ተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዛቢዎቻችን ተባረዋል አሉ

– ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅሬታ አልደረሰኝም ብሏል
በአምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተሳታፊ የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫውን እንዲታዘቡ ያሰማሯቸው ግለሰቦች በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት መገለላቸውን ገለጹ፡፡ የክልል የምርጫ ኃላፊዎች ክልከላው የተከናወነው ሕጉን መሠረት አድርጎ ነው ያሉ ሲሆን፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግን ከየትኛውም ፓርቲ ቅሬታ አልደረሰኝም ብሏል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በተመሳሳይ በባሌ፣ በየም፣ በሲዳማና በደብረ ማርቆስ ያሰማራኋቸው ታዛቢዎች ተባረዋል ብሏል፡፡ በሐዋሳ ከተማ ከተሰማሩ ታዛቢዎች ሦስት አራተኛው እንዲሁ ለእስር ተዳርገዋል ያለው ሰማያዊ፣ አንዳንዳቹ በሚሊሻ ተከበው በቤታቸው በቁም እስር ላይ እንደሚገኙ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡
መድረክ በበኩሉ በሐዋሳ ከተሰማሩ የፓርቲው ታዛቢዎች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት መታሰራቸውን በአካባቢው መድረክን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት ዶ/ር አየለ አሊቶ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ መድረክ በተመሳሳይ በመቐለ ያሰማራቸው ታዛቢዎች በተለያዩ ጫናዎች ራሳቸውን ከታዛቢነት ማግለላቸውን ገልጿል፡፡
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲም እንዲሁ በሐዋሳ ያሰማራቸው ታዛቢዎች መባረራቸውን ገልጿል፡፡ የአካባቢው የምርጫ ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዱካሞ የሌላ ፓርቲ የታዛቢነት መታወቂያ ይዘው በመገኘታቸው ጉዳዩ እየተጣራ እንደሆነ ገልጸው፣ ግለሰቦቹ እንደሚፈቱ አስታውቀዋል፡፡
በባህር ዳር ከተማ ኢዴፓ ያሰማራቸው ከ60 በላይ ታዛቢዎች ቢኖሩትም፣ ድምፅ በመስጪያው ቀን ከ155 የምርጫ ጣቢያዎች በጣት የሚቆጠሩ ነው የተገኙት፡፡ ይህን በተመለከተ ሻምበል ያየህራድ ዘለቀ የባህር ዳር ከተማ ኢዴፓ አመራርና የተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ ለሪፖርተር፣ ‹‹አብዛኛዎቹ የፓርቲው ታዛቢዎች በምርጫ ጣቢያው ያልተገኙበት ምክንያት አላውቅም ፈርተው ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም በሁለት ምርጫ ጣቢያዎች ግን መታወቂያ ላይ ፎቶ አለጠፋችሁም ተብለው ከመግባት ተከልክለዋል፤›› ብለዋል፡፡ በባህር ዳር ምርጫ ክልል 115 የምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉ ምርጫ ቦርድ ቢያሳውቅም፣ ኢዴፓ በደብዳቤ የተገለጹለት 111 ብቻ መሆናቸውን ሻምበል ያየህራድ ገልጸዋል፡፡
መኢአድም በሰሜን ሸዋ ዞን በደረሰባቸው ወከባ ታዛቢዎች ማሰማራት እንዳልቻለ የዞኑ የመኢአድ ምርጫ አስተባባሪ ሻምበል ባሻ አበራ በቀለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከአንድም ፓርቲ በጉዳዩ ላይ ቅሬታ እንዳልደረሰው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫ ታዛቢዎቻቸውን እንዲያሳውቁ በሰጠናቸው ጊዜ ብዙ ፓርቲዎች አልተጠቀሙም፡፡ በመሆኑም ጊዜውን አራዝመን ነበር፡፡ ከተራዘመም በኋላ ያላሳወቁ አሉ፡፡ በሕጉ እንዲያሳውቁ የሚያስገድድ ነገር ስለሌለ ዝም ብለናል፤›› ያሉት አቶ ደምሰው፣ ምናልባትም ይህን መታወቂያ ያልያዙ ሰዎች በታዛቢነት ቀርበው ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ቅሬታዎች የሚመጡት ከታችኛው እርከን ወደ ላይ በመሆኑ፣ ከክልል የምርጫ ኃላፊዎች ሲያልፍ ብቻ ወደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደሚመጣ አስገንዝበዋል፡፡