–ባለሥልጣኑ በጣቢያውና በኢትዮፒካሊንክ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ውድቅ ተደርጓል የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በዛሚ 90.7 ኤፍኤም ራዲዮ ጣቢያ በሚተላለፈው ኢትዮፒካሊንክ ፕሮግራም ላይ የቀረበን አቤቱታ ምክንያት በማድረግ ሰኔ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሬዲዮ ጣቢያው የጻፈው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያና ኢትዮፒካሊንክ የተባለው ፕሮግራም ላይ የሰጠው ዕግድ …

ብሮድካስት ባለሥልጣንና ዛሚ ራዲዮ የፈጠሩት ውዝግብ በባለሥልጣኑ ቦርድ ውሳኔ ተፈታ Read more »

የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን (ኢትዮ ቴሌኮም) ዋና መሥሪያ ቤት ዋና መሐንዲስና የደቡብ ምሥራቅ ሪጅን ሁለት ሥራ አስኪያጆች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው፣ ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 18ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች፣ የዋናው መሥሪያ ቤት ዋና መሐንዲስ የነበሩት አቶ ተክለ ማርያም ለአከ ተክለ ማርያም፣ የኮርፖሬሽኑ የደቡብ ምሥራቅ ሪጅን ምክትል ሥራ አስኪያጅና የማርኬቲንግ ኃላፊ የነበሩት አቶ መስፍን ሙርጋና የደቡብ ምሥራቅ ሪጅን ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ጌታቸው ተረፈ አየለ ሲሆኑ፣ በግል ሥራ የተሰማሩ አቶ ግርማ ተስፋዬ የተባሉ ግለሰብም በክሱ ተካተዋል፡፡ 

ተከሳሾቹ የማይገባ ጥቅም ለማግኘትና ለሌላ ሦስተኛ ወገን ጥቅም ለማስገኘት በማሰብ፣ በሕዝብና በመንግሥት ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡ ክሱ እንደሚያስረዳው፣ አቶ ተክለ ማርያም ያላቸውን የቴክኖሎጂ ዕውቀት፣ ልምድና ክፍተት በመጠቀም በግል ሥራ ከሚተዳደሩት አቶ ግርማ ጋር ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ (ናዝሬት) ይሄዳሉ፡፡ አዳማ እንደደረሱ ለሕገወጥ ዓላማ ማስፈጸማያ የሚውል ቤት በደላላ አማካይነት አቶ ታደሰ ጅማ ከሚባሉ ግለሰብ ይከራያሉ፡፡ የቤቱን ውል ከመፈጸማቸው በፊት ቤት አከራዩ አቶ ታደሰ ጂማ 30 ቀጥታ የስልክ መስመሮችን ከቴሌ ማስገባት እንዳለባቸው ይስማማሉ፡፡ አቶ ተክለ ማርያም አብረዋቸው የሚሠሩ የውጭ አገር ዜጎች እንዳሉም ለአከራዩ አቶ ታደሰ እንደነገሯቸው ክሱ ያብራራል፡፡ 

ከውጭ አገር የሚመጡት ኢንቨስተሮች በመሆናቸው ለስልኩ ወጪ ክፍያ ምንም ሥጋት እንዳይገባቸው ለአቶ ታደሰ ተነግሯቸው፣ የስልክ መስመሮቹ ከገቡ በኋላ ኅዳር 21 ቀን 1995 ዓ.ም. በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት ሁለተኛ ተከሳሹ አቶ ግርማ ተስፋዬና አቶ ታደሰ የቤት ኪራይ ውሉን መፈጸማቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ አቶ ተክለ ማርያም ሳተላይት መቀበያ መሆኑን እያወቁ ከአቶ ግርማ ጋር በመመሳጠር በተከራዩበት ቤት ዲሽ በመትከል፣ አገሪቱ ከዘርፉ ልታገኝ የሚገባትን ገቢ እንድታጣ በማድረግ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ መሞከራቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ 

አቶ ግርማ የተባሉት ተከሳሽ ቤት አከራዩን አቶ ታደሰን በዜግነት ጥቁር አሜሪካዊ እንደሆኑ በመግለጽ ከተዋወቋቸው በኋላ፣ አብረዋቸው ከነበረ ኤም ዴቪድ ከሚባል ነጭ አሜሪካዊ ጋር ያስተዋውቋቸዋል፡፡ ወደ ተከራዩት ቤት በመውሰድ በአከራይ ተከራይ ውል ላይ ካስፈረሟቸው በኋላ፣ ስልክ ላስገቡበት 16,500 ብር ለቴሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እንደከፈላቸው ክሱ ይገልጻል፡፡ 

ለሕገወጥ ድርጊት የሚውሉ ዘመኑ ያፈራቸውን ዕቃዎች በኤርፖርት ታክሲ ጭነው አዳማ በመውሰድ፣ በታኅሳስ ወር 1995 ዓ.ም. ዲሹን መትከላቸውንም ክሱ አክሏል፡፡ በመሆኑም በወንጀሉ በመሳተፍ በሕዝብና በመንግሥት ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ መሞከራቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡ 

የቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅና የማርኬቲንግ ኃላፊ የነበሩት አቶ መስፍን ሙርጋም፣ ቤት ያከራዩት አቶ ታደሰ 30 ቀጥታ መስመር እንዲገባላቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ተረፈ ማኅተም ሳያደርጉ የመሩትን ደብዳቤ ‹‹ለምን?›› ብለው ምክንያቱን ሳያረጋግጡ የቀረበውን ጥያቄ በማፅደቃቸው፣ በሕዝብና በመንግሥት ጥቅም ላይ ጉዳት ለማድረስ መሞከራቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ አቶ ጌታቸውም ኮርፖሬሽኑ ያወጣውን የደንበኞች አገልግሎት አፈጻጸም መመርያ በመጣስ፣ ስልኮቹ ለምን ዓላማ እንደሚውሉ ሳይጠይቁና ሳያጣሩ በተዋረድ ላሉ ኃላፊዎች በመምራትና በማፅደቃቸው፣ በሕዝብና መንግሥት ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስና አላግባብ ሥልጣንን መገልገል ወንጀል እንደተከሰሱ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ 

ሁሉም ተጠርጣሪዎች በሕዝብና በመንግሥት ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ በግብረ አበርነት በፈጸሙት ሥልጣንን ያላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በሌሉበት ስለተከሰሱ፣ ኮሚሽኑ ተከሳሾቹን አፈላልጎ ለሐምሌ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. እንዲያቀርብ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 18ኛ ወንጀል ችሎት አዟል፡፡ 

 

በታኅሳስ ወር 2007 ዓ.ም. ኢትዮ ቴሌኮም ኤሪክሰን ለተባለው የስዊድን ኩባንያ ሰጥቶ ከነበረው የቴሌኮም ማስፋፊያ አራት ፕሮጀክቶች መካከል፣ መዘግየት አይቼበታለሁ ያለውን የአንዱን ፕሮጀክት (ሰርክል) ውሉን ሰርዞ ሁዋዌ ለተባለው የቻይና ቴሌኮም ኩባንያ መስጠቱን አስታወቀ፡፡ 

ኤሪክሰን ከማስፋፊያ ፕሮጀክቶች መካከል አራት ‹ሰርክሎች›ን ለመሥራት ተዋውሎ የነበረ ቢሆንም፣ በተለይ ደቡብ ደቡብ ተብሎ በተለየው የማስፋፊያ ፕሮጀክት አንዱን ‹ሰርክል› በውሉ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ማጠናቀቅ ባለመቻሉ መነጠቁን፣ የኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ አብዱራሒም አህመድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

አቶ አብዱራሒም ለሁዋዌ በቀጥታ የተሰጠውን ፕሮጀክት አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ሁዋዌ ከዚህ በፊት የወሰዳቸውን ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በተሻለ አፈጻጸም ተግባራዊ ማድረግ በመቻሉ ከኤሪክሰን ተነጥቆ የተሰጠው መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡ 

‹‹ሁዋዌ በአዲስ አበባ ያከናወናቸውን የማስፋፊያ ሥራዎች ከውሉ ቀድሞ መጨረስ በመቻሉ፣ በቀጥታ እንዲሰጠው ተወስኗል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

የኤሪክሰን ፕሮጀክትን አስመልክተው አቶ አብዱራሒም ሲገልጹ፣ ፕሮጀክቱ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ አጠናቆ ማስረከብ ባለመቻሉ፣ የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አካል የነበረውን የቴሌኮም ማስፋፊያ ሥራ ማጓተቱን ጠቁመዋል፡፡ 

‹‹ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ሁዋዌ ስድስት ‹ሰርክሎች›ን እያከናወነ ሲሆን፣ በእስካሁን አፈጻጸሙ በጣም አመርቂ የሚባል ውጤት እያየንበት ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ እነዚህም የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች የሰሜን፣ የሰሜን ምሥራቅ፣ የሰሜን ምዕራብ፣ የምሥራቅና የአፋር ቀጣናዎች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በመላ አገሪቱ የሞባይል አገልግሎት ኔትወርክ ተደራሽነትን  ለማስፋፋት ባወጣው ጨረታ፣ ሁለቱ የቻይና ኩባንያዎች ሁዋዌና ዜድቲኢ ያሸነፉ ቢሆንም፣ ዜድቲኢ በስምምነቱ መሠረት እንቅስቃሴ ባለመጀመሩ ከወሰዳቸው ስድስት የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች አራቱ ለስዊድኑ ኤሪክሰን የቴሌኮም ኩባንያ መተላለፋቸው  በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ታኅሳስ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ኢትዮ ቴሌኮምና ኤሪክሰን ባደረጉት የቬንደር ፋይናንሲንግ ፕሮጀክት ማስፋፊያ ስምምነት፣ የቻይናው ዜድቲኢ ቴሌኮም ኩባንያ ከአገሩ አቻው ሁዋዌ ቴሌኮም ኩባንያ ጋር ከተካፈለው የ800 ሚሊዮን ዶላር የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ውስጥ፣ አራቱ ለኤሪክሰን መሰጠታቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

ዜድቲኢና ሁዋዌ በመላው ኢትዮጵያ ያሉትን 13 ‹ሰርክሎች› ወይም የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ሲካፈሉ፣ ሁዋዌ አዲስ አበባን ጨምሮ ሰባት ‹ሰርክሎች›ን ሲወስድ ዜድቲኢ ስድስት ‹ሰርክሎች›ን ለመሥራት መዋዋሉ ይታወሳል፡፡

 

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ማውጫ ጊዜ ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉ ተጠቆመ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. 40/60ን ጨምሮ 40 ሺሕ የሚሆኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ዕጣ እንደሚያወጣ የገለጸ ቢሆንም፣ የዕጣ ማውጫውን ቀን ላልተወሰነ ጊዜ ማስተላለፉ ተጠቆመ፡፡ 

ዕጣ ይወጣላቸዋል ከተባሉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተለይ ለመጀመሪያ ጊዜ በዕጣ ይከፋፈላል የተባለው 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት፣ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት አለፍ ብሎ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊትና ሰንጋ ተራ የሚገኙት ሕንፃዎች ግንባታ የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ አብረው መጠናቀቅ የነበረባቸው መሠረተ ልማቶች ባለመጠናቀቃቸው የዕጣ መውጫው ጊዜ እንዲራዘም መደረጉን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

የአስተዳደሩ ካቢኔና ቦርድ ተሰብስቦ ውሳኔ አለማሳለፉም ለዕጣው አለመውጣት ሌላው ምክንያት መሆኑን የጠቆሙት ምንጮች፣ የአስተዳደሩ ከፍተኛ ሹማምንት በሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ሳይቀር ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚተላለፉ ቤቶች እንዳሉ ሲገለጽ ከርሞ፣ ቃላቸው አለመጠበቁ ‹‹ለምን?›› የሚል ጥያቄ እያስነሳ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የመሠረተ ልማት አለመሟላት እንደ ምክንያት ሊወሰድ እንደማይችል የሚናገሩት ምንጮች፣ በአሥረኛው ዙር ዕጣ ከወጣባቸው 35 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል የአብዛኞቹ ሳይቶች መሠረተ ልማታቸው ገና ያልተጀመረ በመሆኑ ነው፡፡ 

ለሪፖርተር አስተያየት የሰጡ የተወሰኑ የ40/60 ተመዝጋቢዎች፣ ሙሉ በሙሉ ክፍያ የፈጸሙ ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ገልጸው፣ አሁን ግን ዋጋው በጣም ሊጨምር ስለሚችል ሙሉ በሙሉ የከፈሉም ቢሆኑ ተጨማሪ ክፍያ እንደሚጠየቁ መስማታቸው አሳስቧቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ሁሉም በዕጣው ተካተው ዕድለኞች በዕጣ እንደሚያገኙ፣ የቤቶቹን መገንባት ያዩ ሌሎች ተመዝጋቢዎች በመሀል ሙሉ በሙሉ መክፈላቸውም ስላሳወቁ፣ ሲጀመር አጠናቀው ከከፈሉት ጋር ሊቀላቀሉ መሆኑንና ሌሎች ወሬዎችን እየሰሙ ግራ መጋባታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተባለው ጊዜም ዕጣ አለመውጣቱ እንዳሳሰባቸው ይናገራሉ፡፡

የ20/80 ተመዝጋቢዎች በበኩላቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ዕጣው ሰኔ 30 እና እስከ ነሐሴ መጨረሻ ድረስ ወጥቶ ዕድለኞች የቤት ባለቤት እንደሚሆኑ የተነገረበት ወቅት የምርጫ ጊዜ በመሆኑ፣ ሕዝቡን ለመያዝ ነው የሚል ግምታቸውን ዕውን እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ዕጣው በተባለው ጊዜ መውጣት ነበረበት ሲሉም ይከራከራሉ፡፡ 

ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ዕጣ እንደሚወጣ በአስተዳደሩ ከፍተኛ ሹሞች ከገለጹ በኋላ ለምን ዕጣውን እንዳላወጡ ወይም ያልወጣበትን ምክንያት እንዲገልጹ፣ የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትንም ሆነ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ 

ነገር ግን አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ባልደረባ እንደሚሉት፣ ዕጣው ያልወጣው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው የአስተዳደሩ ካቢኔና ቦርድ ተሰብስቦ ውሳኔ ባለማስተላለፉ ሲሆን፣ ሌላው በታሰበበት ወቅት ይጠናቀቃሉ የተባሉ መሠረተ ልማቶች ባለመጠናቀቃቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዋናነት የ40/60 የቤት ፕሮግራም የመጀመሪያ ከመሆኑ አንፃር ሁሉም ነገር ተጠናቆ፣ ዕጣው በወጣበት ዕለት ለባለዕድለኞች ወዲያውኑ ቁልፍ ለማስረከብ በመታሰቡ መሆኑን አክለዋል፡፡

   

 

በአልሸባብ ተመልምለው የሕዋስ (ሴል) አባላት ናቸው የተባሉ ኢትዮጵያ ውስጥ በተመረጡ ቦታዎችና በመንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ የተባሉ አምስት ተጠርጣሪዎች፣ ኢትዮጵያውያን፣ ሐምሌ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1/ሀ)ን በመተላለፍ በዋና ወንጀል ተካፋይ በመሆን፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 38 (1 እና 2) በመተላለፍ ወንጀል ለመፈጸም አድማ በማድረግና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (4)ን በመተላለፍ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም የማቀድ፣ የመዘጋጀት፣ የማሴርና የማነሳሳት ሙከራ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል ብሎ ክስ የመሠረተባቸው፣ በድሪ የሱፍ ሮባ፣ አነስ ኡስማን ዑመር፣ አህመድ ኑር ሳኒ፣ መሐመድ አህመድ ኡስማንና እስማኤል አደም መሐመድ ናቸው፡፡

ዓቃቤ ሕግ ለፌዴል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ 

ተከሳሾቹ ከአልሸባብ ጋር በመስማማትና አባል በመሆን ከሶማሊያ ግዛት ወደ ኢትዮጵያ የሚላኩ ተቀጣጣይ ፈንጂዎች መሥራት የሚችሉ የአልሸባብ የፈንጂ ሥራ ባለሙያዎችን ለመቀበል፣ ለፈንጂ መሥሪያ የሚሆን ቤት ለመከራየት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ክሱ ያስረዳል፡፡

በድሪ የሱፍ ሮባ የተባለው ተጠርጣሪ በሽር ቱሬ በሚባል የአልሸባብ አመራር በ1999 ዓ.ም. በአባልነት ከተመለመለ በኋላ፣ ሞቃዲሾ ውስጥ በሚገኘው አቡሐረሬ ተብሎ በሚጠራው መስጊድ ውስጥ ለስድስት ወራት ወታደራዊና የፖለቲካ ትምህርት ሥልጠና መውሰዱን ክሱ ያስረዳል፡፡ ተጠርጣሪው በ2002 ዓ.ም. ወደ መቋዲሾ በመሄድ ለአልሸባብ አባል የሚሆኑ ወጣቶችን በመመልመል ለሥልጠና እዚያ እንዲሄዱ ሲያዘጋጅ እንደነበርም በክሱ ተጠቁሟል፡፡ 

ግለሰቡ ጥቃት ለመፈጸም ከሞቃዲሾ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት የሚመጡትን የህዋስ አባላት መኖሪያ ቤት ተከራይቶ ለማስቀመጥ፣ የተመለሱትን ወጣቶች በኃላፊነት ለመምራት፣ መረጃ እየሰበሰበ ለአልሸባብ አባላት እንዲልክ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም ሲንቀሳቀስ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡

አብዱልአዚዝ አልዩ (አቡ ያሲን) የተባለ የአልሸባብ አመራርና የፈንጂ ባለሙያ በ2006 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ገብቶ ባሌ ሮቤ ከተማ ውስጥ መልምሎ በህዋስ ያራጃቸውን ስድስት አባላት፣ አንደኛ ተከሳሽ እንዲመራቸው ኃላፊነት መውሰዱንም ክሱ ያስረዳል፡፡

ሻሸመኔ ከተማ ውስጥ ‹‹ቁርዓን አስተምራለሁ ወይም የቁርዓን መምህር ነኝ›› በሚል ሽፋን አባላትን መመልመልና ማደራጀት እንዳለበት በሽር ቱሬ ከሚባለው የአልሸባብ አመራር ተልዕኮ መቀበሉንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡ አገር ውስጥ ባሉ የተለያዩ ባንኮችም ገንዘብ ይላክላቸው እንደነበር የገንዘቡን መጠንና የባንኮቹን ስም ጠቅሶ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አካቷል፡፡

በኅዳር ወር 2007 ዓ.ም. በጊኒር በኩል ወደ ኢትዮጵያ ይገባል ለተባለው የአልሸባብ አመራር አብዱላዚዝ፣ በነገሌ ቦረና በኩል በታኅሳስ ወር 2007 ዓ.ም. ፈንጂ ይዘው የሚገቡትን አባላት አንደኛ ተከሳሽ ሻሸመኔ በሚገኘው ቤቱ አሳርፏቸው ፈንጂ የሚሠራበትን ማቴሪያል እንዲያዘጋጅና የማፈንጃ ዒላማዎችን እንዲያጠና ተልዕኮ ተቀብሎ ይንቀሳስ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ሻሸመኔ፣ አሰላና ባሌ ሮቤ ከተሞች ውስጥ ባንክ ቤትና ፖስታ ቤት መኖር አለመኖሩን አጥንቶ እንዲቆይም ትዕዛዝ ተሰጥቶት እንደነበር አክሏል፡፡ ተጠርጣሪው የሽብር ቡድኑ አደራጅና አመራር በመሆን ተሳታፊ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር ገልጿል፡፡ 

ሁለተኛው ተጠርጣሪ ተከሳሽ አነሰ ኡስማንም እንደ አንደኛ ተከሳሽ በተለይ ባሌ ዞን ሮቤ ከተማ ውስጥ በመንቀሳቀስ አባላት በመመልመል፣ በተለይም አራተኛና አምስተኛ ተከሳሾችን መልምሎ ወደ ሶማሊያ ሥልጠና ሊልክ ሲል በቁጥጥር ሥር መዋሉን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ ሦስተኛ፣ አራተኛና አምስተኛ ተከሳችም በሁለተኛ ተከሳሽ ከተመለመሉ በኋላ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠና ለመውሰድ ወደ ሶማሊያ ለመሄድ በመንቀሳቀስ ላይ እያሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው በክሱ ተገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ ክሱ በችሎት ከተነበበላቸው በኋላ በራሳቸው ጠበቃ ማቆም እንደማይችሉ በመግለጻቸው፣ የተከላካይ ጠበቃ ጽሕፈት ቤት ጠበቃ እንዲመደብላቸው ትዕዛዝ በመስጠት ፍርድ ቤቱ ለሐምሌ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተከናወነው አምስተኛውን ዙር ጠቅላላ ምርጫ በኋላ፣ በአባላት፣ በአመራሮችና በምርጫ አስፈጻሚ ግለሰቦች ላይ በተጠናከረ ሁኔታ እየደረሰ ያለውን ወከባ፣ እስራትና ግድያን በተመለከተ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት፣ በጉዳቱ ላይ ቁርጠኛ ውሳኔ ለመስጠት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ …

መድረክ የአባላቱ እስራትና ሞት ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታወቀ Read more »

ቄራዎች ድርጅት በልኳንዳ ነጋዴዎች ምክንያት አገልግሎቱ መስተጓጎሉን አስታወቀ

የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ ጠየቀ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቄራዎች ድርጅት የዘንድሮው ሰኔ ፆም ሲፈታ አንድ ቀን ሲቀረው በልኳንዳ ነጋዴዎች ምክንያት አገልግሎቱ እንደተስተጓጎለበት አስታወቀ፡፡

ለ2,800 እንስሳት የዕርድ አገልግሎት ለመስጠት አቅዶ እንደነበር፣ ለእርድ አገልግሎት የቀረቡት ግን 900 እንስሳት ብቻ እንደሆኑ፣ ይህም ለሕገወጦች በር መክፈቱንና መንግሥትም ከአገልግሎቱ ማግኘት የሚገባውን ገቢ ማጣቱን  የድርጅቱ ዋና ሥራ አቶ ኤፍሬም ደሳለኝ አስኪያጅ አስታውቀዋል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ ይህንን የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በቁም እንስሳት ንግድ አዋጅ በከተማው ክልል ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ባዘጋጀው የተግባር ምዕራፍ ላይ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመወያየት ሐምሌ 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ላይ ነው፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ ይህ ዓይነቱ ድርጊት ገቢ በማሳጣት ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ኅብረተሰቡ ጤንነቱ ያልተመረመረ ሥጋ በመብላት ለተለያዩ በሽታዎች እንዲጋለጥ ማድረጉ መታወቅ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ 

ድርጅቱ ዕቅዱን ያላሳካው የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ከደረሰኝ ጋር በተያያዘ ችግር ሳቢያ እንስሳቱን ከመግዛት በመቆጠባቸው፣ በዚህም የተነሳ የንግድ ቤቶቻቸውን ዘግተው ለኅብረተሰቡ የሽያጭ አገልግሎት መስጠቱን እርግፍ አድርገው በመተዋቸውና በዚህም ምክንያት የሥጋ እጥረት በማስከተሉ ነው፡፡

 ከዚም በተጨማሪ ቄራዎች ድርጅት ለዕርድ አገልግሎት የ2,000 ብር ዋጋ ጭማሪ እንዳደረገ የተነዛው አሉባልታ፣ ለልኳንዳ ንግድ ቤቶች መዘጋትና ነጋዴዎቹም እንስሳቱን ላለመግዛት ለማንገራገራቸው ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቄራዎች ድርጅት ለዕርድ አገልግሎት የሚያስከፍለው በአንድ እንስሳ 230 ብር ብቻ እንደሆነ፣ ይህም የተመረተውን ሥጋ በተሽከርካሪ እስከ ልኳንዷ ቤቶች ድረስ የማጓጓዙንም ሥራ እንደሚያካትት፣ ከዚህ ውጪ ግን ምንም ዓይነት ጭማሪ እንዳላደረገ በመገናኛ ብዙኃን ጭምር ማስታወቃቸውን ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

‹‹ድርጅቱ አገልግሎቱን የሚሰጠው የንግድ ፈቃድ ላላቸው ብቻ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የተቋቋመው ጤናማነቱ የተረጋገጠ የዕርድ አገልግሎት ለከተማው ነዋሪዎች መስጠት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለተለያዩ ጉዳዮች ማለትም ሠርግ፣ ተዝካር፣ ወዘተ ላላቸው ወገኖች አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር እንዲቀጥል እናበረታታለን፡፡ ከክፍያ አንፃር ግን ከነጋዴው የተለየ ጭማሪ ሳይደረግ ነው የዕርድ አገልግሎቱን የሚያገኙት፤›› ብለዋል፡፡

በተረፈ ለድርጅቱም ደረሰኝ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው፣ በተለይ እንስሳት ከገበያ ወደ ቄራ በሚጓጓዙበት ጊዜ ሲሞት ካሳ የሚከፈልበት አሠራር እንዳለ፣ በዚህም የተነሳ ደረሰኝ ላይ የሚታወቅ ሁኔታ ካለ በዚያው ልክ እንደሚከፈል፣ ይህ ባለመሆኑ የተነሳ ግን አንዳንድ ጊዜ ከዋጋው በላይ እየተጠየቀ ድርጅቱን ላላስፈላጊ ወጪ እንደተዳረገ አልሸሸጉም፡፡

የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ሳህሌ ከደረሰኝ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ሁኔታ አስመልክተው እንዳብራሩት፣ የቁም እንስሳት ነጋዴዎች ባለፈው ሳምንት ማዘጋጃ ቤት አካባቢ ስብሰባ አድርገው ልኳንዳ ነጋዴዎች ለገዙት በሬ ደረሰኝ እንደማይፈልጉ፣ ምክንያቱ ደግሞ ያለደረሰኝ መሸጥ ስለሚፈልጉ ነው የሚል መረጃ በተባራሪ ልኳንዳ ነጋዴዎች ጆሮ ይደርሳል፡፡ 

ይህ ጉዳይ ተጋግሎ እየመጣ ረቡዕ ሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ደረሰኝ ካላገኙ ከብት እንደማይገዙ በልኳንዳ ነጋዴዎች ዘንድ ጎልቶ ታየ፡፡ በዚህም ብቻ ሳይወሰኑ የማኅበሩ ቢሮ ድረስ እየመጡ ‹የሠራችሁልን ነገር የለም፣ በመብታችን ትደራደራላችሁ፡፡ እንዲያውም ማኅበሩን እናፈርሳለን› የሚል አቋም እንደያዙ ነው ምክትል ሥራ አስኪያጁ የተናገሩት፡፡

በዚህም ምክንያት ልኳንዳ ነጋዴዎች ደረሰኝ ወይም ለሕጋዊነታቸው ማረጋገጫ ካላገኙ እንስሳት መግዛት አንችልም በማለት በራሳቸው መንገድ ንግድ ቤታቸውን እንደዘጉ፣ ማኅበሩም እስከ ፆም ፍቺው ዕለት ድረስ የማረጋጋት ሥራ ቢያከናውንም ሊሳካለት እንዳልቻለ አቶ አየለ ጠቅሰው፣ ‹‹በዚህም ምክንያት የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ለተፈጠረው ችግር የከተማይቱን ሕዝብ ይቅርታ ይጠይቃል፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አለባቸው ንጉሴ ‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ በተዘጋጀ ጉባዔ 5,000 የሚሆኑ እንግዶች እየተስተናገዱ ባሉበት፣ የሰኔ ፆመኞች ፆማቸውን ሲፈቱ የልኳንዳ ንግድ ቤቶችን መዝጋት በማንኛውም ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ሕገወጥ ተግባር ነው፡፡ ምንም ዓይነት ችግር ቢኖርም መዝጋቱ መፍትሔ አይሆንም፡፡ የታወቅንበት መቻቻል፣ ሰላምና ፍቅር ደፍርሶ ሌላ ነገር እንዲከስት ያደርጋል፤›› ብለዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ የቁም እንስሳት ነጋዴዎች ማኅበር ስብሰባ ስለማድረጋቸው ለቢሮው የደረሰ ምንም መረጃ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ በተረፈ በቁም እንስሳት የገበያ ማዕከላት ውስጥ በጉልበት የታጀበ ጣልቃ ገብነትንና ሕገወጥነትን እንዲቀር ለማድረግ እንታገላለን፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መተጋገዝ ያስፈልጋል ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡ 

 

ከአንድ ዓመት በፊት ሚያዝያ 26 እና 27 ቀን 2006 ዓ.ም. በድንገት ተይዘው ከታሰሩ በኋላ፣ በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ ተመሥርቶባቸውና የሰነድና የሰው ማስረጃ ቀርቦባቸው፣ ለብይን የተቀጠሩበትን ቀን እየተጠባበቁ ከነበሩት አሥር ተከሳሾች መካከል አምስቱ በድንገት ሐምሌ 1 እና 2 ቀን 2007 ዓ.ም. መፈታታቸው እያነገጋገረ ነው፡፡

Ali Sirajየኢፌዲሪ ንግድ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል በመሆን እያገለገሉ የቆዩት አቶ አሊ ሲራጅ በድንገት አረፉ፡፡ አቶ አሊ ሲራጅ በድንገት ያፉት ዛሬ ሰኔ 4 ቀን 2007 ዓ/ም ማለዳ በአዳማ በኦህዴድ ስብሰባ ላይ አንዳሉ በድንገት ህመም ተሰምቷቸው ወደ ሆስፒታል እየሄዱ እንዳለ ሆስፒታል ሳይደርሱ ህይወታቸው ሊያልፍ እንደቻለ ምንጮች ገልፀዋል፡፡ አቶ አሊ ሲራጅ የ 46 አመት ጎልማሳ ሲሆኑ በቅርቡ በተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ኦህዴድ/ኢህአዴግን ወክለው በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ምክር ቤት ለቀጣዩ በጀት ዓመት 31.8 ቢሊዮን ብር አፀደቀ

ለካፒታል ፕሮጀክቶች 65 በመቶ ተመደበ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ለ2008 ዓ.ም. 31.8 ቢሊዮን ብር በጀት ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. አፀደቀ፡፡ ይህ በጀት ከ2007 ዓ.ም. በጀት ጋር ሲነፃፀር የ14 በመቶ ብልጫ አለው፡፡

ከተያዘው በጀት 65 በመቶ ለካፒታል ፕሮጀክቶች፣ 35 በመቶ ለመደበኛ ወጪዎች ተመድቧል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካፀደቀው በጀት ውስጥ በማዕከል ደረጃ ለሚካሄዱ የካፒታል ፕሮጀክቶች 16.9 ቢሊዮን ብር፣ ለመደበኛ ወጪዎች 5.2 ቢሊዮን ብር፣ ለመጠባበቂያ 1.99 ቢሊዮን ብር መድቧል፡፡ በክፍላተ ከተሞች ለሚካሄዱ የካፒታል ፕሮጀክቶች 2.2 ቢሊዮን ብር፣ ለመደበኛ ወጪዎች 5.5 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡ 

ይህ ትልቅ በጀት የሚሸፈነው ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ነው፡፡ ከአገር ውስጥ ታክስ ገቢ 22.97 ቢሊዮን ብር፣ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች 2.9 ቢሊዮን ብር፣ ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢዎች 2.98 ቢሊዮን ብር፣ ከመንገድ ፈንድ 50.4 ሚሊዮን ብር ለማግኘት መታቀዱን የበጀቱ ረቂቅ ያመለክታል፡፡ በፌዴራል መንግሥት አማካይነት ከውጭ አገሮች በተለይ በብድር መልክ 2.6 ቢሊዮን ብር፣ ከዕርዳታ ደግሞ 238 ሚሊዮን ብር ይገኛል ተብሎ ታቅዷል፡፡ በወጪ ደረጃም 12.7 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ የተመደበ ሲሆን፣ 19.09 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪ ተበጅቷል፡፡ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የቀረበው በጀት አዋጅ እንደሚያስረዳው፣ ከተያዘው በጀት ትልቁ ተጠቃሚ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣንና የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ናቸው፡፡ 

መንገዶች ባለሥልጣን 156.9 ሚሊዮን ብር ለመደበኛ የተያዘለት ሲሆን፣ 5.9 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለካፒታል ፕሮጀክቶች ተመድቦለታል፡፡ ለውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን 1.2 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ በጀት ሲያዝለት፣ 4.4 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለካፒታል ፕሮጀክቶች ተመድቦለታል፡፡ 

የከተማው ምክር ቤት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት (2007 ዓ.ም.) 27.9 ቢሊዮን ብር ማፅደቁ ይታወሳል፡፡ በተጠናቀቀው በዚህ በጀት ዓመት በማዕከል ደረጃ ለሚገነቡ የካፒታል ፕሮጀክቶች 16.6 ቢሊዮን ብር፣ ለመደበኛ ወጪዎች 4.1 ቢሊዮን ብር፣ ለመጠባበቂያ ደግሞ 1.4 ቢሊዮን ብር መመደቡ ይታወሳል፡፡ በክፍላተ ከተሞች ለሚካሄዱ የካፒታል ፕሮጀክቶች 1.6 ቢሊዮን ብር፣ ለመደበኛ ወጪዎች 4 ቢሊዮን ብር መመደቡ አይዘነጋም፡፡ 

ከንቲባ ድሪባ ኩማ ባቀረቡት የ2007 ዓ.ም. ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባለፉት 11 ወራት 25.674 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ የተሰበሰበው 19.4 ቢሊዮን ብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም የዕቅዱን 75 በመቶ ብቻ ያሳካ ነው፡፡ 

ከዚህ በጀትም ለመደበኛና ለካፒታል ወጪዎች 15.6 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አምስት ቢሊዮን ብር (32.11 በመቶ) ለመደበኛ፣ 10.6 ቢሊዮን ብር (68 በመቶ) ለካፒታል ወጪዎች ማስፈጸሚያ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ 

‹‹በአጠቃላይ የገቢ አፈጻጸማችን ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ዕድገት ያሳየ ቢሆንም፣ ከዕቅዳችን አኳያ ሲታይ ዝቅተኛ ነው፡፡ በቀጣይነት የገቢ መሠረቱን የማስፋት፣ የሕግ ማስከበር ሥራዎችን የማጠናከርና ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ መሰብሰብ የሁሉንም አካላት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፤›› በማለት የከንቲባ ድሪባ ሪፖርት በቀጣዩ ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ማሳየት አስፈላጊነት ላይ አፅንኦት ሰጥቷል፡፡ 

 

በሁለቱ የጡረታ አዋጆች ላይ የተካተተው ማሻሻያ ከፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ጋር ይጋጫል የሚል ክርክር አስነሳ

በግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ አዋጅና በመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ አዋጅ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን እንዲያፀድቅ ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. የቀረበለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሻሻያዎቹን ቢቀበላቸውም፣ ተፈጻሚ

የሚሆኑበት ጊዜ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከመፈረማቸውና በነጋሪት ጋዜጣ ከመታወጃቸው በፊት ሊሆን አይገባም የሚል ክርክር ተነሳ፡፡

ምክር ቤቱ ሰኔ 29 ቀን ባደረገው ጉባዔ ካፀደቋቸው ረቂቅ አዋጆች መካከል፣ የመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅና የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ላይ የተደረጉት ማሻሻያዎች ይገኙበታል፡፡ ከሁለቱ አዋጆች መካከል የግል ድርጅቶች ጡረታ አዋጅ ማሻሻያ ቀደም ሲል አማራጭ አድርጎ ያቀረበውን የፕሮቪደንት ፈንድ ሥርዓት የሚያነሳ አንቀጽ በማካተቱ፣ በርካታ ድርጅቶች ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ከዚህም ውጪ ይህ አዋጅ በመንግሥት ድርጅቶች የተጠራቀሙ በፕሮቪደንት ፈንድ የሚተዳደር ገንዘብ ወደ ግል ጡረታ እንዲዘዋወር የሚል አንቀጽ በማስገባቱ፣ ከፍተኛ ሥጋትን በግል ሠራተኞች ላይ ፈጥሮ ነበር፡፡ 

ይህንን ሥጋት የቀረፈ ማሻሻያ ፓርላማው አንቀጹን በመሠረዝ ያደረገ ቢሆንም፣ በፕሮቪደንት ፈንድ የታቀፉ ድርጅቶች አሁንም በምርጫው ይቀጥሉ የሚለውን ጥያቄ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ ሁለቱ አዋጆች ላይ ማሻሻያ ያቀረቡት የመንግሥት ድርጅቶች ጡረታ ኤጀንሲና የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ ኤጀንሲ አዋጆቹ የሚፀኑበትን ጊዜ በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡ በኋላ በሚል አስቀምጠው የነበረ ቢሆንም፣ የፓርላማው የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሁለቱም አዋጆች ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ የፀኑ ይሆናል በሚል አሻሽለውታል፡፡ 

ጉዳዩን በተመለከተ አንድ የፓርላማ አባል፣ ‹‹አዋጆች ተፈጻሚ መሆን የሚጀምሩት በሕገ መንግሥቱ መሠረት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፈርመውበት በነጋሪት ጋዜጣ ታውጆ ነው፡፡ ይህ ማሻሻያ አዋጅ የተለየ አሠራር ያመጣው ለምንድነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ማሻሻያ አዋጁ እንዲፀድቅ ለፓርላማው የውሳኔ ሐሳብ ያቀረቡት የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ፣ ከበጀት ዓመቱ ጋር የተጣጣመ ለማድረግ እንዲሆን ጠቁመው፣ የበለጠ ግን በምክር ቤቱ የሚገኙ የሕግ ባለሙያዎች አስተያየት እንዲሰጡበት ጠይቀዋል፡፡ 

በዚሁ መሠረት የሕግ ባለሙያዎች አስተያየት እንዲሰጡ አፈ ጉባዔው በጋበዙት መሠረት፣ የምክር ቤቱ የመከላከያና የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ የተነሳውን የሕገ መንግሥት ጥያቄ በመደገፍ መስተካከል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥት የመሸርሸር ጉዳይ እንዳይሆን ፍርኃት አለኝ፡፡ በሕገ መንግሥቱ ለፕሬዚዳንቱ ከተሰጡ ሥልጣኖች ውስጥ አንዱ ይኼ ነው፤›› በማለት ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በማከልም ሕግ ሲወጣ በተቻለ መጠን ምንም ዓይነት ውዥንብር መፍጠር እንደሌለበት የተናገሩት አቶ ተስፋዬ፣ ‹‹አዋጁ ተፈጻሚ መሆን ያለበት በፕሬዚዳንቱ ተፈርሞ በነጋሪት ጋዜጣ ከወጣ በኋላ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ ተፈጻሚ ቢሆን ዓላማው ገንዘብ የመሰብሰብ ያስመስለዋል፡፡ ስለዚህ አሠራራችንን ባንጥስ የሚል አስተያየት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡ ሌላኛው የሕግ ባለሙያ የፓርላማው፣ የሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ ‹‹የሕግ ክርክር ለማንሳት አይደለም፡፡ በዚህ ምክር ቤት ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት አዋጆች የሚፀኑበትን ቀን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ሳያስቀምጥም ዝም ሊል ይችላል፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ተፈጻሚ ሊሆን ይችላል ብሎ ሊወስንም ይችላል፤›› በማለት ተቃርነዋል፡፡ 

ሕገ መንግሥቱ የሚለው ፕሬዚዳንቱ በ15 ቀናት ውስጥ ይፈርማሉ እንጂ፣ ከአሥራ አምስተኛው ቀን በኋላ እንደማይል የተናገሩት አቶ አስመላሽ፣ ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል መባሉ ፕሬዚዳንቱን ከመፈረም እንደማያግዳቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጉዳዩ የፕሮሲጀር ጉዳይ ስለሆነ ምክር ቤቱ በቀረበው መልኩ ቢቀበለው ችግር የለውም፡፡ ከሕገ መንግሥቱም ሆነ ከሌሎች ሕጎች ጋር አይጋጭም፤›› ብለዋል፡፡ በዚሁ የአቶ አስመላሽ ማብራሪያ መሠረት የመንግሥት ጡረታ አዋጅ ላይ የተደነገገው ማሻሻያ ላይ ተቃውሞ አቅርበው የነበሩትን አቶ ተስፋዬ ዳባን ጨምሮ፣ በሰጡት ድምፅ ያለ ተቃውሞ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል፡፡ 

ቀጥሎ የቀረበው የግል ድርጅቶች ማሻሻያ የውሳኔ ሐሳብም በተመሳሳይ አዋጁ ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ እንዲፀና የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ የውሳኔ ሐሳብ በቀረበበት ወቅት በድጋሚ ዕድል ያገኙት አቶ ተስፋዬ ዳባ፣ ‹‹አቶ አስመላሽ ያነሱትን መከራከሪያ አከብራለሁ፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም እርሳቸው የተለከቱት ከመብት አንፃር መሆኑን፣ አቶ አስመላሽ ደግሞ ከሥነ ሥርዓት (Procedure) አንፃር መሆኑን በዚህም መሠረት፣ ‹‹ሁለታችንም ኤ ነው ያገኘነው›› በማለት ምክር ቤቱን ፈገግ አሰኝተዋል፡፡ 

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች ግን አዋጆች ተፈጻሚ መሆን ያለባቸው በነጋሪት ጋዜጣ ከታተሙ በኋላ መሆን እንዳለበት ይከራከራሉ፡፡ ፓርላማው ራሱ ያወጣው የፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ 3/1995 አንቀጽ 2(2) ማናቸውም የፌዴራል መንግሥት ሕግ የሚወጣው በፌዴራሉ ነጋሪት ጋዜጣ ይሆናል እንደሚል፣ በነጋሪት ጋዜጣ የወጣን ሕግ ማንኛውም ኅብረተሰብ የማወቅና የመቀበል ኃላፊነት እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ 

በዚሁ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 2(3) ላይ፣ ‹‹ማናቸውም የፌዴራል ወይም የክልል ሕግ አውጪ፣ አስፈጻሚና ተርጓሚ እንዲሁም ማንኛውም የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ የሚወጣ ሕግን የመቀበል ግዴታ ይኖርበታል፤›› እንደሚል የሚጠቅሱት የሕግ ባለሙያዎች፣ ፓርላማው ያፀደቀውን ሕግ ኅብረተሰቡ አውቆታል ተብሎ የሚገመተው በነጋሪት ጋዜጣ ከወጣ በኋላ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ 

በመሆኑም በነጋሪት ጋዜጣ ያልወጣን ሕግ ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል ብሎ አንቀጽ ማስገባት፣ አዋጁ ተፈጻሚ በሚሆንባቸው ዜጎች ወይም ድርጅቶች ላይ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ 

በተለይ የፀደቁት አዋጆች ጡረታ ሰብስበው በማያስገቡ ቀጣሪዎች ላይ ወለድና ቅጣት የሚጥሉ በመሆናቸው፣ አዋጁ ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ መፅደቁን የማያውቁ ድርጅቶች ወይም ቀጣሪዎች ላይ የሕግ ተጠያቂነትን መጣል አግባብ አይሆንም ብለዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ ዳባ በፓርላማው ስላነሱት ክርክር ተጨማሪ አስተያየት ይኖራቸው እንደሆነ ለማጣራት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 57 ፕሬዚዳንቱ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ባይፈርም፣ ሕጉን በሥራ ላይ ከማዋል የሚያግድ እንደማይሆን ይደነግጋል፡፡ 

 

የግል ባንኮች ትርፍ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል

ንግድ ባንክ ከታክስ በፊት 12 ቢሊዮን ብር ማትረፉ ተሰምቷል

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 16 የግል ባንኮች በ2007 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ እንደሚያገኙ ሲጠበቅ፣ አንዳንድ ባንኮችም የትርፍ ምጣኔያቸውን ከእጥፍ በላይ ማሳደጋቸው ታወቀ፡፡ 

የ2007 ዓ.ም. የባንኮቹ የመጀመሪያ ደረጃ ጥቅል መረጃ እንደሚያሳየው ሁሉም ባንኮች በአትራፊነታቸው ዘልቀዋል፡፡ ከአምናው የበለጠ ትርፍ ማግኘትም ችለዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ሁሉም ባንኮች ከታክስ በፊት አትርፈውት የነበረው ግርድፍ ትርፍ ከ4.6 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ሁሉም የግል ባንኮች በ2007 በበጀት የሒሳብ ሪፖርት ተቀናናሽ ሒሳብ ቢኖርባቸውም፣ ጥቅል ትርፋቸው ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ይሆናል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ከፍተኛ ትርፍ በማግኘት ዘንድሮም ከግል ባንኮች ከፍተኛውን ትርፍ ያስመዘገበው ዳሸን ባንክ ሲሆን፣ ከታክስ በፊት ከ950 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉ ተጠቁሟል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ባንኩ ከታክስ በፊት 928 ሚሊዮን ብር ማትረፉ አይዘነጋም፡፡

አዋሽ ባንክም ወደ 890 ሚሊዮን ብር ገደማ ማትረፉ እየተነገረ ነው፡፡ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ከግል ባንኮች በትርፍ መጠኑ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የመጣው የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በማትረፍ ደረጃውን ይዞ መቀጠሉ ታውቋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በትርፍ ምጣኔው ከፍተኛ ዕድገት ካሳዩ ባንኮች መካከል እናት ባንክ አንዱ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ ከ72 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፍ ችሏል፡፡ ይህ ትርፍ ባለፈው በጀት ዓመት ካገኘው ትርፍ ጋር በንፅፅር ሲቀመጥ ከእጥፍ በላይ ማደጉን ያሳያል፡፡ ባንኩ በ2006 በጀት ዓመት አስመዝግቦት የነበረው ትርፍ 31 ሚሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡

እንደ እናት ባንክ ሁሉ ከአምናው የትርፍ ምጣኔ ጋር ሲነፃፀር ከ50 በመቶ በላይ ብልጫ ያለው ትርፍ ያስመዘገበው አንበሳ ባንክ ነው፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ የአንበሳ ባንክ በ2007 ዓ.ም. ያልተጣራ ትርፍ 275 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ ትርፍ አምና አስመዝግቦት ከነበረው 127 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር ከ145 ሚሊዮን ብር በላይ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ 

አንበሳ ባንክ በትርፍ ዕድገቱ ብቻ ሳይሆን 580 ሚሊዮን ብር የነበረውን የተቀማጭ ገንዘብ አቅሙን ወደ 1.7 ቢሊዮን ብር በማድረስ ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉ ይጠቀሳል፡፡

ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ በ2006 ዓ.ም. 131 ሚሊዮን ብር የነበረውን ትርፍ ወደ 140 ሚሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ ንብ ባንክ ከ430 ሚሊዮን ብር በላይ እንዳተረፈ ሲነገር፣ አምና 350 ሚሊዮን ብር ያተረፈው አቢሲኒያ ባንክ ደግሞ ከ365 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉ ተጠቁሟል፡፡ ደቡብ ግሎባል ባንክም ከአምናው በተሻለ ከታክስ በፊት 31 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል፡፡ ይህ ትርፍ ከሁሉም ባንኮች ያነሰ ነው፡፡ ባንኩ አምና ያገኘው ትርፍ 19 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡

ሌሎቹም ባንኮች የትርፍ ምጣኔያቸው ዕድገት የተለያየ ቢሆንም፣ የትርፍ ዕድገት በማሳየታቸው በአጠቃላይ የግል ባንኮችን የትርፍ መጠን አምና ከነበረበት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ያሳድገዋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2007 በጀት ዓመት 12 ቢሊዮን ብር ከታክስ በፊት ማትረፉ ተሰምቷል፡፡ ንግድ ባንክ ባለፈው ዓመት 9.7 ቢሊዮን ብር ከታክስ በፊት ማትረፉ ይታወሳል፡፡ የዘንድሮው ግን ትልቅ ትርፍ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ 

 

ሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫው ውጤት ሰላማዊውን ትግል ውስብስብ አድርጎታል አሉ

በአምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ የተሳተፉት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) የምርጫው ውጤት ሕዝቡን ወዳልተፈለገ

አቅጣጫ ሊያመራ ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው አስታወቁ፡፡ ሰላማዊውን የፖለቲካ ትግል ውስብስብ እንዳደረገውም ገልጸዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ይህንን ያስታወቁት ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. በራስ ሆቴል በጋራ በሰጡት መግለጫ ወቅት ሲሆን፣ መግለጫውን የሰጡት ደግሞ የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሐሪ፣ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደና የኢራፓ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ ናቸው፡፡

ሥርዓቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍሬያማ ከመሆን ይልቅ እየቀጨጨና እየኮሰመነ በመሄድ ላይ ለመሆኑ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ዋና መገለጫ የሆነው የምርጫ ሒደት ችግር ቁልጭ አድርጐ እያሳየን ሲሉም ደምድመዋል፡፡ 

የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እውን እንዳይሆን ገዥው ፓርቲ እንቅፋት ሆኗል የሚለው የፓርቲዎቹ መግለጫ፣ ‹‹ገዥው ፓርቲ ከዚህ ግትር አቋሙ ፈቀቅ የማይል ከሆነ የአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም ሆነ አጠቃላይ የአገሪቱ ሰላም አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል ብለን እናምናለን፡፡ ገዥው ፓርቲ የምርጫ ዴሞክራሲያዊነትና ፍትሐዊነት መርሆዎችን ካላከበረ ሕዝቡን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ይመራዋል ብለን እንሰጋለን፤›› ሲልም ያክላል፡፡ የምርጫውን ውጤት ተከትሎ የከሰመው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በአገሪቱ ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ጥያቄ ያስቀመጠ መሆኑንም ፓርቲዎቹ አመልክተዋል፡፡  

‹‹በ2007 ዓ.ም. የተከናወነው አምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ባለመሆኑ ምክንያት፣ በአገራችን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሏል፡፡ ይህም በመሆኑ በአገራችን ያለው አንፃራዊ ሰላም አስተማማኝ አይሆንም የሚል ሥጋት አድሮብናል፤›› በማለትም የፓርቲዎቹ ፕሬዚዳንቶች በጋራ በሰጡት መግለጫ አስረድተዋል፡፡ 

‹‹በአገራችን ዴሞክራሲ እንዲጠናከርና እንዲያብብ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁ ተቋማት በምርጫው ሒደት ላይ የፈጠሯቸው ተግዳሮቶች በሰላማዊ ትግሉ ላይ ትልቅ ጋሬጣ በመሆናቸው፣ የወደፊቱን ሰላማዊ ትግል እጅግ ውስብስብና አስቸጋሪ አድርጐታል፤›› በማለት በመግለጫው አትቷል፡፡

የፓርቲዎቹን አጠቃላይ የወደፊት አቅጣጫ በተመለከተ የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሐሪ ሲናገሩ፣ ‹‹ከሦስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁለቱ የጋራ ምክር ቤት አባል ናቸው፡፡ እኛ ግን አይደለንም፡፡ ልንሆንም አንችልም፡፡ ሙሉ በሙሉ በአጠቃላይ ጉዳዮች ላይ አብረን እንሠራለን ማለት አይደለም፤›› በማለት ለጊዜው በጋራ የሚሠሩት በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በጋራ ለመሥራት ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መካከል ጋዜጣዊ መግለጫዎችን በጋራ መጥራትና የተቃውሞ ሰላማዊ ሠልፎችን ማዘጋጀት ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹ሙሉ በሙሉ በአንድ ላይ ለመሄድ የምናርቃቸውና የምንመለከታቸው ጉዳዮች ይኖራሉ፤›› በማለትም ፓርቲዎቹ በጋራ የሚሠሩባቸውን ተጨማሪ ጉዳዮች ለመለየት በድርድር ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ 

የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ ‹‹በተለይ ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም የምናራምድ ፓርቲዎች በተጠናከረ ስልትና ስትራቴጂ ሐሳቦቻችንን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ እያደረግን ለመሥራት እንድንችል የሚያስችለንን ስልት ነድፈን እንሄዳለን ብለን እናምናለን፤›› በማለት ሦስቱ ፓርቲዎች የሚያግባቧቸውን ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ እንዳለዩ ገልጸዋል፡፡

ኅብረት፣ ግንባር ወይም ውህደት ፈጥሮ ለመሥራት በርካታ ሒደቶችን የሚጠይቅ በመሆኑ ይህንን በሌሎች የፖለቲካ ተንታኞችም እየታገዝን በጉዳዩ ላይ ወደፊት እንወስናለን፤›› በማለት ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

በምርጫ 97 ጠንካራ ተወዳዳሪ የነበረው ቅንጅት እንዲዳከም ትልቅ በር የከፈተው የመኢአድና የኢዴፓ ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከቅንጅት ራሱን ያገለለው ኢዴፓ ከምርጫ 97 በኋላ ከተለያዩ ኅብረቶች፣ መድረኮችና ጥምረቶች ራሱን በማግለል የቅንጅት አባል ከነበሩ ፓርቲዎች ጋር አንድ ላይ ለመሥራት የሚያስችል መሠረት እንደሌለ፣ በጫና አባል መሆኑ ስህተት እንደነበር በራሱ ላይ ግለ ሒስ ማቅረቡም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

የፖለቲካ ተንታኞች ከዚህ አንፃር ኢዴፓ መሥራች አባላቱ ተገንጥለው የወጡበት መአሕድ ራሱን በሒደት ወደ መኢአድ ከመቀየሩ አንፃርና ኢራፓ ከ1997 በኋላ በ2001 ዓ.ም. የተፈጠረ አዲስ ፓርቲ ከመሆኑ አኳያ፣ ከእነዚህ ፓርቲዎች ጋር የጀመረው ግንኙነት ያልተጠበቀ መሆኑን እየገለጹ ነው፡፡  

 

ውሳኔውን አንብቦ ለመጨረስ ሦስት ቀናት ፈጅቷል

ራሳቸውን የሙስሊሙ ኅብረተሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ በማለት ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ዓላማዎችን ለማራመድ፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመጣል፣ ኢስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት፣ በህቡዕ

በመደራጀትና የሽብር ድርጊት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል ተብለው የሽብርተኝነት ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው 18 ግለሰቦች ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ጥፋተኛ ተባሉ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. የሽብር ድርጊት ክስ የመሠረተባቸው ሁለት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና 29 ግለሰቦችን የነበረ ቢሆንም፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ጥፋተኛ ያላቸው 18 ተከሳሾችን ብቻ ነው፡፡ የቀድሞ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ወ/ሮ ሐቢባ መሐመድ መሐሙድን ጨምሮ 11 ግለሰቦችና ድርጅቶቹ ከክሱ በነፃ መሰናበታቸው ይታወሳል፡፡

ፍርድ ቤቱ ለሦስት ዓመታት ያህል ሲያከራክርና ሲመረምር የከረመውን የፍርድ ሒደት አጠናቆ የጥፋተኝነት ውሳኔ የሰጠው በአቶ አቡበከር አህመድ፣ አህመዲን ጀበል፣ ያሲን ኑሩ፣ ካሚል ሸምሱ፣ በድሩ ሁሴን፣ ሼክ መከተ ሙሔ፣ ሳቢር ይርጉ፣ መሐመድ አባተ፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ ሙራድ ሽኩር፣ አቡበከር ዓለሙ፣ ኑሩ ቱርኪ፣ ሼክ ባህሩ ዑመር፣ ሙኒር ሁሴን፣ ሼክ ሰዒድ ዓሊ፣ ጋዜጠኛ የሱፍ ጌታቸው፣ ሙባረክ አደምና ካሊድ ኢብራሂም ላይ ነው፡፡

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በሁሉም ተከሳሾች ላይ አራት ክሶችን ያቀረበ ቢሆንም፣ ሦስተኛና አራተኛ ክሶች የሚያተኩሩት መንግሥታዊ ባልሆኑት ድርጅቶች ላይ በመሆናቸው ድርጅቶቹ ነፃ በመሆናቸው ክሶቹም ቀሪ ሆነዋል፡፡ በአንደኛና በሁለተኛ ክሶች ላይ ተከሳሾቹ ድርጊቱን ክደው በመከራከራቸው ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ ያስረዱኛል ያላቸውን የሰዎችና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡ ከመቶ በላይ ምስክሮችንም አሰምቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን የሰዎችና የሰነዶች ማስረጃዎች ጨምሮ፣ የተከሳሾች መስቀለኛ ጥያቄ የዓቃቤ ሕግን ክስና የምስክሮች ቃል ማፍረስ አለማፍረሱን መርምሮ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹም ከ400 በላይ መከላከያ ምስክሮችን አስመዝግበው 157ቱን በማሰማት ቀሪዎቹን ትተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግና ተከሳሾቹ በምስክሮቻቸው ያስረዱትን የምስክርነት ቃል ከክሱና ተገቢ ሕግ ጋር በመመርመር፣ ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሰብሳቢ ዳኛ በሆኑበት ችሎት የጥፋተኝነት ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት፣ አምስት ጭብጦችን ይዞ የክስ መዝገቡን መመርመሩን ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱ የያዛቸው ጭብጦች፣ ‹‹መንግሥት በሙስሊሙ ጉዳይ ጣልቃ ገብቷል ወይስ አልገባም? መንግሥት የሙስሊሙን ማኅበረሰብ ከፋፍሏል  ወይስ አልከፋፈለም? የመጅሊሱ ምርጫ በቀበሌ እንዲሆን መደረጉ አግባብ ነው ወይስ አይደለም? ተከሳሾችን ለመያዝ የተደረገው የብርበራ ሒደት የኢትዮጵያን ሕግና ሕገ መንግሥት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችን የተከተለ ነው ወይስ አይደለም? እና ተከሳሾች የቀረበባቸውን ክስ ተከላክለዋል ወይስ አልተከላከሉም?›› የሚሉ ናቸው፡፡

ፍርድ ቤቱ የሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ ከመቶ ገጾች በላይ በመሆኑ ማንበብ የተጀመረው ሰኔ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ቢሆንም የተጠናቀቀው ከሦስት ቀናት በኋላ ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው፡፡ ሰኔ 26 ቀን 2007 (ዕለተ ዓርብ) ችሎት አልነበረም፡፡ ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ያቀረቡት በርካታ ገጾች ያሉት የሰነድ መከላከያ መስረጃ ማቅረባቸውን ገልጾ፣ ከክሱ ጋር የሚዛመዱትንና ፍሬ ነገር ያለባቸውን ሰነዶች መውሰዱን ገልጾ ባጭሩ አሰማ፡፡

ተከሳሾቹ ከመቀመጫቸው ተነስተው ‹‹ጥያቄ አለን›› በማለት ሲያመለክቱ፣ ‹‹ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እየተነበበ ጥያቄ ማቅረብ አይቻልም፤›› ቢልም መናገራቸውን ቀጠሉ፡፡ እስካሁን መታፈናቸውን (የጥፋተኝነት ውሳኔው እስከተሰጠበት ቀን) ተናግረው ያቀረቡት 20,000 ገጽ ማስረጃ ሆኖ ሳለ አራት ገጽ እንኳን የማይሞላ ማስረጃ ተደርጎ መወሰዱን እንደሚቃወሙ ገለጹ፡፡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን እንዳልሠራው በመናገር ይኽንን ሊያስብላቸው የቻለው በውሳኔው ውስጥ የተፈቱ ሰዎች ስም ዝርዝር ሲጠቀስ በመስማታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ሠርቶት ቢሆን ኖሮ የተፈቱ ሰዎች ሊካተቱ እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በተነበበላቸው ውሳኔ ውስጥ በርካታ ስህተቶች እንዳሉም አክለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ በመግባት በተለይ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያምና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሙስሊሙን ኅብረተሰብ በመሰብሰብ እየከፋፍሉትና የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛትና ሙስሊሙን ሊከፋፈሉ እንደሆነ በመግለጽ የሃይማኖት ተከታዮችን ማነሳሳታቸውን የዓቃቤ ሕግ ማስረጃዎች እንደሚያረጋግጡ ገልጿል፡፡ የወሃቢያ አስተምህሮ መጥቶ ሃይማኖታቸውን ሊያስቀይራቸው መሆኑን የፌዴራል ጉዳዮች ለሙስሊሞች መንገሩን፣ የአወሊያ ተማሪዎች በመጅሊሱ መባረራቸውን፣ የወሃቢያ አስተምህሮ ሕገ መንግሥቱን ለማፈራረስ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን፣ ሙስሊሞች በጨለማ ውስጥ መታሰራቸውን፣ መንግሥት ከአወሊያ ላይ እጁን ያላነሳና መጅሊሱ ያወጣው መተዳደሪያ ደንብ ሙስሊሙን የሚያከብር እንዳልሆነ በመናገር መንግሥት አስቸኳይ መልስ ካልሰጠ፣ በሌላው ዓለም የሚታየው አክራሪነት በኢትዮጵያም የማይታይበት ምንም ምክንያት እንደሌለ፣ ምርጫ ከመስጊድ ውጪ መደረግ እንደሌለበት በመንገርና በመቀስቀስ አመፅ ማነሳሳታቸውን ዓቃቤ ሕግ ካቀረበው የሰነድና የሰው ምስክሮች መረጋገጡን ፍርድ ቤቱ አብራርቷል፡፡

ተከሳሾቹ በተለያዩ ቦታዎች ባደረጉዋቸው ንግግሮች የፖለቲካ አጀንዳ እንደሌላቸው፣ ኢስላማዊ መንግሥት የመመሥረት ዓላማ እንደሌላቸውና ሞኝ አለመሆናቸውን፣ የሚፈልጉት ጥያቄያቸው እንዲመለስላቸው ማለትም የመጅሊስ ምርጫ በመስጊድ እንዲሆንና ታዛቢ እንደማያስፈልግ፣ ሕዝበ ሙስሊሙን የሚወክለው መፍትሔ አፈላላጊው ኮሚቴ ብቻ ምርጫውን የማድረግ ኃላፊነት እንዲወስድ፣ ወዘተ እንዳሉ የገለጹ ቢሆንም፣ ሃይማኖቱን ሽፋን በማድረግ ሙስሊም ኅብረተሰቡን ለአመፅ ማነሳሳታቸውን ዓቃቤ ሕግ በሰነድና በምስክሮች ማረጋገጡን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ ሰላማዊ መሆናቸውን፣ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠላቸውን የሃይማኖት እኩልነትና መንግሥት በሃይማኖት፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጣልቃ አይገቡም የሚለውን ለማረጋገጥ ስለእምነታቸው ከመጠየቃቸው ባለፈ፣ ምንም ወንጀል አለመፈጸማቸውን የሚያስረዱላቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ማቅረባቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ 

ሁሉም ተከሳሾች ከአንደኛ ተከሳሽ አቶ አቡበከር በስተቀር ዓቃቤ ሕግ ፈጽመዋል ያለውን የወንጀል ድርጊት ፖሊስ በወንጀል ሕግ 27 መሠረት በግዳጅ ቃላቸውን እንዲሰጡ ያደረጋቸው መሆኑን መናገራቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ነገር ግን ዓቃቤ ሕግ በምስክሮቹና በሰነድ ማስረጃዎቹ ተከሳሾቹ በፖሊስ ጣቢያ አምነው የተናገሩትን በማረጋገጡ፣ ተከሳሾቹ ያቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ የዓቃቤ ሕግን ክስ ከማረጋገጥ ባለፈ ከተጠያቂነት የሚያድናቸው አለመሆኑን ገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ የተመሠረተባቸውን ክስ ማስተባበል አለመቻላቸውን አንድ በአንድ ሲገልጽ፣ መጀመርያ አቶ አቡበከር ከመቀመጫቸው በመነሳት ‹‹አሏህ አክበር፣ ነፃነቴን ያረጋገጥኩበት ፍርድ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ፤›› ሲሉ፣ ሁሉም እጅ ለእጅ ታይዘው ‹‹አሏህ አክበር›› በማለታቸው ፍርድ ቤቱ ፖሊስ አስፈላጊውን ዕርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ መደብዳባቸውንና ከፍተኛ በደል እንደደረሰባቸው በመከላከያ ምስክሮች ቢያስረዱም፣ በተለይ እርስ በርስ (እስረኞቹ) ከመመሰካከራቸው አንፃር ምስክርነቱ ተዓማኒ ሊባል እንደማይችል ፍርድ ቤቱ በመግለጽ ውድቅ አድርጎታል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የኢትዮጵያን ሕግ፣ ሕገ መንግሥትና ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን የሚጥስ ድርጊት የፈጸሙ መሆናቸውን በመግለጽ ሁሉንም ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡ ተከሳሾቹ የቅጣት ማቅለያቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ የቅጣት ማክበጃውን እስከ ሐምሌ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያስገቡ በማዘዝ ፍርድ ለመስጠት ለሐምሌ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጥሯል፡፡

 

የባንኩ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ የተቀጡት በሌሉበት ነው

መንግሥታዊ ሰነዶችን በሐሰት በማዘጋጀት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰባራ ባቡር ቅርንጫፍ፣ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ማጭበርበራቸው የተረጋገጠባቸው የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅና ሁለት ግለሰቦች፣

ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ከአምስት እስከ 12 ዓመታት ከስድስት ወራት የሚደርስ ጽኑ እስራት ተፈረደባቸው፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ በሙስና ወንጀል ክስ የመሠረተባቸው፣ የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ አቶ መኳንንት አበጀ፣ ይፈመን ቲምበር ፕሮሰሲንግ የተባለ ድርጅት ተወካይ አቶ ብርሃኑ አዳፍሬና የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ይትባረክ አፈወርቅ ናቸው፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው፣ የባንኩ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ መኳንንት በ2005 ዓ.ም. የተለያዩ ሀሰተኛ የባንክ ዋስትና ሰነዶችን አዘጋጅተዋል፡፡ ያዘጋጁትን ሐሰተኛ ሰነድ ይፍመን ቲምበር ፕሮሰሲንግ ለተባለው ድርጅት በመስጠት ወንጀሉን መፈጸማቸውን ያስረዳል፡፡

በሥራ አስኪያጁ የተዘጋጀውን ሐሰተኛ ሰነድ የድርጅቱ ተወካይ አቶ ብርሃኑ በመቀበልና ሐሰተኛ የሽያጭ ዋስትና በማስያዝ፣ ከአንድ የማደያ ድርጅት ውል ተዋውለው 900,000 ብር የሚያወጣ የሞተር ዘይት፣ ቅባቶችና የነዳጅ ኩፖን ወስደው በወንጀሉ መሳተፋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

የይፈመን ቲምበር ፕሮሰሲንግ ሥራ አስኪያጅ ናቸው የተባሉት አቶ ይትባረክ፣ ከአቶ ብርሃኑ ጋር በመተባበር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ላደረጉት የእንጨት ምሰሶዎች አቅርቦት ውል፣ ሐሰተኛ ሰነዱን በዋስትና በማቅረብ 4,908,623 ብር ቅድመ ክፍያ ከኢትዮ ቴሌኮም በቼክ መውሰዳቸውን ይገልጻል፡፡ ገንዘቡንም ወደ ድርጅታቸው አካውንት በማስገባትና አውጥተውም ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውም በክሱ ተጠቁሟል፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ሦስቱም ተከሳሾች ድርጊቱን መፈጸማቸውን በምስክሮችና በሰነድ በማረጋገጡ፣ የባንኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ መኳንንት በሌሉበት በስምንት ዓመታት ጽኑ እስራት፣ አቶ ብርሃኑ አዳፍሬ በ12 ዓመት ከስድስት ወራት ጽኑ እስራትና አቶ ይትባረክ አፈወርቅ በአምስት ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ሰጥቷል፡፡  

 

 

 

የሽብረተኝነት ክስ የተመሠረተባቸው እነ አቡበከር መሐመድ ከሁለት ዓመት በላይ ጊዜ ከወሰደ ክርክር በኋላ በዛሬው ዕለት ጥፋተኛ ተባሉ፡፡

በፌዴራል ዓቃቢ ሕግ ክስ ተመሥርቶባቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት ከጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ በተካሄደ ክርክር፣ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸውን የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃዎች ማስተካከል አልቻሉም የተባሉት

አቡበከር መሐመድ፣ አህመዲን ጀበል፣ ያሲን ኑሩ፣ ከሚል ሸምሱ፣ በድሩ ሁሴን፣ ሼክ መከተ ሙሔ፣ ሳቢር ይርጉ፣ መሐመድ አባተ፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ ካሊድ ሽኩር፣ አቡበከር ዓለሙ፣ ጉሩ ቱርኪ፣ ሼክ ባህሩ ኡመር፣ ሙኒር ሁሴን፣ ሼክ ሰኢድ፣ ጋዜጠኛ የሱፍ ጌታቸው፣ ሙባረክ አደም፣ እንዲሁም ካሊድ አብርሃም በዛሬው  ዕለት ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡

ተከሳሾቹ የተሰጠባቸውን የፍርድ ውሳኔ ከመቀመጫቸው በመነሳት በተደጋጋሚ  ተቃውመዋል፡፡ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ለሐምሌ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን፣ ዓቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃውን ተከሳሾች ደግሞ የቅጣት ማቅለያቸውን እስከ ሐምሌ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያስገቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና ፕሬዚዳንት ኦባማ በነዳጅ ማስተላለፊያ ግንባታ ላይ እንደሚወያዩ ታወቀ

ግዙፉ የአሜሪካ ኩባንያ ብላክ ስቶን ከጂቡቲ ኢትዮጵያ ድረስ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት በያዘው ዕቅድ ላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እንደሚወያዩ ምንጮች ገለጹ፡፡

በሐምሌ አጋማሽ ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ ተብለው የሚጠበቁት ፕሬዚዳንት ኦባማ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ከሚወያዩባቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል፣ የአሜሪካ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ለማካሄድ ያቀዷቸው ፕሮጀክቶች እንደሚገኙበት ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል ብላክ ስቶን ከጂቡቲ አዋሽ ድረስ ለመገንባት ያቀደው፣ 550 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር አንዱ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ኩባንያው ይህንን ፕሮጀክት ለማካሄድ ቀደም ብሎ ምክረ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ አቅርቧል፡፡ ኢንተርፕራይዙ ከኩባንያው ጋር ሲደራደር ቢቆይም፣ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ አቅጣጫ መስጠት አለበት ተብሎ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አቅርቧል፡፡

ገንዘብ ሚኒስቴር ጉዳዩ ነዳጅ የማጓጓዝ በመሆኑ ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ድረስ እየተገነባ ያለው የባቡር መስመር ከሚያጓጉዛቸው ሸቀጦች አንዱና ዋነኛው ነዳጅ ማመላለስ በመሆኑ፣ በዚህ ላይ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ አስተያየት እንዲሰጥ ምክረ ሐሳቡን ልኮታል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ የነዳጅ ማመላለሻ መስመሩ አዋጭ ስለመሆኑ እያጤነ መሆኑን፣ እስካሁን ቦርዱ ውሳኔውን እንዳላሳወቀ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ከጂቡቲ አዲስ አበባ ድረስ ናፍጣ፣ ቤንዚንና የአውሮፕላን ነዳጅ ለማጓጓዝ በተያዘው ፕሮጀክት 1.4 ቢሊዮን ዶላር ይፈልጋል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ይህንን ገንዘብ ኩባንያው ከራሱና ከፋይናንስ ምንጮች የሚሸፍን ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ እንዲሰጠው የሚፈልገውም በኮንሴሽን ነው፡፡

ኩባንያው እዚህ ሥራ ውስጥ ለመግባት የፈለገው በማደግ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ የነዳጅ ፍላጐቷ በየዓመቱ 15 በመቶ ዕድገት የሚያሳይ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡ ይህንንም ነዳጅ በየቀኑ 500 የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በጠባብ መንገድ ላይ 800 ኪሎ ሜትር እየተጓጓዙ የሚያመላልሱ በመሆናቸው አዋጭነቱን በመገንዘብ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ፕሮጀክት ቢፈልገውም፣ የባቡር መስመሩ በከፍተኛ ብድር በመገንባቱና ብድሩን ለመመለስ የግድ የአገሪቱ ነዳጅ በባቡር መመላለስ ይኖርበታል በሚል ምክንያት በጥልቀት መመርመር አስፈላጊ በመሆኑ እንዳዘገየው ምንጮች ይናገራሉ፡፡

ነገር ግን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ግን፣ መንግሥት የአገሪቱ ነዳጅ በባቡርም፣ በነዳጅ ማስተላለፊያ መስመርም ቢጓጓዝ ጠቀሜታ ይኖረዋል ይላሉ፡፡

ምክንያቱን ሲያስረዱም በሁለቱም ማስተላለፊያ መስመሮች ነዳጅ ቢጓጓዝ የትራንስፖርት ዋጋ ላይ ውድድር ስለሚኖር ቅናሽ ይኖራል የሚል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንዱ ማጓጓዣ መስመር እንከን ቢገጥመው፣ በአንደኛው መጓጓዣ ዘዴ መጠቀም ስለሚቻል የፕሮጀክቶቹ መደራረብ ጥቅም እንጂ ጉዳት እንደሌለውም ያስረዳሉ፡፡

ብላክ ስቶን ይህንን ፕሮጀክት ለማከናወን ያቀደው በእህት ኩባንያው ብላክ ሬይ አማካይነት ሲሆን፣ ከዓመት በፊት በአጠቃላይ ጉዳዮች ላይ ከጂቡቲና ከኢትዮጵያ መንግሥታት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

የአሜካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለጉብኝት አዲስ አበባ በሚመጡበት ወቅት፣ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥታቸው የሚሰጠውን ድጋፍ በማስረዳት ድርድሩ ተቋጭቶ ወደ ሥራ ለመግባት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ ፕሮግራም መያዙን፣ ምንጮች ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡   

 

ከቻይና በኮንቴይነር ታሽጎ ወደ ኢትዮጵያ የተላከው ዘይት የድንጋይ ንጣፍ ሆኖ ተገኘ

ከ1.9 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል

-የጋላፊንና የሚሌን ፍተሻ ጣቢያዎች ማለፉ ግርምት ፈጥሯል

-ተጠያቂዎቹ ንግድ መርከብና የቻይና ድርጅት መሆናቸው ተጠቁሟል

በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ የሚገኘው አሚድአብ ጄኔራል ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ከቻይናው ዌይፋንግ ሹኦፌንግ ኢምፖርትና ኤክስፖርት ኩባንያ ገዝቶ ወደ ኢትዮጵያ ያስመጣው በአራት ኮንቴይነሮች የአኩሪ አተር ዘይት፣

ሰኔ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. መቐለ ደረቅ ወደብ ደርሶ ሲከፈት ኮንክሪት የድንጋይ ንጣፍ ሆኖ ተገኘ፡፡

የሪፖርተር ምንጮች ከደረቅ ወደብ አስተዳደር የመቐለ ቅርንጫፍ እንደገለጹት፣ አሚድአብ ጄኔራል ቢዝነስ ከቻይናው ኩባንያ የገዛውን አራት ኮንቴይነሮች አኩሪ አተር ዘይት አጓጉዞ ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገባለት፣ ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጋር ተስማምቷል፡፡ ድርጅቱም በገባው ውል መሠረት ሲአይኪው የተባለው የቻይና ድርጅት አረጋግጦና ሠርተፊኬት አሳይቶት ዕቃው መጫኑን ሰነዶች እንደሚያስረዱም ምንጮች ተናግረዋል፡፡ 

አሚድአብ ጄኔራል ቢዝነስ ዘይቱን ለሚልከው የቻይናው ኩባንያ እስከ ወደብ ማድረሻና የዘይቱን ዋጋ 67,860 ዶላር ከፍሏል፡፡ ለመርከብ ማጓጓዣ ደግሞ ከቻይና እስከ ጂቡቲ 7,684 ዶላር ከፍሏል፡፡ ከጂቡቲ እስከ መቐለ ደግሞ የማጓጓዣ 6,433.75 ዶላር ከፍሏል፡፡ በድምሩ 81,977.75 ዶላር ወይም 1,861,550.87 ብር መክፈሉን ምንጮች ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ 

አራት ኮንቴይነር አኩሪ አተር ዘይት በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት የደረቅ ጭነት ማጓጓዣ ተሽከርካሪ ተጭኖ መቐለ ደርሶ ሲከፈት፣ በኮንቴይነሮቹ ውስጥ የተጫነው ንፁህነቱ የተረጋገጠና የተመሰከረለት የአኩሪ አተር የምግብ ዘይት ሳይሆን፣ መንገድ ላይ የሚነጠፍ (በተለይ ለውኃ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ከላይ ሽፋን የሚውል ጠፍጣፋና ረዘም ያለ መዝጊያ ድንጋይ) ኮንክሪት ንጣፍ ድንጋይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ 

በሥፍራው የነበሩ የደረቅ ወደቡ ሠራተኞችም ሆኑ ስማቸው ያልተገለጸው የድርጅቱ ባለቤት ከመደንገጣቸው የተነሳ፣ ለደቂቃዎች በፀጥታ ውስጥ ሆነው እርስ በርስ ሲተያዩ መቆየታቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡ 

ኤክስፖርት የሚያደርገው የቻይናው ኩባንያ ኮንቴይነሮቹን ሲወስድ ባዶ መሆናቸው ተረጋግጦና ማሸጊያ (ሲል) አብሮ እንደሚሰጠው የጠቆሙት ምንጮች፣ ኩባንያው ምርቶቹን በገባው ውል መሠረት ጥራታቸውን የጠበቁና ጉድለት እንዳይኖርም ሲአይኪው የሚባለው የጥራት ተቆጣጣሪ የቻይናው ድርጅት መከታተል እንደነበረበት፣ የመጫን ኃላፊነቱን የወሰደው የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅትም ቁጥጥር ማድረግ ይገባው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የመጫኛው ትዕዛዙ (ቢል ኦፍ ሎዲንግ) ዘይት ቢልም፣ ሲከፈት ግን ድንጋይ መሆኑን አክለዋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ መንግሥት የተወከለው የቻይናው ሲአይኪው ድርጅት ተከታትሎ ማሳሸግና ማስጫን ሲገባው፣ የማይታወቅ ዕቃ እንዲላክ ማድረጉ ግራ እንዳጋባቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ጊዜው አስፈሪ ከመሆኑ አንፃር፣ ማለትም አሸባሪ መላ ዓለምን እያሰጋ ባለበት ‹‹የተጫነው ዕቃ ፈንጂ ቢሆንስ?›› በማለት የሚጠይቁት ምንጮች፣ የድንጋዩ ጉዳይ ሕጉን ተከትሎ መፍትሔ የሚያገኝ ቢሆንም፣ መንግሥት ግን ችግሩን ሊፈትሽ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ 

ሌላው ምንጮችን ያስገረመው ኮንቴይነሮቹ የባህር ላይ ጉዞአቸውን ጨርሰው መቐለ ደረቅ ወደብ ከመድረሳቸው በፊት፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ቅርንጫፍ መፈተሻ ጣቢያዎች የጋላፊንና የሚሌን የፍተሻ ጣቢያዎች የመፈተሻ እስክሪን ውስጥ ሲያልፉ፣ የታየውን የዕቃ ዓይነት ሪፖርት አለማድረጋቸው ወይም እዚያው አለማስቆማቸው ነው፡፡ በስክሪን ውስጥ ስለሚታይ ጥብቅ ቁጥጥር አድርገው ቢሆን ኖሮ እዚያው ሊይዙት ይችሉ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ 

ዕቃውን ያስጫኑትን የአሚድአብ ጄኔራል ቢዝነስ ድርጅት ባለቤትን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ችግሩን የፈጠረው ወይም ቁጥጥሩን በአግባቡ ያልተከታተለው ማን እንደሆነ፣ በአስጫኙ ላይ ለደረሰው ኪሳራ ተጠያቂው ማን እንደሆነ፣ በተለይ ጥብቅ ቁጥጥር መደረግ ያለበት የባህር ላይ ትራንስፖርትን በሚመለከት ምን መደረግ እንዳለበት ማብራሪያ እንዲሰጥ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትን ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ በጋላፊና በሚሌ የፍተሻ ጣቢያዎች እንዴት ኮንቴይነሮቹ ሊያልፉ እንደቻለም ማብራሪያ ለመጠየቅ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዎችን ለማግኘት የተደረገው ጥረትም እንዲሁ አልተሳካም፡፡ 

 

ለመርማሪዎች የይምሰል ጋብቻ ከመፈጸም እስከ ወንጀል ድርጊት መሳተፍ ይፈቅድላቸዋል

-የውጭ ሥራ ስምሪት አዋጅም ለፓርላማው ቀርቧል

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ልዩ የምርመራ ቴክኒኮችን የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ሰኔ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፓርላማ ቀረበ፡፡ 

ረቂቅ አዋጁ ‹‹ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ 

ረቂቅ አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ፣ ምክር ቤቱ ለሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ለማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቶታል፡፡ የረቂቅ አዋጁ መፅደቅ በአስቸኳይ የሚፈለግ መሆኑ በአፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ የተገለጸ ሲሆን፣ ረቂቁ ፓርላማው ማክሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. የሥልጣን ዘመኑን ከማብቃቱ በፊት ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

ረቂቅ አዋጁ በሃምሳ አንቀፆችና በሰባት ምዕራፎችም የተከፋፈለ ነው፡፡ ምዕራፎቹም ጠቅላላ ድንጋጌዎችን፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን፣ የመከላከል፣ የምርመራ፣ የክስና የማስረጃ ሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎችን፣ የተጎጂዎችን ጥበቃ፣ መልሶ ማቋቋምና ካሳ፣ ስለፈንድ መቋቋም፣ የባለድርሻ አካላት ትብብርና ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘ ነው፡፡ 

ረቂቅ አዋጁ በኢትዮጵያ በጥብቅነቱና አወዛጋቢነቱ ከሚታወቀው የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ሁሉ እጅግ የጠበቀ የሚያደርጉ አንቀጾችን ይዟል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱና በዋነኝነት የሚጠቀሰው ልዩ የምርመራ ዘዴዎችን ስለመጠቀም የሚፈቅደው አንቀጽ 18 ይገኝበታል፡፡ 

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎች በባህሪያቸው በቡድን የሚፈጸሙ በመሆናቸው፣ የወንጀል ድርጊቱ ከአንድ አገር በላይ በተደራጀ የወንጀል ቡድን የሚፈጸም በመሆኑ፣ በተለይም ከምልመላ ጀመሮ እስከ መጨረሻው ሒደት ያለው የወንጀሉ አፈጻጸም በቅብብሎሽና በቅንጅት የሚሠራ በመሆኑ፣ በዚህ ወንጀል ውስጥ የሚሳተፉ ተጠርጣሪዎችን በተሟላ ሁኔታ ለመያዝ መደበኛውን የምርመራ ሒደት መጠቀም አዋጭ እንዳልሆነ የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡ 

እነዚህን ወንጀሎች ከሥር ከመሠረታቸው ለመረዳትና በወንጀል ድርጊት አፈጻጸሙ የሚሳተፉ ሰዎችን ማንነት፣ የወንጀሉን ማስረጃ፣ የአፈጻጸም ሥልት፣ የሚፈጸምበትን ሁኔታና ጥቅም ላይ የዋሉ የጉዞ አቅጣጫዎች በአግባቡ ለማወቅና በመረጃ ላይ የተመሠረተ የምርመራ ሒደትን ለማከናወን ልዩ የምርመራ ዘዴዎች መጠቀም እንደሚያስፈልግ ማብራሪያው ያስረዳል፡፡ 

ከእነዚህም ቴክኒኮች መካከል ሰርጎ የመግባት ማለትም በአንድ የተደራጀ የዚህ ወንጀል ቡድን ውስጥ ራሱን የዚያ ድርጊት ደጋፊ በማድረግ፣ በወንጀል ቡድኑ ውስጥ አባል በመሆን መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ማሰባሰብ ይገኝበታል፡፡ 

ሌላኛው ደግሞ በድብቅ ክትትል ማድረግ ወይም ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎችን ቢያንስ በሁለት ዓይነት መንገድ ክትትል ማድረግን እንደሚመለከት ማብራሪያው ይገልጻል፡፡ አንደኛው ዘዴ ተጠርጣሪው ላይ በአካል የሚደረግ ክትትልና መረጃ የመሰብሰብ ሒደት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ እንደ አመቺነቱ የሚኖርበትን አካባቢ፣ ቤት፣ የሥራ ቦታ፣ ወዘተ በድብቅ የስለላ ካሜራዎች በመጠቀም እንቅስቃሴውን የመከታተል ሒደት ነው፡፡ ሌላኛው የምርመራና መረጃ የመሰብሰብ ዘዴ ደግሞ የይምሰል ግንኙነት መፍጠርን የሚመለከት ነው፡፡ ‹‹የይምሰል ግንኙነት ማለት በሕግ ውጤት የሌለው ነገር ግን በወንጀል ድርጊቱ የሚሳተፉ አካላት ላይ ማስረጃ ለማሰባሰብ የሚረዳ ግንኙነት ሲሆን፣ ለምሳሌ የወንጀል ቡድኑ ወንጀሉን ለመፈጸም ገንዘብ የሚያስፈልገው መሆኑ ከታወቀ ቀድሞ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሚገኝ ፈቃድ አንድ ሰው የወንጀል ድርጊቱን በገንዘብ እንዲረዳ በማድረግ ማስረጃ ማሰባሰብ›› መሆኑን የረቂቁ አባሪ ማብራሪያ ይገልጻል፡፡ 

ሌሎች ዓይነቶችን የይምሰል ግንኙነቶችን መፍጠር እንደሚቻልም ማብራሪያው ያትታል፡፡ ከእነዚህም መካከል ‹‹ከተጠርጣሪዎች ጋር ጋብቻ መፈጸም››፣ ‹‹የንግድ ተቋም በጋራ መመሥረት››፣ ወዘተ ሊያጠቃልል የሚችል ሲሆን፣ ዋነኛ ዓላማው ከሌሎች ወገን ወንጀሉን አስመልክቶ መረጃ ለማግኘት ታሳቢ ተደርጎ የሚፈጠር ግንኙነት እንደሆነና በሕግ ፊት ተጠያቂነትን እንደማያስከትል ይገልጻል፡፡

አንድ መርማሪ ሠርጎ በገባበት የወንጀል ቡድን ውስጥ አባልነቱን እንዲቀበሉት፣ የወንጀል ቡድኑ አባላት ይህንን ሠርጎ ገብ መርማሪ በግልጽ ወንጀል እንዲፈጽም ሊያደርጉት እንደሚችሉ የሚያትተው የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ፣ መርማሪው በተግባር ወንጀል እየፈጸመ ቢሆንም ዓላማው ማስረጃ ለማሰባሰብ በመሆኑ በወንጀል እንደማይጠየቅ ያስረዳል፡፡ 

ለዚህም ሲባል መርማሪው አስቀድሞም የወንጀል ነፃ ስምምነት መፈራረም እንደሚኖርበትና ይህን የወንጀል ነፃ መብት አለ በሚል ግን ግድያ ከመፈጸም፣ አስገድዶ መድፈር የመሳሰሉት ከባድ ወንጀሎች መፈጸም እንደሌለበት ያብራራል፡፡ 

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ማለት፣ በአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛን ለማገናኘት ወይም ለሥራ፣ ለሥራ ልምምድ ወደ ውጭ አገር መላክ በሚል ሽፋን የሚፈጸም፣ በጉዲፈቻ ስምምነት በማድረግ ወይም በጉዲፈቻ ሽፋን፣ ወይም በሌላ ማንኛውም መንገድ ለምሳሌ ዛቻን፣ ኃይልን፣ ጠለፋን፣ ማታለልን፣ የተስፋ ቃልን፣ ስለሌላው ኃላፊነት ያለበትን ሰው ፈቃድ ለማግኘት በመደለል፣ ጥቅም በመስጠት ሰዎችን የመመልመል፣ የማጓጓዝ፣ የማዘዋወር፣ የማስጠለል፣ የመቀበል ወንጀል መሆኑን ረቂቅ አዋጁ ይገልጻል፡፡ 

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው የራሱንም ሆነ በይዞታው ሥር ያለውን ቤት፣ ሕንፃ ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ዓላማ ያከራየ፣ እንዲጠቀሙ የፈቀደ ወንጀሉን በመደገፍና በማመቻቸት ተጠያቂ እንደሚሆን ይገልጻል፡፡ 

በተፈጸመ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ድርጊት በተጎጂው ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ወይም ሞት ያስከተለ እንደሆነ ወንጀል አድራጊው ድርጊቱን የፈጸመው በተደራጀ የወንጀል ቡድን አባል በመሆን፣ ቡድኑን በመምራት ወይም በማስተባበር እንደሆነ ወይም ወንጀሉ የተፈጸመው በብዛትና በስፋት ከሆነ ቅጣቱ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም ሞት እንደሚሆን በረቂቁ ተካቷል፡፡

በዚህ ወንጀል ዓይነት ላይ ይርጋ እንደማይኖር የተቀመጠ ሲሆን፣ ማንኛውም ሰው ወንጀል መፈጸሙን ወይም ሊፈጽም መሆኑን የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ለሕግ አካል የማሳወቅ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ በተመሳሳይም ለዚህ የወንጀል ድርጊት ዓላማ የቤተሰቡ አባል የሆነ ሰው ከመደበኛ የመኖሪያ አካባቢው የጠፋ መሆኑን ያወቀ ከሆነ፣ ወዲያውኑ ለሕግ አካል እንዲያሳውቅ ረቂቁ ያስገድዳል፡፡ በዚህ ረቂቅ አዋጅ መሠረት የተከሰሰ ሰው ወንጀሉን ስላለመፈጸሙ ለፍርድ ቤት የማስረዳት ሸክም እንደሚወድቅበትም ይደነግጋል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተመሳሳይ እጅግ በጣም ጥብቅ የሆነ የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅም ለፓርላማው ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀርቧል፡፡ በዚህ ረቂቅ አዋጅ መሠረት ወደ ውጭ አገር በቤት ሠራተኝነት ለመሄድ ቢያንስ የስምንተኛ ክፍል ደረጃ ሊኖር እንደሚገባና ይህንኑም በማስረጃ ማስደገፍን ይጠይቃል፡፡ በተጨማሪም የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መያዝ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ በሠራተኝነት መሄድ የሚቻለው ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ስምምነት ያደረገችባቸው አገሮች ብቻ ነው፡፡ 

በዚህ የሥራና ሠራተኛ የማገናኘት ሥራ ላይ ለመሰማራት የሚፈልጉ ኤጀንሲዎች በግለሰብ ደረጃ ከሆነ አንድ ሚሊዮን ብር ካፒታል እንደሚያስፈልግ፣ በአክሲዮን ደረጃ ከሆነ ደግሞ አምስት ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ረቂቁ ያስረዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ማንኛውም ኤጀንሲ ለሠራተኛው መብትና ደኅንነት ዋስትና ማስከበሪያ የሚውል 100,000 ዶላር ወይም ተመጣጣኙን የኢትዮጵያ ብር በዝግ ሒሳብ በባንክ እንዲያስቀምጥ ይገደዳል፡፡ 

እንዲሁም ሠራተኛን የሚቀጥር አካል ሠራተኞች በሥራ ውል መጣስ ምክንያት የሚያነሱትን የገንዘብ ክፍያ ጥያቄዎች መሸፈን እንዲቻል፣ የውጭ አሠሪዎች የዋስትና ፈንድ እንደሚቋቋምና ለዚሁ ይረዳ ዘንድ እያንዳንዱ ቀጣሪ ለአንድ ሠራተኛ 50 ዶላር ወደ ፈንዱ እንዲያስገባ ይገደዳል፡፡ 

ይህ አዋጅ በተጠናቀቀው የፓርላማው የሥልጣን ዘመን ይፀድቃል ተብሎ የማይጠበቅ ቢሆንም፣ የፓርላማው የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጋራ እንዲያዩት ተመርቶላቸዋል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ስኳር ልማት ኮርፖሬሽን ባለፈው ዓመት ክረምት ተከስቶ የነበረው ዓይነት የስኳር ዕጥረት እንዳያጋጥም፣ በቀናት ውስጥ ከውጭ የገዛውን አንድ ሚሊዮን ኩንታል ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገባ አስታወቀ፡፡

ከውጭ እንደሚገባ ከሚጠበቀው ስኳር በተጨማሪ፣ በሙከራ ምርት ላይ የሚገኙት የተንዳሆና የከሰም ስኳር ፋብሪካዎችም ምርታቸው እንደሚያቀርቡ፣ የኮርፖሬሽኑ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ዘመድኩን ተክሌ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ዘመድኩን እንደሚሉት፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ የሚገባው የስኳር ምርት በአገር ውስጥ ያሉ ፋብሪካዎች በክረምቱ ምክንያት ምርት ቢያቆሙ እንኳ፣ ቅድመ መጠባበቂያ እንዲሆን ከዱባይ የተገዛ ነው፡፡

በተለይ የመተሐራና የወንጂ ስኳር ፋብሪካዎች እስካሁን እያመረቱ ቢሆንም፣ በክረምቱ ምክንያት የሸንኮራ አገዳ አቅርቦት ዕጥረት እንደሚያጋጥም ይጠበቃል፡፡

ይሁን እንጂ በመኩራ ምርት ላይ ያሉት የተንዳሆና የከሰም ፋብሪካዎች የክረምቱ ዝናብ ብዙም ተፅዕኖ ስለማያደርግባቸው፣ በመጠኑም ቢሆን እንደሚያመርቱ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

የወንጂ ስኳር ፋብሪካ የማምረት አቅሙን ወደ 2.2 ሚሊዮን ቶን ለማድረስ ማቀዱን በቅርቡ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ የፋብሪካው ኃላፊዎች እንደገለጹት፣ በተለይ የሸንኮራ ምርት አሁን ካለው ከአምስት ሺሕ ሔክታር ወደ 12,500 ሔክታር ለማሳደግ ታቅዷል፡፡

በከፊል የሙከራ ምርት ከጀመሩት ውስጥ የተንዳንሆና የኩራዝ ስኳር ፋብሪካዎችም ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚጀምሩ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የከሰም ስኳር ፋብሪካ በቀን እስከ 10,000 ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም እንዳለው የገለጹት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው፣ ሆኖም በአሁኑ ወቅት 6,000 ቶን አገዳ በቀን በመፍጨት ሙከራ እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡

 እንደ ስኳር ኮርፖሬሽን መረጃ ከሆነ፣ የከሰም ስኳር ፋብሪካ በ20,000 ሔክታር መሬት ላይ የተንጣለለና በመስኖ ውኃ የሚለማ የአገዳ እርሻ አለው፡፡ ሥራ በሚጀምርበት ወቅት 153 ሺሕ ቶን ስኳር፣ 12,500 ሜትር ኩብ ኤታኖል በዓመት እንደሚያመርት የሚጠበቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር 260 ሺሕ ቶን ስኳርና 30,000 ሜትር ኩብ ኢታኖል፣ እንዲሁም 15 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎም ይጠበቃል፡፡  

 

የሰማያዊ ፓርቲ የዞን አመራር ገድሏል የተባለው ግለሰብ በጽኑ እሥራት ተቀጣ

‹‹ይህ ራስን ማታለልና አገርን ማዋረድ ነው›› የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር

‹‹ቅጣቱ የተሰጠው በፖሊስ ከተጣራና ፍርድ ቤቱም በምስክሮች ካረጋገጠ በኋላ ነው›› የአማራ ክልል መንግሥት

በአማራ ክልል በምሥራቅ ጎጃም ደብረ ማርቆስ ከተማ ውስጥ ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. የተገደለው የሰማያዊ ፓርቲ የዞን አመራርና የሕግ ባለሙያው የአቶ ሳሙኤል አወቀ ገዳይ ነው የተባለ ግለሰብ፣ በ19 ዓመታት ጽኑ እሥራት እንዲቀጣ ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ተሰጠ፡፡ 

 

ፍርዱን የሰጠው የምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ማርቆስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን፣ ሰኔ 8  ቀን 2007 ዓ.ም. ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት አካባቢ ግድያውን መፈጸሙ በምስክሮች ተረጋግጧል የተባለው ፍርደኛ ተቀበል ገዱ ይባላል፡፡ 

የፓርቲው የዞን አመራር አቶ ሳሙኤል በተገደለበት ወቅት የክልሉ መንግሥት በሰጠው መግለጫ፣ አቶ ሳሙኤል የተገደለው ጥብቅና ቆሞለት ከነበረ አርሶ አደር ጋር በፈጠሩት አለመግባባት እንደነበር ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ገዳዩ የቅጣት ማቅለያ እንዲያቀርብ ሲጠይቀው፣ በደብረ ማርቆስ ከተማ ቤት ተከራይቶ የቀን ሥራ እየሠራ ቤተሰቦቹን የሚያስተዳድር መሆኑን በመግለጽ ቅጣቱ እንዲቀልለት ማመልከቱ ተነግሯል፡፡ በመሆኑም ገዳይ መሆኑ የተረጋገጠበት ፍርደኛ፣ ከአርሶ አደርነት እንዴት የቀን ሠራተኛ ሊሆን እንደቻለ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ግራ መጋባታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በዕለቱ በችሎት ከተገኙት ቤተሰቦቹና የችሎቱ ታዳሚዎች እንደተረዱት፣ የወንጀሉ አፈጻጸም አልተገለጸም፡፡ ገደለ የተባለው ግለሰብ ሟችን አያውቀውም ብለው፣ በወቅቱ ወንጀሉን አብረው የፈጸሙ ተባባሪዎች እንዳልተያዙ የተገለጸ ቢሆንም፣ ክትትል ተደርጎ የእነሱ መያዝና አለመያዝ ሳይረጋገጥ፣ በጥድፊያ የቅጣት ውሳኔ መስጠቱ በራሱ የሚያሳየው ነገር እንዳለ አስረድተዋል፡፡ 

የፓርቲያቸው አባል የተገደለበት ሁኔታ የተቀነባበረና ሊድበሰበስ የማይችል መሆኑን የሚገልጹት ሊቀመንበሩ፣ የወንጀል ሒደቱ በትክክል እንዳልተጣራ ፍርድ ቤቱ እንኳን ከሰጠው ፍርድ መረዳት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ 

ሟች አቶ ሳሙኤል አወቀ እነማን እየተከታተሉት እንደሆነ፣ ሊገደል እንደሚችል፣ እሱ ቢሞትም ትግሉ እንደሚቀጥል ጽፎና አሳውቆ መሞቱን የጠቆሙት ኢንጂነር ይልቃል፣ አንድ ሰው የማያውቀውን ሰው ሊገድል እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ ‹‹የተፈጸመው ድርጊት ራስን ማታለልና አገርን ማዋረድ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ቤተሰቦቹና ሕዝቡ በጣም ማዘናቸውንም አክለዋል፡፡ 

ገዳይ ተቀበል ገዱ ወንጀሉን ሲፈጽም የአካባቢው ነዋሪዎች ጮኸው እጅ ከፍንጅ እንደያዙት የገለጹት ደግሞ፣ የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው፡፡ 

በፖሊስ ተጣርቶና ፍርድ ቤቱ በምስክሮች አረጋግጦ ተገቢ ነው ያለውን ቅጣት መወሰኑን የገለጹት ኃላፊው፣ አንዳንድ ወገኖችና የፓርቲው አመራሮች ግድያውን ከፖለቲካ ጋር ለማገናኘት የሚያደርጉት ጥረት ተገቢነት እንደሌለው አስታውቀዋል፡፡ 

ጉዳዩን ከምርጫ ጋር ለማያያዝ ቢሞከርም ሁሉም ነገር ከተጠናቀቀ በኋላ የተፈጸመ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ንጉሡ፣ ሰማያዊ ፓርቲ በምርጫው ያጣውን የኅብረተሰቡን ውሳኔ (ድምፅ) ወደጎን በመተው ሰበብ እየፈለገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሰላማዊውን ሕዝብ ሰላም ለመንሳትና የእርስ በርስ ቅራኔ ለመፍጠር ካልሆነ በስተቀር፣ ወንጀሉን የፈጸመው አካል በምስክር ተረጋግጦበት ቅጣቱን ማግኘቱን አስረድተዋል፡፡ ገዳይ በደብረ ማርቆስ ከተማ ቤት ተከራይቶ የቀን ሥራ በመሥራት ወንድሞቹን እንደሚያስተዳድር አቶ ንጉሡም አረጋግጠዋል፡፡ 

የደብረ ማርቆስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው የጽኑ እሥራት ቅጣት ላይ አስተያየት የሰጡ ደግሞ፣ ድርጊቱ በተፈጸመ በ17 ቀናት ውስጥ የቅጣት ውሳኔ መሰጠቱ ጥሩ ቢሆንም፣ ተመሳሳይ ወንጀል ፈጽመው ለዓመታት ውሳኔ ሳይሰጥባቸው በየማረሚያ ቤቱ ያሉትን ተጠርጣሪዎች ሲያስቡ ግን፣ ጥርጣሬ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡ አንድ ሰው በወንጀል ተጠርጥሮ ሲታሰር፣ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ ዝቅተኛ የሚጠይቀው የምርመራ ጊዜ 14 ቀናት በተለመደበት ሁኔታ፣ ይኼኛው የክስ ሒደት በ17 ቀናት ውስጥ መፈጸሙ ግራ እንዳጋባቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ ንጉሡ ግን ወንጀለኛው እጅ ከፍንጅ የተያዘና ሁሉም ማስረጃ በአንድ ጊዜ በአጭር ቀናት በመሟላቱ፣ ተገቢ ውሳኔ መሰጠቱን ገልጸው አስተያየት ሰጪዎቹን ተቃውመዋል፡፡ 

 

ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመልካም አስተዳደር ዕጦትና ለሙስና ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለውይይት የቀረበው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ቢያቅፍም፣ ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት ሥጋት እንደሆነበት ተገለጸ፡፡ 

ከአብዛኛዎቹ ተሰብሳቢዎች ጐልተው የተነሱ ነጥቦች ይህንን ግዙፍ ብሔራዊ ዕቅድ ለመተግበር፣ ቅድሚያ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ጉዳዮች መፍትሔ ሊያገኙ እንደሚገባ የሚገልጹ ናቸው፡፡ 

አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት፣ በአዲስ አበባና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የመልካም አስተዳደር እጦት ተባብሷል፡፡ ሙስና የዕለት ተዕለት ክስተት እየሆነ መምጣቱ በምሬት ተገልጿል፡፡

መንግሥት የቀረፀው የዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት ስኬት በቀጥታ ከመልካም አስተዳደር ጋር የሚገናኝ በመሆኑ፣ አገርን በማዳን አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ዕርምጃ ሊወሰድ ይገባል በማለት አስተያየት የሰጡ በርካታ ናቸው፡፡

ከጥቂት ቀናት በኋላ የሚጠናቀቀው የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ይዞ መቅረቡ ይታወሳል፡፡ 

ከእነዚህ መካከል አሥር የስኳር ፕሮጀክቶች፣ ከሁለት ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን አዲስ የባቡር መስመር ግንባታ፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብና የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ 

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እነዚህ ፕሮጀክቶች ተስፋፍተው እንደሚቀጥሉ፣ ቀደም ባለው ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ያልነበሩ የፔትሮሊየምና የኬሚካል ፋብሪካዎች ይገነባሉ ቢባልም፣ ከመጀመሪያው ዕቅድ ተነጥሎ ሊታሰብ የሚያስችለው ዓይነተኛ መለያ የለውም ተብሏል፡፡

ይህ ሐሳብ ባለፈው ረቡዕና ሐሙስ በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ በተካሄደው የዕቅድ ሰነድ ውይይት፣ የኢሕአዴግ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የአንድ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ሴኮቱሬ ጌታቸው በሰጡት አስተያየት፣ የመጀመሪያው ዕቅድ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ይዞ በመቅረቡ ብሔራዊ መነሳሳት ፈጥሯል ብለው፣ የአሁኑ ዕቅድ ፕሮጀክቶችን ቢይዝም ከመጀመሪያው ዕቅድ ጋር በግልጽ የተቀመጠ ልዩነት የለውም በማለት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ 

‹‹እኛ የምንከተላቸው ልማታዊ መንግሥታት አንድ ዕቅድ አጠናቀው ሌላ ሲያቅዱ ልዩነቱ በግልጽ ይታያል፤›› በማለት የተናገሩት አቶ ሴኮቱሬ፣ ‹‹እኛም ብሔራዊ መነሳሳት ለመፍጠር ልዩነቱን በግልጽ በማውጣት ብሔራዊ ግብ ልናስቀምጥ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ሴኮቱሬ ቢካተቱ ያሏቸውን ሐሳቦችም ሰንዝረዋል፡፡ ከሰነዘሯው ሐሳቦች ብሔራዊ አገልግሎት አንዱ ነው፡፡ ‹‹በወታደራዊው መንግሥት የሥልጣን ዘመን ብሔራዊ ውትድርና መጥፎ ጠባሳ ጥሎ ቢያልፍም፣ በአሁኑ ወቅት በሩቁ ከምንሸሸው በበጐ ጐኑ ልንጠቀምበት ይገባል፤›› ካሉ በኋላ፣ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት ለተወሰኑ ጊዜያት ወደመጡበት ኅብረተሰብ ተመልሰው እንዲያገለግሉ ቢደረግ ጥቅሙ የጐላ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይህ ሁኔታ ኅብረተሰቡን ከመጥቀሙ ባሻገር ተማሪዎቹ ከፍተኛ ዕውቀት የሚያገኙበት ይሆናል፡፡ በአገራቸው እንዲኮሩም ያደርጋል፤›› ብለዋል፡፡ 

ስብሰባውን ይመሩ የነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ለአቶ ሴኮቱሬ አስተያየት ምላሽ ሲሰጡ፣ የብሔራዊ አገልግሎት ጉዳይ እንደ ስትራቴጂ ሊወሰድ ይችላል ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ይበልጥ በመነጋገር የሚያዋጣውን ማየት ይቻላል ካሉ በኋላ፣ በኢትዮጵያ ይህንን ጉዳይ መተግበር አዋጭ ስለመሆኑ ከባህልና ከታሪክ አንፃር መርመር ያስፈልጋል በማለት አክለዋል፡፡ አቶ ድሪባ ጉዳዩ ከኢሕአዴግ መስመር ጋር ያለውን ልዩነትም አስረድተዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ የምትከተላቸው ሌሎች አገሮች ልማታዊ መንግሥት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ግን ልማታዊ ዴሞክራሲን የምትከተል በመሆኑ ጉዳዩን በጥልቀት ማየት ያስፈልጋል፤›› በማለት አቶ ድሪባ ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ በተካሄደው ስብሰባ አብዛኛዎቹ ተሰብሳቢዎች በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ጥልቅ ሐሳቦች ላይ አስተያየት ከመሰንዘር ይልቅ፣ ብዙም ግንኙነት በሌላቸው የዕለት ተዕለት ጉዳዮች ላይ አስተያየት ሲሰጡ ተስተውለዋል፡፡

በዚህ ጉባዔ የአምስት ዓመቱን ዕቅድ ያቀረቡት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው አዳም ሲሆኑ፣ ከአቶ ድሪባ ጋር መድረኩን የመሩት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው ናቸው፡፡ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ 192 ገጽ ያለው ሲሆን፣ ለውይይት የቀረበው በ65 ገጽ ተጨምቆ መሆኑን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡    

 

ሚድሮክ ጐልድ ምንም ዓይነት የመንግሥት ዕዳ የለብኝም አለ

ዋና ኦዲተር ማስተባበያውን አጣጥሎታል 

የፌዴራል ዋና ኦዲተር በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት፣ የማዕድን ሚኒስቴር የሼክ መሐመድ አል አሙዲ የወርቅ ልማት ኩባንያ ከሆነው ሚድሮክ ጐልድ በሕግ የተወሰነውን ገቢ ባለመሰብሰቡ

፣ አገሪቱ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ አጥታለች ማለቱን የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አርጋ ይርዳው ‹‹ፍፁም ሀሰት›› ነው ሲሉ አስተባበሉ፡፡ ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው፣ የሚድሮክ ጐልድን ማስተባበያ በማጣጣል ማዕድን ሚኒስቴር ያልሰበሰበውን የመንግሥት ገንዘብ አሁንም ገቢ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

በማዕድን አዋጁ 78/2002 መሠረት በከፍተኛ የማዕድን አምራቾች ላይ ስምንት በመቶ የሮያሊቲ ክፍያ፣ እንዲሁም በከፍተኛ የማዕድን አምራች ኩባንያዎች ላይ መንግሥት አምስት በመቶ ነፃ የአክሲዮን ድርሻ እንደሚኖረው ቢደነገግም፣ የማዕድን ሚኒስቴር ከ2004 እስከ 2006 ዓ.ም. ባሉት የበጀት ዓመታት ከሚድሮክ ጐልድ የሰበሰበው የሮያሊቲ ክፍያ አምስት በመቶ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም ከመንግሥት ነፃ የአክሲዮን ድርሻ ሁለት በመቶ ብቻ መሆኑን በማዕድን ሚኒስቴር ላይ በተካሄደው የክዋኔ ኦዲት ቁጥጥር መረጋገጡን ዋና ኦዲተሩ ለፓርላማ ሪፖርት አድርገዋል፡፡ ፓርላማው ካፀደቀው የሮያሊቲና የመንግሥት ድርሻ ምጣኔ ውጪ ሚኒስቴሩ ሚድሮክ ጐልድን በዝቅተኛ ምጣኔ በማስከፈሉ፣ በድምሩ 429 ሚሊዮን ብር ገቢ መንግሥት ማጣቱን ሪፖርት በማድረግ ማዕድን ሚኒስቴር በአገሪቱ ሕግ መሠረት ገቢዎችን እንዳልሰበሰበ ገልጿል፡፡ 

ሪፖርተር ይህንን የዋና ኦዲተሩን የኦዲት ሪፖርት መሠረት በማድረግ በሰኔ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ዕትሙ ዘገባ ያቀረበ መሆኑ ይታወሳል፡፡ የሚድሮክ ጐልድ ዋና ሥራ አስኪያጅና የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ለሪፖርተር በላኩት ደብዳቤ፣ ‹‹ኩባንያው ሕግን አክብሮ ኃላፊነቱን የሚወጣ ድርጅት ነው፡፡ አሥር ሳንቲም የመንግሥት ዕዳ የለበትም፤›› ብለዋል፡፡

ሚድሮክ ጐልድ የማዕድን አዋጅ ቁጥር 52/1985 መሠረት በማድረግ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር የ20 ዓመታት የማዕድን ማውጣት ውል መግባቱን፣ በውሉ መሠረትም አምስት በመቶ የሮያሊቲ ክፍያና ሁለት በመቶ ነፃ የአክሲዮን ድርሻ በኩባንያው ላይ እንዲኖረው መደረጉን በደብዳቤያቸው አብራርተዋል፡፡

ውሉ መሠረት ያደረገበት የማዕድን አዋጅ በአዋጅ ቁጥር 678/2002 ተሻሽሎ በሐምሌ ወር 2002 ዓ.ም. ሥራ ላይ መዋሉን የሚያስታውሰው የዶ/ር አረጋ ደብዳቤ፣ በዚህ አዋጅ ላይ የሮያሊቲ ክፍያ ወደ ስምንት በመቶ እንዲያድግ፣ የመንግሥት ነፃ ድርሻ ሁለት በመቶ እንዲሆንና ለወርቅ ማምረት ሥራ የቀረጥ ነፃ መብት እንዳይፈቀድም መከልከሉን ገልጸዋል፡፡ ይህንን አዋጅ መሠረት በማድረግም የማዕድን ሚኒስቴር ለሚድሮክ ጐልድ እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 24 ቀን 2011 ክፍያዎች በአዲሱ አዋጅ መሠረት እንዲከናወኑ ማሳሰቡን ጠቅሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ቀደም ብሎ ለ20 ዓመታት የተገባን የውል ስምምነት አዲሱ አዋጅ ሊቀይር አይገባም በማለት፣ ሚድሮክ ጐልድ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ለሦስት ዓመታት የተከራከረ መሆኑንና በመጨረሻም ሚኒስቴሩ በሚድሮክ ጐልድ አቋም መስማማቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ጥር 28 ቀን 2005 ዓ.ም. መላኩን ገልጸዋል፡፡ በደብዳቤው መሠረትም ሚድሮክ ጐልድ በገባው ውል መሠረት እንዲቀጥል መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ዋናው ኦዲተር ሪፖርቱን ለፓርላማ ከማቅረቡ በፊት ሙያው በሚጠይቀው መሠረት ከማዕድን ሚኒስቴር ወይም ከሚድሮክ ጐልድ ማግኘት የሚችለውን ሰነድ ሳይመረምር የሰጠው መግለጫ፣ በኩባንያው ላይ ተገቢ ያልሆነ ገጽታ እንዲያጠላበት በማድረጉ ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ ‹‹በሚድሮክ ጐልድ ላይ የኦዲት ቁጥጥር አናደርግም፡፡ ቁጥጥር ያደረግነው በማዕድን ሚኒስቴር ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ቢሆንም በኦዲት መርህ መሠረት ተገቢው ምርመራ በሚኒስቴሩ ላይ መደረጉንና ለ20 ዓመታት የተደረገውን ውል መሠረት በማድረግ ተደርጐ የነበረውን ክርክርና የተሰጠውንም እልባት መመርመራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ፓርላማው ያወጣውን ሕግ ማዕድን ሚኒስቴር በደብዳቤ ሊቀይረው አይችልም፡፡ ፓርላማው ራሱ በአዋጁ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኃላፊነት ደግሞ የመንግሥት ተቋማት ሕግን አክብረው መሥራታቸውን ተቆጣጥሮ ለፓርላማው መረጃ ማቅረብ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ማዕድን ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 678/2002 አንቀጽ 81 ላይ፣ ‹‹ይህ አዋጅ በሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት የተሰጠ ፈቃድ ወይም የተደረገ የማዕድን ስምምነት ከዚህ አዋጅ ጋር እስካልተቃረነ ድረስ ፀንቶ ለሚቆይበት ቀሪ ዘመን ተፈጻሚነቱ ይቀጥላል፤›› የሚለውን አንቀጽ ተላልፏል ብለዋል፡፡

በኦዲቱ ወቅት የሚድሮክን ጥያቄም ሆነ ሚኒስቴሩ የሰጠውን ምላሽ የኦዲት ቡድኑ ማየቱን የገለጹት ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ፣ ‹‹ተቀባይነት ያለው አሠራር አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ማዕድን ሚኒስቴር ይህንንና ሌሎች በኦዲት የተለዩ የአሠራር ችግሮቹን ለማስተካከል የድርጊት መርሐ ግብር አውጥቶ ለዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት መላክ የሚኖርበት መሆኑንና መንግሥት ከሚድሮክ ጐልድ ያጣውን ገንዘብ ማስከፈል አለበት በማለት አስታውቀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፓርላማው በ2006 ዓ.ም. በማዕድን አዋጁ ላይ ባደረገው ማሻሻያ፣ በኢትዮጵያ በከፍተኛ የማዕድን ልማት ብቸኛ የሆነውን ሚድሮክ ጐልድ የመከራከሪያ ነጥብ የተገነዘበ ማስተካከያ አድርጓል፡፡ 

የማሻሻያ አዋጁ 816/2006 በአንቀጽ 9 ‹‹ይህ አዋጅ በሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት የተሰጠ ወይም የተደረገ ማንኛውም የማዕድን ማምረት ፈቃድ ወይም የማዕድን ማምረት ስምምነት ፀንቶ ለሚቆይበት ቀሪ ዘመን፣ ፈቃዱ በተሰጠበት ወይም ስምምነቱ በተደረገበት ወቅት ተፈጻሚ በነበረው ሕግ መሠረት ባለበት ይቀጥላል፡፡ ሆኖም በፈቃዱ ወይም የስምምነቱ ዘመን አብቅቶ ሲታደስ በዚህ አዋጁ ድንጋጌዎች መሠረት ይፈጸማል፤›› የሚል ማስተካከያ አድርጓል፡፡ 

  

 

 

የአካባቢና የደን ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው ጠቋሚ ዕቅድ የሙቀት አማቂ ወይም በካይ ጋዞች (ግሪን ሐውስ ጋዝ) ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁበትን መጠን በመቀነስ፣ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ 147 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ላይ እንዲገደቡ ለማድረግ ማቀዱን አስታወቀ፡፡ 

 

ሚኒስቴሩ ባለፈው ሐሙስ ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ለውይይት ባቀረበው የአምስት ዓመት ሰነድ ላይ በአገሪቱ ለበካይ ጋዞች ወይም ለሙቀት አማቂ ጋዞች መለቀቅ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ዘርፎች ላይ የሚሠሩ ሥራዎች፣ የልቀት መጠኑን ለመቀነስ እንደሚያስችሉ አመላክቷል፡፡ የአካባቢና ደን ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑርመደድ ጀማል ባቀረቡት የአምስት ዓመት መነሻ ዕቅድ መሠረት፣ በአገሪቱ ለሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት መካከል የደን መጨፍጨፍ፣ የአፈር መከላትና መሸርሸር፣ የጋማ ከብቶች ሲያመሰኩና እበት ሲጥሉ የሚመነጩ ጋዞች፣ የኢነርጂ ዘርፍና የመጓጓዣ ዘርፍ የሚያመነጩት፣ የኢንዱስትሪና የከተሞች መስፋፋት ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው፡፡ 

በመሆኑም እንስሳት ያመነጩታል ተብሎ የሚጠበቀውን የ88 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ልቀት ወደ 44 ሚሊዮን መቀነስ ከታቀዱት መካከል ይገኝበታል፡፡ በአፈር መከላትና መሸርሸር ምክንያት 40 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ጋዝ ይለቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ በመሆኑ፣ ሚኒስቴሩ ይህንን መጠን ወደ 12 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዝቅ የማድረግ ዕቅድ አስቀምጧል፡፡ 

መንግሥት ከአራት ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ ይፋ ያደረገው የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተነሳው ስትራቴጂ አካል የሆነው የመጪዎቹ አምስት ዓመታት ዕቅድ፣ በጠቅላላው በ147 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የበካይ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስ ተነስቷል፡፡ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂው እንዳሰፈረው ከሆነ፣ እ.ኤ.አ. እስከ 2030 ባለው ጊዜ ውስጥ ሊመነጭ ይችላል ተብሎ የሚታሰበው ሙቀት አማቂ ጋዝ መጠን 400 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነው፡፡ ሆኖም ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ በየዓመቱ እየመነጨ የሚገኘው በካይ ጋዝ መጠን 150 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደሚገመት አስፍሯል፡፡ 

አቶ ኑርመደድ እንዳስታወቁት፣ በኢትዮጵያ የሚመነጨው የሙቀት አማቂ ጋዝ መጠን 0.3 በመቶ በመሆኑ ከዓለም አኳያ ያለው ድርሻ ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህም ቢባል ግን የአገሪቱን የልቀት መጠን በታቀደው ዝቅተኛ መጠን ለማቆየትና በመጨረሻም ወደ ዜሮ ለማውረድ መንግሥት ያለፉት አምስት ዓመታትን ጨምሮ፣ በሃያ ዓመት ውስጥ 150 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው በአረንጓዴ ስትራቴጂው ማስፈሩ አይዘነጋም፡፡

 በሌላ በኩል መንግሥት ለመሠረተ ልማት ግንባታ ብቻ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ 50 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገው እንደነበር በአረንጓዴ ስትራቴጂ ሰነድ ላይ ያሰፈረ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱም ጠቅላላ ዕቅዱን ለማስፈጸም ከ75 እስከ 79 ቢሊዮን ዶላር በጅቶ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ በተጠናቀቀው የአምስት ዓመት ዕቅድ ዘመን ውስጥ  ከዚህን ያህል ገንዘብ ውስጥ ምን ያህሉ እንደተገኘና ሥራ ላይ እንደዋለ መንግሥት ማብራሪያ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡  

 

ለሁለት ቀናት በሸራተን አዲስ ሲካሄድ ቆይቶ የተጠናቀቀውን ጉባዔ በማስመልከት በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ተጨማሪ ፋይናንስ በማቅረብ ኢትዮጵያ የምትገነባቸውን ፕሮጀክቶች እንደምትደግፍ ቻይና ይፋ አደረገች፡፡ 

የቻይና ልማት ባንክ የዓለም አቀፍ ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዳሬክተር ሺ ጂያንግ ከዓለም ባንክ ተጠሪ፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) ጋር በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት እንዳስታወቁት፣ ኢትዮጵያ ለምታካሂዳቸው የመሠረተ ልማትና የልማት ፕሮጀክቶች ባንካቸው ተጨማሪ ፈንድ ለመልቀቅ ዝግጁ ነው፡፡ 

በዚህም መሠረት ለኢንዱስትሪ ዞኖች ግንባታ፣ ለባቡር ትራንስፖርት፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫና ማስተላለፊያ የሚውል ፋይናንስ ለኢትዮጵያ እንደሚቀርብ ጂያንግ አስታውቀዋል፡፡ ጂያንግ ለጋዜጠኞች ሲያብራሩ፣ መንግሥታቸው በአፍሪካ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም በመሆኗ በተለይ ለኢንዱስትሪ ዞኖች ግንባታ የምታውለው ፋይናንስ ከቻይና ልማት ባንክ እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡ 

ሊለቀቅ የሚችለው የገንዘብ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ከመግለጽ የተቆጠቡት ጂያንግ፣ በተለይ በቅርቡ ፈንድ ሊያገኝ ይችላል ያሉት የኢንዱስትሪ ዞን የትኛው እንደሆነ መግለጽ አልፈለጉም፡፡ ሆኖም በድሬዳዋ የሚገነባው ኢንዱስትሪ ዞን ሊሆን እንደሚችል ፍንጮች ታይተዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ ይፋ የተደረጉ መረጃዎች እንደጠቆሙት፣ በሐዋሳ ለሚገነባው የኢንዱስትሪ ዞን የ250 ሚሊዮን ዶላር ፋይናንስ ከቻይና ተገኝቷል፡፡ በቦሌ ለሚ ለተገነባው የኢንዱስትሪ ዞን የዓለም ባንክ የ250 ሚሊዮን ዶላር ብድር መልቀቁ ይታወሳል፡፡ 

በርካታ የቻይና ኢንቨስተሮችና ባለሥልጣናት እንዲሁም ምሁራን የተሳተፉበት ጉባዔ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ሲካሄድ፣ ‹‹ኢንቨስት ኢን አፍሪካ ፎረም›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነው፡፡ በየዓመቱ በቋሚነት እንዲካሄድ ስምምነት መደረጉን፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አህመድ ሺዴ አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ቻይና ለአፍሪካ የምትሰጠውን የልማት ፋይናንስ በዚህ ዓመት ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር ማሳደጓን አስታውቃለች፡፡ እስካሁን ለአፍሪካ አገሮች የልማት ድጋፍ በብድር ሲሰጥ የቆየው የገንዘብ መጠን ሦስት ቢሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት መጨረሻ ወደ አምስት ቢሊዮን ማደጉን ጂያንግ ይፋ አድርገዋል፡፡ 

በአፍሪካ የቻይና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እያደገ መምጣቱ ቢነገርም፣ ከዚህ ይልቅ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የንግድ መጠን ነው፡፡ የቻይና ኩባንያዎች በአፍሪካ ኢንቨስት ያደረጉት መጠን ከአራት ቢሊዮን ዶላር እንደማይበልጥ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በአንፃሩ ለቻይና በሚያደላው የንግድ ልውውጥ ከ220 ቢሊዮን ዶላር በላይ ግብይት እንደሚፈጸም የቻይና ልማት ባንክ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ 

በኢትዮጵያ በቀጥታ ኢንቨስት ካደረጉ ኩባንያዎች መካከል ኋጂዬን ግሩፕ፣ ሐንሰም ኢንተርናሽናል ግላስ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ፣ እንዲሁም በቅርቡ ወደ አገር ውስጥ የገባው ጆርጅ ሹ ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ለሙከራ ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን እንዴት ልታስተናግድ እንደምትችል ለመገምገም ሲባል የመጡ መሆናቸውን ጂያንግ ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ ኩባንያዎች ኢንቨስትመንት ፈተናዎች አጋጥመዋል ያሉት ጂያንግ የጉምሩክ፣ የኃይል አቅርቦት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የአስተዳደርና የሰው ኃይል፣ የገበያና የቴክኖሎጂ ችግሮች ማጋጠማቸውን አስታውቀዋል፡፡ 

አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው፣ አገሪቱ ለኢንዱስትሪ መስክ ጀማሪ በመሆኗ ያጋጠሙ ችግሮች እንዳሉ፣ በተለይ በኢንዱስትሪ ዞን ግንባታና አስተዳደር ላይ ከዜሮ በመነሳት ልምድ ለማካበት እየሞከረች መሆኗን ጠቅሰው፣ የቻይና ኢንቨስትሮች መምጣት መጀመራቸውንና ወደፊትም እየተበራከቱ እንደሚመጡ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

 

የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ለ40 ዓመታት የራሱ ያደረገው ንብረት ለባለቤቶቹ እንዲመለስ ተወሰነ

በደርግ መንግሥት ከ13 ዓመታት በላይ ታስረው ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠር በ1983 ዓ.ም. ከእስር የተፈቱት አምባሳደር ታደለች ኃይለ ሚካኤልና ቤተሰቦቻቸው፣ ለ40 ዓመታት በመንግሥት እጅ የነበረን

ንብረታቸውን በፍርድ ቤት ክርክር በመርታታቸው እንዲመለስላቸው ፍርድ ተሰጠ፡፡

በአዋጅ 47/67 ተወርሶ ንብረትነቱ ለመንግሥት እንደተዘዋወረ በመግለጽ፣ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በእነአምባሳደር ታደለች የቀረበበትን ክስ ያስተባበለ ቢሆንም፣ ያቀረባቸው ማስረጃዎች ፍርድ ቤቱን ሊያሳምኑ ባለመቻላቸው፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት፣ ንብረቱን ለከሳሾች እንዲያስረክብና በክስ ሒደቱ ወቅት ያወጡትን ወጪና ኪሳራ እንዲከፍል ፈርዶበታል፡፡ 

እነአምባሳደር ታደለች ከሁለት ዓመታት የፍርድ ቤት ክርክር በኋላ አሸናፊ ሆነው ፍርድ ያገኙበት የንብረት ክርክር የጀመረው፣ ደርግ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅን ካወጀ ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በአባታቸው አቶ ዋኬኔ ፊሊጶስ (በኋላ ኃይለ ሚካኤል ፊሊጶስ ተብሏል) ነበር፡፡

የኅብረተሰባዊ ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት በ1967 ዓ.ም. ባወጣው የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅ ቁጥር 47/67 መሠረት፣ ማንኛውም ትርፍ ቤት ያለው ነዋሪ አንዱን መርጦ እንዲወስድ ሲደረግ፣ አቶ ኃይለ ሚካኤል በአሁኑ አራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ ወደ እሪ በከንቱ መውረጃና ወደ እቴጌ ጣይቱ ሆቴል መታጠፊያ አካባቢ የሚገኘውን ቤታቸውን (የአሁኑ ፓርክ ሆቴልን) ይመርጣሉ፡፡ በወቅቱ ቤቱ ኮሎኔል ሥዩም ኃይሌ የሚባሉ ባለሥልጣን ይኖሩበት ነበር፡፡ ቤቱ በባለሀብቱ የተመረጠ መሆኑ ተገልጾ ለኮሎኔል ሥዩም እንዲለቁ ደብዳቤ ይጻፍላቸዋል፡፡ አቶ ኃይለ ሚካኤል የመረጡት ቤት እስከሚለቀቅላቸው ድረስ፣ 160 ብር እየከፈሉ ተከራይተው ይኖሩበት የነበረው ቤት ኪራይ እንዲቆምም ተደርጓል፡፡ ኪራዩ እንዲቆም የተደረገው በሥራና ቤቶች ሚኒስቴር የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ነው፡፡ ቤቱን የያዙት ኮሎኔል ሥዩም ኃይሌ ግን ቤቱን ሊለቁ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ 

በሌላ በኩል ኮሎኔሉ ቤት አለቅም ቢሉም፣ አቶ ኃይለ ሚካኤል ለጊዜው የሚኖሩበት ቤት ለሌላ ሰው ሊሰጥ መሆኑ ተገልጾ ቤቱን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ይደርሳቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ከማስጠንቀቂያው ቀን በኋላ አቶ ኃይለ ሚካኤልን ከቤት አስወጥተው እንዳይጥሏቸው ሲባል በአስቸኳይ ቤት ተፈልጐ እንዲሰጣቸው፣ ለከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ኃላፊ ለነበሩት አቶ ኃይሌ ተድላ ደብዳቤ እንደተጻፈላቸው ለፍርድ ቤቱ በማስረጃነት የቀረቡ ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ከላይ የተጻፉ ማስረጃዎች በእነአምባሳደር ታደለች በኩል የቀረቡ ሰነዶች መሆናቸውን ፍርድ ቤቱ በፍርዱ ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱ በደረሰበት ድምዳሜ በ1969 ዓ.ም. እና በ1978 ዓ.ም. የተሰጡ የሰነድ ማስረጃዎች (በተለያዩ የመንግሥት አካላት) የሚያመለክቱት ቤቱ የአቶ ዋኬኔ (ኃይለ ሚካኤል) ፊሊጶስ መሆኑን እንደሆነ ገልጿል፡፡

አቶ ኃይለ ሚካኤል ሕይወታቸው እስካለፈበት 1972 ዓ.ም. ድረስ የመረጡትና እንዲረከቡ የተወሰነላቸውን ቤት ማግኘት አልቻሉም፡፡ እሳቸውን በመተካት ባለቤታቸው ወ/ሮ ብርአልጋ አንብሬ ክርክራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ነገር ግን በ1978 ዓ.ም. ደግሞ ቤቱ መኖሪያ ቤት ሳይሆን ድርጅት መሆኑ ተገልጾ፣ ጉዳዩ እስከሚጣራ በሚል ለአቶ ኃይለ ሚካኤል ቤተሰቦች አንድ ቤት ተመርጦ እንዲሰጣቸው ትዕዛዝ ተላለፈ፡፡ 

ተከሳሽ የሆነው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ (ኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት) ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 47/67 የተወረሰ መሆኑን የሚያስረዱለትን ማስረጃዎች ማቅረቡንም ፍርዱ ይገልጻል፡፡ በወቅቱ ቤቱ እንዲመለስላቸው ለከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አቤቱታ አቅርበው፣ በ1982 ዓ.ም. መመለስ እንደማይቻልና ማካካሻ ግምት እንዲሰጣቸው መወሰኑን የሚያሳይ ሰነድ ለፍርድ ቤቱ ማቅረቡንም አስረድተዋል፡፡

ኤጀንሲው ያቀረበው ሰነድ ግን አቶ ኃይለ ሚካኤል ወይም ቤተሰቦቻቸው ያቀረቡት ሰነድ ሳይሆን፣ ቤቱን አለቅ ብለው አሻፈረኝ ያሉት የኮሎኔል ሥዩም መሆኑን እንደሚያስረዳ ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ቤቶች ኤጀንሲ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 47/67 የተወረሰ መሆኑን የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ሥራ አመራር ቦርድ ማረጋገጡን ገልጾ ሰነድ ያቀረበ ቢሆንም፣ ሰነዱ የሚያስረዳው ግን ስለቤቱ የተነሳው ጉዳይ ለኤጀንሲው ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ መሆኑን ጠቅሶ መዝገቡን እንደዘጋው መሆኑን ፍርድ ቤቱ ጠቅሷል፡፡

አዋጅ ቁጥር 47/67 አንቀጽ 16(1) የሚደነግገው፣ በአንድ ከተማ ውስጥ ከአንድ መኖሪያ ቤት ውጪ ትርፍ ቤት ያለው ሰው፣ በራሱ ፍላጐት አንድ መኖሪያ ቤት በመምረጥ መልሶ መረከብ እንደሚችል ነው፡፡ የንግድ ቤት ወይም ከአንድ ቤተሰብ በላይ የሚያስተናግድ መሆኑ በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የተረጋገጠ ከሆነ፣ የማይመለስና ማካካሻ የሚሰጥ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ጠቅሷል፡፡

በመሆኑም ቤቶች ኤጀንሲ ቤቱ የንግድ እንደሆነና ከሳሾች ማካካሻ እንዲወስዱ የተከራከረ ቢሆንም፣ ማስረጃ አለማቅረቡን ገልጿል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 47/67ም ቤቱን እንደመረጡና ለአቶ ኃይለ ሚካኤል እንደተወሰነላቸው እንጂ፣ ንግድ ቤት ስለመሆኑ ምንም ያለው እንደሌለ አስረድቷል፡፡ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲም ማረጋገጡን አክሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ በአጠቃላይ ከሳሾች ካቀረቡት የሰነድ ማስረጃ አኳያ ከሳሾች ቤቱን በውርስ ያገኙት ስለመሆኑ መገንዘቡን አውስቷል፡፡

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 14ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ሰኔ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. የአቶ ኃይለ ሚካኤል ፊሊጶስ ወራሾች፣ አምባሳደር ታደለች ኃይለ ሚካኤልና አቶ ዓለማየሁ ኃይለ ሚካኤል ንብረቱ ይገባቸዋል የሚል ፍርድ የሰጠው ባደረገው የሰነዶች ምርመራ ነው፡፡ 

ክሱ በ2005 ዓ.ም. ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍትሐ ብሔር ችሎት ቀርቦ ተከሳሽ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ፣ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 47/67 የተወረሰ መሆኑንና ከሳሾች ወራሾች ባልሆኑበት የመንግሥት ንብረት መከራከር እንደማይችሉ ገልጾ ያቀረበውን መከራከሪያ ሰምቶ፣ ሐምሌ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. ክሱን ውድቅ አድርጐት ነበር፡፡ በክሱ ላይ ግን ከሳሾች አሁን ፍርድ እንዲያገኙ ያደረጓቸው ሰነዶችን አያይዘው አቅርበው ነበር፡፡

እነአምባሳደር ታደለች ግን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለታቸው፣ ፍርድ ቤቱ ሰኔ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ብይን ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን እንደገለጸው፣ ከሳሾች ያቀረቧቸው ሰነዶች ቤቱ በአቶ ዋኬኔ (ኃይለ ሚካኤል) ፊሊጶስ ስም ነው፡፡ በመሆኑም ወራሾች የአቶ ዋኬኔ ፊሊጶስ ወራሾች ናቸው፡፡ በመሆኑም ክሱ ውድቅ የሚሆን ባለመሆኑና ብይኑ ግድፈት ያለበት መሆኑን በመጥቀስ፣ የሥር ፍርድ ቤት ወደ ፍሬ ነገሩ በመግባት ሁለቱን ወገኖች አከራክሮ ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥ በማዘዝ መዝገቡን መመለሱን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ ክሱ የተመለሰለት የሥር ፍርድ ቤት (አሁን ፍርድ የሰጠው ፍርድ ቤት) አምስት ጭብጦችን ይዟል፡፡ ከሳሾች ባለቤት መሆን አለመሆናቸውን፣ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 47/67 መወረስ አለመወረሱን፣ ካልተወረሰ ተከሳሽ ለከሳሾች ቤቱን ማስረከብ አለበት የለበትም፣ በኤጀንሲውና ቤቱን በተከራየው ሁለተኛ ተከሳሽ አሁን ቤቱን ፓርክ ሆቴል ብሎ እየሠራበት ያለውና ከኤጀንሲው የተከራየው ነጋዴ መካከል ያለው የኪራይ ውል ካልፈረሰ፣ ቤቱን ለከሳሾች ማስረከብ አለበት የለበትምና ወራሾች የቤቱ ባለቤት ስለመሆናቸው የግድ በአዋጅ ቁጥር 47/67 መሠረት ማስረዳት አለባቸው የለባቸውም የሚሉ ጭብጦችን በመያዝ፣ ከላይ የተዘረዘሩትን ምርመራዎች በማድረግ ፍርድ መስጠቱን ሰነዶቹ ያብራራሉ፡፡ ኤጀንሲው ቤቱን እንዲያስረክብ፣ የወጪና ኪሳራም ተሰልቶ ሲቀርብ እንዲከፍል ተፈርዶበታል፡፡     

 

ሰበር ዜና፡- ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሆነው ተሾሙ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሊቀ መንበር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሆነው ተሾሙ፡፡

ዶ/ር አዲሱ የምርጫ ቦርድ ምክትል ሊቀ መንበር በመሆን ያለፉትን ሁለት አጠቃላይ ምርጫዎች ያገለገሉ ሲሆን፣ ገዢው ፓርቲና አጋሮቹ 547ቱንም የፓርላማ መቀመጫ ያሸነፉበትን የ2007 ዓ.ም አጠቃላይ ምርጫ በመምራት በሕግ የተፈቀደላቸውን የሥልጣን ዘመን አጠናቀዋል፡፡ 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ የዶ/ር አዲሱን፣ የምክትል ኮሚሽነርና የኮሚሽን አባላት ሹመት በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሆነው ላለፉት አምስት ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና በዶ/ር አዲሱ ተተክተዋል፡፡

   

በርካታ ድርጅቶች በግል ጡረታ አዋጅ ማሻሻያ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ለፓርላማ አቀረቡ

በርካታ የግል ድርጅቶችና የሲቪክ ማኅበራት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቀረቡ፡፡ የምክር ቤቱ የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማሻሻያውን አስመልክቶ

ባዘጋጀው የሕዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ ላይ የተጋበዙ ከ300 በላይ የሚሆኑ የግል ድርጅቶችና ሲቪክ ማኅበራት፣ ማሻሻያውን ያረቀቀው የግል ድርጅት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ባለድርሻ አካላትን ሳያነጋግር ወይም ሳያወያይ ይህንን ረቂቅ ማሻሻያ ለፓርላማ ማቅረቡ ፍፁም ተገቢ አይደለም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ 

በዋናነት ከተካተቱት ማሻሻያዎች መካከል በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 715/2003 ቀደም ሲል የፕሮቪደንት ፈንድ ሥርዓት በፈቃደኝነት እንዲቀጥል ቢወሰንም፣ በማሻሻያው ግን ወደ ግል ሠራተኞች ጡረታ ፈንድ ይዞራል የሚለው ይገኝበታል፡፡ 

ይህ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ከቀረበ በኋላ ግን አርቃቂው አካል የግል ድርጅት ሠራተኞች ማኅበራዊ ኤጀንሲ ማሻሻያውን በድጋሚ በማየት ፕሮቪደንት ፈንዱ በቀጥታ ይዞራል ወይም የተጠራቀመው ገንዘብ ወደ ጡረታ ፈንድ ይገባል የሚለው እንዲስተካከል ማድረጉን የኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎች በውይይቱ መጀመርያ ላይ ተናግረዋል፡፡ 

በውይይቱ እንዲገኙ የተጋበዙት ድርጅቶች በሙሉ ሠራተኞቻቸውን በፕሮቪደንት ፈንድ ዋስትና የሚያስተዳድሩ በመሆናቸው፣ በመጀመርያ እፎይታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ይገኙበታል፡፡ 

‹‹ይህንን ማሻሻያ በመስማቴ ደስ ብሎኛል፤›› ያሉት ዶ/ር አረጋ መንግሥት ስለ ግል ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ማሰብ ከመጀመሩ በርካታ ዓመታት ቀደም ብሎ፣ የግል አሠሪዎችና ሠራተኞቻቸው ተነጋግረው ፕሮቪደንት ፈንድ ሥርዓትን መፍጠራቸውን አስታውሰዋል፡፡ 

‹‹ስለዚህ ፕሮቪደንት ፈንድ የአሠሪና የሠራተኛው የግላቸው ነው፡፡ ማንም ሌላ ሰው ሊወስንበት አይችልም፤›› ብለዋል፡፡ በዚህም መልክ መወሰኑን ጥሩ ነው ብለዋል፡፡

ሲአርዲኤ የተባለው የሲቪክ ማኅበራት ጥላ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ዶ/ር መሸሻ ሸዋረጋ፣ በተመሳሳይ የማሻሻያ አዋጁ አርቃቂዎች ባለድርሻ አካላትን አወያይተናል በማለት ያቀረቡት ሪፖርት ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ 

በሲአርዲኤ ሥር ከ350 በላይ ሲቪክ ማኅበራት የሚገኙ መሆኑንና ኢትዮጵያ ከዚህ ዘርፍ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደምታገኝ አስታውሰው፣ ይህንን ዘርፍ እንደ ባለድርሻ አካል ሳያወያዩ ሪፖርት ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

የአዋጁ አርቃቂዎች ባለድርሻ አካላትን አወያይተናል የሚሉት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽንና የአሠሪዎች ፌዴሬሽን ነው፡፡ 

‹‹ዛሬ በድፍረት መናገር ያለብኝ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ተቋማት እንደማይወክሉን ታውቃላችሁ፡፡ እንዲያውም ለመንግሥት ነው የሚሠሩት፤›› ሲሉ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ተችተዋል፡፡ 

ዶ/ር መሸሻ ፕሮቪደንት ፈንድን በቀጥታ ወደ ጡረታ እንዳይዞር በመጨረሻ መወሰኑን ተቀብለዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ ፕሮቪደንት ፈንድ ምንም እንዳልሠራ መቆጠር የለበትም፡፡ በ2003 ዓ.ም. እንደተፈቀደው ሁሉ አሁንም በሠራተኞች ምርጫ ሊቀጥል ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ 

የሲቪክ ማኅበራት ፀባይ ከሌሎቹ ስለሚለይ ሠራተኞች የሚቆዩት ፕሮጀክቶች እስካሉ ድረስ ብቻ ስለሆነ፣ ፕሮጀክቶች ሲያበቁ እንደሚሰናበቱ አስታውሰዋል፡፡ 

ዶ/ር መሸሻ ሠራተኞች በሚሰናበቱበት ጊዜ ለሥራ መፈለጊያም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደሪያ ሆኖ የሚያገለግለው ፕሮቪደንት ፈንድ በመሆኑ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡ ምክንያቱም እንደ ሌላው አገር ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ‹ኢምፕሎይመንት ፈንድ› ወይም ሥራ አጥ በሚኮንበት ወቅት የኑሮ ዋስትና አለመኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹እኛ አገር ይህ ባለመኖሩ ፕሮቪደንት ፈንድን ይዞ መቀጠል ምን ችግር አለው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ 

የሴንተር ፎር ዲስኤቢሊቲስ ዴቨሎፕመንት ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሤ በበኩላቸው፣ ‹‹የፕሮቪደንት ፈንድ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ምክንያቱም በተለይ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ወጣቶች እስከ 60 ዓመት ዕድሜያቸው በተቀጣሪነት ቆይተው የጡረታ ተከፋይ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትን ወክለው የተገኙት የሕግ ባለሙያው አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል፣ ‹‹የፕሮቪደንት ፈንድ ማኅበራዊ ዋስትና ሥርዓት የራሱ ደካማ ጎኖች አሉት፡፡ እነዚህ ደካማ ጎኖች ግን መንግሥት ለፕሮቪደንት ፈንድ ጥበቃ ለመስጠት ኃላፊነት ባለመውሰዱ የተከሰቱ ችግሮች እንጂ የግሉ ዘርፍ የፈጠረው አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ፕሮቪደንት ፈንድ ለግሉ ዘርፍ ትልቅ ዋስትና ነው፡፡ አሠሪው ለሠራተኛው ዋስትና እንዲኖረው የሚያደርግ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ምክትል ፕሬዚዳንት በበኩላቸው፣ ኮንፌዴሬሽኑ ከኤጀንሲው ጋር በተወያየበት ወቅት ፕሮቪደንት ፈንድን በተመለከተ ኮንፌዴሬሽኑ ያቀረበው ሐሳብ የጡረታ ዐቅድ እየሰፋ በሄደ ቁጥር ፕሮቪደንት ፈንድ እየተዋጠ እንደሚሄድ፣ በመሆኑም በራሱ ጊዜ ሊሞት ስለሚችል መነካካት አያስፈልግም የሚል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ 

አሁንም ቢሆን ፕሮቪደንት ፈንድን የማይፈልጉ ድርጅቶች ብቻ ወደ ጡረታ በምርጫቸው እንዲመጡ መደረግ እንዳለበት ኢሠማኮ እንደሚያምን ተናግረዋል፡፡ ሌሎች በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦችም ፓርላማው ይህንን አዋጅ በዚህ ዓመት ሊያፀድቀው እንደማይገባ ተከራክረዋል፡፡ 

ይህንን ያሉበት ምክንያት የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 19 ላይ የተደረገው ማሻሻያን በመቃወም ነው፡፡ አንቀጹ ‹‹በተቀጠረ ሦስት ዓመት ወይም ከዚህ ባነሰ ጊዜ ውስጥ በጡረታ የሚገለል ሠራተኛ፣ በጡረታ ከሚገለልበት ወር ሦስት ዓመት አስቀድሞ ባለው ወር ሲከፈለው ከነበረው መደበኛ የወር ደመወዝ በ25 በመቶ የሚበልጥ ዓመታዊ አማካይ የደመወዝ ጭማሪ ያገኘ እንደሆነ፣ በየዓመቱ 25 በመቶ ያለው የደመወዝ ጭማሪ ብቻ በደመወዙ ላይ ተደምሮ የሦስት ዓመት አማካይ የወር ደመወዙ ተይዞ ይታሰባል፤›› ይላል፡፡ 

ይህንን የተቃወሙት የድርጅት ተወካዮቹ አገሩን በዝቅተኛ ደመወዝ ሲያገለግሉ የነበሩ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ ወታደሮችንና የመሳሰሉትን የሚጎዳ ነው ሲሉ ተቃውመዋል፡፡ በዕድሜው መጨረሻ ላይ የተሻለ ገንዘብ ቢያገኝ ለአገሩ ያበረከተውን በገንዘብ የማይለካ አስተዋጽኦ ወደጎን በመተው፣ 25 በመቶ ጭማሪውን ብቻ ማሰብ ተገቢ አይደለም በማለት ተቃውመዋል፡፡ 

የኤጀንሲው የሕግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሲሳይ ፕሮቪደንት ፈንድን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፣ ፕሮቪደንት ፈንድ ዘለቄታዊ ማኅበራዊ ዋስትና መሆን አይችልም ብለዋል፡፡ 

‹‹የፕሮቪደንት ፈንድ ገንዘብን የወሰደ ሠራተኛ ገንዘቡ ካለቀበት አለቀበት ነው፡፡ በማኅበራዊ ዋስትና (በግል ጡረታ) ቢታቀፍ ግን አሥር ዓመት ብቻ አገልግሎ ዕድሜ ልኩን እስከነ ተተኪዎቹ ሚስቱንም ጨምሮ ዕድሜው ስልሳ ዓመት ከደረሰ በኋላ ማግኘት ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ 

አንቀጽ 19 ላይ የተደረገውን ማሻሻያ በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፣ አንድ ሠራተኛ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ከ25 ዓመት በላይ ያገለግልና በ25/55 የጡረታ መብት መሠረት በአምስት ሺሕ ብር ጡረታውን አስከብሮ፣ ቀሪውን ዕድሜ ማለትም አምስት ዓመቱን በግል ድርጅት በወር እስከ 30 ሺሕ ብር ቢቀጠር አጠቃላይ የጡረታ አበሉ የሚሰላው በ30 ሺሕ ብር ደመወዝ ተመን ነው፡፡ ያላዋጣውን በመብላት ፈንዱን የሚያደርቀው በመሆኑ ገደብ ሊጣልበት የሚገባ ነው ብለዋል፡፡ 

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው፣ ማኅበራዊ ዋስትናን በተመለከተ በየትም አገር ስምምነት ኖሮ እንደማያውቅ ገልጸዋል፡፡ በኋላ ላይ የኅብረተሰቡን ዋስትና ማስከበር የመንግሥት ኃላፊነት በመሆኑ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡ 

የፓርላማው የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ፣ ከውይይቱ በርካታ ቁም ነገሮችን መገኘታቸውን፣ ለፓርላማ የቀረበ ነገር ሁሉ እንደማይፀድቅ፣ በተደረገው ውይይት ላይ በድጋሚ በመነጋገር ተጨማሪ የሕዝብ ውይይት ካስፈለገም ሊጠራ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ 

 

አዳዲስ የፋይናንስ ድጋፎች በሚጠበቁበት ፎረም የቻይና ባለሥልጣናትና ኩባንያዎች ታድመዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የቻይናና የኢትዮጵያ መንግሥታት የፋይናንስና የኢኮኖሚ ሚኒስትሮች፣ የዓለም ባንክና የሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎችና ኢንቨስተሮች የተገኙበት ፎረም፣ ቻይና በአፍሪካ

ስለምታካሂደው የኢንቨስትመንትና የንግድ ልውውጥ እየመከረ ነው፡፡ አዳዲስ ስምምነቶችና የፋይናንስ ድጋፎች ይፋ እንደሚደረጉበት ይጠበቃል፡፡ 

‹‹ኢንቨስቲንግ ኢን አፍሪካ ፎረም›› በሚል ስያሜ የመጀመሪያውን ጉባዔ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም እንዳስታወቁት፣ በአፍሪካ ከ2,200 ያላነሱ ኩባንያዎች በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያም ኋጂዬን ግሩፕ የተባለው ጫማ አምራች 3,500 ሠራተኞችን በመቅጠር፣ በዓመት ሁለት ሚሊዮን ጫማዎችን በማምረት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ 

ከካቻምና ጀምሮ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ካደረጉ የውጭ ኩባንያዎች የሚገኘው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 1.2 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቱርኩ አይካ አዲስን ጨምሮ የታይዋኑ ጆርጅ ሹ ኩባንያና ሌሎችም ሥራዎችን እያስፋፉ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡ አዳዲሶቹ ፒቪኤችና ኤችኤንድኤም የተባሉ ትልልቅ ኩባንዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውም፣ በዓመት 13 በመቶ እያደገ ለሚገኘው አምራች ኢንዱስትሪው ትልቅ ተስፋ እንደሆነ አቶ ኃይለ ማርያም ተናግረዋል፡፡ 

የቻይና ምክትል የፋይናንስ ሚኒስትሯ ሊዩ ዢያንሁዋ፣ እንዲሁም የቻይና ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዩዋን ሊ ባደረጉት ንግግር፣ አገራቸው ከአፍሪካ ጋር ያላትን የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስር ለማጠናከር እንደምትፈልግ አስታውቀዋል፡፡ በተለይ ዩዋን ሊ እንዳሉት፣ ባንካቸው በ34 የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በቻይና-አፍሪካ ልማት ፈንድ በኩል እ.ኤ.አ. በ2006 በ82 ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት ካደረገው የ3.15 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ በተጨማሪ፣ 16 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት የማድረግ ሐሳብ አለው፡፡ ይህም ወደ አፍሪካ የሚመጣውን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ፣ የአፍሪካን የወጪ ንግድ በየዓመቱ በሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ፣ እንዲሁም የታክስ ገቢንም በአንድ ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ በአንፃሩ እስካሁን በቻይና ኩባንያዎች አፍሪካ ውስጥ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አማካይነት የተመዘገበው አራት ቢሊዮን ዶላር መሆኑን የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንት ሊ፣ የሁለትዮሽ ንግዱ ግን 222 ቢሊዮን ዶላር ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ከቻይና ወደ አፍሪካ የሚገቡ ሸቀጦች የሚሸፍኑት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ 

በኢትዮጵያ ቻይናውያን ያስመዘገቡት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በሚመለከት የዓለም ባንክ ካቻምና አካሂዶት በነበረው ጥናት መሠረት፣ እ.ኤ.አ. ከ2004 እስከ 2011 ባለው ጊዜ ውስጥ ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው ኢንቨስትመንት በየዓመቱ በአማካይ የ58 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህም ቢባል ግን የቻይና ኩባንያዎች በመንግሥት የታክስና ጉምሩክ አስተዳደር የሚታዩ ውጣ ውረዶች፣ በውጭ ምንዛሪ በኩል መንግሥት ግልጽነት አለማሳየቱን፣ በሠራተኛ ሕግ፣ በሠለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦትና በመሳሰሉት መስኮች ላይ ችግሮች እያጋጠሟቸው እንደሚገኙ የዓለም ባንክ በጥናቱ አሳይቷል፡፡ 

በሰው ጉልበት ዋጋ መወደድና በማምረቻ ወጪዎች ከፍተኛነት ሳቢያ ከቻይና እየነቀሉ ወደ አፍሪካ የሚመጡ የቻይና ኩባያዎች እንደሚበራከቱ ከሰባት ዓመት በፊት ጀምሮ ሲነገር ነበር፡፡ በዚህ መስክ ኢትዮጵያ መጠቀም አለባት በማለት ደጋግመው ሲናገሩ እንደነበር የሚታወሱት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ ሆኖም የተገመተውን ያህል ግን በርካታ የቻይና ኩባንያዎች ሳይመጡ ቀርተዋል፡፡ ይህንን በሚመለከት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ልዩ ረዳት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አገሪቱ ይህንን ዕድል ለመጠቀም በሚያስችላት ደረጃ ዝግጁ እንዳልነበረች ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ ፓርኮች አማካይነት የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችንና ሌሎች እንደ ጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ያሉ አገልግሎቶችን በፋብሪካዎቻቸው ደጅ ማግኘት የሚችሉበት ሥርዓት መዘርጋቱን ጠቅሰዋል፡፡ 

በአፍሪካ ኢንቨስት ስለማድረግ በዝግ እየመከረ የሚገኘው ጉባዔም መሠረታዊ በሚባሉ ችግሮች ላይ ከመነጋገር ባሻገር፣ በአፍሪካ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ረገድ አዳዲስ ስምምነቶች ላይ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሌሎችም የመሠረተ ልማት መስኮች ላይ የቻይና መንግሥት ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ አገሮች የሚደረጉ አዳዲስ ብድሮችንና የፋይናንስ ድጋፎችን ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

በአፍሪካ የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ማክታር ዲዮፕ እንዳስታወቁት፣ በአፍሪካ በየዓመቱ የ90 ቢሊዮን ዶላር የመሠረተ ልማት ግንባታ ፍላጎት ቢኖርም፣ የአፍሪካ አገሮች ኢንቨስት ማድረግ የቻሉት ግን ከ20 ቢሊዮን ዶላር ያልዘለለ ነው፡፡ ይህንን በመንተራስ የቻይና ኩባንያዎች በቋሚ ንብረቶች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው፣ የቻይና የፋይናንስ ተቋማትም አስፈላጊውን ፋይናንስ ለማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸው ታውቋል፡፡ 

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርን ጨምሮ የዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) እንዲሁም የቻይና መንግሥት ያዘጋጁት ይህ ፎረም፣ በየዓመቱ በአፍሪካና በቻይና እየተፈራረቀ በቋሚነት እንዲካሄድ ስምምነት መደረጉን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አህመድ ሺዴ አስታውቀዋል፡፡ 

 

 

  

 

ኤጀንሲው 31 ሺሕ ያህሉ ከፍለው መዋዋላቸውን አስታውቋል

-የተዋዋሉት ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ከፍለዋል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአሥረኛ ጊዜ ባወጣው የኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ ዕድለኛ ከሆኑ የከተማው ነዋሪዎች መካከል አራት ሺሕ ተመዝጋቢዎች ለክፍያ ይጠበቃሉ፡፡

ክፍያቸውን በሁለት ሳምንት ውስጥ ካላጠናቀቁ ቤቶቹን እንደማያገኙ ተገለጸ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ዕጣ ከወጣላቸው 35 ሺሕ ዕድለኞች ውስጥ 31 ሺሕ ያህሉ ውል መፈጸማቸውን አስታውቋል፡፡

ዕጣው ከደረሳቸው መካከል 31 ሺሕ ያህሉ ውል ተዋውለው መጨረሳቸውንና ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ቅድመ ክፍያ መፈጸሙን አስታውቋል፡፡ ቀሪዎቹ ዕድለኞችም እስከ ሐምሌ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ውላቸውን ፈጽመው መጨረስ እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡ ውል የመፈጸሚያ ጊዜው ካለፋቸው ቤቱን እንደማያገኙም አስታውቋል፡፡ 

መክፈል ያልቻሉ ዕጣው የወጣላቸው ዕድለኞች ደግሞ ቅድመ ክፍያ (ሃያ በመቶውን) ለመክፈል ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡ ብዙዎቹ በብድርና በተለያዩ ወገኖች ድጋፍ ሊከፍሉ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ኪራይ እየከፈሉ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ለደረሳቸው ኮንዶሚኒየምና ለሚኖሩበት የቤት ኪራይ በየወሩ መክፈል ስለማይችሉ፣ ክፍያውን በሁለት ሳምንት አጠናቁ በመባላቸው ከወዲሁ ሥጋት ገብቷቸዋል፡፡ 

አራት ኪሎ፣ ልደታና ለመሀል ከተማው ቀርበው በተሠሩ ኮንዶሚንየም ቤቶች የደረሳቸው ዕድለኞች፣ ኮንዶሚኒየም ቤቱ ባይፀዳ እንኳን ገብተው ለኪራይ የሚከፍሉትን እየከፈሉ እንደሚኖሩ የገለጹት ዕድለኞቹ፣ ከመሀል ከተማው በ10 እና በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የደረሳቸው ግን ግራ እንደተጋቡ ተናግረዋል፡፡ 

ቤቶቹ የተገነቡት አገር ውስጥ በተመረቱ የግንባታ ግብዓቶች በመሆኑ ቅናሽ እንዲደረግላቸው የሚጠይቁት ነዋሪዎቹ፣ የመሠረተ ልማት ባልተሟላባቸው አካባቢዎች ዕጣ የደረሳቸው በኮንዶሚኒየም ቤቶቹ አካባቢ ትምህርት ቤቶች እስከሚከፈቱና ትራንስፖርት ተሟልቶ እስከሚገባ ድረስ፣ የባንክ ክፍያ መጀመሪያው ጊዜ እንዲያራዝምላቸው ጠይቀዋል፡፡ በተለይ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ያለፉና በመሰናዶ ትምህርት ቤት የተመደቡ ልጆቻቸውን እንዴት አጓጉዘው ማስተማር እንደሚችሉ ሥጋት ውስጥ እንደከተታቸው ተናግረዋል፡፡ 

በሌላ በኩል ዕጣ የወጣላቸው የተወሰኑ ዕድለኞች ቅድሚያ ክፍያ የሚከፍሉት አጥተው በየመሥሪያ ቤቱ፣ በካፌ፣ በሬስቶራንትና በመዝናኛ ቦታዎች በመገኘት እውነቱን እየተናገሩ ዕርዳታ እየጠየቁ መሆኑ ታውቋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንዶቹ ዕድለኞች ከአሥር ዓመታት ቆይታ በኋላ የደረሳቸው ዕድል መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ዕድል ካመለጣቸው ዳግመኛ ስለማያገኙት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውን ዕርዳታ በመጠየቅ ለማሟላት እየተሯሯጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በልመና ምን ያህሉን መሸፈን እንደሚችሉ አለማወቃቸውን የሚናገሩት ዕድለኞቹ፣ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ የቻሉትን ጥረት አድርገው ካልሞላላቸው ምንም ማድረግ ስለማይችሉ ሳይወዱ በግድ እንደሚተውት ተናግረዋል፡፡

የቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ግን ቤቶቹን ለማዋዋል የተቀመጠው ቀነ ገደብ ሐምሌ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ስለሚያበቃ፣ በአስቸኳይ መዋዋሉን እንዲያጠናቅቁ አስታውቋል፡፡ የዕጣ ዕድለኞች የሆኑት አራት ሺሕ ያህል ግለሰቦች በተቀመጠው ቀነ ገደብ ውስጥ የማያጠናቅቁ ከሆነ ቤቶቹን እንደማያገኙ ገልጿል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በተለይ በአሥረኛው ዙር ዕጣ የወጣባቸው ኮንዶሚኒየም ቤቶች ዋጋ በመጋነኑ ምክንያት፣ ልዩ ኮሚቴ አቋቁሞ የዋጋውን ሁኔታ ማጥናት መጀመሩ የታወቀ ቢሆንም፣ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡   

 

ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ ወደብ ድረስ የተዘረጋው የባቡር መስመር ጥቅምት 2008 ዓ.ም. ሥራ የሚጀምር ቢሆንም፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችለውን ነዳጅ ለማጓጓዝ፣ የሚያስፈልገው የመሠረተ ልማት ቀደም ብሎ አለመጠናቀቁ አለመግባባት ፈጠረ፡፡ 

ኢትዮጵያ የምትጠቀመው አብዛኛው ነዳጅ የሚገባው በጂቡቲ በኩል ሲሆን የሚጫነውም ከሆራይዘን ተርሚናል ነው፡፡ ነገር ግን የተገነባው የባቡር መስመር ቀጥታ ወደ ጂቡቲ ወደብ የሚያመራ ነው፡፡ የአገሪቱ ነዳጅ ወደሚጫንበት ሆራይዘን ተርሚናል የባቡር ሐዲድ አለመገንባቱ አለመግባባት መፍጠሩን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ 

ከሆራይዘን ተርሚናል ባቡሩ ነዳጅ ቢጭን እንኳን የተጫነው ነዳጅ ኢትዮጵያ ከደረሰ በኋላ የሚያራግፍበት ዲፖ አለመገንባቱ ሌላ ችግር እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ ጉዳዩ ላይ የበለጠ አለመግባባት የፈጠረው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የትራንስፖርትና የዕቃ ማጓጓዣ ባቡሮችን እንዲያመርት ከቻይናው ኩባንያ ኖሪንኮ ጋር አስቀድሞ ውል መግባቱ ነው፡፡ ኖሪንኮ በበኩሉ ከአገር በቀሉ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በገባው ውል መሠረት ከ50 በላይ የሚሆኑ የነዳጅ ማመላለሻ ባቡር ፉርጎዎች ተመርተው ለሥራ ዝግጁ መሆናቸውን እየገለጸ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የእሳቸው ኩባንያ ከውጭ ነዳጅ ገዝቶ ጂቡቲ ሆራይዘን ተርሚናል ያራግፋል፡፡ ከዚህ በኋላ የነዳጅ ኩባንያዎች በተሽከርካሪዎች ለአገር ውስጥ ገበያ ያቀርባሉ፡፡ ነገር ግን ነዳጅን በባቡር ለማጓጓዝ ወደ ሆራይዘን ተርሚናል የሚጓዝ የባቡር ሐዲድ አልተገነባም፡፡ በአገር ውስጥም ማጠራቀሚያ ዲፖ አልተገነባም፡፡ ‹‹ጉዳዩ በደንብ መታየት ነበረበት፡፡ ትንሽ ክፍተት አለው፤›› በማለት አቶ ታደሰ የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልጸዋል፡፡ 

ይህ ጉዳይ ክፍተት እንዳለው ዘግይቶ የተገነዘበው ትራንስፖርት ሚኒስቴር አጀንዳ ቀርጾ መሠረተ ልማት ለማሟላት ውይይት ማካሄድ መጀመሩ ታውቋል፡፡ 

ትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ በሥሩ የሚገኘውን ትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ኢንተርፕራይዝንና አሥሩን ነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች በማሰባሰብ በመፍትሔ ሐሳቦች ላይ እየተነጋገረ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

በዋናነት የቀረበው መፍትሔ ከጂቡቲ ወደብ ወደ ሆራይዘን ተርሚናል የሚወስድ የባቡር ሐዲድ መዘርጋትና በሆራይዘን ተርሚናል ባቡሮቹ ነዳጅ የሚጭኑባቸውን መሣሪያዎች ማሟላት ነው፡፡

በአገር ውስጥ ደግሞ አዲስ አበባ (ሰበታ) አካባቢ በሚገኘው ግዙፍ የባቡር ተርሚናል ውስጥ የነዳጅ ማራገፊያ ዲፖ መገንባት ዋነኛ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት እነዚህ ጉዳዮች በውይይት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ግንባታዎቹን ለማካሄድ የበጀት ጉዳይ ቀጣዩ መነጋገሪያ ይሆናል ተብሏል፡፡ 

ምንጮች እንደገለጹት፣ በጀት ተወስኖ የግንባታ ቦታ ከተዘጋጀ ግንባታው ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት የሚፈጅ በመሆኑ፣ በባቡር መሠረተ ልማት ነዳጅ ለማመላለስ ረዥም ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ ይህ ፕሮግራም ቀድሞ ባለመታሰቡ ብቻ የተገነባው የባቡር መሠረተ ልማት ላልተወሰነ ጊዜ ነዳጅ ከማመላለስ ውጪ ይሆናል፡፡

በጂቡቲ ሆራይዘን ተርሚናል ነዳጅ በተሽከርካሪ የሚያቀርቡ ኩባንያዎች አሥር ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ በወር በ250 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በሚያቀርበው ነዳጅ ትልቅ ድርሻ ያላቸው ኖክ፣ ቶታል፣ ኦይል ሊቢያና የተባበሩት ናቸው፡፡ እነዚህና ሌሎች ስድስት ኩባንያዎች በመላው አገሪቱ ባላቸው ከ250 በላይ ነዳጅ ማደያዎች አማካይነት ነዳጅ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ 

ሰበታ አካባቢ የነዳጅ ዲፖ እንደሚገነባ የሚጠበቀው በግል ኩባንያዎቹ ሲሆን፣ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከጂቡቲ ነዳጅ እያጓጓዙ በዲፖው የማራገፍ ኃላፊነት እንዳለበት ይጠበቃል፡፡ ኩባንያዎቹ ደግሞ በተሽከርካሪዎች ወደ ነዳጅ ማደያዎች ያደርሳሉ በሚለው ዕቅድ ላይ ውይይት እየተካሄደ መሆኑም ታውቋል፡፡ 

ከአዲስ አበባ (ሰበታ) እስከ ጂቡቲ ወደብ ድረስ የተዘረጋው የባቡር መስመር 656 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው፡፡ መስመሩ እስከ አዳማ ድረስ ሁለት ባቡሮች በአንዴ የሚያስተናግድ ሲሆን፣ ከአዳማ እስከ ጂቡቲ ድረስ ደግሞ አንድ መስመር ይኖረዋል፡፡

የባቡር መስመሩ ለመንገደኞችና ለዕቃ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ የትራንስፖርት ወጪን በ50 በመቶ ይቀንሳል ተብሏል፡፡ በሁለት የቻይና ኩባንያዎች እየተገነባ ያለው ይህ የባቡር መስመር የሐዲድ ማንጠፍ ሥራው የተጠናቀቀ በመሆኑ፣ በመጪው ጥቅምት አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሏል፡፡ ነዳጅ ለማጓጓዝ በተፈጠረው ክፍተት ላይ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ጌታቸው በኩረ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡  

 

ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት የአፍሪካ የሰላም ማዕከል በአዲስ አበባ ተገነባ

ለአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት እንቅስቃሴዎች ድጋፍ እንዲሰጥ ታስቦ በአዲስ አበባ የተገነባውና ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት የሰላም ማዕከል፣ ሰኔ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ተመርቆ ተከፈተ፡፡ 

ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ መርቀው የከፈቱት ይኼ የደኅንነት ተቋም፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ግጭትን ለመፍታት ለሚደረጉ የሰላም ማስከበር ጥረቶች አስፈላጊ የሥልጠናና የጥናት ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ታስቦ የተገነባ ነው፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፣ የተሳካ ሰላም የማስከበር ሥራዎች ለማከናወን ማዕከሉ ትልቁ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ማዕከሉን አስመልክተው ሲናገሩ፣ ‹‹የሰላም ማዕከሉ ወታደራዊና የሰላም አስከባሪ ተቋማት ዓላማቸውን በተሳካ ሁኔታ እንዲወጡ የምርምርና የሥልጠና አገልግሎት በመስጠት የሰላም ማስከበር ሥራዎች ማዕከል ሆኖ ያገለግላል፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጪ ሰላምና ደኅንነት ከማስጠበቅ አንፃር ላደረገው አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን ለመከላከያ ሚኒስቴር የቸሩት ፕሬዚዳንት ሙላቱ፣ የአገሪቱ መረጋጋትና የኢኮኖሚ ዕድገት ምክንያት ኢትዮጵያ በአካባቢው የሰላምና የፀጥታ ተምሳሌት መሆን በመቻሏ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ 

የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በበኩላቸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ኢትዮጵያ ሰላምን በማስከበር ሥራዎች የማይተካ ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝ ገልጸው፣ ማዕከሉ ይህንን ጥረት በዕውቀትና በምርምር ለመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ የተገነባው ይኼው የሰላም ማዕከል ግጭትን ለመከላከል፣ ዕርቅ ለመፍጠርና ሰላም ለማስከበር ለአካባቢውና ለመላው አፍሪካ ጥቅም ይውል ዘንድ፣ በተለይ ከአፍሪካ ኅብረትና ከምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ጋር በትብብር እንደሚሠራ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስን ጨምሮ፣ በርካታ የመከላከያና የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡    

 

የአይኤስ አሸባሪ ቡድን ሊቢያ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ላይ በፈጸመው አሰቃቂ ግድያ ምክንያት መንግሥት በጠራው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ረብሻ በመፍጠር ተከሰው የተፈረደባቸው የሰማያዊ ፓርቲ አባላት፣

የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲወጡ ከማረሚያ ቤት በራፍ ላይ ተይዘው ከተመሠረተባቸው ክስ በዋስ እንዲለቀቁ ብይን ተሰጠ፡፡

የፓርቲው አባላት ሰኔ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. እያንዳንዳቸው በ5,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቄራ ምድብ ችሎት ብይን የሰጠው በወይንሸት ሞላ፣ በኤርሚያስ ፀጋዬ፣ በዳንኤል ተስፋዬና በቤተልሔም አካለ ወርቅ ላይ ነው፡፡

በተከሳሾቹ ላይ ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ተሰጥቶ የነበረው፣ ሰላማዊ ሠልፉን በማወክ የተለያዩ ስድቦችን መንግሥትንና ዜጎችን በመሳደብ፣ ሥርዓቱን በማንጓጠጥና በፖሊስ አባላት ላይ ድንጋይ በመወርወር ወንጀል ተከሰው ነው፡፡

ፍርደኞቹ ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፍርድ በቀረቡበት ዕለት ሁለት ወር ከአንድ ቀን በእስር መቆየታቸው በመረጋገጡ፣ በዕለቱ ከእስር እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም ፖሊስ ሌላ ወንጀል መፈጸማቸውን በመግለጽ፣ ሰኔ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ከእስር ተፈትተው ወደ ቤታቸው ለማምራት ማረሚያ ቤት ደጃፍ ላይ ሲደርሱ ተይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደዋል፡፡

ፖሊስ ለፍርድ ቤት ያቀረበው ክስ፣ ተከሳሾቹ ቀደም ብሎ በተከሰሱበት ወንጀል ላይ በምስክርነት ያቀረባቸውን ማስፈራራታቸውንና መዛታቸውን በመግለጽ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ክሱን ተቀብሎ ለሰኔ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. መዛታቸውን የሚያስረዱለትን ምስክሮቹን እንዲያቀርብ ቀጠሮ የሰጠ ቢሆንም፣ ፖሊስ ምስክሮቹን በተለያዩ ምክንያቶች ሊያቀርብ አለመቻሉን ገልጾ፣ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡ 

ተከሳሾቹ ግን ፖሊስ ምስክሮቹን በተሰጠው ቀጠሮ ቀን ማቅረብ እንደነበረበት ገልጸው፣ ፍርድ ቤቱ ዋስትና እንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ጥያቄውን ተቀብሎ እያንዳንዳቸው በ5,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ ፈቅዷል፡፡ በሌላ በኩል ተከሳሾቹ ቀደም ብሎ ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ሁለት ወራት ተፈርዶባቸው በነበረውና እስራቸውን ጨርሰው በወጡበት ክስ፣ ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ እንዳለባቸውና ሰኔ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ተጠቁሟል፡፡

 

አፍሪካ ከእስያ አገሮች ትልቅ ፉክክር ይጠብቃታል  

የአሜሪካና የአፍሪካ የእርስ በርስ የኢኮኖሚ ግንኙነት ላይ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ታምኖበት ላለፉት 15 ዓመታት ሲተገበር የቆየውን ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የገበያ ዕድል፣ ለተጨማሪ አሥር ዓመታት ማራዘሙን የአሜሪካ ኮንግረስ ይፋ አደረገ፡፡ 

ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የገበያ ዕድል ወይም ‹‹አፍሪካ ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት – አጎዋ›› ሚያዝያ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በአምባሳደር ማይክል ፍሮማንና አምባሳደር ሱዛን ራይስ በኩል ቀርቦለት ሲመክር የከረመው ሕግ መወሰኛው ምክር ቤት፣ ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት እንዲራዘም ይፋ ያደረገው አጎዋ እንደከዚህ በፊቱ ሳይሆን በእስያ አገሮች ዘንድ ፈተና እንደሚገጥመው እየተነገረለት ነው፡፡ አምባሳደር ፍሮማን የአሜሪካ የንግድ ዘርፍ ተወካይ ሲሆኑ፣ የቀድሞዋ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር ሱዛን ራይስ በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ናቸው፡፡ በአምባሳደሮቹ የቀረበው የአጎዋ ረቂቅ ሕግ ለአሥር ዓመታት የሚራዘም ከሆነ ከ30 በላይ ለሚሆኑ የአፍሪካ አገሮች ትልቅ እፎይታ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በኮንግሬሱ ተቀባይነት አግኝቶ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በፊርማቸው እንዲያፀድቁት መርቶታል፡፡ 

እ.ኤ.አ. በ2009 ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በጋና ተገኝተው አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ትስስር የማጠናከር አስፈላጊነት ሲገልጹ፣ ‹‹ለልጆቻችን ማውረስ የምንፈልገውን ዓለም በመቅረፅ ረገድ አፍሪካ የአሜሪካ አጋር ነች፡፡ አጋርነታችንም በጋራ ኃላፊነትና በመከባበር ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል፤›› ብለው ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት የአፍሪካና የአሜሪካ የመሪዎች ጉባዔ በተካሄደበት ወቅት፣ ፕሬዚዳንቱ የአፍሪካ የዕድገትና የገበያ ዕድል የሚያበቃበት ጊዜ ማለትም የመጪው ዓመት መስከረም ወር ደርሶ ከመጠናቀቁ በፊት፣ የጊዜ ገደቡ እንዲራዘም ኮንግረሱን መጠየቃቸውም ይታወሳል፡፡ በዚህ መሠረት አጎዋ እንዲራዘም መጠየቅ ብቻ ሳይሆን፣ ማሻሻያዎች ተደርገውበት የበለጠ ውጤታማ የሚሆንበት መንገድ እንዲመቻች ሲጠየቅ እንደቆየ አይዘነጋም፡፡

ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገትና የገበያ ዕድል ለመፍጠር በሚል መነሻ እ.ኤ.አ. በ2000 ሕግ ሆኖ የፀደቀው አጎዋ፣ በአሜሪካና በአፍሪካ መካከል እያደገ ስለመምጣቱ ለሚነገርለት አጋርነት መጠናከር አስተዋጽኦ ማድረጉን በማስረጃ ደፍገው የሚያቀርቡት የአሜሪካ ባለሥልጣናት ብቻ አይደሉም፡፡ አፍሪካውያንም ይጠቀሳሉ፡፡ በአፍሪካ ወሳኝ የልማትና የዕድገት መርሐ ግብሮች እንዲከናወኑ፣ የተለያዩ የአኅጉሪቱ ቀጣናዎች የኢኮኖሚ ጥምረት እንዲፈጥሩ፣ ኩባንያዎች ተወዳዳሪ እንዲሆኑና የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ለሚያደርገው የካፒታልና የኢንቨስትመንት ፍሰት ምቹነትን በመፍጠር በኩል ሚናው አሌ እንደማይባል የሚገልጹ አሉ፡፡  

በአልባሳት ንግድ ዘርፍ ከተሰማሩ ተቋማት በተገኘ መረጃ መሠረት ከነዳጅ መስክ ውጭ ያለው የወጪ ንግድ፣ መርሐ ግብሩ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በቀጥታ ወደ 350,000 ለሚቆጠሩ ሰዎች የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር፣ በተዘዋዋሪም ሌሎች በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩትን በማገዝ ዘርፉን በሦስት እጥፍ አሳድጎታል፡፡ 

የአፍሪካን ልማት ከመደገፍ ባሻገር አጎዋ ለአሜሪካ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችንም አስገኝቷል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2000 ጀምሮ አሜሪካ ከሰሃራ በታች ወዳሉት አገሮች የምትልካቸው ሸቀጦች መጠን ይበልጥ እየጨመረ መምጣቱን የሚያመላክቱ ክስተቶች በአፍሪካ እየታዩ ነው፡፡ መካከለኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል እያደገ መጥቶ ከሩብ ቢሊዮን በላይ እንደሚደርስ የኢኮኖሚ ትንበያዎች ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑም በአሜሪካ የተመረቱ ሸቀጦችን የመሸመት አቅማቸው በማደጉ፣ የሸቀጦች ወጪ ንግድ መጠን በሦስት እጥፍ ሊጨምር ችሏል፡፡ በአፍሪካ የሚገኙ የንግድ ተቋማት የአሜሪካ ግብዓቶች፣ ዕውቀት፣ ክህሎትና አጋርነት አስፈልጓቸዋል፡፡ አሜሪካ በአፍሪካ የምታደርገው የኢንቨስትመንት ፍሰት፣ በአፍሪካም ሆነ በአሜሪካ ለሚገኙ ሠራተኞች የሥራ ዕድሎችን ከመፍጠሩም በላይ፣ ገቢያቸው እንዲያድግ ምክንያት ሆኗል፡፡ 

አሜሪካ በአጎዋ በኩል ከአፍሪካ ጋር የምታደርገውን የንግድ ልውውጥ እንዳፋጠነ የሚነገርለት ቢሆንም፣ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ግን ተጠቃሚ ሳይሆኑበት እንደቀረ ይታወቃል፡፡ በግብርና ውጤቶች፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች አኳያ ተጠቃሚ መሆን ከሚገባቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ እንደነበረች ይታመናል፡፡ ቢሆንም በአጎዋ በኩል አገሪቱ ከቀረጥና ከኮታ ነፃ ወደ አሜሪካ የላከቻቸው ምርቶች መጠን እጅግ ዝቅተኛ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ ባለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ውስጥ በአጎዋ በኩል ከላከቻቸው ምርቶች በአማካይ በዓመት ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት አልቻለችም፡፡ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት የአሜሪካ ከፍተኛ የንግድ ባለሙያና በኢትዮጵያ የአሜሪካ የውጭ ንግድ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ታንያ ኮል እንዳስታወቁት፣ አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በአጎዋ በኩል ከምትልካቸው ምርቶች ቦይንግ አውሮፕላንን ጨምሮ በዚህ ዓመት ብቻ ከ1.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ስታገኝ፣ ኢትዮጵያ ግን ከ225.6 ሚሊዮን ዶላር የዘለለ ገቢ አላገኘችም፡፡ በመሆኑም ምርቶችን በገፍ ማምረትም ሆነ ወደ አሜሪካ መላክ ፈተና ሆኖ ይገኛል፡፡ ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት አጎዋ በመራዘሙ ግን እየተስፋፉ ያሉት የቆዳና የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ትልቅ የገበያ ዕድል እንደሚያገኙ ይጠበቃል፡፡ በአንፃሩ አሜሪካ ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የገበያ ዕድል ለእስያ አገሮች ‹‹ትራንስ ፓስፊክ ፓርትነርሺፕ›› በተሰኘው ማዕቀፍ ውስጥ ተመሳሳይ የነፃ ገበያ ዕድል መስጠቷ ግን በርካታ ጨርቃ ጨርቅ አምራቾችን ሥጋት ውስጥ የጣለና የአፍሪካን የተወዳዳሪነት አቅም የሚፈታተን ተብሎለታል፡፡ የሥጋቱ ምክንያት ደግሞ በእስያ አገሮች ውስጥ የማምረቻ ወጪዎች ከአፍሪካ ይልቅ ዝቅተኛ መሆናቸው ነው፡፡ 

 

የዶ/ር አርከበ ዕቁባይ አዲስ መጽሐፍ ለኢትዮጵያ ገበያ ቀረበ

ዋጋው በጣም ውድ ነው ተብሏል

ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ‹‹ሜድ ኢን አፍሪካ ኢንዱስትሪያል ፖሊሲ ኢን ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ያሳተሙት አዲስ መጽሐፍ፣ በኢትዮጵያ ገበያ ቀረበ፡፡

መጽሐፉ በዓለም ገበያ ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. የቀረበ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በቡክ ወርልድ አማካይነት ገበያውን ተቀላቅሏል፡፡

ዋቢና ኢንዴክስን ጨምሮ 348 ገጽ ያለው ይህ የዶ/ር አርከበ ዕቁባይ መጽሐፍ፣ ከአፍሪካ አጠቃላይ ሁኔታ በመነሳት የኢትዮጵያን ኢንዱስትሪ በጥልቀት ይተነትናል፡፡

ዶ/ር አርከበ ለዚህ መጽሐፍ መነሻ የሆናቸው በለንደን ስኩል ኦፍ ኦርየንታል ኤንድ አፍሪካን ስተዲስ ለተከታተሉት የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ያቀረቡት ጽሑፍ ነው፡፡

ዶ/ር አርከበ በአራት ዓመት የሚጠናቀቀውን ትምህርታቸውን በዩኒቨርሲቲው ባልተለመደ ሁኔታ በ23 ወራት ውስጥ በከፍተኛ ማዕረግ በማጠናቀቃቸው፣ በወቅቱ ከፍተኛ አድናቆትን ተችሯቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡

የተመረቁበትን ዴቨሎፕመንት ስተዲስ የዶክትሬት ዲግሪ የጥናት ጽሑፍ በማስፋት በመጽሐፍ መልክ ያዘጋጁት ሲሆን፣ የተማሩበት ለንደን ስኩል ኦፍ ኦርየንታል ስተዲስ ይኼንን መጽሐፍ እንዲታተም ለኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ልኮታል፡፡

ለዶ/ር አርከበ ቅርበት ያላቸው የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ዶ/ር አርከበ ይኼንን መጽሐፍ ያዘጋጁት በዘርፉ ጥልቅ ጥናት አካሂደው ነው፡፡

ዶ/ር አርከበ መጽሐፉን ለማዘጋጀት በ150 ኩባንያዎች ላይ ጥልቅ ጥናት ማድረጋቸው፣ ሃምሳ ፋብሪካዎችን በአካል በመገኘት ማጥናታቸው፣ ለዚሁ ጽሑፍ 250 ጥያቄዎችን በማዘጋጀት ከፋብሪካዎች መረጃ እንደሰበሰቡና ከሁለት እስከ አራት ሰዓት የፈጁ 200 ቃለ መጠይቆችን ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡ ለኢንዱስትሪ ልማት ማነቆ ናቸው የተባሉ ችግሮችን ለመለየት በውጭና በአገር ውስጥ የሚገኙ ፋብሪካዎች ላይ ጥናት ማድረጋቸው እንዲሁ ተነግሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሌሎች ጥናቶች መረጃ ሆነው ያልቀረቡ አንድ ሺሕ ሰነዶችን በማገላበጥ የተሟላ ጥናት ማድረጋቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ይህ አጠቃላይ ጥናት አራት ዓመት የፈጀ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ይህ የዶ/ር አርከበ መጽሐፍ የተወሳሰቡ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ሐሳቦችን በጥልቅ አረዳድ የተነተነ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ‹‹ጸሐፊው በንድፈ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባራዊ ልምዳቸውና በፖሊሲ ቀረፃ የረዥም ጊዜ ልምድ ስላላቸው ነው፤›› በማለት የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሀ ጁን ቻንግ ለመጽሐፉ ያላቸውን አድናቆት በመጽሐፉ ላይ ገልጸዋል፡፡ 

የቀድሞ የዓለም ባንክ ዋና ኢኮኖሚስት ጀስቲን ይፋ ሊን በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በልማት ተዓምር እየፈጠረች በመሆኑ ለአፍሪካ አገሮች መነቃቃት፣ በራስ መተማመንና መልካም ተሞክሮ ማካፈል ትችላለች ያሉ ሲሆን፣ ዶ/ር አርከበ ይኼን ለውጥ በመጽሐፉ በግሩም ሁኔታ እንደተረኩት መስክረዋል፡፡ ጃፓን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለምሥራቅ እስያ አገሮች ምሳሌ እንደሆነችው ሁሉ፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አገሮች ተመሳሳይ አስተዋጽኦ ማበርከት ትችላለች ብለዋል፡፡ መጽሐፉ ኢትዮጵያ ዕድገቷን እንዴት እያፋጠነችና ባለሁለት አኃዝ ዕድገት እያስመዘገበች እንደመጣች፣ ጥልቅ ግንዛቤ ይሰጣል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

መጽሐፉ በእንግሊዝ ገበያ ውስጥ 55 ፓውንድ ሲሸጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ 1,815 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡

ከቡክ ወርልድ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የመጽሐፉ ዋጋ መወደዱን ከተለያዩ አቅጣጫዎች አስተያየት እየተሰጠበት ነው፡፡ መጽሐፉ ሊወደድ የቻለው ሐርድ ከቨር ያለውና ደረጃውን ጠብቆ በመታተሙ፣ እንዲሁም በጣም የተለፋበት በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡

መጽሐፉ በዋነኛነት ትኩረት የሚያደርገው በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት መሄድ ባለባቸው አቅጣጫዎች ላይ ነው፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍን ማሳደግ ለግብርና የላቀ ዕድገት ወሳኝ መሆኑም ተተንትኗል፡፡

ዶ/ር አርከበ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ እንደጠቀሱት፣ በመጽሐፉ ያንፀባረቋቸው ምልከታዎች የመንግሥትንም ሆነ አብረዋቸው እየሠሩባቸው ወይም የሠሩባቸው ተቋማትን አይወክሉም፡፡ የመጽሐፉ ዋናው ዓላማ የተለያዩ ምልከታዎች፣ ልምዶችና ተግዳሮቶችን ለማቅረብ ለተጨማሪ ጥናትና ውይይት መጋበዝ መሆኑም ተገልጿል፡፡

 

ኤርትራውያን ስደተኞች አገራቸው ከአፍሪካ ኅብረት አባልነት እንድትሰረዝ ጥያቄ አቀረቡ

በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ሰኔ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በተለያዩ አገሮች ባደረጉት የተቃውሞ ሠልፍ፣ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራውን የኤርትራ አስተዳደር በማውገዝና ሕጋዊ የሆነ መንግሥት

የማያስተዳድራት አገር የአፍሪካ ኅብረት አባል መሆን እንደማትችል በመግለጽ፣ ኤርትራ ከኅብረቱ አባልነት እንድትሰረዝ ጥያቄ አቀረቡ፡፡

በአዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት በመገኘት ቁጥራቸው ከ1,000 የሚበልጡ ስደተኛ ኤርትራውያን ባሰሙት ተቃውሞ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግንቦት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ኤርትራን በሚመለከት ያወጣውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ሪፖርትን ደግፈዋል፡፡ ‹‹ኢሳያስ አፈወርቂ ከሥልጣን መውረድ አለበት፤›› የሚለውንና ሌሎችንም መፈክሮች በማሰማት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ መንግሥት በተለይ በኤርትራውያን ወጣቶች ላይ እየፈጸመው የሚገኘውን ስቃይ፣ በደልና ሌሎች በዝርዝር ያቀረባቸውን ሪፖርቶች ኅብረቱ እንዲያፀድቀው ጠይቀዋል፡፡

ሕጋዊነት የሌለው መንግሥት የኅብረቱ አባል ሆኖ መቀጠል እንደሌለበት የጠቆሙት ኤርትራውያኑ፣ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣናቸው እንዲወገዱ ኅብረቱ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡ 

ለአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ደብዳቤ ያስገቡ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ለአውሮፓ ኅብረት ጽሕፈት ቤትም ተመሳሳይ ደብዳቤ አስገብተዋል፡፡

የቀይ ባህር አፋር ነፃ አውጭ በሚባለው ድርጅት በተዘጋጀው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ ቁጥራቸው ከ30 ሺሕ በላይ የሆኑ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ፣ በሰመራ፣ በዱብቲ፣ በበራ ኃይሌ ካምፕ መገኘታቸው ሲታወቅ፣ በውጭ አገሮች በኒውዮርክና በጄኔቭም የተቃውሞ ሠልፉ መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሠልፍ በማድረግ ለአፍሪካ ኅብረት ያቀረቡትን ደብዳቤ፣ የዶ/ር ድላሚኒ ዙማ ጸሐፊ ተቀብለው፣ ሊቀመንበሯ አስቸኳይ ምላሽ እንደሚሰጧቸው ነግረዋቸዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግንቦት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ኤርትራን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፣ በእርስ በርስ ጦርነት እየወደመች ከምትገኘው ሶሪያ ቀጥላ ወጣት ዜጐቿ ወደ ስደት የሚጐርፉባት አገር መሆኗን ገልጿል፡፡

የኤርትራ ሰብዓዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን በቀጥታ ኤርትራ ውስጥ ሆኖ በአገሪቱ ዜጐች ላይ የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መከታተልና መመራመር ባይችልም፣ ከ550 በላይ ስደተኛ ኤርትራውያንን በማነጋገርና የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ 484 ገጾች ያሉት ሪፖርት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ 24ኛ ዓመት የነፃነት ቀኗን በቅርቡ ያከበረችው ኤርትራ ላለፉት 24 ዓመታት ዜጐቿ የስቃይ፣ የሞትና የእስራት ሰለባ መሆናቸውን ሪፖርቱ አካቷል፡፡ የሚፈጸሙባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም ሆን ተብሎና ታስቦበት የሚደረጉና የዘር ማጥፋትን የሚያካትቱ መሆናቸውን ሪፖርቱ እንደሚያስረዳ መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ 

 

በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የኦዲት ሪፖርት አተገባበር ላይ ትችት ቀረበ

የፓርላማው የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተሾመ እሸቱ፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሚቀርብበትን የኦዲት ትችት ማስተካከል አልቻለም ሲሉ ከፍተኛ ወቀሳ ሰነዘሩ፡፡ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወቀሳውን ተቃውመዋል፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ በከር ሻሌ የተቋማቸውን የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሰኔ 18 ቀን 2007 ዓ.ም. አቅርበዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ በሪፖርታቸው ገጽ 19 ላይ ከተለያዩ አካላት ለመሥሪያ ቤታቸው የተሰጡ አስተያየቶች ትልቅ ጠቀሜታ እንደነበረው ገልጸዋል፡፡ ‹‹የፌዴራል ዋና ኦዲተር በተቋማችን ላይ የሚያደርገውን ኦዲት ተከትሎ የሚላክልን የኦዲት ግኝት ለሥራ አፈጻጸማችን ትልቅ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጎልናል፤›› ብለዋል፡፡

የሪፖርት አቀራረብ ትክክል አይደለም ብለው ያመኑት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰበሳቢ አቶ ተሾመ እሸቱ፣ በአቶ በከር ላይ ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

የኦዲት ግኝትን በተመለከተ መቅረብ የነበረበት ሪፖርት በዝርዝር የተወሰደውን ዕርምጃ የሚገልጽ መሆን ነበረበት ያሉት አቶ ተሾመ፣ ይህንን ሕጋዊ ግዴታ ወደ ጎን ትቶ በደምሳሳው የኦዲት ሪፖርቱን ግብዓት አድርገነዋል ብሎ ማስቀመጥ ተገቢ አይደለም ብለዋቸዋል፡፡ 

የፌዴራሉ ዋና ኦዲተርን የሚከታተለው የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ተሾመ፣ ‹‹ምናልባት የወሰድነውን ዕርምጃ ብንዘረዝር ከፓርላማው ክርክር ይገጥመናል ወይም ሪፖርቱ እንዳይረዝም ብዬ ነው የሚል ምላሽ ይቀርብ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከፋኝ ተብሎ ሕግ አይጣስም፡፡ የከፋን ቀን ሕግ ጥሰን መሄድ አንችልም፤›› ብለዋል፡፡

ችግሩ ለአምስት ዓመታት መቆየቱን ጠቅሰው፣ በዚህ  የሕግ ጥሰት ላይ ምን ዕርምጃ እንደተወሰደ ጠይቀዋል፡፡ ለቀረቡላቸው ትችት አዘል ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የጀመሩት አቶ በከር፣ ‹‹ዋና ኦዲተር ያቀረበውን ሪፖርት አልካድኩም፤›› ብለዋል፡፡

ዋና ኦዲተር በትክክል ግኝት እንዳገኘ የተናገሩት አቶ በከር፣ ከዋና ኦዲተሩ ጋር በማጠቃለያ ስብሰባ ተነጋግረው ችግሮቹን ማየት መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ነገር ግን በፖሊሲ አስተዳደር ቦታ ላይ ተቀምጦ ማየትን ይጠይቃል፡፡ ግብር የተጣለበት ከፋይ ቅሬታ አቅርቦ ሲከራከር የተጣለው ግብር ለረዥም ጊዜ ሳይሰበሰብ ይቀራል፡፡ ይህ በኦዲት ቋንቋ ያልተሰበሰ ሒሳብ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሌላው አምራች ኩባንያዎችን ለመደገፍ የታክስ ክፍያ ጊዜያቸውን እያሰፋንላቸው እንሄዳለን፡፡ ይኼንን በማድረጋችንም ባለሀብቶችን እየደገፍን የመንግሥትን ግብር እያስከፈልን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በቂ መረጃ እያለ ያልተሰበሰቡ ገቢዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም  የዋና ኦዲተርን አስተያየት እንደ ግብዓት እየተጠቀሙበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለያዩ ኬላዎች የተያዙትን የውጭ ገንዘቦችና የከበሩ ማዕድናት በተመለከተ ተገቢውን የሕግ ሥርዓት አለመከተል ተገቢ ባይሆንም፣ ሕግን ባለማወቅ ሠራተኞች የፈጸሙት ስህተት ነው ብለዋል፡፡

 

ከአጋሮቹ ጋር በመሆን የፓርላማውን ወንበሮች ሙሉ በሙሉ ያሸነፈው ኢሕአዴግ፣ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አገሪቱ በምትመራበት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውይይት ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንደሚያሳትፍ አስታወቀ፡፡ 

ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ኢሕአዴግና አጋር ፓርቲዎች ሙሉ በሙሉ ማሸነፋቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡ በዚህ መሠረት በሕዝብ ተወካዮችም ሆነ በክልል ምክር ቤቶች ውስጥ ተቃዋሚዎች ሐሳባቸውን የሚገልጹበት ዕድል ባለመኖሩ፣ ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ እንደሚመቻች፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንንና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን አስታውቀዋል፡፡

በዚህ መሠረት በዚህ ሳምንት በመላ አገሪቱ በሚጀመረው የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውይይት ላይ ተቃዋሚዎች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ከሰኔ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት በሚካሄደው ውይይት ተቃዋሚዎች እንዲሳተፉ ባይጋበዙም፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለዕቅዱ ግብዓት ወይም ሐሳብ የሚሰጡበት ራሱን የቻለ መድረክ ይዘጋጃል፡፡ 

‹‹ተቃዋሚዎች ከሕዝብ ጋር ተቀላቅለው ለውይይት ቢቀርቡ ሐሳባቸው ሊዋጥና በሚገባ ላይስተናገዱ ይችላሉ፤›› በማለት አቶ ሬድዋን ተቃዋሚዎች ለብቻቸው መድረክ እንደሚዘጋጅላቸው ገልጸዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሁለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተለያዩ ሐሳቦችን አራምደዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ጉዳዩን አጣጥለውታል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግር በእንደዚህ ዓይነት መንገድ አይፈታም፡፡ ሥር የሰደደ ችግር አለ ከተባለ ሥር የሰደደ መፍትሔ ነው መቅረብ ያለበት፡፡ ለብ ለብ ሊሆን አይችልም፤›› በማለት በውይይቱ መሳተፍ ኢሕአዴግን እንደማጀብ አድርገው ገልጸዋል፡፡ 

የኢዴፓ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ተሾመ በበኩላቸው፣ መንግሥት በዕቅድ ሰነዱ ላይ ለመወያየት ይፋዊ ጥያቄ ያላቀረበ ቢሆንም ኢዴፓ ከመኢአድና ከኢራፓ ጋር በመሆን ሰላማዊ ትግሉ በሚቀጥልበት መንገድ ላይ መምከር መጀመራቸውንና በቅርቡም መግለጫ እንደሚሰጡበት አስታውቀዋል፡፡ በኢዴፓ በኩል መንግሥት ጥያቄ ካቀረበ በሥራ አስፈጻሚው በኩል ውይይት ተደርጎ እንደሚወሰን አቶ ወንድወሰን ተናግረዋል፡፡ 

በአቶ መኮንን ማንያዘዋል በሚመራው ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽንና በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሚመሩ ኮሚቴዎች የተዘጋጀው ሁለተኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ ሰነድ በዘርፍ፣ በዘርፍ ተከፍሎ ለውይይት ይቀርባል፡፡ 

በአዲስ አበባ ከተማ በተዘጋጁት አምስት መድረኮች አቶ ሬድዋን፣ ከንቲባ ድሪባ ኩማና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ዓባይ ፀሐዬ ውይይቱን ይመራሉ፡፡ 

በክልሎች የሚካሄዱትን የውይይት መድረኮች በተለይ በትግራይ ክልል የሚካሄደውን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ በአማራ ክልል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ በኦሮሚያ ክልል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደርና ሲቪል ሰርቪስ ክላስተር አስተባባሪና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሯ ወ/ሮ አስቴር ማሞና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድር፣ በደቡብ ክልል የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ በሐረሪ ክልል የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ መመደባቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ 

ሁለተኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ ሰነድ ውይይት የሚካሄደው በዘርፍ በዘርፍ ተከፋፍሎ ሲሆን፣ ጥሪ ከተደረገላቸው መካከል ወጣቶችና ሴቶች ለየብቻ፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች፣ የመንግሥት ሠራተኞችና ምሁራን፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችና የአካባቢ ልማት ኮሚቴ ተወካዮች ይገኙበታል፡፡ 

አቶ ሬድዋን እንደገለጹት፣ ከፋፍሎ ማወያየቱ አስፈላጊ የሆነው ሁሉም በተሰማራበት መስክ በቂ ጊዜ ወስዶ ለመነጋገርና ስትራቴጂውን ለማሳካት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ 

ጥሪ የተደረገላቸው ተወያዮችም በኢሕአዴግ መዋቅር ውስጥ ያሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚወክሉ እንደሆኑ አቶ ሬድዋን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

 

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የፌዴራልና የክልል የጋራ ገቢ ተብሎ ከሚሰበሰበው ገቢ ውስጥ ድርሻው እንዲከፈለው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረበው ጥያቄ፣ የክልል መንግሥትነት ዕውቅና የሌለው በመሆኑ ውድቅ ተደረገ፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 98 የፌዴራሉ መንግሥትንና የክልሎችን የጋራ ታክስና የግብር ሥልጣንን ይደነግጋል፡፡

በዚህም መሠረት የፌዴራል መንግሥትና ክልሎች በጋራ በሚያቋቁሟቸው የልማት ድርጅቶች ላይ የንግድ ትርፍ ግብር፣ የሥራ ግብር፣ የሽያጭና የኤክሳይስ ታክስ በጋራ እንደሚጥሉና እንደሚሰበስቡ ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም በድርጅቶች የንግድ ትርፍ ላይና በባለአክሲዮኖች የትርፍ ድርሻ ላይ የግብርና የሽያጭ ታክስ በጋራ እንደሚጥሉና እንደሚሰበስቡ፣ በመጨረሻም በከፍተኛ የማዕድን ሥራዎች፣ በማናቸውም የፔትሮሊየምና የጋዝ ሥራዎች ላይ የገቢ ግብርና የሮያሊቲ ክፍያዎች በጋራ እንደሚጥሉና እንደሚሰበሰቡ ይደነግጋል፡፡ 

ይህንኑ ድንጋጌ መሠረት በማድረግ ከሚሰበሰበው የጋራ ገቢ ክልሎች ድርሻቸውን በመውሰድ ለልማት እያዋሉ የሚገኙ መሆኑን፣ በዚሁ አግባብም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የጋራ ገቢ ክፍፍል ድርሻውን እየወሰደ እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ ለልማት ሲያውል መቆየቱን፣ አስተዳደሩ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በደብዳቤ አሳውቋል፡፡ ከ2001 ዓ.ም. በኋላ ግን የገቢ ድርሻው መቋረጡን በመጥቀስ እንዲለቀቅለት ጥያቄውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቧል፡፡ የአስተዳደሩን ጥያቄ ለበጀት ድጐማና የጋራ ገቢዎች ድልድል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመራው የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ቋሚ ኮሚቴው ያቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ ሰኔ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. አዳምጧል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የትምህርት ሚኒስትሩና የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተወካዩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ቋሚ ኮሚቴው በድሬዳዋ አስተዳደር ጥያቄ ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም የሚያስፈልገው መሆኑ ስለታመነበት፣ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ እንዲመራ በማድረግ ምላሽ ማግኘቱን አስታውቀዋል፡፡

የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው ባደረገው ምርመራ ‹‹የኢፌዴሪ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 46(1) መሠረት በክልል መንግሥትነት ዕውቀና የተሰጣቸው ዘጠኙ ክልሎች መሆናቸውን፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49(1) የፌዴራል መንግሥቱ አካል ተደርጐ የሚወሰደው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው፤›› በማለት መግለጹን አቶ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በፌዴራል መንግሥት በወጣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 416/1996 መሠረት ለጊዜው የፌዴራል መንግሥት አስተዳደራዊ አካል ቢሆንም፣ በሕገ መንግሥቱ በክልልነትም ሆነ በፌዴራል መንግሥት የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ የሌለ በመሆኑ የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚያስፈልገው ጥያቄ አይደለም በማለት ጉባዔው እንደወሰነ ተናግረዋል፡፡

በዚሁ መሠረትም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ውሳኔውን እንዲያውቀው መደረጉን አቶ ሽፈራው ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

‹‹በሌላ በኩል ግን ከኅብረተሰቡ የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት አንፃር የከተማ አስተዳደሩ ያቀረበው ጥያቄ አግባብነት ያለው መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ያምናል፤›› ሲሉ አቶ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡ 

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የድሬዳዋ ከተማ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ፈቃዱ በየነ የከተማው አስተዳደር በውሳኔው ደስተኛ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የድሬዳዋ ከተማ በሕገ መንግሥቱ የክልል መንግሥትነት ዕውቅና እንደሌላት የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን የፌዴራል መንግሥት ከከተማው የሚሰበሰበው ገቢ ተቋዳሽ መሆን አለበት፡፡ ከተማዋ ወደ ኢንዱስትሪ መንደርነት እየተቀየረች ነው፡፡ መሠረተ ልማት ማሟላት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተጨማሪ ገቢ የከተማው አስተዳደር ሊያገኝ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ከከተማው የሚሰበሰውን ገቢ የፌዴራል መንግሥት ብቻ እየወሰደ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ በሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወይም አሁን በሚፈጠሩት ኢንዱስትሪዎች የሚለቀቅ ጢስና የአካባቢ ጉዳት ገፈት ቀማሽ ብቻ መሆን የለባቸውም ብለዋል፡፡ አስተዳደሩ በካቢኔ ደረጃ ተነጋግሮ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ 

የኦሮሚያ ክልልና የሶማሌ ክልል በድሬዳዋ ላይ ባነሱት የይገባኛል ጥያቄ የፌዴራሉ መንግሥት ባወጣው አዋጅ፣ ድሬዳዋ በጊዜያዊነት የፌዴራሉ መንግሥት መዋቅር አካል እንድትሆን መደረጉ ይታወሳል፡፡  

 

ግንባታው በመገባደድ ላይ ባለው የአዲስ አበባ-ሜኤሶ የባቡር መስመር ላይ በሐዲዶችና በመጋዘን የተከማቹ ንብረተቶች ላይ ተደጋጋሚ የዘረፍ ሙከራ እየተካሄደበት መሆኑ ተጠቆመ፡፡ ፖሊስ መሠረተ ልማቱንም ሆነ በግንባታ የሚሳተፉ

ሠራተኞች ደኅንነት ለማስጠበቅ የተጠናከረ ጥበቃ ማድረጉንና ዘራፊዎችንም ለሕግ ማቅረቡን ገልጿል፡፡

በተለይ በአዳማ ከተማ አካባቢ በመገንባት ላይ ባለው ጣቢያ ተደጋጋሚ ዘረፋ እንደሚፈጽም ተነግሯል፡፡ የጥበቃ ሠራተኞችና ቻይናዊያን ባለሙያዎችም በዘራፊዎች ተኩስ ተከፍቶባቸው እንደነበር ሪፖርተር ሥፍራው ድረስ በመሄድ ለመገንዘብ ችሏል፡፡

በግንባታ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ዘራፊዎች በጦር መሣሪያ ጭምር በሌሊት ካምፑን ሰብረው በመግባት በመጋዘን የሚገኙ ብረታ ብረቶችንና የግንባታ ግብዓቶችን ለመስረቅ ሙከራ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡

ከአዲስ አበባ-ሜኤሶ ባለው አጠቃላይ መስመር ላይ አንድ ሻምበል የተጠናከረ ፌዴራል የፖሊስ ኃይል የሚጠበቅ ቢሆንም፣ በአዳማ መጋዘኖች በሚገኙ ቦታዎች ግን ዘራፊዎች ከሠራተኞች ጋር በመመሳጠርም ዘረፋ ለማድረግ መሞከራቸው ተገልጿል፡፡

ግንባታውን እያካሄደ ከሚገኘው የቻይናው ሲአርሲሲ የተገኘ መረጃ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ100 ጊዜ በላይ የዘረፋ ሙከራዎች መፈጸማቸውን ያሳያል፡፡

የአዳማ 03 ቀበሌ አስተዳደር ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ ተጠርጣሪ ዘራፊዎችን አድነው በመያዝ ለሕግ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ ምን ያህል የዘረፋ ሙከራ እንደተካሄደ ባይገልጹም፣ ሁለት ተጠርጣሪዎች ተይዘው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን አንድ የአዳማ ከተማ አስተዳደር ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር ከፖሊስ መረዳት እንደቻለው፣ ዘራፊዎች በምርመራ ወቅት ሲጠየቁ የዘረፉት ንብረት የአገሪቱ ሳይሆን የቻይና እንደሆነም አድርገው ይቆጥሩታል፡፡

የጥበቃ ሥራውን እያስተባበሩ የሚገኙት ምክትል ኢንስፔክተር እንግዳው ባዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ የመሠረተ ልማቱን በተመለከተ የተሻለ ግንዛቤ ያለ ቢሆንም፣ በጥቂቶች ዘንድ ያለው ግንዛቤ በተቃራኒው ስለሆነ ሰፊ የግንዛቤ ትምህርት መሰጠት አለበት፡፡

ኩባንያው በበኩሉ በቡድን የተደራጁና የጦር መሣሪያ የታጠቁ ዘራፊዎች በኢትዮጵያውያንና በቻይናውያን ሠራተኞች ላይ በተደጋጋሚ ማስፈራሪያ ሲፈጽሙ፣ በተለያዩ ካምፖች ግንባታ የሚቆምበት ጊዜ እንደነበር ገልጿል፡፡ 

የአገር አቀፍ የባቡር ትስስር አካል የሆነው የሰበታ-ሚኤሶ የባቡር መስመር  ግንባታው በቻይናው ሲአርሲሲ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ 329 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይኼ ፕሮጀክት በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ለግንባታው 1.8 ቢሊዮን ዶላር በጀት እንደወጣበት ይነገራል፡፡ 

 

ድርጅታቸውን ለመታደግ አገር ቤት የተመለሱት የሆላንድ ካር ባለቤት ያቀረቡት ሐሳብ ውድቅ ተደረገ

በኪሳራ የተዘጋውን ሆላንድ ካር የመኪና መገጣጠሚያ ኩባንያቸውን ለመታደግ፣ ከሦስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ግንቦት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ኢንጂነር ታደሰ ተሰማ፣ ኩባንያውን እንዴት ሊታደጉት እንደሚችሉ

ያቀረቡትን ሐሳብ 201 የሚሆኑ ገንዘብ ጠያቂዎች ውድቅ አደረጉት፡፡

ኩባንያውን ከጨረታ ሽያጭ ያድናል ያሉትን ዕቅድ ነድፈውና ለመንግሥት አቅርበው ተቀባይነት በማግኘታቸው ወደ አገር ቤት የተመለሱት ኢንጂነር ታደሰ፣ ስድስት ሚሊዮን ብር ይዘው መምጣታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

201 የሚሆኑት የኩባንያው ደንበኞች መኪና ለመግዛት ከ62 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ የፈጸሙ ቢሆንም፣ ኩባንያው በገባው ቃል መሠረት ሊፈጽም ባለመቻሉ ኪሳራ አሳውጆ ነበር፡፡

ቁጥራቸው 201 መሆናቸው የተጠቀሰው ገንዘብ ጠያቂዎች፣ ሰኔ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. የኩባንያው ባለቤት፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሬጅስትራርና የተለያዩ ኮሚቴዎች ተሰብስበው በኩባንያው ባለቤት ሐሳብ ላይ ውሳኔ አስተላልፈዋል፡፡

በጠበቃቸው አቶ ጥላሁን ምትኩ አማካይነት የኩባንያው ባለቤት ሐሳብ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት ኩባንያው ከኪሳራ ወጥቶ የባለገንዘቦቹን መብት እንደሚያስጠብቅ፣ በመገጣጠሚያ ፋብሪካው ውስጥ ያሉ 174 መኪኖችን ገጣጥሞ ለገበያ ለማቅረብ ስድስት ሚሊዮን ብር እንደተዘጋጀ፣ ተሽከርካሪዎቹ ተገጣጥመው እስከሚሸጡ ድረስ ንብረቶቹ በሙሉ በንብረት ጠባቂና መርማሪ ዳኛ ሥር እንደሚቆዩ ተናግረው፣ በሐራጅ ቢሸጡ ግን የሚገኘው ገንዘብ ከመንግሥት ግብር፣ ከባንክ ዕዳ፣ ከሠራተኞች ክፍያና ከንብረት ዕዳ ማጣሪያ ክፍያ እንደማይተርፍ በመግለጽ፣ በኢንጂነሩ ሐሳብ መስማማት ምርጫ የሌለው መሆኑን ጠበቃው አብራርተዋል፡፡ 

ገንዘብ ጠያቂዎቹ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ እንዳብራሩት፣ ኢንጂነር ታደሰ ያቀረቡት ሐሳብ ቀደም ብሎ በእንግሊዝኛ ካቀረቡላቸው የሚለየው በአማርኛ መቅረቡ ነው፡፡ የቀረበው የአፈጻጸም ዕቅድ ተዓማኒ እንዳልሆነና ለገንዘብ ጠያቂዎቹ ገንዘባቸው እንዴት እንደሚመለስና ምን ያህል ወለድ እንደሚያካትት አይገልጽም፡፡ ለ174 መኪናዎች መገጣጠሚያ ብለው ያቀረቡት ገንዘብ፣ ባለአንድ ፎቅ የሆነ ቤት እንኳን መግዛት አይችልም ብለዋል፡፡ ኩባንያው ሐሳብ ሲያቀርብ ስለዕዳው አከፋፈል በቅድሚያ የገንዘብ ዋስትና ማቅረብ ቢኖርበትም አለማቅረቡን፣ የከሰረው ኩባንያ ከፍተኛ ዕዳ ቢኖርበትም ከባንክና ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ ግብር ከፋዮች መሥሪያ ቤቶች ጋር ምን ዓይነት ስምምነት ላይ እንደደረሰ ባለማሳወቁ፣ ሐሳቡን ለመቀበል እንደማይችሉ አስረድተዋል፡፡

የከሰረው ኩባንያ ንብረት ጥበቃ ሹም አቶ ግርማ ዓለሙ የሚባሉት ግለሰብ ደግሞ፣ የኢንጂነር ታደሰን ሐሳብ ሌላ ጊዜ ጽፈው ከሚያቀርቡት የተለየ አለመሆኑን ተናግረው፣ የመክሰር ሥርዓት ሒደቱን ለማቋረጥና በስምምነት ሐሳቡ ለመቀጠል የሚያስችል፣ በንግድ ሕጉ ያሉ አስገዳጅ ሁኔታዎችን አሟልተው አለመቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ስድስት ሚሊዮን ብር እንዳቀረቡ ኢንጂነሩ ቢናገሩም፣ በቅድሚያ መፍትሔ ማግኘት ያለባቸው የቀድሞ ሠራተኞች ክፍያ፣ የፎርክሎዠር (በሐራጅ የመሸጥ) መብት ያለው ዘመን ባንክ ብድር ጉዳይና ለሌሎች የመንግሥት ክፍያዎች የሚበቃ ገንዘብ ስለመኖሩ ተጨባጭ ማረጋገጫ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

በንግድ ሕግ ቁጥር 1064(3) መሠረት የስምምነት ሐሳቡ በኩባንያው ሥልጣኑ በተሰጠው አስተዳዳሪ የፈረመበት ሆኖ ባለመገኘቱ፣ የኢንጂነር ታደሰ ውክልና ሥልጣን የተሰጣቸው ስለመሆኑ ማስረጃ ማቅረብ ስላልቻሉ፣ ሐሳቡ ተቀባይነት እንደሌለውም ተናግረዋል፡፡

በሕግ መሟላት የሚገባቸው ነገሮች ሳይሟሉ ስምምነት ላይ ቢደረስና ሥራ ቢጀመር፣ ንብረቶች ሊሸሹና ሊጠፉ ስለሚችሉ ሊመለስ የማይችል ጉዳት ሊደርስ እንደሚችልም አክለዋል፡፡

በመጨረሻም በውይይቱ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች በመቅረባቸው ድምፅ እንዲሰጥበት ተደርጐ፣ በዕለቱ የተመዘገቡ 201 ግለሰቦች ወይም 62,516,068 ብር ካላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች ውስጥ 54,982,120 ብር ያላቸው 134 ሰዎች ሐሳቡን ውድቅ አድርገውታል፡፡ በመሆኑም በንግድ ሕግ ቁጥር 1084 (1) መሠረት የስምምነት ሐሳቡ ተቀባይነት አለማግኘቱን፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዋና ሬጅስትራር አቶ መሠረት አያሌው በፊርማቸው አረጋግጠዋል፡፡    

 

የዛይ ሕዝብ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ አቅርቧል

የአማራ ክልል ምክር ቤት የቅማንት ሕዝብ ላነሳቸው ተጨማሪ የማንነትና ራስን የማስተዳደር ጥያቄ፣ ከዚህ ቀደም ዋናውን ችግር ለመፍታት በሄደበት መንገድ እንዲፈታ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ አሳለፈ፡፡ 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻ የሥልጣን ዘመኑን ማጠቃለያ ጉባዔ ሰኔ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ባካሄደበት ወቅት፣ የምክር ቤቱ የሕገ መንግሥትና ክልሎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በቅማንት ሕዝቦች የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ላይ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ ነው ውሳኔውን ያሳለፈው፡፡ 

በአማራ ክልል የሚኖሩ የቅማንት ሕዝቦች የማንነትና ራስን የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄያቸውን በመጀመርያ ያቀረቡት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ ምክር ቤቱም ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የሕገ መንግሥትና የክልል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኃላፊነቱን እንዲወስድ ማድረጉን የቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት ያስታውሳል፡፡ 

ቋሚ ኮሚቴው የጥናት ቡድን አቋቁሞ ከአማራ ክልል፣ ከሰሜን ጎንደርና በየደረጃው ከሚገኙ የወረዳና የቀበሌ አመራሮችና ከአቤቱታ አቅራቢ ኮሚቴ ጋር በመተባበር ጥናት ማካሄዱን ይገልጻል፡፡ በዚሁ ጥናት በላይ አርማጭሆ፣ በጭልጋና በመተማ ወረዳዎች የወረዳ አመራሮችና የጥያቄ አቅራቢው ሕዝብ አስተባባሪ ኮሚቴ በመስማማት በመረጧቸው ናሙና ቀበሌዎች ባደረገው ጥናት ዕድሜ ጠገብ አዛውንቶች፣ አልፎ አልፎም ወጣቶች ቋንቋውን እንደሚናገሩና ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሕፃናት ቋንቋውን ለመማር ከፍተኛ ጉጉት እንዳላቸው የጥናት ቡድኑ ማረጋገጡን የኮሚቴው ሪፖርት ይገልጻል፡፡ 

በጥናቱ ያልተሸፈነ ነው ያለውን ማኅበረሰቡ በተያያዘ መልከዓ ምድር መኖር ያለመኖራቸውን ያካተተ ጥናት ተጠንቶ እንዲቀርብለት ቋሚ ኮሚቴው ለጥናት ቡድኑ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውሷል፡፡ 

የጥናት ቡድኑ ከላይ በተገለጸው መሠረት ጥናቱን ለመቀጠል በተንቀሳቀሰበት ወቅት፣ የክልሉ መንግሥት በራሱ ተነሳሽነት ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት ኮሚቴ አቋቁሞ ሥራ መጀመሩን ገልጿል፡፡ በቋሚ ኮሚቴው የተላኩ አጥኚዎች ተልዕኮ ለጊዜው እንዲቆይና የክልሉ መንግሥት በራሱ ጥያቄውን ለመመለስ የጀመረው እንቅስቃሴ ውጤት እንዲጠበቅ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ ጥያቄውን ቋሚ ኮሚቴው እንደተቀበለው ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ 

ክልሉ ባካሄደው ጥናት የራስ አስተዳደር ጥያቄውን ዕውቅና ሰጥቶ የቅማንት ሕዝብ ራሱን ችሎ በኩታ ገጠም በሚኖርባቸው የጭልጋና የላይ አርማጭሆ ወረዳዎችን ማዕከል በማድረግ፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ጀምሮ የአስተዳደር በጀት ለመመደብና ሌሎች አስፈላጊ ሥራዎችን ለመሥራት የአማራ ክልል ምክር ቤት በ14ኛ መደበኛ ጉባዔው ውሳኔ ማሳለፉን በመግለጽ፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሪፖርት ማድረጉን ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡ የክልሉ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት በተነሳሽነት ያሳየው ትብብርና ቁርጠኝነትን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አድንቆታል፡፡ 

ይሁን እንጂ የማኅበረሰቡ ተወካዮች የክልሉ ምክር ቤት የሰጠው ውሳኔ ሁሉንም ቀበሌዎች ያላካተተና የተሸራረፈ ውሳኔ ነው በማለት ተቃውሟቸውን በድጋሚ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረባቸውን፣ የሕገ መንግሥትና የክልል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ይገልጻል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው በጥያቄው ላይ ውይይት በማድረግ የቀረበውን ተጨማሪ ጥያቄ ክልሉ ከዚህ በፊት ከፈታው ችግር በላይ ሊሆን እንደማይችል ግንዛቤ በመውሰድ፣ የክልሉ መንግሥት በጀመረው አግባብ ተጨማሪ ጥያቄውን እንዲፈታ የሚል አቋም በመያዙ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ይህንን ውሳኔ በመቀበል ለክልሉ ኃላፊነቱን በመስጠት እንዲወስን ሲል ጠይቋል፡፡ በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ በመወያየትም ምክር ቤቱ ውሳኔውን ተቀብሎ አፅድቆታል፡፡ 

የቅማንት ሕዝብ በአማራ ክልል በስምንት ወረዳዎች በሚገኙ 126 ቀበሌዎች ውስጥ የራስ አስተዳደር ጥያቄ ያነሰ ቢሆንም፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ግን ባካሄደው ጥናት ላይ ተመሥርቶ መጋቢት 2 ቀን 2007 ዓ.ም. የሰጠው ውሳኔ በሁለት ወረዳዎች በሚገኙ 42 ቀበሌዎች ላይ ነው፡፡ የቅማንት ሕዝብ ተወካዮች ለሪፖርተር በጽሑፍ እንደገለጹት፣ የክልሉ መንግሥት ጥያቄያቸውን እየሸራረፈና ተጨማሪ ጥያቄዎችን እያነሱ ባሉት ተወካዮች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ 

‹‹ከዚህ ሁሉ የችግር ጫና ውስጥ የቅማንት ሕዝብ እየገባ ያለው ጥያቄው በይግባኙ መሠረት በፌዴሬሽን ምክር ቤት መመለስ ባለመቻሉ ነው፡፡ ይግባኝ የቀረበለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 251/1993 በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት የማያዳግም ውሳኔ ቢያስተላልፍ ይህ ሁሉ ችግር ውስጥ አይገባም ነበር፡፡ አሁንም በቀረበለት ይግባኝ መሠረት ውሳኔ እንዲያስተላለፍ አቤቱታችንን እናሰማለን፤›› ሲሉ ሰኔ 9 ቀን 2007 በጻፉት ደብዳቤ ፌዴሬሽን ምክር ቤትን ጠይቀዋል፡፡ 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥትና የክልል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ግን በአዋጁ መሠረት ኃላፊነት ቢኖረውም፣ ለክልል መንግሥታት ቀርበው ውሳኔ በተሰጠባቸው የማንነት ጥያቄዎች ቅር በመሰኘት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚቀርቡ አቤቱታዎችን በመመርመር፣ በምክር ቤቱ የውሳኔ ሐሳብ እንደሚያቀርብ በተሻሻለው የምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 1/1999 ኃላፊነት የተሰጠው በመሆኑ የክልሉን ውሳኔ በመመርመር እንደተቀበለው ገልጿል፡፡ 

ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ኃላፊነት በመውሰድ ጥናት ጀምሮ የነበረው አጥኚ ቡድንና የክልሉ ምክር ቤት ባካሄደው ጥናት ላይ በመመሥረት ያሳለፈው ውሳኔ ተመሳሳይነት ያላቸው በመሆኑ፣ ተጨማሪ ጥያቄውን የክልሉ መንግሥት በቀደመው አግባብ ቢመልሰው ችግር እንደማይኖረውም ቋሚ ኮሚቴው እምነቱ እንደሆነ ገልጿል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል ዝዋይ ሐይቅ ደሴት ላይ የሚኖሩት የዛይ ማኅበረሰብ የማንነትና ራስን የማስተዳደር ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡ የምክር ቤቱ የሕገ መንግሥትና የክልሎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ የክልሉ መንግሥትና ምክር ቤት የዛይ ማኅበረሰብ ጥያቄን በተመለከተ ውይይት እያደረጉ መሆኑን በመጥቀሳቸው ጉዳዩ ለክልሉ ተትቷል፡፡ 

 

በደቡብ ክልል በጋብቻ ምክንያት በሐዲቾና በወላቢቾ ጎሳዎች መካከል የተቀሰቀሰውን ከፍተኛ ግጭት፣ የክልሉ ፖሊስ በአስቸኳይ እንዲቀርፍና ጥፋተኞችን ለሕግ እንዲያቀርብ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አሳሰበ፡፡ 

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ሰኔ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ለደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በጻፈው ደብዳቤ፣ የፌዴራል ፖሊስን ወደ አካባቢው ማሰማራት አግባብነት እንደሌለው፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት ኅብረተሰቡ ተረጋግቶና ደኅንነቱ ተጠብቆ እንዲኖር ለማድረግ የሕዝብ አደራና ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስቧል፡፡ 

በዚህ የጎሳ ግጭት ተሳታፊ የሆኑት ሕገወጥ ድርጊት ፈጻሚዎች ላይ ምርመራው ተጣርቶ ለሕግ እንዲቀርቡ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደ ቀድሞ መኖሪያ ቤታቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡ 

በሒዲቾና በወላቢቾ ጎሳዎች መካከል ግጭቱ የተቀሰቀሰው ከግንቦት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ወዲህ ሲሆን፣ ምክንያቱ ደግሞ የሐዲቾ ጎሳ አባል የሆነ ግለሰብ ከወላቢቾ ጎሳ አባል ከሆነች አንዲት ግለሰብ ጋር በመጋባቱ ነው፡፡ 

ይህንን ጋብቻ ያልተቀበሉ የወላቢቾ ጎሳ አባላት፣ ‹‹እንዴት አናሳ ዘር ከእኛ ዘር ይጋባል?›› በማለት በአንድ ላይ በመነሳት በሐዲቾ ጎሳ አባላት ላይ ጥቃትና የንብረት ውድመት መፈጸማቸውን ከአካባቢው ለፌዴራል መንግሥት ተቋማት አቤት ለማለት ተወክለው የመጡ ግለሰቦች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

የወላቢቾ ነዋሪዎችን ቤቶችና ንብረቶች በማቃጠልና ያገኙትን በመደብደብ፣ በበርካታ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው በተጨማሪ ሰዎችን መግደላቸውን ተወካዮቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የወንዶ ገነት ወረዳ ፖሊስ ኃላፊ የተፈጠረው ግጭት በአሁኑ ወቅት መቀረፉን ገልጸው፣ የሞተ ሰው አለ መባሉን አስተባብለዋል፡፡ 

የፖሊስ ኃላፊው ይህንን ይበሉ እንጂ፣ የሐዲቾ ጎሳ አባላት በርካቶቹ እስካሁን ወደ መኖሪያቸው እንዳልተመለሱና አሁንም ሥጋት ውስጥ መሆናቸውን ተወካዮቹ ይናገራሉ፡፡  

 

በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ተብለው የሚጠበቁ ስምንት የዓለም አቀፍ ብራንድ ሆቴሎች መምጣትን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ ከአሥር ዋና ዋና የአፍሪካ አገሮች ውስጥ አንዷ

ለመሆን እንደቻለች ታወቀ፡፡ በአፍሪካ በሆቴል ኢንቨስትመንት ውስጥ ስማቸው ከሚጠቀስ ኩባንያዎች መካከል ሒልተን ዓለም አቀፍ፣ በአዳዲስ ሆቴሎች ግንባታና በመኝታ ክፍሎች ብዛት ቀዳሚውን ሥፍራ መያዙን ጥናቶች ጠቁመዋል፡፡ 

ላለፉት አራት ዓመታት ‘አፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም’ በሚል ርዕስ ዓመታዊ ጉባዔ በማካሄድ ላይ የሚገኘው የእንግሊዙ ቤንች ኤቨንትስ ይፋ ባደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ መሠረት፣ በኢትዮጵያ የሚገነቡት ስምንት ሆቴሎች በጠቅላላው ከ1,300 በላይ ክፍሎች እንደሚኖሯቸው ይጠበቃል፡፡ በአንፃሩ በአፍሪካ ከ270 በላይ ሆቴሎች እንደሚገነቡ ሲጠበቅ፣ ከ30 ሺሕ ያላነሱ ክፍሎች እንደሚይዙም ቤንች ኤቨንትስ ጥናቶችን ጠቅሶ ያሠራጨው መግለጫ ያመለክታል፡፡ 

በአፍሪካ ግብፅ በ18 አዳዲስ ሆቴሎች ግንባታ የመጀመሪያውን ረድፍ በመያዝ እየመራች ትገኛለች፡፡ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ አልጄሪያ፣ ቱኒዝያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሊቢያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሩዋንዳ በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ አሥር ያለውን ደረጃ በመያዝ ግብፅን ይከተላሉ፡፡ በእነዚህ የሆቴል ግንባታዎች ላይ ትልቁን ድርሻ የያዘው ሒልተን ዓለም አቀፍ መሆኑም ታውቋል፡፡ በክፍሎች ብዛት ቀዳሚነቱን የያዘው ሒልተን ከ7,200 በላይ ክፍሎች ያሏቸውን 29 ሆቴሎች በአፍሪካ እየገነባ እንደሚገኝ ሲገለጽ፣ ማሪዮት ሆቴል በበኩሉ በ36 ሆቴሎች እየመራ ቢሆንም፣ በክፍሎች ብዛት ግን 6,412 ላይ በመወሰኑ ከሒልተን ባሻገር በካርልሰን ሬዚዶር ተቀድሟል፡፡ 

በሌላ በኩል ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ተካሂዶ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስቦ የነበረው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም፣ በመጪው ዓመት መጀመሪያ ላይ በድጋሚ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የፎረሙ አዘጋጆች ከወራት በፊት ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ለአራተኛ ጊዜ ተካሂዶ በነበረው ፎረም ሪከርድ የሰበረ ተሳትፎና ያልተጠበቀ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ሽፋን ማግኘቱ በአዲስ አበባ በድጋሚ እንዲካሄድ ለመወሰን ምክንያት ሆኗል፡፡ ከዚህም ባሻገር በሆቴልና በሌሎች የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ ትልልቅ ኩባንያዎች ያሳዩት ፍላጎትና ተሳትፎም ጉባዔው በድጋሚ አዲስ አበባ እንዲካሄድ ማስገደዱን፣ ፎረሙን የሚያዘጋጀውና መገኛው እንግሊዝ የሆነው ቤንች ኤቨንትስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ማቲው ዌይስ ገልጸው ነበር፡፡ 

ከአምስት ዓመት በፊት ጀምሮ የአፍሪካ ሆቴሎች ኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ የቆየው አገር በቀሉ ካሊብራ ሆስፒታሊቲ ኮንሰልታንሲ ኤንድ ቢዝነስ ኩባንያ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ ስለፎረሙ በድጋሚ መምጣት ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የካሊብራ አማካሪ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነዋይ ብርሃኑ፣ በመጪው ዓመት መስከረም ወር አጋማሽ ላይ እንዲካሄድ ቀነ ቀጠሮ የተያዘለት ፎረም እንዲመጣ መወሰኑ እንደማይቀር ከዚህ ቀደም የታየው ስኬታማ ዝግጅት ጠቋሚ እንደነበር መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

ከሆቴሎች ባሻገር በካሊብራ አማካሪ ኩባንያ በኩል ድርድር እያደረጉ ከሚገኙ መካከል ሦስት ተጨማሪ ሆቴሎች፣ ቀጣዩ ፎረም ከመካሄዱ በፊት ስምምነት ይፈጽማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ነዋይ ለሪፖርተር መግለጻቸውን በመጥቀስ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ በሸራተን አዲስ ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ፎረም፣ በቅርቡ ሥራ የጀመረው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትና የኢትዮጵያ ቱሪዝም ምክር ቤት እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተሰምቷል፡፡ ቤንች ኤቨትንስ ኩባንያም ለእነዚህ መንግሥታዊ ተቋማት ፎረሙ በድጋሚ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ የኩባንያው ቦርድ መወሰኑን በደብዳቤ እንዳሳወቃቸው ታውቋል፡፡

በዚህ ቀደም የተካሄዱትን የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረሞችን ሞሮኮ አንድ ጊዜ፣ ኬንያ ሁለት ጊዜ ያስተናገዱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ መጪውን ጨምሮ ለሁለተኛ ጊዜ በማስተናገድ ኬንያን ትስተካከላለች፡፡ ከስድስት መቶ በላይ ተሳታፊዎች፣ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ዓለም አቀፍ ሆቴሎችና አማካሪዎች፣ እንዲሁም የሆቴል አስተዳዳሪዎች በስፖንሰርነት የታሰተፉበት ከፍተኛው ፎረም በአዲስ አበባ መካሄዱን ቤንች ኤቨንትስ አስታውቋል፡፡ በመጪው ፎረም በስፖንሰርነት ለመሳተፍ ከወዲሁ ከተመዘገቡት መካከል ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ግንባር ቀደምት ሆኗል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎች ቁጥር ሦስት ብቻ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት አገሪቱ ይኖራታል ተብሎ የሚጠበቀው ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የሚያሟሉ ብራንድ ሆቴሎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር ትንበያዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአገሪቱ ያሉ ጠቅላላ ባለ ኮከብ ሆቴሎች ቁጥር 120 ሲሆን፣ ያሏቸው የመኝታ ክፍሎች ብዛትም ከአንድ ሺሕ በታች ነው፡፡ 

 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከግንቦት 1988 እስከ ሚያዝያ 1997 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ጊዜያት በሕገወጥ መንገድ የተያዙ ይዞታዎችን ሕጋዊ ለማድረግ ባወጣው መመርያ ለመስተናገድ ከቀረቡ 91 ሺሕ ጥያቄዎች፣ ለተወሰኑት ሕጋዊ ካርታ ተሰጠ፡፡ 

የአዲስ አበባ ይዞታ አስተዳደር ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የቀረቡለት ጥያቄዎች ላይ ባካሄደው ማጣራት 32 ሺሕ የሚጠጉት ጥያቄዎች ቦታውን የያዙት ከ1997 ዓ.ም. በኋላ በመሆኑ ውድቅ ሲያደርግ፣ በበጀት ዓመቱ ለአምስት ሺሕ ሕገወጥ ባለይዞታዎች ሕጋዊ ካርታ መስጠቱ ታውቋል፡፡  

የአዲስ አበባ ከተማ ይዞታ አስተዳደር ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ ላቀው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በሕገወጥ መንገድ የተያዙ ቦታዎች 44,547 ናቸው፡፡ ነገር ግን ምዝገባ በሚካሄድበት ወቅት ከ91 ሺሕ በላይ ጥያቄዎች መቅረባቸውን አቶ ደረጀ ገልጸው፣ 32 ሺሕ ያህሉ በመመርያው መሠረት ሊስተናገዱ የማይችሉ ናቸው ብለዋል፡፡

በዚህ ወር መጨረሻ በሚጠናቀቀው የበጀት ዓመት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ አምስት ሺሕ ቦታዎች ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሰጥቷል፡፡ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ አጠቃላይ ሥራውን በዚህ በጀት ዓመት የማጠናቀቅ ዕቅድ ቢኖረውም፣ የማጣራት ሥራው በመብዛቱ በሚቀጥለው በጀት ዓመት ቀጣይ ሥራዎች እንደሚኖሩ አቶ ደረጀ አስረድተዋል፡፡

ከ1988 እስከ 1997 ዓ.ም. ባለው ጊዜ የተያዙ ይዞታዎች ቢሆኑም፣ ከማስተር ፕላኑ ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸው 2,346 ባለይዞታዎች ምትክ ቦታ እንዲሰጣቸው ለመሬት ባንክና ማስተላለፍ ኤጀንሲ መላካቸውን አቶ ደረጀ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከሕጋዊ ይዞታ ውጪ አስፋፍተው መሬት ከያዙና የይጠቃለልኝ ጥያቄ ካቀረቡ 14 ሺሕ ባለይዞታዎች ውስጥ፣ 3,160 የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንደታተመላቸው፣ ከሁለት ሺሕ በላይ የሚሆኑት ከማስተር ፕላኑ ተቃርኖ ያለው ይዞታ አጠቃለው በመያዛቸው ጥያቄዎቻቸው ተቀባይነት እንዳላገኙ አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1988 ዓ.ም. በፊት የተያዙ 65 ሺሕ ሰነድ አልባ ይዞታዎች ጥያቄ ማስተናገዱም ይታወቃል፡፡ ከዚህ በኋላ ከ1988 እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስ የተያዙ ቦታዎች ከማስተር ፕላኑ ጋር ተቃርኖ የሌላቸው መሆኑ ከተረጋገጠ እንዲያስተናግዱ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ነገር ግን አሁንም ቢሆን ከ1997 ዓ.ም. በኋላ በሕገወጥ መንገድ ይዞታ የያዙ ግለሰቦች መንግሥት እንዲያስተናግዳቸው በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

 

የተከሰሱት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እስር ተፈረደባቸው

መንግሥት በጠራው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ሁከት ፈጥረዋል ተብሎ ክስ የተመሠረተባቸው የሰማያዊ ፓርቲ አባላት፣ በሁለት ወራት እስራት እንዲቀጡ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምብድ ችሎት ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ሰጠ፡፡

በሊቢያ አይኤስ የተባለው ቡድን በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ ለማውገዝ፣ መንግሥት ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ በጠራው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ረብሻ በመፍጠር፣ በመሳደብና ድንጋይ በመወርወር ሰላማዊ ሠልፉን አውከዋል ተብለው የተከሰሱት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ወይንሸት ሞላ፣ ኤርሚያስ ፀጋዬ፣ ዳንኤል ተስፋዬና ቤተልሔም አካለወርቅ መሆናቸው ይታወሳል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ ሊከላከሉ እንዳልቻሉ ገልጾ ጥፋተኛ ካላቸው በኋላ፣ የቅጣት አስተያየት ጠይቋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ቅጣቱ ከብዶ እንዲቀጡ አመልክቷል፡፡ ተከሳሾቹም የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን፣ በተለይ ወይንሸት ሞላ ረብሻ ተፈጠረ በተባለበት ዕለት ጠዋት የታሰረች መሆኗንና የታሰረችበትን ፖሊስ ጣቢያ ገልጻ ቅጣቱ እንዲቀልላት ጠይቃለች፡፡

ፍርድ ቤት በሰጠው ፍርድ ቅጣቱ ከብዶ እንዲቀጡ የሚለው የዓቃቤ ሕግን የቅጣት ማክበጃ አስተያየት የተቀበለ ቢሆንም፣ በቡድን ስለመረበሻቸው ያቀረበው ማስረጃ እንደሌለ ገልጿል፡፡ በመሆኑም እያንዳንዳቸው እጃቸው ከተያዘበት ጀምሮ ያለው ጊዜ ተቆጥሮ፣ በሁለት ወራት እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾቹ ሁለት ወራት ከአንድ ቀን የታሰሩ በመሆናቸው በዕለቱ እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ፍርደኞቹ የማስፈቻ ትዕዛዝ ተዘጋጅቶላቸው ከማረሚያ ቤት የተፈቱት ሰኔ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ቢሆንም፣ ከማረሚያ ቤት ሲወጡ ተይዘው በፀጥታ ኃይሎች ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውን ሰማያዊ ፓርቲ አስታውቋል፡፡ 

 

 

መድረክ የሟች አባላቱ ቁጥር አራት መድረሱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ግንቦት 16 ቀን 2007 ከተካሄደው አምስተኛውን ዙር ጠቅላላ ምርጫ በኋላ፣ ለሞት የተዳረጉ አባላቱ ቁጥር አራት መድረሱን አስታወቀ፡፡

በዚህም መሠረት ቀደም ሲል መሞታቸው ከተነገረው ሦስት የመድረክ አባላት በተጨማሪ፣ በደቡብ ክልል በሐድያ ዞን ሶሮ ወረዳ በዳና ቶራ ቀበሌ ነዋሪና የመድረክ አባል ድርጅት የሆነው የኢትዮጵያ ማኅበረ ዴሞክራሲ ደቡብ ሕዝቦች አንድነት ፓርቲ (ኢማዴ-ደሕአፓ) መሠረታዊ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ ብርሃኑ ኤረቦ መገደላቸውን አስታውቋል፡፡ 

‹‹በ2007 ጠቅላላ ምርጫ በቅስቀሳ ላይ ተሰማርተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ የቆዩት አቶ ብርሃኑ ኤረቦ፣ ሰኔ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ በመኖሪያ መንደራቸው በተፈጸመባቸው ድብደባ ከተገደሉ በኋላ ወንዝ ውስጥ ተጥለው ተገኝተዋል፤›› ሲሉ የመድረክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በሥፍራው ካሉ የፓርቲው አደረጃጀቶች መረጃ እንደሚሰባሰብ የገለጹት አቶ ጥላሁን፣ ‹‹መጀመርያ ቀን ላይ በአካባቢው ያሉ ፖሊሶችንና ሌሎች ካድሬዎችን ያካተተ አካል እየተንቀሳቀሱ፣ ሟችንና ሌሎች ለመድረክ የምርጫ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አባላትና ወጣቶችን ‹የማዳበሪያ ሒሳብ እንዳይከፈል ሕዝቡም በመንግሥት ላይ እንዲያምጽ ቅስቀሳ እያደረጋችሁ ነው፤› በማለት ሟችንና ወጣቶችን ለማስፈራራትና ለማሰር ሲንቀሳቀሱ ነበር፤›› በማለት፣ አጋጠመ ያሉትን አስረድተዋል፡፡

‹‹በተለይ ‹ማዳበሪያን በሚመለከት ዕዳው እንዳይከፈል ያደረጋችሁት እናንተ ናችሁ› ተብለው ፖሊስ ሊይዛቸው ሲል ሸሽተው ነበር፤›› ያሉት አቶ ጥላሁን፣ ‹‹ሟች ሸሽቶ ከቆየበት ሥፍራ ምሽት ላይ ወደ ቤቱ በሚያመራበት ወቅት ነው ግድያው የተፈጸመበት፤›› በማለት የፓርቲውን አባል የአሟሟት ሁኔታ አስረድተዋል፡፡

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በሥፍራው የመድረክ ተወካይና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ የነበሩት ግለሰብ ስለሁኔታው ለማጣራት ፖሊስ ጣቢያ ቢሄዱም፣ በፖሊስ ጣቢያው የዕለት ሁኔታ መመዝገቢያ ላይ የተመዘገበው ‹‹ሰክሮ ውኃ ውስጥ ወድቆ›› የሚል እንደሆነ መመልከታቸውን፣ አቶ ጥላሁን ከደረሳቸው ሪፖርት ለመረዳት መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹የምናካሂደው ሰላማዊ ትግል ብዙ መስዋዕነት እንደሚያስከፍለን እናውቃለን፤›› ያሉት አቶ ጥላሁን፣ ‹‹ቢሆንም ግን ሰላማዊውን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን፤›› በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡

ሟች አቶ ብርሃኑ ኤረቦ የ40 ዓመት ጎልማሳና የአምስት ልጆች አባት እንደሆኑ መድረክ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል፡፡

መድረክ ከምርጫው ዕለት ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሚዳ ቀኝ ወረዳ አቶ ጊዲሳ ጨመዳ፣ በምዕራብ  አርሲ ዞን ቆራ ወረዳ አቶ ገቢ ጥቤ፣ እንዲሁም በትግራይ ክልል ምዕራብ ትግራይ ዞን በማይካድራ ከተማ አቶ ታደሰ አብርሃ የተባሉ ዕጩዎቹ መገደላቸውን ቀደም ብሎ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

 

ማዕድን ሚኒስቴር በአገሪቱ የሕግ አግባብ መሠረት ባለመሥራቱ፣ መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ የማዕድን ማምረት ሥራ ላይ ከተሰማራው ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማግኘት የሚገባውን ከ429 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማሳጣቱን የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስታወቀ፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በማዕድን ሚኒስቴር ላይ በ2006 ዓ.ም. አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ላይ ባደረገው የክዋኔ ኦዲት ነው መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ ማጣቱን ያረጋገጠው፡፡ 

የማዕድን ሥራ አዋጅን በተመለከተ የወጣው የ1986 ዓ.ም. አዋጅ ከከበሩ ማዕድናት ሽያጭ አምስት በመቶ የሮያሊቲ ክፍያ እንደሚወስን፣ ባልከበሩ ማዕድናት ላይ ምንም የሚለው ነገር እንደሌለ የኦዲተሩ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ያስረዳል፡፡

ይህ አዋጅ ግን በአዋጅ ቁጥር 678/2002 መሻሻሉን በዚህ መሠረትም የከበሩ ማዕድናት ላይ ስምንት በመቶ የሮያሊቲ ክፍያ መጣሉን፣ ያልከበሩ ማዕድናት ላይ ስድስት በመቶ መጣሉን ሪፖርቱ ያትታል፡፡

ይሁን እንጂ ማዕድን ሚኒስቴር ከሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ የከበሩና በከፊል የከበሩ ማዕድናት ላይ አምስት በመቶ ብቻ ሮያሊቲ ክፍያ በመሰብሰቡ፣ ከ2004 ዓ.ም.  እስከ 2006 በጀት ዓመት ከሚድሮክ የወርቅ ሽያጭ መንግሥት ሊያገኝ የሚችለውን 252.9 ሚሊዮን ብር ማጣቱን፣ እንዲሁም ካልከበሩ ማዕድናት በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ብቻ 413,394 ብር ማጣቱን፣ በድምሩ በሁለት ዓመታት ውስጥ 253.37 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ገቢ መደረግ የነበረበት የሮያሊቲ ገንዘብ አለመሰብሰቡን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

በተጨማሪም ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በ2000 ዓ.ም. ማምረት የጀመረ ቢሆንም፣ ማዕድን ሚኒስቴር ግን ይህንን ተቋም በየወቅቱ እየተከታተለ ሒሳባቸውን እንዳልመረመረ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ማረጋገጡን ይገልጻል፡፡ ይህም በመሆኑ በሮያሊቲ ሥሌቶች ላይ በሕግ ማሻሻያዎች የሚመጡ ለውጦችን በመከተል የመንግሥትን ገቢ ለማስገባት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዳልቻለ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት በሚድሮክ የወርቅ ማዕድን አክሲዮን ማኅበር ላይ ያለውን የነፃ ድርሻ በሕግ አግባብ ማስላት ባለመቻሉ፣ እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ 108.7 ሚሊዮን ብር እንዲሁም እስከ መጋቢት 2006 ዓ.ም. ድረስ 67.4 ሚሊዮን ብር በድምሩ 176.2 ሚሊዮን ብር አገሪቱ ማጣቷን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

ይህ በመሆኑም የተፈጠረውን ስህተት በማረም መንግሥት ያጣው ገንዘብ እንዲመለስ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ማዕድን ሚኒስቴሩን አሳስቧል፡፡

 

ከ17.7 ሚሊዮን ብር በላይ መመዝበሩ ተጠቅሷል

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደቡብ ሱዳን ሊሚትድ ጁባ ቅርንጫፍ ከ17.7 ሚሊዮን ብር በላይ በተጭበረበረ መንገድ ለግለሰቦች እንዲውል አድርገዋል ተብለው የሙስና ክስ የተመሠረተባቸው አምስት የባንኩ ሠራተኞች፣ ዋስትና

ተከልክለው ወደ ማረሚያ ቤት ወረዱ፡፡ አንዲት የቅርንጫፍ ባንኩ ከፍተኛ ኦዲተር በዋስ ተለቀቁ፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው የባንኩ ሠራተኞች፣ የሒሳብ ሹም አቶ ረሚላ ለወይ ኡስማን፣ የደንበኞች ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም ብርሃን ዓለም ስምኦን፣ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ሀብታሙ ዮሴፍ ማርዬ፣ ማኔጂንግ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ሚካኤል ተክለ እግዚ ገብረ ማርያም፣ የንግድ አገልግሎት መኰንን አቶ ደስታው ፈንታሁን መንበር (ያልተያዙ)፣ ዋና ኦዲተር ወ/ሮ ሙሉሸዋ ክብረት፣ እንዲሁም አቶ መሐመድ ሁሴን ጣቢር (ያልተያዙ) እና አቶ ሁሴን ለወይ ኡስማን የተባሉ ግለሰቦች ናቸው፡፡ 

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ሲቴፕ ፎር ትሬድ ኤንድ ኢንቨስትመንት ካምፓኒ ሊሚትድ የተባለ ድርጅት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጁባ ቅርንጫፍ ደንበኛ ነው፡፡ በባንኩ በኩል 4,360,000 ዶላር ኤልሲ በደቡብ ሱዳን ማዕከላዊ ባንክ ይፈቀድለታል፡፡ ዶላሩ የሚለቀቅለት በሦስት ጊዜ ክፍያዎች ነው፡፡ ክፍያው የሚፈጸመው ገንዘቡ ኬንያ ወደሚገኘው ስታንቢክ ባንክ ከተላለፈ በኋላ ነው፡፡ የመጀመርያው 1,453,33 ዶላር ተልኮለታል፡፡ ለድርጅቱ የሚላከው ዶላር ከደቡብ ሱዳን ፓውንድ ጋር ተመጣጣኝ የሆነና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደቡብ ሱዳን ማዕከላዊ ባንክ ካለው ሒሳብ ተቀንሶ መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡

ነገር ግን አንደኛ ተከሳሽ አቶ ረሚላ ለድርጅቱ የተላከውን የገንዘብ መጠን መቀነስ ሲገባው ሳይቀንስ መቅረቱን ክሱ ያክላል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ሒሳብ ሲሠራ (Reconciliation) ሳይቀነስ የቀረው ገንዘብ ተንጠልጣይ ሆኖ ሲያየው ማዕከላዊ ባንኩ እንዲቀንስ ማድረግ ቢገባውም አለማድረጉ ክሱ ጠቅሷል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ በሌሉበት ክሱ በተመሠረተባቸው አቶ መሐመድ ሁሴን ጣቢር ስም በ200 የደቡብ ሱዳን ፓውድ አካውንት እንዲከፍቱ ማድረጋቸውም ተጠቅሷል፡፡ በመቀጠልም በተለያዩ ጊዜያት በድምሩ 3,008,813 የደቡብ ሱዳን ፖውንድ የያዙ አራት ቼኮች ወደ  ኬንያ ንግድ ባንክ ለቼክ ማጣራት በማዕከላዊ ባንኩ በኩል ሲላኩ፣ የኬንያ ባንክ በግለሰቡ ገንዘብ እንደሌለው የገለጸ ቢሆንም አንደኛው ተከሳሽ ቼኮቹንና ተያያዥ ቅጾችን በማጥናት ግለሰቡ ገንዘብ ያለው ማስመሰሉ ክሱ ያብራራል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ የዴቢት ትኬት በማዘጋጀትና ከሁለተኛ ተከሳሽ ጋር አቶ ፍፁም ብርሃን ጋር በጣምራ ፈርመው የተንጠለጠለው ገንዘብ መሐመድ ሁሴን በተባለ ተከሳሽ ስም ወደ ተከፈተው ሒሳብ እንዲገባ በማድረግ በባንኩ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ በአጠቃላይ ገንዘቡ በኢትዮጵያ ብር ሲሰላ 17,768,589 ብር መሆኑን፣ ተከሳሾቹ በሥልጣን ያላግባብ መጠቀም የሙስና ወንጀል ክስ እንደተመሠረተባቸው የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ተጠርጣሪ ተከሳሾቹ ከላይ የተገለጸውን ገንዘብ በሕገወጥ መንገድ የተገኘ መሆኑን እያወቁ፣ በሐሰተኛ መንገድ በስድስተኛ ተከሳሽ አቶ መሐመድ ስም በተከፈተ ሒሳብ የተቀመጠውን ገንዘብ ከተለያዩ አካውንቶች የተላኩ በማስመሰልና ወደተለያዩ የባንክ ሒሳቦች አዘዋውረናል፡፡ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን፣ አንድ ባለሁለት መኝታ የኮንዶሚኒየም ቤት በመግዛት፣ በአጠቃላይ አንደኛ ተከሳሽና ስድስተኛ ተከሳሽ የአንደኛ ተከሳሽን ወንድም ሰባተኛ ተከሳሽ አቶ ሁሴን ለወይንን በመጠቀም፣ ገንዘቡን ማቀናነሳቸውንና በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስለው በማቅረብ የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

ሁለተኛ ተከሳሹ አቶ ፍፁም ብርሃን ዓለም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 411 (2)ን በመተላለፍ የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት በሕጋዊ መንገድ ማግኘት ከሚገባቸው በላይ 6,620,600 ብር ይዘው መገኘታቸውንና ይኼም የሙስና ወንጀል መሆኑን ክሱ ይገልጻል፡፡ ሦስተኛ ተከሳሽ አቶ ሀብታሙ ዮሴፍም ማግኘት ከሚገባቸው በላይ 8,298,880 ብር ከሕጋዊ ገቢያቸው በላይ ይዘው በመገኘታቸውን፣ አራተኛም ተከሳሽ አቶ ሚካኤል ተክለ እግዚም 27,930,429 ብር ከሕጋዊ ገቢያቸው በላይ ይዘው በመገኘታቸው፣ አቶ ደስታው ፋንታሁንም 2,684,876 ብር ከሕጋዊ ገበያቸው በላይ ይዘው በመገኘታቸው፣ በፈጸሙት ምንጩ ያልታወቀ ንብረትና ገንዘብ ይዞ መገኘት የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

በቅርንጫፉ ዋና ኦዲተር የነበሩት ወ/ሮ ሙሉሸዋ ክብረት ሒሳቦችን በአግባቡ ባለመቆጣጠራቸውና የሥራ ኃላፊነትን ባለመወጣት የሚፈጸም የወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡ ተጠርጣሪ ተከሳሾቹ ችሎት ቀርበው ክሱ ከተነበበላቸው በኋላ በጠበቆቻቸው አማካይነት ክሱ ዋስትና እንደማያስከለክል፣ ምክንያቱ ደግሞ አዲስ በወጣው የኮሚሽኑ አዋጅ መሠረት ዋስትና የሚከለክል አንቀጽ መሻሩን ጠቅሰው በዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የተጠቀሰው አንቀጽ ዋስትና እንደሚከለክልና በአዲሱ አዋጅ ዋስትናን የሚመለከተው አንቀጽ እንዳልተሰረዘ በመግለጽ ጥያቄውን ተቃውሟል፡፡ ፍርድ ቤቱ የደቂቃዎች ረፍት ወስዶ በሁለቱ ወገኖች ክርክር ላይ ከተወያየ በኋላ፣ በድጋሚ በመሰየም ከኦዲተር በስተቀር ሌሎቹን ተከሳሾች ዋስትና ከልክሏቸዋል፡፡ ኦዲተሯም ዋስትና ተፈቅዶላቸዋል፡፡ የክስ መቃወሚያ ለመስማት ለሐምሌ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

 

የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በደረሱት የአስተዳደራዊ በደል ጥቆማዎች ላይ ተመሥርቶ በሚያደርገው ምርመራ የመፍትሔ ሐሳቦችን ቢያቀርብም፣ አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች እምቢተኝነት እያሳዩ መሆናቸውን አስታወቀ፡፡ ከእነዚህም መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ገለጸ፡፡

 

ዋና የሕዝብ እንባ ጠባቂዋ ወ/ሮ ፎዚያ አሚን የተቋማቸውን የአሥር ወራት የሥራ ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት፣ በአስተዳደር ጥፋት ምክንያት የደረሰ በደል እንዲታረም የተመርማሪ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ትብብርና ድጋፍ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የአስተዳደር በደል አቤቱታዎች ሲደርሱት አልያም በተደጋጋሚ ከሚደርሰው ጥቆማ በመነሳት የራሱን ምርመራ እንደሚያደርግ የገለጹት ወ/ሮ ፎዚያ፣ በምርመራው መሠረት የመፍትሔ ሐሳቦችን ለሚመለከታቸው ተቋማት እንደሚልክና የመፍትሔ ተቀባይነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም የተወሰኑ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች በተቋሙ የምርመራ ውጤት ላይ ተንተርሶ በተላከላቸው የመፍትሔ ሐሳቦች መሠረት አለመፈጸም ወይም የማይፈጸሙበት በቂ ምክንያት ካላቸው ለተቋሙ ያለመግለጽና በምርመራ ሒደት አስፈላጊውን ትብብር ያለማሳየት እንቢተኝነት እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህም ተቋማት መካከል በተደጋጋሚ ስሙ የተገለጸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው፡፡ ከአስተዳደሩ አካላት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና ክፍለ ከተሞች ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም የኦሮሚያ የአርሲ ዞን አስተዳዳር ጽሕፈት ቤት፣ የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳር ጽሕፈት ቤት፣ የሐዋሳ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና በሐረሪ ክልል የፍትሕና የፀጥታ ጉዳይ ቢሮ በእነዚህ ችግሮች የተጠቁ መሆናቸውን ዋና እንባ ጠባቂዋ ወ/ሮ ፎዚያ ገልጸዋል፡፡

የተገለጹት ተቋማት በቀረበላቸው የመፍትሔ ሐሳቦች መሠረት የእርምት ዕርምጃ ባለመውሰዳቸው ልዩ ሪፖርት ለፓርላማው የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳዳር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር መላካቸውን የጠቀሱት ወ/ሮ ፎዚያ፣  ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው ክትትል በደሎቹ በከፊል የታረሙ መሆኑን ነገር ግን ሙሉ በሙሉ አለመቀረፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ራሱ ተቋሙ ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ለምን እነዚህን ተቋማት እንደማያስቀጣ የተጠየቁት ዋና እንባ ጠባቂዋ፣ በአስተዳደራዊ በደል አቤቱታ ላይ ምርመራን መሠረት ያደረገ የመፍትሔ ሐሳብ አቤቱታ ለቀረበበት ተቋም የሚቀርብ መሆኑን ገልጸው፣ ተቋሙ በቂ ምክንያት ካለው ይኼንኑ ገልጾ የመፍትሔ ሐሳቡን ላለመተግር እንደሚችል በአዋጁ መደንገጉን ተናግረዋል፡፡

‹‹በቂ ምክንያት ካለው›› የሚለው ሐረግ ለትርጉም ክፍት በመሆኑ ዕርምጃ ለመውሰድ እንዳላስቻላቸው የገለጹት ወ/ሮ ፎዚያ፣ ይኼን ችግር ለመቅረፍ አዋጁን ለማሻሻል በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡