ከጳጉሜ 1 እስከ መስከረም 2 በኦሮሚያ በማህበራዊ የንግድ አድማ መጠራቱን ተከትሎ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ተግባራዊ መደረጉን የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ያስታወቀ ሲሆን መንግስት በበኩሉ፤ የአድማ ጥሪው በህብረተሰቡ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ከሽፏል ብሏል፡፡
የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ለአዲስ አድማስ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ “በሁሉም የኦሮሚያ አካባቢዎች የንግድም ሆነ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የለም፤ ሁሉም ነገር እንደታገደ ነው” ብለዋል፡፡ ሆቴል ቤቶች፣ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮችና የገበያ ስፍራዎች ዝግ ሆነው መሰንበታቸውን ኦፌኮ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በነቀምትና ደምቢዶሎ ከተማ ውስጥ ባለፈው ሰኞና ማክሰኞ 4 ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው አቶ ሙላቱ ተናግረዋል፡፡
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዩች ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መሃመድ ሠኢድ ስለጉዳዩ ከአዲስ አድማስ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ በሁለቱ ክልሎች የተፈጠሩት ችግሮች ከህገ መንግስቱ ጋር የማይጣጣሙ እንደሆኑ ጠቁመው ሁከቱ በዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ ጥፋት ማስከተሉን አስታውቀዋል፡፡
“ህዝቡ በቅንነት የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ከህዝቡ ከራሱ ጋር ተመካክሮ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነቱን መንግስት በመግለጫዎቹ አሳይቷል” ያሉት አቶ መሃመድ፤ ከዚህ በመነሳት የህብረተሰቡን አጀንዳ ቀምተው ለራሳቸው አላማ ለመጠቀም የሚሞክሩ አውዳሚ ኃይሎች እንዳሉ ህዝቡ የተረዳበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
“ህዝብ ከመንግስት ጋር እየተግባባ ችግሮችን ለመፍታት እየጣረ ነው” ያሉት አቶ መሃመድ፤ “በአማራም ሆነ ኦሮሚያ የተረጋጋ ሁኔታ ተፈጥሮ ህብረተሰቡ ቀድሞ ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ እየተመለሰ ነው ብለዋል፡፡
ሱቆች እንዲዘጉ፣ ከበአል ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩ ምርቱን ባለማውጣት የንግድ አድማ እንዲደረግ መልዕክት የተላለፈ ቢሆንም ጥሪው በተጨባጭ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኝ ከሽፏል ብለዋል፤ አቶ መሃመድ፡፡
በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የአድማ ሙከራ ቢኖርም ህብረተሰቡ ወደ ተጨባጭ ሰላማዊ ህይወቱ ተመልሶ በበአል ስሜት ውስጥ ሆኖ እየተገበያየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያን ከተሞች አቋርጠው ወደተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጉዞ ያደረጉ የአይን እማኞች፤ በአብዛኞቹ ከተሞች የንግድ ቤቶች ተዘግተውና ሆቴል ቤቶች ከአገልግሎት ውጪ ሆነው መመልከታቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡  

በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ለደረሰው የህይወት መጥፋት መኢአድ መንግስትን ተጠያቂ አደረገ

የእርቅ መንግስት እንዲመሰረት ፓርቲው ጠይቋል

ባለፈው ሳምንት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በተነሳው የእሳት ቃጠሎ ለደረሰው የህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት መንግስትን  ተጠያቂ ያደረገው የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፤ ጉዳዩ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠይቋል፡፡
ፓርቲው ሰሞኑን በፅ/ቤቱ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤መንግስት በአደጋው 23 ታራሚዎች መሞታቸውን ቢናገርም ቁጥሩ ከተጠቀሰው በላይ ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬ አለኝ ብሏል፡፡
መንግስት ለታራሚዎች ህገ መንግስታዊ ከለላ በመስጠት ደህንነታቸውን መጠበቅ ሲገባው፤ ይህ ሳይፈፀም መሞታቸውም ሆነ ድርጊቱ ከተፈፀመ በኋላ ለታሳሪ ቤተሰቦች ግልፅና የማያሻማ ፈጣን መልስ በመስጠት ፈንታ በቤተሰብ ላይ ከፍተኛ ጭንቀትና አሳዛኝ መጉላላት እንዲደርስ መደረጉን በጥብቅ አወግዛለሁ ብሏል መኢአድ፡፡ በጉዳቱ በደረሰው የሰው ህይወት መጥፋት ማዘኑንም ፓርቲው አስታውቋል፡፡
ፓርቲው በመግለጫው፤ በማረሚያ ቤቱ የደረሰውን ጉዳት ጨምሮ በአማራና ኦሮሚያ ክልል የደረሡ ጉዳቶች በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ፣ ለጠፋው ህይወት መንግስት በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅና የደም ካሣና የዜጎች ማቋቋሚያ ካሣ እንዲከፍል  ጠይቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሣለኝ ነሀሴ 24 የሠጡት መግለጫ ‹‹ጦርነት ከማወጅ የማይተናነስ አሳዛኝም አስደንጋጭም ተግባር ነው›› ያለው ፓርቲው፤ በአስቸኳይ ትዕዛዙ እንዲሠረዝ አሳስቧል፡፡ ፓርቲው ከግጭቶችና ተቃውሞዎች ጋር በተያያዘ የታሠሩ እንዲፈቱና መንግስት ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር ውይይት በማካሄድ የዕርቅ መንግስት እንዲመሰረት ጠይቋል፡፡
አንጋፋ የኢህአዴግ አመራሮች ሠሞኑን በኢቢሲ እየሰጡ ያሉትን ማብራሪያ፣ አዲስ የመፍትሄ ሃሳብ ያፈለቀና ችግሩን አግባቡ የተረዳ አይደለም ሲል ፓርቲው አጣጥሎታል፡፡
የቂሊንጦ ማረምያ ቤት ቃጠሎን ተከትሎ በህይወት ያሉ ታራሚዎች ወደ ዝዋይ፣ ሸዋ ሮቢትና አዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች መዘዋወራቸውን ታውቋል፡፡   

       በጎንደር በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉትን የወልቃይት ኮሚቴ አባላት የፍርድ ጉዳይ ለመከታተል ትናንት ፍ/ቤት አካባቢ ተሰብስበው በነበሩ ነዋሪዎችና የፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ህይወት መጥፋቱን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ የወልቃይት ኮሚቴ አባላትን የፍርድ ቤት ውሎ ለመከታተል ጎንደር ፒያሣ አካባቢ በሚገኘው ፍ/ቤት በጠዋቱ በሺዎች የሚቆጠሩ  የከተማዋ ነዋሪዎች ተሰብስበው የነበረ  ሲሆን ፍ/ቤቱ የተጠርጣሪዎቹን ጉዳይ ለነሐሴ 4 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ እንደተሰማ ግርግር መፈጠሩን ምንጮች አስረድተዋል፡፡ ፖሊስ በአስለቃሽ ጭስ ተቃውሞ የሚያሰሙትን ነዋሪዎች ለመበተን ሙከራ ማድረጉን የጠቆሙት ምንጮች፤ ከቆይታ በኋላ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የመሳሪያ ተኩስ መሰማቱንና ተኩሱ በየአቅጣጫው እስከ አመሻሹ ድረስ መዝለቁን ተናግረዋል፡፡  
የከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች በድንጋይ መዘጋጋታቸውንና ወጣቶች በቡድን እየሆኑ ተቃውሞ ሲያሰሙ መዋላቸውንና ከቀኑ 5 ሰዓት ጀምሮ በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ መቋረጡን ምንጮች አስረድተዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ የከተማዋን ከንቲባ ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት የሞባይል ስልካቸው ዝግ በመሆኑ ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡ በግጭቱ የሰዎች ህይወት ማለፉን ምንጮች ቢጠቁሙም ከፖሊስ ለማረጋገጥ አልቻልንም፡፡
ባለፈው እሁድ በከተማዋ መንግስትን የሚቃወም ሰልፍ ተካሂዶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

“በወረዳ አመራሮች የሚሰሩ ስህተቶች መንግስትን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለው ነው”

   መንግስት ‹‹ህገ ወጥ›› ያላቸውን ቤቶች ያፈረሠበት መንገድ በአለማቀፍ የሠብአዊ መብቶች ድንጋጌና በህግ ተቀባይነት እንደሌለው የገለጹ የህግ ባለሙያዎች፤ድርጊቱ የህግ ተጠያቂነትን ሊያስከትል እንደሚችል ተናገሩ፡፡ ቤታቸው ለፈረሰባቸው ዜጎች፣መንግስት ተለዋጭ ቤት መስጠት አለበትም ብለዋል – የህግ ባለሙያዎቹ፡፡  
ዓለማቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት፤ማንኛውም ሰው ደህንነቱ እንዲጠበቅና መኖሪያ ቤቱ እንዲከበር በፅኑ ይደነግጋል ያሉት አለማቀፍ የህግ ባለሙያው ዶ/ር ያዕቆብ ወ/ማርያም፤በተለያዩ የሠብዓዊ መብት ስምምነቶች፣ የመኖሪያ ቤት ጉዳይ በዋናነት ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡   
‹‹ሠዎች ህገ-ወጥ ቤት ቢሠሩ እንኳን ቤቶቹ ሲሠሩ በዝምታ የታለፉ እንደመሆናቸው በድጋሚ አይፈርሱም›› ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ፤ ‹‹በተለያዩ ሃገራት በህገ ወጥ መንገድ ቤት የሠሩ ሰዎች ካሳ ከፍለው ቤቱ ህጋዊ ይሆንላቸዋል” ሲሉ የሌሎች አገራትን ተመክሮ ጠቅሰዋል፡፡ በቅርቡ የአዲስ አበባ አስተዳደር ያፈረሳቸው ቤቶች አፈራረስም የኢትዮጵያንም ሆነ ዓለማቀፍ የሠብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን የጣሰና ዜጎችን ያለ አግባብ ለእንግልት የዳረገ ነው የሚሉት የህግ ባለሙያው፤ ‹‹የከተማ አስተዳደሩ የግድ ማፍረስ አለብኝ ካለም በቅድሚያ ቤት ሊያዘጋጅላቸው ወይም ቤት ሊያሰራቸው የሚችል ተመጣጣኝ ካሣ መክፈል ነበረበት፤ይህን አለማድረጉ በሠብአዊ መብት ጥሰት ሊያስጠይቀው ይችላል›› ብለዋል፡፡
“አስተዳደሩ ቤቶቹ ሲሠሩ እያየ ዝም ካለ፣የቤቶቹን መሰራት እንደፈቀደ ይቆጠራል” ያሉት የህግ ባለሙያው፤ነዋሪዎች መብራትና ውሃ የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶችን ሲያሟሉ በዝምታ ማለፉ ብቻውን ቤቶቹን ህጋዊ ያደርጋቸዋል ሲሉም ይሞግታሉ፡፡ ቤቶቹ መፍረስ አይገባቸውም ነበር፤ ስለዚህ አስተዳደሩ የፈፀመው ህገ-ወጥ ድርጊት ነው” ብለዋል፡፡
ይህን የአስተዳደሩን ድርጊት ማረም የሚቻለው መንግስት ለተጎጂዎቹ በቂ ካሳ ሲከፍልና ቤት ሰርቶ ሲሰጣቸው ብቻ ነው ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ፤‹‹ወቅቱን ባላገናዘበ መልኩ ቤቶችን በጅምላ አፍርሶ ዜጎችን ሜዳ ላይ መጣል አለማቀፍ የሠብአዊ መብት ድንጋጌዎችን ፈፅሞ የተቃረነ ኢ-ሠብአዊ ድርጊት ነው” ብለዋል፡፡ ቤቶቹን በማፍረስ ተግባር ላይ የተሣተፉ ግለሰቦችም ሆኑ ባለስልጣናትም በግላቸው በህግ መጠየቅ እንዳለባቸው ዶ/ር ያዕቆብ ይናገራሉ፡፡
የህግ መምህርና ባለሙያ አቶ ቁምላቸው ዳኜ በበኩላቸው፤የመጠለያ ጉዳይ በአለማቀፍ የሠብአዊ መብት ድንጋጌዎች ውስጥ በህይወት ከመኖር መብት ጋር ተያይዞ የሚታይ መሆኑን ጠቅሰው፣መጠለያን በዚህ መልኩ ማሳጣት የሠብዓዊ መብት ክብርን የመግፈፍ ድርጊት ነው ብለዋል፡፡ አለማቀፉ የሠብአዊ መብት ድንጋጌ፣ የመንግስት በሲቪል መብቶች ላይ ጣልቃ መግባትን እንደሚከለክል የጠቀሱት ባለሙያው፤መንግስት ቤቶቹን ያፈረሠበት መንገድም በዚህ የህግ ጥሰት የሚታይ ነው ሲሉ አሰረድተዋል፡፡
መንግስት ለዜጎች መጠለያ ማቅረብ ካልቻለ ለራሳቸው እንዲሰሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንዳለበት የጠቀሱት የህግ ባለሙያው፤ለዚህ አንደኛው መፍትሄ ቤቶቹን ከማፍረስ ይልቅ ወደ ህጋዊ መስመር የሚገቡበትን መንገድ ማመቻቸት ነበር ብለዋል፡፡ ቤቶቹ ሲገነቡ መጀመሪያ ማስቆም ይገባ ነበር ያሉት የህግ ባለሙያው፤ቤቶቹ ከተገነቡ በኋላና ዜጎች በተለያየ መንገድ ህጋዊነት እንዲሰማቸው ከተደረገ በኋላ ማፍረሱ የሠብአዊ መብት ጥሰት ነው ብለዋል፡፡
ግለሰቦቹ መብራት ያስገቡበት፣ ሌሎች የልማት መዋጮዎችን ያወራረዱበት ሰነድ ካላቸውና ወረዳው እያወቀ መሰረተ ልማቶችን ያሟሉ ከሆነ፣ በከፊል ህጋዊ እንደሆኑ ይቆጠራል ያሉት ሌላው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የህግ ባለሙያ፤ መንግስት ከዚህ አንፃር መሰረታዊ ስህተቶች መሰራታቸውን አምኖ፣ለተጎጂዎች ተገቢውን ካሳና መጠለያ ሊያቀርብ ይገባል ብለዋል፡፡
ግለሰቦቹ ህገወጥ ናቸው ከተባሉም ግልፅ አማራጮች ተቀምጠው፣በቀጥታ የሚያርፉበት ምትክ መጠለያ ተዘጋጅቶላቸው፣ፍትሃዊ በሆነ ሂደት ተዳኝተው፣ የፍ/ቤት ትዕዛዝ ሲገኝ ብቻ ነው ቤቶች ሊፈርሱ የሚገባው ሲሉ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ “በቂ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠን ነው ቤታችን እንዲፈርስ የተደረገው” የሚለው የዜጎች አቤቱታም ከህግ አንፃር መንግስትን ሊያስጠይቀው ይችላል ብለዋል፤የህግ ባለሙያው፡፡
 የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ በበኩላቸው፤መንግስት ቤቶቹን ከማፍረሱ በፊት ደጋግሞ ማሰብና የተለያዩ አማራጮችን ማስቀመጥ ይገባው ነበር ይላሉ፡፡ ህዝቡ መኖሪያ ቤት የሚያገኝበትን መንገድ መንግስት በሚገባ ማሰብ አለበት የሚሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ “ሰዎቹ ከገበሬ ላይ ቦታ ገዝተው ቤት ሰርተው የሚኖሩ ከሆነ፣መጠነኛም ቢሆን ገንዘብ ያላቸው መሆኑን የሚያመለክት በመሆኑ፣መንግስት ራሱ ዲዛይን አውጥቶላቸው በህጋዊ መንገድ በማህበር ተደራጅተው ኮንዶሚኒየም እንዲሰሩ ቢያደርግ ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል” ብለዋል፡፡  
“ፈረሱ የተባሉት ቤቶች መሰረተ ልማት እስኪሟላላቸው ድረስ ወረዳና ክ/ከተማ ያሉ የመንግስት አካላት የት ነበሩ?” ሲሉ የሚጠይቁት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤“በወረዳና ክፍለ ከተማ አመራሮች የሚሰሩ ስህተቶች መንግስትን በከፍተኛ መጠን ዋጋ እያስከፈለው ነው” ብለዋል፡፡
መንግስት በወረዳ ደረጃ በአመራርነት መመደብ ያለበት ብቃት ያላቸውን ሰዎች ሊሆን ይገባል የሚሉት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው፤እነዚህ የፈረሱ ቤቶች ይሄን ያህል አመት የቆዩት በተለያየ መንገድ የወረዳ አመራሮች ቢፈቅዱላቸው ነው፤በቤቶቹ ግንባታ ላይ የወረዳ አመራሮች እጅ አለበት ብለዋል፡፡ ቤቶቹ ከመፍረሳቸው በፊት ሌሎች አማራጮች በስፋት ሊታዩ ይገባ ነበር ያሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤በቀጣይም ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጎች ቤት ማግኘት መቻል አለባቸው፤መንግስትም መፍትሄ ያገኝለታል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡

በዘውዲቱ ሆስፒታል የእንቅርት ታካሚዋ ለሃሞት ጠጠር ህክምና ሆዷ ተከፈተ

– የህክምና ስህተቱን የፈፀሙት ሃኪም ከሥራ ተባረዋል
– “የሃሞት ጠጠሩ በነፃ ስለወጣልሽ ዕድለኛ ነሽ” ሲሉ ዋሽተዋታል

   በዘውዲቱ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ በተፈፀመ የህክምና ስህተት ሣቢያ እንቅርት ለማስወጣት የሄደችው ታካሚ በስመ ሞክሼ በተፈጠረ ስህተት ለሃሞት ጠጠር ህክምና ሆዷ ተከፈተ። ታካሚዋ ከሁለት ዓመታት ወረፋ ጥበቃ በኋላ ተራዋ ደርሶ በአንገቷ ላይ የወጣውን እንቅርት ለማስወጣት ነበር ወደ ሆስፒታሉ የሄደችው፡፡
ሠላም ደሞዜ የተባለችው ታካሚ በአንገቷ ላይ የወጣውን እንቅርት ለማስወጣት አስፈላጊውን ምርመራ አድርጋ በሆስፒታሉ አልጋ ትይዛለች። በሌላ በኩል ሰላም ኪሮስ የተባለች ታካሚ ደግሞ ለሃሞት ከረጢት ጠጠር ህክምና ወረፋ ጠብቃ ቀጠሮዋ በመድረሱ ነበር ወደ ሆስፒታሉ ያመራችው፡፡ ወጣቷ በቀዶ ህክምና ከህመሟ ለመፈወስ አስፈላጊውን ምርመራ አከናውና በተመሳሳይ ክፍል ውስጥ እንድተኛ ይደረጋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ ሁለቱም ህሙማን የቀዶ ህክምና ሊደረግላቸው ቀጠሮ ተይዞላቸው ሲጠባበቁ ከቆዩ በኋላ ለእንቅርት ህክምና ወደ ሆስፒታሉ ያመራችው ሰላም ደሞዜ በቅድሚያ ወደ ቀዶ ህክምናው ክፍል ትገባለች። የእንቅርት ታካሚዋ በቀዶ ህክምናው ክፍል ከገባች በኋላ ለሃሞት ከረጢት ጠጠር ህክምና ሆዷ ይከፈታል፡፡ ይሁን እንጂ በታካሚዋ ሃሞት ውስጥ ለቀዶ ህክምና የሚያበቃ ችግር አለመኖሩን ያስተዋሉት የቀዶ ህክምና ባለሙያው፤ ሆዷን መልሰው በመዝጋት የእንቅርት ማውጣት ህክምናውን ያደርጉላታል፡፡
ጉዳዩ ከፍተኛ መደናገጥ የፈጠረባቸው ሃኪሙ፤ በወቅቱ ስለተፈፀመው ሁኔታ አንዳችም ነገር ሳይናገሩ የቀዶ ህክምና ክፍሉን ለቀው ይወጣሉ። ከስፍራው ያገኘናቸው ምንጮች እንደገለፁልን፤ የሀኪሙ ረዳቶችና በስፍራው የነበሩ የህክምና ባለሙያዎች ችግሩን ለመሸፈንና የተፈጠረውን ስህተት ለመደበቅ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ሲሆን፤ ታማሚዋ ለእንቅርት ቀዶ ህክምና ወደ ሆስፒታሉ ቢመጡም የሃሞት ከረጢት ጠጠር ችግር ስለተገኘባቸው ህክምናው በነፃ እንደተደረገላቸውና በዚህም ዕድለኛ እንደሆኑ በመንገር ቤተሰቦቻቸውን ለማሳመን ጥረት አድርገዋል ተብሏል፡፡ ሁኔታው ያልተዋጠላቸው የታማሚዋ ቤተሰቦች ቀደም ሲል ምንም ዓይነት የህመም ምልክት ባልታየበት፣ ምርመራና ቅድመ ህክምና ባልተደረገበት ሁኔታ በድንገት ለሃሞት ጠጠር ቀዶ ህክምና የሚያበቃ ችግር ሊፈጠር አይችልም በሚል ከሆስፒታሉ አስተዳደርና ከህክምና ባለሙያዎቹ ጋር ውዝግብ ይፈጥራሉ፡፡ ጉዳዩ የሆስፒታሉ አስተዳደር  ኃላፊዎች ጋር ደርሶም እንዲጣራ ከተደረገ በኋላ ትልቅ የህክምና ስህተት መፈጠሩ ታምኖበት፣ የህክምና ባለሙያዎቹና አስተዳደሩ ቤተሰቦቿን ይቅርታ በመጠየቅ ለታካሚዋ የቅርብ የህክምና ክትትል እንዲደረግላት የተወሰነ ሲሆን የቀዶ ህክምና ባለሙያውና ረዳቶቹ ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የዘውዲቱ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ተረፈ አሰፋ፤ የህክምና ስህተቱ መፈፀሙን አምነው ስህተቱ የተፈፀመው በወቅቱ የቀዶ ህክምናውን ያደረጉት ሃኪምና ረዳቶቻቸው ታካሚዋ በትክክል የመጣችው ምን ዓይነት ህክምና ልትፈጽም መሆኑንና ሌሎች ሁኔታዎችን በአግባቡ ሳያረጋግጡ ህክምናውን በመጀመራቸው ነው ብለዋል፡፡
አንድ ሰው የቀዶ ህክምና ከማድረጉ በፊት በአግባቡ ሊደረግ የሚገባው “ሰርጂካል ሴፍቲ ቼክ ሊስት” መኖሩን የጠቆሙት ዶ/ር ተረፈ፤ በዚህች ወጣት ታካሚ ላይ ይህ ጥንቃቄ ሳይደረግ በመቅረቱ ስህተቱ መከሰቱን አስረድተዋል፡፡
የስህተቱ መፈፀም ሳያንስ በወቅቱ ስህተቱ አምኖና ስለ ሁኔታው ለቤተሰቦቿ ትክክለኛ መረጃ ሰጥቶ ይቅርታ መጠየቅ ተገቢ የነበረ ቢሆንም ይህም አለመደረጉን ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡
“አሁን ታካሚዋ ለህይወቷ የሚያሰጋት ምንም አይነት ችግር የሌለባት መሆኑ በህክምና ባለሙያዎች በሚገባ ስለተረጋገጠ ስለጉዳዩ ለቤተሰቦቿ በቂ መረጃ በመስጠት ይቅርታ ጠይቀናቸዋል፡፡ ታማሚዋ ግን ከሆስፒታሉ እንድትወጣ በሃኪሞቿ ቢፈቀድላትም ሁለት ቀዶ ህክምና በማድረጓ በቅርብ ሆና የጤናዋን ሁኔታ እንድንከታተላት ስለፈለግን አሁንም በሆስፒታሉ ውስጥ ትገኛለች፡፡ የጤናዋ ሁኔታ ግን በጣም ጥሩ ነው” ብለዋል – ዶ/ር ተረፈ አሰፋ፡፡ ስህተቱን የፈፀሙት የቀዶ ጥገና ሃኪም በኮንትራት የተቀጠሩ መሆናቸውን ያመለከቱት የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ፤ ከሥራና ከደመወዝ እንዲታገዱ በማድረግ የዲሲፕሊን እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል፡፡
ትልቁ ስህተት የቀዶ ሃኪሙ ቢሆንም ሥራው ላይ የተሳተፉት የሀኪሙ ረዳቶችም ከተጠያቂነት ሊያመልጡ እንደማይችሉ ጠቁመው እነሱም የዲሲፕሊን እርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል – ዶ/ር ተረፈ፡፡  

ከሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ የተመለሰው የብራና መጽሐፍ እያወዛገበ ነው

• ከዩኒቨርስቲው ጋር የተፈራረሙት የደብረ ሊባኖስ ገዳም አስተዳዳሪ ከሥራቸው ታግደው ነበር
• ሐዋርድ ያዘጋጀው ውል የባለቤትነት መብትን ይነፍጋል
• ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትቀበለው ውል እንዲዘጋጅ ትዕዛዝ ተሰጥቷል

  “እውነት እና አገልግሎት” ተቋማዊ ብሂሉና መፈክሩ ነው፡፡ በተለይ፣ ለጥቁሮች በሚሰጠው የከፍተኛ ትምህርት ዕድልና አስተምሮ በሚያወጣቸው ጥቁር ምሁራን ብዛት ይታወቃል – የአሜሪካው ሐዋርድ ዩኒቨርስቲ፡፡
የዘርና የቀለም ልዩነቶች፣ ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ በደሎች ያስከተሏቸውን መድልዎች፤ ለማኅበራዊ ፍትሕ በቆሙና ለሰብአዊ ነፃነት በሚሟገቱ ምሁራን ማስወገድ ዓላማው ያደረገው ዩኒቨርስቲው፤ በአፍሪካ፣ በአሜሪካና በሌላውም ዓለም የተበተኑ ጥቁሮችን የታሪክና የባህል ቅርሶች ያካበተበት የምርምር ማዕከሉም ከዓለም በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል ያደርገዋል፡፡
በየአጋጣሚው ያሰባሰባቸውን ቅርሶችና ውርሶች፣ ወደ ጥንት ቦታቸውና ትክክለኛ ባለቤቶቻቸው በሕጋዊ መንገድ መመለስ፣ “ታሪካዊና ባህላዊ ሀብቶቹን ማክበር ነው፤” ይላሉ፣ የዩኒቨርስቲው የሥነ መለኰት ት/ቤት የአካዳሚያዊ ጉዳዮች ተባባሪ ዲን ዶ/ር ጌይ ባይረን፡፡ በተለይም ኢትዮጵያዊ ቅርሶችን ለኢትዮጵያ የመመለስ ጉዳይ፣ የት/ቤቱ የቆየ ፍላጎት እንደነበርና ይህም በአሜሪካም ሆነ በሌላው ዓለም ቅርሶቹን በግልና በተቋም ለያዙ ግለሰቦች፣ ሙዝየሞችና ተቋማት አርኣያነት እንዳለውና ተነሣሽነትንም እንደሚፈጥር ዶ/ር ባይረን ያስረዳሉ፡፡
በት/ቤቱ ማኅደረ ቅርስ ከተከማቹት ኢትዮጵያዊ የብራና ሥነ ጽሑፍ ሀብቶች መካከል፣ ገድለ ቅዱስ ሰራባሞንና ገድለ ቅዱስ ጳውሎስ አንዱ ነው፡፡ የብራና መጽሐፉ፣ በ1993 ዓ.ም. ዶ/ር አንድሬ ቲውድ ከተባሉ የዩኒቨርስቲው የቀድሞው ተማሪ በስጦታ የተበረከተ ሲሆን የ4ኛው መ/ክ/ዘመኑን ሰማዕት ቅዱስ ሰራባሞንና የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን ገድል በአንድ ጥራዝ የያዘ ነው፡፡ ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከዐረብኛ ወደ ግእዝ የተተረጎመው በዘጠነኛው የደብረ ሊባኖስ ዕጨጌ አባ መርሐ ክርስቶስ አስተዳደር(ከ1456-1490 ዓ.ም.) ነበር፡፡
የጥንተ ክርስትና እና የሐዲስ ኪዳን ምሁር የሆኑት ዶ/ር ባይረን፣ የብራና መጽሐፉን ወደ ዲጅታል በመለወጥ፣ የትመጣውን ለማወቅ ጥናት ካደረጉት የሥነ መለኰት ት/ቤቱ ምሁራን አንዱ እንደነበሩ፣ የዩኒቨርስቲው ድረ ገጽ ዘግቧል፤ የገድሉ ጥንተ ባለቤት የደብረ ሊባኖስ ገዳም መሆኑ የታወቀውና ወደ ጥንት ቦታው ለመመለስ የተወሰነውም በጥናቱ ሒደት እንደነበር በዘገባው ተገልጧል፡፡ ከገድሉ ይዞታ ጋር በተያያዘ አስተዳደራዊና ሕጋዊ አካሔዶችን ጨምሮ የተለያዩ ዕንቅፋቶች ዩኒቨርስቲውን እንዳጋጠሙት፣ ድረ ገጹ በጥናቱ የተሳተፉ ምሁራንን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ዩኒቨርስቲው ገድሉን ወደ ጥንት ቦታው በሕጋዊ መንገድ ለመመለስ በማሰብ፣ በሕግ አማካሪው አርቃቂነት “የስጦታ ውል” የተሰኘና በስምንት ነጥቦች የተዘረዘረ የስምምነት ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡ ውሉ በሐዋርድ ዩኒቨርስቲና በደብረ ሊባኖስ ገዳም መካከል የተፈፀመ መሆኑን የሚገልፀው ዘገባው፤ በሥነ መለኰት ት/ቤቱ ዋና ዲን ዶ/ር አልቶን ፖላርድና በገዳሙ ፀባቴ (አስተዳዳሪ) አባ ወልደ ማርያም አድማሱ እንደተፈረመበትም ጠቁሟል፡፡ ይሁንና የውሉ ይዘት  ከባለቤትነት መብትና ከቅርሱ አመላለስ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ሆኖ ተገኝቷል ይላሉ ምንጮች፡፡
ዩኒቨርስቲው÷ “ከማናቸውም ግዴታ ነፃ የሆነ የባለቤትነት መብት በብራና መጽሐፉ ላይ አለው” የሚለው የውሉ መግቢያ፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚመልሰውም “በስጦታ ለመስጠት በመፈለጉ” እንደኾነ ይገልፃል፡፡ የብራና መጽሐፉን ለገዳሙ በስጦታ የሚሰጥበት የባለቤትነት መብት እንዳለው ገዳሙ መስማማቱን የሚገልፀው ውሉ፤ ገዳሙም የብራና መጽሐፉን ሲቀበል፣ ዩኒቨርስቲው ሙሉ በሙሉ የሚያስተላልፈው፣ “አካላዊ የባለቤትነት መብት”ን እንደሆነ አስፍሯል፡፡ ገዳሙን በመወከል የፈረሙት ሓላፊም፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውል ስምምነቱን እንድታከብር የሚያደርግ ዋስትና የመስጠት ሥልጣን እንዳላቸው በውል ሰነዱ ላይ ተመልክቷል፡፡
ባለፈው ሰኞ፣ የዩኒቨርስቲው ሓላፊዎችና ምሁራን በፓትርያርኩ ጽ/ቤት ተገኝተው ገድለ ቅዱስ ሰራባሞን ወጳውሎስን ለገዳሙ ባስረከቡበት ወቅት፣ በግልጽ የተነሡት ተቃውሞዎችና ስጋቶች፣ አስተዳዳሪው ከዩኒቨርስቲው ጋር የተፈራረሙት ሰነድ፣ የገድሉን ባለቤትነት ለገዳሙ ሳይሆን ለዩኒቨርስቲው መስጠቱን አረጋግጧል፡፡
ዩኒቨርስቲው ገድሉን ወደ ጥንት ቦታው መመለሱን ቤተ ክርስቲያኒቱ በከፍተኛ አድናቆት እንደምትመለከተውና እንደሚያስደስታት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ተናግረዋል፡፡ “ጥንታዊው ብራና ቅርሳችን በመሆኑ ብንቀበለውም ስምምነቱ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕጋዊ የባለቤትነት መብት የሚጎዳ፣ በትውልዱም ዘንድ የሚያስነቅፍ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም፤” ሲሉ ተቃውመዋል፡፡
የውል ሰነዱም፣ በልዩ ጽ/ቤታቸው፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የውጭ ግንኙነት መምሪያ፣ በሕግ አገልግሎቱና በቅርሳቅርስ ጥበቃ መምሪያ በጋራ እንዲታይና እንዲመረመርም ፓትርያርኩ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
የደብረ ሊባኖስ ገዳም የሚገኝበትን የሰሜን ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሊቀ ጳጳስነት የሚመሩት አቡነ ቀውስጦስ በበኩላቸው፣ የቅርሱ መመለስ የሁላችን ደስታ ቢሆንም የተመለሰበት ሒደት ግን የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓትና መዋቅር እንዲሁም የገዳሙን ክብር እንዳልጠበቀ ገልጸዋል፡፡ ሦስተኛ ወገን በማስገባት በአስተዳዳሪውና በዩኒቨርስቲው የተፈረመውን ስምምነት÷ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ ሊቀ ጳጳሱ፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፣ ቅዱስ ፓትርያርኩና ቅዱስ ሲኖዶሱ ሳያውቁትና ሳይመረምሩት ሕጋዊ የባለቤትነት መብትን በሚያሳጣ መልኩ መፈጸሙን ብፁዕነታቸው አስረድተዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖናና መዋቅር በመጣስ “ለመታየት እና ለመግነን” ሲባል የተፈጸመው ድርጊት አግባብ ያለመሆኑን ሊቀ ጳጳሱ በርክክቡ ወቅት በመናገራቸውም፣ “እዚያች ገዳም ትኖራታለህ፤ እንተያያለን፤ የፈለከውን ሹምበት” በሚል በገዳሙ አስተዳዳሪ መዘለፋቸው ተጠቅሷል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የገዳሙ አስተዳዳሪ ባለፈው ረቡዕ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በተጻፈ ደብዳቤ÷ ከሥራ፣ ከደመወዝና ከአገልግሎት ታግደው እንደነበር ታውቋል፡፡ ከትላንት በስቲያ የገዳሙን መነኰሳት አስከትለው በመምጣት በፓትርያርኩ ፊት ሊቀ ጳጳሱን ይቅርታ በመጠየቃቸው በመካከላቸው  ዕርቀ ሰላም ወርዷል፤ ተብሏል፡፡  ይኹንና አስተዳዳሪው “ተጠሪነቴ ለቅዱስ ፓትርያርኩ ነው” በሚል ያለሥልጣናቸው ከዩኒቨርስቲው ጋር ፈጽመውታል የተባለው ስምምነት ያስነሣቸው ስጋቶችና ተቃውሞዎች ግን መቋጫ አላገኙም፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ የባለቤትነት መብቷን አሳልፋ ሰጥታ መልሳ በስጦታ መልክ የምትቀበልበት አንዳችም ምክንያት እንደሌለና የዩኒቨርስቲውም ፍላጐት እንዳልሆነ ሒደቱን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡  የስጦታ ውሉ ባስነሳው ውዝግብ ሳቢያ ዩኒቨርስቲው የሕግ አማካሪውን ሳያሰናብት እንዳልቀረም እኒሁ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቷ በበኩሏ፤ “የስጦታ ውል” ሰነዱን እንደምትቃወመው ለዩኒቨርስቲው በይፋ በማሳወቅ፣ ተቀባይነት ያለው ስምምነት እንዲዘጋጅ ጥያቄ ማቅረብ እንዳለበት ተወስኗል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ቤ/ክርስቲያኗ የአሜሪካንና የአውሮፓን ዩኒቨርሲቲዎች፣ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ባደመቁት  ሌሎች ቅርሶቿ አመላለስ ላይ የራሱ አዎንታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለዋል፡፡

ይድረስ ለኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር
ሰሞኑን ሥርጭቱን በጀመረው “ቃና ቲቪ” ይዘት እና አሰራር ላይ ለመወያየት በደብዳቤ
ባሳወቅናችሁ መሰረት ተወካያችሁን መላካችሁ ይታወቃል፡፡  የኪነ ጥበብ ሞያ ማኅበር ተወካዮቹ (የእናንተም ባሉበት) በተጠቀሰው ጉዳይ ለሁለት የተለያዩ  ቀናት የጋራ ውይይት አካሂደው የጋራ የአቋም መግለጫ ማውጣታቸው ይታወቃል፡፡ ይህ የጋራ  አቋም በፅሁፍና በንባብ ለሚዲያ ከመቅረቡ በፊት የእናንተ ሁለት ተወካዮችን ጨምሮ የሁሉም   የሞያ ማኅበር ተወካዮች መስመር በመስመር በጥንቃቄ ተመልክተው ማሻሻያና ማረሚያ ካደረጉ  በኋላ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫው የተሰጠ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ መግለጫ ከመሰጠቱ አንድ ቀን ቀደም  ብሎ (በ20/07/2008) የደራስያን ማኅበር ልሳን በሆነውና ዘወትር ማክሰኞ ምሽት በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 በሚቀርበው ፕሮግራም ላይ የመግለጫውን ፍሬ ሃሳብ ለህዝብ በመግለፅ ሚዲያዎች እንዲገኙ መረጃ ስታደርሱ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ይህ ጥሬ ሀቅ ባለበት ሁኔታ ባለፈው ቅዳሜ ሚያዚያ 1 ቀን 2003 ዓ.ም በወጣው የአዲስ አድማስ  ጋዜጣ ላይ የደራስያን ማኅበር ፕሬዝደንት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ የሰጡት ከእውነት የራቀና የተዛባ  መግለጫ እጅግ የሚያሳፍርና የሚያሳዝን ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ የመላው የደራስያን ማኅበር አመራርና አባላት እምነት እንዳልሆነም እናምናለን፡፡ የእሳቸው ማኅበር ተወካይና ሌሎች የጥበብ ማኅበራት በጋራ ተወያይተው ያወጡትን መግለጫ በምን ምክንያትና መነሳሳት ለመካድ እንዳነሳሳቸው ለጊዜው ያወቅነው ነገር የለም፡፡ በሂደቱ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ሲሳተፍ የነበረውን የማኅበራቸውን ተወካይ፤ “መግለጫውን ለመከታተል የተገኘ ነው” በማለት ከደራሲያን ማኅበር ተወካይነት ወደ ሚዲያ ተወካይነት ለውጠው፣ ለጋዜጣው ለመግለፅ ለምን እንደተገደዱም አልተረዳንም፡፡ ከዚህም በላይ ማህበራቱ የቴሌቪዥን ጣቢያውን በሚመለከት እያቀረቡት ካለው አመክንዮና ለህዝብ ከገለፁት አቋም ፈፅሞ የራቀና የማናውቀውን ጉዳይ በመናገር አንባቢን ግራ ከማጋባታቸውም በላይ የማኅበራቱን ጥያቄ ያልተገባ ለማስመሰል መሞከራቸው ከምን በመነጨ አስተሳሰብና ዓላማ እንደሆነ ለጊዜው አልደረስንበትም፡፡ በእሳቸውና በመላው የጋዜጣዊ መግለጫው ተሳታፊ በነበሩ የሚዲያ አካላት እጅ በሚገኘው ባለ አምስት ገፁ የሞያ ማኅበራቱ የአቋም መግለጫ በየትኛው አንቀፅ ላይ ይሆን የሳንሱር ጉዳይ የተነሳው!? የኢትዮጵያ ደራስያንን እወክላለሁ የሚል
የማኅበር ፕሬዚደንት የተፃፈን ፅሑፍ አንብቦ መረዳት ተሳነው ቢባልስ ማን ያምን ይሆን!? የሆነስ
ሆነና “እነ በዓሉ ግርማን የመሳሰሉ ፀሐፍት በሳንሱር ምክንያት የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል”
ማለታቸውስ የደራስያን ጉዳይ ጉዳዬ ነው ብሎ የፕሬዚደንትነት ሥልጣን ከተቆናጠጠ ግለሰብ ይጠበቃል ወይ!? ሌላው ቢቀር የደራስያን ማኅበር የአመራር አባል በነበረው ደራሲ እንዳለጌታ  ከበደ ጥልቅ ጥናትና ምርምር የታተሙትን “ማዕቀብ” እና “የበዓሉ ግርማ ሕይወትና ሥራዎች” የተሰኙ በብዙዎች የተነበቡ መፃሕፍትን ቢያነቡ ኖሮ በዓሉ ግርማን ጨምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ በሳንሱር ምክንያት የሕይወት መስዋዕትነት የከፈለ (የተገደለ) አንድም ደራሲ እንደሌለ በተረዱ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው የኪነ ጥበብ ሞያ ማኅበራቱ በመግለጫቸው ያሉት ዋና ፍሬ ሀሳብ ዶ/ር ሙሴ በስህተት አልያም በችኮላ ተረድተው እንዳሉት ሳይሆን “ቃና” ቴሌቪዥን ለውጭ ሀገር ፕሮግራሞች የሰጠው (70%) ተገቢ አይደለም የሚል ነው፡፡ ይህ ሀሳብ የሳንሱር ሳይሆን በሀገር ውስጥ፣ በሀገር አቅም በሚሰሩ ፊልሞች ላይ ጫና ፈጥሮ ፍትሀዊ ተወዳዳሪነት እንዳይኖር በማድረግ፣ ዳዴ በማለት ላይ ያለውንና የብዙ ዓይነት ጥበቦችና ባለሙያዎች ውህደት ውጤት የሆነውን የኢትዮጵያ ሲኒማ አቀጭጮ ያጠፋል፣ አዲስ ለሚከፈቱ ጣቢያዎች በቀላሉና በውስን ሰዎች ሳይለፉ ገንዘብ እንደሚሰራ በማሳየት በመስኩ የተሰማሩ የኢትዮጵያ ዜጎች በሀገራቸው ስለ ሀገራቸው ጉዳይ የሚተርክ ፊልም በመስራት እንዳይጠቀሙና ሞያውን እንዳያሳድጉ እንቅፋት ይሆናል፣ ህዝብን የሚያረካ ሥራን የሰሩና ይሁንታን በማግኘት የተደነቁ ባለሙያዎችም ዝናቸውን በመጠቀም የደሀ
ህዝባቸውን ችግር ለመቅረፍ በሚደረጉ የማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ የሚያደርጉትን በጎ እንቅስቃሴና ቅስቀሳ ተፅዕኖ አልባ በማድረግ ያዳፍነዋል የሚል ነው፡፡ በእግረ መንገድም ፊልሞቹ በአብዛኛው ከምዕራባውያን የሚመጡ እንደመሆናቸውና የሚተላለፈው ለቤተሰብ ቅርብ በሆነው የቴሌቪዥን ሚዲያ በኩል ከመሆኑ አንፃር አጉል ባህል በቀላሉ ታዳጊ ህፃናትና ልጆች ላይ እንዳይሰርፅ ሥጋታችንን የገለፅንበት ነው፡፡ የኪነ ጥበብ ሞያ ማኅበራቱ በጋራ ባካሄዱት ውይይት ዶ/ር ሙሴ የእሳቸውን ማኅበር በመወከል በተገኘው ግለሰብ እምነት ከሌላቸው፣ ከቢሮአቸው በአራት እርምጃ ከሚርቀው የጋራ ማኅበራቱ
መሰብሰቢያ ቢሮ በመምጣት ጉዳዩን ማጣራት ይችሉ ነበር፡፡ አልያም በአሁን ሰዓት የደራስያን አመራር አባል የሆኑት የሥራ ባልደረባቸው በዚሁ ጋዜጣ ሚያዝያ 26 ቀን 2008 ዓ.ም የፃፉትን ጥልቅና ለብዙዎች ስለ ጉዳዩ የበለጠ ግንዛቤ ያስጨበጠ ፅሑፍ ቢቻል አንብበው ካልሆነም ካነበበ ሰምተው አስተያየታቸውን ቢሰጡ ኖሮ ትዝብት ላይ የሚጥል ስህተት ባልሰሩ፣ መልካም ሥም የነበረውን ማኅበራቸውንም ባላቀለሉ ነበር እንላለን፡፡
(ተፃፈ፡- ከ “የኢትዮጵያ  የኪነ ጥበብ ማኅበራት
ጊዜያዊ አስተባባሪ”)

አዲሱ “ቃና” ቴሌቭዥን የአርቲስቶችን መንደር አናወጠ

      የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች፣ የቲያትር ባለሙያዎች ፣ የሙዚቀኞችና  የሰአሊያን ማህበራት እንዲሁም አላቲኖስ የፊልም ሰሪዎች ማህበር ሰሞኑን በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ አዲሱ የ“ቃና” ቴሌቪዥን የፕሮግራም ይዘት የአገሪቱን የሲኒማ ጥበብ አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ይዘቱን ሊያስተካክል ይገባል አሉ፡፡
“ቃና” ቴሌቪዥን በበኩሉ፤ የአገሪቱን የፊልም ኢንዱስትሪ ለማሳደግ እተጋለሁ ብሏል፡፡
“ቃና” 70 በመቶ የውጭ ሀገር ፊልሞችን፣ 30 በመቶ የአገር ውስጥ ፕሮግራሞችን ሊያቀርብ መዘጋጀቱን የጠቆሙት ማህበራቱ፤ የይዘት ምጣኔው የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያላገነዘበና የባህል ወረራን የሚያስፋፋ ነው ሲሉ ነቅፈዋል፡፡ የአደጋው ምንጭ በዋናነት የውጭ ሀገር ፊልሞችን ተርጉሞ በዳቢንግ (ድምጽ በመቅዳትና አስመስሎ በመለጠፍ) ማቅረቡ ነው ብለዋል፡፡
በቴሌቪዥን ጣቢያው የሚቀርቡት የውጭ ሀገር ፊልሞች ንግድ ተኮር በመሆናቸው ምንም አይነት ትምህርታዊና ሞራላዊ ይዘት የላቸውም ያሉት ማህበራቱ፤ የባህል ወረራን በማስፋፋት ትውልድን ከማጥፋታቸው በፊት መንግስት ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡
ጣቢያው አጭር እድሜ ያለውን የተከታታይ ድራማ ታሪካችንን በማቀጨጭ የፊልም ኢንዱስትሪውን ዕድገት የሚያሰናክል በመሆኑ ፕሮግራሙን በድጋሚ ሊከልስ ይገባዋል ብለዋል፤ ማህበራቱ፡፡
ባለፈው ዓመት “ዳና” የቴሌቪዥን ድራማ 8 ሚሊዬን ብር ገቢ ለመንግስት ማስገኘቱን የጠቀሱት ማህበራቱ፤ “ቃና” በዚህ ይዘቱ የሚቀጥል ከሆነ ግን ትውልድ ከማጥፋቱ በተጨማሪ መንግስት ማግኘት የሚገባውን ጥቅም ያሳጣዋል ብለዋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ በብሄራዊ ቲያትር በሰጡት በመግለጫ ላይ የቴሌቪዥን ጣቢያውን የሥራ ሐላፊዎች ለምን እንዳልጋበዙ የተጠየቁት ማህበራቱ፤ የተቻላቸውን ያህል ጥረት ቢያደርጉም ሊያገኙአቸው እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ የ“ቃና” ቴሌቪዥን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ኃይሉ ተክለሃይማኖት በበኩላቸው፤ ጣቢያው በመግለጫው ላይ አለመጋበዙን ገልፀው፤ በይዘቱ ዙሪያም ቀርቦ ሊያናግራቸው የሞከረ ማህበርም ሆነ ግለሰብ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ በፕሮግራሙ ይዘት ላይ ችግር አለ ብሎ የሚያምን አካል በማንኛውም ጊዜ ሊያነጋግራቸው እንደሚችልም ገልፀዋል – ሃላፊው፡፡
ባለፉት 50 ዓመታት የቴሌቭዥን ታሪክ በተለያዩ አገራት በራሳቸው ቋንቋ ተተርጉመው ባህልና እሴቶችን ሳይጋፉ የቀረቡና እየቀረቡ ያሉ የመዝናኛ ስራዎች፣ በየአገሩ ያሉትን የፊልምና የቴሌቪዥን ኢንዱስትሪ አሁን ላለበት ደረጃ አድርሰውታልም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ጣቢያው ከመቋቋሙ በፊት በአገሪቱ ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው፤ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ከሚመለከቱ ኢትዮጵያውያን ግማሽ ያህሉ የሚያዩት የውጭ አገር ይዘት ያላቸውንና  በሌላ ቋንቋ የተሰሩትን ሲሆን የሚያዩትም እንዲሁ እንደወረዱ መሆኑን የጠቆሙት  አቶ ኃይሉ፤ አሁን ጣቢያው ለእይታ የሚያበቃቸው ፊልሞች ግን የተመረጡና  ለማህበረሰቡ ትርጉም ሊሰጡ የሚችሉት ብቻ ናቸው፡፡
ፊልሞቹ በቀጥታ የተተረጐሙ ሳይሆኑ በእኛ ሀገር ባህል፣ አባባልና አስተሳሰብ የተቃኙ እንደሆኑም ጠቁመው፤ ያልተገቡ የተባሉ የፊልሙ ክፍሎችም ተቆርጠው እንደሚወጡ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ጣቢያው በቲያትር ጥበባት የተመረቁ ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያንን በፀሐፊነት፣ በዳይሬክቲንግ፣ በድምጽና በቪዲዮ ኤዲቲንግ ቀጥሮ እያሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኃይሉ፤ በቀጣይም የእራሱን አገራዊ ስራዎች ለመስራት በእንቅስቃሴ ላይ ነው ብለዋል። ለ“ቃና” ፕሮግራሞቹን የሚያቀርበው “ቢ. ሚዲያ” የተባለው ኢትዮጵያዊ ድርጅትም ፕሮግራሙን በዶላር በመሸጥ፣ የውጪ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገባም የጣቢያው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አክለው ገልፀዋል፡፡
ደራሲያንና የፊልም ምሁራን በጉዳዩ ዙሪያ ያላቸውን አስተያየት ለማወቅ አዲስ አድማስ ሁለት አንጋፋ ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡ የጣቢያው ይዘት ለኢትዮጵያዊው ተመልካች ያን ያህል ይጠቅማል ብዬ አላምንም፤ ጉዳቱ ግን ከፍተኛ ነው ያለው ደራሲ ኃይሉ ፀጋዬ፤ የፕሮግራሙ ይዘት የአገር ውስጥ 30፣ የውጪው 70 እጅ መሆኑ ለአገር ውስጥ እጅግ ዝቅተኛ ትኩረት መሰጠቱን ያሳያል፤ ይሄ ደግሞ እየተንገዳገደ ያለውን የፊልም ኢንዱስትሪ ያቀጭጨዋል ብሏል፡፡
የጣቢያው የፕሮግራም ይዘት ከፍተኛ የባህል ወረራን ከማስፋፋቱም በላይ ለጥቂት ሰዎች የስራ እድል በመፍጠር በመስኩ የተሰማሩ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎችን ስራ እንደሚያሳጣም ደራሲው ገልጿል፡፡
ተቋሙ ገንዘብን መሰረት ያደረገ መሆኑን የገለፀው ኃይሉ ፀጋዬ፤ ይህ ደግሞ ኃላፊነት የጎደለው ስራ ነው ብሏል፡፡
የትያትር ባለሙያው ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ጀዋሬ በበኩሉ፤ “የጣቢያው መፈጠር ገንቢ ነገር አለው፤ ለምሳሌ የህብረተሰቡን የፊልም ማጣጣም አቅም ይጨምራል፡፡ ሆኖም ጣቢያው ለውጪ ፊልሞች የሚሰጠው ድርሻ ዝቅ ማለት አለበት” ሲል አስተያየቱን ሰንዝሯል፡፡
“ባህልን ባላገናዘበና ይህንን ለመቆጣጠር የሚያስችል ህግ ባልተረቀቀበት ሁኔታ በስፋት መልቀቁ ግን አደጋ አለው ያለው ፕሮፌሰሩ፤ መጀመሪያ ህግ መውጣት አለበት፤ ፊልሞቹ ባህልን፣ ስነ ልቦናንና፣ እምነትን ጠብቀው ተጣርተው የሚቀርቡና በህግ የሚመሩ መሆን አለባቸው ብሏል፡፡ “በርግጥ ውድድር መኖር አለበት፤ ውድድር መኖር ያለበት ግን በእኩል የመወዳደሪያ ሜዳ ላይ ነው፡፡ ካልሆነ ግን የውድድር አምዱን ኢ-ፍትሃዊ ያደርገዋል፡፡  ይህ ለኔ ወንጀል ነው” ሲልም አስረድቷል ሙሉጌታ ጀዋሬ፡፡
በሳተላይት የሚሰራጩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ፤ “በሳተላይት ለሚሰራጩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፍቃድ አልሰጥም፤ እነዚህ ጣቢያዎች ከውጪ አገራት ፍቃድ አውጥተው የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው ከባለስልጣኑ እውቅና ውጪ ናቸው” ብሏል፡፡ ሆኖም ጣቢያዎቹ በኢትዮጵያ የሚያዘጋጁአቸው ፕሮግራሞች ሲኖሩ ባለስልጣን መ/ቤቱ የብቃት ማረጋገጫን እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን የፕሮግራሞች ይዘት የሚቆጣጠርበት አሰራር ግን እንደሌለው ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡   

“የጥጥ ግብይት ቆሟል፤ አምራቹ ከጥጥ ስራ ሊወጣ ነው”

  የኢትዮጵያ ጥጥ አምራቾች ማህበር፤ ያመረትነውን ጥጥ የሚገዛን አጥተናል ሲል ያማረረ ሲሆን መንግስት አምራቾቹን ለመርዳት በኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት በኩል ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል ተብሏል።
የጥጥ አምራቾች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሐዱሽ ግርማይ፤ የመንግስት ጥረት ያልተሳካው ድርጅቱ ለግዥ ያቀረበው ዋጋ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ የኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት፤ የራሱን ትርፍ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ለአምራቹ እንደየጥጡ ደረጃ በኪሎ ከ30-33 ብር የግዥ ዋጋ መተመኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልፀው፣ ይሄን የዋጋ ተመን ግን አምራቹ አያዋጣኝም ብሎ አልተቀበለውም፡፡
የሌሎች አገራት አምራቾች መንግስታቸው ይደግፋቸዋል፤ በእኛ ሀገር የጥጥ ሴክተሩ በተገቢው ሁኔታ እየተደገፈ አይደለም የሚሉት አቶ ሐዱሽ፤ “አለም በሄክታር ከ50 እስከ 60 ኩንታል ሲያመርት፤ እኛ ግን በሄክታር እያመረትን ያለነው ከ10 እስከ 15 ኩንታል ብቻ ነው” ብለዋል፡፡
አምራቹ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉበት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይናገራሉ፡፡ “ኬሚካልና የተለያዩ ማሽኖችን ከውጪ እያመጣ ነው የሚሰራው፤ በዚያ ላይ የምርጥ ዘር ችግሮች አሉበት፤ የምርምር ስራው በጣም የተዳከመ በመሆኑም የምንጠቀመው ዝርያ ከዛሬ 25 አመት በፊት እንጠቀምበት የነበረውን ነው” – ብለዋል፤ አቶ ሃዱሽ። ይህም የዘርፉን ጥራትና ምርታማነት እንደጐዳው ይገልፃሉ፡፡ “በአሁኑ ወቅት የጥጥ ግብይት ቆሟል፤ አምራቹ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ እንሄዳለን፤ ሰላማዊ ሰልፍም እንወጣለን፣ መንግስት መልስ መስጠት ይኖርበታል” እስከማለት ደርሰዋል ያሉት አቶ ሃዱሽ፤ ይህ ሁሉ ችግር ቢያልፍ እንኳን በሚቀጥለው ዓመት አምራቹ ከጥጥ ምርት ለመውጣት ወስኗል ብለዋል። እኛም እንደ ማህበር ድልድይ ሆነን ከመንግስት ጋር ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ሞክረን ነበር፤ ግን አልቻልንም ይላሉ – ምክትል ፕሬዚዳንቱ፡፡
የኢንዱስትሪ ግብአት አቅርቦት ድርጅት (የቀድሞው ጅንአድ) በበኩሉ፤ የጥጥ ዋጋው የወጣው በገለልተኛ አካል መሆኑንና አምራቹን ለማበረታታት በኪሎ 2 ብር ድረስ ጭማሪ መደረጉን ገልጿል፡፡ የድርጅቱ የግዥና አቅርቦት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይ ከበደ ስለሁኔታው ሲያስረዱ፤ “እኛ ገዝተን የምንሸጠው ለጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪው ነው፤ ኢንዱስትሪው ምርቱን አምርቶ በአገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ገበያም ተወዳዳሪ መሆን አለበት። ዋጋው የተሰላውም የዓለም አቀፍ ገበያውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ከዚህ በላይ ዋጋው ቢጨምር ገዥ አይኖርም፡፡ ድርጅታችን የተቋቋመው በዋናነት አምራቹንና ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ እንጂ ለትርፍ አይደለም” ብለዋል፡፡   
አምራቹ በተባለው ዋጋ አያዋጣኝም ካለ፣ እናንተም በዚህ ዋጋ ካልሆነ አንገዛም ካላችሁ የመጨረሻ መፍትሔው ምንድነው ያልናቸው አቶ አባይ፤ “አልሸጥም ያለ አካል የራሱን አማራጭ ይወስዳል” ሲሉ መልሰዋል፡፡

ባል ሚስቱን ገድሎ ራሱን ሳያጠፋ አልቀረም ተብሏል

   በአዲስ አበባ ቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 7 ጃክሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኝና ትናንት ጠዋት የእሣት ቃጠሎ በደረሰበት ቤት ውስጥ ባልና ሚስት ሞተው የተገኙ ሲሆን የሰዎቹ ሞት ከቃጠሎው ጋር የተገናኘ እንዳልሆነ ታውቋል፡፡
የእሣት አደጋ ሠራተኞች በደረሳቸው ጥሪ መሰረት ትናንት ጠዋት 2 ሰዓት ገደማ በስፍራው ደርሰው እሣቱን ያጠፉ ሲሆን ባልና ሚስቱ የቃጠሎ አደጋ ሳይደርስባቸው ሞተው መገኘታቸውን የጠቆሙት የአዲስ አበባ እሣትና ድንገተኛ አደጋ መከላከል የኮሚኒኬሽን ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ፤ 30ሺ ብር የሚገመት ንብረት መውደሙንም ገልፀዋል፡፡
ሟቾች የ60 ዓመቱ አቶ ብርሃኑ ቡሌና የ44 ዓመቷ ወ/ሮ አስቴር አሰፋ፤ የ6 ልጆች ወላጆች ሲሆኑ ባል፣ ሚስቱን ገድሎ ራሱን ሳያጠፋ እንዳልቀረ መጠርጠሩን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የእሣቱ መነሻ ሲሊንደር ነው ያሉት ምንጮቹ፤ ፖሊስ በእሣቱ መነሻና በባልና ሚስቱ አሟሟት ላይ ተጨማሪ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የዛምቢያ መንግስት፤ በህገ ወጥ መንገድ የሃገሬን ድንበር ጥሰው ገብተዋል ያላቸውን 77 ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ማሰሩን የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
የሀገሪቱ ፖሊስ እንደሚለው፤ በመጀመሪያ የተያዙት 10 ኢትዮጵያውያን መነሻቸውን ከዛምቢያ ዋና ከተማ ሉሳካ በማድረግ በክፍት መኪና ተጭነው ለመውጣት ሲሞክሩ፣ በአካባቢው ሰዎች ጥቆማ የተያዙ ሲሆን በምርመራ ወቅትም ሌሎች 67 ኢትዮጵያውያን በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ታጭቀው እንደሚገኙ በመግለፃቸው በክትትል ተይዘዋል፡፡  ከታሰሩት 77 ኢትዮጵያውያን መካከል 19 ያህሉ ህጋዊ ፓስፖርት እንዳላቸው የገለጸው ፖሊስ፤እንዲያም ሆኖ ሁሉም ወደ ሀገሪቱ የገቡት በህገወጥ መንገድ በመሆኑ በህግ ከመጠየቅ አያመልጡም ብሏል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ በሉሳካ ማዕከላዊ እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ያስታወቀው ፖሊስ፤በአገሪቱ ህግ መሰረት ፍ/ቤት ቀርበው ተገቢው ቅጣት እንደሚተላለፍባቸው ጠቁሟል፡፡

     የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት በመብራት መቆራረጥ አገልግሎቱ እየተደናቀፈ ሲሆን ተጠቃሚዎች ላይም እንግልት እየፈጠረ ነው ተባለ፡፡
ባለፈው ሣምንት ቅዳሜና እሁድ ለረዥም ሰአታት አገልግሎቱ ተቋርጦ እንደነበር የጠቀሱት ተገልጋዮች፤ ማክሰኞ ዕለትም ተመሳሳይ ችግር ማጋጠሙን ጠቁመዋል፡፡
መብራት ሲጠፋ ባቡሩ ለረዥም ሰዓት ቢቆምም ለምን እንደቆመ ገልፆ ሌላ የትራንስፖርት አማራጭ ተጠቀሙ የሚል አካል እንደሌለ ተገልጋዮች ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በበኩሉ፤ የመብራት መቆራረጥ በአገልግሎቱ ላይ እንቅፋት እየሆነበት መምጣቱን ጠቁሞ ችግሩ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም እያጠና እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ለብቻው ለባቡሩ የሃይል አቅርቦት መዘጋጀቱን ኮርፖሬሽኑ ጠቁሞ፤ የሃይል መቋረጡ እያጋጠመ ያለው ከምንጩ ነው ብሏል፡፡
ህብረተሰቡ በከፍተኛ መጠን የባቡር ተጠቃሚ እየሆነ በመጣበት ሰዓት በሃይል መቋረጥ አገልግሎት መስተጓጐሉ አግባብ አለመሆኑን የተናገሩት የኮርፖሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ምክትል ሃላፊ፤ ችግሩ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የተከሰተ በመሆኑ መፍትሔ እስኪገኝ ህብረተሰቡ  አገልግሎቱን በትዕግስት እንዲጠቀም ጠይቀዋል፡፡

ኦፌኮ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከ500 በላይ አባላት ታስረውብኛል አለ

• “ግጭቱን ተከትሎ እስከ 4ሺ ሰዎች ታስረዋል” ፓርቲው
• “በፓርቲ ሽፋን የሻዕቢያን ተልዕኮ ለማሳካት በተሯሯጡት ላይ እርምጃ ይወሰዳል” – ጠ/ሚ ኃይለማርያም

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በቀለ ገርባና 6 ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከ500 በላይ አባላት ሰሞኑን እንደታሠሩበት ፓርቲው ገለፀ፡፡ የኦፌኮ ዋና ፀሐፊ አቶ በቀለ ነጋ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ጉርሜሣ አያኖ የፓርቲው ም/ሊቀመንበር፣ አዲሱ ቡላላ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ፣ ደረጀ መርጋ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ፣ መ/ር አለሙ አብዲሳ ፀሐፊ፣ መ/ር ታሪኩ ኦዲተር፣  አቶ ደጀኔ ጣፋ ም/ዋና ፀሐፊ እንዲሁም አቶ በቀለ ገርባ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር ሰሞኑን በፖሊስ ተይዘው ታስረዋል፡፡
ከፓርቲው አማካሪ ም/ቤት አባላት መካከልም የታሠሩ እንዳሉ የገለፁት ዋና ፀሐፊው፤ ከዞን አመራሮች የቄለም ወለጋ ዞን አመራር አቶ መሠረት ዳባ፣ የምስራቅ አርሲ ዶዶላ አመራር አህመድ ኢቦ፣ የባሌ አመራር አቶ ሁሴን አምዳ፣ የሆሮ ጉዱሩ አቶ ደገባስ ዋቀዩ፣ የኢሊባቡር አመራር አቶ እስማኤል ሁሴንና አቶ ያዛቸው አብዲሣ ታስረዋል ብለዋል፡፡
የወረዳ አመራሮችና ባለፈው ግንቦት በምርጫ የተሳተፉ ግለሰቦችን ጨምሮ እስከ 500 የሚደርሱ የፓርቲው አባላት በተለያዩ አካባቢዎች መታሠራቸውን አቶ በቀለ ገልፀው፤ ፓርቲው ባለው መረጃ መሰረት በአጠቃላይ ተቃውሞውን ተከትሎ የታሠረው ሰው ብዛት እስከ 4ሺ ይደርሳል ብለዋል፡፡
ከ300 በላይ የደረሱበት ያልታወቁ ሰዎች እንዳሉ የተናገሩት ዋና ፀሐፊው፤ በግጭቱ የቆሰሉ ከ1500 በላይ ተጎጂዎች በወሊሶ ሉቃስ ሆስፒታል፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ በሚኒልክና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምናቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
የፓርቲው አመራሮችና አባላት የታሠሩበት ምክንያት ባይገለጽም በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ትናንት በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባደረጉት ገለፃ “የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳን ይዘው የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በማሠራጨት ህዝብን በማደናገር የሰው ህይወት እንዲጠፋ አቅደው የመሩ አካላት በህጋዊ ፓርቲ ሽፋን የሻዕቢያን ተልዕኮ የማሳካት በተሯሯጡ ሃይሎች ላይ መንግስት ህገመንግስታዊ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡

    ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ታመው ተክለሃይማኖት ጠቅላላ ሆስፒታል ከገቡትና ለ10 ቀናት በህክምና ላይ ቆይተው ጥቅምት 6 ቀን ህይወታቸው ካለፈው ወይዘሮ አየለች ደግፌ ጆሮ ላይ የጠፋው 5 ግራም የጆሮ ወርቅ፤ ሆስፒታሉንና የሟች ቤተሰብን እያወዛገበ ነው፡፡ የሆስፒታሉ የፅኑ ህሙማን ክፍል ኃላፊ ሲስተር አስናቀች ተጠይቀው ሲመልሱ፤ “ወርቁ ከአስከሬኑ ጋር አብሮ የተገነዘ በመሆኑ መቃብሩ ይቆፈርልኝ” ማለታቸውን የሟች ልጅ አቶ ሰለሞን ጌታቸው ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡
እናቴን “ለመጨረሻ ጊዜ ፅኑ ህሙማን ክፍል ገብተን ስናያት ወርቁ ጆሮዋ ላይ መሆኑን ተመልክቻለሁ” ያለው አቶ ሰለሞን፤ “ከሞተች በኋላ ወርቁን ስጠይቅ ከአስከሬኑ ጋር ተገንዟል ተባልኩኝ፤ እውነቱ እንዲወጣ ስለምፈልግ መቃብሩ እንዲቆፈር ብፈቅድም እስካሁን ምንም ምላሽ አላገኘሁም” ብሏል፡፡
“ዛሬ ነገ እያሉኝ በመመላለስ ብዙ ተንከራተትኩ፤ እኔ ጉዳዬ ከወርቁ አይደለም፤ ነገር ግን መቃብሩ ተቆፍሮ እውነቱ እንዲወጣና ለሌሎችም ትምህርት እንዲሆን እፈልጋለሁ” ይላል አቶ ሰለሞን፡፡ ሆኖም ሥራዬንና ጊዜዬን ከማባከን በቀር እስካሁን አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት አልቻልኩም ሲል አማርሯል የሟች ልጅ፡፡
የሆስፒታሉን ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታሁን ስዩምን አነጋግሬ ነበር ያለው አቶ ሰለሞን፤ “ኃላፊዋ ወርቁን እንድትከፍል ወስነው ነበር፤ ነርሷ ዋጋውን ከጠየቀችኝና ከነገርኳት በኋላ ነው መቃብሩ ይቆፈር ያለችኝ” ብሏል፡፡ እኔ ከራሴ ጋር እየታገልኩም ቢሆን እውነት እንዲወጣ፣  ወጪውን ሸፍና ቁፋሮውን እንድታካሂድ ብፈቅድም ኃላፊዋ የተለያዩ ምክንያቶች እየፈጠረች ጊዜዬን እያባከነች ነው ያለው አቶ ሰለሞን፤ ሆስፒታሉ ለጉዳዩ እልባት የማይሰጠኝ ከሆነ ማስረጃዎቼን ይዤ ወደ ፍርድ ቤት አመራለሁ ብሏል፡፡
አንድ ህመምተኛ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል (ICU) ሲገባ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ የጠይቀናቸው የህክምና ባለሙያ እንደነገሩን፤ ህመምተኛው “እንኳን ጌጣጌጥ ከቤቱ ያመጣውን ፒጃማ እንኳን መልበስ አይችልም፤ ብዙ ጊዜ ፅኑ ህሙማን በማሽን ስለሚተነፍሱና የልብ ምታቸው በየጊዜው ስለሚታይ በአብዛኛው ደረታቸው ክፍት መሆን አለበት፤ ስለዚህ በአንሶላና በብርድልብስ ብቻ ይሸፈናሉ” ከዚህ አንፃር ህመምተኞች ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል ሊገቡ ሲዘጋጁ ማናቸውም ጌጣጌጥና ብራስሌት ወላልቆ ለቅርብ ቤተሰባቸው እንደሚሰጥ የጠቆሙት ባለሙያዋ፤ ይህም የፅኑ ህሙማን ክፍል ኃላፊዎች ሥራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡  
“የጆሮ ጌጡ ከአስከሬኑ ጋር ተገንዞ ቢሆን እንኳን የፅኑ ህመምተኛ ክፍል ኃላፊዋ ስራቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ከተጠያቂነት አያመልጡም” ብለዋል – ባለሙያዋ፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታሁን ስዩም ምላሽ እንዲሰጡን ጥረት ብናደርግም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

መንግሥት ሁከት በሚፈጥሩት ላይ የማያዳግም እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል

   በጎንደር ጭልጋ አካባቢ ቅማንትና አማራ በሚል በተደራጁ ቡድኖች መካከል በተፈጠረ ግጭት በርካቶች ለሞት መዳረጋቸው የተገለፀ ሲሆን ነዋሪዎች በስጋት ከቤታቸው ሳይወጡ እንደሰነበቱ ምንጮች ገለፁ፡፡
ግጭቱ ስር የሰደደ እንደነበር የጠቆሙት የአካባቢው ምንጮቻችን፤ ከመስከረም ጀምሮ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መከታተል እንዳልቻሉ፣ ከሳምንት በላይ ባስቆጠረው አደገኛ ግጭትም ኢትዮጵያን ከሱዳን የሚያገናኘው መንገድ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡
ቅማንት በሚል የተደራጀው ቡድን፣ “የቅማንት ጥያቄ እስኪመለስ ትምህርት የለም፤ እናንተም አትማሩም” በሚል ት/ቤቶች ላይ ጥቃት ሲፈፅሙ እንደነበር የጠቀሱት ምንጮች፤ በዚህም የተነሳ የአካባቢው ልጆች ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለዋል ይላሉ፡፡ የቅማንቶች የማንነት ጥያቄ ምላሽ ካገኘ በኋላ ከሰሞኑ ለተፈጠረው ግጭት መነሻ የሆነው “ዞን ይዋቀርልን፣ ድንበር ይከለልልን” በሚል በተነሳ ጥያቄ ነው ተብሏል፡፡
ቅማንቶች የማንነት ጥያቄ ማቅረብ ከጀመሩበት ከ3 ዓመት በፊት አካባቢው ውጥረትና ግጭት ተለይቶት እንደማያውቅ የሚጠቅሱት ነዋሪዎች፤ ከሁለት አመት በፊት ሚያዚያ ወር ላይ በአይከል ከተማ ከፍተኛ ረብሻ ተነስቶ ሰዎች መጎዳታቸውንና በርካታ ሱቆችና መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ያስታውሳሉ፡፡
ባሳለፍነው ሐሙስ ህዳር 30 ቀን 2008 ዓ.ም ግጭቱ በከፍተኛ ደረጃ መቀስቀሱን የጠቀሱት ምንጮቻችን፤ በእለቱ አንድ የቅማንት ወጣት መገደሉን ተከትሎ ቅማንት በሚል የተደራጁ ቡድኖች፤ ዳቦ ቤት ማቃጠላቸውንና ሱቅ ማውደማቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ይህን ተከትሎ የአማራ ብሔር ተወላጆች በሚል የተደራጁ ወገኖች በቋራ፣ ሺንፋ፣ ነጋዴ በሃርና ገንዳ ውሃ በተባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ቅማንቶችን እያባረሩ ቤት ንብረት ማቃጠል እንደጀመሩ ይገልፃሉ፡፡
ከእነዚህ አካባቢ የተባረሩ ሰዎች በአሁኑ ወቅት ጭልጋ ውስጥ በየድንኳኑ ተጠልለው የአካባቢው ህብረተሰብ የእለት ጉርስ እያቀረበላቸው እንደሚገኝና ሰሞኑን ምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ የክልሉ ባለስልጣናት ህዝቡን ሰብስበው እንዳወያዩ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም የተነሳ በአካባቢው ውጥረት መንገሱን የሚጠቅሱት ምንጮች፤ ሰዎች ከቤት መውጣት እንደተሳናቸውና በየመንገዱ ጦር፣ ገጀራ፣ ቢለዋ፣ መጥረቢያና የጦር መሳሪያዎች የያዙ ሰዎች እንደሚዟዟሩ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ትናንት በአንፃሩ ሠላማዊ እንቅስቃሴ እንደነበር ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
በገጠር አካባቢዎች ተደራጅተው ለጠብ የተዘጋጁ የቅማንት ተወላጆችን መበተን እንዳልተቻለ የሚጠቅሱት የሚናገሩት ምንጮች፤ የመንግስት ባለስልጣናት ከህዝቡ ጋር ባደረጉት ውይይት ግን ከዚህ በኋላ በግጭቱ ተሳታፊ የሚሆኑና ፀብ የሚጭሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ መናገራቸን ጠቅሰዋል፡፡ ህብረተሰቡም የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ላለመግባት ተስማምቷል ተብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፤ ከቅማንት ብሄረሰብ የማንነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ግጭቶች በመንግስት ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመው የአካባቢውን ሰላም በሚያውኩት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

         በሀገሪቱ የሚታየው የእርስ በእርስ ግጭትና ህዝባዊ አመፅ ሀገር ከመበታተኑ በፊት የሃይማኖት አባቶች ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው የሰላም ጥሪ እንዲያቀርቡ ተጠየቁ፡፡
የመግባባት አንድነትና ሰላም ማህበር (ሰላም) ባወጣው መግለጫ፤ በሌሎች ሀገራት የሚታየው የእርስ በእርስ ግጭት ያስከተለው ጉዳትና ቀውስ በአገራችን እንዳይፈጠር የሃይማኖት አባቶች የሽምግልና ሸንጎ በማቋቋም፣ በሀገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ የብሄራዊ እርቅ ጥሪ እንዲያቀርቡ ተማፅኗል፡፡
ሀገርና ዜጎች ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት ጭንቀት ውስጥ የገቡበት አጋጣሚ አለመከሰቱን የጠቆመው ማህበሩ፤ የሃይማኖት አባቶች በሀገሪቱ የሚታየው በዘር፣ በጎሣ፣ በሃይማኖትና በቀዬ የመከፋፈል አባዜ እስራትና ስደት እንዲሁም፣ ግጭትና ጦርነት መፍትሔ ይበጅለት ዘንድ እንዲተጉ ጠይቋል፡፡ በሃይማኖት አባቶች መካከል ያለው ግጭትም እልባት እንዲያገኝ ማህበሩ ተማፅኗል፡፡
ኢትዮጵያ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኖባት መቆየቷ ባይካድም ያልተቋረጠ ግጭት እያስተናገደች ባለበት በአሁኑ ሰዓት “ፍፁም ሰላም የሰፈነባት አገር ናት” በሚል ከእውነታው መሸሽ ተገቢ አይደለም ያለው ማኅበሩ፤ “በሀገሪቱ የበቀል እርምጃ እየሰፋና እየከፋ በመምጣቱ ምክንያት ማብቂያ ወደሌለው የጥፋት ጎዳና እያመራን እንገኛለን” ብሏል፡፡
“አስከፊ የእርስ በእርስ ግጭትና ህዝባዊ አመፅ እንደሚመጣ አስቀድመን ስጋታችንን ተናግረን ነበር” ያለው ማህበሩ፤ ሆኖም ለእርቀ ሰላም ስንማፀን “በሀገሪቱ ፍፁም ሰላም ሰፍኗል” በሚል ሰሚ ጆሮ ሳናገኝ ቀርተናል ብሏል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት በመተባበር ሀገሪቱ አሁን ከገባችበት አስጊ ሁኔታ ትወጣ ዘንድ እንዲፀልዩና የሀገር ሽማግሌዎች ሸንጎ ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረትም እገዛ እንዲያደርጉ ማኅበሩ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

      ከድርቁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያና የኬንያ አዋሳኝ ከተማ በሆነችው ሞያሌ ከተማ፣ የአተት ወረርሽኝ ተከስቶ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ ወደ 90 ገደማ የሚሆኑ በበሽታው ተይዘው ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡
በከተማው በአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ተይዘው በጤና ተቋማት የታከሙት 91 ያህል ሲሆኑ 71 ህክምናቸውን ተከታትለው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፣ 18 ደግሞ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ ህክምና ሲወስዱ ነበር ተብሏል፡፡
እስከ ትላንት በስቲያ ወረርሽኙ ከሞያሌ ከተማ እንዳይወጣ የህክምና ርብርብ እየተደረገ እንደነበር የጠቆሙት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊው አቶ አህመድ አማኖ፤ ከተማዋ የንግድ ከተማ እንደመሆኗ የተጠቂዎች ቁጥር ሊቀንስም ሊጨምርም የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ገልፀው ጤና ጥበቃ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ሰፊ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
በድርቁ ምክንያት የውሃ እጥረት መከሰቱን ተከትሎ የንፅህና ጉድለት ስለሚፈጠር በቫይረስና በባክቴሪያ የሚፈጠሩ በሽታዎች በድርቁ ተጎጂ አካባቢዎች ሊቀሰቀሱ እንደሚችሉ የጠቀሱት አቶ አህመድ፤ እስካሁን መሰል ችግር ከሌሎች የድርቅ ተጎጂ አካባቢዎች ሪፖርት አለመደረጉንና መንግስት የሚከሰቱ ወረርሽኞችን ለመከላከል በዘረጋው የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ፕሮግራሙ ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርቱ፤ በተለይ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ የሚፈጠር ጎርፍ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ውሃ ወለድ በሽታዎችን ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁሞ ድርጅቱ ችግሩን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ ለመቋቋም ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ልኮ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከድርቁ ጋር ተያይዞም ከ400 ሺህ በላይ ህፃናትና ከ700 ሺህ በላይ እናቶች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ በማድረግ ለወረርሽኝ ያላቸውን ተጋላጭነት መቀነስ እንደሚገባም የዓለም ጤና ድርጅት አሳስቧል፡፡ በተለይ ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ ካላገኙና የጤና ክትትል ካልተደረገላቸው አደጋው የከፋ ይሆናል ያለው ድርጅቱ፤ አሁን ባለው ሁኔታ የተቀናጀ የጤና አገልግሎት ለማቅረብ ሀገሪቱ በቂ አቅም የላትም ብሏል በሪፖርቱ፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው ያለው ይኸው ሪፖርት፤ የተለያዩ የአለማቀፍ ድርቶችን ድጋፍ እንደሚሻም አስታውቋል፡፡
በአጠቃላይ ድርቁና የኢሊኖ ክስተት ባስከተለው ችግር ምክንያት የሚፈጠርን የጤና መታወክ ለመከላከል 8 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለጉዳዩ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጥም የዓለም ጤና ድርጅት አሳስቧል።
ሰሞኑን መንግሥትና የአለማቀፍ ተቋማት የድርቁን ሁኔታ አስመልክቶ ባቀረቡት የዳሰሳዊ ቅኝት ሪፖርት፤ የድርቅ ተጎጂዎች 10.2 ሚሊዮን መድረሳቸው እስከ ቀጣይ አመት ለሚቆየው የድርቅ አደጋ መቋቋሚያም ወደ 30 ቢሊዮን ብር ገደማ በጀት እንደሚያስፈልግ የታወቀ ሲሆን 1.9 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እህልም ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
ድርቁ 189 ወረዳዎችን ክፉኛ የጎዳ ሲሆን በ89 ወረዳዎች ደግሞ መለስተኛ ጉዳት ማድረሱ ተገልጿል፡፡

• 10.12 ሚሊዮን ለረሃብ አደጋ የተጋለጡ ተረጂዎች
• 7.9 ሚሊዮን ከጥር እስከ ሰኔ ድረስ ድጋፍ የሚሹ ችግረኞች

   በድርቅ ሳቢያ ለረሃብ የተጋለጡ ኢትዮጵያዊያን ከአስር ሚሊዮን በላይ እንደሆነ በመጥቀስ በይፋ የእርዳታ ጥሪ የቀረበ ሲሆን፤ የተረጂዎች ጠቅላላ ቁጥር 18 ሚሊዮን እንደደረሰ ተገለፀ፡፡
የድርቁ አደጋ ከባድ መሆኑን በመግለጽ ለቀረበው የእርዳታ ጥሪ ፈጣን ምላሽ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት የእንግሊዝ የውጭ ተራድኦ ሚኒስትር፤ በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ድጋፍ የሚያገኙት 7.9 ሚሊዮን ሰዎችን ጨምሮ የተረጂዎቹ ቁጥር 18 ሚሊዮን ሆኗል ብለዋል፡፡  
በድርቁ ተጎጂ የሆኑ ዜጎች በጥር ወር ወደ 10.2 ሚሊዮን እንደሚያሻቅብ መንግስት ይፋ ያደረገ ሲሆን ለመጀመሪያው ዙር እርዳታ 516 ሺህ ሜትሪክ ቶን የምግብ እርዳታ ያስፈልገኛል ብሏል፡፡ መንግስት ለለጋሽ ሀገራትና ተቋማት የእርዳታ ጥሪ በይፋ አቅርቧል፡፡
ለምግብ ግዢ ብቻ 1.1 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልገው የጠቀሰው መንግስት፤ አጠቃላይ የድርቁን ችግር ለመቋቋም ከ1.4 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ እንደሚያስፈልገው አስታውቋል፡፡
በትግራይ የድርቁ ተጎጂዎች 1.2 ሚሊዮን፣ በአማራ ክልል 2.3 ሚሊዮን፣ በአፋር 409,200፣ በኦሮሚያ 3.8 ሚሊዮን፣ በደቡብ ክልል 668,900፣ በሱማሌ 1.5 ሚሊዮን፣ በድሬደዋና በሐረሪ በድምሩ ከ80 ሺህ በላይ፣ በጋምቤላ 37 ሺህ 450 እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል 83,476 መሆናቸውን የመንግሥት ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ለድርቁ የውጭ ሀገራት ለጋሽ ድርጅቶችና ተቋማት ድጋፍ እንዲቸሩት በትናንትናው እለት መንግስት ጥሪ ያቀረበ ሲሆን ከ50 በላይ ለሚሆኑ ዲፕሎማቶችና አለማቀፍ ለጋሽ ተቋማት ስለድርቁ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
ከድርቁ ጋር በተያያዘ ከ400 ሺህ በላይ ህፃናት አስቸኳይ አልሚ ምግብ ይፈልጋሉ ያለው መንግሥት፤ 3.6 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ ድርቅ አምጪ በሆኑ የተለያዩ በሽታዎች ሊጠቁ እንደሚችል ሪፖርት አድርጓል፡፡  ድርቁ በአጠቃላይ 429 ወረዳዎች የተከሰተ ሲሆን 286 ሺህ 400 ሰዎችን ሊያፈናቅል ይችላል ተብሏል፡፡

    በቅርቡ የተቋቋመው የኩላሊት እጥበት ማዕከል፣ ለኩላሊት ሕመምተኞች የእጥበት ህክምና ለመስጠት በኤስ ኤም ኤስ እያሰባሰበ ያለው ገንዘብ፣ “ለታለመለት ዓላማ አልዋለም”፤ መባሉ እያወዛገበ ነው፡፡ ባለፈው አርብ ጥቅምት 26 ሬዲዮ ፋና ባስተላለፈው ዘገባ፣ ማዕከሉ ለኩላሊት ህመምተኞች የእጥበት አገልግሎት ለመስጠት ከህዝብ ከሚሰበሰበው የበጐ አድራጐት ገቢ፣ ኮሚሽን እየከፈለ መሆኑን ጠቅሶ ድርጊቱ ህገወጥ ነው ብሏል፡፡ 524 ሺህ ብር ኮሚሽን ተቀብያለሁ ያሉ ግለሰብም በዋቢነት ማቅረቧ ታውቋል፡፡ የማዕከሉ የቦርድ አባልና የገቢ አሰባሳቢ ኦፊሰር ደራሲና ዳይሬክተር አንተነህ ሃይሌ በበኩሉ፤ “የኩላሊት እጥበት ማዕከሉ በSMS ከህዝብ ከሰበሰበው 7 ሚሊዮን ብር ውስጥ 4 ሚሊዮን ብር ተመዝብሯል የሚል ዘገባ በሬዲዮ ፋና መሰራጨቱን ጠቁሞ፤ 7 ሚ. ብር የሚለውን ከየት አምጥቶ እንዳወራ አናውቅም ብሏል፡፡ “የፋና ሃሰተኛ ዘገባ የህዝቡን በጐነት የሚረብሽና የህሙማንን ህልም የሚያጨልም ነው፤” ሲልም ተችቷል፡፡“የፋና ዘገባ እውነትን ማዕከል ያደረገ አይደለም፤” ያሉት የማዕከሉ የቦርድ ሰብሳቢ ኢንጂነር ሳሙኤል ይርጋ፤ “ለሚሠራው ሥራ የሚከፈል ኮሚሽን የለም” ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ማዕከሉ ከገራዶ ፊልም ፕሮዳክሽን ጋር ስለፈጸመው የሥራ ውል የተጠየቁት ሰብሳቢው፣ “ማዕከሉ ሥራ ሲጀምር ምንም ገንዘብና የሰው ሃይል ስላልነበረው የኤስኤምኤሱን አጠቃላይ ሥራ እንዲያከናውንና ለእድለኞች ሽልማት ከገቢው ከ10 በመቶ ያልበለጠ ሒሳብ እንዲወራረድለት ውል ፈጽመናል” ብለዋል፡፡ እያንዳንዱም ወጪ በደረሰኝ እንደሚገባና እንደሚወጣ ከቀሪው ጋር የሚያሳይ የባንክ ስቴትመንት እንዳለ ገልፀዋል፡፡ ሬዲዮ ፋና ያለ መረጃ ያሰራጨውን ዜና በተመለከተ፣ ይቅርታ እንዲጠይቀን ደብዳቤ አስገብተናል – ብለዋል ሰብሳቢው፡፡

ፓትርያርኩ ከካቶሊክ ጋር ያለን ሃይማኖታዊ ልዩነት “ጠባብ ነው” ማለታቸው እያነጋገረ ነው

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለን ልዩነት “ጠባብ ነው” ማለታቸው እያነጋገረ ነው፡፡ፓትርያርኩ ይህን የተናገሩት ባለፈው ሳምንት በዓዲግራት ሀገረ ስብከት ተገኝተው የደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን በመረቁበት ወቅት ሲሆን በሥነ ሥርዓቱ ላይ የትግራይ ክልል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ተስፋ ሥላሴ መገኘታቸውን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ድረ ገጽ ዘግቧል፡፡
ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ፣ “ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር  ያለንን ጠባብ የሃይማኖት ልዩነት ጠብቀን፣ በዜግነታችንና በክርስቶስ ልጅነታችን በዋና ዋና የልማት ሥራዎች ዙሪያ በጋራ በመሥራት፣ ለክርስቶስም ለሰው ልጅም ደስታን የሚሰጥ አገልግሎት ማበርከት  ይጠበቅብናል፤” ብለዋል – ድረ ገጹ እንደዘገበው፡፡ይሁንና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ያላቸው የእምነትና የሥርዓት አስተምህሮ ልዩነት መሠረታዊ መሆኑን የጠቀሱ አስተያየት ሰጪዎች፣ ፓትርያርኩ ሃይማኖታዊ ልዩነቱ ጠባብ እንደሆነ ተናግረዋል ተብሎ በሰፈረው ዘገባ ግር መሰኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

   በስፔናዊው ሚጌል ሊያንሶ ተፅፎ የተዘጋጀውና ከ60 በላይ በሚሆኑ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ተሳትፎ፣ 10 ሽልማቶችን ያሸነፈው “Crumbs” (ስብርባሪ) የተሰኘው ሳይንሳዊ ልብወለድ ፊልም፤ ትላንት ምሽት በአቤል ሲኒማ ተመረቀ፡፡ ከዓለም ጦርነቶች ፍፃሜ በኋላ ምን ሊፈጠር እንደሚችል በሚያመለክተው በዚህ ፊልም ላይ ዳንኤል ታደሰ (ጋጋኖ) በመሪ ተዋናይነት የተጫወተ ሲሆን ባሳየው የትወና ብቃትም አድናቆት ተችሮታል ተብሏል፡፡ ለትወናው አምስት ሺህ ዩሮ (125ሺ ብር) እንደተከፈለው ጋጋኖ ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ ፊልሙ በአውሮፓና በአሜሪካ በተለያዩ ከተሞች ለእይታ ቀርቦ አድናቆትን ያተረፈ ሲሆን ከ60 በላይ ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ተሳትፎ፣ ከ10 በላይ ሽልማቶችን ማግኘቱን የፊልሙ ፕሮዲዩሰር አርቲስት ዮሐንስ ፈለቀ ገልጿል፡፡ “ክረምብስ” ፊልምን፣ ለመስራት 200ሺ ዶላር እንደፈጀ ተናግሯል፡፡   

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን እንዳንጠይቅ ተከለከልን ሲሉ ቤተሰቦቹ አመለከቱ

የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ችግራቸውን እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል

       በእስር ላይ የሚገኘውን ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላለፉት 20 ቀናት መጠየቅና ማግኘት እንዳልቻሉ የጠቆሙት ቤተሰቦቹ፤ የጤንነቱ ጉዳይ እንዳሳሰባቸው በመግለፅ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ለችግራቸው እልባት እንዲሰጣቸው በደብዳቤ አመለከቱ፡፡
የጋዜጠኛው ቤተሰቦች በደብዳቤያቸው እንደገለፁት፤ ከጥቅምት 7 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ  ምክንያቱን ባላወቁት ሁኔታ ተመስገን በሚገኝበት ዝዋይ ማረሚያ ቤት ቤተሰብም ሆነ ወዳጅ ዘመድ እንዳይጠይቀው መከልከሉ መላው ቤተሰቡን ስጋት ላይ ጥሎታል፡፡
የጤናው ጉዳይ በእጅጉ ያሳስበናል ያሉት ቤተሰቦቹ፤ በተለይ ቀደም ብሎ የነበረበት ህመም ተባብሶ የግራ ጆሮው መስማት እስከመቸገር እንዳደረሰውና የወገብ ህመሙ እረፍት ነስቶ አላስተኛ እያለው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በተደጋጋሚ ወደ ዝዋይ ማረሚያ ቤት ቢመላለስም ተመስገንን ማግኘት እንዳልቻለ የሚናገረው የተመስገን ታናሽ ወንድም ታሪኩ ደሳለኝ፤ የማረሚያ ቤቱ ጥበቃዎች “ለምን መጠየቅ ተከለከልን?” ስንላቸው፤ “የበላይ ትዕዛዝ ነው” ይሉናል፤ ብሏል፡፡ በዚህም የተነሳ ተመስገንን ላለፉት 20 ቀናት እንዳላዩትና ቤተሰቡንም ለጭንቀት እንደዳረገ ይገልፃል፡፡
“የቤተሰባችን አባል በሆነው ተመስገን ላይ በተለየ ሁኔታ ተደጋጋሚ የህግ ጥሰት እየደረሰ ነው” ያሉት ቤተሰቦቹ፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ጣልቃ በመግባት ችግሩን እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ቀድሞ ይሠራበት በነበረው “ፍትህ” ጋዜጣ ላይ በወጡ ጽሑፎች ምክንያት፣ ተከሶ የ3 አመት እስራት ተፈርዶበት፣ ማረሚያ ቤት እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ 

ቴክኖ ሞባይል ላለፉት 3 ወራት አላመረተም

    በሀገሪቱ በተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ምርት ማምረት እስከማቆም የደረሱ ሲሆን በአስመጪና ላኪነት የንግድ ስራ ላይ የተሠማሩ ነጋዴዎችም መቸገራቸውን ገልፀዋል፡፡
ከ900 በላይ ሠራተኞችን ይዞ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በማምረት ሥራ ላይ የተሠማራው የቴክኖ ሞባይል አምራቹ ዊጉዩ ኩባንያ፤ በውጭ ምንዛሪ እጥረቱ የተነሳ ላለፉት 3 ወራት ምርት ማምረት ማቆሙን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው የውጭ ምንዛሪ ከባንክ ቢጠይቅም “ትንሽ ጊዜ ታገሱ” የሚል መልስ እንደተሰጠው የቴክኖ የአስተዳደር ክፍል ሃላፊ አቶ ገነነ አዘነ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ሃላፊው እንዳሉት፤ ኩባንያው ጠንካራ የገንዘብ አቅም ያለው በመሆኑ ለኪሣራ ባይዳረግም ስራ ባቆመባቸው ወራት በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አጥቷል፡፡
“ችግራችንን ለመንግስት አሳውቀናል፤  በቅርብ ጊዜ ችግሩ ይፈታል የሚል ተስፋ አለን” ብለዋል፤ ሃላፊው፡፡
ኩባንያው በቀን ከ10ሺህ በላይ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን አምርቶ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት ያቀርብ እንደነበርና በአሁን ሰአት በምንዛሪ እጥረቱ የተነሣ ሙሉ ለሙሉ ምርት ማቆሙን ጠቁመው፣ ያጋጠማቸው ችግር ጠንከር ያለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው በአስመጪነትና ላኪነት ስራ ላይ የተሠማሩ ነጋዴ በበኩላቸው፤ የዶላር እጥረቱ ከአንድ አመት በላይ እንደሆነው፤ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እጥረቱ እየተባባሰ እንደመጣና በንግድ ስራቸው ላይ ከፍተኛ ፈተና እንደጋረጠባቸው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡   
“ከ5ሺ ዶላር ጀምሮ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ለባንክ ፕሮፎርማ ካስገባን በኋላ እድል ከቀናን ከ3 እና 4 ወር በኋላ ነው የምናገኘው” የሚሉት ባለሃብቱ፤ በችግሩ የተነሳ ሠራተኛ በትነው ስራ ፈተው እስከመቀመጥ መድረሣቸውን ገልፀዋል፡፡
የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ስራ አስኪያጅ የሆኑ ግለሰብም ፋብሪካቸው በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ከውጭ ጥሬ እቃ ማስገባት መቸገሩን ጠቅሰው ባለፉት 4 ወራት ኢንዱስትሪያቸው ለከፍተኛ ኪሣራ እየተዳረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ “መንግስት በተደጋጋሚ ችግሩ በአጭር ጊዜ ይቀረፋል” የሚል ምላሽ ሲሰጠን ቆይቷል ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ችግሩ ይበልጥ እየተባባሰ መጥቷል ብለዋል፡፡
በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ችግሩ ካልተቃለለላቸው ሠራተኛ እስከመቀነስ የሚደርስ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ፤ በቅርብ የሚያውቋቸው ፋብሪካዎችም ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዳቸውን እንደታዘቡ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ በአስመጪነትና ላኪነት የንግድ ስራ ላይ የተሠማሩ ሌላው አስተያየት ሰጪ፤ የዶላር እጥረቱ ስራቸውን ሙሉ ለሙሉ እንዳስተጓጐለባቸው ጠቁመው፤ መንግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት ካላበጀለት የስራ ዘርፋቸውን ለመቀየር እንደሚገደዱ ተናግረዋል፡፡
“የምንዛሬ ጥያቄ ስናቀርብ በአሁን ሰአት መንግስት ከውጭ ስንዴ እያስገባ ስለሆነ ትንሽ ታገሱ የሚል ቀጥተኛ ያልሆነ የቃል መልስ እየተሰጠን ነው ብለዋል – ባለሀብቶቹ፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሃጂ ኢብሣ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ “ይሄ የኛም
ጥያቄ ነው ትክክለኛ ምላሽ የሚገኘው ከብሔራዊ ባንክ ነው” የሚል ምላሽ የሰጡን ሲሆን የብሔራዊ ባንክ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ መስፍን ደምሴ ጋር ደውለን መረጃ ለማግኘት ብንሞክርም በደብዳቤ መጠየቅ እንዳለብን ተገልፆልናል፡፡  

    ነገሩ፣ ለዘመናት ከምናውቀው እውቀት የተለየ በመሆኑ ግራ ማጋባቱ አይቀርም፡፡ እስካሁን ለሕፃናት ዕድገትና ጥንካሬ ጥሩ ነው በማለት ሕፃናትን ስንመግብ የኖርነው ወተት፤ በተቃራኒው ለሕፃናት ዕድገት ጥሩ አይደለም፤ ያቀጭጫቸዋል ቢባሉ ምን ይላሉ? የሚገርም ነው!ሰሞኑን በሂልተን ሆቴል ሲካሄድ በቆየው 4ኛ የአፍሪካ የምግብና የኑትሪሽን ፎረም ላይ አንድ ተመራማሪ፤ በመርዛማ ኬሚካሎች (አልፋ ቶክሲን) ላይ ያደረጉትን የምርምር ውጤት ሲያቀርቡ፤ እግረ መንገዳቸውን የአዲስ አበባና አካባቢዋ ወተት ከመጠን በላይ መርዛማ ኬሚካል (አልፋ ቶክሲን) እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ተመራማሪው ዶ/ር አሻግረ ዘውዱ፤ ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት (ILRI) ባወጣው ሪፖርት፤ በ2016 በአዲስ አበባና አካባቢዋ ባደረገው ጥናት፣ ከተሰበሰቡት 140 ናሙና ከ90 በመቶ በላይ ዓለምአቀፍ ሕግ ከሚፈቅደው በላይ መርዛማ ኬሚካል (አፍላቶክሲን M1) እንዳለው ማስታወቁን ተናግረዋል፡፡
አልፋ ቶክሲን በሻጋታ ምክንያት የሚፈጠር መርዛማ ኬሚካል ነው ያሉት ተመራማሪው፤ መርዛማ ኬሚካሉ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ቢጐዳም በሕፃናት ላይ የበለጠ ጉዳት ያደርሳል፣ መቀጨጭና መጫጫት ያስከትላል፡፡ በዕድሜያቸው ልክ ቁመታቸው አያድግም፡፡ በኢትዮጵያ 40 በመቶ ሕፃናት ቀጫጫ ናቸው፡፡ መርዛማ ኬሚካሉ ከማጫጨት በተጨማሪ ረዥም ዕድሜ ሲቆይ የጉበት ካንሰር ያስከትላል ብለዋል፡፡
አልፋ ቶክሲኖች የተለያዩ ናቸው፡፡ እህል ላይ የሚገኙትና በይበልጥ የሚታወቁት 4 ናቸው፡፡ እነሱም B1 B2 G1 G2 ይባላሉ ያሉት ዶ/ር አሻግሬ፤ እህሉ ላይ የሚገኘውን B1 አልፋ ቶክሲን የበላ ከብት በሰውነቱ ውስጥ በሚካሄደው ሜታቦሊዝም፣ B1 መርዛማ ኬሚካል ወደ M1 ይቀየራል፡፡ ኤች አይ ቪ ከእናት ወደ ልጅ እንደምታስተላልፍ እናት ለልጇ ጡት ስታጠባ መርዛማውን ኬሚካል ወደ ሕፃኑ ታስተላልፋለች፡፡ ከብትም እንደዚሁ፡፡ ሕፃኑ በአልፋ ቶክሲን የሚጠቃው፣ ጡት መጥባት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡ ወተት ለሕፃናት ዕድገት ጥንካሬና ውፍረት ጥሩ ነው ስለሚባል ወተት እየጠጡ ያድጋሉ፤ ለአልፋ ቶክሲን እየተጋለጡ ናቸው ያሉት ተመራማሪው፤ “በወሎ ድርቅ ጊዜ የእርጐ ፈንገስ የሚባል ነገር ተፈጥሮ ነበር፡፡ የሚበላ ነገር ሲጠፋ ፈንገስ የተቀላቀለበት ምግብ በልተው፤ ጋንግሪን ተፈጥሮባቸው እግራቸው የተቆረጠ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡” ብለዋል፡፡ ዓለምአቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ያወጣውን መረጃ በተመለከተ፤ መንግስት ከኢትዮጵያ ፐብሊክ ኢንስቲትዩት፣ የደረጃዎች ምዘናና ተስማሚነት፣ የምግብ ሳይንስና ኑትሪሽን ማዕከል እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ባለሙያዎች ጥናት እንዲያደርጉበት ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ ውጤቱ ልክ እንደተባለው ከሆነ ምን እናድርግ? በማለት ምክክር ይደረጋል ያሉት ዶ/ር አሻግሬ፤ ልክ ካልሆነ ደግሞ ኅብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ግድያ ለመፈፀም ዝቷል- አቃቤ ህግ
    በፌስቡክ፤ “አይኤስ ነኝ” ከሚል መልእክት ጋር የግድያ ዛቻ በማስተላለፍ የሽብር ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ የተከሰሰው ወጣት ላይ፤ የአቃቤ ህግ ከትናንት በስቲያ ምስክሮችን አቀረበ፡፡ አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ፣ ሰይድ መሃመድ፣ በሚያዚያ ወር 2007 ዓ.ም፤ “አይኤስ ነኝ” በማለት በፌስቡክ እንደጻፈ ይገልጻል፡፡ የአይኤስ ወታደር ነኝ … በቅርቡ በረመዳን ወር የሚታረዱትን ለመያዝ ወደ ባቲ እመጣለሁ” የሚል የዛቻ መልዕክት በግል በፌስቡክ ገፁ ላይ ለጥፏል ብሏል – አቃቤ ህግ፡፡
1ኛ የአቃቤ ህግ ምስክር፤ ከላይ የተጠቀሰው መልዕክት ላይ ሰዎች አስተያየት በሰጡበት ወቅት ይህንን መልዕክት በፌስቡክ መመልከቱን  የገለፀ የአቃቤ ህግ ምስክር፤ ከአካባቢዬ ወጣቶች ጋር በመመካከር ለፖሊስ ጠቁሜያለሁ ብሏል፡፡
የባቲ ከተማ ፖሊስ መሆናቸውን የገልፁ ሌላ የአቃቤ ህግ ምስክር በበኩላቸው፣ ጥቆማ ከደረሰን በኋላ ተጠራጣሪውን በቁጥጥር ስር አውለናል ብለዋል፡፡ በተጠርጣሪው የፌስቡክ ገፅ ላይም፤ “አይኤስ ማለት እንደኔ አይነት ነው፡፡ በረመዳን ወር ለእርድ ወደ ባቲ እመጣለሁ” የሚል መልዕክት አይቻለሁ ብለዋል፡፡
በወቅቱ “ለምን ይሄን አደረግህ” ብዬ ጠይቄዋለሁ፤ እሱም፤ “እኔ ጓደኞቼን ለማስፈራራት ነው  እንጂ አይኤስ አይደለሁም” ሲል መልሶልኛል ብለዋል – እኚሁ የአቃቤ ህግ ምስክር፡፡ በሚያዚያ ወር፤ አይኤስ የተሰኘው አሸባሪ ቡድን፣ በሊቢያ በርካታ ኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን በሚያዝያ ወር፣ አይ ኤስ የተሰኘው አሸባሪ ቡድን በሊቢያ በርካታ ኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ ለማውገዝ፤ ወደ ሰላማዊ ሰልፍ ለመሄድ እየተዘጋጀሁ እንደነበር አስታውሳለሁ፤ ተጠርጣሪው የተያዘውም በዚያኑ እለት ነው በማለት ምስክሩ ተናግረዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው፤ ተጠርጣሪው ለምርመራ ወደ አዲስ አበባ የመጣው ተብሏል፡፡
የአቃቤ ህግ 3ኛ ምስክር የአዲስ አበባ ነዋሪ እንደሆኑ ጠቅሰው፤ ተጠርጣሪው የፌስቡክ ገፁ የራሱ መሆኑን አምኖ ሲፈርም እኔ በታዛቢነት ፈርሜያለሁ ብለዋል፡፡ በፌስቡክ አካውንቱ ላይ የተፃፈውንም መልዕክት እንደተመለከቱ ተናግረዋል፡፡
ፍ/ቤቱም የምስክሮቹን ቃል ካደመጠ በኋላ በመቅረፀ ድምፅ የተቀረፀው ምስክርነት ወደ ፅሁፍ ተገልብጦ የመዝገቡ አካል እንዲሆን ትዕዛዝ ያስተላለፈ ሲሆን ምስክርነቱን መርምሮ ብይን ለመስጠትም ለህዳር 30 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
 ተከሳሹ ወጣት፤ የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ እስከማገኝ ድረስ በንፁህነት የመታየት መብቴን እንዳላጣ፣ የፍርድ ሂደቱ፤ ተመልካችና ጋዜጠኛ ሳይኖር፤ በዝግ ይታይልኝ ሲል ጠይቋል በጠበቃው አማካኝነት፡
፡ ፍ/ቤቱ ግን፤ ክሱ መታየት የጀመረውና የተነበበው ተመልካቾች ባሉበት በግልፅ ችሎት መሆኑን በመጥቀስ፣ አቤቱታውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ በተከሳሹ የፌስቡክ ገፅ ላይ የተለጠፈው መልእክት፤ “እኔ አይኤስ አይኤስ ነኝ፣ የስራ ድርሻዬም ሰውን እጅና እግሩን አንጋልዬ መያዝ ነው፤ ደሞዝ የሚከፈለኝ በያዝኩት ሰው ልክ ነው፣ የአይኤስ ወታደር ነኝ፤ በቅርቡ ወደ ባቲ ለእርድ እመጣለሁ” የሚል ነው ብሏል – አቃቤ ህግ፡፡ ተከሳሹ በበኩሉ፤ “የፃፍኩት ለቀልድ ነው” ማለቱ ተገልጿል፡፡

መምህር ግርማ የታሰሩት 800ሺህ ብር በማታለል ተጠርጥረው ነው ተጠርጣሪው አስተባብለዋል

      ታዋቂው መምህር ግርማ ወንድሙ የታሰሩት እምነትን መነሻ በማድረግ፣ በተፅዕኖ መኖሪያ ቤት በማሸጥና ገንዘብ አታሎ በመውሰድ ወንጀል ተጠርጥረው መሆኑን ፖሊስ ለፍ/ቤት ያስረዳ ሲሆን ተጠርጣሪው ግን አስተባብለዋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ዘንድ በአጥማቂነት የሚታወቁት መምህር ግርማ ወንድሙ፤ በተጠረጠሩበት ወንጀል ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ያስፈልገኛል በማለቱ ፍ/ቤቱ 7 ቀን ሰጥቷል፡፡
በተጠርጣሪው ላይ እየተጣራ ያለው የፖሊስ የምርመራ መዝገብ፤ መስከረም 2006 ዓ.ም አቶ በላይነህ ከበደ የተባሉ ግለሰብን ሃይማኖትና እምነትን መነሻ በማድረግ በየካ ክፍለ ከተማ ወሰን ግሮሰሪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ላይ ከሚገኝ መኖሪያ ቤቱ እስከ ጥር 30 ቀን 2006 ዓ.ም ሸጦ ካልወጡ አስከሬናቸው መውጣቱ የማይቀር መሆኑን በመንገር ግለሰቡ ቦታውን እንዲሸጡ አድርገዋል ይላል፡፡
ግለሰቡም ከባለቤታቸው ጋር በመሆን እንደተባሉት ቤቱን በ800ሺህ ብር ይሸጣሉ፡፡
 ቤቱ በተጠቀሰው ዝቅተኛ ዋጋ እንዲሸጥ ተጠርጣሪው መምህር ግርማ አስተዋጽኦ ነበራቸው ይላል የፖሊስ የምርመራ መዝገብ፡፡ ግለሰቡ ቤታቸውን ከሸጡ በኋላ ተጠርጣሪው “በራዕይ ያየሁት ቦታ “ቦሌ” አለ፤ እሱን ነው መግዛት ያለብህ፣ ቤቱ የተሸጠበትን 800ሺህ ብር አምጣና እንዲበረከትልህ ልፀልይበት” ብለው ወሰዱት፡፡ የግል ተበዳይ ገንዘባቸውን ለማስመለስ ያደረጉት ጥረት እንዳልሠመረላቸውና ከሀገር ወጥተዋል እንደተባሉ የፖሊስ ምርመራ መዝገብ ያብራራል፡፡
 የግል ተበዳይ ጉዳዩ ውሎ ሲያድር ማታለል መሆኑን በመረዳታቸው በመጋቢት 2007 ዓ.ም ወር ገደማ ለፖሊስ ያመለከቱ ሲሆን ፖሊስ ከሄዱበት ሀገር እስኪመለሱ የተበዳዩን ቃልና የምስክሮችን ቃል ሲቀበል መቆየቱን ያትታል፡፡
መምህሩ በበኩላቸው፤ ከሣሽ የተባለውን ግለሰብ ጥቁር ይሁን ቀይ አንድም ቀን አይተውት እንደማያውቁ በመግለጽ ከጀርባዬ የተሴረብኝ ሴራ አለ ሲሉ ለፍ/ቤቱ ተናግረዋል፡፡
 ጉዳዩን የያዘው የፖሊስ የምርመራ ቡድን ከትናንት በስቲያ ተጠርጣሪውን በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ወ/ችሎት ያቀረባቸው ሲሆን ግለሰቡ በተጠረጠሩበት የማታለል ወንጀል ቀሪ የምርመራ ስራ ስላለኝ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ብሎ ፍ/ቤቱን ቢጠይቅም ፍ/ቤቱ የ7 ቀን ጊዜ በመፍቀድ ጉዳዩን ለጥቅምት 25 ቀጥሯል፡፡
ተጠርጣሪው ፖሊስ የተጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የተቃወሙና የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው የጠየቁ ቢሆንም ፖሊስ በዋስ ቢለቀቁ መረጃ ያሸሹብኛል በማለቱ ፍ/ቤቱ የመምህር ግርማን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፡፡

ድርቁ ከ4.6 ሚ. በላይ ህጻናትን የረሃብ ተጠቂ ሊያደርግ ይችላል ተባለ

ተመድና ኦክስፋም የተረጂዎች ቁጥር 15 ሚ. ይደርሳል ሲሉ፣ መንግስት 8.5 ሚ. ብቻ ናቸው ብሏል
ፖለቲከኞችና ባለሙያዎች ፖለቲካዊ ጥቅምን ትተን ችግሩን ለመፍታት እንረባረብ አሉ

በኤልኒኖ ሳቢያ በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ህጻናትን የርሃብ ተጠቂ ሊያደርግ ይችላል ሲል ሴቭ ዘ ችልድረን የተባለው አለማቀፍ ተቋም አስጠነቀቀ፡፡350 ሺህ ያህል የአገሪቱ ህጻናት የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግር ተጠቂ ሆነዋል ያለው ተቋሙ፣ ችግሩ ተገቢው መፍትሄ ካልተሰጠው  በህጻናቱ ዕድገት ላይ የመቀጨጭ፣ የአካላዊና አእምሮአዊ ዝግመት ሊያስከትል ብሎም ለህልፈተ ህይወት ሊዳርግ ይችላል ብሏል፡፡የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ኦክስፋም ሰሞኑን ባወጡት ሪፖርት፣ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር እስከ 15 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል የገለፁ ሲሆን፣ መንግስት በበኩሉ፤ የተረጂዎቹ ቁጥር 8.5 ሚሊዮን ብቻ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ታዋቂ የአገሪቱ ፖለቲከኞችና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በበኩላቸው፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወት አደጋ ላይ በሚገኝበት በዚህ አሳሳቢ ወቅት፣ ለፖለቲካዊ ጥቅም መሯሯጡን ትተን ድርቁ ያስከተለውን የርሃብና የምግብ እጥረት ችግር ለመፍታት በጋራ መረባረብ አለብን ብለዋል፡፡

“ዴርቶጋዳ” በተሰኘው የመጀመሪያ ረዥም ልብወለዱ ዕውቅና ያተረፈው ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ፤ በአይናለም የመጽሐፍት መደብር ባለቤት፣ በአቶ አይናለም መዋ የ330 ሺህ ብር  ክስ እንደቀረበበት ምንጮች ጠቆሙ፡፡ ከክስ መዝገቡ ላይ ለመረዳት እንደተቻለው፤ ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ “ዴርቶጋዳ” እና “ዣንቶዣራ” የተሰኙ መጽሐፎቹን በራሱ ማተሚያ ቤት አሳትሞ ለአይናለም መዋ ለመስጠት ከተዋዋለ በኋላ፣ ውሉን አፍርሶ ከሌላ ሰው ጋር ተዋውሏል፡፡ አይናለም የመፅሀፎቹን ዋጋ አስቀድሞ መክፈሉም በክሱ ተጠቅሷል፡፡ ደራሲው መጽሐፎቹን አትሞ ለመስጠት የተዋዋለው እስከ ሰኔ 4 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ የነበረ ቢሆንም “ዴርቶጋዳ” የተሰኘውን መጽሐፍ 5ሺህ ኮፒ አሳትሞ ለመስጠት ተዋውሎ 2ሺህ ኮፒ ብቻ ለውል ሰጪው በማድረስ ቀሪውን 3ሺህ ኮፒ ለሌላ ሰው ከውል ውጪ ማስተላለፉ በክሱ ላይ ተገልጿል፡፡ ክሱ የቀረበለት ፍ/ቤትም፤ ተከሣሽ ቀርቦ ምላሽ እንዲሰጥ ለፊታችን ሰኞ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ደራሲና አሣታሚ ይስማዕከ ወርቁ በበኩሉ፤ ስለክሱ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ለአዲስ አድማስ በስልክ በሰጠው ምላሽ ገልጿል፡፡ አስራ አንደኛ መፅሀፉን ለማውጣት በማስተዋወቅ ላይ የሚገኘው ዝነኛው ደራሲ ይስማዕከ፤ “ዴርቶጋዳ” የተሰኘ የመጀመሪያ ልብወለዱ ከ200ሺ በላይ ቅጂዎች እንደተሸጡለት ይታወቃል፡፡ የሙሉ ጊዜ ደራሲ የሆነው ይስማዕከ፤ በአዋሳ የህክምና ትምህርቱን አጠናቋል፡፡  

በጎጃም በርካታ ሰዎች እንዲረሸኑና በጅምላ እንዲቀበሩ አድርገዋል ተብሏል

በደርግ የአገዛዝ ዘመን ዜጎችን በመግደል፣ በማሰርና በማሰቃየት ተከስሰው ሞት የተፈረደባቸው አንድ ስማቸው ያልተገለጸ የቀድሞ የደርግ ባለስልጣን፤ በሆላንዷ ከተማ አምስቴልቪን በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኤንኤል ታይምስ የተባለው የአገሪቱ ድረገጽ ትናንት ዘገበ፡፡
በሆላንድ የሚገኘው የአለማቀፍ ወንጀሎች ምርመራ ቡድን አቃቤ ህግ፣ ግለሰቡ እ.ኤ.አ በ1978 ባስተላለፉት ትዕዛዝ፣ በጎጃም አካባቢ ታስረው የነበሩ በርካታ ሰዎች ተረሽነው አስከሬናቸው በጅምላ መቃብር እንዲቀበር ተደርጓል ማለታቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡ተጠርጣሪው ከሁለት ሳምንታት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋሉ የጠቆመው ዘገባው፣ አምስቴልቪን ከተማ ውስጥ በሚገኘው የግለሰቡ መኖሪያ ቤት ውስጥ በተደረገ ፍተሻ የተለያዩ ማስረጃዎች የተገኙ ሲሆን በሄግ የሚገኘው ፍርድ ቤትም ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት፣ ግለሰቡ ለ90 ቀናት በእስር ላይ እንዲቆዩ ወስኖባቸዋል ብሏል፡፡የሆላንድ ፖሊስ ግለሰቡ የተጠረጠሩባቸውን የወንጀል ድርጊቶች ስለመፈጸማቸው ምርመራ ማድረግ መጀመሩን ዘገባው ገልጾ፣ ፖሊስም የምስክሮችን ቃል መቀበሉንና ተጠርጣሪው ድርጊቶቹን ስለመፈጸማቸው ምስክርነታቸውን ከሰጡ ግለሰቦች አብዛኞቹ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን  እንደሆኑ አስታውቋል፡፡ምስክሮቹ በሰጡት ቃል ግለሰቡ በጎጃም አካባቢ የደርግ ባለስልጣን ሆነው ባገለገሉባቸው አመታት የተጠቀሱትን የወንጀል ድርጊቶች ስለመፈጸማቸው ተናግረዋል ያለው ዘገባው፣ የሆላንድ የወንጀል ምርመራ ባለስልጣናትም ግለሰቡን ለሞት ቅጣት ያበቃቸውን የወንጀል ክስ የተወሰነ መረጃ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት መረከቡን ገልጧል፡፡የአለማቀፍ ወንጀሎች ምርመራ ቡድን፣ በደርግ የአገዛዝ ዘመን በደብረ ማርቆስና በመተከል እስር ቤቶች ውስጥ የግድያና የስቃይ ድርጊቶችን በፈጸሙ ግለሰቦች ላይ ትኩረት በማድረግ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ዘገባው አስታውቋል፡፡
61 አመታቸው እንደሆነ የተነገረላቸው እኒሁ ባለስልጣን፤ ከጥቂት አመታት ወዲህ ነዋሪነታቸውን በሆላንድ እንዳደረጉና የአገሪቱ ዜግነት እንደተሰጣቸው ያስታወሰው ዘገባው፣ ግለሰቡ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት በሌሉበት የእድሜ ልክ እስራትና የሞት ቅጣቶች እንደተጣሉባቸውም ገልጧል፡፡

“ያልተዘመረለት ትልቅ ሰው ነው” (የዌ. ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት)

    የቀድሞ የኢህአፓ ብርቱ ታጋይ እንደነበር የሚገርለት አንጋፋው ደራሲ አስማማው ኃይሉ (አያ ሻረው)፤ ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ባለፈው ረቡዕ በስደት በኖረባት አሜሪካ ህይወቱ አለፈ፡፡ አስማማው፤ “ከጎንደር ደንቢያ እስከ ዋሽንግተን” (ክፍል አንድና ሁለት) በተሰኙ ልብወለድ መፃህፍቱ በይበልጥ የሚታወቅ ሲሆን አምስተኛ የሥነ ፅሁፍ ሥራውን በቅርቡ ለአሳታሚዎች እንደሰጠ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአሲምባ በረሃ ለአራት አመታት በትግል የቆየ ሲሆን፤ በ1975 ዓ.ም የኢህአፓ ሰራዊት ሲበተን በስደት ወደ ሱዳን ሄዶ ጥቂት ዓመታት ከቆየ በኋላ ወደ አሜሪካ አቅንቷል፡፡ ለረዥም ዓመታት በአሜሪካ በስደት የኖረው ደራሲው፤ በተለይ ከሶስትና አራት አመታት ወዲህ “ከጎንደር ደንቢያ እስከ ዋሽንግተን፤ ክፍል አንድና ሁለት”፣ “ኢ.ህአሰ፣ አሰብ ክፍል አንድና ሁለት” የተሰኙ አራት መፃህፍትን ለንባብ ያበቃ ሲሆን “አያ ሻረው” የተሰኘ የግጥም ሲዲ ማሳተሙንም የቅርብ ወዳጁ ደራሲና ሀያሲ አለማየሁ ገላጋይ ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ አስማማው በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አምስተኛ መፅሃፉን የረዥም ልብ ወለድ ሥራ ለአሳታሚዎች ከሰጠ በኋላ ልቡን ታሞ ቦሌ አካባቢ በሚገኘው አዲስ የልብ ህክምና ማዕከል ገብቶ እንደነበር ያስታወሰው አለማየሁ፤ ወደ አሜሪካ ከሄደ በኋላ ግን በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ደውሎ እንደነገረው ይገልፃል፡፡
ሌላው የአስማማው የቅርብ ወዳጅ በኢትዮጵያ የዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አቶ አቤይቱ መላኩ ስለሁኔታው ሲያስረዱ፤ አስማማው ቀደም ሲል የካንሰር ህመም አጋጥሞት በህክምና መዳኑን ጠቁመው፣ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ በመጣበት ወቅት በሳንባ ህመም መያዙንና ቦሌ በሚገኘው አዲስ የልብ ህመም ህክምና ማዕከል አስገብተው እንዳሳከሙት፣ ከህመሙም ድኖ ወደ አሜሪካ መመለሱን ገልፀዋል፡፡ አሜሪካ ከሄደ በኋላ እንደተሻለው ገልፆልኝ ነበር የሚሉት አቶ አቤይቱ፤ ሆኖም እንደገና ታሞ ኮሎምቦስ ኦሃዩ በሚገኝ ሆስፒታል ገብቶ መታከሙን ተናግረዋል፡፡ ከዚያም ፊላደልፊያ ሄዶ እዚያም መታመሙንና ሳንባው ውሃ ቋጥሮ ለህልፈት መዳረጉን አቶ አቤይቱ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ ቀብሩ የትና እንዴት ይከናወን በሚለው ጉዳይ ላይ ከዘመድ ወዳጆቹ ጋር እየመከሩ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል፡፡ “አስማማው ያልተዘመረለት ትልቅ ሰው ነው” ያሉት አቶ አቤይቱ፤ “የእሱ ስራና ታሪክ በአግባቡ ሊዘከር ይገባል” ብለዋል፡፡
ሌላው የቅርብ ወዳጁ፤ ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ በበኩሉ፤ “አስማማው ብዙ ፅሁፍና ታሪክ ማምረት በጀመረበት ወቅት መሞቱ ያስቆጫል” ሲል በሀዘን ተሞልቶ ተናግሯል፡፡

ኢትዮጵያ አምና ወደዚያው ከላከችው ስጋ 58.8 ሚ ዶላር አግኝታለች
     የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢትዮጵያ የስጋ ምርት ወደ ግዛቷ እንዳይገባ ከአንድ ሳምንት በፊት ጥላው የነበረችውን ማዕቀብ ማንሳቷን ተርኪሽ ዊክሊ ድረገጽ ትናንት ዘገበ፡፡
ከሳምንት በፊት ከኢትዮጵያ ሰባት ስጋ ላኪ ኩባንያዎች ወደ አገሪቱ ከገባው 36 ቶን የበግ ስጋ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ አገሪቱ የኢትዮጵያ የስጋ ምርት ወደ ግዛቷ እንዳይገባ ገደብ ጥላ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግስት አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩን መፍታት መቻሉን ገልጧል፡፡
ይህን ተከትሎም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢትዮጵያ የስጋ ምርት ወደ ግዛቷ እንዳይገባ የጣለችውን ማዕቀብ ማንሳቷንና አገሪቱ ያሳለፈችው ውሳኔ በዘርፉ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያንን እንዳስደሰተ ዘገባው አስረድቷል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢትዮጵያን የስጋ ምርት በስፋት በመግዛት ቀዳሚዋ አገር እንደሆነችና ኢትዮጵያ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከምትልከው የምግብ ኤክስፖርት ምርት በአመት በአማካይ 30 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደምታገኝም ገልጧል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፈው አመት ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከላከችው 11.692 ቶን የስጋ ምርት 58.8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷንም ዘገባው አክሎ አስታውሷል፡፡

ጉዳዩን ለአለም የሚያሳውቅ ገለልተኛ አካል እንዲቋቋም ጠይቋል
                                
    ሠማያዊ ፓርቲ፤ በኢትዮጵያ የተከሰተው “ረሃብ”፤ ከገዥው ፓርቲ የፖሊሲ ውድቀት የመነጨ ነው በማለት ችግሩን ለአለም የሚያሳውቅ ገለልተኛ አካል እንዲቋቋምና አለማቀፉ ህብረተሰብ እርዳታውን እንዲለግስ ጠየቀ፡፡ ፓርቲው ከትናንት በስቲያ “ረሃቡ የገዥው ፓርቲ የፖሊሲ ውድቀት ነው!” በሚል ርዕስ በሠጠው መግለጫ፤ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ አለማቀፉ ማህበረሰብ ለዜጐች እርዳታ እንዳያቀርብ መንግስት ጉዳዩን ሲሸፋፍን ቆይቷል ሲል ተችቷል፡፡
“መንግስት የኋላ ኋላ ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት ችግሩ እንደተከሰተ ቢገልጽም ዜጐች ተገቢውን እርዳታ በሚያገኙበት መልኩ እርምጃ እየተወሰደ አይደለም” ብሏል ፓርቲው በመግለጫው፡፡ የተከሰተው ችግር የፖሊሲ ውድቀትን ያመላክታል ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ገዥው ፓርቲ ቆሜለታለሁ የሚለውን አርሶ አደርና አርብቶ አደር ህይወት ለማሻሻል የረባ ስራ እንዳልሠራ ማረጋገጫ ነው ብሏል፡፡ “ግብርናው ኢኮኖሚውን ይመራል የሚለው በተግባር አልታየም፤ ምክንያቱም ሚሊዮኖች በየአመቱ ለ“ረሃብ” ችግር መጋለጣቸውን ቀጥለዋል” ሲል ገልጿል ፓርቲው፡፡
ለተከሰተው ሀገራዊ ችግር መንግስት አፋጣኝ እርምጃዎችን እንዲወስድ ያሳሰበው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ስለ ችግሩ ለኢትዮጵያውያንና ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚያስረዳ ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ፤ በችግሩ ለተጠቁ ዜጐች መፍትሔ እንዲፈለግ ጠይቋል፡፡
የምግብ እጥረቱ (ረሃቡ) ከተፈጠረባቸው አካባቢዎች መረጃ በማሰባሰብና በማጣራት ለህዝብ በየጊዜው እንደሚያሳውቅ የገለፀው ፓርቲው፤ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ኢትዮጵያውያንና የአለም ህብረተሰብ ከተጐጂዎች ጐን እንዲቆሙ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
መንግስት በበኩሉ፤ ችግሩ የተፈጠረው በአለማቀፍ ደረጃ ከተከሰተው የአየር ፀባይ ለውጥ (ኤሊኖ) ጋር ተያይዞ መሆኑን በመግለፅ፣ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ዝናብ ባለመዝነቡ የምግብ እጥረት ቢያጋጥምም “ረሃብ” አለመከሰቱን በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡

     በቅርቡ በሳዑዲ አረቢያ በሃጂ ስነስርአት ወቅት በተፈጠረ መጨናነቅ ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 47 መድረሱን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገልጿል፡፡
ባለፈው መስከረም 13 ቀን 2008 በሳዑዲ አረቢያ ሚና አካባቢ በደረሰ አደጋ ከ1ሺህ በላይ የተለያዩ ሀገር የሃይማኖታዊ ስነ ስርአቱ ተሳታፊዎች ህይወታቸውን ባጡበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ላይ አደጋ ስለመድረሱ ወዲያው ማወቅ ያልተቻለ ሲሆን ከቀናት በኋላ 2 ኢትዮጵያን ህይወታቸው ማለፉ ተዘግቦ እንደነበርና ኋላም የሟቾች ቁጥር ወደ 31 ማደጉ ይታወቃል፡፡ ከትናንት በስቲያ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ቁጥሩ 47 መድረሱንና ተጐድተው ሆስፒታል ገብተው ከነበሩት 26 ኢትዮጵያውያን 24 ተሽሏቸው ከሆስፒታል ሲወጡ፣ 2ቱ ተኝተው ህክምና እየተከታተሉ መሆኑ ታውቋል፡፡
ለሃጅ ስነስርአት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሄደው የነበሩ ከ1ሺህ 100 በላይ አማኞች መመለሳቸውንም ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡ በዘንድሮ የሃጂ ስነስርአት ላይ 10ሺ ኢትዮጵያውያን መሣተፋቸውም ታውቋል፡፡

 ኤርትራ ዝቅተኛ የኢንተርኔት ተጠቃሚ በመሆን አለምን ትመራለች
   በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነው ከአጠቃላዩ ህዝብ 1.7 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው መባሉን የአሜሪካው የቢዝነስ መጽሄት ፎርቹን ዘገበ፡፡ኢንተርኔት ላይቭ ስታትስ የተባለው አለማቀፍ ተቋም ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ እጅግ ዝቅተኛ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦት ካላቸው አስር የአለማችን አገራት መካከል ስምንቱ በአፍሪካ አህጉር እንደሚገኙና ኢትዮጵያም አንዷ እንደሆነች በጥናት ተረጋግጧል፡፡በኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦት ዝቅተኛነት ከአለማችን ቀዳሚውን ስፍራ የምትይዘው ኤርትራ መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፣ ከአገሪቱ ህዝብ የአገልግሎት ተጠቃሚ የሆነው 0.91 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጧል፡፡ከአውስትራሊያ በስተሰሜን የምትገኘው ቲሞር ሌሴቴ ደሴት በ1 በመቶ፣ ማይንማር በ1.16 በመቶ፣ ብሩንዲ በ1.39 በመቶ እንዲሁም ሴራሊዮን በ1.49 በመቶ በኢንተርኔት አቅርቦት ዝቅተኛነት እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል ተብሏል፡፡  ሶማሊያ በ1.51 በመቶ፣ ኒጀር በ1.61 በመቶ፣ ኢትዮጵያና ጊኒ በ1.7 በመቶ እንዲሁም ኮንጎ በ1.92 በመቶ እንደሚከተሉም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

  መንግስት በጠራው ውይይት ላይ ዋናዎቹ ተቃዋሚዎች አልተሳተፉም
  •  ፓርቲዎቹ መቅደም ይገባቸዋል ሏቸውን ጉዳዮች አስቀምጠዋል

         መንግስት በነደፈው የ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ውይይት ላይ ትናንትናና ዛሬ ተቃዋሚዎች እየመከሩ ሲሆን ዋናዎቹ ተቃዋሚዎች መድረክ፣ ሠማያዊ እና መኢአድ በውይይቱ ላይ አልተሳተፉም፡፡
መንግስት ለሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች 20 አባሎቻቸውን አርብና ቅዳሜ በሚደረግ ውይይት ላይ እንዲያሳትፉ በደብዳቤ ያሳወቀ ሲሆን ኢዴፓን ጨምሮ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በውይይቱ መሳተፋቸውን ሲያረጋግጡ ዋናዎቹ ተቃዋሚዎች ግን ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ በውይይቱ ሳይሳተፉ ቀርተዋል፡፡
ሠማያዊ ፓርቲ የመንግስት እቅድ ላይ ለውይይት ከመቀመጤ በፊት በብዙሃን ፓርቲ ዲሞክራሲ፣ በሰብአዊ መብት አያያዝ፣ የነፃ መገናኛ ብዙሃንና ሲቪክ ማህበራትን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ መወያየት አለብኝ ሲል በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፃፈው የምላሽ ደብዳቤ አስታውቋል፡፡
“በኢትዮጵያ ሰላምና እድገት እቅድ ላይ ከመወያየት በፊት በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ መወያየት አስፈላጊ ነው” ያለው የፓርቲው መግለጫ፤ መሠረታዊ ጉዳዮች መፍትሔ ባልተበጀላቸው ሁኔታ በዕቅዱ ዝርዝር አፈፃፀም ላይ መወያየት ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና ያመጣል ብሎ እንደማያምን በደብዳቤው አመልክቷል፡፡
የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በበኩሉ፤ በውይይቱ ላይ እንዲሳተፉ ከመንግስት በቀረበለት ጥሪ ላይ ስራ አስፈፃሚ ተሰብስቦ መቅደም ያለባቸው ብሔራዊ ጉዳዮች አሉ በማለት ከመሳተፍ መቆጠብን እንደመረጠ ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡ ፓርቲው ስብሰባው ላይ ለመሳተፋ የማይችልባቸውን ሶስት ምክንያቶች ጠቅሷል፡፡ የብሔራዊ እርቅና መግባባት ላይ ያተኮረ ስብሰባ በቅድሚያ እንዲጠራም ጠይቋል፡፡
ግዙፉ ብሔራዊ እቅድ ሁሉንም አሣታፊ በሆነ መልኩ ከግብ እንዲደርስ መጀመሪያ ሁሉንም ተቃዋሚ ያሳተፈ የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ጉባኤ መጠራት አለበት ያለው ፓርቲው፤ “የልማት መሠረቱ የዜጐችን ሰብአዊ መብት መጠበቅ ስለሆነ የመኢአድ አባላትም ሆኑ ሌሎች የተቃዋሚ አባላት እየተሰቃዩ፣ እየተሳደዱ፣ እየተዋከቡ ባለበትና አጠቃላይ የሰብአዊ መብታቸው በተገፋበት ሁኔታ እንዲሁም ዜጐች ክልልህ አይደለም በሚል እየተፈናቀሉ፣ በስብሰባው ላይ መገኘት ፍሬ ሊሰጥ የሚችል አይደለም” ብሏል፡፡ የሚካሄደው ውይይት ለሠፊው የኢትዮጵያ ህዝብ በሚዲያዎች በቀጥታ የሚሠራጭ ባለመሆኑ ሃሳባችን ተቆራርጦ የተሳሳተ መልዕክት ሊተላለፍ ይችላል በሚል ስጋት ከውይይቱ ራሱን ያገለለው ደግሞ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ነው፡፡
ትናንት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ በተደረገው የመጀመሪያ ቀን ውይይት መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የተገኙ ሲሆን “የተለያዩ የፖለቲካ አቋሞች ቢኖሩም ያለን አንድ አገር በመሆኑ ሁሉም አካላት በአገሪቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መወያየትና ግብአት መስጠት አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡ በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን አፈፃፀም ላይ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው አደም ጽሑፍ ካቀረቡ በኋላ የፓርቲ ተወካዮቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የኢዴፓ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱ መልካም መሆኑን ጠቅሰው በመጀመሪያው የእቅድ ዘመን ላይ ተመዘገበ ተብሎ የቀረበው የኢኮኖሚ እድገት አሃዝ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ በተለይ የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅና ግብርናን ከማዘመን አንፃር የሚቀሩ ስራዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ተወካይ በበኩላቸው፤ የኑሮ ውድነቱ ላይ መንግስት ትኩረት አድርጐ አልሠራም፤ በቀጣይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ያሉ ሲሆን የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ተወካይ ደግሞ ከመሠረተ ልማት ግንባታና ከሃብት ብክነት ጋር የተያያዙ አስተያየቶች ሰጥተዋል፡፡ ትናንት በመጀመሪያው የእቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት ሲደረግ የዋለ ሲሆን በዛሬው እለት በቀጣይ ሊተገበር በታሰበው ሁለተኛው እቅድ ላይ ውይይት ይካሄዳል ተብሏል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ ኢዴፓ፣ አንድነት፣ ቅንጅት እና ኢራፓን ጨምሮ 20 ያህል ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ተሣታፊ መሆናቸውም ታውቋል፡፡

“መንግሥት ተቃዋሚዎችን አወያያለሁ
የሚለው ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ነው”

አንድም ተቃዋሚ ፓርቲ ወይም የግል ተወካይ የማይኖርበት 5ኛው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የፊታችን ሰኞ የሚመሰረት ሲሆን ም/ቤቱ አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦችና የሰሉ ትችቶች የማይደመጡበት እንደሚሆን ተቃዋሚዎች ገለፁ፡፡
በፓርላማው የተቃዋሚ ፓርቲ ድምፅ አለመኖር ህዝቡን ይጐዳል ያሉት የመድረክ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ “ከዚህ ቀደም በፓርላማ በነበረን ጊዜ ያለመታከት የህዝብን ሰቆቃና እሮሮ ስናሰማ ነበር፤ አሁን ፓርላማው ከዚህ አይነቱ ጥያቄና አስተያየት ውጭ ነው” ብለዋል፡፡  በውጭም በሃገር ውስጥም ከማንኛውም መድረክ ይልቅ ተደማጭ የሚሆነው በፓርላማ የሚሰነዘር ሃሳብ ነው የሚሉት ፕ/ር በየነ፤ ይህ መድረክ አለመኖሩ ተቃዋሚው በሃገሩ ጉዳይ ያለውን ሃሳብ ህብረተሰቡ እንዳይረዳ እንቅፋት ይሆናል ብለዋል፡፡
ገዢው ፓርቲ እንደ ተምሳሌት ከሚከተለው የቻይና መንግሥት ጋር በዚህ ረገድ በሚገባ ተቀራርበዋል ያሉት ፕ/ሩ፤ ይህ ሁኔታ ግን ለኢትዮጵያ ህዝብ አደገኛ እንደሆነና የህዝብ እውነተኛ ድምፅ ሊታፈን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፤ “እስከዛሬ ከመንግሥት ጋር ተቀራርበን ለመስራት ያደረግነው ጥረት ውጤት አላስገኘም፣ ከዚህ በኋላ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራው የስርዓት ለውጥ እንዴት መምጣት አለበት በሚለው ላይ ነው” ብለዋል፡፡  
የመድብለ ፓርቲ ስርአት ፍፁም የደበዘዘበትና ህዝቡ ተስፋ የቆረጠበት ሁኔታ ነው የሚታየው የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ፓርላማውም ቢሆን የአንድን ፓርቲ አስተሳሰብ በቻ የሚያንፀባርቅ በመሆኑ ለመጪዎቹ 5 አመታት ከፓርላማው ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅም ነገር ይገኛል ብለን አናምንም ብለዋል፡፡
በፓርላማው የህግና የፖሊሲ ክርክር አድርጐ ለውጥ ለማምጣት ገዢው ፓርቲ ፍላጐት የለውም የሚሉት ዶ/ር ጫኔ፤ ምናልባት ይህ አካሄድ የተቃዋሚ ሃሳቦችን ከመድረኩ የማጥፋት ስትራቴጂ ውጤት ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡
የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሃሪ ደግሞ አዲስ የሚመሰረተው ፓርላማ  ለሃገሪቱም ሆነ ለመንግስት አይበጅም ባይ ናቸው፡፡  ምክንያታቸውን ሲጠቅሱም፤ ፓርላማው ሁሉን አቀፍ አሳታፊ ባለመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ “አሳታፊ ያልሆነ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ በምንም መልኩ ውጤታማ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም” ብለዋል አቶ አበባው፡፡
የተቃዋሚዎች ድምፅ በፓርላማ አለመኖሩ እምብዛም እንደማያሳስበው የሚገልፀው መንግሥት በበኩሉ፣ በሌላ መንገድ ከተቃዋሚዎች ጋር የተለያዩ የውይይት መድረኮችን በመክፈት በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አደርጋለሁ ብሏል፡፡ በኢህአዴግ 10ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ መንግስታቸው ከተቃዋሚዎች ጋር በወሳኝ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ዝግጁ እንደሆነ  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
ተቃዋሚዎች ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር እምነት እንደሌላቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
መድረክ በተደጋጋሚ ከገዢው ፓርቲ ጋር ለመወያየት ያቀረባቸው ጥያቄዎች ምላሽ አለማግኘታቸውን የሚያስታውሱት ፕ/ር በየነ፤ “የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም እንደ ወቅቱ  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሁሉ ተቃዋሚዎችን እናወያያለን ሲሉ የነበረ ቢሆንም አንድም ቀን አላወያዩንም፤ አሁንም እናወያያለን የሚለው ሃሳብ የለጋሾችን ቀልብ ለመግዛት ካልሆነ በስተቀር ተግባራዊ የሚሆን አይደለም ብለዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ መድረክ አሁንም ከመንግሥት ጋር ለመወያየት ጥረት እንደሚያደርግ ፕሮፌሰር በየነ ገልፀዋል፡፡ ፡
የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፤ በየጊዜው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃዋሚዎችን እናወያያለን የሚሉት  ፈፅሞ አምባገነናዊ ስርአት ነው ላለመባልና ዲሞክራሲያዊ ስርአት ያለ ለማስመሰል ነው ብለዋል፡፡ “አንድም ቀን መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲን  አቅርቦ አወያይቶ አያውቅም፣ በየጊዜው እናወያያለን ቢልም ወደ ተግባር ሲቀየር አላየንም” ብለዋል ዶ/ር ጫኔ፡፡ ነገሩ ከፖለቲካና ዲፕሎማሲያዊ ንግግር የዘለለ አይደለም ባይ ናቸው፡፡
የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሃሪም የሁለቱን ፖለቲከኞች ሃሳብ ይጋራሉ፡፡  መንግሥት በተደጋጋሚ ተቃዋሚዎችን አወያያለሁ ቢልም እስከዛሬ ሲፈጽመው አልታየም፤ ለወደፊትም ያነጋግረናል የሚል ተስፋ የለኝም ይላሉ፡፡ “በትክክል ዲሞክራሲን ለማስፈን የሚደረግ ጥረት ያለ አይመስለኝም፤ ተቃዋሚዎች ‘አባሎቻችን ላይ ወከባና ድብደባ ደረሰብን’ ሲሉ ጆሮ ዳቦ ልበስ እየተባሉ፣ መንግሥት በምን ጉዳይ አወያያለሁ እንደሚል አይገባኝም” ብለዋል፡፡
የህዝብ ውይይት እየተካሄደበት እንደሆነ በሚነገርለት 2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዙሪያ መንግሥት ተቃዋሚዎችን እንደሚያወያይ መግለፁ የሚታወቅ ሲሆን በቅርቡም ለሁሉም ፓርቲዎች በስልክ የውይይት ግብዣ ጥሪ መደረጉንና ተቃዋሚዎችም ጉዳዩ በደብዳቤ  ተጠቅሶ ጥሪ ይቅረብልን የሚል ምላሽ መስጠታቸው ታውቋል፡፡ ይህን ተከትሎም በደብዳቤ ጥሪ ይደረግላችኋል እንደተባሉና የውይይት ጊዜው እንደተቀየረም ተቃዋሚዎቹ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

የአቶ አቢሴሎም ይህደጐ የቀብር ስነስርአት ዛሬ ይፈፀማል

   የአትሌቲክስ ስፖርት ወዳጅ የነበሩት የቀስተ ደመና ስፖንጅ ፋብሪካ ባለቤት አቶ አቢሴሎም ይህደጐ፤ ከትላንት በስቲያ ከዚህ አለም በሞት የተለዩ ሲሆን የቀብር ስነስርአታቸው ዛሬ ከቀኑ 9 ሰአት በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተክርስቲያን ይፈፀማል፡፡ ባደረባቸው ህመም ለአንድ አመት ያህል በውጭ ሀገርና በሃገር ውስጥ ህክምና ሲከታተሉ የቆዩት አቶ አቤሲሎም፤ በ72 አመታቸው ነው ያረፉት፡፡
ከወላጅ አባታቸው ብላታ ይህደጐ ለማ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ምትክ ተስፋዬ፣ ኤርትራ አስመራ ውስጥ የተወለዱት ባለሃብቱ፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም የተከታተሉት በአስመራ ነው፡፡ በአዲስ አበባ በስዊድሽ ሚሽንና በተፈሪ መኮንን ት/ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መከታተላቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ታዋቂው ባለሃብት አቶ አቤሴሎም የቀድሞ ሳምሶን ዳቦ ቤት ባለቤት እንደነበሩና በኋላም ቀስተደመና ስፖንጅ ፋብሪካን በማቋቋም ለበርካታ ወገኖች የስራ እድል እንደፈጠሩ  ከቤተሰቦቻቸው ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
አቶ አቤሴሎም የ3 ልጆች አባት ነበሩ፡፡

በሳዑዲው አሰቃቂ አደጋ የአገሪቱ ባለሥልጣናት እየተወዛገቡ ነው

131 ዜጎቿን ያጣችው ኢራን፤ ሳኡዲ አረቢያን ተጠያቂ አድርጋለች
እስካሁን በአደጋው 717 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል

በሳዑዲ አረቢያ በሀጂ ስነስርዓት ላይ ከትናንት በስቲያ 717 ሰዎች በሞቱበት አደጋ የአገሪቱ ባለስልጣናት እየተወዛገቡ ሲሆን፤ የኢራን መንግስት 131 ዜጐቹ መሞታቸውን በመግለጽ የሳዑዲን መንግስት ተጠያቂ አድርጓል፡፡
ከመካ በ5 ኪ.ሜትር ርቀት በሚገኘው ሚና የሚባል አካባቢ፣ በሰይጣን ላይ ድንጋይ የመወርወር ሃይማኖታዊ ስነ ስርአት ላይ በተፈጠረ ግርግር ነው አደጋው የተከሰተው ተብሏል፡፡ የብዙዎችን ህይወት በቀጠፈው አደጋ፤ 863 ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ለሃጂ ስነስርዓት በሄዱ ኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰ አደጋ ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም፡፡
የኢራን መንግስት መሪ አያቶላ ሆሚኒ፤ አደጋው የተፈጠረው በሳዑዲ መንግስት ዝርክርክ አሰራር ነው፤ ለአደጋው ሙሉ ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት ብለዋል፡፡
የሳኡዲ የጤና ሚኒስትር ካሊድ አል-ፍሌህ በዚህ አይስማሙም፡፡ አደጋው የተከሰተው በምዕመናን ጥፋት ነው ብለዋል፡፡ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መንሱር አልቱርኪ፤ ተመሳሳይ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ብዙ ምዕመናን፤ በተመሳሳይ ሰአት በጠባብ መተላለፊያ ላይ የፈጠሩት ግርግር የአደጋው መንስኤ ነው ብለዋል – ቃል አቀባዩ፡፡
የሀጂ ኮሚቴ ሊቀመንበር ልዑል መሃመድ ቢን ናይፍ በበኩላቸው፤ የአደጋው መንስኤ በአስቸኳይ ተጣርቶ እንዲቀርብላቸው ትዕዛዝ የሰጡ ሲሆን፣ የሀገሪቱ ንጉስ ሰልማን ግን የሀጂ ጉዳይ ድርጅቱ እንደገና እንዲዋቀር አዘዋል፡፡
በአደጋው ከሞቱት መካከል፣ 131 የኢራን፣ 14 የህንድ፣ 18 የቱርክ፣ 7 የፓኪስታን፤ 3 የአልጄሪያ እና 3 የኢንዶኔዢያ ዜጎችን ጨምሮ፣ ቁጥራቸው ያልተጠቀሰ የናይጄሪያ፣ ኒጀር፣ ቻድ፣ እና ሴኔጋል ዜጎች የአደጋው ሰለባ ሆነዋል ተብሏል፡፡
በሳኡዲ የብዙዎችን ህይወት የቀጠፈ አደጋ በአንድ ወር ውስጥ ሲያጋጥም ያሁኑ ሁለተኛው ነው፡፡ ከቀናት በፊት በመካ ታላቁ መስጊድ ላይ፤ የግንባታ ክሬን ወድቆ፣ 109 ሰዎች መሞታቸው ይታወቃል፡፡
ከትናንት በስቲያ ያጋጠመው አደጋ ከተሰማ በኋላ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ ባንኪሙን እና የካቶሊክ ፓፓስ ፍራንሲስ የሀዘን መልዕክታቸው ካስተላለፉት ቀዳሚዎቹ ሆነዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ1990 ካጋጠመውና 1426 ሰዎችን ለህልፈት ከዳረገው ተመሳሳይ አደጋ ቀጥሎ የሰሞኑ የበርካታ ምዕመን ህይወት የተቀጠፈበት አደጋ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የ44 ሚ. ብር ግብር ዕዳ ያለበት “ሪል ውሃ” ከፍተኛ ምርመራ እየተደረገበት ነው

    ቲ ጂ ኤም ዲ በሚል ስያሜ የተመሰረተው የ “ሪል ውሃ” አምራች ኩባንያ፤ ያለበት 44 ሚ.ብር የግብር ዕዳ በምርመራ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ገለፀ፡፡ ኩባንያው ከ1999 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ ታደለ ዳለቻ በተባለ ግለሰብ ስራ አስኪያጅነት ሲመራ የቆየ ሲሆን ከ2002 እስከ 2003 ዓ.ም አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ይመሩት እንደነበር የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የትምህርትና ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ በላይ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ በመቀጠል ድርጅቱ አቶ መሃመድ ለተባሉ ግለሰብ የተሸጠ ሲሆን የኩባንያው እንቅስቃሴ ሲጠና ቆይቶ፣ 44 ሚ ብር የግብር እዳ እንዳለበት መታወቁን ይህንንም እዳ ግለሰቡ እንዲከፍሉ የሚጠይቅ ደብዳቤ በ2005 ዓ.ም ከባለስልጣኑ መ/ቤት እንደተፃፈላቸው ምክትል ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡ ግለሰቡ “ኩባንያውን ስገዛው ይሄ ሁሉ እዳ እንዳለበት አላውቅም’ የሚል ምክንያት አቅርበዋል” ያሉት አቶ ፋሲካ፤ አንድ ኩባንያ በሽያጭ ሲዘዋወር ክሊራንስ ሳይወጣበት ስለማይዘዋወር የሰውየው ምክንያት ተቀባይነት ያለው አልነበረም ብለዋል – አቶ ፋሲካ፡፡ በኋላ ግን ኩባንያውን የገዙት ግለሰብ ወደ ባለስልጣኑ በመቅረብ፤ “ያለበትን እዳ ቅድሚያ 25 በመቶ ከፍዬ ቀሪውን ቀስ በቀስ እከፍላለሁ” እያሉ ሲያዘናጉ ቢቆዩም፣ ኩባንያው ግን እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ ማምረት አለማቆሙን ባለስልጣኑ ደርሶበታል ብለዋል ም/ዳይሬክተሩ፡፡ ኩባንያው ክስ ያልተመሰረተበት ጉዳዩ ውስብስብ በመሆኑ ነው ያሉት አቶ ፋሲካ፤ በአሁኑ ወቅት የግብሩ ዕዳ በከፍተኛ ምርመራ ላይ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡የሪል ውሃ ማምረቻ ድርጅት ከ190 በላይ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ያለፉትን ሁለት ወራት ደመወዝ ያልተከፈላቸው መሆኑንና የሪል ውሃ ማምረቻው የሚገኝበት የቡራዩ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ፅ/ቤትም ለዓመታት ከሰራተኞቹ ደመወዝ የሚቆረጠው የስራ ግብር አልደረሰኝም ማለቱን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግቧል፡፡

የመንገድ ላይ ንብረቶች ውድመት ተባብሷል

     በግጭት ምክንያት የሚደርሰው የመንገድ ንብረቶች ውድመት እየተባባሰ መምጣቱን በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ መብት ጥበቃና አስተዳደር ገለፀ፡፡
አስተዳደሩ ያለፈው ዓመት የስራ አፈፃፀሙን አስመልክቶ ከትላንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ በበጀት ዓመቱ በ569 የመንገድ ንብረት ላይ አደጋዎች ደርሰው ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን የጠቆመ ሲሆን ከነዚህም አደጋዎች ውስጥ 244 ያህሉ አደጋዎች በቀለበት መንገድ ላይ መከሰታቸውንና የንብረቶቹ ውድመት በገንዘብ ሲተመን፣ ከ1.3 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነም የአስተዳደሩ ንዑስ የስራ ሂደት መሪ አቶ አስመላሽ ኪዳነማርያም ተናግረዋል፡፡
ቀሪዎቹ 325 አደጋዎች በሌሎች ዋና ዋና መንገዶች ላይ የተከሰቱ ሲሆን ግጭቶች ያደረሱት ጉዳት በገንዘብ ሲተመን ከ3.6 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በአብዛኛው ለጉዳት የሚዳረጉት የመንገድ ላይ ንብረቶች የመንገድ ዳር መብራቶች፣ የእግረኛ  መከላከያ አጥሮች፣ የመንገድ ማካፈያ፣ መከላከያ ግንብና የትራፊክ ምልክቶች ሲሆኑ በግጭት ምክንያት ከሚደርስባቸው ጉዳትና ውድመት ባሻገር በህገ ወጥ ግለሰቦችም ስርቆት እንደሚፈፀምባቸው ተገልጿል፡፡ በበጀት ዓመቱ በግጭትና በስርቆት ምክንያት በመንገድ አካላቶች ላይ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት መድረሱንም አቶ አስመላሽ አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ አስመላሽ ገለፃ፤ ባለስልጣኑ በግጭት ጉዳት የሚደርስባቸውን ንብረቶች በክትትል ካሳ ከማስከፈልም በተጨማሪ በመንገድ ላይ በሚያጋጥሙ ህገ-ወጥ ተግባራት ላይ የቁጥጥርና የክትትል ስራ የሚያከናውን ሲሆን በዚህም ክትትልና ቁጥጥር በዋና መንገዶች ላይ የግንባታ መስሪያዎች ያከማቹ 105 ግለሰቦች ላይ የገንዘብ መቀጫ ጥሏል፡፡
የመንገድ ላይ ንግድ፤ በግንባታ ስም እግረኛ መንገድን ማጠር፣ ከባድ መኪናን ለረጅም ጊዜ አቁሞ መጥፋት፣ ህገወጥ ማስታወቂያዎችን መለጠፍ፣ ማንጠልጠልና መትከል፣ በባለስልጣኑ ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሲሆን እነዚህን ህገ ወጥ ድርጊቶችን ባከናወኑ አካላት ላይ እርምጃ መውሰዱንም ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
ህብረተሰቡ የመንገድ ላይ ንብረቶችን እንደራሱ ንብረት እንዲጠብቅና ህገ-ወጦችን እንዲጠቁም ባለስልጣኑ የግንዛቤ ስራዎችን የሚራ ሲሆን በህገ-ወጦች የሚፈፀሙ ጥፋቶችን እንዲጠቆም 917 ነፃ የስልክ መስመርን ማስተዋወቁንም ገልፀዋል፡፡
“ምንም እንኳ ባለስልጣኑ በመንገድ አካላት ላይ የደረሱ ውድመቶችን ካሳ ሙሉ በሙሉ ማስከፈል ቢችልም የግጭቱ መጠን ግን ከ2006 የበጀት ዓመት ጨምሯል ያሉት ኃላፊው፤ በ2007 የደረሱት የመንገድ ንብረት አደጋዎች ቀደም ካለው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ126 አደጋዎች ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
ባለስልጣኑ በ2008 የበጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ለመከወን የዓምናውን ልምድ መነሻ በማድረግ ቀመር ማውጣቱንም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡