የምርጫ 2007 ዜናዎች

እሑድ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በመላ አገሪቱ ድምፅ የመስጠት ሥነ ሥርዓት ተጀምሯል፡፡ ሪፖርተር ከአዲስ አበባ ከተማና ከተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ዘገባዎችን ያስተላልፋል፡፡ በዚህም መሠረት አንባቢያን ድረ ገጹን እንዲጎበኙ እናሳስባለን፡፡

ደቡብ ክልል

በደቡብ ክልል በወላይታ ዞን በቦሎሶ ሶሬ ምርጫ ክልል 01 ጠቅላላ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ድምፃቸውን ይሰጣሉ ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን፣ መራጮች ቤተ ክርስቲያን በመሄዳቸው ምክንያት የመራጮች ቁጥር ዝቅተኛ እንደነበር ሪፖርተራችን ዘግቧል፡፡ በዚህ ምርጫ ከመድረክ በስተቀር ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች ይወዳደራሉ፡፡ በወላይታ ዞን ሐረካት 3 የምርጫ ጣቢያ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ደኢሕዴግ/ኢሕአዴግን ወክለው ይወዳደራሉ፡፡ በእዚህ ምርጫ ክልል መራጮች በብዛት ታይተዋል፡፡ የመድረኩ ፕሮፌሰር በየነና የደኢሕዴግ/ኢሕአዴግ አቶ ዮሴፍ ዳኢሞ የሚወዳደሩበት የሐዲያ ዞን ማካማ 02 ምርጫ ክልል መራጮች በብዛት ወጥተው እየመረጡ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታዛቢዎችም አሉ፡፡

አዲስ አበባ

ምርጫ ክልል 17

የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ በቀለ ከኢሕአዴግ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ የኢዴፓ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ተሾመ እንዲሁም የኢራፓ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮን ያገናኘው የምርጫ ክልል 17 ምርጫ በከፍተኛ ተሳትፎ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ባያቸው የምርጫ ጣቢያዎች ቺቺንያ አካባቢ ከሚገኝ አንድ ጣቢያ በስተቀር ረጃጅም ሠልፎች ታይተዋል፡፡ 

ይህ ነው የሚባሉ ግድፈቶች ባይስተዋሉም በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዛቢዎችን አላስቀመጡም፡፡ በተጨማሪም የምርጫ ሒደቱ ላይ ማብራሪያ እየተሰጠም ጭምር ምን ማድረግ እንዳለባቸው ምንም ዓይነት ግንዛቤ የሌላቸው መራጮችም ታይተዋል፡፡