የአገሪቱ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከአቅም በታች እያመረቱ ነው

ዳንጎቴ የገነባውን ግዙፍ ሲሚንቶ ፋብሪካ በእጥፍ እንደሚያሳድግ አስታወቀ

በአገሪቱ ሲሚንቶ በማምረት የተሰማሩ 17 ፋብሪካዎች በኤሌክትሪክ ኃይል እጦት ሳቢያ፣ ከአቅማቸው ከግማሽ በታች እያመረቱ ነው፡፡ ሰሞኑን ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለው ዳንጎቴን ጨምሮ ዋና ዋና የአገሪቱ ፋብሪካዎች በአሁኑ ወቅት ማምረት የቻሉት በዓመት 5.4 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ብቻ ነው፡፡ 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው እንዳስታወቁት፣ በአገሪቱ ይመረታል ተብሎ የታቀደው የሲሚንቶ መጠን ከ17 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ነበር፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት ፋብሪካዎቹ ያመርታሉ የተባለው መጠን 11.2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሆን፣ ፋብሪካዎቹ ማምረት የቻሉት ግን 5.47 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ብቻ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ሲሚንቶ ወደ ሶማሊያ፣ ጂቡቲና ደቡብ ሱዳን እየተላከ እንደሆነ አቶ አህመድ አስረድተዋል፡፡

እነዚህን ፋብሪካዎች ይቀላቀላል ተብሎ የሚጠበቀው ዳንጎቴ፣ በዓመት 2.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሚንቶ የሚያመርተውን ፋብሪካ ሥራ ያስጀመረው ግንቦት 26 ቀን 2007 ዓ.ም ነው፡፡ በማግሥቱም የናይጄሪና የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ፋብሪካውን አስመርቋል፡፡ ከአዲስ አበባ 85 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ሙገር ከተማ አዳዓ በርጋ ወረዳ ውስጥ በ134 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈው ግዙፍ ፋብሪካ 600 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት መሆኑን ናይጄሪያዊው ቢሊየነር የዳንጎቴ ግሩፕ ሊቀመንበርና መሥራች አሊኮ ዳንጎቴ አስታውቀዋል፡፡ 

አሊኮ ዳንጎቴ አዲሱ ፋብሪካ ገና ሥራ ከመጀመሩ የእሱን ተመሳሳይ ፋብሪካ በተመሳሳይ ወጪ ለመገንባት መነሳታቸውንና የፋብሪካው ግንባታም በዚህ ዓመት ውስጥ እንደሚጀመር፣ ፋብሪካውን ለመመረቅ ለተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ለሌሎች ባለሥልጣናት ይፋ አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በበኩላቸው፣ አሊኮ ዳንጎቴ ተጨማሪ ማስፋፊያ ለማካሄድ መወሰናቸው እንዳስደሰታቸውና በግላቸውም የማስፋፊያ ፕሮጀክቱን ክትትል እንደሚያደርጉለት ለዳንጎቴ ቃል ገብተውላቸዋል፡፡ 

መቶ በመቶ ከራሳቸውና ከአገራቸው በተገኘ ገንዘብ ፋይናንስ ተደርጓል የተባለለት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ምርት መጀመር፣ በአገሪቱ በወቅቱ የተከሰተውን የሲሚንቶ እጥረትና የዋጋ ንረት ያረግባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከ400 ብር በላይ በኩንታል እየተሸጠ የሚገኘው ሲሚንቶ ከጥቂት ወራት በፊት በ230 ብር በችርቻሮ ገበያው ውስጥ ሲሸጥ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ዳንጎቴ ሲሚንቶ አንዱን ኩንታል በፋብሪካ ዋጋ በ207 ብር እንደሚያቀርብ ይፋ አድርጓል፡፡ በአገሪቱ ካሉት 17 ፋብሪካዎች በተጨማሪ 18ኛው ሆኖ የተመዘገበው ዳንጎቴ፣ 40 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት የሚያስችለው መሠረተ ልማት ተዘርግቶለታል፡፡ 

በአንፃሩ ሌሎች ትልልቅ ፋብሪካዎች በኃይል አቅርቦት እጦት ሳቢያ ከአቅማቸው በታች ለማምረት መገደዳቸው ይታወቃል፡፡ በሰኔ ወር በከፊል ማምረት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ የሚጠበቀው የግልገል ጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ችግር እንደሚያቃልል ተስፋ ተደርጓል፡፡ 

ዳንጎቴ ግሩፕ ምንም እንኳ በኢትዮጵያ ዕውን ያደረገው ፋብሪካ በምሥራቅ አፍሪካ ግዙፉ እንደሆነ ቢነገርለትም፣ በናይጄሪያ ያሉት ሦስት ፋሪካዎች በዓመት ከ20 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ሲሚንቶ ያመርታሉ፡፡ 

በሌላ በኩል በናይጄሪያው ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴ የሚመራው ዳንጎቴ ግሩፕ፣ በኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ የፖታሽ ማዕድን ምርት ላይ ለመሠማራት ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ መስጠቱን የማዕድን ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ዳንጎቴ ሲሚንቶ በምሥራቅ አፍሪካ ግዙፍ የተባለውን ፋብሪካ ሥራ ኢትዮጵያ ውስጥ አስጀምሯል፡፡ 

የማዕድን ሚኒስትሩ አቶ ቶሎሳ ሻጊ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ኩባንያው ፈቃድ እንዲሰጠው በደብዳቤ ጠይቆ ነበር፡፡ ሚኒስቴሩ ኩባንያው ያቀረበውን የፖታሽ ማዕድን የማምረት ፈቃድ ሲያጠና ቆይቶ እምነት የሚጣልበት ሆኖ በማግኘቱ፣ ያቀረበውን የፈቃድ ጥያቄ መቀበሉን አቶ ቶሎሳ ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ሦስት የውጭ ኩባንያዎች በፖታሽን ማዕድን ምርት ላይ በማሰማራት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ የማዕድን ሚኒስቴር ለመሥራት ቆርጠው የመጡ መሆናቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ ፈቃድ መስጠት አቋርጦ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ዳንጎቴ ፈቃድ መስጠት ከቆመ በኋላ ፈቃድ የተሰጠው ኩባንያ ሆኗል፡፡ 

‹‹ደብዳቤ አስገብተው ነበር፡፡ የዳንጎቴ ኩባንያ ባለቤት አገራችንን አምኗል፡፡ ይህን ሁሉ ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ሲያደርግ የሚሠራ ሰው መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ ስለዚህም ፈቃድ ልንሰጠው ወስነናል፡፡ ቦታውን ለይቶ እንዲያቀርብ እየጠበቅነው ነው፡፡ ልክ እንደ ሲሚንቶው በፖታሽም እንደሚሠራ ይጠበቃል፤›› በማለት አቶ ቶሎሳ ለዳንጎቴ ፈቃድ እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ በፖታሽ ማዕድን ላይ ለመሰማራት እየተንቀሳቀሱ ካሉት ሦስት የውጭ ኩባንያዎች በተጨማሪ ዳንጎቴ አራተኛው እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ 

ዳንጎቴ ግሩፕ በኢትዮጵያ አፋር ክልል በዳሎል አካባቢ በከፍተኛ ደረጃ ክምችት እንዳለው የሚታወቀውን የፖታሽ ማዕድን፣ በናይጄሪያ ለሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ ግብዓት ሊያውለው ይፈልጋል፡፡ ከዳንጎቴ በተጨማሪ የካናዳው አላና ፖታሽ የምርት ፈቃድ ማግኘቱን አቶ ቶሎሳ አስታውሰዋል፡፡ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የምርት ፈቃድ ያገኘው አላና ፖታሽ፣  የመሠረተ ልማትና የማምረቻ ፋብሪካ የመትከል ሥራ ማከናወን እንደሚጠቅበት፣ ሚኒስቴሩም ኩባንያው ይህንን ሥራ በወቅቱ ያከናውናል ብሎ እንደሚጠብቅ ገልጸዋል፡፡ 

የኖርዌይ ያራ ኢንተርናሽናል እህት ኩባንያው በሆነው ያራ ዳሎል ቢቪ አማካይነት ባቀረበው ጥናት መሠረት የምርት ፈቃድ ሊሰጠው መሆኑን፣ የፋይናንስ ችግር ስለሌለበትም በፍጥነት ማምረት ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥም የመሠረተ ልማት ሥራዎችን አጠናቆ ወደ ምርት እንደሚገባ ይታሰባል፡፡ ሦስተኛው የእንግሊዝ ኩባንያ የሆነው ሰርከም ሚነራልስ የሚባለው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የአዋጭነት ጥናቱን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተነግሮለታል፡፡ በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ የምርት ፈቃድ ለማግኘት ወደ ሚኒስቴሩ እንደሚመጣ አቶ ቶሎሳ ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ ቁንጮ ከበርቴ የሆኑት አሊኮ ዳንጎቴ በአንዳንዶች ዘንድ ‹‹ከብክለትና ከብድር የፀዳ›› እየተባለ ከተነገረለት የሲሚንቶ ፋብሪካቸው በተጨማሪ፣ በጥጥና በሸንኮራ አገዳ ልማት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ሆኖም የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ዳንጎቴ ጥናት ላይ በመሆኑ ያቀረበው የፈቃድ ጥያቄ የለም፡፡

ቢሊየነሩ አሊኮ ዳንጎቴ ከዓለም ሀብታሞች ተርታ ያሰለፋቸው የ20 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ የግል ሀብት ያላቸው ባለፀጋ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ 2018 ባለው ጊዜ ውስጥም 16 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ በ16 አፍሪካ አገሮች ውስጥ ያንሰራፏቸውን የንግድና የኢንቨስትመንት መስኮች እንደሚያስፋፉ፣ አዳዲሶችንም እንደሚገነቡ ይፋ አድርገዋል፡፡ በቀን 650 ሺሕ በርሜል ነዳጅ የማጣራት አቅም ያለውን ማጣሪያ ጨምሮ፣ ሦስት ሚሊዮን ቶን ዩሪያና አሞኒያ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ ዕውን ለማድረግ እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ 

እ.ኤ.አ. በ1996 ወደ አምራች ኢንዱስትሪዎች ፊታቸውን በማዞር በአፍሪካ ግዙፍ ግዛት የፈጠሩት አሊኮ ዳንጎቴ፣ በ20 ዓመታቸው ከአያታቸው በተበደሩት 500 ሺሕ ኒያራ (የናይጄሪያ መገበያያ ገንዘብ) በሲሚንቶ ንግድ ሥራ እጃቸውን አፍታትዋል፡፡ በሁለት ዓመት የሚከፍሉትን ገንዘብ በሦስት ወራት ውስጥ ለአያታቸው በመመለስ ስኬታማ የንግድ ጉዞ የጀመሩት ዳንጎቴ፣ ፎርብስ መጽሔት በሚያወጣው የሀብታሞች ዝርዝር ውስጥ ከአፍሪካ አንደኛው በመሆን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ 

 

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ የቀጣዩን ዓመት 223.4 ቢሊዮን ብር ረቂቅ በጀት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ካቀረቡ በኋላ፣ ምክር ቤቱ አፅድቆ ለፓርላማ ላከው፡፡ 

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ በ2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት በጀት 223 ቢሊዮን 397 ሚሊዮን 819 ሺሕ 216 ብር እንዲሆን ወስኗል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንን ከፍተኛ በጀት ተቀብሎ ካፀደቀ፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል፡፡ 

ይህ በጀት በ2007 ዓ.ም. ከተያዘው 178.6 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር በ44.8 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡ ነገር ግን ለደመወዝ ጭማሪ በዓመቱ መጀመሪያ በተያዘው በጀት ላይ ስምንት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ የበጀት ሥሌት ቀርቦ በመፅደቁ፣ የ2007 ዓ.ም. በጀት በአጠቃላይ 186.6 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡

ለ2008 ዓ.ም. ከተያዘው በጀት ትልቁ ለፕሮጀክቶች የተመደበው ነው፡፡ ከአጠቃላይ በጀቱ 37.4 በመቶ ለካፒታል ፕሮጀክቶች፣ 34.7 በመቶ የሚሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባቀረበው ቀመር ላይ ተመሥርቶ ለክልሎች የሚከፋፈል ነው፡፡ የበጀቱ 22.6 በመቶ ለመደበኛ ወጪዎች ይውላል፡፡ 5.4 በመቶ ደግሞ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ይውላል ተብሏል፡፡

ለክልሎች ከሚከፋፈለው በጀት የአዲስ አበባ አስተዳደር በቀጥታ ተቋዳሽ ባይሆንም፣ በተለይ ለግዙፍ ፕሮጀክቶች በፌዴራል መንግሥት አማካይነት ያገኛል ተብሏል፡፡ 

በተለይ በመጠጥ ውኃ፣ በቀላል ባቡር ትራንስፖርትና በተወሰነ ደረጃ ለቤቶች ልማት በጀት እንደሚመደብለት ታውቋል፡፡ 

ይህ በጀት ይሸፈናል ተብሎ የሚጠበቀው በተለይ ከአገር ውስጥ የገቢ ምንጮች፣ ከዕርዳታና ከብድር ነው፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በየዓመቱ የሚያቀርበው በጀት እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሚጀመርበት 2008 ዓ.ም. የቀረበውም በጀት በአገሪቱ ታሪክ ትልቁ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህንን በጀት በማስፈጸም በኩል ዘንድሮ በተካሄደው ምርጫ መንግሥት መመሥረቱን ያረጋገጠው ኢሕአዴግ የሚያዋቅረው አዲስ ካቢኔ ኃላፊነት ይሆናል ተብሏል፡፡ 

 

የቀድሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት ቅጣት ተቀንሶላቸው ከእስር ተፈቱ

ጥፋተኛ የተባሉበት የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ፀንቷል

ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀም የሙስና ወንጀል ተከሰው ሰባት ዓመታት ጽኑ እስራትና 20 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት የተጣለባቸው የቀድሞው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ያረጋል አይሸሹም፣ ከሦስት ዓመታት የእስር ቆይታ በኋላ ቅጣቱ ተቀንሶላቸው ግንቦት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ከእስር ተለቀቁ፡፡

አቶ ያረጋል በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር በነበሩበት ወቅት ከፌዴራል መንግሥት በተሰጠ የበጀት ድጎማ ከክልሉ በጀት የግልገል በለስ መምህራን ኮሌጅ፣ የጣና በለስ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤትና የአሶሳ የቴክኒክና የሙያ ማሠልጠኛ ተቋማትን  ለማስገንባት በክልሉ የወጣውን የግዥ መመርያ ቁጥር 1/1992 አንቀጽ 9.1 እና 2 ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ ግዥ እንዲፈጸም፣ የሦስቱ ፕሮጀክቶች ጨረታ ያላግባብ እንዲሰጥ አድርገዋል በሚል ግብረ አበሮቻቸው ከተባሉ ጋር መከሰሳቸው ይታወሳል፡፡

የሥር ፍርድ ቤት የቀረቡለትን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች መርምሮ እንዲከላከሉ ካደረገ በኋላ፣ የዓቃቤ ሕግን ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ በማለት ቅጣቱን ወስኖባቸው ነበር፡፡

አቶ ያረጋል በሕዝብና በመንግሥት ጥቅም ላይ ጉዳት በማድረሳቸው የሰባት ዓመታት ጽኑ እስራትና የ20 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት ሲጣልባቸው፣ የሥር ፍርድ ቤት ፍርድን በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለው ነበር፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረበለትን አቤቱታ ተመልክቶ፣ ‹‹የሥር ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ የሚነቀፍ ሆኖ እንዳላገኘው ጠቁሞ ‹‹አያስቀርብም›› ብሎ መዝገቡን ዘግቶት ነበር፡፡ የሥር ፍርድ ቤቶች የሕግ ጥሰት ፈጽመዋል በማለት ለሰበር ሰሚ ችሎት የመጨረሻ አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡

ለሰበር ችሎቱ ባቀረቡት አቤቱታ እንዳስረዱት በወንጀል ድርጊት እንዲጠየቁ የተደረገው ተገቢ ማስረጃ በዓቃቤ ሕግ በኩል ስላልቀረበ ነው፡፡ ከወንጀል ተጠያቂነት መርህ መንፈስና ይዘት ውጪ ነው ብለዋል፡፡ የመከላከያ ማስረጃቸው ይዘት ውድቅ የተደረገውም ያላግባብ እንደሆነ፣ የእስራት ቅጣቱም በወቅቱ ያለውን የቅጣት መመርያ መሠረት ያላደረገ መሆኑን፣ እሳቸው ያቀረቧቸው የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች የታለፉት ያላግባብ መሆኑን ዘርዝረው የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሻርላቸው ወይም እንዲስተካከልላቸው ጠይቀው ነበር፡፡

አቶ ያረጋል የተከሰሱት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) (ለ) በዋና ወንጀል አድራጊነት በአንቀጽ 33 በወንጀል ድርጊቱ በዋናነት በመሳተፍና በአንቀጽ 407 (1) (ሀ) (ለ)፣ (2) እና (3) ሥልጣንን አለግባብ መጠቀም ወንጀሎች ነበር፡፡ ወንጀሉን ክደው በመከራከራቸው ከሳሽ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹንና የሰነድ ማስረጃዎቹን አቅርቦ ወንጀሉን መፈጸማቸውን ማረጋገጡን የሥር ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ ተረጋግጧል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱም የክርክር ሒደቱንና ውሳኔውን አልተቃወመውም፡፡ የመመርመርም ሥልጣን እንደሌለውም አስታውቋል፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤት የወንጀል ቅጣቶችን የሚወስነው የወንጀል አድራጊውን የሕይወት ታሪክ፣ ወንጀል ለመፈጸም ያነሳሱትን ምክንያቶችንና የሐሳቡን ዓላማ፣ የግል ኑሮውን ሁኔታ፣ የትምህርት ደረጃውን፣ የወንጀሉን ከባድነትና የአፈጻጸሙን ሁኔታዎች በማመዛዘን መሆኑን ጠቁሟል፡፡

የወንጀል ሕጉንና የቅጣት መመርያውን ያገናዘበ መሆኑን የሥር ፍርድ ቤት ከሰጠው ውሳኔ መገንዘቡን የገለጸው ሰበር ችሎቱ፣ መነሻ ቅጣቱ ከተወሰነ በኋላ መጠኑ መሰላት ያለበት ሕጉ ስለቅጣት አወሳሰን የተመለከቱትን ድንጋጌዎች፣ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወጣው የቅጣት አወሳሰን መመርያም እንደሚያሳይ ጠቁሟል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በአቶ ያረጋል ላይ የቅጣት ማክበጃ አለማቅረቡን የሥር ፍርድ ቤት ማረገገጡን ሰበር ችሎቱ ገልጾ፣ ቅጣቱን በተሻሻለው የቅጣት አወሳሰን መመርያ ማስላቱ ግን የሕግ ስህተት መሆኑን አስረድቷል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ቅጣቱን ሲወስን የቅጣት ውሳኔ የሚመጣው የጥፋተኝነት ውሳኔ ሲሰጥ መሆኑንና የጥፋተኝነት ውሳኔ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ቆይቶ ሊወሰን የሚችል በመሆኑ፣ የጥፋተኝነት ውሳኔ በተሰጠበት ጊዜ በሥራ ላይ ያለው የቅጣት አወሳሰን መመርያ ተፈጻሚነት ሊኖረው ይገባል የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱ አግባብ አለመሆኑን ሰበር ችሎቱ በፍርዱ ተችቷል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 (1) እና ኢትዮጵያ ተቀብላ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ስምምነት አንቀጽ 14 (2) (ሐ)፣ በአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀጽ 7 (1) (መ) መሠረት አንድ ተከሳሽ የተፋጠነ ውሳኔ የማግኘት መብት ያለው ስለመሆኑ የተደነገጉትን ድንጋጌዎች፣ የሥር ፍርድ ቤት በውሳኔው አለማገናዘቡን በመጥቀስ ሰበር ችሎቱ ተችቷል፡፡

አቶ ያረጋል ክስ የተመሠረተባቸው ጥቅምት 20 ቀን 2004 ዓ.ም. መሆኑን የጠቆመው ሰበር ችሎቱ፣ ክሱ በቀረበበት ወቅት የነበረው የቅጣት አወሳሰን መመርያ ቁጥር 1/2002 መሆኑን ገልጿል፡፡ ይኼ መመርያ በቁጥር 2/2006 መሻሻሉንም እክሏል፡፡ መመርያው ቁጥር 1/2002 የቅጣት ማቅለያ በሚያስቀንሰው እርከን ላይ የእርከን ቅጣት መጠኑን መሠረት አድርጎ ቅጣትን የሚቀንስ ሲሆን፣ የተሻሻለው መመርያ ቁጥር 2/2006 ግን የማቅለያ ምክንያቶች በሚያስቀንሱት የእርከን መጠን ላይ ያደረገው ልዩነት አለመኖሩን ሰበር ችሎቱ በፍርዱ አስቀምጧል፡፡ በቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች ምላሽ የእርከን አቀናነስ ላይ መመርያ ቁጥር 1/2002 ከመመርያ ቁጥር 2/2006 የተሻሻለና አቶ ያረጋልን የሚጠቅም መሆኑንም ሰበር ችሎቱ አስረድቷል፡፡ ከወንጀል ሕግ አንቀጽ ስድስትና ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ አንፃር የተሻለው መመርያ ተፈፃሚነት አንዲኖረው እንደሚገባ በሰበር ችሎቱ የተለያዩ መዝገቦች የሕግ ትርጉም እንደተሰጠበት አስታውሶ፣ ለአቶ ያረጋል አይሸሹም የቅጣት አወሳሰን መመርያ 1/2002 የተሻለ ሆኖ በማግኘቱ የሥር ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ የሕግ ስህተት ፈጽሞ እንዳገኘው አስታውቋል፡፡

ሌላው የፍርድ ቤት ለአቶ ያረጋል ከያዘላቸው ሦስት የቅጣት ማቅለያዎች በተጨማሪ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነው በሚሠሩበት ወቅት ለረዥም ጊዜ ሕዝብንና መንግሥትን ማገልገላቸው የራሱ የሆነ ዋጋ ያለው አገልግሎት እንጂ በደፈናው ‹‹የኃላፊነት ግዴታ ነው›› ተብሎ በሥር ፍርድ ቤት የሚታለፍ አለመሆኑን ሰበር ችሎቱ ገልጿል፡፡ አቶ ያረጋል በአካባቢ ጥበቃና በአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ  ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ የመሪነት የሚናቸውን የተወጡ በመሆናቸው በወቅቱ ከአገሪቱ ፕሬዚዳንትና ከአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም የበላይ ጠባቂ ሽልማት የተቀበሉና ሌሎች ልማቶችን በአመርቂ ሁኔታ የፈጸሙ መሆናቸው፣ እንደ አንድ የቅጣት ማቅለያ ሊያዝላቸው እንደሚገባ ሰበር ችሎቱ ገልጿል፡፡ በድምሩ አራት የቅጣት ማቅለያ ሲያዝላቸው በመመርያ ቁጥር 1/2002 አንቀጽ 16(17) ድንጋጌ መሠት እያንዳንዱ የቅጣት ማቅለያ ሦስት እርከን የሚያስቀንስላቸው በመሆኑ፣ አቶ ያረጋል በ12 የቅጣት ማቅለያ የሥር ፍርድ ቤት ለቅጣት ከያዘው እርከን 27 ወደ እርከን 15 ወርዶ ቅጣቱ የሦስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲሆን ፍርድ ሰጥቷል፡፡ የገንዘብ መቀመጫውን እንደማይነካም አክሏል፡፡ የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች መሻራቸውንም አስታውቋል፡፡

 

በ120 ሚሊዮን ብር ወጪ በለቡ ኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ የተገነባው የግል የቆርኪ ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታው ተጠናቆ ማምረት መጀመሩ ተገለጸ፡፡ 

ጵንኤል ኢንዱስትሪ በተባለ ኩባንያ የተገነባው ፋብሪካ፣ አሁን ባለው የማምረት አቅም አንድ ቢሊዮን ቆርኪዎችን በዓመት እንደሚያመርት፣ በቅርቡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም አቅሙ 1.8 ቢሊዮን እንደሚደርስ ታውቋል፡፡ 

የኩባንያው ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሪት ብርቱካን በቀለ፣ ፋብሪካውን ገንብቶ ለመጨረስ ሁለት ዓመት እንደወሰደና 40 በመቶ የሚሆነው የግንባታ ወጪ ከኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በተገኘ ብድር መሸፈኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የለቡ ኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ ፋብሪካው 2,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ መገንባቱን ዋና ሥራ አስኪያጇ አስረድተዋል፡፡ ፋብሪካው ዓለም አቀፍ ጥራቱን እንዲያሟላ ተደርጎ የተገነባ መሆኑንና የእጅ ንክኪ ሳይኖረው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ቆርኪዎችን እንደሚያመርትም ወ/ሪት ብርቱካን አስታውቀዋል፡፡

ፋብሪካው ምንም ዓይነት ብክነት እንዳይኖረው ተደርጎ መገንባቱን፣ በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የምርት ሥራ እንዳይስተጓጎል የራሱ ጄኔሬተር ተተክሎለታል ብለዋል፡፡ 

ፋብሪካው በዋናነት ለአገር ውስጥ የቢራ፣ የለስላሳና የኮስሞቲክስ ውጤቶችን ለሚያመርቱ ፋብሪካዎች ምርቱን እንደሚያቀርብ፣ ከአጠቃላይ ምርቱ 40 በመቶ የሚሆነውን ወደ ጂቡቲና ፑንትላንድ የመላክ ዕቅድ እንዳላቸው ወ/ሪት ብርቱካን ገልጸዋል፡፡ 

ፋብሪካው ለ63 ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን፣ በቅርቡም መጠነ ሰፊ የማስፋፋት ሥራ እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡ ጵንኤል ኢንዱስትሪ በ2006 ዓ.ም. በ120,000 ብር የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ በአገሪቱ ሥራ ፈጣሪ ከሆኑ ሴቶች አንዷ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ወ/ሪት ብርቱካን፣ አልሙኒየምን ከመሳሰሉ ምርቶች የሚሠሩ የሕንፃ በርና መስኮቶች፣ መሰል ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል፡፡ 

በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ አምስት የቆርኪ ፋብሪካዎች ሲኖሩ፣ አጠቃላይ የማምረት አቅማቸው የምርቱን ፍላጎት ባለሟሟላቱ ዋና ዋና የመጠጥ አምራቾች ከውጭ አገር በብዛት ቆርኪ ለማስገባት መገደዳቸው ይነገራል፡፡ 

 

የፌዴራል ዋና ኦዲተር የፋይናንስ ሕጋዊነትን ያልተከተሉ ቢሊዮን ብሮች መኖራቸውን ይፋ አደረገ

እየተገነቡ ያሉ የባቡር ፕሮጀክቶች ችግሮችን ጠቆመ

-የደመወዝ ማስተካከያ እንዲደረግለት ፓርላማውን በአፅንኦት ጠየቀ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የፋይናንስ ሕጋዊነትን ያልተከተሉ ቢሊዮን ብሮችን ለፓርላማው ግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ይፋ አደረገ፡፡

የተሟላ ማስረጃ ሳይኖር በወጪ የተመዘገበ 368 ያልተወራረደ ሒሳብ መገኘቱን፣ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ውዝፍ ገቢ መኖሩንና ሌሎችንም ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ ለምክር ቤቱ አሳውቀዋል፡፡

ዋና ኦዲተር በ2006 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት በጀት ተጠቃሚ የሆኑ 135 መሥሪያ ቤቶችን ኦዲት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲትን ያልተከተሉ 78 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሕጉ መሠረት ያላወራረዱት ሁለት ቢሊዮን ሃያ አምስት ሚሊዮን ብር መኖሩን ጠቁሟል፡፡ በዚህ ያልተወራረደ ሒሳብ ተጠያቂ ከሆኑት መሥሪያ ቤቶች መካከል የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት 666.4 ሚሊዮን ብር፣ የትምህርት ሚኒስቴር 433.4 ሚሊዮን ብር፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር 144.2 ሚሊዮን ብር ሕጉን ባልተከተለ መልኩ ወጪ ማድረጋቸው ተጠቅሷል፡፡ 

ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች በወጣው ሕግና ደንብ መሠረት የመንግሥት ገቢ በወቅቱና በአግባቡ መሰብሰባቸውን ለማረጋገጥ፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና በሌሎች 12 ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች ላይ በድምሩ አንድ ቢሊዮን ብር ሰላሳ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ያልተሰበሰበ ገቢ መኖሩንም ዋና ኦዲተር ይፋ አድርጓል፡፡

በወጪ ለተመዘገቡ ሒሳቦች የተሟላ መረጃ መኖሩን ለማረጋገጥ ባደረገው ኦዲት በ29 መሥሪያ ቤቶች የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ፣ 368 ሚሊዮን ብር በወጪ ተመዝግቦ መገኘቱን ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ ገልጸዋል፡፡ 

ተሟልተው ካልቀረቡ ማስረጃዎች መካከልም ከዕቃ አቅራቢው የተሰጠ ማስረጃ ሳይቀርብ፣ ላቀረበው የክፍያ ጥያቄ ብቻ በወጪነት የተያዘ፣ ተራና አግባብነት የሌላቸው ደረሰኞች ማለትም የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር የሌላቸው ደረሰኞችንና የመሳሰሉትን ሕጋዊ ያልሆኑ ማስረጃዎች በመያዝ የተከፈሉ ወጪዎች እንደሚካተቱም ዋና ኦዲተሩ ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ (በ2006) መሥሪያ ቤቶች የፈጸሙት ክፍያ ትክክለኛነትን ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ በ19 መሥሪያ ቤቶች በተለያዩ ምክንያቶች የወጪውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያልተቻለ 473.469 ሚሊዮን ብር መኖሩን የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት ያሳያል፡፡ ከእነዚህም መሥሪያ ቤቶች መካከል ትልቁን ድርሻ ማለትም የ273.845 ሚሊዮን ብር ትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠ ወጪ የተመዘገበበት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት ነው፡፡

ይህ መሥሪያ ቤት ከደኅንነት ጋር የተያያዙ ግዥዎችን በተመለከተ ኦዲት ያለማስደረግ ሥልጣን ከዓመት በፊት በአዋጅ የተሰጠው ሲሆን፣ የዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝትም ይህንን መብቱን ያልጣሰ እንዲያውም ራሱ መሥሪያ ቤቱ ኦዲት መደረግ ይችላል ብሎ ያቀረበው ሰነድ ላይ የተደረገ ኦዲት ውጤት መሆኑን ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ለፓርላማው ግልጽ አድርገዋል፡፡ 

የዕቃ አገልግሎትና ግዥ በመንግሥት ደንብና መመርያ መሠረት የተፈጸመ መሆኑን ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ፣ በ63 መሥሪያ ቤቶች ሕግን ያልተከተለ የ957.5 ሚሊዮን ብር ግዥ መፈጸሙን ዋና ኦዲተሩ ገልጸዋል፡፡ 

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በአሁኑ ወቅት 98 በመቶ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ኦዲት የማድረግ አቅም ቢፈጥርም፣ ከዚህ ቀደም በኦዲት ያገኛቸው ችግሮች ዛሬም አለመፈታታቸው አሳሳቢ እንደሆነ አቶ ገመቹ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

‹‹በተለይ ረጅም ዓመታት ያስቆጠሩ ተሰብሳቢ ሒሳቦች፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ ግንባታዎችና ግዥዎች በልዩ ሁኔታ ሊታዩ የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን ማስገንዘብ እወዳለሁ፤›› ሲሉ ዋና ኦዲተሩ አሳስበዋል፡፡

የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ከፋይናንስ ሕጋዊነት በተጨማሪ የክዋኔ ኦዲት ማለትም የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሥራ አፈጻጸምን ከተሰጣቸው ኃላፊነትና ከአገሪቱ ሕጐች ጋር ያለውን መጣጣም በመገምገም ሪፖርት ያደርጋል፡፡ በዚህም መሠረት በ2006 ዓ.ም. የክዋኔ ኦዲት ከተከናወነባቸው መሥሪያ ቤቶች መካከል የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የመሠረተ ልማት ግንባታ አፈጻጸም ይገኝበታል፡፡

በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የመንግሥት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም መመርያ መሠረት መጀመርያ የፕሮጀክት ምርመራ እንደሚደረግ፣ ፕሮፋይል በተዘጋጀላቸው ፕሮጀክት ሐሳቦች ላይ ዝርዝር ጥናት ከመደረጉ አስቀድሞ የፕሮጀክት ረቂቅ ሰነድ ይዘጋጅና ቅድሚያ የሚሰጣቸው የፕሮጀክት ሐሳቦች ወደ ዝግጅት ሒደት እንዲገቡ ይደረጋል ቢልም፣ በኮርፖሬሽኑ እየተተገበሩ ያሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በ1999 ዓ.ም. በትራንስፖርት ሚኒስቴር መሪነት አጥኚ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ አማራጭ የየብስ ትራንስፖርትን አስመልክቶ ያደረገው ጥናት እንጂ፣ እያንዳንዱን ፕሮጀክት አስመልክቶ የተጠና የፕሮጀክት ጥናት ሰነድ አለመኖሩን ዋና ኦዲተሩ ይፋ አድርገዋል፡፡ 

የባቡር መሠረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች ክትትል፣ ቁጥጥርና ድኅረ ትግበራው በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የፕሮጀክት አዘገጃጀት ማኑዋል መሠረት ሊካሄድ የሚገባው ቢሆንም፣ በዚያ መልኩ እየተካሄደ አለመሆኑን የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት ያስረዳል፡፡

በመሆኑም በአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ግንባታ የሚያገለግል በኮንትራት ውሉ ውስጥ የተጠቀሱ ለግንባታ ሥራ፣ ለቁጥጥርና ክትትል አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችና ማኑዋሎች ለምሳሌ የጥራት ማረጋገጫ ማኑዋል የመሳሰሉትን ኦዲቱ እስከተከናወነበት ጊዜ ድረስ ኮርፖሬሽኑ ማቅረብ ባለመቻሉ፣ የፕሮጀክት ውሉ በሚለው የጥራት መሥፈርት መሠረት ፕሮጀክቱ እየተከናወነ መሆኑን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በፕሮጀክቶች የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ውስጥ የሚጠቀሱ ምክረ ሐሳቦች ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገባ ቢሆንም፣ ኮርፖሬሽኑ በሚዘረጋው የአዲስ አበባ ሚኤሶ መስመር ይህ እየሆነ አለመሆኑን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

ለአብነትም የባቡር መስመሩ በሚያልፍበት በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በርካታ የቱሪስት መተላለፊያ መንገዶችን ሳያስፈቅዱ መዘጋት፣ ያለፈቃድ መንገዶችን በፓርኩ ውስጥ እየቀደዱ ማውጣት፣ በፕሮጀክቶቹ የሚሠሩ የውጭ አገር ባለሙያዎች የዱር እንስሳትን ያለ ፈቃድ እያደኑ ለምግብነት የሚጠቀሙ መሆኑን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡

በሚኤሶ-ደወሌ የባቡር መስመር ዝርጋታ ያለውን የእሳተ ገሞራ መከሰት ሁኔታ ሊገመግም የሚችል ጥናት እንዲደረግ ኮንትራቱን የወሰደው ድርጅት ቢጠይቅም፣ በአካባቢው የላይኛው የመሬት ክፍል ላይ የመሬት መሰንጠቆች እየታዩ እሳተ ገሞራ የመከሰቱን ሁኔታ ሳያጠኑ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እንዲደረግ መፍቀዱ ተገቢ አለመሆኑን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ 

የባቡር ፕሮጀክቶች ሲተገበሩ ከኮንትራት ውሉ ውጪ ለሚጨመሩና ለሚቀነሱ ጉዳዮች ኮርፖሬሽኑ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አቅርቦ እንዲፈቀድ ማድረግ ሲገባው፣ ኮርፖሬሽኑ ግን የሰበታ ሚኤሶ ፕሮጀክት ከ1.639 ቢሊዮን ዶላር ወደ 1.841 ቢሊዮን ዶላር የኮንትራት ዋጋው ከፍ ሲል ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ቀርቦ ያልተፈቀደ መሆኑን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዳቢሶ የሪፖርታቸው ማጠናቀቂያ ላይ የቀረቡት የኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ እንዲደረግላቸው ፓርላማው መንግሥትን በማሳመን እንዲተባበር ነው፡፡

በፓርላማውና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በኩል በተደረጉ ጥረቶች ከሐምሌ 2006 ዓ.ም. ጀምሮ የመሥሪያ ቤቱ የደመወዝ ስኬል ከምርጫ ቦርድ እኩል እንዲሆን ቢወሰንም፣ በተመሳሳይ ጊዜ በተደረገው አጠቃላይ የሲቪል ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት እንዳይካተት በመደረጉ የተፈቀደው የደመወዝ ማስተካከያ የነበረውን ሠራተኛ የማረጋጋት ፋይዳ ሳያስገኝ መቅረቱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የተነሳ ከ60 በላይ የመሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሒሳብ ባለሙያዎች በአብዛኛው ቁልፍ ቦታ ላይ ይገኙ የነበሩ መሥሪያ ቤቱን ለቀው መሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡ 

በመሆኑም ጥራት ያለውና በርካታ መሥሪያ ቤቶችን የሚሸፍን የኦዲት ሥራ እንዲሠራ የሚፈለግ ከሆነ፣ መንግሥት የደመወዝ ማስተካከያ ማድረግ ይኖርበታል ያሉት ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ፣ ‹‹ፓርላማው በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንዲገባ›› በይፋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ባለሙያ ኦዲት የሚደረገው ሥራ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ሆኖ ሳለ ለዋና ኦዲተር የደመወዝ ጭማሪ የሚያደርገው ሥራ አስፈጻሚው መሆን እንደሌለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ስለሆነም ነፃነቱን ጠብቆ ሥራውን እንዲሠራ ጭማሪው ውሳኔ ማግኘት ያለበት በፓርላማው መሆን እንዳለበት ተከራክረዋል፡፡

ዋና ኦዲተሩ ላቀረቡት ፓርላማው ጣልቃ እንዲገባ የሚል ጥሪ ወዲያውኑ ምላሽ የሰጡት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ፣ በጉዳዩ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ከሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ላይ እንደሆኑና በቅርቡ ይፈታል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡  

 

 

የሰማያዊ ፓርቲ አባል ጽኑ እስራት ተፈረደበት

ሰባት አባላቱ ተከላከሉ ተባሉ

አይኤስ በሊቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን አረመኔያዊ ግድያ ለማውገዝ፣ መንግሥት ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠርቶ በነበረው የተቃውሞ ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ ፈጥረዋል›› ከተባሉት የሰማያዊ ፓርቲ

አባላት መካከል ናትናኤል ያለምዘውድ የተባለው አባል፣ በሦስት ዓመታት ከሦስት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ተፈረደበት፡፡

በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የቀረበለትን የወንጀል ክስ ሲሰማ የከረመው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ መናገሻ ወንጀል ችሎት በፍርዱ እንዳብራራው፤ ፍርደኛው ናትናኤል ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ አብዮት አደባባይ ሁከትና ብጥብጥ ፈጥሯል፡፡ ‹‹ወያኔ አረደን፣ ኢቲቪ ሌባ›› የሚል መፈክር በማሰማት፣ ከግብረ አበሮቹ ጋር መረበሹንም አመልክቷል፡፡ በፌዴራል ፖሊሶች ላይ ድንጋይ መወርወሩም ተመልክቷል፡፡ የሰዎችና በዕለቱ በሞባይል የተቀረፀ የቪዲዮ ማስረጃ ቀርቧል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ሁለት ምስክሮችን ካሰማ በኋላ ናትናኤል ተከላከል ቢባልም መከላከያ ምስክር እንደሌለው በመግለጹ፣ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ እንዳለው በፍርዱ ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሁለቱም ወገኖች የቅጣት አስተያየት እንዲሰጡ ጠይቆ፣ ዓቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ 

ተከሳሽ ናትናኤል በሰላማዊ ሠልፉ ላይ ብጥብጥ የፈጠረውን ቡድን መምራቱን፣ በሠልፉ ላይ የተገኙት ብዛት ያላቸው ስለነበሩ ብጥብጡ በፖሊስ ኃይል ባይበተን ኖሮ፣ ውጤቱ የከፋ ሊሆን ይችል እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ብጥብጡ ጠቅላላ ምርጫው ሊደረግ በነበረበት ዋዜማ የተደረገ ስለነበር ብጥብጡ አገር አቀፍ ሊሆን ይችል እንደነበር በመግለጽ፣ ቅጣቱ ከብዶ እንዲወስንለት ዓቃቤ ሕግ የክስ ማክበጃ ሐሳቡን ማቅረቡን ፍርዱ ያስረዳል፡፡

ፍርደኛው ናትናኤል ግን ‹‹ትምህርቴን አቋርጫለሁ፡፡ ለሚቀጥለው ዓመት እንድጀምር ይፈቀድልኝ፤›› ከማለት ባለፈ ያቀረበው የቅጣት ማቅለያ እንደሌለ ፍርድ ቤቱ ፍርዱን ሲያነብ ተሰምቷል፡፡ 

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ፍርድ ላይ እንደገለጸው፣ ፍርደኛው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 490 (3) ማለትም፣ ስብሰባን ወይም ጉባዔን የማወክ ጥፋት የተፈጸመው በቡድን ወይም የጦር መሣሪያ በመያዝ ከሆነ፣ ከሰባት ዓመታት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ የሚደነግገውን መተላለፉን ጠቁሟል፡፡ ፍርደኛው መንግሥት በሊቢያ ኢትዮጵያውያን የተፈጸመባቸውን አሰቃቂ ግድያ በተመለከተ ሕዝቡ ሐዘኑን እንዲገልጽና ተቃውሞውን እንዲያሰማ በጠራው ሠልፍ ላይ ድርጊቱን በመፈጸሙ፣ ብጥብጡ የተፈጠረው አገራዊ ምርጫ በሚደረግበት ዋዜማ ከመሆኑ አንፃር ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ቀላል ሊሆን እንደማይችል የሚያመለክት መሆኑን ጠቁሞ፣ የወንጀሉን ደረጃ ከባድ ብሎታል፡፡ 

ዓቃቤ ሕግ ፍርደኛው ከግብረ አበሮቹ ጋር በሚል ለማክበጃ የተጠቀመበትን ሐሳብ የወንጀሉ ማቋቋሚያ መሆኑን በመጠቆም፣ ማክበጃውን ውድቅ አድርጐበታል፡፡ ፍርደኛው የወንጀል ሪከርድ የሌለበት በመሆኑ አንድ ቅጣት ተቀንሶለት በሦስት ዓመታት ከሦስት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ 

ማትያስ መኩሪያ፣ ብሌን መስፍን፣ ተዋቸው ዳምጤ የተባሉ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና መሳይ የሚባል አንድ ወጣት በተመሳሳይ ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ዓቃቤ ሕግ ሁለት የሰው ምስክሮች ካሰማባቸው በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ 

ተከሳሾቹ የመከላከያ ምስክር ለማቅረብ የፈለጉት እርስ በርሳቸው ለመመሰካከር የነበረ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ በተመሳሳይ የክስ መዝገብ የተከሰሱ ምስክር መሆን እንደማይችሉ በመግለጽ ሌላ መከላከያ ካላቸው እንዲያቀርቡ አዟል፡፡ የመከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ለሰኔ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡   

በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተባቸው የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ወይንሸት ሞላ፣ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ኤርሚያስ ፀጋዬ፣ ማስተዋል ፍቃዱና ቤተልሔም አካለ ወርቅ በቀረበባቸው ተመሳሳይ፣ ‹‹ሰላማዊ ሠልፍን ማወክና ብጥብጥ ማስነሳት ወንጀል›› የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን በመከላከያ ምስክርነት ለማሰማት ለሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ተቀጥረዋል፡፡

 

 

ግድያውን ፈጽሟል የተባለው ተጠርጣሪ እጁን ሰጥቷል

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመቀሌ ዲስትሪክት የማይፀብሪ ቅርንጫፍ ዋና ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ፣ ስድስት የባንኩ ሠራተኞች ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በባንኩ የጥበቃ ሠራተኛ በጥይት ተገደሉ፡፡

ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. የተለመደ ሥራቸውን በማከናወን ላይ እያሉ፣ በባንኩ የጥበቃ ሠራተኛ በጥይት ተደብድበው የሞቱት የቅርንጫፉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወልዳይ ገብሩ፣ የባንኩ ኮንትሮለር አቶ አትንኩት ደምሴና የደንበኞች አገልግሎት ኦፊሰሮች የነበሩት ወ/ሮ ለምለም ግደይና አቶ አስማማው ገብረ ማርያም መሆናቸውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ አረጋግጠዋል፡፡ አቶ ንጉሤ ግርማና አቶ ጌትነት ባዩ የተባሉ በኮሜርሻል ኖሚኒስ አማካይነት የተቀጠሩ የባንኩ ሠራተኞችም መገደላቸውን አቶ ኤፍሬም አክለዋል፡፡

የባንኩ ሠራተኞችን በመግደል የተጠረጠረው የጥበቃ ሠራተኛ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሆኖ፣ ግድያውን ሊፈጽም የቻለበት ምክንያት እየተጣራ መሆኑን የገለጹት አቶ ኤፍሬም፣ ግድያውን የፈጸመው ግለሰብ የሥራ አፈጻጸሙን በሚመለከት ምክር፣ ተግሳጽና ማስጠንቀቂያ ከተሰጠው ከደቂቃዎች በኋላ መሆኑን መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጥበቃና የፅዳት ሠራተኞችን የመቅጠርና የመቆጣጠር ሥራን ለኮሜርሻል ኖሚኒስ መስጠቱን የጠቆሙት አቶ ኤፍሬም፣ የባንኩን ሠራተኞች በመግደል የተጠረጠረው ግለሰብም የተቀጠረው ከዚያው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ተጠርጣሪው በሥራው ላይ ተገቢ ያልሆነ ባህሪያትን በማሳየቱ በባንኩ ኃላፊዎች ቢመከርም ሊስተካከል ባለመቻሉ፣ የቅርንጫፍ ዋና ሥራ አስኪያጁ መቐለ ለሚገኘው የኮሜርሻል ኖሚኒስ ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ በመጻፍ፣ የጥበቃ ሠራተኛውን በሌላ እንዲተካላቸው ጠይቀው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ 

የኮሜርሻል ኖሚኒስ ኃላፊዎች በሠራተኞቻቸው ላይ ቅሬታ ሲደርሳቸው በቦታው በመገኘትና ሠራተኞቹንና የተቋሙን ኃላፊዎች በማነጋገር፣ ሠራተኛው ተገስጾና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ሥራውን እንዲቀጥል ወይም እንዲባረር እንደሚያደርጉ የገለጹት አቶ ኤፍሬም፣ ተጠርጣሪውም በዕለቱ ተመክሮ፣ ተገስጾና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት በዕለቱ ተረኛ ስለነበር መሣሪያውን ይዞ ወደ ሥራው መሰማራቱን ተናግረዋል፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ግን ሁለት የፍተሻ ሠራተኞችን አቁስሎ ሌሎቹን መግደሉን አስረድተዋል፡፡ 

የተገደሉት የባንኩ ሠራተኞች የቀብር ሥነ ሥርዓት መፈጸሙን ያስታወቁት አቶ ኤፍሬም፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ወልዳይ ገብሩ ቤተሰቦቻቸው በሚኖሩበት በዓደዋ ልዩ ስሙ ወርኢ ዳጋብር ቀብራቸው እንደተፈጸመም አክለዋል፡፡ ኮንትሮለሩ አቶ አትንኩት ደምሴ በትውልድ ሥፍራቸው ባህር ዳር የቀብራቸው ሥርዓት ተፈጽሟል፡፡ ወ/ሮ ለምለም ግደይና የኮሜርሻል ኖሚኒስ ሁለቱ ሠራተኞች አቶ ንጉሤና አቶ ጌትነት፣ በዚያው በማይፀብሪ ቀብራቸው ሲፈጸም፣ አቶ አስማማው ከማይፀብሪ በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ዲማ በሚባለው አካባቢ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡

ባንኩ በሠራተኞቹ ላይ በደረሰው ያልታሰበና ድንገተኛ አደጋ ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማው የገለጹት አቶ ኤፍሬም፣ ሠራተኞቹ መገደላቸው ከተሰማበት ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ቀብራቸው እስከተፈጸመበት ዕለት ድረስ፣ የመቀሌ ዲስትሪክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሻግሬ አስመላሽ በሥፍራው ተገኝተው ያደረጉት አስተዋጽኦም ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የንግድ ባንክ ጠቅላላ የጥበቃዎች ሥራ አስኪያጅም እዚያው ሆነው ጉዳዩን እየተከታተሉ መሆኑን አቶ ኤፍሬም አስታውቀዋል፡፡  

 

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የተካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ ውጤት እንደማይቀበሉት፣ ግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በየጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቁ፡፡

መኢአድ ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ምርጫውን አስመልክቶ በፕሬዚዳንቱ አቶ አበባው መሐሪና በሌሎች የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች መግለጫ ሲሰጥ፣ በምርጫው ወቅት ገጠመኝ ያላቸውን ችግሮችና ጫናዎች ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡

‹‹ባለፉት አራት ምርጫዎች በተከሰቱ ችግሮች ዙሪያ መፍትሔ አስቀምጦ ሙሉ በሙሉ ተሻሽሎ ይካሄዳል የሚል ዕምነት ቢኖረንም፣ ራሱን ሙሉ በሙሉ ወደ አምባገነንነት በቀየረው ገዥ ፓርቲ አፈና፣ ወከባ፣ እስራትና ግድያ የተነሳ ምርጫው ሳይሳካ ቀርቷል፤›› በማለት መኢአድ አስታውቋል፡፡

መኢአድ በምርጫው ዕለትና ከዚያ ቀደም ብሎ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ደረሰብኝ ያላቸውን ችግሮች ዘርዝሯል፡፡ ከአዲስ አበባ በስተቀር ኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎችን ጨምሮ አባላቱ መታሰራቸውንና ታዛቢዎቹ ከምርጫ ጣቢያ መባረራቸውን ገልጿል፡፡ 

‹‹ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና፣ ሰላማዊ እንደሆነ ይገለጽ እንጂ በተግባር የታየው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፤›› ብሏል፡፡ ‹‹ሰው እየደበደቡ፣ እያሰሩ፣ እያንገላቱ፣ ከመኖሪያ እያፈናቀሉና የግድ ንብን ምረጡ ብለው ለማስፈራራታቸው ተጨባጭ መረጃ ባለበት ሁኔታ እንዴት ብሎ ነፃ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ምርጫ እንደተካሄደ የሚያውቀው አፋኙ ሥርዓት ብቻ ነው፤›› በማለት መኢአድ በመግለጫው አስታውቋል፡፡ 

በምርጫው ምክንያት የታሰሩ የፓርቲ አባላትና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡ ‹‹ምርጫው ታዋቂ የሆኑ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችና ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆኑ የሲቪክ ማኅበራት ባልተገኙበት ኢሕአዴግ ባደራጃቸው የሲቪክ ማኅበራትና አባብሎ ወደ ታዛቢነት ያሰማራቸው የምርጫ ታዛቢዎች በተገኙበት የተካሄደ በመሆኑ፣ ይህንን የፖለቲካ ድራማ የተከናወነበት ምርጫ የማንቀበለው መሆኑን እናስታውቃለን፤›› በማለት መኢአድ መግለጫውን አጠቃሏል፡፡

የፓርቲውን የወደፊት አቅጣጫ በተመለከተ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አበባው ሲገልጹም፣ ‹‹ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር መክረን ዘክረን ወደፊት የምናሳውቀው ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡ 

በተመሳሳይም በዋና ጽሕፈት ቤቱ መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ)፣ የዘንድሮው ምርጫ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መካሄዱን ያስረዱልኛል ያላቸውን የተለያዩ ክስተቶች በማንሳት አስረድቷል፡፡ በፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮና በሌሎች ኃላፊዎች በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለጸው፣ ለምርጫ ቦርድ ፓርቲው ያቀረባቸው ዕጩዎች ቁጥራቸው ያለምንም አሳማኝ ምክንያት ተቀንሶ ፓርቲው በተወሰኑለት ዕጩዎች ብቻ እንዲወዳደር መደረጉ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮበታል፡፡

እንዲሁም በአማራ፣ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዕጩ ምዝገባ ወቅት፣ በቅስቀሳና በምርጫው ዕለት አጋጠሙኝ ያሏቸውን ችግሮች በባለ 6 ገጽ መግለጫው አስታውቋል፡፡ አብዛኛዎቹ ችግሮችም ከዕጩዎች አለመመዝገብ፣ ከአባላት መዋከብና መታሰር እንዲሁም የታዛቢዎች በሥፍራው ተገኝተው መታዘብ ከመከልከላቸው ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡

‹‹ጠጣር ግድፈቶች በተንፀባረቁበትና በተስተዋሉበት ሁኔታ የሕግ የበላይነት ተሟልቷል ተብሎ ከነጉድፉ መቀበል የፖለቲካ ቃር የሚያስይዝ ከመሆኑም በላይ፣ ከቀደምቶቹ ምርጫዎች 2002 እና 2005 (ማሟያና አካባቢያዊ) ባልተለየ መልኩ በአንድ ቅርጫት የተቀመጠ የቅድመ ምርጫ ሒደትና ውጤት በመሆኑ ፓርቲው አልተቀበለውም፤›› በማለት አስታውቋል፡፡ 

ቀጣይ አቅጣጫቸውን በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸውም ጥያቄ፣ ‹‹በትግል ደክመን ሳይሆን በመንግሥት ጫና ምክንያት መፈናፈን ባለመቻላችን ምንም እንኳን ዛሬ በዝረራ ብንወጣም፤ ዝረራው ግን ለነገው ቁጭት ጭሮብናል፤›› በማለት መልሰዋል፡፡ 

ፓርቲው ለወደፊቱ ሁለት አቅጣጫዎች ማዘጋጀቱን ገልጿል፡፡ አንደኛው ብሔራዊ መግባባትን ማስገኘት የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ መሥራት የሚሉ ናቸው፡፡

 

 

 

በቅርቡ ተጨማሪ የግንባታ ጊዜ የተሰጠው ሚድሮክ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ለዓመታት አጥሮ ባስቀመጣቸው 13 ቦታዎች ከመስከረም 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ግንባታ ለማካሄድ 18 ቢሊዮን ብር መመደቡ ታወቀ፡፡

 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እነዚህን ቦታዎች በሕጉ መሠረት መንጠቅ ቢኖርበትም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በጉዳዩ  ጣልቃ በመግባት በልዩ ሁኔታ ተጨማሪ የግንባታ ጊዜ እንዲሰጥ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በዚህ መሠረት የግንባታ ጊዜ የተጨመረለት ሚድሮክ በቦታዎቹ ላይ ግንባታ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ ነው ተብሏል፡፡

የሚድሮክ ባለቤትና ሊቀመንበር ሼክ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ የ13 ቦታዎች ግንባታ በመስከረም 2008 ዓ.ም. እንዲጀመር፣ ለሚድሮክ ኮንስትራክሽን መመርያ መስጠታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በ13ቱም ቦታዎች ላይ የሚሠሩት ሕንፃዎች ዲዛይንን ናሽናል ኮንሰልት ኩባንያ ከጣሊያንና ከስፔን ኩባንያዎች ጋር በጋራ የሠራ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄ እያቀረበ መሆኑ ታውቋል፡፡

የደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፕሮጀክቶቹን ግንባታ በመስከረም ወር ለማስጀመር ሙሉ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ሚድሮክ ለዓመታት አጥሮ የያዛቸው ቦታዎች ካዛንቺስ፣ ሜክሲኮ፣ ሳር ቤት፣ ፒያሳና ጉርድ ሾላን ጨምሮ በተለያዩ የከተማው ክፍሎች ይገኛሉ፡፡

እነዚህ ቦታዎች ቀደም ሲል የተሰጣቸው የግንባታ ጊዜ በማለፉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲነጠቁ የውሳኔ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ አስተዳደሩ እነዚህን የሚድሮክ 13 ቦታዎች ጨምሮ ታጥረው የተቀመጡ 109 ቦታዎች ላይ ስለሚወስደው ዕርምጃ ጥናት ማስጠናቱ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን አስተዳደሩ በሚድሮክ የተያዙትን ቦታዎች በተመለከተ መውሰድ ያለበትን ዕርምጃ እንዲያጠና ልዩ የባለሙያዎች ኮሚቴ አዋቅሮ አስጠንቷል፡፡

ኮሚቴው ባጠናው ጥናት ሚድሮክ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ብቻ መሠረት ያወጣ ቢሆንም፣ በአብዛኛዎቹ ቦታዎች ምንም ዓይነት ግንባታ አለማካሄዱን በመግለጽ ቦታዎቹ  ለሌሎች አልሚዎች እንዲሰጡ የውሳኔ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡

በዚህ መሠረት በተለይ በልደታ ክፍለ ከተማ ሜክሲኮ ዋቢ ሸበሌ አጠገብ የሚገኘውን ቦታ፣ በየካ ክፍለ ከተማ ደግሞ ጉርድ ሾላ በሻሌ ሆቴል አካባቢ የሚገኘውን ቦታ ካርታ አምክኗል፡፡ 

ነገር ግን ሼክ አል አሙዲ በቦታዎቹ ላይ ግንባታ ያልተካሄደው በሚድሮክ ብቻ ሳይሆን በከተማ አስተዳደሩ ጥፋት ጭምር ነው በማለት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ በእነዚህ ቦታዎች ላይ የሚያካሂዷቸው ግንባታዎች ግዙፍና ውብ በመሆናቸው ለከተማው ከፍተኛ ጠቀሜታ ስለሚኖራቸው የግንባታ ጊዜ እንዲራዘም ጠይቀዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከመከረ በኋላ የሼክ አል አሙዲ አላሙዲ ጥያቄ በልዩ ሁኔታ እንዲስተናገድ ወስኗል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለአዲስ አበባ ከተማ በሰጠው መመርያ መሠረት ሚድሮክ የውል ማሻሻያ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

 

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በ2008 በጀት ዓመት ለማከናወን ላቀዳቸው የመንገድ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ የበጀት ጥያቄ አቀረበ፡፡

ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ለ2008 ዓ.ም. የተጠየቀው በጀት ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡ በ2007 በጀት ዓመት ተፈቅዶለት የነበረው በጀት 30 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ 

የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለ2008 ዓ.ም. ከተጠየቀው በጀት ውስጥ ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው በኢትዮጵያ መንግሥት ይሸፈናል ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡ ወደ 11 ቢሊዮን ብር የሚሆነው በጀት ግን በውጭ የፋይናንስ ተቋማት የሚሸፈን ይሆናል ተብሎ የተቀመረ እንደሆነ አቶ ሳምሶን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ለዘርፉ የሚመድበው በጀት ማደግ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የበለጠ እንዲሳተፉ ይረዳል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በመንግሥት ከፍተኛ በጀት ከሚበጀትላቸው ተቋማት መካከል በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ሲሆን፣ ተጨማሪ በጀት በማስፈቀድም የሚታወቅ ነው፡፡

በየዓመቱ የሚፈቀድለት በጀት እየጨመረ የመጣው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ለ2008 በጀት ዓመት እንዲፈቀድለት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ያገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ሳምሶን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በ2007 በጀት ዓመት በአሥር ወራት ውስጥ 19 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለኮንትራክተሮች አስተላልፏል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ከ25.3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 1,529.4 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ናቸው፡፡ በ2008 በጀት ዓመትም ከ25 ያላነሱ አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ያስጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

 

ምርጫው ከምንጊዜውም የተሻለ ቢሆንም የሕግ ጥሰቶች እንደነበሩበት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለጸ

ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም ቢጠናቀቅምና በአንድ ምርጫ ጣቢያ 1,000 ሰዎች ብቻ መመረጥ ቢኖርባቸውም፣ ሕጉ ከሚያዘው በተቃራኒ በአንዳንድ ጣቢያዎች ከ1,000 በላይ ድምፅ ሰጪዎች

መመዝገባቸውና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካይ  ታዛቢዎች መጓደል፣ ከታዩ ችግሮች መካከል እንደሚጠቀሱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ግንቦት 22 ቀን 2007 ዓ.ም. የምርጫውን መጠናቀቅ አስመልክቶ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የዘንድሮው ምርጫ ከዚህ በፊት ከተካሄዱት ሁሉ የተሻለና ሰላማዊ እንደነበር ገልጾ፣ ከሁለት ሺሕ ጣቢያዎች በላይ ባደረገው ክትትል የተወሰኑ ስህተቶችን ማስተዋሉን ገልጿል፡፡

ዋና ኮሚሽነሩ አምባሳደር ጥሩነህ ዜና በሰጡት የቅድመ ሪፖርት መግለጫ፣ ኮሚሽኑ ከ45,000 በላይ የምርጫ ጣቢያዎች በ2,000 ያህሉ 200 ሠራተኞችን አሰማርቶ የምርጫውን ሒደት መገምገሙን ገልጸዋል፡፡ 

ኮሚሽነሩ በተለያዩ ጣቢያዎች በሕጉ መሠረት በአንድ ጣቢያ ከ1,000 ያልበለጡ ተመዝጋቢዎች ድምፅ መስጠት ሲገባቸው፣ ከዚያ በላይ ድምፅ የተሰጠባቸው አካባቢዎችን መታዘቡን በመግለጽ ለወደፊቱ መስተካከል እንደሚገባው በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች የተቃዋሚ ፓርቲዎችን የወከሉ ታዛቢዎች መጓደል በኮሚሽኑ ሠራተኞች ከተስተዋሉ እንከኖች እንደሚካተት ጠቁመዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባን በሚመለከት በምርጫ ሕጉ መሠረት በቂ ጊዜ ተሰጥቶት መከናወኑን፣ በአንዳንድ ፓርቲዎች ከሒደቱ ጋር ተያይዞ የቀረቡ ቅሬታዎችን ለመፍታት ቦርዱ ያደረገውን ጥረት በቅድመ ምርጫ ወቅት በበጐ ከታዩ ጥረቶች እንደሚካተት ኮሚሽኑ አውስቷል፡፡ በተጨማሪም በዘንድሮው ምርጫ የሴቶች ተመራጭነት ተሳትፎ በገዢው ፓርቲ ተወዳዳሪዎች ባለፈው ምርጫ ከነበረበት 28 በመቶ ወደ 37 በመቶ ከፍ እንዲል መደረጉ፣ ለዚህም ደግሞ ቦርዱ በገንዘብና በተለያዩ ድጋፎች ማበረታቻ መስጠቱንም በኮሚሽኑ ከተገለጹ በጎ ጎኖች ውስጥ ተካቷል፡፡

እንዲሁም ለፓርቲዎቹ የምርጫ ቅስቀሳ እንዲረዳ የአየር ጊዜና የኅትመት ሚዲያ ድልድል መደረጉ ለምርጫው መልካም አስተዋጽኦ ማድረጉን አምባሳደር ጥሩነህ አስረድተዋል፡፡ በአንፃሩ አንዳንድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰጣቸው የአየር ጊዜና የጋዜጣ ዓምዶችን በአግባቡ መጠቀም ያለመቻላቸው በቅድመ ምርጫ ወቅት ከታዩ ችግሮች ውስጥ እንደሚካተቱ ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡

በምርጫው ዕለትም ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት የምርጫ አስፈጻሚዎች ድምፅ የሚሰጠቱንም ሆኑ ሌሎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነቶች መወጣታቸውንና በአግባቡ ማጠናቃቃቸውን የኮሚሽኑ ቅድመ ሪፖርት ገልጿል፡፡ በተመሳሳይም በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተፈጠረውን የምርጫ ወረቀት እጥረትም በኮሚሽኑ ሪፖርት ተካቷል፡፡

በምርጫ ወቅት ለመራጩ ሕዝብ ስለአመራረጥ ግንዛቤ መስጠቱን ያወሱት ኮሚሽነሩ፣ አልፎ አልፎ ድምፅ አልባ የምርጫ ወረቀቶች እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡

በድኅረ ምርጫ ወቅት በሁለት ምርጫ ጣቢያዎች የኮሚሽኑ የክትትል ሥራን ባለመረዳት ባለሙያዎች የድምፅ ቆጠራውን መከታተል ባይችሉም፣ በሌሎች ኮሚሽኑ በመረጣቸው ጣቢያዎች የድምፅ ቆጠራውን በሚገባ ለመታዘብ ችሏል ሲሉ አምባሳደር ጥሩነህ ገልጸዋል፡፡

የድኅረ ምርጫ ሒደቱን አሁንም ቢሆን በኮሚሽኑ ክትትል እያደረገበት መሆኑን፣ እስካሁን ያለው ሒደትም ከምንጊዜው በበለጠ ሰላማዊ እንደሆነ ኮሚሽነሩ ማስተዋላቸውን አመልክተዋል፡፡

ነገር ግን በመላው አገሪቱ ከነበሩ ጣቢያዎች አምስት በመቶውን ብቻ ተከታትሎ ምርጫው ፍትሐዊና ነፃ ነው ብሎ መደምደም ተዓማኒነቱን ሊያመለክት ይችላል ወይ? የሚል ጥያቄም ለኮሚሽነሩ ቀርቦ ነበር፡፡ እሳቸውም ሲመልሱ፣ ‹‹በስታትስቲክስ የአሠራር ሕግ መሠረት አምስት በመቶ የሚሆን ናሙና በመውሰድ አጠቃላይ ድምዳሜ መድረስ ስለሚቻል፣ ባሰማራናቸው 200 ሠራተኞች 2,000 በሚሆኑ ጣቢያዎች ክትትል በማድረጋችን አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ ውጤት ላይ መደምደም ያስችላል፤›› ሲሉ መልሰዋል፡፡ ኮሚሽኑ የምርጫውን አጠቃላይ ሪፖርት በሰኔ ወር መጨረሻ ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡

 

ጦማሪ አቤል ዋበላ የእስራት ቅጣት ተፈረደበት

ፍርድ ቤት በመድፈር ወንጀል ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ጥፋተኛ የተባለውና በሽብር ወንጀል ተከሰው በክርክር ሒደት ላይ ከሚገኙት ጦማሪያን መካከል አንዱ የሆነው ጦማሪ አቤል ዋበላ፣ በአራት ወራት እስራት እንዲቀጣ ግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ተሰጠ፡፡ 

ተከሳሹ በሌሎች ቀጠሮዎች መልካም ፀባይ እንደነበረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ጠቁሞ፣ የአራት ወራት እስራቱን በሁለት ዓመታት ገድቦለታል፡፡

ጦማሪ አቤል ጥፋተኛ የተባለው ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ አዲስ ሲዲ ለፍርድ ቤቱ ሲያቀርብ፣ የቀረበው ሲዲ ‹‹የሚመለከተው ሶሊያና ሽመልስን ብቻ ነው? ወይስ እኛንም ያካትታል?›› የሚል ጥያቄ  ሲያቀርብ ፍርድ ቤቱ እንዳይናገር ሲከለክለው በመናገሩና ፍርድ ቤቱን ‹‹ራሳችሁ ሥነ ሥርዓት›› በማለት  ኃይለ ቃል ተናግሯል ተብሎ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

 

 

ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫውን ውጤትም ሆነ ሒደት እንደማይቀበል አስታወቀ

በዘንድሮ አምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ለመጀመርያ ጊዜ ተካፋይ የሆነው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የተካሄደውን ምርጫ ውጤትም ሆነ ሒደት እንደማይቀበል አስታወቀ፡፡

የፓርቲው ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ስለሺ ፈይሳና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በፓርቲው ጽሕፈት ቤት ለአገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፣ የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉት ያስታወቁት፡፡

‹‹ነፃነት በሌለባት ኢትዮጵያ ሕዝባዊ አስተዳደር መትከል ዘበት ነው›› በሚል ርዕስ በሰጠው መግለጫ ፓርቲው እንዳስታወቀው፣ የ2007ን ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ ሲወስን በዚህች አገር ገለልተኛና ብቃት ያላቸው ተቋማት እንደሌሉና ገዥው ቡድንም እውነተኛ ምርጫ እንደማይፈቅድ ግልጽ ማድረጉን፣ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ የተካሄደው ምርጫ ውጤትም ተቀባይነት የለውም ሲል በመግለጫው አስታውቋል፡፡

‹‹በሕገወጥ የአፈና ሥርዓት የተካሄደው የ2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ የሚያመለክተው ኢትዮጵያ አሁንም ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ልታካሂድ ቀርቶ፣ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ምርጫዎች ጋር እንኳን ሊወዳደር የሚይችል እጅግ ኢ-ፍትሐዊ፣ ወገንተኛና ተዓማኒነት የሌለው በመሆኑ ሰማያዊ ፓርቲ ሒደቱንም ሆነ ውጤቱን አይቀበለውም፤›› በማለት ሰማያዊ ፓርቲ አስታውቋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ከጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣ አመራሮቹም ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከተነሱ ጥያቄዎችም መካከል ቁጥራቸው ካልተገለጹ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮች የማሸነፍ ዕድል ይኖረናል የሚል ግምት አላችሁ ወይ የሚል የነበረ ሲሆን፣ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃል፣ ‹‹ያልተገለጹ መቀመጫዎችን ለማሸነፍ ምንም ተስፋ የለንም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ በመግለጫው፣ ‹‹ፓርቲያችን በዚህ አፈናና ጭቆና ውስጥ ከሕዝብ ለተሰጠው ክብር ያመሰግናል፡፡ በምርጫ ሒደቱ የተደበደባችሁና የተሰደዳችሁ የፓርቲያችን አባላትና ደጋፊዎች፣ ፓርቲያችን ዛሬ በኢትዮጵያ ሕዝብ ተዓማኒ፣ ተወዳጅና ተስፋ የተጣለበት እንዲሆን እናንተ ላይ የደረሰው መከራና በደል ትልቁን ድጋፍ ይወስዳልና ክብርና ምሥጋና ይገባችኋል፤›› ብሏል፡፡

‹‹የዜጎች ነፃነት ሳይከበር ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ሊደረግ ስለማይችል አሁንም ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታችን እስከሚከበሩ ድረስ ሰማያዊ ፓርቲ በሚያካሂደው የነፃነት ትግል ኢትዮጵያዊያን ከጎኑ እንዲቆሙ ይጠይቃል፤›› በማለት የፓርቲው መግለጫው ያትታል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ በበርካታ የምርጫ ክልሎች ከኢሕአዴግ በመቀጠል የመራጮችን ድምፅ ማግኘቱን፣ ከተለጠፉት የውጤት ማሳወቂያ ዝርዝሮች ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

በ2007 ጠቅላላ ምርጫ ተሳታፊ ለመሆን ወደ ፉክክር መድረኩ ገብቶ የነበረው የአዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) የምርጫ በጀት የት እንደገባ አለመታወቁን የፓርቲው ዕጩዎች ተናገሩ፡፡ 

በኦሮሚያ ክልል በኢተያ ምርጫ ክልል የፓርቲው ዕጩ የነበሩትን አቶ ተሾመ ደረሰን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎችም የፓርቲው ተወካዮች የነበሩት ግለሰቦች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አስፈላጊውን የምርጫ ፎርማሊቲ አሟልተው ወደ ምርጫ ፉክክሩ ከገቡ በኋላ በቅድመ ምርጫው ወቅት ምንም ዓይነት የምረጡኝ ቅስቀሳም ሆነ ማስታወቂያ ሳያከናውኑ የቀሩት፣ ፓርቲው የተመደበለት በጀት ሥራ ላይ ባለመዋሉ ምክንያት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ 

የፓርቲው ሊቀመንበር የነበሩት አቶ አስፋው ጌታቸው ውጭ አገር ከሄዱ በኋላ፣ በተወካዩ ግለሰብ እጅ የነበረው ገንዘብ ለምርጫ ተግባራት መዋል ሲገባው የውኃ ሽታ ሆኖ መቅረቱን አባላቱ ጠቁመዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ባከፋፈለው በጀት መሠረት የአዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) 487,999.03 ብር የደረሰው ሲሆን፣ ፓርቲው ግን በበርካታ ቦታዎች ዕጩ ተወዳዳሪዎችን በምርጫው ቀን ማቅረብ አለመቻሉ ታውቋል፡፡ 

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት ባልደረባ አቶ ደምሰው በንቲ፣ ቦርዱ ይህንን በተመለከተ ምንም ዓይነት ሪፖርት እስካሁን እንዳልቀረበለት ጠቁመው፣ ፓርቲው ግን አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልቶ ለምርጫው የተመዘገበ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የፓርቲው መሥራችና ሊቀመንበር እንደሆኑ የሚነገርላቸው አቶ አስፋው ጌታቸው በ1968 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ ተወልደው በግብርና ኢኮኖሚ ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በቢኤ ዲግሪ የተመረቁ መሆናቸው በፌስቡክ አካውንታቸው ላይ የሠፈረውና ፓርቲውን አስመልክቶ የተቀመጠው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ቀደም ሲል የነበረውን የፖለቲካ ሁኔታና አሁን ያለውን ገዥ ሥርዓት በማጣጣም፣ አዲሱ ትውልድ የሚኖረውን ሚና ከግምት በማስገባት እንደተቋቋመ የሚነገርለት አዲስ ትውልድ ፓርቲ ከተመሠረተ ሦስት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡

ለጊዜው በጉዳዩ ላይ ምንም ነገር ማለት እንደማይቻል ለሪፖርተር የገለጹት አቶ ደምሰው፣ ምርጫ ቦርድ የሚከታተለው ነገር ካለ ወደፊት የሚታወቅ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ ሪፖርተር በሊቀመንበሩ ተወክለዋል የተባሉትን ግለሰብ በተደጋጋሚ በስልክ ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ ግለሰቡ የስልክ ጥሪ ባለመመለሳቸው ምክንያት አልተሳካም፡፡

አቶ አስፋው አሜሪካ ከሄዱ ሁለት ወራት እንዳለፏቸው የሚገልጹት የፓርቲው አባላት፣ የመመለሳቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡  

 

የኮበለሉ መኮንንና አክራሪነትን ሰበኩ የተባሉ ሼክም ክስ ተመሥርቶባቸዋል

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ፕሬዚዳንት መሆናቸው የተገለጸውና አድራሻቸው በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ማክሰኝት ከተማ መሆኑ የተጠቀሰው አቶ ዘመነ ምሕረቱ ታከለ፣ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ግንቦት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

 

ተከሳሹ በሰው ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፈራረስ ዓላማ ካለውና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ግንቦት ሰባት ድርጅት ጋር አብረው ለመሥራት መስማማታቸውን፣ ክስ የመሠረተባቸው የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስፍሯል፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቱ መስከረም 18 ቀን 2007 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ በሚገኘው የመኢአድ ጽሕፈት ቤት ውስጥ አባላቱን በመሰብሰብ ‹‹የወያኔ መንግሥት መውደቂያው ደርሷል፡፡ አንድ የጦር አውሮፕላን፣ 12 የጦር ጄኔራሎች መንግሥትን ከድተው ወደ ኤርትራ ገብተዋል፡፡ ኢሕአዴግን በጦር ካልሆነ በሰላማዊ መንገድ ከሥልጣን አይለቅም፡፡ የሕዝብ እምቢተኝነትን በመፍጠር የወያኔን መንግሥት መጣል አለብን፡፡ በ2007 ዓ.ም. የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ አይካሄድም፡፡ ወደ ምርጫው አንገባም፡፡ ሌላ አማራጭ መጠቀም አለብን…›› በማለት ሕጋዊ አማራጮችን ትተው የኃይል አማራጮች ለመጠቀም ሲቀሰቅሱ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡ 

ምክትል ፕሬዚዳንቱ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቦምብ አወራወርና መሣሪያ መፍታት የሚችል በማነጋገርና በጥምቀት በዓል ላይ ተልዕኮ መፈጸም የሚችል ሰው ሲያፈላልጉ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ በአጠቃላይ ምክትል ፕሬዚዳንቱ የሽብር ዓላማን ለማራመድ በማሰብና የሽብርተኝነትን ድርጊት ለመፈጸም ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማሴርና ማነሳሳት ወንጀል መከሰሳቸውን የክስ ሰነዱ ያብራራል፡፡

ከመኢአድ ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር በአንድ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው፣ አድራሻቸው አዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ውስጥ መሆናቸው የተጠቆመው አቶ ጌትነት ደርሶ አዱኛ ናቸው፡፡ እሳቸውም የግንቦት ሰባት ድርጅት አባል በመሆን እንደ አቶ ዘመነ ምሕረቱ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም መንቀሳቀሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ 

ተከሳሹ ከድርጅቱ ጋር አብሮ ለመሥራት በመፈለግ ወደ ኤርትራ በመሸጋገር የግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራር ከሆኑት ዶ/ር ክፈተው አሰፋ ጋር በመገናኘት፣ ስለድርጅቱ ዓላማ ፖለቲካዊ ሥልጠና መውሰዳቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ በወታደራዊ ሥልጠና የመሣሪያ ተኩስ፣ የዒላማ ተኩስ፣ መከላከልና ማጥቃት በድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮችና በኤርትራ መንግሥት ወታደሮች መሠልጠናቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡ ተከሳሹ ለድርጅቱ አባላትን እንዲመለምሉና ወደ ኤርትራ ወታደራዊ ሥልጠና መስጫ ካምፕ እንዲልኩ የፌስቡክ አካውንት [email protected] የሚል አድራሻ እንደተሰጣቸውም ክሱ ያብራራል፡፡ በአጠቃላይ የሽብር ድርጅቱ አባል በመሆናቸው፣ በማንኛውም መልኩ በሽብርተኝነት ድርጅት ውስጥ መሳተፍ ወንጀል መከሰሳቸው የክስ ቻርጁ ያስረዳል፡፡ 

በተመሳሳይ የክስ መዝገብ ክስ የተመሠረተባቸው ሌላው  ተጠርጣሪ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ ውስጥ ነዋሪ መሆናቸው የተገለጸው አቶ መለሰ መንገሻ የተባሉ ግለሰብ ሲሆኑ፣ ራሱን የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ብሎ በሚጠራው ቡድን ውስጥ አባል ሆነው የተገኙ መሆናቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ጠቁሟል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በሰው ሕይወትና አካል ላይ ጉዳይ ለማድረስ መንቀሳቀሳቸውን፣ በትጥቅ ትግል ሥልጣን ለመያዝ ከሚንቀሳቀስ ቡድን ጋር ማበራቸውን፣ በኤርትራ አውሃጅራ አካባቢ ለሚንቀሳቀሰው የሽብር ቡድን ከፍተኛ አመራር ከሆኑት ግለሰብ ጋር በተለያዩ ጊዜያት በስልክ በመገናኘት አባላትን ይመለምሉ እንደነበር በክሱ ተካቷል፡፡ ተከሳሹ የኢትዮጵያ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሚበዙበት አካባቢ እንዴት ጥቃት መፈጸም እንዳለበት ለሽብር ድርጅቱ አመራሮች ገለጻ በማድረጋቸው፣ በሽብር ተግባር ላይ በመሳተፍ ወንጀል መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ 

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ግንቦት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ሌላው ክስ የመሠረተው የአየር ኃይል ባልደረባ በሆኑት ምክትል መቶ አለቃ አንተነህ ታደሰ ዘውዴ በተባሉት ተጠርጣሪ መኮንን ላይ ነው፡፡

ምክትል መቶ አለቃው ወደ ኤርትራ እንዲኮበልሉ ምክንያት የሆናቸው ቀደም ብሎ የአየር ኃይል ባልደረባ የነበረውና ባልታወቀ ምክንያት በጥቅምት ወር በ2007 ዓ.ም. ወደ ኤርትራ መሄዱ በተጠቀሰው ምክትል መቶ አለቃ ዳንኤል የሸዋስ ጋር በፌስቡክ በመገናኘት መሆኑን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ “Doni Yeshu Sweet” በሚል አድራሻና በተለያዩ ስልኮች ይገናኙ እንደነበርና ታኅሳስ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ከደብረ ዘይት አየር ኃይል በመነሳት ወደ ኤርትራ ጉዞ እያደረጉ መንገድ ከሚያሳያቸው ሌላ ሰው ጋር ታኅሳስ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ወሮታ ከተማ ላይ መያዛቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ ወንጀልም መከሰሳቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በተለያዩ የክስ መዝገቦች ክስ ከመሠረተባቸው ውስጥ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ቶንጎ ወረዳ ሻንቦላ ከተማ ሻንቦላ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ ነዋሪ መሆናቸው የተጠቀሰው ሼክ መሐመድ አብዱል ቃድር የሚባሉ ተጠርጣሪ ናቸው፡፡ 

ተከሳሹ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደርና ኅብረተሰቡን ለማስፈራራት የእስልምና ሃይማኖትን እንደ ሽፋን በመጠቀም፣ በኃይል እስላማዊ መንግሥት ለማቋቋም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ሼክ ሐመድ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቶጎ ወረዳ ጎሬ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ በሚገኙ መስጊዶች በመዘዋወርና ሙስሊሙን ማኅበረሰብ በማሰባሰብ፣ ‹‹እኛ የካዋርጃ እምነት ተከታይ መሆን አለብን፡፡ ለመንግሥት አትታዘዙ፡፡ ግብር አትክፈሉ፡፡ ጤና ጣቢያ ሄዳችሁ እንዳትወልዱ፡፡ ወላጆች ልጆቻችሁን ትምህርት ቤት አትላኩ፡፡ የእኛን አስተምህሮ የማይከተል ካፊር ነው፤›› ብለው በግልጽ በመናገር፣ ኅብረተሰቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይኖረው ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡

‹‹የሻንቦላና የአካባቢው ነዋሪዎች በአጠቃላይ መመራት ያለብን በሸሪዓ ሕግ ወይም እስላማዊ መንግሥት መሆን አለበት፤›› በማለት በመቀስቀስና የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማቀድ በማሴር፣ በማዘጋጀትና በማነሳሳት ወንጀል ሼኩ መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡

 

ለአፍሪካ ልማት ባንክ የተወዳደሩት አቶ ሱፍያን አህመድ ሳይመረጡ ቀሩ

የአፍሪካን ልማት ባንክን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ዕጩ ሆነው የቀረቡት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፍያን አህመድ ሳይመረጡ ቀሩ፡፡

ናይጄሪያዊ የግብርናና የገጠር ልማት ሚኒስትር የ55 ዓመቱ ኦኪንውሚ ኦዴሲና የባንኩ ፕሬዚዳንት አድርጎ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ግንቦት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. መርጧቸዋል፡፡

ባንኩን ላለፉት አሥር ዓመታት ሲያስተዳድሩት የቆዩትን ሩዋንዳዊውን ዶናልድ ካቤሩካን ለመተካት አቶ ሱፍያንን ጨምሮ ስምንት ዕጩዎች ቀርበው የነበረ ቢሆንም፣ በምርጫ ሥነ ሥርዓቱ አቶ ሱፍያን በሁለተኛ ዙር ከውድድር ውጪ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

አቶ ሱፍያን ቀደም ብሎ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ሆነው ባስመዘገቡት ስኬት የማሸነፍ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሚሆን ተጠብቆ ነበር፡፡ አቶ ሱፍያን ከ20 ዓመታት በላይ በመሩት ሚኒስቴር ካከናወኗቸው ዓበይት ተግባራት መካከል፣ በአገሪቱ ሲከሰት የነበረውን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ወደ ነጠላ አኃዝ በማውረድ ረገድ የተጫወቱት ሚና ይነገርላቸዋል፡፡ በአገሪቱ አዲስና የቅርብ ክስተት ከሆኑት ውስጥ፣ አገሪቷ በዓለም ቦንድ ገበያ ውስጥ ተሳታፊ መሆኗም ከሚጠቀሱላቸው ተግባራት መካከል ይካተታል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ አቶ ሱፍያን የባንኩ ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ የሆነውን ፈረንሳይኛ ቋንቋ መናገር የማይችሉ በመሆናቸው ከፍተኛ ፈተና ሊገጥማቸው እንደሚችል የገመቱም ነበሩ፡፡ በተለይ አንዳንድ የመስኩ ባለሙያዎች የፕሬዚዳንትነቱን ውድድር ለምዕራብ አፍሪካ አገሮች ተወካዮች የተሻለ ቅድመ ግምትን ሰጥተውም ነበር፡፡

በስምንተኛው የባንኩ ጉባዔ ላይ ይፋ በሆነው የምርጫ ሥነ ሥርዓት ላይ አሸናፊ በመሆን የተመረጡት ናይጄሪያዊው ኦዴሲና ‹‹ዛሬ ታላቅ ኃላፊነትን ተቀብያለሁ፤›› በማለት ደስታቸውን ከሚጠብቃቸው ኃላፊነት ጋር በማያያዝ ገልጸዋል፡፡

በቅድመ ምርጫ ወቅት ስምንቱ ዕጩዎች ለውድድሩ የየራሳቸውን ስኬትና አሸናፊ ከሆኑ ለባንኩ ይበጃል ያሉዋቸው ዕቅዶች አቅርበው ነበር፡፡ በተለይ አቶ ሱፍያን ኢትዮጵያ ላለፉት አሥር ዓመታት አስመዝግባዋለች ያሉትን የኢኮኖሚ ዕድገትና የገንዘብ ግሽበትን በመቆጣጠር ልማትን እንዴት ማፋጠን ያስችላል ያሉትን ዕቅድ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ካቤሩካ በበኩላቸው በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ለተተኪያቸው የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት በማስተላለፍ መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡ ‹‹ለተተኪዬ መልካሙን ሁሉ እመኝለታሁ፡፡ አሥር ዓመት በፍጥነት መሄዱን አይቻለሁ፡፡ እጅግ ውስብስብና ውጥረት የተሞላበት ሥራ ነበር፡፡ ቢሆንም ግን አስደሳች የሥራ ወቅት ነበር፡፡ በእርግጥ ይኼን ሥራ ብዬ ከምጠራው ተልዕኮ ብለው ይሻለኛል፤›› ሲሉ ባንኩን ለአሥር ዓመት ያስተዳደሩት ዶናልድ ካቤሩካ በባንኩ ስላሳለፉት የሥራ ዘመን ተናግረዋል፡፡

 

በፕሮቪደንት ፈንድ የታቀፉ የግል ድርጀት ሠራተኞች ወደ ግል ድርጅቶች ጡረታ እንዲዘዋወሩ የሚያስገድድ ማሻሻያ አዋጅ ተረቀቀ፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጪው ሳምንት ይወያይበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 715/2003 በሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም. ተግባራዊ መሆን ከመጀመሩ በፊት፣ የፕሮቪደንት ፈንድ ሽፋን ያላቸው የግል ድርጅት ሠራተኞች በነበራቸው የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚነት ለመቀጠል እንዲወስኑ፣ ወይም በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ስለሚሸፈኑበት ሁኔታ ሊስማሙ እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡

ይሁን እንጂ በሠራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን ላይ ልዩነት እንዳይኖር ለማድረግ ሲባል፣ ይኼንንና ሌሎች አንቀጾችን የሚያሻሽል ረቂቅ በግል ድርጅቶች ሠራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ተዘጋጅቶ ለፓርላማው ተልኳል፡፡

በፕሮቪደንት ፈንድ ይሸፈኑ የነበሩ ሠራተኞችን አንድ ወጥ ወደሆነው የግል ሠራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና ማምጣት ያስፈለገው፣ ዜጎችን በአንድ የማኅበራዊ ዋስትና ሥርዓት ውስጥ ተጠቃሚ ማድረጉ በዜጎች መካከል የሚኖረውን የመብትና የጥቅም ልዩነት የሚያስወግድ በመሆኑ እንደሆነ የረቂቅ ማሻሻያ አዋጁ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሠራተኛው በነበረው የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚነት እንዲቀጥል ማድረጉ የሠራተኛውን ተተኪዎች (ልጆችና ቤተሰቦች) የዘለቄታ የማኅበራዊ ዋስትና መብትና ጥቅም የሚያሳጣ በመሆኑ መሻሻሉ አስፈላጊ እንደሆነ ማብራሪያው ይጠቅሳል፡፡

በመሆኑም ከሰኔ 16 ቀን 2003 ዓ.ም. በፊት ተቀጥረው ይሠሩ በነበሩት የግል ድርጅቶች ውስጥ የጡረታ ወይም የፕሮቪደንት ፈንድ ሽፋን የነበራቸውና በዚሁ በነበራቸው የጡረታ ወይም የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚነታቸውን የቀጠሉ ሠራተኞች በግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ ሥርዓት እንዲሸፈኑ ማሻሻያ ረቂቁ መቅረቡን ያስረዳል፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ማሻሻያ የሃይማኖት ድርጅቶች ሠራተኞች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ሠራተኞችና መደበኛ ባልሆነ የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሰዎች በፈቃደኝነት ላይ ተመሥርተው የግል ድርጅት የማኅበራዊ ዋስትና ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡

በፕሮቪደንት ፈንድ ወይም ቀድሞ በነበራቸው ጡረታ ለመቀጠል ተስማምተው ሲቆጥቡ የነበሩ ሠራተኞች ፈንድ፣ ወደ ግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ ፈንድ እንደሚዘዋወር ረቂቅ ማሻሻያው ያስረዳል፡፡ ይህ ቢሆንም በፕሮቪደንት ፈንድ የቆጠቡት ወደ ግል ድርጅቶች ጡረታ ፈንድ በሚዘዋወርበት ጊዜ፣ በፕሮቪደንት ፈንዱ የተቀመጠው ከሚገባው መጠን በላይ የተከፈለ ከሆነ ልዩነቱ ለሠራተኞች ተመላሽ እንደሚደረግ ማሻሻያ ረቂቁ ይገልጻል፡፡

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ፓርላማው በቀጣዩ ሳምንት ተወያይቶ ረቂቁን ለተጨማሪ ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

ምርጫ ቦርድ ማጣራት አደርጋለሁ ብሏል

የተሻሻለው የምርጫ ሕግ በአንድ የምርጫ ጣቢያ መመዝገብና መምረጥ ያለበት መራጭ ከአንድ ሺሕ በላይ መሆን የለበትም ቢልም፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በርከት ያሉ የምርጫ ጣቢያዎች ከአንድ ሺሕ በላይ ነዋሪዎችን በማስመረጥ ሕጉን

መጣረሳቸው ታይቷል፡፡ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፣ ‹‹እኛ የምናውቀው በሁሉም ምርጫ ጣቢያ አንድ ሺሕና ከዚያ በታች መራጭ መመዝገቡንና መምረጡን ነው፡፡ የተባለውን ስህተት አጣራለሁ፤›› ብሏል፡፡

ይኼንኑ ችግር የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድን ግንቦት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ጊዜያዊ ሪፖርቱ ጠቁሞታል፡፡ የሪፖርተር ዝግጅት ክፍል ያሰማራቸው ጋዜጠኞችም በአንድ የምርጫ ጣቢያ ከአንድ ሺሕ በላይ መራጮች መሳተፋቸውን በማስረጃ ማረጋገጥ ችለዋል፡፡

የሪፖርተር ጋዜጠኞች ከጎበኟቸው የምርጫ ጣቢያዎች መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ የተወዳደሩበት በኦሮሚያ አርሲ ዞን ምርጫ ጣቢያ ኢተያ 01-2ሀ-1 ማሳያ ነው፡፡

አቶ አባዱላ ከላይ በተገለጸው የምርጫ ጣቢያ 1,214 ድምፅ በማግኘት አንደኛ ደረጃ ሲይዙ፣ የኦብኮ ተፎካካሪያቸው ደግሞ 10 ድምፅ አግኝተዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ምርጫ ጣቢያ ብቻ 224 መራጮች ከሕጉ በተቃራኒ ተሳትፈዋል፡፡

በፓርላማው የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በተወዳደሩበት በስልጤ ዞን ዱና ምርጫ ጣቢያ በብቸኝነት ተወዳድረው 1,459 ድምፅ አግኝተዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ምርጫ ጣቢያ ከሕጉ በተቃራኒ 459 መራጮች ተስተናግደዋል ማለት ነው፡፡ ወ/ሮ ሙፈሪያት በተወዳደሩበት ሌላ ምርጫ ጣቢያ በቅበት ምርጫ ክልል ሸ/ገሬም ቁጥር 0-1 ምርጫ ጣቢያ ብቻቸውን ተወዳድረው 1,370 ድምፅ አግኝተዋል፡፡ ይኼ ማለት በምርጫ ጣቢያ ከሕጉ በተጣረሰ መልኩ 370 መራጮች ተሳትፈዋል፡፡

 በተጨማሪም በወላይታ ሁለገብ ምርጫ ክልል በቦዲቱ ቆርኬ ምርጫ ጣቢያ ከመድረክ ዕጩ ጋር የተወዳዳሩት የኢሕአዴግ ተወካይ አቶ አማኑኤል አብረሃም 1,182 ድምፅ ሲያገኙ፣ የመድረክ ተፎካካሪያቸው አንደ ድምፅ አግኝተዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ የምርጫ ጣቢያ 183 መራጮች ያላግባብ ተስተናግደዋል፡፡

ሌላው በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን ስቄ 02 ምርጫ ክልል የኢሕአዴጉ አቶ ዮሴፍ ዳኤሞ 1,051 ድምፅ ያሸነፉ ሲሆን የመድረክ፣ የሰማያዊና የቅንጅት ተፎካካሪዎቻቸው ደግሞ አንደ ቅደም ተከተላቸው 171፣ 19፣13 ድምፆች አግኝተዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ የምርጫ ጣቢያ 254 መራጮች ያላግባብ ተሳትፈዋል፡፡

በደሴ ከተማ ሮቢት ክፍለ ከተማ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው በሚወዳደሩበት ምርጫ ጣቢያ 22 ላይም 1,049 መራጮች ተመዝግበው የነበረ መሆኑን ሪፖርተሮቻችን አረጋግጠዋል፡፡

ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቱን ቦርዱ ይፋ ባደረገበት ወቅት ስለጉዳዩ የተጠየቁት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር፣ ‹‹አንድ ምርጫ ጣቢያ የሚያስተናግደው አንድ ሺሕ መራጮችን ብቻ ነው፡፡ እኛ የምናውቀው በአንድ ምርጫ ጣቢያ ከአንድ ሺሕ በላይ መራጭ አለመመዝገቡን ነው፤›› ብለዋል፡፡

የምርጫ ሕጉ በአንድ ምርጫ ጣቢያ ከአንድ ሺሕ በላይ መራጭ መመዝገብ የለበትም እንደሚል የገለጹት ዶ/ር አዲሱ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ 45,795 ምርጫ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ የተደረገውም በዚሁ ሥሌት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ከአንድ ሺሕ በላይ ያስተናገዱ ምርጫ ጣቢያዎችን ማጣራትና መመርመር ይኖርብናል፡፡ በመሆኑም ይኼንን ጥያቄ በተመለከተ ይኼ ነው ብለን የምንሰጠው መልስ የለም፤›› ብለዋል፡፡ 

የተሻሻለው የኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 ዓ.ም. በአንቀጽ 22(6) ላይ ‹‹እያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ የሚያስተናግደው የመራጮች ብዛት ከ1,000 መብለጥ የለበትም፤›› በማለት ይደነግጋል፡፡

 

ኢሕአዴግና አጋሮቹ በጊዜያዊ ውጤት ሙሉ በሙሉ ማሸነፋቸው በመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ላይ ጥያቄ አስነሳ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ካደረገው የ442 የፓርላማ መቀመጫ ውጤት ውስጥ ኢሕአዴግና አጋር ድርጅቶቹ ሙሉ ለሙሉ አሸነፉ፡፡ በቦርዱ ጊዜያዊ የውጤት መግለጫ መሠረት፣ በምርጫው የተወዳደሩ ተቃዋሚ

ፓርቲዎች አንድም የፓርላማ ወንበር አላገኙም፡፡ ይህም ውጤት በመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ላይ ጥያቄ አስነስቷል፡፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንን ጊዜያዊ ውጤት ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ይፋ ካደረገ በኋላ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ ላይ ጥያቄ ማንሳት ጀምረዋል፡፡ የአገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትም ወደ ውድቀቱ እየተሽቆለቆለ ነው ብለዋል፡፡ የ2007 ጊዜያዊ የምርጫ ውጤትም ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ መሆኑን እየጠቀሱ ይገኛሉ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ ‹‹በአገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲኖር ዋናው ነገር አሠሪ ሕግ መኖሩ ነው፡፡ ይህ ካለ በማንኛውም ጊዜ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ሊመጣ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

በማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ የልማት ፖሊሲና አስተዳደር የዶክትሬት ተመራማሪ የሆኑት አቶ ኢዮብ ባልቻ ግን፣ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ማለት በርካታ ፓርቲዎች መኖራቸው ብቻ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም በአገሪቷ ውስጥ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃዋሚና ጠንካራ ሆነው ሊንቀሳቀሱ የሚችሉበት ሥርዓት ሊኖር ይገባል ብለዋል፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ መብዛት ይልቅም ፓርቲዎቹ የሚንቀሳቀሱበት ተቀባይነት ያለው ሥርዓት መኖሩ ነው ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ማበብ ወሳኝ የሆነው ነገር ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ርዕዮተ ዓለምን የሚከተለው የኢሕአዴግ ፓርቲ የራሱን ኃይል ሲያደራጅ ቆይታል፡፡ ይህ ገዢ ፓርቲም የአገሪቱን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ ከመቆጣጠሩም ባለፈ በልማታዊ ትርክት እየተደገፈ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢሕአዴግ ለዚህ ዓይነት ድል የበቃው ተቃዋሚዎች ለሕዝቡ አማራጭ ሐሳብ ማቅረብ ባለመቻላቸው መሆኑን አቶ ሬድዋን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ሕዝቡ ምንም እንኳን ቅሬታ ቢኖረውም፣ ከተቃዋሚዎች የቀረበለት አማራጭ ስለሌለ ከእኛ ጋር መቀጠሉን ያመላከተ ውጤት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ተመራማሪው አቶ ኢዮብ ግን ኢሕአዴግ በየደረጃው የፈጠረው የሕዝብ አደረጃጀት ሕዝቡን ለመቆጣጠር፣ ለማታለል፣ ለመቅጣትና ለመሸለም ዓይነተኛ መንገድ ስለሆነለት ይህንን ዓይነት ውጤት በቀላሉ ሊያገኝ ችሏል ብለዋል፡፡ በፓርቲና በመንግሥት መካከል ያለው መዋቅር ልዩነት የለውም የሚሉት አቶ ኢዮብ፣ የገዢው ፓርቲ ፍላጐት ከሌሎች ማናቸውንም ዓይነት ፍላጐቶች ቀድመው ይታያሉ ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የአንድ ለአምስት አደረጃጀት፣ የልማት ሠራዊት አደረጃጀት፣ የወጣት ሊግ፣ የሴቶች ሊግና ሌሎችም አደረጃጀቶች ኢሕአዴግ ምርጫውን እንዲያሸንፍ አስችለውታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ ሬድዋን ግን ኢሕአዴግ በአርሶ አደሩ፣ በዝቅተኛውና በመካከለኛው ኅብረተሰብ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱ ማሸነፉን ገልጸዋል፡፡

የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መርጋ በቃና በበኩላቸው፣ ‹‹ምርጫው ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያደረጉት የምርጫ ቅስቀሳና ያቀረቡት የዕጩዎች ብዛት የዚህ ማሳያ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ አሳታፊ የሆነ የውድድር ሜዳ አዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ ውጪ ሕዝቡ ይጠቅመኛል ብሎ ድምፁን የሰጠውን ውጤት ተቀብሎ ማወጅ ነው የምርጫ ቦርድ ሥራ፤›› ብለዋል፡፡ የቦርዱ ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር ደግሞ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አማራጭ ሐሳቦቻቸውን ለሕዝብ ለመግለጽ ያደረጉት ፉክክር፣ ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ መኖር አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ፓርቲዎቹ ተወዳድረው ያገኙት ውጤት ሌላው ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በምሳሌነት ባቀረቡት የምሥራቅ ሸዋ የምርጫ ውጤት መድረክ 12,834 ድምፅ ሲያገኝ፣ ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ 40,357 ድምፅ አግኝቷል ብለዋል፡፡ ሆኖም ግን አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ይህን የዶክተሩን ሐሳብ አይቀበሉትም፡፡ ምክንያቱም ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ያገኙት የድምፅ ልዩነት እጅግ ሰፊ ነው በማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተወዳደሩበት የምርጫ ጣቢያ ተቃዋሚዎች ምንም ድምፅ አለማግኘታቸው ሌላው ማሳያ ነው ይላሉ፡፡

አቶ ሬድዋን በ2007 ምርጫ ድምፃቸውን ለኢሕአዴግ ያልሰጡትን ዜጐች አሁን ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግርና የመንግሥት አገልግሎትን አሳታፊነትን በማስተካከል በቀጣይ የእነዚህን ዜጐች ድምፅ እንደሚያገኙ እምነት አላቸው፡፡ ተመራማሪው አቶ ኢዮብ ግን ኢሕአዴግ ይህን የማድረግ ብቃቱም ሆነ ፍላጐቱ ስለሌለው፣ ተቃዋሚዎች ጠንክረው በመሥራትና የተሻለ ስትራቴጂ በመከተል የመረጧቸው ዜጐችን የሚያገለግሉበትን መንገድ ሊፈልጉ ይገባል ብለዋል፡፡  

ቦርዱ ባወጣው ጊዜያዊ ውጤት መሠረት በትግራይ ክልል ሕወሓት/ኢሕአዴግ ካሉት 38 መቀመጫዎች 31 ሲያገኝ፣ በአማራ ክልል ካሉት 138 መቀመጫዎች ብአዴን/ኢሕአዴግ 107ቱን ማሸነፍ ችሏል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ከ178 የፓርላማ መቀመጫዎች 150 ሲያገኝ፣ በደቡብ ክልል ደኢሕዴን/ኢሕአዴግ ከ123 መቀመጫዎች 95ቱን ማግኘት ችሏል፡፡

በአፋር ክልል አብዴፓ ከስምንት መቀመጫዎች ስድስት አግኝቷል፡፡ በቤንሻንጉል ጉምዝ ቤጉሕዴፓ ከዘጠኝ መቀመጫዎች ሰባት አግኝቷል፡፡ በጋምቤላ ክልል ጋሕዴን ከሦስት መቀመጫዎች ሦስቱንም አግኝቷል፡፡ በሐረሪ ከሁለት መቀመጫዎች ሐብሊና ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ አንድ አንድ ማግኘታቸውን የቦርዱ ጊዜያዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል ሶሕዴፓ ከ23 መቀመጫዎች 16 አግኝቷል፡፡ በአዲስ አበባ ካሉት 23 መቀመጫዎች ኢሕአዴግ 23ቱን ማሸነፉ ተገልጿል፡፡         

 

ጦማሪ አቤል ዋበላ ችሎት በመድፈር ጥፋተኛ ተባለ

በተጠረጠሩበት የሽብርተኝነት ወንጀል ከአንድ ዓመት በላይ በእስር በቆዩት ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ላይ ተጨማሪ ምስክሮችን ለማሰማት፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ግንቦት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፍርድ ቤት ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ተደረገ፡፡

ክሱን እየሰማ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የዓቃቤ ሕግን የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ ውድቅ ያደረገው፣ የተከሳሾቹ ጠበቆች ያቀረቡትን መቃወሚያና ራሱ ፍርድ ቤቱ ቀደም ባለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ መሠረት አድርጎ ነው፡፡ 

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ቀደም ባሉት ችሎቶች 18 የሰው ምስክሮችን አሰምቶ ቀሪ ምስክሮችን ሊያገኛቸው እንዳልቻለ በመግለጽ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠውና ቀሪ ምስክሮችን ለማቅረብ ሲጠይቅ፣ ፍርድ ቤቱ “ለመጨረሻ ጊዜ” በማለት ተጨማሪ ምስክሮችን እንዲያቀርብ ማዘዙን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ግንቦት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. በነበረው ቀጠሮ ቀርቦ ምስክሮቹን ሊያገኛቸው እንዳልቻለ በመግለጽ፣ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር፡፡ 

የተከሳሾች ጠበቆች ቀደም ብሎ በነበረው ችሎት ዓቃቤ ሕግ ጥያቄውን ማንሳቱንና ፍርድ ቤቱም “የመጨረሻ” ብሎ ትዕዛዝ ሰጥቶት እንደነበር አስታውሰው፣ ድጋሚ ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግ ጠየቁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጠበቆቹ ቀደም ባለው ችሎት ዓቃቤ ሕግ በኤግዚቢትነት እንዳስያዛቸው ለፍርድ ቤቱ ያሳወቀውን ሲዲዎች ኮፒ እንዲሰጣቸው አመለከቱ፡፡

ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ተከሳሾችም ሆኑ ጠበቆቻቸው የማያውቁት አዲስ ቪሲዲ እንዳለው ለፍርድ ቤቱ ሲያመለክት፣ የተከሳሾች ጠበቆችም እንዲሰጣቸው ጠየቁ፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹ ጠበቆች ያቀረቡትን ተቃውሞና አዲስ የቀረበውን ቪሲዲ ይሰጠን ጥያቄ ላይ እንዲሁም ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ቪሲዲ ላይ ብይን ለመስጠት በይደር ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ ተጠናቀቀ፡፡ 

ፍርድ ቤቱ በማግሥቱ ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ተሰይሞ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን እንዲያሰማ የተሰጠው ጊዜ ለመጨረሻ መሆኑን በመንገር፣ ተጨማሪ የጊዜ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉንና ምስክሮቹን እንደማይሰማ አስታወቀ፡፡

በኤግዚቢት የተያዙ ሲዲዎች ተገልብጠው (ኮፒ) ተደርገው እንዲሰጣቸው የተከሳሾች ጠበቆች ያቀረቡትን ጥያቄ በሚመለከት ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ፣ ሲዲዎቹ የተዘጋጁት ከተከሳሾቹ ላፕቶፖች ላይ ተገልብጠው በመሆኑና ዓቃቤ ሕግ በሰነድ አዘጋጅቶ ያቀረባቸው ወይም ለተከሳሾችም የተሰጡ ዶክመንቶች ተመሳሳይ ስለሆኑ በድጋሚ መስጠቱ አስፈላጊ አለመሆኑን አስረድቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ አዲስ ያቀረበውን ቪሲዲ በሚመለከት “ማስረጃ ይሆናል ወይስ አይሆንም?” የሚለውን ፍርድ ቤቱ በቅድሚያ አይቶ ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ብይን እንደሚሰጥበት ገልጿል፡፡  

ፍርድ ቤቱ በይደር ያቆየውን የዕለቱን ሥራ በማጠናቀቅ ላይ እያለ ከጦማሪያኑ መካከል፣ ጦማሪ አቤል ዋበላ እጁን በማውጣት ጥያቄ እንዳለው በማመልከት “ቪሲዲው ሶሊያና ሽመልስን ብቻ የሚመለከት ነው ወይስ እኛንም ይጨምራል?” የሚል ጥያቄ ሲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ‹‹አልተፈቀደልህም ተቀመጥ›› አለው፡፡ አቤል ጥያቄውን በመቀጠሉ ፍርድ ቤቱ ‹‹ሥነ ሥርዓት ተቀመጥ›› ሲለው ‹‹ራሳችሁ ሥነ ሥርዓት›› የሚል ምላሽ ሰጠ፡፡ 

የተከሳሾቹ ጠበቃ ወደ አቤል በመጠጋት ካረጋጉትና እንዲቀመጥ ካደረጉት በኋላ ለችሎቱ አመለከቱ፡፡ ተከሳሹ መጠየቅ የፈለገው ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ቪሲዲ የሚመለከተው ሶሊያናን ብቻ ወይም እነሱንም ያጠቃልል እንደሆነ ለማወቅ እንደሆነና ለችሎቱም ምላሽ የሰጠው በስሜታዊነት ስለሆነ ፍርድ ቤቱ ይቅርታ እንዲያደርግለት ጠየቁ፡፡

ፍርድ ቤቱ የጠበቃውን ማመልከቻ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ‹‹ራሱ ሊናገር ያሰበውን ገልጾ ይቅርታ ይጠይቅ››  በማለት አዘዘ፡፡ 

ጦማሪ አቤል ዋበላ ምንም ያጠፋው ነገር እንደሌለና ይቅርታ የሚያስጠይቀው ነገር አለመኖሩን ሲናገር፣ ፍርድ ቤቱ በችሎት መድፈር ጥፋተኛ ብሎታል፡፡ 

በዚህ ጊዜ ሁሉም ተከሳሾቹ (9ኙም) ከተቀመጡበት ተነስተው አቤል የተናገረው የሁሉም እንደሆነ በመግለጽ እሱ ብቻ ተነጥሎ ጥፋተኛ መባል እንደሌለበት በመግለጽ፣ አንድነታቸውን ለማሳየት ቢሞክሩም ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ፀንቷል፡፡ ጠበቃውም ችሎቱ በተግሳጽ እንዲያልፈው የቅጣት ማቅለያ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ፍርድ ለመስጠት ለግንቦት 25 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

መድረክ የምርጫው ውጤት በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠየቀ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የተከናወነው አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ መሠረታዊ የሆኑ ሕገ መንግሥታዊና ሌሎች የምርጫ ሕጎችን በጣሰ ሁኔታ የተከናወነ በመሆኑ፣ ይኼንን የሕግ ጥሰት የሚያጣራ ገለልተኛ የሆነ አጣሪ አካል እንዲቋቋም ጠየቀ፡፡ 

ፓርቲው ይህን ጥያቄ ያቀረበው ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ለአገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡ 

በዕለቱ መግለጫውን የሰጡት የወቅቱ የመድረክ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ የፓርቲው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲናና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ናቸው፡፡ 

‹‹ምርጫው የአገሪቱን ሕገ መንግሥትና ያሉትንም ሕግጋት ሁሉ የጣሰ ነው፡፡ ስለሆነም ወገንተኛ ያልሆኑ ዜጎች ያሉበት ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ፣ በምርጫው ሒደት የተከሰቱት የሕግ ጥሰቶች እንዲያጣራ መድረክ አበክሮ ይጠይቃል፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል፡፡ 

ፕሮፌሰር በየነ ከምርጫው ዕለት ቀደም ብሎ በከፍተኛ ሁኔታ መሠረታዊ የሕገ መንግሥት፣ የምርጫ ሕግጋትና ሌሎች የሥነ ምግባር ጥሰቶች ተፈጽመዋል ብለዋል፡፡ 

ለአብነትም ያህል ሲጠቅሱ፣ ‹‹ለመድረክ 303 የፓርላማ ተወዳዳሪዎችን አዘጋጅተን ያቀረብን ቢሆንም፣ ምርጫ ቦርድ ግን ዕውቅና የሰጠልን ለ270 ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱንም የሚያስረዳን አካል አልነበረም፤›› በማለት መድረክ መጉላላት የጀመረው ከምርጫው ዕለት ቀደም ብሎ እንደነበር አውስተዋል፡፡ 

ሌላው ፕሬዚዳንቱና ሌሎች የመድረክ አመራሮች ያነሱት ነጥብ ደግሞ፣ ከምርጫው ቀደም ብለው የተከናወኑት የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫና የምርጫ ቅስቀሳ በችግር ውስጥ መከናወናቸውን ነው፡፡ 

‹‹የምርጫው ዕለት ሲቃረብ ደግሞ ዕጩ ተወዳዳሪዎቻችን ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የዘንድሮ ምርጫ የምርጫ ሕጎችን፣ የሥነ ምግባር ደንቦችንና ሕገ መንግሥቱንም ጭምር የጣሰ የምርጫ ሒደትና አፈጻጸም ያሳየ መሆኑን መድረክ ገምግሟል ብለዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ ፓርቲው ደርሷል፤›› በማለት አክለው አብራርተዋል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪም የፓርቲው አመራሮች የታሰሩ አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን መንግሥት እንዳፈታ ጠይቀዋል፡፡ 

 

የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በዕቅድ ዘመኑ ለማጠናቀቅ ታስቧል

ሙሉ ትኩረቱን በአምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ አድርጎ የቆየው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት፣ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተገለጸው ጊዜያዊ ውጤት መንግሥት መመሥረት መቻሉን ካረጋገጠ በኋላ፣ በጅምር የሚገኘውን ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዝግጅት ላይ ትኩረት አደረገ፡፡

በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ባለቤትነትና በ13 ዓብይ ኮሚቴዎች አማካይነት የመጀመርያው ረቂቅ ፕላን ቢዘጋጅም፣ ዝግጅቱ በምርጫውና በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች በተያዘለት የጊዜ ገደብ መካሄድ አልቻለም ተብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ምርጫው ከሞላ ጎደል በመጠናቀቁ የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከአንድ ወር በኋላ ተጠናቆ ሁለተኛው ዕቅድ መተግበር መጀመር ስለሚኖርበት፣ መንግሥት ሙሉ ትኩረቱን በዕቅድ ዝግጅቱ ላይ ማድረጉ ታውቋል፡፡

የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ለማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቀን ባይቆረጥለትም ሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ረቂቅ ዕቅድ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ይፀድቃል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዕቅዱን ካፀደቀ በኋላ ኅብረተሰቡ እንዲወያይበት የሚደረግ መሆኑን፣ ከኅብረተሰቡ የሚቀርበው አስተያየት ታክሎበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ አቶ ፈቃዱ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ምንጮች እንደገለጹት፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በአገሪቱ እየተካሄደ ያሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በአጠቃላይ ለማጠናቀቅ ታቅዷል፡፡ በተለይ በመንገድ መሠረተ ልማት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ በቴሌኮም ማስፋፊያና በባቡር መስመር ግንባታ ከፍተኛ በጀት እንደሚመደብ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ በቅርቡ የመሠረተ ልማት ተቋማት ኃላፊዎችን ሰብስበው በአምስት ዓመት ውስጥ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ማገባደድ እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ከመሠረተ ልማት ግንባታዎች በተጨማሪ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በተመረጡ ከተሞች የኢንዱስትሪ ዞኖችን ለመገንባት ታቅዷል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዶ/ር አርከበ እቁባይ የሚመራው የኢንዱስትሪ ዞን ልማት ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ፣ በሐዋሳ፣ በባህር ዳር፣ በመቐለ፣ በኮምቦልቻና በድሬዳዋ ከተሞች በአሥር ቢሊዮን ዶላር ወጪ የኢንዱስትሪ ዞኖችን በሰፊው የማልማት ዕቅድ እንዳለው ተገልጿል፡፡ ይህ ዕቅድ ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም. መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንድትሠለፍ የማድረግ አቅም እንዳለው በመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ታምኖበታል፡፡

ነገር ግን ምንጮች እንደለገጹት፣ እስካሁን በሁለተኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ የሚካተቱና የማይካተቱ ዝርዝር ፕሮጀክቶች አልታወቁም፡፡ ለምሳሌ ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚጠናቀቀው የአምስት ዓመት ዕቅድ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት የነበረው በመላ አገሪቱ የሚገኙ ቀበሌዎችን የሚያገናኝ መንገድ ግንባታ፣ በሁለተኛው ዕቅድ መካተቱ ወይም አለመካተቱ አልታወቀም፡፡

ሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ግንባታ ፕሮግራም ሲካሄድ የቆየው በማዕከላዊ መንግሥት በሚመደብ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ልዩ በጀት ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ ፕሮግራም በመጠናቀቁ በ2008 ዓ.ም. የሚመደብ በጀት የለም፡፡  

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአሁኑ ሰዓት እየሰጠ ባለው መግለጫ፣ እስካሁን በደረሰው ጊዜያዊ ውጤት መሠረት ኢሕአዴግና አጋሮቹ 434 የፓርላማ ወንበሮችን ማግኘታቸውን አስታወቀ፡፡ በቦርዱ ጊዜያዊ ውጤት መግለጫ መሠረት ኢሕአዴግ ከአጋሮቹ ጋር መንግሥት መመሥረት የሚያስችለው ውጤት አግኝቷል፡፡

በቦርዱ መግለጫ መሠረት ኢሕአዴግ በአዲስ አበባ ሃያ ሦስቱንም የፓርላማ ወንበሮች የተቆጣጠረ ሲሆን፣ እስካሁን በተገኘው ውጤት መሠረት ከትግራይ ክልል 38 የፓርላማ ወንበሮች 31 ማግኘቱ ተረጋግጧል፡፡

 

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በታዛቢ ድርቅ የተመቱበት ምርጫ

ባለፈው እሑድ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በተካሄደው የምርጫ 2007 የድምፅ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ የታየው ለየት ያለ ክስተት፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታዛቢዎች ጉዳይ ነው፡፡

አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ ሪፖርተር በተሰማራባቸው ብዙዎቹ የክልል ከተሞች በአብዛኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢዎችን ማግኘት አዳጋች ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በገዥው ፓርቲ ጫና ታዛቢዎቻቸው እንዳልተገኙ ቢገልጹም፣ በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች በብዙዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎች ለማሰማራት አለመቻላቸው እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡ በተወሰኑ ሥፍራዎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች በበጀት እጥረት ምክንያት ታዛቢ ማሰማራት አለመቻላቸውን በግልጽ ሲናገሩም ተደምጧል፡፡ በአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ታዛቢ አለማስቀመጣቸው የገረማቸው ብዙ ሰዎች፣ ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች እንዴት ሊያሰማሩ ይችላሉ ብለው ትዝብታቸውን ገልጸዋል፡፡ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታዛቢ ላለማሰማራታቸው ምክንያቱ የገዥው ፓርቲ አፈናና ጫና ከመጠን በላይ በመሆኑ ነው ቢሉም፣ በሁሉም ሥፍራዎች የሚገኙ የምርጫ አስፈጻሚዎች ግን አስተባብለዋል፡፡ በበርካታ ቦታዎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች ፖስተሮችና ባነሮችም አልታዩም፡፡ ከገዥው ፓርቲ ጋር ሲነፃፀሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምርጫው ዝግጅት ያደረጉም አይመስሉም፡፡ ሪፖርተር በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች በመሰማራት የተዘጋጁ የተለያዩ የምርጫ ዘገባዎች በውስጥ ገጾች ሠፍረዋል፡፡   

 

ምርጫ በአምቦና በጉደር

በምዕራብ ሸዋ ዞን በአምቦና አካባቢዋ የሚደረገው ምርጫ ጠንካራ ፉክክር የሚታይበት በመሆኑ የብዙዎችን ቀልብ ይስባል፡፡ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)

የትጥቅ ትግል በሚያካሂድበት ወቅት በ1983 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ያደርግ የነበረውን ግስጋሴ፣ በአምቦ አካባቢ ሕዝብ ድጋፍ የነበረው ወታደራዊ ደርግ የኢሕአዴግን ጥቃት መመከት ችሎ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት የአምቦና አካባቢዋ ሕዝብ ከደርግ ሠራዊት ጋር ተባብሮ በፅናት መዋጋቱ ይነገራል፡፡ 

ይሁን እንጂ በስተኋላ ኢሕአዴግ ኃይሉን አጠናክሮ በአምቦና በጉደር ከተሞች አካባቢ የነበረውን የደርግ መከላከያ መስመር ጥሶ አዲስ አበባን ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. መቆጣጠሩ የሚታወስ ነው፡፡ የኢሕአዴግና የአምቦ አካባቢ ሕዝብ ቁርሾ የሚጀመረው ከዚያን ወቅት ነው፡፡ 

ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ በሚያካሂዳቸው አገራዊ ምርጫዎች በአብዛኛው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲያሸንፉ ቆይተዋል፡፡ በተለይ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ የነበራቸው በመሆኑ፣ ቀደም ሲል ይመሩት የነበረው የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) በምዕራብ ሸዋ ዞን በአብዛኛው ጊዜ ሲያሸንፍ ቆይቷል፡፡ 

ይህ ታሪክ በምርጫ 2002 ተቀይሮ ኦሕዴድ/ኢሕአዴግን ወክለው የተወዳደሩትና የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ዮሐንስ ምትኩ ዶ/ር መረራን አሸንፈዋል፡፡ በዘንድሮ አምስተኛ አገር አቀፍ ምርጫ በዶ/ር መረራ የኦሮሞ ሕዝቦች ኮንግረስና በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ይመራ የነበረው ኦፌዴን ጥምረት ከሆነው ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ማን ያሸንፍ ይሆን የሚለው ጥያቄ በምዕራብ ሸዋ ዞን የሚካሄደውን ምርጫ አጓጊ አድርጎታል፡፡ 

ኦፌኮ የአራት ፓርቲዎች ጥምረት የሆነውን መድረክ ወክሎ ወደ ምርጫ ገብቷል፡፡ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃን ዘጋቢዎቻቸውን ወደ ምዕራብ ሸዋ ዞን አሰማርተዋል፡፡ 

የምርጫ ዋዜማ 

በምርጫው ዋዜማ ቅዳሜ ግንቦት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. የአምቦ ከተማ ሕዝብ የተለመደውን የዕለት ተዕለት ኑሮውን በማካሄድ ላይ ነበር፡፡ በከተማው የተጠናከረ ጥበቃ መኖሩ ታይቷል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት አምቦና አካባቢዋን በመዘዋወር ሲጠብቁ ነበር፡፡ የኦሮሚያ ፖሊስ አድማ በታኝ ኃይል ከነሙሉ ትጥቁ በየፖሊስ ጣቢያው ሰፍሯል፡፡ 

ከአምቦ በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በጉደር ከተማ በተመሳሳይ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ሲዘዋወሩ የነበረ ሲሆን፣ አድማ በታኝ ኃይልም ዝግጁ ሆኖ ሲጠባበቅ ማየት ተችሏል፡፡ በተጨማሪም በአምቦና በጉደር አካባቢ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት በፒክአፕ ተሽከርካሪዎች ዋናውን አስፋልት መንገድ ፓትሮል ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ 

የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች የጋራ ማስተር ፕላን ዝግጅት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ መፍጠሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በወቅቱ የአምቦ ከተማ ወጣቶች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተው የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ በምርጫው ሒደት ላይ የራሱን ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ አሳድሯል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች በአምቦ የሚካሄደውን ምርጫ ውጥረት የሰፈነበት እንዲሆን አድርገውታል፡፡ 

በአምቦ ከተማ በምርጫው ዋዜማ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለባጃጆችና ቡና ቤቶች ሥራ ከቀዘቀዘ አምስት ስድስትና ቀናት እንደተቆጠሩ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ከ12 ሰዓት በኋላ አብዛኛው የአምቦ ከተማ ነዋሪ ወደ መኖሪያ ቤቱ ከቷል፡፡ ምግብ ቤትና መጠጥ ቤቶች ማምሻውን ጭር ብለው ተስተውሏል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሆቴልና አበበች መታፈሪያ ያሉ ትላልቅና ታዋቂ ሆቴሎች የምግብ አዳራሾቻቸው ውስጥ በጣት የሚቆጠሩ ደንበኞች ብቻ ሲስተናገዱ ታይተዋል፡፡ 

የምርጫ ዝግጅት 

የምዕራብ ሸዋ ዞን የምርጫ አስተባባሪና የአምቦ አንድ የምርጫ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሁንዴሳ ማዴሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን ለምርጫ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 533,444 ነው፡፡ በዞኑ 11 የምርጫ ክልል 862 የምርጫ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ አሥር ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ማስመዝገባቸውን አቶ ሁንዴሳ ተናግረዋል፡፡ ለተወካዮች ምክር ቤት 62፣ ለክልል ምክር ቤት 137 በአጠቃላይ 199 ዕጩዎች ተመዝግበዋል፡፡ ከዕጩ ተወዳዳሪዎቹ ውስጥ 176 ወንድ፣ 23 ሴቶች ናቸው፡፡ 

ለጋዜጠኞች መረጃ ያለመታከት ይሰጡ የነበሩት አቶ ሁንዴሳ፣ በምርጫ ዋዜማ ለምርጫ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በሰዓቱ መድረሳቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በከተማ ለሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ድንኳንና መብራት እንዲገባላቸው የተደረገ ሲሆን፣ በገጠር ለሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ዳስ፣ የእጅ ባትሪዎችና ሻማ ተገዝቶ መላኩን አስታውቀዋል፡፡ 

ከአዲስ አበባ በስተ ምዕራብ 114 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የአምቦ ከተማ ስድስት ቀበሌዎች (ሦስት የከተማ፣ ሦስት የገጠር ቀበሌዎች) ሕዝብ ብዛት ከ100,000 በላይ ይገመታል፡፡ በአምቦ ከተማ 31 የምርጫ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ በአምቦ ከተማ 22,849 ነዋሪዎች በመራጭነት ተመዝግበዋል፡፡ በሦስቱ የገጠር ቀበሌዎች 33,169 ነዋሪዎች በመራጭነት ተመዝግበው ካርድ ወስደዋል፡፡ 

በአምቦ ከተማ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘጠኝ፣ ለክልል ምክር ቤት ደግሞ 18 ተወዳዳሪዎች ቀርበዋል፡፡ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ኦሕዴድ (ኢሕአዴግ)፣ ኦፌኮ (መድረክ)፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ ቅንጅት፣ አንድነት፣ መላው ኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኦሕዴፓ)፣ መኢብንና የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ (ገሥአፓ) ናቸው፡፡ 

ፀጥታን በተመለከተ ዞን፣ ወረዳ፣ ቀበሌ እስከ ምርጫ ጣቢያ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ የአካባቢው፣ የዞን ፖሊስና የአካባቢው ፀጥታ ዘርፍ አካላት ጋር በመቀናጀት ሚሊሻና ታጣቂዎችን በማደራጀት አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አቶ ሁንዴሳ ተናግረዋል፡፡ 

ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት እስከ ግንቦት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ሰላማዊ የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ከምርጫው ቀደም ሲል የዞኑ የምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ በምርጫ ሕጉ ዙሪያ ትምህርት ሰጥቷል፡፡ ‹‹የምርጫ ሥነ ምግባር ደንብን በተመለከተ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂደናል፡፡ ምንም እንኳ መድረክ የሥነ ምግባር ሕጉን ባይፈርምም በውይይቱ ተካፋይ ሆኗል፤›› ያሉት አቶ ሁንዴሳ ኢሕአዴግ፣ መድረክና ገሥአፓ የሚገኙበት የጋራ መድረክ አቋቁመው በሥነ ምግባር ሕጉ ዙሪያ ሲወያዩ ቆይተዋል ብለዋል፡፡ 

ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰላማዊ የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡ በአምቦ ከተማ የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጨመዳ ለሪፖርተር እንደገለጹት ፓርቲያቸው ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ እንዲሆን አቅዶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ አቋቁመን የሚገጥሙንን ጥቃቅን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ስንፈታ ቆይተናል፤›› ያሉት አቶ አሸናፊ፣ ፖስተር ተቀዳደደብኝ የሚሉ ቅሬታዎች ከገዢው ፓርቲና ከመድረክ መቅረባቸውን፣ የምርጫ ቅስቀሳ በተከለከሉ ሥፍራዎች (እንደ ትምህርት ቤት ባሉ ቦታዎች) ማካሄድና ያልተገቡ ዘፈኖች (ግጭት ሊጭሩ የሚችሉ) ማሰማት ችግሮች በመድረክ በኩል ነበሩ፡፡ ‹‹እነዚህንና የመሳሰሉትን ችግሮች ቦርዱም ባለበት የጋራ መድረክ ተነጋግረን ፈተናቸዋል፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ቅድመ ምርጫው ሰላማዊ እንደነበር አቶ አሸናፊ አረጋግጠዋል፡፡ 

ኦፌኮ/መድረክ በአምቦ፣ በጉደርና በሌሎችም ከተሞች ሰፊ የቅስቀሳ ዘመቻ አካሂዷል፡፡ ከምርጫው አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በአምቦ ከተማ በርካታ ሕዝብ የተሳተፈበት ስብሰባ አካሂዷል፡፡ የኦፌኮ ሊቀመንበርና የመድረክ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲና ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መድረክ የተሳካ የምርጫ ቅስቀሳ አካሂዷል፡፡ ‹‹ከምርጫ 97 የበለጠ የቅስቀሳ ሥራ ሠርተናል፤›› ያሉት ዶ/ር መረራ፣ ‹‹ሜዳው የተስተካከለ ባይሆንም ችግሮችን ተቋቁመን ሰፊ የቅስቀሳ ሥራ ሠርተናል፤›› ብለዋል፡፡ 

ዶ/ር መረራ በቅስቀሳ ወቅት በአምቦና በጉደር ከተሞች ችግር እንደገጠማቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ትምህርት ቤት፣ ቤተ ክርስቲያን አለ እያሉ የምርጫ ቅስቀሳ እናዳናካሂድ ከልክለውናል፡፡ በገበያ ቀንም ቅስቀሳ እንዳናካሂድ ተከልክለናል፡፡ ተማሪዎች እንዳይገኙልን በዕረፍት ቀን (ቅዳሜና እሑድ) ከልክለው በሥራ ቀን እንድናካሂድ ያደርጋሉ፤›› ሲሉ ወቀሳቸውን አቅርበዋል፡፡ 

አያይዘውም ‹‹አጠቃላይ የምርጫውን ሒደት ያበላሸው አንድ ለአምስት የሚሉት ፖለቲካ ነው፡፡ የቀበሌ አለቆች ሕዝቡን ድምፅ የምትሰጡት በተደራጀ መልክ ነው በማለት፣ ሕዝቡ ድምፁን ለገዢው ፓርቲ እንዲሰጥ እየተደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

የምርጫ ዕለት 

እሑድ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የአምቦና የጉደር ከተማ ነዋሪዎች ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በየምርጫው ጣቢያ ተሰልፈዋል፡፡ በተለይ በጉደር ከተማ መራጩ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ለመምረጥ ረዥም ሠልፍ ይዞ ተስተውሏል፡፡ 

በአምቦ ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫው ሒደት በሰዓቱ (ከጠዋቱ 12 ሰዓት) መጀመሩን ተመልክቷል፡፡ በየምርጫ ጣቢያው አምስት የሕዝብ ታዛቢዎች የድምፅ አሰጣጥ ሒደቱ ከመጀመሩ አስቀድመው ተገኝተዋል፡፡ በእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች ተወካዮቻቸውን ያስቀመጡት ኢሕአዴግ፣ መድረክና ኢዴፓ ብቻ ናቸው፡፡ የተቀሩት ስድስት ፓርቲዎች በአብዛኛው ጣቢያዎች ታዛቢዎቻቸውን እንዳላስቀመጡ ታይቷል፡፡ 

የሰማያዊ ፓርቲ ተወካይ አቶ አዲሱ ፈቃዱ ፓርቲያቸው በሰው ኃይልና በበጀት እጥረት ምክንያት ተወካዮቹን በየምርጫ ጣቢያው ማስቀመጥ እንዳልቻለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ የገሥአፓ ተወካይ አቶ አሸናፊ ጅፋራ ድርጅታቸው በተቻለ መጠን በአብዛኛው ምርጫ ጣቢያቸው ታዛቢዎች የመደበ ቢሆንም፣ በሰው ኃይልና በበጀት እጥረት ሁሉንም የምርጫ ጣቢያ ማዳረስ እንዳልቻለ አስረድተዋል፡፡ 

በአምቦ ከተማ በእያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ የተመዘገበው ሕዝብ በአማካይ ከ600 እስከ 700 ነው፡፡ የምርጫ አስፈጻሚዎቹ በሚገባ የሠለጠኑ ይመስላሉ፡፡ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ማለዳ በአምቦ ከተማ ሪፖርተር ከደረሰባቸው በርካታ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል በ03-ሀ-1፣ በ01-ለ-2፣ 02-ሀ-12፣ 04-ሀ-2እና በሌሎችም ጣቢያዎች መራጩን ሕዝብ በተቀላጠፈ ሁኔታ ሲያስተናግዱ ታይተዋል፡፡ በመሆኑም ማለዳ የታየው ሠልፍ ረፋዱ ላይ (ከአራት ሰዓት በኋላ) በብዙ የምርጫ ጣቢያዎች አልታየም፡፡ 

በየምርጫ ጣቢያው መራጮች ድምፅ ከመስጠታቸው በፊት ስለ ድምፅ አሰጣጡ በቂ ማብራሪያ የተሰጣቸው ቢሆንም፣ በዕድሜ የገፉ አዛውንቶች በድምፅ መስጠቱ ሒደት ላይ ግራ ሲጋቡ ታይተዋል፡፡ አንዳንድ አዛውንቶች የድምፅ መስጫ ወረቀቱን ምን ማድረግ እንዳለባቸው አያውቁም፡፡ አንድ እናት የድምፅ መስጫ ወረቀቱን በሚስጥር ድምፅ መስጫ ክፍል ውስጥ አስቀምጠው ሲወጡ ተስተውሏል፡፡ 

በአምቦ ከተማ ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ሕዝቡ በሰላማዊ መንገድ ድምፁን ሰጥቶ ሲወጣ ታይቷል፡፡ በምርጫ ጣቢያ 03-ሀ-1 ድምፃቸውን ሰጥተው ሲወጡ ሪፖርተር ያገኛቸው ሻለቃ ታምራት ዓሊ፣ በድምፅ አሰጣጡ ሒደት መርካታቸውን ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑት የ59 ዓመቱ ሻለቃ ታምራት በቂ ገለጻ እንደተደረገላቸው፣ ያለምንም ችግር መርጠው መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የምርጫ ክርክሩ በቂ ግንዛቤ አስጨብጦናል፡፡ ዛሬም ያለምንም ግርግር መርጠን ወጥተናል፤›› ብለዋል፡፡ በምርጫ ጣቢያ 04-ሀ-2 የመረጡት ወ/ሮ በቀለች ታደለ ከቤተ ክርስቲያን መልስ ቁርሳቸውን ሳይበሉ ድምፃቸውን ለመስጠት እንደመጡ ገልጸዋል፡፡ የ78 ዓመቷ ወ/ሮ በቀለች በሁለት ልጆቻቸው እየተጦሩ እንደሚኖሩ ገልጸው በንጉሡ ሥርዓት እከሌን ምረጡ እየተባሉ ይመርጡ እንደነበር፣ በዘመነ ደርግ ምርጫ አለመምረጣቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ደርግ መሬት ወርሶብኝ ስለነበር ተቀይሜ መምረጥ አልፈለግኩም ነበር፡፡ አሁን ግን በነፃነት የምንፈልገውን እየመረጥን ነው፡፡ ያለምንም ችግር የምወደውን መርጫለሁ፤›› ብለዋል፡፡ 

በድምፅ አሰጣጡ ሒደት ላይ አንዳንድ ችግሮች መከሰታቸው አልቀረም፡፡ በምርጫ ጣቢያ 04-ሀ-2 ያገኘነው የኦፌኮ/መድረክ ታዛቢ ወጣት ዋቅጅራ ቃበታ የተማሪ መታወቂያ ይዞ በመምጣቱ ወደ ምርጫ ጣቢያው እንዳይገባ መደረጉን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ‹‹ከሌሊቱ 11 ሰዓት በምርጫ ጣቢያው የተገኘሁ ቢሆንም፣ የምርጫ ኃላፊዎቹ የትምህርት ቤት መታወቂያ ተቀባይነት የለውም፡፡ የቀበሌ መታወቂያ አምጣ በማለት እንዳልገባ ከልክለውኛል፡፡ የካርድ ቆጠራ ሲካሄድና ኮሮጆ ሲከፈት መታዘብ አልቻልኩም፡፡ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች መጥተው 12፡25 ሰዓት ሲሆን ነው ተፈቅዶልኝ የገባሁት፤›› ብሏል፡፡ 

የምርጫ ጣቢያ ኃላፊው አቶ ሊካሣ ኢርካታ ችግሩ መፈጠሩን አምነዋል፡፡ ‹‹የመድረክ ተወካይ ነኝ ብሎ ሲመጣ መታወቂያ ጠየቅነው፡፡ ያሳየን መታወቂያ የትምህርት ቤት ብቻ ነው፡፡ እኛ ደግሞ ማሳየት ያለበት የቀበሌ ነዋሪነት መታወቂያ ነው በሚል አስቁመነዋል፡፡ በኋላ የዞኑ የምርጫ ቦርድ ኃላፊ አቶ ሁንዴሳ መጥቶ አግባብነት እንዳለው ካስረዳን በኋላ አስገብቸዋለሁ፤›› ብለዋል፡፡ 

በኦዶ ሊበን የምርጫ ጣቢያ የተገኘው ፌሌንበር ዲቦ የተባለ የመድረክ ተወካይ፣ የኦሕዴድ ካድሬዎችና ታጣቂዎች ወደ ምርጫ ጣቢያው በተደጋጋሚ ገብተዋል ሲል ቅሬታውን አሰምቷል፡፡ ወጣት ፌሌንበር ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ የምርጫ ሕጉ ታጣቂዎች ከምርጫ ጣቢያው 500 ሜትር መራቅ አለባቸው ቢልም አንዳንድ ታጣቂዎች ወደ ምርጫ ጣቢያው ዘልቀው እንደገቡ ተናግሯል፡፡ 

‹‹ካድሬዎችም ከመረጡ በኋላ የምርጫ ጣቢያውን ለቀው መሄድ ቢኖርባቸውም በምርጫ ጣቢያው ውስጥ ሲዞሩ ይታያሉ፡፡ ታጣቂዎችም በሩ ላይ ይታያሉ፤›› ብሏል፡፡ የኦዶ ሊበን ምርጫ ጣቢያ ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ሙሴ አቤቱታውን አስተባብለዋል፡፡ ‹‹ወደ ምርጫ ጣቢያው የገባ ታጣቂ የለም፡፡ ከ500 ሜትር ርቀት ላይ ፀጥታ ለማስከበር የተሰማሩ ፖሊሶች ይኖራሉ፡፡ ምንም የተፈጠረ ችግር የለም፤›› ብለዋል፡፡ 

በአምቦ ከተማ ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው የተለያዩ ቦታዎች በምርጫ ጣቢያ አቅራቢያ የክልሉ ፖሊስ አባላት ታይተዋል፡፡ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች በር ላይ ፖሊሶችና የአካባቢ ታጣቂዎች ተስተውለዋል፡፡ በአምቦ 03-ለ-1 የምርጫ ጣቢያ (አውራ ጎዳና ግቢ ውስጥ) የታጠቁ የፖሊስ አባላት ተስተውለዋል፡፡

ሌላው ችግር በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የምርጫ ወረቀቶች ተሟልተው አለመቅረብ ነው፡፡ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ከ5,000 በላይ ተማሪዎች የሚገኙ ሲሆን፣ 3,578 ተማሪዎች በመራጭነት ተመዝግበዋል፡፡ ስድስት የምርጫ ጣቢያዎች ተቋቁመው፣ በእያንዳንዱ ጣቢያ 700 ያህል ተማሪዎች ተመዝግበዋል፡፡ በሥፍራው የነበረች የምርጫ አስተባባሪ ዓለም አድነው በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ከ10 እስከ 15 የሚሆኑ የምርጫ ወረቀቶች ጉድለት መታየቱን ገልጻለች፡፡ በዚህም ምክንያት 70 ያህል ተማሪዎች በወቅቱ መምረጥ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ጉዳዩን ለምርጫ ቦርድ አሳውቀው ከአዲስ አበባ የምርጫ ወረቀት እስኪመጣ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ዓለም ተናግራለች፡፡ 

በድምፅ መስጫ ዕለት የጠነከረ ቅሬታ ያሰሙት ዶ/ር መረራ ናቸው፡፡ ‹‹በተለያዩ አካባቢዎች ታዛቢዎችን በታጣቂ ኃይሎች ተባረውብናል፤›› ያሉት ዶ/ር መረራ፣ ጀልዱ፣ ጨልያና ጅባት በተባሉ ቦታዎች ታዛቢዎች በመባረራቸው ምክንያት ምርጫው የተካሄደው ታዛቢዎቻችን በሌሉበት ነው ብለዋል፡፡ 

‹‹ታዛቢዎቻችን ላይ ዘመቻ ነው የተካሄደው፡፡ ማስፈራራት፣ በገንዘብ ለመግዛት መሞከር፣ ከዚህ አልፎ አልበገር ያለውን በጠመንጃ የማባረር ተግባር በሰፊው ተፈጽሟል፡፡ የታሰሩና የተደበደቡ ታዛቢዎችም አሉ፤›› ብለዋል፡፡ 

በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት አቶ ሁንዴሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አንዳንድ የመድረክ ታዛቢዎች ተገቢውን መረጃ ይዘው ባለመቅረባቸው ከታዛቢነት ተገልለዋል፡፡ ‹‹ከተመዘገበ መታወቂያ ውጪ የተለየ መታወቂያ ይዘው በመምጣታቸው የተከለከሉ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በምርጫ ቦርድ በታዛቢነት የተመዘገቡ ግለሰቦች ሳይሆኑ፣ ሌሎች ግለሰቦች ተገኝተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በታዛቢነት እንዳይገኙ ተከልክለዋል፤›› ብለዋል አቶ ሁንዴሳ፡፡ 

አያይዘውም አንዳንድ የመድረክ ተወካዮች በምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የምርጫ ሕጉ የሚከለክለውን ድርጊት ሲፈጽሙ በመገኘታቸው፣ ከምርጫ ጣቢያዎች እንዲወጡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአንዳንድ ጣቢያዎች የመድረክ ታዛቢዎች የፓርቲውን ምልክት ለሕዝብ ሲያሳዩ በመታየታቸው በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም፣ ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ባለመቻላቸው ከምርጫ ጣቢያዎቹ እንዲወጡ ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡ 

አቶ ሁንዴሳ ከመድረክ የቀረቡትን አቤቱታዎች ለማጣራት መሞከራቸውን ገልጸው አንዳንድ ታሰሩ የተባሉ ግለሰቦች ጉዳዩ ስህተት መሆኑን፣ ሌሎች ደግሞ በግለሰብ ጠብ ታስረው የተፈቱ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ 

ዶ/ር መረራ በበኩላቸው ባቢች፣ ወልሮጌና ጨካ በተባሉ አካባቢዎች በመድረክ ደጋፊዎችና በታጣቂ ኃይሎች መካከል ፍጥጫ ተፈጥሮ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር መረራ ከአምቦ አልፎ ሚዳቀኝ በሚባል አካባቢ ግጭት ተፈጥሮ ተኩስ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አቶ ሁንዴሳ ይህን በተመለከተ የደረሳቸው ሪፖርት እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ 

ቆጠራ

በአምቦ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ከምሽቱ 12 ሰዓት በሮቻቸውን ዘግተዋል፡፡ ቆጠራው በሰዓቱ ተጀምሯል፡፡ ሪፖርተር በተገኘባቸው አንዳንድ ጣቢያዎች መድረክና ኢሕአዴግ ብርቱ ተፎካካሪ መሆናቸውን ለመታዘብ ተችሏል፡፡ ቀላል የማይባሉ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ምንም ዓይነት ምልክት ያልተደረገባቸው በመሆኑ ሲመክኑም ታይቷል፡፡ በአምቦ 03-ለ-1 የምርጫ ጣቢያ ቆጠራው ሲካሄድ ሁለት የታጠቁ ፖሊሶች (አንድ ወንድና ሴት) ቆጠራው የሚካሄድበት ክፍል ውስጥ ገብተው የቆጠራውን ሒደት ሲከታተሉ ታይተዋል፡፡ የቆጠራው ሒደት በአንዳንድ ጣቢያዎች እስከ ሌሊቱ አሥር ሰዓት ዘልቋል፡፡ 

ውጤት 

የምርጫ ጊዜያዊ ውጤቶች በአምቦና በጉደር ከተሞች ግንቦት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ መለጠፍ ተጀምሯል፡፡ ሪፖርተር በተገኘባቸው ጣቢያዎች በሮች ላይ ጥቂት ወጣቶች የምርጫ ውጤቶችን ሲያነቡ ነበር፡፡ 

አቶ ሁንዴሳ በፓርቲዎች አካባቢ የምርጫ ውጤትን አምኖ የመቀበልና ያለመቀበል ሁኔታ እንደሚኖር ተናግረዋል፡፡ ‹‹የቆጠራ ሒደቱ ሲጠናቀቅ አንፈርምም ብለው የወጡም አሉ፡፡ ይህን እኛ ምንም ማድረግ አንችልም፤›› ብለዋል፡፡ በምርጫው ማግስት ግንቦት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. የክልሉ ፖሊስ በአምቦ ከተማ የተጠናከረ ጥበቃ ሲያካሂድ ነበር፡፡ 

 

ምርጫ በአዲስ አበባ

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አምስት የፓርላማ ምርጫዎችን (1948-1965)፣  በደርግ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ብሔራዊ ሸንጎን አንድ ምርጫ (1979)፣ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ

ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) አራት የፓርላማ ምርጫዎችን (1987-2002) ያካሄደችው አዲስ አበባ ከተማ፣ አምስተኛውን ምርጫ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. አድርጋለች፡፡

ባለፈው እሑድ በተካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ለመሳተፍ አዲስ አበቤዎች ማልደው ነበር ከየምርጫ ጣቢያዎች የተገኙት፡፡ የመዲናይቱ ነዋሪዎች የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ጥሎት በሄደው ጠባሳ ምክንያት እንደሌላው ኢትዮጵያዊ በእኩል ጊዜ ሁለቱንም ማለትም የክልልና የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ባንዴ ለማካሄድ አልታደሉም፡፡ ከሌላው ሕዝብ በሁለት ዓመት ወደኋላ ዘግይተው ነው የክልል ምርጫውን የሚያካሂዱት፡፡ በመሆኑም በዕለቱ ለተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ይመጥናሉ የሚሏቸውን ፓርቲዎች ሲመርጡ ውለዋል፡፡

 ከ2002 ምርጫ ጋር ሲነፃፀር በዛ ያለ የሕዝብ ቁጥርና ሠልፍ የታየበትም ነው፡፡ በ2002 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ምርጫ ለመዘገብ ሪፖርተር ከተዘዋወረባቸው አካባቢዎች አብዛኞቹ ምርጫ ጣቢያዎች ሠልፍም ሆነ የወጣቱ ክፍል አይበዛባቸውም ነበር፡፡ አመዝነው የሚታዩት እናቶች ነበሩ፡፡ የ2007ቱ ምርጫ ከ1997ቱ ጋር ሲነፃፀር ተቀራራቢ የሕዝብ መነቃቃት ነበረው ለማለት ባያስደፍርም ከ2002 ዓ.ም. ግን የሕዝቡ ተሳትፎ የተሻለ ነበር፡፡ መነቃቃትም ታይቶበታል፡፡ 

ከዚህ ቀደም በተደረጉ ሁለት ጠቅላላ ምርጫዎች ሁለት ፈጽሞ የተራራቁ ውጤቶችን ያስተናገደችው አዲስ አበባ፣ በምርጫ 2007 ተቃዋሚዎች ለማሸነፍ ተስፋ ያደረጉባት ሆና ነበር፡፡ በምርጫ 1997 ኢሕአዴግ አንድ ወንበር ከማሸነፍ ውጪ 22 ወንበሮችን ያሸነፈው በወቅቱ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረው ቅንጅት ነበር፡፡ በ2002 ዓ.ም. ይህ ውጤት ተገልብጦ ኢሕአዴግ 22 ወንበሮችን ሲያሸንፍ በወቅቱ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረው መድረክ ውስጥ የታቀፈው የአንድነት ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ብቸኛዋን ወንበር ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡

በምርጫ 2007 ምርጫ በተደረገባቸው አብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች በአዲስ አበባም የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ድምፅ መስጠት ተጀምሮ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ተጠናቋል፡፡

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 36,851,461 ሕዝብ የምርጫ ካርድ የወሰደ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 1,481, 521 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ያገኘነው መረጃ ደግሞ፣ በአዲስ አበባ ለመምረጥ ከተመዘገቡት ውስጥ ድምፅ የሰጡት 1,342,582 እንደሆኑ ያሳያል፡፡

በሁለት መደዳ የተሠለፉት በርካታ መራጮች ድምፅ መስጫ ሰዓት እስከሚደርስ ይጠባበቃሉ፡፡ ጎህ ሳይቀድ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ (ምርጫ ክልል 26/27) ወረዳ ሰባት ምርጫ ጣቢያ አንድ ከተገኙት የመጀመርያዎቹ ተሠላፊዎች የ19 ዓመቷ ሰላም አስካለ  አንዷ ነች፡፡ የመጀመርያ ዓመት ሕክምና ተማሪ ናት፡፡ ‹‹የመጀመሪያዬ ምርጫ ስለሆነ ድምፅ ለመስጠት ጓጉቻለሁ፤ በለሊት የተገኘሁትም ለዚሁ ነው፤›› ትላለች፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በተደረገው ክርክር የምትመርጠውን እንደተገነዘበችና በፓርቲዎቹ መካከል የነበረውን ፉክክር ጠንካራ እንደነበር ትገልጻለች፡፡ ‹‹የአንድ ሰው ተሳትፎ ትልቅ ሚና ስላለው ያመንኩበትን ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ፤›› ብላለች፡፡

በምርጫ ጣቢያው በተጣለው ድንኳን ድምፃቸውን ሰጥተው ሲወጡ ያነጋገርናቸው የ68 ዓመቱ አቶ ሀብተማርያም ምሕረትአብ፣ በአገሪቱ በተካሄዱ ምርጫዎች ባጠቃላይ ድምፅ መስጠታቸውንና የዘንድሮው ምርጫ ከቀደሙት የተሻለ ሆኖ እንዳገኙት ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሰው ያለምንም ጫና እየመረጠ ነው፤›› ይላሉ፡፡ 

የ69 ዓመቱ አቶ ተፈራ ድሩ ሐሳቡን ይጋሯቸዋል፡፡ የዘንድሮውን ጨምሮ በሁሉም በኢሕአዴግ መንግሥት በተካሄዱ ምርጫዎች የሕዝብ ታዛቢ ሆነዋል፡፡ እንደሳቸው ገለጻ፣ የዘንድሮው ምርጫ ‹‹የተረጋጋና የሠለጠነ አካሄድ ያለው›› ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ አስቀድመው ያደረጉት እንቅስቃሴ አገርን ለማሳደግ በቁጭት እንደተነሳሱ ያሳያል ይላሉ፡፡ ‹‹እንደቀደሙት ጊዜያት መናቆር የለም፤›› በማለት የሚሸነፉ ፓርቲዎች ከአሸናፊው ጋር በሰላም እጅ ለእጅ ተጨባብጠው ኑሮ በሰላም እንደሚቀጥል እምነታቸው ነው፡፡

በምርጫ ጣቢያው የሕዝብ ታዛቢዎችና የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች ተገኝተው ሒደቱን ይከታተሉ ነበር፡፡ የጣቢያው የምርጫ አስተባባሪዎችም የምርጫ ቅደም ተከተል ለሕዝቡ ያብራሩ ነበር፡፡ የምርጫ ክልሉ ኃላፊ አቶ ተሾመ አበበ በክልሉ በሚገኙ 110 የምርጫ ጣቢያዎች መሰል ሒደት እንዳለ ተናግረዋል፡፡ በሒደቱ ይህ ነው የሚባል ችግር እንዳልገጠማቸውና ቅሬታዎችም እንዳልተነሱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ረፋድ ላይ ሳር ቤት አካባቢ በምርጫ ክልል 20 በሚገኙ 59 የምርጫ ጣቢያዎች ኢሕአዴግን ወክለው የሚወዳደሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌ ድምፅ ሲሰጡ ሪፖርተር አግኝቷቸዋል፡፡ ‹‹ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ በሰላማዊ መንገድ መምረጡ አገሪቱን ለአፍሪካና የዓለም አገሮች ተምሳሌት ያደርጋታል፤›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የዴሞክራሲ ባህል እየዳበረ መሆኑን አመላካች እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ሕዝቡ የሚመራውን ፓርቲ በራሱ ድምፅ መርጦ እንደሚያስቀምጥና በሰላማዊ መንገድ እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ በምርጫ ጣቢያው የመኢአድ ተወካይ ታዛቢ አቶ በለጠ የሺጥላ ምርጫው በጥሩ ሁኔታ መከናወኑን ይናገራሉ፡፡ በቦታው ከገጠማቸው ችግሮች አንዱ የምርጫ ካርድ ሳይዙ ወደ ጣቢያው የሚሄዱ ሰዎች ሲሆኑ፣ ግለሰቦቹ በምዝገባ ላይ ምርጫ ካርድ መውሰዳቸው ተረጋግጦ ተስተናግደዋል ብለዋል፡፡ 

ተመሳሳይ ችግር የተስተዋለው የምርጫ ክልል 19 ውስጥ ከተካተቱ አካባቢዎች በአንዱ መብራት ኃይል ኮንዶሚኒየም ነው፡፡ መታወቂያ ሳይዙ ድምፅ ለመስጠት ወይም የምርጫ ካርድ ሳይኖራቸው (እንደጠፋባቸው የሚናገሩም አሉ) ድምፅ ለመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ያመሩ ግለሰቦች ተስተውለዋል፡፡ በወረዳ 6 ምርጫ ጣቢያ 20 የሰማያዊ ፓርቲ ታዛቢ የነበሩና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ ያቀረቡት ቅሬታም ይኼው ነው፡፡

‹‹መታወቂያ የሌለው ወይም የጠፋበት ሰው የሕዝብ ታዛቢዎች የሚያውቁት ከሆነ እንዲመርጥ ይደረጋል፡፡ ሕጉ ባያስማማኝም ከምርጫ ቦርድ የወረደ ስለሆነ ተቀብያለሁ፡፡ መራጮች በዚህ ምርጫ ጣቢያ ያለመታወቂያ መምረጥ እንደማይቻል ሲገለጽላቸው፣ መጀመርያ ያለመታወቂያ ምርጫ ካርድ ሰጥታችሁናል፡፡ ስለዚህ መምረጥ እንችላለን የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፤›› የሚሉት ታዛቢው፣ በሕጉ መሠረት መታወቂያ የሌላቸውን ሰዎች እናውቃቸዋለን ብለው ምስክርነት የሚሰጡት የሕዝብ ታዛቢዎች ብቻ ሳይሆኑ የኢሕአዴግ ታዛቢዎች ጭምር እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ አሠራሩ የአገሪቱን ሕግ የሚፃረር መሆኑን በማስረገጥ ታዛቢው ተከራክረው ያለመታወቂያ እንዳይመርጡ ያደረጓቸው ግለሰቦች ቢኖሩም የመረጡም አሉ ይላሉ፡፡

የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ አቶ ታደሰ አሽኔ ቅሬታውን እንደማይቀበሉት ነው የገለጹት፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ መታወቂያ የጠፋባቸው ወይም ያልያዙ የኮንዶሚኒየሙ ነዋሪዎች የሕዝብ ታዛቢዎች ማንነታቸውን እስካወቁ ድረስ ድምፅ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ ከሕዝብ ታዛቢዎች ውጪ ግን የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ስለግለሰቦቹ ማንነት ምስክርነት አልሰጠም ይላሉ፡፡ 

በጣቢያው የኢሕአዴግ ታዛቢ ወ/ሪት ጽጌ ፀጋዬ በበኩላቸው የምርጫ ካርድ ሲወስዱ መታወቂያ ኖሯቸው የጠፋባቸው ግለሰቦች በሕዝብ ታዛቢዎች እስከታወቁ ድረስ ድምፅ መስጠታቸው አግባብ ነው ይላሉ፡፡ የኮንዶሚኒየሙ ነዋሪዎች በርካታ በመሆናቸው የሁሉንም ማንነት ለማወቅ አይቻልም የሚሉት ታዛቢዋ፣ ማንነታቸው ሳይታወቅ የመረጡና ፓርቲያቸውም ጣልቃ ገብቶ እናውቃቸዋለን ያላቸው ግለሰቦች እንደሌሉ ገልጸዋል፡፡ በጣቢያው የሕዝብ ታዛቢ ወ/ሮ ዘውድነሽ ድንቁ እንደሚናገሩት፣ መታወቂያ የሌላቸውና እሳቸውና የተቀሩት የሕዝብ ታዛቢዎች ያላወቋቸው ሰዎች ድምፅ እንዳይሰጡ አግደዋል፡፡ 

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሳሪስ የተካሄደውን የድምፅ ቆጠራ ሪፖርተር የተከታተለው በወረዳ 10 ምርጫ ጣቢያ ሰባትና ስምንት ነበር፡፡ 12 ሰዓት ካለፈ በኋላ የድምፅ መስጫ ኮሮጆዎች ተቆልፈው በአቆጣጠሩ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ የሕዝብ ታዛቢዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮችና የምርጫ አስፈጻሚዎች ተወያይተዋል፡፡

መራጮች ድምፅ በሚሰጡበት ወቅት ‹‹X›› ምልክት ማድረግ እንዳለባቸው ቢገለጽም፣ በመዘንጋት ወይም በተለያየ ምክንያት ‹‹ü›› ያደረጉት ድምፅ እንደሰጡ መቆጠር አለበት የሚል ክርክር በምርጫ ጣቢያ ሰባት ቢነሳም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ከአሻራና ‹‹X›› ምልክት ውጪ ያሉ ወረቀቶች ፊርማ ወይም ጽሑፍ የተቀመጠባቸውና ከአንድ በላይ ፓርቲ ላይ ምልክት የተደረገባቸው ድምፅ አልባ ሆነዋል፡፡ 

በሁለቱ ምርጫ ጣቢያዎች ለሰዓታት የዘለቀው ቆጠራ ሁሉንም ታዛቢ አካላት ለማሳተፍ የተሞከረበት ነበር፡፡ በምርጫ ጣቢያ ሰባት ታዛቢ የነበሩት የመድረክ ተወካይ አቶ ኪሳ ተመስገን፣ ምርጫ ቦርድ ባወጣው ሕግ መሠረት ቆጠራው መካሄዱንና ሒደቱም ‹‹ፍትሐዊ ነው›› ብለዋል፡፡ በጣቢያው የኢሕአዴግ ተወካይ አቶ የሥጋት ፈጠነም ቅሬታ እንደሌላቸው ነው የተናገሩት፡፡

በዞን ሁለት ምርጫ ክልል 24 ጦር ኃይሎች አካባቢ የተወዳደሩት የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሐሪ ምርጫ ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት፣ ምርጫው ካልተጭበረበረ እንደሚያሸንፉ ነው፡፡ አቶ አበባው በዕለቱ ለመምረጥ የምርጫ ካርዳቸውን ይዘው የነበረ ቢሆንም ከሚመርጡበት ጣቢያ ስምዎት የለም በመባላቸው ሲንከራተቱ ነበር፡፡ ሆኖም ተሳክቶላቸው በዞን ሁለት ምርጫ ክልል 24 ምርጫ ጣቢያ ስምንት ላይ መምረጥ ችለዋል፡፡

በዞን ሦስት ምርጫ ክልል 18 የተወዳደሩት የ32 ዓመቷ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ በአዲስ አበባ ኢሕአዴግን ወክለው ለተወካዮች ምክር ቤት ከቀረቡ 23 ዕጩዎች አንዷ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቅም ግንባታ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት ወ/ሮ ዳግማዊት፣ የምርጫ ጣቢያዎቹ ሒደት ጥሩ ሊባል የሚችል፣ እናቶች፣ ወጣቶችና አዛውንቶች ያዩባቸውና ይኽም ኅብረተሰቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ለመጠቀም ያለውን ዝግጅት ያሳየ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ወ/ሮ ዳግማዊ የ2007 ዓ.ም. ምርጫ ከ2002 ጋር ሲነፃፀር በሒደቱ የተሻለ ነው፡፡

በዞን ሁለት ምርጫ ክልል 24 ጣቢያ 2 ድምፅ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እውነቱ ብላታ ምርጫው ሰላማዊና ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የሒደቱን ሰላማዊነትና አሳታፊነት በቃላቸው የገለጹበት መሆኑን ጥቃቅን ችግሮች ሲከሰቱ ወዲያው የመፍታት ሒደት እንደነበር አመልክተዋል፡፡ 

በአዲስ አበባ ካሉ የምርጫ ክልሎች ውስጥ በምርጫ ክልል 17 (ቦሌ) የተሻለና የተቀራረበ ውጤት እንዲጠበቅ ላደረገው ግምት መነሻ የሆነው ደግሞ በክልሉ የሚወዳደሩት እጩዎች ማንነት ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በአዲስ አበባ አስተዳደር የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ በአቶ ዮሐንስ በቀለ፣ ሰማያዊ ፓርቲ በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው በአቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ ኢዴፓ በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው በአቶ ወንድወሰን ተሾመ እንዲሁም ኢራፓ በፕሬዚዳንቱ በአቶ ተሻለ ሰብሮ ተወክለው ነበር፡፡

ሪፖርተር በምርጫ ክልሉ በሚገኙ ጣቢያዎች ውስጥ ያገኛቸው የምርጫ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች ሒደቱን ያልተረዱት መራጮች እጅግ ትንሽ እንደሆኑና አብዛኛዎቹ ግን ስለ ሒደቱ አስቀድመው ግንዛቤው ያላቸው እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ በምርጫ ክልሉ በሚገኘው ወረዳ 13 ውስጥ 18 የምርጫ ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን፣ ገርጂ ታክሲ ተራ አካባቢ የሚገኘው ምርጫ ጣቢያ 4 ኃላፊ አልማዝ ደሳለኝ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በጣቢያው ድምፃቸውን የሰጡት መራጮች ያለምንም ግራ መጋባት ሒደቱን ፈጽመዋል፡፡ የወረዳ 6 የምርጫ አስተባባሪ አቶ ታምራት ፍርድአወቅ በተመሳሳይ መራጩ ሒደቱን አስቀድሞ ተረድቶ በመምጣቱ አስረዱኝ ብሎ የሚጠይቀው እጅግ ጥቂቱ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በምርጫ ሒደት ውስጥ ከሽግግር መንግሥቱ አንስተው ተካፋይ እንደሆኑ የገለጹት አቶ ታምራት፣ የሕዝቡ ንቃተ ህሊና ከምንጊዜውም በላይ አሁን ያደገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ 

በወረዳ 3 ከሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በአንዱ ያገኘናቸው የኢሕአዴግ ታዛቢ አቶ አዲሱ አካለ የምርጫ አስፈጻሚዎች የተሻለ አቅምና አደረጃጀት በመገንባታቸው መራጩ በቀላሉ በምርጫው ሒደት እንዲያልፉ አስችሏል፡፡ በዚያው የምርጫ ጣቢያ ያገኘናት የሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ታዛቢ ወጣት ቅድስት ግርማ መራጮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው በሚገባ የተረዱ እንደሆኑ አስገንዝባለች፡፡ ይሁንና በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዛቢዎች አልነበሩም፡፡ 

በምርጫ ሒደቱ ሲሳተፉ ካገኘናቸው መካከል አቶ ገናናው ጃቢር፣ ወጣት ሔኖክ ተስፋዬና ወጣት አሰገደች አብርሃም በሒደቱ በመሳተፍ በአገራቸው ጉዳይ ላይ ውሳኔ በማሳረፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የ21 ዓመቱ ወጣት ሔኖክ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ መሳተፉ ነበር፡፡ ‹‹የምፈልገውን ተወካይ በነፃነት በመምረጥ በአገሬ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ የምችልበት ዕድሜ ላይ በመድረሴ ደስተኛ ነኝ፤›› ብሏል፡፡ 

በምርጫ ጣቢያ 4 የድምፅ መስጠት ሒደቱ 12 ሰዓት ምሽት ላይ ተጠናቆ ቆጠራው 1 ሰዓት ተጀምሮ ከምሽቱ 5 ሰዓት ላይ እስኪጠናቀቅ ሪፖርተር ሒደቱን የተከታተለ ሲሆን፣ በጣቢያው የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢዎች ተገኝተው ነበር፡፡ 

በምርጫ ክልል 5 መርካቶ አካባቢ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ ማልደው ከመጡ መራጮች ውስጥ አንዱ በሠላሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ታሪኩ ደምሴ ነበር፡፡

ታሪኩ በ1997 ዓ.ም. እና 2002 ዓ.ም. በተደረጉት ጠቅላላ ምርጫዎች ተሳትፏል፡፡ ‹‹የሚበጀኝን ፓርቲ የመረጥኩበት መሥፈርት የፓርቲው የወደፊት ራዕይና እስካሁን ያሳያቸው ነገሮች ናቸው፡፡ ይህንንም ከተከታተልኳቸው የምርጫ ክርክሮች ተረድቻለሁ›› ሲል አስተያየቱን ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡

በምርጫ ክልል 5 በ2002 ዓ.ም. በተደረገው ጠቅላላ ምርጫ መድረክ አብላጫ ድምፅ በማግኘት ያሸነፈበት ነው፡፡ መድረክን የወከሉት አቶ ግርማ ሰይፉ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራጭ መሆናቸው ይታወሳል፡፡ 

በዚሁ የምርጫ ክልል ዘንድሮ ኢሕአዴግና መድረክን ጨምሮ 12 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፎካክረዋል፡፡ ምርጫ ክልል 5 የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በዕጣ ከተወዳዳሪነት ውጪ በመሆናቸው ፓርቲው በዚህ ክልል ተወዳዳሪ አልነበረውም፡፡ 

ቲና ወልደ ማርያም፣ ከእህቷ ከቤዛ ወልደ ማርያምና ከጎረቤቷ ውድነሽ ወርቁ ጋር በመሆን ቲና የስድስት ወር ውድነሽ ዓመት ከሁለት ወር የሆናቸውን ወንድ ልጆቻቸውን ታቅፈው ድምፅ ለመስጠት ማልደው ካዛንቺስ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ፊት ለፊት በሚገኘው የምርጫ ጣቢያ ተገኝተዋል፡፡ 

ቲናና ውድነሽ በምርጫ ክልል 15 የነባር ቀበሌ 31 ምርጫ ጣቢያ አዳራሽ ውስጥ የተገኙት በዕለቱ ወንድ ልጆቻቸውን ኪዳነ ምሕረት ከማቁረባቸው በፊት ለመምረጥ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ 

በእነዚህ ጣቢያዎች ከሚወዳደሩት 12 ፓርቲዎች መካከል የኢሕአዴግ፣ የሰማያዊ፣ የመድረክና የመኢአድ ታዛቢዎች የተገኙ ሲሆን፣ በድምፅ አሰጣጥ ሒደቱ ችግር እንዳላጋጠማቸው ገልጸዋል፡፡

ሾላ መገናኛ አካባቢን ከያዘው ምርጫ ክልል 16 ውስጥ ከሚገኙት የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች አንዱ የሆነውና መገናኛ የካ ተራራ ላይ የሚገኘው የወረዳ 5 ምርጫ ጣቢያ 4 የቦታው አቀማመጥና አቀበታማው መልክዓ ምድርና ወደ ጣቢያው የሚወስዱት መንገዶች በቀላሉ ለመንቀሳቀስ አዳጋች ነበሩ፡፡ 

ምንም እንኳ ጣቢያው የሚገኝበት ቦታ አቀማመጥ ቀና ባይሆንም መራጮችን በሰዓቱ ተገኝተው ድምፅ የመስጠቱን ሒደት እንዳልገደበው የጣቢያው አስተባባሪ አቶ ሰለሞን አሞኘ ገልጸውልናል፡፡ 

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በወረዳ ዘጠኝ ከሚገኘው የምርጫ ጣቢያ ሦስት ቅጥር ግቢ አጠገብ አንዲት በዕድሜ የገፉ ባልቴት በምርኩዛቸው እየተደገፉ ወደ ቤታቸው ሲያመሩ አግኝተናቸዋል፡፡ ባልቴቷ ወ/ሮ ጠይባ አቡበከር ይባላሉ፡፡ ወይዘሮ ጠይባ እንዳጫወቱን ከሆነ ዕድሜያቸው 100 ሊሞላ ሦስት ዓመት ብቻ ነው የቀረው፡፡ “ሌላ የምርጫ ካርድ ለማምጣት ወደ ቤቴ እየሄድኩ ነው፤” አሉን፡፡ 

ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ደበበ የጣቢያው ምርጫ አስፈጻሚ የሚሉት ደግሞ ባልቴቷ ለመምረጥ በቅድሚያ መመዝገባቸው ተረጋግጧል፡፡ ይሁን እንጂ ሳይመርጡ የተመለሱትም በ2005 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ የተመዘገቡበትን የምርጫ ካርድ ይዘው በመምጣታቸው በመሆኑ የአሁኑን ምርጫ ካርድ ይዘው መጥተው እንዲመርጡ ተነግሯቸዋል፡፡  

ሽሮ ሜዳ አካባቢ በሚገኘው የዞን 4 ምርጫ ክልል 11 ጣቢያ ጧት 2፡20 ሰዓት ላይ ተገኝተው ድምፅ የሰጡት የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩው አቶ ስለሺ ፈይሳ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንትና የምርጫ ጉዳዮች አስተባባሪ ናቸው፡፡ በምርጫው ሒደት ታዛቢዎቻቸው በተዘዋዋሪ ታዛቢዎች ምርጫውን ለመከታተል እንደሞከሩ ገልጸውልናል፡፡ 

በወረዳ 11 ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው የምርጫ ጣቢያዎች የተለያዩ የምርጫ ታዛቢዎችን የተመለከተ ቢሆንም፣ በ20 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የተገኘው አንድ የሰማያዊ ፓርቲ ታዛቢን ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የኢሕአዴግ፣ የሲቪክ ማኅበራት ጥምረትና የሕዝብ ታዛቢዎችን ተመልክቷል፡፡ 

በሌላ በኩልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚገኙ 17 የምርጫ ጣቢያዎችም የክልል ተወላጆች ሲመርጡ ውለዋል፡፡ ሆኖም እስከ ቀኑ 8፡30 ድረስ ለአንዳንዶቹ የመምረጫ ሰነድ ተማልቶ ባለመቅረቡ መራጮች ተቸግረው ነበር፡፡

በዩኒቨርሲቲው ሥር በሚገኙ 15 ካምፓሶች የሚማሩ 7,029 የክልል ተወላጆች በክልልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ለመሳተፍ ካርድ የወሰዱ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ ከትግራይ አክሱም፣ ከጋምቤላ አንዳንድ አካባቢዎች፣ ከአማራ አምባሰል፣ ከሐረሪ አንዳንድ አካባቢ ለመጡ ተማሪዎች በምርጫው ሙሉ ለሙሉ ለመሳተፍ የሚያስችላቸው ሰነድ እስከተጠቀሰው ሰዓት ድረስ ተሟልቶ አልቀረበም፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚዳንት አቶ ቢኒያም ጫኔ እንደሚሉት፣ ችግሩ የተፈጠረው በዩኒቨርሲቲው ሳይሆን በምርጫ ቦርድ ነው፡፡ በመሆኑም ችግሩን ለምርጫ ቦርድ አሳውቀዋል፡፡ የምርጫ ቦርድ በሰጠው መግለጫ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በክልል በሚገኙ ከፍተኛ ተቋማት ምርጫ ሒደት ላይ ለተፈጠረው ክፍተት ይቅርታ ጠይቋል፡፡ አንድም ተማሪ ሳይመርጥ እንደማይቀርና ችግሩም እንደሚፈታ አሳውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዕለቱ ሰነድ ተሟልቶላቸው ምርጫ ያጠናቀቁ ሲሆን የክልል ተማሪዎች ግን ምርጫውን ያጠናቀቁት በማግስቱ ሰኞ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ሲመርጥ ያገኘነው የ23 ዓመቱ ይድነቃቸው ጥላሁን ውልደቱ ኢሉአባቡራ ዞን ጎሬ ከተማ ሲሆን፣ የሁለተኛ ዓመት የሶሻል ወርክ ተማሪ ነው፡፡

ለመጀመርያ ጊዜ በምርጫ እንደተሳተፈ የሚናገረው ይድነቃቸው በያሉበት ዩኒቨርሲቲ ሆነው መምረጣቸው መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ተከልለው መምረጣቸውም ምንም ጫና እንደማይፈጥርበት፣ የመምረጥም ሆነ ያለመመረጥ መብቱን ሊጠቀም እንደሚችልም ነው የገለጸልን፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቢሾፍቱና በፍቼ የሚገኙት ካምፓሶችን ጨምሮ በ17 የምርጫ ጣቢያዎች የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የደቡብ፣ የትግራይ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የአፋር፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ የሐረሪና የጋምቤላ ተወላጅ ተማሪዎች ድምፅ ሰጥተዋል፡፡

በተያያዘም በአዲስ አበባ ከተማ በዞን 5 የምርጫ ክልል በወረዳ 2 እና 14 ምርጫ ጣቢያ፣ በብሔራዊ ሎተሪ ግቢ ድምፅ መስጫ የተዘጋጀላቸው የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች፣ ለክልልና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ሦስት ቢሆኑም፣ ለውድድሩ ብቸኛ ተወዳዳሪ ሆኖ የቀረበው ሐብሊ (የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ) መሆኑን አስተባባሪው አቶ አደም አቡበከር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

በአዲስ አበባ ነዋሪ ለሆኑት ሐረሪዎች ክልላቸውን የሚመሩላቸው 14፣ በፓርላማ የሚወክሏቸውን አንድ ዕጩ ለመምረጥ በአዲስ አበባ በተለያዩ አምስት ጣቢያዎች ሲመርጡ መዋላቸውን አውስተዋል፡፡ ለፓርላማው ብቸኛ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ወ/ሮ ኑሪያ አብዱራህማን ኡመር ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ሐረሪዎች ለሚኖሩበት ወረዳ በፓርላማ የሚወክላቸውን፣ በሐረሪነታቸውም ከሐረር በፓርላማ ለሚወክላቸው ድምፆች ይሰጣሉ፡፡ 

የሐረሪ ተወላጆች ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ በአዲስ አበባ ከተማ ከ1987 ዓ.ም. የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ጀምሮ እንደሚመርጡ ይታወቃል፡፡

(ዘገባውን ያጠናቀሩት ምሕረተሥላሴ መኰንን፣ ምሕረት ሞገስ፣ ታምሩ ጽጌ፣ ታደሰ ገብረማርያም፣ ይበቃል ጌታሁን፣ ቴዎድሮስ ክብካብ፣ ሚኪያስ ሰብስቤ፣ ሰሎሞን ጎሹና ሔኖክ ያሬድ ናቸው)

 

ምርጫ በባህር ዳር

ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ የባህር ዳር ከተማ ንግድ መደብሮች በጊዜ መዘጋት ጀምረዋል፡፡ በምርጫው ዕለትም የሕዝቡና የተሸከርካሪዎች ተቀዛቅዞ፣ አብዛኛው ሕዝብ በሌሊት ወጥቶ ድምጽ ከመስጠት ውጭ እንደወትሮው በባህር ዳር

ጎዳናዎች ላይ የነበረው እንቅስቃሴ ተዳክሞ ታይቷል፡፡ በቀድሞው የከተማዋ አስተዳደር በ17 ቀበሌዎች በአሁኑ አስተዳደራዊ መዋቅር ደግሞ በዘጠኝ ክፍለከተሞች የተደራጀችው ባህር ዳር ከተማ፣ ለ2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ በከተማው ከሚኖረው ሕዝብ ውሰጥ ድምጽ ለመስጠት ከ92 ሺሕ በላይ ነዋሪ ተዝግቦ ነበር፡፡ የከተማው ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ማስተባበሪያ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት 86 ከመቶ ያህል የባህር ዳር ነዋሪ ግንቦት 16 2007 ዓ.ም. ድምጽ በመስጠት ተሳትፏል፡፡ 

ፋሲሎ ክፍለ ከተማ ወይም በቀድሞው ጊዜ ቀበሌ 03ና 15 የነበሩት፣ ሕዳር 11 ወይም ቀበሌ 11፣ ጣና  ክፍለ ከተማ (ቀበሌ 11)፣ ሽንብጥ (ቀበሌ 13)፣ በላይዘለቀ (ቀበሌ 07/08)፣ ሠፈረ ሰላም (ቀበሌ04)፣ ግሽ አባይ (ቀበሌ 12ና 16)፣ ሹም አቦክፍለከተማ (ቀበሌ 10) በሚባሉትና በሌሎችም የተደለደሉ 115 የምርጫ ጣቢዎች ውስጥ ምርጫ ሲካሔድ በዋለበት ዕለትም ሆነ ከምርጫው ዋዜማ በፊትም ቢሆን በሦስት ወገን የሚሰሙ ምርጫውን የተመለከቱ ድምጾች ነበሩ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ገዥው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ኢሕኣዴግና ምርጫ ቦርድ በየፊናቸው በባህር ዳር ሊካሔድ ስላለው ምርጫ ተናግረዋል፡፡ 

በምርጫው ዋዜማ ፓርቲዎች ምን አሉ 

በባህር ዳር ከሚወዳደሩ ፓርቲዎች መካከል ከምርጫው አስቀድሞ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሰማያዊና የኢትዮጵያውያውን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እንዲሁም የገዥው የብአዴን/ኢሕኣዴግ አመራሮች በፊናቸው የሚሉት አላቸው፡፡ 

በአማራ ክልል ከተወዳደሩት 16 የፖለቲካ ፓርቲዎችና አንድ የግል ዕጩ አኳያ፣ በሁሉም መስኩ ብኣዴን ፈርጣማ ነበር፡፡ በመላው አማራ ክልል ካቀረባቸው 137 ዕጩ ተወዳዳሪዎች ባሻገር የምርጫ ቅስቀሳ ሲያካሒድ፣ በጀት ሲመድብ፣ ታዛቢ ሲያሰማራ ወዘተ. ከፍተኛውን የበላይነት ይዞ ነው፡፡ በአንጻሩ የብኣዴን ተፎካካሪዎች በራሳቸው የአቅም ችግርና በገዥው ፓርቲ ደረሱብን ባሏቸው ጫናዎች ከቅስቀሳ እንከ ታዛቢ ማሰማራት ባለው ሒደት ላይ ደካማ ሆነው ታይተዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 51፣ ለክልል ምክር ቤት 82፣ ኢዴፓ ለተወካዮች 56፣ ለክልል 25፣ መኢኣድ፣ ቅንጅት ለተወካዮች 37፣ ለክልል 22፣ አምድነት ለተወካዮች ምክር ቤት 24፣ ለክልል 28 ዕጩ ተመራጮችን ካስመዘገቡ መካከል ናቸው፡፡ 

ኢዴፓ፣ ቅንጅት፣ ኢዴኣን፣ አገሕዴፓ/ የአገው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/ ብኣዴን/ በየ15 ቀኑ በጋራ ይነጋገራሉ፡፡ የባህር ዳር ከተማ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ፈንታ ደጀን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ብኣዴን ኢሕኣዴግ እንደ ፓርቲ የተቃሚዎቹ ተወዳዳሪ ቢሆንም፣ እንደመንግሥት ግን ተወዳዳሪዎቹ ላይ ጫና ይደረግባቸው እንደሆነ፣ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች እገዛ ይፈልጉ እንደሆነ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡ አቶ ፈንታ ደጀን በባህር ዳር ከተማ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የብኣዴን አመራር ናቸው፡፡ አቶ ፈንታ ለፓርቲዎች ይህንን ማድረጋችን ለዴሞክራሲ ስንል ነው ባይ ናቸው፡፡ ‹‹ይህንን የምናደርግበት ምክንያት ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓትና ለዴሞክራሲ መጎልበት የሚናቸውን አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ በማገባት ነው፤›› ብለዋል፡፡  

ሆኖም በባህር ዳር ምርጫ ክልል በገዥው፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪዎች የተነሱ ቅሬታዎች ነበሩ፡፡ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢው አቶ ፈንታ ከሚጠቅሷቸው ችግሮች መካከል የፖስተር መቀደድ፣ የባነር ማስታወቂያ መነሳት ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡ ያለመጣጣም ‹‹የመገፋፋት››፣ የሥነ ምግባር ደንብ ጥሰት በፓርቲዎች ሲፈጸሙ ነበር የሚሉት አቶ ፈንታ በተለይ አገዴፓ በገበያ ቀናትና በአብያተ ክርሲያናት ውስጥ ቅስቀሳ በማድረጉ ጥሰት ፈጽሟል ብለዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ክሶች ሲቀርቡበት የነበረው አገዴፓ ስህተቶቹን እንዲያርም መደረጉን፣ በጨለማ ስብሰባ ሲያካሒዱ የነበሩ ፓርቲዎች እንደነበሩም አቶ ፈንታ ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች በውይይትና በመነጋገር መፈታታቸውን አስታውቀዋል፡፡ 

ሰማያዊ ፓርቲ ከሌሎች ይልቅ በ2007ቱ ምርጫ ተራማጅ የነበረና ለመንግሥትም ስጋት መሆኑ የታየ ይመስል ነበር፡፡ በአጥፊነት መንግሥት ደጋግሞ ስሙን ሲያነሳው ከርሟል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ውስጥ አባል አይደለም፡፡ አባል ያልሆነበት ምክንያትም ምክር ቤቱ ላይ እምነት ስለሌው እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ሆኖም ሰማያዊን ጨምሮ የምክር ቤቱ አባል የሆኑ ፓርቲዎች በባህር ዳር፣ በዘጌ መሸንቴ፣ በዘንዘልማና በጢስ አባይ ዙሪያ የታሰሩባቸው ታዛቢዎችና ዕጩ ተወዳዳሪዎች እንደነሩ ገልጸዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዴምካራሲያዊ ፓርቲ(ኢዴፓ)ና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች በባሕር ዳርና በዙሪያው በሚገኙ የምርጫ ክልሎች ለተመራጭነት ያቀረቧቸው ዕጩዎችና የምርጫ ታዛቢዎች ላይ ምርጫው ሊካሔድ አንድ ቀን እስኪቀረው ድረስ እሥራትና ድብደባ ሲፈጸምባቸው እንደነበር ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ የአካባባው ምርጫ አስፈጻሚዎች ችግሩን እንደማያውቁት አስታወቀዋል፡፡ 

ሻምበል ያየህይራድ ዘለቀ የኢዴፓ ተወካይና በባህር ዳር ምርጫ ክልል ፓርቲያቸውን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ ናቸው፡፡ ሻምበል ያየህይራድ በባህር ዳር ከተማ  ለሪፖርተር የምርጫ ዘጋቢ እንዳስታወቁት፣ እሳቸው በሚወዳደሩበት የምርጫ ክልልም ሆነ በባህር ዳር ዙሪያ በሚገኙት ዘጌ መሸንቲ፣ ጢስ አባይ-ዘንዘልማ የምርጫ ክልሎች ውስጥ የኢዴፓ አባላት ላይ እሥራትና እንግልት ተፈጽሟል፡፡ በተለይ በዘጌ መሸንቲና በጢስ አባይ-ዘንዘልማ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ለታዛቢነት ተመድበው የነበሩት ሁለት የፓርቲው ተወካዮች አርብ ዕለት ታሥረው በማግሥቱ መፈታታቸውን ገልጸዋል፡፡ በምን ምክንያት እንደታሰሩ እንዳላወቁ ገልጸዋል፡፡ የፖስተሮች መቀደድ፣ የባነር ማስታወቂያዎች መነሳት ሲያጋጥሙ ከነበሩ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ሻምበል ያየህይራድ አስታውቀዋል፡፡ በጎንጂ፣ በቆለላ፣ በአዴት ምርጫ ክልሎች እንዲወዳደሩ ያቀረባቸው ዕጩዎች በምርጫ ቦርድ መሰረዛቸውንና የተሠረዙበት ምክንያትም ለኢዴፓ እንዳልተገለጸት ተናግረዋል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲም ተመሳሳይ ጫና ሲደርስበት እንደቆየ አስታውቋል፡፡ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም ዘኖች ያቀረባቸው ዕጩዎች ላይ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ለበርካታ ጊዜያት እሥራትና ድብደባ ተፈጽሟል፡፡ በተለይ ሲነን በምትባለው ወረዳ በርካታ አባላቱ ሲታሰሩ እንደነበር አቶ ናትናኤል ገልጸዋል፡፡ በባህር ዳር ምርጫ ክልል እንዲወዳደሩ ካቀረባቸው ሁለት ዕጩዎች አንዱ ተሰርዘው፣ በአንድ አባል ብቻ ለተወካዮች ምክር ቤት ለመወዳደር መገደዱን አስታውቀዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የባህር ዳር ጽሕፈት ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ማሩ ዳኜም በርካታ እንግልት በአባሎች ላይ ሲደርስ መቆየቱን ገልጸው፣ ሚዲያው በሚደርስብን በድልና እንግልት ላይ ዝምታን መርጧል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡  ሰማያዊ ፓርቲ በአገርአቀፍ ደረጃ 200 ዕጩዎች አንደተሰረዙበት ሲገልጽ፣ ኢዴፓ በበኩሉ 90 ዕጩዎች እንደተዘሩበት ይፋ አድርጓል፡፡

የባህር ዳርና ዙሪያው የምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪዎች በበኩላቸው ታሠሩ ስለተባሉት የሁለቱ ፓርቲዎች አባላት የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ አቶ ገረመው አሥራት የባህር ዳር ምርጫ ክልል፣ የምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ናቸው፡፡ አቶ ገረመው ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በምርጫ ቦርድ አሠራር መሠረት ፓርቲዎች በደብዳቤ የደረሱባቸውን ችግሮች ማሳወቅ ሲኖርባቸው፣ ቦርዱ ከሰማያዊም ሆነ ከኢዴፓ በጽሑፍ የደረሰው ምንም ዓይነት አቤቱታ የለም፡፡ በዘጌ መሸንቲ ምርጫ ክልል የምርጫ አስተባባሪዎች ኢዴፓ ታስረውብኝ ነበር ስላላቸው የምርጫ ታዛቢዎች የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በበኩሉ ‹‹አንድም ዕጩ ሆነ ታዛቢ ስለመታሠሩ ምንም የመጣ አቤቱታ የለም፡፡ እርግጥ ቀደም ሲል በምዕራብ ጎጃም ውስጥ በምትገኝ አንዲት ወረዳ ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ተይዞ ነበር፡፡ ማንነቱ ሲጠየቅ ዕጩ ነኝ እናንተ ልትጠይቁኝ አይገባም በማለት ግጭት ተፈጥሮ ታስሮ ነበር፡፡ ይሄ ሰው ታስሮ የነበረው በዕጩ ምዝገባ ጊዜ ሲሆን ያኔውኑ ተለቋል፤›› በማለት አቶ ፈንታ ስለፓርቲዎቹ ቅሬታ ከሪፖርተር ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ ነበር፡፡ ምርጫው ሊካሄድ አንድ ቀን እስኪቀረው ድረስ ዘጌ መሸንቲም ሆነ ጭስ አባይ ላይ አንድም ሰው አልታሰረም ካሉ በኋላ ‹‹የታሠረ፣ የተደበደበ፣ የተሰረዘ እኔ የማውቀው ዕጩ የለም፤›› በማለት በተቀናቃኝ ፓርቲዎች በኩል ለሪፖርተር ያነሷቸውን ቅሬታዎች እንደማያውቋቸው ገልጸዋል፡፡ 

የፓርቲዎች የዕጩ ተወዳዳሪ ወኪል ታዛቢ መመዝገብ ያለበት የምርጫ ቀን ከመድረሱ አሥር ቀናት በፊት ሲሆን፣ መመሪያ ቀጥር 3/2001 አንቀጽ 19 ላይ በሰፈረው መሠረት ፓርቲዎች ታዛቢዎቻቸውን በማቅረብ እንዲያስመዘግቡ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ምርጫው አንድ ቀን እስኪቀረው ድረስ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በመወከል ለሚገኑ ታዛቢዎች መታወቂያ ሲሰጥ እንደነበር በባህር ዳር ዙሪያ ከሚገኙ ምርጫ አስተባባሪዎች ተገልጿል፡፡

በምርጫው ዕለት ያልታዩት የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢዎች

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ታዛቢ ብቻም ሳይሆን ዕጩዎቻቸውን ማስዝገብና ለምርጫ ማወዳደር እንዳይችሉ መደረጋቸውን ሲገልጹ ከርመዋል፡፡ ያለምንም ማብራሪያ ዕጩዮቼ ተሰርዘውብኛል ካለው ኢዴፓ እስከ ሰማያዊ ፓርቲ በተወዳዳሪ ዕጩ ስረዛ ምርጫ ቦርድን አጥብቀው ሲኮንኑ ከርመዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ 200 ዕጩዎቹ፣ ኢዴፓም ከ90 በላይ ተወዳዳሪዎቹ መሰረዛቸውን በማስመልከት ደጋግመው ሲጠይቁና ፍርድ ቤት ሲመላለሱ ከከረሙ ፓርቲዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ 

ድምጽ በተሰጠበት ዕለት በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዛቢዎችን ማየት አልተቻለም፡፡ የምርጫ አስፈጻሚዎች ስለጉዳዩ ሲጠየቁም፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢዎች አንዳልመጡና እንዳላነጋገሯቸው ጠቅሰዋል፡፡ በአንጻሩ የብኣዴን/ኢህኣዴግ ታዛቢዎች በሁሉም የባህር ዳር ምርጫ ክልልና በዙሪያው በሚገኙ ምርጫ ጣቢዎች ሁሉ ላይ ተገኝተዋል፡፡ 

የክልሉም ሆነ የባህር ዳር ከተማ ምርጫ አሳታፊነቱና ለሌሎች ተቀናቃኝ ፓርቲዎች የሰጠው ቦታ ፍትሃዊ ነው ብሎ ብአዴን ያምናል ወይ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ፈንታ፣ ‹‹በአማራ ክልል ለተወካዮች ምክር ቤት 137 ወንበር አለ፡፡ ለክልል ምክር ቤት 292 ወንበር አለ፡፡ ለእነዚህ ወንበሮች ዕጩ የማቅረብ ሥራ ሠርተናል፡፡ እነሱም [ተቃዋሚዎች] ዕጩ የማቅረብ ሥራ ይሠራሉ፡፡ ቀድመው ያላፈሩትን አባልና ዕጩ በዚህ ወቅት ሊያገኙ አይችሉም፡፡ ይህ ዓይነት ነገር ገጥሟቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ብኣዴን ስለፈለገ ወይም ስላልፈለገ ዕጩ ከማቅረብ የሚያግዳቸው ነገር የለም፡፡ እስከሁን በመደበኛ ሁኔታ እየሔድን ነው የነበረው፤›› ብለዋል፡፡ 

በአንጻሩ ተቃዋሚዎች የሚሰረዙባቸው ዕጩዎች ብቻ ሳይሆኑ ታዛቢዎች መሆናቸውንም ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ በባህር ዳር ምርጫ ክልል ከሚወዳደሩ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የኢትጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የታዛቢነት መታወቂያ ከሰጣቸው ከ60 በላይ ታዛቢዎች ውስጥ አብዛኞቹ እንዳልተገኙለት የባህር ዳር ከተማ የኢዴፓ አመራርና ፓርቲውን ወክለው ለተወካዮች ምክር ቤት የተወዳደሩት ሻምበል ያየህይራድ ዘለቀ ናቸው፡፡ ሻምበል ያየህራድ የፓርቲው ታዛቢዎች ያልተገኙት በፍርሃት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ሁለት ታዛቢዎች መታወቂያችሁ ላይ ፎቶግራችሁ አልተለጠፈበትም ተብለው ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆኖ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫኔ ከበደ ከተወዳደሩባቸውና ጠንካራ ፉክክር ይኖራቸዋል ተብለው ከሚጠበቁት አካባቢዎች አንዱ የባህር ዳር ዙሪያ ዘንዘልማ ምርጫ ክልል ቢሆንም፣ ሪፖርተር በተገኘበት የዘንዘልማ ሚካኤል ምርጫ ቁጥር 2፣ በብኣዴንና ከሕዝብ ታዛቢዎች እንዲሁም ዘግይተውም ቢሆን ከሲቪክ ማኅበራት ጥምረት ታዛቢዎች ታይተዋል፡፡ ከዚህ ውጭ የኢዴፓ ታዛቢዎች በቦታው አልተገኙም ነበር፡፡  በባህር ዳር ምርጫ ክልል ዶክተር በቃሉ አጥናፍና አቶ ወርቁ ጥላሁን የተባሉትን ዕጩዎች በመወከል ከሰማያዊ ፓርቲ የተገኙ የምርጫ ታዛቢዎች ቁጥርም የሉም በሚያስብል መጠን ተገኝተዋል፡፡  

በባህር ዳር ምርጫ ክልል ካሉት 115 ምርጫ ጣቢዎች፣ 663 መራጮች የተመዘገቡበት የሰፈረ ሰላም 04-2ለ ምርጫ ጣቢያ የብኣዴን፣ የኢዴፓና የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ታዛቢዎች ተገኝተዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ታዛቢ  አቶ እንደሻው አቤ ‹‹…ችግሮች አይከሰቱም አይባልም፡፡ ጥቃቅን ችግሮች ተከስተዋል፡፡ ለምሳሌ ለአረጋውያን በድምጽ መስጫ ጣቢያ ውስጥ የድምጽ አሰጣጥ ገለጻ መስጠት ተገቢ ባለመሆኑ ይህ ሒደት ከድምጽ መስጫው ውጭ እንዲደረግ ከብኣዴን፣ ከሕዝብ ታዛቢዎችና ከሲቪክ ማኅበራት ታዛቢዎች ጋር ተነጋግረን እየተስተካከለ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ አቶ ደረጄ ተሾመ የኢዴፓ ዕጩ ተዋወዳዳሪ ታዛቢ ናቸው፡፡ ድምጽ አሰጣጡ ጥሩ አካሔድ ማሳየቱን ገልጸው፣ ሆኖም አረጋውያንን በተመለከተ ከሰማያዊ ፓርቲ ተወካይ ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን አንዳንድ አስገራሚ ክስተቶችንም መታዘብ ተችሏል፡፡ ገነቱ በላይ በሽንብጥ ክፍለከተማ ምርጫ ጣቢያ 1-ሀ-1 አስተባባሪ ናቸው፡፡ በዚህ ጣቢያ ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡ 851 መራጮች ድምጽ እየሰጡ በነበረበት ዕለት ያልተለመደ አሠራር ሲካሔድ ታይቷል፡፡ 

በምርጫ ጣቢያው አንድ ወጣት አቅመ ደካሞችና አረጋውያንን እንዲሁም የአካል ጉዳት ያለባቸውን መራጮች ለማገዝ በሚል በምስጢር ድምጽ መስጫ ቦታው አብሮ ሲገባ ታይቷል፡፡ የምርጫ አስተባባሪው የወጣቱን ገለልተኛነት፣ የትኛውንም ፓርቲ ያልወከለና ያልወገነ እንደሆነ በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡ ይህም ሆኖ ወጣቱ አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢ ባልተገኘበት ምርጫ ጣቢያ በፖለቲካ ፓርቲ ዕጩ ታዛቢዎች ወንበር ላይ ተቀምጦ ታይቷል፡፡  

ምርጫው መጠናቀቁን ተከትሎ በባህር ዳር ድምጽ ይሰጣል ተብሎ ከሚጠበቀው 92, 379 መራጭ ሕዝብ ውስጥ 86 ከመቶ ያህሉ ድምጹን መስጠቱን የባህር ዳር ምርጫ ክልል አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ይፋ አድርጓል፡፡ በባህር ዳር ከተማ በሚገኙት የምርጫ ጣቢያዎች በሁሉም የምርጫ ውጤቶች መለጠፋቸውም ታውቋል፡፡ እስካሁንም ከየትኛውም ተወዳዳሪ ፓርቲ አንድም ቅሬታም ሆነ ክስ  እንዳልደረሳቸው ለጽሕፈት ቤታቸው እንዳልቀረበ የገለጹት በባህር ዳር ምርጫ ክልል የምርጫ አስተባባሪው አቶ ገረመው አሥራት ናቸው፡፡ 

 

ምርጫ በድሬዳዋ

ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሁለት የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ ድሬዳዋ ከተማ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሉትን ሁለት ወንበሮች ለመወከል ተወዳድረዋል፡፡ 

የድሬዳዋ ከተማ በቻርተር ራሱን እንዲያስተዳድር የተፈቀደለት የፌዴራሉ መንግሥት ግዛት ሲሆን፣ በፌዴራል ፓርላማ ውስጥ የሁለት ወንበሮች ውክልና አለው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ሁለት ወንበሮች የሚወክሉ ዕጩዎችን ለመምረጥ ድሬዳዋ በሁለት የምርጫ ክልልና ከሁለት መቶ በላይ የምርጫ ጣቢያዎች ተከፋፍላለች፡፡ 

ድሬዳዋ ከተማን ለሁለት በሚከፍላት አሸዋ ተብሎ የሚጠራውን አካባቢ መሠረት በማድረግ ከአሸዋ በታች ያለውን አካባቢ ምርጫ ክልል አንድ፣ ከአሸዋ በላይ ያለውን ምርጫ ክልል ሁለት ተብሎ ተከልሏል፡፡ በእነዚህ የምርጫ ክልሎች ለመወዳደር የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦሕዴድ)፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)፣ የወለኔ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ወህዴፓ)፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት)፣ የኦሮሞ አቦ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦአነግ) እና ሁለት የግል ተወዳዳሪዎች የምርጫ ቦርድን ዕውቅና አግኝተው በዕጩ ተወዳደሪነት ራሳቸውን አቅርበዋል፡፡

የግል ተወዳዳሪዎቹ ሙክታር ኢብራሂምና ሙስጠፌ ሞሚን የሚባሉ ሲሆን፣ እንደ ቅደም ተከተላቸው ፀሐይና ዳክዬ የምርጫ ምልክቶቻቸው አድርገው የከተማው ነዋሪ እንዲመርጣቸው ቀስቅሰዋል፡፡

ሙክታር ኢብራሂም የ30 ዓመት ወጣት ነው፡፡ ተመርጦ የፓርላማውን መቀመጫ ቢያገኝ፣ ‹‹የተሻለ ኅብረተሰብ ለመፍጠርና በተሻለ የእርሻ ኢኮኖሚ ላይ የተመሠረተ ኅብረተሰብን ማየት ነው፤›› ይላል፡፡ ሙክታር ይህን ይላል እንጂ በዋናነት ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ግንባር ቀደሙ፣ ‹‹በክልላችን መንገዶች እንዲስፋፉና የኢንዱስትሪ ክልል ለማድረግ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፤›› የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡

ከምርጫው በፊት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በከተማዋ ለሚወዳደሩ አራት ፓርቲዎች ከፍተኛ ግምት ሰጥተዋል፡፡ እነዚህም ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ፣ ኢሶዴፓ፣ መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ናቸው፡፡ በተለይ ኢሶዴፓና ኦሕዴድ ከፍተኛ የምርጫ ቅስቀሳ ያደረጉ መሆናቸው፣ የኢሶዴፓ የምርጫ ቅስቀሳ ደግሞ የበለጠ የተደራጀ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ 

በኢሶዴፓ በኩል በዕጩነት የቀረቡት መሐመድ የሱፍ ዑመር ናቸው፡፡ አቶ መሐመድ የሱፍ ባለፈው ምርጫ በዚሁ የምርጫ ክልል ሁለት ተወዳድረው የፓርላማ መቀመጫ ያገኙ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፓርላማው የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

በኦሕዴድ በኩል የቀረቡት ዕጩ አቶ አብዱሰመድ መሐመድ ኢብራሂም ናቸው፡፡ አቶ አብዱሰመድ እንደ ኢሶዴፓው ተወካይ በ2002 ዓ.ም. በነበረው አገር አቀፍ ምርጫ የሕዝብን ውክልና አግኝተው የፌዴራል ፓርላማውን የተቀላቀሉ ቢሆንም፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ በመሆናቸው አብዛኛውን ጊዜ በመንግሥት ሥራ ላይ ነው የሚያሳልፉት፡፡

በሰማያዊ ፓርቲ በኩል በዕጩነት የቀረቡት ደግሞ አቶ ዳንኤል ጉግሳ ገመቹና ገዛኸኝ አሰፋ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው፡፡ በመድረክ በኩል ደግሞ አቶ አህመድ ጀማል ብቻ ናቸው፡፡ 

የሰማያዊ ፓርቲ ተወካይ አቶ ዳንኤል ጉግሳ በምርጫ ክልል አንድ ከኦሕዴዱ ከአቶ አብዱሰመድ ጋር ለፉክክር ቀርበዋል፡፡ የሰማያዊው አቶ ገዛኸኝ አሰፋ ደግሞ ከኢሶዴፓ ተወካዩ አቶ መሐመድ የሱፍና ከመድረኩ ተወካይ አቶ አህመድ ጀማል አህመድ ጋር ቀርበዋል፡፡

የድሬዳዋን ሞቃታማ የአየር ሁኔታ ምክንያት ኅብረተሰቡ ባዳበረው ባህል መሠረት ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ከጠዋቱ 1፡30 ሥራ እንደሚጀምር ይታወቃል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ከዚያ ቀድመው መንቀሳቀስ የሚጀምሩ በመሆናቸው ገበያውም ይደራል፡፡ በመሆኑም የምርጫውን ዕለት ኅብረተሰቡ እንዴት እንደሚጠቀምበት ቀድሞ መገመት ይቻላል፡፡ 

በዚሁ መሠረት ሪፖርተር በምርጫው ዕለት ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በተዘዋዋረባቸው የምርጫ ጣቢያዎች፣ በርካታ ነዋሪዎች (አብዛኞቹ ሴቶች ናቸው) ተሠልፈው ድምፃቸውን ሲሰጡ ለመመልከት ችሏል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አሰድ ዚያድ ገንደቆሬ አካባቢ ማለትም በምርጫ ክልል አንድ ምርጫ ጣቢያ ሦስት ድምፃቸውን ለመስጠት ከጠዋቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ተገኝተዋል፡፡ ከእሳቸው በፊት ግን 103 ነዋሪዎች ድምፃቸውን እንደሰጡ የምርጫ ጣቢያው አስተባባሪ አቶ ጃፋር አሚን ገልጸዋል፡፡ 

ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ የምርጫ ጣቢያው አስተባባሪዎች ተገናኝተው ዝግጅታቸውን እስከ 12 ሰዓት ድረስ አጠናቀው፣ 12 ሰዓት ላይ ድምፅ ለማሰጠት ክፍት ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ 

የድሬዳዋ ከንቲባ አቶ አሰድ ዚያድ ድምፃቸውን ከሰጡ በኋላ፣ ቅድመ ምርጫ ዝግጅቱ በድሬዳዋ በሰላማዊ ሁኔታ ተጠናቆ በስኬት ለምርጫው ዕለት መድረስ መቻሉን ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡

የምርጫው ሒደትም ከተጠበቀው በላይ በፍጥነት እየተከናወነ እንደነበር የገለጹት ከንቲባው፣ እንደ ቅድመ ምርጫው ሁሉ ድኅረ ምርጫውም ሰላማዊ ሆኖ እንደሚጠናቀቅ እርግጠኛ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው 32 የምርጫ ጣቢያዎች በእያንዳንዳቸው በአማካይ የተመዘገቡ መራጮች (ካርድ የወሰዱ ነዋሪዎች) ቁጥር 650 ይሆናል፡፡ የድሬዳዋ ነዋሪዎች የዕለት ሥራቸውን በጠዋት ከውነው እንደሚፈጽሙት ሁሉ፣ ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው የምርጫ ክልሎች ከረፋዱ 5፡30 ሰዓት ላይ 600 የሚሆኑ መራጮች በአማካይ ድምፃቸውን ሰጥተው ነበር፡፡

በከዚራ ሁለት ምርጫ ጣቢያ ለመምረጥ የተመዘገቡ መራጮች ብዛት 562 ሲሆን፣ እስከ ጠዋቱ 1፡30 ድረስ 136 መራጮች ድምፃቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

‹‹በአመዛኙ ምርጫው ከእኩለ ቀን በፊት የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ የግዴታ በሕጉ መሠረት እስከ 12 ሰዓት ድረስ መቆየታችን ግድ ነው፤›› በማለት የምርጫ ጣቢያው አስተባባሪ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው አካባቢዎች በጥቂቶቹ ብቻ የወለኔ ፓርቲ ተወካዮችን ቢመለከትም፣ ከኢሕአዴግ/ኦሕዴድና ከኢሶዴፓ ውጪ የፓርቲ ታዛቢዎችን ያሰማራ ተቃዋሚ ድርጅት የለም፡፡ 

የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪ የሆኑት አቶ ዳንኤል ጉግሳ ፓርቲያቸው የመደበው በጀት በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ የፓርቲ ታዛቢዎችን አበል ከፍሎ ሙሉ ቀናቸውን በመታዘብ ሥራ ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ይቅርና በራሪ ወረቀቶችን ከመበተን ያለፈ የቅስቀሳ ሥራ እንዳላደረጉ ገልጸዋል፡፡

ከሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች በተለየ የፓርላማ ዕጩዎችን ብቻ የሚመርጡት የአገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች ናቸው፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ምርጫ መደረግ የጀመረው በ1999 ዓ.ም. ነው፡፡ ከዚያ ቀደም ድሬዳዋ ከተማ ተጠሪነቷ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሆኑ በሹመት እንጂ ድሬዳዋ ራሷን ማስተዳደር አልጀመረችም ነበር፡፡ 

ይህ የሆነበት ምክንያት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግሥት በድሬዳዋ ላይ የይገባኛል ጥያቄ በማንሳታቸው፣ ጥያቄው እስኪመለስ ድሬዳዋ በፌዴራል አስተዳደር ሥር እንድትሆን በሽግግር መንግሥት ወቅት በመወሰኑ ነው፡፡

ይህንን ጥያቄ እስካሁን መመለስ ባለመቻሉም ድሬዳዋ በፌዴራሉ መንግሥት ሥር ሆና ራሷን የማስተዳደር ሥልጣን በፓርላማ በፀደቀ ቻርተር ያገኘች ከተማ ነች፡፡ ይህንን ዕድል ካገኘች ጀምሮ የኦሕዴድና የኢሶዴፓ ተመራጭ ከንቲባዎች እያስተዳደሯት ይገኛሉ፡፡

 

 

 

 

ምርጫ በኢተያ

ሰማኒያ ስድስት የምርጫ ጣቢያዎች በሚገኙበት በኦሮሚያ ክልል በኢተያ የምርጫ ክልል ሒጦሳ ወረዳ፣ በ2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ ለአራተኛ ጊዜ በተከታታይ ኦሕዴድ/ኢሕአዴግን ወክለው ለምርጫ የቀረቡት የሕዝብ ተወካዮች

ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳን ለመቀበል ሲጠባበቁ የነበሩት ደጋፊዎቻቸው ያልጠበቁትን ዜና ሰምተዋል፡፡ አቶ አባዱላ የምርጫ ካርዳቸውን በአዲስ አበባ በመውሰዳቸው የሚመርጡትም እዚያው አዲስ አበባ በመሆኑ፣ በዘንድሮው ብሔራዊ ምርጫ አቶ አባዱላን ኢተያ ላይ ማግኘት አልቻሉም፡፡ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በትውልድ አካባቢያቸው በመገኘት ምርጫ ሲያደርጉ በቴሌቪዥን የተመለከቱ ደጋፊዎቻቸው የአቶ አባዱላ በወረዳቸው አለመገኘት ቅር እንዳሰኛቸው ለሪፖርተር የገለጹም ነበሩ፡፡ ‹‹እዚህ ተገኝቶ ሲመርጥ ብናየው ደስ ይለን ነበር፣›› ያሉት አቶ ቶሎሳ አዱኛ እና ወ/ሮ ደሚቱ ገመቹ፣ የአቶ አባዱላን በምርጫ ጣቢያው አለመገኘት ያልጠበቁት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሥራ ምክንያት እንደማይመጡም ከአካባቢው የኦሕዴድ ባለሥልጣናት እንደተነገራቸው ጠቁመዋል፡፡ 

‹‹እሱ ሥራውን ቀድሞ ስለጨረሰ እዚህ የመምረጥ ያለመምረጡ ጉዳይ ችግር የለውም፡፡ በዚያ ላይ የሥራ ጫና አለበት፣›› ያሉት የወረዳው ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ተጠሪ አቶ ገመቹ አደራ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በአንፃሩ የአቶ አባዱላ በምርጫ ጣቢያው ተገኝቶ አለመምረጥ ለ28 ዓመቱ ብቸኛው ተፎካካሪያቸው አቶ ደረሠ ነገሠ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ የተናገሩት የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) ታዛቢ ሻለቃ አደም ኑራ፣ በምርጫው ብዙ ችግሮችን እየተጋፈጡ ቢሆንም ብቸኛው የኦብኮ ተወዳዳሪ ውጤታማ ሊሆን የሚችልበት ዕድል መኖሩንም ተናግረው ነበር፡፡

‹‹በምርጫው ዕለት መራጮችን በድብቅ በመጥራት ትዕዛዛዊ ምርጫ እንዲያደርጉ መንገርን ጨምሮ የምርጫ ወረቀቶቹን ጥሎ የመውጣት ሒደት ነበር፤›› የሚሉት ታዛቢው፣ የምርጫ ኮሮጆዎቹ ደኅንነት፣ የምርጫ ቁሳቁሶቹ ጤናማነትና የምርጫ ሰዓቱን የመጠበቅ ሁኔታ ግን በግልጽ የታዘቡት ሀቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቅድመ ምርጫ 2007 ኢተያ በኦሕዴድ/ኢሕአዴግ በኩል ሰፊ ሥራ የተሠራበት መሆኑን በአካባቢው የተለጠፉትን ፖስተሮች፣ መፈክሮችና ዓርማዎች በማየት መገንዘብ ይቻላል፡፡ በአንፃሩ አንድ የተቃዋሚ (ተፎካካሪ) ፓርቲ ዓርማም ሆነ ፖስተር ተለጥፎ አይታይም፡፡ ይህን በተመለከተ በሪፖርተር ተጠይቀው ምላሻቸውን የሰጡት የኦብኮው ዕጩ ተፎካካሪ አቶ ደረሠ፣ ፖስተሮቹና ዓርማዎቹ በተለጠፉበት ቅፅበት ተቀዳደው ይነሱ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከለጠፍን ከ20 እና ከ30 ደቂቃ በኋላ ስንመለስ በቦታው አናገኝም ነበር፤›› የሚሉት አቶ ደረሠ፣ ማን ይህን እንደሚፈጽም ግን በግልጽ እንደማያውቁ ያክላሉ፡፡ በአዳራሽ ደጋፊዎቻቸውን በመሰብሰብ ለማነቃቃት ሰፊ ጥረት ቢያደርጉም፣ የአካባቢው ባለሥልጣናት በሕዝቡ ላይ በነዙት ፍርኃትና ዛቻ አዳራሹ ቢፈቀድም ሰው ሊሰበሰብ እንዳልቻለ ገልጸዋል፡፡ አቶ ገመቹ ግን ይህንን ያስተባብላሉ፡፡ በምርጫ ጊዜ የሚደረግ የተለመደ አቤቱታ ነው በማለት፡፡

በምርጫው ዋዜማ የሒጦሳ ወረዳ እስከ ምሽቱ ድረስ ተረጋግታ የታየች ቢሆንም፣ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ ግን ጭር ብላ አንግታለች፡፡ በኢተያ ከተማ የሚገኙ ሆቴሎችና መሸታ ቤቶች በምርጫው ምክንያት በሮቻቸውን መዝጋት እንዳለባቸው ለደንበኞቻቸው ሲናገሩ ነበር፡፡ በወረዳው የሚገኙ አብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች አስፈላጊውን የምርጫ ቅድመ ዝግጅት አሟልተው እሑድ ማለዳን ሲጠባበቁ እንደነበር መታዘብ ተችሏል፡፡ በአንዳንድ ገጠራማ ቦታዎች ግን እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ድረስ ድንኳኖች ሲተከሉ ተስተውሏል፡፡ በምርጫው ዕለት ሕዝቡ በማለዳ ተሠልፎ ምርጫውን በሰላም ማካሄዱን በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች የተስተዋለ ሲሆን፣ ከረፋዱ አራት ሰዓት ጀምሮ ግን ብዙዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ጭር ብለው ታይተዋል፡፡ የኢተያ ከተማና አጎራባች ከተሞችም በምርጫው ዕለት ጭር ብለው ነበር፡፡ 

የኢተያ ምርጫ ክልል የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተጠሪ አቶ ቱሉ ሹሜ ምርጫው ያለምንም ችግር መከናወኑንና ከተወዳዳሪ ፓርቲዎችም የጎላ ቅሬታ እንዳልቀረበ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም የኦብኮ ተወዳዳሪ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች መራጮች በትዕዛዝ ምርጫ እንዲያደርጉ አቶ ከማል በሚባል የአካባቢው ባለሥልጣን በሚስጥር ይነገር ነበር የሚባለውን፣ ከኦብኮ ተፎካካሪ በቃል ሪፖርት እንደተደረገላቸው አቶ ቱሉ ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው ለፉክክር የቀረቡት አራት ፓርቲዎች ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ፣ ኦብኮ፣ አዲስ ትውልድና አንድነት ፓርቲ የነበሩ ቢሆንም፤ በምርጫው ሒደት ግን ተካፋይ የነበሩት ኦሕዴድ/ኢሕአዴግና ኦብኮ ብቻ ነበሩ፡፡ በአካባቢው አዲስ ትውልድ ፓርቲን የወከሉት አቶ ተሾመ ደረሰ ናቸው፣ አንድነትን የወከሉት ደግሞ ሻምበል አማን ሐሰን የተባሉ ግለሰብ ነበሩ፡፡ የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ተወካይ አቶ ተሾመ በምርጫው ለመካፈል ምዝገባቸውን ከጨረሱ በኋላ በምርጫ ቅስቀሳውም ሆነ በውድድሩ ላይ አለመካፈላቸውን አስመልክቶ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ለምርጫው የተመደበልን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ አቶ ሰለሞን በሚባል ሰው ስለተበላብን አቅም አጥሮን ነው፤›› በማለት መልሰዋል፡፡ እንደ አቶ ተሾመ ገለጻ፣ አቶ ሰለሞን የተባሉት ግለሰብ ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ ሲሆን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አስፋው ጌታቸው ወደ ውጭ አገር ሲሄዱ፣ በጊዜያዊነት በአደራ አመራሩን የተረከቡ ናቸው፡፡ ሪፖርተር ግለሰቡን ለማግኘት ባደረገው ጥረት ግለሰቡ ስልካቸውን መመለስ ባለመቻላቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ሰኞ ግንቦት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢተያና በአጎራባች ወረዳዎች የምርጫ ውጤቱ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ መለጠፍ የጀመረ ሲሆን፣ በአንዳንድ ቦታዎች ግን ውጤቱ በተለጠፈበት ቅጽበት ተቀዶ ታይቷል፡፡ ለምሳሌ በአሰላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ተለጥፎ የነበረው የምርጫ ውጤት የኦሕዴድ/ኢሕአዴግን የምርጫ ውጤትና ደረጃን ብቻ ሲያሳይ፣ የሌሎቹን ተፎካካሪዎች ውጤትና ደረጃን የሚያሳየው ሰንጠረዥ ግን እንደተቀደደ ታይቷል፡፡

በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ውጤቱ ከተለጠፈ በኋላ ግርግም አልነበረም፡፡ ከወትሮው የተለየ ነገርም አልተስተዋለም፡፡ የምርጫ ኮሮጆዎቹ ከየምርጫ ጣቢያው እየተሰበሰቡ በፖሊስ ታጅበው ወደየምርጫ ቦርዱ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሲደርሱም ተስተውሏል፡፡ ሰኞ ዕለት በኢተያም ሆነ አሰላን ጨምሮ በሌሎቹ አጎራባች ወረዳዎች ሕይወት እንደተለመደው ቀጥላ ታይታለች፡፡ በ1992፣ በ1997፣ በ2002 እና በ2007 ዓ.ም. በኢተያ ለክልል ምክር ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ዕጩ ተወዳዳሪ የነበሩት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ በአራት ተከታታይ ምርጫዎች በመወዳደር ይታወቃሉ፡፡ 

 

ምርጫ በሰሜን ሸዋ ዞን

በምርጫ 2007 በሰሜን ሸዋ ዞን ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሕዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤት ዕጩዎቻቸውን በማቅረብ ዝግጅት ሲያደርጉ ከርመዋል፡፡

አሉ የሚሏቸውን ችግሮች ይዘው ወደ ምርጫ የገቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስሞታቸው ተመሳሳይ ነው፡፡

በሰሜን ሸዋ ዞን የምርጫ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሰማ ከበደ፣ በዞኑ  በሚገኙት 18 ምርጫ ክልሎች ብአዴን/ኢሕአዴግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 17 ለክልል ምክር ቤት 36 ተወዳዳሪዎችን ማቅረቡን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ሰማያዊ ፓርቲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስት፣ ለክልል ምክር ቤት ደግሞ 16 ማቅረቡን፣ መኢአድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰባት ለክልል 14፣ ኢዴፓ ለተወካዮች ምክር ቤት አራት ለክልል ምክር ቤት አላቀረበም፡፡ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስት ለክልል ምክር ቤት አንድ ተወዳዳሪ ሲያቀርብ፣ መኢብን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንድ ለክልል ምክር ቤት ደግሞ ሁለት አቅርቧል፡፡ አዲስ ትውልድ ፓርቲ ለክልል ምክር ቤት አንድ ሲያቀርብ ለክልል ምክር ቤት አላቀረበም፡፡ አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራት፣ ለክልል ምክር ቤት አራት ሲያቀርብ፣ የአርጎባ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አብዴን) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንድ ለክልል ምክር ቤት አላቀረበም፡፡ የአርጎባ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (አሕዴድ) በተመሳሳይ ለተወካዮች ምክር ቤት አንድ ተወዳዳሪ ሲያቀርብ ለክልል ምክር ቤት አለማቅረቡን አቶ ተሰማ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ በዞኑ ባሉት የምርጫ ክልሎች ሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች  ለሕዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤት በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች የምርጫውን ሒደት ለሚከታተሉ ተቀማጭና ተንቀሳቃሾች ወኪሎች፣ በጊዜውና በሰዓቱ መታወቂያ ተሰጥቷል፡፡ ለአብነትም ሰማያዊ ፓርቲ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙትን 44 ምርጫ ጣቢያዎች ጨምሮ በሁሉም ወረዳዎች ተቀማጭና ተንቀሳቃሽ ወኪሎቹን አቅርቦ ለሁሉም መታወቂያው መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡ በምርጫው ዕለት ግን የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሲከውኑ የተገኙት በደብረ ብርሃን ከተማ በሦስት ቀበሌዎች በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች ብቻ እንደነበረ፣ ቦርዱም ምናልባት ችግሩ ከገዥው ፓርቲ በሚደርስባቸው ጫናና ማስፈራት ሊሆን ይችላል በሚል ለማጣራት ባደረገው ሙከራ፣ አንድም የቀረበለት አቤቱታ እንደሌለ ነው ያስረዱት፡፡

በሰሜን ሸዋ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ምርጫ አስተባባሪ ወ/ሮ ሰርካለም ከበደ በበኩላቸው፣ የዞኑ ምርጫ ቦርድ አስተባባሪ እንዳሉት በዞኑ ደብረ ብርሃን ከተማን ጨምሮ በወረዳዎች ከጥቂቶቹ በስተቀር በአብዛኛው ለምርጫ ታዛቢ ወኪሎቻቸው መታወቂያ ተሰጥቶ ምደባውም የተከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ በምርጫው ዕለት ግን በአብዛኛው በሚያስብል ሁኔታ ወኪሎቻቸው በየምርጫ ጣቢያው ለምን እንዳልተገኙ የደረሳቸው መረጃ እንደሌለ ነው የተናገሩት፡፡ ኃላፊዋ ከፋይናንስ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጥያቄዎች ይቀርቡላቸው የነበረ መሆኑን ግን አልሸሸጉም፡፡

በወረዳዎች በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች በአባሎቻቸውና በደጋፊዎቻቸው ላይ በገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ደጋፊዎች አልፎ አልፎ ድብደባዎች፣ ማስፈራራቶችና ወከባዎች እያደረሱባቸው መሆኑን ሪፖርቶች እንደደረሷቸው፣ በደብረ ብርሃንና በአካባቢው ግን በተለይ ጠዋት ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መራጭ በየምርጫ ጣቢያው ተሠልፎ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ሲመርጥ እንደነበረ መመልከታቸውን ነው ያስረዱት፡፡

በመሀል ሜዳና አካባቢው የሰማያዊ ፓርቲ ምርጫ አስተባባሪ አቶ ካሳዬ ዳኜ በበኩላቸው፣ ከምርጫ ዋዜማ ጀምሮ በገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ደጋፊዎች እጅግ አሳዛኝ የሆነ እንግልትና ማስፈራራት እንደደረሰባቸው፣ በዚህም የተነሳ በመሀል ሜዳና አካባቢው በነበሩ 93 ምርጫ ጣቢያ የሰማያዊ ፓርቲ ወኪሎች በሙሉ የምርጫውን ሒደት እንዳይከታተሉ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ዛቻና ማስፈራሪያውን ወደ ጎን ብለው የሄዱት ለእስራት እየተዳረጉ ማስጠንቀቂያ እየተሰጣቸው መፈታታቸውን ጭምር አስረድተዋል፡፡ እሳቸውም ቢሆኑ የገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ደጋፊዎች ‹‹በዚህ ምርጫ  አንድ ነገር ቢከሰት የመጀመርያው ዕርምጃ በአንተ ነው የሚጀመረው፤›› ብለው ስላስፈራሯቸው ቤት ውስጥ መቀመጣቸውን በስልክ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የዞኑ የምርጫ ቦርድ ኃላፊው አቶ ተሰማ ከበደ በበኩላቸው፣ ምርጫው በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች በሰላም እየተከናወነ መሆኑን፣ ‹‹ችግር ተፈጥሯል›› በሚል ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የቀረበላቸው አቤቱታ እንደሌለ ነው የተናገሩት፡፡

በዞኑ ከሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኢአድ ይጠቀሳል፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞን የመኢአድ ምርጫ አስተባባሪ ሻምበል ባሻ አበበ በቀለ፣ ከምርጫ ዋዜማ ጀምሮ በገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ደጋፊዎች በደረሰባቸው ወከባና ማስፈራራት እንደማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በምርጫ ካርዳቸው አማካይነት መብታቸውን ከመጠቀም ባለፈ፣ እንደ ፓርቲ የምርጫውን ሒደት ለመከታተልም ሆነ ለመቆጣጠር አለመቻላቸውን ነው ያስረዱት፡፡ በመሆኑም በዞኑ በሚገኙ በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ምንም ዓይነት የምርጫ ታዛቢ ወኪሎቻቸውን እንዳልመደቡም ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው ለዚህ ያበቃቸውን ውሳኔ ሲገልጹ፣ በባሶና ወረና በቀይት ምርጫ ጣቢያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መኢአድ ያቀረባቸው ወ/ሮ ደስታ ካሳና በደብረ ብርሃን ከተማ በተመሳሳይ አቶ ጌራ ፍቅረ የተባሉ ተወዳዳሪዎቻቸው ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ በአካልም ሆነ በስልክ ሊያገኟቸው እንዳልቻሉ፣ ይህንኑም ወደ ማዕከል አስተላልፈው መፍትሔ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

በወረዳ ደረጃ ከቀረቡት ተወዳሪዎቻቸው ለምሳሌ በሸዋ ሮቢት፣ በቀወት ወረዳ፣ በአጣየ፣ በጣርማ በር፣ በደብረ ሲናና በሌሎችም አካባቢዎች መኢአድ ያቀረባቸው ተወዳዳሪዎች በገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ደጋፊዎች በደረሰባቸው እንግልት፣ ዛቻና ማስፈራራት ሁሉም ችግሩን በመግለጽ ራሳቸውን ማግለላቸውን ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ እያጋጠመው ያለውን እንግልት፣ ወከባና ማስፈራት ለዞኑ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት በስልክና በተለያዩ አጋጣሚዎች ቢያሳውቅም ምንም ዓይነት መፍትሔ ሊያገኝ ባለመቻሉ፣ ለሁሉም አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው እንደ ፓርቲ ሳይሆን እንደማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ካርዶቻቸውን ብቻ እንዲጠቀሙ ጥሪ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ የዞኑ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሰማ ከመኢአድም ሆነ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ተቃዋሚ በመሆናቸው ምክንያት ከገዥው ፓርቲ ደርሶብናል ሲሉ በአካልም ሆነ በጽሑፍ የቀረበላቸው አንዳችም አቤቱታ እንደሌለ ነው ያስረዱት፡፡ 

ከዚህ ባለፈ ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ እስከ ምርጫው ፍፃሜ ከገዥው ፓርቲ ብአዴን/ኢሕአዴግ፣ ከሰማያዊና ከመኢአድ በስተቀር ሌሎቹን የፖለቲካ ፓርቲዎች  በቅስቀሳው ወቅት መራጮች እንደማያውቋቸው ነው ለሪፖርተር የገለጹት፡፡ ከእነዚህ አንዳንዶቹ በተለይ በገጠር ቀበሌዎች ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው መራጮች በሚመርጡበት ምርጫ ጣቢያ ከብአዴን/ኢሕአዴግ ውጪ የሌሎች ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ተወካዮች እንዳልነበሩ ተናግረዋል፡፡

 

ምርጫ በሐድያ ዞን

በደቡብ ክልል የሚገኙ 123 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን አሸንፎ ለመያዝ ምርጫ ከተከናወነባቸው ከተሞች መካከል አንዷ፣ በሀድያ ዞን በምሥራቅ ባደዋቾ ወረዳ የምትገኘው የሾኔ ከተማ ነች፡፡ 

ምሥራቅ ባደዋቾ በ30 ቀበሌዎችና በ72 የምርጫ ጣቢያዎች ሲከፋፈል፣ በዚሁ ዞን የምትገኘው ሾኔ ከተማ ደግሞ በስድስት የምርጫ ጣቢያዎች ነው፡፡ በሾኔ ለዘንድሮ አጠቃላይ ምርጫ የተመዘገቡት መራጮች ደግሞ 61,101 ናቸው፡፡

በከተማዋ የሚገኙት የምርጫ ጣቢያዎችም ጤና ኬላ፣ ፀረ ኤድስ 1 እና 2፣ ታተም፣ መናኸሪያና ማክማማ የተሰኙ ናቸው፡፡ 

የወቅቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ሊቀመንበርና በተቃውሞ ፖለቲካ ጐራው ዘለግ ያለ ዕድሜ ያስቆጠሩት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ በዚሁ ዞን በሚገኘው አንደኛ ሀሙበርሴ በተባለ የምርጫ ክልል አካባቢ ተወልደው ያደጉና በሥፍራውም ለሦስት ጊዜያት ያህል ምርጫውን አሸንፈው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆናቸው፣ በሥፍራው የሚደረገውን ውድድር ለመዘገብ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በከተማው እንዲከትሙ አድርጐ ነበር፡፡ 

ፕሮፌሰሩ በ1987 ዓ.ም.፣ 1992 ዓ.ም. እና እንዲሁም በ1997 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫዎች በማሸነፍ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆናቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ደግሞ በገዥው ፓርቲ ደኢሕዴን/ኢሕአዴግ ተወካይ አቶ ዮሴፍ ዳኤሞ ተሸንፈው ነበር፡፡ ፕሮፌሰሩንና የገዥው ፓርቲ ተወካይ የሆኑትን አቶ ዮሴፍን ለመወዳደር ደግሞ የሰማያዊና የቅንጅት ፓርቲዎች ተወካዮቹ የሆኑት አቶ መብራቱ ተካና አቶ ያሬድ ደበበ ተመዝግበዋል፡፡ 

በዚሁ ከተማ ከሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል ፕሮፌሰር በየነ ድምፃቸውን የሚሰጡበት የምርጫ ጣቢያ ማክማማ የሚባል ሲሆን፣ በድምፅ መስጫው ዕለት ግን ፕሮፌሰሩ በሥፍራው ተገኝተው ድምፅ አልሰጡም፡፡ በአንፃሩ በፀረ ኤድስ አንድ የምርጫ ክልል ድምፅ የሚሰጡት አቶ ዮሴፍ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ቀደም ብለው ድምፅ ሰጥተዋል፡፡

ፕሮፌሰር በየነ፣ ‹‹ያልመጣሁት ምርጫው ሥነ ሥርዓቱ ተጥሶ ሙሉ በሙሉ በኢሕአዴግ ቁጥጥር ሥር መዋሉን ስለተረዳሁ ወደዚያ ለማድረግ  ያሰብኩትን ጉዞ በመተው፣ እዚሁ ማዕከል ሆኖ ሁኔታዎችን መከታተል የተሻለ ይሆናል በሚል ነው፤›› ብለዋል፡፡

በዞኑ ከምርጫው ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ደግሞ የምሥራቅ ባደዋቾ መድረክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሊቀመንበር አቶ ኤልያስ ሀደሮን ማነጋገርና መረጃ ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

ምርጫ በሾኔ

የሾኔ ከተማ በምርጫው ዋዜማ በጣም ቅዝቅዝ ያለ እንቅስቃሴ የሚታይባት ነበረች፡፡ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ ግለሰቦችን በመጠየቅ ሪፖርተር መረዳት እንደቻለው፣ ከተማዋ ለወትሮው ሞቅ ያለች ነበረች፡፡ የምርጫ ዋዜማው ግን ከተማዋን ቀዝቀዝ እንዳደረጋት ገልጸዋል፡፡

ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ደግሞ የከተማዋና የነዋሪዎቿ እንቅስቃሴ እጅጉን የተገደበ ነበር፡፡ ለወትሮው በክልል ከተሞች ወዲህና ወዲያ የሚሉት ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጆች) ቢሆኑም እንኳን፣ አልፎ አልፎ ውርውር ከማለትና ከጥቂት ሞተሮች እንቅስቃሴ በስተቀር ከተማዋ ፀጥ ረጭ ብላ ከእንቅስቃሴ ነፃ ሆና ነበር ማለት ይቻላል፡፡

የምርጫው ዕለት

በዕለቱ የተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የምርጫውን ሒደት በንቃት እየታዘቡ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፣ የአብዛኛዎቹ ምላሽ ችግር እንዳላገጠማቸው የሚገልጽ ነበር፡፡

ከዚህ በተለየ ግን የወረዳው የመድረክ ሊቀመንበር የምርጫው ዕለት ቀትር ሊሆን ሲቃረብ በተለያዩ ቦታዎች የመድረክ ተወካዮች ከምርጫ ጣቢያዎች ተባረዋል የሚል ቅሬታዎችን፣ ወደ ምርጫ ጣቢያውና ወደ መገናኛ ብዙኃን እየደወሉ ያሳውቁ ነበር፡፡

ቡልጊታ በተባለው የምርጫ ጣቢያ የመድረክ ተወካይ ከምርጫ ጣቢያው እንዲወጣ ጫና እየተደረገበት እንደሆነ ለጋዜጠኞች ገልጸው ነበር፡፡ የቡልጊታ 02 የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ተረፈ ዴንሴሞ ግን የተባለውን በመቃወም የመድረክን ክስ አጣጥለዋል፡፡

በተመሳሳይ እንዲሁ መድረክን የወከሉት አቶ ዓለሙ ኦርዶሎ በጣቢያው ከፍተኛ እንግልት እንደደረሰባቸው ከመግለጽ ባለፈ፣ ‹‹አንድ ግለሰብ በርከት ያሉ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን የምርጫ ኮሮጆ ውስጥ ሲከት አይቻለሁ፤›› በማለት በሥፍራው ለተገኙ የጋዜጠኞች ቡድን ገልጸዋል፡፡

የምርጫ ጣቢያው አስፈጻሚ አሁንም ክሱ ከእውነታ የራቀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሒደቱ በሥነ ሥርዓት ለመካሄዱ አባሪ የሚሆኑ አቶ ዓለሙ የፈረሙባቸውን የቃለ ጉባዔ ሰነዶችን በማሳየት የተባለው ሀሰት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በሥፍራው የነበሩ የሰማያዊና የቅንጅት ፓርቲ ተወካዮችም አቶ ዓለሙ ያቀረቡትን ክስ አለመመልከታቸውን በመግለጽ፣ ከተወካዩ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ 

ሲቄ 02 የምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ያዕቆብ ዮሴፍ በበኩላቸው፣ ‹‹መድረክ ያቀረባቸው ክሶችና ቅሬታዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ችግር አለባቸው በተባሉ አካባቢዎች በአካል በመገኘትና የሌሎች ፓርቲዎችን ተወካዮች በማናገር እንዳረጋገጥነው የቀረበው ቅሬታ ተጨባጭነት የሌለውና አሉባልታ ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 

በዕለቱ ከመድረክ ተወካይ በኩል ይቀርብ ከነበረ ቅሬታ በስተቀር ሌሎቹ ለተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ያቀረቡ ፓርቲዎች ያነሱት ቅሬታ አልነበረም፡፡ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ባያቸው አብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ከቀትር በፊት ከግማሽ በላይ የሚሆኑ መራጮች ድምፅ ሰጥተው ሄደዋል፡፡          

 

ምርጫ በሐዋሳ

ቅዳሜ ግንቦት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በአምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዋዜማ የደቡብ ክልል መዲና ሐዋሳ መንገዶች ከወትሮው ቀዝቀዝ ብለው ነበር፡፡ በመዝናኛዎች የነበረው ሁኔታም ተመሳሳይ ነበር፡፡

ፒያሳ የሚገኘው ሐውልት ፏፏቴ ግን ተከፍቶ ነበር፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ትልልቅ ድንኳኖች ለድምፅ መስጫ ጣቢያነት ተጥለውም ነበር፡፡ 

በምርጫው ዕለት ብዙዎች ድምፅ ወደሚሰጡባቸው ጣቢያዎች ያመሩት ማልደው ነበር፡፡ በየድምፅ መስጫ ድንኳኖች ደጃፍ ላይ ሰዎች ተሠልፈው ይታይ ነበር፡፡ ደኢሕዴን/ኢሕአዴግን ወክለው ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩት የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ዮናስ ዮሴፍና የ27 ዓመቱ አካል ጉዳተኛ በቃሉ አሰፋ፣ ከንጋቱ 12፡30 ሰዓት ገደማ ነበር ከታቦር ክፍለ ከተማ ሒጠታ ቀበሌ ወሜ ድምፅ መስጫ የተገኙት፡፡ ባገኘው የመምረጥ ዕድል ‹‹የመጠቀም ግዴታ አለብኝ›› የሚለው በቃሉ ምርጫው እንደ ከንቲባው አቶ ዮሴፍ ሁሉ ለእሱም በጣም አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻል፡፡ 

ሪፖርተር ተዘዋውሮ ባያቸው መናኸሪያ ክፍለ ከተማ ፒያሳ ቀበሌ ቁ 4፣ ሐይቅ ዳር ጉዱማሌ ምርጫ ጣቢያ 3፣ መናኸሪያ ፒያሳ ቁጥር ሦስትና በታቦር ክፍለ ከተማ የድምፅ መስጫዎች ጨፌ ተጎዝጉዞ ቡና እየተፈላ በዓል በዓል ይመስል ነበር፡፡ ከበር የተሠለፉ ሰዎችን ስሜት መገመት ግን ከባድ ነው፡፡ ሠልፍ ላይ ጎን ለጎን ተሠልፈው ደቂቃዎችን ቢያሳልፉም ብዙዎች ሲነጋገሩ አይታይም፡፡ በዝምታ ተራቸው ደርሶ ወደ ድንኳን ውስጥ መግባትን የመረጡ ይመስላሉ፡፡ በብዙዎቹ ድምፅ መስጫዎች ስለድምፅ አሰጣጥ በመሀል በመሀል ገለጻ ሲሰጥ ተስተውሏል፡፡

በሲዳማና በሐዋሳ 1,437,697 ሰዎች ካርድ እንደወሰዱና 1,327,082 (624,72  ሴቶችና 702,361 ወንዶች) ድምፃቸውን እንደሰጡ በምርጫው ማግሥት የሲዳማና የሐዋሳ ከተማ ምርጫ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዱካሞ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በሐዋሳ 151 ድምፅ መስጫዎች የነበሩ ሲሆን፣ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በማግሥቱ ቀኑን ሙሉ ምርጫው ቀጥሎ ነበር፡፡ 

ምርጫ እዚህ ታዛቢ እዚያ 

ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ ነበር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዛቢዎቻቸው እየታሰሩና በተለያዩ መንገዶች ጫና እየደረሰባቸው እንደነበር ቅሬታ ማሰማት የጀመሩት፡፡ አንድነት ፓርቲን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወዳደሩት አቶ ሲዳ ኃይሌ፣ ‹‹የስም ፊደል ስህተት አለ›› በሚል ሁለት ታዛቢዎቻቸው መታሰራቸውን ገልጸዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወዳደሩት አቶ ተስፋ ማርያም ጉቻ ደግሞ፣ ከሐዋሳ 27 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘውና እሳቸው በሚወዳደሩበት የቦሪቻ ምርጫ ጣቢያ 16 ወይም ሦስት አራተኛ የሚሆኑ ታዛቢዎቻቸው፣ በሐዋሳ ምርጫ ጣቢያ መድረክን ወክለው ለተወካዮች ምክር ቤት የተወዳደሩት ዶ/ር አየለ አሊቶም ቦሪቻ ላይ በርካታ ታዛቢዎቻቸው መታሰራቸውንና መደብደባቸውን ለሪፖርተር ገልጸው ነበር፡፡ 

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዛቢዎቻቸው ለመታሰራቸውና ደረሰባቸው ለሚሉት እንግልት በምክንያትነት ካስቀመጧቸው መካከል የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢ ሆነው መገኘታቸው በራሱ፣ ታዛቢ የሚሆኑባቸው ቦታዎች ላይ የተመዘገቡ ባለመሆናቸው ታዛቢነታቸው አግባብነት የለውም መባልና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በሌላ በኩል የሲዳማና የሐዋሳ ምርጫ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ የታሰሩ ታዛቢዎች መኖራቸውን ባይክዱም፣ ታሰሩ በተባሉት ታዛቢዎች ቁጥርና ለእስራታቸው በተሰጠው ምክንያት አይስማሙም፡፡ ቢሆንም ግን የታሰሩበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን ከሚመለከታቸው ጋር እየተነጋገሩ እንደነበርና እንዲፈቱ ትዕዛዝ ያስተላለፉላቸው ታዛቢዎችም እንደነበሩ፣ በምርጫው ዕለት እኩለ ቀን ላይ ለሪፖርተር ገልጸው ነበር፡፡ እዚህ ላይ ታዛቢዎቹ ስንት ሰዓት ላይ ተፈቱ? ከተፈቱ በኋላስ በቀሪው ጊዜ ከታዛቢነት ኃላፊነታቸው እንዲገኙ ተፈቅዶላቸዋል? እነሱስ ከእስራቱ በኋላ ታዛቢ ለመሆን ፈቅደዋል የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

ምሽት ምርጫ ከተጠናቀቀ በኋላ ሪፖርተር ተዘዋውሮ በተመለከታቸው የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች በአንዳንዶቹ ምንም እንኳ የሕዝብ ተወካዮች ቢኖሩም፣ አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢ ያልነበረበትም አጋጥሟል፡፡ አንድ ወይም ሁለት የፖለቲካ ፓርቲ ታዛቢዎች ብቻ የተገኙባቸውም እንዲሁ፡፡ በሌላ በኩል የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢዎች ከነበሩበት (ጉድማሌ ቁ 3) ድምፅ መስጫም ሪፖርተር ተገኝቶ ነበር፡፡ 

በመናኸሪያ ፒያሳ ቁጥር 3 ድምፅ መስጫ ድምፅ በመቆጠር ላይ ሳለ ሪፖርተር ያገኘውና አስተያየቱን የጠየቀው በጣቢያው ወጣቶችን ወክሎ ታዛቢ የነበረው የ12ኛ ክፍል ተማሪ፣ ሥልጠና ሲወስዱ አስተያየት እንዳይሰጡ ስለተነገራቸው ለመናገር ፈቃደኛ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ በዚያው ጣቢያ ድምፅ በመቆጠር ላይ ሳለ ምንም እንኳ መንገዱን በድንጋዮች ለመዝጋት ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም፣ አንድ ሞተር ድንኳኑን ጥሶ በመግባቱ አራት ሰዎች ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን የምርጫ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

ምርጫ በዩኒቨርሲቲ 

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ አራት ሺሕ የሚሆኑ ተማሪዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚገመት፣ ከዚህ ውስጥም 3,678 ያህሉ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ከምርጫ አስተባባሪዎቹ አንዱ የሆነው ተስፋዬ ጥሩነህ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ እሱ እንደገለጸው፣ በዩኒቨርሲቲው ስድስት ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ነበሩ፡፡ በእያንዳንዱ ጣቢያ 700 ተማሪዎች ድምፅ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ ብዙ ድምፅ ሰጪ የሌለባቸው እንደ አፋርና ትግራይ ክልሎች እንዲጣመሩ ተደርጎ ነበር፡፡ በዕለቱ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ተሟልተው ቀርበው ስላልነበር፣ በማግሥቱ 12፡00 ሰዓት ድረስ ምርጫው እንዲቀጥል መደረጉን ሰኞ ጠዋት በዩኒቨርሲቲው ተገኝቶ ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡

በምርጫ ጣቢያዎቹ ረዥም ሠልፎች ታይተዋል፡፡ ጣቢያዎቹ የነበሩበት የዩኒቨርሲቲው አካባቢ በእንቅስቃሴ የተሞላ ነበር፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በርካታ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቅጥር ተማሪዎች እንዲመርጡ መደረጉ ለአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ብቻም ሳይሆን፣ በዚህ ምርጫ የግቢያቸውን ፍትኅዊነት ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ይህ እውነት ዴሞክራሲ ስለመስፈኑ ያረጋግጥንበት ነው፤›› ያለው ከምዕራብ ሐረርጌ ገለምሶ የመጣው የአንደኛ ዓመት ጋዜጠኝነት ተማሪ ዮናስ ወንድሙ ነው፡፡ ከአርባጉና ወረዳ የመጣችው ሰላማዊት ፀጋዬ (ሲዳምኛ ቋንቋ ተማሪ) የዮናስን አስተያየት የምትጋራና የምርጫ አስተባባሪም ነበረች፡፡ 

የሌሎች ተማሪዎችም ሐሳብ ተመሳሳይ ነው፡፡ ምርጫው የዴሞክራሲየዊ ሥርዓት መገለጫ እንደሆነና ለሕዝብ ሰላምና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ሪፖርተር በግቢው በነበረው የአንድ ሰዓት ቆይታ ተዘዋውሮ አስተያየት ሲጠይቅ ለየት ያለ አስተያየት ያላቸው ተማሪዎች አላገኘም፡፡ ምንም እንኳ ተማሪዎቹ ምን ያህል ዩኒቨርሲቲውን ይወክላሉ የሚለው ጥያቄ ቢነሳበትም፣ የተገኙት አስተያየቶች ተመሳሳይ መሆን የሚናገረው ነገር ይኖራል፡፡ 

በኢትዮጵያ ፖለቲካ በተለያዩ ሥርዓቶች የከፍተኛ ተቋም ተማሪዎች ስለሕዝብ ጥቅም፣ ነፃነትና ሌላም ሌላም በመጠየቅ የታገሉ መሆናቸውን በማስታወስ፣ በኢሕአዴግ ሥርዓት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተማሪዎች የተለያዩ ሐሳቦች (የሚቃረኑም ሊሆኑ ይችላሉ) የሚንፀባረቁባቸው መሆን እያቆሙ ነው የሚለው ከዚህ ቀደምም በበርካታ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጭምር ይገለጽ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ስለዛሬው ብቻም ሳይሆን ስለቀጣዩ የአገሪቱ ፖለቲካ ብዙ የሚናገረው ሊኖር ይችላል የሚለው ብዙዎችን ያነጋግራል፡፡ በእርግጥ በተለያዩ ምክንያቶች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የኢሕአዴግ አባል መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር መሆኑን በተደጋጋሚ የሚገልጹ ብዙዎች ናቸው፡፡ 

የምርጫው ማግሥት 

በምርጫው ማግሥት ጠዋት በነበረው ቅኝት በአንዳንዶቹ ጣቢያዎች ውጤት ሲለጠፍ በሌሎች ደግሞ አልተለጠፈም ነበር፡፡ የምርጫ አስፈጻሚ ከቤት ከእንቅልፉ ተቀስቅሶ እንደዋዛ አጣጥፎ የያዛቸውን ሁለት የውጤት ወረቀቶች ሲለጥፍ በአንድ የድምፅ መስጫ ጣቢያ ተስተውሏል፡፡ አንድ ምርጫ ጣቢያ ላይ ከፕላስቲክ ጠርሙስ ኮላ በእንጨት እየተሟጠጠ ውጤት ለመለጠፍ ሲሞከር፣ በቦታው የነበሩ ሰዎች የምርጫው በጀት ይህን ታሳቢ አላደረገም? በሚል ቀልድ በሥፍራው የነበሩትን ፈገግ አሰኝተዋል፡፡

 

ምርጫ በጅማ ዞን

የምዕራብ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እምብርት በሆነችው ጅማ፣ በተካሄደው ምርጫ የኦሮሚያ ክልል ገዢ ፓርቲ ኦሕዴድ ከመድረክ፣ ከሰማያዊና ኢዴፓን ጨምሮ ከተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተወዳድሯል፡፡

ሪፖርተር በምርጫው ዋዜማ፣ በምርጫው ቀንና በምርጫው ማግሥት በተለይ በጅማ ከተማና በአጋሮ ከተማ የሚገኙ የምርጫ ተወካዮችን ከማነጋገሩም በላይ በምርጫ ጣቢያዎች ቅኝት አድርጓል፡፡ 

በምርጫው ዋዜማ የጅማ ከተማ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤትና የዞኑ ምርጫ ጣቢያ ማስተባበሪያ ሲያካሂድ የቆየውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቆ ነበር፡፡ ኦሕዴድ የምርጫ ካርድ የወሰዱ መራጮች በምርጫው ቀን ጠዋት ወጥተው ድምፅ እንዲሰጡ ያሉትን አደራጃጀቶች በመጠቀም ሲያሳስብ ተስተውሏል፡፡ 

ነገር ግን በምርጫው ዕለት ከሌሊት ጀምሮ በጅማ ከተማና በአብዛኛው ጅማ ዞን ክልል ውስጥ የጣለው ኃይለኛ ዝናብ የመምረጫ ሰዓታትን መሸራረፉ አልቀረም፡፡ ይህም ቢሆን ግን ቁጥራቸው ቀላል የማይባል መራጮች በዝናብ ውስጥ ሲመርጡ ተስተውሏል፡፡ 

ረፋዱ ላይ ዝናቡ ካባራ በኋላ በርካታ መራጮች በረዣዥም ሠልፎችና በድንኳን ውስጥ በመቀመጥ ተራቸውን ጠብቀው ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ ምርጫው በሰላም ተጀምሮ በሰላም መጠናቀቁን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ የጅማ ዞን ጅማ ከተማን ሳይጨምር 1.9 ሚሊዮን ሔክታር ስፋት አለው፡፡ በዞኑ ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ እንደሚኖር የዞኑ አስተዳደር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዞኑ ውስጥ ከሚኖረው ሕዝብ 1.3 ሚሊዮን የሚሆነው በምርጫው ድምፅ ለመስጠት ተመዝግቧል፡፡ 

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጅማ ከተማ ምርጫ ጣቢያ ኃላፊና የጅማ ዞን ምርጫ ክልል አስተባባሪ አቶ አወጣኸኝ ኪዳነ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጅማ ከተማን ጨምሮ በአጠቃላይ በጅማ ዞን 18 ምርጫ ክልሎች አሉ፡፡ በእነዚህ 18 የምርጫ ክልሎች 1,551 ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች አሉ፡፡ 

በጅማ ዞን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎችን አቅርበዋል፡፡ ኦሕዴድ፣ መድረክ፣ ሰማያዊ፣ ኢዴፓና አንድነት በምርጫው ተሳታፊ ነበሩ፡፡ 

ኦሕዴድ በሁሉም መወዳደርያ ጣቢያዎች ዕጩ ሲያቀርብ መድረክ፣ ሰማያዊ፣ ኢዴፓና አንድነት በተነፃፃሪ ቁጥሩ የቀነሰ ዕጩ አቅርበው ተወዳድረዋል፡፡ ኦሕዴድ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካባ ኡርጌሳ የጅማ ከተማ የፓርላማ ተመራጭ አድርጎ ሲያቀርብ፣ 17 ነባር የፓርላማ ተመራጮችን በሌሎቹ የምርጫ ክልሎች እንዲወዳደሩ አድርጓል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድርን ጨምሮ 54 አባላቶቹን ደግሞ ለክልሉ ምክር ቤት ዕጩ አድርጎ አቅርቧል፡፡ 

በሁለቱ የጅማ ዞን ትላልቅ ከተሞች የኦሕዴድ ፖስተሮችን በስፋት መመልከት ቢቻልም፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ፖስተር ግን ማየት አዳጋች ነበር፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ፖስተሮች ሊኖሩ ያልቻሉበትን ምክንያት በሪፖርተር የተጠየቁት የአጋሮ ከተማ ከንቲባ አቶ ሞጋ አባቡልጋ፣ በአብዛኛው በግለሰቦች በተያዙ አካባቢዎች የሚለጠፉ በመሆናቸው ግለሰቦች ሲፈቅዱ ፖስተሮች ይለጠፋሉ ብለዋል፡፡ ኦሕዴድም አስፈቅዶ መለጠፉን ተናግረዋል፡፡ ተቃዋሚዎቹ በግለሰቦች ስላልተፈቀደላቸው መለጠፍ ባለመቻላቸው ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ 

በምርጫው ዕለት ልዩ ክስተት ከሆኑት መካከል በጅማ ዞን ሲግሞ ምርጫ ክልል ከጠዋቱ አራት ሰዓት ላይ ድምፅ ተሰጥቶ መጠናቀቁ ነው፡፡ የጅማ ዞን የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ታምራት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሲግሞ ምርጫ ክልል 49 ሺሕ ነዋሪዎች ድምፅ ለመስጠት ተመዝግበዋል፡፡ የአካባቢው አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች የእስልምና እምነት ተከታዮች በመሆናቸው፣ ከሌሊቱ 11 ሰዓት የሱቢህ ስግደት ከሰገዱ በኋላ ወደ ምርጫ ጣቢያ መሰማራታቸውን አስረድተዋል፡፡ 

‹‹በዚህ ምክንያት መራጮች ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ድምፅ ሰጥተው አጠናቀዋል፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ የምርጫ ካርድ በሚሰጥበት ወቅት እነዚህ የሲግሞ ነዋሪዎች በሁለት ቀን ውስጥ የምርጫ ካርድ ወስደው አጠናቀዋል ብለዋል፡፡ 

የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት መቀመጫውን ጅማ ከተማ አድርጎ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተቃራኒ በጠንካራ መዋቅሩ አማካይነት የዞኑን የምርጫ ሒደት በቅርበት ተከታትሏል፡፡ ሪፖርተር በኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ተገኝቶ መረዳት እንደቻለው፣ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ኦሕዴድ በእያንዳንዱ ድምፅ መስጫ የሚካሄደውን እንቅስቃሴ ከመከታተሉም ባሻገር፣ ሪፖርት በማዘጋጀት ወደ ማዕከል ኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ይልካል፡፡ 

ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የተደራጀ መረጃ ማግኘት ባይቻልም፣ በአጋሮ ጎማ አንድ ምርጫ ክልል የፓርላማ ተወዳዳሪ የሆኑት አቶ አብዱ አባዎሪ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የምርጫው ቅስቀሳም ሆነ ሒደቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ‹‹ምርጫው ፍትሐዊ መሆኑን እስካየን ድረስ፣ ውጤቱን በፀጋ እንቀበላለን፤›› በማለት አቶ አብዱ ገልጸዋል፡፡ 

በጅማ ክልል በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች የፖለቲካ ፓርቲ ታዛቢዎች ተሟልተው አለመገኘት ተጠቃሽ ችግር ሆኖ ቀርቧል፡፡ ይኼ የታዛቢዎች አለመገኘት በብዙ የምርጫ ጣቢያዎች ተስተውሏል፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የምርጫ ቁሳቁስ እጥረት በመከሰቱ የድምፅ መስጠት ሒደቱ ተስተጓጉሏል፡፡ አቶ አወጣኸኝ እንዳሉት ሰኞ ከሰዓት በኋላ የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶች በሔሊኮፕተር በመምጣታቸው ድምፅ መስጠቱ በምርጫው ቀን ማግሥት ተካሂዷል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የምርጫ ቁሳቁሶች እጥረት በመከሰቱ መምረጥ ያልቻሉ ተማሪዎች ጥያቄ አንስተው የተወሰነ አለመግባባት ተከስቶ ነበር፡፡ 

አቶ አወጣኸኝ ‹‹መምረጥ መብት ነው፡፡ ተማሪዎቹ ባልመረጡት አካል ሊተዳደሩ በመሆኑ ጥያቄ ማንሳታቸው አግባብ ነው፡፡ የምርጫው ሒደት በምርጫ ቦርድ የቴክኒክ ችግር መካሄድ ባለመቻሉ ድምፅ ያልሰጡ ተማሪዎች ድምፅ እንዲሰጡ ይደረጋል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ 

 

አቶ ዮናታን ተስፋዬ          -               አቶ ደምሰው በንቲ

–  ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅሬታ አልደረሰኝም ብሏል

በአምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተሳታፊ የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫውን እንዲታዘቡ ያሰማሯቸው ግለሰቦች በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት መገለላቸውን ገለጹ፡፡ የክልል የምርጫ ኃላፊዎች ክልከላው የተከናወነው ሕጉን መሠረት አድርጎ ነው ያሉ ሲሆን፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግን ከየትኛውም ፓርቲ ቅሬታ አልደረሰኝም ብሏል፡፡ 

ሰማያዊ ፓርቲ በተመሳሳይ በባሌ፣ በየም፣ በሲዳማና በደብረ ማርቆስ ያሰማራኋቸው ታዛቢዎች ተባረዋል ብሏል፡፡ በሐዋሳ ከተማ ከተሰማሩ ታዛቢዎች ሦስት አራተኛው እንዲሁ ለእስር ተዳርገዋል ያለው ሰማያዊ፣ አንዳንዳቹ በሚሊሻ ተከበው በቤታቸው በቁም እስር ላይ እንደሚገኙ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

መድረክ በበኩሉ በሐዋሳ ከተሰማሩ የፓርቲው ታዛቢዎች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት መታሰራቸውን በአካባቢው መድረክን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት ዶ/ር አየለ አሊቶ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ መድረክ በተመሳሳይ በመቐለ ያሰማራቸው ታዛቢዎች በተለያዩ ጫናዎች ራሳቸውን ከታዛቢነት ማግለላቸውን ገልጿል፡፡ 

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲም እንዲሁ በሐዋሳ ያሰማራቸው ታዛቢዎች መባረራቸውን ገልጿል፡፡ የአካባቢው የምርጫ ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዱካሞ የሌላ ፓርቲ የታዛቢነት መታወቂያ ይዘው በመገኘታቸው ጉዳዩ እየተጣራ እንደሆነ ገልጸው፣ ግለሰቦቹ እንደሚፈቱ አስታውቀዋል፡፡

በባህር ዳር ከተማ ኢዴፓ ያሰማራቸው ከ60 በላይ ታዛቢዎች ቢኖሩትም፣ ድምፅ በመስጪያው ቀን ከ155 የምርጫ ጣቢያዎች በጣት የሚቆጠሩ ነው የተገኙት፡፡ ይህን በተመለከተ ሻምበል ያየህራድ ዘለቀ የባህር ዳር ከተማ ኢዴፓ አመራርና የተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ ለሪፖርተር፣ ‹‹አብዛኛዎቹ የፓርቲው ታዛቢዎች በምርጫ ጣቢያው ያልተገኙበት ምክንያት አላውቅም ፈርተው ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም በሁለት ምርጫ ጣቢያዎች ግን መታወቂያ ላይ ፎቶ አለጠፋችሁም ተብለው ከመግባት ተከልክለዋል፤›› ብለዋል፡፡ በባህር ዳር ምርጫ ክልል 115 የምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉ ምርጫ ቦርድ ቢያሳውቅም፣ ኢዴፓ በደብዳቤ የተገለጹለት 111 ብቻ መሆናቸውን ሻምበል ያየህራድ ገልጸዋል፡፡

መኢአድም በሰሜን ሸዋ ዞን በደረሰባቸው ወከባ ታዛቢዎች ማሰማራት እንዳልቻለ የዞኑ የመኢአድ ምርጫ አስተባባሪ ሻምበል ባሻ አበራ በቀለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከአንድም ፓርቲ በጉዳዩ ላይ ቅሬታ እንዳልደረሰው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫ ታዛቢዎቻቸውን እንዲያሳውቁ በሰጠናቸው ጊዜ ብዙ ፓርቲዎች አልተጠቀሙም፡፡ በመሆኑም ጊዜውን አራዝመን ነበር፡፡ ከተራዘመም በኋላ ያላሳወቁ አሉ፡፡ በሕጉ እንዲያሳውቁ የሚያስገድድ ነገር ስለሌለ ዝም ብለናል፤›› ያሉት አቶ ደምሰው፣ ምናልባትም ይህን መታወቂያ ያልያዙ ሰዎች በታዛቢነት ቀርበው ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ቅሬታዎች የሚመጡት ከታችኛው እርከን ወደ ላይ በመሆኑ፣ ከክልል የምርጫ ኃላፊዎች ሲያልፍ ብቻ ወደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደሚመጣ አስገንዝበዋል፡፡ 

 

እሑድ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በመላ አገሪቱ ድምፅ የመስጠት ሥነ ሥርዓት ተጀምሯል፡፡ ሪፖርተር ከአዲስ አበባ ከተማና ከተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ዘገባዎችን ያስተላልፋል፡፡ በዚህም መሠረት አንባቢያን ድረ ገጹን እንዲጎበኙ እናሳስባለን፡፡

ደቡብ ክልል

በደቡብ ክልል በወላይታ ዞን በቦሎሶ ሶሬ ምርጫ ክልል 01 ጠቅላላ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ድምፃቸውን ይሰጣሉ ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን፣ መራጮች ቤተ ክርስቲያን በመሄዳቸው ምክንያት የመራጮች ቁጥር ዝቅተኛ እንደነበር ሪፖርተራችን ዘግቧል፡፡ በዚህ ምርጫ ከመድረክ በስተቀር ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች ይወዳደራሉ፡፡ በወላይታ ዞን ሐረካት 3 የምርጫ ጣቢያ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ደኢሕዴግ/ኢሕአዴግን ወክለው ይወዳደራሉ፡፡ በእዚህ ምርጫ ክልል መራጮች በብዛት ታይተዋል፡፡ የመድረኩ ፕሮፌሰር በየነና የደኢሕዴግ/ኢሕአዴግ አቶ ዮሴፍ ዳኢሞ የሚወዳደሩበት የሐዲያ ዞን ማካማ 02 ምርጫ ክልል መራጮች በብዛት ወጥተው እየመረጡ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታዛቢዎችም አሉ፡፡

አዲስ አበባ

ምርጫ ክልል 17

የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ በቀለ ከኢሕአዴግ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ የኢዴፓ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ተሾመ እንዲሁም የኢራፓ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮን ያገናኘው የምርጫ ክልል 17 ምርጫ በከፍተኛ ተሳትፎ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ባያቸው የምርጫ ጣቢያዎች ቺቺንያ አካባቢ ከሚገኝ አንድ ጣቢያ በስተቀር ረጃጅም ሠልፎች ታይተዋል፡፡ 

ይህ ነው የሚባሉ ግድፈቶች ባይስተዋሉም በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዛቢዎችን አላስቀመጡም፡፡ በተጨማሪም የምርጫ ሒደቱ ላይ ማብራሪያ እየተሰጠም ጭምር ምን ማድረግ እንዳለባቸው ምንም ዓይነት ግንዛቤ የሌላቸው መራጮችም ታይተዋል፡፡
       

ምርጫ 2007

እሑድ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሒደት በጊዜ ሰሌዳው መሠረት፣ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈጻሚነት በሚካሄደው አምስተኛ ጠቅላላ ምርጫ፣ ከ36.8 ሚሊዮን በላይ መራጮች ተመዝግበው ድምፅ እንደሚሰጡ ሲጠበቅ፣ በመላ አገሪቱ 46 ሺሕ ምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን ለማስተናገድ ተዘጋጅተዋል፡፡ በምርጫ ቦርድ መረጃ መሠረት እስካሁን ድረስ 319 ሚሊዮን ብር የወጣበት የዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ በርካታ ክስተቶች የታዩበት ሲሆን፣ በምርጫው ለመወዳደር ተመዝግበው የምርጫ ምልክቶች ከወሰዱ 58 ፓርቲዎች መካከል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) እና ሰማያዊ ፓርቲዎች ከምርጫ ቦርድ ጋር ሲነታረኩ ከርመዋል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በመጨረሻው ምዕራፍ በደቡብ ክልል በካፋ ዞን፣ በጊምቦ የምርጫ ክልል በግል ተወዳዳሪው ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስና በደኢሕዴግ/ኢሕአዴግ ዕጩ ዶ/ር መብራቱ ገብረ ማርያም ደጋፊዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ምርጫው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ አስገድዷል፡፡ በገጽ 6 ላይ የተስተናገደው የነዓምን አሸናፊ ዘገባ ከምርጫ 2007 ጋር የተገናኙ በርካታ ክስተቶችን ያስቃኛል፡፡  

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከመከናወኑ ከቀናት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጥያቄ ጊዜ ላይ እንዲገኙ የተደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ እሑድ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚካሄደው ምርጫ ውጤት ይፋ የማድረግ ሥልጣን ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ ነው አሉ፡፡   

በፓርላማው የአሠራር ሥነ ሥርዓት ደንብ መሠረት ፓርላማው በወር አንድ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የመጥራትና የመጠየቅ ሥልጣን አለው፡፡ በዚሁ መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንቦት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ተገኝተው በሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅድመ ምርጫው ሒደት ከሞላ ጎደል ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ እንደነበር መገምገሙን ተናግረዋል፡፡ 

‹‹እጅግ አብዛኞቹ የአገራችን ፓርቲዎች ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያላቸውን ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ይኼ እጅግ አበረታች ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የምርጫው ዕለትና ከዚያም በኋላ ያለው በዚህ መልኩ ሊቀጥል እንደሚችል አመላካች ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

ይሁን እንጂ አንዳንድ ለሰላማዊ ምርጫ በሙሉ ልባቸው ያልገቡ ፓርቲዎች መኖራቸውን፣ በተግባር የታየውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ የማደፍረስ እንቅስቃሴ ውስጥ ናቸው በማለት ወቅሰዋል፡፡ 

‹‹አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ገና ከወዲሁ አሸንፈናል እያሉ እየቀሰቀሱ ነው፡፡ ይህንን የሚያደርጉት በግዳጅም ቢሆን ድምፃችንን ማስመለስ አለብን ብለው ለማነሳሳት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህንን የሚያስቡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች የመጨረሻ ውጤቱ ጥሩ እንደማይሆንና ተመልሶ የሚበላው ራሳቸውን መሆኑን አውቀው በጥንቃቄ እንዲይዙት አስጠንቅቀዋል፡፡

‹‹ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች ሥርዓቱን ጠብቀን ነው መሄድ ያለብን፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ‹‹የምርጫውን ውጤት ገላጭ የምርጫ ቦርድና የምርጫ ቦርድ ብቻ ነው፤››  ብለዋል፡፡

ምርጫውን ለመታዘብ ፈቃድ ያገኙት የአፍሪካ ኅብረትና የኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበራት ጥምረትም ቢሆኑም፣ ትዝብታቸውን ከመናገር ውጪ ውጤት የመግለጽ ኃላፊነት የላቸውም ብለዋል፡፡ 

ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ይቀጥላል የሚል ግምገማ ቢኖርም፣ አልፎ አልፎ የሚታዩ የግጭት ምልክቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን የአንድ ሉዓላዊ መንግሥት ኃላፊነት ሕግና ሥርዓትን ማስከበር በመሆኑ መንግሥታቸው ለአንድ አፍታ እንኳን ‹‹ሸብረክ›› እንደማይል አስታውቀዋል፡፡

 

 

ሟች ሃና ላላንጎ ይህቺ ነበረች

– ከ17 ዓመታት እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደባቸው

ሃና ላላንጎ የተባለችውንና 16 ዓመቷ እንደሆነ የተነገረውን ታዳጊ፣ አስገድደውና ተፈራርቀው በመድፈር ለሞት መዳረጋቸው ተረጋግጦ ጥፋተኛ የተባሉት የታክሲ ሾፌሮችና ረዳቶቻቸው፣ ግንቦት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ከ17 ዓመታት እስከ ዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተፈረደባቸው፡፡

የክስ ሒደቱን በዝግ ችሎት ሲሰማና ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በአብላጫ ድምፅ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የፈረደባቸው፣ አንደኛ ተከሳሽ ሳምሶን ስለሺና ሁለተኛ ተከሳሽ በዛብህ ገብረ ማርያም ናቸው፡፡

እንዳልተማረና ነገሮችን ማገናዘብ እንደማይችል የቅጣት ማቅለያ ቢያቀርብም፣ በማስረጃ የተደገፈ ባለመሆኑ ፍርድ ቤቱ ያልተቀበለው ሦስተኛ ተከሳሽ በቃሉ ገብረ መድኅን በ17 ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተፈርዶበታል፡፡ አራተኛው ተከሳሽ ኤፍሬም አየለ በ20 ዓመታት ጽኑ እስራት፣ አምስተኛው ተከሳሽ ተመስገን ፀጋዬ በ18 ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ በልዩነት ፍርድ ሰጥቷል፡፡ 

ፍርደኞቹ ከዚህ በፊትም የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽመው የተቀጡ መሆናቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ለቅጣት ማክበጃ ባቀረበው ሰነድ ላይ እንደተረጋገጠው አንደኛ ተከሳሽ በቅሚያ፣ ሁለተኛ ተከሳሽ አስገድዶ በመድፈር፣ ሦስተኛ ተከሳሽ ደግሞ በስርቆት ተፈርዶባቸው የነበረ ሲሆን፣ ሁሉም ፍርደኞች ቀደም ብሎ የተፈረደባቸውን ቅጣት ፈጽመው ከወጡ አምስት ዓመታት እንኳን ሳይቆዩ፣ በሃና ላይ ሌላ የወንጀል ድርጊት በመፈጸማቸው ቅጣቱን ከፍ እንዳደረገባቸውም ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡

18 ዓመት ያልሞላትንና ልዩ ጥበቃ የምትፈልግን ታዳጊ፣ ጭካኔ በተሞላበትና ለሕሊና (ሞራል) ተቃራኒ በሆነ መንገድ ተፈራርቀው በመድፈርና ከፍተኛ ደም እየፈሰሳት መንገድ ላይ አውጥተው በመጣል ከባድ ወንጀል መፈጸማቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበባቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች መረጋገጡን ፍርድ ቤቱ በአብላጫ ድምፅ አስረድቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ክስ ከመስማት እስከ ውሳኔ (ጥፋተኛ እስከተባሉበት) ድረስ ችሎቱን ዝግ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፣ ፍርዱን ግን በግልጽ ችሎት ወስኗል፡፡ 

ሃና ላላንጎ በመስከረም ወር 2007 ዓ.ም. ትምህርት ቤት ውላ ስትመለስ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አየር ጤና አካባቢ ስትደርስ፣ አንድ ሚኒባስ የያዘ ወጣት “እንሸኝሽ” ብሎ ካስገባት በኋላ፣ ከረዳቱ ጋር በመሆን ወደ ጦር ኃይሎች አካባቢ ይዘዋት ይሄዳሉ፡፡ አንድ ቤት ውስጥ ይዘዋት ካመሻሹ በኋላ፣ በዚያው ክፍለ ከተማ ከቀራኒዮ መድኃኒዓለም ከፍ ብሎ ታጠቅ መንገድ ላይ ይዘዋት በመሄድ፣ ጓደኛቸው በተከራየበት አንድ ትልቅ ግቢ ውስጥ ባለ አንድ ክፍል ቤት ይዘዋት እንደገቡ፣ ፖሊስ በጊዜ ቀጠሮው ወቅት በግቢው የነበሩ እማኞች በመጥቀስ አስረድቷል፡፡ 

እንደ ፖሊስ የምርመራ ውጤት፣ ሃናን ከወሰዷት ሾፌርና ረዳቱ በተጨማሪ ሌሎች ሦስት ሰዎች እዚያው ስለነበሩ ሌሊቱን ለአምስት እየተፈራረቁ እንደደፈሯት፣ ሃና በመጨረሻዎቹ ቀናት እንደተናገረችም አመልክቷል፡፡ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ባደረሱባት የመድፈር ጥቃት ደም ሲፈሳት፣ ጦር ኃይሎች አካባቢ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን አጥር ሥር ተጥላ መገኘቷም በወቅቱ ተነግሯል፡፡ 

እህትና ወንድሟ ጦር ኃይሎች አካባቢ እንዳገኟት ወደ አለርት ሆስፒታል የወሰዷት ቢሆንም፣ በቂ ሕክምና ሳታገኝ ቆይታ ወደ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ሪፈር ብትደረግም፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ያለምንም ሕክምና ወደ ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ሪፈር መደረጓን መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ጋንዲ ሆስፒታልም ወደ ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ሪፈር አድርጓት፣ ዘውዲቱ ሆስፒታል የቻለውን ዕርዳታ እንዳደረገላት ተገልጿል፡፡ ሐና በደረሰባት ጉዳት አፋጣኝ የሕክምና ዕርዳታ ባለማግኘቷ፣ ብዙ ደም ፈሷት ስለነበርና ጉዳቱም ወደ ኢንፌክሽን ተቀይሮ ስለነበር ሕይወቷ ሊተርፍ አልቻለም፡፡ መስከረም 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡

 

 

 

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ችግር ለመፍታት፣ ለአልሚዎች መሬት እንዲቀርብ ከሁለት ሳምንት በፊት መመርያ መስጠቱን ምንጮች ገለጹ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርበት እየተከታተለ 48 ቦታዎች ላይ ለመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) የሚያገለግሉ ሕንፃዎች እንዲገነቡ እንዲያደርግ መመርያ መስጠቱንም ጠቁመዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰሎሞን ኃይሌ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ትዕዛዙ መስጠቱን ባያረጋግጡም፣ ለፓርኪንግ አገልግሎት የሚውሉት ቦታዎች ተለይተው መዘጋጀታቸውን ግን ገልጸዋል፡፡ 

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ይህን መመርያ ሊሰጥ የቻለው የሊዝ አዋጁና መመርያው ለመኪና ማቆሚያ ቦታ በመስጠት በኩል ክፍተት ያለበት በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ አገር አልሚዎች በተለያዩ ጊዜያት ለማኅበራዊ አገልግሎቶች ማለትም ለሆቴል፣ ለሆስፒታል፣ ለሞል፣ ለሪል ስቴትና ለመኪና ማቆሚያ የሚውል ቦታ እንዲሰጣቸው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ 

ነገር ግን አስተዳደሩ እነዚህን የቦታ ጥያቄዎች ላስተናግድ ቢል እንኳ በሊዝ አዋጁ አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 21 እና በአገራዊ ፋይዳ መመርያ ቁጥር 15/2005 ላይ በግልጽ እንደሰፈረው፣ ‹‹ልዩ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች›› የሚባሉት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጡ የልማት ፕሮጀክቶች ወይም የትብብር መስኮች ለማስፋት ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መሠረት እንዲጥሉ በመንግሥት የታቀዱ ፕሮጀክቶች ናቸው የሚል በመሆኑ፣ ለመኪና ማቆሚያ የሚያገለግሉ ሕንፃዎች ለመገንባት ቦታ መፍቀድ ከሊዝ አዋጁ ጋር ይጋጫል ተብሏል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ባለሙያዎች ከአልሚዎች የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ መቸገራቸውን መግለጻቸውን፣ የከተማ አስተዳደሩም የሊዝ አዋጁ እንዲሻሻል ጥያቄ ማቅረቡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

አዳዲስ የቦታ ጥያቄዎች እስካሁን ምላሽ ባያገኙም የአዲስ አበባ የመኪና ማቆሚያ ችግር ሥር እየሰደደና ለከተማው ትራንስፖርት ፍሰት ማነቆ ሆኗል በሚል፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጣልቃ መግባቱን ምንጮች አመልክተዋል፡፡ 

ምንጮች ጨምረው እንደገለጹት፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ሞዴል ፓርኪንግ ሕንፃዎችን እንዲሠራና የግል ባለሀብቶች ደግሞ ፕሮጀክታቸው እየታየ በልዩ ሁኔታ እንዲስተናገዱ ነው መመርያው የተሰጠው፡፡ 

ሌሎቹ ማኅበራዊ ፋይዳ ፕሮጀክቶች በምን መንገድ እንደሚስተናገዱ የተሰጠ አቅጣጫም ሆነ የአዋጅ ማሻሻያ እንዳልተደረገ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የመኪና ማቆሚያ ችግር መኖሩ ይታወቃል፡፡ 

 

ባንክ ለማቋቋም በምሥረታ ላይ እንዳሉ ያስፈልጋቸው የነበረውን ካፒታል ማሟላት ሳይችሉ የቀሩና በተለያዩ ምክንያቶች ሳይቋቋሙ ከቀሩ የግል ባንኮች ላይ አክሲዮን ገዝተው የነበሩ ባለአክሲዮኖች፣ ገንዘባቸውን እንዲወስዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ  አሳሰበ፡፡

ብሔራዊ ባንክ ሳይቋቋሙ በጅምር ከቀሩት ከዘምዘም፣ ከኖኅ፣ ከፀሐይ፣ ከሐዋሳ፣ ከኮከብ፣ ከመርካቶ ሲቲና ከአፍሪ አግሮ ኢንዱስትሪ ባንኮች አክሲዮን ገዝተው የነበሩ ባለአክሲዮኖች፣ ገንዘባቸውን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. መውሰድ እንደሚኖርባቸው አሳስቧል፡፡

ከተጠቀሱት ባንኮች አክሲዮን ገዝተው እስካሁን ያልወሰዱ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ከአደራጅ ኮሚቴዎቹ ክፍያ የሚገባቸው ለመሆኑ መረጃ በመያዝ ገንዘባቸውን ሊወስዱ እንደሚችሉ፣ የብሔራዊ ባንክ ማሳሰቢያ ያስረዳል፡፡ ገንዘብ አለን የሚሉት ወገኖች ለአክሲዮን ግዥ አውለውት የነበረውን ገንዘብ መውሰድ የሚችሉት፣ ባንኮቹን ለማቋቋም አክሲዮን ግዥ ካከናወኑበት የባንክ ቅርንጫፎች እንደሆነም ገልጿል፡፡

ከብሔራዊ ባንክ የተገኘው ተጨማሪ መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ብሔራዊ ባንክ ገንዘባቸውን ላልወሰዱ አክሲዮን ገዥዎች ይህንን መልዕክት ያስተላለፈው አብዛኛዎቹ ባለክሲዮኖች ገንዘባቸውን የወሰዱ ቢሆንም፣ አሁንም በተለያዩ ምክንያቶች ገንዘቡን መውሰድ ያልቻሉ መኖራቸውን በማረጋገጡ ነው፡፡ ባለአክሲዮኖቹ ገንዘባቸውን ማግኘት ስላለባቸው የተላለፈ መልዕክት መሆኑን የሚገልጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የባለአክሲዮኖች ገንዘብ በዝግ አካውንት የተቀመጠ በመሆኑ አስፈላጊውን መረጃ በማቅረብ ሊወስዱ ይገባል፡፡ 

ሳይቋቋሙ ከቀሩት ባንኮች መካከል ዘምዘም ባንክ በወቅቱ ባንክ ለማቋቋም ይፈቀድ የነበረውን የተከፈለ ካፒታል ማሟላት የቻለ ቢሆንም፣ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎትን ብቻ ነጥሎ ለመሥራት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ወደ ሥራ ሳይገባ መቅረቱ ይታወሳል፡፡

መደበኛውና የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎቶችን አጣምሮ እንዲሠራ የቀረበውን ጥያቄ ባለመቀበሉ ዘምዘም ባንክ ወደ ሥራ መግባት ባይችልም፣ የሰበሰበውን ካፒታል ለሌላ ኢንቨስትመንት ለማዋል ዕቅድ ነበረው፡፡ ሆኖም የተሰበሰበው ገንዘብ ይመለስ በመባሉ ለባንክ ማቋቋሚያ ከተፈረመውና ከተከፈለው ከ370 ሚሊዮን ብር በላይ ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን ባለአክሲዮኖች ወስደዋል ተብሏል፡፡ 

ሌሎቹ ባንኮች ሳይቋቋሙ የቀሩት ግን አክሲዮን በማሰባሰብ ላይ እያሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ማቋቋሚያ የተከፈለ ካፒታል መጠን ከ100 ሚሊዮን ብር ወደ 500 ሚሊዮን ብር እንዲያድግ መመርያ በመውጣቱ ነው፡፡ በአዲሱ መመርያ መሠረት የተጠየቀውን ካፒታል ለማሟላት የማይቻል በመሆኑ፣ በመቋቋም ላይ የነበሩት ባንኮች የአክሲዮን ሽያጫቸውን እንዳቋረጡ ይታመናል፡፡ ፀሐይ ባንክ ደግሞ ለባንክ የሰበሰውን አክሲዮን ወደ ሌላ ኢንቨስትመንት እንዳዛወረው መግለጹ ይታወሳል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከሁለት ዓመታት ተኩል በፊት የባንክ ማቋቋሚያ ካፒታል መጠንን 500 ሚሊዮን ብር እንዲሆን ከመወሰኑ በፊት፣ በ100 ሚሊዮን ብር ካፒታል መቋቋም የቻሉት የመጨረሻ ባንኮች ደቡብ ግሎባልና እናት ባንክ ናቸው፡፡ የባንክ ማቋቋሚያ የተከፈለ ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ከተወሰነ ወዲህ፣ እስካሁን አዲስ ባንክ አልተመሠረተም፡፡

 

 

 

–  ታግዶ የነበረው ብይን እንዲቀጥል ትዕዛዝ ተሰጠ

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ከቤቶች ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ የግብዓት አቅርቦትና አስተዳደር መምርያ ጋር በተገናኝ የመሠረተውን የሙስና ወንጀል ክስ እየሰሙ የሚገኙት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ዳኞች እንዲነሱለት፣ ሚያዝያ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. አቅርቦት የነበረው የአቤቱታ ደብዳቤ ውድቅ ተደረገ፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ አቤቱታውን አቅርቦ የነበረው፣ በሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን ገልጾ ክስ በመሠረተባቸው የቤቶች ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ግብዓት አቅርቦትና አስተዳደር መምርያ ምክትል ሥራ አስኪያጅና  የኤቢፕላስት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ኩባንያ ባለቤት ጉዳይ ሲሆን፣ የችሎቱ ዳኞች ገለልተኛ ሆነው ይሠራሉ የሚል ዕምነት እንደሌለው በመግለጽ ነው፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የቅሬታ አቤቱታ እንደገለጸው፣ በአዋጅ ቁጥር 343/1997 አንቀጽ 38(2) መሠረት የምስክሮቹ ስም በሚስጥር እንዲያዝለት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም፡፡

በዚህም ምክንያት ምስክሮቹ በተከሳሾች ማስፈራሪያ ስለደረሰባቸው ለመመስከር ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን፣ ያቀረባቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች በአንድነት ሳይመረምሩና መጣራት ያለበት ፍሬ ነገር መኖር አለመኖሩን ከማስረጃው አንፃር ሳይጣራ ፍርድ ቤቱ ምስክሮችን ሰምቶ ባጠናቀቀበት ዕለት የማጣርያ ምስክሮችን ጠርቶ መስማቱንም አስረድቷል፡፡ በመሆኑም በመዝገቡ አያያዝም ሆነ አጠቃላይ የክርክር ሒደት በችሎቱ ዳኞች ገለልተኛነት ላይ ጥርጣሬ ስላደረበትና በቀጣይ ለሚሰጠው ብይንም ሆነ ፍርድ ፍትሐዊነት ላይ እንደሚጠራጠር ዓቃቤ ሕግ በአቤቱታው ገልጿል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 28(1) መሠረት በሌላ ችሎት እንዲታይለት ወይም ለዳኞች አስተዳዳር ጉባዔም አቤቱታ በማቅረቡ፣ ጉባዔው ምላሽ እስከሚሰጠው ድረስ  ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ሊሰጥ የነበረው ብይን ታግዶ እንዲቆይ አድርጎ ነበር፡፡

ጉዳዩን እየሰማ የነበረውና እንዲነሳ የተጠየቀው ችሎትም በኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ አቤቱታ ላይ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ ችሎቱ በትዕዛዙ ላይ እንደገለጸው፣ ዓቃቤ ሕግ የምስክሮቹ ስም በሚስጥር እንዲያዝለት ጠይቆ ተቀባይነት ካላገኘ ይግባኝ በማለት ‹‹ጉድለት አለ›› የሚልበትን አግባብ ማስረዳት ነበረበት፡፡ ምስክሮቹም ማስፈራርያ እንደ ደረሰባቸው ለችሎት ማመልከት ሲገባው አላመለከተም፡፡ ሌላው ፍርድ ቤቱ በማንኛውም ጊዜ ማንኛውንም ምስክር ጠርቶ መስማት እንደሚችል በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 143 (1) ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ የቀጠሮ አያያዝ ደግሞ የችሎት ሥልጣን በመሆኑና የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ለችሎቱ ያቀረበውም የክስ ሒደት ከሌሎች ክሶች በተለየ አግባብ የታየበት ሁኔታ ስለሌለ፣ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 27 መሠረት ዳኞችን ከችሎት ከሚያስነሱ ምክንያቶች ውስጥ አለመሆኑን ጠቅሶ አቤቱታውን ውድቅ አድርጎት ነበር፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ‹‹ዳኞች ይነሱልኝ›› ጥያቄና ለመነሳታቸው ባቀረበው ምክንያቶች ላይ ችሎቱ ዝርዝር ማስረጃዎችን ከሕጉ ድንጋጌ ጋር ካስረዳ በኋላ፣ በአዋጁ አንድ ቅሬታ የቀረበበት ዳኛ እንዴት ከችሎት እንደሚነሳ ከማሳወቁ ውጪ ሦስት ዳኞች በአንድ ጊዜ እንዴት እንደሚነሱ ያለው ነገር እንደሌለም ጠቅሷል፡፡ ነገር ግን ምንም እንኳን ስለሦስት ዳኞች መነሳት ሕጉ የሚለው ነገር ባይኖርም፣ አንድ ዳኛ ከችሎት እንዲነሳ አቤቱታ ሲቀርብበት፣ የማይነሳበትን ምክንያት በያዘው መዝገብ ላይ አስፍሮ በሬጅስትራር በኩል ወደ ሌላ ችሎት ተመርቶ እንዲመረመር በሚያዘው መሠረት፣ ሦስቱም ዳኞች ዝርዝር ሐሳባቸውን በመዝገቡ አስፍረው በሬጅስትራር በኩል ለሌላ ችሎት እንዲመራ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር፡፡

በሬጅስትራር በኩል መዝገቡ የደረሰው ሌላው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት፣ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1998 አንቀጽ 28/3/ መሠረት የዓቃቤ ሕግን አቤቱታ ፍሬ ነገር ከተገቢው የሕግ ድንጋጌ ጋር በማገናዘብ መርምሮ ብይን ሰጥቷል፡፡

ችሎቱ እንደመረምረው ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹ በሚስጥር እንዲያዙለትና ማንነታቸው እንዳይገለጽ ያቀረበውን አቤቱታ ችሎቱ (ስምንተኛ ወንጀል ችሎት) ውድቅ ያደረገው ‹‹ዳኞቹን ከችሎት ሊያስነሳቸው ይችላል ወይስ አይችልም?›› የሚለውን አይቶ ነው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 27(1) ከ‹‹ሀ›› እስከ ‹‹መ›› ዳኞች እንዴት ከችሎት መነሳት እንዳለባቸው ከተዘረዘሩት ውስጥ የማይካተት ቢሆንም፣ በዚሁ አዋጅ ቁጥር ንዑስ አንቀጽ 1‹‹ሠ›› ሥር ዳኞች የሚነሱበት በቂ ምክንያት ካለ እንዴት እንደሚነሱ መደንገጉን ችሎቱ ጠቁሟል፡፡ 

በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ፍሬ ነገር ‹‹ሊካተት ይችላል? ወይስ አይችልም?›› የሚለውን ጭብጥ ይዞ ችሎቱ ሲመረምረው፣ ዓቃቤ ሕግ የምስክሮቹን ማንነት መግለጽ ያቀረበውን ክስ እውነታ እንዳያውጣጣ የሚያደርገው ከሆነ ይግባኝ መጠየቅ ከሚገባው በስተቀር ለዳኞች መነሳት ምክንያት ሆኖ ሊወሰድ የሚያበቃ፣ ወይም አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 27(1-ሠ)ን የሚያሟላ አለመሆኑን ገልጿል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ በአንድነት ሳይመረምር ችሎቱ ምስክሮችን ሰምቶ በጨረሰበት ዕለት ማጣሪያ ምስክሮችን ጠርቶ መስማቱ አግባብ መሆን አለመሆኑን መመርመሩንም ችሎቱ ገልጿል፡፡ የክስና ማስረጃ አሰማምን በሚመለከት በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ክፍል ሁለት አንቀጽ 136ና ተከታዮቹ ላይ መደንገጉንም ጠቁሟል፡፡ አንድ ችሎት መዝገብ ሳይመረምር በወ/ሥ/ሥ/ሕግ አንቀጽ 143(1) መሠረት ማስረጃ መስማት ይችላል፡፡ ችሎቱ ከመጀመርያ ጀምሮ እየሰማው የመጣ ጉዳይ ከሆነ የምስክር ቃልና ማስረጃን መርምሮ ለመለየት ቀጠሮ መስጠት ላያስፈልገው እንደሚችልም ችሎቱ አክሏል፡፡ በችሎቱ ተጨማሪ ማስረጃ አለመስማት፣ በችሎቱ ተጨማሪ ማስረጃ በማዘዝ መስማት፣ ዳኞቹ የሥነ ሥርዓት ሕጉን ሳይከተሉ ሠርተዋል አስብሎ ገለልተኛነታቸውን የሚያስጠረጥር አለመሆኑን ገልጾ ከችሎት የሚነሱበት በቂ ምክንያት አለመሆኑን አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ሌላው ያቀረበው አቤቱታ ችሎቱ (18ኛ ወንጀል ችሎት) ቀጠሮዎችን ሲሰጥ የቀኑን መቀራረብ (በአጭር በአጭር ቀናት) የዳኞችን ገለልተኝነት ላይ ጥርጣሬ እንዳሳደረበት ሲሆን፣ መዝገቡን የመረመረውም ችሎት ማብራርያ ሰጥቷል፡፡ መዝገቡ የሚያመለከትው ችሎቱ የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን ቀጠሮዎችን በቀናት፣ በሳምንታትና በ15 ቀናት ልዩነት ሲሰጥ እንደነበር ከመዝገቡ ለመረዳት መቻሉን ገልጿል፡፡ የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 94 (1) እና 94 (2 – መ) ላይ ተደንግጎ እንደሚታየው ፍርድ ቤት ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ ይረዳል ብሎ ካመነበት፣ የቀጠሮውን ሥርዓት የመምራት ሥልጣን የችሎቱ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 (1) ላይም የተከሰሱ ሰዎች ክሳቸውን በአጭር ጊዜ መስማትና እልባት ማግኘትም እንዳለባቸው መደንገጉንም አክሏል፡፡

በኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ አቤቱታ የቀረበበት 18ኛ ወንጀል ችሎትም የሰጠው ቀጠሮ፣ ሕጋዊ መሠረት ያለውና ሕገ መንግሥቱን በማክበርና የማስከበር ግዴታውን ከመወጣት የመነጨ እንጂ፣ ትክክለኛው ፍትሕ እንዳይሰጥ የሚያደርግ በቂ ምክንያት ሊሆን እንደማይችል ችሎቱ አስታውቋል፡፡

በአጠቃላይ በኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የቀረቡት ‹‹ዳኞች ከችሎት ይነሱልኝ›› ምክንያቶች፣ ከምክንያቶቹ በስተጀርባ የዳኝነት ሥርዓቱ የማይፈቅደውና ከሥነ ምግባር ውጪ የተከናወነ ተግባር መኖሩን ካላመለከተና ዳኞቹ እውነተኛውን ፍርድ እንዳይሰጡ የሚያደርጓቸውን ምክንያቶች ያላስደገፈ መሆኑን ችሎቱ በብይኑ ገልጿል፡፡ ዳኞች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 70 (3) በሙሉ ነፃነት ሕግን መሠረት አድርገው መሥራት እንዳለባቸው ከሚደነግገው አንቀጽ ጋር የሚጣረስና የአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 27ን ዓላማና መንፈስን ያልተከተለ መሆኑን አብራርቶ፣ የቀረበውን አቤቱታ እንዳልተቀበለው በመግለጽ ውድቅ አድርጎታል፡፡ መዝገቡም ወደሚታይበት 18ኛ ወንጀል ችሎት ተመልሶ ቀጠሮውን ተከትሎ ብይኑ እንዲሰጥ አዟል፡፡

 

 

ኢንጂነር ታደሰ ተሰማ  ---------------    ዶ/ር ፍሬሕይወት ወልደሃና

– የኩባንያው ንብረት መዘረፉ ይነገራል

የከሰረው የሆላንድ ካር ኩባንያ ባለቤት ኢንጂነር ታደሰ ተሰማ ከሦስት ዓመት የውጭ አገር ቆይታ በኋላ ባለፈው ሳምንት ወደ አገር ቤት በመመለስ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ ኩባንያቸውን ለመታደግ ያስችላል ብለው ያቀረቡት ዕቅድ ከድርጅቱ ደንበኞች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው፡፡ 

ኢንጂነር ታደሰ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ሐሙስ ግንቦት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል በሰጡት መግለጫ፣ የከሰረው ኩባንያቸው በሐራጅ ቢሸጥ ማንም ተጠቃሚ እንደማይሆን ገልጸው፣ ይልቁንም ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ዕቅድ ይዘው መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ኢንጂነር ታደሰ ሞጆ በሚገኘው የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ውስጥ የሚገኙትን ያልተገጣጠሙ መኪኖች ገጣጥሞ የቅድሚያ ክፍያ ለከፈሉ ደንበኞች በማስረከብ፣ በቀጣይም ኩባንያው ያለበትን የባንክና የመንግሥት ዕዳ ለመክፈል ማቀዳቸውን አስታውቀዋል፡፡ ዕቅዳቸውን ለመንግሥት አቅርበው ተቀባይነት በማግኘቱ የሕግ ከለላ ተሰጥቷቸው ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን፣ ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ስድስት ሚሊዮን ብር ይዘው መምጣታቸውን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል፡፡ 

ኢንጂነር ታደሰ የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በኩባንያው ደንበኞች አካባቢ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀስቅሷል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ከኩባንያው መኪና ለመግዛት ቅድሚያ ክፍያ ከፍለው መኪኖቻቸውን ሳይረከቡ የቀሩ ግለሰቦች ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ 

የከሰረው የሆላንድ ካር ገንዘብ ጠያቂዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር ፍሬሕይወት ወልደሃና ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢንጂነር ታደሰ ከመኪና ገዢዎች ጋር ሳይመክሩ ያቀረቡት ዕቅድ ተቀባይነት የለውም፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባዮሜዲካል ማዕከል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ፍሬሕይወት፣ ባለሀብቱ ያቀረቡት ዕቅድ አዲስ አለመሆኑን፣ ለኪሳራ አጣሪ ዳኛና ለገንዘብ ጠያቂዎች ኮሚቴ ቀርቦ ተጨባጭ ማስተማመኛ የሌለው በመሆኑ ውድቅ የተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 

‹‹በዕቅዱ መሠረት ኢንጂነር ታደሰ ስድስት ሚሊዮን ብር ይዤ መጥቻለሁ ነው የሚሉት፡፡ ኩባንያው ያለበት ዕዳ በትክክል መናገር ባይቻልም፣ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ስድስት ሚሊዮንና 80 ሚሊዮን ብር በጣም የተራራቁ ናቸው፤›› ያሉት ዶ/ር ፍሬሕይወት፣ ‹‹ይህንን ዕቅድ መኪና ገዢዎችን (የኩባንያው ደንበኞችን) ሰብስበው ቢያወያዩ መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን እስካሁን ካለው ሁኔታ ግለሰቡ በተጨባጭ ያደረጉት ነገር የለም፡፡ ደንበኞች የደረሰባቸውን ችግር ለመፍታት ያደረጉት ጥረት የለም፡፡ ከዘመን ባንክ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረው ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚያ ውጪ ከደንበኞች ጋር ያደረጉት ውይይት የለም፤›› ብለዋል፡፡ 

ደንበኞች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደው ሲከታተሉ ብዙ ውጣ ውረድ እንደደረሰባቸው የሚናገሩት ዶ/ር ፍሬሕይወት፣ የኩባንያው ባለቤት አገር ጥለው በመኮብለላቸውና ኩባንያው በመዘጋቱ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ እንደነበር፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሒደት ውስጥ ኪሳራ መታወጁን፣ የኪሳራ አጣሪ ዳኛና ንብረት ጠባቂ መሾሙን አስረድተዋል፡፡ ገንዘባቸውን ከፍለው ንብረታቸውን ያልተረከቡ ግለሰቦች እንደገና ገንዘብ በማዋጣት ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቶ ወደመቋጫው ላይ ሲደረስ፣ ባለሀብቱ ከስደት ተመልሰው የሰጡት መግለጫ ውዥንብር እንደፈጠረም አመልክተዋል፡፡ 

‹‹መንግሥት ከለላ አድርጎልኝ መጣሁ ቢሉም በትክክል ግዴታቸውን ለመወጣት የሚያስችላቸውን የፋይናንስ አቅም ይዘው እንዳልመጡ ድርጅቱ ያለበት ዕዳና ያለው ንብረት በግልጽ ያሳያል፡፡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መኪኖችን አስረክባለሁ ሲሉ ለዚህ የሰጡት ምንም መተማመኛ የለም፡፡ ከዚህም አልፎ ደንበኞች ለዳኝነት፣ ለጠበቃ፣ ለንብረት ጥበቃና ለመሳሰሉት ተያያዥ ወጪዎች ያወጡትን ተጨማሪ ገንዘብም ሆነ የዋጋ ግሽበትን በተመለከተ ኢንጂነር ታደሰ የጠቀሱት ምንም ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡ 

‹‹የኩባንያው ደንበኞች ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት ሲከታተሉ ቆይተው የተፈረደላቸው አሉ፡፡ በሒደት ላይ ያሉ አሉ፡፡ ይግባኝ የጠየቁ አሉ፡፡ ተወስኖላቸው የፍርድ አፈጻጸም የሚጠብቁ አሉ፡፡ በተለያየ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ የደንበኞች ፍላጎት ግልጽ ነው፡፡ ገንዘባቸውን ማግኘት ነው፡፡ የተወሰኑት መኪናቸውን ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ አብዛኛው ግን የከፈለውን ገንዘብ ከነኪሳራው ማግኘት ይፈልጋል፤›› ያሉት ዶ/ር ፍሬሕይወት፣ ኢንጂነር ታደሰ ያቀረቡት ዕቅድ በኮሚቴያቸው ተቀባይነት እንዳላገኘ አስረድተዋል፡፡ 

‹‹ይዘውት የመጡት ሐሳብ ንብረታችንን እንደምናገኝ ማስተማመኛ ስለሌለው አልተቀበልነውም፡፡ በፍርድ ቤት ሒደት እንጨርሳለን፡፡ ዳር የደረሰ ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አያይዘውም ኢንጂነር ታደሰ ኮሚቴውን ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ ደንበኞችን ማነጋገር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ደንበኞች ምን ይላሉ ብለው ማዳመጥ አለባቸው፡፡ አጠቃላይ ስብሰባ ተጠርቶ ከደንበኞች ጋር መወያየት አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡ 

የሆላንድ ካር ንብረት የአገር ሀብት እንደሆነና ንብረት ለመሸጥ ብዙም ፍላጎት እንደሌለ የሚናገሩት ዶ/ር ፍሬሕይወት፣ አዋጭ የሆነና ለሁሉም ወገን የሚጠቅም ዕቅድ ይዞ መቅረብ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 

ከሆላንድ ካር መኪና ገዝተው ያልተረከቡ ሰዎች ከ200 በላይ ናቸው፡፡ ለኩባንያው ብድር የሰጠው ዘመን ባንክ 34 ሚሊዮን ብር በላይ ይፈልጋል፡፡ የጉምሩክ ቀረጥና ግብር ዕዳ እንዲሁም የኩባንያ ሠራተኞች የአገልግሎት ክፍያ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ኢንጂነር ታደሰ የኩባንያቸው ንብረት 180 ሚሊዮን ብር እንደሚገመትና ኩባንያው ያለበት ዕዳ 63 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የኪሳራ አጣሪ ቡድኑ ይህን አልተቀበለም፡፡ የኪሳራ መርማሪ ዳኛ አቶ አሰፋ ዓሊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የተመሰከረለት የዋጋ ገማች የተመነው የሆላንድ ካር ንብረት 83,058,533 ብር ነው፡፡ ኩባንያው ላይ የቀረበው የዕዳ ጥያቄ 160 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ፣ ከዚያ ውስጥ አጣሪ ቡድኑ መርምሮ በመረጃ ያረጋገጠው 74 ሚሊዮን ብር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አቶ አሰፋ ኢንጂነር ታደሰ ያቀረቡትን ዕቅድ በጥብቅ ተቃውመዋል፡፡ ባለሀብቱ በአካል መጥተው እንዳላናገሯቸው አረጋግጠዋል፡፡ በእርግጥ ከአንድ ወር በፊት የአገሪቱ የንግድ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት የስምምነት ሐሳብ (Composition Proposal) በጠበቆቻቸው አማካይነት ማቅረባቸውን አልሸሸጉም፡፡ 

‹‹የኪሳራ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ፣ ዕዳ ከተጣራ በኋላ ባለቤቱ ድርጅቱን እንደገና ላንቀሳቅሰው እችላለሁ፣ በሐራጅ ቢሸጥ እንጎዳለን፣ ባለቤቶቹ ገንዘብ ጠያቂዎቹ ይጎዳሉ፣ ኩባንያውን አንቀሳቅሼ የእነርሱንም ዕዳ እከፍላለሁ የሚል ዕቅድ አቅርበው ነበር፡፡ ገንዘብ ጠያቂዎች ከተስማሙ (የማይስማሙ ከሆነ እንኳ ፍርድ ቤት ካፀደቀው) መልሰው ሊሠሩ ይችላሉ የሚል የሕግ መብት ስላለ፣ ያንን መብታቸውን ለመጠቀም የስምምነት ሐሳብ ከአንድ ወር በፊት ልከው ነበር፤›› ያሉት አቶ አሰፋ፣ በስምምነት ሐሳቡ ላይ የተጠቀሱ ችግሮችን ነቅሰው አውጥተዋል፡፡ 

‹‹ስድስት ሚሊዮን ብር አገኘሁ ይላል፡፡ ይህ ገንዘብ ያሠራል አያሠራም የሚለውን ለመወሰን አንችልም፣ ሙያችንም አይደለም፡፡ በሕግ የሚጠየቅ ለገንዘብ ጠያቂዎች ዋስትና ተቀማጭ መደረግ አለበት ይላል፡፡ በተጨባጭ ይህን አላደረጉም፡፡ ለማድረግ ስለመቻላቸውና ፈቃደኛ ስለመሆናቸው የገለጹት ነገር የለም፡፡ በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ዕቅዱን እንደማንቀበል በጽሑፍ በጠበቆቻቸው በኩል ምላሽ ሰጥተናል፤›› ብለዋል፡፡ 

በፍርድ ሒደት ብዙ ርቀት ሄደው፣ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ንብረት ተቆጥሮ እንዲጠበቅ አድርገው፣ ከብዙ ትግል በኋላ ወደ ጨረታ ሒደት በገቡበት ወቅት ኢንጂነር ታደሰ በድንገት ከተሰወሩበት ብቅ ብለው መንግሥት ከለላ ሰጥቶኝ መጥቻለሁ በማለት የሰጡት መግለጫ፣ ሁሉንም ወገኖች ግራ ያጋባና የጨረታ ሒደቱንም እንዳጨናገፈ አቶ አሰፋ ተናግረዋል፡፡ 

ገንዘባቸውን ከፍለው መኪናቸውን ሳይረከቡ የቀሩ ግለሰቦች ባዋጡት ሁለት በመቶ ገንዘብ ቢሮ ተከራይተው ባቋቋሙት ተቋም ሥራቸውን እንደሚያካሂዱ የገለጹት አቶ አሰፋ፣ ግለሰቦቹ በፊት የተቀሙት ገንዘብ ሳያንስ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን፣ ይህን ገንዘብ በጥንቃቄ ሥራ ላይ በማዋል ተቋሙ የኩባንያው ደንበኞች ያጡትን ንብረታቸውን ለማስመለስ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ ዘመን ባንክ አለኝ የሚለውን ገንዘብ ለማስመለስ በመያዣነት የያዘውን የኩባንያውን ንብረት (ፋብሪካ፣ መጋዘንና ሕንፃ) ለመሸጥ ሲነሳ እስከ ሰበር በደረሰ የፍርድ ቤት ክርክር ማስቆማቸውን ገልጸዋል፡፡ ባንኩ አለኝ የሚለውን መብቱን በፍርድ ቤት ያሉ ክርክሮች ሲያልቁ ከተወሰነለት ገንዘቡን እንዲወስድ ተስማምተው ወደ ሥራ መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡ የድርጅቱ ሠራተኞችም በፍርድ ቤት አስወስነው የድርጅቱን መኪኖች ለማሸጥ ሲሞክሩ ማሳገዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ እስካሁን 330 ንብረትና ገንዘብ ጠያቂዎች ያሉ መሆናቸውን፣ ከእነዚህ መካከል 242 ያህሉ መኪና ገዢዎች 74 ደግሞ የኩባንያው ሠራተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ 

የኪሳራ መርማሪውና ንብረት ጠባቂው ከዘመን ባንክ ጋር ተባብሮ የመሥራትን አስፈላጊነት ተረድተው የኩባንያውን ንብረት በጨረታ ለመሸጥ በመገናኛ ብዙኃን ማስታወቂያውን አስነግረዋል፡፡ ለማስታወቂያ ብቻ ከ109 ሺሕ ብር በላይ ማውጣታቸውን የሚናገሩት አቶ አሰፋ፣ ስምንት ድርጅቶች የጨረታ ሰነድ መግዛታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የኩባንያው ንብረቶች በአጠቃላይ በ83,058,533 ብር የመነሻ ዋጋ ለሽያጭ ቀርበዋል፡፡ 

የጨረታ ሰነዱን የገዙት ኩባንያዎች ሞጆ የሚገኘውን የድርጅቱን ፋብሪካና ሌሎች ንብረቶች እንዲጎበኙ ተደርጓል፡፡ ጨረታው ሊዘጋ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ኢንጂነር ታደሰ በድንገት የሰጡት መግለጫ ገዢዎችን እንዳራቀ አቶ አሰፋ ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም በጨረታው መዝጊያ ዕለት ቅዳሜ ግንቦት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. የኢንጂነር ታደሰ ጠበቃ የኩባንያው ንብረት እንዳይሸጥ የሚከላከል የፍርድ ቤት ማገጃ ለእነ አቶ አሰፋ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የጨረታው ሒደት ተቋርጧል፡፡ 

‹‹በሕግ ተቀባይነት ያለው አሠራር የሚመስለን ዋስትና የመስጠት አቅም ካላቸው፣ ገንዘብ ጠያቂዎችን በኮሚቴያቸው አማካይነት አነጋግረውና ተስማምተው ያንን ስምምነት በፍርድ ቤት አፅድቀው ወደ ሕጋዊ አሠራር መግባት ነው፡፡ አሁን የሰጡት መግለጫ ግራ መጋባት ፈጥሮ ሥራውም ቆሟል፡፡ ይህ የበለጠ ችግር፣ የበለጠ ጥፋት እንዲደርስ ያደርጋል እንጂ ጥቅም ያለው አይመስለኝም፤›› ያሉት አቶ አሰፋ፣ በቀጣይ ምን እንደሚሆን መናገር እንደሚቸግራቸው ተናግረዋል፡፡ 

የኮሚቴው አባላት በሰጡት አስተያየት ዙሪያ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ኢንጅነር ታደሰ፣ ያቀረቡት ዕቅድ በመንግሥት ተቀባይነት አግኝቶ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተደራድረው እንዲሠሩ ተፈቅዶላቸው ወደ አገር ቤት እንደተመለሱ አስታውሰዋል፡፡

‹‹የቀረበው ዕቅድ ዋስትና አይሰጥም ለተባለው ንብረቱ የሚገኘው በእጃቸው ነው፡፡ በእጃቸው ላለ ንብረት እኔ እንዴት ዋስትና ልሰጥ እችላለሁ? እኔኮ መኪኖቹን ስጡኝና ገጣጥሜ ሸጬ ልስጣችሁ አላልኩም፡፡ እኔ ያልኩት የመንግሥትም ተወካዮች ያሉበት ኮሚቴ ተቋቁሞ እኔ ባመጣሁት ገንዘብ የቴክኒክ ጉዳዮችን ላመቻችና መኪኖቹን ገጣጥመን፣ እሴት ጨምረን ይሸጡና ደንበኞች መኪኖቻቸውን ይረከቡ፡፡ በቀጣይም ሌሎች ባለዕዳዎች ገንዘባቸው ይከፈላቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢንጅነር ታደሰ በአካል መጥቶ አላናገረንም ለሚለው አቤቱታ በሰጡት ምላሽ፣ ከመጡበት ቀን ጀምሮ የኩባንያው ንብረቶች እንዳይሸጡ ለማሳገድ ሩጫ ላይ ስለነበሩ የሚመለከታቸውን ደንበኞች በጊዜ እጥረት ምክንያት እንዳላወያዩ አምነዋል፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ተወካዮች ባሉበት በቅርብ ቀን ከደንበኞች ኮሚቴ፣ ከመርማሪ ዳኛና ከንብረት ጠባቂ ጋር ውይይት እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሞጆ ከሚገኘው የሆላንድ ካር መኪና መገጣጠሚያ 610 የመኪና ጎማዎች ከነቸርኬያቸው በቅርቡ መዘረፉን ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ፍሬሕይወት እንደማንኛውም ሰው መረጃውን እንደሰሙ ለሪፖርተር የገለጹ ሲሆን፣ የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አሰፋ በበኩላቸው ጉዳዩ በምርመራ ላይ ያለና ለፍርድ ቤት የቀረበ በመሆኑ አስተያየት እንደማይሰጡ ተናግረዋል፡፡ 

ኢንጅነር ታደሰ በበኩላቸው በሁኔታው ማዘናቸውን ለሪፖርተር ገልጸው፣ ‹‹610 የመኪና ጐማ ከነቸርኬው ሲዘረፍ ንብረት ጠባቂዎች የት ናቸው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ኢንጅነር ታደሰ፣ ‹‹610 ጐማ ለማጓጓዝ በርካታ የጭነት ተሽከርካሪዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ይህ ታቅዶና በቂ ዝግጅት ተደርጐ የተፈጸመ ወንጀል ነው፡፡ ንብረት ጠባቂዎች ኃላፊነታቸውን እየተወጡ አይደለም፡፡ ንብረቱን ፈርመው የተረከቡ ሰዎች ያስጠይቃቸዋል፡፡ 610 ጐማ ማለት የ110 መኪኖች ጐማዎች ተሰርቀዋል ማለት ነው፡፡ ምን ንብረት እንዳለና ምን ንብረት እንደተሰረቀ አይታወቅም፡፡ የንብረቱ ሁኔታ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አክለውም እርስ በርስ መወነጃጀሉ ቀርቶ በውይይት ችግሮችን ፈቶ ለሁሉም ወገን የሚጠቅም የመፍትሔ ሐሳብ ላይ መድረስ እንደሚበጅ፣ መንግሥትም ያስቀመጠው አቅጣጫ ይህንኑ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

 

ሟች ቀኝ አዝማች ግርማ አበበ

ከንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት እስከ ደርግ ሥርዓት ሶማሊያን አብጠርጥረው በማወቅና ከኢትዮጵያ ወገን የሶማሌ ክልልን በማስተዳደር፣ ብዙ እንደሠሩ የሚነገርላቸው ቀኝ አዝማች ግርማ አበበ በተወለዱ በ86 ዓመታቸው አረፉ፡፡ 

ቀኝ አዝማች ግርማ መንግሥታዊ ኃላፊነት ባለባቸው የሥራ ዘርፎች ላይ በመሰማራት ከ1943 ዓ.ም. ጀምሮ በጡረታ እስከተገለሉበት እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ በተለያዩ ጠቅላይ ግዛቶች እየተሾሙ አገልግለዋል፡፡ በ1943 ዓ.ም. የጋራ ሙለታ አውራጃ ዋና ፀሐፊ በመሆን የተመደቡ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜም በአውራጃው ዘመናዊ ትህምርት እንዲስፋፋ ማድረጋቸውን ሐሙስ ግንቦት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. በቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀብራቸው በተፈጸመበት ወቅት የተነበበው የሕይወት ታሪካቸው ይዘክራል፡፡ 

በ1965 ዓ.ም. የኤልከሬ አውራጃ ገዥ፣ በ1966 ዓ.ም. የገናሌ አውረጃ ገዥ፣ በዚያው ዓመት የጅጅጋ አውራጃ ገዥ፣ እንዲሁም በደርግ መንግሥት በ1967 ዓ.ም. የጨርጨር አውራጃ ገዥ በመሆን ያገለገሉት ቀኝ አዝማች ግርማ በኢትዮጵያና በሶማሊያ ግንኙነት መንግሥታቱን በመምከርና መተግበር አለባቸው ስለሚሏቸው የአስተዳደር ሥርዓቶች ሲናገሩም ይታወቃሉ፡፡ ቀኝ አዝማች ግርማ የሶማሊያን ታሪክ በአራቱም አቅጣጫ አብጠርጥረው ያውቃሉ ከሚባሉ ጥቂት አንጋፋ ሰዎች አንዱ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡ 

ከሦስት ዓመት በፊት ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ለሶማሌ ላንድ ዕውቅና የመስጠት የህልውና ግዴታ አለባት፤›› በማለት የተናገሩት የሚታወስ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ የአልሸባብ ጥቃቶችን ለመመከት ጥሩ አማራጭ አድርገው ከሚያቀርቧቸው የመፍትሔ ሐሳቦች አንዱ የሆነው ለሶማሌ ላንድ እንደ አገር ዕውቅና መስጠትን ሲሆን፣ ምንም እንኳ የሞቃዲሾ ሶማሊያም ኢትዮጵያን በድንበር የሚያዋስን አገር ቢሆንም፣ የሶማሌ ላንድ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ካለው ወዳጅነት፣ ካለው የባህር በርና ሌሎች የኢኮኖሚ ጥቅሞች አኳያ መንግሥት ለሶማሌ ላንድ ዕውቅና መስጠት አለበት ብለው ያምኑ ነበር፡፡ 

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እንግሊዞች የኢትዮጵያን ጦር ለመርዳት መጥተው እንደነበር ለሪፖርተር ሲያስረዱ እንዳስታወሱት፣ በኦጋዴን ማረፊያቸውን አድርገው በቆዩ ጊዜ ሐርጌሳንም ይዘው ስለነበር፣ የኬንያ ሶማሌን ጨምሮ አምስቱን ሶማሌዎች በማዋሀድ አንድ አድርገው ለመግዛት አቅደው ነበር፡፡ ይህም ቢሆን ግን በ1941 ዓ.ም. ኦጋዴንን ለኢትዮጵያ ቢያስረክቡም፣ እንግሊዞች የኦጋዴንን ባላባቶች በመደለል ከኢትዮጵያ እንዲገነጠሉ ለማድረግ ሲሞክሩ እንደነበር ቀኝ አዝማች ግርማ አስታውሰዋል፡፡ 

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ከኦጋዴን ባሻገር ደገ ሃቡርንና ጅግጅጋን ከእንግሊዞች እጅ ቢረከብም፣ እግሊዞች ግን ጂቡቲን ጨምሮ የኬንያ ሶማሌን፣ ሶማሌ ላንድን፣ በወቅቱ በጣሊያን እጅ የነበረችውን ሞቃዲሾ ሶማሌን አንድ ላይ አዋህደው የመግዛት ሐሳባቸው አልተገታም ነበር፡፡ እንግሊዞች እንዳሰቡት አምስቱን ሶማሌዎች በማዋሀድ አንዲት የሶማሊያ አገር ለመመሥረት የነበራቸው ዕቅድ በኢትዮጵያ መንግሥት የወቅቱ ፖለቲካ እየጠነከረ መምጣት፣ በኦጋዴን በተነሳ ተቃውሞ ምክንያት ህልማቸው ሳይሳካ ቀርቷል የሚሉት ቀኝ አዝማች ግርማ፣ እንግሊዞች በእጃቸው ለነበሩት ሶማሌ ላንዶች ነፃነት ለመስጠት መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ ግን የሞቃዲሾ አዲሱ አስተዳደር የአምስቱን ሶማሌዎች ውህደት ዕውን ለማድረግ ሶማሌ ላንድን ወዲያውኑ ወደ ራሳቸው በመቀላቀል ወደ ኢትዮጵያም መምጣት ጀምረው ነበር፡፡ በዚህ አካሄዳቸውም የኢትዮጵያን ሶማሌ ለመገንጠል የመጀመሪያውን ወረራ በ1956 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላይ እንደፈጸሙ ቀኝ አዝማች ግርማ ለሪፖርተር በሰጡት ቃለ ምልልስ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ የሞቃዲሾ ሶማሊያ ከሶማሌ ላንድ መለየት የአምስቱን ሶማሌዎች ውህደትና የታላቋን ሶማሊያ መመሥረት ህልም ቢያከሽፍም፣ ሞቃዲሾ አሁንም ድረስ በሕገ መንግሥቷ ውስጥ ያስቀመጠችው በመሆኑ ይህ አቋም አሁንም ድረስ ለኢትዮጵያና ለሌሎች አገሮች ሥጋት እንደሆነ ቀኝ አዝማች ግርማ ዕምነታቸውን ገልጸው ነበር፡፡ 

‹‹ለጦርነት ስትራቴጂም ሆነ ለፖለቲካ ከሶማሌ ላንድ ጋር መተቃቀፉ ለኢትዮጵያ ትልቅ ጥቅም ይሰጣታል፤›› ያሉት ቀኝ አዝማች ግርማ፣ ለኢትዮጵያ ደኅንነትና ለወሰኗ መከበር ሶማሌ ላንድ ወሳኝ ሚና እንዳላት ገልጸው ነበር፡፡ ለሶማሌ ላንድ ዕውቅና መስጠት አፍሪካውያን ከቅኝ ገዦቻቸው በተረከቡት ወሰን ይፅኑ በሚለው ስምምነት መሠረትም ሶማሌ ላንድ ዕውቅና ማግኘት እንደሚገባት፣ ሞቃዲሾም በዚህ ስምምነት መሠረት ሶማሌ ላንድን ለግዛቷ አካልነት የምትጠይቅበት ምንም ዓይነት የታሪክ አብነት የላትም ብለዋል፡፡ 

ቀኝ አዝማች ግርማ ከወረዳ አስተዳዳሪነት እስከ ምክትል ገዥነት ከዚያም በዋና አገረ ገዥነት በተለያዩ ደረጃዎች የሶማሌ ግዛትንና የሐረር አውራጃዎችን ማስተዳደራቸው ይገራል፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ አራት ጊዜ የተለያየ ሹመት ተሰጥቷቸው አስቸጋሪውን የሶማሌ ክልል፣ ከአጎራባቾቹ ሶማሌ ላንድና ከሞቃዲሾ ሶማሊያ ጋር ተፋጠው እንዳስተዳደሩም የሕወይት ታሪካቸው ይዘክራል፡፡ 

የሁለት ወንዶችና የአንድ ሴት ልጅ አባት የነበሩት ቀኝ አዝማች ግርማ፣ በቀድሞው ሐረርጌ ክፍለ ሀገር በሐብሮ አውራጃ፣ ገለምሶ ከተማ ተወልደው አድገዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት 60ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸው በትዳር አብረዋቸው ከኖሩት ከወ/ሮ ጥሩ ወርቅ ሽፈራው ካፈሯቸው ልጆች በተጨማሪ የአሥር ልጆች አያትና የሁለት ልጆች ቅደመ አያት ለመሆን በቅተዋል፡፡ በሚያዝያ ወር ባለቤታቸው ከዚህ ዓለም ሲለዩ፣ ቀኝ አዝማች ግርማ ከወር በኋላ ተከትለዋቸዋል፡፡

ከመንግሥት አገልግሎት በጡረታ ከተገለሉ በኋላ በ1984 ዓ.ም. የሐረርጌ ተወላጆችና ነዋሪዎች መረዳጃ ማኅበርን በመመሥረትና በምክትል ሰብበሳቢነት በመምራት ተሳትፈዋል፡፡ 

 

 

የኢትዮጵያና የአሜሪካ ሹማምንት ስብሰባው ከተጠናቀቀ በኋላ

አምስተኛው የኢትዮ አሜሪካ የሁለትዮሽ የመከላከያ ምክር ቤት በአሜሪካ ባደረገው ስብሰባ፣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የደኅንነት ድጋፍና ትብብር መገምገሙ ተሰማ፡፡

ስብሰባው ባለፈው ሳምንት ውስጥ በዋሽንግተን ለሦስት ተከታታይ ቀናት የተካሄዱ መሆኑን ከአሜሪካ ኤምባሲ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ የኢትዮጵያን ልዑክ የመሩት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስ ናቸው፡፡ በአባልነት ከተሳተፉት መካከል ደግሞ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተሩ ብርጋዴር ጄኔራል ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይና ሌሎች የደኅንነት ኃላፊዎች ይገኙበታል፡፡

የአሜሪካን ልዑክ የወከሉት ደግሞ የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዴቪድ ሮድሪጌዝና በፔንታጎን የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ጸሐፊ ሚስ አማንዳ ዶሪ ናቸው፡፡ 

የስብሰባው አጀንዳ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያሉ የፀጥታ ጉዳዮችን መገምገምና የተናጠል መረጃዎችን መለዋወጥ እንደሆነ የኤምባሲው መረጃ ያመለክታል፡፡ በውይይቱ ወቅትም ትኩረት አግኘተው የነበሩት የየመን የደኅንነት ቀውስ፣ የሶማሊያና የደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገው የመከላከያና የደኅንነት ትብብር ግምገማ እንደተካሄደም ከመረጃው ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚሁ ወቅትም የአሜሪካ ጂኦ ስፓሻል የደኅንነት ኤጀንሲና የኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ መሠረታዊ መረጃዎችን ለመለዋወጥና ትብብር ለማድረግ ስምምነት ፈርመዋል፡፡

የጅኦ ስፓሻል መረጃዎች ማለት ከአየር ላይ ወይም ከሳተላይት በመሬት ላይ የሚገኙ መረጃዎችን መሰብሰብና መተንተን ነው፡፡ 

ጂኦ ስፓሻል መረጃዎች የማዕድን ሀብቶችን ለማወቅና ለግብርናና ለመሳሰሉት ጥቅም የሚሰጥ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል ይህንን እንዲሠራ ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ካርታ ሥራዎች ኤጀንሲ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲም የጂኦ ስፓሻል ኢንተለጀንስ ሥራ የማከናወን ኃላፊነት በአዋጅ ተሰጥቶታል፡፡ 

ይህም ማለት ከሳተላይት ወይም ከአየር ላይ በመሬት የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎችን ለደኅንነት ሲባል የመከታተልና የመተንተን ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ በሁለቱ ተቋማት መካከል የሚታየውን የኃላፊነት መጣረስ ለማስተካከልም የማሻሻያ ሥራ በመሥራት ላይ መሆኑን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡

 

የኮንትራት ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት

በአዲስ አበባ ከተማ በዋና ዋና ጐዳናዎች ላይ ከ132.6 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ መንገድ ጠቋሚ ምልክቶችን ለማኖር፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ከአንድ አገር በቀል ኩባንያ ጋር ተፈራረመ፡፡

ከ388 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ አምስት የመንገድ ግንባታዎች ለኮንትራክተሮች ተሰጡ፡፡ዓርብ ግንቦት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በባለሥልጣኑ ዋና መሥሪያ ቤት በተደረገው የኮንትራት ስምምነት ላይ እንደተገለጸው፣ በአዲስ አበባ በ52 መንገዶች ላይ የታቀዱትን መንገድ ጠቋሚ ምልክቶች ለመትከል ጨረታውን አሸንፎ ሥራውን የተረከበው፣ ዩኢ ኢንደስትሪያል የተባለው ኩባንያ ነው፡፡ በዚህ ጨረታ ላይ ሦስት ኩባንያዎች ተወዳዳሪ ቢሆኑም፣ ዩኢ ኢንደስትሪያል ያቀረበው ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑ አሸናፊ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከዩኢ ኢንደስትሪያል ጋር ተፎካካሪ በመሆን ቀርበው የነበሩት ጐልድስቶን ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ 145.2 ሚሊዮን ብር፣ ሲልክ ትሬዲንግ ኢንተርናሽናል ደግሞ 160.1 ሚሊዮን ብር አቅርበው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

የመንገድ ጠቋሚ ምልክቶቹን ለመትከል አሸናፊ የሆነው ኩባንያ ከ700 በላይ የሚሆኑ ምልክቶችን ተክሎ የሚያጠናቅቀው የኮንትራት ውሉ ከተፈረመበት ቀን አንስቶ በ270 ቀናት ውስጥ እንደሆነ በኮንትራት ስምምነቱ ላይ ተገልጿል፡፡ ምልክቶቹ አንፀባራቂ በሆነ አልሙኒየም የሚዘጋጁ ናቸው ተብሏል፡፡ ምልክቶቹ የመንገድ ስያሜዎችን፣ ርዝመትና ሌሎች መረጃዎችን የሚይዙ መሆኑን፣ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ምልክቶች የሚታዩት በቀለበት መንገዱ ላይ ብቻ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ 5.73 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸውን አምስት የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶችን ለማስገንባት ባለሥልጣኑ ከአራት ኮንትራክተሮች ጋር ስምምነት ፈጽሟል፡፡ በጥቅሉ ከ388.3 ሚሊዮን ብር በላይ ከሚወጣባቸው ከአምስቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ እንይ ኮንስትራክሽን የሁለቱን ፕሮጀክቶች ጨረታ አሸንፏል፡፡

እንይ ኮንስትራክሽን ያሸነፈው አንዱ መንገድ ከሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ እስከ ቅድስት ማርያም – ምኒልክ ሆስፒታል – ጃንሜዳ ድረስ የሚዘልቀው 1.7 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ ነው፡፡ ይኼንን መንገድ በ74.9 ሚሊዮን ብር እንደሚገነባው ታውቋል፡፡ እንይ ኮንስትራክሽን ከዚህ ፕሮጀክት በተጨማሪ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ግቢ ውስጥ የአስፋልትና የኮብልስቶን መንገድ ለመገንባት የወጣውን ጨረታም አሸንፎ ሁለት የኮንትራት ስምምነቶችን ፈጽሟል፡፡ 

ሁለተኛውን የኢሲኤ ፕሮጀክት ያሸነፈበት ዋጋ 27.7 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ የኢሲኤ የአስፋልትና የኮብልስቶን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ግማሽ ኪሎ ሜትር በአስፋልትና በኮብልስቶን ሲሆን፣  የመኪና ማቆሚያና የአስፋልት መንገድ ነው ተብሏል፡፡ የኢሲኤው ሥራ በ35 ቀናት መጠናቀቅ እንዳለበት ተገልጿል፡፡ 

ይህ ፕሮጀክት በፍጥነት ተሠርቶ እንዲያልቅ የተፈለገው ከሐምሌ 3 ቀን እስከ ሐምሌ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የፋይናንሲንግ ፎር ዴቨሎፕመንት ዓለም አቀፍ ጉባዔ ከመካሄዱ በፊት ለማድረስ እንደሆነ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡  

ከአቦ አደባባይ – ብሥራተ ገብርኤል ድረስ ያለውን 1.4 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ለማከናወን ጨረታውን በማሸነፍ ሥራውን የተረከበው አይኤፍኤች ኢንጂነሪንግ ነው፡፡ 30 ሜትር ስፋት ያለውን መንገድ ለመገንባት አይኤፍኤች አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 99.4 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ሥራውም በ365 ቀናት ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

የኮንትራት ስምምነቱ እንደሚያመለክተው ከሽሮሜዳ – ሐመረ ኖህ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያለውን 2.1 ኪሎ ሜትር መንገድ እንዲገነባ ጨረታውን ያሸነፈው የማነ ግርማይ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው ይህንን መንገድ ለመገንባት አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 187.02 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ መንገዱ ጠባብ በመሆኑ አሁን በ20 ሜትር ስፋት በአስፋልት ኮንክሪት ይገነባል፡፡ በስምምነቱ መሠረት መንገዱ 540 ቀናት ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

      

 

ሰበር ዜና፡- የቦንጋ ምርጫ በግጭት ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተላለፈ

በደቡብ ክልል በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ጊምቦ የምርጫ ክልል በግል ዕጩነት ተመዝግበው የሚወዳደሩት የዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች፣ ደኢሕዴን/ኢሕአዴግን ከወከሉት ዶ/ር መብራቱ ገብረ ማርያም ደጋፊዎች ጋር

በመጋጨታቸው ምክንያት በሥፍራው በመጪው እሑድ ግንቦት 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ይካሄድ የነበረው ጠቅላላ ምርጫ ለሌላ ጊዜ መተላለፉን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድሙ ጐላ ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡

‹‹የሁለቱ ዕጩዎች ደጋፊዎች ግጭት በመፍጠራቸው ምክንያት ምርጫውን በሰከነ ሁኔታ ለማካሄድ ይቻል ዘንድ፣ በዚያ ምርጫ ክልል የሚካሄደው ምርጫ ሌላ ጊዜ እንዲከናወን ተላልፏል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

አቶ ወንድሙ የተቋረጠው ምርጫ መቼ እንደሚካሄድ ግን አልገለጹም፡፡ 

 

በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃቱ በተደራጀ መንገድ መቀጠሉ ተሰማ

በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ የነበረው ጥቃት ጋብ ብሎ የነበረው ቢሆንም፣ በተደራጀ መንገድ እንደገና መጀመሩን በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ 

ለበርካታ አፍሪካውያን ሕይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት የሆነውን ‘ዜኖፎብያ’ (የዘረኝነት ጥቃት) የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ካወገዘ በኋላ፣ ለተወሰኑ ጊዜያት ተቀዛቅዞ የነበረው ጥቃት እንደገና አገርሽቶ 14 የኢትዮጵያውያን ሱቆች በቀናት ውስጥ እንደተቃጠሉ፣ በደርባንና በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በቃጠሎ የሰው ሕይወት ባይጠፋም አንድ ኢትዮጵያዊ አቅሉን ስቶ ሆስፒታል መግባቱን አቶ ኤፍሬም ጠቁመዋል፡፡ 

ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በደርባንና በአካባቢው ወይም ክዋዙሉ ናታል በሚባለው አውራጃ ከጥቂት ቀናት በፊት ለኢትዮጵያውያን የሱቅ ባለቤቶች የማስፈራሪያ ደብዳቤም እንደደረሳቸው ተናግረዋል፡፡ ለሪፖርተር በኢሜይል የደረሰው ደብዳቤ በአሥር ቀናት ውስጥ እስከ እሑድ ግንቦት 9 ቀን 2007 ዓ.ም. አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ፣ ያለበለዚያ ግን ሞት እንደሚጠብቃቸው የሚያትት ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በቅጽል ስማቸው ‹‹የኡምላዚ ነጋዴ ገዳዮች›› ተብለው የሚታወቁት እነዚህ ጥቃት ፈጻሚዎች የሞት ደብዳቤ መሆኑን በመንገር፣ ለኢትዮጵያዊያኑ እንደሰጧቸው አቶ ኤፍሬም አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ኤፍሬም ማብራሪያ፣ ጥቃቶቹ ድንገት ሳይሆን ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ ናቸው፡፡ ‹‹በብዙ ሚዲያዎች ያልተነገረው በመጋቢት ወር አካባቢ የደረሰው የአምስት ኢትዮጵያውያን ተቃጥሎ መሞትም የዚህ ማሳያ ነው፤›› ያሉት አቶ ኤፍሬም፣ የቅርብ ጊዜው ጥቃት በደቡብ አፍሪካ መንግሥትና በዓለም አቀፍ ጫና ለጥቂት ቀናትም ጋብ ብሎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ለዓመታት ለፍተው ያፈሩት ንብረታቸውን ያጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ከተሞች በመሸሽና ከዘመድ ተጠግተው በመኖር ላይ እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡ አንዳንዶች ያላቸውን ንብረት በመያዝ ሱቆቻቸው እንደገና ለመክፈት ጥረት በማድረግ ላይ ቢሆኑም፣ ብዙዎቹ ሱቆች (ኮንቴይነሮችን) ጨምሮ በደቡብ አፍሪካውያን መወረሳቸውንም ይገልጻሉ፡፡

በቀን ይደረግ የነበረው ተቀይሮ ጥቃት ፈጻሚዎች ሱቆችን በምሽት በእሳት እያቃጠሉ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ ግንቦት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. የአቶ ኤፍሬምን ጨምሮ አምስት ሱቆች መቃጠላቸውን፣ አቶ ኤፍሬም ግሮሠሪያቸው በመቃጠሉ ምክንያት 400 ሺሕ ብር ያህል እንዳጡ ተናግረዋል፡፡ ዘረፋዎችም እየጨመሩ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንን የሚኖሩበት ቦታ በመሄድ ማስፈራራቱም እንደቀጠለ ይናገራሉ፡፡ በሚያዝያ ወር አካባቢ በነበረው ጥቃት ምክንያት 15 ያህል ሰዎች በቁጥጥር ሥር ቢውሉም፣ በዋስትና መውጣታቸውን አቶ ኤፍሬም ይናገራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያውያን ለፖሊስ የከሰሱ ሲሆን፣ ጉዳያቸውም እየታየ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በቅርብ የተቃጠሉ ሱቆች 40 ያህል መሆናቸውን አሁን ደግሞ ከ50 መብለጣቸውን ያስረዳሉ፡፡ በሱቆች መቃጠልና በዘረፋው ምክንያት ከ800 እስከ 1,000 የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን እንደተጐዱም ያክላሉ፡፡ 

በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን 6,000 ያህል ይገመታሉ የሚሉት አቶ ኤፍሬም፣ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ ለብዙ ኢትዮጵያውያን ደም መፋሰስ ምክንያት ሊሆን እንደሚችሉም ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የነበረው ጥቃት ጋብ ያለ ቢመስልም ተዳፈነ እንጂ አልጠፋም፡፡ አሁንም እሳቱ እንደተቀጣጠለ ነው፡፡ በዚህ ከቀጠለም የኢትዮጵያውያን ደም እንደሚፈስ ምንም ጥርጥር የለውም፤›› ብለዋል፡፡ 

ኢትዮጵያዊያኑ ሥራ መጀመርና ከደቡብ አፍሪካውያን ጋር አብሮ በሰላም መሥራት እንደሚፈልጉ የሚናገሩት አቶ ኤፍሬም፣ ይህ ግን የማይቻል እንደሆነም ግምታቸውን ይናገራሉ፡፡ ቢሆንም ግን ሕይወታቸው አደጋ ውስጥ ሆኖም ብዙዎች ወደ ሥራ ለመመለስ በመጓጓት ላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ንብረቱን የተቀማና የተቃጠለበት ስደተኛ ብዙ ነገር ያጣ ቢሆንም፣ አሁንም ወደ ሱቁ መሄድን መርጧል፤›› በማለት ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዙሉን ንጉሥ ጉድዊል ዝዌልቲንና ቤተሰቦቻቸውን፣ እንዲሁም ሌሎች የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናትን በማናገር ጉዳዩን ለመፍታት እየጣረ ቢሆንም ሁኔታው ግን አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በሚያዝያው ጥቃት ምክንያት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 30 ያህል ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ ችሏል፡፡ በአጠቃላይ ከ100 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን የተመዘገቡ ሲሆን፣ የመጀመሪያዎቹ ተመላሾች በቅርቡ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ እንደሚሉት፣ ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደቡብ በአፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ችግር እንዲፈታ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ አሁን ደረሰ የተባለውን ጥቃት በተመለከተ ግን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ እንደሌለው አቶ ተወልደ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የመመለሱን ሥራ የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመረው ቢሆንም፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ግን ከሞት ጋር መጋፈጥን መምረጣቸው ታውቋል፡፡ መፍትሔው ምን ይሆን? ለሚለው አቶ ኤፍሬም ሲመልሱ፣ ‹‹የደቡብ አፍሪካ መንግሥትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በዚህ ጉዳይ ጣልቃ ገብተው ጠንካራ ዕርምጃ እንዲወሰድ መደረግ አለበት፤›› ብለዋል፡፡ 

አሁን ደረሰ የተባለውን ጥቃት አስመልክቶ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ሙሉጌታ ከልልን በስልክ ለማግኘት ጥረት ቢደረግም ሊሳካ አልተቻለም፡፡  

 

 

ዳሸን ባንክ የአዲሱ ፕሬዚዳንት ሹመት እንዲፀድቅለት ጥያቄ አቀረበ

ሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶችን ሰይሟል

የዳሸን ባንክ ሥራ አመራር ቦርድ በተሰናባቾቹ የዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ምትክ በተጠባባቂነት የተሰየሙትን አዲስ ተተኪዎች ሹመት እንዲያፀድቅለት፣ ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ ነው፡፡

የዳሸን ባንክ ቦርድ በፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን ለቀዋል የተባሉትን የቀድሞውን ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ወልደ ሥላሴን ተክተው የባንኩ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ያጫቸው አቶ አስፋው ዓለሙን ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክም ሹመቱን እንዲያፀድቅለት ቦርዱ ጥያቄውን አቅርቧል፡፡ ከአቶ ብርሃኑ ቀደም ብሎ የሥራ መልቀቂያ ባስገቡት በቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት በአቶ አበበ ተክሉ ምትክ ደግሞ አቶ ጌትነት ደሴ ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲሠሩ ቦርዱ የሰየማቸው መሆኑ ታውቋል፡፡ አቶ ጌትነት ይህንን ኃላፊነት እንዲይዙ ከመደረጉ በፊት የባንኩ ፕሬዚዳንት ልዩ አማካሪ በመሆን ሲያገለግሉ ነበር፡፡

ባንኩ ለሁሉም የባንኩ ከፍተኛ የኃላፊነት መደቦች በተጠባባቂነት የመደባቸው አዲሶቹ ተሿሚዎች በባንኩ ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች የቆዩ ናቸው ተብሏል፡፡ አዲሱ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው የባንኩ የኦፕሬሽን ማኔጅመንት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው፡፡ በአቶ አስፋው ተይዞ የነበረውን የኦፕሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንትነት ቦታ ደግሞ አቶ ኃይሉ ቡልቡላ  እንዲይዙት ተደርጓል፡፡ አቶ ኃይሉ ወደዚህ ኃላፊነት እንዲያድጉ እስከተደረበት ጊዜ ድረስ የባንኩ ቄራ ቅርንጫፍ ዋና ሥራ አስኪያጅ ነበሩ፡፡ አቶ ብርሃኑ መጋቢት 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ባስገቡት መልቀቂያ ደብዳቤ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል ቢባልም፣ ከኃላፊነት የለቀቁት በግዳጅ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የምክትላቸውም ስንብት በተመሳሳይ የሚታይ ነው እየተባለ ነው፡፡

የዳሸን ባንክ ማኔጅመንት መዋቅር አንድ ፕሬዚዳንትና አራት ምክትል ፕሬዚዳንቶች እንደሚኖሩት ያሳያል፡፡ ሆኖም ከአራቱ የምክትል ፕሬዚዳንቶች ቦታዎች የሦስቱ ኃላፊዎች ተሹመውላቸው ሲሠራባቸው ቆይቷል፡፡ አንድ የምክትል ፕሬዚዳንት (ስትራቴጂክ ፕላኒንግ) ቦታ ግን እስካሁን አልተሾመበትም፡፡ ይህ የስትራቴጂክ ፕላኒንግ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ቦታ አዲስ በመሆኑ ምደባ ሳይደረግ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ አስፈላጊነቱ ታምኖ የፀደቀ ስለሆነ አዲሱ የስትራቴጂክ ፕላኒንግ ምክትል ፕሬዚዳንት ይመደባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

ዳሸን ባንክ በአገሪቱ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የግል ባንኮች ውስጥ በሀብት ክምችቱ በመጀመርያ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነው፡፡ የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት ዓመታዊ ክንዋኔዎች የሚያሳዩ አኅዛዊ መረጃዎችም ከሌሎች የግል ባንኮች ብልጫ ያለው ትርፍ እንደሚያስመዘግብ ያሳያሉ፡፡ የ2007 ዓ.ም. የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸምን የሚያመለክተው የመጀመርያ ደረጃ ሪፖርት የባንኩ ሀብት 24 ቢሊዮን ብር መድረሱን ይጠቁማል፡፡ ይህም ከሌሎች የግል ባንኮች ብልጫ ያለው ሀብት እንዳለው የሚያሳይ ነው፡፡ ከዳሸን ባንክ ቀጥሎ የተቀመጠው አዋሽ ባንክ ሀብቱ 22.4 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

ላለፉት አሥር ተከታታይ ዓመታት ከፍተኛውን ትርፍ እያስመዘገበ የዘለቀው ዳሸን ባንክ የ2007 ዓ.ም. የአሥር ወራት ክንውኑ የሚያሳየው፣ አሁንም ከሌሎች ባንኮች ብልጫ ያለው ትርፍ ማግኘቱን ነው፡፡ 

ባንኩ በአሥር ወራት ከግብር በፊት ያገኘው ጠቅላላ ትርፍ 760 ሚሊዮን ብር መሆኑን መረጃው ያመለክታል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ባንኩ ከ980 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉ ይታወሳል፡፡ ዳሸን ባንክ ከ720 በላይ ባለአክሲዮኖችን ያሉት ሲሆን፣ እስካለፈው ወር መጨረሻ ድረስ የተከፈለ ካፒታሉ 1.23 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይኼም ከአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ቀጥሎ ሁለተኛው ከፍተኛ የተከፈለ ካፒታል ነው፡፡ የአዋሽ ባንክ የተከፈለ ካፒታል 1.48 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

ዳሸን ባንክ ከምሥረታው ጀምሮ የነበሩት አቶ ተከተል ሀብተ ጊዮርጊስ የመጀመርያው ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ቀጥለውም አቶ ልዑል ሰገድ ተፈሪ የተሾሙ ሲሆን፣ እሳቸውን የተኩት ደግሞ አቶ ብርሃኑ ወልደ ሥላሴ ናቸው፡፡ አቶ ብርሃኑ በቅርቡ ከሥልጣናቸው ሲገለሉ፣ አሁን ለፕሬዚዳንትነት አቶ አስፋው ታጭተዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ሹመቱን ካፀደቀው አቶ አስፋው አራተኛው የባንኩ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

ከየመን 2,524 ዜጎች መመለሳቸውን መንግሥት አስታወቀ

የመን ውስጥ በተፈጠረው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት አደጋ ላይ የወደቁ ኢትዮጵያውያን ምን ያህል እንደሆኑ በውል ባይታወቅም፣ ከአራት ሺሕ በላይ ስደተኞች ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው በአስቸኳይ ለመመለስ ሰንዓ በሚገኘው ኤምባሲ መመዝገባቸው ተገለጸ፡፡

ሰኞ ግንቦት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. የገቡትን ጨምሮ 2,524 ዜጎች ወደ አገራቸው መመለስ መቻሉን መንግሥት አስታወቀ፡፡ 

በዕለቱ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ይገባሉ ተብሎ የተጠበቁት የየመን ተመላሾች ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማሪፊያ ሲደርሱ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ ደከምከም ያሉና ሕፃናት የያዙ ተመላሾች ይበዙ ነበር፡፡

በዕለቱ ወደ አገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 260 መሆኑን፣ ቀደም ሲል የገቡትን ጨምሮ እስካሁን 2,524 ስደተኞች ኢትዮጵያ መግባታቸውን፣ ዶ/ር ቴድሮስ በሥፍራው ለተገኙት ጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ 

የየመን መንግሥትን በምትደግፈው ሳዑዲ ዓረቢያና በኢራን በሚደገፉት የሁቲ አማፂያን መካከል በተነሳው የእርስ በርስ ጦርነት በተለይ የውጭ አገር ስደተኞች አደጋ ላይ ወድቀዋል፡፡ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ጥቃት በመፈጸሙ ምክንያት በኢትዮጵያውያኑ ዘንድ ፍርኃትንና ድንጋጤን ፈጥሮ እንደነበር ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተመላሾች ተናግረዋል፡፡ ተመላሾቹ እንደሚሉት፣ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎችና በጠረፍ አካባቢዎች የሚገኙ በመሆናቸው ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው፡፡ 

መንግሥት በቀን ከ200 እስከ 400 ስደተኞች ወደ አገራቸው እየመለሰ መሆኑን፣ እስካሁን የተመዘገቡት ከ4,000 በላይ ዜጎች በሚቀጥሉት አራትና አምስት ቀናት ውስጥ ጠቅልለው ወደ አገራቸው እንደሚገቡ ዶ/ር ቴድሮስ አስረድተዋል፡፡ 

ሚኒስትሩ ከጋዜጠኞች ጋር የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ ተመላሾች ፊታቸውን ሲያዞሩ ከተመላሾቹ አንዱን ወጣት፣ ‹‹ተቸገራችሁ አይደል? ዘገየንባችሁ? ኤርፖርቱ እኮ ጥቃት ስለደረሰበት የእሱን ዕድሳት እየጠበቅን ነበር፡፡ ነገር ግን አልተሳካም፤›› ሲሉት፣ ወጣቱም መልሶ፣ ‹‹ዶ/ር በጣም ነው የምናመሰግነው፡፡ በተቻላችሁ መጠን ደርሳችሁልናል፡፡ ረድታችሁናል፤›› በማለት መልሶላቸዋል፡፡ ሌሎችም ተመሳሳይ አስተያየት ነበራቸው፡፡ 

በየመን እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በሊቢያ በኢትዮጵያን ላይ የተፈጸመው ዓይነት ጉዳት እንዳለ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹እስካሁን ይህ ነው የሚባል ጉዳት የደረሰበት ሰው የለም፡፡ ለደከሙትና ለታመሙት ቅድሚያ ሰጥተን ነው እያመጣን ያለነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 

ከተመላሾች መካከል አንዱ የሆነው ወጣት መኮንን ገበየሁ ሁኔታውን በተመለከተ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ በሶማሊያ በኩል በባህር አድርጎ ነበር ወደ የመን የገባው፡፡ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት እምብዛም አስቸጋሪ ነገር አልገጠመውም፡፡ ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ግን፣ ‹‹ወደ አገሬ የምገባበት ቀን ናፍቆኝ ነበር፡፡ በጣም ነው የሚያስፈራው፤›› ብሏል፡፡ መመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ኤምባሲ ሄደው መመዝገብ እንዳለባቸው የሰማው መኮንን፣ ተቀጥሮ ይሠራው የነበረውን አስተናጋጅነት ጥሎ መምጣቱን ይናገራል፡፡ እሱ ይኖር የነበረው በዋና ከተማ ሰንዓ ነበር፡፡ በጣም የሚያስጨንቀው በጠረፍ አካባቢዎች ስላሉት ኢትዮጵያውያን መሆኑንም ተናግሯል፡፡ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ሠራተኞች የተደረገለትን ትብብርም አመስግኗል፡፡ 

ፈይሰል አህመድም ከተመላሾች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት በጂቡቲ በኩል ነበር ወደ የመን የተሻገረው፡፡ ያለፈበትን አሰቃቂ ጉዞ ማስታወስ አይፈልግም፡፡ ‹‹ስደት ሲባል አስቸጋሪ ነው፡፡ የእኛ ዓይነቱ ስደት ሕገወጥ ነው፡፡ ሕጋዊ የሚባል ስደት የለም፤›› በማለት በስደት ሆኖ የደረሰበት የከፋ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ቀደም ሲል የመን እንደገባ ገጠር በመሄድ በአንድ እርሻ ውስጥ ተቀጥሮ ያርስ እንደነበር ይናገራል፡፡ ቀጥሎም እርሻውን ትቶ ወደ ከተማ በመግባት ተቀጥሮ የፅዳት ሥራ ይሠራ ነበር፡፡ ‹‹አሁን በጣም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ መብራት የለም፡፡ ውኃ የለም፡፡ ምግብ የምናበስለው በጋዝ ነበር፡፡ ጋዝ ደግሞ አይገኝም፡፡ ችግር ላይ ወድቀን ነበር፤›› ብሏል፡፡ 

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ ስደተኞች የከፋ ችግር እንደሚገጥማቸው የገለጸው ፈይሰል፣ በኢትዮጵያዊያን ላይ በተለይ የሚደርስ አደጋ እንዳለ ከሪፖርተር ጥያቄ ቀርቦለት ነበር፡፡ ፈይሰል፣ ‹‹ሁለቱም ወገኖች አንደኛው የሌላኛው ደጋፊዎች ናችሁ እያሉ ያስፈራሩናል፡፡ ነገር ግን በተለየ ጥቃት አልፈጸሙብንም፡፡ ነገር ግን ጦርነቱ የከፋ ነው፡፡ እላይህ ላይ ቤት ይፈርሳል፤›› ብሏል፡፡ 

የፈይሰል ሥጋት ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን በጠረፍ አካባቢዎች ስለሚሠሩና ጦርነቱም የከፋው እዚያ ስለሆነ ጉዳት እየደረሰባቸው ሊሆን ይችላል የሚል ነው፡፡ ‹‹እንዳንድ ጊዜም አልቃይዳ ናችሁ ይሉናል፤›› ብሏል፡፡ ‹‹እባክህን የተቀሩት ኢትዮጵያውያንን እንዳይገድሏቸው መንግሥት እንዲረዳቸው ንገርልን፤›› በማለት አስተያየቱን አጠቃሏል፡፡ 

በተያያዘ ዜና ከሊቢያ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የማስወጣት ሥራ ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን፣ በቅርቡ በሁለቱም አካባቢዎች (በትሪፖሊና በቤንጋዚ) የሚገኙት   100 ስደተኞችን ለማስመለስ መንግሥት በዝግጅት ላይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

 

አክጉን ግሩፕ የተባለው የቱርክ ኩባንያ በአሥር ቢሊዮን ዶላር በሰንዳፋ አካባቢ ለመገንባት ላቀደው ኢትዮ ተርኪሽ የኢንዱስትሪ ዞን ያስጠናውን የአካባቢና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ፣ የአካባቢና የደን ሚኒስቴር ውድቅ አደረገው፡፡

ሚኒስቴሩ ይህንን የተፅዕኖ ጥናት ውድቅ ማድረጉንም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡

ሚኒስትሩ አቶ በለጠ ታፈረ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት፣ ኩባንያው ያቀረበው ጥናት ግልጽነት የጐደለው ነው ብለዋል፡፡ 

አክጉን ግሩፕ ሰንዳፋ አካባቢ ለማስገንባት ከኦሮሚያ ክልል 100 ሔክታር መሬት ተረክቦ የተወሰኑ እንቅስቃሴዎችን ያደረገ ቢሆንም፣ ግንባታ እንዳይጀምር በመንግሥት ታግዶ ቆይቷል፡፡

ይህ የሆነበት ምክንያት የኢንዱስትሪ ዞኑ ይዞታ ከለገዳዲ የውኃ ማጣሪያ ያለው ርቀት አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ብቻ ያለው በመሆኑ፣ በአዲስ አበባ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ላይ ውኃውን በመበከል ችግር ይፈጥራል የሚል ሥጋት ነው፡፡

ይሁን እንጂ ኩባንያው ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሥራዎችን እንደሚያከናውን በመስከረም ወር 2007 ዓ.ም. ለሪፖርተር ገልጾ ነበር፡፡ የአክጉን ግሩፕ የቦርድ አባል የሆኑት ሚስተር ዩኑስ አክጉን በወቅቱ የአካባቢ ተፅዕኖ ማስተካከያ ዕቅድ መንደፋቸውን ጠቁመው ነበር፡፡ ይህንንም ለማድረግ የተፅዕኖ መቋቋሚያ የአካባቢና የማኅበራዊ ተፅዕኖ ጥናት እንደሚያካሂዱ ገልጸው ነበር፡፡ 

የአካባቢና የደን ሚኒስትሩ ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት ግን የቀረበው የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ መሠረታዊነት ግልጽነት የጐደለው፣ አገሪቱ የምትጠቀምበትን አሠራር ያላሟላና ባለድርሻ አካላትን ያላሳተፈ በመሆኑ ውድቅ ተደርጓል፣ በመሆኑም ኩባንያው እንዲያስተካክል ተነግሮታል ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዶ/ር አርከበ እቁባይ አክጉን ግሩፕ ወደ ሐዋሳ ወይም ድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ዞን እንዲሸጋገር ሐሳብ ማቅረባቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ኩባንያው ግን በአዲስ አበባ ዙሪያ እንዲሆንለት ጥያቄ እያቀረበ ይገኛል፡፡