በፌስቡክ “አይኤስ ነኝ” ብሎ ፅፏል የተባለው ወጣት ተከሰሰ
ግድያ ለመፈፀም ዝቷል- አቃቤ ህግ
በፌስቡክ፤ “አይኤስ ነኝ” ከሚል መልእክት ጋር የግድያ ዛቻ በማስተላለፍ የሽብር ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ የተከሰሰው ወጣት ላይ፤ የአቃቤ ህግ ከትናንት በስቲያ ምስክሮችን አቀረበ፡፡ አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ፣ ሰይድ መሃመድ፣ በሚያዚያ ወር 2007 ዓ.ም፤ “አይኤስ ነኝ” በማለት በፌስቡክ እንደጻፈ ይገልጻል፡፡ የአይኤስ ወታደር ነኝ … በቅርቡ በረመዳን ወር የሚታረዱትን ለመያዝ ወደ ባቲ እመጣለሁ” የሚል የዛቻ መልዕክት በግል በፌስቡክ ገፁ ላይ ለጥፏል ብሏል – አቃቤ ህግ፡፡
1ኛ የአቃቤ ህግ ምስክር፤ ከላይ የተጠቀሰው መልዕክት ላይ ሰዎች አስተያየት በሰጡበት ወቅት ይህንን መልዕክት በፌስቡክ መመልከቱን የገለፀ የአቃቤ ህግ ምስክር፤ ከአካባቢዬ ወጣቶች ጋር በመመካከር ለፖሊስ ጠቁሜያለሁ ብሏል፡፡
የባቲ ከተማ ፖሊስ መሆናቸውን የገልፁ ሌላ የአቃቤ ህግ ምስክር በበኩላቸው፣ ጥቆማ ከደረሰን በኋላ ተጠራጣሪውን በቁጥጥር ስር አውለናል ብለዋል፡፡ በተጠርጣሪው የፌስቡክ ገፅ ላይም፤ “አይኤስ ማለት እንደኔ አይነት ነው፡፡ በረመዳን ወር ለእርድ ወደ ባቲ እመጣለሁ” የሚል መልዕክት አይቻለሁ ብለዋል፡፡
በወቅቱ “ለምን ይሄን አደረግህ” ብዬ ጠይቄዋለሁ፤ እሱም፤ “እኔ ጓደኞቼን ለማስፈራራት ነው እንጂ አይኤስ አይደለሁም” ሲል መልሶልኛል ብለዋል – እኚሁ የአቃቤ ህግ ምስክር፡፡ በሚያዚያ ወር፤ አይኤስ የተሰኘው አሸባሪ ቡድን፣ በሊቢያ በርካታ ኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን በሚያዝያ ወር፣ አይ ኤስ የተሰኘው አሸባሪ ቡድን በሊቢያ በርካታ ኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ ለማውገዝ፤ ወደ ሰላማዊ ሰልፍ ለመሄድ እየተዘጋጀሁ እንደነበር አስታውሳለሁ፤ ተጠርጣሪው የተያዘውም በዚያኑ እለት ነው በማለት ምስክሩ ተናግረዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው፤ ተጠርጣሪው ለምርመራ ወደ አዲስ አበባ የመጣው ተብሏል፡፡
የአቃቤ ህግ 3ኛ ምስክር የአዲስ አበባ ነዋሪ እንደሆኑ ጠቅሰው፤ ተጠርጣሪው የፌስቡክ ገፁ የራሱ መሆኑን አምኖ ሲፈርም እኔ በታዛቢነት ፈርሜያለሁ ብለዋል፡፡ በፌስቡክ አካውንቱ ላይ የተፃፈውንም መልዕክት እንደተመለከቱ ተናግረዋል፡፡
ፍ/ቤቱም የምስክሮቹን ቃል ካደመጠ በኋላ በመቅረፀ ድምፅ የተቀረፀው ምስክርነት ወደ ፅሁፍ ተገልብጦ የመዝገቡ አካል እንዲሆን ትዕዛዝ ያስተላለፈ ሲሆን ምስክርነቱን መርምሮ ብይን ለመስጠትም ለህዳር 30 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሹ ወጣት፤ የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ እስከማገኝ ድረስ በንፁህነት የመታየት መብቴን እንዳላጣ፣ የፍርድ ሂደቱ፤ ተመልካችና ጋዜጠኛ ሳይኖር፤ በዝግ ይታይልኝ ሲል ጠይቋል በጠበቃው አማካኝነት፡
፡ ፍ/ቤቱ ግን፤ ክሱ መታየት የጀመረውና የተነበበው ተመልካቾች ባሉበት በግልፅ ችሎት መሆኑን በመጥቀስ፣ አቤቱታውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ በተከሳሹ የፌስቡክ ገፅ ላይ የተለጠፈው መልእክት፤ “እኔ አይኤስ አይኤስ ነኝ፣ የስራ ድርሻዬም ሰውን እጅና እግሩን አንጋልዬ መያዝ ነው፤ ደሞዝ የሚከፈለኝ በያዝኩት ሰው ልክ ነው፣ የአይኤስ ወታደር ነኝ፤ በቅርቡ ወደ ባቲ ለእርድ እመጣለሁ” የሚል ነው ብሏል – አቃቤ ህግ፡፡ ተከሳሹ በበኩሉ፤ “የፃፍኩት ለቀልድ ነው” ማለቱ ተገልጿል፡፡