(ክፍል ፭)
ባለፈው ከሳሚ ጋር ስለመጠለያ ጣቢያ ስንጨዋወት ስሙን መቀየር ስላልፈለገው ጓደኛቸው ያጫወተኝን እየነገርኩሽ ነበር ያቆምነው፡፡የሳሚ ታሪክ ይህንን ይመስላል፡፡ እሱን አንብቢና ስደተኛ በአውሮፓ የሚጠብቀውን ህይወት ገምቺ፡፡
ከዚያጊዚያዊ ካምፕ የመቆያዬን ጊዜ ጨርሼ ወደተመደብኩበት ቋሚ መኖርያ ስሄድ ካገሬ ሥሰደድ ያልተሸኘሁትን አይነት ሽኝት በዚያ ካምፕ ባገኘኋቸው ወገኖቼ ተደረገልኝ። በውድቅት ሌሊት የምሔድበት መኪና የሚቆምበት ቦታ ድረስ መጥተው መልካም ምኞታቸውን ገለጡልኝ። እኔም አፀፋውን መለስኩና ወደዚያ ከተማ ሄድኩ። ከነዚህ የአጭር ጊዜ ወዳጆቼ ጋር እስከአሁን እንደዋወላለን። ወዴት እንደሄዱ ሳላውቅ ደብዛቸው የጠፉም ሞልተዋል።
ከትልቁ ጊዚያዊ መጠለያ ወደዚያ ስንሄድ አንድ አበሻ ብቻ ነበር የማውቀው። እሱም ከኔው ጋር ተመድቦ በአንድ ባቡር አብሮኝ የነበረ ነው። እዚያ የደረስነው ጥር አጋማሽ ላይ ስለነበር የነበረው አየር እጅግ ይገርም ነበር። መሬት የሚባል ነገር አይታይም። በሙሉ ነጭ ነው፣ ዛፉም የእግዜር ስሪት አይመስልም፣ ከመንጣቱና ከቅርፁ የተነሳ ሰውሰራሽ ይመስላል። ብርዱ ለመግለፅ በሚያስቸግር መልኩ ተስፋ ያስቆርጣል።
ከባቡር እንደወረድን የመጠለያው ሰራተኞች ፎቷችን ያለበትን ወረቀት ይዘው ስለነበር ገና ከደረጃው ስንወርድ በስማችን እየጠሩ ተቀበሉን። ወደውጭ ባየሁት ነጭ መልክዓምድርና የሚያቃጥል ቅዝቃዜ የተፈጠረብኝን ስጋት ለማርገብ ስለከተማውና ስለምንኖርበት ቦታ እየተርበተበርኩ እንደምንም ብዬ በምችላት ጥቂት እንግሊዝኛ መጠየቅ ጀመርኩ። ሁኔታዬን የተረዳው ሰራተኛም “አይዞህ ሁሉም ሲመጣ እንዳንተው ይሆንና ትንሽ ሲቆይ ይለምደዋል” አለኝ።
ከመኪናው አስገብቶን ለ30 ደቂቃ ነዳው። ግራ በመጋባት አብሮኝ ካለው ልጅ ጋር ተያየን። ወዴት ነው የምትወስደን ብለን ጠየቅነው። “እዚሁ ነው! የናንተ መጠለያ ከከተማው ወጣ ይላል፣ አይዟችሁ ባካባቢው የሚኖር ማሕበረሰብ ስላለ የገበያ ችግር የለም” አለን።
ሶስት የዶከካቸው ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃዎች እንደመልክዓ ምድሩ ነጩን በረዶ ተሸከመው ተኝተዋል። በመካከላቸው ባለ ክፍት ቦታ ላይ እንደጨው ክምር የተቆለለ በረዶ ሶስተኛውን ሕንፃ ሸፍኖታል። የሰውየው መኪና እየተንደረደረ ሄዶ እዚህ ግዙፍ የበረዶ ክምር ስር አረፈ። አወረዱንና ቢሮው ወደሚገኝበት ወደመኻለኛው ሕንፃ አስገቡን። በስርዓት አስተናገዱን። የመጠለያውን ሕግ አነበነቡልን፣ ለሶስት እንድንኖር ብቻውን ይኖር ወደነበረ ወደ አንድ ኤርትራዊ ክፍል አመላከቱን። የክፍሉን ቁልፍና የምንበላውን እንድንገዛ ገንዘብ ሰጡን። ሁሉን ጨርሰን ቢሯቸውን ለቀን ወደውጭ ወጣን።
ስገባ አንድ ሕንፃ ብቻ ነበር ያየሁት፤ ስለ ሶስት ሕንፃዎች ሲነግረኝ ግር አለኝ ። ‘እዚህ ከመምጣትህ በፊት ሌላ ቦታ ኖረህ ነበር ማለት ነው?’ብዬ ጠየቅኩት።
አዎ፤ እዛ ሶስት ወር ኖሬ አመመኝ ብዬ ነው ወደዚህ የቀየሩኝ። አውቆ መታመም እችልበታለሁ፤ በስደተኛውም ዘንድ አውቆ ማበድና መታመም የተለመደ ነው። አመመኝ ብዬ ጠብ ስል ደንግጠው ወደዚህ መደቡኝ። ያ ቦታ በጣም ከባድ ነበር። ሰው የምርጫዎቹ ጥርቅም ነው ይባል ነበር። እዛ ተመድቤ የሄድኩ ቀን ግን እንዳልሆነ ታረዳሁ። እኔና ጓደኛዬም እንደተራራ በተከመረው በረዶ ስር ቆመን ተኮራረፍን፣ አብዝተን ተከዝን፣ ተስፋ ቆረጥን። ተስፋ ከመቁረጣችን የተነሳ የሚያቃጥለውን ብርድ ረስተን እውስጡ ተገትረን ቀረን። ወደምንሔድበት ግራ ገባን። ራቅ አድርገን ስናይ ከጎናችን ያለውን የበረዶ ክምር አብዝቶ የሚበልጥ ነጭ ተራራ እይታችንን ይገድበዋል። ቀና ስንል የከፋው ሰማይ ምን እንደያዘ’ንኳ እንዳያስታውቅ ሆኖ በቅርብ ርቀት በጉም ተጠቅጥቋል። የሚታዩን ሶስቱ ሕንፃዎች ድኃዋ አገራችን ላይ ለእህል መጋዘንነት የሚታነፁትን አይወዳደሩም። ውስጣቸው ያሉት ስደተኞች ለምንም ግድ ያላቸው አይመስሉም። ይወጣሉ ይገባሉ። በረዶውን በትልቅ ጫማቸው እየሰነጠቁ ያልፋሉ ያገድማሉ እኛም ላይ እንደትንግርት ያፈጣሉ።
ያንን መጠለያ ካለፈው የሚለየው የጥገኝነት ጥያቄ መልስ የሚሰጠን በዚህ ቦታ ተቀምጠን በመጠበቅ ነበር። ብዙ ጊዜ እንደሚያስጠብቁን ሳስበው ደግሞ ቦታው የበለጠ እየቀፈፈኝ ሄደ። ከዚህ የባሰ የሚያስጠብቁ አገሮች እንዳሉ ግን እሰማ ነበር። እዚያ የሚኖሩት ስደተኞች እንደበፊቱ ከብዙ አገር የመጡ አይደሉም። ከአፍጋኒስታን፣ ከኤርትራ፣ ከሶማሌ፣ ከኢራን፣ ከኢራቅና ከኮንጎ የተሰደዱ ይበዛሉ።
ቢሆንም ግን በዚያኛው መጠለያ አበሻው እራሱን አግሎ ለብቻው ነው የሚኖረው። እዚያ መጠለያ የሄድን ቀን ከቆምንበት የበረዶ ክምት ስር እንደተገተርን አንድ አበሻ መጣና ጨበጠን። ስሙንም ነገረን። ከመጣሁ ሰባት ወሬ ነው ሲለን እንደጀግና በተደሞ ተመለከትነው። እዚህ ነጭ ጫካ ውስጥ፣ የበረዶ ግግር መኃል ሰባት ወር! ጓደኛዬም አብሮኝ ተገረመ። መልስ አግኝቶ እንደሁ ስንጠይቀው አላገኘሁም አለን። እንዲያውም አመትና አመት ተኩል እምደሚያስጠብቁ አረዳንና እዛው ጥሎን ሄደ።
“ይሄ ደግሞ ምን ጋግርታም ነው፣ እንግዶች ነን፣ እቤት እንግባ’ንኳ አይልም ‘ንዴ” እያልን እየወረድንበት ባይናችን ሸኘነው። እየዘፈነ ጥሎን ሄደ። አማትረን አማትረን ያገኘነው ሰው ሰው አልሆን ሲለን ተያይዘን ጉዞ ጀመርን፣ ወደሱፐር ማርኬት። ባናውቀውም ይሆናል ብለን ወደገመትንበት አቅጣጫ መራመድ ጀመርን። መኪናዋ ይዛን ስትመጣ በረዶው ላይ የተወችውን የጎማ ምልክት ተከትለን መራመድ ጀመርን።
በነጩ ምድር ላይ ኮቴያችንን ሿ ሿ ሲል እየሰማን በፀጥታ ስንራመድ ሱፐር ማርኬት አገኘን። በቃ እንዲህ ጀመርነው ኑሮውን። ገዛዝተን ስንመለስ የተመደብንበት ክፍል ውስጥ የሚኖረውን ልጅ ከቤት አገኘነው። ቁጭ ብሎ እኛን ይጠብቃል። እንግዳ ይመጣብሓል ተብሎ የተነገረው ቀደም ብሎ ስለነበር አልጋችንን ብቻ ሳይሆን ምግባችንንም አዘጋጅቶልን ነበር የጠበቀን። አበሻዊ አቀባበል ሲገጥመን የገዛነውን ከነፌስታሉ ገለል አድርገን ክሽን አድርጎ ያሰራውን ዶሮ መብላት ጀመርን። እኛ ስለመጠለያው እየጠየቅነው፣ እሱ እየመለሰ በልተን ጨረስን። አንድ ኢትዮጵያዊና ብዙ ኤርትራዊ በመጠለያው እንደሚኖር ነግሮን ማታ ሊያስተዋውቀን እንደሚወስደን ነግሮን ክፍሉን ጥሎልን ውልቅ አለ። እኛም አመስግነን አልጋችንን ማንጠፍ ጀመርን።
‘ከኤርትራዊ ጋር ኖረኻላ? እንዴት ናቸው ኤርትራውያን? እንዴት ነበር አንተ የነበርክበት መጠለያ?’ ስለ ኤርትራውያን ስደተኞች ለማወቅ ያለኝን ጉጉት በጥያቄ መዓት በማቅረብ ገለፅኩለት።
እንዲህ ሲል መተረክ ጀመረ። እዚያ መጠለያ ውስጥ ሶስት ኢትዮጵያውያኖች ብቻ ነበርን። አንዱ ያ ጋግርታሙ ስለሆነ እንደሌለ ቁጠረው፣ አንዱ አብሮኝ የሄደው ልጅ ሲሆን ዘመድ አለው መሰል ወዲያው መጠለያውን ለቆ ወደከተማ ሄደ። እኔም ኬዜ ኤርትራዊ ስለሆነ ለመምሰል ጥረት አላደርግም። ኤርትራዊ ነኝ ማለት እንዴት እንደሚከብድ ይገርምሃል፤ ስጠየቅ ወይ ዝም እላለሁ ወይ ኢትዮጵያዊ ነበር የምለው። ታዲያልህ ለሶስት ወራቶች ስኖር የገጠሙኝ ስደተኞች በአብዛኞቹ ኤርትራውያን ናቸው። ከተሰደድኩ<