መንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ 50 በመቶ እንደሚጨምር ይፋ አደረገ

መንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ 50 በመቶ እንደሚጨምር ይፋ አደረገ

ፋብሪካዎች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል

መንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ከሚያወጣው ወጪ ባነሰ ታሪፍ እየደጎመ ሲያቀርብ መቆየቱን በመግለጽ፣ በአሁኑ ወቅት ቢያንስ ወጪውን የሚሸፍን ታሪፍ ማስከፈል በማስፈለጉ 50 በመቶና ከዚያም በላይ ሊደርስ የሚችል ጭማሪ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡ 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ እንዳስታወቁት፣ መንግሥት ለበርካታ ዓመታት በድጎማ ሲያቀርበው የቆየው የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ በጣም ዝቅተኛ ነበር፡፡ ዝቅተኛ ብቻም ሳይሆን በአሁኑ ወቅት ኃይል አምርተው ለመንግሥት ለመሸጥ ፍላጎት ካላቸው ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ፣ የታሪፉ ዝቅተኛነት የድርድር አቅሙን እንዳዳከመበት አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት የታሪፍ ለውጥ የማድረግ አቋም እንዳለው፣ ዘ ኢኮኖሚስት ሰሞኑን በአዲስ አበባ ባካሄደው የኢትዮጵያ ጉባዔ ላይ ለታደሙ ኢንቨስትሮች ገልጸዋል፡፡ 

ኢንጂነር አዜብ እንዳብራሩት፣ መንግሥት በአሁኑ ወቅት አንድ ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ዘጠኝ የአሜሪካ ሳንቲም እያወጣ ይገኛል፡፡ በአንፃሩ አንድ ኪሎ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ስድስት የአሜሪካ ሳንቲም እያስከፈለ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የ50 በመቶና ከዚያም በላይ ለውጥ ሊሆን እንደሚችል ይፋ አድርገዋል፡፡

ኢንጂነሯ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ዝቅተኛ ነው ያሉት ታሪፍ በኃይል ማመንጨት ዘርፍ የሚፈለገውን ያህል የውጭ ኢንቨስትመንት እንዳይመጣ በማድረግ ሲጎዳው ቆይቷል፡፡ በመሆኑም የታሪፍ ለውጥ እንደሚደረግ በመገለጹ 14 ያህል የውጭ ኩባንያዎች ኃይል አመንጭተው ለመንግሥት ለማቅረብ ድርድር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ ኩባንያዎች መካከል የአራት ቢሊዮን ዶላር የጂኦተርማል ኃይል ፕሮጀክት ይዞ የመጣው ሬይክቪክ ጂኦተርማል፣ ጄነራል ሞተርስና ብላክ ራይኖ የተሰኙት ይጠቀሳሉ፡፡

ብላክ ስቶን ለተባለው የአሜሪካ ኩባንያ እህት የሆነው ብላክ ራይኖ፣ በአሁኑ ወቅት ከጂቡቲ እስከ አዋሽ 550 ኪሎ ሜትር የሚዘረጋውን የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ይህ ኩባንያ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ስምምነት ከመድረሱም በተጨማሪ፣ በመጪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ወሳኝ ወደሆነው ምዕራፍ እንደሚሸጋገር ኩባንያውን በመወከል የተገኙት ሺሌሽ ሙራሊዳሃ አስታውቀዋል፡፡ እንዲሁም በኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ሥራ ላይ ለመግባት ፍላጎት እንዳለውም ለመንግሥት ማስታወቁን ኢንጂነር አዜብ ጠቁመዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል የታሪፍ ማሻሻያ እንደሚደረግ ይፋ መደረጉ ካስደነገጣቸው መካከል የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ጨርቃ ጨርቅና ጥጥ ኢንዱስትሪዎች ፌደሬሽን የቦርድ አባል አቶ ፋሲል ታደሰ አንዱ ናቸው፡፡ ኢንጂነር አዜብ የጠቀሱት የታሪፍ ጭማሪ ኢንዱስትሪዎችን ሳይሆን ኃይል ወደ ውጭ የሚልኩትን ኩባንያዎች የሚመለከት ነው በማለት ለመከራከር ቢሞክሩም፣ ጭማሪው ሁሉንም እንደሚመለከት ኢንጂነር አዜብ አረጋግጠውላቸዋል፡፡ ‹‹ይኼማ ሙቱ ማለት ነው፤›› ያሉት አቶ ፋሲል፣ የታሪፍ ጭማሪ ከዚህ ቀደም ተነስቶ አምራች ኢንዱስትሪዎችን እንደማይመለከት ከመንግሥት ጋር ስምምነት ተደርጎ እንደነበር በመግለጽ፣ የመረጃ ችግር እንዳይሆን በማለት ሥጋታቸውን ሲገልጹ ቢደመጡም፣ ኢንጂነሯ በድጋሚ አረጋግጠውላቸዋል፡፡ ሆኖም የታሪፉ ጭማሪ ሚዛናዊ እንዲሆን መደረጉን ኢንጂነር አዜብ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

ይሁንና ይጨመራል የተባለው ታሪፍ ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ኢንጂነሯ ባይገልጹም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆን ግን ተናግረዋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት የአፍሪካ ልማት ባንክ በአፍሪካ በከፍተኛ ወጪ ኃይል የማመንጨት አዝማሚያዎችን የሚያስቃኘው ጽሑፍ ላይ እንዳሰፈረው፣ መንግሥታት ኃይል የማመንጨት አቅማቸው ደካማ እንዲሆን ከሚያደርጉ ፈተናዎች መካከል ከፍተኛ ወጪ አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥታት የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትን ለማሟላት በድጎማ ለማቅረብ መገደዳቸውን ባንኩ አስፍሯል፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት በኢነርጂው መስክ ማስተካከል ይገባዋል ከተባሉት ችግሮች መካከል የውጭ ምንዛሪ ለውጥና ሊያስከትል የሚችለውን የኪሳራ ሥጋት እንዴት እንደሚመለከተው ተጠይቋል፡፡ የቢሮክራሲ ጣጣዎች፣ በጂኦተርማል መስክ የፋይናንስና የማበረታቻ ፓኬጆችን ማሻሻል እንዳለበት የሬይክቪክ ጂኦተርማልና የብላክ ራይኖ ኃላፊዎች መንግሥትን አሳስበዋል፡፡