ሕመሜ
አንድ ወዳጅ አለኝ፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያብሰከስከው፡፡ ሯጮቻችን ሲያሸንፉ፣ ተጨዋቾቻችን ድል ሲያደርጉ፣ ስለ ኢትዮጵያ መልካም ነገር ሲሰማና ሲነገር፣ በሀገሩ ላይ ልማትና ዕድገት ሲታይ፣ አንዳች የሆነ ሀገራዊ ለውጥ ሲታይ፣ ይፈነድቃል፤ መልክዐ ገጹ ይፈካል፤ ደስታው ከልክ አልፎ ጣራ ይነካል፡፡ የሚያሳዝን፣ አንገት የሚያስደፋ፣ የሀገርን ስም የሚሰብር፣ ገጽዋን የሚያበላሽ ነገር ሲሰማና ሲያይ ደግሞ ከሥራ እንደተባረረ ሠራተኛ አንገቱን ይደፋል፤ የእናቱን መርዶ እንደ ሰማ ልጅ ዓይኑ ዕንባ ይሞላል፤ ከጨለማ እሥር ቤት እንደ ገባ እሥረኛ ፊቱ ከል ይለብሳል፤ ሲብሰከሰክ ሲብከነከን ውሎ ያድራል፡፡
አንድ ቀን ‹‹ለአንተ ግን ሀገር ማለት ምንድን ናት? ወይስ ያንተ ሀገር የተለየች ናት? ምን እንደዚህ ያብከነክንሃል?›› አልኩት፡፡
‹‹ታውቃለህ›› አለኝ ፊቱን በቀኝ መዳፉ እየሞዠለጠ፡፡ የጎፈረ ፀጉሩን ደግሞ በግራ ጣቶቹ ይልጋቸዋል፡፡ አጭርና ድንቡሼ ነው፡፡ ወግ ሲጀምር ‹ታውቃለህ› ማለት ይቀናዋል፡፡
‹‹ታውቃለህ፤ ሀገር ማለት ‹ሕመሜ› ማለት ናት›› አለኝ፡፡ ከንፈርና አፍንጫዬን አገናኚቼ በጆሮዬ በኩል ወሬውን ዋጥኩና ወደ ኋላዬ ለጠጥ አልኩ፡፡ ሰምቼው የማላውቀው ትርጓሜ ነው፡፡ ‹‹ሀገር ማለት ሕመሜ ነው››፡፡ ይህንን ሳሰላስል ‹‹ሕመም ያልኩህ እንዳይመስልህ፣ ‹ሕመሜ› ነው ያልኩህ›› አለኝ፡፡
‹‹ሕመምና ሕመሜ፣ ምን ልዩነት አላቸው››
‹‹ዘፋኞችና አንጎራጓሪዎች በጣም የሚወዱትን ሰው ‹ሕመሜ› እያሉ ሲዘፍኑለት ሰምተህ አታውቅም››
‹‹ዐውቃለሁ፡፡ ታድያ ሀገርና ያ ምን ና ምን ናቸው››
‹‹የጆሮ ጉትቻ ያንገት ሐብል ናቸው – አልልህም መቼም›› አለኝ፡፡
‹‹ሕመሜ እያሉ የሚዘፍኑትኮ ስለሚወዱት ነገር ነው፡፡ እያለቀሱ አይምሰልህ፤ ሙሾ እያወረዱም አይደለም፤ የኀዘን እንጉርጉሮ እያዘነቡም አይደለም፡፡ ደስ ብሏቸው እየዘፈኑ ነው፡፡ እስክስታ እየወረዱ የሚዘፍኑት ግን ‹ሕመሜ› እያሉ ነው፡፡ የሚወዱትን፣ ሊያገኙት የሚፈልጉትን፣ እንዲያጡት የማይሹትን፣ መልካሙን ነገር ሁሉ የሚመኙለትን፤ ልቤ፣ አንጀቴ፣ ኩላሊቴ፣ ዓይኔ፣ ሆዴ፣ ነፍሴ የሚሉትን፤ ሞትም አይለየንም፣ ካንተ ውጭ ሌላ አልሻም፣ ሌላው ሁሉ ሰው አይመስለኝም፣ የሚሉለትን ፍቅረኛቸውን ‹ሕመሜ› እያሉ ይዘፍኑለታል፡፡
‹‹ አየህ ይህ ፍቅራቸው ሕመም ያለው ፍቅር ነው፡፡ ፍቅር ብቻ አይደለም፡፡ ሰናፍጭ ነው ያድናል፣ ግን ይሰነፍጣል፤ ሚጥሚጣ ነው ደስ ይላል፣ ግን ያቃጥላል፤ መርፌ ነው ይፈውሳል፣ ግን ያማል፤ ፈረስ ነው ይጋልባል፣ ግን ይገለብጣል፤ የሱፍ አበባ ነው ይመስጣል፣ ግን በእሾህ ተከብቧል፡፡ ውስጡ ደስ የሚል ሕመም አለበት፡፡ ደስታ ነው ብለህ እፎይ እንዳትል ሕመሙ እንደ ፍልስጣ ጎን ጎንህን ይወጋሃል፤ ሕመም ነው ብለህ እንዳትተወው ደስታው እንደ ወይን ጠጅ ‹እስኩ ድግሙ ድግሙ› ያሰኝሃል፡፡ ለዚህ ነው ‹ሕመሜ› እያልክ የምትዘፍንለት፡፡ የሚዘፈንለት ሕመም አይተህ ታውቃለህ? ሕመምን ይታከሙታል እንጂ ይዘፍኑለታል እንዴ? ሕመምን ያስታግሡታል እንጂ ያዜሙለታል እንዴ? እንዲያ ነው የምልህ፡፡
‹‹እና ሀገር እንዴት ነው ‹ሕመሜ› የምትሆነው?›› አልኩት ፍልስፍናው ደስ ብሎኝ፡፡ በጎድጓዳ መንገድ እንደሚሄድ ገልባጭ መኪና ወደ ግራና ወደ ቀኝ ወዝወዝ ብዬ ተስተካከልኩ፡፡
‹‹ሀገርማ ደንበኛዋ ‹ሕመሜ› ናት፡፡ ሀገር ብለህ ስታስብ ጤናና ሕመም ነው የሚሰማህ፡፡ የምትኮራበት፣ ምነው በዚያ ዘመን በኖርኩ ብለህ የምትመኝበት፣ ስታየውና ስትሰማው ደምህ የሚሞቅበት፣ ስታስበውና ስትናገረው ኩራትህ የሚጨምርበት ነገር አላት ሀገር፡፡ ምን እንደሆነ የማታውቀው እንዲሁ ፍቅር የምታስይዝህ ነገር አላት ሀገር፡፡ ታስጨፍርሃለች፣ ታስቦርቅሃለች፣ ታስዘልልሃለች ሀገር፡፡ የትም ቦታ ሆነህ ስሟን ስትሰማው ልብህን ቀጥ የሚያደርግ ነገር አላት ሀገር፡፡ ሙትልኝ ሙትልኝ፣ ድማልኝ ድመልኝ፣ ተሠዋ፣ተሠዋ የሚያሰኝ ኃይል አላት ሀገር፡፡ ምንም ጥቅም ሳታገኝ፣ ምንም ነገር ላንተ ሳይደርስህ፣ የሞተላት ቀርቶ የገደላት እየበላ እንኳን ቢሆን፤ ሞኝ ነሽ ተላላ እያል እየዘፈንክላትም ቢሆን፣ ላንዱ በጭልፋ ላንዱ በአካፋ እየሰጠች እንኳን ቢሆን፤ አንዱ እንገሯን አንዱ አሬራዋን እየጠጣም ቢሆን፤ ላንዱ ቅቤ ላንዱ ዝቃቅቤ እየሰጠችውም ቢሆን – ግን በፍቅር እንድትሞትላት የሚያደርግ ኃይል አላት ሀገር፡፡ እንዳትቀየማት፣ ቂም እንዳትይዝባት፣ እንዲሁ ይቅር እንድትላት የሚያደርግ ኃይል አላት ሀገር፡፡
‹‹ደግሞ ገልብጠህ ስታያት ሀገር ሕመም ናት፡፡ ቀዶ ጥገና አድርገህ የማታወጣት፣ ቆርጠህ የማትገላገላት፤ ታክመህ የማትድናት፤ በአበሻ መድኃኒት ነቅለህ የማትጥላት፤ ኮሶ ወስደህ የማታሽራት፤ ሕመምህ ናት ሀገር፡፡ ምነው እዚህ ሀገር ባልተደረገ የምትለው ስንት ታሪክ አላት፤ ምነው በዜጋሽ ላይ እንዲህ ታደርጊያለሽ ብለህ የምታዝንባት ስንት ግፍ አለባት ሀገር፤ ምነው እንደ እንጀራ እናት ታዳያለሽ ብለህ አንጀትህ እርር የሚልባት ስንት አድሎ አላት ሀገር፤ አንዱ
ሀገሬ ኢትዮጵያ ምድራዊት ገነት
አደላድለሽኛል በሥልጣንና በሀብት፣
ብሎ ሲያወድሳት፣ አንተ ግን –
ሀገሬ ኢትዮጵያ ምድራዊት ገነት
እስኪ ፈልጊልኝ የሚከራይ ቤት፣
ትላታለህ፤
ለሚያሥረው ሀገር ናት፣ ለታሣሪው ሀገር፤ ለገዳይ ሀገር ናት ለሟቹም ሰው ሀገር፤ ለአሳዳጅ ሀገር ናት ለተሰዳጅ ሀገር፡፡
‹‹ ‹ሌቦ› እያሉ እንደመዝፈን ያለ፡፡ አሁን ለሌባ ምን ይዘፈንለታል፡፡ ሀገርህ ሰጭ፣ ለጋስ፣ ቸር፣ ደግ፣ ብቻ አይደለችም፡፡ ሀገርህ ሌቦም ናት፡፡ የስንቱን ሕጻን፣ ወጣት፣ ሽማግሌ፣ ልጃገረድ፣ እናት፣ ባልቴት ሕይወት ቀጥፋ ነው እዚህ የደረሰችው፡፡ ግን ሌባ አይደለችም ‹‹ሌቦ›› ናት፡፡ የሚዘፈንላት ሌባ ማለት ነው፡፡ ‹‹ያዛት፣ ያዛት፣ በላት፣ በላት፣ ኡኡኡ›› ብለህ በፖሊስ የምታስይዛት፣ በጎረምሳ የምታስደበድባት ሌባ አይደለችም፡፡የምትዘፍንላት ‹ሌቦ››፡፡
አሣሪ ሆነህ እንደወድካት ሁሉ ታሣሪም ሆነህ ትወዳታለህ፣ አሳዳጅ ሆነህ እንደወደድካት ሁሉ ተሳዳጅ ሆነህም ትወዳታለህ፤ ቀማኛ ሆነህ እንደወደድካት ሁሉ ተቀምተህም ትወዳታለህ፤ተምረህ እንደወደድካት ሁሉ ደንቁረህም ትወዳታልህ፡፡ ሀገር ማለት ይህቺ ናት፡፡ ሀገር ‹‹ሕመሜ›› ናት፡፡ ሀገር አደዋ አላት፤ ሀገር ማይጨው አላት፡፡ የአኩስም ሐውልት አላት፣ የቆሻሻ ክምርም አላት፤ መንገድ ሠሪም አላት፣ መንገድ ላይ የሚሸናም አላት፤ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የስልክ ታሪክ አላት፣ ከአፍሪካ መጨረሻ የሆነ የስልክ ኔትወርክም አላት፤ ታሪክ ትሠራለች፣ ታሪክም ታፈርሳለች፤ ቅርስ ትሠራለች፣ ቅርስም ታፈርሳለች፡፡ ሀገርህ ይህቺ ናት፡፡
‹‹ርግፍ አድርጌ ልተዋት ብትል እሺ አትልህም፡፡ ለቅቀሃት በመሄድ፣ ጥለሃት በመጥፋት፣ ዜግነት ቀይረህ፣ ቋንቋህን ለውጠህ እንኳን እሺ ብላ አትተውህም፡፡ ሞተህ እንኳን አትለቅህም፣ አስከሬን ታስጭንሃለች፡፡ ደግሞ በዚያ ወገን ዝም ብዬ ብቻ ልውደድሽ፤ ዝም ብዬ ብቻ ላድንቅሽ ስትላት ደግሞ እሺ አትልህም፡፡ አንዳች ሕመም ነገር አላት፡፡ ያለህ አማራጭ ‹‹ሕመሜ›› እያልክ መዝፈን ነው፡፡ በሳቅህ ውስጥ ልቅሶ፣ በልቅሶም ውስጥ ሳቅ ትቀላቅልብሃለች፡፡ የጠቦቱን ሥጋ ከመራራ ቅጠል ጋር ታበላሃለች፡፡
‹‹ለእኔ ሀገር ማለት ይህቺ ነች፡፡ ‹‹ሕመሜ›› ››
ዝም ብዬ አየሁት፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው