ዐፄ ምኒሊክ በአዲስ አቀራረብ
የወረዳው ሊቀ መንበር ለስብሰባው በሚገባ መዘጋጀታቸው ሲወራ ነው የሰነበተው፡፡ ሕዝቡን ለፀረ ሽብርተኛት ዘመቻ በሚገባ ማንቀሳቀስ አለብኝ ብለዋል አሉ፡፡ አንድም ሰው ከዚህ ስብሰባ መቅረት እንደሌለበት በየሰፈሩ ሲወራ ነበር፡፡
የስብሰባው ቀን ሕዝቡ እግር ኳስ የሚያይ መስሎ አዳራሹን ሞላው፡፡ ቦታ የጠበባቸውም በመስኮት በኩል ጉርድ ፎቶ የሚነሡ ይመስል አንገታቸውን ብቻ አስግገው ያጮልቃሉ፡፡ እስካሁን ማንም ሊቀ መንበር ያልተናገረውን ንግግር ሊያደርጉ ነው ስለተባለ ሰው ምን እንደሚናገሩ ለመስማት ጓጉቷል፡፡ በተለይ አንዳንዱ የወረዳው ነዋሪ እንደ ክትባት ለሁሉ የታዘዘ የሚመስል ተመሳሳይ ንግግር መስማት ሰልችቶታል፡፡ ተናጋሪዎች እንደ ኮካኮላ ጠርሙስ አንድ ዓይነት ሆነው እንደ ተመረቱ ሁሉ እንኳን ቃሎቻቸው ሳሎቻቸው እንኳን ስለሚመሳሰሉ አንዳንዱ ‹ይህንን ንግግር የት ነበር የሰማሁት›› እስከማለት ደርሷል፡፡ አሁን የኛ ወረዳ ሊቀ መንበር ይህንን እንደ ኮንዶሚንየም መልክ የተመሳሰለ ንግግር ሰብረው ሪኮርድ ሊያስመዘግቡ መሆኑን ስንሰማ ተገልብጠን መጣን፡፡
አንድ በስብሰባው ውስጥ ያገኘሁት ሰው ‹‹እነዚህ ባለ ሥልጣናት ግን አንድ ዓይነት ቃላት ከየት ነው የሚያገኙት?›› ብዬ ስጠይቀው ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ ‹‹የባለ ሥልጣናት መዝገበ ቃላት›› የሚባል ያልታተመ መጽሐፍ አለ፡፡ከዚያ ብቻ ነው ቃላት መምረጥ የሚችሉት፡፡ እዚያ ውስጥ የንግግር ቅጽ አላቸው፡፡ ወረዳውን፣ ቀኑን፣ የተሰብሳቢዎቹን ዓይነትና የበዓሉን ስም ብቻ ትቀይርና ንግግሩን ትወስዳለህ›› ብሎ ቀለደብኝ፡፡
አሁን ሊቀ መንበሩ እየገቡ ነው፡፡ ሕዝቡ አጨበጨበ፡፡ ፕሮግራሙን የሚመራው ሰው ማይክራፎኑን ያዘና ‹አሁን ስብሰባችንን የምናከናውንበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡›› ሲል ሕዝቡ አጉረመረመ፡፡ ግራ ገባው፡፡ ‹ይህ ሕዝብ ባይገባው ነው›› ብሎ አዘነልን፡፡ ‹‹ወረዳችን በዕድገት እመርታ ላይ መሆኗን ታውቃላችሁ፡፡ ልዩ ልዩ ጽሕፈት ቤቶችና አጋር አካላት ተሳልጠው በመሥራታቸውና ሙስናንና ብልሹ አሠራን አስወግደን ልማታዊ አስተሳሰብን በማምጣታችን …›› ሕዝቡ ትዕግሥት አጣ፤ አንድ ጎረምሳ እንዲያውም ‹‹ይህንነን ንግግር የዛሬ ሦስት ዓመት ሰምተነው ነበር፡፡›› ሲል ተሰብሳቢው ሳቀ፡፡
አንደኛዋ ወይዘሮማ ‹‹ምነው መንግሥት በየቦታው ተዋንያኑን ብቻ ነው እንዴ የሚቀይራቸው? የፊልሙን ስክሪፕትስ ለምን አይቀይረውም፡፡ ያ ይሄዳል ይሄ ይመጣል፤ ፊልሙ ያው ነው፡፡›› ሳቅና ጭብጨባ አጀባቸው፡፡ ሰውዬው ግራ እንደገባው ነው፡፡ ‹‹ይህ ንግግር ከራሴ የወጣ ነው፡፡ ይህንን ማን ተናግሮት ነው የዛሬ ሦስት ዓመት የሰሙት›› አለ ተገርሞ፡፡ ‹‹ባክህ ሃርድ ዌሩ ነው እንጂ ሶፍት ዌሩ ያው ነው፡፡ ወይ አብዴት አድርጉት ወይ ቀይሩት›› ወጣቱ ሲናገር በዐዋቂነቱ ተጨበጨበለት፡፡
የወረዳችን ሊቀ መንበር አዝማሚያው ስለገባቸው ማይክራፎኑን ከፕሮግራም መሪው ተቀበሉት፡፡ ‹‹ወደ መጣንበት ጉዳይ ብንገባ ይሻላል፡፡›› ሲሉ አንድ ካህን ድምጻቸውን ከፍ አደረጉና ‹‹ልክ ነው ከተአምሩ መቅድሙ ረዘመብንኮ›› አሏቸው፡፡ ሊቀ መንበሩ ፈገግ ብለው ወረቀታቸውን ከቦርሳቸው አወጡ፡፡ አሁን ስፒል ቢወድቅ የሚሰማበት ዝምታ ተፈጠረ፡፡ የሰው ጆሮ እንደ ዲሽ ተዘረጋ፡፡
ሊቀ መንበሩ ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡ ‹ፈጣሪ በቸርነቱ እስካሁን ሀገር አስፍቶ ጠላት አጥፍቶ አኑሮናል› ብለው ሲጀምሩ ሕዝቡ ቀጣዩን እንኳን ሳይሰማ አጨበጨበ፡፡ የተከበራችሁ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት፣ የክፍለ ከተማ አመራሮች፣ የድርጅት ኃላፊዎች፣ የሥራ አስፈጻሚ አባላት፣ የወጣት ሊግ አመራሮች፣ የሴቶች ሊግ አመራሮች፣ የአነስተኛና ጥቃቅን አመራሮችና አባላት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅት ኃላፊዎች፣ የአደረጃጀቶች ኃላፊዎች….. እያሉ እንደ ስም ጠሪ መምህር ወይም እንደ ሙሾ አውራጅ ሲዘረዝሩ ሊውሉ ነው ተብሎ ነበር የተጠበቀው፡፡
‹‹ድርጅታችንም እስካሁን በፈጣሪ ቸርነት፣ በታጋዮች መሥዋዕትነት፣ በአመራሩ ብስለትና በሕዝቡም ይሁንታ ይህንን ሀገር እየመራ መጥቷል፡፡›› ሲሉ ከጎኔ የነበሩት አንድ ሽማግሌ ‹‹ይኼ ነገር የሆነ የሆነ ነገር ሸተተኝ›› አሉኝ፡፡ በዚህ እድሜያቸው የሆነ ነገር ለማሽተት መቻላቸውን አደነቅኩና ‹‹ምን ሸተተዎት›› አልኳቸው፡፡ ‹‹ቆይ እስኪ ቀጣዩን እንስማው›› አሉ፡፡ እንደ ሬዲዮ አንቴና አንገታቸውን ወደ ላይ መዝዘው፡፡
ሊቀመንበራችን እንደ ቀጠሉ ናቸው ‹‹ደግሞም ሕዝባችን እስካሁን አሳፍሮን አያውቅም፤ ከእንግዲህም ያሳፍረናል ብለን አናምንም›› ሲሉ ጭብጨባው ቀለጠ፡፡ እኒያ ሽማግሌ ግን ወደ ላይ የዘረጉትን የአንገታቸውን አንቴና ወደ ውስጥ ሰበሰቡት፡፡ ከዚያም ራሳቸውን ወደ ቀኝና ግራ ወዘወዙ፡፡ ‹‹ይኼ የተከተፈ ንግግር ነው›› አሉ፡፡ በግራ በቀኝ፣ በፊት በኋላ የተቀመጡት ተሰብሳቢዎች ዘወር ዘወር እያሉ አዩዋቸው፡፡ ሊቀ መንበራችን ግን ቀጠሉ፡፡ ‹‹አሁን ግን አገር የሚያጠፋ፣ ገጽታ የሚለውጥ፣ ዕድገት የሚገታ፣ የሕዝብን ሰላም የሚያናጋ ጠላት መጥቶብናል›› ሽማግሌው አንገታቸውን አውልቀው መጣል ይፈልጋሉ መሰል ከአመድ እንደተነሣች አህያ ያርገፈግፉታል፡፡
‹‹እኛም ብሔር ብሔረሰቦች ፊታቸውን ወደ ልማት ማዞራቸውን፣ ሀገራችንም በአንጻራዊ ሰላም ላይ መሆኗን ተመልክተን፤ ዐቅማችንንም ለልማት እንጂ ለሌላ ነገር ማዋል የለብንም ብለን ዝም ብንለው፤ ደግሞ እያለፈ እንደ ዘንዶ አደጋ ማድረስ ጀመረ››፡፡ ሽማግሌው የአንገታቸው አልበቃ ብሏቸው በጫማቸው መሬቱን ይፎግሱ ጀመር፡፡ ‹‹አሁን ግን ሕዝባችንን አጋዥ አድርገን ሀገራችንን አሳልፈን አንሰጥም በማለት ተነሥተናል፡፡ ሕዝባችን ሆይ እስካሁን የበደልንህ አይመስለንም፡፡ አንተም አልበደልከንም፡፡ ዐቅም ያለህ በዐቅምህ እርዳን፤ ዐቅም የሌለህ ለሚስትህ/ለባልሽ፣ ለእምነትህ ስትል መረጃ በመጠቆም እርዳን፡፡›› አሁን ሽማግሌው እጃቸውን ከእጃቸው ጋር ማፋተግ ጀመሩ፡፡ ሊልጡት ነው እንዴ፡፡ ‹‹ወስልቶ ከዚህ ዘመቻ የቀረ ካለ ግን ይጣላናል፡፡ አንተወውም፤ ድርጅታችንን፤ እንምረውም››
‹‹ኦህ›› አሉ ሽማግሌው፡፡
‹ለዚህ አማላጅ የለንም፡፡ ፀረ ሽብር ዘመቻችን ተጀምሯልና የሀገራችን ሰው በዚሁ ወቅት በየራስህ ከትተህ እናግኝህ፡፡››
ሕዝቡ አጨበጨበ፡፡ ጭብጨባውም ረዘመ፡፡
ሽማግሌው ማንም ሳይቀድማቸው ተሥፈንጥረው ተነሡ፡፡
‹‹እሽ አባቴ›. አሉ ሊቀመንበሩ፡፡ ሽማግሌው ወኔ ይዟቸው የተነሡ መስሏቸው፡፡
‹‹ይህ ንግግር የማን ነው?›› አሉ፡፡ እየተንቀጠቀጡ፡፡ ሰው አጉረመረመ፡፡
‹‹እንዴት ማለት›› አሉ ሊቀ መንበሩ፡፡
‹‹ይህ ንግግር ዐፄ ምኒሊክ ለዐድዋ ዘመቻ ከተናገሩት ንግግር የተወሰደ አይደለም?›› አሉ ሽማግሌው፡፡
‹‹ነው›፡፡ ግን ሬሚክስ አድርጌ በአዲስ አቀራረብ ነው ያመጣሁት፡››
‹‹ምኑን ነው ሬሚክስ ያደረጉት››
‹‹ከዓላማዬ ልጀምርልዎት፡፡ የቀድሞ መሪዎችን ንግግር እንዲህ ሬሚክስ እያደረግን ካላቀረብነው ይረሳሉ፡፡ ትውልዱ አያስታውሳቸውም፡፡ ይህንን ያደረግኩት ለምኒሊክ ክብር ብዬ ነው፡፡ አላዩም ዘፋኞቻችንን፤ የቀድሞ ዘፋኞችን ዘፈን ሬሚክስ እያደረጉ በአዲስ አቀራረብ ሲያቀርቡ፡፡ እኔም እንደዚያው ነው ያደረግኩት፡፡ ሬሚክስ ያደረግኩት ደግሞ የምኒሊክን ባላባታዊ አስተሳሰብ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ጋር ነው፡፡ በአዲስ አቀራረብ ያልኩት ንግግሩን ልማታዊ፣ ሕዝባዊ፣ ፌዴራላዊ፣ ብዝኃነትን የያዘ አድርጌ ነው ያቀረብኩት፡፡›› አሉ ሊቀ መንበሩ፡፡
‹‹እና ዐፄ ምኒሊክን በአዲስ አቀራረብ አቀረቧቸው ማለት ነው›› አሉ ሽማግሌው፡፡
‹‹አዩ አባቴ ማዘመን ማለት ይኼ ነው፡፡ ታሪክን ማረም ይገባል፡፡ አዲስ መፍጠር ካልተቻለ የነበረውን ሬሚክስ እያደረጉ በአዲስ አቀራረብ ማቅረብ ነው፡፡ ሕዝቡም የሚወደው ይኼንን ነው›› አሉና ወደ ሕዝቡ ሲመለከቱ ጎረምሶቹ ‹‹ሼባው አቦ ተወና፣ እኛ ተመችቶናል›› አሏቸው ሽማግሌውን፡፡
ሽማግሌውም ‹‹በጦርነት ያልጠፋች ሀገር በሬሚክስ መጥፋቷ ነው በሉኛ›. ብለው ተቀመጡ፡፡ በአዲስ አቀራረብ በሬሚክስ ላስደሰቱን ለሊቀ መንበራችን ግን ጭብጨባው ቀለጠላቸው፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው
