የመምህር ግርማ ቤት በፖሊስ ተበረበረ

Memehir Girma Wendimu

በማታለል ወንጀል ተጠርጥረው ጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት መምህር ግርማ ወንድሙ አያት የሚገኘው መኖርያ ቤታቸው በፖሊስ መበርበሩ ታወቀ፡፡ 

ፖሊስ ቤታቸውን ሲበረብር ያገኘው ነገር ባይገለጽም፣ ለተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ማስረጃ የሚሆነውና ሌሎች ተጨማሪ ነገሮች ፍለጋ ሳይሆን እንዳልቀረ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ 

መምህር ግርማ ከሁለት ወራት በፊት የእስር ትዕዛዝ ተሰጥቶባቸው እንደነበር ተጠቁሞ፣ አንድ ቀን ፖሊስ ጣቢያ አድረው ጥቅምት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡ በወቅቱም ፖሊስ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸው ነበር፡፡ የፖሊስን ጥያቄ በመቃወም የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲፈቱ በጠበቃቸውና በራሳቸው የጠየቁ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ አልተቀበላቸውም፡፡