የመንገድ ላይ ንብረቶች ውድመት ተባብሷል

በግጭት ምክንያት የሚደርሰው የመንገድ ንብረቶች ውድመት እየተባባሰ መምጣቱን በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ መብት ጥበቃና አስተዳደር ገለፀ፡፡
አስተዳደሩ ያለፈው ዓመት የስራ አፈፃፀሙን አስመልክቶ ከትላንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ በበጀት ዓመቱ በ569 የመንገድ ንብረት ላይ አደጋዎች ደርሰው ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን የጠቆመ ሲሆን ከነዚህም አደጋዎች ውስጥ 244 ያህሉ አደጋዎች በቀለበት መንገድ ላይ መከሰታቸውንና የንብረቶቹ ውድመት በገንዘብ ሲተመን፣ ከ1.3 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነም የአስተዳደሩ ንዑስ የስራ ሂደት መሪ አቶ አስመላሽ ኪዳነማርያም ተናግረዋል፡፡
ቀሪዎቹ 325 አደጋዎች በሌሎች ዋና ዋና መንገዶች ላይ የተከሰቱ ሲሆን ግጭቶች ያደረሱት ጉዳት በገንዘብ ሲተመን ከ3.6 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በአብዛኛው ለጉዳት የሚዳረጉት የመንገድ ላይ ንብረቶች የመንገድ ዳር መብራቶች፣ የእግረኛ መከላከያ አጥሮች፣ የመንገድ ማካፈያ፣ መከላከያ ግንብና የትራፊክ ምልክቶች ሲሆኑ በግጭት ምክንያት ከሚደርስባቸው ጉዳትና ውድመት ባሻገር በህገ ወጥ ግለሰቦችም ስርቆት እንደሚፈፀምባቸው ተገልጿል፡፡ በበጀት ዓመቱ በግጭትና በስርቆት ምክንያት በመንገድ አካላቶች ላይ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት መድረሱንም አቶ አስመላሽ አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ አስመላሽ ገለፃ፤ ባለስልጣኑ በግጭት ጉዳት የሚደርስባቸውን ንብረቶች በክትትል ካሳ ከማስከፈልም በተጨማሪ በመንገድ ላይ በሚያጋጥሙ ህገ-ወጥ ተግባራት ላይ የቁጥጥርና የክትትል ስራ የሚያከናውን ሲሆን በዚህም ክትትልና ቁጥጥር በዋና መንገዶች ላይ የግንባታ መስሪያዎች ያከማቹ 105 ግለሰቦች ላይ የገንዘብ መቀጫ ጥሏል፡፡
የመንገድ ላይ ንግድ፤ በግንባታ ስም እግረኛ መንገድን ማጠር፣ ከባድ መኪናን ለረጅም ጊዜ አቁሞ መጥፋት፣ ህገወጥ ማስታወቂያዎችን መለጠፍ፣ ማንጠልጠልና መትከል፣ በባለስልጣኑ ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሲሆን እነዚህን ህገ ወጥ ድርጊቶችን ባከናወኑ አካላት ላይ እርምጃ መውሰዱንም ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
ህብረተሰቡ የመንገድ ላይ ንብረቶችን እንደራሱ ንብረት እንዲጠብቅና ህገ-ወጦችን እንዲጠቁም ባለስልጣኑ የግንዛቤ ስራዎችን የሚራ ሲሆን በህገ-ወጦች የሚፈፀሙ ጥፋቶችን እንዲጠቆም 917 ነፃ የስልክ መስመርን ማስተዋወቁንም ገልፀዋል፡፡
“ምንም እንኳ ባለስልጣኑ በመንገድ አካላት ላይ የደረሱ ውድመቶችን ካሳ ሙሉ በሙሉ ማስከፈል ቢችልም የግጭቱ መጠን ግን ከ2006 የበጀት ዓመት ጨምሯል ያሉት ኃላፊው፤ በ2007 የደረሱት የመንገድ ንብረት አደጋዎች ቀደም ካለው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ126 አደጋዎች ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
ባለስልጣኑ በ2008 የበጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ለመከወን የዓምናውን ልምድ መነሻ በማድረግ ቀመር ማውጣቱንም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡