ዳንኤል ክብረት
ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓም
ባሕርዳር
ለባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ማበልጸጊያ ተቋም ምሥረታ ማብሠሪያ ቀን የቀረበ የማሳሰቢያ ሐሳብ
ዩአን ሊ የተሰኘ ጃፓናዊ Breaking the message, በተሰኘው የ2006 ዓም መጽሐፉ ላይ እንዲህ ይላል፡፡ በኢንዶኔዥያ ገጠሮች ውስጥ በሠራባቸው 7 ዓመታት የታዘበው ትልቁ የሕዝብ ግንኙነት ችግር ለሕዝቡ መልእክት ለማስተላለፍ የሚመጡት ባለሞያዎች መልእክታቸው ተሟልቶ ወደ ሕዝቡ ለመድረስ አለመቻሉ ነው፡፡ ለዚህ ችግር መፈጠር ምክንያት ናቸው ያላቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው መልእክቱ ለሕዝቡ በሚመጥን መልኩ ተዘጋጅቶ አለመቅረቡ ነው፡፡ የሚተላለፈው መልእክት የአስተላላፊውን ማንነት፣ የዕውቀት ደረጃ፣ የፖለቲካ ጠገግ፣ የተማረውን የትምህርት ዓይነትና የአስተሳሰቡን መጠን የሚያሳይ እንጂ ለመልእክት ተቀባዩ ታስቦ በደረጃውና በመጠኑ የቀረበ አይደለም፡፡
‹‹ምንም እንኳን ሥጋ ሥጋ ቢሆንም ለሕጻንና ለዐዋቂ ግን በእኩል መጠንና ዓይነት አይቀርብም፡፡ ሕጻኑ ጥርሱና የምግብ ማዋሐጃ አካሉ ስላልጠነከረ በቀላሉ ሊፈጨው በሚችለው መጠን ሥጋው ደቅቆ መቅረብ አለበት፡፡ ለዐዋቂው ግን ሥጋው ጠንክሮና በቅመማ ቅመም ዳብሮ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ሥጋ ግን ሥጋ ነው›› ይላል ዩአን ሊ፡፡ መልእክት ሲቀርብም ከአቅራቢው በላይ የሚቀርብለትን ወገን ዐቅምና ችሎታ፣ ደረጃና ፍላጎት የመጠነ መሆን አለበት፡፡ ምንም የመልእክቱ ይዘት ባይቀየርም፡፡
ሌላው ለመልእክቱ መሰበር ምክንያት ነው ብሎ የታዘበው ነገር ምሁራኑና ሌሎችም ሕዝቡ በማይገባው ቋንቋ መናገራቸው ነው፡፡ አቅራቢዎቹ ለምዶባቸው ወይም እነርሱ የተማሩት በእንግሊዝኛ በመሆኑ ያለበለዚያም (እንደ እኛ ሀገር የኛ ሙሽራ ኩሪባቸው በእንግሊዝ አናግሪያቸው የሚለው ዘፈን እነርሱም ጋር አለ መሰል) እንግሊዝኛ መቀላቀል የዕውቀትና የደረጃ ማሳያ አድርገውት፣ እንግሊዝኛውን ከኢንዶኔዥያ ቋንቋ ጋር (በነገራችን ላይ ኢንዶኔዥያ 700 ሀገራዊ ቋንቋ የሚነገርባት ሀገር ናት፤ ብዙዉ ሰው ‹ባሐሳ ኢንዶኔዥያ› የተሰኘውን ብሔራዊ ቋንቋ ይናገረዋል፡፡) እየቀላቀሉ በሚያስፈልገውም በማያስፈልገውም ስለሚጠቀሙ መልእክቱ እየተሰበረ እንዲደርስ አድርገውታል፡፡
‹‹በቴሌቭዥን ኳስ ስንከታተል›› ይላል ዩአን ሊ ‹‹የኳሱን ፍሰት ሳይቋረጥ መከታተል እንፈልጋለን፡፡ የቴሌቭዥን ጣቢያው ይኼንን ትቶ በየመካከሉ ሙዚቃ እየጋበዘ ኳሱን ቢያስተላልፍልን የኳስ ጨዋታው ሙሉ ሥዕል አይኖረንም፡፡ ምናልባትም በመካከል ጎል ገብቶ፣ ተጨዋች በቀይ ወጥቶ፣ ግጭት ተፈጥሮ፣ ተጨዋች ተቀይሮ፣ አስደናቂ ወይም አሳዛኝ ክስተት ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህን ነገሮች አሳልፈን የምናየው ጨዋታ ግርታን ይፈጥራል እንጂ ደስታን አያመነጭም፡፡ በየመካከሉ ሕዝቡ የማይረዳውን ቋንቋ እየደባለቁ መልእክት ለማስተላለፍ መጣርም እንደዚሁ ነው፡፡ ድምፁን ለማስተላለፍ እንጂ መልእክቱን ለማስተላለፍ አይረዳም›› ይላል፡፡
እንዲያውም በአንድ በሰሜናዊ ኢንዶኔዥያ ክፍል ጥናት ሲያደርግ አንድ አዛውንት የነገሩትን እንደ ምሳሌ አስቀምጦታል፡፡ በዚያ መንደር ውስጥ አንድ የሕክምና ባለሞያ መጥቶ ለመንደሯ ሰዎች ስለ ኢንፍሉዌንዛ ገለጻ ያደርጋል፡፡ በገለጻው መካከል የአካባቢውን ቋንቋ ሱንዳኒዝንና እንግሊዝኛን እየደባለቀ ይናገር ነበር፡፡ መንደርተኞቹ ተቸገሩ፡፡ አንድ ሰውም ተነሡና ‹ልጄ፣ ወይ በእንግሊዝኛ ንገረንና ከመካከላችን ዕውቀቱ ያላቸው ይተርጉሙልን፤ ያለበለዚያ ደግሞ በአካባቢያችንን ቋንቋ በሱንዳኒዝ ንገረንና ያለ ችግር እንስማው›› ብለው አስተያየት ሰጡት፡፡ ከባለሞያው ይልቅ መንደርተኞቹ እንደሚቆራረጥ ስልክ መልእክቱ እየተሰበረ እንደደረሳቸው ገብቷቸዋል፡፡
አሁን አሁን በሀገራችን እየገጠመን ያለውም ልክ ዩአን ሊ በኢንዶኔዥያ የገጠመውን ዓይነት ነው፡፡ አማርኛን የሚናገር ሰው የጠፋ እስኪመስል ድረስ በአማርኛ መልእክት መለዋወጥ ከባድ እየሆነ ነው፡፡ የመልእክት ልውውጦቻችን በስሕተቶች የተ