የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት ድጎማ  እንዲያደርግለት ያዘጋጀውን ፕሮፖዛል፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ሊያቀርብ ነው፡፡

ታኅሳስ 26 ቀን 2006 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትሩና በኢሠማኮ አመራሮች መካከል በተደረገ የምክክር መድረክ ላይ፣ ኢሠማኮ ለመንግሥት ይደረግልኝ ብሎ ያቀረበውን ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቃል አወንታዊ ምላሽ ሰጥተው እንደነበር ይታወሳል፡፡

 

በዚሁ ምላሽ መሠረት ኢሠማኮ የመንግሥትን ድጎማ እሻባቸዋለሁ ያላቸውን ጉዳዮች በዝርዝርና በፕሮፖዛል መልክ አዘጋጅቷል፡፡ ያስፈልገኛል ያለውንም የገንዘብ መጠን በመጥቀስ  ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አቅርቦ ነበር፡፡

ይህንን ፕሮፖዛል ያቀረበው ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ቢሆንም፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ምንም ዓይነት ምላሽ ሳይሰጠው ቆይቶ ነበር፡፡ ቆይቶም ግን ኢሠማኮ ለሚኒስቴሩ ያቀረበው ጥያቄ መቅረብ ያለበት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ነው የሚል ምላሽ ስለተሰጠው፣ ‹‹ድጎማ ይሰጠኝ›› የሚለውን ጥያቄውን በድጋሚ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለማቅረብ እየተዘጋጀ መሆኑን፣ የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹መንግሥት ድጎማ እንዲያደርግልን የፈለግነው ለግንዛቤ ማስጨበጫና ለአቅም ግንባታ ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ የሚውል ነው፤›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ይህንንም በፕሮፖዛላቸው ላይ ማስፈራቸውን ተናግረዋል፡፡

በተከታታይ በየዓመቱ የአሠሪና ሠራተኞችን ግንኙነት በሚመለከት የኢንዱስትሪ ሰላምን ለመፍጠር በሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት፣ ሁሉም ወገን መብትና ግዴታውን እንዲወጣ ለማድረግ ለሚያስፈልገው ወጪ መንግሥት ድጎማ እንዲያደርግ በኢሠማኮ ተጠይቋል፡፡ ሥልጠናዎቹና የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞቹ በአሠሪና በሠራተኛ ዘንድ አሉ የሚባሉትን ችግሮች ለመፍታት፣ ሠራተኛውና አሠሪውን የሚመለከቱ ሕጎች ምን እንደሚመስሉ ለማሳየትና በዚሁ መሠረት ተፈጻሚ እንዲሆን ለማስቻል ጭምር ነው፡፡ ድጎማው ለተፈለገው ዓላማ ብቻ የሚውል ነው ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ከመንግሥት የሚገኘው የገንዘብ ድጎማ ለኢሠማኮ ውስጣዊ በጀት ወይም ለአስተዳደር ሥራ እንደማይውልና ደመወዝን ለመሰሉ ወጪዎች ማስፈጸሚያም እንደማይጠቀምበት ገልጸዋል፡፡

ኢሠማኮ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተመራው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር አድርጎት በነበረው የምክክር መድረክ ላይ፣ ሊፈጸሙልኝ ይገባሉ ብሎ ካቀረባቸው ከ30 በላይ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ ‹‹መንግሥት ኢሠማኮን ይደጉም›› የሚል ሲሆን፣ መንግሥትም ኢሠማኮን ለመደገፍ ፈቃደኝነቱን አሳይቷል፡፡

በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ድጎማ የሚለው ቃል ጸያፍ ነው…በድጎማ ያደገ አገርና ድርጅት የለም፡፡ ሥራ ለመሥራት የገበያ ክፍተት ስላለ እንደ ልማታዊ መንግሥት ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አጋር ይሆናል ተብሎ እስከታመነ ድረስ በኢሠማኮ የተጠየቀውን እንሰጣለን፤›› ብለው፣ ‹‹ይህ ድጎማ ግን ለሽርሽር የምትጠቀሙበት አይደለም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሠራተኞችን ማስጨብጨቡ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ ሊፈቱልን ይገባል ተብለው ከኢሠማኮ ከቀረቡት ጥያቄዎች ውስጥ አብዛኞዎቹ አዎንታዊ ምላሽ እንዳገኙ የተነገረ ሲሆን፣ ከቀረጥ ነፃ ተሽከርካሪዎችም እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ አሠሪዎች ለሠራተኞቻቸው የሚያቀርቡት ምግብ ታክስ እንዳይደረግ የሚለውም ጥያቄያቸው አወንታዊ ምላሽ እንዳገኘም ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

 

በአሁኑ ወቅት 85 በመቶ የተጠናቀቀው ከአዲስ አበባ-ጂቡቲ ድረስ እየተገነባ ያለው የባቡር መስመር በሚቀጥለው ዓመት አገልግሎት ይስጣል ተባለ፡፡

በሎስጂቲክስ ችግሮች ላይ መሠረታዊ ለውጥ ከማምጣቱም በላይ፣ ከውጭ ለሚገባ ከፍተኛ መጠን ያለው ማዳበሪያ ትራንስፖርት ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ግብዓት አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ በየነ ገብረ ሥላሴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባቡሩ ሥራ የሚጀምር ከሆነ ማዳበሪያው ታሽጎ ወይም በብትን ይግባ የሚለው ይታያል፡፡ ነገር ግን ባቡሩ ሥራ ከጀመረ በብትን ማስገባቱ አዋጭ ይሆናል ሲሉ አቶ በየነ አስረድተዋል፡፡

ለሚቀጥለው ምርት ዘመን የሚፈለገውን ማዳበሪያ መጠን ለማወቅ ግብርና ሚኒስቴር ቅኝት እያደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ግብርና ሚኒስቴር ዘርፉ የሚፈለገውን የማዳበሪያ መጠንና ዓይነት ከክልሎች እየሰበሰበ ሲሆን፣ በይደር የሚቆየውን ማዳበሪያ መጠን በመገምገም ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

የአገሪቱ ግብርና ዘርፍ የሚፈለገውን የማዳበሪያ መጠን እንደታወቀ፣ የግብርና ግብዓት አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ በጥቅምት 2008 ዓ.ም. ጨረታ አውጥቶ ግዥ እንደሚፈጽም ተጠቁሟል፡፡

ለ2007 ዓ.ም. ምርት ዘመን 894 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ዩርያና ኤንፒኤስ ማዳበሪያዎች ግዥ ተፈጽሞ፣ አብዛኛው አገር ውስጥ መግባቱ ይታወሳል፡፡ አገር ውስጥ የገባው ማዳበሪያ በኩንታል 1,200 ብር አካባቢ በመሸጥ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

ነገር ግን በ2007 ዓ.ም. ግዥ ከተፈጸመው ማዳበሪያ ውስጥ አንድ መርከብ ማዳበሪያ በአሁኑ ወቅት በጂቡቲ ወደብ በመራገፍ ላይ ይገኛል፡፡ አቶ በየነ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ግብርና ሚኒስቴር አገሪቱ የምትፈልገውን የማዳበሪያ መጠንና ዓይነት እንዳሳወቃቸው ግዥ ለመፈጸም ወደ ገበያ ይወጣሉ፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ግብርና ግብዓት ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ላቀው በበኩላቸው፣ ክልሎች የማዳበሪያ ፍላጎታቸውን በነሐሴ ወር እንደሚያሳውቁና በጥቅምት ወር ወደ ግዥ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በዚህ የምርት ዘመን ግዥ የተፈጸመው 894 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ሲሆን፣ አንዱ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ከ412 ዶላር እስከ 480 ዶላር ግዥ ተፈጽሟል፡፡ በምርት ዘመኑ ለማዳበሪያ ዘርፍ አስቸጋሪ ጉዳይ የነበረው የትራንስፖርት ጉዳይ ሲሆን፣ ይህም የሆነው ማዳበሪያን በዝቅተኛ ዋጋ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ሲባል በትራንስፖርት ሒሳብ ላይ ተመን በመውጣቱ ነበር፡፡

ይህም የትራንስፖርት ድርጅቶችን ትኩረት መሳብ ባለመቻሉና በወቅቱ በርካታ ዕቃዎች ጂቡቲ ወደብ ደርሰው የነበረ በመሆኑ፣ ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ ለማጓጓዝ ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡

አቶ በየነ እንዳሉት፣ በሚቀጥለው ዓመት ይህንን ችግር ለመፍታት ከወዲሁ ከባህር ትራንስፖርትና ከሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ጋር ንግግር ይጀመራል፡፡ ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ድረስ በሚገነባው የባቡር መስመር ችግሩ ሊቀረፍ እንደሚችል አቶ በየነ ያላቸውን እምነት ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የዓለም አቀፍ የማዳበሪያ ዋጋም በዚህ የምርት ዘመን ከተገዛበት ዋጋ ቅናሽ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የሚናገሩት አቶ በየነ፣ በሚቀጥለው ምርት ዘመን ለአርሶ አደሩ የሚቀርበው ማዳበሪያ የዋጋ ቅናሽ ሊኖረው ይችላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚፈልገው ማዳበሪያ መጠን እያደገ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ አፈሩ የሚፈልገው ማዳበሪያ ዓይነትም ተለይቶ እንደታወቀ ተገልጿል፡፡ በግብርና ዘርፍ ውስጥ ብዙም  የማይታወቀው ኤንፒኤስ ማዳበሪያ፣ የአገሪቱን ግብርና የተቀላቀለ በመሆኑ በአገሪቱ አምስት ማዳበሪያ ፋብሪካዎችም አፈሩ የሚፈልገውን ማዳበሪያ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

 

ኢሕአዴግና አጋር ድርጅቶቹ ምርጫውን ሙሉ በሙሉ ማሸነፋቸውን ምርጫ ቦርድ አረጋገጠ

‹‹መድረክና ሰማያዊ ፓርቲዎች ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነዋል›› ፕሮፌሰር መርጋ በቃና

-የጊምቦ ገዋታ የምርጫ ውጤት አልተካተተም

በመላው ኢትዮጵያ (ከጊምቦ ገዋታ ምርጫ ጣቢያ በስተቀር) ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የተካሄደውን የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች አገራዊ ምርጫ ኢሕአዴግና አጋር ድርጅቶቹ ሙሉ በሙሉ ማሸነፋቸውን፣

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ይፋ አደረገ፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና እንደገለጹት፣ ቦርዱ በአዋጅ ቁጥር 532/99 አንቀጽ 77 መሠረት አጠቃላይ የምርጫውን ውጤት ይፋ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም ለአምስተኛው አገራዊ ምርጫ 36,851,461 ሕዝብ በመራጭነት ተመዝግቦ፣ 34,351,444 ሕዝብ ድምፁን ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግና አጋር ድርጅቶቹ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 334 ወንዶችና 212 ሴቶች በዕጩነት አቅርበው አሸናፊ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ምክር ቤቱ ካለው 547 መቀመጫዎች 546ቱን ሲያሸንፉ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት ብቸኛው የግል የፓርላማ አባል የነበሩት ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስና የኢሕአዴግ ዕጩ ዶ/ር መብራቱ ገብረ ማርያም (የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት) የሚወዳደሩበት የቦንጋ ጊምቦ ገዋታ ምርጫ ክልል ውጤት  ይፋ ባለመደረጉ፣ ከተገለጸው ውጤት ጋር አለመካተቱን ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡

ለክልል ምክር ቤቶች ኢሕአዴግና አጋሮቹ፣ 1187 ወንዶችና 800 ሴቶች በድምሩ 1,987 አባላት በዕጩነት አቅርበው ሙሉ በሙሉ ማሸነፋቸውን ፕሮፌሰሩ አክለዋል፡፡

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 52 የፖለቲካና ዘጠኝ የግል ዕጩዎች ለ547 መቀመጫዎች የተወዳደሩ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ በአምስት ክልሎች ማለትም በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በሐረሪ፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች 27,347,332 ድምፅ በማግኘት 500 መቀመጫዎችን ያለምንም ተቀናቃኝ ማሸነፉን ፕሮፌሰሩ አብራርተዋል፡፡

ለሁለቱ ምክር ቤቶች 40,536,607 የድምፅ መስጫ ወረቀቶች መቅረቡን የገለጹት ፕሮፌሰሩ፣ 1,130,390 ድምፅ መስጫ ወረቀቶች ዋጋ አልባ መሆናቸውንና 520,379 ድምፅ መስጫዎች መበላሸታቸውን ተናግረዋል፡፡

በምርጫ ውድድሩ መድረክና ሰማያዊ ፓርቲዎች ሁለተኛና ሦስተኛ መውጣታቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር መርጋ፣ የምክር ቤቶቹን መቀመጫዎች የሚያስገኝ ድምፅ ባለማግኘታቸው ተሸናፊ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ቦርዱ የሕዝብ ድምፅ ማስከበር እንዳለበት የተናገሩት ሰብሳቢው፣ ይኽንኑ ተግባራዊ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ በደቡብ ክልል የጊምቦ ገዋታ ምርጫ ክልል የምርጫ ውጤት ለቦርዱ መድረሱን ጠቁመው፣ ቦርዱ ውጤቱን ባለማፅደቁ በዕለቱ በገለጹት ውጤት ላይ አለመካተቱን፣ ነገር ግን  በቅርቡ ፀድቆ በቦርዱ ድረ ገጽ ይፋ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

ሰኔ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በደቡብ ክልል በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ በጊምቦ ገዋታ ምርጫ ክልል በተካሄደው ምርጫ፣ የኢሕአዴግ ዕጩ ዶ/ር መብራቱ ገብረ ማርያም የግል ዕጩውን ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስን በሰፊ ውጤት ማሸነፋቸውን ከምርጫ ጣቢያዎቹ ከተገኘው መረጃ መረጋገጡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

 

የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስ አዲስ አበባ እስከ አዳማ የተገነባው የፍጥነት መንገድ አካል የሆኑ ሁለት መንገዶች በከፊል ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሊሆኑ ነው፡፡

ከአቃቂ ለቡና ከአቃቂ የረር በመገንባት ላይ ያሉት መንገዶች አንደኛው መስመራቸው ለትራፊክ ክፍት እንዲሆን፣ ግንባታቸው በፍጥነት እንዲካሄድ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

ሁለቱ መንገዶች ግንባታቸው በየካቲት 2008 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሎ ቢታቀድም፣ በአካባቢው እየተፈጠረ ያለው የትራፊክ መጨናነቅ በጣም እየጨመረ በመምጣቱ ትራንስፖርት ሚኒስቴር በሰጠው መመርያ፣ አንደኛው ረድፍ በአፋጣኝ ተገንብቶ ለትራፊክ ክፍት እንዲሆን ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

በዚህ መሠረት የቻይናው ግዙፍ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲሲሲሲ ግንባታው በማገባዳደድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በቅርቡ ለትራፊክ ክፍት እንደሚደረግ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጠን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የፍጥነት መንገዱ መጨረሻ ከሆነው አቃቂ ተነስቶ ለቡ ድረስ ያለው 13.6 ኪሎ ሜትር እና ከአቃቂ ተነስቶ አይሲቲ ፓርክ (የረር ጎሮ) ድረስ የሚገነቡት መንገዶች ናቸው ለትራፊክ ክፍት የሚሆኑት፡፡

እነዚህ መንገዶች በአጠቃላይ ስድስት መኪኖችን በአንድ ጊዜ የሚያስተላልፉ ሲሆን፣ በቅርቡ ለትራፊክ ክፍት የሚሆነው አንደኛው ረድፍ ሦስት መኪኖችን በአንድ ጊዜ ያስተላልፋል ተብሏል፡፡ በአጠቃላይ ሁለቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች 4.6 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚደረግባቸው ሲሆኑ፣ ከአጠቃላይ ወጪ 75 በመቶ የቻይና ኤግዚም ባንክ ቀሪውን 25 በመቶ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ይሸፍናሉ፡፡

የመንገዶቹ ግንባታ ባለፈው 2006 ዓ.ም. መጨረሻ ነው የተጀመረው፡፡ በሁለት ዓመት ከስምንት ወር ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ ነገር ግን አንዱ ረድፍ የግድ ማለቅ አለበት በመባሉ ግንባታው እየተፋጠነ በመሆኑ በቅርቡ ለትራፊክ ክፍት ይሆናል፡፡

እነዚህ ሁለት መንገዶች ከአዲስ አበባ-አዳማ ድረስ የተገነባው ግዙፍ የፍጥነት መንገድ አካል ናቸው፡፡ የአዲስ – አዳማ የፍጥነት መንገድ 84.6 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው  12.2 ቢሊዮን ብር ወጥቶበታል፡፡ ሁለቱ መንገዶች እንደተጠናቀቁ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ከቃሊቲ እስከ አቃቂ ድረስ ያለውን መንገድ ደረጃ የሚያሻሽል መሆኑ ታውቋል፡፡

ይኼ መንገድ ብቸኛው የአገሪቱ ወጪና ገቢ ንግድ የሚከናወንበት በመሆኑ ተለዋጭ መንገድ ሳይገነባ የመንገዱን ደረጃው ማሻሻል አይቻልም ተብሎ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የፍጥነት መንገዱ በሁለት አቅጣጫዎች ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመዘርጋቱ፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ወደ ግንባታ ይገባል በማለት ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ አገር ውስጥ ባለመኖራቸው አስተያየታቸውን ማካተት ሳይቻል ቀርቷል፡፡

 

ትውልደ ኢትዮጵያዊው ገጣሚና ጸሐፊ ተውኔት የማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ሆነ

በእንግሊዝ ማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ለቻንስለርነት ከተወዳደሩ ሦስት ግለሰቦች መካከል ትውልደ ኢትዮጵያዊው ገጣሚና ጸሐፈ ተውኔት ለምን ሲሳይ አብላጫውን ድምፅ በማግኘት አሸነፈ፡፡

ለምን በወድድሩ የተሳተፉትን የሙዚቃ ባለሙያውን ሰር ማርክ ኤልደርና የቀድሞውን የእንግሊዝ ፖለቲከኛ ሎርድ ፒተር ማንዴልሰንን ሰፊ በሆነ የድምፅ ብልጫ አሸንፏል፡፡

ለምን ውድድሩን ያሸነፈው 7,131 የማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞችና የቀድሞ ተማሪዎችን ድምፅ በማግኘት ሲሆን፣ ሰር ማርክ ኤልደር 5,483 ድምፅ በማስመዝገብ ሁለተኛ ሆነዋል፡፡ እንዲሁም ፖለቲከኛው ሎርድ ፒተር 5,269 ድምፅ በማግኘት ሦስተኛ ሆነዋል፡፡

ለምን ከምርጫው በኋላ የዩኒቨርሲቲው ቻንስለር ለመሆን ያበቃውን ድምፅ የሰጡትን መራጮች አመስግኗል፡፡ ከነሐሴ አንድ ጀምሮ በሥልጣን ላይ ያሉትን ቶም ብሎክሳምን ተክቶ ለሰባት ዓመታት እንደሚሠራ ታውቋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ዴም ናንሲም ዩኒቨርሲቲውን በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ 

ገጣሚና ጸሐፊ ተውኔት ለምን ሲሳይ እ.ኤ.አ. በ1967 በዊጋን ከተማ ከኢትዮጵያዊ ቤተሰቦች የተወደለ ሲሆን፣ ከወላጆቹ ዘንድ ለማደግ አልታደለም ነበር፡፡ እስከ 12 ዓመቱም እንግሊዛዊ አሳዳጊዎቹ ዘንድ ቆይቷል፡፡ በኋላም በአካባቢው በሚገኝ ሕፃናት ማሳደጊያ ዕድሜው 17 እስኪሆን ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1988 በ21 ዓመቱ የግጥም መድበል አሳትሟል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1995 ‹ኢንተርናል ፍላይት› የሚባል በቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅቶ ለዕይታ አብቅቷል፡፡ ሌሎች በርካታ ስኬቶችም ተቀዳጅቷል፡፡

 

ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሠራተኞች መልቀቅ ችግር ሆኖብኛል አለ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በክፍያና በሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ማነስ ምክንያት፣ በጣም በርካታ ሙያተኞች መልቀቃቸውንና በምትካቸውም ብቁ ሙያተኛ ለመቅጠር ክፍያው ሳቢ አለመሆኑን ገለጸ፡፡ 

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ያለፉትን አሥራ አንድ ወራት የኮሚሽኑን የዕቅድ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሰኔ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት ነው ይኼንን ችግር ያነሱት፡፡

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፣ 12 ወንዶችና ሰባት ሴቶች በድምሩ 19 ሠራተኞች ሥራቸውን ለቀዋል፡፡ መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች መልቀቅና በምትካቸው መቅጠር ባለመቻሉ ባለፉት 11 ወራት ያጋጠመው ችግር በማለት ለፓርላማው አባላት አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ለኮሚሽኑ ዕቅድ ማስፈጸሚያ ከመንግሥት የተፈቀደው የመደበኛ በጀት አነስተኛ ከመሆኑም በላይ፣ በየወሩ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የሚለቀቀው ወይም አንድ-አሥራ-ሁለተኛ የሚባለው አሠራር፣ በተለይም በኮሚሽኑ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አሠራር ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ ሌላው ኮሚሽኑን ያጋጠመው ተፅዕኖ እንደሆነ ኮሚሽነሩ  አስረድተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙት እነዚህ ችግሮች ቢኖሩም፣ ኮሚሽኑ ያከናወናቸው ተግባራት መኖራቸውን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡ በዚህም ረገድ በአጠቃላይ የ2007 ዓ.ም. አምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ሕገ መንግሥቱን፣ የምርጫ ሕጎችንና ዓለም አቀፍ መሥፈርቶችን መሠረት ባደረገ ሁኔታ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብቶችን ጨምሮ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መንገድ እንዲፈጸም ክትትል ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የሴቶችና የሕፃናት መብትን ለማስጠበቅ እንዲቻል፣ በተለይም የመብት ጥሰት መንስዔ የሆኑትን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና የግል ጥቃቶች ለመከላከል ብሎም ለማስወገድ የተጀመሩ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችና መድረኮች እንዲጠናከሩ ኮሚሽኑ ያደረገው ድጋፍ እንዲሁ በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ ጠንካራ ክንውኖች መሀል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡

ላለፉት አምስት ዓመታት ኮሚሽኑን በኮሚሽነርነት ሲያገለግሉ የነበሩት አባላት በአዲስ ለመተካት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኅብረተሰቡ የዕጩዎች ጥቆማ እንዲያደርግ ያስነገረ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በአዲሱ የፓርላማው የመጀመሪያ ዓመት  አዲስ ኮሚሽነር የሚመረጥ በመሆኑ፣ ይህ ሪፖርት በአምባሳደር ጥሩነህ አማካይነት የቀረበ የመጨረሻው ነው፡፡

 

የእነ አቶ መላኩ ፈንታ ክስ ለሁለተኛ ጊዜ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ አስነሳ

በቀድሞው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በእነ አቶ መላኩ ፈንታ መዝገብ በከባድ ሙስና የተከሰሱ ነጋዴዎችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የጉምሩክ አዋጅ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይገባል ወይስ አይገባም በሚለው

ጉዳይ ላይ ለመወሰን፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ሰኔ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ጉዳዩን መራለት፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክሱን መሠረት ያደረገው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 411 (የመንግሥት ሥራን ለማያመች አኳኋን መምራት) እና በተሻሻለው የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 ላይ ነው፡፡ ይሁንና አዲሱ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 በቀድሞው ሕግ በወንጀልነት የተፈረጁ ድርጊቶችን የሚሽር ነው፡፡ ተከሳሾቹም ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት ጥያቄ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 22(2) ላይ የወንጀል ክስ የቀረበበት ድርጊት ከተፈጸመ በኋላ የወጣ ሕግ ለተከሳሹ ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ፣ ከድርጊቱ በኋላ የወጣው ሕግ ተፈጻሚ እንደሚሆን ስለሚደነግግና የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 5(3)ም በተመሳሳይ ይኼንኑ የሚደነግግ በመሆኑ፣ በአዲሱ ሕግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተሻሩት አንቀጾች ነፃ እንዲወጡ ነው፡፡

ይኼን ጥያቄ ካቀረቡት ተከሳሾቹ መካከል አቶ መላኩ ፈንታ፣ አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ (የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር)፣ አቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር (የነፃ ትሬዲንግ ባለቤት)፣ አቶ ስማቸው ከበደ (የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት) እና ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ (የአዲስ ካርዲያክ ሆስፒታል መሥራችና ባለድርሻ) ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ የሆኑት ዶ/ር ፍቅር ማሩ የተከሰሱት ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር የሕክምና ዕቃዎችን በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ አስገብተዋል ተብለው ነው፡፡ በአዲሱ የጉምሩክ አዋጅ ይኼ ድርጊት በገንዘብ የሚያስቀጣ እንጂ፣ የወንጀል ድርጊት ባለመሆኑ ነፃ መውጣት እንዳለባቸው ተከራክረዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ግን ድርጊቱ ኮንትሮባንድ በመሆኑ ይኼ ድርጊት ግለሰቡን በወንጀል ከመጠየቅ አያድናቸውም ሲል ተከራክሯል፡፡ በተጨማሪም የወንጀል  ሕግ አንቀጽ 411 አሁንም እንዳልተሻረ አስታውሷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከራካሪ ወገኖችን ክርክር ከሰማ በኋላ አዲሱ አዋጅ ተከሳሾቹን ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም የሚለውን ጭብጥ መርምሯል፡፡ ፍርድ ቤቱ በአዲሱ የጉምሩክ አዋጅ በቀድሞው አዋጅ ወንጀል የነበሩ ድርጊቶች መሻራቸውን ማረጋጡን ገልጿል፡፡ ይሁንና በአዲሱ አዋጅ አንቀጽ 182 ላይ ‹‹በሌሎች ሕጎች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ይኼ አዋጅ ከፀናበት ቀን በፊት የተጀመሩ ጉዳዮች በነበረው ሕግ መሠረት ፍፃሜ ያኛሉ፤›› ተብሎ መደንገጉ ልዩ ሁኔታን እንደሚፈጥር አስገንዝቧል፡፡ የወንጀል ሕጉ ጠቅላላ ሕግ በመሆኑና የጉምሩክ አዋጅ ደግሞ ልዩ ሕግ በመሆኑ፣ በመርህ ደረጃ ልዩ ሕግ ከጠቅላላ ሕግ ቅድሚያ ተሰጥቶት ተግባራዊ እንደሚሆን አመልክቷል፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ሕግ በሕግነት ፀንቶ የማይቆም በመሆኑ፣ አዲሱ ሕግ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጣጣም ስለመሆኑ መመርመር እንደሚያስፈልግ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡

በፍርድ ቤቱ ዕይታ የአዲሱ የጉምሩክ አዋጅ አንቀጽ 182 በሕገ መንግሥቱ ከተቀመጡት አንቀጽ 9፣ 13 (ሕገ መንግሥቱ የበላይ ሕግ ስለመሆኑና ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚፃረር ማንኛውም ሕግና ውሳኔ እንደማይፀና ይደነግጋሉ) እና 22 ጋር የሚጣጣም ባይሆንም፣ ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን የሌለው በመሆኑ የዚሁ ሥልጣን ባለቤት የሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩን መርምሮ ሕገ መንግሥቱን በመተርጎም፣ ውሳኔውን ለሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. እንዲያቀርብ መርቶታል፡፡ 

ይኼው ክስ ከዚህ ቀደም ባስነሳው ሌላ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ የከፍተኛ የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጉዳይ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጀመርያ ደረጃ ሥልጣን እንዲታይ የሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 8(1)፣ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ይግባኝ የመጠየቅ መብት የሚጥስ ነው ተብሎ እንዲሻር ማድረጉ ይታወሳል፡፡

 

የቻይና መንግሥት ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ትኩረት እንዲደረግ፣ ዝቅተኛና መካከለኛ ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ያደረጉ ፋብሪካዎች ደግሞ ተነቅለው ወደ አፍሪካ እንዲሄዱ ማዘዙ ተሰማ፡፡

ከአፍሪካ አገሮች በተለይ ግብፅና ኢትዮጵያ ተመርጠዋል፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ዕድገት ይበጃሉ ያላቸውን ፋብሪካዎች ለመቀበል፣ ከቻይና ናሽናል ዴቨሎፕመንትና ሪፎርም ኮሚሽን ጋር ለመደራደር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የቻይና መንግሥት ዝቅተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ከአገር ወጥተው እንዲሠሩ ውሳኔ ያሳለፈው፣ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ያላትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል በማለቱ ነው ተብሏል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪም በቻይና የአገልግሎት ዘርፍን ለማሳደግና ከዚህ ቀደም ርካሽ የነበረው የሰው ኃይል በአሁኑ ጊዜ እየተወደደ በመምጣቱ፣ ፋብሪካዎቹ ከአገር ወጥተው በማደግ ላይ ባሉት ኢትዮጵያና ግብፅ እንዲተከሉ መመርያ ማስተላለፉ ተነግሯል፡፡

ይህንን እንደ መልካም አጋጣሚ የተመለከተው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ለአገሪቱ ዕድገት ወሳኝ የሚባሉ ፋብሪካዎችን በመምረጥና የቻይና መንግሥት ሊያቀርብ ስለሚችለው የፋይናንስ ሁኔታ ድርድር እንዲያደርግ፣ ኃላፊነቱን ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መስጠቱ ታውቋል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፍያን አህመድ የሚመሩት የልዑካን ቡድን በቅርቡ ወደ ቻይና ተጉዞ፣ ከቻይና ብሔራዊ ዴቨሎፕመንትና ሪፎርም ኮሚሽን ኃላፊዎች ጋር የመጀርያውን ድርድር ማካሄድ እንደሚጀምር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ 

የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከግብርና በማላቀቅ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ መሠረት ላይ ለማሳረፍ ያቀደው የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይ ለጨርቃ ጨርቅ፣ ለቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ፣ ለስኳር ልማትና ለኬሚካል ኢንዱስትሪ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል፡፡

ይህንን ዕቅድ ለማሳካትም በዶ/ር አርከበ እቁባይ የሚመራው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ በአሥር ቢሊዮን ዶላር ወጪ በተለያዩ ከተሞች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም ላይ ይገኛል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲቀላቀሉ የሚመረጡት የቻይና ፋብሪካዎች በእነዚህ የኢንዱስትሪ ዞኖች ውስጥ ወይም ራሳቸው በሚያቋቁሟቸው የኢንዱስትሪ ዞኖች ውስጥ ፋብሪካዎቻቸውን እንዲተክሉ እንደሚደረግ፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ለማምረት አመቺ መሆኑን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ መንግሥት ኢንቨስትመንት በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ተዋናዮችን ለማረበታታት ያወጣቸው በርካታ ሕጎችና ማበረታቻዎች፣ እንዲሁም በአገሪቱ ያለው የሰው ኃይል አገሪቱን ተመራጭ ማድረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

  

 

በቴክኒክና በንግድ ሥራ የሠለጠኑ 63 ሴቶች ሰኔ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ተመረቁ፡፡ በሥልጠናው በወተትና የሥጋ ምርት አቅርቦት፣ እንዲሁም የቁም ከብት ንግድ ላይ ክህሎት የሚያሳድግ ግንዛቤ ማግኘታቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ሥልጠናውን ያዘጋጀው የአሜሪካ መንግሥት በዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲው (USAID) ሲሆን፣ በ2004 ዓ.ም. በሴቶች ላይ በተደረገ ጥናት በወተት ምርት፣ በእንስሳት ዕርባታ፣ በአመራር ዕውቀት፣ በንግድ ሥራ አገልግሎቶች ተደራሽነት፣ ውሳኔ በመስጠት፣ በስኬታማ የንግድ ሥራ ዕቅድ አዘገጃጀት ረገድ የታዩትን ክፍተቶች ለመሙላት ነው ተብሏል፡፡ 

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ ‹‹ወደፊትን መመገብ›› በተሰኘ ፕሮግራሙ በግብርና ዕድገት ፕሮግራም የእንስሳት ገበያ ልማትና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ በሚያስችል አቅም መመረቅ በተሰኙ መርሐ ግብሮች፣ በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም. ሥልጠና ሰጥቷቸዋል፡፡ በሥልጠናው የተካተቱት ሴቶች የሥራ ፈጠራ አቅም እንዳላቸው የታመነባቸው መሆናቸው በመግለጫው ተመልክቷል፡፡ ሴቶቹ በአስተዳደርና በሥራ አመራር ክህሎት ሥልጠና የተሰጣቸው ሲሆን፣ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዝ የንግድ ሥራ ዕቅድ በመንደፍ ረገድም የቴክኒክ ዕውቀት ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡

ሠልጣኞቹ ከአማራ፣ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እንዲሁም ከትግራይ ክልል የተውጣጡ ናቸው፡፡ በቆይታቸው ያገኙትን ክህሎት በአካባቢያቸው ለሚገኙ ሴቶችም እንደሚያካፍሉ ይጠበቃል፡፡

ሴቶች በእንስሳት ዕርባታና በእንስሳት ምርት አያያዝ የሚጫወቱትን ሚና ማሳደግ ለቤተሰብም ሆነ በአገር ደረጃ ከፍ ያለ ጠቀሜታ አለው ያሉት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ ተወካይ ካለን ሒዩስ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በንግድ ሥራ አስተዳደርና በአመራር ላይ ያተኮረው ሥልጠና፣ በእንስሳት ዕርባታ ዕምቅ አቅም ያላቸው አርዓያ ሴቶች ላይ ማተኮሩ፣ በዘርፉ የመሪነቱን ሚና እንዲጫወቱ ያግዛቸዋል፡፡ በሥልጠናው ያልተካተቱ ሴቶችም በሠልጣኞቹ አማካይነት ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል፡፡ 

 

መንግሥት የፓርቲዎቹን መግለጫ ውድቅ አድርጓል

በአንድ ቀን ልዩነት የአረና/መድረክ እና የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በተለያዩ ሥፍራዎች ተገድለው በመገኘታቸው ምክንያት ሰማያዊ ፓርቲና አረና/መድረክ በመንግሥት ላይ ወቀሳ አቀረቡ፡፡

ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. በአማራ ክልል በምሥራቅ ጎጃም ዞን በደብረ ማርቆስ ከተማ አቶ ሳሙኤል አወቀ የተባሉ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ ሲገደሉ፣ በማግሥቱ አቶ ታደስ አብረሃ የተባሉ የአረና/መድረክ አባል በትግራይ ክልል ምዕራብ ዞን ማይካድራ ከተማ  መገደላቸውን ሁለቱም ፓርቲዎች አስታውቀዋል፡፡

አረና/መድረክ ባወጣው መግለጫ አባሉ በምዕራብ ትግራይ ዞን የድርጅቱ ጉዳይ ኃላፊ ሆነው በ2007 ምርጫ ወቅት፣ የፓርቲውን ሥራ በማደራጀትና በማንቀሳቀስ ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ የቆዩ መሆናቸውን፣ ሰኔ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት ለጊዜው ባልታወቁና ቤታቸው በመጡ ሦስት ሰዎች ግድያ እንደተፈጸመባቸው አስታውቋል፡፡

ፓርቲው የገዳዮቹን ማንነት አለመታወቁን በጠቆመበት መግለጫ፣ ሟች አባሉ ከግድያው ቀደም ብሎ በመንግሥት የፀጥታ ሠራተኞች ወከባና ማስፈራርያ ይደርስባቸው እንደነበር ጠቁሟል፡፡

‹‹ለጉዳተኛው የሕክምና ዕርዳታ እንዲደረግላቸው ለማስተባበርና ወንጀለኞችም ለመከታተልና ለማስያዝ የተደረገው ሙከራ በፖሊሶች አለመተባበር›› ሳይሳካ መቅረቱን በመግለጫው አረና/መድረክ አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይም ሰማያዊ ፓርቲ አቶ ሳሙኤል የተባሉ አባሉ ከመገደላቸው በፊት፣ በደኅንነት ሠራተኞችና በአካባቢው ሹሞች የግድያ ማስፈራርያ ይደርሳቸው እንደበር ገልጿል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምርያ በበኩሉ አቶ ሳሙኤል በሁለት ግለሰቦች መገደላቸውን ገልጾ፣ አንደኛው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ውሎ ሲመረመር ግድያውን መፈጸሙን ማመኑን አስታውቋል፡፡

ነገር ግን የፖሊስን መግለጫ ሙሉ በመሉ ውድቅ ያደረገው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ‹‹የሰማዕታት ደም ይጮሃል፣ ይጣራል›› በሚል ርዕስ ሰኔ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ይህ ሥርዓት በሕግም፣ በሞራልም ኢትዮጵያን የማስተዳዳር ብቃት የለውም፡፡ ወንጀለኞችን ለፍርድ ይቅረቡ እያልን አናላዝንም፣ ወንጀለኞቹ የመንግሥት አካላት ናቸውና፤›› ሲል መንግሥትን ምንም ዓይነት ፍትሕ እንደማይጠብቅም ገልጿል፡፡

እንዲሁም አረና/መድረክ በበኩሉ በትግራይ ክልል ከ17 በላይ አባላት ጨምሮ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች በአባላት ላይ እስራት፣ ግርፋትና ግድያ እየተፈጸመባቸው መሆኑን በመግለጫው አስፍሯል፡፡

መንግሥት በበኩሉ ክሶቹን ውድቅ በማድረግ ተገደሉ በተባሉት ሰዎች እጁ እንደሌለበት ገልጾ፣ ትችቶቹ ሁሉ እውነትነት የሌላቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሽመልስ ከማል፣ ‹‹ሁለቱም የተቃዋሚዎች አባላት በግለሰቦች መገደላቸውንና ጉዳዮችን ይዞ ለፍርድ ለማቅረብ ፖሊስ ምርመራውን ቀጥሏል፡፡ መንግሥት እንደሚያምነው የሁለቱ ዜጎች መገደል ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ይዘት የለውም፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተለይ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ግድያ አሳዛኝ እንደሆነ፣ ሟች ከቀድሞ ደንበኞቹ ጋር በተፈጠረው አለመግባባት መገደሉን ፖሊስ አረጋግጧል  ካሉ በኋላ፣ አቶ ታደሰ በማይታወቁ ሰዎች ከመገደላቸውና ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ከማወቃቸው ውጪ፣ ገና መረጃው እንዳልደረሳቸው አቶ ሽመልስ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአረና/መድረክ አባልን ግድያ በተመለከተ የትግራይ ክልል የፀጥታና የደኅንነት ቢሮን ምላሽ ለማግኘት ሪፖርተር ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም፣ ኃላፊዎችን በስብሰባ ምክንያት ለማግኘት ባለመቻሉ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡ 

 

የ120 ሚሊዮን ዶላር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ስምምነት ተፈረመ

ኢትዮጵያና ኬንያን በኤሌክትሪክ ኃይል ለማገናኘት፣ በኢትዮጵያ በኩል የ433 ኪሎ ሜትር ኃይል ማስተላለፊያ መስመር መገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ፡፡ ስምምነቱ ሰኔ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል

አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀና ግንባታውን ለማካሄድ የተመረጠው የቻይናው ስቴት ግሪድ እህት ኩባንያ ሲኢቲ ኩባንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ሚስተር ቸንግ ዊ በሸራተን አዲስ ተፈራርመዋል፡፡ የኃይል መስመሩ አንደኛው ኮንትራት በ120 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባ ሲሆን፣ ወጪው በአፍሪካ ልማት ባንክ ይሸፈናል ተብሏል፡፡ ግንባታው ከወላይታ ሶዶ ተነስቶ ኬንያ ድንበር ሞያሌ ላይ የሚቆም ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለውን 612 ኪሎ ሜትር የኃይል መስመር ኬንያ ትገነባለች፡፡ ኢትዮጵያ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬንያ ለመሸጥ ስምምነት ያረገች በመሆኗ፣ አንዱን ኪሎ ዋት በሰባት የአሜሪካ ሳንቲም ለመሸጥ ስምምነት ተደርጓል፡፡

የቻይናው ኩባንያ የፈረመው በኢትዮጵያ በኩል ከሚገነቡት ሁለት ኮንትራክተሮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በቅርቡ አንደኛው ኮንትራት ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በኬንያ በኩል የሚገነባው የኃይል መስመር በሦስት ኮንትራቶች የተከፈለ ነው፡፡ ግንባታውን ለማካሄድ አሸናፊ ከሆኑ የህንድ ኩባንያዎች ጋር በቅርቡ ስምምነት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ ግንባታ በ26 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ የቻይናው ኩባንያ ምክትል ፕሬዚዳንትም ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ገደብ እንደሚጠናቀቅ ቃል ገብተዋል፡፡ በምሥሉ ላይ ኢንጂነር አዜብ አስናቀና የቻይናው ኩባንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ቸንግ ዊ ስምምነቱን ከተፈራረሙ በኋላ፡፡

 

የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ባለፉት 11 ወራት አርባ ያህል ከፍተኛ ኪሳራ ሊያስከትሉ የሚችሉ የሳይበር (ኮምፒዩተርን መሠረት ያደረጉ) ጥቃቶችን ማምከኑን፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

ኤጀንሲው ከተቋቋመ በርካታ ዓመታት ቢያልፉም፣ እንደ አዲስ በተነደፈው አሠራር መሠረት ለመጀመርያ ጊዜ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ሰኔ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ አቅርቧል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይ እንደገለጹት፣ የአገሪቱን ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ለማጥቃት የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶች ነበሩ፡፡

‹‹ወደ አገራችን የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶች በርካታና ብዙ መልክ  ያላቸው ናቸው፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹አንዳንድ የጥቃት ዓይነቶች አገራችንን በተለየ ሁኔታ ዒላማ ያላደረጉ ነገር ግን ማንኛውም ተጋላጭ መሠረተ ልማትን የሚያጠቁ ሲሆን፣ እንደዚህ ዓይነት ጥቃቶች በየቀኑ ከዚህ አልፎም በየሰዓቱ የሚሠራጩ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ሌሎች ሆን ተብሎ የኢትዮጵያን የሳይበር መሠረተ ልማት ለማጥቃት የሚለቀቁ ቫይረሶች መኖራቸውን የገለጹት ሜጀር ጄኔራል ተክለ ብርሃን፣ ወደ አርባ የሚጠጉ በአጠቃላይ መሠረተ ልማቱንና የተወሰኑ ቁልፍ ተቋማትን ዒላማ ያደረጉ ከፍተኛ ኪሳራ ሊያደርሱ የነበሩ የሳይበር ጥቃቶችን ለማምከን መቻሉን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ጥቃቱ ቢደርስ ኖሮ ሊያስከትል የነበረው ኪሳራ በጣም ትልቅ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ከዚህ ውጪ የሳይበር ጥቃቶቹ በየትኞቹ ቁልፍ ተቋማት ላይ እንደተሠነዘሩ፣ እንዲሁም ከየት አካባቢ እንደሆነ አልገለጹም፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ በቴሌኮም ማጭበርበር ተግባር ላይ የተሰማሩ 55 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን፣ ለዚህ የወንጀል ተግባር ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ወደ 170 የተራቀቁና ዘመናዊ ሕገወጥ የቴሌኮም መሣሪያዎች መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡ ግለሰቦቹ በቴሌኮም ወንጀል ተሰማርተው በነበረበት ወቅት 700 ሚሊዮን ብር ኪሣራ በኢትዮ ቴሌኮም ላይ ማድረሳቸውንም ተናግረዋል፡፡

ኤጀንሲው የተሰጠውን ተልዕኮ በተቀናጀና በተጠናከረ መንገድ ለመወጣት እንዲችል ቀደም ሲል የተጀመረውን በዘርፉ ያሉትን የሕግ፣ የፖሊሲና የስታንዳርድ ክፍተቶች በመለየት ክፍተቶችን ለመዝጋት እየሠራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል የሳይበር ወንጀል ሕግ ረቂቅ ማዘጋጀት አንዱ ሲሆን፣ በ2005 ዓ.ም. ለካቢኔ ቀርቦ የነበረ ነው፡፡ ረቂቅ ሕጉ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በመሆን እንደገና እንዲታይ በመወሰኑ በድጋሚ በመታየት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

  

እስራኤላዊው ምሁር ከስደት ተመላሽ ወገኖች አክራሪነት እንዳላጠላባቸው እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል አሉ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥርጣሬውን አጣጥሏል

በዓለም አቀፍ የፀረ ሽብር ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪና በእስራኤል መንግሥት የዲፕሎማሲና የስትራቴጂ ተዛምዶ ማዕከል አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ዮናታን ፋይን፣ ኢትዮጵያ ከስደት የምትመልሳቸው ዜጐቿ ከአክራሪነት ጥላ የራቁ መሆናቸውን

ማረጋገጥ እንደሚገባት አሳሰቡ፡፡ የደኅንነትና ዓለም አቀፍ ጥናት ምሁሩ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት ከየመን፣ ከሊቢያና ከሌሎችም የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ወደ አገር ቤት በሚመለሱ ዜጐች ላይ መንግሥት አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡

ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖችና ጽንፈኛ እምነትን የሚያራምዱ ግለሰቦችና ድርጅቶች በሞሉባቸው የመካከለኛው ምሥራቅና የሰሜን አፍሪካ አገሮች በብዛት የሚገኙት ኢትዮጵያውያን፣ በአንድም ሆነ በሌላ አጋጣሚ በእነዚህ አካላት ተፅዕኖ ሥር ወድቀው ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡ ይህም እነዚህ ወገኖች ወደ አገራቸው ገብተው ከሚገጥሙዋቸው የመልሶ መዋሀድ ተግዳሮቶች ጋር ተዳምሮ ላልተፈለገ የባህርይ ለውጥ ሊዳርጋቸው እንደሚችል ምሁሩ ገልጸዋል፡፡

ይህ ጥርጣሬ ለምን እንደገባቸው ተጠይቀው የመለሱት ምሁሩ፣ በተለያዩ የዓለም አገሮች የተደረጉ ጥናቶች የሚያሳዩት መረን ላወጣ አፈንጋጭነትና አክራሪነት እርሾ የሚሆኑት ባህርያት በሆነ ወቅት ወደ አገር ቤት ተመልሰው መኖር በሚጀምሩ ዜጎች ምክንያት የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ በተለይ በርካታ ዜጐቿን በስደት የምታጣው አፍሪካ ዜጎቿ በልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች ከሚገጥማቸው የኑሮ ውጣ ውረድ ጋር ተዳምሮ፣ ለአዳዲስና የኑሮ ሁኔታን ሊቀይሩ ይችላሉ ለተባሉ አስተሳሰቦች በቀላሉ የመንበርከክ ዕድል እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡ በግብፅ፣ በሊቢያ፣ በምዕራብና በመካከለኛው አፍሪካ የሚገኙ በርካታ ዜጐች በእነዚህ አዳዲስ አስተሳሰቦች በመማረካቸው ምክንያት ወደ አገራቸው ሲመለሱም ይህንኑ አቋማቸውን እንደሚገፉበት ምሁሩ ያስረዳሉ፡፡

እስራኤላዊው ምሁር እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ የሚታየው ሁኔታ በዚህ ደረጃ የሚጠቀስ አለመሆኑን፣ የሕዝቡ የረጅም ዘመናት ተቻችሎ የመኖር ልማድ ለዚህ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን እንደሚያምኑ ገልጸው፣ ነገር ግን ይህ ሁኔታ በተለያዩ የውጭ ተፅዕኖዎችና አካባቢያዊ ሁኔታዎች ሊሸረሸር እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋትና ለአደገኛ ቡድኖች አመቺ ሥፍራ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ 

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ፣ የምሁሩ አስተያየት ምንም መሠረት የለውም ባይባልም ዓለም አቀፋዊ ገጽታን የተላበሰ መሆኑን በመጠቆም፣ ለጊዜው ግን ሥጋትን የሚያጭር አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህንን ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቀጥታ ባይመለከተውም፣ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ተገቢውን ሥራ እንደሚያከናውን እገምታለሁ፡፡ በእኛ በኩል ከየትም አገር የሚመጣ ዜጋ በኤምባሲዎችና በቆንስላዎች አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ሲያሟላ እናስተናግዳለን፤›› ሲሉ አቶ ተወልደ ገልጸዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቀዳሚ ዓላማም የዜጐችን ማንነትና ምንነት ማጥናት ሳይሆን፣ የነፍስ አድን ተግባሩን በማቀላጠፉ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 

እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይኦኤም መረጃ፣ በየመን ብቻ ከ50 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ሲታወቅ እስካሁን ድረስ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ታውቋል፡፡ በሊቢያ የሚገኙ ዜጐችም በግብፅ በኩል ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆናቸውንም የድርጅቱና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጀመረውን የነፍስ አድን ዘመቻ አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት፣ በየትኛውም አገር የሚገኝ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊጠቀምበት የሚችል ዕድል መሆኑንም አቶ ተወልደ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በእስራኤል የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያንን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ምንም የቀረበ ጥያቄ አለመኖሩን፣ ጥያቄው ከቀረበ ግን እነሱንም ለመርዳት መንግሥት ዝግጁ መሆኑን አቶ ተወልደ አስታውቀዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ያጋሩት እስራኤላዊው ምሁር ዶ/ር ዮናታን፣ ኢትዮጵያውያኑ ቤተ እስራኤላውያን በእስራኤል እየገጠማቸው ያለው ፈተና አሳሳቢ መሆኑን፣ በአንዳንድ ምግባረ ብልሹ የፀጥታ ኃይሎች የሚፈጸመውን ጥቃትም አጥብቀው የሚቃወሙ በርካታ እስራኤላውያን መኖራቸውን በመጠቆም፣ የቤተ እስራኤላውያኑ የመብት ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ ሊያገኙ እንደሚገባቸው አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህ የዘር መድልኦ ዛሬም ድረስ በአሜሪካና በሌሎችም ያደጉ አገሮች የሚስተዋል በመሆኑ፣ የእስራኤልን ሁኔታ አዲስ አያደርገውም፡፡ ከዚህ በፊት ሩሲያውያንን ጨምሮ ሌሎችም ትውልደ እስራኤላውያን በተመሳሳይ ችግር ውስጥ አልፈው እዚህ በመድረሳቸው፣ ቤተ እስራኤላውያኑም በቅርብ ጊዜ ችግራቸው እንደሚፈታ እገምታለሁ፤›› በማለት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የቤተ እስራኤላውያን ቁጣና የእስራኤል ባለሥልጣናትን ዘገምተኛ የመፍትሔ ዕርምጃ ገልጸውታል፡፡     

 

ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ በሐምሌ ወር አጋማሽ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና ከአፍሪካ ኅብረት አመራሮች ጋር እንደሚመክሩ፣ ዋይት ሀውስ አስታወቀ፡፡

በሥራ ላይ ያለ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን ጎብኝቶ አያውቅም፡፡

የበርካታ አገሮች መሪዎች ይታደሙታል ተብሎ የሚጠበቀው ከሐምሌ 5 እስከ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚካሄደው ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ጉባዔ ባራክ ኦባማ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ይሁንና የዋይት ሀውስ መግለጫ ፕሬዚዳንቱ ለዚሁ ጉባዔ ስለመምጣታቸው የሚያወሳው ነገር የለም፡፡ 

ጉባዔው በመስከረም ወር 2008 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀውን የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብን ይተካል የተባለለት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለመተግበር የሚያስችሉ የፋይናንስ ምንጮች ላይ ይመክራል፡፡ ይህንኑ ጉባዔ ለመከታተል ከ5,000 በላይ የአገር መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የግል ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበራትና የሚዲያ ተወካዮች አዲስ አበባ እንደሚመጡ ይጠበቃል፡፡

የዋይት ሀውስ የፕሬስ ጉዳዮች ኃላፊ ጆሽ ኧርነስት የኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝት አሜሪካ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከርና በአፍሪካ ኢንቨስት የማድረግ ቁርጠኝነት ያላት መሆኑን ለማሳየት ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮችና ዜጎች ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲያመጡ፣ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲገቡና የደኅንነት ይዞታቸውን እንዲያጠናክሩ አሜሪካ የምታደርገው ጥረት አካል እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡ 

ፕሬዚዳንት ኦባማ በኬንያ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የሥራ ፈጠራ ጉባዔ ከተከታተሉ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ታውቋል፡፡ የባራክ ኦባማ አባት ኬንያዊ ቢሆኑም ይህ ጉዟቸው እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ ነው፡፡   

 

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ምስማር ለማምረት ከሚያገለግለው ስታፋ ብረት (ዋየር ሮድ) ለዓመታት የቆየውን ታሪፍ ከለላ እንዲነሳ ማድረጉ ውዝግብ አስነሳ፡፡

የታሪፍ ከለላው መነሳት በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የምስማር ንግድ፣ አንድ ኩባንያ ብቻ በሞኖፖል እንዲቆጣጠር በር ከፍቷል የሚሉ ምስማር አምራች ኩባንያዎች ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ወስደውታል፡፡

ስታፋ ብረት ላይ የታሪፍ ከለላ በመነሳቱ ቅሬታቸውን ካቀረቡት 76 ፋብሪካዎች መካከል 46 የሚሆኑት ትላልቅ የምስማር ፋብሪካዎች፣ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በሚገኘው ኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከምስማር አምራቾች በተጨማሪ በታሪፍ ከለላ መነሳቱ በትግራይ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ለውኃና ለአፈር ጥበቃ የሚያገለግለው ጋብዮን (በሽቦ የተሠራ መረብ) የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ይገኙበታል፡፡ 

ሚኒስቴሩ ሚያዚያ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ባስተላለፈው መመርያ የስታፋ ብረት ከውጭ ሲገባ፣ 20 በመቶ የጉምሩክ ታክስና አምስት በመቶ ዊዝ ሆልዲንግ ታክስ እንዲከፈል አድርጓል፡፡ ሚኒስቴሩ እዚህ ውሳኔ አይ የደረሰው በአገር ውስጥ ስታፋ ብረት በብቸኝነት የሚያመርተው ስቲሊ አርኤምአይ ኩባንያ ለመጥቀም ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ምስማር አምራቾች ስታፋ ብረት ከስቲሊ አርኤምአይ በመግዛት ሥራቸውን እንዲያካሂዱ ለማድረግ የታሪፍ ከለላውን አንስቷል፡፡

ቅሬታ አቅራቢ ምስማር አምራቾች የተላለፈው መመርያ አንዱን ወገን ማለትም ጥሬ ዕቃውን ማምረት ለጀመረው ስቲሊ አርኤምአይ ኩባንያ ለመደገፍ የወጣ እንጂ ፍትሐዊነት የሌለው አሠራር ነው በሚል ይተቻሉ፡፡

“በስታፋ ብረት ላይ የሁለተኛ ደረጃ ታሪፍ ከለላ መነሳቱን ይበልጥ አስቸጋሪ ያደረገው የስታፋ ብረት አገር ውስጥ ማምረት የጀመረው እስቲሊ አርኤምአይ እህት ኩባንያ የሆነው አስመን ላለፉት 15 ዓመታት የምስማር ገበያን 65 በመቶ ድርሻ የያዘ በመሆኑ ነው፤” በማለት ቅሬት አቅራቢ ኩባንያዎች ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ባስገቡት ደብዳቤ ተገልጿል፡፡

ስቲሊ አርኤምአይ እና እህት ኩባንያው አስመን የስታፋ ብረትና የምስማር ዋጋ በሞኖፖል ለመወሰን እንዲችሉ ከፍተኛ አቅም ይሰጣል በማለት፣ የሚኒስቴሩን መመርያ አግባብነት የሌለው እንደሆነ የቅሬታ አቅራቢዎቹ ደብዳቤ ጨምሮ ያስረዳል፡፡ የስቲሊ ኤምአርአይ የኦፕሬሽንና ፖሊሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተፈራ ለማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ስታፋ የሚሸጥበት ዋጋ ለሁሉም አምራች ኩባንያዎችም ሆነ ለእህት ኩባንያ አንድ ነው በማለት ምሳሌ ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡ ደብዳቤው ሚኒስቴሩ መመርያውን ካስተላለፈ ከጥቂት ወራት በኋላ ጉዳዩን የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቁሞ እንደነበርም ያስታውሳል፡፡ ኮሚቴውን የንግድ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ አህመድ ኑሩ የመሩ ሲሆን፣ ኮሚቴው ባካሄደው ጥናትም ስቲሊ አርኤምአይ የስታፋ ብረት በበቂ መጠንና በሚፈለገው ጥናት እያመረተ መሆኑን፣ የቀረበው የሞኖፖሊ ሥጋትም “በአሠራር ማስወገድ እንደሚቻል” በመጥቀስ የታሪፍ ማሻሻያው ተገቢ መሆኑን አስተያየት ሰጥቷል፡፡

የብረት አምራቾች ግን ይህንን ሐሳብ በፍፁም አልተቀበሉትም፡፡ የታሪፍ ከለላው የተነሳው ስቲሊ አርኤምአይን ሆን ብሎ ለመጥቀም ነው በማለት መከራከርያቸውን ያቀርባሉ፡፡ ይህ ውሳኔ የኢንቨስትመንት ፈቃድና የኢንቨስትመንት ማበረታቻ በተሰጣቸው በርካታ አምራቾች ላይ ሊያስከትል የሚችለው ተፅዕኖ አልታየም፡፡ ስቲሊ አርኤምአይ ከሚያመርታቸው ልዩ ልዩ ምርቶች አንዱን በመነጠልና በአንዱ ምርት ላይ ያነጣጠረና በርካታ አምራቾችን ከገበያ የሚያስወጣ ነው በማለት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ፡፡ 

የበለጠ እሴት ጭማሪ ያለውና ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚቀጥረው የምስማር ፋብሪካ ከውጭ በሚያስገባው የስታፋ ብረት ላይ የተነሳው የታሪፍ ከለላ በጥልቀት ያልታየና በጥናት ላይ ያልተመሠረተ ነው በማለት፣ ቅሬታቸውን በጽሑፍ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቅርበዋል፡፡ 

የምስማር ፋብሪካዎቹ እንደሚሉት የታሪፍ ከለላ በመነሳቱ ስታፋ ብረት ከውጭ በማስገባት ምስማር ማምረት አዋጭ አይደለም፡፡ ከስቲሊ አርኤምአይ ስታፋ ብረት ገዝቶ ምስማር ማምረትም አዋጭ አይደለም ይላሉ፡፡

አዋጭ ያልሆነበት ምክንያት ሲያብራሩ፣ በተወሰደው ዕርምጃ የጥሬ ዕቃ መግዣና የምርቱ የመሸጫ ዋጋ በዋናነት የሚወሰኑት ስቲሊ አርኤምአይ እና እህት ኩባንያው አስመን ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ለብዙ ዓመታት በሥራ ላይ የቆዩ የምስማር አምራች ኩባንያዎች፣ ‹‹ከሥራ እንድንወጣ እያደረገን ነው›› በማለት ቅሬታቸውን አስተጋብተዋል፡፡ “በተቀመጠው አቅጣጫ ጥሬ ዕቃ ከስቲሊ በመግዛት ሥራችንን እናስቀጥል ብለው የጀመሩ አንዳንድ የምስማር ፋብሪካዎችም ቢሆኑ፣ በዋናነት በስቲሊና በአስመን እየተፈጠረ ባለው የዋጋ መዛባት ሥራውን በተገቢው መንገድ ለመቀጠል ተቸግረዋል፤” በማለት ቅሬታ አቅራቢዎቹ በደብዳቤ ይገልጻል፡፡ 

በአቶ አህመድ የሚመራው ኮሚቴ በምስማር አምራቾቹ የቀረበው የሞኖፖሊ ሥጋት በአሠራር ማስወገድ እንደሚቻል የገለጸ ቢሆንም፣ የሞኖፖሊ ሥጋት እንዴት እንደሚወገድ የሚገልጽ የአሠራር ዘዴ ግን አያይዞ አላቀረበም በማለትም ይወቅሳሉ፡፡ 

“በስታፋ አምራቹ ስቲሊ አርኤምአይ እና በምስማር ምርት ትልቁን ድርሻ በሚያመርተው እህት ኩባንያው አስመን የሞኖፖል አሠራሮች ለማስወገድ የሚያስችል አሠራር ተቀይሶ ተግባራዊ ማድረግ ሲገባ፣ አንድ ወገን ብቻ በማየት የተወሰነው ውሳኔ በዋጋ ላይ እንደተጠበቀው ከፍተኛ ችግር ያስከተለ መሆኑንና እንዲያውም አንዳንድ ፋብሪካዎች ከነጭራሱ እስከ መዘጋት ደርሰዋል፤” በማለት ቅሬታ አቅራቢ የምስማር ፋብሪካዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባቀረቡት ቅሬታ ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት ስቲሊ አርኤምአይ በስታፋ ብረት የነበረው ከለላ ሲነሳ፣ የምስማር ፋብሪካዎች የስታፋ ብረት ከውጭ ሲያስገቡና የምስማር ነጋዴዎች ያለቀለት ምስማር ከውጭ ሲያስገቡ የሚከፍሉት የጉምሩክ ቀረጥና ዊዝ ሆልዲንግ ታክስ ተመሳሳይ ስለሚሆን፣ ስታፋ ብረት ከውጭ አስገብቶ ምስማር ከማምረት ይልቅ ያለቀለት ምስማር በተመሳሳይ ቀረጥ ከውጭ አስመጥቶ መሸጥ የቀለለ እንደሆነ፣ የምስማር አምራቾች ከአስመጭዎች የተሻለ ከለላ እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡

ነገር ግን የጥናት ቡድኑ “ይህ ጉዳይ ወደፊት ሊጠና ይገባል” በማለት ጉዳዩን በቀላሉ እንዳለፈውም ይጠቁማሉ፡፡ በምስማር ፋብሪካዎች የተነሱት ሥጋቶችና ችግሮች ከከለላው መነሳት ጋር ተያይዘው ካልተመለሱ የታሪፍ ከለላ ብቻ ማንሳቱ ለአንዱ ወገን ያደላ መሆኑን፣ ይህም የመልካም አስተዳደር እንዲሁም ፍትሐዊነት ጥያቄ የሚያስነሳ ነው በሚል ኩባንያዎቹ የቅሬታቸውን ስፋት በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ የተወሰደው ዕርምጃ ያስገኛል ተብሎ ከሚጠበቀው ፋይዳ አንፃር ሲታይ ያስከተላቸው ችግሮች ሚዛን የደፉ በመሆናቸው፣ ወደ ተግባር ሲለወጥም የተገመቱ ሥጋቶችን ለመከላከል አስቸጋሪ ስለሆነና እንዲሁም በውሳኔው ችግሮች ሲከሰቱ ለመፍታት የሚያስችል ሥርዓት አብሮ ያልታየ በመሆኑ፣ በብዙ መመዘኛዎች ሲታይ በስታፋ ብረት ላይ የተነሳው ከለላ እንደገና ሊጠና ይገባል በማለት ምስማር አምራች ኩባንያዎች ቅሬታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቅርበዋል፡፡

ስቲሊ አርኤምአይ በመስከረም 1997 ዓ.ም. በ486 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት የብረት ማቅለጥና የሮሊንግ ፋብሪካ በማቋቋም ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ከዚህ በመቀጠል ኩባንያው አቅሙን በማሳደግ በአገር ውስጥ የሚመረት ስታፋ ብረት ባለመኖሩ በ726 ሚሊዮን ብር ወጪ ታኅሳስ 2006 ዓ.ም. አዲስ ፋብሪካ አቋቁሟል፡፡ ድርጅቱ በአጠቃላይ ሦስት ፋብሪካዎች አሉት፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች በዓመት 30 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በመጠቀም የአርማታ ብረትና ስታፋ ብረት ያመርታሉ፡፡ ስቲሊ አርኤምአይ ያቋቋመው አስመን ኩባንያ በበኩሉ ስታፋ ብረት በመጠቀም የተለያዩ ምስማሮችን ያመርታል፡፡ ስቲሊ አርኤምአይ ለሪፖርተር በሰጠው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ የግል ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ልማት ቀድመው ለሚገቡ ባለሀብቶች መንግሥት ሰፊና ጠንካራ ድጋፍ እንዳደረገለት አስረድቷል፡፡ “ይህ ከለላ የተሰጠው ለስቲሊ ሳይሆን ለብረት አምራች ኢንዱስትሪ ስለሆነ የኋልዮሽ የእሴት ጭማሪ አድርገው መዋለ ንዋያቸውን ላፈሰሱ ባለሀብቶች የተሰጠ ነው፤” በማለት አቶ ተፈራ ገልጸዋል፡፡ “በዚህ መሠረት ወደ ኢንዱስትሪው ቀድመው ለሚገቡም ሆነ የምርት ሰንሰለቱን ጠብቀው ለሚሠሩ፣ የታክስ ከለላና ሌሎችንም ማበረታቻዎች ይሰጣል፤” በማለትም መንግሥት ያደረገለትን ድጋፍ አስረድቷል፡፡ ኩባንያው በመቀጠል መንግሥት እነዚህን ማበረታቻዎች የሚሰጠው ባለሀብቶች በእነዚህ ማበረታቻዎች ተበረታተው በሰፊው ወደ ልማቱ እንዲገቡና በአገሪቱ የተያዘው የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ ግቡን እንዲመታ ለማድረግ እንጂ፣ የተወሰኑ ሰዎችን ጠቅሞ ሌላውን ለመጉዳት አይደለም ብሏል፡፡ 

ኩባንያው የቀረበበትን ክስ በሚመለከት እንደገለጸው፣ ከአሁን በፊት ስታፋ ብረት ከሚጠይቀው የተራቀቀ ቴክኖሎጂ፣ ዕውቀትና ከፍተኛ የካፒታል መጠን ምክንያት በአገሪቱ የማይመረት ነበረ፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ስቲሊ አርኤምአይ ለአርማታ ብረት እንደተደረገው ሁሉ የስታፋ ብረት በአገር ውስጥ በመመረቱና ምንም እንኳ ስታፍ ብረት ከአርማታ ብረት ጋር ሲነፃፀር የሚጠይቀው የማምረቻ ሒደትና የሚፈጀው ወጪ ከፍተኛ ቢሆንም፣ ለአርማታ ብረት ከተሰጠው የታክስ ከለላ እኩል ከለላ እንዲሰጠው መንግሥት ወስኗል፡፡ ይህም ምስማር ፋብሪካዎች ያቀረቡት በዘርፉ ውስጥ ለአንድ ዓይነት ምርት ብቻ ከለላ ተሰጥቷል የሚለው ትክክል አለመሆኑን ያስረዳል ሲሉ አቶ ተፈራ ተናግረዋል፡፡ 

“ይህ ማለት ከአሁን በፊት ለምስማር ጥሬ ዕቃነት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ሲገባ የነበረው የስታፋ ብረት ላለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ሲደረግለት የነበረው የታክስ ከለላ ተነስቶ ቀረጥ እንዲቀረጥበት አደረገ እንጂ፣ ከውጭ ማስመጣት አልተከለከለም፤”  በማለት የስቲሊ አርኤምአይ መረጃ ይተነትናል፡፡

“ይህ የመንግሥት ውሳኔ የስታፋ ምርት በከፍተኛና በብዛት አገር ውስጥ የሚመረት በመሆኑ ካለው የኢንዱስትሪ ፖሊሲና የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ቁጠባ ከማጎልበት አንፃር ተመልክቶ የወሰነው ጉዳይ ነው፡፡ ውሳኔውም የተሰጠው ለእኛ ድርጅት ሳይሆን ለምርቱ የተሰጠ ዕውቅና ነው፤” በማለትም አክሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአንድ ወገን ስቲሊ አርኤምአይ በሌላ ወገን ደግሞ በርካታ ምስማር አምራቾች በከፍተኛ ደረጃ በመወዛገብ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ውዝግብ ለመፍታት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያዳረጓቸው ጥረቶች ያልተሳኩ በመሆናቸው፣ ቅሬታ አቅራቢዎቹ መንግሥት በመስከረም 2005 ዓ.ም. ባሳተመው የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ሰነድ ላይ በተዘረዘረው መሠረት ልንስተናገድ ይገባል በማለት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጉዳያቸውን መውሰዳቸውን አስታውቀዋል፡፡

 

ሁለቱን ዶክተሮች ያፋጠጠው የቦንጋ ምርጫ

ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም.መካሄድ ሲገባው፣ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ የተላለፈው ምርጫ ሰኔ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በደቡብ ክልል በካፋ ዞን፣ በቦንጋ ጊምቦ ገዋታና በዴቻ ወረዳ ተከናውኗል፡፡

የግል ዕጩውን ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስና የደኢሕዴን/ኢሕአዴግ ዕጩ ዶ/ር መብራቱ ገብረ ማርያም ያፋጠጠው ይህ ምርጫ፣ ቀደም ብሎ ግጭት ስለተካሄደበት ነበር ለሌላ ጊዜ የተላለፈው፡፡ ለዚህ ምርጫ 67,707 መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን፣ 95 በመቶ የሚሆኑ መራጮች ድምፃቸውን መስጠታቸውን የምርጫ ክልሉ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡ በውጤቱም ዶ/ር መብራቱ ዶ/ር አሸብርን በሰፊ ውጤት ማሸነፋቸውን በማግሥቱ በምርጫ ጣቢያዎች ከተለጠፉ ውጤቶች ለመረዳት ተችሏል፡፡

በምርጫ 2002 በወቅቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ብርሃኑ አዴሎን በሰፊ ልዩነት ያሸነፉት ዶ/ር አሸብር፣ በዘንድሮ ምርጫ አልቀናቸውም፡፡ ዶ/ር አሸብር በቅርቡ ለፓን አፍሪካ ፓርላማ ሁለተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ቢመረጡም፣ የዘንድሮ ምርጫ ከብዷቸዋል፡፡ ተፎካካሪያቸው ዶ/ር መብራቱ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ በምርጫ 2002 ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ተወዳድረው ሲያሸንፉ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለምርጫ የቀረቡት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ባለፈው እሑድ በተካሄደው ምርጫ በምርጫ ጣቢያዎቻቸው ተገኝተው ድምፃቸውን የሰጡት ዶ/ር መብራቱ (በስተቀኝ)፣ ዶ/ር አሸብር (በስተግራ) ድምፃቸውን ለመስጠት ተሠልፈው ይታያሉ፡፡ የቦንጋን የዘገየ ምርጫ በተመለከተ የተዘጋጀው የነዓምን አሸናፊ ዘገባ ለመመልከት እዚህ ይጫኑ፡፡ 

 

ሰማያዊ ፓርቲ በደብረ ማርቆስ ለምርጫ በዕጩነት ያቀረበው አባሉ ተገደለ

ፓርቲው ክፍፍል ተፈጥሯል መባሉን አስተባበለ 

ሰማያዊ ፓርቲን በመወከል በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ለተወካዮች ምክር ቤት በደብረ ማርቆስ ከተማ ተወዳዳሪ የነበረው አባሉ ወጣት ሳሙኤል አወቀ፣ ሰኞ ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡00 አካባቢ

በስለት ተወግቶና ተደብድቦ ተገደለ፡፡ ፓርቲው አባሉ መገደሉን ለሪፖርተር በማረጋገጥ፣ ነገር ግን በማን እንደተገደለ ማጣራቱን አለማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

ወጣት ሳሙኤል ወደ መኖሪያ ቤቱ ሲያመራ በሁለት ሰዎች ተደብድቦ ጉዳት ስለደረሰበት ወደ ሆስፒታል እንደተወሰደ ሕይወቱ ሊያልፍ መቻሉን፣   የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

ወጣት ሳሙኤል ከቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ጀምሮ በተቃውሞ ጎራ ሲታገል የቆየ መሆኑንና ፓርቲው ለሁለት ሲከፈል ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የፓርቲው ጸሐፊ ሆኖ መሥራቱን አቶ ዮናታን ጠቁመዋል፡፡ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ለተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድሮ ነበር፡፡

ነገር ግን ከምርጫው በኋላ ሟች ወጣት ሳሙኤል ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያ ይደርሰው እንደነበር አቶ ዮናታን ገልጸዋል፡፡ የሟቹ የፌስቡክ ግድግዳ ላይ በተጻፈ ማስታወሻም ይህንን የሚጠቁሙ መረጃዎች መስፈራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ አቶ ዮናታን ግን በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ስለመገደሉ ለጊዜው ተጨባጭ ማስረጃ እንደሌላቸው፣ ፓርቲው ጉዳዩን በመከታተል ላይ እንደሆነ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ወጣት ሳሙኤል በፌስቡክ ግድግዳ ላይ ግንቦት 26 ቀን 2007 አሰፈረው በተባለው ማስታወሻ ላይ፣ ‹‹በስልኬ እየተደወደ ያለ ፍላጎቴ ደኅንነት እያስገደደኝ ይገኛል፡፡ ተገደልሁም፣ ታሰርሁም፣ ታፈንኩም ነፃነት አይቀርምና ለማስረጃነት የደኅንነቶችን ስም፣ ፎቶግራፍና አድራሻ፣ እንዲሁም በሐሰት ምስክርነትና በከሳሽነት የተደራጁ አካላት ተወካዮች አስመዘግባለሁ፡፡ ማንኛውንም የምከፍለው ዋጋ ለአገሬና ለነፃነት ነው፡፡ ከታሰርኩም ህሊናዬ አይታሰርም፡፡ ከገደሉንም ትግሌን አደራ…›› የሚል ይነበባል፡፡ ይህንን ማስታወሻ በተመለከተ በመንግሥት በኩል ምንም ዓይነት አስተያየት አልተሰጠም፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ሰማያዊ ፓርቲ ከሰኔ 4 እስከ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. የምክር ቤት ስብሰባ ማድረጉን፣ በዋነኛነት በሚቀጥለው ወር ጠቅላላ ጉባዔ ከመካሄዱ በፊት የቅድመ ሪፖርት ውይይት እንዳደረገ አቶ ዮናታን ገልጸዋል፡፡ ለግንቦቱ ምርጫ ማስፈጸሚያ በተደረጉ ወጪዎችና የበጀት አጠቃቀም ጉዳይና ፓርቲው ከተመሠረተ ጀምሮ ሲጠቀምበት በነበረው ሕገ ደንብ ጉዳይ፣ በከፍተኛ ክርክር የታጀበ ውይይት መደረጉንም አቶ ዮናታን አስረድተዋል፡፡

በተለይ በበጀት ጉዳይ በአባላት መካከል የጋለ ክርክር ተካሂዶ የነበረ ቢሆንም፣ በመግባባት ተጠናቋል ብለዋል፡፡ ነገር ግን በፓርቲ ውስጥ ‹‹ከፍተኛ ፍትጊያ ያለው›› ክርክር የተለመደ ቢሆንም፣ በፓርቲው ውስጥ መከፋፈል እየተፈጠረ ነው ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ መሠረተ ቢስ ነው ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛ ዝም ብለን ተሰብስበን አንበተንም፡፡ ከፍተኛ የሐሳብ ፍጭት የምናደርግ ስብስብ በመሆናችን ክርክራችን መከፋፈል የሚባል ነገር አያመጣም፤›› በማለት አስታውቀዋል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ከምርጫው በፊት 92 ሚሊዮን ብር ለምርጫ ማስፈጸሚያ መድቤያለሁ ብሎ ከገለጸ በኋላ፣ መንግሥት በፓርቲው የገንዘብ ምንጭ ላይ ምርመራ አደርጋለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን አቶ ዮናታን ፓርቲው እስካሁን ምንም ዓይነት ምርመራ እንዳልተደረገበት ጠቁመዋል፡፡

 

መንግሥት በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የግል ኩባንያዎች በግዙፍ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲሳተፉ ሊፈቅድ ነው፡፡ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የግል ኩባንያዎች

የፍጥነት መንገድ መገንባት፣ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትና ለመስኖ አገልግሎት የሚውሉ ግድቦች መገንባት እንዲችሉ ፈቅዷል፡፡ 

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሕግ ዲፓርትመንት ኃላፊ አቶ ዋሲሁን አባተ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ትብብር ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል፡፡

በዚህ መሠረት የግል ኩባንያዎች በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዲኖራቸው ከማድረጉ ባሻገር፣ ከዚህ ቀደም ተሳታፊ ባልሆኑባቸው የመሠረተ ልማት ዘርፎች ውስጥ ተዋናይ እንዲሆኑ እየተመቻቸ መሆኑን አቶ ዋሲሁን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት በቅርቡ ይፋ በሚያደርገው የአምስት ዓመት ዕቅድ ሰነድ በተዘረዘረው መሠረት፣ የግል ባለሀብቶች የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን አካሂደው አገልግሎት በመስጠት የንግድ ሥራ ማካሄድ ያስችላቸዋል፡፡

ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የሕግ ዲፓርትመንት ባዘጋጀው የሕግ ማዕቀፍ ላይ የተቀጠሩ አማካሪ ድርጅቶች አስተያየት እየሰጡ መሆኑ ታውቋል፡፡

ረቂቅ ሕጉ ከፀደቀ በኋላ የግል ኩባንያዎቹ በሚፈልጓቸው የመሠረተ ልማት ዘርፎች የሚሰማሩ ሲሆን፣ ከአዋጁ ባሻገር አሠራሩን የሚደግፍ ደንብ እንደሚዘጋጅም ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ የመንገድና የኃይል ማመንጫ ባለቤት የሆነ የግል ኩባንያ የለም፡፡ ለመስኖ አገልግሎት የሚውል ግድብም ቢሆን ከራስ ፍጆታ አልፎ ለኪራይ አገልግሎት ያዋለ የግል ኩባንያ እንደሌለ ይታወቃል፡፡ እየተዘጋጀ ባለው ዕቅድ ግን አንድ ኩባንያ በራሱ ወጪ የፍጥነት መንገድ ገንብቶ ለተጠቃሚዎች ክፍት በማድረግ መንገድ እንደሚችል ተቀምጧል ተብሏል፡፡ 

በኢትዮጵያ ብቸኛው የፍጥነት መንገድ ከአዲስ አበባ አዳማ ድረስ የተዘረጋው 80 ኪሎ ሜትር ባለ ስድስት ረድፍ መንገድ ብቻ ነው፡፡ በቻይናው ሲሲሲሲ ኩባንያ የተሠራው ይህ መንገድ የሚተዳደረው መንግሥት ባቋቋመው የልማት ድርጅት ሲሆን፣ መንገዱ የአገልግሎት ክፍያ እየተከፈለበት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ 

‹‹ከእነዚህ ግንባታዎች የግሉ ዘርፍ ልምድ በመውሰድ የራሱን ግንባታ ሊያካሂድ ይችላል፤›› በማለት አቶ ዋሲሁን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በብቸኝነት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ሥልጣን ያለው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ነው፡፡ የገጠሩን የአገሪቱ ክፍል የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለማሻሻል ብሔራዊ ኃይል ማስተላለፊያ ከተዘረጋበት መስመር 15 ኪሎ ሜትር ርቀው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ከተለያዩ አማራጭ የኃይል አቅርቦቶች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጩ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ የመነጨውን ኃይል የሚያስተዳድሩትም ያመነጩት የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ 

በአሁኑ ዕቅድ ግን የታሰበው የግሉ ዘርፍ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወሰን ታሪፍ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያቀርብ ይደረጋል ተብሏል፡፡

መንግሥት በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን ራሱን የቻለ 12 ሺሕ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት አቅዷል፡፡ ይህ ዕቅድ ይተገበራል ተብሎ የሚጠበቀው የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ከተሳተፉ ብቻ ነው ተብሎ በመታመኑ፣ በተለይ በአሁኑ ወቅት በግድብ ግንባታ የተሰማሩ ኩባንያዎች ተስፋ እንደተጣለባቸው ተመልክቷል፡፡ 

በሌላ በኩል ለመስኖ ልማት አመቺ በሆኑ ወንዞች ላይ የግሉ ዘርፍ ግድብ እንዲገነባ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ ተብሏል፡፡ በግድቡ ዙርያ በእርሻ ሥራ የተሰማሩ ኩባንያዎች ውኃውን እንዲጠቀሙ እየተደረገ የአገልግሎት ክፍያ ይፈጽማሉ ተብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት ይህንን ሥራ እየሠራ የሚገኘው የአዋሽ ተፋሰስ ባለሥልጣን ብቻ ነው፡፡ ባለሥልጣኑ በአዋሽ ወንዝ ላይ ሥልጣን የተሰጠው በመሆኑ ከአዋሽ ወንዝ ጠልፈው የሚጠቀሙ አልሚዎች ኪራይ እንዲከፍሉ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ 

አሁን በተያዘው ዕቅድ፣ የግል ኩባንያዎች የግድብ ግንባታ በማካሄድ የውኃው አገልግሎት ኪራይ ማስከፈል እንዲችሉ ይደረጋል፡፡ 

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት መንግሥት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በዋናነት ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ይህንን ዕቅድ ለማሳካት በዋናነት የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ፣ አገሪቱን ከአላስፈላጊ ብድር ለመታደግ ተስፋ እንደተደረገ ተመልክቷል፡፡ የልማታዊ መንግሥት ሞዴል በሚከተሉ አገሮች የግሉ ዘርፍ መንግሥት በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሠረት በኢኮኖሚው ውስጥ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡     

 

የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደቡብ ሱዳን (ጁባ) ቅርንጫፍን በመመሳጠር መዝብረዋል ብሎ በጠረጠራቸው ሠራተኞች ላይ ሰኔ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ መሠረተ፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ክሱን የመሠረተው፣ በስምንት የቅርንጫፉ ሠራተኞች ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡ 

ተጠርጣሪዎቹ በቅርንጫፍ ባንኩ በኃላፊነትና በተለያዩ የሥራ መደቦች ላይ ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ሰኔ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ግለሰቦቹን የጠረጠራቸው እርስ በእርስ በመመሳጠር ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ከጁባ ቅርንጫፍ ንግድ ባንክ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የተለያዩ ቅርንጫፎች የመጋዘን ሠራተኞችን በሙስና ወንጀል በመጠርጠር ምርመራ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

የተጠረጠሩት ሠራተኞች በተለያዩ የምርት ገበያው ስድስት መጋዘኖች የ11 ሚሊዮን ብር ምርት ማጉደላቸውን ክሱ ያመለክታል፡፡

 

ኢትዮጵያና ኬንያ በኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነታቸው መሠረት፣ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ለማካሄድ ሐሙስ ሰኔ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ኮንትራክተሮች ጋር ውል ይፈርማሉ፡፡

በሁለቱ አገሮች በጋራ የሚካሄደው የኃይል መስመር ዝርጋታ 1,068 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ መገንባት ያለባትን 437 ኪሎ ሜትር የኃይል መስመር በሁለት ኮንትራቶች ተከፍሎ ለቻይና ስቴት ግሪድ ኩባንያ ይሰጣል፡፡ ስቴት ግሪድ በአሁኑ ወቅት ከህዳሴ ግድብ የሚወጣው ኤሌትሪክ የሚተላለፍበትን መስመር በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከቻይናው ስቴት ግሪድ ጋር ሐሙስ ይፈራረማል፡፡

በኬንያ በኩል የሚገነባው 631 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ የኬንያ መንግሥት በሦስት ኮንትራቶች የሚከፈለውን ይህን ፕሮጀክት በዚህ ሳምንት ለህንድ ኩባንያዎች ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 1.2 ቢሊዮን ዶላር የሚፈልግ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ወገን ያለውን የአፍሪካ ልማት ባንክ ፋይናንስ ያደርገዋል፡፡ በኬንያ በኩል ያለውን አፍሪካ ልማት ባንክና የፈረንሣይ የልማት ኤጀንሲ ፋይናንስ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ ባይጠቃለልም በሁለቱም አገሮች ሁለት የማከፋፈሪያ ጣቢያዎች ይገነባሉ፡፡ ፕሮጀክቶቹን የዓለም ባንክ ፋይናንስ እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡ የማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ ኮንትራት በግምገማ ሒደት ላይ የሚገኝ በመሆኑ በጀቱ አልታወቀም፡፡

የሚገነባው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር 500 ኪሎ ቮልት ኃይል በአንድ ጊዜ ማስተላለፍ (ዳይሬክት ከረንት) አቅም ያለው ሲሆን፣ ይህም በአፍሪካ ትልቁ እንደሚያደርገው ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ኮንስትራክሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ሆሮ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህ ፕሮጀክት ለሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚያዊ ትስስር ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡

ኢትዮጵያ ለኬንያ 400 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ከዓመታት በፊት የመግባቢያ ስምምነት አድርጋለች፡፡ ይህ መስመር ኢትዮጵያ ለታንዛኒያ የምትሸጠውን የኤሌክትሪክ ኃይል ይተላለፋል ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ ሰፊ እንደመሆኑ መጠን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ረዥም ጊዜ የፈጀ በመሆኑ፣ ኮንትራቱ ከተፈረመ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ግንባታ ይገባል፡፡ 

በቀጣይ በኢትዮጵያ በኩል ወላይታ ሶዶ፣ በኬንያ በኩል ሱሳዋ ላይ 2,000 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል የመሸከም አቅም ያለው ማከፋፈያ ጣቢያ ይገነባል፡፡ 

 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሙስና ወንጀል የተገኙ የመሬት ይዞታዎችን ያለምንም ዕውቀት የገዙ የከተማ ነዋሪዎች የመሬት ባለቤትነት ዕጣ ፈንታ ሊወስን ነው፡፡

ምንጮች እንደገለጹት፣ የከተማው አስተዳደር በመሬት ይዞታዎቹ ላይ አስተዳደራዊ ውሳኔ ለመወሰን ያስችለው ዘንድ በይዞዎቹ ላይ ጥናት የሚያደርግ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡

ኮሚቴው ከሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባለሙያዎች ጋር በመሆን ምን ያህል ነዋሪዎች የመሬት ይዞታቸው በሙስና የተገኘ መሆኑን እየተገነዘቡ ግዥ ፈጽመዋል? ምን ያህሉስ ባለማወቅ ግዥ ፈጽመዋል? የሚለውን የመለየት ሥራ በማከናወን ለአስተዳደሩ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌማን፣ የሙስና ወንጀል ፍሬ የሆኑ የመሬት ይዞታዎች ላይ የሚኖሩ ዜጎች የመጨረሻ እልባት ለምን እንዳልተሰጠው ተጠይቀው ነበር፡፡

በመኖሪያ ማኅበራት ስም በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ይዞታዎችን በሙስና በሕገወጥ መንገድ የያዙትን ኮሚሽኑ እንዲቀጡ ማድረጉን ያስታወሱት ኮሚሽነሩ፣ በሕገወጥ መንገድ የተያዙትን የመሬት ይዞታዎችም የአዲስ አበባ አስተዳደር ሕጋዊ ሥርዓት እንዲያስይዘው ከፍርድ ቤት ጭምር ትዕዛዝ መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡

‹‹በዚህ ጉዳይ ውስጥ ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንዱ በትክክል በሕገወጥ መንገድ የተያዘ መሬት መሆኑን እያወቁ ተሳትፎ ያደረጉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ወንጀለኞች በማኅበር ውስጥ የተያዙ ቦታዎችን በሙሉ አልያዙትም፣ ለንፁኃን ሸጠውታል፡፡ ምናልባትም ትክክለኛ ነው በማለት የየክፍላተ ከተማ ማኅበራት ማደራጃዎች አረጋግጠውላቸው ገዝተውታል፡፡ ስለዚህ ሁለቱን ለይቶ አስተያየት መስጠት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

ፀረ ሙስና ኮሚሽን ወንጀለኞችን የወንጀል ፍሬያቸው ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ማድረጉን የተናገሩት ኮሚሽነር ዓሊ፣ በቅን ልቦና የገዙና የመስተዳደር አካላት ሕጋዊ ነው ብለዋቸው ማረጋገጫ ሰጥተዋቸው የገዙ ሰዎች ደግሞ እንዴት ሊስተናገዱ እንደሚገባ አስተዳደሩ የሚወስነው ይሆናል ብለዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አፀደ ዓባይ መረጃ እንዲሰጡ ቢጠየቁም፣ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

በ1997 ዓ.ም. የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጠረውን የሥልጣን ክፍተት በመጠቀም፣ ከ500 በላይ የመኖሪያ ቤት ማኅበራት በሕገወጥ መንገድ ከሁለት ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ መያዛቸውና ፀረ ሙስና ኮሚሽንም ተከታትሎ መሬቱን ማስመለሱ ይታወቃል፡፡

 

 

‹‹ተከሳሾች ማስረጃ የማየት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተጥሷል››  የተከሳሾች ጠበቃ

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በዞን ዘጠኝ ጦማሪያንና በጋዜጠኞች ክስ ላይ ያቀረበው የሲዲ ማስረጃ በችሎት ውስጥ እንዳይታይ፣ ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. የከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በየነ፡፡

የዓቃቤ ሕግ የሲዲ ማስረጃ ጉዳይዋ በሌለችበት የሚታየው አንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ላይ የቀረበ ነው የተባለ ሲሆን፣ ሌሎች ዘጠኝ ተከሳሾች በግብረ አበርነት በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ በዚሁ ክስ ተካተዋል፡፡

‹‹በአንደኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበውን የሲዲ ማስረጃ በጽሕፈት ቤት ተመልክተነዋል፡፡ ከሌሎች ተከሳሾች ጋር የተገናኘ ባለመሆኑ በችሎት መታየቱ አስፈላጊ ሆኖ አላገኘነውም፤›› በማለት የችሎቱ ዳኛ ባለፈው ሰኞ በዋለው ችሎት ብይን ሰጥተዋል፡፡

የፍርድ ቤቱን ውሳኔ የተቃወሙት የተከሳሾች ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን፣ ‹‹እኛ የነበረን አረዳድ ቀጠሮው የተያዘው የሲዲ ማስረጃው በዝግ ችሎት ወይም በክፍት ችሎት፣ ማለትም ታዳሚዎች ባሉበት ወይም በሌሉበት ይታይ በሚለው ላይ እንጂ ዳኞች ብቻ በጽሕፈት ቤት ይዩት በሚል ጉዳይ አልነበረም፤›› ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡

‹‹አሁን የተደረገው ትክክለኛ የዳኝነት አሠራር ነው ብለን አናምንም፡፡ የእኛ ደንበኞች በግብረ አበርነት በተከሰሱበት መዝገብ የቀረበውን ማስረጃ ሊያዩ ይገባል፤›› ሲሉ አቶ አመሐ ተከራክረዋል፡፡

የተከሳሾቹ ሌላው ጠበቃ አቶ ሽብሩ በለጠ በበኩላቸው፣ የቀረበው የሲዲ ማስረጃ ከተከሳሾች ዕይታ ውጪ መሆን እንደሌለበትና ማስረጃውን ማየት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መሆኑን በፍርድ ቤት ተከራክረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ጉዳዩ ብይን የተሰጠበት እንደሆነና የተከሳሽ ጠበቆች አስተያየት ተመዝግቦ ወደፊት ይግባኝ ሊሉበት እንደሚችሉ ገልጿል፡፡

የሰባቱ ጦማሪያንና የሦስቱ ጋዜጠኞች የክስ ሒደት ከ13 ወራት በላይ የፈጀ ሲሆን፣ ዘጠኙ ተከሳሾች ከሚያዝያ 2006 ዓ.ም ጀምሮ የዋስ መብት ተከልክለው በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ ባለፈው ሰኞ ማለዳ በዋለው ችሎት ደማቅ ቀይ ካኒቴራ ለብሶ ከነበረው አቤል ዋበላ በስተቀር ስምንቱ ተከሳሾች አንድ ዓይነት ጥቁር ካኒቴራ ለብሰው ችሎቱን ታድመዋል፡፡ አቤል ከሁለት ሳምንት በፊት በዚሁ የክስ ሒደት ፍርድ ቤት ተዳፍረሃል ተብሎ የስድስት ወራት እስራት በገደብ እንደተፈረደበት ይታወሳል፡፡     

የዓቃቤ ሕግ ማስረጃዎች መጠቃለላቸውን ተከትሎ ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ይገባቸዋል ወይስ አይገባቸውም በሚለው ላይ ፍርድ ቤቱ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዟል፡፡ 

በአገሪቱ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት ፍርድ ቤቱ ይከላከሉ የሚል ብይን ከሰጠ ተከሳሾች የመከላከያ ማስረጃ ማቅረብ ይጀምራሉ፡፡ የዓቃቤ ሕግ ማስረጃ በቂ ሆኖ ካላገኘው ግን በነፃ ሊያሰናብታቸው ይችላል፡፡

ተከሳሾቹ የግንቦት ሰባትና የኦነግን ዓላማ ተቀብለው ለሽብር ተግባር ተደራጅተዋል ተብለው በፀረ ሽብር ሕጉ አንቀጽ ሦስት ንዑስ አንቀጽ ሁለት ‘የኅብረተሰቡን ወይም የኅብረተሰቡን ክፍል ደኅንነት ለከፍተኛ አደጋ ማጋለጥ’ እንደተከሰሱ የዓቃቤ ሕግ የክስ ቻርጅ ያስረዳል፡፡ 

 

ኢትዮጵያና ሱዳን የሁለቱ አገር ሕዝቦች ያለቀረጥና ታክስ መገበያየት የሚችሉበትን ነፃ የንግድ ቀጣና ለማቋቋም ከስምምነት ላይ ደረሱ፡፡

ሰኔ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. የሁለቱ አገሮች የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ፣ በሁለቱም አገሮች ነፃ የንግድ ቀጣናው እንዲቋቋምና በእነዚህ የንግድ ቀጣናዎች የሁለቱም አገሮች ገንዘብ መገበያያ እንዲሆን መስማማታቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡ 

የሱዳን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልራህማን ዲራር ለመገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት፣ የንግድ ቀጣናዎቹን ከማቋቋም በተጨማሪ የሁለቱ አገሮች የመገበያያ ገንዘቦች ዝውውር መኖሩም ለሁለቱ አገሮች የንግድ ልውውጥ እንደሚጠቅም ተናግረዋል፡፡ 

በሁለቱ አገሮች የሚቋቋሙትን ነፃ የንግድ ቀጣናዎችን ምቹ ቦታ የሚለይ አማካሪ ኩባንያ እንደሚቀጠር፣ ኩባንያውም በተቀጠረ በ45 ቀናት ውስጥ ውጤቱን ለጋራ የቴክኒክ ኮሚቴው እንደሚያቀርብ መረጃው ያመለክታል፡፡

የጋራ ቴክኒክ ኮሚቴው ከነፃ የንግድ ቀጣናው በተጨማሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሱዳን ቅርንጫፉን እንዲከፍት፣ እንዲሁም የሱዳን ባንኮች በኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤታቸውን እንዲከፍቱ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሌሎች አገሮች ቅርንጫፎቹን መመሥረት የሚችል ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በደቡብ ሱዳን ቅርንጫፎች ያሉት መሆኑ ይታወቃል፡፡ 

በኢትዮጵያ ግን የውጭ አገር ባንኮች የባንክ አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ በሕግ ተከልክሏል፡፡ በመሆኑም ሊከፈት የሚችለው የሱዳን ባንክ ጽሕፈት ቤት የማማከር አገልግሎትና ሌሎች ባንክ ነክ ያልሆኑ አገልግሎቶችን ነው መስጠት የሚችለው፡፡ 

የሁለቱ አገሮች የቴክኒክ ኮሚቴ ከዚህ ቀደም በተስማማው መሠረት፣ ሁለቱን አገሮች በየብስ የሚያገናኝ ትራንስፖርት ለመጀመር ከወራት በፊት ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል፡፡ 

 

በመጠጥ ውኃ ችግር ውስጥ ከሚገኙት ሦስት የትግራይ ክልል ከተሞች አንዷ ለሆነችው ታሪካዊቷ የአክሱም ከተማ ንፁህ የመጠጥ ውኃ ለማቅረብ 440 ሚሊዮን ብር ብድር ተገኘ፡፡

ለአክሱምና ለአካባቢዋ ንፁህ የመጠጥ ውኃ ለማቅረብ ለኢትዮጵያ ብድር የሰጠው የኩዌት መንግሥት ነው፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አህመድ ሼዴና የኩዌት ፈንድ ለዓረብ ኢኮኖሚ ልማት ምክትል ዳይሬክተር ሚስተር ሀሜድ ኤስ አል ኦማር የብድር ስምምነቱን ሰኔ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ተፈራርመዋል፡፡

በዚህ ፕሮጀክት 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ማይጨው ወንዝ ላይ ግድብ በመገንባት፣ ለአክሱምና ለአካባቢው ንፁህ የመጠጥ ውኃ የማቅረብ ዓላማ የያዘ መሆኑን አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ፕሮጀክት የውኃ ማጠራቀሚያ ጋኖች፣ የውኃ መሳቢያ ፓምፖች፣ ትራንስፎርመሮችና የማጣሪያ ጣቢያዎች ግንባታ ተካተዋል፡፡ 

ይህ ብድር በረዥም ጊዜ የሚከፈል ከመሆኑም በተጨማሪ፣ የኩዌት ፈንድ ለኢትዮጵያ የሚያደርገው ድጋፍ 110 ሚሊዮን ዶላር አድርሷል፡፡

በትግራይ ክልል በውኃ እጦት ችግር ውስጥ የሚገኙ ከተሞች ችግርን ለመፍታት፣ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸው ከአካባቢው የሚመጡ መረጃዎች አስረድተዋል፡፡  

 

ፕሬዚዳንት አል በሽር ከደቡብ አፍሪካ እስኪወጡ በሱዳን የሚገኙ የደቡብ አፍሪካ ወታደሮች በጦር ኃይል ተከበው ነበር

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለምን እንዳላከበረ ማብራሪያ ተጠየቀ 

ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ወደ ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ ያቀኑት የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር፣ የአገሪቱ ፍርድ ቤት በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ትዕዛዝ ቢሰጥም በሰላም ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡

የሱዳን ጦር ኃይል በበኩሉ የደቡብ አፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይል አባላትን በቁጥጥር ሥር አውሎ እንደነበር ታወቀ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2009 እና በ2010 በዳርፉር በተፈጸመው ጅምላ ጭፍጨፋ ምክንያት በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) የእስር ማዘዣ ዋራንት የተቆረጠባቸው የሱዳን ፕሬዚዳንት አል በሽር፣ ከአይሲሲ ውሳኔ በኋላ የደቡብ አፍሪካን ምድር ሲረግጡ ለመጀመርያ ጊዜ ነበር፡፡ 

የአይሲሲ ፈራሚ አገሮች አንድ የእስር ማዘዣ የተቆረጠበት ግለሰብ (መሪ) የመያዝና የማስረከብ ግዴታ ያለባቸው ሲሆን፣ ደቡብ አፍሪካም ከፈራሚዎቹ መካከል ነች፡፡ የኅብረቱን ስብሰባ ለመሳተፍ ወደ አካባቢው ያቀኑት ፕሬዚዳንቱ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ የአገሪቱ መንግሥት ግን ፕሬዚዳንቱ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ በመፍቀድ አስመልጧቸዋል እየተባለ ነው፡፡ 

ተቀማጭነቱ ፕሪቶሪያ የሆነው አይዊትነስ ኒውስ የተባለ ሚዲያ እንደዘገበው ደግሞ፣ የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አል በሽር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ በዳርፉር አካባቢ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የደቡብ አፍሪካ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች የሚገኙባቸው ሦስት ካምፖች በሱዳን ጦር ኃይል ተከበው ነበር፡፡ የደቡብ አፍሪካ የመከላከያ ባለሥልጣናት እንዳረጋገጡት፣ የሱዳን ጦር ኃይል በቁጥጥር ሥር አውሏቸው የነበሩ ካምፖችን የለቀቀው ፕሬዚዳንት አል በሽር ከአገሪቱ መውጣታቸው በተረጋገጠ ጊዜ ነበር፡፡ 

የደቡብ አፍሪካ መከላከያ ኃይል ባለሥልጣናት በሱዳን የሚገኙት አባሎቻቸው ደኅንነትና የተባለውን ነገር እንዲጣራ፣ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማን መጠየቃቸውን ዘገባው ያመለክታል፡፡  

ከፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ በኋላ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አጀንዳ ሆነው የሰነበቱት ፕሬዚዳንት አል በሽር፣ ከፕሪቶሪያ ከተማ ወጣ ብሎ ከሚገኘው አንድ የአየር ኃይል ሠፈር ተነስተው ነበር ሰኞ ጠዋት በራሳቸው አውሮፕላን ወደ አገራቸው የበረሩት፡፡ በካርቱም ኤርፖርትም በደጋፊዎቻቸው ከፍተኛ አቀባበል እንደተደረገላቸው ዘጋርድያን ከአካባቢው ዘግቧል፡፡

ውሳኔ እስኪሰጥባቸው ድረስ ከደቡብ አፍሪካ ምድር እንዳይወጡ አስፈላጊው ዕርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ያወጣው የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ለአይሲሲ ተላልፈው እንዲሰጡ ውሳኔ ያስተላለፈው ግን እሳቸው ወደ አገራቸው በመጓዝ ላይ ሳሉ ሰኞ ጠዋት ነበር፡፡ 

የአገሪቱ ፍርድ ቤት መንግሥት ትዕዛዙን በመጣስ ሕገ መንግሥቱን የሚጋፉ ተግባር መፈጸሙን ጠቅሶ፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ የጽሑፍ ማብራርያ ይዞ እንዲቀርብ አዟል፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንዲወጡ ያደረገበትን ምክንያት ማብራሪያ ይዞ እንዲቀርብ የተጠየቀው የደቡብ አፍሪካ መንግሥት፣ ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ የሚመጣ ማንኛውም የአገር መሪ ሙሉ ያለመከሰስ መብት (Immunity) የተሰጠው መሆኑን በመጥቀስ ራሱን እየተከላከለ ይገኛል፡፡ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ውድቅ ያደረገበትም ምክንያት ይኼው መብት እንደሆነ፣ ፕሬዚዳንት አል በሽር ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጡት በመንግሥት ግብዣ መሆኑን የመንግሥት ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡ 

የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ፕሬዚዳንት የዚምባብዌ መሪ ሮበርት ሙጋቤ ስብሰባውን የመሩት ሲሆን፣ ቀደም ሲል የኅብረቱ አባላት ከአይሲሲ ፈራሚነት ራሳቸውን እንዲያገሉ ሲወተውቱ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት አይሲሲ እየነጠለ የአፍሪካ መሪዎችን ፍርድ ቤት የሚያቀርብ ተቋም መሆኑን በመግለጽ ተቃውሞ በማሰማቱ፣ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በኅብረቱና በፍርድ ቤቱ መካከል የነበረው ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ አሜሪካና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ግን ፕሬዚዳንቱን በቁጥጥር ሥር ባለማዋሉ የደቡብ አፍሪካ መንግሥትን እየወረፉ ይገኛሉ፡፡ 

የተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን በጀኔቭ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹አይሲሲ በፕሬዚዳንት አል በሽር ላይ ያወጣው የእስር ማዘዣ ትልቅ ትኩረት የምሰጠው ነው፡፡ የተቋሙ ትዕዛዝ መከበርና ተፈጻሚ መሆን ነበረበት፤›› ብለዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ገዥ ፓርቲ ኤኤንሲ ግን የአይሲሲ ‹‹አግባብነትና ገለልተኝነት›› ወደፊት የሚከለስበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡ 

 

ሁለት የስኳር ፋብሪካዎች በስድስት ወራት ውስጥ የሙከራ ምርት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል

ዳንጎቴ የምርት ማሸጊያ ፋብሪካ ለመገንባት ጠይቋል 

ሦስት የስኳር ፋብሪካዎች የሙከራ ምርት መጀመራቸውን በማስመልከት ለሪፖርተር ማብራረሪያ የሰጡት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው፣ ከሰም ስኳር ፋብሪካ ሙሉ ለሙሉ የሙከራ ሥራ መጀመሩንና በቅርቡም ወደ ዋናው የምርት ሒደት እንደሚገባ ገለጹ፡፡ 

በከፊል የሙከራ ምርት ከጀመሩት ውስጥ የተንዳንሆና የኩራዝ ስኳር ፋብሪካዎችም ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ሙከራ ተግባር ይገባሉ ብለዋል፡፡ የከሰም ስኳር ፋብሪካ በቀን እስከ 10,000 ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም እንዳለው የገለጹት አቶ አህመድ፣ ሆኖም በአሁኑ ወቅት 6,000 ቶን አገዳ በቀን በመፍጨት ሙከራ እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡ እንደ ስኳር ኮርፖሬሽን መረጃ ከሆነ፣ የከሰም ስኳር ፋብሪካ በ20,000 ሔክታር መሬት ላይ የተንጣለለና በመስኖ ውኃ የሚለማ የአገዳ እርሻ አለው፡፡ 153 ሺሕ ቶን ስኳር፣ 12,500 ሜትር ኩብ ኤታኖል ሥራ በሚጀመርበት ወቅት እንደሚያመርት የሚጠበቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር 260 ሺሕ ቶን ስኳርና 30,000 ሜትር ኩብ ኢታኖል፣ እንዲሁም 15 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በሁለት ምዕራፍ ግንባታው እተካሄደ መሆኑን የገለጹት  አቶ አህመድ፣ በጠቅላላው 26 ሺሕ ቶን አገዳ በቀን የመፍጨት አቅም እንዳለውና በመጀመርያው ምዕራፍ 13,000 ቶን አገዳ በቀን ይፈጫል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ ሙከራ እየገባ ያለው በስድስት ሺሕ ቶን አገዳ ይጀምራል ተብሏል፡፡ ይህ የሆነውም የተርባይንና የእንፋሎት ሥራዎች ስለሚቀሩ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ለሙከራ የሚያበቃው ሥራ ተጠናቆ ምርት እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡

  ሆኖም ተንዳሆ የሚያመርተው 63 ሺሕ ሜትር ኩብ የኢታኖል ምርት ለኢንዱስትሪዎች ፍጆታ ሊውል መታሰቡን አቶ አህመድ ገልጸዋል፡፡ በኬሚካል አምራችነት የተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎችና የከብት መኖ በማምረት ላይ የሚገኙ ፋብሪካዎች ኢታኖል እንዲቀርብላቸው በመጠየቃቸው የተንዳሆ ኢታኖል ምርት ለእነዚህ እንደሚውል አስታውቀዋል፡፡ 

በአገሪቱ እስካሁን እየተመረተ የሚገኘው ዓመታዊ የስኳር ምርት መጠን 300 ሺሕ ቶን እንደሆነ የሚገልጸው ስኳር ኮርፖሬሽን፣ ይህንን መጠን ወደ 2.25 ሚሊዮን ቶን ለማድረስ እየሠራ እንደሚገኝ፣ በአሁኑ ወቅት እየተመረተ የሚገኘውን 18 ሚሊዮን ሊትር ኢታኖል ወደ 44 ሚሊዮን ሜትር ኩብ የማሳደግ ዕቅድ መያዙን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ሆኖም አገሪቱ ከ137 ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ ኢታኖል የማምረት አቅም እንዳላት ይፋ አድርጓል፡፡ አምስት የስኳር ፋብሪካዎች ይኖሩታል የተባለውን የኩራዝ ፕሮጀክትን ጨምሮ፣ የወልቃይትና የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ 

በሌላ በኩል በስኳር ኢንዱስትሪው ውስጥ ይሳተፋሉ ከሚጠበቁ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንዎች እስካሁን ያልተሳካለቸው ሲኖሩ፣ በቅርቡ በሲሚንቶ ምርት ላይ በመሰማራት ሥራ የጀመረው ዳንጎቴ ግሩፕ በስኳር ልማት እንደሚሳተፍ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ አቶ አህመድ እንደሚሉት የናይጄሪያው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ፣ በስኳር ልማት ለመሰማራት የሚያስችላቸውን ጥናት እያካሄዱ ሲሆን፣ የምርት ማሸጊያ ፋብሪካ ለመገንባት በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡  

 

 

ድሬዳዋ ምድር ባቡር የቀድሞ ሠራተኞች እንዲለቁ የተደረገባቸውን ቤቶቻቸውን ተረከቡ

በድሬዳዋ ከተማ በቀድሞው ኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር ጣቢያ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ሠራተኞች በአገልግሎታቸው ወቅት ተሰጥተዋቸው ከነበሩት መኖሪያ ቤቶች እንዲለቁ ሲደረጉ፣ የከተማው ከንቲባ ጣልቃ በመግባት የተፈናቀሉት ሠራተኞች ቤቶቻቸውን መልሰው ማግኘታቸው ታወቀ፡፡

ከ2,000 በላይ ቤተሰቦችን እንደሚያስተዳድሩ የተነገረላቸው ቁጥራቸው 240 ገደማ የሚሆኑ የምድር ባቡር ሠራተኞች፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በጣቢያው ኃላፊዎች ቤቶቹን ለድርጅቱ አስረክበው እንዲለቁ ታዘው ነበር፡፡ በተፈጠረው ውዝግብ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ የድሬዳዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለድርጅቱ የፍርድ ውሳኔ ሲሰጥ፣ ሠራተኞች መበተናቸውንና ለችግር ተዳርገው እንደበር ሠራተኞቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ተፈናቃዮቹ ያለመጠለያ መቅረታቸውን ያወቀው የከንቲባው ጽሕፈት ቤት፣ ከጣቢያው ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ሠራተኞችን ወደ ቀድሞ ቤታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ጥረት አድርጎ እንደነበር የቀድሞ ሠራተኞች ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም  የጽሕፈት ቤቱ ጥረት ውጤት ማስገኘት ባለመቻሉ የከተማው ከንቲባ ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ለጂቡቲ መንግሥት አቅርበው እንደነበር፣ የቀድሞ ሠራተኞች መሠረታዊ ማኅበር ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ሽመልስ እሸቱ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በፌዴራል ደረጃ ያሉ ተቋማት በተለይም ከትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ምድር በቡር ኮርፖሬሽን፣ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ጋር ኮሚቴ አቋቁመዋል፡፡ በኮሚቴው አባላት በዝርዝር ምርመራ ከተደረገ በኋላ የተፈናቀሉ ሁሉም የቀድሞ ሠራተኞች የመኖሪያ ቤታቸውን እንዲያገኙ ተወስኗል፡፡ በውሳኔው ምክንያት ወደ መኖሪያ ቤታቸው መመለሳቸውንና ፍትሕ መገኘቱን አቶ ሽመልስ ተናግረዋል፡፡ 

‹‹በአገራችን እኛን ያጋጠሙን ዓይነት መሰል ችግሮች በተለያዩ ጊዜያት ይከሰታሉ፡፡ ከአንድ ተቋም ጋር በሚፈጠሩ ችግሮች ዜጎች በአብዛኛው ፍትሕ አጥተው ለችግር ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡ ለእኛ የተወሰነው ውሳኔ ለዜጎች ተቆርቋሪነትን ያሳየና ፍትሕ ወይም መልካም አስተዳዳርን ያስፈነ በመሆኑ፣ እንደ አርዓያ መታየት ያለበት ይመስለኛል፤›› ሲሉ አቶ ሽመልስ በከተማው ከንቲባ የተደረገላቸውን ፍትሐዊ ዕርዳታ አወድሰዋል፡፡

ችግሩ ሊያስከትል የሚችለውን ማኅበራዊ ቀውስ በመረዳት የተቻለውን ጥረት በማድረግ ዜጎችን ከችግር ለማዳን የተደረገው ጥረት ውጤት በማስገኘቱ፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተደደር የነዋሪዎችን ደስታ መካፈሉ እንዳስደሰተው የአስተዳደሩ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ፍቃዱ በየነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ ቀበሌ 03 ወይም ከዚራ በሚባለው አካባቢ የኢትዮና የጂቡቲ ምድር ባቡር ኩባንያ ከ30 ዓመታት በፊት ለሠራተኞቹ ቤቶቹን መገንባቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ነገር ግን በድርጅቱና በሠራተኞቹ መካከል በቤቶቹ ጉዳይ ውዝግቡ ከደርግ ዘመን ጀምሮ እንደነበረ፣ የሠራተኞቹ ጡረተኞች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ አብዱሰላም ሁሴን ይናገራሉ፡፡ እሳቸውም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ላደረገላቸው እገዛ ምሥጋናቸውን ገልጸዋል፡፡

 

ባለሥልጣኑ ክሱን አልተቀበለውም

የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እየተካሄደ ያለው የመንገድ ልማት ዘርፍ ለሙስና የተጋለጠ ነው አለ፡፡ ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በሚያካሂዳቸው ሥራዎች ላይ ያካሄደውን ጥናት ባለፈው ሐሙስ ይፋ አድርጓል፡፡ 

ኮሚሽኑ ‹‹የመንገድ ልማትና የግንባታ ዘርፍ ለሙስናና ብልሹ አሠራር ያለው ተጋላጭነት›› በሚል ርዕስ ባቀረበው ጥናት፣ ተቋራጮች የተረከቡትን ሥራ ሳያጠናቅቁ ሌላ ሥራ ያገኛሉ ብሏል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪም የዲዛይን ሥራዎች በአግባቡ አለማከናወን፣ የጨረታ ሒደት ግልጽነት የጎደለው መሆኑ፣ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸው፣ በካሳ ክፍያ ወጥ የሆነ አሠራር አለመኖር ተጠቃሽ ችግሮች ሆነው ቀርበዋል፡፡ 

በዋናነት ጎልተው ከተነሱት ጉዳዮች መካከልም የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች በተደጋጋሚ ከተመሳሳይ አማካሪ ድርጅቶች ጋር እንዲሠሩ ተደርጓል የሚል ነው፡፡ 

ለዚህ እንደ አብነት የቀረቡት ሳትኮን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ከቤዛ ኮንሰልት ጋር በሁለት ፕሮጀክቶች መገናኘታቸው፣ ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ከኮኪር ኮንሰልት ጋር በተለያዩ ፕሮጀክቶች መሥራታቸው ነው፡፡ 

ነገር ግን ይህንን ጉዳይ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊዎችም ሆኑ ስማቸው የተጠቀሰው ኩባንያዎች አልተቀበሉትም፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊዎች እንዳሉት፣ ጨረታ ሲወጣ የብቃት ጉዳይ እንጂ እከሌ ተወዳዳር፣ ወይም አትወዳደር አይባልም፡፡ ኩባንያዎቹ ያካሄዷቸው ፕሮጀክቶች ሁሉ ጥሩ አፈጻጸም ያሳዩ ናቸው በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ሳትኮን ኮንስትራክሽን 12 ፕሮጀክቶች ይዟል የተባለው ትክክል እንዳልሆነ፣ ኩባንያው በአሁኑ ወቅት በእጁ አምስት ፕሮጀክቶች ብቻ እንደሚገኙና የኩባንያው የሥራ አፈጻጸምም መልካም ነው የሚል ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ ከሦስት ዓመታት ወዲህ ፕሮጀክት እንዳላገኘ ተገልጿል፡፡

ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽንም እንዲሁ የሚያካሂደው ግንባታ መጠናቀቅ ካለበት ጊዜ ቀድሞ በማጠናቀቅ የሚያስረክብ ኮንትራክተር በመሆኑ፣ ወቀሳው ተቀባይነት እንደሌለው ተገልጿል፡፡ 

የፀረ ሙስና ኮሚሽን የሙስና መከላከል ዋና አማካሪ አቶ ፈለቀወርቅ ኃይሌ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ከተነሱት ችግሮች በተጨማሪ፣ በትግራይ ክልል ከአዲ ረመጥ ጀምሮ እስከ ደጀናና ዳንሻ ድረስ የሚገነባው 97 ኪሎ ሜትር መንገድ በተያዘለት የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቁ ነው፡፡ 

ሁናን ሁንዳ የተባለው የቻይና የሥራ ተቋራጭ የሚገነባው ይህ መንገድ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቁ ከተያዘለት በጀት 35 በመቶ ያህል የገንዘብ ጭማሪ እንዲደረግ ማስደዱ ተገልጿል፡፡ አቶ ፈለቀወርቅ እንደሚሉት፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠር በጀት የሚመደብለት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ብዛት ያላቸው አካላትን የሚያሳትፍ በመሆኑ ለሙስና ተጋላጭ ነው፡፡ 

‹‹በቅድመ ግንባታ ወቅት፣ ከዲዛይን ጀምሮ ጥራቱን ያልጠበቀ መንገድ ገንብቶ እስከ ማስረከብ ድረስ ሙስና ይፈጸማል፤›› በማለት አቶ ፈለቀወርቅ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊዎች የቀረበውን ጥናት ሙሉ በሙሉ አልተቀበሉትም፡፡ ነገር ግን የአሠራር ማሻሻያ ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ አምነዋል፡፡ 

አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የባለሥልጣኑ የሥራ ኃላፊ በጥናቱ አቀራረብ ላይ ጥያቄ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ይኸውም ኮንትራክተርና ኮንሰልታንት በጨረታ ሒደት በሚገኝ ውጤት አብረው በተደጋጋሚ ሊሠሩ እንደሚችሉ፣ ዋናው ጉዳይ በፕሮጀክቶች ጥራት ላይ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ነው መገምገም ያለበት ይላሉ፡፡ ኮንትራክተርና ኮንሰልታንት ዛሬ ተዋውቀው ችግር መፍጠር እንደሚችሉ የጠቆሙት ኃላፊው፣ ጥናቱ በመንገዶች ግንባታ አፈጻጸም ላይ የታዩ ጉልህ የሚባሉ የጥራትና የመጓተት ችግሮች ላይ ቢያተኩር ጠቃሚ ነበር ብለዋል፡፡ 

የመንገድ ዘርፍ ልማት መርሐ ግብር ከተጀመረ የዛሬ 18 ዓመት ጀምሮ ከአንድ ሺሕ በላይ ኮንትራቶች መፈረማቸውን ገልጸው፣ ከእነዚህ መካከል እጅግ በጣም ጥቂት ምሳሌዎችን ነቅሶ በማውጣት ሙስና አለ ማለት ይከብዳል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ዋናው መተኮር ያለበት በመንገድ ዘርፍ አፈጻጸም ላይ የታዩ ዋነኛና መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መሆኑን ገልጸው፣ ጉልህ የሆኑ ግድፈቶች ሲኖሩ ነቅሶ ማውጣትና በግልጽ መነጋር የሚያግባባ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

 

የማዕድን ሚኒስቴር ስለኩባንያው ሽያጭና ዝውውር የቀረበልኝ ጥያቄ የለም ብሏል

ላለፉት ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ የፖታሽ ማዕድን ፍለጋና ማምረት ሥራ ይገባል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው አላና ፖታሽ ኩባንያ፣ እስራኤል ኬሚካልስ ለተባለ የእስራአል ኩባንያ በመሸጡ ምክንያት ሽያጭና ዝውውሩ ሰኞ ሰኔ 8 ቀን

2007 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ፡፡ ማዕድን ሚኒስቴርን ስለኩባንያው ዝውውር እስካሁን በይፋ የደረሰኝ መረጃ የለም ብሏል፡፡

አላና ፖታሽ ለኩባንያው ሠራተኞች ባለፈው ሳምንት ባስተላለፈው መልዕክት፣  ለእስራኤሉ ኩባንያ ዝውውር ተፈጻሚ እንዲሆን ከሁሉም የአላና ፖታሽ ባለአክሲዮኖች ድጋፍ በማግኘቱ የኩባንያው ዝውውር በይፋ ይካሄዳል ብሏል፡፡ የእስራኤሉ ኩባንያ  ከሰኞ ጀምሮ በይፋ ሥራ የሚጀመር መሆኑን በማረጋገጥ፣ በኢትዮጵያ የሚገኙት የአላና ፖታሽ የማኔጅመንት አባላትና ሠራተኞች አብረውት እንዲሠሩም የተላለፈው መልዕክት አመልክቷል፡፡

የኩባንያው ዝውውር ለአላና ፖታሽ ስኬታማነትን የሚያረጋግጥና ለድርጅቱ ሠራተኞችም መልካም አጋጣሚዎችን የሚፈጥር መሆኑን የሚጠቁመው መልዕክት፣ እስካሁን ያሉት ሠራተኞች ከእስራኤሉ ኩባንያ ጋር የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጦላቸዋል፡፡ አላና ፖታሽ 120 ያህል ሠራተኞች አሉት፡፡

የእስራኤሉ ኩባንያ አላና ፖታሽ ኩባንያ ያሉትን 300 ሚሊዮን አክሲዮኖች እያንዳንዳቸው በ0.50 የካናዳ ዶላር ዋጋ እንደገቸዛው ታውቋል፡፡ ይህም ከ150 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር በላይ ይሆናል፡፡ አላና ፖታሽ የተሸጠበት ይህ ዋጋ አላና ፖታሽ እስካሁን ለፕሮጀክቱ ካወጣው ወጪ አንፃር ሲታይ አትራፊ የሆነበትን የሽያጭ ገቢ እንዳገኘ የሚያመላክት ነው ተብሏል፡፡ 

የአላና ፖታሽ በአፋር ክልል በዳሎል ጠቅላላ የኢንቨስትመንት ወጪው ከ750 እስከ 800 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል ተብሎ ይገመት ነበር፡፡ ከእስራኤሉ ኩባንያ ጋር የሽያጭ ስምምነቱ እስከተፈጸመበት ጊዜ ድረስ አላና ፖታሽ ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጉን፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ነጅብ አባቢያ ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ የእስራኤል ኩባንያ አላና ፖታሽን ሙሉ በሙሉ ከመግዛቱ ቀደም ብሎ፣ የ16 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ለመውሰድ የሚያስችለውን ከ85 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች ግዥ ለመፈጸም ስምምነት ተደርሶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ እስራኤል ኬሚካልስ ኩባንያ ከ85 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለአላና ፖታሽ ገቢ ሳያደርግ በመቆየቱ ስምምነታቸው ሳይፈርስ እንዳልቀረ ተነግሮ ነበር፡፡ በመሀል ግን አላና ፖታሽ ለፕሮጀክቱ ኢንቨስትመንት የሚውል ካፒታል ለማሰባሰብ በሽርክና ሊሠሩ የሚችሉ ሌሎች አማራጮችን ወደማፈላለግ ገብቶ፣ ከሦስት ኩባንያዎች ጋር ድርድር በማድረግ በመጨረሻ ከእስራኤሉ ኩባንያ ጋር ስምምነት ላይ በመደረስ ግዥውን ሊፈጽም ችሏል፡፡ ይህም ስምምነት መጋቢት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ተፈጽሟል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር ግን የአላና ፖታሽን ሽያጭና ዝውውር የሚመለከት ምንም ዓይነት ይፋዊ የሆነ መረጃ ያልደረሰው መሆኑን ይገልጻል፡፡ የሚኒስቴሩ አንድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አላና ኩባንያውን ሸጫለሁ ስለማለቱ መረጃ ቢኖርም እስካሁን በሕጋዊ መንገድ ጥያቄ አለመቅረቡን ነው፡፡

‹‹እስካሁን ለእኛ የቀረበልን ነገር የለም፤›› ያሉት እኚሁ ኃላፊ፣ “አላና ፖታሽ ለእስራኤሉ ኩባንያ ሊተላለፍ መሆኑን የሚያመለክት ጥያቄ አላቀረበም፤” ብለዋል፡፡ በጆይንት ቬንቸር ለመሥራት ከሆነ በራሳቸው ስምምነት ሊፈራረሙ የሚችሉ ቢሆንም፣ ኩባንያውን ለሌላ ኩባንያ አስተላልፋለሁ ካለ ግን ጉዳዩ ለማዕድን ሚኒስቴር መቅረብ እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡

የዝውውሩ ጥያቄም ተቀባይነት የሚኖረው መጀመሪያ አላና ፖታሽ ግዴታውን የተወጣ መሆኑ ከተረጋገጠ ነው፡፡ ኩባንያው የሚተላለፍለት ድርጅት ሕጋዊ፣ የቴክኒክና የፋይናንስ ብቃት ያለው መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ነው ብለዋል፡፡ ኩባንያዎቹ በግላቸው የሚደርሱበት ስምምነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የኩባንያው ዝውውር የሚፈቀደው ማዕድን ሚኒስቴር ማረጋገጫ ሲሰጥ ብቻ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

አላና ፖታሽ ላከ በተባለው መልዕክት ላይ ኩባንያዎቹ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚደራደሩ መሆናቸው ጠቅሷል፡፡ የመጨረሻ የሽያጭ ርክክቡ በካናዳ ይካሄዳል የተባለ ሲሆን፣ መንግሥት የሚጠይቃቸውን ፎርማሊቲዎች ከርክክቡ በኋላ ሊከናውኑ ይችላሉ ተብሎ ተገምቷል፡፡ የእስራኤሉ ኩባንያ በዳሎል የሚገኘውን ፕሮጀክት ለረጅም ጊዜ እንደ ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክት የሚመለከተው መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ከሚገኘው የአላና ፖታሽ ቡድን ጋር በመሆን የፕሮጀክቱን ሥራ  እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በኩባንያው ይፋ በሆነው መረጃ መሠረት የእስራኤሉ ኩባንያ አላና ፖታሽን ሙሉ ለሙሉ ለመግዛት የወሰነው በቀጣይ በአፍሪካ፣ በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ገበያ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው  ተብሏል፡፡ ከኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የሚቀርበው የፖታሽ ማዕድን ምርት በዋነኝነት ለግብርና ማዳበሪያ ማምረቻ የሚጠቅም ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ለሚገነቡ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች በአገር ውስጥ ጥሩ ገበያ አለው ተብሎ ስለሚታመን ጭምር ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ማምረት ሲጀምር ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ መሆኑን የሚገልጸው በኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ፣ አሁን ባለው ገበያ በዓመት የፖታሽ ወጪ ንግድ ገቢው ከ400 እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሆን ይጠቁማል፡፡

የአላና ፖታሽ ፕሮጀክት ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም በመገንዘብ መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተለይ የፖታሽ ምርትን በዓለም ገበያ ለማቅረብ ይረዳሉ የተባሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን እያካሄደ ነው፡፡ ከደንከል-ጂቡቲ ታጁራ ወደብ ድረስ በመገንባት ላይ ያለው መንገድ ይጠቀሳል፡፡  

ተቀማጭነቱን ካናዳ ያደረገው አላና ፖታሽ በኢትዮጵያ ውስጥ ፖታሽ ለማምረት በአፋር ክልል በደንከል ዝቅተኛ አካባቢ የፖታሽ ፍለጋውን በስኬት በማጠናቀቁ፣ ከማዕድን ሚኒስቴር የፖታሽ ማዕድን የማውጣት ፈቃድ አግኝቶ ነበር፡፡ የፖታሽ ምርቱንም በዚህ ዓመት አውጥቶ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ የነበረው ሲሆን፣ ይህንን ሳያሳካ ኢንቨስትመንቱን ሸጧል፡፡ አላና ፖታሽ ይዞት የነበረው ዕቅድ ሳያሳካ ወደ ሽያጭ የገባው ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ወጪ ማሟላት ባለመቻሉ ነው፡፡ በተለይ የእስራኤሉ ኩባንያ እገዛዋለሁ ላለው የ16 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ይከፍላል ተብሎ የነበረውን ገንዘብ በወቅቱ ባለመክፈሉ ሌላ አማራጭ ፍለጋ ሊገባ እንደቻለም ይነገራል፡፡ አላና ፖታሽ በበኩሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፖታሽ ዋጋ ማሽቆልቆል ኩባንያውን ለመሸጥ እንዳስገደደው ይገልጻል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከዓመታት በፊት አንድ ቶን ፖታሽ ከ570 ዶላር በላይ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ 280 ዶላር ወርዷል፡፡ በካናዳ ባለው የፖታሽ ስቶክ ገበያም ከአራት ዓመት በፊት 2.8 ዶላር ይሸጥ የነበረው የአላና የአንድ አክሲዮን ዋጋ፣ አሁን ከ0.40 የካናዳ ዶላር በታች በመውረዱ አላና ፖታሽን ለመሸጥ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ እንዳደረገው ተነግሯል፡፡ አቶ ነጅብ እንደገለጹት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፖታሽ ዋጋ ዝቅ እያለ በመምጣቱ አላና ፖታሽ ሊሸጥ ችሏል፡፡ የእስራኤል ኩባንያ የሽያጩ ሒደት ስምምነት መፅደቁን ተከትሎ በፍጥነት ወደ ሥራ በመግባትና የቅድመ ግንባታ ጥናት በመጀመር፣ የፕሮጀክቱን የኢንጂነሪግ ዲዛይንና የቦታ መረጣ፣ የውኃ አቅርቦትና የትራንስፖርት ሎጂስቲክስ ሥራዎችን ተፈጻሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ፕሮጀክቱ ተፈጻሚ የሚሆንበትን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እንደሚመክርበት የኩባንያው መረጃ ያመላክታል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኘውን የአላና ፖታሽ የማኔጅመንት ቡድን የእስራኤሉ ኩባንያ  ሲረከብ ዓላማውንና የሥራ ድርሻውን በመግለጽ፣ ለአዲሱ ኩባንያ የሚያስረዳበትን ዝግጅት እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡

የእስራኤሉ ኩባንያ በንግድ ድርጅትነት በኒውዮርክ የአክሲዮን ገበያና በቴልአቪቭ አክሲዮን ገበያ የተመዘገበ ነው፡፡ የኩባንያውን የቅድመ ታሪክና ወቅታዊ አቋሙን በሚመለከት ባለፈው ሳምንት ለአላና ፖታሽ ሠራተኞች በተሠራጨው መልዕክት ላይ፣ እስራኤል ኬሚካልስ እ.ኤ.አ. በ2014 አጠቃላይ ገቢው ወደ 6.1 ቢሊዮን ዶላር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ኩባንያው በዋናነት በምግብ፣ በምህንድስና መገልገያ መሣሪያዎች ምርትና ሥርጭት ላይ የተሰማራ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በቀዳሚነት በፖታሽ፣ በፎስፌትና በብሮሚን ምርቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ የሚገኝ ሲሆን፣ በመላው ዓለም ከ30 በላይ በሚሆኑ አገሮች ይንቀሳቀሳል፡፡ 12,500 ያህል ሠራተኞች አሉት፡፡ የኩባንያው ጠቅላላ ሀብትም 12 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ የፖታሽ ምርትን በዓለም ገበያ ለማቅረብ በቅድሚያ ተነሳሽነቱን ያሳዩት የአላና ፖታሽ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ነጅብ አባቢያ፣ ወደ ኢንቨስትመንቱ ሲገቡ ተሰማርተው የነበሩት በወርቅ ማዕድን ፍላጋ ላይ ነበረ፡፡ ነገር ግን በመጨረሻ በአገሪቱ ያለውን የፖታሽ ማዕድን ዕምቅ ሀብት መኖሩን በጥናት በማረጋገጥ፣ ወደ ዘርፉ ፊታቸውን ሊያዞሩ መቻላቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ አቶ ነጅብ ኢትዮጵያ ውስጥ በጂኦተርሚል ኃይል ማመንጨት ኢንቨስትመንት ውስጥ ለመሥራት እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ይታወቃል፡፡

 

የዓለም ባንክ 150 ሚሊዮን ዶ

-ላር ሊያበድር ነው

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ለ2008 በጀት ዓመት፣ በታሪኩ ከፍተኛ የተባለውን የ12 ቢሊዮን ብር የበጀት ጥያቄ ሊያቀርብ እንደሆነ ተጠቆመ፡፡

ምንጮች እንደገለጹት፣ ባለሥልጣኑ ለ2008 በጀት ዓመት ለሚያከናወናቸው የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታዎች ያስፈልገኛል ያለውን የበጀት ጥያቄ፣ በሚቀጥለው ሳምንት ለከተማው የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ባለሥልጣኑ የጠየቀው በጀት እስካሁን ለከተማዋ የመንገድ መሠረተ ልማት ለአንድ የበጀት ዓመት ያስፈልገኛል ብሎ አቅርቧቸው ከነበሩ  የበጀት ጥያቄዎች ሁሉ ከፍተኛው እንደሆነ ታውቋል፡፡ 

ባለሥልጣኑ በ2007 በጀት ዓመት የ6.6 ቢሊዮን ብር በጀት ይዞ ሲንቀሳቀስ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አስተዳደሩ የፈቀደለት በጀት 6.1 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ቀሪውን ከመንገድ ፈንድና ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ያገኘው ነው፡፡ በ2006 ዓ.ም. ደግሞ 3.8 ቢሊዮን ብር በጀት ተፈቅዶለት እንደነበር ይታወሳል፡፡

ባለሥልጣኑ በመጪው ዓመት ለሚያስጀምራቸው በርካታ አዳዲስ መንገዶችና በግንባታ ላይ ለሚገኙ መንገዶች ማጠናቀቂያ፣ እንዲሁም ለአዳዲስ መንገዶች ዲዛይን ሥራዎች ይህንን ከፍተኛ የበጀት ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል፡፡

በአስተዳደሩ ሥር ካሉ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ከፍተኛ የሚባለውን በጀት የሚያገኘው የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ለ2008 በጀት ዓመት   ያስፈልገኛል ብሎ የሚጠይቀውን 12 ቢሊዮን ብር አስተዳደሩ ሙሉ ለሙሉ ይደግፈዋል ተብሎ እንደማይገመት ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ ባለሥልጣኑ ከዚህ ቀደም ለ2008 በጀት ዓመት ያቀረበውን ያህል አይሁን እንጂ፣ ከፍተኛ የተባለ በጀት ጠይቆ ከጠየቀው በጀት ግማሽ ያህሉ የተፈቀደለት ጊዜ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም ባንክ ለመንገድ መሠረተ ልማትና ለአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ማሻሻያ ፕሮግራም የሚውል የ150 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመፍቀድ የተስማማ መሆኑ ታውቋል፡፡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደገለጹት፣ የዓለም ባንክ በመንገድና በትራንስፖርት ዘርፍ ለአስተዳደሩ ብድር ሲፈቅድ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡  ከዓለም ባንክ በሚገኘው ብድር በዋነኝነት የመንገድና የትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎቶችን ለማቀላጠፍ በሚያስችሉ መሠረተ ልማት ሥራዎች ላይ የሚውል ነው ተብሏል፡፡ ብድሩ ሙሉ በሙሉ ከመለቀቁ በፊት ብድሩ ለታቀደለት ዓላማ እንዲውል ለሥራዎች ማስጀመርያ 4.5 ሚሊዮን ዶላር የተሰጠ መሆኑም ታውቋል፡፡ ዋናው ብድር በሚቀጥለው ዓመት እንደሚለቀቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ከዓለም ባንክ ብድር በተጨማሪ በ2008 በጀት ዓመት ከውጭ የፋይናንስ ምንጮች በሚገኝ ብድር የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችም አሉ ተብሏል፡፡ በተለይ ጃፓን ለአዲስ አበባ የመንገድ ጥገና ሥራና ለአሴት ማኔጅመንት የሚውል የሚውል ብድር መፍቀዷ ታውቋል፡፡ ፈረንሣይና ቻይናም ለአዲስ አበባ መንገድ መሠረተ ልማት የሚውል በተመሳሳይ ብድር ለመስጠት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይነገራል፡፡ ከእነዚህ የፋይናንስ ምንጮች የሚገኘው ገንዘብ በ2008 ዓ.ም. የአስተዳደሩ በጀት ውስጥ ተካቶ የሚቀርብ እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 

አስተዳደሩ ለመንገድ ዘርፍ ከውጭ የፋይናንስ ምንጮች ይህንን ያህል ገንዘብ አግኝቶ እንደማያውቅ፣ ከዚህ በኋላም እንደ ዓለም ባንክ ያሉ አበዳሪዎች ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ግንባታ የሚውል ብድር እንዲሰጡ የሚያስችል ፕሮጀክቶች እየተሠሩ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ተሾመ

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሱር ኮንስትራክሽን ኩባንያ የኮንስትራክሽን ዲፓርትመንት ኃላፊ የነበሩትን ኢንጂነር አርዓያ ግርማይ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አድርጐ ሾመ፡፡ 

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ፊርማ የወጣው ደብዳቤ፣ አቶ አርዓያ ከሰኔ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው መሾማቸውን ይገልጻል፡፡ 

ኢንጂነር አርዓያ በዋና ዳይሬክተርነት መሾማቸውን ለሪፖርተር አረጋግጠው፣ መንግሥት በመንገድ ልማት ዘርፍ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ 

ኢንጂነር አርዓያ በ1987 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ትምህርት መስክ ተመርቀዋል፡፡ ከትምህርት ዓለም በኋላ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከጌዶ – ፊንጫ ድረስ ባካሄደው የመንገድ ግንባታ የፕሮጀክት ኃላፊ ሆነው መሥራታቸው ታውቋል፡፡

ኢንጂነር አርዓያ በ1999 ዓ.ም. በኤፈርት ሥር ተቋቁሞ በሥራ ላይ የሚገኘውን ሱር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተቀላቅለዋል፡፡ 

የሱር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ታደሰ የማነ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢንጂነር አርዓያ በ1999 ዓ.ም. ኩባንያውን እንደተቀላቀሉ በሰሜን ጎንደር ከሻውራ – ገለጎ ድረስ ለተገለነባው 147 ኪሎ ሜትር መንገድ የፕሮጀክት ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ 

‹‹ይህ መንገድ እጅግ አስቸጋሪ የነበረ ሲሆን፣ ኢንጂነር አርዓያ ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገበበት ነው፤›› በማለት ምስክርነታቸውን አቶ ታደሰ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በኋላም ከመነቤኛ – ለምለም በረሃ የተገነባውን መንገድ ጨምሮ አራት የመንገድ ፕሮጀክቶችን መርተው በስኬት ማጠናቀቃቸውን ኢንጂነር ታደሰ አስረድተዋል፡፡ 

ኢንጂነር አርዓያ የአሁኑ ሹመት እስኪሰጣቸው ድረስ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የሚያስገነባውን የዛሪማ ግድብ በኃላፊነት እየመሩ፣ ውጤታማ ሥራ መሥራታቸውን ኢንጂነር ታደሰ ገልጸዋል፡፡

‹‹ኢንጂነር አርዓያ ካሉን የፕሮጀክት ኃላፊዎች መካከል በውጤታማነታቸው ከሚታወቁት አንዱ በመሆኑ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት አምጥተን ለከፍተኛ ኃላፊነት አጭተነው ነበር፤›› በማለት የሚናገሩት ኢንጂነር ታደሰ፣ መንግሥት ለበለጠ ከፍተኛ ኃላፊነት ስለመረጣቸው ምንም ማድረግ አለመቻላቸውን የኢንጂነር አርዓያን ብቃት በማድነቅ ገልጸዋል፡፡ 

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ላለፉት አሥር ዓመታት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉትን አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤልን፣ ከጥቅምት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ማሰናበቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ በቀለ አቶ ዛይድን በመተካት የራሳቸውን ሥራ ጨምረው ላለፉት ስምንት ወራት በተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ሳምንት ኢንጂነር አርዓያ ሥራቸውን ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡   

 

በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ለማስቀረት አንድ ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል

በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙ 12 የኦሮሚያ ክልል ልዩ ዞን ከተሞች በየጊዜው የሚገጥማቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ለማስቀረት ማስተር ፕላን ተነደፈ፡፡ አዲሱን ማስተር ፕላን ተግባራዊ ለማድረግ አንድ ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡

‹‹አዲስ አበባና ዙሪያዋ የኤሌክትሪክ ዲስትሪቢውሽን ማስተር ፕላን ጥናት ፕሮጀክት›› በሚል ስያሜ የተነደፈው ማስተር ፕላን፣ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡ 

ባለፈው ሐሙስ ሰኔ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በማስተር ፕላኑ ላይ ውይይት በተደረገበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ እንደተናገሩት፣ እ.ኤ.አ. እስከ 2017 ድረስ ተግባራዊ በሚደረገው የአጭር ጊዜ ዕቅድ አሮጌ ኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ይለወጣሉ፡፡ 

በአጠቃላይ ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ አንድ ቢሊዮን ዶላር በጀት መያዙ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ውስጥ እ.ኤ.አ. እስከ 2017 ለሚተገበረው የአጭር ጊዜ ዕቅድ ማስፈጸሚያ 285 ሚሊዮን ዶላር፣ እ.ኤ.አ. ከ2018 እስከ 2022 ተግባራዊ ለሚሆነው መካከለኛ ዘመን ዕቅድ ማስፈጸሚያ 37 ሚሊዮን ዶላር፣ ለረዥም ጊዜ ዕቅድ ማስፈጸሚያ (እ.ኤ.አ. ከ2023 እስከ 2034) 745 ሚሊዮን ዶላር መበጀቱ ተገልጿል፡፡ 

በአጠቃላይ በአዲስ አበባና አካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትና ዕድገት ለማጣጣም የተያዘውን ዕቅድ ለማስፈጸም፣ 1,067 ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል ተብሎ ተገምቷል፡፡ 

ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚደረገው በአዲስ አበባ በሚገኙት አሥር ክፍላተ ከተሞችና በኦሮሚያ ልዩ ዞን በሚገኙት አዲስ ዓለም፣ ኢሉ፣ ወልመራ፣ ሙሎ፣ ሱሉልታ፣ በረህ፣ አሌልቱ፣ ጊምቢቹ፣ አደአ፣ አቃቂ፣ ዓለም ገና፣ ቀርሳና ማሊሞ ወረዳዎች ናቸው፡፡ 

አዲስ አበባና ዙሪያዋ አገሪቱ ከምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ 60 በመቶውን እንደሚጠቀሙ ኢንጂነር አዜብ ገልጸው፣ አካባቢዎቹ የሚያጋጥማቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርጭት መቆራረጥ ለማስቀረት የፕሮጀክቱ ተግባራዊ መሆን ወሳኝ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ 

ይህንን ማስተር ፕላን ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ 3.5 ሚሊዮን ዶላር ያጠናው የእንግሊዝ ኩባንያ የሆነው ፓርሳን ብሪንኤርሆፍ ሊሚትድ ነው፡፡ የኩባንያው ተወካይ ናንካ ብሩስ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት፣ አዲስ አበባ በፍጥነት እያደገች በመሆኑ እያጋጠማት ካለው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ወጥታ፣ ለዕድገቷ የሚያስፈልጋትን ኃይል ለማግኘት ማስተር ፕላኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ 

ይህ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሲሆን፣ በከተማው የሚገኙ አሮጌ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያዎች በአዲስ ይተካሉ፡፡ መሻሻል ያለባቸውም እንዲሻሻሉ ይደረጋል በማለት ኢንጂነር አዜብ ተናግረዋል፡፡ 

በቀጣይነት ይህ ፕሮጀክት በሐዋሳ፣ በመቐለ፣ በባህር ዳርና በሌሎች ትልልቅ የክልል ከተሞች ተግባራዊ እንደሚሆን ኢንጂነር አዜብ አስረድተዋል፡፡ 

በአዲስ አበባና በአካባቢው ለረጅም ጊዜ እያጋጠመ ያለው የኃይል መቆራረጥ፣ በዋናነት በኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያና ማሠራጫ ጣቢያዎች እርጅና ምክንያት ነው ሲባል ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ወራት ወዲህ ለኃይል መቆራረጡ የበልግ ዝናብ በተፈለገው መጠን ባለመዝነቡ ምክንያት፣ ግድቦች በቂ ውኃ ባለመያዛቸው እንደሆነ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው፡፡ 

 

አውሮፓ ኅብረት ለኤርትራ ቃል የገባው የ312 ሚሊዮን ዩሮ ዕርዳታ እንዲታገድ ጀርመን ጠየቀች

በቅርቡ አውሮፓ ኅብረት ለኤርትራ በዕርዳታ መልክ ሊሰጠው የወሰነው 312 ሚሊዮን ዩሮ ዕርዳታ እንዲታገድ፣ የጀርመን ፓርላማ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

ሰኔ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. የጀርመን የፓርላማ አባላት ባደረጉት ስብሰባ፣ ሰሞኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኤርትራ ሰብዓዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን ያወጣውን ባለ 484 ገጾች ሪፖርት ይዘት አስመልክቶ ከተወያዩ በኋላ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአስመራ መንግሥት ላይ ጠንካራ ዕርምጃ እንዲወስድ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ፓርላማው በኤርትራ ላይ የወጣውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርት ዝርዝር ለአንድ ሰዓት ያህል ከተወያየበት በኋላ፣ በተለይ ጀርመን ዋነኛ አስኳል የሆነችበት የአውሮፓ ኅብረት ከጥቂት ወራት በፊት ለኤርትራ እ.ኤ.አ. እስከ 2020 በዕርዳታ ሊሰጠው ያቀደው የልማት ድጋፍ እንዲታገድ በፅኑ ጠይቋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን የኤርትራን ልማት ለመደገፍ በሚቀጥሉት አምስት ዓመት ውስጥ ለመስጠት ቃል የገባው ዕርዳታ 312 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡ ሒውማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ማኅበር፣ ‹‹የአስመራ መንግሥትን መርዳት በኤርትራ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲቀጥል ማድረግ ነው፤›› በማለት በተመሳሳይ አቋም መቃወማቸው ይታወሳል፡፡

 በኤርትራ ያለውን ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያጋለጠው የተመድ የሰብዓዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን ሪፖርት ከመውጣቱ ቀደም ብሎ፣ ከ20 በላይ የኤርትራ የሚዲያ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰቦችና ተቃዋሚዎች ይህንን የአውሮፓ ኅብረትን ውሳኔ ተቃውመዋል፡፡ የድጋፍ ድምፅ ፊርማ በማሰባሰብ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ማቅረባቸውም ይታወሳል፡፡

ስዊድን ቀደም ሲል በኤርትራ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ ያለቻቸውን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ፣ የተለያዩ የሲቪልና የወታደራዊ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት እንዲያዙ መወሰኗ አይዘነጋም፡፡

የተመድ የሰብዓዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን በ484 ገጾች ባወጣው ሪፖርት፣ የኤርትራ መንግሥት በዜጎች ላይ የሚፈጽማቸው የሰብዓዊ መብት ጥቃቶች ሆን ተብለውና ታስቦባቸው የሚፈጸሙ ናቸው ብሏል፡፡ ድርጊቱም በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው በማለት ያትታል፡፡ 

‹‹የኤርትራ መንግሥት ሕዝቡ ውስጥ በርካታ ሰላዮችን በማስረግ ዜጎችን ይሰልላል፡፡ በሕገወጥ መንገድ ዜጎችን በማሰር የፈለገውን ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በመደፍጠጥ ነፃነት እንዳይሰማቸው ያደርጋል፡፡ ተቃውሞ ያስነሳሉ ወይም የተለየ አስተሳሰብ ያንፀባርቃሉ ተብሉ የሚጠረጠሩ ግለሰቦች ለእስር ይዳረጋሉ፡፡ አንዳንዶቹ የት እንደደረሱ ሳይታወቅ ይሰወራሉ…›› ይላል፡፡

 በኤርትራ ወታደራዊ አገልግሎት ከባርነት እንደማይተናነስና ሴቶች ለወሲብ ባርነት እንደሚዳረጉ ሪፖርቱ አመልክቶ፣ ሕዝቡ በፍርኃትና በድንጋጤ ውስጥ ነው የሚኖረው ብሏል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ግን ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ የአጣሪ ኮሚሽኑን ሪፖርት መሠረተ ቢስ በማለት አጣጥሎታል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ የግብፅና የሱዳን የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ካይሮ ሊገናኙ ነው

የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን መንግሥታት የታላቁ የህዳሴ ግድብን ለመገምገም የቋቋሙት የቴክኒክ ኮሚቴ ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. በካይሮ እንደሚገናኙ ተሰማ፡፡

የቴክኒክ ኮሚቴው ከእያንዳንዱ አገር አራት ባለሙያዎች የተወከሉበት ሲሆን፣ ዓላማውም ከዚህ ቀደም ግድቡን የገመገመው ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ሦስቱ አገሮች በጋራ እንዲተገብሯቸው ያቀረቧቸውን ሁለት ምክረ ሐሳቦች ዕውን ማድረግ ነው፡፡ ሁለቱን ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ በወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ከተወዳደሩት አምስት ኩባንያዎች መካከል፣ ሁለት ኩባንያዎች ማለትም የፈረንሣዩን ቢአርኤል ግሩፕና የኔዘርላንዱ ዴልታሪዝ በመጨረሻ መቅረታቸው ይታወሳል፡፡

በሚያዝያ ወር በአዲስ አበባ የተገናኙት የሦስቱ አገሮች የኮሚቴ አባላት ሁለት ቀናት የፈጀ ውይይት በማድረግ የፈረንሣዩ ቢኤርኤል ግሩፕ አጠቃላይ ጥናቶችን በበላይነት እንዲያከናውን፣ የኔዘርላንዱ ዴልታሪዝ ደግሞ ከፈረንሣዩ ኩባንያ የተወሰኑ ሥራዎች እንዲሰጠው ተስማምተዋል፡፡

በዚህ ውሳኔ መሠረት ሁለቱ ኩባንያዎች ውሳኔውን እንዲያውቁት ከተደረገ በኋላ፣ ረዥም ቀናት ፈጅተው በግንቦት ወር የቴክኒክ ሰነድ ለኮሚቴው አስረክበዋል፡፡

ይኼ ሰነድ ምን እንደሚያትት ባይታወቅም፣ የሦስቱ አገሮች የኮሚቴ አባላት በዚሁ የቴክኒክ ሰነድ ላይ ከሰኞ ጀምሮ እንዲሚወያዩ ታውቋል፡፡

የዓለም አቀፍ አጥኚዎች ቡድን ቀደም ሲል የሰጠው ምክረ ሐሳብ የግድቡ ኃይድሮ ሲሙሌሸን ሞዴል ማለትም ግድቡ ውኃ የሚይዝበትና የሚለቅበት በተለያዩ የዝናብ ወቅቶች ምን መሆን አለበት የሚለው አንዱ ሲሆን፣ የግድቡ ግንባታ በሦስቱ አገሮች ላይ ሊፈጥረው የሚችለውን የአካባቢያዊና የማኅበራዊ ጥናት ተፅዕኖ ግምገማ ደግሞ ሁለተኛው ምክረ ሐሳብ ነው፡፡

 

ሕልመኛው አውሮፕላን ሠሪ

ከ19 ወራት ያላነሰ ጊዜ የፈጀችውና በሰንዳፋ ዳቢ ጊዮርጊስ ሜዳ ላይ ተንደርድራ ልትበር የነበረችው አነስተኛ አውሮፕላን ባጋጠማት ብልሽት ሳትበር ቀረች፡፡ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ለበረራ ዝግጁ ትሆናለች ተብሏል፡፡ 

ትውልዱ ትግራይ ክልል ዋጅራት አካባቢ ነው፡፡ ያደገው ሐዋሳ ሲሆን የተማረው በአለማያ (ሐሮማያ) ዩኒቨርሲቲ የጤና መኮንንነት ነበር፡፡ ይህን የተማረው አማራጭ ስላጣ እንጂ የልጅነት ሕልሙ አውሮፕላን አብራሪ መሆን እንደነበረ ይናገራል፡፡ 

የ35 ዓመቱ አስመላሽ ዘፈሩ ከ14 ዓመታት በፊት የጤና መኮንን ለመሆን ያስገደደውን አጋጣሚ ለሪፖርተር የገለጸው፣ ለመሥራት አንድ ዓመት ከሰባት ወራት የፈጀችበትን አውሮፕላን ለማብረር እየተዘጋጀ በነበረበት ወቅት ነበር፡፡ አስመላሽ  አውሮፕላን ለማብረር ከልጅነቱ ጀምሮ ሲመኝ ኖሯል፡፡ በትምህርቱ አጥጋቢ ውጤት አምጥቶ ዩኒቨርሲቲ ቢገባም፣ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የበረራ ትምህርት የማይሰጥ በመሆኑ የጤና መኮንንነትን ለማጥናት ተገዷል፡፡ ይህም ሆኖ በድሬዳዋ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአብራሪዎች ምልመላ ሲያካሂድ ተመዝገቦ ቢቀርብም፣ ቁመትህ በሚፈለገው ልክ አይደለም ተብሎ ሳይመረጥ መቅረቱን ይናገራል፡፡ 

‹‹ቁመትህ አንድ ሳንቲ ሜትር አጥሯል ተብዬ የአብራሪነት ሕልሜ ሳይሳካ ቀረ፤›› የሚለው አስመላሽ፣ ከ21 ዓመት ዕድሜው ጀምሮ የራሱን አውሮፕላን ሠርቶ የማብረር ፍላጎት እንዳደረበት ተናግሯል፡፡ በዚህ አኳኋን ከጤና መኮንንነት ሙያው ባሻገር የምህንድስና ትምህርት በማታው ክፍለ ጊዜ በመከታተልና ስለአውሮፕላን አሠራር በማጥናት በመጨረሻም ‹‹K-570A›› የሚል ስያሜ የሰጣትንና ሁለት ሰው ማሳፈር የምትችል የድሮ ሞዴል አውሮፕላን ሠርቶ ለማብረር ተቃርቦ ነበር፡፡ ከእናቱ ወይዘሮ ኪሮስ ስም የመጀመርያ የእንግሊዝኛ ፊደል በመውሰድና አውሮፕላኑን ለመሥራት የፈጁበትን 570 ቀናት፣ እንዲሁም ‹‹ኤርክራፍት›› ከሚለው ፊደል የመጀርያውን ተጠቅሞ ለአውሮፕላኑ ስያሜ ሰጥቷል፡፡ 

ባለፈው ሐሙስ ሰኔ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. አውሮፕላኗን ከአዲስ አበባ በ40 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ሰንዳፋ ከተማ፣ ዳቢ ጊዮርጊስ በተባለ ሜዳ ላይ አንደርድሮ ለማብረር ዝግጅት በማድረግ ላይ ሳለ፣ ሁለት ጊዜ በተሰበሩበት የአየር መቅዘፊያዎች ምክንያት በረራውን ሳያካሄድ ቀርቷል፡፡ አየር መቅዘፊያውን በጥቂት ቀናት ውስጥ በመሥራት ለሞት አደጋ ሊያጋልጠው የሚችለውን አስፈሪ በረራ በድጋሚ ለመሞከር መወሰኑን አስታውቋል፡፡ 

የመትረፍ ዕድሉ ግማሽ በግማሽ እንደሆነ የሚገልጸው አስመላሽ፣ እስካሁን እልህ አስጨራሽ ጉዞ ማድረጉንና ያለውን ነገር ሁሉ አሟጦ በአቅሙ መሥራት የቻለውን አውሮፕላን ዕውን ማድረጉን በመግለጽ ከማብረር እንደማይመለስ ይፋ አድርጓል፡፡ ለሠራው አውሮፕላን 160 ሺሕ ብር ማውጣቱን፣ ከዚህ አውሮፕላን ውጪ ምንም ነገር እንደሌለው፣ ሙሉ ጊዜውን አውሮፕላን ለመሥራት ሲል ከሥራ ገበታው ራሱን ማግለሉን አስመላሽ ይናገራል፡፡ ከወዳደቁ ቁሳቁሶች፣ 40 የፈረስ ጉልበት ካለው የቮልስ ዋገን ሞተር፣ ከእንጨት፣ ከብረት፣ ከሱዙኪ ሞተር ብስክሌት ጎማዎች፣ ከአልሙኒየምና ከመሳሰሉት ቁሳቁሶች የሠራት አውሮፕላን አንዴ ከበረረች በኋላ ዳግመኛ ስለማትበር ሙዚየም የምትገባ መሆኗን ገልጿል፡፡ የቅርብ ጊዜ ህልሙ ናይጄሪያዊው ወጣት ከውድቅዳቂዎች የሠራትንና በአራት ሜትር ከፍታ ላይ ያበረራትን አውሮፕላን በመብለጥ፣ ተጨማሪ ሜትሮችን ወደ ሰማይ በመንሳፈፍ ለማብረር አቅዷል፡፡ 

እጁን ካፍታታባትና ሙሉ በሙሉ ሜካኒካል በሆነ መንገድ ከምትሠራው አውሮፕላን በተጨማሪ፣ ዲጂታል የሆነና አራት ሰዎችን ማሳፈር የሚችል ዘመናዊ አውሮፕላን የመሥራት ሕልም የሰነቀው አስመላሽ፣ በሰንዳፋ የሠራትን አውሮፕላን ለማበረር ሲሰናዳ የሕይወት አድን ጃኬትም ሆነ ከአየር መዝለያ ፓራሹት አልታጠቀም ነበር፡፡ የሞተር ብስክሌት ሔልሜት በአናቱ ላይ ከማጥለቁ በቀር ለአውሮፕላን አብራሪ የሚመጥን ምንም ዓይነት ቅድመ ዝግጅት አይታይበትም፡፡ ይህ ሁሉ አቅም ስለሌለው እንጂ ሳያስፈልገው ቀርቶ እንዳልሆነ ይገልጻል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የሠራት አውሮፕላን በርካታ ማሟላት የሚገባት መሠረታዊ ነገሮች እንደሚቀረም ያምናል፡፡ ይህም ሆኖ አሥር ሜትር ያህል አብርሮ ለማሳረፍ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጎባት ነበር፡፡ 

የአስመላሽ አባት አቶ ዘፈሩ፣ ከ90 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸውና የ11 ልጆች አባት ሲሆኑ፣ አሥረኛው ልጃቸው አስመላሽ ራሱ በሠራው አውሮፕላን እየሩሳሌም እንደሚወስዳቸው ከልጅነቱ ጀምሮ ይነግራቸው እንደነበር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አስመላሽን ጨምሮ አብዛኞቹ ልጆቻቸው በሰማይ ላይ መብረርን አጥብቀው የሚመኙ፣ የራሳቸውን መኪና ለመሥራት ሲጥሩ የነበሩ መሆናቸውን ገልጸው፣ አንድ ቀን እየሩሳሌምን የመጎብኘት ሕልማቸው በልጃቸው እንደሚሳካ ተስፋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ልጃቸው በሠራት አውሮፕላንም ከመደሰት በላይ ለአገሩ የሚያኮራ ሥራ መሥራቱን እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡ 

  

 

ለቀላል ባቡሩ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያሰራጩ ጣቢያዎች ሥራ ጀመሩ

ለአዲስ አበባ የቀላል ባቡር መስመር ከብሔራዊ ኃይል ማሰራጫ በመሳብ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያዳርሱ አራት ሰብስቴሽኖች ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመሩ፡፡ በአያት አደባባይ አቅራቢያ ሲገነባ ቆይቶ የተጠናቀቀውን ኃይል

ማሰራጫ ሰብሰቴሽን፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኪኖሚ ክላስተር አስተባባሪ፣ የመገናኛና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ  ግንቦት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ሥራ አስጀምረዋል፡፡ 

በስድስት ወራት ውስጥ ግንባታቸው ያለቀው አራት ሰብስቴሽኖች በጠቅላላው 160 ሜጋ ዋት ኃይል ለከተማው ባቡር የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ ለባቡሩ መስመር ግንባታ ከተመደበው 470 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ በ85 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነቡት እነዚህ የኃይል ማሰራጫዎች በአያት፣ በምንሊክ አደባባይ፣ በጦር ኃይሎችና በቃሊቲ አካባቢ ተገንብተው ዝግጁ ሆነዋል፡፡ 

የሰብስቴሽኖቹን ግንባታ ያከናወነው የቻይናው ናሽናል ግሪድ ኩባንያ በእህት ኩባንያው ቻይና ኤሌክትሪካል ኤንድ ኢንጂነሪንግ ቴክኖሎጂ በኩል አከናውኗል፡፡ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ለጋዜጠኞች እንዳብራሩት፣ ለባቡሩ ኃይል የሚያቀርቡት ማከፋፈያዎች በቀጥታ ከዋናው ማሰራጫ እንዲቀበሉ በማድረግ ምንም ዓይነት የኃይል መቆራረጥ እንዳያጋጥማቸው የራሳቸው መስመር ተዘርግቶላቸዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ለባቡሩ የሚያቀርቡት ማከፋፈያዎች ሙሉ ለሙሉ ግንባታቸው ተጠናቆ ቢዘጋጁም፣ በቀጥታ ወደ ባቡሩ ለማድረስ የሚስችሉ ዝርጋታዎች በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡ ኢንጂነር አዜብ በበኩላቸው ከማከፋፈያዎቹ ኃይል ተቀብለው ለባቡሩ የሚያደርሱ ኬብሎች ቀበራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ይፋ አድርገዋል፡፡ 

ምንም እንኳ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ በፍጥነት ግንባታቸው ተጠናቋል ቢባልም፣ የተወሰነ መዘግየት እንዳጋጠመና ይህም ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ መሆኑን ዶ/ር ደብረ ጽዮንና ኢንጂነር አዜብ ይፋ ተናግረዋል፡፡ የኃይል ማከፋፈያዎቹ ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ደምሰው ዘለቀ በበኩላቸው፣ ለኃይል ማከፋፈያ ግንባታ ማካሄጃ የሚያስፈልጉትን ቦታዎች ማግኘት የተቻለው፣ በዚህ ዓመት ኅዳር ወር ውስጥ እንደነበርና ምንም እንከን ሳያጋጥም ሥራው ተጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የከተማው ቀላል ባቡር አገልግሎት ለመጀመር ፍተሻዎች እየተካሄዱ እንደሚገኙ የገለጹት ዶ/ር ደብረ ጽዮን፣ እየተካሄዱ የሚገኙት ሙከራዎችና ፍተሻዎች መጠናቀቅ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡ ባቡሩ በየትኛውም ጊዜ ሊጀምር ዝግጁ ቢሆንም፣ የሚካሄዱበት ሙከራዎች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ለሚዘረጋው የባቡር መስመር በ100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እየተገነባ ለሚገኘው መስመርም ስቴትግሪድ የተሰኘው የቻይና ኩባንያን ጨምሮ አራት ተቋራጮች ኮንትራቱን ወስደው እየገነቡት እንደሚገኝ የገለጹት ዶ/ር ደብረ ጽዮን፣ በመጪው ዓመት የአዲስ-ጂቡቲ መስመር ተጠናቆ እንደሚመረቅ ይፋ አድርገዋል፡፡ 

ኢንጂነር አዜብ በበኩላቸው፣ በመጪው ዓመት ጥር ወር ይጀመራል ተብሎ በሚጠበቀው የባቡር ኃይል ማሰራጫ ግንባታ የጂቡቲ መንግሥት የሚያካሂደውን ግንባታ እኩል መጀመርና ማጠናቀቅ እንደሚጠበቅበት ስምምነት መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ 

በአዲስ አበባና በጂቡቲ መካከል የሚዘረጋው የባቡር መስመር በየቀኑ 1,500 የጭነት ተሽከርካሪዎች የሚያደርጉትን ምልልስ በመቀነስ፣ ሁለት ቀናት ይፈጅ የነበረውን ጉዞም ወደ አሥር ሰዓት ዝቅ በማድረግ፣ የገቢና የወጪ ንግዱን እንደሚያቀላጥፍ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ 752 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የአዲስ አበባ -ጂቡቲ መስመር ከቻይና መንግሥት በተገኘ ፋይናንስ በቻይና ኩባንያዎች በመገንባት ላይ ነው፡፡

 

 

 

ኢዴፓ ምርጫው ተዓማኒ አይደለም አለ

ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና በኅብረተሰቡም ዘንድ ተዓማኒ አልነበረም በማለት፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ተቃውሞውን አሰማ፡፡ በዚህ ምክንያትም የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበለው አስታውቋል፡፡ 

በተደጋጋሚ ሲያጋጥሙ የነበሩ እንቅፋቶችና ችግሮች በምርጫው ፍትሐዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነትና ተዓማኒነት ላይ ችግር እየፈጠሩ መሆናቸውን በማሳሰብ በቅድመ ምርጫ ወቅት የገጠሙን ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም፣ ችግሮቻቹ መፍትሔ እንዳላገኙ ኢዴፓ ጠቁሟል፡፡ ‹‹ችግሮቹ ከመፈታት ይልቅ ይበልጥ በመባባስና ታቅዶ የሚፈጸም በሚመስል ሁኔታ ጫናዎች የፓርቲያችንን እንቅስቃሴ በሚፈታተን ደረጃ ተጠናክረው ቀርበዋል፤ ያለው ፓርቲው፣ በቅድመና በድኅረ ምርጫ ገጠሙኝ በማለት የነቀሳቸውን 22 ተግዳሮቶች በባለ አራት ገጽ መግለጫው ውስጥ አካቷል፡፡ 

ፓርቲው ይህን ያስታወቀው ግንቦት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ሲሆን፣ መግለጫውን የሰጡት ደግሞ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደና ሌሎች የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ናቸው፡፡  

ፓርቲው በቅድመ ምርጫውና በምርጫው ዕለት አጋጠሙኝ ካላቸው ችግሮች መካከል የዕጩዎች መዋከብ፣ ከሥራ ገበታቸው መፈናቀል፣ ከዕጩነት ራሳቸውን እንዲያገሉ ማስፈራራት፣ በአካባቢያቸው የፀጥታ ችግሮች ቢፈጠሩ ተጠያቂ እንደሚሆኑ በመግለጽ ማሸማቀቅ፣ መደለያ መስጠት፣ ማሰር፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች በግልጽ የኢሕአዴግ የመወዳደርያ ምልክት ያለበትን ካኔቴራ ለብሰው ኢሕአዴግን ምረጡ በማለት በአደባባይ ሲቀሰቅሱ ምርጫ ቦርድ በዝምታ መመልከቱ፣ እንዲሁም ተቃዋሚዎች ፀረ ሰላምና የልማት ሒደታችንን ያደናቀፉ ኃይሎች ናቸው በማለት በአንድ ለአምስት አደረጃጀት በየመንደሩ የጥላቻ ሐሳቦችን በኅብረተሰቡ ውስጥ መበተን ተጠቃሾች ናቸው ሲል ኢዴፓ ገልጿል፡፡

በተጨማሪም ታዛቢዎችን በመደለል እንዳይታዘቡ ማድረግ፣ ማስፈራራትና ይህን ሁሉ ተቋቁመው ወደ ምርጫ ጣቢያ የሄዱትን ማባረርና ማሰር፣ በምርጫ ጣቢያ ውስጥ የታጠቁ የፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት በመገኘት መራጩን ሕዝብ በማሸማቀቅ ተፅዕኖ ውስጥ መክተት፣ እንዲሁም በቅሬታ አቀራረብ ደንብና አሠራር መሠረት ቅሬታዎችን ለመቀበል በየትኛውም ደረጃ ያሉ የምርጫ አስፈጻሚ አካላት ፈቃደኛ አለመሆናቸው በምርጫው ዕለት የገጠሙት ችግሮች እንደሆኑ ኢዴፓ አስታውቋል፡፡ 

‹‹በሒደቱም ሆነ በምርጫው ዕለት የተፈጸሙትን ድርጊቶች በነቂስ የመረመረው የኢዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ምርጫው በየትኛውም መመዘኛ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ እንዳልነበር አረጋግጧል፤›› በማለት ሒደቱንና ውጤቱን ፓርቲው ተቃውሟል፡፡ 

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ከሌላው ዓለም በተለየና በላቀ ሁኔታ የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ያለ ቢሆንም፣ የምርጫው ውጤት ግን ይህንን ፈጽሞ በማያሳይ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡ በዓለማችን ዴሞክራሲያዊ ምርጫም ሆነ የይስሙላ ምርጫ በሚያካሂዱ አገሮች ላይ እንደዚህ ዓይነት ውጤት ተመዝግቦ አያውቅም፡፡ ውጤቱም ሆነ ሒደቱ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ነፃ አለመሆኑን ያረጋገጠ ነው፤›› በማለት አትቷል፡፡

ይህን መግለጫ ለመስጠት ለምን እንደዘገዩ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ ‹‹ፓርቲያችን ሕግ መከበር፣ በመርህ ላይ የተንተራሰ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ይገነዘባል፡፡ እንደ ሌሎች ፓርቲዎች ቀድመን መግለጫዎችን ያልሰጠንበት ምክንያት በጥናት ላይ መመሥረትና ምክንያታዊ መሆን ስላለብን፣ እንዲሁም ደግሞ ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የሚደርሱን መረጃዎች እውነትና ተዓማኒ መሆናቸውን እስክናረጋግጥ ሒደቱ ጊዜ በመውሰዱ ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ኢዴፓ ፓርቲው የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ሕዝብ ‘እኔ ምን አገባኝ’ ከሚልና ከዳር ተመልካችነት ስሜት ራሱን በማራቅ፣ ለዚህች አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ ይበልጥ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርቧል፡፡  

 

 

የበጀት ጉድለቱ 27.6 ቢሊዮን ብር ይሆናል

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ የ2008 ዓ.ም. አጠቃላይ በጀትን ሰኔ 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ማክሰኞ ለሕዝብ ተወካዮች ሲያቀርቡ፣ ካቀረቡት 223.39 ቢሊዮን ብር ውስጥ መንገዶች፣ ትምህርትና ዕዳ ክፍያ ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ድርሻ ይዘዋል፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ ለ2008 ዓ.ም. ያቀረቡት አጠቃላይ በጀት ከዘንድሮው በ19.7 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ከጠቅላላው የወጪ በጀት ውስጥ 50.288 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ ማለትም ለደመወዝ፣ ለአበልና ልዩ ልዩ ሥራ ማስኬጃ ክፍያዎች መመደቡን ገልጸዋል፡፡ ለካፒታል በጀት ደግሞ ብር 84.3 ቢሊዮን ብር መመደቡን፣ ለክልሎች ድጎማ ደግሞ 76.8 ቢሊዮን ብር መመደቡን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እ.ኤ.አ. 2015 ማገባደጃ ላይ የሚጠናቀቁትን የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ለሚተካው ዘላቂ የልማት ግቦች ማስኬጃ 12 ቢሊዮን ብር መመደቡን አብራርተዋል፡፡

ሚኒስትሩ ካቀረቡት 223.39 ቢሊዮን ብር  ጠቅላላ በጀት ውስጥ የካፒታል በጀት 37.4 በመቶ በመያዝ ትልቁን ድርሻ አግኝቷል፡፡ ለክልል መንግሥታት የሚደረገው ድጎማ 34.7 በመቶ ሲሆን፣ ለመደበኛ ወጪዎችና ለዘላቂ ልማት ግቦች ማጠናከሪያ ወጪዎች በጀት ደግሞ በቅደም ተከተል 22.5 በመቶ እና 5.4 በመቶ ናቸው፡፡

ከአጠቃላይ የ2008 ዓ.ም. መደበኛና ካፒታል በጀት ውስጥ 66.6 በመቶ የሚሆነው የተመደበው ቅድሚያ ለተሰጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት ዝቅተኛ ትኩረት የነበረው የዕዳ ክፍያ በጀት በዚህ በጀት እጅግ ከፍተኛ ትኩረት ማግኘቱን ከበጀት ሰነዱ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከመደበኛና ከካፒታል ወጪ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ካገኙት መካከል የኢትዮጵያ የመጀመርያው መንገዶች ባለሥልጣን ሲሆን፣ 33.386 ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡ የትምህርት ዘርፍ 32.927 ቢሊዮን ብር በማግኘት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የዕዳ ክፍያ ወጪ 11.903 ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡

መከላከያ ሚኒስቴር 9.5 ቢሊዮን ብር የተመደበለት ሲሆን፣ ግብርና ሚኒስቴር 9.125 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ በጀት በማግኘት አራተኛና አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ትልቁን በጀት ማግኘት የቻለው የዋና መንገዶች ግንባታና አገናኝ መንገዶች ግንባታ ለማከናወን ነው፡፡ ነባሮቹን ለማሻሻልና ለማጠናከርም ከፍተኛ በጀት መያዙን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

የትምህርት ዘርፍ በሁለተኛ ደረጃ ትልቁን በጀት ማግኘት የቻለው ለአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታና ነባሮቹንም ዩኒቨርሲቲዎች ለማጠናከር መሆኑን የበጀት ሰነዱ ያስረዳል፡፡ ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን ያቀረቡትን የ2008 ዓ.ም. በጀት ለመሸፈን መንግሥት ያቀደው ከአገር ውስጥ ገቢ፣ ከውጭ ዕርዳታና ብድር ነው፡፡

በዚህም መሠረት 157.06 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ገቢ ለመሰብሰብ፣ ከመሠረታዊ አገልግሎት ከለላ 6.67 ቢሊዮን ብር፣ ከፕሮጀክት ዕርዳታ 13.06 ቢሊዮን ብር፣ ከፕሮጀክት ብድር 18.95 ቢሊዮን ብር እንደሚገኝ ታስቧል፡፡ ይህም ማለት ከአጠቃላይ በጀት ውስጥ 195.7 ቢሊዮን ብር ገቢን እንደሚይዝ የሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን የበጀት ሰነድ ይገልጻል፡፡

በ223.397 ቢሊዮን ብር የታቀደ በጀትና ታሳቢ በተደረገው 195.754 ቢሊዮን ብር ገቢ መካከል የ27.643 ቢሊዮን ብር ጉድለት ይታያል፡፡ 

መንግሥት የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈን ያቀደው ከአገር ውስጥ ምንጮች መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ የበጀት ጉድለቱ ከአጠቃላይ የአገሪቱ ምርት ያለው ድርሻ 1.8 በመቶ ብቻ በመሆኑ በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ምክር ቤቱ የሚኒስትሩን የበጀት መግለጫ ካዳመጠ በኋላ የመጀመርያ ዙር ጠቅለል ያለ ውይይት አካሂዷል፡፡ በዚህም መሠረት በቀረበው በጀት ላይ የሚታየው የበጀት ጉድለት የሚሸፈነው ከአገር ውስጥ በመሆኑ የዋጋ ግሽበት አያስከትልም ወይ? የአገሪቱ የወጪ ንግድ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት ያሳየውን ዝቅተኛ አፈጻጸም ለማስተካከል በዚህ በጀት ዓመት ምን ታቅዷል? መንግሥት ዓለም አቀፍ ቦንድ በመሸጥ ያገኘው አንድ ቢሊዮን ዶላር የት ደረሰ? የሚሉ ዋና ዋና ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል፡፡

አቶ ሱፊያን የቀረበው በጀትና የበጀት አሸፋፈን የዋጋ ግሽበት እንደማያስከትል፣ በአጠቃላይ የ2008 ዓ.ም. የዋጋ ግሽበት በአማካይ ስምንት በመቶ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

መንግሥት የበጀት ጉድለቱን የሚሞላው ከአገር ውስጥ ቢሆንም በቀጥታ ከብሔራዊ ባንክ በመበደር አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት እንደሚቻልና ይህ መንገድ ደግሞ የዋጋ ንረት እንደማያስከትል ገልጸዋል፡፡

የአገሪቱ የኤክስፖርት ዘርፍ በጣም ደካማ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ይህ ዘርፍ በጣት በሚቆጠሩ የምርት ዓይነቶች ላይ መንጠልጠሉን ካላቆመ ወዳቂ ነው ብለዋል፡፡

ትልቁ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማነቆ በኤክስፖርት (ወጪ ንግድ) ያለው ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በሌሎች ዘርፎች ያሉ ችግሮች፣ በዋና ኦዲተር የሚጋለጡ ችግሮችና የመሳሰሉ የፕሮጀክት ዝግጅት ችግሮች በስኬት ውስጥ ተሁኖ የሚታዩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹በኤክስፖርት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ካልቀረፍን ግን ኢኮኖሚው መቀጠል የሚችል አይመስለኝም፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ ችግር ላይ መንግሥት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየተወያየ ይገኛል ያሉት ሚኒስትሩ፣ በተለይ ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውጤቶች ላይ ማተኮር እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በኤክስፖርት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የኢንዱስትሪ ዞኖችን መንግሥት በራሱ ወጪ በመገንባት የውጭ ባለሀብቶች በፍጥነት ገብተው እንዲያመርቱ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ አዋጭ መሆናቸው በተለያዩ ጥናቶች የተረጋገጡ የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ዘርፎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ 

ከዓለም አቀፍ የቦንድ ሽያጭ የተገኘው አንድ ቢሊዮን ዶላርም የሚውለው ለዚሁ ልማት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ብሔራዊ ባንክ ይህንን ገንዘብ ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን በማበደር ጥቅም ላይ ያውለዋል ብለዋል፡፡

 

 

 

 

ከ3.5 ሚሊዮን ብር በላይ ያላግባብ ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸው ተጠቅሷል

የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዘካርያስ አሰፋና የኢንስቲትዩቱ የፋሲሊቲና ሰርቪስ አስተዳደር ኃላፊና የጨረታ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ጉይቴ ወልደ ማርያም፣ ሳሊም መሐመድ ባሙኒፍ

ከሚባል አጠቃላይ አስመጪ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ጋር በመመሳጠር ሙስና ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው ክስ ተመሠረተባቸው፡፡ 

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዘካርያስ ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም፣ ለኢንስቲትዩቱ አገልግሎት የሚውሉ የአዳራሽ ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎች፣ ፑልፒት/አንትሮንስና መድረክ ከእነአክሰሰሪዎቹ ግዢ ሲፈጸም፣ የፌዴራል የግዥ አፈጻጸም መመርያን በመተላለፍ 3,590,179 ብር ክፍያ አላግባብ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡ ግዢው የተፈጸመው ከ1998 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ ባሉት የተለያዩ ጊዜያት መሆኑንም ክሱ ይጠቁማል፡፡ 

ለኢንስቲትዩቱ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎችን ለመግዛት በተለያዩ ጊዜያት የወጡትን ጨረታዎች ማሸነፉ የተጠቆመው ሳሊም መሐመድ ባሙኒፍ አጠቃላይ አስመጪ ቢሆንም፣ ሐምሌ 1 ቀን 1997 ዓ.ም. የወጣውን የፌዴራል መንግሥት የግዥ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 28ን የጣሰ መሆኑን ክሱ ይገልጻል፡፡ መመርያው እንደሚያብራራው በማንኛውም ሁኔታ ጨረታውን ላሸነፈ ድርጅት ከጠቅላላ ዋጋው 30 በመቶ በላይ ቅድሚያ ክፍያ አይፈጸምም፡፡ ነገር ግን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ለአሸናፊው ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ከጠቅላላ ዋጋው 60 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ በቅድመ ክፍያ እንዲሰጥ መፍቀዳቸውን ክሱ ያብራራል፡፡ 

የግዥ መመርያ ቁጥር 28 አንቀጽ 2 እንደሚያስረዳው፣ ቅድመ ክፍያ የሚፈጸመው አሸናፊው ድርጅት በቅድሚያ ክፍያ ከሚወስደው ገንዘብ መጠን ጋር እኩል የሆነ ዋስትና ሲያቀርብ ብቻ መሆኑን ቢደነግግም፣ ዋና ዳይሬክተሩ ግን ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ያለምንም ዋስትናና ከመመርያ ውጪ 60 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ያለዋስትና እንዲከፈል መፍቀዳቸውን፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ 

በሌላ በኩል የመንግሥት የግዥ ሥርዓትን ለመወሰንና ተቆጣጣሪ ኤጀንሲውን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 430/1997 አንቀጽ 43 እና የግዥ መመርያ ቁጥር 28 አንቀጽ 11.14 ላይ የተደነገገውን፣ ተከሳሾቹ መተላለፋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ ድንጋጌዎቹ እንደሚያስረዱት፣ የጨረታው አሸናፊ ቢያንስ የውሉን ዋጋ አሥር በመቶ ለውል ማስከበሪያነት ለመንግሥት መሥሪያ ቤቱ ማስያዝ እንዳለበት ቢገልጽም፣ ድንጋጌውን በመተው ግዴታዎቹ በውሉ እንዳይካተቱ ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ አሸናፊው ድርጅትም በድንጋጌው መሠረት ገቢ ማድረግ ያለበትን ገንዘብ እንዳላስያዘ ክሱ አክሏል፡፡ 

የጨረታው አሸናፊ ዕቃዎቹን በውሉ መሠረት ገቢ ማድረግ ሲገባው ሳያደርግ ቢቀር፣ በግዥ መመርያው መሠረት ዕቃውን ካላቀረበበት ቀን ጀምሮ የሚታሰብ ዜሮ ነጥብ አንድ በመቶ በጠቅላላ ሒሳቡ (በተከፈለው መጠን) ተባዝቶ ቅጣት እንደሚከፍል መደንገጉን ክሱ ያስረዳል፡፡ ተከሳሾቹ ይህንን ባለመፈጸማቸው መንግሥት 1,058,953.4 ብር በድምሩ ማጣቱን ጠቁሟል፡፡ 

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘካርያስና አቶ ተስፋዬ በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ ጠቅላላ አስመጪው አቶ ሳሊም መሐመድ (በሌሉበት) በልዩ ወንጀል ተካፋይነት የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ 

አቶ ሳሊም በሌሉበት የተከሰሱ ሲሆን፣ አቶ ዘካርያስ የተጠቀሰባቸው የሕግ አንቀጽ ዋስትና እንደሚከለክል ተነግሯቸው ክሳቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ታዟል፡፡ አቶ ተስፋዬ የተከሰሱበት የወንጀል ሕግ ዋስትና እንደማይከለክል ተገልጾ በ7000 ብር ዋስትና ውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የአቶ ሳሊምን መቅረብ ለመጠባበቅ ለሰኔ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ 

 

ውኃ እስኪሞላ የሚጠበቀው ግልገል ጊቤ ሦስት በአምስት ተርባይኖች ሊጀምር ነው

የግልገል ጊቤ ሦስት ኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት ግንባታው ከ92 ከመቶ በላይ ተጠናቆ ግድቡ ውኃ ማጠራቀም እንደጀመረ ተገልጾ፣ በክረምቱ ወራት ጥሩ ዝናብ ማግኘት ከቻለ በአምስት ተርባይኖች ኃይል ለማሰራጨት ዝግጁ መሆኑ ተነገረ፡፡ 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ እንዳስታወቁት፣ የፕሮጀክቱ ግንባታ በአብዛኛው ተጠናቋል፡፡ ከ1,870 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቀው ጊቤ ሦስት፣ በአሁኑ ወቅት ከጠቅላላው የማመንጨት አቅሙ ግማሽ ያህሉን ለማሰራጨት ዝግጁ መሆኑም ተገልጿል፡፡ 

በጠቅላላው አሥር ተርባይኖች ያሉትና በአንዱ ብቻ 187 ሜዋ ጋት ኃይል የሚያመነጨው ጊቤ ሦስት፣ ቁመቱ 276 ሜትር የሚረዝም ግድብ አለው፡፡ ምንም እንኳ የዚህ ግድብ ቁመት ሙሉ ለሙሉ ተገንብቶ ባይጠናቀቅም፣ ውኃ የመያዝ አቅም ላይ በመድረሱ ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ ግድቡ ውኃ እንዲያጠራቅም መዘጋቱን ኢንጂነር አዜብ አስታውቀዋል፡፡ 

ግልገል ጊቤ ሦስት ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በመንግሥት ከተገነቡ አራት ትልልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በርዝማኔው ከአፍሪካ ትልቁ ሲሆን፣ 11.8 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ የመያዝ አቅም አለው፡፡ ከቻይና መንግሥት ከተገኘ 470 ሚሊዮን ዶላር ብድር ጨምሮ በጠቅላላ ወጪው 1.47 ቢሊዮን ዶላር እንደወጣበት የሚነገርለት ጊቤ ሦስት፣ አካባቢያዊ ተፅዕኖው ሰፊ ነው ተብሎ በርካታ ተቃውሞዎች ሲነሱበት መቆየቱ አይዘነጋም፡፡  

 

 

 

የምስክሮች ቃል እንዳይዘገብ ፍርድ ቤት ከለከለ

በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የቀድሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት)፣ የአረናና ሰማያዊ ፓርቲዎች አመራሮች ላይ፣ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ከሰኔ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ማሰማት ጀመረ፡፡

ክሱን የመሠረተው የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን አቅርቦ ከማሰማቱ በፊት፣ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀጽ 32 መሠረት ምስክርነቱ በዝግ እንዲታይ ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ‹‹በምስክሮቼ ላይ ማስፈራሪያና ዛቻ ደርሶባቸዋል›› የሚል ነበር፡፡ 

ተከሳሾቹ ግን የተጠቀሰባቸው ሕግ እስከ ሞት ድረስ ሊያስቀጣ የሚችል መሆኑን በመጠቆምና ምስክርነቱን ሕዝብ መስማት እንዳለበት በመግለጽ፣ ምስክርነቱ በግልጽ ችሎት እንዲታይ ፍርድ ቤቱን በመጠየቅ የዓቃቤ ሕግን ማመልከቻ ተቃውመዋል፡፡ 

ሁሉንም እስረኞች በመወከል ለፍርድ ቤቱ ያመለከቱት የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራር አቶ ሀብታሙ አያሌው ሲሆኑ፣ ያሉት ማረሚያ ቤት ውስጥ መሆኑንና የምስክሮቹ ዝርዝር ሊደርሳቸው የሚገባ ቢሆንም መከልከላቸውን አስረድተዋል፡፡ 

በመሆኑም በምስክሮቹ ላይ ማንም ዛቻና ማስፈራሪያ ሊያደርስ የሚችልበት መንገድ እንደሌለ ጠቁመው፣ የዓቃቤ ሕግ ጥያቄ ውድቅ እንዲደረግላቸው አመልክተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ምስክርነቱን በዝግ ችሎት የሚያየው ከሆነ፣ ሁሉም ተከሳሾች የግፍ ፍርደኛ ሆነው ወደ እስር ቤት እንደሚመለሱና በቀጣይም ምንም ዓይነት ክርክር እንደማያደርጉ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ 

ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገኖች ክርክር በማዳመጥ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ የዓቃቤ ሕግን ማመልከቻ ውድቅ በማድረግ፣ ምስክርነቱ በግልጽ ችሎት እንዲታይ ብይን ሰጥቷል፡፡ ነገር ግን የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች የሚናገሩትንም ሆነ ስማቸውን ጠቅሰው የኅትመትም ሆነ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኃን መዘገብ እንደማይችሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ 

በዕለቱ በአሥረኛ ተከሳሽ አቶ ተስፋዬ ተፈሪ ላይ አንድ የዓቃቤ ሕግ ምስክር ተሰምተዋል፡፡ 

ተከሳሾቹ አቶ ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ ጋሻው፣ የአንድነት አመራር የነበሩት አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ የአረና ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታ፣ እንዲሁም አቶ ዮናታን ወልዴ፣ አቶ አብርሃም ሰለሞን፣ አቶ ሰለሞን ግርማ፣ አቶ ባህሩ ደጉና አቶ ተስፋዬ ተፈሪ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሪል ስቴትና ለባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ግንባታ የሚውሉ ቦታዎችን ለአልሚዎች ለማስተላለፍ ልዩ ጨረታ አወጣ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ባንክና ማስተላለፍ ኤጀንሲ ለሁለተኛ ጊዜ ያወጣው ይህ ልዩ ጨረታ፣ ስምንት ቦታዎችን ብቻ የያዘ ቢሆንም ቦታዎቹ ሰፋፊ መሆናቸው ታውቋል፡፡ 

ስድስቱ ቦታዎች ለሪል ስቴት ልማት፣ ሁለቱ ቦታዎች ደግሞ ለባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ግንባታ የሚውሉ ናቸው፡፡ ቦታዎቹ በአራት ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ ሲሆን፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አራት ቦታዎች ለሪል ስቴት ልማት ቀርበዋል፡፡ ዝቅተኛው የቦታ ስፋት 14,089 ካሬ ሜትር ሲሆን፣ ከፍተኛው ደግሞ 55,386 ካሬ ሜትር ነው፡፡ የቦታዎቹ መነሻ ዋጋ በካሬ ሜትር 191 ብር ሆኖ 60 ዓመት የሊዝ ዘመን ተሰጥቷቸዋል፡፡ 

በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ሁለት ቦታዎች ለጨረታ የቀረቡ ሲሆን፣ 23,913 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው አንድ የሪል ስቴት ቦታና 8,998 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው አንድ ቦታ ለባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ግንባታ ቀርቧል፡፡ የእነዚህ ቦታዎች የመነሻ ዋጋም በካሬ ሜትር 191 ብር ነው፡፡ 

በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማም አንድ ቦታ ለሪል ስቴት ልማት ቀርቧል፡፡ የቦታው ስፋት 57,752 ካሬ ሜትር መነሻ ዋጋው በካሬ ሜትር 299 ብር ነው፡፡ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ውስጥ አንድ ቦታ ለባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ግንባታ የሚውል 6,014 ካሬ ሜትር ቦታ ለጨረታ ቀርቧል፡፡ 

ጨረታው እስከ ሐምሌ 23 ቀን ድረስ ይፋ ሆኖ የሚቆይ ሲሆን፣ በዚያው ዕለት ከሰዓት በኋላ ይከፈታል ተብሏል፡፡ 

የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ፣ መሬት በዋነኛነት ለአልሚዎች የሚቀርበው በጨረታ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቀላል ፕሮጀክቶች 14 ጊዜ ጨረታ አውጥቷል፡፡ ለሆቴል፣ ለሪል ስቴት፣ ለትምህርትና ለጤና ተቋማት ግንባታ የሚውሉ ቦታዎችን ለአልሚዎች ያቀረበው በሁለት ጨረታዎች ብቻ ነው፡፡ 

የመጀመርያው ጨረታ ግንቦት 2 ቀን 2006 ዓ.ም. ወጥቶ ሰኔ 3 ቀን 2006 ዓ.ም. መከፈቱ ይታወሳል፡፡ በዚህ ጨረታም የወጡት ቦታዎች ሰፋፊ ቢሆኑም ቁጥራቸው አሥር ብቻ ነበር፡፡ 

ባለሙያዎች አስተዳደሩ የመሬት ዋጋ ንረትን ለማርገብ በርካታ ቦታዎችን ለጨረታ ማቅረብ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ 

 

የቻይና ሪል ስቴት ኩባንያ በአራት ቢሊዮን ብር ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ሊገነባ ነው

ከፀሐይ ሪል ስቴት ቀጥሎ ሁለተኛው የቻይና ኩባንያ በአራት ቢሊዮን ብር በአዲስ አበባ ከተማ የሪል ስቴት ፕሮጀክት ግንቦት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ አኖረ፡፡

ሲኖ ማርክ የተባለው ይህ የቻይና ኩባንያ አገር በቀል ኩባንያ ከሆነው ሳባ ኢንጂነሪንግ ጋር ግንባታ ለማካሄድ ስምምነት የፈጸመው፣ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ለመገንባት ነው፡፡ 

ግንባታው የሚካሄደው ሳባ ኢንጂነሪንግ ከፕራይቬታይዜሽንና ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ በገዛው አዲስ ብሎክ ሼር ኩባንያ ይዞታ በሆነው፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጎተራ አካባቢ በሚገኝ 60 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው፡፡ 

የሳባ ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ሳምሶን በኩረ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዚህ ሥፍራ ላይ ከፍታቸው 20 ፎቅ የሆኑ 21 ሕንፃዎች ይገነባሉ፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ግንባታ አራት ቢሊዮን ብር በጀት የተያዘ ሲሆን፣ በኢንቨስትመንቱ ላይ ሁለቱም ኩባንያዎች እኩል ድርሻ እንደሚኖራቸው ኢንጂነር ሳምሶን ተናግረዋል፡፡ 

ሕንፃዎቹ በ30 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፉ ሲሆን፣ በተቀረው ቦታ ላይ የተለያዩ የስፖርት ማዕከላት፣ የገበያ ማዕከላት፣ የሕፃናት መጫወቻዎችና አረንጓዴ ሥፍራዎች ይካተታሉ፡፡

ይህ ግንባታ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚጠናቀቅ መሆኑን፣ ሽያጩም ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ እንደሚካሄድ ኢንጂነር ሳምሶን ተናግረዋል፡፡ 

የሕንፃዎቹን ግንባታ ለማስጀመር ባለፈው እሑድ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል፡፡ የመሠረት ድንጋይ በተቀመጠበት ወቅት የሲኖ ማርክ ኩባንያ ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ያን ሲን ሊ እንደተናገሩት፣ የሕንፃዎቹ ግንባታ በፈረንሳይ የሕንፃ አሠራር ዘይቤ ይከናወናል፡፡ 

የቻይና ኩባንያዎችን ጨምሮ የህንድ፣ የቱርክና የአውሮፓ ኩባንያዎች በአዲስ አበባ ከተማ በሪል ስቴት ልማት ለመሳተፍ ፍላጎት ከማሳየት አልፈው ፕሮፖዛል በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ 

ነገር ግን መንግሥት የውጭ ኩባንያዎች በራሳቸው መንገድ፣ በሪል ስቴት ልማት እንዲሳተፉ ለማድረግ የጀመረውን የፖሊሲ ጥናት ማጠናቀቅ ባለመቻሉ ጉዳዩ በእንጥልጥል ላይ ይገኛል፡፡ 

የቻይናው ግዙፍ ኩባንያ ሲጂሲ ኦቨርሲስ መንግሥት ለውጭ ኩባንያዎች መሬት ስለመስጠትም ሆነ ስለመከልከል አቅጣጫ ከመያዙ በፊት፣ በየካ ክፍለ ከተማ ሲኤምሲ አካባቢ ባገኘው መሬት የሪል ስቴት ልማት በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ 

ሲጂሲ ኦቨርሲስ ከሌላ የቻይና ኩባንያ ጋር በመሆን ያቋቋመው ፀሐይ ሪል ስቴት በ30 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በ2.5 ቢሊዮን ብር በጀት፣ ከፍታቸው 12 ፎቅ የሆኑ የመኖሪያ ሕንፃዎችን እየነባ ይገኛል፡፡ 

አዲሱ የቻይና ኩባንያ ሲኖ ማርክ ከሳባ ኢንጂነሪንግ ጋር ግንባታ የሚያካሂድበት መሬት ባለቤት አዲስ ብሎክ ሼር ኩባንያ የተለያዩ የኮንስትራክሽን ዕቃዎችን የሚያመርት ሲሆን፣ ሳባ ኢንጂነሪንግ ከፕራይቬታይዜሽንና ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ገዝቶታል፡፡ 

ሳባ ኢንጂነሪንግ ከኢትዮጵያ ባሻገር በሩዋንዳ፣ በኡጋንዳ፣ በታንዛኒያ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በመክፈት በውኃ ሥራዎችና በተለያዩ የግንባታና የማማከር ሥራዎች የተሰማራ አገር በቀል ኩባንያ ነው፡፡ ሲኖ ማርክ ደግሞ ከአሥር ዓመታት በላይ በሪል ስቴት ልማት ውስጥ እንደቆየ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከዘጠኝ ዓመት በኋላ በድጋሚ በተደረገበት ኦዲት ጥሩ ውጤት ማስመዝገቡንና የደኅንነት ደረጃውን አስጠብቆ መቀጠሉን አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ጠንካራ ከሚባሉት አምስቱ አንዱ ተቋም መሆኑም ተገልጿል፡፡ 

አምስት አባላት ያሉት የዓለም የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ኦዲተሮች ለአሥር ቀናት ባካሄዱት የኦዲት ምርመራ፣ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና የሚቆጣጠራቸውን ኢትዮጵያ የአየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ የበረራ ደኅንነትን ለማስጠበቅ የተሠሩትን ሥራዎችና የተወሰዱ ቁጥጥሮችን በመመርመር ኦዲት አካሂደዋል፡፡

 በዚህም መሠረት ባለሥልጣኑ በአጠቃላይ ውጤት 68.68 በመቶ በማግኘቱ ከዓለም አማካይ ውጤት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው አስታውቀዋል፡፡ በዓለም የአቪዬሽን ድርጅት የዓለም አማካይ ውጤት ተብሎ የተቀመጠው 60 በመቶ ነው፡፡ 

ሲቪል ኢቪዬሽን ባለሥልጣን ከተፈተሸባቸው ስምንት ዋና ዋና የኦዲት ይዘቶች ውስጥ በተለይ በአምስቱና ባለሥልጣኑ በራሱ በሚተገብራቸው መስኮች 78 በመቶ በማምጣት ትልቅ ውጤት ማስዝገቡን አስታውቀው፣ ባለሥልጣኑ በሚቆጣጠራቸው ሦስቱ ተቋማት የተገኘው ውጤት 51 በመቶ በመሆኑ በአንፃራዊነት ዝቅተኛ ሊባል እንደሚችል ይፋ አድርገዋል፡፡ ምንም እንኳ በአጠቃላይ ውጤቱ በዓለም ከተቀመጠው አማካይ ውጤት ከፍ ያለ ቢሆንም፣ በሦስቱ ተቋማት የተመዘገበውን ዝቅተኛ አንፃራዊ ውጤት ለማሻሻል ሥራዎች እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ 

ከዘጠኝ ዓመት በፊት ኦዲት ተደርጎ ያስዘመገበው ውጤት 66 በመቶ ነበር ያሉት ኮሎኔል ወሰንየለህ፣ በአሁኑ መጠነ ሰፊና አጠቃላይ ኦዲት ተፈትሾ ያስመዘገው ውጤት፣ ሲቪል አቪዬሽን የመቆጣጠር ብቃቱና ጥንካሬው የታየበት ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየትኛውም መዳረሻ የመብረርና የተጓዦችን ደኅንነት የማስጠበቅ ብቃት እንዳለው የተረጋገጠበት ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በኦዲት ሪፖርቱ መሠረት ምንም ዓይነት መሠረታዊ የደኅንነት ክፍተቶች አለመኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ 

ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በአሜሪካው የአቪዬሽን አስተዳደር ኦዲት ተደርጎ በዘርፉ ደረጃ አንድ የተባለውን ደኅንነት ደረጃ በማስጠበቅ፣ በአሜሪካም ሆነ በሌሎች አገሮች ያለምንም የደኅንነት ክፍተቶች በረራዎችን ማካሄድ እንደሚችል አረጋግጦ እንደነበር አይዘነጋም፡፡  

 

 

 

በሁለት የዓባይ ተፋሰስ ገባር ወንዞች ላይ 2026 ሜጋ ዋት የኃይል ማመንጫ ሊገነባ ነው

መንግሥት ለዓባይ ተፋሰስ ገባር በሆኑ ሁለት ወንዞች ላይ በድምሩ 2,026 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ለመገንባት በዝግጅት ላይ መሆኑ ታወቀ፡፡ 

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ግንቦት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የበጀት ዓመቱ የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ በሚቀጥለው ዓመት ሊተገበሩ የታቀዱትን የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ይፋ አድርገዋል፡፡ 

የሚኒስትሩ ሪፖርት እንደሚያስረዳው፣ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተጠኑ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል በታምስ ወንዝ ላይ በጋምቤላ ክልል ውስጥ የሚገነባው 1,700 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ታምስ ኃይድሮ ፓወር ፕሮጀክት አንዱ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ በዳቡስ ወንዝ ላይ የሚገነባውና 326 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የዳቡስ አንድ ኃይድሮ ፓወር ፕሮጀክት መሆኑን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ የሁለቱም የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ዝርዝር ጥናት በመካሄድ ላይ መሆኑንና የታምስ ኃይድሮ ፓወር ፕሮጀክት ዝርዝር ጥናት 81 በመቶ መከናወኑን፣ የዳቡስ አንድ ኃይድሮ ፓወር ፕሮጀክት ደግሞ 71 በመቶ መከናወኑን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፕላንና ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ መኩሪያ ለማ፣ የታምስ ኃይድሮ ፓወር ፕሮጀክት ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሸካ ተራራ አናት የሚመነጨውና በጋምቤላ አድርጐ የባሮ ወንዝን፣ በመቀጠልም ከነጭ ዓባይ ተፋሰስ ጋር የሚቀላቀለው የታምስ ወንዝ ላይ የሚገነባው ነው፡፡ የታምስ ወንዝ ባሮ ወንዝን ከመቀላቀሉ በፊት በጋምቤላ ክልል ኃይል አመንጭቶ እንዲያልፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ 

ይህንንም እውን ለማድረግ በኢትዮጵያ ውኃ ሥራዎች ዲዛይን ድርጅትና በአንድ የጣሊያን ኩባንያ ዝርዝር ጥናቱ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት አጠቃላይ ወጪ ምን ያህል ይሆናል የሚለው ዝርዝር ጥናቱ ሲጠናቀቅ እንደሚታወቅ አስረድተዋል፡፡ ከታምስ ኃይድሮ ፓወር ፕሮጀክት የማመንጨት አቅም በመጠኑ ብልጫ ያለውና በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክት ግንባታው ከ90 በመቶ በላይ የተጠናቀቀው 1,870 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሲጀመር፣ የተያዘለት በጀት 1.8 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከተጀመረ አምስት ዓመታትን ያሳለፈ ቢሆንም፣ የታምስ ኃይድሮ ፓወር ፕሮጀክት አጠቃላይ ወጪ ማነፃፀሪያ ተደርጎ ይገመታል፡፡

የዳቡስ ኃይድሮ ፓወር ማመንጫ ፕሮጀክት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልን በወለጋ በኩል ከኦሮሚያ በሚያዋስን አካባቢ በሚፈሰው የዳቡስ ወንዝ ላይ የሚገነባ ነው፡፡ ይህ ወንዝ የጥቁር ዓባይ ገባር ሲሆን፣ ዓባይን ከመቀላቀሉ በፊት ቤንሻንጉልን ከወለጋ በሚያዋስነው አካባቢ 326 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ ታቅዶ፣ የፕሮጀክቱ ጥናት በመካሄድ ላይ መሆኑን አቶ መኩሪያ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

ይህ ፕሮጀክት በመንግሥት ቅድሚያ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን፣ በመጀመሪያ ጥናቱ 628 ሚሊዮን ዶላር በጀት ያስፈልገዋል ተብሎ እንደተገመተ፣ ነገር ግን ትክክለኛ ወጪው የተጀመረው ዝርዝር ጥናት ሲጠናቀቅ የሚታወቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

መንግሥት ዘንድሮ በሚጠናቀቀው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ከአምስት ዓመት በፊት በአገሪቱ የነበረውን አጠቃላይ 2,000 ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦት ወደ 10,000 ሜጋ ዋት ለማሳደግ አቅዶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የዕቅድ ዘመኑ ሊጠናቀቅ የአንድ ወር ዕድሜ እየቀረው በተግባር ማቅረብ የቻለው ተጨማሪ ኃይል 310 ሜጋ ዋት መሆኑን፣ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ለፓርላማ ያቀረቡት ሪፖርት ያስረዳል፡፡

ይሁን እንጂ በዕቅድ ዘመኑ ይጠናቀቃሉ ተብለው የተገመቱት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች አማካይ አፈጻጸማቸው ከ60 በመቶ በላይ በመሆኑ፣ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ወደ አገሪቱ የኃይል ማስተላለፊያ ቋት ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

በተለይ 1,870 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትና 254 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ገናሌ ሦስት ፕሮጀክት በግንቦት ወር ውስጥ የነበራቸው አጠቃላይ የፕሮጀክት አፈጻጸም 90.27 በመቶ እና 73.82 በመቶ በመሆኑ፣ በ2008 ዓ.ም. 2,521 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ወደ ሥርጭት ሥርዓት ውስጥ እንደሚገባ ይገመታል፡፡

ከቀሪዎቹ መካከል የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 6,000 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም፣ ከቆሻሻና ከጂኦ ተርማል ኃይል ለማመንጨት ከተጀመሩት ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ደረጃ በመነሳት፣ እስከ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ማገባደጃና እስከ 2009 ዓ.ም. እንደ ቅደም ተከተላቸው እንደሚጠናቀቁ ይጠበቃል፡፡ 

 

ከጁባ የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ 20 ሚሊዮን ብር የመዘበሩ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ከሁለት ዓመት በላይ ካስቆጠሩት፣ የቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር የተያያዙ ሌሎች አምስት የንግድ ተቋማት ላይ ክስ ለመመሥረት በምርመራ ላይ መሆኑን፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በነበሩት አቶ መላኩ ፈንታና በምክትላቸው አቶ ገብረዋህድ ገብረጊዮርጊስ እንዲሁም በሌሎች የባለሥልጣኑ ሠራተኞችና በንግድ ሥራ በተሰማሩ የግል ተቋማት ባለሀብቶች ከግብርና ከታክስ ጋር በተገናኘ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በቁጥጥር ሥር የዋሉት፣ በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. እንደነበር ይታወሳል፡፡ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ረጅም የምርመራ ጊዜ ቢወስድም ክስ ከተመሠረተባቸውና ክርክር ከተጀመረ ከዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት ጉዳዩን በማየት ላይ የሚገኘው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዓቃቤ ሕግ ምስክርን በመስማት ላይ ይገኛል፡፡

የእነ አቶ መላኩ ፈንታና ሌሎች የባለሥልጣኑ ሠራተኞችና ባለሀብቶች የክስ ሒደት ከላይ በተገለጸው ደረጃ ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፣ የ11 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ከእነ አቶ መላኩ ፈንታ የወንጀል ምርመራ ጋር የተያያዙ ናቸው ያላቸው አምስት ድርጅቶች በመንግሥት ላይ የ361.6 ሚሊዮን ብር ጉዳት እንዳደረሱ በማረጋገጥ፣ በተጨማሪ ምርመራ ላይ እንደሚገኝ ለምክር ቤቱ አሳውቋል፡፡ 

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌማን ባለፈው ሐሙስ ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት፣ ‹‹በቀድሞ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣናት፣ አንዳንድ የባለሥልጣኑ ሠራተኞችና ከፍተኛ ነጋዴዎች ላይ ተጀምሮ ከነበረው ምርመራ ጋር በተያያዘ የአገር ውስጥ ግብርና የጉምሩክ ቀረጥ ባለመክፈል በተጠረጠሩ አምስት የግል ኩባንያዎች ላይ የኢንስፔክሽን ኦዲት በማስደረግ በተገኘው ማጣራት፣ 361.6 ሚሊዮን ብር የመንግሥት ታክስ አለመከፈሉ በመረጋገጡ ምርመራው እየተከናወነ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

ኮሚሽነሩ ባቀረቡት ሪፖርት የተጠረጠሩትን ድርጅቶች ማንነት አልገለጹም፡፡ የድርጅቶቹን ማንነት ለማጣራት ሪፖርተር ያደረገው ሙከራም አልተሳካም፡፡ ይሁን እንጂ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በእነ አቶ መላኩ ፈንታና በሌሎች ባለሀብቶች ላይ ክስ በመሠረተበት ወቅት፣ ምርመራ የተደረገባቸውና ክስ ያልተመሠረተባቸው 15 የግል ኩባንያዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡

እነዚህም ኒያላ ሞተርስ፣ ፔትራም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ሞኤንኮ፣ ጌትአስ ትሬዲንግ፣ አልሳም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ሜቴክ፣ አይካ አዲስ ትሬዲንግ፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ፣ ሆላንድ ካርስ፣ ቶታል ኢትዮጵያ፣ ሚድሮክ፣ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን፣ ድሬ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ፣ ኢትዮ ሌዘር፣ ኢትዮ ቆዳ ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር ናቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኮሚሽኑ በሌሎች በጠረጠራቸው የሙስና ወንጀሎች ላይም ምርመራ እያደረገ መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ 

ቦሌ ክፍለ ከተማ በሐሰተኛ ማስረጃ መሬት እንዲያገኙ ተደርጓል በሚል በቀረበ ጥቆማ፣ 89 የመሬት ጉዳዮች ላይ ምርመራ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በተለያዩ የግንባታ ሳይቶች ለሚከናወኑ ግንባታዎች የሚውሉ ጠጠር፣ ፕሪካስትና ብሎኬት ግዥ ጋር በተያያዘ አምስት ሚሊዮን ብር ጉዳት በማድረስ በተጠረጠሩ ሠራተኞችና አቅራቢዎች ላይ ምርመራ እየተከናወነ መሆኑን የኮሚሽኑ ሪፖርት ያስረዳል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደቡብ ሱዳን (ጁባ) ቅርንጫፍ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በመመሳጠር ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በመውሰድ ለግል ጥቅም በማዋላቸው፣ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ሆነው ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ 

  

 

 

በፕሮቪደንት ፈንድ የታቀፉ የግል ድርጅት ሠራተኞችን በመንግሥት በሚተዳደረው የግል ድርጅቶች ጡረታ እንዲዘዋወሩ የሚያስገድድ ማሻሻያ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡ፣ በግል ድርጅቶች ሠራተኞች ዘንድ ተቃውሞ ቀሰቀሰ፡፡

የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ 7/5/2003 በሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም. ተግባራዊ መሆን ከመጀመሩ በፊት፣ የፕሮቪደንት ፈንድ ሽፋን ያላቸው የግል ድርጅት ሠራተኞች በነበራቸው የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚነት ለመቀጠል እንዲወስኑ፣ ወይም በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ስለሚሸፈኑበት ሁኔታ ሊስማሙ እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡

በዚህ የተነሳም በአገሪቱ የሚገኙ በርካታ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች በተሰጣቸው አማራጭ ላይ ውይይት በማድረግ በፕሮቪደንት ፈንድ መታቀፍን መምረጣቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ከአራት ዓመት በኋላ ባለፈው ሐሙስ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ማሻሻያ አዋጅ የቀድሞውን አማራጭ በማስቀረት፣ ሁሉም የግል ድርጅቶች ሠራተኞች በጡረታ ዕቅድ እንዲሸፈኑ ማሻሻያ አቅርቧል፡፡

ማሻሻያው በዚህ ላይ ብቻ ሳይሆን የግል ኩባንያ ባለቤቶች በግል ድርጅቶች ሠራተኞች የጡረታ ዐቅድ ሥር እንዲታቀፉ፣ እንዲሁም ከአሥር ዓመት በታች ያገለገሉ የግል ድርጅት ሠራተኞች በሚለቁበት ወቅት ቀደም ሲል ይፈቀድ የነበረውን ክፍያ ያስቀራል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የግል ባንክ ኃላፊ፣ አሁን በሥራ ላይ በሚገኘው የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የጡረታ አዋጅ በሚፈቅደው መሠረት፣ በሁሉም ቅርንጫፎች የሚገኙ ሠራተኞች በፕሮቪደንት ፈንድ እንዲታቀፉ በፍላጎታቸው መምረጣቸውን ገልጸዋል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ለፓርላማ በመቅረቡ ግን ከሠራተኞች ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት እያደረጉ መሆኑንና ውሳኔ ለመወሰን መቸገራቸውን አስረድተዋል፡፡

ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት ደግሞ በፕሮቪደንት ፈንድ ወይም ቀድሞ በነበራቸው ጡረታ ለመቀጠል ተስማምተው ሲቆጥቡ የነበሩ ሠራተኞች፣ የፕሮቪደንት ፈንድ ወደ ግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ ፈንድ እንደሚዘዋወር በረቂቅ አዋጁ የተካተተ በመሆኑ ቢፀድቅ የሕግ ተጠያቂነትን ያስከትል እንደሆነ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ 

አንድ ስማቸውንም ሆነ የሚሠሩበትን መሥሪያ ቤት መጥቀስ ያልፈለጉ ሥራ አስኪያጅ ‹‹እንዴት በሕግ የተሰጠን መብት ተጠቅመው ፕሮቪደንት ፈንድን የመረጡ ሠራተኞችን ገንዘብ ለመውሰድ መንግሥት ሕግ ያወጣል?›› ሲሉ ድርጊቱን ተችተውታል፡፡ 

በማከልም ጉዳዩ የሠራተኞችን መብት መደፍጠጥ እንደሆነና መንግሥት ማድረግ የነበረበት ለፕሮቪደንት ፈንድ የማኅበራዊ ዋስትና የሕግ ከለላ በመስጠት፣ በቀጣሪዎች እንዳይመዘበር መቆጣጠር ነበረበት በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የግልግልና ዳኝነት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተርና የሕግ ባለሙያው አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ የግል አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ አስተያየታቸውን መስጠት የጀመሩት፣ የግል ጡረታ ቦርድ ውስጥ የግል ባለሀብቶች እንዲወከሉ በሕጉ የተቀመጠ መሆኑን አስታውሰው፣ በዚህ ቦርድ ውስጥ የግሉ ዘርፍን በመወከል የተቀመጠ ሰው በዚህ ረቂቅ ማሻሻያ ላይ በስምምነት ፈርሞ ከሆነ፣ የግሉን ዘርፍ የሚወክል ግለሰብ ነው ብለው እንደማያምኑ በመግለጽ ነው፡፡ ‹‹እነዚህ ተወካዮች የግሉን ዘርፍ የሚወክሉ ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም የግሉ ዘርፍ የመንግሥት ተጧሪ የመሆን ፍላጐት አለው ብዬ አላምንም፤›› ብለዋል፡፡ 

በ2003 ዓ.ም. ፀድቆ ወደ ሥራ የገባው የግል ድርጅቶች ጡረታ አዋጅ ቀደም ሲል በፕሮቪደንት ፈንድ ወይም በጡረታ ዐቅድ ተሸፍነው የነበሩ ሠራተኞች፣ ከፕሮቪደንት ፈንድና ከጡረታ ዐቅድ እንዲመርጡ በተሰጣቸው ዕድል ነፃ ውይይት አድርገው ፕሮቪደንት ፈንድን ይጠቅመናል ብለው መወሰናቸውን አቶ ዮሐንስ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹የግሉ ዘርፍ ሠራተኞች ውሳኔ እንዳልወሰኑ አድርጐ በመውሰድ እንደገና ወደኋላ ሄዶ ሠራተኛው የወሰነውን ውሳኔ መሻር የሕግ መርሆዎችን የሚጥስ ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

‹‹በንጉሡ ጊዜ ፀረ አብዮት ወንጀል ፈጽመሃል፤›› ተብለው በደርግ ጊዜ ሰዎች እንደሚከሰሱ ገልጸው፣ ይህንንም ረቂቅ አዋጅ ከዚህ ሥርዓት ጋር አነፃፅረውታል፡፡ ሌላው አቶ ዮሐንስ  ያነሱት በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ የግል ኩባንያ ባለሀብቶች በጡረታ ዐቅድ እንዲታቀፉ ማሻሻያ ማቅረቡ ትክክለኛነት ላይ ነው፡፡

የኩባንያ ባለቤቶች ወይም ባለሀብቶች በርካታ የማኅበራዊ ዋስትና አማራጮች እንዳሏቸው፣ ከእነዚህም መካከል የጡረታ ኢንሹራንስ ሊገዙ እንደሚችሉና ሌሎች የመሳሰሉትን ማድረግ እንደሚችሉ እየታወቀ፣ መንግሥት የራሱ ተጧሪ ሊያደርጋቸው መፈለጉ አስገራሚ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የግል ድርጅት ማለት በኢትዮጵያውያን ብቻ የተያዘ አለመሆኑንና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የውጭ ዜጎች ያቋቋማቸው ኩባንያዎችም እንዳሉ የሚገልጹት የሕግ ባለሙያው፣ እነዚህ የውጭ ዜጎች በአገራችው የተሻለ የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን የሚያገኙ ሆነው ሳለ መንግሥት እነዚህንም ተጧሪ ለማድረግ ማሰቡ አስደናቂ ነው ብለዋል፡፡

መንግሥት ይህንን ማሻሻያ እያደረገ የሚገኘው ካለው ከፍተኛ የገንዘብ ፍላጎት አንፃር እንደሆነ እንደሚገምቱ የሚገልጹት ባለሙያው፣ ‹‹መንግሥት ያልተረዳው ከመንግሥት የተሻለ አገር የሚያለማው የግል ባለሀብቱ መሆኑን ነው፤›› ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

ይህ ረቂቅ ማሻሻያ ሙሉ አይደለም ብለው የሚከራከሩበት ሌላው ነጥብ የጡረታ ሽፋን ያላቸው የቤተሰብ መሪዎች፣ ‹‹የተሽከርካሪ አደጋ ሊሆን ይችላል ወይም በፍትሕ እጦት በሚደርስ የሕግ ተጠያቂነት ለእስር በሚዳረጉበት ወቅት፣ የእሱን ወይም የእሷን እጅ ጠበቀው የሚኖሩ ቤተሰቦቹን የማይሸፍን ጎደሎ ነው፤›› ብለውታል፡፡

እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅና ሞሪታንያ የመሳሰሉ አገሮች በተገለጸው ዓይነት ችግር ለሚፈጠር የቤተሰብ ቀውስ ‹‹የቤተሰብ አበል›› የሚል ዋስትና እንዳላቸው፣ ይህ ማሻሻያ የሚፀድቅ ከሆነ ይህንን ነጥብ ሕግ አውጪው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

ፓርላማው ባለፈው ሐሙስ በአዋጁ ላይ አጭር ውይይት ካደረገ በኋላ ጉዳዩን ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋናነትና፣ በተደራቢነት ደግሞ ለሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ መርቶታል፡፡

 

የሸራተን አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

ሸራተን አዲስን ከ16 ዓመታት በላይ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ የቆዩት፣ የዴንማርክና የፈረንሣይ ጥምር ዜግነት እንዳላቸው የሚነገረው ሚስተር ዢያን ቪ. ማኒጐፍ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡

ከሸራተን አዲስ ማኔጅመንት የወጣው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ሚስተር ማኒጐፍ ላለፉት ወራት በከባድ ሕመም ሲሰቃዩ ከርመው በቅርቡ በሕክምና እየተረዱ ባሉበት አሜሪካ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ 

ከ20 ዓመታት በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደኖሩና ላለፉት 16 ዓመታት ሸራተን አዲስን ሲመሩ የነበሩት ሚስተር ማኒጐፍ፣ የአርመን ዝርያ እንዳላቸውም ተጠቁሟል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ ሆቴሉን እየመሩ በቆዩባቸው ጊዜያት፣ በተለይ ከሆቴሉ ሠራተኞች ጋር ባለመስማማታቸውና ከሠራተኞቹ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲደርስባቸው መቆየቱም ይታወሳል፡፡ አንድ የውጭ ዜጋ በአገሪቱ ዜጐች ላይ በደል መፈጸም እንደሌለበትና ካለመኖሪያ ፈቃድ ለረጅም ጊዜ መኖር እንደሌለበት በመጠቆም፣ ሠራተኞቹ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተቃውሞ ደብዳቤ ማቅረባቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በርካቶችም ከሥራ መሰናበታቸው አይዘነጋም፡፡ 

ስለሚስተር ማኒጐፍ ሕልፈት የሸራተን አዲስ ማኔጅመንት ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጠው ሪፖርተር ጥረት ቢያደርግም፣ ‹‹ፋክስ እናደርግላችኋለን›› ከማለት ባለፈ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ 

ሚስተር ማኒጐፍ ልጅም ሆነ ትዳር እንደሌላቸው በቅርብ የሚያውቋቸው የሪፖርተር ምንጮች ተናግረዋል፡፡

 

መርካቶ ሸራ ተራ በደረሰ እሳት ቃጠሎ ንብረት ወደመ

ሰባት ሰዎች በጭስ ታፍነው ጉዳት ደርሶባቸዋል

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ሸራ ተራ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ፣ ግንቦት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ሰዓት አካባቢ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ግምቱ ያልታወቀ ንብረት ወደመ፡፡ 

አደጋውን ለመቆጣጠር በአካባቢው ያለው የፕላስቲክ ጫማ፣ ዘይት፣ ሳሙና፣ ብርድ ልብስና ለመቀጣጠል አደገኛ የሆኑ ዕቃዎች ክምችት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ አካባቢው በጭስ በመታፈኑ እሳት አደጋ ተቆጣጣሪዎች ወደ ውስጥ ደፍረው ለመግባት እንዳዳገታቸውና ለረዥም ሰዓታት እሳቱን መቆጣጠር ሳይቻል መቆየቱንም አክለዋል፡፡ 

የእሳት ቃጠሎው ከቀኑ 8፡00 ሰዓት አካባቢ መጀመሩን በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው ነጋዴዎች በመተባበር ከየጊቢው ውኃ በመቀባበልና በየጣራው ላይ ወጥተው ውኃ በመርጨት የተቻላቸውን ካደረጉ በኋላ፣ የእሳት አደጋ መከላከል ሠራተኞች እንደደረሱላቸውም ተናግረዋል፡፡ 

የእሳቱ መነሻ በውል ባይታወቅም ከመሀል አካባቢ እንደተነሳና ቤቶቹም እርስ በርስ የተያያዙ በመሆናቸው፣ ለመኪና መግቢያ አስቸጋሪ እንደነበር የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ባለሥልጣን ሠራተኞች ገልጸዋል፡፡ እሳቱ እየጨመረ በመሄዱ ከሰባቱም ክፍለ ከተማ የእሳት መከላከያ ማሽነሪዎች ቢመጡም፣ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት አለመጥፋቱም ታውቋል፡፡ አራት የውኃ ቦቴዎች ውኃ በማቅረብ ሲተባበሩ እንደነበር፣ አንድ የኤርፖርቶች የእሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪ ተጨምሮ በቁጥጥር ሥር ለማዋል እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡ የተዳፈነ እሳት፣ የፕላስቲክ ዕቃዎችና ጨርቃ ጨርቆች ለማጥፋት ሲያስቸግሩ ተስተውሏል፡፡ ሠራተኞቹ እሳቱን እያጠፉ ባለበት ጊዜ ከሥር ከሥር የሱቆቹ ባለቤቶችም ከተቃጠለው ዕቃ ክምር የተለያዩ ዕቃዎችን ለማውጣት ሲረባረቡ ታይተዋል፡፡

አብዛኞቹ በአካባቢው ያሉ ነጋዴዎች ዕቃቸውን በማውጣትና እሳቱ ያልደረሰበት ቦታ በመከመር የማዳን ሥራ ሲሠሩ ተስተውለዋል፡፡ ነጋዴዎቹ አይሱዙ በመከራየት ዕቃቸውን በመጫን ወደተለያዩ ቦታዎች ሲወስዱና ቤታቸውም የተቃጠለባቸው ነዋሪዎች እያለቀሱ በከፍተኛ ሐዘን ሲዋከቡ ታይተዋል፡፡ ንብረታቸውንም አድነው በየቦታው የከመሩት ነጋዴዎች ሲመሽባቸው በላስቲክ እየሸፈኑ ወደ ቤታቸው ለመሄድ ተገደዋል፡፡ 

በወቅቱ ከአሥር በላይ የእሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪዎች በማሰማራት ከ150,000 ሊትር በላይ ውኃ፣ 300 ሊትር ፎም እንደተጠቀሙ የገለጹት አቶ ሰለሞን መኰንን፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠሪያ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ናቸው፡፡ እንደሳቸው ገለጻ፣ የእሳት አደጋው ተነስቷል ተብሎ የተደወለው ከቀኑ 8፡57 ሰዓት ላይ ነው፡፡ ከተደወለላቸው በኋላ ግን፣ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቀድሞ በመድረስ ዕርዳታ እንደጀመረ፣ ሌሎቹም ስድስቱ ክፍላተ ከተሞች በየተራ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ እሳቱ አስቸጋሪ ቢሆንም ከአራት ሰዓት በኋላ ለመቆጣጠር መቻሉን አስረድተዋል፡፡ እስከ ዓርብ ግንቦት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ምሽት ድረስ ስለደረሰው ጉዳት መጠን ማወቅ አልተቻለም ነበር፡፡ 

 

አብረዋቸው የተከሰሱ የድርጅት ባለቤት በዋስ ተለቀቁ

በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የግብዓት አቅርቦትና አስተዳደር መምርያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ በፈቃዱ አሰፋ፣ ተጠርጥረው ከተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ግንቦት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በነፃ ተሰናበቱ፡፡

አብረዋቸው ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የኤቢ ፕላስት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ጌታቸው በየነ፣ የተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ወደ ማታለል ወንጀል ተቀይሮ የ200 ሺሕ ብር ዋስ አስይዘው እንዲፈቱ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

ሁለቱም ተጠርጣሪዎች ተመሳጥረው በሕገወጥ መንገድ የ3,211,411 ብር የግዥ ውል እንዲፈረም በማድረግ በመንግሥትና በሕዝብ ጥቅም ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን በመጥቀስ፣ የሙስና ወንጀል ክስ መስከረም 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በሐምሌ ወር 2006 ዓ.ም. ነው፡፡

አስተዳደሩ ለሚያስገነባቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግብዓት የሚሆን የሳኒተሪ ዕቃ እንዲገዛ የወጣውን የጨረታ የግዥ አፈጻጸም መመርያን ባልተከተለ መንገድ፣ ከደረጃ በታች የሆነ የሳኒተሪ ዕቃ እንዲገዛ መደረጉን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ ሁለተኛ  ተከሳሽ ጨረታውን አሸንፈው ያቀረቡት ምርት ደግሞ ዩፒቪሲ መሆኑ ሲገባው ዩፒቪሲ የሚል ማኅተም የተለጠፈበት የፒፒሲ ምርት መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡ ይኼም የሆነው ምክትል ሥራ አስኪያጁና ነጋዴው ተመሳጥረው መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሶ፣ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ የ3.2 ሚሊዮን ብር ጉዳት እንደደረሰም አስረድቷል፡፡ ሁለተኛው ተከሳሽም በተደጋጋሚ በጨረታ እንዲሳተፉና አሸናፊ እንዲሆኑ አቶ በፍቃዱ እንደረዷቸው  ክሱ ይገልጻል፡፡ 

አቶ አብርሃም ጌታቸው የተባሉት የፒቪሲ ፕላስት ድርጅት ባለቤት የሌሎችን ሰዎች አለማወቅ ተጠቅመው በፒፒሲ ምርት ላይ ዩፒቪሲ የሚል ማኅተም በማስቀመጥና በማታለል፣ በመንግሥት ላይ የ78,147,296 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

አቶ በፈቃዱ ሌላው የተከሰሱበት ወንጀል በጽሕፈት ቤቱ የግብዓት አቅርቦትና አስተዳደር መምሪያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲሠሩ ተገቢ ምክንያት ሳይኖራቸው፣ የ8551 ብር ባለ24 ካራት ስምንት ግራም ብራስሌት ወርቅ ቶፕና ሰላም ኮንስትራክሽን ከተባሉ ተቋራጮች መቀበላቸውን የሚገልጽ ነው፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ አሰምቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸው የሰዎች ምስክሮች፣ የሰነድ ማስረጃዎችና የኤግዚቢት ማስረጃዎች በተጠርጣሪዎቹ ላይ የቀረቡት ክሶች ስለመፈጸማቸው አስረድተዋል? ወይስ አላስረዱም? የሚለውን ጭብጥ ይዞ መመርመሩን በውሳኔው ገልጿል፡፡

አቶ በፍቃዱ ሁለተኛው ተከሳሽ ጨረታ እያሸነፉ የሚያቀርቧቸው የሳኒተሪ ምሮቶች ከስፔስፊኬሸን በታች ስለመሆናቸው ጥቆማ ሲደርሳቸው፣ ሁለተኛው ተከሳሽ (ኤቢ ፕላስት) እንዳይሳተፍ የማድረግና ጨረታውንም የመሰረዝ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል? የሚለውን ከፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የአደረጃጀትና የሥራ መዘርዝር መመርያ ላይ መመልከቱን እንዲሁም ከሁለተኛ ተከሳሽ ጋር መመሳጠራቸው በዓቃቤ ሕግ ማስረጃዎች መረጋገጥ አለመረጋገጡንም ጭብጥ ይዞ መመርመሩን ዘርዝሯል፡፡

አቶ በፈቃዱ ኤቢ ፕላስት የተባለው ድርጅት የሚያቀርበው የሳኒተሪ ዕቃ ከጥራት በታች መሆኑ ጥቆማ ሲደርሳቸው፣ ወደሚመለከተው የሥራ ክፍል መምራታቸውንና በኢትዮጵያ ምዘናና ተስማሚነት ተቋም ተልኮ እንዲመረመር መደረጉን ፍርድ ቤቱ በተጨማሪ አስረጂነት የጠራቸው የጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መመስከራቸውን ገልጿል፡፡ ከጥራት በታች መቅረቡ ተረጋግጦ ጨረታው መሰረዙን ማስረዳታቸውንም አክሏል፡፡ ቅሬታ ቀርቧል ተብሎ ሳይጣራ ጨረታ  መሰረዝ እንደማይችልና ወደሚመለከተው ክፍል ተልኮ ማጣራት መደረጉን፣ ከምስክሩ መረዳት መቻሉን ፍርድ ቤቱ በስፋት ተንትኗል፡፡ አቶ በፍቃዱ ለሚመለከተው ክፍል መርተውና ለዋና ሥራ አስኪያጁ የክፍሉን ውሳኔ አቅርበው ጨረታውን ያሰረዙ በመሆኑ፣ በቀረበው ክስ የአቶ በፈቃዱ ኃላፊነት ነው ተብሎ በማስረጃነት የቀረበው እሳቸውን የማይመለከትና እሳቸውም ቢሆኑ ኃላፊነታቸውን የተወጡ መሆኑን ከማስረዳት ባለፈ፣ የሚያስጠይቃቸው ሆኖ አለመገኘቱን በውሳኔው ጠቅሷል፡፡

ጥራትን የመቆጣጠር ሥልጣን በጽሕፈት ቤቱ አደረጃጀት መሠረት የአቶ በፍቃዱ ሳይሆን የሌላ ኃላፊ መሆኑን፣ የተለያዩ ጽሕፈት ቤቱ ያወጣቸው መመርያዎች እንደሚያረጋግጡ ፍርድ ቤቱ በዝርዝር ገልጿል፡፡ ቀርበው በመሰከሩት ሰዎችም ሆነ የሰነድ ማስረጃዎች በአቶ በፈቃዱ ላይ ስላላስረዱባቸው በወ/መ/ሥ/ሥ/ቁ/141 መሠረት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

አቶ አብርሃም ጌታቸው የኤቢ ፕላስት ድርጅት ባለቤትም የተጠረጠሩበት ወንጀል ሙስና ሳይሆን ወደ ማታለል ወንጀል ተቀይሮላቸው በ200 ሺሕ ብር ዋስ ሆነው እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ አቶ በፍቃዱ ላይ የቀረበው ስምንት ግራም  ብራስሌት ወርቅን በሚመለከት ምስክሮች ካለመሰማታቸውም በተጨማሪ፣ ወርቁ የተገዛው በስማቸውና በአግባቡ መሆኑን ጠቅሶ በእሱም በነፃ እንዲሰናበቱ ብይን ሰጥቷል፡፡ አቶ በፍቃዱ ከእስር እንዲፈቱና ብራስሌት ወርቃቸው ከኮሚሽኑ ኤግዚቢት ክፍል እንዲመለስላቸው አዟል፡፡ በሁለተኛ ተከሳሽ ላይ የመከላከያ ምስክር ለመስማት ለሐምሌ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡