ስታንዳርድ ባንክ ኢትዮጵያዊቷን የባንክ ባለሙያ ወይዘሪት ጣይቱ ወንድወሰንን ለኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤቱ ሾመ

በአፍሪካ ባካበተው ሀብት ቁንጮ በመባል የሚታወቀው የደቡብ አፍሪካው ስታንዳርድ ባንክ፣ የኢኮኖሚና የባንክ ባለሙያዋን ወይዘሪት ጣይቱ ወንድወሰንን የኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤቱ ተጠሪ አድርጎ ሾመ፡፡
ወይዘሪት ጣይቱ የግዙፉ ባንክ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን የኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ከተሾሙ ቢቆዩም፣ የጽሕፈት ቤቱ በይፋ ሥራ መጀመር በተበሰረበት ጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ወቅት ሹመታቸው ታውቋል፡፡ ስታንዳርድ ባንክ የጽሕፈት ቤቱን አድርሻ ቦሌ አካባቢ፣ ከሞናርክ ሆቴል አጠገብ በሚገኘው ፕላኔት ሌን ታወር ሕንፃ ላይ አድርጓል፡፡
የስታንዳርድ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቤን ክሩገር የጽሕፈት ቤቱን መከፈት በማስመልከት እንደተናገሩት፣ ስታንዳርድ ባንክ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ ደንበኞቹ ድልድይ ሆኖ ይሚሠራል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ በሚሰጠው መመርያ መሠረት ጽሕፈት ቤቱ እንደሚመራ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የኢነርጂ እምብርት በመሆን ላይ እንደምትገኝ ያስታወቁት ክሩገር፣ ወደፊት የኃይል ኤክስፖርት የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ አስገኝ እንደሚሆንም አክለዋል፡፡
ወይዘሪት ጣይቱ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳብራሩት፣ ባንኩ ትኩረት ከሚያደርግባቸው መስኮች መካከል የኢነርጂ፣ የመሠረተ ልማት፣ የአግሪ ቢዝነስና የፍጆታ ሸቀጦች ትልቁን ቦታ ይይዛሉ፡፡ የጽሕፈት ቤቱ መከፈት ከደንበኞች እየመጣ ያለውን ጥያቄ ለማስተናገድ ስለሆነ ለጥያቄያቸው ምላሽ እንደሚሰጥ አብራርተዋል፡፡ ‹‹እዚህ የመጣነው ሰዎች እንዲያውቁን፣ ገበያውን ለመረዳት፣ የጥናት አቅማችንን ለማሳደግ፣ ነገሮች እንዴት እንደሚጓዙ ለማየትና ኢኮኖሚው እንዴት እንደሚንቀሳቀስ ለመረዳት ነው፤›› ያሉት ኃላፊዋ፣ የባንኩ ደንበኞች በዚህ አገር ለመሠማራት ቢፈልጉም ድጋፍ ለመስጠት ባንኩ ጽሕፈት ቤት ከፍቷል ብለዋል፡፡ ባንኩ ከአፍሪካ በተጨማሪ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በእስያ፣ በደቡብ አሜሪካና በሌሎችም አገሮች ደንበኞች እንዳፈራ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ተወልደው ያደጉት ወይዘሪት ጣይቱ በአሜሪካ የኢኮኖሚክስና የፋይናንስ ትምህርቶችን ተከታትለዋል፡፡ በአሜሪካ ታዋቂና ግዙፍ ከሆኑት መካከል በኒው ዮርክ ፌደራል ሪዘርፍ ባንክ፣ እንዲሁም በጂፒ ሞርጋን ባንክ በኮርፖሬት ባንክ ዘርፍ በማገልገል የካበተ ልምድ አላቸው፡፡ በኒው ዮርክ ሪዘርቭ ባንክ በነበራቸው ቆይታ ወቅት የአሜሪካ ባንኮችን ጨምሮ የዓለም የፋይናንስ ተቋማትን ቀውስ ውስጥ የከተተውን አጋጣሚ አስተናግደዋል፡፡
ከስምንት ዓመት በፊት የተከሰተው ቀውስ ሌህማን ብራዘርስ የተባለውን የአሜሪካ ባንክ የውኃ ሽታ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ የኒው ዮርክ ሪዘርቭ ባንክ በወቅቱ የተከሰተውን ቀውስ የማጣራት ተግባር እንዲያከናውን በተደረገበት ወቅት ወይዘሪት ጣይቱ የባንኩ ባልደረባ ነበሩ፡፡
ስታንዳርድ ባንክን ጨምሮ የናይጄሪያው ኤኮ ባንክ፣ የእንግሊዙ ኤችኤስቢሲ፣ የህንዱ ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ ኦፍ ኢንዲያ ጽሕፈት ቤቶቻቸውን በአዲስ አበባ ከከፈቱት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡