ባቡር – የሐበሻ መድኃኒት

በተለምዶ ሲኤም ሲ በሚባለው ሰፈር፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ሥር ካለው ክልል ወደ የካ ከተማ ክልል ለባቡር የተሠራውን መንገድ እንደ ጦጣ እየዘለልኩ በማቋረጥ ላይ ነበርኩ፡፡ ከእኔ ፊት ፊት ሁለት ሽማግሌዎች በምርኩዛቸው እየተረዱ እንደ ሽሪ ሚሪ የተከረተፈውን የባቡር መንገድ በጥንቃቄ ይሻገራሉ፡፡ ሽሪ ሚሪውን ተሻግረው የተነጠፈው ሐዲድ ላይ ሲደርሱ ልባቸው መለስ አለላቸው መሰል የአኩስም ጋቢ የመሰለ ፀጉር የለበሱት አንደኛው ሽማግሌ ‹‹እንዴው በቃ ይህንን ባቡር የሐበሻ መድኃኒት አደረጉት ማለት ነው?›› ብለው ጓደኛቸውን ጠየቁ፡፡
‹‹እንዴት እንዴት በል?›› አሉ ሪዛቸው እንደ ዝቋላ ጥድ ወደታች የወረደላቸው ሌላው አረጋዊ፣ በከዘራቸው የባቡሩን ሐዲድ ነካ ነካ እያደረጉ፡፡
‹‹ቆይ ይኼ ባቡር ምንድን ነው የሚመስለው? ባቡሩ ሲያልቅስ ይኼ መንደራችን ምን ይመስላል? መሳፈሪያው እንዴት ነው?በዚህ በመገናኛስ በዋሻ ያልፋል የሚባለው እንዴት እንዴት ሆኖ ነው? እንዴት የሁላችንን ሕይወት ዋጋ ያስከፈለ፤ ስንት ቤቶችን ያስነሣ፣ ስንት ሠራተኞችን ያስረፈደ፣ ስንት ሚሊዮን ብር የፈጀ፣ ለሀገራችንም እንግዳ የሆነ ነገር ሲሠራ፣ እንዴት አንድ ቦታ እንኳን ሥዕሉ አይለጠፍም? ቆይ ይህንን ሁሉ መሥዋዕትነት ከፍለን፣ ጠዋት አርፍደን፣ ማታ ተሠልፈን፣ የሃያ ሁለትና የዑራኤል ሆቴሎች ቀዝቅዘው፣ እኛም መሻገሪያ አጥተን በስተርጅና እንደ ጉሬዛ እየዘለልን የሚሠራው ባቡር ምንድን ነው የሚመስለው? ለመሆኑ ታውቃለህ?››
‹‹ይኼው የሀብታሙ ሁሉ ሕንጻ ሲሠራ ከፊት ለፊቱ ሥዕሉ በትልቁ ይሰቀል የለም እንዴ? እኛም ዐቅምና ዕድል ኖሮን ባንሠራም ቆመን ሥዕሉን አይተን እናደንቃለን፡፡ ሕንጻው ሲያልቅ ሠፈሩ ምን እንደሚመስልም እንገምታለን፤ እንደ ሽምግልናችንም ‹አልቆ ለማየት ያብቃን› ብለን እንመርቃለን፡፡ የከተማው ባቡርማ ለምርቃትም ለጸሎትም አስቸጋሪ ሆነኮ፡፡ እኛ የከተማ ባቡር አይተን አናውቅ፣ ምናለ በየሠፈሩ ሥዕሉን ቢለጥፉልን፤ ብናደንቅ፣ ሠሪዎችንም ብንመርቅ፣ እንዲያስፈጽመውም ብንጸልይ፡፡››
ሽማግሌዎቹ የባቡሩን መንገድ አቋርጠው ወደ ሲ ኤም ሲ ሚካኤል አቅጣጫ ተጓዙ፡፡ መንገዴን ትቼ ወጋቸውን ሽቼ ተከተልኳቸው፡፡
‹‹አይህ ወዳጄ እነዚህ የሃይማኖት ሰዎች ‹መንግሥተ ሰማያት ይህንን ትመስላለች› የሚሉትኮ ያለምክንያት እንዳይመስልህ፡፡ የሚደርስብህን ሁሉ መከራ የምትቋቋመው የምታገኘውን አስረግጠህ ካወቅከው ብቻ ነው ብለው ነው፡፡ መንግሥተ ሰማያትን ይስሉብህና ‹ለዚህች ልዩ ሀገር ስትል ዋጋ ክፈል፣ መከራውን በጸጋ ተቀበል፤ እስከ ጊዜው ነው ቻለው› ይሉሃል፡፡ ምነው እነዚህ ባቡር የሚሠሩ ሰዎች ከእነርሱ ቢማሩ፡፡ ለመሆኑ ይኼ ሁሉ ጉድጓድ ተቆፍሮ፣ መንገድ ተከልክሎ፣ ሠፈር ፈርሶ፣ ሐውልት ተነቅሎ፣ ማቋረጫ ጠፍቶ፣ መንገድ ተዘጋግቶ፣ ንግዱ ተቀዛቅዞ የምናገኘው ነገር ምንድን ነው? ምን ይመስላል? አሁን እኛ መሥዋዕትነት እየተቀበልን ያለነው ምን ለማግኘት ነው? ማንም አያውቅም፡፡ ምነው ግን ይህንን ባቡር የሐበሻ መድኃኒት አደረጉትሳ››
‹‹እኔም ሁልጊዜ የሚገርመኝ እርሱ ነው፡፡ መገናኛ ሄድኩ፣ ዑራኤል ሄድኩ፣ መስቀል አደባባይ ሄድኩ፣ ሜክሲኮ ሄድኩ፣ በቀደምም መርካቶ ሄድኩ፤ ሕዝቡ የመሰለውን ብቻ ነው የሚያወራው፡፡ አንዱ ኤሌክትሪኩ ከላይ ነው ይላል፣ ሌላው መሬት ውስጥ ተቀብሯል ይላል፤ አንዱ ማውረጃው ከላይ ነው ይላል፣ ሌላው መሬት ውስጥ ነው ይላል፤ አንዱ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት አይመለስም፣ ቦታ የለውም ይላል፤ ሌላው ይመለሳል፣ ግን ከድሮው ሬዲዮ ጣቢያ አጠገብ ይተከላል ይላል፡፡ ይህንን ሁሉ ምን አመጣው? አንተ እንዳልከው የሐበሻ መድኃኒት ይመስል ምሥጢር ስላደረጉት ነው፡፡ እንጂማ ሲሆን እኛ ሽግሌዎቹም እንድናይ ከፍ ከፍ አድርገው፣ ካልሆነም ባቅም ባቅሙ ሥዕሉን መለጠፍ ነበረባቸው፡፡››
አሁን ሽማግሌዎቹ ወደ ሲኤም ሲ ሚካኤል እየገቡ ነው፡፡ ባርኔጣቸውን ሊያወልቁና እጅ ሊነሡ በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡
‹‹በቀደም አያ ተሰማ ምን አለኝ መሰለህ››
‹‹ምን አለህ ደግሞ፤ መቼም እርሱ ወግ አያልቅበትም፡፡››
‹‹የካና ቦሌ አሁን ነው ትክክለኛ ድንበር ያገኙት፡፡ ይኼው የባቡሩ መንገድ የማያገናኝ ድንበር አበጅቶላቸዋል፡፡ ካሁን በኋላ የምንገናኘው በሞባይል ብቻ ነው፡፡ ከመንገድ ማዶና ማዶ ሆነህ በስልክ እያወራህ በእጅ ሰላምታ መለዋወጥ ብቻ ነው›› አለኝ፡፡
‹‹እንዴ መሻገሪያ አያደርጉልንም እንዴ? እኛ ወዲያ ተሻግረን ሚካኤልን ላንሳለም፣ ሙስሊሞችም ወዲህ መጥተው ላይሰግዱ ነው ማለት ነው? ይህማ ደግ አይደለም››
‹‹ቢለጥፉትኮ ይኼ ጥያቄ ይመለስልን ነበር፡፡ ግን የሐበሻ መድኃኒት ነው፡፡ ያውም የወፍ መድኃኒት፡፡ ፌርማታው የት ጋ ነው? መንገዱንስ እንዴት አቋርጠን ነው የምንሳፈረው? ሰው ዘሎ ቢገባስ? እንዴው ተጨነቁ ብሎን የሚመስለንን ስንገምት እንውላለን፡፡ ቤት ስትሠራ እንኳን መሐንዲሱ የቤቱን መልክ በወረቀት ስሎ ይሰጥሃል፤ አንተም አይተህ ደስ ሲልህ ይህንንስ ወገቤን አሥሬ እሠራዋለሁ ትላለህ፤ ሰው ዛሬ ወደፊት የሚቀበርበትን ቦታ እንኳን ለማወቅ ፈልጎ በቁሙ መቃብር ያሠራል፤ ልብስ ሰፊ እንኳን ዋናው ልብስ እስኪደርስ በቾክ ጨርቁ ላይ ስሎየልብሱን መልክ ያሳይሃል፤ ደጋሽም ድግሱ እስኪደርስ ቅምሻ ብሎ ይጠራሃል፤ የሞሰቡን እንጀራም በእንጎቻው ትገምተዋለህ፤ ባቡሩን ግን እንዴት እንገምተው? ለመሆኑ ምን መልክ ይኖረዋል? እንዴት ነው የምንሳፈረው? ወጭውስ በኛ ዐቅም ይቻላል? እንደ ሰርዲን ታጭቀን ነው ወይስ ወንበር አለው? ለመሆኑ እንደ አውቶቡስ ቁጥር አለው? ሲሆን አንድ ቦታ ላይ ሠርተው እንደ ኤግዚቢሽን ቢያሳዩን፤ ‹አሃ ለካ እንደዚህ ነው› ብንል አእምሯችን ለምዶት ቢቆይ መልካም ነበር፡፡ ካልሆነም ሥዕሉን በየሠፈራችን ቢያኖሩት››
‹‹በቀደም ታናሿ ልጄ የምወልደውኮ ሴት ልጅ ነው አለችኝ››
‹‹ያቺ ነፍሰ ጡሯ››
‹‹አዎ፤ በምን ዐወቅሽው፣ የዛሬ ልጆች መጠንቆል ጀመራችሁ ወይ አልኳት››
‹‹ሐኪሙ አሳየኝ – አለችኝ››
‹‹ሆድሽን ከፍቶ አሳየሽ – ብዬ ቀለድኩባት››
‹‹አይደለም በመሣሪያ ማየት ይቻላልኮ – አለችኝ፡፡ ዛሬ ያልተወለደን ልጅ ወንድ ይሁን ሴት ማወቅ እየተቻለ እንዴት ነው እንዲህ ሠፈሩን ሁሉ አቋርጦ የሚሄደውን ባቡር መልክ ቀድሞ ማየት ያልተቻለው፡፡ ሲቆፍሩ፣ ሲገነቡ፣ ሲሚንቶ ሲሞሉ፣ አቧራ ሲያቦኑ ብቻ ነው የምናያቸው፤ የሐበሻ መድኃኒት አደረጉት አልክ፣ እውነትክን ነው፡፡››
አረጋውያኑ ወደ ሚካኤል ግቢ ዘልቀው ተሳለሙና አጥሩ ጥግ ዛፎቹ ሥር ዐረፍ አሉ፡፡
‹‹እኔ ግን ምን እንደሚመስለኝ ታውቃለህ?›› አሉ ሽበት ያጀባቸው ሽማግሌ
‹‹ምን ይመስልሃል?›› አሏቸው ሪዛሙ አረጋዊ
‹‹እኛ ብቻ ሳንሆን እነርሱም አሟልተው ያወቁት አይመስለኝም››
‹‹መጠርጠር እርሱን ነው›› አሉና መዳፋቸውን በመዳፋቸው መቱት፡፡

© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው