ሙስና በአዲስ አበባ በኔትወርክ በመያያዙ ከኢሕአዴግ በስተቀር የሚፈታው እንደሌለ ተነገረ

ተመዘገበ የተባለው የባለሥልጣናት ሀብት ይፋ እንዲደረግ ተጠየቀ 

‹‹በየስብሰባው እየተወዳደሱና በጭብጨባ እየተደጋገፉ መለያየት ይቁም›› የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን

ሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር እጦት ከወረዳ እስከ ከተማ አስተዳደሩ ድረስ በኔትወርክ የተያያዙ በመሆናቸው ሊፈታቸውም ሆነ ሊያስቆማቸው የሚችለው ‹‹ድርጅቱ›› ኢሕአዴግ ብቻ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ 

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መስከረም 20 ቀን 2008 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ለግማሽ ቀን አዘጋጅቶት በነበረው የውይይት መድረክ ላይ ከተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት፣ የሁሉም ክፍላተ ከተሞች፣ ወረዳዎች ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተው ነበር፡፡ ተሳታፊዎቹ እንደተናገሩት የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ 

በመጠናቀቅ ላይ ካለው መስከረም ወር አጋማሽ ጀምሮ በሁሉም ክፍላተ ከተሞች ሊባል በሚችል ሁኔታ ከግንባታ፣ ከመሬትና ቤቶች ጋር በተገናኘ ነዋሪዎች እያለቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የመድረኩ ተሳታፊዎች በተለይ በአዲሱ የሥራ ዘመን ከኃላፊነታቸው እንደሚነሱ ያወቁ፣ የጠረጠሩና ሹክሹክታ የሰሙ የክፍላተ ከተሞችና የወረዳዎች ተሿሚዎች ‹‹የሚፈርስ የማይፈርስ፣ መንገድ የሚወጣበት የማይወጣበት፣ ክርክር ያለበት የሌለበት፣ ግንባታ የተፈቀደለት ያልተፈቀደለት…›› በማለት በሥራ ሰዓትና ከሥራ ውጪ የነዋሪዎችን ግድግዳና የውጭ በር ቀለም ሲቀቡ እንደሚውሉ ጠቁመዋል፡፡ ያለምንም ማስጠንቀቂያ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡን ሰላም እየነሳው በመሆኑ፣ የአስተዳደሩና የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ትኩረት ሰጥተው ሊያስቆሟቸው ወይም ዕርምጃ ሊወስዱባቸው እንደሚገባ ተሳታፊዎቹ አሳስበዋል፡፡ 

በመቐለ ከተማ በተደረገው የገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ አሥረኛ ጉባዔ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ጥሩ ሥራ መሠራቱ የተገለጸ ቢሆንም፣ በመልካም አስተዳደር በኩል ግን ከፍተኛ ችግር እንደነበር መታመኑንና ፓርቲው ‹‹ተጠያቂ ነኝ ማለቱን››፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌይማን ለተሳታፊዎች አስታውሰዋል፡፡ በመቀጠልም ይህንን ምቹ ሁኔታ ሕዝቡ መጠቀም ስላለበት ከመንግሥት ጎን በመቆም ብልሹ አሠራርን፣ ሙስናንና ሌሎች ለሕዝቡም ሆነ ለአገር የማይጠቅሙ አሠራሮችንና ድርጊቶችን ማጋለጥ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ 

በየስብሰባው በመወዳደስና በጭብጨባ በመደጋገፍ መንቀሳቀስ መቆም እንዳለበትና ሕዝብ ያስቀመጠው ኃላፊ ለሕዝብ ማገልገል እንዳለበት መንገር ያለበት ኅብረተሰቡ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ በየስብሰባው የጉንጭ ጅምናስቲክ ሠርቶ መለያየትን ቆም አድርጎ ባለሥልጣኑ የሚጓዝበት ተሽከርካሪ፣ የሚኖርበትና የሚከፈለው ደመወዝ ሕዝቡ በሚከፍለው ታክስ መሆኑን በመግለጽ፣ በአግባቡ እንዲያገለግለው መናገር እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ 

የኮሚሽነሩን ማብራሪያ ተከትሎ የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ የመንግሥት ተሿሚዎች የሕዝብ ሀብት በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት እንዳይበዘብዙና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን በማለት የሕዝብ ተሿሚዎች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ማድረጉ ትልቅ ነገር ነበር፡፡ ነገር ግን በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የመንግሥት ተሿሚዎች መመዝገባቸው ከመገለጹ ውጪ ለሕዝቡ ይፋ አልተደረገም፡፡ ተመዝግቦ በድብቅ መያዙ ትርጉም ስለሌለው የትኛው ባለሥልጣን ምን ያህል ሀብት እንዳስመዘገበ ለሕዝብ ይፋ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ለሕዝብ ይፋ መደረጉ ሕዝቡ የሚያውቀውን ያህል ማስመዝገቡንና ያላስመዘገበም ከሆነ ተጨማሪ መረጃ በመስጠት እውነቱ ላይ እንዲደርስ እንደሚረዳ ተሳታፊዎች አውስተዋል፡፡ 

ሀብታቸውን ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ይፋ እንዲደረጉ በተነሳው ጥያቄ ላይ ምላሽ የሰጡት ኮሚሽነር ዓሊ፣ መሥሪያ ቤታቸው ለማንም ክፍት መሆኑንና ማንም መጥቶ የሚፈልገውን ማስረጃ ማግኘት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ መረጃ የሚፈልግ ማንኛውም ዜጋ ደብዳቤ ጽፎ፣ ‹‹የእከሌን ባለሥልጣን ሀብት ማወቅ እፈልጋለሁ?›› ካለ ወዲያውኑ እንደሚገለጽለት ተናግረው፣ በመገናኛ ብዙኃን ግን ‹‹የእከሌ ባለሥልጣን ሀብት ይህንን ያህል ነው፤›› ብሎ ይፋ ማድረግ ከሕግ አንፃርም እንደሚያስኬድና ነውር መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ በዓለም ደረጃም ከሲንጋፖር በስተቀር የሁሉንም ዜጎች ሀብት መዝግቦ ይፋ ያደረገ አገር አለመኖሩን አክለዋል፡፡ በቅርቡ በኮሚሽኑ ድረ ገጽ በኢሜይል መጠየቅና መረጃ ማግኘት እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡ 

የመድረኩ ተሳታፊዎች በርካታ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፣ በተለይ በሙስና ተጠርጥረው ስለሚታሰሩና ስለሚፈረድባቸው ተከሳሾች ተናግረዋል፡፡ አንድ በሙስና የተጠረጠረ ሰው በርካታ ገንዘብ በሙስና ካገኘ በኋላ ዘመዶቹ ዘንድ በታትኖ በማስቀመጥ፣ ሲፈተሽ የሚገኝበት ጥፋት በጣም ትንሽ ስለሚሆን የተወሰነ ዓመት ታስሮ እንደሚፈታ ገልጸዋል፡፡ 

ከእስር እንደተፈታ ለተወሰኑ ወራት ቀድሞ ከሚኖርበት አካባቢ በመልቀቅ ከቆየ በኋላ አስመጪና ላኪ ሆኖ እንደሚታይ የገለጹት ተሳታፊዎቹ፣ ይህንን የሚያዩ ተሿሚዎች የተወሰኑ ዓመታት ታስረው ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው እንደሚተርፉ ራሳቸውን በማሳመን ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ሀብትን እየበዘበዙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህንን ተግባር የሚመለከተው አካል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ዕርምጃ ሊወስድበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ 

ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ ለመፍጠር ትምህርቱ ከአምስት ዓመት ሕፃን እንዲጀምር በኮሚሽኑ የቀረበውን ሐሳብ የውይይቱ ተሳታፊዎች ድጋፍ ሰጥተውታል፡፡ 

በመቐለው ጉባዔ የተደረገው ስምምነት እንዳለ ሳይቀነስ ወደ ታች መውረድ እንዳለበት ያሳሰቡት የውይይቱ ተካፋዮች፣ በተለይ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ዕጦት በሚታይባቸው ግብር አስከፋይና ንግድ ፈቃድ አዳሽ መሥሪያ ቤቶች የማይተገበር መመርያ እያወጡ የንግዱን ኅብረተሰብ ሳይወድ በግድ ወደ ሙስና እንዲገባ የሚያደርጉበት አሠራር ትኩረት እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ዕጦት ቢስተካከል ለውጥ ሊመጣ እንደሚችልም አክለዋል፡፡ 

‹‹ድርጅቱ ይታማል›› ያሉ አንድ አስተያየት ሰጪ፣ ተሿሚው እንክት አድርጎ ከበላ በኋላ እሮሮ ሲበዛበት ከነበረበት ቦታ ወይም ክፍለ ከተማ ተነስቶ ወደ ሌላ ክፍለ ከተማ ወይም ማዘጋጃ ቤት እንደሚሾም ገልጸው፣ ‹‹እርስዎ (አቶ ዓሊን) ለድርጅቱ ቅርብ ስለሆኑ ቢወያዩበትና መፍትሔ እንዲመጣ ቢያደርጉ የተሻለ ነው፤›› ማለታቸው የስብሰባውን ተሳታፊዎች አስፈግጓል፡፡ ከድርጅቱ ውጪ ማንም ሊፈታው እንደማይችልም አክለዋል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችን ችግር የሚፈታ መንግሥት እንዴት የሙስናን ችግር መፍታት እንዳቃተው እንዳልገባቸውም ተናግረዋል፡፡ 

ገዢው ፓርቲ ብቻውን የሚያደርገው ነገር እንደሌለ የገለጹት አቶ ዓሊ፣ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ድርጊቶችን ማስፈጸም እንዳልተቻለ የገለጹት አቶ ዓሊ፣ የማይገባ ድርጊት መፈጸሙ እየታወቀ ዞር ተደርጎ በከፍተኛ ደረጃ የሚሾም ተሿሚ መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡ 

 

በአዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ በተሰናዳው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ የታደሙት የሒልተንና የሸራተን ኃላፊዎች፣ መንግሥት በቅርቡ መተግበር በጀመረው የሆቴሎች ደረጃ አሰጣጥ አለመደሰታቸውን ገለጹ፡፡ 

በሒልተን ዓለም አቀፍ የአውሮፓና የአፍሪካ ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት ፓትሪክ ፊትዝጊቦን ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ስለሚገኘው የሆቴሎች ደረጃ አሰጣጥ ተጠይቀዋል፡፡ ሒልተን አዲስ አበባ የአራት ኮከብ ደረጃ ማግኘቱን ተከትሎ ቅሬታቸውን ካቀረቡ 11 ባለኮከብ ሆቴሎች ውስጥ አንዱ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ምንም እንኳ በደረጃ አሰጣጡ ሒደትና በሒልተን ውጤት ላይ አስተያየት ከመስጠት ቢጠነቀቁም፣ ደረጃ መዳቢዎች ከሚያወጡት የኮከብ ደረጃ ይልቅ የሒልተንን ማምነት የሚገልጸው ደንበኞች ከሒልተን የሚጠብቁት አገልግሎት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የሒልተን ብራንድ ከሚሰጠው የኮከብ ደረጃ ይልቅ በደንበኞቹ ይታወቃል ያሉት ፊትዝጊቦን፣ በተዘዋዋሪ ከመናገር ውጪ በቀጥታ ቅሬታቸውን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ 

በሌላ በኩል ሸራተን አዲስ ሆቴልን የሚያስተዳድረው ስታርውድ  ሆቴሎችና ሪዞርቶች ዓለም አቀፍ ኩባንያ ምክትል ፕሬዚዳንትና የአፍሪካና የህንድ ውቅያኖስ የቀጣናው የኦፕሬሽን ዘርፍ ዳይሬክተር ሐሳን አህዳብም ከሪፖርተር ስለደረጃ አሰጣጡ ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እንደ አህዳብ አባባል በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በተለያዩ አገሮች ያሉ ደረጃ አውጪዎች ሊገነዘቡት የሚገባው የሆቴል ደረጃ አሰጣጥ ‹‹ጊዜው ያለፈበት›› ሥርዓት መሆኑን ነው፡፡ ሆቴሎች ባላቸው የብራንድና የቄንጠኝነት ደረጃ መመደብ አለባቸው የሚሉት አህዳብ፣ ከደረጃ አሰጣጥ ይልቅ በብራንድ ላይ መተኮር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በየጊዜው እየተቀየረ ባለው የሰዎች አኗኗር ሳቢያ የኮከብ ደረጃ ሆቴሎችን ገላጭ ሆኖ እንዳላገኙት በመጥቀስ፣ ሸራተን ባለአምስት ኮከብ ከመባል ይልቅ ‹‹ለግዠሪ ኮሌክሽን›› በሚለው ደረጃው በደንበኞቹ ዘንድ እንደሚታወቅ፣ ይኸው ብራንድም መገለጫው እንደሆነ በመግለጽ የኮከብ ደረጃ አሰጣጥን አጣጥለውታል፡፡ 

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሆቴሎች ደረጃ አሰጣጥን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት ከሆኑት መካከል ከዓለም የቱሪዝም ድርጅት ባለሙያዎች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ባስተዋወቀው የደረጃ አሰጣጥ ሥርዓት መሠረት፣ እስካሁን መግለጫ የተሰጠባቸው 95 ባለኮከብ ሆቴሎች በአዲስ አበባ ተመዝነው ውጤት ቢነገራቸውም እነማን እንደሆኑ ለሕዝብ ይፋ ከማድረግ ግን ሚኒስቴሩ ተቆጥቦ ቆይቷል፡፡ የአዲስ አበባ ሆቴሎች ደረጃ አሰጣጥን ካጠናቀቀ በኋላ ለቀረቡለት ቅሬታዎች ምላሽ በመስጠት የደረጃ አሰጣጡ ያካተታቸው ሆቴሎችና ያገኙትን ደረጃ ይፋ እንደሚያደርግ ቢያስታውቅም እስካሁን ዝምታን መርጧል፡፡ ይሁንና ባለአምስት ኮከብ ደረጃ ያገኙት ሸራተን፣ ኢሊሊ ኢንተርናሽናል እንዲሁም ካፒታል ሆቴልና ስፓ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውጪ የተቀሩት ሆቴሎች ከአራት እስከ አንድ ኮከብ ባለው ደረጃ የተመደቡ ናቸው፡፡ 

ሒልተን ኢንተርናሽናል ሁለተኛውን ሆቴል በሐዋሳ ለማስተዳደር ከሰንሻይ ቢዝነስ ጋር በተዋዋለበት ሳምንት፣ ሸራተንን የሚያስተዳድረው ስታርውድ በበኩሉ በአፍሪካ 20 የሆቴል ፕሮጀክቶች ላይ እየሠራ መሆኑንና ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱን በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ይፋ አድርጓል፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ ምንም ይፋ የሚያደርገው የሆቴል ፕሮጀክት እንደሌለ የስታርውድ የአፍሪካና የህንድ ውቅያኖሶች ቀጣና ልማት ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት ኔል ጆርጅ አስታውቀዋል፡፡ 

አህዳብ በበኩላቸው ሸራተን አዲስን ከጥንስሱ ጀምሮ ሲያተዳድሩ ቆይተው በቅርቡ ያረፉት ዣን ፔዬር ማኒጎፍ በምክትላቸው ተተክተው ሆቴሉን የማስተዳደር ኃላፊነት እንደተረከቡና ሆቴሉ ይሰጣቸው የነበሩ አገልግሎቶችም ሳይስተጓጎሉ መቀጠላቸውን ከሪፖርተር ተጠይቀው አብራርተዋል፡፡ በሟቹ ማኒጎፍ አስተዳደር ጊዜ ከሠራተኞች ጋር የነበረውን ግጭት በሚመለከትም ተጠይቀዋል፡፡ ሟቹ በነበራቸው ሥራን በፍጥነት የመሥራት ፍላጎትና ችኮላ ይከሰቱ ከነበሩ ችግሮች ውጪ የጎላ ችግር እንዳልተፈጠረ ጠቅሰዋል፡፡ በአንፃሩ በተለያዩ ጊዜያት መብታቸውን በመጠየቃቸው ያለምንም ማስጠንቀቂያ ከሥራ ገበታቸው መሰናበታቸውን ሠራተኞች ሲገልጹና አስተዳደሩን ሲከሱ እንደነበር አይዘነጋም፡፡  

 

ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል በማፈራረስና ኦሮሚያ ክልልን የመገንጠል ፖለቲካዊ ዓላማ በመያዝ፣ ዓላማውን ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉ ሦስት ተጠርጣሪዎች ተከሰሱ፡፡

በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ በማሳደር፣ ኅብረተሰቡን በማስፈራራትና የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተቋማትን ለማናጋት፣ ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ብሎ ከሚጠራው ድርጅት ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉት ተከሳሾች ቶሎሳ በየነ፣ ቱሉ ሞኦ አቤቱና መገርሳ መሸሻ የሚባሉ መሆናቸውን የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ያቀረበው ክስ ያብራራል፡፡ 

ተከሳሾቹ በኦነግ አማካይነት ‹‹የኦሮሞን ብሔር ከመንግሥት ጫና ለማላቀቅና ነፃ ለማውጣት መታገል አለብህ፤›› ተብሎ የቀረበላቸውን ጥያቄ በመቀበል አባል መሆናቸውን ክሱ ይጠቁማል፡፡

ተከሳሾቹ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን በነቀምት ከተማ በሚገኙ የተለያዩ የንግድ ቤቶች ከኦነግ አባላት ጋር በመገናኘት፣ ድርጅቱ የሚሰጠውን ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠና ለመውሰድ ወደ ኤርትራ መጓዛቸውንም ክሱ ያክላል፡፡ ኤርትራ አገር ከደረሱ በኋላ ኢን ተብሎ በሚጠራው ማሠልጠኛ ካምፕ፣ ከሌሎቹ የድርጅቱ አባላት ጋር በመሆን ወታደራዊ የአካል ብቃት ሥልጠና መውሰዳቸውም በክሱ ተገልጿል፡፡ የጦር መሣሪያ አገጣጠም፣ ዒላማ ተኩስ፣ ቦምብ አፈታት፣ አገጣጠምና አወራወር ያካተተ ወታደራዊ ሥልጠና ለተከታታይ ሦስት ወራት መውሰዳቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ 

በቁጥጥር ሥር ካልዋሉት ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የኤሌክትሪክና የውኃ መስመሮችን መቁረጥ፣ የመኪና መንገዶችን በድንጋይ መዝጋትና የኦሮሞ ገበሬዎች እህል ወደ ገበያ እንዳያወጡ ለማድረግ ተልዕኮ በመቀበል፣ በተለይ ቶሎሳ በየነ የተባለው ተከሳሽ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ክሱ ያስረዳል፡፡ ተልዕኮ ማስፈጸሚያ ተብሎ 8,000 ብር ተቀብሎ ከኤርትራ በጂቡቲ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር 2007 ዓ.ም. መግባቱንም ጠቁሟል፡፡

ተከሳሾቹ ቁጥሩን በማያሳይ ‹‹UN KNOWN›› በሚል ስልክ በመደዋወል የጦር መሣሪያ ይቀባበሉ እንደነበርና ጥይቶቹን በፍራሽ ጠቅልለው በትራንስፖርት ሲያሳልፉ እንደነበሩ የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ቱሉ ሞኦ አቤቱ የተባለው ተከሳሽ ከኤርትራ ወደ ጂቡቲ ከዚያም በሚሌ አድርጐ ወደ ኮምቦልቻ ከሄደ በኋላ፣ ወደ አዲስ አበባ ከዚያም ወደ ነቀምት በመሄድ አንደኛ ተከሳሽ አባት ቤት ውስጥ ክላሽኒኮቭ ጠመንጃውን ከ60 ጥይቶች ጋር መደበቁን ክሱ ይገልጻል፡፡ ካልተያዙ ግብረ አበሮቹ ጋር ተቀብሎት የነበረው ተልዕኮ፣ ኦሮሚያ ውስጥ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችን ለመግደል እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ 

ተከሳሾቹ በአጠቃላይ የወንጀል ሕግ ቁጥር 32(1ሀን) እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652 አንቀጽ 7(1)ን በመተላለፍ በፈጸሙት በሽብርተኛ ድርጅት ተግባር ውስጥ በመሳተፍ ወንጀል መከሰሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡ ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተሰጥቶ የቀረበባቸውን ክስ ለመስማት ለጥቅምት 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ተረኛ ችሎቱ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

 

በሙስና ወንጀል ለተከሰሱት የልብ ሕክምና ስፔሻሊስት መንግሥት ትብብር እንዲያደርግላቸው ማኅበሩ ጠየቀ

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ በተመሠረተባቸው በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ የተካተቱትን የልብ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ወርዶፋን መንግሥት ትብብር እንዲያደርግላቸው፣ የግል ሆስፒታሎች ማኅበር ጠየቀ፡፡ 

በማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሲሳይ ማሩ ጆፋ ፊርማ በቀጥታ ክስ ለመሠረተው ለፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ተጽፎ በግልባጭ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለፍትሕ ሚኒስቴር፣ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ለዳያስፖራ ዴስክ እንዲደርስ የተደረገው ደብዳቤ ማኅበሩ ለምን የመንግሥት ትብብር እንደተፈለገ ያብራራል፡፡ 

ደብዳቤው እንደሚገልጸው፣ በሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ የሚገኙት ዶ/ር ፍቅሩ፣ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን አዲስ የልብ ሕክምና ማዕከልን የከፈቱ ፈር ቀዳጅ የልብ ሕክምና ባለሙያ ናቸው፡፡ 

በሆስፒታሉ የተዘጉ የልብ የደም ሥሮች ማየት የሚችል ሕክምና፣ የልብ ምታቸው ለቀነሰ ሕሙማን የልብ ምት ማስተካከል፣ ድንገተኛ የልብ መቆም መከላከል ሕክምናና ሌሎችም በርካታ ከልብ ጋር የሚገናኙ ሕክምናዎች እንደሚሰጡ ማኅበሩ፣ በደብዳቤው ጠቁሟል፡፡ 

የነፍስ አድን መሣሪያዎች በሰውነታቸው የተገጠመላቸው ታካሚዎች በየሦስት ወራት እየተከታተሉ በሕይወት የመቆየት ተስፋ እንደነበረባቸው የሚገልጸው ማኅበሩ ዶ/ር ፍቅሩ በመታሰራቸው ይሰጥ የነበረው ሕክምና በመቋረጡ የልብ ታካሚዎቹ ለከፋ ችግር እየተጋለጡ መሆኑን አስረድቷል፡፡ 

ዶ/ር ፍቅሩ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞችን ወደ ስዊድን በመላክ የልብ ሕክምና ስፔሻሊስት እንዲሆኑ ማድረጋቸውን ማኅበሩ በደብዳቤው ጠቁሞ፣ ከስዊድን ከሚመጡ ሐኪሞች ጋር በሚደረግ የሕክምና ሒደት ደግሞ የዕውቀት ሽግግርም ይካሄድ የነበረ ቢሆንም፣ እሳቸው በመታሰራቸው መቋረጡን አስረድቷል፡፡ 

በመሆኑም ዶ/ር ፍቅሩ በመታሰራቸው ምክንያት በእሳቸው ክትትል ይደረግላቸው የነበሩ ሕሙማን ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን፣ በጤና አገልግሎቱም ክፍተት እየተፈጠረ መሆኑን፣ መንግሥት የእሳቸውን አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባትና ኅብረተሰቡ የደረሰበትን የሕክምና ዕጦትና መንገላታት ታሳቢ በማድረግ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግላቸው ጠይቋል፡፡ 

ማኅበሩ ለሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ የጻፈው ጳጉሜን 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ቢሆንም፣ እስከ መስከረም 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ከማናቸውም አካላት ምንም ዓይነት ምላሽ አለማግኘቱ ታውቋል፡፡ 

 

የግንቦት 7 ድርጅትን ተልዕኮ በመቀበል የሽብር ተግባር ለመፈጸም የፌዴራል ፖሊስ አባል በመሆን መረጃ ሲያስተላልፉ ተደርሶባቸዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሁለት ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር ውለው ክስ ተመሠረተባቸው፡፡ 

በፌደራል ፖሊስ ተቋም ውስጥ ተመድበው ሕገ መንግሥቱን ለመጠበቅ የተጣለባቸውን አደራ በመተው፣ የግንቦት 7 ጥምረት ነው የተባለውን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች የሰጣቸውን ተልዕኮ በመቀበል ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉት፣ ኮንስታብል ነገደ ሸዋ ቀናና ረዳት ሳጅን እንዳለ ዘየደ የሚባሉ መሆናቸውን፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት መስከረም 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ያቀረበው ክስ ይገልጻል፡፡

ኮንስታብል ነገደ የተባለው ተጠርጣሪ ኤርትራ ከሚኖርና የግንቦት 7 ድርጅት አባል ጋር በስልክ በመገናኘት፣ ለመንግሥት ጥሩ አመለካከት የሌላቸውን እየመለመለ አድራሻቸውን እንዲሰጠው መስማማታቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ በፌዴራል ፖሊስ ተመሳሳይ የሥራ ድርሻ የነበረው ተከሳሽ ረዳት ሳጅን እንዳለ ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸሙን የሚገልጸው የዓቃቤ ሕግ ክስ፣ ሁለቱም ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በማናቸውም መልኩ መሳተፍ ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡ ክሱን ተቀብሎ ያየው ተረኛ ችሎትም ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ በማዘዝ፣ ክሱን ለመስማት ለጥቅምት 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ሌላው የመከላከያ ሠራዊት አባል መሆኑ የተጠቀሰውና የኦነግ አባል በመሆን አባላትን በመመልመልና መረጃ በማስተላለፍ ተጠርጥሮ ክስ የተመሠረተበት ወታደር አማኑኤል ደስታ ጅማ ይባላል፡፡

ተከሳሹ ኅብረተሰቡን አደጋ ላይ ለመጣል፣ ሕይወት ለማጥፋትና ንብረት ለማውደምና በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር፣ ከመስከረም ወር 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ሻኪሶ አካባቢ ከድርጅቱ አባላት ጋር ይገናኝ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ተከሳሹ የኦነግን ተልዕኮ ለማሳካት በጥር ወር 2007 ዓ.ም. በአገር መከላከያ ሠራዊት በመቀጠርና ለአራት ወራት ሁርሶ ወታደራዊ ሥልጠና በመውሰድ፣ ሠራዊቱን ተቀላቅሎ መመደቡን ክሱ ያብራራል፡፡ 

በሠራዊቱ ውስጥ ከተመደበ በኋላ አባላትን በመመልመልና በማደራጀት በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን፣ ሻኪሶ ወረዳ፣ ሻኪሶ ከተማ ከሚገኘውና የኦነግ አባል ከሆነው ደበበ ሚደቅሳ ከተባለው የድርጅቱ አባል ጋር ግንኙነት ሲያደርግ መቆየቱ በክሱ ተጠቅሷል፡፡ 

የመለመላቸውን ሻምበል ባሻ ስንታየሁና ሃምሳ አለቃ ሸለመ ሞቱማ የተባሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላትንና ሌሎች ወታደሮችን አስከድቶ፣ ወደ ኤርትራ ሄደው ለመቀላቀል በዝግጅት ላይ እያሉ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ክሱ ይገልጻል፡፡ ክሱን ለመስማት ፍርድ ቤቱ ለጥቅምት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡    

 

በተጠረጠሩበት የነፍስ ግድያ መርማሪዎችና ዓቃቤ ሕግ መመሳጠራቸው ተጠቆመ

የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣን አቶ ወንድሙ ቢራቱን በተጠረጠሩበት ከባድ የሙስና ወንጀል በቁጥጥር ሥር አውሎ እየመረመራቸው የሚገኘው የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን፣ ሰሞኑን ባካሄደው

ምርመራ ተጠርጣሪው ከግለሰቦች 10.5 ሚሊዮን ብር ጉቦ የተቀበሉበትን ሰነድ መሰብሰቡን ገለጸ፡፡

መርማሪ ቡድኑ ከግለሰቦች ጉቦ ለመቀበላቸው የምስክሮችን ቃል መውሰዱን አክሏል፡፡ ተጠርጣሪው በሕገወጥ መንገድ ከቀረጥ ነፃ ተሽከርካሪዎችን በሌሎች ግለሰቦች ስም ማስገባታቸውን የጠቆመው መርማሪ ቡድኑ፣ ተሽከርካሪዎቹን ማሳገዱን አስረድቷል፡፡

የኮሚሽኑ መርማሪ በድን ባለፉት ሳምንታት ባካሄደው ምርመራ፣ ተጠርጣሪው በተጠረጠሩበት የነፍስ ግድያ ወንጀል በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖችና በአዲስ አበባ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ አቶ ወንድሙ በነፍስ ግድያ ተጠርጥረው እያለ፣ መርማሪዎችና ዓቃቤ ሕግ ተመሳጥረው ወደ ምስክርነት እንዲዛወሩ ማድረጋቸውንም የሚያስገነዝብ ማስረጃ መሰብሰቡን ገልጿል፡፡

ቀደም ብሎ እንደሚያከናውናቸው ከገለጻቸው የምርመራ ሥራዎች ውስጥ በተጠርጣሪው ላይ በጉምሩክ ተጀምሮ የነበረውንና በመመሳጠር ተቋርጦ የነበረውን ጅምር የምርመራ መዝገብ ከጉምሩክ መቀበሉንም ገልጿል፡፡ ሐሰተኛ ሰነድ እያሳተሙ በተለያዩ ከተሞች ሲፈጽሙ የነበረውን ግብር የመሰብሰብ ድርጊት የሚያስረዱ ምስክሮችን እያፈላለገ እንደሚገኝ መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡

የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ጨምሮ እንደገለጸው፣ ለተጠርጣሪው ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥት ግብርን እንዲሰበስቡ ደረሰኝ አትሞ ከሰጣቸው ግለሰብ የምስክርነት ቃል መቀበል ይቀረዋል፡፡ ሌሎች ለመንግሥት መግባት የነበረባቸውን የተጨማሪ እሴት ታክስና ግብር ለማስቀረት ጉቦ የተቀበሉበትን የባንክ ሰነድ መሰብሰብና ተጨማሪ የሰው ማስረጃ መሰብሰብ ይቀረዋል፡፡ 

ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሰው ማስረጃ ቃል መቀበሉን፣ ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃ መሰብሰብ እንደሚቀረውና ሎሎች ተፈላጊ ተጠርጣሪዎችን አድኖ መያዝ እንዳለበት ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ጉቦ ሲቀበሉና ሲያቀብሉ የነበሩበት የባንክና ሌሎች ሰነዶችን ከመጠቀም በተጨማሪ፣ በሥልጣን ዘመናቸው ሲያጠራቅሙ የነበረውን ተጨማሪ የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ሀብት ማፈላለግ እንደሚቀረው ለፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ ይኼንን ለሚያከናውንበት ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀዱለት ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቃ መርማሪ ቡድኑ ያቀረበውን ተጨማሪ ጊዜ በመቃወም፣ እስካሁን ያደረገው ምርመራ በቂ መሆኑንና ተጨማሪ ምርመራ እንደማያስፈልግ በማስረዳት፣ የደንበኛቸው የዋስትና መብት እንዲጠበቅላቸውና ከእስር እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ግን ቀሪ ምርመራ እንደሚቀረው ማስረዳቱን በማስታወስ ዋስትናውን ተቃውሟል፡፡

ተረኛ ችሎቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ፣ የተጠርጣሪውን ጠበቃ አቤቱታ ውድቅ በማድረግ ለመርማሪ ቡድኑ የሰባት ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዷል፡፡ 

 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5፣ በተለምዶ ውቤ በረሃ በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን (አራዳ ጊዮርጊስ) አዲሱ የባቡር ተርሚናል እስከ አፍንጮ በር የሚገኙ ነጋዴዎች፣ ምትክ

የንግድ ቦታ ሳይሰጣቸው የንግድ ቤቶቻቸውን በግዳጅ ለማፍረስ ወረው እያሸገ መሆኑን ገለጹ፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር እኩል ሊባል የሚችል ዕድሜ ያስቆጠሩ ንግድ ቤቶች በአንድ ሳምንት ማስጠንቀቂያ ማፍረስ ተገቢ አለመሆኑን የሚናገሩት ነጋዴዎቹ፣ አስተዳደሩ የገባላቸውን ቃል በማጠፍ፣ ‹‹ተለዋጭ ቦታ የምሰጣችሁ አሁን ያላችሁበትን የንግድ ቦታ አፅድቼ ስጨርስ ነው›› ማለቱ፣ ከሕግም ሆነ ከመንግሥት ፖሊሲ አንፃር የዜጐችን መብት የማያስከብር በመሆኑ አግባብነት የለውም ብለዋል፡፡ 

የከተማ አስተዳደሩ ነጋዴዎቹን ከዓመት በፊት ሰብስቦ በአክሲዮን እንዲደራጁና እያንዳንዳቸው 25,000 ብር በማዋጣት በባንክ እንዲያስቀምጡ፣ እንዲሁም በየወሩ ከ2000 ብር በላይ ገቢ እንዲያደርጉ ያቀረበውን ሐሳብ መቀበላቸውንና ተግባራዊ ማድረጋቸውን የሚናገሩት ነጋዴዎቹ፣ በንግድ ቦታቸው ላይ ግንባታ ተካሂዶ እያንዳንዳቸው 25 ካሬ ሜትር ቦታ እንደሚሰጣቸው የተነገራቸው ሁሉ ታጥፎ፣ በቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ መወሰኑ እንዳስደነገጣቸው ተናግረዋል፡፡ 

መንግሥት ከወሰነ በኋላ የገባውን ቃል ተላልፎ በአስቸኳይ እንዲለቁ የሚያደርግ ከሆነ፣ ለሌሎች የልማት ተነሺ ነጋዴዎች የተሰጠው ዕድል ለእነሱም መነፈግ ስለሌለበት፣ ተለዋጭ የኮንዶሚኒየም የንግድ ቦታዎች እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ቤተሰቦቻቸውንና ቀደምት ነጋዴዎችን በመተካት ሥራቸውን በንግድ ላይ በማድረግ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት፣ የሚመግቡትና ራሳቸውንም እያኖሩ የሚገኙት በያዙት ንግድ ቤት እየነገዱ በሚያገኙት ገቢ መሆኑን የሚናገሩት ነጋዴዎቹ፣ በሕገወጥ መንገድ በ‹‹አፍራሽ ግብረ ኃይል›› አማካይነት ወደ ጎዳና ተገፍተው ከመጣላቸው በፊት መንግሥት ሊደርስላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ 

ዕድሜ ጠገብ የንግድ ቤቶች ከሆኑት መካከል የታዋቂው ክራር ተጫዋች ከተማ መኰንን ቤት የነበረው አሁን ብሔራዊ ሆቴል በቅጽል ስሟ ‹‹ጭራ ቀረሽ›› በሚል መጠሪያ የምትታወቀው የዘነበች ታደሰ የነበረውና አሁን ግሪን ባርና ሬስቶራንት፣ መዲና በመባል የሚታወቀው አሁን ያሲን ሱፐር ማርኬት፣ ድምፃዊት አበበች ደራራ የነበረችበት አሁን ሰላም ልኳንዳ፣ ዘመናት ያስቆጠረው አባ ገዳ ማተሚያ ቤት፣ አርቲስት አሰለፈች አላምረው ትሠራበት የነበረው ሆቴል፣ ኤፍሬም ግሮሰሪና ሌሎችም ታዋቂ የንግድ ቤቶች የሚፈርሱ መሆናቸውንም ነጋዴዎቹ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ለልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን እነሱም የሚደግፉት ተግባር እንደሆነ የገለጹት ነጋዴዎቹ፣ ከሁሉም በፊት የዜጐች መብትና ክብር መቅደም ስላለበት፣ እንዲሁም መንግሥት ዜጐቹን የመንከባከብና እንደየሥራ ዘርፋቸው ማሰማራት የሚጠበቅበት በመሆኑ ምትክ ቦታ ሰጥቶ እንዲታደጋቸው ጠይቀዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ የቀድሞ ቀበሌ 03/09 (ወረዳ 5) አስተዳደር፣ በደል ሊፈጽምባቸው መሆኑን እየገለጹ ስለሚገኙት የውቤ በረሃ ነጋዴዎች ጉዳይ ለማነጋገር ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

በተመሳሳይ ከአራዳ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደርና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤቶችም በተመሳሳይ ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡   

 

የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት አብዛኛዎቹን የክፍላተ ከተሞችና የወረዳ አመራሮች በማንሳት፣ በአዳዲስ አመራሮች እየተካ መሆኑ ታወቀ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት

ወረዳዎችና ክፍላተ ከተሞች መመራት ያለባቸው ዲፕሎማና ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃ ባላቸው መሆን አለበት የሚል አዲስ አቋም መያዙ፣ ለሹም ሽሩ ምክንያት መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረት በአሥሩም ክፍላተ ከተሞችና በሥራቸው በሚገኙ 116 ወረዳዎች የሚገኙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አመራሮች ተነስተዋል፡፡ በተጨማሪም ሹም ሽሩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰፈነውን የመልካም አስተዳደርና የሙሰኝነት ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ከያዘው ዕቅድ ጋር የሚያያዝ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍ በቅድሚያ ይህ ችግር ያለባቸው አመራሮች ተገምግመው እንዲነሱ መደረጉም ተገልጿል፡፡ ለማሳያ ያህል በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ 12 ወረዳዎች ከዲፕሎማ በታች ያላቸው አመራሮች 70 የሚጠጉ ሲሆን፣ እነዚህ ሁሉ እንደተነሱ ተገልጿል፡፡ በሙስናና በተለያዩ ግድፈቶች ደግሞ 30 አመራሮች እንዲነሱ መደረጉም ተመልክቷል፡፡ 

በሌሎች ክፍላተ ከተሞችና በሥራቸው በሚገኙ ቀበሌዎችም በተመሳሳይ ከ100 ያላነሱ አመራሮች በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች መነሳታቸው ተገልጿል፡፡ ይሁንና ከዲፕሎማ በታች የትምህርት ደረጃ ኖሯቸው አመራር ሲሰጡ የቆዩ አባላት ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት እነዚህ አመራሮች ትምህርት ለመማር ጥያቄ  በሚያቀርቡበት ወቅት መንግሥት ቅድሚያ ሥራችሁን ሥሩ የሚል ምላሽ የሰጣቸው በመሆኑ ትምህርት መማር እንዳልቻሉ አስታውሰው፣ ውሳኔው ፍትሐዊ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡ 

በአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ይህንን አለመግባባት ለማስቀረት የውይይት መድረኮች ፈጥሮ እንደነበርም ታውቋል፡፡ በዚህም ያላቸው የትምህርት ደረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ የተነሱ አመራሮች የሦስት ወራት ደመወዝ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ሥራዎችን እንዲሠሩ ወይም ዕድሜያቸው ለጡረታ የደረሰው ደግሞ በጡረታ እንዲገለሉ ሐሳብ ቀርቦ፣ ከሞላ ጎደል መግባባት ላይ መደረሱ ተመልክቷል፡፡

ዋነኛው የአዲስ አበባ ከተማ ችግር የመልካም አስተዳደር እጦትና ኪራይ ሰብሳቢነት [ሙስና] እንደሆነ ነዋሪዎች ባገኙት አጋጣሚ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ይህ ችግር የ2007 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም በሚገመገምበት ወቅት በሰፊው ተነስቷል፡፡ በተለይ በመሬት፣ በንግድና በአገልግሎት መስጫ ዘርፎች ላይ ኅብረተሰቡ ከፍተኛ እሮሮ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

በእነዚህ ዘርፎች ለተገልጋዮች ተገቢውን አገልግሎት አለመስጠት፣ ተገልጋዮችን ለማስተናገድ ዝግጁ አለመሆን፣ ለሚቀርቡ ቅሬታዎች አፋጣኝ ውሳኔ አለመስጠት፣ ‹‹ጉዳዩ አልታየም›› በማለት ተገልጋዮችን ማጉላላትና ጉቦ መጠየቅ ከሚቀርቡት ቅሬታዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በንግድ በኩል የንግድ ፈቃድ ዕድሳት፣ የንግድ ስያሜ አሰጣጥ፣ የንግድ አድራሻ ማረጋገጫ አሰጣጥ፣ ሕገወጥ ንግድ በሰፊው የሚታዩ ችግሮች ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ በአጠቃላይ የንግድ ሥርዓቱ የተተረማመሰ እንደሆነ ቅሬታ ይቀርባል፡፡

በእነዚህ ሁሉ ችግሮች ሙስና ዋነኛ መገለጫ መሆኑ ከኅብረተሰቡ በሰፊው የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን የኅብረተሰብ ሮሮ በመቀበል፣ የራሱን ግምገማ አካሂዶ ችግሩ እንዳለ አምኗል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ከሕዝብ ጋር ተወያይቶ ወደ ተግባር እንደሚገባ ገልጾ ነበር፡፡ 

ይህንን ችግር ለመፍታት በተካሄዱ ተከታታይ ግምገማዎች ግድፈት እንዳለባቸው የተለዩ አመራሮችን ከክፍላተ ከተሞችም ሆነ ከወረዳዎች ማንሳት ዋነኛ ዕርምጃ ሆኗል፡፡

በዚህ መሠረት ቢያንስ ችግሩ ጎልቶ በሚታይባቸው ክፍላተ ከተሞች ከ30 በላይ አመራሮች፣ በወረዳ ደረጃም በተመሳሳይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አመራሮች እንደተነሱ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ 

ይሁንና በአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ባለቤትነት የሚካሄደው ይህ ሹም ሽር ባለፈው ሳምንት መገባደዱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተወልደ ገብረ ፃድቃን ሥራው እየተካሄደ መሆኑን ለሪፖርተር አረጋግጠው፣ ሥራው ባለመጠናቀቁ መረጃ ለመስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ 

ከዚህ በመቀጠል የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት በማዕከል ደረጃ የሚገኙ ቢሮዎችንና ኤጀንሲዎችን የሚመሩ አመራሮች ላይ ሹም ሽሩን እንደሚቀጥልም ተገልጿል፡፡ ሹም ሽሩ በርካታ አመራሮችን ከካቢኔ የሚያስወጣና በምትካቸው አዳዲስ የካቢኔ አባላትን እንደሚሾም ምንጮች ተናግረዋል፡፡

የካቢኔ አባላቱ ሹም ሽር በቅርቡ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ቀርቦ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

 

የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የአገር መከላከያ ሚኒስቴርን ጨምሮ በ23 መንግሥታዊ ተቋማት ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑንና በተወሰኑት ላይ ደግሞ ማስረጃ በማጠናቀር ክስ መመሥረቱን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ የተጠናቀቀውን በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጠው እስከ ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ያለውን ሒደት ብቻ በሚያሳየው መግለጫ፣ በመከላከያ ሚኒስቴር በተፈጸሙ ሁለት የሙስና ወንጀሎች ጥቆማ የደረሰው መሆኑን ገልጿል፡፡ ከእነዚህም አንዱ በመከላከያ ሚኒስቴር ሕግን ባልተከተለ መንገድ ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ለግዥ ውሏል የሚል ነው፡፡ ኮሚሽኑ ለጋዜጠኞች ባሰራጨው ሪፖርት በዚህ ጉዳይ ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡ 

ሌላኛው በመከላከያ ተፈጸመ ተብሎ የተጠረጠረው ጉዳይ በመከላከያ ሚኒስቴር 171 ሬጅመንት፣ ዘጠኝ መኮንኖች ከመከላከያ ፋውንዴሽን በዝቀተኛ ዋጋ ለክፍለ ጦሩ አባላትና ለቤተሰቦቻቸው ፍጆታ የሚውል ስኳር ከነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር ከ2.2 ሚሊዮን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ተብለው መጠርጠራቸው ነው፡፡ ኮሚሽኑ በተጠርጣሪ መኰንኖች ላይ ክስ መመሥረቱ ተጠቁሟል፡፡ 

ኮሚሽኑ ምርመራና ክስ ካቀረበባቸው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች መካከል የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ፣ የአዲስ አበባ ቤቶች ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና ጂንአድ ይገኙበታል፡፡

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የሳሪስ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ የነበሩ ግለሰብ፣ ከቀረጥ ነፃ ተሽከርካሪ ለማስገባት የመድን ሽፋን ዋስትና ማስያዣ ያስያዘ ግለሰብ እንዳለው በማስመሰል ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በመስጠቱ፣ እንዲሁም ሚድሮክ ጐልድ ያለመያዣ (ኮላተራል) 600,000 ብር ቦንድ ዋስትና በመስጠቱ ተጠርጣሪው ግለሰብ ክስ እንደተመሠረተበት ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች የሆኑ ተጠርጣሪዎች የባንክ ገንዘብ ማስተላለፊያ የሚስጥር ቁልፍ በመጠቀም፣ ለግለሰቦች ሰባት ሚሊዮን ብር እንዲተላለፍላቸው በማድረግ ተጠርጥረው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑንም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጁባ ቅርንጫፍ ሠራተኞችና ኃላፊዎች 20 ሚሊዮን ብር አጭበርብረዋል ተብለው ተጠርጥረው ክስ እንደተመሠረተባቸው ተገልጿል፡፡

የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ በቅሎ ቤት ቅርንጫፍ ሠራተኞች በሐሰተኛ አካውንት ጣሊያን ኤምባሲ በሚል፣ 2.2 ሚሊዮን ብር እንዳለው አድርገው ሰነድ ካዘጋጁ በኋላ 700,000 ብር ወደ ሌላ ባንክ በማስተላለፍ ወንጀል ተጠርጥረው ምርምራ እየተካሄደባቸው ነው፡፡

በአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት (ፕሮጀክት 15) ያላግባብ የጠጠር ግዥ በመፈጸም ሁለት ሚሊዮን ብር መጠን ያለው የሕዝብና የመንግሥት ንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል በተባሉ ለጊዜው ቁጥራቸው ባልታወቁ ሠራተኞች ላይ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ቤቶች ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ከ1997 ዓ.ም. እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ የሳኒተሪ ዕቃዎች ግዥ በሕገወጥ መንገድ ግዥ እንዲፈጸም በማድረግ በ81 ሚሊዮን ብር ተጠርጥረው ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ 

ከእነዚህ ጉዳዮች በተጨማሪ ሁለት አስመጪ ነጋዴዎች ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር በመመሳጠር 301.9 ሚሊዮን ብር በመመዝበር ተጠርጥረው ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በእነ አቶ መላኩ ፈንታ መዝገብ ክስ ከተመሠረተባቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣናት አንዳንድ የባለሥልጣኑ ሠራተኞችና ከፍተኛ ነጋዴዎች ላይ ተጀምሮ ከነበረው ምርመራ ጋር በተያያዘ፣ የአገር ውስጥ ግብርና የጉምሩክ ቀረጥ ባለመክፈል በተጠረጠሩ አምስት የግል ኩባንያዎች ላይ የኢንስፔክሽን ኦዲት በማስደረግ በተገኘው ማጣራት፣ 361.6 ሚሊዮን ብር ታክስ አለመከፈሉን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ገልጾ፣ ቀጣይ ምርመራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ከእነዚህ ውጪ ደግሞ የጅምላ ንግድ አቅራቢ ድርጅት (ጅንአድ) የሻሸመኔ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ፣ ከገቢያቸው በላይ ሀብት ይዘው መገኘታቸው ነው፡፡ ኃላፊው በሁለት ሆቴሎች፣ በመኖሪያ ቤቶችና በተሽከርካሪዎች ተጠርጥረው ጉዳያቸው በምርምራ ላይ እንደሚገኝ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡ 

 

በተለምዶ አያት አደባባይ እየተባለ በሚጠራው አያት ቁጥር ሁለት ኮንዶሚኒየም አካባቢ፣ ባልተከደነ ቱቦ ምክንያት የአራት ዓመት ሕፃን ሕይወት መስከረም 5 ቀን 2008 ዓ.ም. አለፈ፡፡

በአካባቢው በሚገኙት ኮንዶሚኒየም ቤቶች ውስጥ በአብዛኛው የሚኖሩት በመልሶ ማልማት ከአራት ኪሎና ከተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ ነዋሪዎች ሲሆኑ፣ አደጋው የደረሰው ከእነዚህ መካከል አንዱ በሆኑት አቶ እንግዱ ዘለቀ ሕፃን ልጅ ላይ ነው፡፡

የሕፃኑ ሕይወት የተቀጠፈውም የቤቶቹ ግንባታ ባለመጠናቀቁና የተከፈቱ ቱቦዎች በመኖራቸው እንደሆነ ቤተሰቦቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል…

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መጋቢት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ዕጣ ያወጣባቸው 35 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ካርታ ተሠርቶ ባለመጠናቀቁ፣ ቤቶቹ ለደረሳቸው ዕድለኞች ማስረከብ አለመቻሉ ተጠቆመ፡፡ 

አስተዳደሩ በአራት ኪሎ፣ የካ አባዶ፣ ገላን፣ ቱሉ ዲምቱና በተለያዩ ቦታዎች 41 ሺሕ ቤቶችን አዘጋጅቶ ስድስት ሺሕ ያህሉን ለልማት ተነሺዎች፣ 35,000 የሚሆኑትን ደግሞ ለነባር ተመዝጋቢ ዕድለኞች በዕጣ እንዲደርስ ካደረገ በኋላ፣ እስከ ሰኔ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ከአስተዳደሩ ጋር ውል እንዲፈጽሙ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ 

ውሉን ከአስተዳደሩ የተለያዩ ወረዳ ጽሕፈት ቤቶች በመቅረብ (በየክፍላተ ከተሞቹ) ተዋውለው ከጨረሱ በኋላ 20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ሲፈጽሙ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጠርቶ የብድር ውል እንደሚፈራረሙ ገልጾላቸው እንደነበር፣ በዕጣ ዕድሉ የደረሳቸው ግለሰቦች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ 

የቤቶቹ ዕጣ ከወጣ ስድስት ወራት እንደሞላውና 20 በመቶውን ከከፈሉ አራት ወራት እንደሞላቸው የሚናገሩት አቶ በዛብህ ንጉሡ የተባሉ ዕድለኛ፣ ባንኩ በሁለት ወራት ውስጥ እንደሚጠራቸው የነገራቸው ጊዜ ከማለፉም በተጨማሪ፣ 11ኛው ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ሊወጣ መሆኑን በመገናኛ ብዙኃን ሲሰሙ ሥጋት እንደገባቸው ገልጸዋል፡፡ ዕጣው እንደወጣላቸው ከታወቀ ጊዜ ጀምሮ አከራዮቻቸው ‹‹ነገ ጥሎት ለሚሄደው›› በማለት የኪራይ ዋጋ በእጥፍ እንደጨመሩባቸው የሚናገሩት አቶ በዛብህ፣ ባንክ በሁለት ወራት ውስጥ ውል ፈጽሞ ቤቱን እንደሚረከቡ ተስፋ በማድረጋቸው የተጨመረባቸውን የቤት ኪራይ በወቅቱ ችላ ቢሉም፣ አሁን ግን ባንኩ ዝም በማለቱ ግራ እንደገባቸው ተናግረዋል፡፡ 

ለእሳቸውና ለሌሎች ዕድለኞች የደረሰው መኖሪያ ቤት ሳይተላለፍ ስለሌላ ዕጣ ሲወራ ሲሰሙ ግራ በመጋባታቸው ወደ ባንክ ሄደው ሊጠይቁ ቢሞክሩም በቂ ምላሽ እንዳላገኙ የሚናገሩት አቶ በዛብህ፣ አስተዳደሩ ወይም ሌላ የሚመለከተው አካል ችግሩ ምን እንደሆነ እንዲያስረዷቸው ጠይቀዋል፡፡ 

እንደ አቶ በዛብህ ሁሉ አብዛኛዎቹ የዕድሉ ተጋሪዎች ከባንክ ጋር ውል አለመፈጸሙና ቤቱን አለመረከባቸው ግራ እንዳጋባቸው እየገለጹ መሆኑን የ65 ዓመት ዕድሜ እንዳላቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ቀለሟ ተገኝም አስረድተዋል፡፡ ችግር ካለም የሚመለከተው አካል ግልጽ እንዲያደርግላቸው እሳቸውም እንደ አቶ በዛብህ ጠይቀዋል፡፡ 

በአሥረኛው ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ የደረሳቸው ዕድለኞች በየክፍለ ከተማው ከሚገኙ ከቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች ጋር የመጀመርያውን የቤት ባለቤትነት ውል ከፈጸሙ በኋላ፣ 20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ለባንክ ከፍለዋል፡፡ 

የቤቱን ካርታ በመያዝ የብድር ውል ከዕድለኞቹ ጋር መፈጸም ያለበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ለምን ውሉን እንዳልፈጸመ ከሪፖርተር ለቀረበለት ጥያቄ የባንኩ የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ሲመልሱ፣ ‹‹ችግሩ የባንኩ አይደለም፡፡ ባንኩ ካርታ ተሠርቶ ከተሰጠው ትክክለኛነቱን በማረጋገጥ ውል ይፈጽማል፡፡ ነገር ግን በየሳይቱ ተሠርቶ የቀረበለት ካርታ በጣም ትንሽ ነው፡፡ በመሆኑም ካርታው ተሠርቶ ካልተሰጠው ውል መፈጸም አይችልም፤›› ብለዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግሥቱ በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ካርታ የሚያዘጋጀው የመሬት አስተዳደር ነው፡፡ ‹‹እስካሁን ሰባት ሺሕ ካርታዎችን አዘጋጅቷል፡፡ በእርግጥ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተጠቀሱት ክፍተቶች አሉ፡፡ ክፍተቶቹን ለመሙላት በጋራ እየሠራን ነው፡፡ የመሬት አስተዳደር፣ የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲና ሌሎችም ያሉበት ኮሚቴ ተዋቅሮ በመረባረብ እየተሠራ ነው፤›› ሲሉ አቶ መስፍን አስረድተዋል፡፡ 

ካርታው ሲሠራ ጥንቃቄ የሚፈልግ መሆኑንና አብዛኛው የዕድሉ ባለቤት የሚያቀርበው ሰነድ ደግሞ ከጋብቻ መኖርና መፍረስ፣ ከስም ስህተትና ከመሳሰሉት ጋር የተገናኘ በመሆኑ፣ እሱን ማስተካከሉ ጊዜ የሚወስድ መሆኑንም አቶ መስፍን አክለዋል፡፡ ባንክ አንድ ፊደል ቢጎድል ስለማይረከብ ሥራው ልዩ ጥንቃቄ የሚፈልግ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ካርታውን በዋናነት የሚሠራው መሬት አስተዳደር መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ወደ ሥልጠና መግባታቸውም ጫና መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡ 

ሌላው እያንዳንዱ ቤት የማን እንደሆነ የሚያረጋግጠው የዲዛይንና የቴክኒክ ሥራ በተለይ በየካ አባዶ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በገላንና ገነት መናፈሻ ሳይቶች ላይ ችግር በመፈጠሩ፣ እንደገና እየተከለሰ እንደነበር አክለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን የአውቶካድ ኤክስፐርቶች በየሳይቱ በቋሚነት ተመድበው እየሠሩ በመሆናቸው ችግሩ እየተቀረፈ እንደሆነ አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡ 

ሁሉም ባለድርሻ ተረባርቦ በመሥራት እስከ መስከረም 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ሁሉም ካርታ ተጠናቆ ለባንክ መሰጠት እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ በመሆኑ፣ ሥራው እንደሚጠናቀቅና ለዕድለኞቹ ቁልፍ ማስረከብ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡ አዲስ ይወጣል ስለሚባለው 11ኛ ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጉዳይ የተጠየቁት አቶ መስፍን፣ ጎን ለጎን ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመው የወጡ ዕጣዎች ለዕድለኞች ሳይተላለፉ ሌላ ዕጣ እንደማይወጣ፣ ቀጣዩ ዕጣ መቼና በየትኛው ወር እንደሚወጣ አሁን መናገር እንደማይቻል አስታውቀዋል፡፡

 

በመሀል አዲስ አበባ ለዘመናት ታጥረው በተቀመጡና ግንባታ ባልተካሄደባቸው ቦታዎች ላይ ጠበቅ ያለ ዕርምጃ እንደሚወስድ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሀል አዲስ አበባን በድጋሚ መገንባት ያስፈልጋል በማለት ነዋሪዎችን ማስነሳቱ ይታወሳል፡፡ አስተዳደሩ በርካታ ኪስ ቦታዎችን ለባለሀብቶች ቢሰጥም፣ ባለሀብቶቹ ግንባታ ከማካሄድ ይልቅ አጥረው የያዟቸው ቦታዎች በርካታ ናቸው፡፡ 

እነዚህ ሕግን ያልተከተሉ አሠራሮች በነዋሪዎች ላይ ቅሬታ እያሳደሩ መሆኑ በተገኙ መድረኮች እየተገለጸ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የ2007 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ካካሄደ በኋላ፣ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አሠራሩን ማጥበቅ እንደሚያስፈልገውና የወጡ ሕጐችን በብቃት ማስፈጸም እንደሚገባ መግባባት ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኃየሎም ጣውዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለመልሶ ማልማት ፕሮጀክቶች ተይዘው ወደ ግንባታ ያልተገባባቸው ቦታዎች ያለባቸውን ችግር በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት በዓመቱ ወደ ሥራ ለመግባት ታቅዷል፡፡ በዚህ መስክ ያለውን ችግር አቶ ኃየሎም ሲያስረዱ፣ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ አስፈላጊውን ሥራ ቀደም ብሎ ማጠናቀቅ ቢችልም ለተወሰኑ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት የማቅረብ ችግር አጋጥሟል፡፡ ‹‹ከዚህ በተጨማሪም ሙሉ በሙሉ ቦታው እስኪፀዳም ግንባታ በመጀመር በኩል መጓተት አለ፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ከመሠረተ ልማት ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት ይኖርብናል፡፡ መንግሥታዊ ተቋማትም በተሰጣቸው ቦታ ላይ ተነሺዎችን በማይጐዳ ሁኔታ ግንባታ እንዲካሄዱ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡ 

በርካታ አልሚዎች የወሰዷቸውን ቦታዎች አጥረው ማስቀመጣቸውን በተመለከተም፣ ‹‹በዚህ በኩል ያሉ ችግሮችን በመለየት ውል እንዳይራዘም በማድረግ መሬቱን ወደ መሬት ባንክ የማስገባት ሥራ ይሠራል፤›› በማለት አቶ ኃየሎም ተናግረዋል፡፡ መሥሪያ ቤታቸው ከወትሮው በተለየ ዘንድሮ ጠንካራ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ አስገንዝበዋል፡፡ 

በመልሶ ማልማት ሥራ ከተያዙት አንዱ የሸራተን አዲስ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ይገኝበታል፡፡ ለዚህ ቦታ በ2002 ዓ.ም. ነዋሪውን የማንሳት ሥራ ቢጠናቀቅም በዚህ ቦታ ላይ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ጋራዥ ባለመነሳቱ ብቻ ወደ ግንባታ ሳይገባ ቆይቷል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ተለዋጭ ቦታ የተሰጠው የራሱን ግንባታ ሳያካሂድ ከዚህ ቦታ ላይ የመነሳት ፍላጐት አላሳየም ተብሏል፡፡ ነገር ግን የአካባቢው ነዋሪዎች ቦታውን ከለቀቁ ከአምስት ዓመት በላይ ተቆጥሯል፡፡  

ከዚህ በተጨማሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስፋፊያ፣ አሮጌው ቄራ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት ማስፋፊያ፣ ተክለ ሃይማኖት መልሶ ማልማት፣ ሸበሌ ሆቴል ጀርባ መልሶ ማልማት ቦታዎች ይገኛሉ፡፡

እነዚህና ሌሎች በሒደት ላይ ካሉ የመልሶ ማልማት ቦታዎች ላይ ነዋሪዎች እንዲነሱ ቢደረግም፣ የተወሰኑ መኖሪያ ቤቶችንና መንግሥታዊ ተቋማትን ማንሳት ባለመቻሉ ቦታዎቹ ታጥረው ለዓመታት እንዲቀመጡ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህም የነዋሪዎችን ኑሮ አስቸጋሪ ከማድረጉም በላይ በተነሱበት ምክንያት ላይም ጥያቄ እያነሱ እንደሚገኝ እየተገለጸ ነው፡፡ አቶ ኃየሎም እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ከመሠረተ ልማት ድርጅቶች ከኤሌክትሪክ፣ ከውኃ፣ ከቤቶች ልማት ጋር በተጠናከረ ሁኔታ በጋራ በመሥራት መሬቱን ነፃ በማድረግ ወደ ልማት ለማስገባት እየተሠራ ነው፡፡

‹‹አስቸጋሪ ሁኔታ እንኳ ቢፈጠር ግንባታውን ከሥር ከሥር ለማካሄድ ዕቅድ ተይዟል፤›› በማለት አቶ ኃየሎም የዘንድሮን ዕቅድ አስረድተዋል፡፡

ከንቲባ ድሪባ ኩማ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ፣ 360 ሔክታር መሬት በመልሶ ማልማት ፕሮግራም ለማልማት ታቅዷል፡፡ ይህ ልማት የሚካሄደው እንደ አዲስ ሲሆን፣ ለቦታው ለቤቶች ልማት፣ ለቢዝነስና ለባለ ኮከብ ሆቴል የሚውል ነው፡፡  በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ90 ባለሀብቶች የተሰጠ መሬት ግንባታ ያልተካሄደበት በመሆኑ መናጠቁን ገልጸዋል፡፡

ከንቲባው እንዳሉት፣ በተካሄደው ግምገማ በአዲስ አበባ ከተማ መሬት ወስደው ግንባታ ያላካሄዱ አልሚዎች ከፍተኛ አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ አልሚዎች ለምን ግንባታ እንዳላካሄዱ በሚመረመርበት ወቅት የከተማው አስተዳደር ችግር አንዱ ምክንያት ሆኖ ተገኝቷል፡፡ 

በዚህ ምክንያት አስተዳደሩ ያለበትን ችግር በመቅረፍ በዚህ ዓመት ወደ ግንባታ እንዲገባ ግፊት እንደሚደረግ፣ አልሚዎቹ ወደ ግንባታ የማይገቡ ከሆነ ግን ዕርምጃ ይወስዳል በማለት ከንቲባው አስረድተዋል፡፡ 

 

የግብፅ ፖፕ ቴዎድሮስ ዳግማዊ ለመስቀል በዓል አዲስ አበባ ይገባሉ

የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፖፕና ፓትርያርክ ቴዎድሮስ ዳግማዊ በመስቀል በዓል አከባበር ላይ ለመታደምና የአራት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ፣ መስከረም 15 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡

የኮፕቲክ ፓትርያርክ ቴዎድሮስ አራት ቀናት በሚወስደው ቆይታቸው መስከረም 16 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚከበረውን የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ከመታደማቸው በተጨማሪ፣ ወደ አክሱምና ላሊበላ አቅንተው ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ሥፍራዎችን እንደሚጎበኙም ታውቋል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪም በሚኖራቸው ቆይታ በአዲስ አበባ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትን፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ከታዋቂ ግለሰቦች ጋር እንደሚነጋገሩ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመና ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩ፣ እስካሁን ግን የተረጋገጠ ነገር አለመኖሩን አክለው አብራርተዋል፡፡  

ፓትሪያርኩ የአዲስ አበባ ጉዟቸውን አስመልክቶ ከሳምንት በፊት ከግብፅ የውኃ ሀብት ሚኒስትር ሆሳም አል ሞጋሃዚ ጋር መነጋገራቸው የተዘገበ ሲሆን፣ በውይይታቸውም ወቅት ግብፅ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን ጥያቄዎች አንስተው ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና ከአቡነ ማትያስ ጋር ውይይት እንዲያደርጉ ሚኒስትሩ መጠየቃቸውና የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ተዘግቧል፡፡ 

ፖፕ ቴዎድሮስ በበኩላቸው ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ሁለቱ ቤተ ክርስቲያናት ባላቸው ታሪካዊ ግንኙነት የተነሳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዚህ ረገድ እየተባበሯቸው እንደሆነና አስተዋጽአቸውም ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል በማለት ስታር አፍሪካ የተሰኘ ድረ ገጽ ላይ የወጣ ዘገባ ያትታል፡፡

የኢትዮጵያ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ባለፈው ጥር ወር ግብፅን ለስድስት ቀናት በይፋ በጎበኙበትና በካይሮ ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት ከፕሬዚዳንት አልሲሲ ጋር በተወያዩበት ወቅት፣ ፕሬዚዳንቱ የዓባይ ወንዝ ለኢትዮጵያውያን የልማት ምንጭ ቢሆንም ለግብፅ ግን ልማት ብቻ ሳይሆን የደም ሥር መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል፡፡ 

አቡነ ማትያስም በበኩላቸው በጠንካራ ትስስር ላይ የተመሠረተው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት፣ ከዓባይ የሚመነጭ ውኃ የማያቋርጥ የጋራ ሀብት በመሆኑ በፍትሐዊነትና በእኩልነት ተጠቃሚ የሚኮንበት ይሆናል ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡ 

ፖፕ ቴዎድሮስ ዳግማዊ እ.ኤ.አ. በ1952 ማንሱራ በተሰኘ የግብፅ ከተማ የተወለዱ ሲሆን፣ በ1975 ከኤሌክሳንዳርያ ዩኒቨርሲቲ በፋርማሲ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ ለጥቂት ዓመታት በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኝ መድኃኒት ፋብሪካን ከአስተዳደሩ በኋላ፣ ቅዱስ ፒስሆግ የተባለ ገዳም በመግባት የሥነ መለኮት ትምህርት በማጥናት እ.ኤ.አ. በ1989 ተመርቀዋል፡፡ 

የአቡነ ሺኖዳ ሕልፈተ ሕይወትን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት 118ኛው የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በመሆን ከሦስት ዓመት ወዲህ በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡   

 

 

ድርጅቱ ችግሩን ቀርፌያለሁ ይላል

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የክፍያ ሥርዓት ችግር እንደገጠመው ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅት በበኩሉ ችግር ተፈጥሮ እንደነበር አምኖ በአሁኑ ወቅት መቀረፉን ገልጿል፡፡ 

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅቱ ማዕከላዊ የክፍያ ሥርዓት (ቢሊንግ ሲስተም) ከሁለት ወራት በፊት በገጠመው ችግር ሳቢያ፣ የደንበኞችን ወርኃዊ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ ለሁሉ ለተባለው የተቀናጀ የአገልግሎት መክፈያ ማዕከል መላክ እንዳልተቻለ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ 

ደንበኞች ወደ ክፍያ ለሁሉ በሚሄዱበት ጊዜም ትክክለኛ መረጃ እንደማይነገራቸውና በሌላ ጊዜ እንዲመጡ ብቻ እንደሚገልጹላቸው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ 

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የክፍያ ለሁሉ የሥራ ኃላፊዎች የተፈጠረው ችግር እነሱን እንደማይመለከት ይገልጻሉ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሚሰጠን የደንበኞች ወርኃዊ ፍጆታ መረጃ መሠረት ደንበኞችን ማስከፈል ነው ሥራችን፡፡ መረጃ ካልደረሰን ማስከፈል አንችልም፤›› ብለዋል፡፡ 

በመሆኑም ጉዳዩ የበለጠ የሚመለከተው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዚሁ መሠረት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅት የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገብረ እግዚአብሔር ታፈረ ተጠይቀው ችግሩ ተፈጥሮ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ 

የማዕከላዊ የክፍያ ሥርዓት ሰርቨር የመረጃ ካርድ በመቃጠሉ ምክንያት ችግሩ እንደተፈጠረ የተናገሩት የውጭ ግንኙነት ኃላፊው፣ ካርዱ በአገር ውስጥ ስለማይገኝና ከውጭ ተገዝቶ እስኪገባ ድረስ የሐምሌ ወር የኤሌክትሪክ ፍጆታን ደንበኞች ማለትም ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚዎች ከሆኑ ድርጅቶች በስተቀር መክፈል አለመቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ግን ችግሩ የተቀረፈ በመሆኑ የሐምሌ ወር የክፍያ ቢል መውጣቱንና ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ ደንበኞች የነሐሴ ወር ፍጆታቸውን መክፈል እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ 

የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንን ለሁለት በመክፈል በ64.7 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታልና በ16.2 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ማኔጅመንት ፓወር ግሪድ ኮርፖሬሽን ለተባለ የህንድ ኩባንያ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡ 

ኩባንያው ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎትን በመስጠት ደንበኞችን ማርካት ዋነኛ ኃላፊነቱ ሲሆን፣ መንግሥት ለሁለት ዓመት 16.7 ሚሊዮን ዶላር በመክፈል የሰጠው የማኔጅመንት ኮንትራት ነሐሴ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ተጠናቋል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላንን የጠለፈው ረዳት ፓይለት መኪና ለጨረታ ቀረበች

በጥር 2006 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ወደ ሮም ጣሊያን ሲበር የነበረውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 767 አውሮፕላን ጠልፎ ጄኔቫ ስዊዘርላንድ ያሳረፈው ረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን አበራ ንብረት የሆነች የቤት መኪና በሐራጅ ለጨረታ ቀረበች፡፡ 

የሰሌዳ ቁጥር አአ 2-A32521 መኪና ጨረታ ያቀረበው ዘመን ባንክ ነው፡፡ ረዳት አብራሪው ለመኪና ግዢ ከዘመን ባንክ የተበደረው ብድር ስላልተከፈለው ባንኩ ተሽከርካሪዋን በጨረታ ለመሸጥ መገደዱን አስታውቋል፡፡ 

ባንኩ ተሽከርካሪዋን ለጨረታ ያቀረበው በሐራጅ መነሻ ዋጋ ብር 261,503.37 ነው፡፡ ጨረታው የሚካሄደው በመስከረም ወር 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ ረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን መኪናዋን የገዛው ከአውሮፕላን መጥለፉ ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ኃይለ መድኅን ስዊዘርላንድ ውስጥ የፖለቲካ ጥገኝነት ቢጠይቅም የአገሪቱ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎት ፍርድ ቤት አንድ ጊዜ የቀረበ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ጉዳዩ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ አይታወቅም፡፡ ለስዊዘርላንድ ኢሚግሬሽን ባለሥልጣን በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ 

ኢትዮጵያ ውስጥ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በግለሰቡ ላይ ክስ መሥርቶ፣ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሌለበት 19 ዓመት ፅኑ እስራት እንደተፈረደበት ይታወሳል፡፡ 

 

የአገሪቱ የነዳጅ ግዢ ጥያቄ ተነሳበት

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዓመታዊ የአገሪቱን የነዳጅ ፍጆታ ለመሸፈን የሚያካሂደውን ዓለም አቀፍ ጨረታ በመተው፣ በድርድር ከኩዌት መንግሥት ለመግዛት የተከተለውን አቅጣጫ ነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች ተቃወሙ፡፡ ድርጅቱ ተቃውሞውን አልተቀበለም፡፡

የአንዳንድ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ተወካዮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የነዳጅ ግዢ ጨረታ ማውጣት በመተው የተለያዩ የነዳጅ ውጤቶችን ከኩዌት በድርድር በመግዛት ላይ ይገኛል፡፡ ዕርምጃውን የተቃወሙት የኩባንያ ተወካዮች ውሳኔው አገሪቱን ዋጋ እንደሚያስከፍላት ይናገራሉ፡፡ 

‹‹አንደኛ ከኩዌት የሚገዛው ነዳጅ ውድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከኩዌት ለሚገዛው ነዳጅ በበርሜል 0.30 ዶላር ጭማሪ ይከፍላል፡፡ ወይም በአንድ የነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ የ60 ሚሊዮን ብር ጭማሪ አለው፤›› ይላሉ፡፡ 

የኩባንያው ተወካዮች በሁለተኛ ደረጃ የሚያነሱት የነዳጅ ጥራት ጥያቄ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በአሁኑ ወቅት በመግዛት ላይ ያለው ነዳጅ የሊድ (እርሳስ) እና ሰልፈር መጠን ከፍተኛ በመሆኑ በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በበኩሉ የቀረቡትን ወቀሳዎች አስተባብሏል፡፡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ፣ ከኩዌት መንግሥት ነዳጅ በቀጥታ መግዛቱ የተለያዩ ጠቀሜታዎች አሉት ብለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዓመታዊ የነዳጅ ፍላጎት ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተቀራራቢ በሆነ ቁጥር፣ በዓመት አሥር በመቶ በማደግ በአሁኑ ወቅት ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ደርሷል፡፡ አገሪቱ ለነዳጅ ግዢ የምታወጣው የውጭ ምንዛሪ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከወጪ ንግድ የምታገኘው ደግሞ በዓመት ሦስት ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አገሪቱ ላላት የአውሮፕላን ነዳጅ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ከኩዌት የሚገዛ ሲሆን፣ 50 በመቶ የሚሆነውን የናፍጣ ፍላጎት የምታሟላው ከኩዌት በድርድር በሚገዛ ናፍጣ ነው፡፡ ሰባ አምስት በመቶ የሚሆነው የቤንዚን ፍጆታ ከሱዳን መንግሥት ይሸመታል፡፡ ሃያ አምስት በመቶ የሚሆነው የቤንዚን ፍጆታና 50 በመቶ የናፍጣ ፍጆታ የገዛው በግልጽ ጨረታ ከነዳጅ ነጋዴዎች ነው፡፡ የኩዌቱን ነዳጅ የሚያቀርበው የኩዌት መንግሥት ንብረት የሆነው ኩዌት ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ 20 በመቶ ቤንዚንና 50 በመቶ የሚሆነው ናፍጣ የሚመጣው ሳዑዲ ዓረቢያ ከሚገኘው ያንቡ የድፍድፍ ነዳጅ ማጣሪያ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ የዕለት የቤንዚን ፍጆታ አንድ ሚሊዮን ሊትር፣ ናፍጣ 5.8 ሚሊዮን ሊትር፣ የአውሮፕላን ነዳጅ 1.8 ሚሊዮን ሊትር ነው፡፡ ዓመታዊ የነጭ ጋዝ ፍላጎት ደግሞ 260,000 ሜትሪክ ቶን ነው፡፡ ኅብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ምድጃዎች በስፋት መጠቀም በመጀመሩ የነጭ ጋዝ ፍላጎት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች በ13 የመጠባበቂያ ነዳጅ ዴፖዎች የሚገኙ ሲሆን፣ 360,000 ሜትር ኪዩብ የማጠራቀም አቅም አላቸው፡፡ 

ኢትዮጵያ ከኩዌት ነዳጅ መግዛት የጀመረችው ከኩዌት መንግሥት ጋር ረዥም ጊዜ የፈጀ ውይይት ከተደረገ በኋላ እንደሆነ አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሚኒስትሮቻችን ሁለት ሦስት ጊዜ ወደ ኩዌት የተመላለሱ ሲሆን፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ከኩዌት የነዳጅ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ከስምምነት ላይ በመድረሳቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

በተደረሰው ስምምነት መሠረት 70 በመቶ የአውሮፕላን ነዳጅ ፍጆታ፣ 50 በመቶ የናፍጣ ፍጆታ ከኩዌት ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን መገዛት መጀመሩን አቶ ታደሰ አስታውሰዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የአውሮፕላን ነዳጅ አቅርቦት ኢትዮጵያ ለኩዌት ባቀረበችው ጥያቄ መሠረት ወደ 100 በመቶ አድጓል፡፡ 

ባለፈው ሳምንት በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በአቶ አህመድ ሺዴ የሚመራ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑክ ወደ ኩዌት ተጉዞ፣ ከኩዌት የነዳጅ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ በወቅቱም አቶ አህመድ የኩዌት ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሚያቀርበውን የናፍጣ መጠን እንዲጨምር ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ከተቻለ የኢትዮጵያን 100 በመቶ የናፍጣ ፍላጎት እንዲያሟሉ ካልሆነ ግን 70 በመቶ እንዲሸፍኑ ጥያቅ አቅርበዋል፡፡ 

የኩዌት ባለሥልጣናት በበኩላቸው ቀደም ብለው የገቡዋቸው በርካታ ውሎች ስላሉ፣ 100 በመቶ መሸፈን እንደማይችሉ ገልጸው 70 በመቶ የሚለውን ጥያቄ (በ20 በመቶ ማሳደግ) ግን ገምግመው ምላሽ እንደሚሰጡ ለኢትዮጵያ ልዑክ አስረድተዋል፡፡ 

‹‹ከኩዌት ነዳጅ የመግዛት ዕድልን በብዙ ልምምጥ ያገኘነው ዕድል ነው፤›› የሚሉት አቶ ታደሰ፣ ከኩዌት ነዳጅ መገዛቱ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ 

‹‹ከኩዌት በምንገዛበት ወቅት 90 ቀናት የመክፈያ ጊዜ ይሰጡናል፡፡ ሱዳን የምትሰጠን 30 ቀናት ነው፡፡ ነዳጅ ነጋዴዎች ከ30 እስከ 45 ቀናት ብቻ ነው የሚሰጡን፡፡ የኩዌት ነዳጅ አቅርቦት አስተማማኝ ነው፡፡ ባሉት ቀነ ገደብ ያቀርባሉ፡፡ የዋጋ ክለሳ እንደ ነጋዴዎቹ በየጊዜው አያደርጉም፡፡ የሚጠቀሙት የራሳቸውን መርከቦች በመሆኑ ርካሽ መርከብ ሲፈልጉ ጊዜ አያቃጥሉም፤›› የሚሉት አቶ ታደሰ፣ የዋጋ ልዩነትን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ዝርዝር ጠቀሜታዎችን መመልከት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡ 

‹‹ለምሳሌ እኛ ለኩዌት በበርሜል የምንከፍለው ፕሪሚየም ክፍያ (ትራንስፖርትና አገልግሎት) 4.50 ዶላር ነው፡፡ ለነዳጅ ነጋዴዎች በበርሜል 4.10 ዶላር ነው፡፡ ከነጋዴዎች ስንገዛ ኢንሹራንስ የምንከፍለው ራሳችን ነን፡፡ ነጋዴዎቹን ኢንሹራንስ ጨምሩበት ብንላቸው ዋጋቸው ሰባት ዶላር ይገባል፡፡ የኩዌት ግን ኢንሹራንስን ጨምሮ 4.50 ዶላር ብቻ ነው፤›› ብለዋል አቶ ታደሰ፡፡ 

የነዳጅ ጥራትን አስመልክቶ ለቀረበው ተቃውሞ በሰጡት ምላሽ የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት በአሁኑ ወቅት የሚገዛው ቤንዚን ከእርሳስ ነፃ የሆነ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ሊድ ያለው ቤንዚን መግዛት አቁመናል፡፡ ዓለም ሊድ ያለው ቤንዚን መግዛት አቁሟል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ 

‹‹ኢትዮጵያ ከኩዌት የምትገዛው ናፍጣ ውስጥ ያለው የሰልፈር መጠን 0.2 በመቶ ሲሆን፣ ከነጋዴዎች የሚገዛው ናፍጣ 0.05 በመቶ ሰልፈር ይዘት አለው፡፡ የናፍጣ ዋጋ ባለው የሰልፈር መጠን ይወሰናል፡፡ 0.2 በመቶ ሰልፈር ያለው ናፍጣ በበርሜል 57.76 ዶላር፣ 0.05 በመቶ ሰልፈር ያለው 58.76 ዶላር፣ 0.005 በመቶ 60.16 ዶላር፣ 0.001 በመቶ 61.16 ዶላር ዋጋ አለው፤›› ብለዋል፡፡ 

‹‹0.001 በመቶ ሰልፈር ያለውን ናፍጣ ገዝቶ ማምጣት ይቻላል፤›› የሚሉት አቶ ታደሰ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት መኪኖች ዕድሜ ጠገብ በመሆናቸው የሰልፈር ይዘቱ ዝቅተኛ የሆነ ናፍጣ ገዝቶ ማምጣቱ ጠቀሜታ እንደሌለው ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት መኪኖች በአብዛኛው አሮጌ በመሆናቸው ከፍተኛ የካርቦን ልቀት አላቸው፡፡ 

‹‹በአገራችን ያሉት ብዙዎቹ መኪኖች ሦስት መንግሥታት ያገለገሉ ናቸው፡፡ ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ናፍጣ ገዝተን ብናመጣ መኪኖቹ ነዳጁን በአግባቡ መጠቀም የሚችሉ ባለመሆናቸው አላስፈላጊ ዋጋ መክፈል ብቻ ይሆናል፤›› ያሉት አቶ ታደሰ፣ ሌሎች አገሮች ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ነዳጅ ሲያስገቡ የመኪና ዕድሜ ገድበው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ኬንያ ከስምንት ዓመት በላይ ዕድሜ ያለውን መኪና ማስገባት አይቻልም፡፡ በናይጄሪያ ከአምስት ዓመት በላይ ያለውን መኪና ማስገባት አይቻልም፡፡ ወደ እኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ ይህን ማድረግ አይቻልም፡፡ አንድ ኤንትሬ የጭነት መኪና አሥር ቤተሰብ ያስተዳድራል፡፡ ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ናፍጣ ከማስመጣታችን በፊት ዕድሜ ጠገብ ተሽከርካሪዎችን ማስወገድ አለብን፡፡ በርካታ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ አሮጌ መኪኖችን በአሁኑ ወቅት ማስወገድ አይቻልም፡፡ ምናልባት ያን ማድረግ የሚቻለው ወደ መካከለኛ ገቢ አገርነት ስንሸጋገር ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡ 

የነዳጅ ኩባንያ ተወካዮች የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እ.ኤ.አ. ለ2016 የሚውል ነዳጅ ለመግዛት ነሐሴ 17 ቀን ጨረታ ማውጣት የነበረበት ቢሆንም፣ እስካሁን ጨረታውን አለማውጣቱን ይህም የጨረታ ግዢ ሙሉ በሙሉ ቀርቷል የሚል ሥጋት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡ 

አቶ ታደሰ ድርጅታቸው ጨረታ ማውጣቱን እንዳልተወ፣ የጨረታ ሒደቱ እንዲዘገይ የተደረገው ከኩዌት የሚገዛው የነዳጅ መጠን እስከሚታወቅ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ 

የኩዌት መንግሥት የሚያቀርበው የነዳጅ መጠን ከታወቀ በኋላ ጨረታው እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ተጨማሪ የአውሮፕላን ነዳጅ እንዲያቀርቡ ጠይቀናል፡፡ የሚያቀርቡትን የናፍጣ መጠን የፍጆታችንን 70 በመቶ እንዲሆንም ጠይቀናል፡፡ ምላሻቸውን አይተን ጨረታውን እናወጣለን፤›› ብለዋል፡፡ 

ከሱዳን እስከ 80 በመቶ ቤንዚን የሚገኝ በመሆኑ የተቀረው 20 በመቶ ለጨረታ የሚቀርብ ሲሆን፣ ኩዌት ከናፍጣ ፍጆታ 70 በመቶ ልታቀርብ ትችላለች፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት 800,000 ሜትሪክ ቶን ናፍጣና 60,000 ሜትሪክ ቶን ቤንዚን ለመግዛት ጨረታ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

 

የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አጋር የሆነው የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ሥራ አስፈጻሚ አባላት መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ተሰማ፡፡ በዚህ ምክንያት የክልሉን ቋሚ መስተዳድር መመሥረት እንዳልተቻለ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ 

አለመግባባቱ የተፈጠረው አብዴፓንና የአፋር ክልልን ላለፉት 20 ዓመታት ሲመሩ በቆዩት የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ እስማኤል ዓሊ ሴሮ ቡድንና እሳቸውን ተክተው በተመረጡት የአብዴፓ ሊቀመንበር አቶ ጠሃ መሐመድ ቡድን መካከል መሆኑን፣ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የአብዴፓ ሊቀመንበር አቶ ጠሃ መሐመድ የክልሉ መንግሥት የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሲሆኑ፣ በሌሎች ክልላዊ መንግሥቶች የሥልጣን አወቃቀር መሠረት የፓርቲው ሊቀመንበር እንደመሆናቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርም ሊሆኑ ይገባል የሚል ክርክር፣ በአቶ ጠሃ ቡድን አማካይነት መነሳቱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ይህ ጥያቄ ግን አብላጫ ድምፅ ባለው የአቶ እስማኤል ዓሊ ሴሮ ቡድን በኩል ተቀባይነት ማግኘት አለመቻሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚህ ምክንያት አቶ ጠሃ መሐመድና አቶ እስማኤል ዓሊ ሴሮ የሌሉበት የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ከአንድ ወር በፊት ተካሂዶ፣ አቶ እስማኤል ለተጨማሪ ሦስት ወራት በጊዜያዊ ፕሬዚዳንትነት እንዲቆዩ፣ ካልሆነ ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ጊዜያዊ አስተዳደር ይመሥርት በሚለው ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ በስተመጨረሻም ከክልሉ ምክር ቤት ውጪ ሥራ አስፈጻሚው ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት መሾሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚሁ መሠረት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የውኃ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ አወል አርባ፣ በጊዜያዊ ፕሬዚዳንትነት ለሦስት ወራት መመረጣቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ በወደፊቱ ጉዳይ ላይ መግባባት ባለመቻሉ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን በአዲስ አበባ እየመከረ እንደነበር፣ በዚህ ስብሰባ ላይም የኢሕአዴግ ተወካዮች ለታዛቢነትና ለማስታረቅ መገኘታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ 

በትጥቅ ትግሉ ወቅት አቶ እስማኤል ዓሊ ሴሮ የሕወሓት አባል የነበሩ ሲሆን፣ በትጥቅ ትግሉ የተሳተፉ የአፋር ክልል ተወላጅ ናቸው፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የአብዴፓ ሊቀመንበር በመሆን ለ20 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ 

በግንቦት ወር 2007 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ክልሉን በመወከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ተመርጠዋል፡፡    

በአብዴፓ ውስጥ የተፈጠረውን አለመግባባትና እየተካሄደ ስለነበረው ድርድርና ምክክር ለአብዴፓ ጽሕፈት ቤት፣ ለክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ፣ ለኢሕአዴግ የውጭ ግንኙነት ጽሕፈት ቤትና ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ ቢቀርብም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡  

 

‹‹ምርመራ ዘመናት የሚያስቆጥር የአርኪዮሎጂ ቁፋሮ አይደለም›› የተጠርጣሪው አቶ ወንድሙ ቢራቱ ጠበቃ

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ነሐሴ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣን አቶ ወንድሙ ቢራቱ፣ የአውሮፕላን ትኬት በመግዛት በግብዣ መልክ ለባለሥልጣናት ጉቦ መስጠታቸው ተገለጸ፡፡

አቶ ወንደሙ የተጠረጠሩባቸውን የሙስና ወንጀሎች እየመረመረ የሚገኘው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪው በሥልጣን ዘመናቸው ወደ ውጭ አገር በመሄድ ምን ያህል ገንዘብ እንዳወጡና ለባለሥልጣናት የአውሮፕላን ትኬት በመቁረጥ በግብዣ መልክ ጉቦ የሰጡበትን ሰነድ ከሚመለከተው ተቋም መጠየቁን አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪው የተጭበረበረ ሰነድ ሕጋዊ በማስመሰል መሬት የሸጡበትና ከባንክ ገንዘብ የተቀበሉበት ሰነድ ተሰብስቧል፡፡ ጉቦ በቼክ የተቀበሉበት ሰነድ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተሰብስቧል፡፡ ከሁለት ሰዎች ሦስት ሚሊዮን ብር ጉቦ መቀበላቸውን ከሚያረጋግጡ ሰዎች የምስክርነት ቃል መቀበሉንም ቡድኑ ገልጿል፡፡ ከጉምሩክ ከጠየቀው የማስረጃ ሰነድ ከፊሉን መሰብሰቡን፣ በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ለሚደረገው ምርመራ ደጋፊ ሰነድ በማቅረብ እየተከታተለ እንደሆነና አንድ ተጨማሪ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር አውሎ ቃሉን መቀበሉን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡

የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት የጠየቀ ሲሆን፣ ምክንያቱንም አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪው ብዙ ቤቶችና ቦታዎች እንዳሏቸው ጥቆማዎች በመምጣታቸው ከአራት ከተሞች ማኅደሮችን መሰብሰብ እንደሚቀረው፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ ያልተሰበሰቡ ማስረጃዎችን መሰብሰብ፣ ተጨማሪ ሰነዶችን ለፎረንሲክ ምርመራ በመላከ ትክክለኛነቱን አረጋግጦ መሰብሰብ፣ ሌሎች ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን አድኖ መያዝና የምስክሮችን ቃል መቀበል ስለሚቀረው መሆኑን አስረድቷል፡፡

አቶ ወንድሙ ቀደም ባሉት ቀጠሮዎች እሳቸው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ በእሳቸው ላይ የሚቀርብ ማንኛውንም ተጠያቂነት የመጠየቅ ሥልጣን ያለው የክልሉ መንግሥት መሆኑን በመናገር ሲከራከሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ተጠርጣሪው አሁንም በጠበቃቸው አማካይነት እንደገለጹት፣ የተጠረጠሩበትን የሙስና ወንጀል የማየት ሥልጣን ያለው የኦሮሚያ መንግሥት ብቻ ነው፡፡ የመመርመርና የመክሰስ ሥልጣን ያለው የኦሮሚያ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ብቻ ነው፡፡ ይሄም በፌዴራል የፀረ ሙስና አዋጅ 433/97 አንቀጽ 7(4) እና በአዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 7(2/4) ተደንግጓል ብለዋል፡፡ ፌዴራል የክልሉን ሥልጣን ማክበር እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50(8) መደንገጉንም አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ የዳኝነት ሥልጣን ስለሌለውና ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ መስጠት ስለማይችል፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50(8) እና በወ/መ/ሥ/ሥ/ቁ 110 መሠረት ክሱን ዘግቶ ተጠርጣሪው እንዲያሰናብታቸው ጠይቀዋል፡፡

የፖሊስ ምርመራ ተጠናቆ ቀዳሚ ምርመራ ውስጥ መግባቱን የጠቆሙት የአቶ ወንድሙ ጠበቃ፣ የምርመራ ሥራ ዘመናት የሚያስቆጥር የአርኪዬሎጂ ቁፋሮ አለመሆኑንና በፍጥነት መፈጸም ያለበት የሕግ ሥራ በመሆኑን በመጠቆም ተጨማሪ ቀጠሮ መሰጠት እንደሌለበት አመልክተዋል፡፡

የወንጀሉ መፈጸም አጠራጣሪ መሆኑንና ተጠርጣሪውን ዋስትና ሊያስከለክላቸው እንደማይችል የገለጹት ጠበቃው፣ ወንጀሎቹ መፈጸማቸውን የሚያስረዳ ምንም ዓይነት ማስረጃ ካለመገኘቱም በተጨማሪ ተጠርጣሪው ወንጀሉን መፈጸማቸውም አጠራጣሪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አጠራጣሪ ወንጀል የቅጣት ጣሪያው ምንም ያህል ቢሆንም የዋስትና መብት እንደማያስከለክል ጠቁመው፣ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ታልፎና መዝገቡ ተዘግቶ ከእስር እንዲፈቱ ወይም የመንቀሳቀስ መብታቸው ተገድቦ በዋስ እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡ 

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ፣ የተጠርጣሪው ጠበቃ ቀደም ባለው ቀጠሮ መርማሪ ቡድኑ በጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ምንም እንዳልሠራ መግለጻቸውን በሚመለከት መዝገቡን ተመልክቶ፣ ጠበቃው እንዳሉት ሳይሆን ቡድኑ ምርመራ ማድረጉን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ የተጠርጣሪ ጠበቃ የደንበኛቸውን ጉዳይ የፌዴራል መንግሥት ወይም ፍርድ ቤቶች ማየት እንደማይችሉና ሥልጣኑ የክልሉ መሆኑን በመጥቀስ መዝገቡ ተዘግቶ አቶ ወንድሙ በነፃ እንዲሰናበቱ ያቀረቡትን አቤቱታ እንዳልተቀበለው አስረድቷል፡፡ ያልተቀበለበት ምክንያት ቀደም ባሉ ቀጠሮዎች ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦ ችሎቱ ብይን የሰጠበት መሆኑን በመግለጽ፣ ለመርማሪ ቡድኑ ተጨማሪ ዘጠኝ ቀናትን በመፍቀድ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

አቶ ወንድሙ ሥልጣናቸውን በመጠቀምና ከፌዴራል ባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር አገራዊ ጠቀሜታ ላላቸው የተለየ ክህሎት ለሚጠይቁ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተፈቀደውን ከቀረጥ ነፃ መኪና ማስገባት መብት በመጠቀማቸው፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ሀብት በማከማቸት፣ በሕገወጥ መንገድ ያካበቱትን ሀብት ሕጋዊ በማስመሰል፣ በዘመዶቻቸው ስም ሀብት በማስቀመጥ፣ ለመንግሥት መግባት የነበረበትን ታክስና ቀረጥ ለግል መጠቀሚያ በማድረግ፣ ጉቦ በመቀበልና በማቀባበል ወንጀሎች መጠርጠራቸውን የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ቀደም ባሉት ችሎቶች ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

 

ኤርትራ የኢትዮጵያ ወረራ ያሰጋኛል አለች

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ጳጉሜን 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ኤርትራን ለመውረር እያስፈራራች መሆኗን አስታውቋል፡፡ ምንም እንኳ የመረጃው ምንጭ ማን እንደሆነ የኤርትራ መንግሥት ባይናገርም፣

ኢትዮጵያ ኤርትራን ለመውረር ከአሜሪካ ይሁንታ ማግኘቷንና ኢትዮጵያም በይፋ መግለጿን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ምንም እንኳ ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ኤርትራን በተመለከተ በፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ፣ የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያንና ሌሎች የጎረቤት አገሮችን ለማተራመስ የያዘውን ስትራቴጂ የማይተው ከሆነ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተገዶ ዕርምጃ እንደሚወስደና የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደሚያሳውቅ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ የኤርትራ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ምንም ሳይል አሁን የኢትዮጵያ ወረራ ያሰጋኛል ማለቱ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በምሥሉ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስ በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ቀን አከባበር ሥነ ሥርዓት በቅርቡ በተካሄደበት ወቅት የሚታዩ ሲሆን፣ ዝርዝር ዘገባው ለመመልከት እዚህ ላይ ይጫኑ ወይም በ ፖለትካ ገጽ ላይ ይመልከቱ፡፡ 

 

ጦማሪያኑ ለአራተኛ ጊዜ ለብይን መቀጠራቸውን ተቃወሙ

‹‹አንድ ዳኛ ምንም ማድረግ አይችልም›› ዳኛ ዘሪሁን ደሳለኝ

‹‹ከዳኞች ጋር ምንም ችግር የለብንም ከማን ጋር እንደተጣላን ገብቶናል›› በእስር ላይ ያሉ ጦማሪያን

በተጠረጠሩበት የሽብር ተግባር ወንጀል ክስ ከተመሠረተባቸው በኋላ የከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ቀርቦባቸው ለብይን የተቀጠሩት አራት ጦማሪያን፣ ለአራተኛ ጊዜ ጳጉሜን 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን ተቃወሙ፡፡ 

ተከሳሾቹ ጦማሪያን ናትናኤል ፈለቀ፣ አቤል ዋበላ፣ አጥናፍ ብርሃኔና በፍቃዱ ኃይሉ ጳጉሜን 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ብይን እንደሚሰጥ የጠበቁ ቢሆንም፣ ጉዳያቸው በሦስት ዳኞች የሚታይ ከመሆኑ አንፃር በዕለቱ አንድ ዳኛ አቶ ዘሪሁን ደሳለኝ ብቻ የተገኙ በመሆናቸው ብይኑ ሳይሰጥ ቀርቷል፡፡ ብይኑ ተሠርቶ የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ ዳኞች ባለመሟላታቸውና በመዝገቡ ላይ ባለመፈረማቸው ብይኑ ሊነገር እንደማይችል ዳኛ ዘሪሁን ገልጸዋል፡፡ 

በዳኞች አለመሟላት ለሁለተኛ ጊዜ መቀጠሩ ያበሳጫቸው ተከሳሾቹ፣ ‹‹እኛ ከዳኞች ጋር ምንም ችግር የለብንም፡፡ ከማን ጋር እንደተጣላን ገብቶናል፡፡ የምንፈልገው ቁርጥ ያለው እንዲነገረን ነው፡፡ ወይ በነፃ እንሰናበት ወይም ተከላከሉ እንባል፡፡ ብይን ለመስጠት በሚቀጠሩት ቀናት መካከል ያለው ጊዜ ለእኛ ሕመም ነው፤›› በማለት ቅሬታቸውን ተናግረዋል፡፡ 

የጦማሪያኑ ጠበቃ አቶ አመሀ መኰንን ‹‹ዳኞች እንዲሟሉ መተባበር ያለብን ነገር ካለ እንተባበር ወይም ለፍርድ ቤቱ አስተዳደር እናመልክት፤›› የሚል ሐሳብ ለዳኛ ዘሪሁን አቅርበዋል፡፡ ዳኛው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የሚቻል ከሆነ ሞክሩ፤›› ብለዋል፡፡ እሳቸውም ብይኑ ቢሰጥ እንደሚመርጡ፣ ተጠርጣሪዎቹን ዓይናቸውን ባያዩ ደስ እንደሚላቸውና (በተደጋጋሚ በመመላለሳቸው) በግላቸው እንደሚከብዳቸው ተናግረዋል፡፡ 

ያልተሟሉት ዳኞች በተለያዩ ምክንያቶች መቅረታቸውን በመጠቆም፣ እንደተሟሉ እስከ መስከረም 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ለማረሚያ ቤቱ ተነግሮ ብይኑ ሊሰጥ እንደሚችል በጽሕፈት ቤት አስታውቀዋል፡፡

 

በቁጥጥር ሥር የዋሉት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ነው

የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን) ተብሎ በሚጠራው የሽብር ቡድን ውስጥ አባል ከሆኑትና በካናዳ፣ በእንግሊዝ፣ በኤርትራና በተለያዩ አገሮች ከሚገኙ አባላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ የጋምቤላን ክልልን ለመገንጠል ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉ ሦስት ተጠርጣሪዎች ጳጉሜን 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ተከሰሱ፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ተረኛ ችሎት ክስ የመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች ኦሞት አጉዋ ኦክዋይ፣ አሽኔ አስቲን ቲቶይክና ጀማል ዑመር ሆጃሌ የሚባሉ ናቸው፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከስድስት ወራት በፊት የሽብር ቡድን የተባለው ጋሕነን ኬንያ ናይሮቢ በሚያካሂደው ስብሰባ ላይ ለመካፈል ሲሄዱ፣ መጋቢት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መሆኑን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

አንደኛው ተከሳሽ ኦሞት አጉዋ ኦክዋይ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ ‹‹የጋምቤላን ክልል ከፌዴሬሽኑ መገንጠል›› የሚል ፖለቲካዊ ግብ በማስቀመጥ፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፈራረስ የአገር ውስጥ አስተባባሪ በመሆን ሲንቀሳቀስ እንደነበር በክሱ ተገልጿል፡፡ የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራር ከሆነውና በደቡብ ሱዳን ከሚገኘው ኡቺች ከሚባለው ግለሰብ ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ ኤርትራ ውስጥ ወታደራዊ ሥልጠና የወሰዱ አባላትን ወደ ጋምቤላ እንዲልክለት በማድረግ፣ የሽብር ቡድኑን ተልዕኮ እንዲያስፈጽሙ በጋምቤላ ልዩ የፖሊስ አባላት ውስጥ እንዲቀጠሩ ማድረጉንም አክሏል፡፡

ተከሳሹ በጋምቤላ ከተማ ውስጥም የቡድኑን አባላት በመሰብሰብና አመራር በመስጠት፣ እንግሊዝ ለንደን ውስጥ ከሚኖረውና ከፍተኛ አመራር ከሆነው ኝኬው አቡላ ከሚባል ግለሰብ ጋር በኢሜል በመገናኘት የአባላቱ ቁጥር እንዲጨምር መጠየቁን ክሱ ያስረዳል፡፡ ኝኬው አቦላ በውጭ አገር የሚገኙ ጋዜጠኞች አኝዋክ ዞን ሄደው መረጃ እንዳይሰበስቡ የኢትዮጵያ መንግሥት የከለከለ መሆኑን ለኦሞት ገልጾለት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ አምስት ሰዎች፣ ከጋምቤላ አኝዋክ ዞን የቡድኑ አባላት፣ ከደቡብ ኦሞ አሥር ሰዎችን መልምሎ ኬንያ በሚደረገው የቡድኑ ስብሰባ ላይ እንዲሳተፉ እንዲያደረግ ባዘዘው መሠረት፣ መልዕክት በማስተላለፍና በማደራጀት ተግባር ላይ መሳተፉን ክሱ ያብራራል፡፡ ለሽብር ተግባር ማስፈጸሚያ 3,000 የእንግሊዝ ፓውንድ የተላከለት መሆኑንም አክሏል፡፡

ሁለተኛው ተከሳሽ አሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት ውስጥ በሚኖረው የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራር በሆነውና በቅጽል ስሙ ኡጆ በሚባለው ግለሰብ አማካይነት በ2006 ዓ.ም. የሽብር ቡድኑ አባል ሆኖ መመልመሉን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ ከዚያም እንግሊዝ አገር ከሚኖረው የሽብር ቡድኑ አባል ኝኬው አቡላ ጋር በኢሜል በመገናኘት፣ ‹‹የጋምቤላን ክልል ከሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች በመገንጠል ራሱን የቻለ ሉአላዊነት አገር መመሥረት›› በሚለው ሐሳቡ ተስማምቶ፣ በማጃንግ ዞን የሚኖሩ የማጃንግ ብሔርና ደገኞች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት፣ የማጃንግ ብሔሮች ተጐድተው እያለ፣ መንግሥት ዕርምጃ የወሰደው በማጃንግ ከፍተኛ አመራሮችና በጋምቤላ ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ ላይ ብቻ እንደሆነ በመግለጽ፣ ሐሰተኛ መረጃ ለሽብር ቡድኑ ያቀብል እንደነበር በክሱ ተብራርቷል፡፡ 

ተከሳሹ የአገር ውስጥ ከፍተኛ አመራር ከሆነው አንደኛ ተከሳሽ ኦሞት ጋር በስልክ ግንኙነት በማድረግ ቀኑ በትክክል ባልታወቀበት የካቲት ወር 2007 ዓ.ም. አራት ኪሎ አካባቢ በመገናኘት፣ ኑዌሮች ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመመሳጠር የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብት ጥሰት እያደረሱ መሆኑን፣ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ለማዳረስ የጋሕነን ከፍተኛ አመራሮች በኬንያ ናይሮቢ በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ እንዲገኝ መመካከራቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ መንግሥት በጋምቤላ ነባር ብሔረሰቦች፣ በተለይም በማጃንግ ላይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን እየፈጸመ መሆኑንና በክልሉ የመሬት ወረራ እያደረገ መሆኑን ለማስገንዘብ ‹‹Deforstation, Dis-Possission and Displacement of Gambella in General and Major People in Particular›› የሚል ጥናታዊ ጽሑፍ በስብሰባው ላይ እንዲያቀርብ ተሰጥቶት እንደነበር ክሱ ያብራራል፡፡ 

ሦስተኛው ተከሳሽ ደግሞ በጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም. ‹‹የአካባቢ ግንኙነትና ጥበቃ›› በሚል ሽፋን በኬንያ ናይሮቢ የሽብር ቡድኑ በሚያደርገው ስብሰባ ላይ በመገኘት፣ መንግሥት የአካባቢው ተወላጆችን ከመሬታቸው በማፈናቀል ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ለቡድኑ አመራሮች መረጃ በመስጠት 8,800 ብር መቀበሉን የተመሠረተበት ክስ ይገልጻል፡፡ በስብሰባው ላይ እንደሚገኝ ለአንደኛ ተከሳሽ ማረጋገጫ በመስጠቱና በመገኘቱ 6,039 ብር መቀበሉንም አክሏል፡፡

በአጠቃላይ ሁሉም ተጠርጣሪ ተከሳሾች የሽብር ቡድኑ በኬንያ ናይሮቢ በሚያደርገው ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ለመሄድ መጋቢት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውለው፣ ላለፉት ስድስት ወራት ምርመራ ሲደረግባቸው ሰንብተው ጳጉሜን 2 ቀን 2007 ዓ.ም. በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በአመራርነት፣ በማናቸውም መልኩ መሳተፍና ድጋፍ መስጠት ወንጀል እንደ ቅደም ተከተላቸው ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡        

 

መንግሥት ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመጀመር ታሳቢ ካደረጋቸው መሥፈርቶች መካከል አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በነጠላ አኃዝ ውስጥ ይሆናል የሚል ቢሆንም፣ በሐምሌ ወር የጀመረው ባለሁለት አኃዝ የዋጋ ግሽበት በነሐሴ ወርም 11.6 በመቶ ማደጉ ተገለጸ፡፡

ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ነሐሴ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ያወጣው የነሐሴ ወር አገር አቀፍ የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ እንደሚያሳየው፣ የነሐሴ ወር አገር አቀፍ ጠቅላላ የችርቻሮ ዋጋ ኢንዴክስ ከ2006 ዓ.ም. ነሐሴ ወር ጋር ሲነፃፀር 11.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

 ለዚህ ጭማሪ ምክንያት የሆኑት የምግብና አልኮል ያልሆኑ መጠጦች 14.7 ከመቶ፣ መጠጥ፣ ሲጋራና ትምባሆ 7.8 በመቶ፣ ልብስና መጫሚያ 8.9 በመቶ፣ የቤት ኪራይ፣ የቤት መሣሪያ ዕቃዎች፣ ውኃና ኢነርጂ 11.1 በመቶ ዋጋቸው በመጨመሩ እንደሆነ ኢንዴክሱ ያስረዳል፡፡

በተጨማሪም የቤት ዕቃዎች፣ የቤት ማስጌጫዎች፣ የቤት ቁሳቁስና የቤት ሠራተኛ ደመወዝ 7.0 ከመቶ፣ ሕክምና 4.1 ከመቶ፣ ኮሙዩኒኬሽን (መገናኛ) 2.7 ከመቶ፣ ሬስቶራንትና ሆቴሎች 7.7 በመቶና ሌሎች ዕቃዎችና አገልግሎቶች 4.3 ከመቶ ጭማሪ በማሳየታቸው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ 11.6 በመቶ ሊሆን መቻሉን ባለሥልጣኑ ያስረዳል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ለታየው የ11.6 በመቶ የዋጋ ዕድገት ምክንያት ከሆኑት መካከል ዋነኛው አብዛኞቹ የምግብ ዓይነቶች ጭማሪ በማሳየታቸው መሆኑን፣ የባለሥልጣኑ የነሐሴ ወር የዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ሪፖርት ይገልጻል፡፡

ከእነዚህም መካከል ሥጋ 10.7 በመቶ፣ ወተት፣ አይብና እንቁላል በ15.9 በመቶ፣ አትክልት፣ ጥራጥሬ፣ ድንችና ሌሎች የሥራ ሥር ምግቦች 26.7 በመቶ፣ ስኳር፣ ማርና ቸኮሌት 2.4 በመቶ፣ እንዲሁም ሌሎች ምግቦች 61.4 ከመቶ ዕድገት በየኢንዴክሶቻቸው ላይ ማስመዝገባቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ 

በሌላ በኩል ዳቦና እህል 0.1 በመቶና አልኮል ያልሆኑ መጠጦች 12.4 ከመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

የነሐሴ ወር 2007 ዓ.ም. የአገር አቀፍ ጠቅላላ ችርቻሮ ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ከ2006 ዓ.ም. ነሐሴ ወር ሲነፃፀር በ11.6 በመቶ ጭማሪ ለማሳየቱ አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል አዲስ አበባ 15.5 በመቶ፣ አፋር 18.5 በመቶ፣ አማራ 10.0 በመቶ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ 9.0 በመቶ፣ ድሬዳዋ 3.9 በመቶ፣ ጋምቤላ 6.8 በመቶ፣ ደቡብ ክልል 6.8 በመቶ፣ ሶማሌ 8.3 በመቶና ትግራይ 6.0 በመቶ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

መንግሥት ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ግቦችን ሲያቅድ መነሻ ካደረጋቸው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች መካከል አንዱ የዋጋ ግሽበት በነጠላ አኃዝ ሥር መሆኑን ነበር፡፡ በእርግጥም የዋጋ ግሽበት ላለፉት ሁለት ዓመታት ባለሁለት አኃዝ ዕድገት ጭማሪ አድርጎ አያውቅም፡፡ ይሁን እንጂ በ2007 ዓ.ም. ሐምሌ ወር የዋጋ ግሽበቱ ወደ 11.9 በመቶ ከፍ ብሎ ነበር፡፡ ከስታትስቲክስ ባለሥልጣን መረጃ ማየት እንደሚቻለው፣ የነሐሴ ወር የዋጋ ግሽበት መጠነኛ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

 

ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ መታሰራቸውን ተቃወሙ

የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ የነበሩትና በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ወንድሙ ቢራቱ፣ ለፌዴራልና ለክልል መንግሥታት ገቢ ማድረግ የነበረባቸውን 500 ሚሊዮን ብር ለግል ጥቅማቸው አውለዋል የሚል ጥርጣሬ በመኖሩ ኦዲት እያስደረገ መሆኑን፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ለፍርድ ቤት ገለጸ፡፡

 

መርማሪ ቡድኑ ነሐሴ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ተጠርጣሪውን ይዞ ቀርቦ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪው ለግል ጥቅማቸው አውለውታል ከተባለው 500 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ፣ በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ስም የሚገኙ የቦታዎችና የቤት ሰነዶችን በማሰባሰብ ለፎረንሲክ ምርመራ መላኩን ገልጿል፡፡ ያልተያዙ ግብረ አበሮችን አድኖ መያዝ፣ የስምንት ምስክሮችን ቃል መቀበልና ሌሎች የምርመራ ሥራዎች እንደሚቀሩት በመግለጽ፣ ፍርድ ቤቱ ለተጨማሪ ምርመራ የ14 ቀናት ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ 

ተጠርጣሪው አቶ ወንድሙ በበኩላቸው ባቀረቡት መቃወሚያ እንደገለጹት፣ እሳቸው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል ናቸው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸው ያለመከሰስ መብት ሳይነሳ ሕገ መንግሥቱ ተጥሶ መታሰራቸው አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቀዋል፡፡ እሳቸው የክልል ባለሥልጣን በመሆናቸው የማሰርም ሆነ የመጠየቅ መብት ያለው የክልሉ መንግሥት እንጂ የፌዴራል መንግሥት አለመሆኑን በመግለጽ ተቃውመዋል፡፡ 

ከሌሊቱ 7፡00 ሰዓት መያዛቸው ሕገወጥ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በተያዙበት ወቅት 22 ሺሕ ብርና መኪናቸው የት እንዳለ አለማወቃቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በሰጠው ምላሽ ተጠርጣሪው ባቀረቡት ተቃውሞ ላይ ፍርድ ቤቱ ቀደም ባለው ችሎት ብይን የሰጠበት መሆኑን አስታውሷል፡፡ 

ፍርድ ቤቱም ተጠርጣሪው ፍርድ ቤት ቀርበው በነበሩ ጊዜ ተመሳሳይ ተቃውሞ አቅርበው ትዕዛዝ የተሰጠበት መሆኑን አስታውቋል፡፡ በድጋሚ እንደማይቀበልም ገልጾላቸዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን በፍጥነት አከናውኖ እንዲያጠናቅቅ አሳስቦ፣ ለተጨማሪ ምርመራ አሥር ቀናት ፈቅዶለታል፡፡ 

 

የፋብሪካው ሠራተኞች ሥጋታቸውን ገልጸዋል

ታዋቂው ነጋዴ ሐጂ በዳዳ ጫሊ ጅሩ ከፍተኛ ባለድርሻ የሆኑባቸው ድሬ ኢንዱስትሪዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሞጆ ቆዳ ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር፣ ቦረን ሪል ስቴትና ድሬ ኃይላንድ አክሲዮን ማኅበር አክሲዮኖችን ለሦስተኛ ወገን እንዳይሸጡና እንዳይተላለፉ ታግደው እንዲቆዩ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ነሐሴ 13 ቀን 2007 ዓ.ም.  የሰጠውን ጨምሮ ውሳኔ በተለያዩ ጊዜያት በሰጠው ትዕዛዝ በወጋገን ባንክ፣ በአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በተለያዩ ቅርንጫፍ ባንኮች የተቀመጠ ገንዘብና አክሲዮንም ካለ ታግዶ እንዲቆይ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

የታዋቂው ነጋዴ ሐጂ በዳዳ አክሲዮኖችና ገንዘብ እንዲታገዱ ምክንያት የሆነው፣ ለ50 ዓመታት የትዳር አጋራቸው መሆናቸውን የገለጹት ወ/ሮ ልኬለሽ ያዴሳ ለፍርድ ቤት ባቀረቡት የፍች ጥያቄ ምክንያት ነው፡፡

ወ/ሮ ልኬለሽ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 81 መሠረት የፍች ውሳኔ እንዲሰጣቸው ያቀረቡት፣ ሐጂ በዳዳ ትዳራቸውን አክብረው መኖር ሲገባቸው ቤታቸውን ጥለው በመውጣት ከጋብቻ ውጪ ከሌላ ሰው ጋር መኖር መጀመራቸውን በመግለጽ መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡

ሐጂ በዳዳ በራሳቸው፣ በባለቤታቸውና በአራት ልጆቻቸው በተቋቋመው 112.9 ሚሊዮን ብር ዋጋ ካለው ድሬ ኢንዱስትሪዎች አክሲዮኖች ውስጥ 86,580 አክሲዮን ወይም 86.5 ሚሊዮን ብር ድርሻ ያላቸው መሆኑን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ከፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የገዙት ሞጆ ቆዳ ፋብሪካም ከ25 በላይ ባለአክሲዮኖች ያሉት ሲሆን፣ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ሐጂ በዳዳ መሆናቸውን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ባለቤታቸው ባቀረቡት የፍች ጥያቄ ክስ ምክንያት የባንክ ገንዘባቸውና አክሲዮኖቻቸው የታገደባቸው ሐጂ በዳዳ፣ ለፍርድ ቤቱ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 

ሐጂ በዳዳ ለፍርድ ቤቱ በሰጡት ምላሽ ከባለቤታቸው ጋር መስማማት ባለመቻላቸው ለ50 ዓመታት የጠበቁትን ትዳራቸውን ለመተው መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ከራሳቸው ይልቅ ለቤተሰባቸውና ለአገራቸው ዕድገትና ልማት በማሰብ ሁሉን ነገር ሆነው ፋብሪካዎች ማቋቋማቸውንና ከ1,200 በላይ ሠራተኞች እንዳሏቸው አስረድተዋል፡፡ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ልዩ ልዩ ብድር እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡ ፍች ለጠየቁት ባለቤታቸው በ2,310 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባ መኖሪያ ቤትና ሦስት ሚሊዮን ብር በመስጠት ትዳራቸው ሳይፈርስ ለየብቻ እንዲኖሩ በማቀድ በሰላም እየኖሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ 

በሸሪዓ ሕግ መሠረት ሌላ ሰው በማግባት ልጆች ወልደው እየኖሩ መሆኑንና ከሳሽ ባለቤታቸውን ጨምሮ ሁሉም ሰው የሚያውቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም እንዲከፋፈሉና ትዳር እንዲፈርስ የተጠየቀው አግባብ ባለመሆኑ ክሱ ተሰርዞ እንዲሰናበቱ ጠይቀዋል፡፡ ሐጂ በዳዳ ባቀረቡት ሌላ አቤቱታ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ የተለያዩ ዕዳዎች እንዳለባቸው በድጋሚ ጠቅሰው፣ በገቢና በወጪ ንግድ ላይ ተሰማርተው ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስገቡ መሆኑን በመግለጽ፣ ፍርድ ቤቱ ወደ ክርክር እንዲገቡ የሚያደርግ ከሆነ ክርክሩ በዝግ እንዲሆን ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን አልተቀበላቸውም፡፡ 

ሐጂ በዳዳ በበኩላቸው በወ/ሮ ልኬለሽ ያዴሳ ስም በአዋሽ ኢንተርናሽል ባንክ የተቀመጠ ገንዘብ በአራዳ ሕንፃ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ያለ የኤሌክትሮኒክስ መደብር፣ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ሰዴን ሶዶ ወረዳ አሌ አበባን ቀበሌ የሚገኝ ንብረትና ድሬ ኢንዱስትሪዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ግቢ ውስጥ የሚገኝ መጋዘን ውስጥ ያለ ንብረት ታግዶ እንዲቆይ ጠይቀው፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ዕግድ ጥሏል፡፡ 

በድርጅቶቹ ከፍተኛ ባለድርሻ ሐጂ በዳዳና የአክሲዮን ድርሻና የባንክ ባለቤት ሒሳብ ላይ ፍርድ ቤቶች የሚጥሉት ዕድግ እንዳስፈራቸው የሞጆ ቆዳ ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር መሠረታዊ ሠራተኞች ማኅበር  ገልጿል፡፡ ባለሀብቱ ፋብሪካውን ከገዙት በኋላ ውጤታማ እየሆነ እንደሚገኝ የገለጸው ማኅበሩ፣ 992 ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኛ በፋብሪካው መኖሩን ገልጾ፣ በተለይ በባንክ ሒሳብ ላይ ዕግድ በመጣሉ የላብ አደሩ ደመወዝ እንዴት እንደሚከፈል ሥጋት እንደገባው አመልክቷል፡፡ ችግሩ የፋብሪካ ሠራተኞቹ ብቻ ሳይሆን ከ5,000 በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦቻቸውም ጭምር መሆኑን ጠቁመው፣ የሚመለከተው አካል ችግሩን በቀላሉ እንዲፈቱት እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለመስጠት ለጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

  

 

 

የመኢአድ ፕሬዚዳንት በነፃ ተሰናበቱ

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው የግንቦት ሰባት ድርጅት ጋር ለመቀላቀል ሲጓዙ በቁጥጥር ሥር ውለዋል ተብለው ክስ የተመሠረተባቸው አራት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ላይ የምስክርነት ቃል ተሰጠ፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን የሽብር ድርጊት ወንጀል ክስ እየመረመረ ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት ምስክሩን ያሰማው ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የተመሠረተባቸውን ክስ እንደማይቃወሙና ድርጊቱን መፈጸማቸውን በማመናቸው፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ የጠቀሰውን አንድ ምስክር አሰምቷል፡፡ 

የዓቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው የቀረቡት ግለሰብ እሳቸውም የሰማያዊ ፓርቲ አባል እንደነበሩ አስታውቀው፣ የፓርቲው የተለያዩ ክፍሎች አመራሮች የነበሩትን ብርሃኑ ተክለ ያሬድ፣ እየሩሳሌም አስፋውንና ፍቅረ ማርያም አስማማውን የሚያውቋቸው በፓርቲው ውስጥ በነበሩበት ጊዜ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ተከሳሽ ብርሃኑና እየሩሳሌም የካቲት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ሰላማዊ ትግሉ እንደማያዋጣ ተነጋግረው ግንቦት ሰባትን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ለመሄድ ሲንቀሳቀሱ ምስክሩም አብረው ባህር ዳር ድረስ መሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡ 

ባህር ዳር እንደደረሱ እሳቸው (ምስክሩ) ሐሳባቸውን በመቀየር ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ያስረዱ ሲሆን፣ ተከሳሽ ብርሃኑ ‹‹ለምን ትመለሳለህ? ቢያንስ ጎንደር የምናገኘው ሰው ስላለ እሱን ካገኘህ በኋላ ትመለሳለህ፤›› ቢላቸውም ሳይስማሙ ቀርተው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹በወቅቱ ስሜታዊ ሆኜ መወሰኔ አግባብ እንዳልሆነ ስለተረዳሁ ነው፤›› በማለት ‹‹ለምን ሐሳብህን ቀየርክ?›› ለሚለው መስቀለኛ ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ምስክር ለመሆን መገደድ አለመገደዳቸውን፣ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው፣ ታስረው እንደነበርና ግንቦት ሰባት ነፃ አውጪ ወይም አሸባሪ ድርጅት መሆኑን እንዲያስረዱ በተከሳሾቹ ሲጠየቁ ዓቃቤ ሕግ ተቃውሟል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀን ድርጅት መጠየቁ አግባብ አለመሆኑን ዓቃቤ ሕግ በማስረዳቱ፣ ፍርድ ቤቱም የተከሳሾቹ ጥያቄ እንዲታለፍ በይኗል፡፡ ምስክሩ በአራተኛ ተከሳሽ ደሴ ካህሳይ ላይ የምስክርነት ቃል አልሰጡም፡፡

ፍርድ ቤቱ ብይን ለመስጠት ለመስከረም 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

ይህ በዚህ እንዳለ አይኤስን ለመቃወም መንግሥት ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠርቶት በነበረው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ የተፈጠረውን ብጥብጥ በማደራጀትና በመምራት ተጠርጥረው ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩት የመኢአድ (የቀድሞ) ሊቀመንበር  አቶ ማሙሸት አማረ በነፃ ተለቀዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸውን ክስ ሲመረምር የከረመው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት አቶ ማሙሸትን በነፃ ያሰናበታቸው፣ ሰላማዊ ሠልፉ በተደረገበት ዕለት እሳቸው ከምርጫ ቦርድ ጋር በነበረባቸው ክርክር ፍርድ ቤት መዋላቸውን የሚያስረዳ ሰነድ በማቅረባቸው ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው ምስክሮች የሰጡት የምስክርነት ቃል የተጠና መሆኑን በመቃወም ጠበቃቸው ለፍርድ ቤት በማስረዳታቸውና ምስክሮቹም የተለያየና የማይገናኝ የምስክርነት ቃል መስጠታቸው ለአቶ ማሙሸት በነፃ መሰናበት ምክንያት ሆኗል፡፡

 

ከወጪ ንግድ 14 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል

-ዕቅዱ 119 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት አለው

ከ2008 እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ ተግባራዊ የሚደረገው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ረቂቅ ዕቅድ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣትና ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው የዓለም አገሮች የመጀመሪያው ረድፍ ላይ ማሠለፍ ራዕይ አድርጓል፡፡ ለዚህም ዕቅድ መሳካት 2.4 ትሪሊዮን ብር ይጠይቃል፡፡

 

ለዕቅዱ እንደ መነሻ የተወሰዱት የአገሪቱ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መልካም ውጤት እያስገኙ መሆናቸው፣ በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወቅት የተጀመሩና በግንባታ ላይ ያሉ ኢኮኖሚያዊ የልማት ፕሮጀክቶች በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ተካተው መጠናቀቅ ያለባቸው መሆኑን ግንዛቤ ይዟል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ የተስማማችባቸው የድኅረ 2015 የልማት ግቦችም የዕቅድ ዝግጅቱ መነሻ ያደረጋቸው ጉዳዮች መሆናቸውን  ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በዚሁ መሠረት በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ማለትም በ2012 ዓ.ም. መጨረሻ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገቱ 11 በመቶ እንዲሆን ማድረግ በመሠረታዊ የዕድገት አማራጭ የተቀመጠ ግብ መሆኑን የተገኙት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በከፍተኛው የዕድገት አማራጭ ደግሞ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት በ2012 ዓ.ም. መጨረሻ 12.2 በመቶ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ በከፍተኛው የዕድገት አማራጭ መሠረት በአገሪቱ መዋቅራዊ ለውጥ መምጣት የሚችልበትን ሥርዓት መጣል ትልቁ ዓላማ ነው፡፡

በዚሁ በከፍተኛ የዕድገት አማራጭ ረቂቅ ዕቅድ መሠረት የግብርና ዘርፉ የምርት ዕድገት ተጠናክሮ በመቀጠል አማካይ ዓመታዊ ዕድገቱ ስምንት በመቶ እንዲሆን ታቅዷል፡፡ ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር ዕውን ለማድረግ በዕቅዱ ዘመን የኢንዱስትሪ ዘርፉን አማካይ ዓመታዊ ዕድገት 19.8 በመቶ ለማድረስ ረቂቅ ግብ መጣሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአጠቃላይ የግብርና ዘርፍ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የሚኖረው ድርሻ በ2007 ዓ.ም. ከነበረበት 41 በመቶ በ2012 ዓ.ም. ወደ 35.6 በመቶ እንዲወርድ በዕቅዱ ተይዟል፡፡

የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከሁሉም ዘርፎች ቅድሚያ የተሰጠው በመሆኑ በላቀ ፍጥነት ያድጋል የሚል ግምት ተሰጥቶታል፡፡ በመሆኑም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የሚኖረው ድርሻ በ2007 ዓ.ም. ከነበረበት 15.6 በመቶ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ዘመን መጠናቀቂያ ላይ የ22.8 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው በረቂቅ ዕቅዱ ተቀምጧል፡፡ የአገልግሎት ዘርፉ ድርሻ ከግብርናና ከኢንዱስትሪ ዘርፎች ድርሻ ውጪ ያለውን 41 በመቶ እንደሚይዝ የተገመተ ሲሆን፣ ይኼም በ2007 ዓ.ም. ከነበረበት 43.4 በመቶ እንደሚቀንስ ያሳያል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማገባደጃ ላይ የሸቀጦች የወጪ ንግድ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የሚኖረውን ድርሻ 11.8 በመቶ እንደሚሆን ውጥን ተይዟል፡፡

ለዚህም ይረዳ ዘንድ የየዘርፉ የወጪ ንግድ ገቢ ተሰልቶ በረቂቅ ዕቅዱ ተቀምጧል፡፡ በዚህም መሠረት ከግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ 7.7 ቢሊዮን ዶላር በ2012 ዓ.ም. ለማግኘት የታቀደ ሲሆን፣ ከኢንዱስትሪ ምርቶች ወጪ ንግድ ደግሞ 4.6 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል፡፡

በወጪ ንግድ ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸው ልዩ ዘርፎች መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት አንዱ ሲሆን፣ በ2012 ዓ.ም. መጨረሻ 636 ሚሊዮን ዶላር የማግኘት ዕቅድ ተይዟል፡፡ በማዕድን ዘርፍ በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የተገኘው የንግድ ገቢ 508 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን 2.1 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል፡፡

ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የማኑፋክቸሪን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዓላማ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ዘርፉ በሁሉም መለኪያዎች በኢኮኖሚው ውስጥ የቀዳሚነት ሥፍራ እንዲይዝ ማድረግ ነው፡፡

በዚህ መሠረት የመካከለኛና የከፍተኛ ኢንዱስትሪ ኤክስፖርት ገቢ በየዓመቱ በአማካይ በ98 በመቶ እንዲያድግ ዕቅድ የተያዘ ሲሆን፣ በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ 4.6 ቢሊዮን ዶላር እንዲደርስ ታስቧል፡፡

ከፍተኛ ግምት የተጣለባቸው ጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ዘርፎች ሲሆኑ፣ ከጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ አንድ ቢሊዮን ዶላር የኤክስፖርት ገቢ ለማግኘት ታቅዷል፡፡ 

በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ደግሞ 800 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል፡፡

ለዚህ ዘርፍ ይረዳ ዘንድ እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ ሰባት ሚሊዮን ካሬ ሜትር መሬት የማምረቻ ቦታዎችን በማዘጋጀት ለባለሀብቶች ለማቅረብ ታቅዷል፡፡ አራት የተቀናጁ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፖርኮች ፓይለት ፕሮጀክቶችን በማልማት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ምርቶች ከኢንዱስትሪ ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ 

የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ከማስፋፋት ፕሮግራም በተጨማሪ አዳዲስ ዘርፎችን በማምረት፣ በእነዚህ መስኮች ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ለማስፋፋት ትኩረት እንደሚሰጥ ረቂቅ ዕቅዱ ያስረዳል፡፡ ከዚህ አኳያ ዓለም አቀፍ የእሴት ሰንሰለትንና የአገሪቱን ዕምቅ ሀብት የገበያ ፍላጎትን መሠረት በማድረግ የባዮ ቴክኖሎጂ፣ የፔትሮ ኬሚካል፣ የኤሌክትሪካልና የኤሌክትሮኒክስ እንዲሁም የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በተለይም የሶፍትዌርና የሐርድዌር ልማት ለማስፋፋት ታቅዷል፡፡

በመንገድ ዘርፍ ልማት ጠቅላላ የመንገድ ርዝመትን በ2007 ዓ.ም. ከተደረሰበት 120,000 ኪሎ ሜትር ወደ 220,000 ኪሎ ሜትር ለማድረስ ታቅዷል፡፡

በባቡር መሠረት ልማት በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ታቅደው የነበሩትን መስመሮች ማጠናቀቅ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፣ ተጨማሪ አምስት አገር አቀፍ የባቡር መስመሮችን ጥናት ማካሄድና ፋይናንስ የማፈላለግ ሥራ ለማከናወን በዕቅዱ ተካቷል፡፡

በመሆኑም እስከ 2012 ዓ.ም. መጠናቀቅ የሚገባቸው የባቡር መስመሮች 2,782 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ሲሆን፣ እነሱም መቐለ-ሐራ ገበያ፣ ሐራ ገበያ-አሳይታ፣ አሳይታ-ታጁራ ወደብ፣ አዋሽ-ሐራ ገበያ፣ አዲስ አበባ-ሰበታ-ኢጃጂ-ጂማ-በደሌ-ቴፒ-ደማ የሚደርሰው 740 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር፣ እንዲሁም 905 ኪሎ ሜትር የሚሽፍነው የሞጆ-ሐዋሳ-ወይጦ-ሞያሌ መስመሮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተጨሪም በአዲስ አባባ ከተማ የተዘረጋውን 34 ኪሎ ሜትር ቀላል የከተማ ባቡር መስመር በሁለት አቅጣጫዎች በድምሩ 41 ኪሎ ሜትር ለማስረዘም ታቅዷል፡፡

ጥናትና የገንዘብ ማፈላለግ የታቀደባቸው የባቡር መስመሮች ደግሞ ከወልዲያ-ወረታ-ፍኖተ ሰላም፣ ከወረታ-መተማ፣ ከመቐለ-ሽሬ፣ ኢጃጂ-ኩምሩክና ኢተያ-ጊኒር ሲሆኑ፣ አምስት መስመሮች ጠቅላላ ርዝመታቸው 1,820 ኪሎ ሜትር የሚደርሱ ናቸው፡፡

በኢነርጂ ረገድ በ2007 ዓ.ም. የተደረሰበትን 2,220 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም፣ በ2012 ዓ.ም. ወደ 17,347 ሜጋ ዋት ለማድረስ ታቅዷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከውኃ ኃይል አሁን የሚገኘውን 1,953.5 ሜጋ ዋት ኃይል ወደ 13,957 ሜጋ ዋት ለማሳደግ ታቅዷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከንፋስ የሚገኘውን 171 ሜጋ ዋት ወደ 1,222 ሜጋ ዋት ለማድረስ ታቅዷል፡፡

በአጠቃላይ ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ በአምስት ዓመት ፕሮግራም ውስጥ 2.4 ትሪሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ረቂቅ ዕቅዱ ይተነትናል፡፡

ይኼንን ወጪ ለመሸፈን በ2012 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የሚኖረው የአገር ውስጥ የገቢ አቅም 2.03 ትሪሊዮን ብር ነው፡፡ በመሆኑም የበጀት ጉድለቱ ዕርዳታን ጨምሮ 341.2 ቢሊዮን ብር ይሆናል የሚል ታሳቢ በረቂቅ ዕቅዱ ተይዟል፡፡

ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈለገው የውጭ ምንዛሪም 119.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን የተገመተ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የኢንዱስትሪው ዘርፍ 30 በመቶ፣ የአገልግሎት ዘርፍ ደግሞ 41.7 በመቶ እንደሆነ ተተንትኗል፡፡ 

 

የኢሕአዴግ አሥረኛ ጠቅላላ ጉባዔና የሥልጣን ቅብብሎሹ

በጥር ወር 1983 ዓ.ም. የትጥቅ ትግል ላይ እያለ የመጀመርያ ጠቅላላ ጉባዔውን በትግራይ ክልል በቆላ ተምቤን የጀመረው ኢሕአዴግ አሁን አሥረኛ ጉባዔውን በመቐለ ከተማ በማካሄድ ላይ ነው፡፡ ‹‹ሕዝባዊ አደራን በላቀ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን››

በሚል መሪ ቃል ጠቅላላ ጉባዔውን እያካሄደ ያለው ኢሕአዴግ  የመጀመርያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም በዝርዝር ከገመገመ በኋላ፣ ለሁለተኛው ዕቅድ ተግባራዊነት የሚረዱ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሰሞኑን በአራቱ አባል ድርጅቶች (ሕወሓት፣ ብአዴን፣ ኦሕዴድና ደኢሕዴን) በተካሄዱ የተናጠል ጉባዔዎች በሥራ ላይ ያሉት ሊቀመናብርትና ምክትሎቻቸው በድጋሚ ተመርጠዋል፡፡ በኢሕአዴግ ደረጃም ለውጥ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ነገር ግን በአመራር የመተካካት አሠራር መሠረት የአባል ድርጅቶቹና የግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የትጥቅ ትግል ተሳትፎ የነበራቸውና ከ20 ዓመታት በላይ በአመራር ላይ የቆዩ አባላት ሙሉ በሙሉ ይተካሉ በሚለው፣ በ2002 ዓ.ም. ይፋ የሆነው ፖሊሲ ተግባራዊነት ላይ ጥያቄዎች መነሳት ጀምረዋል፡፡ በምሥሉ ላይ ከግራ ወደቀኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድርና የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ዓባይ ወልዱ በመቐለ የጉባዔ አዳራሽ ውስጥ ሲመካከሩ ይታያሉ፡፡ በግንባሩ አባል ድርጅቶች በተመረጡ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ገጸ ታሪክና በመተካካት ፖሊሲው ማዕቀፍ ላይ የተዘጋጀው ዘገባ ለመመልከት እዚህ ላይ ይጫኑ ወይም በ ፖለቲካ ገጽ ላይ ይመልከቱ፡፡

 

በሕገወጥ መንገድ ተይዞ የነበረ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ለመንግሥት ተመለሰ

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በ2008 በጀት ዓመት ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በሙስና ተጠርጥረው በክስ ሒደት ላይ ከሚገኙ ሰዎች፣ 28 ቤቶችን በፍርድ ቤት

ማሳገዱንና ስድስቱ ቤቶች በዱባይና በደቡብ ሱዳን ጁባ ከተማ የሚገኙ መሆናቸውን ገለጸ፡፡

ኮሚሽኑ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንደገለጸው አራት ቤቶችን በዱባይ፣ ሁለት ቤቶችን ደግሞ በደቡብ ሱዳን ጁባ ከተማ ውስጥ አሳግዷል፡፡ ቀሪዎቹ 22 ቤቶች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የሚገኙ መሆኑንም ኮሚሽኑ አክሏል፡፡

በዱባይና በጁባ ከተማ የታገዱት ቤቶች፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጁባ ቅርንጫፍ ላይ ተፈጽሟል በተባለ የሙስና ወንጀል ከተጠረጠሩ የባንኩ ሠራተኞችና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “ወርቅ ነው” በማለት ባሌስትራ በማቅረብ በአጭበረበሩ ግለሰቦች የተገዙ መሆናቸውን፣ ቀሪዎቹ ቤቶች ደግሞ በሌላ የሙስና ወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩ ግለሰቦች መሆናቸውን ኮሚሽኑ አብራርቷል፡፡

ኮሚሽኑ በአዲሱ በጀት ዓመት አንድ ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ከ3.2 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ገንዘብና በየካ ክፍለ ከተማ በአንድ ግለሰብ በሕገወጥ መንገድ ተይዞ የነበረ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ለመንግሥት ማስመለሱን ገልጿል፡፡ በተለያዩ የሙስና ወንጀል ድርጊቶች ጋር በተያያዘ 21 የግንባታና 35 የቤት አውቶሞቢሎች፣ 56 የተለያዩ ዓይነት ተሽከርካሪዎች፣ የአክሲዮን ገንዘብን ጨምሮ ከ53 ሚሊዮን ብር በላይና አንድ የግል ድርጅት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሳገዱን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

የግንባታ ማሽነሪዎች፣ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችና ገንዘብ ያሳገደው በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ ክስ ከተመሠረተበት የእስራኤሉ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ትድሃር ሲሆን፣ አብዛኛው ገንዘብ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደቡብ ሱዳን ጁባ ቅርንጫፍ ሠራተኞች ከነበሩት ተጠርጣሪዎች መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

 

ከነሐሴ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በመቀሌ የሰማዕታት አዳራሽ ሲካሄድ የከረመው 12ኛው የሕወሓት ጉባዔ አቶ ዓባይ ወልዱ ሊቀመንበር ሆነው እንዲቀጥሉ በድጋሚ መረጣቸው፡፡ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል፡፡

ከሁለቱ ሊቀ መናብርት በተጨማሪ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ አቶ በየነ ምክሩ፣ ወ/ሮ አዜብ መስፍን፣ አቶ ዓለም ገብረ ዋህድ፣ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማና ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር (ሞንጀሪኖ) የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ (ፖሊት ቢሮ) አባላት ሆነው ተመርጠዋል፡፡

ሕወሓት ከነባር የፖሊስ ቢሮ አባላት መካከል አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ አቶ አባዲ ዘሞ፣ አቶ ቴድሮስ ሐጎስና አቶ ፀጋይ በረኼ በመተካካት ሸኝቷል፡፡ ወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሴ፣ አቶ ተወልደ ብርሃን በርኼና አቶ ተክለወይኒ አሰፋ በፈቃዳቸው ከማዕከላዊ ኮሚቴ  አባልነት ለቀዋል፡፡

ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት 50 አባላት ታጭተው 45 አባላት የተመረጡ ሲሆን፣ የአቶ ዓባይ ወልዱ ባለቤት ወ/ሮ ትርፉ ኪዳነ ማርያምና የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ክንደያ ገብረ ሕይወት ሳይመረጡ ከቀሩት አምስት አባላት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት በተካሄደው 11ኛው የሕወሓት ጉባዔ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሆነው ከተመረጡት ውስጥ አቶ ቴዎድሮስ ሐጎስ፣ ወ/ሮ ትርፉ ኪዳነ ማርያምና አቶ ገብረ መስቀል ታረቀ ሳይቀጥሉ ቀርተዋል፡፡ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማና ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር አዳዲስ አባላት ሆነው ገብተዋል፡፡
 

ከነሐሴ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በመቐለ ሰማዕታት አዳራሽ እየተደረገ ባለው 12ኛው የሕወሓት ጉባዔ፣ በመተካካት ተሸኝተው የነበሩ የሕወሓት አመራሮች በጉባዔው እንዲመረጡና እንዲመርጡ ተወሰነ፡፡ አዘጋጅ ኮሚቴው የጋበዛቸው ያለ ድምፅ እንዲሳተፉ ነበር፡፡ ከ1,650 በላይ ጉባዔተኞች በታደሙበት ጉባዔ የተገኙ አንድ ተሳታፊ ከዚህ ቀደም …

በመተካካት ተሸኝተው የነበሩት የሕወሓት ነባር አመራሮች ተመለሱ Read more »

በተጠረጠሩበት የሽብር ድርጊት ወንጀል ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ከቆዩ በኋላ ነሐሴ 14 ቀን 2009 ዓ.ም. በነፃ የተሰናበቱት የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣ ዓቃቤ ሕግ ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ ስላለባቸው ሳይፈቱ ቀሩ፡፡

“በተጠረጠሩበት የሽብርተኝነት ወንጀል መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ ተሰናብተዋል” በማለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በነፃ አሰናብቷቸው የነበሩት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ አመራሮች አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የአረና ለትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉዓላዊነት ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታና የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ እንዲሁም በእነሱ የክስ መዝገብ ተካተው የነበሩት አቶ አብርሃም ሰለሞን ነበሩ፡፡ በሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ያልተስማማው ዓቃቤ ሕግ፣ ያቀረባቸው የሰነድና የሰዎች ማስረጃዎች በአግባቡ እንዳልታዩለት በመግለጽ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 188(5) መሠረት የይግባኝ አቤቱታውን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በማስገባቱ፣ በነፃ የተሰናበቱት አምስቱም ሰዎች እንዳይለቀቁ ዕግድ ተጥሏል፡፡

የሥር ፍርድ ቤት በተለይ አቶ ሀብታሙና አቶ አብርሃም ሰለሞን በዕለቱ (ነሐሴ 14 ቀን2007 ዓ.ም.) እንዲፈቱና አቶ አብርሃ፣ አቶ ዳንኤልና አቶ የሺዋስ ችሎት በመድፈር ወንጀል የተጣለባቸውን ቅጣት ሲጨርሱ እንዲለቀቁ የሰጠው ትዕዛዝ ታግዷል፡፡

በዕለቱ እንዲፈቱ ትዕዛዝ የተላለፈላቸው አቶ ሀብታሙና አቶ አብርሃም ቤተሰቦች፣ ነሐሴ 14 ቀን ከሰዓት በኋላና ነሐሴ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ሙሉ ቀን ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በመሄድ፣ የሚፈቱ ቤተሰቦቻቸውን በማጀብ ወደ ቤታቸው ይዘው ለመግባት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ ሲጠብቁ ውለው፣ ምንም ዓይነት ምላሽ ሳያገኙ መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ ነሐሴ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ተመልሰው በመሄድ ሲጠይቋቸው እነ ሀብታሙም ምንም የሰሙትም ሆነ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ እንደነገሯቸው ገልጸዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ ጠይቆ “ይፈቱ” የሚለው ትዕዛዝ መታገዱን ያወቁት ነሐሴ 18 ቀን 2007 ዓ.ም. መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤት በአንድ መዝገብ ላይ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ እንደሰጠው ውሳኔ ስፋትና ጥበት፣ ውሳኔውን አስገልብጦ ለመውሰድ ፈጠነ ቢባል በአምስት ቀናት ውስጥ ሊደርስ እንደሚችል የገለጹት የሕግ ባለሙያዎች፣ የእነ ሀብታሙ አያሌው ውሳኔ 44 ገጽ ከመሆኑ አንፃር፣ አስገልብጦ ለመውሰድ ቢፈጥን ከአንድ ሳምንት በላይ ሊወስድ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ዓቃቤ ሕግ በአንድ ቀን ልዩነት አስገልብጦና የይግባኝ አቤቱታ አዘጋጅቶ በማግሥቱ ውሳኔውን ማሳገዱ ያልተለመደ እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡

ሌላው የሕግ ባለሙያዎቹ የገለጹት አንድ ተከሳሽ በነፃ ከተሰናበተ፣ ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ እንደሚፈልግ ስለገለጸ ብቻ ነፃ የተባለው ሰው በእስር እንዲቆይ የሚያደርግ የሕግ አግባብ በግልጽ እንዳልተቀመጠ ተናግረዋል፡፡ ይልቁንም በሥር ፍርድ ቤት ጥፋተኛ የሚባል ተከሳሽ ለበላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቦ ጉዳይ እስከሚታይለት ድረስ፣ በእስር እንዳይቆይ ታግዶ እንዲቆይለት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር በ188(2) መሠረት መቆየት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ውሳኔ ያረፈበትን መዝገብ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 188(5) መሠረት ማሳገድ እንደሚችል ገልጿል፡፡ 

ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ ባለበት የእነ ሀብታሙ አያሌው መዝገብን መርምሮ “ያስቀርባል ወይም አያስቀርብም” ለማለት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለመስከረም 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል፡፡

 

‹‹መጠየቅ ካለብኝ በክልል እንጂ በፌዴራል አይደለም›› አቶ ወንድሙ ቢራቱ

ለመንግሥት መግባት የነበረበትን ተጨማሪ እሴት ታክስና ሌሎች የመንግሥት የግብር ገቢዎች በማጭበርበር በግላቸውና በዘመዶቻቸው ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በማካበት በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩት፣

የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ወንድሙ ቢራቱ ሰው በመግደል ወንጀል መጠርጠራቸው ለፍርድ ቤት ተገለጸ፡፡

ነሐሴ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው ነሐሴ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው 11 ቀናት ለተጨማሪ ምርመራ ተሰጥቶባቸው የነበሩት አቶ ወንድሙ፣ በሰው መግደል ወንጀል የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች ያደረጉት የምርመራ መዝገብ ቀርቦ እየተጣራባቸው መሆኑ ተነግሯል፡፡ 

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ነሐሴ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ተጠርጣሪውን አቅርቧቸዋል፡፡ ቀደም ብሎ በተፈቀደለት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ 13 ሚሊዮን ብር የተንቀሳቀሰበት ሰነድ ከባንክ ተፈልጐ መሰባሰቡን፣ በፌዴራልና በክልል ባሏቸው ቤቶች ብርበራ መካሄዱን፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሲዲ መረጃ መሰብሰቡንና የሁለት ምስክሮችን ቃለ መቀበሉን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ፣ የሚቀረው ምርመራ እንዳለ በመግለጽ ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ተጨማሪ ቀናት የጠየቀበትን ምክንያት ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ከአዲስ አበባና ከፌዴራል ፖሊስ የነፍስ ግድያ ወንጀል ምርመራ መዝገብ መጥቶለት፣ ምርመራው በደንብ መካሄዱን መገምገም ከፌዴራልና ከክልል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃዎች መሰብሰብ፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ የተለያዩ ሰነዶችን መሰብሰብ፣ ከኦሮሚያ ገቢዎች የኢንስፔክሽን ሪፖርት መሰብሰብና ሌሎች ተጠርጣሪዎችን መያዝ እንደሚቀረው አስረድቷል፡፡ 

በተጠርጣሪው ዘጠኝ ቤቶችና በአራት ከተሞች የተደረገውን የብርበራ መረጃ መተንተን፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሰባሰቡትን የመሬትና የቤት ባለቤትነት ሰነድና  ከተለያዩ ባንኮች ገንዘብ የተቀባበሉባቸውን ደረሰኞች ማስረጃ መሰብሰብ እንደሚቀረው፣ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት የተጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ቀን እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

አቶ ወንድሙ በበኩላቸው ባቀረቡት ተቃውሞ፣ መርማሪው የፈለገውን ሰነድም ሆነ ሌላ ነገር ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡ መርመሪዎች እሳቸውን ካሰሩ በኋላ መኖሪያ ቤታቸው በመሄድ የአምስት ዓመት ሕፃን ልጃቸው ላይ ሽጉጥ በመደቀን ያደረጉትን ማስፈራራት አምርረው ተቃውመዋል፡፡

ከታሰሩበት ዕለት ጀምሮ ማንም ቤተሰብ እንዳልጠየቃቸው፣ ምክንያቱ ደግሞ መርማሪዎቹ እንዳስፈራሯቸው መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡ እሳቸው የክልል ተሿሚና የካቢኔ አባል መሆናቸውን በመግለጽ፣ መጠየቅ ካለባቸውም በክልል እንጂ በፌዴራል አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ኮሚሽኑ በመገናኛ ብዙኃን ስማቸውን እያጠፋ መሆኑን በመግለጽ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

የኮሚሽኑ መርማሪ በበኩላቸው አቶ ወንድሙ ያቀረቡትን አቤቱታ የሰሙት በዕለቱ ለችሎቱ ሲያስረዱ መሆኑን ገልጸው፣ እሳቸው እንዳሉት ሆኖ ከተገኘ ኮሚሽኑ በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ አሳውቀዋል፡፡ ሥልጣኑ የክልል ነው ስለመባሉ ግን፣ የግብር ጉዳይ የፌዴራሉ ጭምር መሆኑን በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ የቫትንና የጉምሩክ ቀረጥን በሚመለከት የማየት ሥልጣን የፌዴራል ፍርድ ቤቶች መሆኑንም አክለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ አቶ ወንድሙ ያቀረቡትን አቤቱታ በሚመለከት በሰጠው ትዕዛዝ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መከበር እንዳለበት አሳስቦ በቤተሰብ፣ በዘመዶቻቸው፣ በሃይማኖት አባትና በሕግ አማካሪያቸው የመጐብኘት መብት እንዳላቸው በመግለጽ ኮሚሽኑ ተግባራዊ እንዲያደርግ አዟል፡፡ 

በሕፃን ልጃቸው ላይ ተደረገ የተባለው እውነት ከሆነና ማስረጃ ከቀረበ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቆ፣ የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን በሕግና በአግባቡ መመርመር እንዳለበት፣ ከዚያ ውጪ የሆነ በግዳጅና በኃይል የሚገኝ መረጃን ውድቅ እንደሚያደርግ በማሳሰብ፣ መርማሪ ቡድኑ ለጠየቀው ተጨማሪ ምርመራ አሥር ቀናትን ፈቅዷል፡፡ 

 

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ከአክሰስ ቦርድ ሰብሳቢነታቸው ተነሱ

‹‹መንግሥት አክሲዮን ማኅበሩን ለማፍረስ በሚደረግ እንቅስቃሴ ላይ ጥብቅ ዕርምጃ ይወስዳል›› አቶ ኑረዲን መሐመድ፣ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ

በድንገት ከአገር ወጥተው በተባበሩት ኤምሬት ዱባይ ከተማ ለሁለት ዓመታት ከቆዩ በኋላ ከመንግሥት ጋር ባደረጉት ድርድር ከለላ ተሰጥቷቸው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣

አገር ውስጥ ከተመለሱ በኋላ ቀድሞ ወደነበሩበት የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙ ቢሆንም፣ ‹‹ምንም ዓይነት ሥራ አልሠሩም›› ተብለው ከሰብሳቢነታቸው ተነሱ፡፡

የቦርድ አባላት ነሐሴ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ አቶ ኤርሚያስን ከቦርድ ሰብሳቢነታቸው ያነሷቸው፣ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ከተሾሙ ከመጋቢት 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በእሳቸው ሰብሳቢነት በርካታ ስብሰባዎችን ያደረጉ ቢሆንም፣ በሥነ ሥርዓት ጉዳዮችና አሉባልታ ወሬዎች ላይ ከመነታረክ ያለፈ ምንም ዓይነት ቁምነገር አለመሥራታቸውን የቦርዱ አስቸኳይ ስብሰባ ቃለ ጉባዔ ያስረዳል፡፡ አቶ ኤርሚያስ በሕግና በሥርዓት ሊሠሩ ባለመቻላቸው፣ ቦርዱ የኩባንያውን ችግር ለመፍታት በመንግሥት ለተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ በማሳወቁ ኮሚቴው መመርያ ሰጥቶ እንደነበርም በቃለ ጉባዔው ተገልጿል፡፡ ኮሚቴው በሰጠው መመርያ ቦርዱ ስለ አክሰስ ሪል ስቴት አካሄድ ፍኖተ ካርታ እንዲያቀርብ አዞ የነበረ ቢሆንም፣ ጥቃቅንና የትም የማያደርሱ ድርጅቱን ሥጋት ላይ የሚጥሉ ነገሮች ከመነሳታቸው ባለፈ ፋይዳ ያለው ነገር ሊሠሩ ባለመቻላቸው ከቦርድ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ በሙሉ ድምፅ መወሰኑን የቦርዱ ቃለ ጉባዔ አስታውቋል፡፡ አክሰስ ሪል ስቴት በአቶ ኤርሚያስ ሲመራ ወደ ድርጅቱ ካዝና መግባት ያለባቸውን ተሰብሳቢ ሒሳቦች ከማንሳት ይልቅ ዕዳ መቀበልን እንዲያስቀድም መደረጉን ቦርዱ ገልጿል፡፡ ድርጅቱን ከውድቀት ሊያነሳ የሚችል ብዙ ተሰብሳቢ በሕጋዊ ሰነድ የተያዘ ገንዘብ ቢኖርም፣ በእሱ ጉዳይ ላይ ውይይት አለመደረጉንም ጠቁሟል፡ 

አቶ ኤርሚያስ ወደ አገር ቤት የተመለሱበት ዓላማ እንዲያሳካ በሚል ቦርዱ ብዙ ነገሮችን እያየ እንዳላየ ማለፉን ጠቁሞ፣ አሁን ግን ሥጋው መሬት ላይ እያለ የደረቀ ቋንጣ እያወረደ መሆኑን በመገንዘብ ዕርምጃውን ለመውሰድ መገደዱን ገልጿል፡፡ አቶ ኤርሚያስ ያለ ቦርዱ ተሳትፎ በራሳቸው ለተለያዩ ድርጅቶች ደብዳቤ መጻፋቸው፣ ቅጥር ማካሄዳቸውና ‹ፒንግል ሪል ስቴት› ከተባለ የቻይና ኩባንያ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ቦርዱ ጠቁሞ፣ ነገር ግን ኩባንያው በሕይወት ይኑር አይኑር የሚታወቅ ነገር እንደሌለ አስታውቋል፡፡ በአጠቃላይ አቶ ኤርሚያስ ከነሐሴ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ከቦርድ ሰብሳቢነታቸው ተነስተው ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት ወ/ሮ መብራት ወልደ ትንሳዔ በሰብሳቢነት እንዲመሩ በመስማማት መወሰኑን አስታውቋል፡፡ 

አቶ ኤርሚያስ መሥራችና የቦርድ ሊቀመንበር ከነበሩበት አክሰስ ሪል ስቴት፣ በአገር ውስጥና በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ከ2,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች የቤት ግዢ የፈጸሙ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ቤትም ሆነ ገንዘባቸውን አለማግኘታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ አቶ ኤርሚያስ በድንገት ከአገር ሲወጡ ቤት ገዢዎቹ የተለያዩ ተቃውሞዎችን ሲያቀርቡ ከርመው፣ በመጨረሻ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ከአቶ ኤርሚያስ ጋር በመደራደር ለተለያዩ ግለሰቦች ቆርጠውት በነበረ ደረቅ ቼክ ምክንያት እንደማይታሰሩ ዋስትና ተሰጥቷቸው፣ በየካቲት ወር 2007 ዓ.ም. ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል፡፡

አቶ ኤርሚያስ በወቅቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ከየካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ እንደሚጀምሩና ማንኛውም ቤት ገዢ የፈለገውን ማለትም ቤቱን ወይም ገንዘቡን ከነወለዱ እንደሚመልሱ ቃል መግባታቸው በወቅቱ ተዘግቧል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ቤት ገዢዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አቶ ኤርሚያስ እንኳን ገንዘብ ሊመልሱና ስለቤት ሊያናግሯቸው ቀርቶ በአካል አይተዋቸው እንደማያውቁ እየገለጹ ነው፡፡ መንግሥት የሰጣቸውን ተስፋም ማየት ባለመቻላቸው ተስፋ እየቆረጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ተብሎ ላለፉት ስድስት ወራት ምንም ነገር አለማየታቸውን አስረድተዋል፡፡ 

የአቶ ኤርሚያስ ፍላጐት በተለያዩ መንገዶች ነገሮችን በማጓተት ድርጅቱ እንዲፈርስና ከተጠያቂነት ለመዳን ስለሆነ፣ ቃል የገባው መንግሥት በነገሩ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ 

በቦርዱ ጽሕፈት ቤት ለሚሠሩ 13 ሠራተኞች የሰኔና የሐምሌ ወር ደመወዝ መክፈል ሳይቻል ቀርቶ ቴክኒክ ኮሚቴውና ከቤት ገዢዎች ለተለያዩ ወጪዎች ከሰበሰበው ገንዘብ አክሲዮን ማኅበሩ ተበድሮ መክፈሉን አስረድተዋል፡፡ ይኼ የሚያሳየው ድርጅቱ ችግር ውስጥ መሆኑን እንደሆነ አስረድተው መንግሥት አስቸኳይ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ 

የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ የንግድ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ኑረዲን መሐመድ ግን በቤት ገዢዎቹም ሆነ በቦርዱ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ሰው የፈለገውን ቢያወራ ኮሚቴው መሥራት የሚችለውን እየሠራ እንደሆነና በሥራውም ውጤታማ መሆኑን ነው፡፡ 

ከየአቅጣጫው እየጮሁ የሚገኙት ከቤት ገዢዎቹ አሥር በመቶ የማይሆኑትና አቶ ኤርሚያስ ሲነኩ የሚነኩ ሰዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ኤርሚያስ የሕግ ከለላ የተሰጣቸው ሥራዎች ተስተካክለው እንዲሄዱ እንጂ ከሕግ ተጠያቂነት ለማዳን አለመሆኑን የገለጹት አቶ ኑረዲን፣ በአቶ ኤርሚያስ በኩል ስላሉ ሰዎች መረጃ መጠየቅ ሲጀመር የእሳቱ ወላፈን የሚነካቸው ሰዎች ብዙ ነገር ለማድረግ እየጣሩና እየተወራጩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ከአንድ ወይም ሁለት ሳምንት በኋላ በተለይ አምቼ አካባቢ ያለው ፕሮጀክት ይፋ እንደሚደረግና ሥራ እንደሚጀመር የጠቆሙት ሰብሳቢው ቦርዱ፣ የቦርዱ አባላትና አስፈጻሚው የየራሳቸው አጀንዳ ስላላቸው ምንም ነገር እንዳልተሠራ የሚያስወሩት ወሬ እንደሚቆም ተናግረዋል፡፡ ሁሉም የሚሮጠው የራሱን መብት ለማስከበር መሆኑን ጠቁመው መንግሥት ግን ተረጋግቶና ሁሉንም ነገር በአግባቡ በመሥራት እያንዳንዷን ነገር ማስተማሪያ ማድረግ እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡ 

አክሲዮን ማኅበሩ ከፈረሰ ተጠያቂነት ስለማይኖር በንግድ ሚኒስቴር የአክሲዮን ማኅበራት ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት የመጀመሪያ የቤት ሥራው ጥንቃቄ አድርጐ ጅምሩን ዳር ማድረስ መሆኑንም አቶ ኑረዲን አስረድተዋል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩን ለማፍረስ የሚደረግ እንቅስቃሴ ከታየ መንግሥት ጥብቅ ዕርምጃ እንደሚወስድም አስረድተዋል፡፡ የሆነ ያልሆነ መረጃ ወጥቶ ቤት ገዢውን ተስፋ የሚያስቆርጥ ወሬ እንደሚሰማ የገለጹት አቶ ኑረዲን፣ መንግሥት አቶ ኤርሚያስ ሳይኖሩ ኃላፊነት መውሰዱን ቤት ገዢው መዘንጋት እንደሌለበት አስታውሰዋል፡፡

አቶ ኤርሚያስ ወደ አገር ቤት እንዲመጡ የተደረገው ሥራ እንዲሠሩ፣ ሚስጥሮችን እንዲያወጡና ሦስተኛ ወገኖችን እንዲታገሉ መሆኑን የገለጹት አቶ ኑረዲን፣ ቦርዱ ራሱ ሾሞ ራሱ እንዳወረዳቸው መግለጹ አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሌላ መሾምም ሆነ መነሳት ካለባቸው በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት የፀደቀ ሰነድ መኖር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ይኼ ባልሆነበት ሁኔታ ስለሚካሄደው ነገር የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ አሁን በቦርዱም ሆነ በጥቂት ቤት ገዢዎች እየተደረገ ያለው ነገር ሥራውን የሚያስትና የሚያደናቅፍ አለመሆኑን አቶ ኑረዲን ተናግረዋል፡፡     

ቦርዱ ባሳለፈው ውሳኔና ቤት ገዥዎች እያቀረቡት ስላለው ተቃውሞ ምላሽ እንዲሰጡ አቶ ኤርሚያስን ሪፖርተር ቢሮቸአው ድረስ በመሄድና በስልክ ጭምር ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡    

 

በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በሽብርተኝነት ክስ ተመሥርቶባቸው በእስር ላይ የቆዩት የቀድሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)፣ የሰማያዊና የአረና ፓርቲ አመራሮችና ሁለት ተከሳሾች በነፃ እንዲሰናበቱ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ወሰነ፡፡ የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ …

የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ሀብታሙ አያሌውና ዳንኤል ሺበሺ፣ የአረና ፓርቲ አመራር አብርሃ ደስታ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የሺዋስ አሰፋና ሌሎች 2 ተጠርጣሪዎች በነፃ እንዲሰናበቱ ተወሰነ Read more »

– የፖለቲካ እስረኞች ምሕረት እንዲደረግላቸው ጠይቋል

– የዳያስፖራ ልማት ባንክ ይቋቋም ተብሏል

መንግሥት የዳያስፖራ ፖሊሲን ይፋ ካደረገ ከሁለት ዓመት በኋላ በአገር አቀፍ ደረጃ በያመቱ እንዲካሄድ በወሰነው መሠረት፣ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰናዳው የዳያስፖራ ቀን በርካታ ቅሬታዎች ከዳያስፖራው ለመንግሥት ኃላፊዎች ቀረቡ፡፡ 

በተለያዩ አገሮች እንደሚኖሩ ከሚገመቱት ሁለት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል አምስት ሺሕ ያህሉ ለአምስት ቀናት በሚሊኒየም አዳራሽ ሲካሄድ ቆይቶ እሑድ ነሐሴ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚጠናቀቀው የዳያስፖራ ቀን በዓል ላይ መሳተፋቸውን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ መሠረት ነሐሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በተደረገ ውይይት ወቅት የዳያስፖራ አባላቱ በመንግሥት በኩል የሚገጥሙዋቸውን ችግሮች በመዘርዘር ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ 

መንግሥት እንዲያስተካክል ከተጠየቀባቸው ጉዳዮች መካከል የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በቢሮክራሲ ውጣ ውረድና በመረጃ እጦት የሚደርስበት እንግልት ይጠቀሳል፡፡ በተለይ ነዋሪነታቸው በእንግሊዝ የነበረውና ወደ አገር ቤት ከመጡ ሁለት ዓመታት ያስቆጠሩት አቶ ሀብቴ ፈረደ፣ ከቱርክ በወኪልነት በባቡር መስመር ግንባታ ላይ ለማሳተፍ ያመጡት ኩባንያ በቢሮክራሲ ሳቢያ ፋይናንሱን ወደ ኬንያና ወደ ኡጋንዳ ለመውሰድ መገደዱን ተናግረዋል፡፡ ሜጀር ግሩፕ የተባለውን የቱርክ ኩባንያ አፈላልገው ማምጣታቸውን የገለጹት አቶ ሀብቴ፣ ኩባንያው 375 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውንና ከአዋሽ-ወልዲያ እስከ ሃራ ገበያ የሚዘረጋውን የባቡር መስመር ለመገንባት ጨረታውን አሸንፎ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ 

ይህ ኩባንያ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን 1.7 ቢሊዮን ዶላር ለማምጣት የአንድ ዓመት ጊዜ ተሰጥቶት እንደነበር አስታውሰው፣ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ምንጮች 1.9 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ችሎ እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኩባንያው ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከማምጣቱ አንድ ወር ቀደም ብሎ፣ ፕሮጀክቱ ያፒ መርከዚ ለተባለ ለሌላ የቱርክ ኩባንያ ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡ ጉዳዩን በማስመልከት የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽንን ሲጠይቁ፣ ሌሎች ያልተነኩ ፕሮጀክቶች ስላሉ እነዚያ ላይ ትሳተፋላችሁ እስከዚያ ጠብቁ የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ 

አቶ ሀብቴ እንደሚሉት፣ መንግሥት ከዚህ በኋላ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሌሎች አዳዲስ የባቡር ፕሮጀክቶችን ያስጀምራል የሚል ዕምነት ያጣው የቱርኩ ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ሊያድርግ ያመጣውን ገንዘብ ወደ ኬንያና ኡጋንዳ ወስዷል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ግን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን ተገቢውን ምላሽ ሊሰጡ ባለመቻላቸው እንደሆነ አክለዋል፡፡ ውይይት እንዲደረግ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም አንድ ጊዜ ሚኒስቴሩ ሌላ ጊዜ ኮርፖሬሽኑን ይመለከተዋል በሚል ተደጋጋሚ ምክንያት ኩባንያው ሳይሳተፍ መቅረቱን ገልጸዋል፡፡ በመድረኩ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ላይ አስረጅ ሆነው የቀረቡትና ጥያቄው በቀጥታ የተሰነዘረላቸው የገንዘብና ኢኪኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አህመድ ሺዴ ምላሽ ሳይሰጡበት አልፈውታል፡፡ 

ከአቶ ሀብቴ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በኩል የሚታደሰውን የትውልደ ኢትዮጵያዊነት መታወቂያ አገልግሎት ለማግኘት የሚገጥማቸውን ውጣ ውረድ የገለጹም ነበሩ፡፡ ከኤምባሲ ሠራተኞች ተገቢውን መረጃና ማብራሪያ የሚሰጣቸው በማጣት ብቻ በእያንዳንዱ የሰነድ ልውውጥ እስከ 40 ዶላር እየከፈሉ እንደሚቸገሩ አባላቱ አስታውቀዋል፡፡ በውጭ አገር ፍች ከፈጸሙ በኋላ የጋራ ንብረታቸውን ጠቅልለው በመምጣት ባዶ ለሚያስቀሯቸው  ባሎቻቸው ፈቃድ እየተሰጠ ችግር ላይ እንደወደቁ የተናገሩ ሴቶችም እያለቀሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምንና አቶ አህመድን መፍትሔ እንዲሰጧቸው ተማጽነዋል፡፡ 

በአሜሪካ ለ30 ዓመታት መኖራቸውን ለሪፖርተር የገለጹት ወይዘሮ ሰብለ ነቢየልዑል፣ ወደ ኢትዮጵያ ጠቅልለው በመምጣት በቆዳና በውበት ክብካቤ ላይ የሚሠራ ‹‹ዚኒያ ኤስቴቲክስ ኤንድ አንታይ ኤጂንግ ክሊኒክ›› የተባለው የጤና ተቋም ሥራ በጀመሩ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ያለማስጠንቀቂያ እንዲዘጋባቸው መደረጉን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ላቀረበላቸው ቅድመ ሁኔታ የአንድ ዓመት ጊዜ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም፣ ከስምንት ወራት በላይ ሊሰጣቸው እንደማይችል ገልጾ ክሊኒካቸው ሊዘጋ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ ክሊኒኩ ፈቃድ ያወጣው አሜሪካ በሚገኙት የወይዘሮ ሰብለ አጋር በሆኑት ዶ/ር ስም በመሆኑ እየተመላለሱ እንዲሠሩ፣ ወይም የአንድ ዓመት ጊዜ ተሰጥቷቸው በአሜሪካ የሚያስፈልጉ ጣጣዎችን ጨራርሰው እስኪመጡ ክሊኒካቸው ከሚዘጋ፣ እስከዚያው ድረስ ተመጣጣኝ በሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች ሥራውን ለማስኬድ እንዲፈቀድላቸው ያቀረቡት ጥያቄም ውድቅ እንደተደረገባቸው አስረድተዋል፡፡ እስካሁን አሥር ሚሊዮን ብር ከግል ሀብታቸው ኢንቨስት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡ 

ከክሊኒኩ ባሻገር አቬላሜድ ቢዝነስ ቴክኖሎጂ የተሰኘ የመረጃና የትንተና ተቋም ለመመሥረት ሲንቀሳቀሱ ቢቆዩም፣ በገጠማቸው ውጣ ውረድ ሳቢያ እውን ሊያደርጉት እንዳልቻሉ የሚናገሩት ወይዘሮ ሰብለ፣ እስከቻሉት ጊዜ ድረስ ሞክረው የማይቻል ከሆነ ግን ወደ ኬንያ ሊወስዱት ወይም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሊያቀኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ በአሜሪካ ሳይቀር ጥቂቶች ብቻ የሚገለገሉበት የዚህ ዓይነቱ ክሊኒክ ተፈላጊነቱ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ጥያቄ እየቀረባለቸው እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡ 

በመድረኩ ለባለሥልጣናቱ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል የፖለቲካ እስረኞችና በሃይማኖት ምክንያት የታሰሩ ካሉ እንዲፈቱ የሚለው ይገኝበታል፡፡ መንግሥት በፖለቲካና በሃይማኖት ምክንያት ያሰራቸው ሰዎች እንዳሉ እንሰማለን ያሉት ጥያቄ አቅራቢዎች፣ ምሕረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ለዳያስፖራው ጥያቄዎች መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ ከተባሉት መካከል የዳያስፖራ ልማት ባንክ እንዲቋቋም፣ ገለልተኛ የዳያስፖራ ኮሚሽን እንዲመሠረት፣ የዳያስፖራው አባላት በአክሲዮን መደራጀት የሚችሉበት ዕድል እንዲሰጥ የሚጠይቁት ይጠቀሳሉ፡፡ ዶ/ር ቴድሮስና አቶ አህመድ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችና ማስተካከያ ይደረግባቸዋል ስላሏቸው የመልካም አስተዳደር፣ የመንግሥት አገልግሎትና መሰል ጉዳዮች ላይ ማሻሸያ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ በፖለቲካና በሃይማኖት ጉዳይ ታሰሩ ስለተባሉት ሰዎች ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በቀጥታ ምላሽ ሳይሰጡበት አልፈዋል፡፡

ተደጋግመው ለባለሥልጣናቱ ከቀረቡት ችግሮች ባሻገር የዳያስፖራው መድረክ ለዶ/ር ቴድሮስ አፍቅሮት የታየበትም ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንደ አንድ ታዋቂ አርቲስት ከፍተኛ ጭብጨባና ፉጨት ተስተጋብቶላቸዋል፡፡ ፎቶ አብረዋቸው እንዲነሱ የሚጠይቋቸውና ፊርማቸውን እንዲያኖሩላቸው የሚወተውቱም በርካቶች ነበሩ፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ ሎሬት ሰዓሊና ገጣሚ ገብረክስቶስ ደስታ ከደረሰው ስደት ተኮር ግጥም በመዋስ የመግቢያ ንግግራቸውን አሰምተዋል፡፡ አንጋፋው ድምፃዊ ዓሊ ቢራን በማጀብም አንጎራጉረዋል፡፡  

በሌላ በኩል ለአሥረኛ ጊዜ በተካሄደው ዓመታዊ የዳያስፖራ ኢንቨስተሮች ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ቢዝነስ ፎረም አምባሳደር ግርማ ብሩን ጨምሮ ሁለት ኢንቨስተሮችን ሸልሟል፡፡ ሐሙስ ነሐሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ምሽቱን በሸራተን አዲስ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት አምባሳደር ግርማ ብሩ ለዳያስፖራ ኢንቨስትመንትና የንግድ መስኮች ላበረከቱት ድጋፍ ‹‹የዓመቱ የቢዝነስ ሻምፒዮና›› ተብሎ የተሰመውን አምና በአሜሪካ የተጀመረውን የተቋሙን ሽልማት ከዶ/ር ቴድሮስ እጅ ተቀብለዋል፡፡ ዶ/ር አከዘ ጣዕመና አቶ ታምራት በቀለ በጤና ዘርፍ ባደረጉት ኢንቨስትመንትና አስተዋጽኦ ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ 

ዘንድሮ የልዩ አስተዋጽኦ ተሸላሚ እንደሚሆኑ ይፋ የተደረጉት በኢትዮጵያ የሕምክና አገልግሎት ዘርፍ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ሁለት ባለሀብቶች ናቸው፡፡ ከቢዝነስ ፎረሙ በተገኘው መረጃ መሠረት በአሜሪካ ሲማሩና ሲሠሩ ቆይተው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢንቨስት በማድረግ ትልልቅ የሕክምና ተቋማትን የሚያንቀሳቅሱት አቶ ታምራት በቀለና ዶክተር አከዛ ጣዕመ ናቸው፡፡

 አቶ ታምራት የኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላብራቶሪስ እህት ኩባንያ ለሆነው ሜድፋርም ሆልዲንገስ አፍሪካ መሥራችና ዋና ሥራ አስፋጻሚ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2004 ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ የላቦራቶሪውን ተቋም በአዲስ አበባ መሥርተዋል፡፡ በአፍሪካ ዓለም አቀፍ መሥፈርቶች የጤና ክብካቤ ዕውቅና በማግኘት የሚሠራ ተቋም ለመሆን የበቃ ላቦራቶሪ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በኢትዮጵያ ብቸኛው ፈቃድ ያገኘ ተቋም በመሆን የሚንቀሳቀሰው ይህ ላቦራቶሪ፣ ባለፉት አሥራ አንድ ዓመታት 900 ሺሕ ደንበኞችን ማፍራት መቻሉም የኩባንያው ዝክረ ታሪክ ይዘረዝራል፡፡ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ታምራት ኑሯቸው በአዲስ አበባ ካደረጉ ሰንብተዋል፡፡ 

ዶ/ር አከዛ በበኩላቸው የቅዱስ ያሬድ ጠቅላላ ሆስፒታልንና በቅርቡም አሜሪካን ሜዲካል ሴንተርን ከሸሪኮቻቸው ጋር በመመሥረት፣ በሜዲካል ዳይሬክተርነት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በግል ሆስፒታሎች ማኅበር ፕሬዚዳንትነት ማገልገላቸውም ይታወቃል፡፡ የሦስት ልጆች አባት የሆኑት ዶ/ር አከዛና አጋሮቻቸው የመሠረቷቸው የሕክምና ተቋማት፣ በአዲስ አበባና በአጎራባች አካባቢዎች ለሚኖሩ አንድ መቶ ሺሕ ታካሚዎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ግማሽ ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ካፒታል የሜዲካል ቱሪዝም ይፈጥራል ያሉትን ዘመናዊ ሆስፒታል ለመገንባት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ ባለፈው ዓመት አቶ አዲስ ዓለማየሁና አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በአሜሪካ በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ተሸላሚ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ 

 

 

 

ፖሊስ ዋና ተጠርጣሪ ያላቸውን አራት ሰዎች ከሷል

በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ሥር በምትገኘው የቦሎሶ ሶሬ ወረዳ ከከተማ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ፣ ሕገወጥ ግንባታዎችን ለማፍረስ የአረካ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በመሞከሩ ነዋሪዎች ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸው ታወቀ፡፡ 

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የትውልድ ቦታ በሆነው የቦሎሶ ሶሬ ወረዳ ዋና ከተማ አረካ ዙሪያ የሚገኙ ስድስት ቀበሌዎችን በከተማው ሥር ለማካለል፣ በሕገወጥ መንገድ ተገንብተዋል በተባሉ ከ940 በላይ ቤቶች ላይ ማዘጋጃ ቤት እንዲፈርሱ ሐሙስ ነሐሴ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀለም መቀባት ጀምሮ ነበር፡፡ 

ነገር ግን ባለይዞታዎች የተገነቡትን ቤቶች በቀጥታ በከተማ ማካለሉ ውስጥ ማስገባት እየተቻለ ሊፈርስብን አይገባም በማለት በመቃወማቸው፣ በተጠቀሰው ዕለት ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ግጭት መነሳቱን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

ፖሊስ የተወሰኑ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ቢያውልም፣ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ በድጋሚ ከረር ያለ ግጭት ተከስቷል፡፡ 

በተለይም በሁለተኛው ግጭት ባለይዞታዎቹ ድንጋይ መወርወር በመጀመራቸው፣ ፖሊስም በድብደባ አፀፋ መመለሱ ተገልጿል፡፡ ከ20 በላይ ሲቪሎችና አሥር የሚሆኑ የአፍራሽ ግብረ ኃይል አባላት መጎዳታቸው ታውቋል፡፡

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢዮብ ዋቴ የተነሳውን ግጭትም ሆነ የደረሱ ጉዳቶችን አረጋግጠው፣ የብጥብጡ ዋና ተጠያቂዎች በሕገወጥ መንገድ ቤት የገነቡ ሰዎችና የእነሱ ተባባሪ ደላሎች ናቸው በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ግጭት ለማነሳሳት ዋነኛ የተባሉ አራት ሰዎች ክስ ተመሥርቶባቸው የጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀባቸውም አቶ ኢዮብ ገልጸዋል፡፡

የቤቶቹን ሕገወጥነት አስመልክቶ ዋና አስተዳዳሪው፣ ‹‹ሕገወጦቹ ከደላሎች ጋር በመሆን ስድስቱ ቀበሌዎች ወደ ከተማ እንደሚካለሉ እያወቁ በሕገወጥ መንገድ ቤቶቹን ገንብተዋል፤›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ቤቶቹን መገንባት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ ግለሰቦች ምንም ዓይነት ግንባታ እንዳያደርጉ የወረዳው አስተዳደር ማስጠንቀቁን አቶ ኢዮብ አስታውሰዋል፡፡ 

እሳቸው የታሰሩት ሰዎች አራት ብቻ ናቸው ቢሉም፣ ምንጮች ግን የታሳሪዎች ቁጥር እስከ 40 እንደሚደርስ ይናገራሉ፡፡ 

ነገር ግን አቶ ኢዮብ ብዛት ያላቸው ሰዎች መቁሰላቸውን አልሸሸጉም፡፡ በፖሊስ በኩልም ሁለት ፖሊሶች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸውም አክለው ገልጸዋል፡፡ 

የከተማ ማስፋፋት ፕሮግራሙን አስመልክተው በሶዶና በቦዲቲ ከተሞችም ተመሳሳይ የማካለል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን፣ ችግሩ ግን የተፈጠረው አረካ ላይ ብቻ እንደሆነ አቶ ኢዮብ አስረድተዋል፡፡ 

በዋነኛነት ግጭቱ በተፈጠረበት የአረካ ማስፋፊያ ፕሮግራም በከተማው ዙሪያ የሚገኙ ስድስት የቀበሌ ገበሬ ማኅበሮችን ለማካለል ታቅዶለታል፡፡ ነገር ግን ግጭቱ የተቀሰቀሰው ዱቦ፣ አቹራ፣ ዶላና ኡቶ በተባሉት አራቱ ቀበሌዎች መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

 

በከባድ ሙስና የተጠረጠሩ የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣን በቁጥጥር ሥር ዋሉ

በመቶ ሚሊዮን ብሮች ተጠርጥረዋል

በከባድ ሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ላለፉት ሁለት ወራት ሲፈለጉ የቆዩት የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ቢራቱ፣ ነሐሴ 3 ቀን 2007 ዓ.ም.  በአዳማ ከተማ በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡

አቶ ወንድሙ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በፌዴራልና በኦሮሚያ ክልል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች ጥምረት ነው፡፡ በሁለቱ ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች የተዋቀረው ግብረ ኃይል ተጠርጣሪውን ግለሰብ ነሐሴ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ምድብ ችሎት በማቅረብ፣ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ የ11 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

አቶ ወንድሙ የተጠረጠሩት የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ በነበሩበት ወቅትና ከዚያ በኋላም የኦሮሚያ ክልል ብድርና ቁጠባ ተቋም ምክትል ኃላፊ ሆነው በሠሩባቸው ጊዜያት፣ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የመንግሥት ገንዘብ በመመዝበር  የሙስና ወንጀል ነው፡፡

የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥነ ምግባር፣ ትምህርትና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አሰፋ፣ አቶ ወንድሙ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና በቁጥጥር ሥር ሊወሉ የቻሉት መንግሥት ማግኘት የነበረበትን በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አሳጥተዋል በሚል ምክንያት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ከክልሉና ከፌዴራል ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ አቶ ወንድሙ ምንጩ ያልታወቀ ከፍተኛ ሀብት፣ ለመንግሥት ገቢ መሆን የነበረበት ግብርና ታክስ፣ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ግዙፍ ኩባንያዎች የሰበሰቡትን ቫት ሆን ብለው ለመንግሥት ገቢ እንዳይሆን በማድረግና ጉቦ በመቀበል ወንጀል ተጠርጥረው ነው በቁጥጥር ሥር የዋሉት፡፡ ግለሰቡ የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሚያ ክልል ማግኘት ያለባቸውን ገቢ አሳጥተዋል ተብለው ስለተጠረጠሩ ሁለቱ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በትብብር መሥራት መጀመራቸው ታውቋል፡፡ ነገር ግን ተጠርጣሪውን ግለሰብ ለፍርድ ለማቅረብ በሚሞከርበት ወቅት ተጠርጣሪው በመሰወራቸው ከሁለት ወራት ፍለጋ በኋላ በአዳማ ከተማ መያዛቸው ታውቋል፡፡

አቶ ወንድሙ በራሳቸውና በቤተሰባቸው ስም ከፍተኛ ንብረት ማካበታቸው ምርመራ እንዲደረግባቸው መንስዔ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ለሁለቱም የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ጥቆማዎች ደርሰዋል ተብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለይ በሻሸመኔና በምሥራቅ ሐረርጌ ቦርዶዴ አካባቢ የሚገኙ የጫት ኬላዎች ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን መንግሥት ማግኘት ያለበትን ገቢ ለግል ጥቅም ሲያውሉ ቆይተዋል የሚል ጥርጣሬ መኖሩን፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽኖቹ መረጃ ያመለክታል፡፡

አቶ ወንድሙ የሥራ ጊዜውን ባጠናቀቀው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ) አባል ነበሩ፡፡ ኦሕዴድ አቶ ወንድሙን በ2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ ዕጩ አድርጎ እንዳላቀረባቸው ታውቋል፡፡ በዚህ መሠረት አቶ ወንድሙ ያለመከሰስ መብት የሌላቸው በመሆኑ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር እንዳዋሏቸው ተገልጿል፡፡

አቶ ወንድሙ የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ሆነው ለአምስት ዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ምክትል ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ ቆይተው፣ ከ30 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ሕገወጥ ግዥ ተጠርጥረው ከወራት በፊት ከምክትል ኃላፊነታቸው መነሳታቸው ታውቋል፡፡

 

በዘንድሮው ክረምት የተፈጠረው የዝናብ እጥረት አሉታዊ ተፅዕኖዎችን እያሳደረ ነው

ለከብቶች መሞትና ለሰብል ውድመት ምክንያት ሆኗል

-ችግሩ አሳሳቢ በመሆኑ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሟል

በአገሪቱ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች በዘንድሮው የክረምት ወቅት የተከሰተው የዝናብ እጥረት አሉታዊ ተፅዕኖዎችን እያሳደረ መምጣቱን፣ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ይፋ አደረገ፡፡

ዘግይቶ የመጣው የነሐሴ ዝናብ ሥርጭት መሻሻል እንደሚታይበት ገልጿል፡፡

ችግሩ ስለመከሰቱ ለመንግሥት ካሳወቀ ከሁለት ወራት በኋላ በይፋ በሰጠው መግለጫ የዝናብ እጥረቱ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች መታየቱን ገልጾ፣ ይህም በእርሻ ሥራ አጀማመር፣ የዘር ጊዜን በማስተጓጎልና የሰብል ውኃ ፍላጎትን ባለማሟላትና በመሳሰሉት ተፅዕኖዎቸ እንዲጠናከሩ አድርጓል በማለት አስታውቋል፡፡ 

ነሐሴ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. በኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎች በተሰጠው በዚሁ መግለጫ የዝናብ እጥረቱ ተፅዕኖ በሰብል ልማት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በተለይ በክረምት ወቅት በአገሪቱ ግድቦች መግባት የነበረበት ውኃ እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑን አስታውቋል፡፡ የዝናብ እጥረት በየወንዞቹ የሚፈሰው ውኃ ዝቅ እንዲል፣ እንዲሁም በሜዳማና በረግረጋማ መሬት ላይ መተኛት የነበረበት የውኃ መጠን መቀነስ ጎልተው ከታዩ ክስተቶች ውስጥ እንደሚካተቱ ተጠቅሷል፡፡ 

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደገለጹት፣ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የታየው የዝናብ እጥረት በተለይ በሐምሌ ወር ጎልቶ ታይቷል፡፡ በሰኔ ወር የነበረው የዝናብ አጀማመር የተሻለ መጠንና ሥርጭት ቢኖረውም፣ በሐምሌ ግን የተዳከመ ገጽታ ስለነበረው በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ዝናብ እጥረት መከሰቱን፣ ይህም አሉታዊ ተፅዕኖዎች እንዳሳደረ ገልጸዋል፡፡

የዝናብ እጥረቱ ስላሳደረው ተፅዕኖ የኤጀንሲው ኃላፊዎች ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጡም፣ የዝናብ እጥረቱና የታየው ድርቅ ለሰብል መጥፋትና ለእንስሳት ሞት ምክንያት መሆኑን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በ31 ወረዳዎች ላይ ድርቅ ተከስቷል፡፡

በአንዳንድ ወረዳዎች እስከ 240 የሚደርሱ ፍየሎችና ግመሎች መሞታቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እንደደረሰም የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ባለሙያ አቶ ኡስማን ኢድሪስ ሙሳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም አደጋውን ለመከላከል የክልሉ መንግሥት፣ በፌዴራል መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጥምረት የፈጠሩት ኮሚቴ እየተንቀሳቀስ ነው ተብሏል፡፡ የተወሰኑ አርብቶ አደሮችም ከብቶቻቸውን የተሻለ አየር ንብረት ወዳለበት አካባቢዎች እየወሰዱ ነው፡፡ 

የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በአፋር አካባቢ ስለተከሰተው ችግር ሲያብራሩ፣ ‹‹በአፋር ክልል ዝናብ ማግኘት በነበረበት ወቅት አላገኘም፡፡ ይህ ትክክል ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አሁን ግን በሥርጭትም በሽፋንም የተሻለ ዝናብ በመኖሩ እዚያ አካባቢ ባሉ ግድቦች ውኃ ለመያዝ ያስችላል፡፡ ይህም ከዚህ በኋላ ሊመጣ የሚችለውን ተፅዕኖ መቀነስ የሚያስችል ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ 

በሌላ በኩል ከዝናብ እጥረት ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ችግር ተጎጂ ከሆኑ አካባቢዎች መካከል የአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ አንዱ መሆኑን የሪፖርተር የመስክ ቅኝት አመላክቷል፡፡ ከሌላው ጊዜ በተለየ የተፈጠረው የዝናብ እጥረት በወረዳው ውስጥ ያሉትን ቀበሌዎች በሙሉ ያዳረሰ መሆኑን የወረዳው ግብርና ቢሮ ገልጿል፡፡ የዝናብ እጥረቱ በግንቦት ወር ከ2,370 ሔክታር በላይ በቆሎ የተዘራበት ማሳ እንዲጠፋ ምክንያት እስከመሆን መድረሱንም፣ የወረዳው የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጀማል ኑራ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዝናብ እጥረቱ ምክንያት ለከብቶች መኖ እጥረት በመፈጠሩ አብዛኛዎቹ አርሶ አደሮች ለመጠባበቂያ ያስቀመጡትን መኖ እንዲጠቀሙ አስገድዷቸዋል፡፡ አንዳንዶችም በዚህ ወቅት ለከብቶቻቸው ይሆን የነበረው ሣርና የበቆሎ አገዳ በዝናብ እጥረቱ ምክንያት ባለማግኘታቸው፣ መኖ ወደ መግዛት እንዳስገባቸው ሪፖርተር ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ገልጸዋል፡፡

የዘንድሮው የክረምት ወቅት ዓለም አቀፍ ክስተት የሆነው የኤልኒኖ ተፅዕኖ ሥር በመውደቁ የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የዝናብ እጥረት ማጋጠሙን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ እጥረቱም በቦታ በጊዜና በመጠን የተለያየ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁን ግን የተስተካከለ ዝናብ እየተገኘ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ተመሳሳይና አንድ ዓይነት እጥረት እንዳላጋጠመ፣ በአንፃራዊነት የተሻለ ዝናብ ያገኙ አካባቢዎች እንዳሉ ሁሉ በዚያው ልክ እጥረት ያጋጠማቸው እንዳሉ ለመገንዘብ እንደተቻለ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ የኤጀንሲው የሚቲዎሮሎጂና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ድሪባ ቆርቻ፣ በዚህ ወቅት የተፈጠረው ችግር ከኤሊኒኖ ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት የተሻለ ዝናብ ቢጠበቅም በአሁኑ ጊዜ እየተጠናከረ ከመጣው የኤልኒኖ ክስተት ጋር ተያይዞ በቀሪዎቹ ነሐሴና መስከረም በመደበኛ ሁኔታ የሚኖረው የዝናብ መጠንና ሥርጭት የተዛባና ያልተስተካከለ እንደሚሆንም፣ ኤጀንሲው ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡ 

የዝናብ እጥረቱ ተከስቶባቸዋል ብለው በምሳሌት ከጠቀሷቸው አካባቢዎች መካከል በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአፋር፣ በሱማሌ አንዳንድ ቦታዎች እጥረቱ በቀጥታ ከኤልኒኖ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ችግር እንደሆነም ታውቋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ተመሳሳይ የአየር ንብረት ያላቸውና በምድር ወገብ አካባቢ ባሉ አገሮችም የታየ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ 

 በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች የተከሰተውን የዝናብ እጥረትና ሥጋት የታወቀው ቀደም ብሎ ቢሆንም፣ መረጃው ዘግይቶ መነገሩ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በተለይ ብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አሁን የሰጠው መረጃ የዘገየ ነው የሚል ጥያቄ አስነስቶበታል፡፡ የኤጀንሲው ኃላፊዎች ግን መረጃው ዘግይቷል የሚለውን ትችት አልተቀበሉትም፡፡ ኤጀንሲው የክረምቱን ወቅት የተመለከተ ዝርዝር መረጃውን በግንቦት ወር መስጠቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከመረጃው በኋላም ላለፉት ሁለት ወራት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሲሠሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡ 

ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ ዱላ ሻንቆ ኤጀንሲው እያንዳንዱን መረጃ በተለያዩ መንገዶች ሲያቀርብ ስለነበር መረጃውን ለመስጠት መዘግየት ታይቷል የሚለውን ሐሳብ ሳይቀበሉት ቀርተዋል፡፡ ችግሩ መኖሩን በግንቦት ወር ማስታወቃቸውንና የየዕለቱን የአየር ፀባይ መረጃ በመመዝገብና በቀጣይ ሊኖር የሚችለውን ሁሉ በማጠናቀር፣ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ጀምሮ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ማሠራጨቱንም ገልጸዋል፡፡

በዚሁ በመረጃ መሠረት ያለውን ሥጋት እንዴት ለመፍታት እንደሚቻልና መንግሥት ዝግጅት እያደረገ መቆየቱን፣ በብሔራዊ ደረጃ የአደጋ መከላከል ኮሚቴም መቋቋሙ ተገልጿል፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራው ይህ ብሔራዊ የአደጋ መከላከል ኮሚቴ ውስጥ በዋናነት የተካተቱትም ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ፣ ግብርና ሚኒስቴር፣ የአደጋ መከላከል ዝግጁነትና የምግብ ዋስትና ቢሮ፣ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ናቸው፡፡ ይህ ኮሚቴ ሰፊ ርቀት መጓዙን አቶ ፈጠነ ገልጸው፣ ‹‹ጉዳዩ በደንብ ታስቦበት እየተሠራበት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር ኤጀንሲው በየክልሉ ያሉት የቅርንጫፍ የሥራ ኃላፊዎቹ ከየክልሉ ፕሬዚዳንቶች ጋር በቀጥታ በመገናኘት መረጃ እንዲሰጡ ጭምር እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡ በይፋ ጋዜጣዊ መግለጫ አልተሰጠበትም እንጂ ሊኖር የሚችለውን ችግር በቅድሚያ በማሳወቅ በጋራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሊከሰት ይችላል ተብሎ ከተተነበየው መረጃ አንፃር መንግሥት ሰፊ ዝግጅት እንዲያደርግ ኤጀንሲው መምከሩን፣ የግብርና ዘርፎች በየደረጃው በመዋቅራቸው መሠረት አርሶ አደሮች ዘንድ እንዲደርሱም ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ 

የኤጀንሲው ዋና ተግባር ትንበያና የምክር አገልግሎት መስጠት መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያዎችን ጉዳዩ የሚመለከታቸው የውሳኔ ሰጪ አካላት እንዲጠቀሙበት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

አሁን የታየው የአየር ለውጥ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ ቀላል ያለመሆኑን ለመግለጽ፣ ‹‹ተፅዕኖው በአንድ አርብቶ አደርና በአርሶ አደር ላይ የሚገለጽ ሳይሆን በጤና ረገድም የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ያሳድራል፤›› ብለዋል፡፡ 

የሚታየው ሙቀት እየተጠናከረ በሚሄድበት ጊዜ በአየር ለውጡ ምክንያት የሚወለዱ በሽታዎችን ጭምር የሚያስፋፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ከጤና ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ኤጀንሲው እየሠራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ 

የዝናብ እጥረቱም ሆነ የአየር ለውጡ ሌሎች ተፅዕኖዎችን ሊያሳድሩ እንደሚችሉ የኤጀንሲው ኃላፊዎች አስረድተዋል፡፡ የአየር መዛባቱ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከባድና ቅፅበታዊ ዝናብ፣ ጎርፍና የወንዞች ሙላትን አስከትሏል ተብሏል፡፡ 

በቀጣይ ወራትም ተመሳሳይ ችግር ሊኖር የሚችልበት ዕድል አንደሚኖር ያመለከቱት ዶ/ር ድሪባ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በአጭር ቅጽበት ከ50 እስከ 80 ሚሊ ሊትር ዝናብ መመዝገቡን አስታውሰዋል፡፡ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት በተለይ በነሐሴ ወር የተሻለ ዝናብ ሊኖር ይችላል የሚል ግምት ያላቸው ዶ/ር ድሪባ፣ በበጋ በአንድ በኩል ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው፣ በሌላ በኩል ግን ዝናቡ አዎንታዊ ገጽታ እንደሚኖረውም ያስረዳሉ፡፡ አሁን በተተነበየው መረጃ መሠረት በመጪው በጋ ዝናቡ የሚኖረው ደግሞ የጎርፍና የወንዞች ሙላትን ሊያስከትል እንደሚችልም ተገልጿል፡፡ 

ከኤልኒኖ ወይም ከሌሎች ክስተቶች ጋር ተያይዞ በአገሪቱ ሊከሰቱ የሚችሉትን ከመደበኛ ወጣ ያሉ የአየር ሁኔታና ፀባይ፣ ክስተቶችንና ተፅዕኖዎችን የዕለት ተዕለት ክትትል በማድረግ መረጃዎችን ለተጠቃሚዎች እንደሚሰጥም ኤጀንሲው አስታውቅል፡፡ አሁን ያለው ችግር ተፅዕኖ ያለው መሆኑ ባይካድም፣ ሰሞኑን የታየው ዝናብ ፍራቻ ያሳደረውን ድርቅ እንዲቀንስ ያደርጋል የሚል ተስፋ እንዳለ ኃላፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡ 

ሰሞኑን የታየው ዝናብ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም አሁንም እስከታች ድረስ ሊከናወኑ ይገባቸዋል የተባሉ ጥንቃቄዎችም ተጠቁመዋል፡፡ በተለይ የሚገኘውን ውኃ በተቻለ መጠን መያዝ አስፈላጊ ነው ተብሏል፡፡ ኤጀንሲው ሊፈጠር የሚችለውን ሥጋት ሲገልጽ፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ሰብሎቻቸውና እንስሳቶቻቸው እንዳይወድሙና እንዳይሞቱ ለምን አልተደረገም ለሚለው ጥያቄ፣ በኤጀንሲው ኃላፊዎች ምላሽ ሳይሰጥበት ታልፏል፡፡ 

 

ሰባት ደላሎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ በአንዱ ላይ ክስ ተመሠረተ

ወደ ተለያዩ ዓረብ አገሮች የሚሄዱ ኢትዮጵያውያንን ሞት፣ አካል መጉደልና እንግልትን እየደረሰባቸው በመሆኑ መንግሥት እንዳይሄዱ ዕግድ የጣለ ቢሆንም፣ በተለይ ቀደም ብሎ ስደት በማይታወቅባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ቁጥራቸው

ከፍተኛ የሆኑ ወጣቶች በሕገወጥ መንገድ እየተሰደዱ መሆኑን፣ መንግሥት ሐምሌ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. አስታወቀ፡፡

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ብሔራዊ ምክር ቤት የ2007 ዓ.ም. ዕቅድ አፈጻጸምን አስመልክቶ ባደረገው ግምገማ፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተሰብስበው ለነበሩ ባለድርሻ አካላት እንደተገለጸው፣ ሕገወጦችን መከላከል የሚያስችል እስከ ሞት ድረስ ቅጣት የሚጥል ሕግ ከማውጣት ባለፈ፣ ለማስፈጸም ተግቶ የሚሠራ አካል ባለመኖሩ ችግሩን ማቆም እንዳልተቻለ ተገልጿል፡፡

በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ጥሩ ሥራ የተሠራና የተሻለ ውጤትም የታየበት መሆኑን የገለጹት የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኰንን፣ የሕገወጥ ደላሎች አሠራር በየጊዜው ስለሚቀያየር የዜጐች ጉዳት እየጨመረ መምጣቱንና የተደረገውም ጥረት አርኪ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዜጐች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳትና አደጋ የሚመጥን እንቅስቃሴ አለመደረጉን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ የሚያሳየው የሕገወጥ ደላሎቹ መተላለፊያ የሆኑት ክልሎች፣ መንግሥትና ኅብረተሰቡ ባለመግባባታቸው ነው ብለዋል፡፡ በአገራቸው ሠርተው መለወጥ የሚችሉ በርካታ ዜጐች ለከፋ ጉዳት እየተዳረጉ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ በዜጐች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት የአገርን ገጽታ ጭምር የሚያበላሽ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ 

በቱሪስት ቪዛ እየተሰደዱ ያሉት ዜጐች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንና ዕግድ በተጣለባቸው ኳታርና የመን ሕጋዊ ሽፋን እየተሰጣቸው ለከፋ አደጋ እየተጋለጡ የሚገኙ ዜጐች ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የገለጹት ደግሞ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ሰለሞን ተስፋዬ ናቸው፡፡ ሕገወጥ ደላሎችን ወደ ሕግ ለማቅረብ የተቀናጀ አሠራር የሚያስፈልግ ቢሆንም፣ እስካሁን ክልሎችም ሊተገብሩት ባለመቻላቸው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ደመቀ ሕገወጥ ደላሎች ባለሁለት ፎቅ ሕንፃ በመገንባት ሀብታቸውን ሲያፈሩ፣ በሕገወጥ ደላሎችና የጉዞ መስመር የሄዱ ወጣቶች ግን የአውሬ ሰለባ እየሆኑ እንደሆነ ጠቁመው፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተባብሮ ሊታገል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ መንግሥት በተለይ በኢትዮጵያውያን ላይ የሳዑዲ ዓረቢያ ዜጐች ግድያ፣ አካል ማጉደልና ከፍተኛ እንግልት ካደረሱ በኋላ በሕጋዊ መንገድ ፈቃድ አውጥተው የውጭ አገር ሥራና አሠሪን የሚያገናኙ ኤጀንሲዎች ሥራቸውን እንዲያቆሙ በመደረጉ፣ በከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

መንግሥት በአጭር ጊዜ አሠራሩን አስተካክሎ ኤጀንሲዎቹ ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ የገለጸ ቢሆንም፣ የቤት ኪራይና የሠራተኛ ደመወዝ እየከፈሉ ከነገ ዛሬ ሥራ እንደሚጀምሩ የሚጠባበቁ ቢሆንም፣ መንግሥት ስለነሱ ምንም ሳይባልና የስብሰባው አካልም ሳያደርጋቸው መቅረቱ እንዳሳዘነው የኤጀንሲዎች ማኅበር ገልጿል፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤቱ እንዳረጋገጠው፣ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ዜጐች እየተሰደዱ መሆኑን የሚናገሩት ኤጀንሲዎቹ፣ ሕንፃ መገንባት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ከፍተኛ ሀብቶችን ሕገወጥ ደላሎች እያከማቹ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሥራ በመሰማራት የተጠረጠሩ ሰባት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ከዓለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ጋር በመተባበር ባደረገው ክትትል ኬንያ፣ ታንዛኒያና ሱዳን ውስጥ የነበሩት እነዚህን ሕገወጥ ደላሎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳስመጣ ተገልጿል፡፡ በሌሎች አገሮች በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሕገወጥ ደላሎች አገር ውስጥ ካሉ ደላሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ በሕገወጥ መንገድ በርካታ ዜጐችን ወደ ተለያዩ አገሮች ይልኩ እንደነበር የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ወንጀል ምርመራ ዲቪዚዮን ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ወንድሙ ጨማ ተናግረዋል፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ነዋሪ መሆኑ የተገለጸው አቶ መሐመድ ሐሰን የተባለ ተጠርጣሪ ደላላ ደግሞ፣ ሰባት ወጣቶችን በሱዳንና በሊቢያ አድርጐ ወደ አውሮፓ እንደሚልካቸው በማነጋገር፣ ከጅግጅጋ ወደ አዲስ አበባ አምጥቷቸው አዲስ አበባ ላይ በቁጥጥር ሥር ውሎ ክስ ተመሥርቶበታል፡፡ ግለሰቡ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ስምንት ክሶች የተመሠረተበት ሲሆን፣ የዋስትና መብቱን ተነፍጐ በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ተደርጓል፡፡ 

ግለሰቡ ሐረር ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ግብረ አበሮቹ ጋር በመቀናጀት፣ ሰባቱን ወጣቶች ከጅግጅጋ ወደ አዲስ አበባ አስመጥቶ ካዛንችስ አካባቢ በአንድ ሆቴል ውስጥ አልጋ ከያዘላቸው በኋላ፣ ማንም ቢጠይቃቸው ኢትዮጵያዊ እንዳልሆኑ እንዲናገሩ በማስጠንቀቅና ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ከታወቀ ለስደት የመጡ መሆናቸው እንደሚታወቅና ሊታሰሩ እንደሚችሉ በመንገር፣ መታወቂያቸውን መፀዳጃ ቤት ውስጥ እንዲከቱ ማድረጉን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ 

ዓቃቤ ሕግ ስምንት ክሶችን የመሠረተበት አቶ መሐመድ፣ ወጣቶቹን ለመምከርና ለማስጠንቀቅ ያደረገው ሙከራ ብዙም ቀናት ሳይጠቀምበት በቁጥጥር ሥር መዋሉን ክሱ ይገልጻል፡፡ በሱዳንና ሊቢያ አድርገው ጣሊያን እንደሚገቡ የተነገራቸው ወጣቶቹ፣ ለጉዞው የሚጠበቅባቸውን ክፍያ ሊቢያ ሲደርሱ ለቤተሰቦቻቸው በመደወል፣ እንዲልኩላቸው እንደሚያደርጉ ተስማምተው እንደነበር ክሱ ይገልጻል፡፡ ተከሳሹ ድርጊቱን እንዳልፈጸመ የገለጸ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ አራት ምስክሮችን አሰምቶ ፍርድ ቤቱ እንዲከላከል ብይን በመስጠት፣ ለጥቅምት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጥሮታል፡፡      

 

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ፍርድ ቤት ያልቀረቡበትን ምክንያት የማረሚያ ቤት ኃላፊ ቀርበው እንዲያስረዱ ታዘዘ

በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው እነ ዘመነ ካሴ በመከላከያ ምስክርነት የቆጠሯቸውና ለሦስት ጊዜያት የተጠሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ሐምሌ 29 ቀን 2007 ዓ.ም.ባለመቅረባቸው የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኃላፊ ያልቀረቡበትን ምክንያት ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲያስረዱና ምስክሩንም እንዲያቀርቡ ሌላ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡

 

በሽብር ድርጊት ወንጀል ተጠርጥረው ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸውን የእነ ዘመነ ካሴን ክስ እየመረመረ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ ለሐምሌ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. አቶ አንዳርጋቸውን መቅረብ አለመቅረባቸውን በችሎት ሲያረጋግጥ ግለሰቡ አልቀረቡም፡፡ ለምን እንዳልቀረቡ የማረሚያ ቤት ተወካይ ቀርቦ እንዲያስረዳ ፍርድ ቤቱ ቢጠይቅም ማንም ምላሽ ሊሰጠው አልቻለም፡፡ 

ፍርድ ቤቱ ሌላ ትዕዛዝ ሊሰጥ ሲል ከተከሳሾቹ አንዱ ተነስተው ማረሚያ ቤቱ የተለያዩ ምክንያቶች እየሰጠ መሆኑን ገልጸው፣ አቶ አንዳርጋቸውን የያዛቸው የፀረ ሽብር የጋራ ግብረ ኃይሉ በመሆኑ ማረሚያ ቤቱ የማያቀርብ ከሆነ ለእሱ ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ 

ተከሳሹ በመቀጠልም፣ ‹‹ተከሳሹ ፍርደኛ ነው፡፡ ፍርደኛ ደግሞ የሚኖረው ማረሚያ ቤት ነው፡፡ ለምን ማረሚያ ቤቱ እንዲያቀርብ ጥብቅ ትዕዛዝ አይሰጠውም?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡ ከታሰሩ ሦስት ዓመታት እንደሞላቸው በመግለጽ ቤተሰቦቻቸው ‹‹የአሸባሪ ቤተሰብ›› እየተባሉ የሚያከራያቸው በማጣታቸው፣ በየቦታው ተበትነው እየተሰቃዩ መሆኑን በመናገር ፍርድ ቤቱ አቶ አንዳርጋቸው በአጭር ቀጠሮ ቀርበው እንዲመሰክሩላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ብዛት ያላቸው ምስክሮችን እንደሚሰማና በአጭር ቀናት ማቅረብ እንደማይችል ገልጾ፣ ለጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በመኪና ሆነው አገሪቱ በልማት እያደረገች ያለውን ግስጋሴ እየጎበኙ መሆኑን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በቅርቡ መናገራቸውን የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

 

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ መዝብረዋል ተብለው በሙስና ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የባንኩ ሁለት ሠራተኞችና ዘመዶቻቸው እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ፡፡ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባለፈው ዓመት ነሐሴ 27 ቀን 2006 ዓ.ም. ያቀረበውን ክስ የሚመረምረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት …

ከንግድ ባንክ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ በመመዝበር የተጠረጠሩ ሠራተኞችና ዘመዶቻቸው ተከላከሉ ተባሉ Read more »

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በ2007 ዓ.ም. የግብር ሥርዓቱን ተከትለው ባልሠሩ የልኳንዳ ቤቶች የግምት ታክስ እንዲከፍሉ እንደሚደረግና በቫት ሥርዓቱም እንደሚጠየቁ አስታወቀ፡፡ ባለሥልጣኑ ሐምሌ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. የዕቅድ አፈጻጸምና ተግዳሮቶችን ባለድርሻ ከሆኑ የታክስ ከፋዩ ተወካዮች ጋር በገመገመበት ወቅት፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር …

ልኳንዳ ነጋዴዎች የግምት ታክስና የቫት ቅጣት ሊጣልባቸው ነው Read more »

የእስራኤሉ ትድሃር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤት ንብረትና ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ ታገደ

ባለቤቱ የተጠረጠሩበትን ከ143 ሚሊዮን ብር በላይ የወንጀል ክስ ተቃወሙ

በመንገድ ግንባታ የሚታወቀው የእስራኤሉ ትድሃር ኤክስካቬሺን ኤንድ ኧርዝ ሙቪንግ ሊሚትድ ኩባንያ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ሚናሼ ሌቭ ዮሴፍ ንብረቶችና ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ ታገደ፡፡ 

የኩባንያው ባለቤት ሚስተር ሚናሼ ሌቭ ዮሴፍ በሙስናና በጉቦ ወንጀል ተጠርጥረው፣ ከሐምሌ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር በመዋል ሐምሌ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡

ክሱን እየመረመረው የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 18ኛ ወንጀል ችሎት፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ማመልከቻ መሠረት የኩባንያው ባለቤት ንብረት የሆኑና በድርጅቱ ስም ተመዝግበው የሚገኙ 16 የተለያዩ ተሽከርካሪዎች፣ 21 የተለያዩ የግንባታ ማሽነሪዎች፣ ኩባንያው ለሠራው ሥራ የሚከፈል ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲታገድ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ 

የኩባንያው ባለቤት ለመንግሥት መክፈል የሚገባቸውን ከ52.7 ሚሊዮን ብር በላይ ላለመክፈል፣ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ሦስት ኦዲተሮች ጋር በመመሳጠርና ለእያንዳንዳቸው 500 ሺሕ ብር በድምሩ 1.5 ሚሊዮን ብር ጉቦ በመስጠት ወንጀል መጠርጠራቸውን የተመሠረተባቸው ክስ ያስረዳል፡፡ ኦዲተሮቹ 46,683,008 ብር ተቀናሽ በማድረግ፣ ሚስተር ዮሴፍ 6,114,770 ብር ብቻ እንዲከፍሉ ማድረጋቸው ታውቆ፣ ክስ ተመሥርቶባቸው በሒደት ላይ መሆኑንም ክሱ ይገልጻል፡፡ 

ትድሃር ኤክስካቬሺን ኤንድ ኧርዝ ሙቪንግ ሊሚትድ በግብር ከፋይነት የሚታወቅ ድርጅት ሆኖ ሳለ፣ ከታኅሳስ 23 ቀን 2002 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ካገኘው ገቢ ውስጥ ለመንግሥት መክፈል የሚገባውን ግብር ላለመክፈል ትክክለኛ ገቢውን መደበቁን ክሱ ይጠቁማል፡፡ 

ድርጅቱ በሦስት ተከታታይ የግብር ዓመታት መክፈል የነበረበት በድምሩ 61,444,033 ብር እንደነበር ክሱ ይገልጻል፡፡ ግብሩን ባለመክፈሉ 13,947,207 ብር ወለድ፣ ግብር አሳንሶ በማሳወቁ የሚጣል መቀጮ 30,722,016 ብር፣ ግብር በማዘግየት መቀጮ 18,318,422 ብር፣ ለባለቤቱ የተከፈለ ክፍያ ግብር፣ ወለድና ቅጣትን ጨምሮ 5,887,185 ብር በድምሩ 130,318,864 ብር አሳውቆ መክፈል ሲገባው፣ ባለመክፈሉና ሕግን በመጣስ ግብርን ባለመክፈል ወንጀል መከሰሱን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ ድርጅቱ ሕግን ጥሶ ግብርን ባለመክፈሉ ወካዩ ባለቤቱ ሚስተር ዮሴፍ በመሆናቸው እሳቸውም ሕግን በመጣስ ግብርን ባለመክፈል ወንጀል ተከሰዋል፡፡ 

ድርጅቱና ባለቤቱ ግብር አሳውቀው መክፈል ሲገባቸው፣ እንዳይከፍሉ የሚያደርግ አሳሳች መረጃ (መግለጫ) በመስጠታቸው በፈጸሙት የሐሰት መረጃ ማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ድርጅቱ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ካደረጋቸው የንግድ እንቅስቃሴዎች ከሰበሰበው ገቢ ላይ፣ ለመንግሥት አሳውቆ መክፈል የነበረበትን የተጨማሪ እሴት ታክስ ፍሬ ግብር 2,132,817 ብር አለመክፈሉን፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ፍሬ ግብር ወለድ 4,141,387 ብር፣ መቀጫ 7,497,249 ብር በድምሩ 13,771,455 ብር ለመንግሥት አሳውቆ ባለመክፈሉና ባለቤቱም የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ በመሆናቸው፣ በፈጸሙት ሕግን በመጣስ ታክስ ያለመክፈል ወንጀል መከሰሳቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ በአጠቃላይ የተከሰሱበት ከ143 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡  

ሚስተር ዮሴፍ የትድሃር ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲሠሩ ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ በትድሃር አማካይነት ካገኙት ገቢ ለመንግሥት መክፈል የሚገባቸውን ሳይከፍሉ፣ ከፍተኛ ገንዘብ ደብቀው ማስቀረታቸውን ክሱ ጠቁሟል፡፡ 

ተከሳሹ የከፍተኛ ገንዘብ ሕገወጥ አመጣጥን ለመሰወርና ሕጋዊ አስመስሎ ለማቅረብ በማሰብ፣ ከሰኔ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 8 ቀን 2006 ዓ.ም. ድረስ በተለያዩ 17 ቼኮች በድምሩ 8,681,500 ብር በለጠ ደጀኔ በተባለ ግለሰብና የድርጅቱ ሠራተኛ ባልሆነ ሰው አማካይነት፣ በውጭ ምንዛሪ በጥቁር ገበያ ተቀይሮ እንዲቀርብላቸው በማድረግ መጠቀማቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ በመሆኑም በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ መጠቀም ወንጀል መከሰሳቸውም በክሱ ተገልጿል፡፡ 

ፍርድ ቤቱ ክሱን ካነበበላቸው በኋላ ተጠርጣሪ ተከሳሾቹ የክስ መቃሚያ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የክስ መቃወሚያውን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡     

 

ከየካቲት 12 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ኅዳር 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ለአምስት ዓመታት በሥራ ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001ን የተካው አዋጅ ቁጥር 859/2006 የተሻሻለው፣ አዋጅ ቁጥር 622/2001 ላይ የተቀመጡ ጉዳዮችን በትኩረት ለማየት እንጂ፣ ተከሳሾችን ወይም የተቀጡ …

የገቢዎችና ጉምሩክ አዋጅ የተሻሻለው የተከሰሱና የተቀጡ ሰዎችን ለመጥቀም ታስቦ አለመሆኑ ተገለጸ Read more »

መቀመጫውን ኤርትራ ውስጥ ማድረጉንና ራሱን ‹‹የአርበኞች ግንባር›› በማለት እንደሚጠራ የተገለጸው ድርጅት አባል በመሆን፣ ተልዕኮ በመቀበልና አባላትን በመመልመል ሲሳተፉና ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል የተባሉ ዘጠኝ የሰሜን ጎንደር ነዋሪዎች፣ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ መሳተፍ ወንጀል ሐምሌ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡    የፌዴራል ዓቃቤ …

በአርበኞች ግንባር አባልነት የተጠረጠሩ ዘጠኝ የሰሜን ጎንደር ነዋሪዎች በአሸባሪነት ተከሰሱ Read more »

በሁለት ክሶች ዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል

በወሰን ግጭት ምክንያት የሦስት ሕፃናት ወላጆችን በ20 እና በ11 ጥይቶች ደብድቦ መግደሉ በሰዎችና በሰነድ ማስረጃዎች የተረጋገጠበት የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ፍርደኛ፣ ከማረሚያ ቤት በማምለጡ ተቋርጦ የነበረው ክስ እንዲቀጥል ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

ፍርደኛው የመከላከያ ሠራዊት አባል እንደነበር የተገለፀው መቶ አለቃ ጌትዬ አለሜ ከማረሚያ ቤት ያመለጠው ሁለት ጊዜ ነው፡፡ መጀመሪያ ያመለጠው የሦስት ሕፃናት ወላጆች የሆኑትን አቶ ዳንኤል ነጋሽና ወ/ሮ ምስለ ማሞን በጥይት ደብድቦ ከገደላቸው ከሁለት ወራት የማረሚያ ቤት ቆይታ በኋላ ነበር፡፡ ፍርደኛው የካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 03 ልዩ ቦታው መካኒሳ ጉልት ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ፣ ሁለቱንም የሕፃናቱን ወላጆች በድንበር ግጭት ምክንያት መግደሉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በግለሰቡ የግድያ ድርጊት ምክንያት የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ሦስት ክሶችን መሥርቶበታል፡፡ አቶ ዳንኤል ነጋሽን በ20 ጥይቶች ደብድቦ በመግደል፣ ወ/ሮ ምስለ ማሞን በ11 ጥይት ደብድቦ በመግደልና ሕገወጥ የጦር መሣሪያ (አንድ ተሽከርካሪ ኮልት ሽጉጥ፣ የተፈታታ ማካሮቭ ሽጉጥ፣ የጦር ሜዳ መነጽር፣ 46 ጥይቶችና ባዶ የክላሽ ካርታዎች) ይዞ መገኘት ወንጀሎች ክሶች ተመሥርተውበታል፡፡ 

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አሰምቶ ፍርደኛው ድርጊቱን መፈጸሙን በማረጋገጡ በከባድ የሰው መግደል ወንጀል (ሁለቱን ግለሰቦች) በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ፍርድ ሰጥቶ ነበር፡፡ ፍርደኛው በድጋሚ በማምለጡ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘቱ የተመሠረተበት ክስ ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም፣ የተገኘ መሆኑን ጠቅሶ ዓቃቤ ሕግ ክሱ እንዲንቀሳቀስለት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በማመልከቱ፣ ክሱ እንዲቀጥል ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡ ለሐምሌ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮም  ሰጥቷል፡፡

 

በደርግ ዘመን በቀይ ሽብር ወቅት የከፍተኛ አንድ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ እርገጤ መድበው፣ በ‹‹ኢሕአፓ እና ስፖርት›› መጽሐፍ ደራሲ አቶ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ላይ የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ መሠረቱ፡፡ ከሳሽ አቶ እርገጤ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ ችሎት በመሠረቱት ክስ ተከሳሽ የመጽሐፉ …

የቀድሞ ከፍተኛ አንድ ሊቀመንበር በ‹‹ኢሕአፓ እና ስፖርት›› መጽሐፍ ደራሲ ላይ ክስ መሠረቱ Read more »

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጉብኝት ባደረጉበት በዚህ ሳምንት፣ በአገራቸው አንድ ፍርድ ቤት ኢትዮጵያን ባልተፈቀደ ስለላ የሚወነጅል ክስ መቅረቡ ተሰማ፡፡ በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት አሜሪካዊ የሆነ ኪዳኔ በተባለ በሜሪላንድ የሚኖር ግለሰብ ላይ የስካይፒና የኢንተርኔት የስልክ ልውውጦችን በመጥለፍ፣ እንዲሁም ቤተሰቦቹ በኢንተርኔት …

የአሜሪካ ዜግነት ባለው ግለሰብ ላይ ያልተፈቀደ ስለላ በማድረግ ወያኔ ቀረበበት Read more »

ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያን የሚጎበኙት የአማሪካን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እንዲያነጋግሯቸው ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አለማግኘቱን ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡ 

ጥያቄውን በይፋ አቅርበው የነበሩት ፓርቲዎች የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ናቸው፡፡ 

የሦስቱ ፓርቲዎች ፕሬዚዳንቶች ሰጥተውት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት፣ ፕሬዚዳንት ኦባማ አግኝተው እንዲያነጋግሯቸውና ወሳኝ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ለፕሬዚዳንቱ ገለጻ ለማድረግና ለመመካከር እንደሚፈልጉ ገልጸው ነበር፡፡ 

ይህንን የፓርቲዎቹን ጥያቄ በተመለከተም አዲስ አበባ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲና ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤ መጻፋቸውን ያስታወሱ ሲሆን፣ ሆኖም ጥያቄያቸው ምላሽ እንዳላገኘና ምንም ዓይነት ቀጠሮ እንዳልተያዘላቸው አስረድተዋል፡፡ 

የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ ‹‹ፕሬዚዳንቱን በጋራ ለማግኘት ያቀረብነው ጥያቄን በተመለከተ ምንም የተሰጠ መልስ የለም፡፡ ነገር ግን በተናጠል ፕሬዚዳንቱ በአፍሪካ ኅብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሚያደርጉትን ንግግር እንድንታደም ኤምባሲው ጥሪ ልኮልናል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ኤምባሲውን ማብራሪያ መጠየቃቸውን የገለጹት ዶ/ር ጫኔ፣ ‹‹ከፕሬዚዳንቱ ጋር ቀጠሮ ማስያዝ ከእነርሱ ቁጥጥርና ኃላፊነት ውጪ እንደሆነና በሌላ አካል እየተመራ ነው፤›› የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን አብራርተዋል፡፡ 

‹‹ምንም እንኳን ፕሬዚዳንቱን አግኝቶ የመነጋገርና የመወያየት ጥያቄያችን ባይሳካም፣ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያካተተው ደብዳቤ ግን ለፕሬዚዳንቱ መድረሱን አረጋግጠናል፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሐሪ ‹‹ፕሬዚዳንቱ በአፍሪካ ኅብረት በሚያደርጉት ንግግር ላይ እንድንገኝ የሚገልጽ ደብዳቤ ከመላክ ባለፈ፣ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ለመወያየት ላቀረብነው ጥያቄ ምንም ዓይነት የተሰጠ ምላሽ የለም፤›› በማለት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አለማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

የኢራፓ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮም በጋራ ፕሬዚዳንቱን የማግኘትና የመወያየት ጥያቄ እስከ ዓርብ ሐምሌ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ምላሽ አለማግኘቱን ገልጸው፣ ‹‹ሦስት ፓርቲዎች በጋራ በመሆን ያቀረብነው የአነጋግሩን ጥያቄ ምላሹን እየጠበቅን ነው፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱን የማግኘት ተስፋ ሊኖር እንደሚችል እምነታቸውን አስረድተዋል፡፡ 

እነዚህ ሦስት ፓርቲዎች በጋራ ለመሥራት ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መካከል ጋዜጣዊ መግለጫዎችንና የተቃውሞ ሠልፎችን በጋራ የመጥራትና የማዘጋጀት ተጠቃሽ እንደሆነ ቀደም ሲል ማስታወቃቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡ 

 

የቡናን ዘርፍን በበላይነት እንዲመራ የሚቋቋመው የኢትዮጵያ የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን፣ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንዲሆን ጥያቄ ቀረበ፡፡  ባለሥልጣኑን ለማቋቋም የተዘጋጀው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቅ ደንብ እንደሚለው ባለሥልጣኑ ተጠሪነቱ ለግብርና ሚኒስቴር ነው፡፡ ሰሞኑን የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር በረቂቅ ደንቡ …

የቡና ባለሥልጣን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ተጠየቀ Read more »