ የተጠራቀመ ውኃ ለከብቶቻቸውም ለራሳቸውም ይጠቀሙበታል፡፡

ቀድሞ ለመጠጥ ይጠቀሙበት የነበረው ኩሬ በመድረቁ መንግሥት በቦቴ የሚያመጣውና የሚያሠራጨው ውኃ የማይዳረስ ስለሆነ፣ አንዳንድ ነጋዴዎች አምጥተው የሚሸጡትን አንድ ሊትር ውኃ በአንድ ብር እየገዙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ይህም ቢሆን በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

አቶ ሃሮን አሊዪ እንደሚሉትም በአካባቢው ያለው የውኃ እጥረት ከፍተኛ ነው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ ካለው ሁኔታ አንፃር በዞኑ የከፋ ችግር ላለባቸው ወረዳዎች 30 የውኃ ማመላለሻ ቦቴዎች እንደሚያስፈልጉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹17ቱን አግኝተን በእነዚሁ ቦቴዎች እያከፋፈልን ነው፡፡ የጠየቅናቸው የውኃ ቦቴዎች ከመጡ የውኃ ሥርጭቱ መጠን ይጨምራል፤›› ይላሉ፡፡

በምዕራብ ሐረርጌ ሚኤሶ ወረዳ ሪፖርተር ያገኛቸው አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፣ እንዲሁም በምሥራቅ ሐረርጌ በድርቅ የተጎዱ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት የሚደረግላቸው ዕርዳታ በቂ ያለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ጨርሶ ዕርዳታ እየተሰጣቸው ያለመሆኑን ነው፡፡ የሚሰጣቸው ዕርዳታ ባለመኖሩም አንዳንዶቹ ወደ ጂቡቲና ወደተለያዩ አካባቢዎች ለመሰደድ መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡

እንደነ አቶ ዓሊ ኢንድሪስ ያሉት ደግሞ ከአዲስ አበባ – ጂቡቲ በተዘረጋው የባቡር ፕሮጀክት ላይ በቀን ሠራተኝነት ተቀጥረው በቀን 30 ብር እየተከፈላቸው ሕይወታቸውን ይመራሉ፡፡ ከዚህ ሲብስም በደህናው ጊዜ ያደለቧቸውን ከብቶች እየሸጡ ነው፡፡

በአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎችም ከብቶቻቸው በድርቁ ምክንያት ስለተጎዱና ከችግር ለማምለጥ ለመሸጥ ወደ ገበያ ሲያወጧቸው ዋጋ እየወደቀባቸው መቸገራቸውን፣ ሲብስም ቀድሞ እስከ 20 ሺሕ ብር ይሸጡ የነበሩትን ከብት ከአምስት ሺሕ ብር ባልበለጠ ዋጋ ለመሸጥ መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡

በዚህ ወረዳ ከ77 ሺሕ በላይ ከብቶች አስቸኳይ የመኖ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ቢገልጹም፣ እስካሁን ግን ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳልተሰጣቸው የወረዳው የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጣሂር ፊኒኖ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት በቶሎ መኖውን ካላቀረበላቸውም በከብቶቹ ላይ የሚደርሰው ጉዳት የከፋ እንደሚሆን ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ 

አቶ አብደላ መሐመድ የሚኤሶ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ በአካባቢያቸው ያለው ድርቅ የከፋ እንደሆነና በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕርዳታ ካላገኙም ችግር ውስጥ የሚወድቁ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ችግሩ ለከብቶቻቸው ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ እስካሁን በ2007 የምርት ዘመን ፍሬ ያላፈራውን የበቆሎና የማሽላ አገዳ እየመገቡ ያቆዩዋቸው ቢሆንም፣ ከብቶቻቸው አሁን ምንም መኖ የላቸውም፡፡

አቶ አብደላ ያሏቸውን ከብቶች ከሚኖሩበት መንደር ውኃ ወዳለበት አካባቢ ማምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ በ2007 የምርት ዘመን የዘሩት በቆሎና ማሽላ ሙሉ በሙሉ በመጥፋቱ፣ በእጃቸው የቀሩትን ከብቶች በአነስተኛ ትንሽ ኩሬ ውኃ እያጠጡ ከኩሬ ዳር ማደርና መዋል ከጀመሩ ሦስት ቀናት አልፏቸዋል፡፡

ይህችም ኩሬ ብትሆን ከአንድ ሳምንት በላይ የሚቆይ ውኃ የሌላት መሆኑን የገለጹት አቶ አብደላ፣ ሦስት ልጆቻቸውን ጥለው እሳቸው ከብቶቻቸውን ለማዳን ሲወስኑ ከከብቶቻቸው ሦስቱን ሸጠው ለቀለብ የሚሆን ገንዘብ ለቤተሰቦቻቸው በመተው ነው፡፡ 

እንደ አቶ አብደላ ገለጻ እስካሁን አምስት ከብቶቻቸውን አርደዋል፡፡ ከሚሞቱ ብለው የወሰዱት ይህ ዕርምጃ በቀሪዎቹ ከብቶቻቸው ላይ እንዳይደርስም የቻሉትን ያህል ውኃ ወዳለበት መጓዝ ግዴታቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሁሉም ወረዳዎች ትልቁ ችግር ውኃ ሲሆን፣ በአንዳንዶቹ አካባቢዎች ሰዎችም ሆኑ ከብቶች ውኃ ለማግኘት በእጅጉ ተቸግረዋል፡፡ ድርቁ ያስከተለው ጉዳት ከዚህም በኋላ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በዚህችው አነስተኛ ኩሬ ዳርቻ ሪፖርተር ያገኛቸው ሌላው አርሶ አደር እየደረሰ ያለውን ጉዳት በማየት ዕርዳታ ያልተደረገላቸው መሆኑን በሐዘኔታ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በተደጋጋሚ ወደ አካባቢው የሚመጡት የመንግሥት ኃላፊዎች ችግሩን ሰምተው ይሄዳሉ እንጂ ዕርዳታ እያደረጉልን አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ 

‹‹የልጆቻችን ሰውነት ቀንሷል፡፡ ከትምህርት ቤትም እየቀሩብን ነው፤›› የሚሉት እኚሁ አርሶ አደር፣ ለውኃ ችግር መፍትሔ ካልመጣ አካባቢውን ለቆ መሄድ ግድ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

‹‹ይህ የፈጣሪ ጉዳይ ስለሆነ ከዘራነው አላገኘንም፡፡ ከፈጣሪ በታች ያለን መንግሥት ነውና ዕርዱን ብለናል፤›› ያሉት አርሶ አደሩ፣ አሁንም ይህ ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ ይማፀናሉ፡፡ 

በሚኤሶ ወረዳ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ዕርዳታ እየተሰጣቸው አለመሆኑን ቢገልጹም፣ የሚኤሶ ወረዳና የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ኃላፊዎች ዕርዳታ እየተሰጠ ነው ይላሉ፡፡

የሚኤሶ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ከማል፣ ‹‹በአጋጣሚ ያነጋገርናቸው በወረዳው ሊረዱ ይገባል ተብለው ከተያዙት ውጪ ሊሆኑ ይችላሉ፤›› በማለት የአልተረዳንም ጥያቄ ለሚያነሱት አርሶ አደሮች ምላሽ ይሰጣሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ የተሻሉ ናቸው የተባሉትም ዕርዳታ የሚሹ እየሆኑ በመምጣታቸው፣ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ዕርዳታ ሊሰጣቸው ይገባል ከሚባሉት ውስጥ ይካተታሉ ብለዋል፡፡

ከዕርዳታ ሥርጭት ጋር በተያያዘ የተለያዩ አስተያየቶችም ይሰነዘራሉ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች በቂ ዕርዳታ እየተሰጠ አለመሆኑን ሲገልጹም ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ያላካተተ አሠራር እንዳለ ያመለክታሉ፡፡

የዕርዳታ አሰጣጡ ፍትሐዊ ነው ብለው የሚያምኑ እንዳሉም የሚናገሩ አርሶ አደሮች አሉ፡፡ የሁለቱ ዞኖች አስተዳዳሪዎች ግን የዕርዳታ አሰጣጡ በግልጽነት የሚካሄድ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ በዚህ ዕርዳታ አሰጣጥ ላይ ችግር ቢፈጠር ወዲያው ዕርምጃ የሚወሰድበት አሠራር ተዘርግቷል ይላሉ፡፡ 

የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳደር እንደገለጸው ለቁጥጥር ከአስተዳደር፣ ከዓቃቤ ሕግና ከሕዝብ አደረጃጀት የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ 

በሚኤሶ ወረዳ ዲርባ ቀበሌ ደግሞ ከዕርዳታ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የቀበሌው የሥራ ኃላፊና የጎጥ አመራሮች እንዲታሰሩ መደረጉን፣ የወረዳው አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

የቀበሌው ሊቀመንበርና የጎጥ አመራሮች የታሰሩት በዕርዳታ ዕደላው ወቅት የአንዳንዱን ቤተሰብ ቁጥር በማሳነሳቸው፣ የአንዳንዶቹን ደግሞ ቁጥራቸውን በመጨመር የተሻለ መጠን ያለው ዕርዳታ እንዲሰጣቸው በማድረጋቸው ነው፡፡ 

ወረዳው ይህንን መረጃ በሕዝብ ጥቆማ ካገኘ በኋላ ባደረገው ማጣራት፣ ድርጊቱ መፈጸሙ በመረጋጡ ዕርምጃው ለመውሰድ መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

በሁለቱም ዞኖች ያለው የከፋ ድርቅ በሰው ሕይወት ላይ ሞት አላስከተለም ተብሏል፡፡ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሚኤሶ ወረዳ ብቻ እስካሁን ከ2,200 በላይ ከብቶች መሞታቸውን የወረዳው የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

ድርቁ ባስከተለው ችግር የተሰደዱ አሉ የሚባለውን ያስተባበሉት የወረዳው አስተዳዳሪ፣ በዚህ አካባቢ ያለ ነዋሪ ወደ ጂቡቲ መሄድና መምጣት የተለመደ በመሆኑ በድርቁ የተሰደዱ ናቸው ሊባል እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ እንዳይሰደዱ በቂ ዕርዳታ እየተሰጣቸው ነው፡፡ ነገር ግን አንፈልግም ብለው የሚሄዱ አሉ፤›› ብለዋል፡፡ በወረዳቸው ደረጃ የበለጠ ዕርዳታ የሚያስፈልገው ተረጂ ቁጥር ከአንድ ወር በኋላ ስለሚጨምር ለዚህ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳዳሪ አሁን ያለውን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ድርቁ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን በሁለቱም ዞኖች መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ከደመወዛቸው ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ በፈቃዳቸው አዋጥተው ለድርቁ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መጠባበቂያ ፈንድ ውስጥ ተይዟል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ድርቁ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን መንግሥት ተከታታይ ዕርዳታዎችን እንደሚያደርግ በእርግጠኝነት አስታውቀዋል፡፡

 

 

ፖሊስ መምህር ግርማን በነፍስ ግድያ በመጠርጠሩ በዋስ አልተፈቱም

በተጠረጠሩበት የማታለልና ሐሰተኛ ሰነድ መጠቀም ወንጀሎች የ50 ሺሕ ብርና የ40 ሺሕ ብር ዋስትና የተፈቀደላቸው [መምህር] ግርማ ወንድሙን፣ ፖሊስ በነፍስ ግድያ እንደሚጠረጥራቸው በማመልከቱ አለመፈታታቸው ታወቀ፡፡

ፖሊስ [መምህር] ግርማ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ ሳያገኙ ፈቃድ እንደተሰጣቸው በማስመሰል ሐሰተኛ ሰነድ እንደተጠቀሙ በመግለጽ፣ ሰነዱን እያስመረመረ መሆኑን ገልጾ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ኅዳር 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎ ተጠርጣሪው በ40 ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ፖሊስ እሳቸውን በነፍስ ግድያ እንደሚጠረጥራቸው በመግለጽ ለፍርድ ቤቱ ማመልከቻ በማቅረቡ፣ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ሰነዶችን እንዲያቀርብ ለኅዳር 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ተጠርጣሪው  ወሰን ግሮሰሪ አካባቢ የሚኖሩ ግለሰብን ቤት በማሸጥና ገንዘቡንም ‹‹ይፀለይበት›› በማለት መውሰዳቸውን በሚመለከት ፖሊስ ካቀረበባቸው ክስ፣ በ50 ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

ነገር ግን በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ቅር የተሰኘው ፖሊስ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያለ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ኅዳር 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የፖሊስን ማመልከቻ ውድቅ በማድረግ የሥር ፍርድ ቤትን ትዕዛዝ አፅድቆ በ50 ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቁ አዟል፡፡ ነገር ግን ተጠርጣሪው በነፍስ ግድያ በመጠርጠራቸው ከእስር አልተፈቱም፡፡ 

ይህ በዚህ እንዳለ በሪፖርተር ቅጽ 21 ቁጥር 1622 ዕትም፣ ‹‹በ50 ሺሕ ብር ዋስ ይፈቱ የተባሉት [መምህር] ግርማ ይግባኝ ተጠየቀባቸው›› በሚለው ዜና ውስጥ ‹‹ከቤተ ክህነት እንደተሰጣቸው የገለጹት ሰነድ በፎረንሲክ ተመርምሮ ሐሰተኛ መሆኑን እንዳረጋገጠ ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፤›› የሚለው አገላለጽ በስህተት ስለሆነ፣ ‹‹ሰነዱን ለምርመራ ለፎረንሲክ ሰጥቶ እየተጠባበቀ መሆኑን አስረድቷል፤›› ተብሎ ተስተካክሎ እንዲነበብ አንባቢያንን ከይቅርታ ጋር እንጠይቃለን፡፡

 

ኤጀንሲው የአቶ በረከት ስምዖንን መኖሪያ ቤት ለባለቤቱ እንዲያስረክብ ታዘዘ

ቤቱ ለባለቤቱ እንዲመለስ ከተወሰነ 17 ዓመታት አልፎታል

የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 17 ቀበሌ 19 ውስጥ የሚገኘውን፣ የቤት ቁጥር 119 የሆነውንና የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ በረከት ስምዖን እየኖሩበት የሚገኘውን መኖሪያ ቤት፣ ታኅሳስ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲያስረክብ ታዘዘ፡፡ 

 

ኤጀንሲው ቤቱን ለባለ ንብረቱ አቶ መሐሪ ተወልደ ብርሃን እንዲያስረክብ፣ የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ከ17 ዓመታት በፊት ሚያዝያ 28 ቀን 1990 ዓ.ም. ትዕዛዝ ያስተላለፈ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን አለማስረከቡ ተጠቁሟል፡፡

የቤቱ ባለቤት አቶ መሐሪ ጥቅምት 5 ቀን 1988 ዓ.ም. ለፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ባቀረቡት አቤቱታ እንዳስታወቁት፣ ቤቱ የተወረሰው ከአዋጅ ውጪ በመሆኑ እንዲመለስላቸው መጠየቃቸውን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ ኤጀንሲውም ባደረገው ምርመራ የአመልካቹ ቤት በአዋጅ ቁጥር 110/87 አንቀጽ 2(3) መሠረት ከአዋጅ ውጪ የተወረሰ መሆኑን እንዳረጋገጠ ጠቁሞ፣ ኤጀንሲው ለቤቱ ማሠሪያ የዋለ የባንክ ዕዳ ካለ ተሳስቦ ለባንክ እንዲከፍልና ምንም ዓይነት የዕዳ ጥያቄ ሳያቀርብ ቤቱን ለአቶ መሐሪ እንዲያስረክብ አዞት እንደነበር ሰነዱ ያሳያል፡፡ ነገር ግን ቤቱ ተጨማሪ ማጣራት እንደሚያስፈልገው ተገልጾ፣ ከሰኔ 12 ቀን 1990 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ታኅሳስ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ድረስ ታግዶ የቆየ ቢሆንም፣ ቤቱ እንዲመለስላቸው የተሰጠው ውሳኔ ትክክል መሆኑ ስለተረጋገጠ፣ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ኤጀንሲ ቦርድ እግዱ እንዲነሳ ጥር 1 ቀን 2006 ዓ.ም. በመወሰኑ፣ ቤቶች ኤጀንሲ ቤቱን ለአቶ መሐሪ እንዲያስረክብ በድጋሚ ማዘዙን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ቤቶች ኤጀንሲ እንዲያስፈጽም ለተላለፈለት ትዕዛዝ በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹ቤቱ ለባለቤቱ እንዲመለስ ውሳኔ ያስተላለፈው ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ነው፡፡ ውሳኔው የሚፈጸመው በአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት በውክልና ነው፡፡ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለማስፈጸም ሥልጣን የለውም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን እንዳብራራው፣ ኤጀንሲው ፍርድ ቤቱ ሥልጣን እንደሌለው ቢገልጽም ማስረጃ አላቀረበም፡፡ ኤጀንሲው ጊዜ እንደሚያስፈልገው ቢገልጽም፣ እንዲያስፈጽም ከስምንት ወራት በላይ ስለተሰጠው በቂ ጊዜ እንደሆነና በቤቱ ውስጥ የሚኖሩት ከፍተኛ ባለሥልጣን ናቸው የሚለው ተቀባይነት እንደሌለው በመዘርዘር፣ ቀደም ብሎ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ፣ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ አቶ በረከት ስምዖን የሚኖሩበት መኖሪያ ቤት ለባለቤቱ አቶ መሐሪ ተወልደ ብርሃን እንዲያስረክብ፣ የቤቶች ኤጀንሲ ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት ኅዳር 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ትዕዛዝ ተላልፎለታል፡፡     

የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ሲሳይ ለከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ፣ በቤቱ ውስጥ የሚኖሩትን ባለሥልጣን የሚመጥን ቤት ስላልተገኘ ለግ

‹‹ሌብነት የለመደ በአንድ ሳምንት ውስጥ ቴሌቪዥን ላይ ወጥተን ስለጮህን እጁን ይሰበስባል ማለት አይደለም›› ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሐሙስ ኅዳር 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጆች ዘካሪያስ ስንታየሁና አሥራት ስዩም ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ቆይታ አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ዓይነት ቆይታ ከግል የኅትመት ሚዲያ ጋር ሲያደርጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸውም ወቅታዊ በሆኑ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በቅርቡ ከተከሰተው ድርቅ አንስቶ ስለመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ እንዲሁም በኤርትራ ጉዳይ ላይ ያደረጉት ልዩ ቃለ ምልልስ ለመመልከት እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡  

 

የአንከር ወተት ማስታወቂያ ታገደ

ከኢትዮጵያ መድኃኒት፣ ምግብና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን ጥቅምት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ለብሮድካስት ባለሥልጣን በተጻፈ ደብዳቤ የአንከር ወተት የቴሌቪዥን ማስታወቂያ ኅዳር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲታገድ

መደረጉን፣ የባለሥልጣኑ ሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ጣፋ ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

ሪፖርተር ከመድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባሥልጣን ምንጮችና ከብሮድካስት ባለሥልጣን መረዳት እንደቻለው፣ ማስታወቂያው እንዲቋረጥ የተደረገው በሦስት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመርያው ወተቱ ከኒውዚላንድ መጣ የሚለው የማስታወቂያው ነጥብ እየተነገረ እንዳለው ሳይሆን፣ እዚህ አገር የሚቀነባበርና የሚታሸግ መሆኑ መገለጽ አለበት የሚል ነው፡፡ 

ሁለተኛው ደግሞ ምንም እንኳ የወተቱ ማሸጊያ ላይ የተቀመጠ ቢሆንም፣ በቴሌቪዥን በሚነገረው ማስታወቂያ ወተቱን ሊጠቀሙ የሚችሉ የዕድሜ ገደብ ሊገለጽ ይገባል የሚል ነው፡፡ የመጨረሻው ከሰላሳ በላይ ንጥረ ነገሮች ያሉት ተብሎ መነገሩ የሚያሳየው ይህ ነው የሚባል ግልጽ ቁጥር ባለመኖሩ፣ በትክክል በውስጡ የሚገኘው ንጥረ ነገር መጠን መቀመጥ ይኖርበታል የሚል ነው፡፡ 

የኒውዚላንድ ሚልክ ፕሮዳክትስ ኢትዮጵያ ሼር ካምፓኒ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘኮ ኢብሮ ማስታወቂያው ሲነገር መገለጽ ነበረባቸው የተባሉት መረጃዎች በወተቱ እሽግ ላይ መገለጻቸውን በመጠቆም፣ በማስታወቂያው ያልተነገሩት በሰላሳ ሰከንድ ውስጥ ዋና ዋና ነገሮችን ለመግለጽ ሲባል መሆኑን ይናገራሉ፡፡ 

የወተቱ ዱቄት በእርግጥም የኩባንያው እናት ኩባንያ ከሆነው የኒውዚላንዱ ፍሮንቴራ ኩባንያ እንደሚመጣ ገልጸዋል፡፡ ያላቸው የንግድ ፈቃድም እዚህ አገር ለማደባለቅና ለማሸግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

እሳቸው እንደገለጹት፣ የተጠቃሚዎች ዕድሜን ስለመግለጽና የወተቱን ‹ከኒውዚላንድ የመጣ› በሚል መተዋወቅን በሚመለከት፣ ከመድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር ተነጋግረው መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ማስታወቂያውን ሲያሠራጭ ከነበረው ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ጋርም እንዲሁ ተነጋግረዋል፡፡ 

ወተቱ ምን ያህል ንጥረ ነገር አለው? (ትክክለኛ ቁጥር) የሚለውን ለማወቅ የላብራቶሪ ምርመራ እንዲደረግ ስምምነት ላይ ተደርሶ ናሙና ወደ ውጭ ተልኮ ውጤት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አቶ ዘኮ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

ማስታወቂያው እንዲቋረጥ የተደረገው ትክክለኛውን ምግብና ምግብ ነክ ነገሮች የሚተዋወቁበትን አግባብ ተከትሎ እንዲተዋወቅ ለማድረግ ሲባል እንደሆነ፣ በሚመለከታቸው የቁጥጥር ተቋማት ተገልጿል፡፡ 

በፋፋ ፉድስ ኢትዮጵያና በኒውዚላንድ ወተት አምራች ድርጅት ፎንቴራ የአሥር ሚሊዮን ዶላር የጋራ ኢንቨስትመንት፣ አንከር ወተት በዚህ ዓመት መጀመርያ ላይ ለገበያ መተዋወቁ ይታወሳል፡፡ 

 

በጦርነቱ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች መሞታቸውና ንብረት መውደሙ ተገልጿል

በደቡብ ክልል ሸካ ዞን ይዞታቸው ለኢንቨስተር በመሰጠቱ ምክንያት ምትክ ቦታ እንዲሰጣቸው ጥያቄ በማቅረባቸው ‹‹ለሕግ ተገዢ አይደሉም›› በማለትና በሽፍታነት በመፈረጅ፣ በሸኮዎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ሸካዎችን በማስታጠቅና

የእርስ በርስ ጦርነት በማነሳሳት የተጠረጠሩ፣ የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ 12 ተሿሚዎች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡ 

የደቡብ ክልል መንግሥት ፍትሕ ቢሮ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተዘዋዋሪ አንደኛ ወንጀል ችሎት ኅዳር 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ የሸኮ ብሔር ተወላጆችና የየኪ ወረዳ ፃኑ ቀበሌ ጉፍታ ንዑስ መንደር ነዋሪዎች ይዞታ ለኢንቨስተር ተሰጥቷል፡፡ ነዋሪዎቹ ለረዥም ዓመታት ምትክ ቦታና የንብረት ግምት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ጥያቄያቸውን በመቀበል ምላሽ መስጠት ያልፈለጉት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አዝመራ አንደሞና የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ‹‹ለሕግ ተገዢ አይደሉም›› በማለትና በወንጀለኛነትና በሽፍታነት በመወንጀል፣ በዞኑ ፖሊሶች ተይዘው እንዲታሰሩ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡ 

ሕጋዊ መብታቸውን በመጠየቃቸው ወንጀለኞች የሚል ስያሜ በመስጠት ነዋሪዎቹን በመተባበር በማሰርና የእርስ በርስ ጦርነት እንዲነሳ ያደረጉት ተጠርጣሪዎች የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አዝመራ አንደሞ፣ በዞኑ የደኢሕዴን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ፣ የየኪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ሻረው፣ የየኪ ወረዳ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አምሳሉ ከሴቶ፣ የቴፒ ከተማ ከንቲባ አቶ ሻሎ አድሎና ሌሎችንም ተጠርጣሪዎች ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡ 

ተጠርጣሪዎቹ ከ30 በላይ የፖሊስ አባላትን መሣሪያ በማስታጠቅ፣ ሚያዝያ 20 ቀን 2006 ዓ.ም. ወደ ፃኑ ቀበሌ ጉፍታ ንዑስ መንደር በመሄድ የሸኮ ብሔር ተወላጆችን ከበው መያዛቸውን የሚገልጸው የዓቃቤ ሕግ ክስ፣ ያልተያዙት የአካባቢው ነዋሪዎች በሁኔታው በመደናገጥና በመረበሽ ንብረታቸውንና ቤታቸውን ጥለው አጎራባች ወደሆነው ጋምቤላ ክልል ዶንቻዬ ቀበሌ መሰደዳቸውንም ያስረዳል፡፡ 

የሸኮ ነዋሪዎች ቀዬአቸውን ትተው ሲሰደዱ ተጠርጣሪዎቹ ‹‹አካባቢውን ተቆጣጥረነዋል›› በማለት አካባቢው ላይ ባንዲራ መትከላቸውንና ተመልሰው ሲመጡ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላቸውን ንዑስ የፖሊስ ጣቢያ መክፈታቸውም ተገልጿል፡፡ በአካባቢው ምሽጎችን ቆፍረው ለውጊያ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አካቷል፡፡ 

ድንገት በተፈጠረባቸው ወረራ ወደ አጎራባች ክልል የተሰደዱት ሸኮዎች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ ሕገወጥ ድብደባና እስር በተጠርጣሪዎቹ ሲፈጸምባቸው ቆይቶ፣ ድርጊቱ ወደ እርስ በርስ ግጭት ተቀይሮ በሸኮዎችና በሸካ ብሔረሰቦች መካከል ጦርነት እንዲፈጠር ማድረጋቸውንም የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ 

በሸኮዎችና በሸካ ተወላጆች መካከል በተደረገ የእርስ በርስ ጦርነት ስማቸው የታወቁ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን ማረጋገጡን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ በተጨማሪም ስማቸውን ማወቅና መለየት ያልተቻለ በርካታ ሰዎች መሞታቸውን ባቀረበው ክስ ላይም ገልጿል፡፡ ከሰባት የሚበልጡ ነዋሪዎችም ከፍተኛ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውና የገቡበት እንዳልታወቀም አክሏል፡፡ ጦርነቱ ከእነሱ አልፎ ወደ አጎራባች ቀበሌዎች እንዲስፋፋና በዞኑ የፀጥታ ችግር እንዲሰፍን ምክንያት መሆናቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡ 

ተከሳሾቹ ‹‹ወደዳችሁም ጠላችሁም የዞኑና የወረዳው ቁልፍ ያለው በእኛ እጅ ነው›› በማለት በሁለቱ ብሔረሰቦች መካከል የተነሳው ግጭት ወደ ቴፒ ከተማ አስፋፍተዋል፡፡ በግንቦት ወር 2007 ዓ.ም. የቴፒ ከተማ ፖሊስ አባላት የሆኑ አምስት ፖሊሶች ወደ ጫካ ገብተው በነበሩ የሸኮ ተወላጆች እንዲገደሉ ማድረጋቸውንና ግጭቱ እስካሁን እንዲቀጥል ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ ተከሳሾቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸውን፣ በሕዝብ ደኅንነትና ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ማስከተላቸውንና የእርስ በርስ ጦርነት የማነሳሳት ወንጀል መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ አብራርቷል፡፡ 

ተከሳሾቹ በተሰጣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት ሕግና ሥርዓትን ተከትለው ኅብረተሰቡን ማገልገል ሲገባቸው፣ ሥልጣናቸውን ተገን በማድረግ ሆን ብለውና አስበው በሕገወጥ ተግባራት በመሰማራት በሕዝብና በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቶ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን ጉዳይ የሚያየው በተዘዋዋሪ ችሎት ቢሆንም፣ የሚቀጥለው ችሎት መቼ እንደሚሰየም አልታወቀም፡፡ 

 

ለሕመም ማስታገሻ የሚውለው ኮዴይን ጥቅም ላይ እንዳይውል ታገደ

የኢትዮጵያ የመድኃኒት፣ የምግብና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 1 ቀን 2015 ባሠራጨው ሰርኩላር፣ ኮዴይን የተባለው የሕመም ማስታገሻ ላልተወሰነ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ እንዳይውል አግዷል፡፡ 

ባለሥልጣኑ ለክልሎችም ሆነ ለፌዴራል መንግሥት የጤና ቢሮዎች በላከው ደብዳቤ እንደገለጸው፣ ኮዴይን የተባለው መድኃኒት ለኢትዮጵያውያን የዘረ መል አወቃቀር (Genetic Makeup) የማይስማማ መሆኑንና ጥቅም ላይ ከዋለም እስከ ሞት ሊያደርስ እንደሚችል በጥናት መረጋገጡን አስታውቋል፡፡

ባለሥልጣኑ ዕገዳውን ያደረገው የአሜሪካ የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር በኢትዮጵያና በሌሎች አገሮች ላይ አተኩሮ ባከናወነው ጥናት፣ ኮዴይን የተባለው የሕመም ማስታገሻ እስከ ሞት የሚያደርስ መሆኑን በማሳወቁ ነው፡፡ 

የተሠራው ጥናት እንዳመለከተው በዘረ መል አወቃቀር ምክንያት አንዳንድ ሰዎች ኮዴይን ሲወስዱ ወደ ሞርፊን እንደሚቀየር፣ በዚህም ምክንያት በደም ውስጥ የሚገኘውን የሞርፊን መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር ለመተንፈስ ችግር ብሎም ለሞት እንደሚያደርስ ተገልጿል፡፡ 

በመሆኑም ማንኛውም የጤና ባለሙያና የጤና ተቋም ኮዴይን የተባለውን የሕመም ማስታገሻ በየትኛውም ዕድሜ ለሚገኙ ታካሚዎች በሕመም ማስታገሻነት ወይም ለብርድና ለሳል ሕመሞች እንዳያዙ ደብዳቤው የደረሳቸው የጤና ቢሮዎች፣ በሥራቸው ለሚተዳደሩ የጤና አገልግሎት ተቋማት እንዲያስተላልፉ አዟል፡፡ ዕገዳው የተደረገው ላልተወሰነ ጊዜ እንደሆነ ቢገልጽም፣ ላልተወሰነ የተባለበት ጊዜ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ደብዳቤው አይገልጸም፡፡ 

ጉዳዩን በተመለከተ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ በተደጋጋሚ ቢደወልም ጥሪውን አልመለሱም፡፡ የአሜሪካ የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር ጥናት እንደሚያመለክተው፣ ምርመራ ከተካሄደባቸው 122 ኢትዮጵያውያን መካከል 29 በመቶ የሚሆኑት ወይም 35 ኢትዮጵያውያን የዘረ መል አወቃቀር ኮዴይን በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ሞርፊን የሚቀይር ኢንዛይም አላቸው፡፡ 

ይህ የጥናት ውጤት ከተገለጸ ስድስት ወራት ቢሆነውም የኢትዮጵያ የመድኃኒት፣ የምግብና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ውሳኔ ሳይወስድ እስከተጠቀሰው ቀን ቆይቷል፡፡ በተመሳሳይ ጥናት የአዲስ አበባ የወተት አቅርቦት ለካንሰር የሚዳርግ አፍላቶክሲን የተባለ ውህድ እንዳለው ከተገለጸ ከስድስት ወራት በኋላ መረጃው በተለያዩ የማኅበራዊ ድረ ገጾች ሲለቀቅ፣ ባለሥልጣኑ የራሱን ተጨማሪ ጥናት እያከናወነ መሆኑን ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን መግለጹ አይዘነጋም፡፡ 

 

ኅዳር 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ረቡዕ ለሐሙስ አጥቢያ ከጓንግዙ ቻይና ወደ አዲስ አበባ በመብረር ላይ የነበረ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 777 አውሮፕላን ውስጥ የተሳፈረ መንገደኛ፣ በስካር መንፈስ ሁከት በመፍጠሩ በመንገደኞች ርብርብ በቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡

የበረራ ቁጥር ኢቲ607 ከ300 በላይ መንገደኞች አሳፍሮ ከጓንግዙ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የተነሳው ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ነበር፡፡ አንድ ሰዓት ተኩል ከበረረ በኋላ በበረራ አስተናጋጆች አማካይነት ለመንገደኞች እራት ቀርቦ ካበቃ በኋላ፣ አብዛኛዎቹ መንገደኞች አሸልበው ነበር፡፡

በአውሮፕላኑ የተሳፈሩ መንገደኞች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከእንቅልፋቸው የነቁት በሰሙት ጩኸት ምክንያት ነበር፡፡ በኢኮኖሚ ክፍል የነበሩ የበረራ አስተናጋጆች እየተጯጯሁ ወደ ቢዝነስ ክፍል ሲሮጡ መመልከታቸውን መንገደኞች ተናግረዋል፡፡ ከእንቅልፋቸው ተደናግጠው የተነሱ የተወሰኑ መንገደኞች የበረራ አስተናጋጆቹን ተከትለው ሮጠዋል፡፡

‹‹የበረራ አስተናጋጆቹ ሊገለን ነው›› እያሉ እየሮጡ ወደ ቢዝነስ ክፍል መምጣታቸውን የገለጹት ተሳፋሪዎች፣ ዕድሜው በ30ዎቹ መጨረሻ የሚገመት ናይጄሪያዊ መንገደኛ በስካር መንፈስ ተገፋፍቶ የበረራ አስተናጋጆችን ለመደብደብ ሲያባርር መመልከታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዚህን ወቅት በቢዝነስ ክፍል ውስጥ የተሳፈሩ አንድ ኢትዮጵያዊ ባለሀብት፣ በቢዝነስ ክፍል መግቢያ ላይ ጠብቀው ከሁከት ቀስቃሹ ናይጄሪያዊ ጋር ግብግብ ፈጥረዋል፡፡ ናይጄሪያዊው ግዙፍ ቢሆንም ኢትዮጵያዊው ባለሀብት እንደምንም ብለው መተናነቃቸውን ገልጸው፣ ሌሎች ናይጄሪያዊያን መንገደኞች ባደረጉላቸው እገዛ ግለሰቡን ከወለል ላይ ሊጥሉት ችለዋል፡፡ መንገደኞቹ ነውጠኛውን ተሳፋሪ በደረቱ በማስተኛት እጁን የኋሊት አስረውታል፡፡ ግለሰቡ መጠጥ መጠጥ ይሸት እንደነበር መንገደኞች ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሪፖርተር በላከው ማብራሪያ፣ ግለሰቡ በአውሮፕላኑ ውስጥ የአልኮል መጠጥ እንዳልቀረበለት ገልጿል፡፡ ለመንገደኛው የቀረበለት ለስላሳ መጠጥና ምግብ ብቻ እንደሆነ የጠቆመው አየር መንገዱ ግለሰቡ ግን ሰክሮ እንደነበር ይታመናል ብሏል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው መንገደኞች ግለሰቡ አውሮፕላኑን ከመሳፈሩ በፊት፣ የአልኮል መጠጥ በብዛት ሳይወስድ እንዳልቀረ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡

የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ነውጠኛው ግለሰብ በሌሎች ተሳፋሪዎችና በአውሮፕላኑ ላይ ጉዳት ሳያደርስ፣ ከሌሎች ተሳፋሪዎች ጋር በመተባበር ሁኔታውን መቆጣጠራቸውን አየር መንገዱ አስታውቋል፡፡

ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ አውሮፕላኑ ለሰባት ሰዓታት ያህል በመብረር ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በሰላም አርፏል፡፡ መንገደኞቹና የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ግለሰቡን ለኤርፖርት ደኅንነት ሠራተኞች አስረክበዋል፡፡ ግለሰቡ ለፌደራል ፖሊስ ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ፣ ፖሊስ ምርመራ እያካሄደበት መሆኑ ታውቋል፡፡

ከግለሰቡ ጋር ግብግብ የፈጠሩት ተሳፋሪዎች ለወደፊቱ ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጠር በግለሰቡ ላይ ጠንከር ያለ ቅጣት ሊጣል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ‹‹የፖሊስን ሪፖርት ተመልክተን በቀጣይ መደረግ ስላለበት ጉዳይ እንመክራለን፤›› ያለው አየር መንገዱ፣ የፖሊስ ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላ በግለሰቡ ላይ የወንጀል ክስ ይመሠረታል የሚል እምነት እንዳለው አስታውቋል፡፡

 

የፕላስቲክ ቱቦዎችንና መገጣጠሚያ ማሽነሪዎችን ለማስመጣትና በአገር ውስጥ ለመገጣጠም ከኢትዮጵያውያን ጋር ባለድርሻ በመሆን ያቋቋሙትን ኩባንያ መጠቀሚያ በማድረግ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤልሲ ከፍተው ካገኙት የውጭ ምንዛሪ ውስጥ ከ62.2 ሚሊዮን ብር በላይ በውጭ ባንክ በመደበቅ የተጠረጠሩ ሁለት የውጭ ዜጐች ተከሰሱ፡፡

 

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ክስ የመሠረተባቸው ተጠርጣሪ ተከሳሾች፣ በትውልድ አሜሪካዊና በዜግነት ደቡብ አፍሪካዊ መሆናቸው የተገለጸው ሚስተር ማይክል ማትሰንርና እንዲሁም ግብፃዊ መሆናቸው የተገለጸው ሚስተር አይመን አብድል ሞተልብ ሙሳ ኢሳ መሆናቸው በክሱ ተገልጿል፡፡

ግለሰቦቹ የተከሰሱት በከባድ የማታለል ወንጀልና በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል መሆኑንም ክሱ ይጠቁማል፡፡

ተከሳሾቹ ድርጊቱን እንዴት እንደፈጸሙት ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንደገለጸው፣ ኢትዮጵያውያንና ግብፃዊው ሚስተር አይመን በጋራ ባቋቋሙት ስታር ፓይፕና ፊቲንግስ ኩባንያ ውስጥ፣ ሚስተር ማትሰን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ይቀጠራሉ፡፡ ሚስተር አይመን ለብቻቸው ያቋቋሙት ጎልደን ትሬዲንግ ከሚባለው ኩባንያ በተጨማሪ ከሚስተር ማትሰን ጋር በጋራ ያቋቋሙት በዱባይ የሚገኝ ዋሶ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የሚባል ኩባንያ አላቸው፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ ከህንድና ከቻይና ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገቡ የገለጹትን የፕላስቲክ ቱቦና መገጣጠሚያ ማሽነሪዎችን፣ በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ለማጓጓዝ የተለያየ መጠን ያለው ዶላር ለማስጫኛ በመክፈል ዕቃዎቹን እንዳስገቡ መግለጻቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ 

ተከሳሾቹ ከቻይናና ከህንድ ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ እያስጫኑ ዕቃውን ሲያስገቡ፣ ለማስጫኛ ያልተከፈለውን የገንዘብ መጠን፣ በሐሰተኛ የማስጫኛ ደረሰኝና የንግድ ሽያጭ ደረሰኝና በሐሰተኛ ማኅተም ተጠቅመው ወንጀሉን እንደፈጸሙ የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ተከሳሾቹ በቻይና የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ወኪል የሆነው ‹‹የቻይና የውቅያኖስ አጓጓዥ ኤጀንሲ ሻንጋይ›› የሚል ሐሰተኛ የጭነት ደረሰኝ በማዘጋጀት፣ ‹‹የመጫኛ መነሻ ወደብ ሻንጋይ ቻይና፣ ጭነት ማራገፊያ ጂቡቲ የባህር ወደብ፣ መድረሻ ሞጆ ደረቅ ወደብና አጓጓዥ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ›› የሚል ሐሰተኛ ሰነድ አዘጋጅተው የተለያየ መጠን ያለው ዶላር እንደተከፈለ በማስመሰል፣ ጠቅላላ ድምሩ 62,278,179 ብር ዱባይ ሚስተር ማይክልና ሚስተር አይመን በጋራ በዱባይ ማሽሩክ ባንክ በከፈቱት ‹‹ዋሶ ቴክኖሎጂ ግሩፕ›› ተብሎ በሚጠራው ድርጅታቸው አካውንት ውስጥ እንዲገባ ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

ተከሳሾቹ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ ዱባይ በሚገኘው የድርጅታቸው አካውንት ማሽሩክ ባንክ ያስገቡት፣ ለምሳሌ ዕቃውን ያስጫኑት በ19,000 ዶላር ከሆነ ኤልሲ ከፍተው የውጭ ምንዛሪ ከጠየቁት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቃሊቲ ቅርንጫፍ በሚያቀርቡት ሐሰተኛ ሰነድ 40,000 ዶላር እየተቀበሉ፣ ልዩነቱን ለግላቸው ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ 

ቻይናና ህንድ ውስጥ ላለው ስታር ፓይፕና ፊቲንግስ ፋብሪካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሲላክ ‹‹የተመረተበት አገር ቻይና፣ ለማሽነሪው ለአንዱ ብቻ የተከፈለ 385,370 ዶላር›› በማለትና ትክክለኛ ምርት ለማስመሰል ‹‹በስቴት ኦፍ ቴክሳስ ንግድ ምክር ቤት የተረጋገጠ›› የሚል ሐሰተኛ ሰነድ ማኅተም ተደርጐበት እንደቀረበ ክሱ ይገልጻል፡፡

በስቴት ኦፍ ቴክሳስ ንግድ ምክር ቤት በተመዘገበው የቻይና ኩባንያ የተመረተ እውነተኛ ምርት ለማስመሰል፣ ተከሳሾቹ ዋሶ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ፕሮፎርማ ሰብስቦ እንዳረጋገጠ የሚያሳይ የንግድ ደረሰኝ በማቅረብ፣ እውነተኛ አስመስለው በሐሰተኛ ሰነድ እየተገለገሉ፣ ከዘጠኝ ጊዜያት በላይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጭ ምንዛሪ በመውሰድ የተጠቀሰውን ገንዘብ ዱባይ ወደሚገኘው አካውንታቸው ለማሸሽ መቻላቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

ተከሳሾቹ ‹‹ለኢትዮጵያ ንግድ መርከብ በቻይና ውቅያኖስ ጉዞ ኤጀንሲ የተከፈለ የውጭ ምንዛሪ›› በማለት በሐሰት ባዘጋጁት የተለያየ ሰነድ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያወጡትን የውጭ ምንዛሪ፣ ወደ ዱባይ ማሽሩክ ባንክ በመላክ ከባድ የማታለል ወንጀል መፈጸማቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ሚስተር ማትሰን በቁጥጥር ሥር ሲሆን፣ በዋስትናው ላይ ብይን ለመስጠትና የክሱን ሒደት ለማስቀጠል ለኅዳር 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ተቀጥሯል፡፡ ሚስተር አይመን ሊገኙ ባለመቻላቸው በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ ተሰጥቶ ለመጠባበቅ ለታኅሳስ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

ከሁለቱ የውጭ ዜጎች ጋር ክስ የተመሠረተባቸውና በ100,000 ብር ዋስ በውጭ ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ትዕዛዝ የተሰጠባቸው ደግሞ አቶ ወሰንዓለም ገብረ እግዚአብሔር ይባላሉ፡፡

አቶ ወሰንዓለም የተጠረጠሩት ሚስተር ማትሰን የስታር ፓይፕና ፊቲንግስ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሳሉ፣ ከድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ውጪ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ካስቀመጠው ገንዘብ ውስጥ፣ ሦስት ሚሊዮን ብር ‹‹ለሚመለከተው ሁሉ›› ተብሎ በተሰጣቸው ውክልና በድርጅቱ ስም በማውጣታቸው መሆኑን ክሱ ያብራራል፡፡ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት በሌላ ሰው ጥቅም ላይ የሥራ አመራር ጉዳት ማድረስ ወንጀል መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡     

 

የወተቱ እንቆቅልሽ

አቶ ደረጀ ዳዲ በሰንዳፋ ከተማ ወተት አምራች ነው፡፡ የራሱን ብቻም ሳይሆን ከአካባቢው ገበሬዎች እየሰበሰበ አዲስ አበባ አምጥቶ ለአከፋፋዮች ያስረክባል፡፡ በቀን እስከ 800 ሊትር ወተት ያቀርብ የነበረ ቢሆንም፣ በቅርቡ የዓለም አቀፍ

የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት (IRLI) ጥናትን በመጥቀስ በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ ከተሞች በተሰበሰቡ ወተቶች ውስጥ አፍላቶክሲን የተሰኘ ኬሚካል መገኘት በመገናኛ ብዙኃን በመዘገቡ ምክንያት፣ ትልቅ ኪሳራ እንደደረሰበት አቶ ደረጀ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት በቀን ከ300 ሊትር በላይ ማቅረብ አልቻለም፡፡ በወተት ውስጥ ለአፍላቶክሲን መገኘት ምክንያት የሆነው የሻገተ ፋጉሎ መሆኑ በጥናቱ ቢጠቀስም፣ ሪፖርተር በተለያዩ የሰንዳፋ ከተማ ወረዳዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ወተት አምራቾች ፋጉሎን ለመኖነት መጠቀም ካቆሙ ዓመታት መቆጠራቸውን ገልጸዋል፡፡ ከኑግ ዘይት ሲጨመቅ ተረፈ ምርት የሆነው ፋጉሎ ዋጋ በኩንታል 800 ብር መሆኑም፣ ከዋጋ አንፃር ተመራጭ እንደማያደርገውም ያስረዳሉ፡፡ በበረህ ወረዳ ከዳቤ ቀበሌ ወተት አምራች የሆነው አቶ ይገዙ አሰፋም የአፍላቶክሲን መገኘት ዜና በእጅጉ ገቢያቸውን እንደጐዳው ገልጿል፡፡

ባለፈው ሳምንት ተቀባዮች ሙሉ በሙሉ ወተት እንዳልተረከቡት ይናገራል፡፡ እሱም በአካባቢው ፋጉሎን ለእንስሳት መኖ ጥቅም ላይ እንደማይውል፣ ይልቁንም ቢሾፍቱ ከተማ ከሚገኝ ዓለማ ካውዳይስ የእንስሳት መኖ ከተሰኘ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተመጣጠነ መኖ እየገዙ እንደሚጠቀሙ አስረድቷል፡፡ በበረህ ወረዳ ግራር ቀበሌ ኗሪና ለሰንዳፋ አካባቢ የእንስሳት መኖ አቅራቢና ወተት አምራች የሆነው አቶ ተሾመ መንግሥቱም፣ በአካባቢው ፋጉሎን ለመኖነት እንደማይጠቀሙ ይናገራል፡፡ እሱም በቀን እስከ 160 ሊትር ወተት ያቀርብ የነበረ ቢሆንም፣ ባለፈው ሳምንት ምንም ተረካቢ አለማግኘቱን ገልጿል፡፡ በወተት ንግዳቸው ላይ እንደዚህ ያለ ኪሳራ ያስከተለው መረጃ ትክክል አለመሆኑ በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙኃን ቢገለጽም፣ ብዙም የተቀየረ ነገር እንደሌለ አምራቾቹ ሪፖርተር ባነጋገራቸው ወቅት ገልጸዋል፡፡

ምርምሩ የተካሄደው ከአዲስ አበባ፣ ከቢሾፍቱ፣ ከሰበታ፣ ከሰንዳፋና ከሱልልታ ከተማ በተወሰዱ የወተት ናሙናዎች ላይ ሲሆን፣ አፍላቶክሲን በወተት ናሙናዎቹ ውስጥ (0.41 ማይክሮ ግራም በሊትር) መገኘት ዜና በኋላ ለወትሮ የወተት ገበያ ግርግር በነበረበት ሰንዳፋ ከተማ፣ ገበያው እረጭ ማለቱን ሪፖርተር በከተማው ተዘዋውሮ ካነጋገራቸው አምራቾች ማረጋገጥ ችሏል፡፡ አምራቾቹ ወጣ የተባለው ምርምር ገበሬውን ክፉኛ የጐዳ፣ በአገር ሀብት ላይም ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደረ በመሆኑ ነገሮች ወደነበሩበት ይመለሱ ዘንድ መንግሥትና የሚመለከታቸው ሁሉ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ጥናቱን በሚመለከት የመንግሥትንና ጥናቱን የሠራው የዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት አስተያየትን፣ እንዲሁም መንግሥት የወሰዳቸውን ዕርምጃዎች በሚመለከት የተጠናቀረው ዘገባ በማኀበራዊ ገጽ ላይ ይመልከቱ፡፡ (በዘገባው ሚሊ ግራም ተብለው የተቀመጡት መለኪያዎች ማይክሮ ግራም ተብለው እንዲነበቡ የዝግጅት ክፍሉ ያሳስባል)   

 

በ50 ሺሕ ብር ዋስ ይፈቱ የተባሉት መምህር ግርማ ይግባኝ ተጠየቀባቸው

በተጠረጠሩበት ሐሰተኛ ሰነድ መጠቀም ወንጀል ተጨማሪ ጊዜ ተጠየቀባቸው

የእሳቸው ተከታይና የሚሏቸውን ነገር ሁሉ ያደርጉ የነበሩን ግለሰብ ቤት በማሸጥና ገንዘቡንም እንዲፀለይበት በማለት ወስደዋል ተብለው ተጠርጥረው የታሰሩት መምህር ግርማ ወንድሙ፣ በ50,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት በሰጠው ትዕዛዝ ላይ ፖሊስ ይግባኝ ማለቱ ታወቀ፡፡ 

የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት ለመምህር ግርማ የፈቀደውን የ50,000 ብር ዋስትና የተቃወመው ፖሊስ፣ ቅሬታውን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት አቅርቧል፡፡ ፖሊስ ባቀረበው መከራከሪያ ነጥብ ላይ ብይን ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ለኅዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

ተጠርጣሪው ሐሰተኛ ሰነድ መጠቀማቸውን ገልጾ ፖሊስ ባቀረበው ክስ ምክንያት መምህር ግርማ ኅዳር 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው የነበረ ሲሆን፣ እሳቸው ከቤተክህነት እንደተሰጣቸው የገለጹት ሰነድ በፎረንሲክ ተመርምሮ ሐሰተኛ መሆኑን እንዳረጋገጠ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ሌላ ተጨማሪ የሚመረመር ሰነድ እንዳለውና ተጨማሪ ሰነድ ሰጥተዋል የተባሉት የቤተ ክርስቲያን አባት በአገር ውስጥ አለመኖራቸውን በማስታወቅ፣ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ 

የመምህር ግርማ ጠበቆች ፖሊስ ያቀረበውን ማመልከቻና ተጨማሪ ቀናት በመቃወም፣ ደንበኛቸው በዋስ ተለቀው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የጠበቆቹን ማመልከቻ በማለፍ የሰባት ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ለፖሊስ ፈቅዷል፡፡ 

 

አርሶ አደሩን በመግደል የተጠረጠረው ፖሊስ መሰወሩ ተጠቆመ

‹‹መያዣ አውጥተን እያፈላለግነው ነው›› ፖሊስ

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሰያን ደብር ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ፣ በአካባቢው የተመደበ ፖሊስ አርሶ አደሩን ገድሎ መሰወሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

ሟች አርሶ አደር ጌቱ ዘውገ የሚባል የ27 ዓመት ወጣት መሆኑን የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ለመሞቱ ምክንያቱ የሆነው ጥቅምት 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ከአንድ ሌላ አርሶ አደር ጋር በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተጋጩበት ምክንያት ባይታወቅም ሟች አቶ ጌቱ ከአንድ የአካባቢው ሰው ጋር ሲጣላ የአካባቢው ነዋሪዎች ገላግለዋቸው ወደየቤታቸው የሄዱ ቢሆንም፣ በአካባቢው ግጭት እንደነበር ሪፖርት የደረሰው ተጠርጣሪ ምክትል ሳጅን ግርማ ብርሃኑ፣ ወደ  ሟች ቤት መምጣቱን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ ተጠርጣሪው ምክትል ሳጅን ግርማ ሟችን ይጠራና ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይዞት ለመሄድ በመነጋገር ላይ እያሉ ሌሎች ሁለት ፖሊሶች ይደርሳሉ፡፡ አንዱ ፖሊስ ሟች ላይ ድብደባ እየፈጸመበት እያለ፣ ምክትል ሳጅኑ በያዘው ክላሽኒኮቭ ጠመንጃ ተኩሶ እንደገደለው የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡

በወቅቱ በተፈጠረው ግርግር ተጠርጣሪውን ማንም ሊይዘው እንዳልቻለና ወደ ላይ እየተኮሰ ከአካባቢው መሰወሩን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ በመተባበር በሟች ላይ ድብደባ የፈጸመበት ሌላው ፖሊስ መያዝና በሕግ መጠየቅ ሲገባው፣ ከአካባቢው ዞር ተደርጎ ሌላ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር መመደቡ የአካባቢውን ነዋሪዎች እንዳስቆጣ ተናግረዋል፡፡ ሟች በቅርቡ ትዳር የያዘ መሆኑንና ቤተሰቡን እንደሚረዳ፣ በአካባቢው ተወዳጅ ወጣት አርሶ አደር እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ በቤተሰቦቹ ፊት በጠራራ ፀሐይ ገድሎት የተሰወረውን የፖሊስ ባልደረባ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት ለሕግ እንዲያቀርቡት ጠይቀዋል፡፡

በአርሶ አደሩ ላይ ተፈጽሟል ስለተባለው የግድያ ወንጀል ማብራርያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደነባ ወረዳ ፖሊስ መምርያ ኃላፊ ኢንስፔክተር መስፍን ደጉ ግድያው መፈጸሙን አረጋግጠዋል፡፡ ወንጀሉ እንደተፈጸመና ተጠርጣሪው ምክትል ሳጅን ግርማ ብርሃኑ ግን እንዳልተያዘ የገለጹት የመምርያ ኃላፊው፣ ፖሊስ ምርመራውን ጨርሶ መያዣ በማውጣት ተጠርጣሪውን ለመያዝ እየሠራ መሆኑንና ከኅብረተሰቡ ጋር ተባብረው በቅርቡ በቁጥጥር ሥር እንደሚያውሉት ተናግረዋል፡፡

ግድያው የተፈጸመው በሁለት ግለሰቦች መካከል በተነሳ ፀብ ምክንያት መሆኑን በተደረገው ምርመራ መረጋገጡን የገለጹት ኢንስፔክተሩ፣ ሟች ለሕግ አልገዛም በማለት በፖሊሶች ላይ ዕርምጃ ሊወስድ ሲል ግድያው ሊፈጸም እንደቻለ መረጃ ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የአካባቢው ፖሊስና ነዋሪዎች ተስማምተውና ተከባብረው እንደሚኖሩ የገለጹት የመምርያ ኃላፊው፣ አንዳንድ ጊዜ ሳይታሰብ ወንጀል የሚፈጸም በመሆኑ ፈጻሚውን በሕግ ፊት ማቅረብ ግድ ስለሆነ፣ የተቻለውን ሁሉ በማድረግ ተጠርጣሪውን ይዞ ለማቅረብ አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

 

በማታለል ወንጀል የተጠረጠሩት መምህር ግርማ ዋስትና ቢፈቀድላቸውም አልተፈቱም

በየካ ክፍለ ከተማ ኮተቤ በተለምዶ ወሰን ግሮሰሪ በመባል በሚታወቀው አካባቢ፣ የሚኖሩ ግለሰብን መኖሪያ ቤት በማሸጥና ገንዘባቸውንም ‹‹ፀሎት ይደረግበት›› በማለት አታለው ወስደዋል ተብለው ተጠርጥረው የታሰሩት [መምህር] ግርማ

ወንድሙ፣ ጥቅምት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በ50 ሺሕ ብር እንዲፈቱ የተፈቀደላቸው ቢሆንም፣ በተጠረጠሩበት ሌላ ወንጀል አልተፈቱም፡፡ 

ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር አድርጐ በመመርመር ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ቡድን፣ ጥቅምት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት ባቀረበው የምርመራ ሥራው፣ ተጠርጣሪው ፈቃድ ማግኘት ከሚገባቸው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን (ቤተ ክህነት) ፈቃድ ሳያገኙ፣ በሐሰተኛ ሰነድ (ፎርጅድ) ሲገለገሉ እንደነበር አስረድቷል፡፡ 

በመሆኑም ቀሪ ምርመራ እንደሚቀረው ገልጾ፣ ከጠየቀው 14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ሰባት ቀናትን ፈቅዶለታል፡፡ በመሆኑም [መምህር] ግርማ፣ ከቤት ሽያጭና ከሲም ካርድ ጋር በተያያዘ በቀረበባቸው ወንጀል በ50 ሺሕ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ በሐሰተኛ ሰነድ የተጠየቀባቸው የሰባት ቀናት ጊዜ የሚያልቀው ኅዳር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በመሆኑ በማረፊያ ቤት ለመቆየት ተገደዋል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሐዋሳ ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅና የደንበኞች አገልግሎት መኮንን፣ በሥልጣን ያላግባብ የመገልገል የሙስና ወንጀል ክስ ጥቅምት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ተመሠረተባቸው፡፡ 

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው ሶስና ሀዲስ ገበየሁ (የደንበኞች አገልግሎት መኮንን)፣ አቶ ጌታቸው ዋቅሹም (የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በደቡብ ክልል መንግሥት ኦዲት ቢሮ የመዝገብ ቤት ሠራተኛ አቶ ፀጋዬ ግርማ ሲሆኑ፣ ክሱ የቀረበው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በጥቅም ተመሳጥረውና ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመገልገል፣ የባንኩ ባልደረባ የሆኑት ወ/ሮ አለፊያ ከድር ለቤት መግዢያ ባንኩ የፈቀደላቸውን 320,000 ብር ለግል ጥቅም ማዋላቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ 

ተከሳሾቹ ባንኩ ለግለሰቧ የፈቀደውን ገንዘብ ቤቱን የሸጡላቸው ወ/ሮ ፅጌረዳ ሰይፉ አካውንት ማስገባት ሲገባቸው፣ በሁለተኛ ተከሳሽ ፀጋዬ ግርማ አካውንት ውስጥ በማስገባትና በተለያዩ ጊዜያት እያወጡ መጠቀማቸውም በክሱ ተገልጿል፡፡

የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ዋቅሹም፣ ገንዘቡ ለወ/ሮ ፅጌረዳ ሰይፉ ገቢ መደረጉን ሳያረጋግጡ በማፅደቃቸው፣ ከባድ ጉዳት በማድረስና ኃላፊነታቸውን ባለመወጣት ወንጀል ተከሰዋል፡፡ አቶ ጌታቸው የተጠረጠሩበት ወንጀል ዋስትና እንደማያስከለክል ተገልጾ፣ በ3,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱ በማዘዝ ለኅዳር 21 ቀን 2008 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

 

አቶ ጋሻው ደበበ

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቦርድ፣ የንግድ ምክር ቤቱን ዋና ጸሐፊ ከሥራ እንዲታገዱ ወሰነ፡፡

ዘጠኝ አባላት ያሉትና በአቶ ሰለሞን አፈወርቅ የሚመራው የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ፣ ዋና ጸሐፊው አቶ ጋሻው ደበበ ከኃላፊነታቸው እንዲታገዱ ውሳኔ ያሳለፈው ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ቦርዱ በዋና ጸሐፊው ላይ የዕገዳ ዕርምጃውን የወሰደበት ዋነኛ ምክንያት ግልጽ ባይሆንም፣ ከሥራ የታገዱ መሆናቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ በንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት በኩል ተፈርሞ እንዲደርሳቸው ቦርዱ ከስምምነት ላይ መድረሱ ታውቋል፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ወገኖች እንደተሰማው፣ በቦርዱና በዋና ጸሐፊው መካከል ከዚህም ቀደም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ አለመግባባቶች ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት እንዲህ ያለው ዕርምጃ ይጠበቅ ነበር ይላሉ ምንጮች፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ቦርዱ በንግድ ምክር ቤቱ ወቅታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉ የሚባሉ ችግሮችን ሲያሰባስብ እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በተለይ ንግድ ምክር ቤቱ በቅርቡ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ዕውቅና በሰጠበት ፕሮግራም ላይ ታየ የተባለው የፕሮግራም መፋለስና ጉድለት፣ የቦርድ አባላቱን አስቆጥቶ ነበር ተብሏል፡፡ በዚህ ምክንያትም አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር በማስታወስ፣ የዋና ጸሐፊው ከሥራ መታገድ አንደኛው ምክንያት ከዚህ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት የሚሰነዝሩ አሉ፡፡

የቦርዱ ዕገዳ ጊዜያዊ ይሁን ሙሉ በሙሉ ከሥራ ማሰናበትን የሚያጠቃልል መሆኑ ማረጋገጫ አልተገኘም፡፡ በሌላ በኩል ግን አቶ ጋሻው ከዚህ ውሳኔ በፊት መልቀቂያ ሳያስገቡ እንዳልቀሩ ይነገራል፡፡

ቦርዱ በአቶ ጋሻው ላይ እንዲወሰድ የወሰነው ዕርምጃ ንግድ ምክር ቤቱ በየዓመቱ በሚያካሂደውና ባለፈው ሐሙስ በይፋ በተከፈተው ‹‹የኢትዮጵያን ይግዙ›› ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት መክፈቻ ዕለት መሆኑ ደግሞ፣ ጉዳዩን አነጋጋሪ አድርጎታል፡፡

በዕለቱ አቶ ጋሻው የንግድ ትርዒቱን የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ሲመሩ እንደነበር፣  የመክፈቻ ፕሮግራሙ ከተጠናቀቀ በኋላ ቦርዱ ተሰብስቦ ውሳኔውን ማሳለፉ የምንጮች መረጃ ያመለክታል፡፡

አቶ ጋሻው ንግድ ምክር ቤቱን ከስድስት ዓመታት በላይ በዋና ጸሐፊነት በመምራት፣ በንግድ ምክር ቤቱ ረዘም ላለ ጊዜ በያዙት ኃላፊነት የቆዩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

በእሳቸው ዋና ጸሐፊነት ወቅት አራት ፕሬዚዳንቶች የተፈራረቁ መሆኑም፣ አቶ ጋሻው ከሌሎች ዋና ጸሐፊዎች በተለየ በቦታው የቆዩ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል፡፡

ወደ ንግድ ምክር ቤቱ ከመምጣታቸው ቀደም ብሎ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በንግድ ሚኒስቴር አገልግለዋል፡፡    

በንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ ዕገዳ የተደረገባቸውን አቶ ጋሻውንና የቦርድ ሰብሳቢውን አቶ ሰለሞን ሪፖርተር ለማነጋገር ጥረት ቢያደርግም፣ ሁለቱንም በአካልም ሆነ በስልክ ለማግኘት አልተቻለም፡፡ 

 

በዚህ ሳምንት በማዕከል የሚደረገው ለውጥ ይፋ ይሆናል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለክፍላተ ከተማና ለወረዳዎች 1,600 አመራሮችን ሾመ፡፡ ለተሿሚዎቹ ባለፈው ሳምንት ለሦስት ቀናት የቆየ የፖሊሲ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሙስናና በብልሹ አሠራር ገምግሞ ካሰናበታቸው አመራሮች በተጨማሪ፣ ከዲፕሎማ በታች የትምህርት ደረጃ ያላቸውን አመራሮች አንስቷል፡፡ በእነዚህ ተሿሚዎች ምትክ ለአሥሩ ክፍላተ ከተሞችና ለ116 ወረዳዎች የተሾሙት 1,600 አመራሮች ከመጀመሪያ ዲግሪና ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ናቸው ተብሏል፡፡ 

እነዚህ ተሿሚዎች አዳዲስና ከዚህ ቀደም በአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች በተለያዩ ደረጃዎች ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ተሿሚዎች ባለፈው ሳምንት ከማክሰኞ ጥቅምት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት የቆየ የፖሊሲ ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ታውቋል፡፡ 

የፖሊስ ማብራሪያውን የሰጡት የአዲስ አበባ አቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ይስሐቅ ግርማይና የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተወልደ ገብረ ፃድቃን ናቸው፡፡ 

በፖሊሲ ማብራሪያው እነዚህ ተሿሚዎች በከተማው መልካም አስተዳደር ማስፈን፣ የፀረ ሙስና ትግል በብቃት ማካሄድ እንዳለባቸውና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት መሥራት እንደሚኖርባቸው፣ በፖሊሲ ማብራሪያው ማሳሰቢያ እንደተሰጣቸው ከአቅም ግንባታ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተለይ አቶ ይስሐቅ በሥልጠና ወቅት እንደተናገሩት፣ ከዲፕሎማ በታች የትምህርት ደረጃ ያላቸው ከኃላፊነት የተነሱ አመራሮች በቀጣይ ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበት አሠራር ይፈጠራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የተነሱት የቀድሞ አመራሮች በጥቃቅንና በአነስተኛ ማኅበራት ተደራጅተው የተለያዩ ሥራዎችን እንዲያካሂዱ ይደረጋል ሲሉ አቶ ይስሐቅ በሥልጠናው ወቅት መግለጻቸው ታውቋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በክፍላተ ከተሞችና በወረዳዎች ሲያካሂድ የቆየውን ሹም ሽር በማጠናቀቅ፣ ትኩረቱን በማዕከል ደረጃ በሚያካሂደው ለውጥ ላይ አድርጓል፡፡ በዚህ ሳምንት መጨረሻ በማዕከል ደረጃ የሚያካሂደውን የመዋቅርና የባለሥልጣናት ሹም ሽር ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡      

 

ጥቅምት 20 ለ21 አጥቢያ 2008 ዓ.ም. የልጃቸውን ጓደኛ በሽጉጥ ተኩሰው በመግደል የተጠረጠሩ ሐኪም፣ ከነመሣሪያቸው በቁጥጥር ሥር ውለው እየተመረመሩ መሆኑ ታወቀ፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 13/14 ልዩ ሥፍራው ማጂክ ካርፔት በሚባለው ትምህር ቤት አካባቢ የተገደለው ወጣት ቴዎድሮስ ሲሳይ ይባላል፡፡

ቴዎድሮስ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በዕለቱ የማንቸስተር ዩናይትድ ግጥሚያ ሲመለከቱ አምሽተው በዚያው ሲዝናኑ ያመሻሉ፡፡ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት አካባቢ ሟች ቴዎድሮስና ጓደኞቹ በግድያ ወደተጠረጠሩት ዶ/ር ተስፋዬ ያዕቆብ (በሰላም ከፍተኛ የጥርስ ክሊኒክ የጥርስ ሐኪም ናቸው ተብሏል) ቤት መሄዳቸውን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች ገልጸዋል፡፡

የተጠርጣሪው ልጅ መጠጥ ሲቀምስ የመጮህና የመበጥበጥ ባህሪ እንዳለበት የሚናገሩት የዓይን እማኞች፣ ጓደኞቹን ይዞ ቤቱ እንደደረሰ ባህሪው በመነሳቱ ሟችና ሌሎች ሁለት ጓደኞቹ ከግቢ ወጥተው በመሄድ ላይ እያሉ ተጠርጣሪው ሽጉጥ ይዘው መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ አንደኛው ወጣት ኳስ ሲያዩ ማምሸታቸውን በማስረዳት ላይ እያለ ተጠርጣሪው ወደ ሟች ተጠግተው በመተኮስ እንደገደሉት የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡

የሟች ጓደኞች ተጠርጣሪው ሐኪም ሆን ብለው እንደገደሉት የገለጹ ቢሆንም፣ ተጠርጣሪው ግን ባርቆባቸው እንደሆነ ለፍርድ ቤት ማስረዳታቸውን ሪፖርተር ከፖሊስ ያገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

ተጠርጣሪውን ሐኪም በቁጥጥር ሥር አድርጎ በመመርመር ላይ የሚገኘው ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት አቅርቦ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል፡፡ ሟች ቴዎድሮስ ሲሳይ በሳሪስ አቦዬ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ጥቅምት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀኑ ስምንት ሰዓት የቀብር ሥርዓቱ መፈጸሙም ታውቋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የመርካቶ ቁጥር ሁለት ቅርንጫፍ ከፍተኛ ኦዲተርና ሦስት ኦፊሰሮች ጉቦ በመቀበል ከባድ የሙስና ወንጀል ጥቅምት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ተከሰሱ፡፡

ተከሳሾቹ የግል ተበዳይ አቶ ዮሐንስ ጥጋቡ የተባሉትን በጨርቃ ጨርቅ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴ፣ ‹‹ግዢና ሽያጭ አልተጣጣመም፣ በቆጠራ የሚፈጠረውን ጉድለት ባላንስ እናደርግልዎታለን፤›› በማለት ሁለት ሚሊዮን ብር ጉቦ መጠየቃቸውን፣ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡

የጉቦ መቀበል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሠራተኞች አቶ መሠረት ታደሰ የተባባሪዎች ምልመላና ሥልጠና ኦፊሰር፣ አቶ አበበ ደቦ ቡልቱሜ የኢንቬስትጌሺን ከፍተኛ ኦዲተር፣ አቶ አያና ጋሩማ የኢንተለጀንስ አሰባሰብ ጀማሪ ኦፊሰር፣ አቶ ሀብታሙ ታደሰ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምቦ ቅርንጫፍ ኦፊሰርና አቶ አብዲሳ ደቦ ቡልቱሜ የባንኩ የሰው ኃይል አስተዳዳር ባለሙያ ናቸው፡፡

ተከሳሾቹ ከላይ የተጠቀሰውን ሁለት ሚሊዮን ብር ጉቦ የጠየቋቸው አቶ ዮሐንስ ባለመስማማታቸው፣ አንደኛ ተከሳሽ አቶ መሠረት አደራዳሪ መስሎ ነጋዴውን በመቅረብ፣ ‹‹ኦዲተሮቹ ብዙ ገንዘብ መቀበል ስለለመዱ አንተ ሁለት መቶ ሺሕ ብር ብትሰጣቸው ምንም አይደለም፤›› ቢላቸውም ተበዳዩ አለመስማማታቸውን ክሱ ይጠቁማል፡፡ 

የነጋዴውን አለመስማማት የተረዱት ተከሳሾች ያላቸውን ዕቃ ብዛት በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋቸው እንደሰጧቸው የሚገልጸው የዓቃቤ ሕግ ክስ፣ በዝርዝር የሰጡት ዕቃ ጉድለት እንደሚያመጣና ጠቅላላ የዕቃውን ብዛት እንዳልሰጧቸው ሲገልጹላቸው፣ ተበዳዩም ካልተቆጠረ እንደማይታወቅ በመግለጽ እንደተከራከሯቸው ክሱ ያስረዳል፡፡

የግል ተበዳዩን በተለያየ መንገድ ስላስጨነቋቸው ግንቦት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ለአንደኛ ተከሳሽ አራት መቶ ሺሕ ብር መስጠታቸውን፣ በድጋሚ በተለያዩ ቀናት በድምሩ ሁለት መቶ ሺሕ ብር መስጠታቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ ተከሳሾቹ ሰነዱን ሲመረምሩ ተበዳዩ 12 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ከፍተኛ ዕዳ እንደሚመጣባቸው ማወቃቸውን በመንገር፣ ተበዳዩን በማስጨነቅ አራት መቶ ሺሕ ብር እንዲሰጧቸው ማድረጋቸውን፣ በአጠቃላይ በተለያዩ ቦታዎች በመቅጠር ተከሳሾች ከተበዳይ 1.2 ሚሊዮን ብር መቀበላቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

አቶ መሠረት የተባለው ተከሳሽ ጉቦ በመቀበል ያገኘውን ገንዘብ ለመሰወርና ለመደበቅ፣ አምቦ ከተማ ለሚኖረውና ለአራተኛ ተከሳሽ ወንድሙ አቶ ሀብታሙ አምስት መቶ ሺሕ ብር መስጠቱ በክሱ ተጠቅሷል፡፡ አቶ ሀብታሙ የገንዘቡ አመጣጥ ሕገወጥ መሆኑን እያወቀ፣ አምቦ ከተማ ቀበሌ 02 ውስጥ ስፋቱ 200 ካሬ ሜትር ቦታ በ140 ሺሕ ብር በእናቱ ስም እንደገዛለት፣ 100 ሺሕ ብር ደግሞ ለሌላ ግለሰብ እንዲያስቀምጥለት መስጠቱን ክሱ ያብራራል፡፡ አቶ አበበ ደግሞ ለአቶ አብዲሳ 287,900 ብር ሲሰጠው ገንዘቡን መሬት ውስጥ መቅበሩን፣ አቶ አያና የተባለው ሦስተኛ ተከሳሽ ደግሞ በአምቦ ከተማ 400 ካሬ ሜትር መሬት በ80 ሺሕ ብር በመግዛት በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ ለማሰመሰል መሥራታቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ፈጽመዋል በተባለው ጉቦ መቀበል ከባድ የሙስና ወንጀልና በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የሙስና ወንጀል የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡

     

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወሳኝነታቸውን ያሳዩበት መድረክ

በኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ እስከዛሬ ሲደረጉ ከነበሩ ከንግግር ያልዘለሉ የቁርጠኝነት ማሳያዎች አንድ እርከን የዘለለ እንደሆነ የተነገረለት በጥናት ላይ የተመሠረተ ውይይት፣ በቅርቡ በመንግሥት ከፍተኛው አስፈጻሚ አካል ተካሂዷል፡፡

ይህ ለሕዝብ ከወትሮው በተለየ በከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል ወቀሳና ተጠያቂነትን ያስነሳው ውይይት፣ መነሻ ምክንያቱ ታች መሬት ተወርዶ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ የዳሰሳ ጥናት መካሄዱ ነው፡፡ የጥናቱ አቅራቢዎች በውይይቱ ወቅት የችግሩን ስፋትና መጠን ሲያስረዱ፣ ለወትሮው የሐሳብ ልዩነቶቻቸውን ከመጋረጃ በስተጀርባ በመጨረስ ለሕዝብ አንድ ሆነው በመቅረብ የሚታወቁት የኢሕአዴግ ቱባ ባለሥልጣናት፣ በአደባባይ ልዩነቶቻቸውን በግልጽ ያወጡበት ውይይት እንደነበር ታይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የአገሪቱ ቁንጮ ባለሥልጣን ሆነው ከመጡበት ጊዜ  ጀምሮ፣ በግልጽ የሥልጣን ባለቤትና የገዥው ፓርቲ አቅጣጫ የመወሰን ሥልጣን እንዳላቸው ያሳዩበትም ነበር፡፡ በተለይ በመሬት፣ በኢንቨስትመንት፣ በፍትሕና በተለያዩ መስኮች በጥናቱ የቀረበው አሳሳቢ ሥጋት ካልተወገደ አደገኛነቱንም በማስጠንቀቅ አውስተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፅንኦት በመስጠት ለአገሪቱም ሆነ ለሕዝቡ አደገኛ የሆነውን የመልካም አስተዳደር ችግር መታገል የሕዝብ አመኔታን እንደሚያስገኝ አስታውቀው፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትም በውስጣቸው መደንገጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ከውይይቱ በኋላ ባለሥልጣናት በብሔር፣ በዝምድና፣ በጥቅማ ጥቅምና በመሳሰሉት ከተሳሰሯቸው ኔትወርኮቻቸው እንዲላቀቁም አስጠንቅቀዋል፡፡ ዝርዝሩን ለመመልከት እዚህ ላይ ይጫኑ ወይም በ ፖለቲካ ገጽ ይመልከቱ፡፡

 

በአማራ ክልላዊ መንግሥት በድርቅ በተጠቁ በተለያዩ ዞኖች የተከለሉ ውኃ ምንጮች ውስንነት፣ ከንፅህና ጋር ለተያያዙ በሽታዎች መፈጠር ምክንያት መሆኑ ተገለጸ፡፡ 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በዚህ ሳምንት በወጣው ሪፖርት፣ ‹‹ስካቢስ›› የተሰኘ ወረርሽኝ በምሥራቅ ጎጃም፣ በሰሜን ጎንደር፣ በደቡብ ወሎና በዋግ ህምራ ዞኖች በሚገኙ 20 ወረዳዎች መከሰቱን አስታውቋል፡፡ በዋግ ህምራ ዞን ብቻ 88,905 ግለሰቦች በወረርሽኙ መያዛቸው ታውቋል፡፡ የጤና ጥበቃ  ሚኒስቴር በበሽታው ለተጠቁ ሥፍራዎች መድኃኒቶችን በመላክ ላይ መሆኑን የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ፣ የችግሩ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ የተለያዩ ዘርፎችን ትብብር የሚጠይቅ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ 

በሽታው ተዛማች በመሆኑ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የተጀመረው ጥረት በአፋጣኝ ተስፋፍቶ መቀጠል እንደሚኖርበት የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ፣ ወረርሽኙ የተከሰተው ከድርቁ ጋር ተያይዞ እንደሆነ በሪፖርቱ አስፍሯል፡፡ 

ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ በምግብ እጥረት የተጎዱ ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ የምግብ ፕሮግራም የሚያስፈልጋቸው ሕፃናት ቁጥር ከሌላው ጊዜ በ20 በመቶ መጨመሩን፣ የተጎጂዎቹ ቁጥር በየወሩ እየጨመረ መሄዱን ጽሕፈት ቤቱ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በመስከረም ወር የተመዘገቡ በምግብ ዕጦት የተጎዱ ሕፃናት ቁጥር 35,216 የነበረ ሲሆን፣ በነሐሴ ወር ከተመዘገቡት 43,391 ሕፃናት የ19 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ቢሆንም፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በመስከረም ወር የተመዘገበው በምግብ ዕጦት የተጎዱ ሕፃናት ቁጥር ከሌላው ማንኛውም ዓመት የ20 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ 

ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበው በአማራ ክልል እንደሆነ የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ፣ በየወሩ በክልሉ 6,489 በምግብ ዕጦት የተጎዱ ሕፃናት ወደ ምግብ ፕሮግራም እንደሚገቡ ጠቁሟል፡፡ 

በኤልኒኖ ምክንያት በተፈጠረው አየር መዛባት የተከሰተው ድርቅ እየተባባሰ መምጣቱን ጠቅሶ፣ እየጨመረ የመጣውን የምግብ ዕርዳታ ፍላጎት መጠን ለማሟላት የኢትዮጵያ መንግሥት ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርብም አጥጋቢ ምላሽ አለመገኘቱን አስታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ. የ2015 እና የ2016 የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል የገንዘብ ምንጭ አለመኖሩ አሳሳቢ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ እ.ኤ.አ. ለ2016 የሚያስፈልገው ዕርዳታ በአስቸኳይ መገኘት እንዳለበት የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ፣ ዕርዳታውን አጓጉዞ ከሚፈለገው ሥፍራ ለማድረስ ከሦስት እስከ አምስት ወራት ቀድሞ መዘጋጀት እንደሚኖርበት ጠቁሟል፡፡ 

መንግሥት ከለጋሾች የሚፈለገውን ያህል የገንዘብ ድጋፍ ባለማግኘቱ ሁኔታዎች በከፉበት አካባቢ በራሱ ወጪ ዕለታዊ ዕርዳታዎች በማድረግ ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ 

ከመንግሥት የመጠባበቂያ ምግብ ክምችት 50,000 ሜትሪክ ቶን ስንዴና 300 ሜትሪክ ቶን የምግብ ዘይት በመከፋፈል ላይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የከብቶች መኖ በመታደል ላይ መሆኑን፣ የውኃ ጉድጓዶች ጥገና ሥራ እየተከናወነ እንደሆነና የውኃ ማጣሪያ ኬሚካሎች በመሠራጨት ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት በተፈጠረው ድርቅ ምክንያት 8.2 ሚሊዮን ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ የዕርዳታ አቅርቦቱ ካልተፋጠነና የአየር ፀባዩ ካልተለወጠ የተረጂዎች ቁጥር በሁለት ወራት ውስጥ 15 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ 

 

በሽብር ድርጊት ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ካቀረበባቸው በኋላ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ የተሰናበቱት የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣

ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው ይግባኝ ተመርምሮ እንደሚያስቀርብና እንደማያስቀርብ ለመንገር በድጋሚ ተቀጠሩ

የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን በመቃወም የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ይግባኝ ተከትሎ ውሳኔው እንዳይፈጸም ዕግድ የሰጠው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ጥቅምት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. የውሳኔ መዝገቡን መርምሮ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ‹‹ያስቀርባል ወይም አያስቀርብም›› ብሎ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ የተቃወመው የሥር ፍርድ ቤት የውሳኔ መዝገብ እንዳልቀረበለት ገልጿል፡፡ በመሆኑም ውሳኔውና ዝርዝር ማስረጃዎቹ ተያይዘው እንዲቀርቡለት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ 

በዕለቱ ይግባኝ የተጠየቀባቸው የአንድነት አመራር የነበሩት አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የአረና ፓርቲ አመራር የነበሩት አቶ አብረሃ ደስታና የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበሩት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ እንዲሁም አብረዋቸው ይግባኝ የተባለባቸው አቶ አብረሃም ሰለሞን በችሎት አልተገኙም፡፡ ፍርድ ቤቱ በችሎት በሰጠው ትዕዛዝ መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

 

መንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ 50 በመቶ እንደሚጨምር ይፋ አደረገ

ፋብሪካዎች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል

መንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ከሚያወጣው ወጪ ባነሰ ታሪፍ እየደጎመ ሲያቀርብ መቆየቱን በመግለጽ፣ በአሁኑ ወቅት ቢያንስ ወጪውን የሚሸፍን ታሪፍ ማስከፈል በማስፈለጉ 50 በመቶና ከዚያም በላይ ሊደርስ የሚችል ጭማሪ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡ 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ እንዳስታወቁት፣ መንግሥት ለበርካታ ዓመታት በድጎማ ሲያቀርበው የቆየው የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ በጣም ዝቅተኛ ነበር፡፡ ዝቅተኛ ብቻም ሳይሆን በአሁኑ ወቅት ኃይል አምርተው ለመንግሥት ለመሸጥ ፍላጎት ካላቸው ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ፣ የታሪፉ ዝቅተኛነት የድርድር አቅሙን እንዳዳከመበት አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት የታሪፍ ለውጥ የማድረግ አቋም እንዳለው፣ ዘ ኢኮኖሚስት ሰሞኑን በአዲስ አበባ ባካሄደው የኢትዮጵያ ጉባዔ ላይ ለታደሙ ኢንቨስትሮች ገልጸዋል፡፡ 

ኢንጂነር አዜብ እንዳብራሩት፣ መንግሥት በአሁኑ ወቅት አንድ ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ዘጠኝ የአሜሪካ ሳንቲም እያወጣ ይገኛል፡፡ በአንፃሩ አንድ ኪሎ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ስድስት የአሜሪካ ሳንቲም እያስከፈለ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የ50 በመቶና ከዚያም በላይ ለውጥ ሊሆን እንደሚችል ይፋ አድርገዋል፡፡ 

ኢንጂነሯ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ዝቅተኛ ነው ያሉት ታሪፍ በኃይል ማመንጨት ዘርፍ የሚፈለገውን ያህል የውጭ ኢንቨስትመንት እንዳይመጣ በማድረግ ሲጎዳው ቆይቷል፡፡ በመሆኑም የታሪፍ ለውጥ እንደሚደረግ በመገለጹ 14 ያህል የውጭ ኩባንያዎች ኃይል አመንጭተው ለመንግሥት ለማቅረብ ድርድር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ ኩባንያዎች መካከል የአራት ቢሊዮን ዶላር የጂኦተርማል ኃይል ፕሮጀክት ይዞ የመጣው ሬይክቪክ ጂኦተርማል፣ ጄነራል ሞተርስና ብላክ ራይኖ የተሰኙት ይጠቀሳሉ፡፡ 

ብላክ ስቶን ለተባለው የአሜሪካ ኩባንያ እህት የሆነው ብላክ ራይኖ፣ በአሁኑ ወቅት ከጂቡቲ እስከ አዋሽ 550 ኪሎ ሜትር የሚዘረጋውን የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ይህ ኩባንያ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ስምምነት ከመድረሱም በተጨማሪ፣ በመጪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ወሳኝ ወደሆነው ምዕራፍ እንደሚሸጋገር ኩባንያውን በመወከል የተገኙት ሺሌሽ ሙራሊዳሃ አስታውቀዋል፡፡ እንዲሁም በኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ሥራ ላይ ለመግባት ፍላጎት እንዳለውም ለመንግሥት ማስታወቁን ኢንጂነር አዜብ ጠቁመዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል የታሪፍ ማሻሻያ እንደሚደረግ ይፋ መደረጉ ካስደነገጣቸው መካከል የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ጨርቃ ጨርቅና ጥጥ ኢንዱስትሪዎች ፌደሬሽን የቦርድ አባል አቶ ፋሲል ታደሰ አንዱ ናቸው፡፡ ኢንጂነር አዜብ የጠቀሱት የታሪፍ ጭማሪ ኢንዱስትሪዎችን ሳይሆን ኃይል ወደ ውጭ የሚልኩትን ኩባንያዎች የሚመለከት ነው በማለት ለመከራከር ቢሞክሩም፣ ጭማሪው ሁሉንም እንደሚመለከት ኢንጂነር አዜብ አረጋግጠውላቸዋል፡፡ ‹‹ይኼማ ሙቱ ማለት ነው፤›› ያሉት አቶ ፋሲል፣ የታሪፍ ጭማሪ ከዚህ ቀደም ተነስቶ አምራች ኢንዱስትሪዎችን እንደማይመለከት ከመንግሥት ጋር ስምምነት ተደርጎ እንደነበር በመግለጽ፣ የመረጃ ችግር እንዳይሆን በማለት ሥጋታቸውን ሲገልጹ ቢደመጡም፣ ኢንጂነሯ በድጋሚ አረጋግጠውላቸዋል፡፡ ሆኖም የታሪፉ ጭማሪ ሚዛናዊ እንዲሆን መደረጉን ኢንጂነር አዜብ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

ይሁንና ይጨመራል የተባለው ታሪፍ ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ኢንጂነሯ ባይገልጹም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆን ግን ተናግረዋል፡፡ 

ከሁለት ዓመት በፊት የአፍሪካ ልማት ባንክ በአፍሪካ በከፍተኛ ወጪ ኃይል የማመንጨት አዝማሚያዎችን የሚያስቃኘው ጽሑፍ ላይ እንዳሰፈረው፣ መንግሥታት ኃይል የማመንጨት አቅማቸው ደካማ እንዲሆን ከሚያደርጉ ፈተናዎች መካከል ከፍተኛ ወጪ አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥታት የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትን ለማሟላት በድጎማ ለማቅረብ መገደዳቸውን ባንኩ አስፍሯል፡፡ 

በሌላ በኩል መንግሥት በኢነርጂው መስክ ማስተካከል ይገባዋል ከተባሉት ችግሮች መካከል የውጭ ምንዛሪ ለውጥና ሊያስከትል የሚችለውን የኪሳራ ሥጋት እንዴት እንደሚመለከተው ተጠይቋል፡፡ የቢሮክራሲ ጣጣዎች፣ በጂኦተርማል መስክ የፋይናንስና የማበረታቻ ፓኬጆችን ማሻሻል እንዳለበት የሬይክቪክ ጂኦተርማልና የብላክ ራይኖ ኃላፊዎች መንግሥትን አሳስበዋል፡፡ 

 

የመምህር ግርማ ቤት ተበረበረ

በማታለል ወንጀል ተጠርጥረው ጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት መምህር (አጥማቂ) ግርማ ወንድሙ፣ አያት የሚገኘው መኖርያ ቤታቸው በፖሊስ መበርበሩ ታወቀ፡፡ 

ፖሊስ ቤታቸውን ሲበረብር ያገኘው ነገር ባይገለጽም፣ ለተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ማስረጃ የሚሆነውና ሌሎች ተጨማሪ ነገሮች ፍለጋ ሳይሆን እንዳልቀረ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ 

መምህር ግርማ ከሁለት ወራት በፊት የእስር ትዕዛዝ ተሰጥቶባቸው እንደነበር ተጠቁሞ፣ አንድ ቀን ፖሊስ ጣቢያ አድረው ጥቅምት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡ በወቅቱም ፖሊስ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸው ነበር፡፡ የፖሊስን ጥያቄ በመቃወም የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲፈቱ በጠበቃቸውና በራሳቸው የጠየቁ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ አልተቀበላቸውም፡፡ 

መምህር ግርማ የተጠረጠሩበትን የማታለል ወንጀል የፈጸሙት፣ በመስከረም ወር 2006 ዓ.ም. እንደሆነና በየካ ክፍለ ከተማ ወሰን ግሮሰሪ አካባቢ ነዋሪ መሆናቸው ከተጠቆመው አቶ በላይነህ ከበደ መኖርያ ቤት ጋር የተገናኘ መሆኑ በምርመራው ተገልጿል፡፡ 

ፖሊስ በምርመራው እንዳረጋገጠው አቶ በላይነህ ከትዳር አጋራቸው ጋር የሚኖሩበት በ400 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ መኖርያ ቤት ነበራቸው፡፡ አቶ በላይነህ ቤታቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ካልሸጡ ሊሞቱ እንደሚችሉ መምህር ግርማ ሲነግሯቸው፣ ከፍተኛ ዋጋ ያወጣላቸው የነበረ ቤታቸውን በ800 ሺሕ ብር ለመሸጥ መገደዳቸውን የፖሊስ ምርመራ ይጠቁማል፡፡ 

መምህር ግርማ ቤቱን ማሸጥ ብቻ ሳይበቃቸው፣ ገንዘቡ እንዲበረክትላቸው እንዲፀለይበት እንዲሰጧቸው የተጠየቁት አቶ በላይነህ፣ ገንዘቡን መስጠታቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡ ሊፀለይበት ወደ መምህር ግርማ ቤት ተወስዷል የተባለው ገንዘብ ውሎ በማደሩ፣ አቶ በላይነህ ወደ መምህር ግርማ ቤት ስልክ ሲደውሉ ስልኩ አልሠራ እንዳላቸውና ወደ ውጭ አገር መሄዳቸውን እንደሰሙ መግለጻቸው በፖሊስ ተጠቅሷል፡፡ 

ተጠርጣሪው መምህር ግርማ ለፍርድ ቤቱ ከሳሻቸውን ቀይ ይሁኑ ጥቁር እንደማያውቋቸውና ሆን ተብሎ የተሸረበባቸው ሴራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የተጠረጠሩበት ወንጀል ዋስትና የማያስከለክል መሆኑን በመግለጽ በዋስ እንዲለቀቁ ቢጠይቁም፣ ፍርድ ቤቱ አልተቀበላቸውም፡፡ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ባለመቀበል ሰባት ቀናትን በመፍቀድ ለጥቅምት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

 

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለምስክርነት እንዲቀርቡ የተላለፈው ትዕዛዝ ታገደ

ተጠርጣሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩና የእንግሊዝ ኤምባሲ እንዲጠየቁ አመለከቱ

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሽብር ድርጊት ወንጀል ተጠርጥረው ለተከሰሱት ለእነ ዘመኑ ካሴ በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ያስተላለፈውን ትዕዛዝ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አገደው፡፡ 

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የሥር ፍርድ ቤት አቶ አንዳርጋቸው በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ ሐምሌ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. የሰጠውን ብይን ያገደው፣ የፌዴራል ማዕከል ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ይግባኝ ሲመረምር የሚያስቀርብ ሆኖ በማግኘቱ መሆኑን ባስተላለፈው ትዕዛዝ አስታውቋል፡፡

አቶ አንዳርጋቸው በመከላከያ ምስክርነት በቆጠሯቸው በእነ ዘመኑ ካሴ የክስ መዝገብ (አሥር ሰዎች) የተካተቱት አቶ አሸናፊ አካሉ፣ አቶ ደህናሁን ቤዛ፣ አቶ ምንዳዬ ጥላሁንና አቶ አንሙት የኔዋስ ሲሆኑ እንዲመሰክሩላቸው የፈለጉትም፣ ተከሳሾቹ ኤርትራ ሄደው ከአቶ አንዳርጋቸው ትዕዛዝና መመርያ እንደተቀበሉ ዓቃቤ ሕግ የጠቀሰባቸውን ክስ እንዲያስረዱላቸው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

በወቅቱ ከሳሸ ዓቃቤ ሕግ፣ ‹‹አቶ አንዳርጋቸው በተለያዩ ጊዜያት በተመሠረቱባቸው የወንጀል ክሶች በአንዱ ዕድሜ ልክ ሲፈረድባቸው በሌላኛው ሞት ተፈርዶባቸዋል፡፡ በመሆኑም ለምስክርነት ስለማይበቁና ሕግም ስለሚከለክላቸው ቀርበው ሊመሰክሩ አይገባም፤›› ብሎ ተቃውሞ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን የዓቃቤ ሕግን ክርክር ውድቅ በማድረግ አቶ አንዳርጋቸው ቀርበው እንዲመሰክሩ ሦስት ጊዜያት ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም፣ ማረሚያ ቤቱ የተለያዩ ምክንያቶችን በመስጠት ሳያቀርባቸው ቀርቷል፡፡ በአራተኛው ቀጠሮ ‹‹አቶ አንዳርጋቸው ማረሚያ ቤት የሉም›› ብሎ ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በደብዳቤ ገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤቱ ምላሽ ተማረው የተወሰኑት ‹‹ብይን ይሰጠን›› ሲሉ፣ አቶ ደህናሁን ቤዛና አቶ ሞንዳዬ ጥላሁን ቀርበው መመስከር እንዳለባቸው በመግለጽ፣ ፍርድ ቤቱ ከውጭ አገር (የመን ሰንዓ) ይዞ ያመጣቸው ፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉና ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲጠየቁ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀው ነበር፡፡

ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በችሎት ያመለከቱትን አቤቱታ በማጠናከር፣ ጥቅምት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ጉዳያቸውን እያየው ለሚገኘው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ጽፈዋል፡፡ ተከሳሾቹ ለፍርድ ቤቱ በጻፉት ደብዳቤ እንደገለጹት፣ አቶ አንዳርጋቸው በትውልድ ኢትዮጵያዊ ቢሆኑም በዜግነት እንግሊዛዊ በመሆናቸው፣ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ጉዳያቸውን እንደሚከታተሉ ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም የእንግሊዝ ኤምባሲ፣ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉና ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲጠየቁ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡

የሥር ፍርድ ቤት በተከሳሾቹ ደብዳቤ ላይ ብይን ከመስጠቱ በፊት ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ይግባኝ የመረመረው ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የሥር ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዳይፈጸም በማገድ፣ ያስቀርባል ባለው ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለኅዳር 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

 

ስታንዳርድ ባንክ ኢትዮጵያዊቷን የባንክ ባለሙያ ለኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤቱ ሾመ

በአፍሪካ ባካበተው ሀብት ቁንጮ በመባል የሚታወቀው የደቡብ አፍሪካው ስታንዳርድ ባንክ፣ የኢኮኖሚና የባንክ ባለሙያዋን ወይዘሪት ጣይቱ ወንድወሰንን የኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤቱ ተጠሪ አድርጎ ሾመ፡፡ 

ወይዘሪት ጣይቱ የግዙፉ ባንክ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን የኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ከተሾሙ ቢቆዩም፣ የጽሕፈት ቤቱ በይፋ ሥራ መጀመር በተበሰረበት ጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ወቅት ሹመታቸው ታውቋል፡፡ ስታንዳርድ ባንክ የጽሕፈት ቤቱን አድርሻ ቦሌ አካባቢ፣ ከሞናርክ ሆቴል አጠገብ በሚገኘው ፕላኔት ሌን ታወር ሕንፃ ላይ አድርጓል፡፡ 

የስታንዳርድ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቤን ክሩገር የጽሕፈት ቤቱን መከፈት በማስመልከት እንደተናገሩት፣ ስታንዳርድ ባንክ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ ደንበኞቹ ድልድይ ሆኖ ይሚሠራል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ በሚሰጠው መመርያ መሠረት ጽሕፈት ቤቱ እንደሚመራ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የኢነርጂ እምብርት በመሆን ላይ እንደምትገኝ ያስታወቁት ክሩገር፣ ወደፊት የኃይል ኤክስፖርት የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ አስገኝ እንደሚሆንም አክለዋል፡፡ 

ወይዘሪት ጣይቱ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳብራሩት፣ ባንኩ ትኩረት ከሚያደርግባቸው መስኮች መካከል የኢነርጂ፣ የመሠረተ ልማት፣ የአግሪ ቢዝነስና የፍጆታ ሸቀጦች ትልቁን ቦታ ይይዛሉ፡፡ የጽሕፈት ቤቱ መከፈት ከደንበኞች እየመጣ ያለውን ጥያቄ ለማስተናገድ ስለሆነ ለጥያቄያቸው ምላሽ እንደሚሰጥ አብራርተዋል፡፡ ‹‹እዚህ የመጣነው ሰዎች እንዲያውቁን፣ ገበያውን ለመረዳት፣ የጥናት አቅማችንን ለማሳደግ፣ ነገሮች እንዴት እንደሚጓዙ ለማየትና ኢኮኖሚው እንዴት እንደሚንቀሳቀስ ለመረዳት ነው፤›› ያሉት ኃላፊዋ፣ የባንኩ ደንበኞች በዚህ አገር ለመሠማራት ቢፈልጉም ድጋፍ ለመስጠት ባንኩ ጽሕፈት ቤት ከፍቷል ብለዋል፡፡ ባንኩ ከአፍሪካ በተጨማሪ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በእስያ፣ በደቡብ አሜሪካና በሌሎችም አገሮች ደንበኞች እንዳፈራ ገልጸዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ ተወልደው ያደጉት ወይዘሪት ጣይቱ በአሜሪካ የኢኮኖሚክስና የፋይናንስ ትምህርቶችን ተከታትለዋል፡፡ በአሜሪካ ታዋቂና ግዙፍ ከሆኑት መካከል በኒው ዮርክ ፌደራል ሪዘርፍ ባንክ፣ እንዲሁም በጂፒ ሞርጋን ባንክ በኮርፖሬት ባንክ ዘርፍ በማገልገል የካበተ ልምድ አላቸው፡፡ በኒው ዮርክ ሪዘርቭ ባንክ በነበራቸው ቆይታ ወቅት የአሜሪካ ባንኮችን ጨምሮ የዓለም የፋይናንስ ተቋማትን ቀውስ ውስጥ የከተተውን አጋጣሚ አስተናግደዋል፡፡ 

ከስምንት ዓመት በፊት የተከሰተው ቀውስ ሌህማን ብራዘርስ የተባለውን የአሜሪካ ባንክ የውኃ ሽታ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ የኒው ዮርክ ሪዘርቭ ባንክ በወቅቱ የተከሰተውን ቀውስ የማጣራት ተግባር እንዲያከናውን በተደረገበት ወቅት ወይዘሪት ጣይቱ የባንኩ ባልደረባ ነበሩ፡፡ 

ስታንዳርድ ባንክን ጨምሮ የናይጄሪያው ኤኮ ባንክ፣ የእንግሊዙ ኤችኤስቢሲ፣ የህንዱ ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ ኦፍ ኢንዲያ ጽሕፈት ቤቶቻቸውን በአዲስ አበባ ከከፈቱት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ 

 

ጥቅምት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ረፋዱ ላይ ሰባራ ባቡር አካካቢ ከሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በመከላከያ ምስክርነት ሊቀርቡ ከነበሩት ሦስት እስረኞች መካከል፣ ሁለቱ የማምለጥ ሙከራ ሲያደርጉ አንዱ ሲገደል አንዱ ማምለጡ ተገለጸ፡፡ 

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሕዝብ ግንኙነት ተወካይ ምክትል ሰርጀንት ሳህለ ገብርኤል ይትባረክ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እስረኞቹ ያመለጡት ፍርድ ቤት ደርሰው ለመውረድ ሲቃረቡ የመኪና በር በመስበር ነበር፡፡ በተለያዩ የውንብድና ወንጀሎች 31 ዓመት የተፈረደበት አንደኛው እስረኛ ሲያዝ፣ በተመሳሳይ ወንጀል የዘጠኝ ዓመት ከስድስት ወራት ፍርደኛ የሆነውና ተጨማሪ ሦስት ክሶች የነበሩበት ሁለተኛው እስረኛ ለማምለጥ ባደረገው ሙከራ ተገድሏል፡፡

እስረኛውን አሳዶ ለመያዝ ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ቢሆንም መንደር ውስጥ በመግባቱ ሁኔታዎች አስቸጋሪ በመሆናቸው፣ በመጨረሻ መተኮስ ግድ እንደነበር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ ‹‹እስረኛውን ረዥም ርቀት ተከታትለነዋል፡፡ ላለመተኮስ ከፍተኛ ጥረት  ተደርጓል፡፡ ነገር ግን መንደር ውስጥ በመግባቱ የተወሰደው ዕርምጃ የግድ የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡

ለማምለጥ ከሞከሩት ሁለት እስረኞች ጋር በአንድ መኪና ውስጥ የነበረው ሌላ እስረኛ ለመንቀሳቀስ ምንም ዓይነት ሙከራ አድርጎ እንዳልነበር የገለጹት ምክትል ሰርጀንት ሳህለ ገብርኤል፣ ያመለጠውን እስረኛ ለመያዝ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ክትትሉ እየተደረገ ያለው ከአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ጋር መሆኑንና የእስረኛው ፎቶግራፎችም መበተናቸውንም አክለዋል፡፡

አልፎ አልፎ እስረኞች ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ሲሉ የማምለጥ ሙከራ እንደሚያጋጥም፣ ነገር ግን እስካሁን አምልጦ ሳይያዝ የቀረ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ሪፖርተር የእስረኞቹን ሙሉ ስም በሚመለከት መረጃ ያለው ቢሆንም የሕዝብ ግንኙነት ተወካዩ እንዳይገለጽ ጠይቀዋል፡፡

 

የቤጂንግ ኦሎምፒክ ድርብ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የእሷ መሆኑ የተገለጸው የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪ፣ በተሳፋሪዎች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት በማድረሱ ምክንያት በተመሠረተባት የፍትሐ ብሔር ክስ ቀርባ ባትከራከርም፣ በኦሮሚያ ክልል የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ አስተላልፎበታል፡፡ ክሱ የተመሠረተው …

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ቀርባ ባልተከራከረችበት ክስ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈባት Read more »

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ከሕግ ውጪ፣ በቃል በሚሰጥ ትዕዛዝ ብቻ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጭ በማድረግ ግዥ እየፈጸመ መሆኑ ታወቀ፡፡

የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥቆማ ደርሶት ምርመራ በመጀመር መረጃዎችን እያጠናቀረ መሆኑ ታውቋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የግዥ መመርያ ከ500 ሺሕ ብር በላይ ወጪ የሚደረግ ከሆነ፣ በውስን ጨረታ ግዥ መፈጸም ይከለክላል፡፡ ነገር ግን የአገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት ሲባል፣ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ውስን ጨረታዎችን እያወጣ በቢሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ ግዥ ሲፈጽም መቆየቱ ታውቋል፡፡

ይህ ሕግን ያልተከተለ ግዥ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ትኩረት የሳበ በመሆኑ፣ ኮሚሽኑ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የፈጸማቸውን የተለያዩ ግዥዎች ለመመርመር መረጃ ጠይቆ ወስዷል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለሚመራው ኮማንድ ፖስት ተጠሪ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በከንቲባ ድሪባ ኩማ የሚመራው የቤቶች ግንባታ ሥራ አመራር ቦርድ፣ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱን ሥራ በቅርብ እየተከታተለ መመርያ ይሰጣል፡፡

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ፣ በቃል በሚሰጥ ትዕዛዝ ብቻ ግዥ እየፈጸሙ መሆናቸውን በግልጽ ተናግረዋል፡፡

አቶ ይድነቃቸው እንዳሉት፣ የበላይ አመራሮች በቃል በሚሰጡት ትዕዛዝ ብቻ ከሕግ ውጪ ግዥ እየተፈጸመ ነው፡፡ በተጨማሪም የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት እየተመራ ያለው በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው ኮማንድ ፖስት፣ በምክትል ከንቲባውና ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ መሆኑን ገልጸው፣ በአብዛኛው በጽሑፍ ሳይሆን በቃል ትዕዛዝ መመርያ እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የሕግ ማዕቀፍ እንዲስተካከል ወይም ሰርኩላር እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ጠይቀናል፣ እስካሁን ምላሽ አላገኘንም፤›› ያሉት አቶ ይድነቃቸው፣ ‹‹የፀረ ሙስና ኮሚሽን ግዥ ስንፈጽም የቆየንባቸውን መረጃዎች ወስዷል፤›› ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 6.3 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለግንባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ግዥ ፈጽሟል፡፡ ‹‹ያለምንም የጽሑፍ ትዕዛዝ አመራሮቻችንን አምነን በ1.6 ቢሊዮን ብር የአርማታ ብረት ግዥ አከናውነናል፤›› በማለት ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው አቶ ይድነቃቸው ሳይሸሽጉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛ ይህንን ገንዘብ እያንቀሳቀስን የአዲስ አበባ የግዥ መመርያ ውስን ጨረታ ከ500 ሺሕ ብር በታች ነው ይላል፤›› በማለት የሕግ ማዕቀፉ ሊሻሻል እንደሚገባም አቶ ይድነቃቸው አሳስበዋል፡፡ 

ነገር ግን የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ግዥዎቹን ለመፈጸሙ በጽሑፍ ሰርኩላር እንዲወርድለት ቢጠይቅም፣ እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል የፀረ ሙስና ኮሚሽን የተለያዩ ሰነዶችን በመውሰድ በግዥ አፈጻጸሙ ላይ ምርመራ ማካሄዱን ቀጥሏል፡፡

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ

–    ተከሳሾቹ እሳቸው የማይቀርቡ ከሆነ ብይን ይሰጠን አሉ

 በተደጋጋሚ ለሦስት ጊዜያት በተጠሩበት የመከላከያ ምስክርነት ያልቀረቡበትን ምክንያት ለጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓም. እንዲያቀርብ የታዘዘው የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደሌሉ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በላከው ደብዳቤ አስታወቀ፡፡

በእነ ዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ የተከሰሱት አቶ አሸናፊ አካሉ፣ አቶ ደህናሁን ቤዛ፣ አቶ ምንዳዬ ጥላሁንና አቶ አንሙት የኔዋስ፣ አቶ አንዳርጋቸውን በመከላከያ ምስክርነት እንደሚፈልጓቸው ለፍርድ ቤት አመልክተው ነበር፡፡ ከየመን በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው መምጣታቸውን በመጠቆም፣ ዋናው ክሳቸው በኤርትራ ከእሳቸው ጋር በመገናኘት መመርያና ትዕዛዝ ስለመቀበላቸው መሆኑን አስታውሰው እንዲያስረዱላቸው መጠየቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን ዓቃቤ ሕግ አቶ አንዳርጋቸው የዕድሜ ልክ እስራትና ሞት የተፈረደባቸው በመሆኑ፣ ቀርበው ሊመሰክሩ አይገባም በማለት ተቃውሞ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱም የዓቃቤ ሕግን ተቃውሞ ውድቅ በማድረግ ጥያቄውን ተቀብሎ ለማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር፡፡

ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. አቶ አንዳርጋቸው ይቀርባሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ማረሚያ ቤቱ በላከው ደብዳቤ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት አለመኖራቸውን በመግለጹ ተከሳሾቹ ብሶታቸውን ገልጸዋል፡፡ ማረሚያ ቤቱ ቀደም ያሉት ትዕዛዞች በትክክለኛ አድራሻ እንዳልተጻፉለት በመግለጽ ሲያመላልሳቸው ከርሞ፣ መጨረሻ ላይ እንደሌሉ መግለጹ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ክሳቸውን መከላከል ከጀመሩ ከአንድ ዓመት በላይ ማስቆጠራቸውንና በማረሚያ ቤት በደል እየደረሰባቸው ከመሆኑ አንፃር የአስተዳደሩ መልስ የማይታመን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዕድሜ ልክና የሞት ፍርደኛ ከማረሚያ ቤት ውጪ ሊታሰር እንደማይችል የገለጹት ተከሳሾቹ፣ አቶ አንዳርጋቸው ከየመን ተይዘው እንደመጡ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይልና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌቪዥን መናገራቸውን በመጥቀስ በወቅቱ ለሁለቱም አካላት ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው ለፍርድ ቤቱ ማመልከታቸውን አስታውሰዋል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው በመከላከያ ምስክርነት እንዳይሰሙ ማረሚያ ቤት ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የእሳቸው ምስክርነት ቀርቶ ብይን እንዲጣቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ተከሳሽ ምንዳዬ ጥላሁን የተባለው ተጠርጣሪ ግን፣ ‹‹ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር ተገናኝተህ መመርያ ተቀብለሀል ስለተባልኩ ቀርበው መመስከር አለባቸው፤›› በማለት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን አቤቱታ ካዳመጠ በኋላ አቶ አንዳርጋቸው ይገኙበታል ለተባለው ተቋም ትዕዛዝ ለመስጠት፣ ለጥቅምት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

–    በክሱ ባልና ሚስት ተካተዋል

የሙስና ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩት የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊዎችን ጨምሮ 15 ሠራተኞች ላይ፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ክስ መሠረተባቸው፡፡

በፌዴራል በከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች፣ አቶ ማስረሻ ምትኩ ፈንቴ የድርጅቱ የሰው ኃይል ልማትና ማኔጅመንት ዳይሬክተር፣ አቶ አስቻለው አወቀ የስትራቴጂክ ፕላኒንግና ፋይናንስ ዳይሬክተር፣ አቶ ፍቅረ ማርያም አያሌው የሰው ኃይል አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ፣ አቶ ጌታቸው ደበበ የፋይናንስ ኦፊሰር፣ የአቶ ጌታቸው ባለቤት ወ/ሮ ስሜነሽ ጌታቸው አበጋዝ (የግል ሠራተኛ)፣ መቅደላዊት ባንቱ የወ/ሮ ስሜነሽ ወንድም ሚስት፣ ወ/ሮ ገነት አረጋ የአቶ ጌታቸው እናት፣ አቶ ሚካኤል አበበ የድርጅቱ የፋይናንስ አገልግሎት የክፍያና የሒሳብ ማጠቃለያ ማስተባበሪያ ኃላፊ፣ አቶ ንጉሤ ካህሳይ የፋይናንስ ኦፊሰር፣ እፀገነት ብርሃኑ ከፍተኛ የሒሳብ ሠራተኛ፣ ሔለን ብርሃነ የከፍተኛ ጥቅማ ጥቅምና መረጃ ኦፊሰር፣ አቶ መላኩ ወርቅነህ የፋይናንስ አገልግሎት ኃላፊ፣ እሌኒ ኤልያስ የፋሲሊቲዎች ዳይሬክቶሬት ኦፊስ ኢንጂነር የነበረች፣ አቶ ዘነበ ወሰኔ የራንዌይ ቴክኒሻን የነበረና አቶ መልካሙ አበበ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት አስተዳደር ጀማሪ የፋይናንስ ኦፊሰር ናቸው፡፡

ባልና ሚስት የሆኑት አቶ ጌታቸውና ወ/ሮ ስሜነሽ በመመሳጠር ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያለውን የሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ክፍያዎች አገልግሎት ውልን በመጠቀም፣ ሠራተኞች ባልሆኑ 189 ሰዎች ስም በድምሩ 3,335,950 ብር ወደ ግል አካውንታቸው ማስገባታቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

ተከሳሾቹ የሐምሌና የነሐሴ ወር ደመወዝ ፔሮል በመሥራትና በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ ኃላፊዎችን በማስፀደቅ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤርፖርቶች ቅርንጫፍ ከድርጅቱ ገንዘብ ላይ ተቀናሽ በማድረግ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጀሞ ቅርንጫፍ በወ/ሮ ስሜነሽ ስም በተከፈተ አካውንት ውስጥ ማስገባታቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ በግለሰቧ ስም ብቻ የተከፈተውን አካውንት (Joint and/or Account) በጥምረት በማድረግ ወደ አቢሲኒያ ባንክ ጀሞ ቅርንጫፍ ማዛወራቸውንም ክሱ ይተነትናል፡፡

አቶ ጌታቸው በድርጅቱ የሚከፈላቸው የተጣራ ደመወዝ 1,173 ብር የነበረ ቢሆንም ደመወዛቸውን ወደ 9,816 ብር ከፍ በማድረግ፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ያላግባብ በመጠቀም በመንግሥትና በድርጅቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡

እሌኒ ኤልያስ የተባለች ተከሳሽ ድርጅቱን ከየካቲት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በራሷ ፈቃድ የለቀቀች መሆኗ እየታወቀ፣ አቶ ጌታቸው ከየካቲት እስከ ነሐሴ 2007 ዓ.ም. ድረስ በፔሮል ውስጥ በማካተት በወር 3,420 ብር በድምሩ 23,943 ብር እንዲከፈላት ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ አቶ ዘነበ ወሰኔ የተባለው ተከሳሽም ከአቶ ጌታቸው ጋር በመመሳጠር፣ ከታኅሳስ 1 እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ በወር 1,562 ብር በድምሩ 14,058 ብር እንዲከፈለው መደረጉም በክሱ ተጠቅሷል፡፡ አቶ ጌታቸው ለአቶ መልካሙ አበበ 13,178 ብር በባንክ ሒሳባቸው እንዲገባላቸው ማድረጋቸውንም ክሱ ያብራራል፡፡

አቶ ጌታቸውና ወ/ሮ ስሜነሽ ከድርጅቱ በተጭበረበረ መንገድ ወስደዋል የተባለውን ገንዘብ፣ በዘመዶቻቸውና በራሳቸው የተለያየ መጠን በማድረግ በባንክ በማስገባት፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስለው ማቅረባቸውን፣ እንዲሁም ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29(2ሀናመ) ሥር የተደነገገውን መተላለፋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

አቶ ፍቅረ ማርያም፣ ማስረሻ፣ ሚካኤልና ንጉሤ የተባሉት ተከሳሾች ደግሞ በደመወዝ መክፈያ ፔሮልና መሸኛ ደብዳቤው ላይ የተገለጸው ደመወዝ ቀድሞ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ልዩነቱ ፍፁም የተጋነነ ሆኖ እያለ፣ የሰነዱን ትክክለኛነት ሳያረጋግጡና ሳይፈትሹ በፊርማቸው በማፅደቃቸው በድርጅቱና በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ክሱ ይዘረዝራል፡፡ እፀገነት ብርሃኑ፣ ሔለን ብርሃነ፣ አስቻለው አወቀና መላኩ ወርቅነህ የተባሉት ተከሳሾች ደግሞ፣ እሌኒ ኤልያስ የተባለችው ተከሳሽ ከድርጀቱ ከየካቲት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በራሷ ፈቃድ ሥራዋን መልቀቋን የካቲት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሰው ሀብት ልማትና ማኔጅመንት በደብዳቤ ካሳወቀች በኋላ፣ ያልሠራችበት ጊዜ ደመወዝ ተመላሽ እንዲሆን ማድረግ ሲገባቸው ሳያደርጉ በመቅረታቸው፣ ግለሰቧ 23,943 ብር ያላግባብ እንዲከፈላት በማድረጋቸውና ግዴታቸውን በአግባቡ አለመወጣታቸውን ገልጿል፡፡

በአጠቃላይ ተጠርጣሪ ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ያላግባብ ሥልጣን መጠቀም፣ የመንግሥትን ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሥራን በማያመች አኳኋን መምራት፣ በሙስና ወንጀል የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ  የሚሉ አምስት የሙስና የወንጀል ክሶች ቀርበውባቸዋል፡፡

ክሱን የሚመረምረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ክሱን ካሰማ በኋላ፣ ተከሳሾቹ ዋስትና እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የአቶ ጌታቸው፣ ወ/ሮ ስሜነሽ፣ ወ/ሮ መቅደላዊትና ወ/ሮ ገነት አረጋን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ ሌሎቹ ተከሳሾች ከ8,000 ብር እስከ 15,000 ብር በሚደርስ ዋስ እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በክሱ ላይ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ ለኅዳር 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጥሯል፡፡   

ዓቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሠርት ቀን ተቆርጦለታል 

ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ከፍተኛ የሆነ ጉቦ በመቀበል አገራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ከቀረጥ ነፃ ተሽከርካሪዎችን በማስገባት፣ በዘመዶቻቸውና በጓደኞቻቸው ስም ሀብት በማስቀመጥ፣ እንዲሁም ለመንግሥት መግባት የነበረበትን

ታክስና ቀረጥ ለግላቸው በማድረግ ከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት አቶ ወንድሙ ቢራቱ፣ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን የሰጠው፣ በተጠርጣሪው ላይ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ምርመራውን ማጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ ነው፡፡ ቡድኑ ምርመራውን ጨርሶ ለዓቃቤ ሕግ ማስተላለፉን ገልጾ፣ ዓቃቤ ሕግ አቶ ወንድሙን ጨምሮ በአራት ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ለመመሥረት የሚያስችለውን በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 109 (1) መሠረት የ15 ቀናት ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የአቶ ወንድሙ ጠበቃ የተጠየቀውን ጊዜ በመቃወም፣ ደንበኛቸው ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀው ነበር፡፡ ዓቃቤ ሕግ ተጠርጣሪውን ዋስትና በሚያስከለክል ወይም በማይከለክል አንቀጽ ስለመክሰሱ ማወቅ እንደማይቻል ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ የዋስትናውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡  

በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ በአቶ ወንድሙና በሦስት ተጠርጣሪዎች ላይ ጥቅምት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ክስ እንዲያቀርብ ታዟል፡፡ 

 

አሜሪካና አውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድብ የታሰበውን ያህል ገንዘብ አልተዋጣም

መንግሥት ከዳያስፖራው በተለይም አሜሪካና አውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለመሰብሰብ የታሰበውን ያህል የገንዘብ መዋጮ አለማግኘቱን፣ በምክትል ጠቅላይ

ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል አስታወቁ፡፡ 

ዶ/ር ደብረ ጽዮን ይህን ያስታወቁት፣ ጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች የግድቡን አጠቃላይ የሥራ ሒደትና ክንዋኔ ለመግለጽ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡ 

‹‹አገር ውስጥ ካሉ ሠራተኞችና ዜጎች የተሰበሰበው የገንዘብ መጠን ከበቂ በላይ ነው፡፡ በተለይ በሠራተኛው በኩል የተለየ ቁርጠኛነት አስተውለናል፤›› በማለት አገር ውስጥ ያለው የገንዘብ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የውጭ የገንዘብ አስተዋጽኦ የተለያየና ቅልቅል የሚስተዋልበት ነው፡፡ በዋናነት የፍላጎት አይደለም፡፡ ነገር ግን የውጭው የገንዘብ አስተዋጽኦ በአጠቃላይ ጥሩ የሚባል አይደለም፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ 

ከውጭ የተጠበቀውን ያህል ገንዘብ መሰብሰብ ያልተቻለበት የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ የገለጹት ዶ/ር ደብረ ጽዮን፣ ‹‹ለምሳሌ አሜሪካ የገጠመን የአሜሪካ መንግሥት ደስተኛ አይደለም፡፡ ምክንያቱም እዚያ አገር ውስጥ የምትከተለው የራሱ ሕግ አለው፡፡ መዋጮ አዋጣ ወይም ቦንድ ግዛ ለማለት የምትከተለው ሕግ አለ፡፡ በቀላሉ የሚሠራ አይደለም፤›› በማለት ባለው የሕግ ክፍተት ምክንያት የታሰበውን ያህል ገንዘብ አለመገኘቱን አብራርተዋል፡፡ 

‹‹ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያንን ስብሰባ ጠርተን አንዱ 400 ዶላር ወይም አንድ ሺሕ ዶላር ይላል፡፡ ነገር ግን ይህ አካሄድ ሕገወጥ ነው በመባላችን አቁመነዋል፤›› ብለዋል፡፡

አሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ብዙ ተጠብቆ እንደነበር የገለጹት ዶ/ር ደብረ ጽዮን፣ ‹‹አሁን ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት አጠናክረን ዘንድሮ እንጀምራለን፤›› ብለው፣ የተፈጠረው የሕግ ክፍተት ተሞልቶ በከፍተኛ ሁኔታ ለመንቀሳቀስ ሥራዎች መጠናቀቃቸውን አስረድተዋል፡፡ በተመሳሳይ ‹‹አውሮፓ ያለው የገንዘብ መዋጮም ደከም ያለ ነው፤›› በማለት አክለው አስረድተዋል፡፡ 

ምንም እንኳን በአሜካሪና በአውሮፓ ለግድቡ የሚደረገው አስተዋጽኦ ከተጠበቀው በታች ቢሆንም፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ ለግድቡ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ተገልጿል፡፡ 

‹‹መካከለኛው ምሥራቅ ጥሩ ነው የሄደው፡፡ ተሳትፎውም ሆነ መጠኑ ጥሩ ነው፡፡ አገር ውስጥ ካለው በስሜትም የሚለይ አይደለም፡፡ የሕግ ጉዳይም የለም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ 

የተጠበቀውን ያህል ገንዘብ ያልተገኘበት ምክንያት በምንም ዓይነት ሁኔታ ከተቃውሞ ጋር እንደማይገናኝ የገለጹት ዶ/ር ደብረ ጽዮን፣ ‹‹ተቃውሞ ይነሳል አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እነርሱ ግን ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ አንፃር በጣት የሚቆጠሩ እብዶች ናቸው፡፡ በጣት የሚቆጠሩ እብዶች ደግሞ የትም ቦታ አሉ፡፡ እነርሱን እንደ ዳያስፖራ አንወስዳቸውም የተነጠሉ ናቸው፤›› በማለት የታሰበውን ያህል ገንዘብ መሰብሰብ ያልተቻለው ከተቃውሞ ጋር በተገናኘ እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡ 

የአገር ውስጥ አስተዋጽኦን በተመለከተ፣ ‹‹አሁን ካለበት መጨመር ነው እንጂ መልካም የሚባል ነው፡፡ ነገር ግን ከባለሀብቱ በኩል አንድ ዓይነትና ወጥ የሆነ አስተዋጽኦ አይደለም ያለው፡፡ ደከም ያሉ አሉ፣ ጥሩ የሄዱ አሉ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በድምር ውጤት ስንመለከተው ከውጤት አንፃር ከውጭና ከባለሀብቱ በቂ አላገኘንም ማለት ይቻላል፡፡ ከምንም በላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተው ሠራተኛው ነው፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

የፕሮጀክቱን አፈጻጸም መንግሥት አሳንሶ እያቀረበ ነው የሚለውን አስተያየት በተመለከተ ምን ምላሽ እንዳላቸው ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የምናሳንስበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ደብቀው እየሠሩ ነው የሚሉ የተወሰኑ ጽሑፎች ተመልክቻለሁ፡፡ ነገር ግን ያለውን ነው እየገለጽን ያለነው፡፡ እንደዚያ ቢሆንልን እንመኝ ነበር፤›› ሲሉ አስተያየቱ መሠረተ ቢስ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ 

በአሁን ወቅት ከአጠቃላይ የግድቡ ግንባታ 47 በመቶ የተጠናቀቀ መሆኑን፣ ለዚህም እስከ ሐምሌ 2007 ዓ.ም. በተሰበሰበ መረጃ መሠረት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማት ቃል ከተገባው ገንዘብ ውስጥ በአገር ውስጥ ሰባት ቢሊዮን ብር፣ በውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ደግሞ 600 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡ ተገልጿል፡፡ 

 

በቢሾፍቱ ከተማ ከታክስ ጋር በተገናኘ የልኳንዳ ቤቶቻቸው የታሸጉባቸው ከ42 በላይ የሚሆኑ ግለሰቦች፣ ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት አቤቱታ ማቅረባቸው ታወቀ፡፡ 

አዲስ በወጣ የግብር ክፍያ ተመን ወደኋላ ተመልሳችሁ አልከፈላችሁም ተብለው የንግድ ቤቶቻቸው እንደተዘጉባቸው የሚገልጹት ልኳንዳ ቤት ባለቤቶች፣ ላለፉት ሦስት ወራት ያለ ሥራ በመቆየታችን ለኪሳራ ዳርጎናል ሲሉም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የከተማዋ ልኳንዳ ቤቶች ማኅበር አባል እንደገለጹት፣ ከከተማዋ ገቢዎችና ጉምሩክ ቢሮ ጋር የተፈጠረውን ችግር በመፍታት ችግራቸው እስከ ኢሬቻ በዓል ቀን ድረስ እልባት ሊያገኝ እንደሚችል ቢጠብቁም ያለመፍትሔ መዝለቁን አስረድተዋል፡፡

የውዝግቡን መነሻ ለሪፖርተር ያስረዱት ሌላ አባል ደግሞ፣ ቀደም ባሉ ዓመታት የትርፍ ግብር ይከፍሉ የነበሩት ከእርድ በፊት በበሬ መግዣ ዋጋ ይተመን የነበረ ሲሆን፣ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ አዲስ ሕግ በመውጣቱ ወደኋላ በመሄድ የ2005 እና የ2006 ዓ.ም. የገቢ ግብር በአዲሱ ሕግ መሠረት ክፈሉ መባላቸውን አስረድተዋል፡፡ የ2005 እና የ2006 ዓ.ም. የገቢ ግብር በነባሩ ሕግ መሠረት የሚፈለግባቸውን ከፍለው የንግድ ፈቃዳቸው ቢታደስም፣ በአዲሱ ሕግ ወደኋላ በመሄድ ክፈሉ መባላቸው አግባብ አለመሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ነጋዴዎቹ አዲሱ ሕግ ከወጣበት ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በሕጉ መሠረት ለመክፈል ፈቃደኛ መሆናቸውን፣ ያለፉት ሁለት ዓመታት ተጨማሪ የግብር ጥያቄ ውድቅ ተደርጎላቸው፣ የታሸጉ የልኳንዳ ቤቶቻቸው እንዲከፈቱላቸው የአቤቱታ ደብዳቤ ለክልሉ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ማስገባታቸውን ነው ለሪፖርተር የገለጹት፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት በአዲስ አበባም ተመሳሳይ ችግር ተነስቶ የነበረ ቢሆንም፣ ጉዳዩ ወዲያውኑ እልባት ማግኘቱ አይዘነጋም፡፡ ይልቁንም የአዲስ አበባ ልኳንዳ ቤቶች ከደረሰኝ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር ተወዛግበው እንደነበረም ይታወሳል፡፡ 

የቢሾፍቱ ከተማ ገቢዎች ቢሮና የኦሮሚያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሕጉ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የሚደረግ እስከሆነ ድረስ፣ በክልሉ ውስጥ የተለየ የግብር ቅነሳ እንደማይደረግ በቅርቡ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ የቢሾፍቱ ከተማ የልኳንዳ ባለቤቶች ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ያስገቡትን አቤቱታ በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡ ጥረት ቢደረግም፣ በአዳማ ከተማ ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ምክንያት ምላሻቸውን ማግኘት አልተቻለም፡፡

 

የአምባሳደር ዘውዴ ረታ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የእውቁ ጋዜጠኛ፣ ዲፕሎማት፣ የታሪክ ተመራማሪና ደራሲ የአምባሳደር ዘውዴ ረታ ሥርዓተ ቀብር ጥቅምት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ፡፡

ለሥራ ጉዳይ በሄዱበት ለንደን ከተማ ድንገት በመታመማቸው በለንደን ቅድስት ማርያም ሆስፒታል ከፍተኛ የሕክምና ክትትል ሲደረግላቸው የነበሩት አምባሳደር ዘውዴ፣ በ80 ዓመታቸው ያረፉት መስከረም 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ነበር፡፡

በሥርዓተ ቀብራቸው ላይ በታሪክ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የቀረበው ዜና ሕይወታቸው እንደሚያመለክተው፣ አምባሳደር ዘውዴ ጥልቅ በሆነ ጥናትና ምርምር ላይ ተመሥርተው በተጠናከሩ መረጃዎች የተደገፉ፣ ‹‹የኤርትራ ጉዳይ እ.ኤ.አ ከ1941 እስከ 1963››፣ ‹‹ተፈሪ መኰንን ረጅሙ የሥልጣን ጉዞ››፣ ‹‹የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት አንደኛ መጽሐፍ ከ1923 እስከ 1948 ዓ.ም›› በሚሉ ርዕሶች ሦስት ታላላቅ የታሪክ መጻሕፍትን በተባ ብዕራቸው፣ ውበትና ለዛ በማይለየው የቋንቋ ችሎታቸው በማሰናዳት፣ ለአገርና ለወገን እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ሥራዎችን አበርክተው አልፈዋል፡፡

በ18 ዓመታቸው በዚያን ጊዜ የጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤት እየተባለ ይጠራ በነበረው የመንግሥት ተቋም በ1945 ዓ.ም. በጋዜጠኝነት ሲሠሩ፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና አቅራቢነት ለሦስት ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡

 በ1952 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሕዝብ የአገር ፍቅር ማኅበር ሥር ይዘጋጁ የነበሩት የኢትዮጵያ ድምፅና መነን መጽሔት ዝግጅት ዋና ዲሬክተር በመሆን እስከ 1954 ዓ.ም. ድረስ አገልገለዋል፡፡ ከዋና ዲሬክተርነት ኃላፊነታቸው በተደራቢ የእነዚሁ ሚዲያዎች የአማርኛ ቋንቋ አዘጋጅ ሆነው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

ቀድሞ አዣንስ ተብሎ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ወሬ ምንጭ ዋና ዲሬክተር፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የፓን አፍሪካን ኒውስ ኤጀንሲ ፕሬዚዳንት፣ የማስታወቂያ ረዳት ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትርም ነበሩ፡፡ በኢጣሊያና በቱኒዝያ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዩ መልእክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በመሆን ለአገራቸውና ለመንግሥታቸው በቅንነት በብቃትና በትጋት እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ ከፍተኛ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡ በዘመነ ደርግ የስደት ዘመናቸውም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ በዓለም አቀፍ የእርሻ ልማት ፈንድ (The International Fund for Agricultural Development) የፕሮቶኮልና የመንግሥታት ግንኙነት ኃላፊ ሆነው ለአሥራ ሦስት ዓመታት ሠርተዋል፡፡ 

የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ቀድሞ ደጃዝማች ገብረ ማርያም በኋላ ደግሞ ሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት የተከታተሉት አምባሳደር ዘውዴ፣ ከ1948 ዓ.ም. እስከ 1952 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ፈረንሣይ አገር ፓሪስ ከተማ በሚገኘው “ECOLE SUPERIEURE DE JOURNALISM DE PARIS” በተሰኘው ታዋቂ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የጋዜጠኝነት ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡

አምባሳደር ዘውዴ ረታ ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ባደረባቸው የደራሲነት ፍላጐት እኔና ክፋቴ፣ የገዛ ሥራዬ፣ ፍቅር ክፉ ችግርና እንግዳሰው የቡልጋው በሚሉ ርዕሶች አራት ቴአትሮችን ራሳቸው ጽፈውና አዘጋጅተው ለሕዝብ ዕይታ አብቅተዋል፡፡ 

በፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ አነጋገር፣ ‹‹ዘውዴ ረታ ስኬት በተሞላበት የሕይወት ዘመኑ ጋዜጠኛ፣ ዲፕሎማት፣ የታሪክ ጸሐፊ ሆኖ ሁሉንም ኃላፊነቱን በምልዓት የተወጣ ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ ሦስቱ ክህሎቶቹ ተወራራሾችም ነበሩ፡፡ በቅርቡ በከፍተኛ ደረጃ ለዓለም ዕይታ በበቃባቸው የታሪክ ሥራዎቹ የምናየውም ይህንኑ ነው፡፡ የጋዜጠኛውን ወዝ፣ የዲፕሎማትን ሥልት፣ የታሪክ ጸሐፊን ጥንቃቄ፡፡ ስለሆነም ነው ብዙውን ጊዜ በጎሪጥ የሚተያዩትን ጋዜጠኝነትንና የታሪክ ጸሐፊነትን ማጣጣም የቻለ ደራሲ ለመሆን የበቃው፤›› የሚል ምስክርነት በፕሮፌሰሩ የተሰጣቸው፡፡

በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ከሃያ ሁለት ዓመት በላይ ላበረከቱት ውጤታማ ተግባር ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የምኒልክ የመኰንን ደረጃና የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ አዛዥ መኰንን ኒሻን ተሸልመዋል፡፡ ከሃያ አምስት የተለያዩ የአፍሪካ፣ የአውሮፓና የእስያ አገሮች ኒሻኖች ተበርክተውላቸዋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በባሕር ማዶና በአገር ውስጥም ልዩ ልዩ ሽልማቶችንም ተቀዳጅተዋል፡፡ 

የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ማስታወሻ ያዥ (ልዩ ጸሐፊ)፣ እንዲሁም በተከታታይ የጦር ሚኒስትሮች የነበሩት የራስ ሙሉጌታ ይገዙና የራስ ብሩ ወልደ ገብርኤል ዋና ጸሐፊ ከነበሩት፣ ከአባታቸው ከቀኛዝማች ረታ ወልደ አረጋይና ከእናታቸው ከእማሆይ አፀደ ረድኤቱ ነሐሴ 7 ቀን 1927 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱት አምባሳደር ዘውዴ፣ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ካልተለዩዋቸው ከወ/ሮ ገሊላ ተፈራ ጋር መስከረም 21 ቀን 1959 ዓ.ም. በሕግ ተጋብተው የሁለት ሴቶችና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ፡፡ 

አንድ ሺሕ ያህል ሰዎች በተገኙበት የአምባሳደር ዘውዴ ረታ ሥርዓተ ቀብር ላይ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል፡፡

 

አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ፈላጊዎች 8.2 ሚሊዮን መድረሳቸውን መንግሥት ይፋ አደረገ

–   ጠቅላላ የሚያስፈልገው የዕርዳታ መጠን 12 ቢሊዮን ብር ደርሷል

–    አራት ቢሊዮን ብር ከመንግሥት ካዝና ወጪ መደረጉ ተጠቁሟል

በድርቅ ምክንያት አስቸኳይ የዕለት ደራሽ የምግብ ዕርዳታ የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር 8.2 ሚሊዮን መድረሱን መንግሥት ይፋ አደረገ፡፡ ለጋሾች አስፈላጊውን ዕርዳታ እያቀረቡ

አለመሆኑን መንግሥት ሲያስታውቅ፣ በጠቅላላው አስከፊነቱ እየተባባሰ ለመጣው ድርቅ 12 ቢሊዮን ብር ወይም 600 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚያስፈልግ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች ይፋ አድርገዋል፡፡ 

ጥቅምት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ከለጋሽ አገሮች፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎችና መንግሥታዊ ካልሆኑ ለጋሾች ጋር በተደረገ የሁለትዮሽ ስብሰባ ላይ የብሔራዊ አደጋ መካከልና ዝግጁነት ኮሚቴ ጸሐፊ አቶ ምትኩ ካሳ እንዳስታወቁት፣ በኤልኒኖ ክስተት ምክንያት በበልግና በመኸር (ክረምት) የዝናብ ሥርጭት በመዛባቱ 8.2 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ 

‹‹የበልግ ዝናብ መዛባት ከመኸር ዝናብ መስተጓጎል ጋር ተዳምረው የፈጠሩት ችግር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ግን በልግ በሚዛባበት ወቅት መኸር ጥሩ ይሆን ነበር፡፡ ለወትሮው በመኸር አምራች የሆኑ አካባቢዎች ለችግር ስለማይጋለጡ የተረጂዎች ቁጥር ዝቅ ያለ ነበር፡፡ አሁን ግን የሁለቱም መዛባት ችግሩን ፈጥሯል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከጥር እስከ ሰኔ ወር በሚተገበረው ሴፍቲኔት ፕሮግራም ታቅፈው የነበሩ 4.4 ሚሊዮን ሰዎችም በ8.2 ሚሊዮን አኃዝ ውስጥ ይገኛሉ፤›› ያሉት አቶ ምትኩ፣ ከጥር ወር በኋላ በመደበኛው የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ የሆኑት ሰዎች ከዕለት ደራሽ ተረጂዎች ሲለዩ፣ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚቀርብላቸው ሰዎች ቁጥር እንደሚቀንስ አስረድተዋል፡፡ 

ባለፈው የበልግ ግምገማ ተካሂዶ ነሐሴ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ይፋ በተደረገው አኃዝ መሠረት የተረጂዎች ቁጥር 4.5 ሚሊዮን እንደነበር መገለጹን ያስታወሱት አቶ ምትኩ፣ ይህ አኃዝ ይፋ ከተደረገ በኋላ መንግሥት በአብዛኛው ምላሽ ሲሰጥ መቆየቱን፣ በተወሰነ ደረጃ የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል ያልሆኑ ድርጅቶች ማለትም በካቶሊክ ሪሊፍ ሶሳይቲ ሥር የሚንቀሳቀሱ ተቋማት ለድርቅ ጉዳተኞች ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸው ተገልጿል፡፡ የበልጉ ዝናብ በመዛባቱ የተከሰተው የምግብ እጥረት 4.5 ሚሊዮኖችን ጉዳት ላይ ጥሏል ቢባልም፣ የክረምቱ ዝናብም በኢልኒኖ ሳቢያ ዘግይቶ ከመግባት ባሻገር በመጠንና በሥርጭት ስለተዛባ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ከ4.5 ሚሊዮን ወደ 7.4 ሚሊዮን፣ ቀጥሎም ወደ 7.7 ሚሊዮን ሊደርስ ችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር 8.2 ሚሊዮን መድረሱ ታይቷል ያሉት አቶ ምትኩ፣ ይህ ቁጥር ከዚህ ቀደም በሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉት 4.4 ሚሊዮን ሰዎች ያካተተ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ 

አቶ ምትኩ በሪፖርተር ተጠይቀው እንዳብራሩት፣ መንግሥት ከራሱ መጠባበቂያ ፈንድና ከክልሎች በተዋጣ በጀት አራት ቢሊዮን ብር ወይም 192 ሚሊዮን ዶላር ለዕርዳታ ማዋሉንና እንደሚቀጥልበትም ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ለአስቸኳይ ዕርዳታ እየዋለ ካለው ገንዘብ ውስጥ አብዛኛውን ከፌደራል መጠባባቂያ ፈንድ ቢያወጣም፣ ክልሎችም በራሳቸው ከያዟቸው የመጠባበቂያ ፈንድ በጀት ለድርቁ ሰለባዎች ማዋላቸው ተነግሯል፡፡ 

የኦሮሚያ ክልል 565 ሚሊዮን ብር በክልሉ ለተጎዱ ሰዎች ሲያውል፣ የአፋር ክልል በበኩሉ 100 ሚሊዮን ብር በመመደብ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ተብሏል፡፡ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም ተመሳሳይ ዕርምጃ በመውሰድ ተጎጂዎችን እየታደገ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በከፍተኛ መጠን የድርቅ ተጎጂዎች ካሉባቸው ክልሎች መካከል አፋር ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡ ሶማሌ ክልልም በተጎጂነት ከፍተኛውን ድርሻ ከሚይዙት ክልሎች ውስጥ ሲካተት የደቡብ፣ የአማራና የትግራይ ክልሎችም በድርቅ ምክንያት ተጎጂዎች የሚገኙባቸው ሆነዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እስካሁን ለተረጂዎች የተገዛውን 450 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ጨምሮ አንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ እንደሚገዛ ይፋ አድርገዋል፡፡ በጠቅላላው ከ620 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ስንዴ ለመግዛት ዓለም አቀፍ ጨረታ መውጣቱን አቶ ምትኩ አስታውቀዋል፡፡ 

ይህም ቢባል ግን ከዚህ ቀደም በተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ጥሪ ያቀረበበት አስቸኳይ የዕርዳታ መጠን 450 ሚሊዮን ዶላር (ከ9.4 ቢሊዮን ብር በላይ) ሊያስፈልግ እንደሚችል የሚጠቁም እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ እስካሁን ግን ይህ ነው የሚባል ድጋፍ አለመገኘቱን መንግሥት አስታውቋል፡፡ አቶ ምትኩ በጽሕፈት ቤታቸው ካነጋገሯቸው የውጭ ዕርዳታ ለጋሾች መካከል የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ልማት መሥሪያ ቤት (ዴፊድ) 45 ሚሊዮን ፓውንድ (ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ)፣ የስዊዝ ትብብር ተቋም ሰባት ሚሊዮን የስዊዝ ፍራንክ (152.74 ሚሊዮን ብር) ለመለገስ ቃል ከመግባታቸው ውጪ፣ ሌሎቹ ተቋማት ዕርዳታ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላቸው ከመግለጽ በቀር ቃል የገቡት የገንዘብ መጠን አልነበረም፡፡ 

መንግሥት ድርቅ ያስከተለው ከባድ አደጋ ከቁጥጥሩ ውጪ እንዳልሆነ ለለጋሽ አገሮች፣ ለተመድ ኤጀንሲዎች ተወካዮችና ለዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ያብራሩት አቶ ምትኩ፣ በአንፃሩ ከእነዚህ አካላት የተጠበቀውን ያህል ምላሽ አለመገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡ የሰብዓዊ ዕርዳታ ከዓለም አቀፍ ለጋሾች ማግኘት አስቸጋሪ ከሆነባቸው ምክንያቶች መካከል፣ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተከሰቱ ቀውሶች የኢትዮጵያን የድርቅና የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ቸል እንዲባል ሰበብ መሆናቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ 

በዓለም የምግብ ፕሮግራም የቀጣናው አስተባባሪና በብሔራዊ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ጆን አይሊፍ የተመራው የለጋሾች ቡድን፣ በኢትዮጵያ የተከሰተው አስከፊ የድርቅ አደጋ አስቸኳይ ምላሽ እንደሚያስፈልገው ከስምምነት በመድረስ፣ በጥቅምት ወር ማብቂያና በኅዳር ወር መጀመሪያ አካባቢ ተጠቃሎ ይፋ እንደሚወጣ የሚጠበቀውን ሪፖርት በመንተራስ፣ የጉዳተኞች መጠንና የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ምን ያህል እንደሚሆን በግልጽ እንደሚታወቅ ገልጸዋል፡፡

ይህም ሆኖ በጠቅላላው ለኢትዮጵያ የድርቅ ሰላባዎች ያስፈልጋል ከተባለው 12 ቢሊዮን ብር ውስጥ እስካሁን 258 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ5.1 ቢሊዮን ብር በላይ ከለጋሾች ቢገኝም ጥቅም ላይ በመዋሉ የምግብ፣ የተጨማሪ ምግብ አቅርቦት፣ የግብርና ዘርፍ ላይ ለህልውና የሚያስፈልጉ ምግብ ነክ አቅርቦቶች ከፍተኛ እጥረት መከሰቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህ መሠረት በመጪዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ ለሰብዓዊ ድጋፎች በአስቸኳይ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን 237 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ዩኒሴፍ ይፋ አድርጓል፡፡ ከዚህ ባሻገር ለልማት ከተያዘው በጀት መንግሥት ወደ አስቸኳይ ዕርዳታ መዋል እንዳለበት ዩኒሴፍ አሳስቧል፡፡ የዴንማርክ ኤምባሲም የዩኒሴፍ ጥያቄን አስተጋብቷል፡፡ በዓለም ላይ በተከሰቱት ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሳቢያ የዕርዳታ ሽሚያ በማጋጠሙ፣ መንግሥት ለልማት ሥራዎች ከሚያውለው ፈንድ ውስጥ ለድርቁ ተጎጂዎች የሚውል ገንዘብ እንዲመድብ ጠይቋል፡፡

  ሴቭ ዘ ችልድረን ኢትዮጵያ ለለጋሾች ቡድን እንዳስታወቀው፣ በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ የከረረ  መሆኑን፣ መንግሥት ምላሽ የሰጠበት መንገድ ከወትሮው የተለየና ያልተለመደ ፍጥነት የታየበት እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ሆኖም አስቸኳይ ዕርዳታ ካልተገኘ ግን አስከፊ የምግብ እጥረት ሊከሰት እንደሚችል ሥጋቱን ይፋ አድርጓል፡፡ የካናዳ ኤምባሲና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) መንግሥት መረጃ በመስጠትና ድርቅ በከሰተባቸው አካባቢዎች ፈጣን ግምገማ በማካሄድ ያገኛቸውን ውጤቶች በማሠራጨት በኩል ጥሩ ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል፡፡ አቶ ምትኩ በበኩላቸው ዘንድሮ በተከሰው ድርቅ መንግሥት ትልቁን ድርሻ በመያዝ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ከማቅረብ በተጨማሪ፣ ዕለታዊ መረጃዎችን ለለጋሾች በመስጠት ግልጽነት የተሞላበት ግንኙነት መመሥረቱን አስታውቀዋል፡፡ 

 

 

 

የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ለተሿሚዎች መኖሪያ ቤት ማቅረብ ተቸግሯል

የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በተለይ ሰሞኑን ለተሾሙ ሚኒስትሮችና የተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ፣ ከምክትል ዋና ዳይሬክተር በላይ ሹመት በሚሰጣቸው የመንግሥት ተሿሚዎች የሚሰጠው በቂ ቤት እንደሌለው አስታወቀ፡፡

በሌላ በኩል ላለፉት 24 ዓመታት አዳዲስ መኖርያ ቤቶችን እንዳይገነባ የተደረገው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ፣ ለተሿሚዎች የሚያቀርበው መኖርያ ቤት በማጣቱ ነባር ነዋሪዎችን ለማስለቀቅ መዘጋጀቱን ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የተቋሙ ከፍተኛ ባለሙያ ገለጹ፡፡ 

ከ600 በላይ የመንግሥት ተሿሚዎች የመኖርያ ቤት ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እየተጠባበቁ ቢሆንም፣ ኤጀንሲው ለተሿሚዎች የሚያቀርበው መኖርያ ቤት በማጣቱ ሦስት አማራጭን ለከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አቅርቧል፡፡ 

የመጀመርያው አማራጭ ለዘመናት በኪራይ ቤት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ግለሰቦችን ማፈናቀል ነው፡፡ ሁለተኛው አማራጭ በቤት ልማት ፕሮግራሞች እየተገነቡ ያሉ ኮንዶሚኒየሞችና ከግለሰቦች ደግሞ ሪል ስቴት ቤቶችን መግዛት ነው፡፡ ሦስተኛው አማራጭ በራሱ አቅምና በጀት መኖርያ ቤቶችን መገንባት የሚሉት መሆናቸው ታውቋል፡፡ 

ነገር ግን የተሿሚዎቹ የመኖርያ ቤት ፍላጎት አጣዳፊ በመሆኑና የመኖርያ ቤት ግዢም ሆነ ግንባታ አማራጮች ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠት የማያስችሉ በመሆናቸው፣ ኤጀንሲው ትኩረቱን ተከራዮችን ማፈናቀል ላይ ማድረጉ እየተነገረ መሆኑን ጥቅምት 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል በተደረገ ስብሰባ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኤጀንሲው ‹‹የተሻሻለው የቤቶች አስተዳደር በግል ርዕስ ባወጣው መመርያ ቁጥር 41/2007 አንቀጽ 3 ለመንግሥት ተሿሚዎች (ብቻ) ቤቶች እንደሚሰጥ አስቀምጧል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም ለፌዴራል መንግሥት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ከኃላፊነት ለሚነሱ ባለሥልጣናት መኖርያ ቤት ይሰጣል ይላል፡፡ በመመርያው ለነዋሪዎች መኖርያ ቤት እንደሚሰጥ የሚገለጽ አንቀጽ አልተቀመጠም፡፡

በዚህ መሠረት ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በግለሰብ ደረጃ ቤት መከራየት የሚታሰብ አለመሆኑን በርካታ ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም የኤጀንሲው ነባር ተከራዮች የመፈናቀል አደጋ እያንጃበበብን ነው በማለት ሥጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ይህ አደጋ ሊያንዣብብ የቻለው ለመንግሥት ባለሥልጣናት አዲስ ሹመት ከመሰጠቱ በተጨማሪ፣ ለአምስት ዓመታት ያገለገሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሥራ ጊዜያቸውን ጨርሰው በአዲስ መተካታቸው ነው፡፡ ይህ ሁኔታ አሳሳቢ ሊሆን የቻለው በርካታ አዳዲስ ተሿሚዎች የመኖርያ ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ሲሆን፣ ከነባሮቹ የፓርላማ ነዋሪዎች መኖርያ ቤቶች ውስጥ 155 የሚሆኑት አገልግሎት ለመስጠት የማይችሉ በመሆናቸው ልዋጭ ያስፈልጋል በመባሉ ነው፡፡ 

ይህ ጉዳይ ገኖ ባይወጣም የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በ2008 የሥራ ዕቅድ ላይ ከተከራይ ደንበኞቹና ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥቅምት 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ባደረገው ውይይት በተወሰነ ደረጃ ተነስቷል፡፡ 

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይለ ማርያም ዓለም ሰገድ፣ ‹‹የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ከዚህ በኋላ ቤት የሚያቀርበው ለመንግሥት ተሿሚዎች ብቻ ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ ኤጀንሲው 17 ሺሕ ቤቶችን እንደሚያስተዳድር ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ ቤቶች ውስጥ የሲኤምሲ አፓርታማዎችን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚኖሩባቸው 141 አፓርትመንቶች ሲኖሩት፣ እነዚህ አፓርትመንቶች 5,294 ቤቶች አሏቸው፡፡ ኤጀንሲው እነዚህን አፓርትመንቶች ለማስተዳደር አዲስ መመርያ ማዘጋጀቱን አቶ ኃይለ ማርያም አስታውቀዋል፡፡ 

የአፓርትመንት አስተዳደር፣ አጠቃቀምና አጠባበቅ ረቂቅ መመርያ ላይ፣ በኤጀንሲው ደንበኞች በተቋቋሙ የአፓርታማ ነዋሪዎች ማኅበራት ተወክለው ከተገኙና ከተለያዩ አካላት ከተወከሉ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ 

ተከራዮች የተከራዩትን ቤት እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ማለትም የንፅህና አጠባበቅ፣ በየሕንፃዎቹ ላይ የተከራዩ ደንበኞች አንዱ የሌላውን መብት ሳይነካ የሕንፃውን ደኅንነት ጠብቀው መኖር እንዳለባቸውና ችግር የሚፈጥር ካለ ቤቱን እስከማስለቀቅ የሚደርስ ቅጣት እንደሚጣልበት በዝርዝር በረቂቅ መመርያው ተካተዋል፡፡ 

ኤጀንሲው፣ ‹‹የደንበኞቼን ደኅንነት ለመጠበቅ የቤቴን ደኅንነት መጠበቅ ግዴታ አለብኝ›› በማለት የሕንፃዎቹን ውበትና ንፅህና ለመጠበቅ ያዘጋጀውን ረቂቅ መመርያ ለተወያዩ ካስተዋወቀ በኋላ፣ መድረኩን ለተሳታፊዎች ክፍት አድርጓል፡፡ 

የውይይቱ ተሳታፊዎች የመመርያው መዘጋጀት ጥሩ መሆኑን በጥቅሉ ከተናገሩ በኋላ ትኩረት የሰጡት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ከዚህ በኋላ የሚሠራው ለመንግሥት ተሿሚ ኃላፊዎች ብቻ ነው፤›› ለሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹ቤት የምንሰጠው ለመንግሥት ባለሥልጣናት ብቻ ነው መባሉ ያሠጋናል፡፡ እናንተ ከቤታችን ልትወጡ ነው የሚል አባባል ይመስላል፤›› ያሉት ተሳታፊዎቹ ምን ማለት እንደሆነ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀው፣ ኤጀንሲው ልብ ሊል የሚገባው የቤት ተከራዮች ታክስ እየከፈሉ አገልግሎት ማግኘት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ 

ኤጀንሲው ተከራዮችን ሊያዳምጥና ያለባቸው ችግርም ሊመለከት እንደሚገባ ተናግረው፣ ፅዳትንና ዕድሳትን በሚመለከት በረቂቅ መመርያው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መቀመጡ ተገቢ በመሆኑ፣ ከኤጀንሲው ጋር ተባብረው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ 

አንዳንዶቹ ሕንፃዎች ለተለያዩ አገልግሎቶች እየዋሉ በመሆናቸው፣ ኤጀንሲው በጥቃቅን ሥራዎች ላይ ማተኮሩን ተወት አድርጎ የትኛው ሕንፃ ለንግድ፣ የትኛው ለመኖሪያና ለቢሮ መዋል እንዳለበት በመለያየት ሥርዓት እንዲያሲዝላቸው ጠይቀዋል፡፡ ኤጀንሲው ከደንበኞቹ በሚቀርቡለት ጥያቄዎች ላይ ተገቢና አፋጣኝ ምላሽ እንደማይሰጥ የተናገሩት የውይይቱ ተካፋዮች፣ በምርኩዝ የሚሄዱ ጥበቃዎችን ቀጥሮ ሁሉም ነገር የተሟላለት ሕንፃ እንዳከራየ አድርጎ የሚናገረው ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ 

በውይይቱ ተሳታፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ የሰጡት የኤጀንሲው የተለያዩ ክፍሎች ኃላፊዎች እንደገለጹት፣ ቤቶች ለመንግሥት ተሿሚዎች ይሰጣሉ ማለት፣ ነባር ተከራዮች ይፈናቀላሉ ማለት አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአንድ አፓርትመንት ውስጥ ብዙ ተከራዮች ስላሉ፣ ወደ ሕንፃዎቹ ማን እንደሚገባ፣ ማን እንደሚወጣና ማን ነዋሪ እንደሆነ ለይቶ ለማወቅ፣ እንደሁም በዓለም ደረጃ ሥጋት እየፈጠሩ ያሉ አንዳንድ ችግሮች በዚህም እንዳይከሰቱ የደንበኞቹንም ደኅንነት ለመጠበቅ ጭምር መሆኑን፣ የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ይገዙ አስረድተዋል፡፡ 

ኤጀንሲው ያስጨነቀው የደንበኞቹን ደኅንነት እንዴት መጠበቅ እንዳለበት መሆኑን የሚያሳየው ለ40 ዓመታት በነበረው የኪራይ ተመን አከራይቶ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ደንበኞች የሕንፃዎችን ደኅነነት ጠብቀው እንዲኖሩና በአብዛኛው መታደስ ያለባቸው ሕንፃዎች ስላሉ ተባብሮ ለማደስ እንዲቻል ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዝቅ ባለ የኪራይ ዋጋ የተከራየ ደንበኛ የቤቱን፣ የግቢውንና የአካባቢውን ንፅህና መጠበቅ እንዳለበትም አክለዋል፡፡ 

ለዜጎች ነፃነት ለመታገል ከመኖሪያ ቤታቸው ወደ ትግል ቦታ ወጥተው የነበሩ ታጋዮች በመንገድና በቱቦ ሥር እየኖሩ ባለበት ሁኔታ፣ በአራትና በስድስት ብር የተከራዩ የኤጀንሲው ደንበኞች የቤቱን ንፅህና አለመጠበቃቸው አሳዛኝ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ኃይለ ማርያም፣ ከኤጀንሲው ባከራዩት ቤት አሥር ሕንፃ የሚያስገነባ ሀብት ያገኙ ነጋዴዎች አንድ ጋሎን ቀለም መግዛት አቅቷቸው ሕንፃው ቆሽሾ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ 

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር ተወያዩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ከአገር አቀፍ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር ውይይት አደረጉ፡፡

ባለፈው ዓርብና ቅዳሜ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክስ ኮሚሽን አዳራሽ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) እና ሰማያዊ ፓርቲ ‘በዕድገትና በልማት አጀንዳዎች ላይ ከመወያየታችን በፊት፣ በሌሎች አጠቃላይ ፖለቲካዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ መወያየት መቅደም አለበት’ በማለት በስብሰባው እንደማይካፈሉ በማስታወቃቸው በአዳራሹ ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡ ባለፈው ዓርብ  በመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ላይ በሚኒስቴር ዴኤታ ማዕረግ የብሔራዊ የፕላን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው አደም አማካይነት ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን፣ በዕቅዱ አጠቃላይ አፈጻጸሞችና ጉድለቶች ላይ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡    

 

  በአሥር ደረጃዎች ተከፋፍሎ ለገበያ ሲቀርብ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና ምርት ወደ ስድስት ደረጃዎች ዝቅ ብሎ ለግብይት እንዲበቃ ተወሰነ፡፡

 ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ እስካሁን የአገሪቱ የቡና ምርት በአሥር ደረጃዎች ተከፋፍሎ እንደየደረጃው  ዋጋ እየተሰጠው ሲሸጥ ቆይቷል፡፡

ይህ የደረጃ አሰጣጥ ግን ለአሠራርም ሆነ የአገሪቱ የቡና ምርት ሊያገኝ የሚገባውን ዋጋ እንዳያገኝ በማድረጉ በአዲስ አሠራር እንዲለወጥ ተደርጓል፡፡ በቡና ደረጃዎች አሰጣጥ ላይ የተደረገ ጥናት አዋጭ የሚሆነው አሥር የነበሩትን የቡና ደረጃዎች ዝቅ ማድረግ እንደሚገባ ነው፡፡ 

በዚህ መሠረት የተደረገውን ጥናት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣንና ንግድ ሚኒስቴር በመቀበላቸው፣ የ2008 ዓ.ም. የቡና ምርት ከሚገባበት ከታኅሳስ ወር ጀምሮ የኢትዮጵያ ቡና በስድስት ደረጃዎች ተከፋፍሎ ለገበያ እንዲቀርብ መወሰኑን፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤርሚያስ እሸቱ አረጋግጠዋል፡፡

እንደ አቶ ኤርሚያስ ገለጻ፣ በዚህ ውሳኔ መሠረት ለምሳሌ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተብሎ ደረጃ ይሰጣቸው የነበሩትን በአንድ ደረጃ ማጠቃለል ያስችላል፡፡ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጣቸው የቡና ዓይነቶች ዋጋ ልዩነት ተቀራራቢ በመሆኑ በአንድ ዋጋ እንዲሸጡ ያስችላል፡፡ የተሻለ ዋጋም ያስገኛል፡፡ በመጋዘን አሠራርም አሥር ቦታዎች ከፋፍሎ ከማስቀመጥ በስድስት ቦታዎች ማስቀመጥ ጊዜና ጉልበትን ይቆጥባል ብለዋል፡፡

በአዲሱ የምርት ዘመን ከታኅሳስ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው ይህ አሠራር፣ በቡና አቅራቢዎችም መደገፉን የምርት ገበያው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከአንድ እስከ አምስት ደረጃ የተሰጣቸው ለኤክስፖርት የሚቀርቡ ሲሆን፣ ደረጃ ስድስት የተሰጠው ቡና ደግሞ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚውል ነው፡፡

 

ዘውዴ ረታ - የታሪኩ ቀንድ ስብራት (1927 – 2008)

‹‹… ዘውዴ! ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ከሆነው ትውልድ መካከል እንደ አንተ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት አመራር በቅርብ የማየትና የመረዳት ዕድል ያገኘ ብዙ ሰው የለም፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ያየውንና የተረዳውን፣ ጣዕም ባለው ጽሑፍ

አብራርቶ ለመግለጽ ተሰጥኦ ያለው እንደ አንተ የመሰለ ጸሐፊ ብዙ የለም፡፡ ስለዚህ በእኔ አመለካከት ሁለት የተጣመሩ ዕድሎች በአንተ እጅ ተይዘው ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ታሪኩን የማወቅና የጽሕፈት ችሎታህ ናቸው፡፡ ስለዚህ እኔ አጥብቄ አደራ የምልህ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት ጉዳይ አንተ ዕድል አጋጥሞህ ያየኸውንና ከአዋቂዎች ዘንድ ቀርበህ ያጠናኸውን እውነተኛውን ታሪክ ገልጠህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጻፍለት፡፡ ለዚህ ሕዝብ ከአንተ በኩል ከዚህ የበለጠ የምታደርግለት ሊኖር አይችልም፡፡ አንተም አስበህ የጀመርከውን ለመፈጸም እግዚአብሔር ይርዳህ፡፡ … እኛም ወዳጆችህ፣ ዕድሜና ጤና አግኝተን የምትደክምበትን ለማንበብ ያብቃን…›› 

ከአሥራ ሁለት ዓመታት በፊት ነበር ታዋቂው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር መርዕድ ወልደ አረጋይ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት አመራርን በቅርቡ የማወቅ ዕድል ለነበራቸው፣ ከእልፍኝ እስከ አደባባይ ከንጉሠ ነገሥቱ ያልተለዩትን ዘውዴ ረታን እውነተኛው ታሪክ ገልጠህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጻፍለት ብለው የተማፀኗቸው፡፡ 

ይህን የማበረታቻ ምክር መቼም ያልረሱት ዘውዴ ረታ አምና እጅግ ግዙፍ የሆነውን ‹‹የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት›› አንደኛ መጽሐፍ ከነገሡበት 1923 እስከ 1948 ዓ.ም. ድረስ የሚሸፍነውን ታሪክ ለንባብ አደባባይ ያዋሉት፡፡ 

የአዲሱ መጽሐፋቸውንም የተለየ ፋይዳም እንዲህ አስቀምጠውታል፡፡ ‹‹እንግዲህ ማንም ሰው በቀላሉ እንደሚረዳው ኢትዮጵያ የነፃነት ችግር ያጋጠማት በሁለት ኮሎኒያሊስት በሆኑ አገሮች ነው፡፡ የመጀመሪያው የፋሽስቱ የሙሶሊኒ የግፍ ወረራ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ነፃ አውጪዎች ነን ብለው በመጡት ወዳጆቻችን በምንላቸው በእንግሊዞች ወታደራዊ የሞግዚት አስተዳደር የተፈጸመብን በደል ነው፡፡ ከእነዚህ ከሁለቱም ኮሎኒያሊስቶች የኢትዮጵያን ነፃነት ለማስመለስ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የደረሰበት መከራና ፈተና በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ይህን ሁሉ በተለይ አዲሱ ትውልድ እንዲያውቀው ስለሚያስፈልግ፣ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ታሪኩ በተቻለ መጠን ተዘርዝሮ ቀርቦለታል፡፡›› 

ጋዜጠኛ፣ ዲፕሎማትና ስመጥር የታሪክ ጸሐፊ (ሦስት ዓይና) የነበሩት አምባሳደር ዘውዴ ረታ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዕረፍት በኋላ የነበረውን የልጅ ኢያሱን፣ የንግሥት ዘውዲቱ፣ ብሎም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ታሪክ ትክክለኛውን ሒደት የዘመኑም ሆነ መጪው ትውልድ ማወቅ ያስፈልጋል በሚል ነበር የታሪክ መጽሐፋቸውን ‹‹ተፈሪ መኰንን ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ›› ለኅትመት ያበቁት፡፡ ‹‹በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የኤርትራ ጉዳይ 1941-1963›› ሌላው በመረጃና በማስረጃ የተደገፈ ታሪካዊ መጽሐፍንም እነሆ ብለዋል፡፡ 

የኤርትራን ጉዳይ የተመለከተው መጽሐፋቸው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገነዘበው በዶ/ር ኃይሉ ሃብቱ አማካይነት “THE ERITREAN QUESTION” በሚል ተተርጉሞ ለሕትመት ዝግጁ መሆኑም ይነገራል፡፡ 

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ሕገ መንግሥቱ ከተሻሻለበት ከ1948 ዓ.ም. በኋላ የነበረውን በለውጥ የታጀበው ዓቢይ ዘመን የሚያወሳውን መጽሐፍ በማዘጋጀት ላይ ነበሩ አምባሳደር ዘውዴ ረታ፡፡ በተለይ በለንደን (እንግሊዝ)፣ ፓሪስ (ፈረንሣይ) እና ሮም (ኢጣሊያ) ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ስለ ዘመነ ኃይለ ሥላሴ የሚያወሱ ሚስጥራዊ ሰነዶች በቅርቡ ክፍት መሆናቸውን ተከትሎ፣ ጥናትና ምርምር ለማድረግ ነበር መስከረም 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ወደ ባሕር ማዶ ያቀኑት፡፡ ያለሙት የዘመናት ሕልም እውን ሳያደርጉት ተቀጨ እንጂ፡፡ ሞት ቀደማቸው፡፡ የጥናታቸው ቀዳሚ መነሻ ባደረጉት ለንደን ከተማ መስከረም 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በድንገት አርፈዋል፡፡ 

በኢጣሊያና በቱኒዚያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት አቶ ዘውዴ ረት የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ በ1927 ዓ.ም. ነው፡፡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በፊት ደጃዝማች ገብረ ማርያም የአርበኞች ትምህርት ቤት በሚባለው፣ ከዚያም ሊሴ ገብረ ማርያም በተባለው ትምህርት ቤት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮ አንባቢነትና በቤተ መንግሥት ዜና አቅራቢነት ተቀጥረው ያገለገሉ ሲሆን፣ በፈረንሣይም በጋዜጠኝነት ተመርቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ድምፅ ዕለታዊ ጋዜጣና ወርኃዊው መነን መጽሔት ዳይሬክተርም ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የፓን አፍሪካን ኒውስ ኤጀንሲ ፕሬዚዳንት፣ የማስታወቂያ ረዳት ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትርም ነበሩ፡፡ በዘመነ ደርግ የስደት ዘመናቸውም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ በዓለም አቀፍ የእርሻ ልማት ፈንድ የመንግሥታት ግንኙነትና የፖለቲካ ኃላፊ ሆነው ለ13 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ 

ሦስት ዓይናው ዘውዴ ረታ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ለሃያ ሁለት ዓመት በላይ ላበረከቱት ውጤታማ ተግባር ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የምኒልክ የመኰንን ደረጃና የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ አዛዥ መኰንን ኒሻን ተሸልመዋል፡፡ ከተለያዩ አገሮችም ኒሻኖችን የተሸለሙ ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በባሕር ማዶና በአገር ውስጥም ልዩ ልዩ ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል፡፡ 

ከ49 ዓመት በፊት ከወይዘሮ ገሊላ ተፈራ ጋር ጋብቻ መሥርተው ሦስት ልጆች ያፈሩት አምባሳደር ዘውዴ አስከሬን፣ በሳምንቱ መገባደጃ ከእንግሊዝ መጥቶ ሥርዓተ ቀብራቸው በአዲስ አበባ እንደሚፈጸም ከቤተሰቦቻቸው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

 

የሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን ሪፖርት ኢትዮጵያን በመልካም አስተዳደር አነስተኛ ደረጃ ሰጣት

በየዓመቱ የአፍሪካ አገሮችን የመልካም አስተዳደር ደረጃን ይፋ በማድረግ የሚታወቀው የሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ  በመልካም አስተዳደር ረገድ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ይፋ አደረገ፡፡

ባለፈው ሰኞ በለንደን ይፋ ባደረገው እ.ኤ.አ. የ2015 የአፍሪካ አገሮች መልካም አስተዳደር ደረጃ ከ54 የአፍሪካ አገሮች 21 የሚሆኑት በመልካም አስተዳደር ዝቅጠት እንዳሳዩ ጠቁሟል፡፡ 

ባለፉት አራት ዓመታት ከአንድ እስከ አሥር ከተቀመጡት መሪ አገሮች መካከል ግማሽ ያህሉ ብቻ መሻሻል እንዳሳዩ የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ እ.ኤ.አ. ከ2011 በኋላ የአፍሪካ አገሮች በመልካም አስተዳደሩ ረገድ የተወሰነ መሻሻል በጥቅሉ በማስመዝገብ ባለፈው ዓመት 50.1 ዕድገት ማስመዝገባቸውን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

‹‹የአፍሪካ አገሮች ከ15 ዓመት በፊት ከነበረው ሁኔታ አንፃር ዛሬ ጤናማና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እየኖሩ ቢሆንም፣ የ2015ቱ ሪፖርት እንደሚያሳየው ወሳኝ በሆኑ መስኮች የታየው መሻሻል በተጠበቀው ደረጃ አልተመዘገበም ወይም በተቃራኒው ተፈጽሟል፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥሩ የመሻሻል መስመር ላይ የነበሩት ጥቂት አገሮች ሳይቀር እየተንገዳገዱ መሆናቸው የማስጠንቀቂያ ደውል ሊሆነን ይገባል፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን የገለጹት የሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን ሊቀመንበር ዶ/ር መሐመድ ኢብራሒም፣ ሁሉንም የአፍሪካ አገሮች ያማከለና ቀጣይነት ያለው መሻሻል በሁሉም መስክ ሲመዘገብ ብቻ የአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታዋ ብሩህ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

ከአንድ እስከ 20 ደረጃን ይዘው ከሚገኙት መሪ አገሮች መካከል የመጀመሪያዎቹ አምስት አገሮች እ.ኤ.አ. በ2015 ሪፖርት ከፍተኛ ለውጥ ያመጡ መሆናቸው ሲጠቆም፣ ከእነዚህም መካከል ሴኔጋል ከነበረችበት የ9ኛ፣ ኬንያ ከነበረችበት የ14ኛ፣ ሞሮኮ ከነበረችበት የ16ኛ፣ ሩዋንዳ ከነበረችበት የ11ኛና ቱኒዝያ ከነበረችበት የ8ኛ ደረጃ ተነስተው ወደ መጀመሪያዎቹ አምስት አገሮች ተርታ መካተታቸው ተገልጿል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ ኢትዮጵያ በጠቅላላው የመልካም አስተዳደር ግምገማ ከአሥሩ የመጀመሪያዎቹ አገሮች ተርታ ውስጥ የተካተተች ቢሆንም፣ በአዲሱ ሪፖርት አጠቃላይ ውጤቷ 48.6 በመቶ ነው፡፡ ይህም ከአፍሪካ አገሮች መካከል 31ኛ ደረጃን እንድትይዝ ሲያደርጋት ከቀጣናዋ ደግሞ 5ኛ አድርጓታል፡፡ ከአራቱ ዋና ዋና የመልካም አስተዳደር እመርታ ከሚታይባቸው ዘርፎች መካከል ሕዝባዊ ተሳትፎና ሰብዓዊ መብት፣ የሰው ሀብት ልማትና በተለይም ደኅንነትና የሕግ የበላይነት በቀዳሚነት ለምዘና የሚቀርቡ መሆናቸውን የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ በደኅንነትና በሕግ የበላይነት ኢትዮጵያ በአኅጉሩ 26ኛ ደረጃ ሲኖራት በምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ 5ኛ መሆኗን ያሳያል፡፡ በዚህ ዘርፍ 13.8 የመሻሻል ዕድገቷን እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ ጠብቃ ብትገኝም፣ በአገር ውስጥ የእርስ በርስ ግጭቶችና በድንበር አካባቢ በሚታዩ ግጭቶች የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ታክሎበት ለውጦች ቢመዘገቡም፣ በአገር ውስጥ በሚፈናቀሉ ዜጎችና በውጭ አገሮች የፖለቲካ ጥገኝነት በሚሹ ዜጎች ቁጥር ረገድ ሲታይ ግን፣ ደካማ አፈጻጸሞች መኖራቸውንም ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡

በግለሰብ ደኅንነት ረገድ በአኅጉሩ 12ኛ ደረጃን እንደያዘች የሚያሳየው ሪፖርት፣ በዚህ ንዑስ ዘርፍ በተለይም በብጥብጥና ወንጀል እንዲሁም በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ከአኅጉሪቱ በቀዳሚነት እንድትቀመጥ የሚያደርጋትን ሥራዎች ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ መሥራቷን የሞ ፋውንዴሽን የ2015 ሪፖርት ያስረዳል፡፡ በአንፃሩ በሕዝባዊ ተሳትፎና በፆታ እኩልነት አገሪቱ ዝቅተኛውን ደረጃ መያዟ ብቻ ሳይሆን፣ ባለፉት አራት ዓመታት ከፍተኛ ዝቅጠት ማሳየቷም ተመልክቷል፡፡ በዚህም ዘርፍ በሕዝባዊ ተሳትፎ ከአኅጉሩ 39ኛ ደረጃን ስትይዝ ለዚህም በዋነኝነት እንደማሳያ የቀረበው ፍትሐዊና ነፃ የሆነ ምርጫን የማካሄድ አቅሟ በኔጋቲቭ (-11.1) የተመዘገበ መሆኑ ታይቷል፡፡ በሴቶች ላይ በሚደርስ አድልኦና ጥቃትም አገሪቱ ኔጋቲቭ (-25.00) ያስመዘገበች መሆኑ ተገልጿል፡፡

የሪፖርቱን ይፋ መሆን ተከትሎ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ከተዘገቡት ጉዳዮች መካከል ኢትዮጵያን ያካተተው የቀዳሚዎቹ አሥር አገሮች ዝርዝር፣ በአፍሪካ መፃኢ ዕድል ከፍተኛ ሚና የሚኖራቸው አገሮች መኖራቸው ነው፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያ በብሔራዊ ደኅንነት፣ በመረጃ ነፃነት፣ በማኅበራዊ አለመረጋጋትና መንግሥትን ያማከለ ግጭቶችን የመፍታት፣ የሥልጣን ሽግግርና የሙስና ወንጀልን ከመከላከሉ ጋር በተያያዘ እየታየ ያለው መሻሻል እንደሆነ ሜይል ኤንድ ጋርዲያን አፍሪካ የተሰኘ ድረ ገጽ አስፍሯል፡፡ ኢትዮጵያ ይፋ በሆነው አዲሱ ሪፖርት በአጠቃላይ ውጤት በ31ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧ ብዙ የሚጠብቃት የቤት ሥራ እንዳለ የሚጠቁም መሆኑን፣ ከላይ በተጠቀሱት ዋና ዋና የመሻሻል ዕርምጃዎች ታግዛ ደረጃዋን ልታሻሽል እንደምትችልም ግምት መኖሩ ተጠቁሟል፡፡ እንደ አገር ምዕራብ አፍሪካዊቷ ኮትዲቯር እጅግ በጣም መሻሻልን ያሳየች አገር ሆና ስትገኝ፣ በአንፃሩ ወጣቷ ደቡብ ሱዳን በከፍተኛ ዝቅጠት የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች፡፡   

የሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን በሱዳናዊ ብሪታኒያዊ ቢሊየነር ዶ/ር ሞሐመድ ኢብራሒም የተመሠረተ ሲሆን፣ በአፍሪካ በመልካም አስተዳደርና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ምርምር የሚያደርግና የተለያዩ ስኬታማ የሥራ ውጤቶችን የሚደግፍ ድርጅት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2006 ጀምሮ በዚህ ሥራ ላይ ሲገኝ መቀመጫውም ለንደን ነው፡፡ 

 

የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ ትምህርት ሚኒስቴር አንድ ሺሕ ሞተር ብስክሌቶችን ለመግዛት ያወጣውን ጨረታ አገደ፡፡ ኤጀንሲው ጨረታውን ያገደው መስከረም 18 ቀን 2008 ዓ.ም.

ለትምህርት ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡ ጨረታው የታገደው በጨረታው ተሳታፊ የሆነው አግታ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት በማግኘቱ ነው፡፡

አግታ መስከረም 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ለመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ቅሬታውን በደብዳቤ አቅርቧል፡፡ አግታ ባቀረበው አቤቱታ ትምህርት ሚኒስቴር የመንግሥትን የግዥ አዋጅ በተፃረረ መልኩ ከፍተኛ ዋጋ ላቀረበ ኩባንያ ሥራው መሰጠቱን ተቃውሟል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር ከሰባት ወራት በፊት አንድ ሺሕ ሞተር ብስክሌቶች ግዥ ለመፈጸም ጨረታ አውጥቶ ነበር፡፡ በጨረታው አራት ኩባንያዎች ቢሳተፉም፣ አንዱ ኩባንያ በቴክኒክ ምክንያት ወዲያውኑ ከጨረታ ውጪ ተደርጓል፡፡ የተቀሩት አግታ፣ ሐግቤስና በላይ አብ ሞተር ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ 

አንድ ሺሕ ሞተር ብስክሌቶች ለማቅረብ አግታ 37 ሚሊዮን ብር ሲያቀርብ፣ ሐግቤስ ኩባንያ ደግሞ ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ አቅርቧል፡፡ የአግታ ኩባንያ ቅሬታ ከዚህ የመነጨ ሲሆን፣ ተመሳሳይ ሞተር ብስክሌቶች ለማቅረብ 13 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው መወዳደርያ ገንዘብ ያቀረበ ኩባንያ አሸናፊ መደረጉ አግባብ አይደለም፣ የመንግሥትን የግዥ ሥርዓት ይፃረራል በማለት የአግታ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግርማይ  ወልደአረጋይ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

“መንግሥትና ሕዝብን ሊከሳራና ለሕገወጥ ወጪ የሚዳርግና ፍትሐዊ የንግድ ውድድር እንዳይኖር ያደርጋል፤” በማለት የትምህርት ሚኒስቴር የግዥ ሒደት ሕገወጥ መሆኑን አቶ ግርማይ ተናግረዋል፡፡ 

የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የአግታን አቤቱታ በመቀበል ለትምህርት ሚኒስቴር ጨረታውን እንዲያቆም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 75 ንዑስ አንቀጽ 1 የግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ፣ አቤቱታ ሲቀርብለት፣ ወዲያውኑ አግባብ ላለው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ማስታወቂያ ይልካል፡፡ ቦርዱ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስም ማናቸውም ቀጣይ እንቅስቃሴ ወዲያውኑ መቆም እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ 

በዚህ መሠረት የጨረታ ሒደቱ የታገደ ሲሆን፣ በአዲሱ አጠራር በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለማየሁ ጉጆ የሚመራው የግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ፣ የመጨረሻ ምላሽ እስኪሰጥ ድረስ ጨረታው በእግድ ይቆያል፡፡

ኤጀንሲው ለትምህርት ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ ዕገዳ ከማስተላለፍ በተጨማሪ፣ የጨረታ ሒደቱ ሙሉ መረጃና ቃለ ጉባዔ እንዲላክለት ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ 

የትምህርት ሚኒስቴር የግዥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገብረየሱስ ገብረ ሚካኤል በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ 

 

ጤፍን ጨምሮ ነባር ዝርያዎች አደጋ እንደተጋረጠባቸው በጥናት ተረጋገጠ

ዝርያዎችን ለመታደግ አገር አቀፍ ፓኬጅ ተዘጋጅቷል

ጤፍን ጨምሮ በአርሶ አደሩ ዕጅ የሚገኙት የስንዴ፣ የገብስ፣ የዳጉሳና የሌሎች አዝርዕት ነባር ዝርያዎች አደጋ ተጋርጦባቸዋል ተባለ፡፡ ከተሻሻሉ ዝርያዎች አኳያ ያላቸውን የተሻለ ምርታማነት ከግምት ባለማስገባት በተሻሻሉና በድብልቅ

ዝርያዎች ለመተካት በሚደረገው ሙከራ ሳቢያ፣ የነባሮቹ ዝርያዎች ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን በጥናት መረጋገጡን፣ የኢትዮጵያና የዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት ተቋማት ገልጸዋል፡፡

በተለይ በጤፍና በስንዴ ላይ በተደረጉ ጥናቶች በተፈጥሮ ይዞታቸው የሚታወቁት ነባር የአርሶ አደሩ ዝርያዎች፣ በሳይንሳዊ መንገድ ተዳቅለው ‹‹የተሻሻለ ዝርያ›› ተብለው የሚሰራጩት በምርታማነታቸውና በተስማሚነታቸው ውጤታማ መሆናቸውን የሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች መስከረም 20 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስረድተዋል፡፡

በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ገመዶ ዳቤ፣ ‹‹በተደጋጋሚ እንደሚነሳው የእኛ ያልሆኑ ዝርያዎች ምርታማ አይደሉም ሲባል ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ከዓለም አቀፉ የብዝኃ ሕይወት ተቋም ጋር በጋራና በተናጠል ባደረግናቸው ጥናቶች ለአገር በቀል ዝርያዎች የተሰጠው ግምት የተሳሳተ እንደሆነ ከመረጋገጡም ባሻገር፣ በዘመናዊና በሳይንሳዊ መንገድ ተሻሽለው ተዘጋጁ ከሚባሉት የተሻለ ምርታማነት እንዳላቸው ተረጋግጧል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም፣ ‹‹በእጃችን ያለውን እምቅ ኃይል ሳንጠቀም ከውጭ በመጡ ዝርያዎች ላይ ትኩረት ለማድረግ በመሞከራችን የራሳችንን አገር በቀል ዝርያዎች አደጋ ውስጥ እየጣልናቸው ነው፤›› በማለት ሥጋታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተቋሙ ተባባሪ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ፋንታሁን ባሳዝነው በበኩላቸው፣ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ጤፍን ለዓለም ያበረከተችና ጤፍም ከ4,000 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ታሪክ ቢኖረውም፣ በአገሪቱ ከስንዴና ከገብስ በፊት ምርምር ማድረግ ቢጀመርም፣ በአሁኑ ወቅት በተሻሻሉ ዝርያዎችና በሌሎችም ምክንያት ጤፍ አደጋ ተደቅኖበታል በማለት፣ ወደፊት ሊጠፋ ይችላል የሚለውን ሥጋት አጠናክረዋል፡፡

‹‹ይህ ዝርያ (ነባሩ ጤፍ) ከባህር ወለል በታች ከ3,000 እስከ 1,500 ሜትር ከፍ ሲልም እስከ 1,700 ሜትር፣ በአገራችን መመረት ይችላል፡፡ እንዲሁም በአገራችን አርሶ አደሮች ዕጅ ያለው የጤፍ ዝርያ በምርታማነቱ የበላይነት ከፍ ያለ ቢሆንም፣ አሁን አሁን ግን በተሻሻሉ ዝርያዎችና በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ነባር ዝርያዎች ከፍተኛ አደጋ መጥቶባቸዋል፤›› በማለት ተባባሪ ተመራማሪው አስጠንቅቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ከ5,900 በላይ የጤፍ ዝርያ ናሙናዎች ተሰብስበው በኢትዮጵያ ዘረመል ባንክ ውስጥ እየተጠበቁ ሲሆን፣ በዚህ ሰብል ዝርያ ላይ የሚደረገው ናሙና የማሰባሰብና የባህርይ ትንተና ሥራ በግብርና ሳይንስ ምርምር ከ1950ዎቹ መጨረሻ አንስቶ ነበር የተጀመረው፡፡

እንደ ኃላፊዎቹ ከሆነ የባህርይ ትንተና አካል የሆነው ምርምር በ2006 እና በ2007 ዓ.ም. ተካሄዶ ነበር፡፡ ምርምሩም 12 የአርሶ አደር ዝርያዎችና ቁንጮ ተብሎ የሚታወቀውን ጤፍ ጨምሮ ሦስት አዳዲስ ዝርያዎችን (የተሻሻሉ ዝርያዎች) ያካተተ ሲሆን፣ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳና በሌሎች አራት ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የአርሶ አደር ማዕከላት ውስጥ የምርምር ሥራዎች መከናወናቸው ተነግሯል፡፡

በምርምር ሥራው የተገኙትን ውጤቶች ይፋ ያደረጉት አቶ ፋንታሁን፣ ‹‹ለማወዳደሪያነት በተረመጡት የተሻሻሉ ዝርያዎችና በአርሶ አደር ዝርያዎች መካከል መመዘኛ በተደረጉት ከመድረሻ ቀን፣ ከእህል ምርት፣ ከቁመት፣ ከዛላ እርዝመት አንፃር ሲታይ በስታትስቲክሳዊ ሥሌት መሠረት ልዩነት እንደሌላቸው ታይቷል፤›› ብለዋል፡፡

ምንም እንኳ የተለቀቁት የተሻሻሉ ዝርያዎች የተሻለ የምርት መጠን እንደሚኖራቸው በስፋት የሚታመን ቢሆንም፣ በተጠቀሱት የናሙና ውጤቶችና በስታትስቲክሳዊ ሥሌቶች መሠረት የአርሶ አደሩ ነባር ዝርያዎች የተሻለ ምርት እንደሚሰጡ መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡

ለአብነት ያህል ቁንጮ በሚባለው የተሻሻለ የጤፍ ዝርያና በነባሩ ዝርያ ላይ በአራት አካባቢዎች በተካሄደ ጥናት መሠረት፣ ነባሩ ዝርያ በሔክታር 22 ኩንታል ምርት ሲሰጥ ቁንጮ ግን 21 ኩንታል ብቻ መስጠቱን በአስረጅነት ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ጤፍ ሁሉ በሌሎችም የአዝርዕት ዓይነቶች ላይ ተመሳሳይ ውጤት መታየቱን የሚገልጹት የተቋሙ ተመራማሪዎችና ኃላፊዎች፣ አገር በቀል ዝርያዎች ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸውና የተለየ የአመራረት ፓኬጅም ተግባራዊ መደረግ እንደለበት አሳስበዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የብዝኃ ሕይወት ተቋም በበኩሉ በአማራና በትግራይ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ሥፍራዎች በስንዴና በዳጉሳ ላይ ባካሄዳቸው የናሙና ጥናቶች፣ ከውጭ ከሚገቡትም ሆነ ከተዳቀሉት የተሻሻሉ ዝርያዎች አኳያ በሚሰጡት የምርት መጠንና በጥራት አገር በቀሎቹ ነባር ዝርያዎች የተሻሉ መሆናቸውን ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል፡፡

በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ብዝኃ ሕይወት ተቋም ተጠሪ ካርሎ ፋዳ፣ ስኮላ ሳንታ አና ከተባለው የጣሊያን ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥምር በተካሄደ ጥናት፣ በአርሶ አደሩ ዕጅ የሚገኙትና ለማካሮኒና ለፓስታ ማምረቻ የሚያገለግሉ ስንዴዎች (ዱረም) በተፈጥሮ ካላቸው የዝርያ ተያያዥነትም ሆነ ዘረመል አወቃቀር አንፃር፣ ለገበሬው ከተሰራጩ የተሻሻሉ ዝርያዎች (Mediterranean Group)  ከሚባሉት በእጅጉ የተሻለ ምርታማነት እንደሚታይባቸው አስረድተዋል፡፡ 

አደጋ ተደቅኖባቸዋል የተባሉ ዝርያዎችንና ሌሎች በይፋ ያልተለዩ አገር በቀል ዝርያዎችን በተሻለ መንገድ ለመጠቀምና ‹‹ከመዋጥ ሥጋት›› ለማዳን፣ የተለየ ፓኬጅ  በመዘጋጀቱ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ዋና ዳይሬክተሩ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

ረዘም ላሉ ዓመታት ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በተያያዘ መንግሥት ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ትኩረት መስጠቱን፣ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ በተለይ ለምርትና ለምርታማነት ዕድገት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሰ መሆኑን የሚገልጸው መንግሥት፣ በግብርና ምርምር አቅምና በቴክኖሎጂ መስክ ዕድገት እየተመዘገበ መምጣቱን ደጋግሞ ሲናገር መቆየቱ ይታወሳል፡፡ የምርምር ማዕከላትን በመላ አገሪቱ እየተስፋፉ በመምጣታቸው በተሻሻሉ ዝርያዎች የተሻለ ውጤትና ተስፋ እየታየ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የአሁኑ የጥናት ውጤት ግን ጥያቄን አጭሯል፡፡ በተለይ ባለፉት ዓመታት መንግሥት የግብርና ምርምር ተቋማት እንዲስፋፉና የነባሮችንም አቅም በማሳደግ በግብርና ምርት ዕድገት መታየቱን ይገልጻል፡፡ ነገር ግን በዘርፉ የተሰማሩ ተመራማሪዎች፣ የእስከዛሬው ጥረት አሁን ይፋ ከወጣው የጥናት ውጤት አኳያ ሲታይ የቀድሞዎቹ ኢንቨስትመንቶችና ጥረቶች ተገቢነት ላይ ትልቅ ጥርጣሬ ያሳደረ መሆኑን እየተናገሩ ነው፡፡