ትናንት አልባዋ ከተማ


click here for pdf

በተፈጥሮ ካልተገኙና ሰው ልጅ ከፈጠራቸው ከማይንቀሳቀሱ የሥልጣኔ ውጤቶች አንዱ ከተማ ነው፡፡ ከተማ የአንድ ሕዝብ ሥልጣኔ የሚታይበትና የሚቀላጠፍበት ማዕከል ነው፡፡ በዚህም የተነሣ የሰው ልጅን ታሪካዊ ሂደት በመመዝገብና የደረሰበትንም ሥልጣኔ በማሳየት ረገድ የከተማን ያህል የተሻለ ቦታ የለም፡፡ የጥንታዊ ሰዎችን ሥልጣኔና ታሪክ የሚያጠኑ ባለሞያዎች የጉዞውን ሂደት የሚገልጡ መረጃዎችን የሚያገኙት በቁፋሮ ከሚገኙ ጥንታውያን ከተሞች ነው፡፡ በእነዚህ ጥንታውያን ከተሞች የሰው አነዋወር፣ ታሪክ፣ የመንግሥት አሠራር፣ የንግድና የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ ወግና ሥርዓት፣ እምነትና ባሕል በተሰናሰለና ሥርዓት በጠበቀ መንገድ ይገኝባቸዋል፡፡
በአብዛኛው የገጠሩ ማኅበረሰብ ባልተሰባሰበ፣ አንድ ወገን በሆነ፣ ግልጽ የአኗኗር መርሕ፣ አስተዳደራዊ መዋቅር እምብዛም ባልተዘረጋበት መንገድ የሚኖር ነው፡፡ የከተማ ማኅበረሰብ ግን በተወሰነ ቦታ፣ ከተለያየ ማኅበረሰብ ተውጣጥቶ፣ በአንድ ውሱን ሕግ እየተዳደረ፣ ለክዋኔዎች ቦታ ወስኖ(ለንግድ፣ ለአምልኮ፣ ለመንግሥት አስተዳደር፣ ለመኖሪያ፣ ወዘተ) የሚኖር በመሆኑ የሥልጣኔ መገለጫዎች በከተሞች የሚገኙትን ያህል በገጠር አናገኛቸውም፡፡ ሐውልቶች፣ አደባባዮች፣ አብያተ መንግሥት፣ ሳንቲሞች፣ የኪነ ጥበብ ሕንጻዎች፣ የተደራጁ ገበያዎች፣ የውኃ መሥመሮች፣ የከተማ መከለያ ግንቦች፣ የእምነት ማዕከሎች በከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ ተሠርተው የምናገኛቸው በከተሞች አካባቢ ነው፡፡

በሀገራችንም የታሪክና ቅርስ ማዕከል የሆኑትን አኩስምን፣ ሮሐን፣ ሐረርን፣ ጎንደርን፣ አንኮበርን፣ አዲስ አበባን፣ ሌሎችንም ብንመለከተ የመንግሥት፣ የኢኮኖሚና፣ የእምነት መናኸሪያ ከተሞች የነበሩና የሆኑ ናቸው፡፡ በእነዚህ ቦታዎች የምናገኛቸውን እርስ በርስ የተግባቡ፣ የተሠናሠሉና የተመጋገቡ የሥልጣኔ መገለጫዎችን ያህል በሌሎች ቦታዎች አናገኝም፡፡ በሌሎች ቦታዎች የምናገኛቸው በተናጠል የተቀመጡ የሥልጣኔ መገለጫዎችን ነው፡፡
የሰው ልጅ በተፈጥሮው ምክንያት ትናንትን ይጠይቃል፡፡ እንዲሁ ዛሬን ብቻ ዝም ብሎ አይቀበልም፡፡ እንደ ሥነ ፍጥረት ሊቃውንት ይህንን የሚጠይቁት መላእክትና ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ መላእክት በተፈጠሩ ጊዜ ‹‹ከየት ተገኘን? እንዴትስ ልንገኝ ቻልን?›› ብለው የጠየቁት ግእዛን ያላቸው (ማሰብና መመርመር የሚችሉና የሚያስፈልጋቸው) ፍጡራን በመሆናቸው ነው፡፡ የሰው ልጅም በምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ዘመን ጀምሮ በእምነትና በፍልስፍና መስኮች ሲጠይቃቸው ከኖራቸው ጥያቄዎች አንዱ ‹‹ዓለም ከየት መጣች?›› የሚለውን ነው፡፡
ሰው ትናንትን የማወቅ፣ ከትናንቱም የመማር፣ ከትናንት ተምሮም ወደፊት የመንደርደር ዕምቅ ፍላጎትና ችሎታ ስላለው መሬት እየጎረጎረ፣ ዋሻ እየበረበረ፣ ዐለት እየፈለጠ፣ ተራራ እየገለበጠ የጥንት ሰዎችን አድራሻ፣ ማንነትና ሥራ ሲመረምር ይኖራል፡፡
ሰው እንደ እንስሳ የዛሬን ብቻ ኑር ሊባል አይችልም፡፡ እንስሳ ትናንትም ነገም የለውም፡፡ ሰው ግን የሦስት ነገሮች ውጤት ነው፡፤ የትናንት አሻራ፣ የዛሬ ሥራ፣ የነገ ራእይ፡፡ ሰው ነገን ያለ ትናንት ማሰብ አይችልም፡፡ ተፈጥሮ አንድን ነገር ለብቻው በንጣሌ እንድንረዳው አልተወችንምና፡፡ ተፈጥሮ ራሷ የትይይዝ ውጤት ናት፡፡ ሊቃውንት ይህንን ለማስረዳት እንደ ቀላል ማሳያ የሚሰጡን ቀለማትን ነው፡፡ አንዱ ቀለም ከሌላ የሚግባባው ቀለም ጋር ስምምነት ፈጥሮ(harmony) ነው የሚኖረው፡፡ ይህንን የቀለማት ተግባቦት የሰዎች አለባበስ፣ የቤት አሠራር፣ የፀጉርና የሰውነት ቀለም፣ የሚተከሉ ዛፎችና እንዲፈጥሩት ይደረጋል፡፡ ምንም እንኳን እነዚህን ቀለማት አስበን ባንመርጣቸውም ተፈጥሮ ተግባቦትንና ስምምነትን ስለምትፈልግ ደመ ነፍሳዊ በሆነ መንገድ እናከናውነዋለን፡፡ 
በአንዲት ከተማ ሕይወት ውስጥም እንደ ቀለማቱ ተግባቦት ሁሉ ትናንት፣ ዛሬና ነገ ተግባብተው መገኘት አለባቸው፡፡ እንኳን እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከመቶ ዓመታት የዘለለ ታሪክ ያላቸው ከተሞች ቀርተው የቅርብ ዘመን የምሥረታ ታሪክ ያላቸው እነ ዱባይ እንኳን አንዳች ከጥንታዊነት ጋር የሚያያዝ ታሪክ ፍለጋ ሲኳትኑ፣ ያንንም ለማሳየትና የከተማቸው የሕይወት አካል ለማድረግ ሲጥሩ እናያቸዋለን፡፡
በአንድ ከተማ ሕይወት ውስጥ በሳል ነቢብ(ቲወሪ)፣ አመራርና አሠራር ከሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አንዱ ትናንትን፣ ዛሬንና ነገን ከከተማዋ ዕድገት፣ ሥልጣኔና የአነዋወር ዘይቤ ጋር አጣጥሞ የመሄድ ብልሃት ነው፡፡ የከተማዋ ጥንታዊነት የዛሬ ዕድገቷንና የነገ ተስፋዋን እንዳይገታው፤ የከተማዋ የዛሬ መስፋፋት፣ ዕድገትና ሥልጣኔ የትናንት አሻራዋን እንዳያጠፋው፤ የከተማዋ የትናንት ታሪክና የዛሬ ዘይቤም የነገውን ትውልድ ድርሻና ዕጣ ፋንታ እንዳያቀጭጨው – በሳል የሆነ ነቢብ፣ አመራርና አሠራር ይጠይቃል፡፡
የአንዲት ከተማ መልክዐ ጠባይ፣ ሕይወትና እሴት የሚገነባው ከዚህ መሰሉ ነቢብ፣ አመራርና አሠራር ነው፡፡ የከተማዋ ሕንጻዎች፣ መኖሪያዎች፣ መንገዶች፣ የሕዝብ ቦታዎች፣ ገበያዎች፣ የእምነት ቦታዎች፣ ማኅበራዊ ተቋማት፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳትና ውበት፣ ከዚህ ነቢብ፣ አመራርና አሠራር ይወለዳሉ፡፡ የሚፈቀዱና የሚከለከሉ ነገሮች ከዚህ ይመነጫሉ፤ የሚጠበቁና ለሕዝብ ክፍት የሚሆኑ ነገሮች ከዚህ ይመሠረታሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ቁልፍ ችግሯ ትናንት፣ ዛሬና ነገን የምታግባባበት የራስዋ የሆነ፣ በዘመናት የዳበረ፣ የተፈተነና ውጤታማነቱ የተመሰከረለት ‹ነቢብ፣ አመራርና አሠራር› ማጣት ይመስለኛል፡፡ በአንድ የውይይት መድረክ አንድ የከተማ ዐቅድ ባለሞያ እንደገለጡት ‹‹አዲስ አበባ እያንዳንዱ መንግሥት የየራሱን ርዕዮተ ዓለም ያነባበረባት ከተማ ናት – The layer of different Ideologies ፡፡ ያ ነው ከተማዋን ሲምታታባት እንዲኖር ያደረገው››
አዲስ አበባ አሁን ዐሥረኛውን የከተማ መሪ ዕቅድ እያዘጋጀች ነው፡፡ እነዚህ መሪ ዕቅዶች ምንም እንኳን ሳይንሳዊ አሠራርን የተከተሉ ሞያዊ ሥራዎች ቢሆኑም የሚዘወሩት ግን በየዘመናቱ ሀገሪቱ በምትመራባቸው ርእዮተ ዓለሞች ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ አዲስ አበባ ‹ወጥ፣ ለዘመናት የዳበረ፣ የተፈተነና የተመሰከረለት የከተማ ዘይቤ› እንዳይኖራት አድርጓታል፡፡
ባለፈው መንግሥት ጊዜ የቁጠባ ቤቶች የአዲስ አበባ የቤቶች መልክዕ ሆኖ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ኮንዶሚኒየምና ሪል እስቴት የአዲስ አበባ የቤት መልክዕ ሆነዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከንቲባነት ለረዥም ዓመታት በማገልገል የሚታወቁት ከንቲባ ዘውዴ እንደሚሉት በአዲስ አበባ ቀበሌ ሲቋቋም ከ2500 – 4000 የሚደርስ ሕዝብ የሚይዝ አንዳች የጉርብትና ማዕከል ለመፍጠር ነበር፡፡ ጉርብትናን ዘመናዊ ለማድረግ፡፡ ‹ከተማ ማለት የጉርብትና ሥርዓት ነውና›፡፡ ርእዮተ ዓለሙ ሲቀየር ግን ቀበሌዎች የጉርብትና ማዕከላት መሆናቸው ቀርቶ የቀይ ሽብርና የነጭ ሽብር ማዕከላት ሆኑ፡፡ ቀበሌ ማለትም የአብዮት ማራመጃ ማዕከል ሆነ፡፡ በሀገራችን መንግሥታት የሚቀያየሩት በመፍረስ በመሆኑ በመንግሥታት መካከል ርክክብ አልተደረገም፡፡
ይህንን መሰሉ በየጊዜው የሚለዋወጡ ነቢቦች፣ አመራሮችና አሠራሮች አንዳቸው ከሌላቸው ጋር ተግባብተው የሚመሠረቱ ባለመሆናቸው አዲስ አበባ ስትፈርስ ስትሠራ የምትኖር መሞከሪያ ከተማ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ እንኳንስ በተለያዩ መንግሥታት ርእዮተ ዓለሞች መካከል ቀርቶ በአንድ መንግሥት ዘመናት እንኳን ሲያፈርሱ ሲሠሩ መኖር እየተለመደ መጥቷል፡፡ ከሸራተን አካባቢ የተነሡ ነዋሪዎች ለድጋሚ ተነሺነት የተጋለጡት በዚህ ያልተግባባ አሠራር ጭምር ነው፡፡ አዳዲስ ቤቶች እንደገና ለመንገድና ለሌሎች ግንባታዎች ተብለው የተሠሩበት ሲሚንቶ ሳይደርቅ እንዲፈርሱ የሚደረጉት በዚህ ወጥነት በሌለው የከተማዋ ነቢብ፣ አመራርና አሠራር የተነሣ ነው፡፡ በተሠሩ በጥቂት ዓመታት ለባቡር ተብለው የፈረሱትንና 900 ሚሊዮን ብር የፈጁትን የአዲስ አበባ መንገዶችን በዚህ በበሰለ ነቢብ፣ አመራርና አሠራር ብቻ ነበር ማትረፍ ይቻል የነበረው፡፡ አንድም ቀድሞ በማሰብ፣ አለያም አጣጥሞ በመሥራት፡፡ 
አዲስ አበባ ዕድገቷንና ታሪኳን የማጣጣም ፈተና ገጥሟታል፡፡ ለመሆኑ ያለፉ ነገሮቿን ሁሉ እንዳሉ ይዛ መቀጠል አለባት? ያለፉ ነገሮቿንስ ሙሉ በሙሉ አፈራርሳስ መቀጠል አለባት? ለመሆኑ ታሪክና ዕድገት፣ ቅርስና ሥልጣኔ እንዴት ነው የሚጣጣሙት? ከተማዋ እነዚህን በትክክል ካልመለሰች ከተማ ሳይሆን ዘመናዊ የሰው ልጅ ማጎሪያ ትሆናለች፡፡ ዛሬ የሚሠሩት ታላላቅ ግንባታዎቻችንስ የነገውን ትውልድ ሥልጣኔ፣ አነዋወርና ፍልስፍና ከግምት ውስጥ እያስገቡ ናቸው? የዛሬ አምስት ዓመት የገነባናቸውንና ስናስመርቃቸው ጉሮ ወሸባ ያረገድንባቸውን እንዲህ በፍጥነት የምናፈርስ ከሆነ ሌሎቹን እንድንጠራጠር ያደርገናል፡፡
አሁን አሁን አዲስ አበባ ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬንም ከነገ የሚያጣጥም ነቢብ፣ አመራርና አሠራር በማጠቷ ምክንያት የአዲስ አበባ ከተማን ጥንታዊነት የሚያሳዩ ቅርሶች እንደ ነፍጠኛና ፊውዳል መገለጫዎች እየተቆጠሩ፣ ቀጥታና ቀጥታ ያልሆነ ሞት እየተፈረደባቸው ነው፡፡ ቀጥተኛ የሆነ ሞት የሚባለው ለዕድገት ፀር፣ለግንባታ ዕንቅፋት፣ ለመስፋፋት እንከን አድርጎ በማየት የማፍረስ ርምጃ መውሰድ ነው፡፡ በዚህ ፍርድ ምክንያት ጥንታውያን መንደሮች፣ ቤቶች፣ ድልድዮች፣ ሐውልቶች፣ አደባባዮች፣ የንግድ ማዕከላት፣ እንዲፈርሱ ተደርገዋል፡፡
ሁለተኛውና ቀጥታ ያልሆነ ሞት የምንለው ደግሞ እነዚህን ጥንታውያን ሀብቶች የመከባከብ ኃላፊነት ያለበት አካል ክብካቤ በመንፈግና ቀስ በቀስ እንዲፈርሱ ሆን ብሎ በመተው የሚደረግ ግድያ ነው፡፡ ይህ ፍርድ የተፈረደባቸው ቅርሶች በአካባቢያቸው ለእነርሱ ሕልውና አሥጊ የሆነ ሥራ ሲከናወን የሚያስጥላቸው የለም፤ የቆሻሻ መጣያ ሲሆኑ በዝምታ ይታለፋሉ፤ ሲፈርሱና ሲበላሹ በዝምታ ይታያሉ፤ ሲዘረፉና ሲወሰዱ የሚያስጥል አያገኙም፤ ጥበቃ አይደረግላቸውም፤ ሞያ በሌላቸው አካላት እንዲጠገኑ ይደረጋል፤ ታጥረውና ተከልለው እንዲቀመጡ ይደረጋል፤ በውስጡ ነዋሪዎች ሲቀመጡባቸውና ግንባታ ሲያከናውኑባቸው ተከታታይ አይኖርም፤ በጢስና እሳት እንዲበላሹ ይተዋሉ፡፡
በአንድ በኩል ያለፈው ነገር ሁሉ መነካት የለበትም የሚሉ የታሪክና ቅርስ ወግ አጥባቂዎች (ወግ አጥባቂነት አዎንታዊ ነው) አሉ፡፡ እንደ እነርሱ ከሆነ የአዲስ አበባ ነባር ነገሮች ሁሉ ተጠብቀውና ተከብረው መኖር አለባቸው፡፡ እነርሱ የከተማዋን፣ ብሎም የሀገሪቱን ጥንት የሚመሰክሩ ናቸውና፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በቦታው ላይ የሚሠራ ሌላ ነገር እስካለ ድረስ የጥንቱ መፍረስ አለበት፡፡ የጥንቱ ጥንት አገልግሏል፡፡ አሁን ዘመኑ የዛሬ ነው፡፡ ጥንቱ ለዛሬ ዕንቅፋት ከሆነ ያለው ዕድል መፍረስ ብቻ ነው ይላሉ፡፡
እነዚህ ሁለቱም ለእኔ ጽንፎች ናቸው፡፡ ሁሉም የጥንት ነገር እንዳለ ሊቀመጥ አይችልም፡፡ በሦስት ምክንያት፡፡ አንድ ሁሉም የጥንት ነገሮች እኩል የሆነ ታሪካዊ፣ ቅርሳዊና ባሕላዊ ዋጋ የላቸውም፤ ሁለተኛ ደግሞ ሁሉም የጥንት ነገሮች ይቀመጡ ካልን ለአዳዲስ ነገሮች ቦታ ላይገኝ ይችላል፤ በመጨረሻም ሁሉንም የጥንት ነገሮች ለማቆየት፣ ለመጠበቅና ለመከባከብ ዐቅም ያስፈልጋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ለአዳዲስና ለዘመናዊ ነገሮችና ሐሳቦች ሲባል ሁሉንም የጥንት ነገሮችን በግዴለሽነት ማፈራረስ ሦስት ጉዳቶች ያስከትላል፡፡ የሰው ልጅን የጥበብ፣ የባሕል፣ የሥልጣኔና የክሂሎት አሻራ ያጠፋል፤ አንድን ነገር ምንጊዜም እንደገና እንድንጀምረው በማድረግ ተያያዥና ተደጋጋፊ ነገርን ያሳጣል፤ በመጨረሻም የከተማዋን የቱሪዝም ገቢ ያመክናል፡፡ 
እነዚህን ሁለት ጽንፎች ለማስታረቅ የሁለቱንም አዎንታዊነት የያዘ አንድ ሌላ መንገድ ያስፈልጋል፡፡ እርሱም አዳዲስ ነገሮችን ከጥንታውያን፣ ዘመናዊነትን ከነባርነት፣ ታሪክን ከዕድገት፣ ቅርስን ከሥልጣኔ ጋር አስማምቶ፣ አደጋግፎና አመጋግቦ መምራት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ወጥነት ያለው፣ በየዘመናቱ የሚዳብር በሳል ሀገራዊ ፍልስፍና ያስፈልጋል፡፡
ይህንን መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ የሚከተሉት አካሄዶች ያስፈልጋሉ
  1. የከተማዋን ታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶች የመለያ መመዘኛ ማስቀመጥ
  2. በመመዘኛው መሠረት የከተማዋን ታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶች በዝርዝር መለየት
  3. እነዚህ የከተማዋ ቅርሶች በልዩ ልዩ መንገድ ለትውልድ የሚተላለፉበትን መሥፈርት ማውጣት
    • እንዳሉ ባሉበት ሁኔታ ለሌላ አገልግሎት ሳይውሉ ለትውልድ መተላለፍ ያለባቸው
    • መጠናቸው ተቀንሶ ናሙናቸው መተላለፍ ያለባቸው( ለምሳሌ አንድን መንደር ሙሉውን ቅርስ አድርጎ ማቆየት ከባድ ቢሆን እንኳን ያ መንደር ምን ይመስል እንደነበር የሚያሳይ አንድ ናሙና ቦታ ለይቶ ማቆየት ይቻላል)
    • በልዩ ልዩ የመቀረሻ መሣሪያዎች(ፎቶ፣ ሥዕል፣ ቪዲዮ፣ ወዘተ) ተመዝግበው መተላለፍ ያለባቸው(አንዳንድ ሠፈሮች የቀድሞ መልካቸውና አሠራራቸው በልዩ ልዩ መቀረሻ መንገዶች ቀርጸ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል)
    • ወደ ሙዝየም ገብተው መተላለፍ ያለባቸው
    • ቅርስነታቸውንና ይዞታቸውን በማይጎዳ መንገድ ለሌላ የማይጣረስ አገልግሎት ተላልፈው ግን ተጠብቀው መተላለፍ ያለባቸው(ጣይቱ ሆቴል እንደተደረገው)
    • ቦታቸውን ቀይረው በቅርስነት መጠበቅ ያለባቸው
  4. ማናቸውም ከተማዊ እንቅስቃሴዎች ከእነዚህ የተመዘገቡ ቅርሶች ጋር ያላቸውን ተግባቦት በቅርብ መከታተል፣ ለክትትሉም እንዲያመች የሚመለከተው አካል ከማናቸውም ግንባታ በፊት አካባቢው ከቅርስ ነጻ መሆኑን ምስክርነት እንዲሰጥ ማድረግ
  5. የከተማዋ መሪ ዕቅድ ሲዘጋጅም እነዚህን ታሪካዊ ቦታዎችና ቅርሶችን በሚገባ የለየና የእነርሱን የሕልውና መብት የጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ
  6. በታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶች አካባቢ ይፋዊ መለያ መለጠፍ፤ ይህ ምልክት የተለየ ቀለም ወይም ዐርማ እንዲኖረው በማድረግ ማንኛውም ሰው እንዲለየው ማስቻል
  7. የፌዴራል ቅርስ አዋጅ ቁጥር 209/92 ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች ምንም ዓይነት ሥልጣን ስለማይሰጥ ይህንን ማስተካከል
  8. የታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶች አካባቢዎች የተዛማጅ ልማቶች ማዕከል (የሆቴል፣ የጥበበ ዕድ መሸጫ፣  የዐውደ ርእይ ማሳያ፣ የባሕላዊ ገበያዎች) መጠቀም
  9. በተማሪዎች፣ በአካባቢው ነዋሪዎችና በቱሪስቶች እንዲጎበኙ መርሐ ግብሮችን ማመቻቸት

እነዚህንና የመሰሉትን ተግባራት በጊዜ ማከናወን ካልቻልን አዲስ አበባ ‹ትናንት የሌላት ከተማ› ትሆናለች፡፡ ያውም በታሪክ አጋጣሚ ሳይሆን ሳያስቡ የሚሠሩ አመራሮችና ነዋሪዎች ስላሏት ብቻ፡፡ ከተማ እንደ ፈጣን ምግብ(fast food) ለዕለት ሆድ መሙያ የምትሠራ አይደለችም፡፡ እንደ ገጠር ጠላ ለነገም ጭምር የምትጠነሰስ ናት፡፡ ከተማዋን ለሰዎች መኖሪያነት ምቹና ተመራጭ ለማድረግ መንገድ፣ ሆቴል፣ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ፣ ባቡር፣ ሱፐር ማርኬት፣ የገበያ ማዕከል፣ የግል ኮሌጅ፣ ዓለም ዐቀፍ ተቋማትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ብቻቸውን በቂ አይደሉም፡፡ ጥንታዊ፣ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ፣ መንፈሳዊና ሞራላዊ እሴቶች፣ ቅርሶችና ቦታዎችም ያስፈልጓታል፡፡ እነዚህ ራሳቸው ነገ ታሪክና ቅርስ ስለሚሆኑ፡፡ ከተማ እንደ ላም ዱካ የሚተው እንጂ እንደ አዞ በጅራታቸው ዱካ የሚያጠፉ አመራሮች አያስፈልጓትም፡፡

 © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው