በማሕሌት ፋንታሁን

መንግሥት አሸባሪ ብሎ ከፈረጃቸው ተቋማት ጋር ማቆራኘት ሳያስፈልገው የጻፈው ጽሑፍ ብቻ ተጠቅሶበት የተከሰሰ እና የተፈረደበት ብቸኛ ጋዜጠኛ ነው – ተመስገን ደሳለኝ። በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የተመሠረተችው ፍትህ ጋዜጣ ጥቂቶቹን የግል ሕትመት ሚዲያ ውጤቶች የተቀላለችው በ2000 ነበር። ከምርጫ 97 በኋላ የተከሰተውን የግል ሚዲያ እጥረት አሳስቦት እና የበኩሉን ለመወጣት ብሎ ነው ፍትሕን ለመመሥረት የተነሳሳው። ፍትሕ ጋዜጣ ሕትመት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ እስከ 2004 ሐምሌ ወር (ላይ እስክትታገድ ድረስ) ድረስ ከዓመት ወደ ዓመት የሕትመት ብዛቷ እየጨመረ መጨረሻ አካባቢ እስከ 35ሺ ኮፒ ትታተም ነበር።

ማንኛውም ዓይነት ቅድመ ሳንሱር እንደሌለ በሚደነግገው ሕገመንግሥት መተዳደር ያለበት ፍትሕ ጋዜጣን የሚያትመው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ የሐምሌ 13/2004 ዓም እትም ላይ ስለ መለስ ዜናዊ የተጻፈ ዜና ካልወጣ እንደማያትሙ አሳወቁ። ይህን የሰማው ተመስገን እያረጉ ያሉት  ቅድመ ሳንሱር መሆኑን፣ ይህ ደግሞ በሕገመንግሥቱ የተከለከለ መሆኑን ከገለጸላቸው በኋላ የታዘዙትን 30ሺ ኮፒ ካተሙ በኋላ እንዳይሰራጭ ከፍትሕ ሚኒስቴር በተላለፈ ትዕዛዝ መሠረት ማገዳቸውን እና የታተመው ጋዜጣም መወረሱን በደብዳቤ ገለፁ። ለ30ሺ ኮፒ ሕትመት፣ ለጸሐፊዎች የሚከፈል እና ለተለያዩ አስተዳደራዊ  ወጪዎች የወጣው ገንዘብ ወደ100ሺ ብር የሚጠጋ ከስሯል። ነሐሴ 2 ቀን  2004 ክስ እንደተመሠረተበት ፋና ዜና ላይ እንደሰማ የሚናገረው ተመስገን፣ በዜናው እንደሰማውም በቀጣይ ቀጠሮ ነሐሴ 9 ቀን 2004 ፍ/ቤት ቀረበ። በ2003 እና በ2004 በፍትሕ ጋዜጣ ላይ በወጡ 5ት ጽሑፎች ሦስት ክስ እንደቀረበበት ተነግሮት የዋስትና መብቱንም ተነፍጎ የዛኑ ቀን ወደ እስር ቤት ገባ። ለስድስት ቀናት በቃሊቲ ጨለማ ቤት ከቆየ በኋላ ባልተጠበቀ ሰዓት እና ምክንያቱ ሳይነግው  ነሐሴ 16/2004 ከእስር ተለቀቀ። በኋላ ሁላችንም እንደሰማነው ከእስር የተለቀቀው ክሱ ተቋርጦለት መሆኑን ነው።

ጋዜጠኛ ተመስገን የቀረቡበት ክሶች 1ኛ) ወጣቶች በአገሪቱ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱ ላይ እንዲያምፁ የመገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር፣ 2ኛ) የሀገሪቱን መንግሥት ሥም ማጥፋት እና የሐሰት ውንጀላ፣ 3ኛ) ክስ የሐሰት ወሬዎችን በማውራት ሕዝብን በማነሳሳት ወይም አስተሳሰባቸውን ማናወጥ ሲሆኑ ይህን ክስ ሊያስመሠርቱበት የቻሉት ጽሑፎች ደግሞ 1) የፈራ ይመለስ (በተመስገን ደሳለኝ) 2) የሁለተኛ ዜግነት ሕይወት በኢትዮጵያ እስከመቼ? (በተመስገን ደሳለኝ) 3) መጅሊሱና ሲኖዶሱ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ማጥመቂያ (በተመስገን ደሳለኝ) 4) ሞት የማይፈሩ ወጣቶች (በተመስገን ደሳለኝ) እና 5) የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከመጨፈር የሚሉት ናቸው።

ፍትሕ በዚ መልኩ ከሕትመት ከታገደች በኋላ ተሜ እጅ እና እግሩን አጣጥፎ አልተቀመጠም ወይም መሰደድን አልመረጠም። በ2005 ፍትሕን በአዲስታይምስ መጽሔት መልክ፣ እሱም እንዲዘጋ ሲደረግ በልዕልና ጋዜጣ እውነትን እንድናነብ ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን ለፍቷል። ልዕልናም ቀኗ ደርሶ ከሕትመቱ ዓለም ስትሰናበት ደግሞ በ2007 በግሉ ዘርፍ ይታተሙ ከነበሩ ተመራጭ ጥቂት መጽሔቶች እና ጋዜጦች ጋር ክስ ተመሥርቶባቸው እንዳይሠሩ ከታገዱት የሕትመት ውጤቶች መሐል አንዷ በሆነችው ፋክት መጽሔት ሥራውን ቀጥሎ ነበር።

በነሐሴ 13፣ 2004 ተቋረጠ የተባለው ክስ መቀስቀሱን አሁንም እሱ በሌለበት በታኅሣሥ ወር 2005 የዋለው ችሎት በፋና ሬዲዮ መዘገቡን ሰማ/ን። በቀጣዩ የቀጠሮ ቀን ሲቀርብ የ50ሺህ ብር የዋስትና ብር አስይዞ ክሱን ከውጪ ሆኖ እንዲከታተል ተፈቀደለት። ክሱን እየተከታተለም ነው ልዕልና ጋዜጣን እና ፋክት መጽሔትን ለኛ ላንባቢዎቹ ሲያደርስ የነበረው። ታኅሣሥ 2005 የተንቀሳቀሰበትን ክስ በዋስትና ሲከታተል ቆይቶ፤  በጥቅምት 3፣ 2007 ጥፋተኛ የተባለው እንዲሁም ጥቅምት 17፣ 2007 ላይ ደግሞ የ3 ዓመት ፍርድ የተፈረደበት።

ተመስገን የሥራ ሰዓት እና የእረፍት ሰዓት የለውም። ብዙውን ጊዜውን በመጻፍ ወይም በማንበብ ነው የሚያሳልፈው። የጻፈውን የኖረ እና እየኖረ ያለ ጋዜጠኛ ነው።

ዝዋይ ከመሄዱ በፊት ቃሊቲ በነበረበት ጊዜያትም ሆነ ዝዋይ ከሄደ በኋላ ተመስገን፣ ሌሎች እስረኞች እንዳይቀርቡት ይደረጋል። ቃሊቲ እያለ የአልሻባብ አባል ተብለው በሽብር ተከሰው ከሱ ጋር የሚኖሩ እስረኞች ከሱ ጋር ካወሩ ወይም ወክ ሲያደርጉ ከታዮ “እንዴት ከአሸባሪ ጋር ትሆናላችሁ?” ይባሉ እና የተለያዩ ማስፈራሪያዎች እንደሚደርስባቸው ነግረውታል። የዝዋዩ ደግሞ የባሰ ሆኖ ነው ያገኘው። ከሱ ጋር ያወራ ማታ ማታ እየተወሰደ ይደበደባል። ይህን በመፍራት ብዙ እስረኞች ከሱ ጋር መሆን ይፈራሉ። መጽሐፍ አይገባለትም። ሕክምና ለማግኘት ሲጠይቅ “ቆይ ያንተን ጉዳይ እየተነጋገርንበት ነው”  ከሚል ውጪ ያገኘው ምላሽ ስለሌለ ከጀርባ ሕመሙ ስቃይ ጋር አብሮ ይኖራል። ምንም ዓይነት መጽሐፍት አይገቡለትም። ከሌሎች እስረኞች ተውሶ ማንበብም አይችልም። እሱ ያለበት ዞን ላይብረሪ የለም። ቤተሰቦቹ እና ጓደኞቹ እንዳይጠይቁት ይከለከላሉ። ብዙ ጓደኞቹ እና ወዳጆቹ ብዙ ርቀት ተጉዘው ከእናቱ እና ወንድሞቹ ውጪ እሱን መጠየቅ አይቻልም ተብለው ይመለሳሉ። የዛሬ ዓመት አካባቢ እናቱን እና ወንድሞቹን ጭምር ለሁለት ወር ያክል እንዳይጠይቁት ተከልክለው ነበር። በተለያዩ ጊዜያትም እነዚሁ የቅርብ ቤተሰቦቹ ገብተው እንዳይጠይቁት ተከልክለው ይመለሳሉ። በአንድ ወቅት ታናሽ ወንድሙ የሆነው ታሪኩ ደሳለኝ ሊጠይቀው በሄደ ወቅት መግባት እንደማይችል ከነገሩት በኋላ በማያቀው ምክንያት በዝዋይ እስር ቤት ፓሊሶች ተደብድቧል።

ምክንያቱን ባይገባኝም ከቅርብ ቤተሰቦቹ ውጪ መጎብኘት የሚፈቀድለትን አንዳንድ ወቅቶች ተከታትለው የሚጠይቁት ጓደኞቹ ብዙ አይደሉም። ተመስገንን የምንወደው ጓደኛችን ከሆነ ከቤተሰብ ውጪ መጠየቅ አይቻልም ብሎ ቁጭ ከማለት ዝዋይ መጠየቅ ከሚፈቀድለት ቤተሰብ ጋር ሄዶ መልዕክት መላክ ወይም መጠየቅ የሚፈቀድበትን ወቅት ጠብቆ መሄድ።

ተሜ በዝዋይ ከሌሎች እስረኞች በተለየ ብዙ ማእቀቦች ተጥሎበት እየኖረ የመንፈሱ ጥንካሬ የሚገርም ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ አራት ፅሁፎችን አስነብቦናል። በእስሩ ወቅት ስላገኛቸው የኢትዮጵያ ሶማሌዎች የሚተርክ በሁለት ክፍል “የኢትዮጵያ መንግሥት ገመና ከዝዋይ እስር ቤት”  እንዲሁም አሁን በኦሮሚያ ስለተነሳው ሕዝባዊ አመፅ የጻፈው “ሁለተኛው ምዕራፍ” የሚሉት ጽሑፎች ይገኙበታል።

ከዓመት በፊት በላከው በአንደኛው ጽሑፉ እንዲህ ይላል  “…ግና! ይህ መንግሥታዊ የጭካኔ ተግባር፣ ዛሬም በምስኪን ዜጎች ላይ እየተፈፀመና ብዙዎችን ሰለባ እያደረገ በመሆኑ ሕዝቡ ይህን ሊሸሸግ እየተሞከረ ያለውን መከራ ተረድቶ ሥርዓቱን በአደባባይ ዓመፅ “ሃይ!” ይል ዘንድ ትርክቴን ለማጠናቀር ተገድጄያለሁ፡፡ ለእስር ያበቃኝ የጋዜጠኝነት ሙያዬም ተጨማሪ ዕዳ ጭኖብኛል፡፡”

ተሜ እንደቃሉ ጉዞውን እስከቀራኒዮ ያደረገ ጋዜጠኛ ነው። አንድ ዓመት ከአምስት ወር በእስር አሳልፏል። የሚወጣበት ቀን እየቀረበ ነው እንጂ እየራቀ አይደለም የሚሄደው። በቀሪዎቹ ጊዜዎች እና ከወጣ በኋላ በብዕሩ የሚያካፍለንን የኢሕአዴግ መንግሥት ገበናዎች ለማንበብ በጣም ነው የምጓጓው። ተሜ ከዚህ በፊት በብዙ ኮፒ ታትሞ ለገበያ ያበቃው “የመለስ አምልኮ” የተሰኘው መጽሐፍ ተወዳጅነትን አትርፎለታል። በ2007 መጨረሻ አካባቢ ደግሞ ከሙያ ባልደረቦቹ እና ከጋዜጠኛ እስክንድር ጋር (ከቃሊቲ እስር ቤት) በአንድነት በተለያየ ጊዜ የተጻፉ ጽሑፎችን በመጽሐፍ መልክ ታትሟል።

ተመስገን ደሳለኝ ከጋዜጠኝነት ሥራው በተጨማሪ ያለውን በማካፈል ይታወቃል። ለጓደኞቹ እና ለወዳጆቹ በችግራቸው ጊዜ ከጎናቸው ሆኖ ለመርዳት የሚችለውን ያደርጋል። በምስሉ ላይ ከተሜ ጋር የሚታዩት ሕፃናት ቤተሰቦቻቸው አቅመ ደካማ በመሆናቸው ወጪያቸውን በመሸፈን የሚረዳቸው ናቸው። ወጪያቸውን ከመሸፈን ባለፈም ባለው ትርፍ ሰዓት ያዝናናቸው፤ እንዲሁም በቋሚነት የሚማሩበት ት/ቤት በመሄድ የትምህርት ሁኔታቸውን ይከታተል ነበር። አሁን ጊዜው ተገልብጦ እነዚህ ህፃናት በወር አንድ ጊዜ ከእናቱ እና ወንድሙ ጋር በመሆን ዝዋይ ድረስ ሄደው ይጠይቁታል።

በነገራችን ላይ ተሜ እነዚህን ሕፃናት እና ቤተሰቡን እንደሚያስተዳድር ለፍ/ቤት ቢገልፅ የቅጣት ፍርዱ ይቀንስለት ነበር። ሆኖም ተሜ ጥፋት ስላላጠፋሁ አቅልሉልኝ ብዬ አልጠይቅም ብሎ ምንም አይነት ማቅለያ ሳያስገባ ነው 3 ዓመት የተፈረደበት።

ብርታትና ጥንካሬን ለተሜ እና ቤተሰቦቹ እየተመኘሁ ተሜን በጨረፍታዬን በዚሁ ላብቃ።

የአዲስ አበባ ከተማና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላንን ተቃውመው ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ተማሪዎች በኦሮሚያ ክልል በርካታ ወረዳዎችና ከተሞች  እያቀረቡት ያለው ሠላማዊ ጥያቄ በሰከነ መንገድ መልስ ለመስጠት ከመሞከር ይልቅ ተመጣጣኝ ያልሆነ ሀይል በመጠቀም ጥያቄውን ለማፈን እየተሞከረ ነው፡፡ በዚህ ሂደትም ብዙዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ ለቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጎችም ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ሰሞኑን ከሚወጡት መግለጫዎችና የመንግስት ባለስልጣናት ቃለመጠይቆች እንደተረዳነው  ጥያቄዎቻቸውን በሃይል ለመመከት ከመዛትና ዜጎችን ከሰው በታች አውርዶ ቁጣን በሚጋብዝ መልኩ ከመጥራት በዘለለ ሀላፊነት እንደሚሰማው አካል ለችግሩ መፍትሔ  ለመፈለግ ዝግጁነት እንደሌለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሁሌም እንዲከበር የምንጠይቀውን የሀገሪቱ ሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ-መንግስት የሚጻረር ነው፡፡

በዚህ ሂደት በጥቂቱ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የሕገ-መንግስቱ አንቀጾች ተጥሰዋል

1.    የሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 15 የሕይወት መብት

‹‹ማንኛውም ሰውበሕይወት የመኖር መብት አለው፡፡ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነበስተቀር ሕይወቱን አያጣም፡፡›› ቢልም ከሰላማዊ ሰልፉ ጋር በተያያዘ ከ8 ዓመት ልጅ አንስቶ እስከ የ80 ዓመት አዛውንት ድረስ ሕይወት እየተቀጠፈ ነው፤ እስከዛሬ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በሶስተኛ ወገን ማረጋገጥ ባይቻልም ጉዳዬን  በቅርበት የሚከታሉ ሰዎች እንደዘግቡት ወደ መቶ እየተጠጋ ይገኛል፡፡

2.   የሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 15 የአካል ደኅንነት መብት

‹‹ማንኛውም ሰውበአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስየመጠበቅ መብት አለው፡፡ ›› አሁንም ከሰላማዊ ሰልፉ ጋር በተያያዘ በጥይት የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ቁጥራቸው በርካታ ነው፡፡ ድብደባ እና አላግባብ አንግልት የደረሰባቸውንም ቤት ይቁጠራቸው፡፡

3.   አንቀጽ 24.1 የክብርና የመልካም ስም መብት

‹‹ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ክብሩና መልካም ስሙ የመከበር መብት አለው፡፡ ›› እየሆነ ያለው ዜጎችን አጋንንት እያሉ መጥራት፣ ጥፋተኛ ተብለው በሕግ ያልተፈረደባቸውን አሸባሪ እያሉ ክብራቸውን በሚዲያ መግፈፍ ነው፡፡

4.   አንቀጽ 30.1 የመሰብሰብ፤ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት

‹‹ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና፣ አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ ከቤት ውጭ የሚደረጉ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሰልፎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ለማድረግ ወይም በመካሔድ ላይ ያለ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ሰላምን፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱ ለማስጠበቅ አግባብ ያላቸው ሥርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉ፡፡ ››  ቢልም መንግስት ይህን የህገ መንግሰቱን አንቀጽ በመጣስ ብዙ ሰብዓዊ ጉዳቶችን አድርሷል፡፡

ዜጎች ለመረጃ ቅርብ በሆኑበት በዚህ ጊዜ መንግስት እያደረጋቸው ያሉትን ተግባራት መካድ፣ እንዲሁም እንደሌሉ አደርጎ ለማስተባበል መሞከር ብዙ ኃላፊነት የሚጠበቅበት መንግስት የሚያሰገምትና ትዝብት ላይ የሚጥል ነው፡፡ ይህ የመንግስት ግዴለሽነት ብዙኃን ዜጎችን እየገፋ ከመስመር እያስወጣ ነው፡፡ ሰላማዊውን የሕዝብ እንቅስቃሴ ወደ አመጽ እና ወደአልተፈለገ ዕልቂት ከመግፋት ይልቅ የተቀናጀ የጋር ማስተር ፕላኑን  መሰረዝ፣ በዚህ ሒደት ጥፋት የፈጸሙ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትን ለፍርድ ማቅረብ፣ የግል ተበዳዮችን  መካስና ሌሎች አስፈላጊ የመፍትሔ እርምጃዎችን ሁሉ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡  ሁልጊዜም እንደምንለው በሰላማዊ መንገድ የመብት ጥያቄ ማቅረብ ወንጀል አይደለም፡፡  መንግሰት በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን ከሚጠይቁ ዜጎች ጋር እልህ አይጋባ ፣ ህገ መንግስታዊ መብቶቻቸው ይከበሩ ፣ የመብት ጥሰት ድብደባ እና ግድያው ይቁም፡፡  ሕገ-መንግስታዊነት የታሰርንለት፣ ከሀገር የተሰደድንለት፣ ብዙ ዋጋ የከፈልንበትና አሁንም እየከፈልንበት ያለ ዐሳብ ነውና  በሀገሪቱ ህጋዊነት እንዲሰፍን ህይወታቸውን እስከመስጠት ድረስ ዋጋ ለከፈሉ ዜጎች ክብር እንሰጣለን፡፡ ለሕገ መንግስታዊ ስርዓት መስፈን ዜጎች የከፈሉት ዋጋ እጅግ ብዙ እና ከበቂ በላይ ነውና ተጨማሪ ሰብዓዊ ዋጋ መክፈል ሳያፈልገን ሕገ መንግስቱ እንዲከበር አንጠይቃለን፡፡


ሕገ-መንግስቱ ይከበር!  

በእነዘላለም ወርቅአገኘሁ መዝግብ ተከሰው የነበሩት 4 የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አብርሃም ሰለሞን ነፃ ቢባሉም በይግባኝ ታግደው ፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት እየተመላለሱ እንደሆነ ይታወቃል። አሁንም ለቃል ክርክር ሕዳር 29, 2008 ተቀጥረዋል። ቀሪዎቹ፣ ማለትም ዘላለም ወ/አገኘሁ፣ ዮናታን ወልዴ፣ ባሕሩ ደጉ፣ ሰለሞን እና ተስፋዬ ከሕዳር 13–16, 2008 ድረስ ከፊል መከላከያዎቻቸውን ያስደመጡ ሲሆን ቀሪውን ዛሬ (ሕዳር 24, 2008) ያስደምጣሉ።
እነዘላለም ተከላከሉ የተባሉት በፀረ–ሽብር ሕጉ አንቀፅ 7/1 መሠረት የግንቦት 7 አባል በመሆን ሠርታችኋል በሚል ነው። በ5ቱም (ዘላለም፣ ዮናታን፣ ባሕሩ፣ ሰለሞን እና ነፃ ተብሎ በይግባኝ የተያዘው አብርሃም ሰለሞን) ላይ የመሰከሩት 3ተኛ የዐ/ሕግ ምስክር አቶ እዮብ ሲሆኑ፣ የምስክርነታቸው ጭብጥ በጥቅሉ ‘ዘላለም ወ/አገኘሁ መልምሏቸው ለግንቦት 7 ወታደርነት 3 ሰዎችን መልምለው ከወሰዱ በኋላ ጎንደር ላይ ባለመስማማታቸው እንደተመለሱ። ከ3ቱ አንዱ እዚሁ መዝገብ ላይ 8ኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ ሰለሞን መሆናቸውን። አቶ ዘላለም በባሕሩ እና ዮናታን ሥር የተደራጀ ቡድን መኖሩን እንደነገሯቸው’ የሚያስረዳ ነው።
አቶ ሰለሞን፣ ዮናታን እና ዘላለም ከፊል ምስክሮቻቸውን ያስደመጡ ሲሆን አቶ ተስፋዬ (10ኛ ተከሳሽ) ጉዳያቸው ከነዘላለም የተለየ ቢሆንም አንድ መዝገብ በመሆናቸው ምስክሮቻቸውን አስደምጠው ጨርሰዋል።
አቶ ሰለሞን ሁለት ምስክሮችን አቅርበው እዮብ “የተሻለ ሥራ አገናኝሃለሁ በሚል አቶ ሰለሞንን ወደጎንደር ከወሰዷቸው በኋላ ጎንደር ሲደርሱ ለግንቦት ሰባት ወታደርነት እንደሆነ ሲነግሯቸው” መመለሳቸውን አስመስክረዋል። ራሰቸውም በሰጡት ቃል እዮብ እየወሰዳቸው እያለ መቶ አለቃ እያለ ከሚጠራው ሰው ጋር በስልክ ይነጋገር እንደነበርና የዘላለምን ስም ጨርሶ እንዳልሰሙ ተናግረዋል። 
ዮናታንም በበኩሉ እስካሁን 4 ምስክሮችን አስደምጧል። የመጀመሪያው አብሮ አደግ ጓደኛው ሲሆን፣ ዮናታን ውጭ አገር ለሚደረግ የሰብኣዊ መብትና ሚዲያ ነክ ሥልጠና ሊሄድ መሆኑን ነግሮት እርሱም ከፈለገ ሲቪውን እንዲሰጠው ጠይቆት መስማማቱን፣ ነገር ግን ሥልጠናው ባልታወቀ ምክንያት መስተጓጎሉን ለችሎቱ አስረድቷል። በሁለተኝነት የቀረበው ምስክር አቶ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ ስለእነዚህ ዓይነት ሥልጠናዎች ሠላማዊነት እና ሰጪዎቹም ዓለምዐቀፍ ዕውቅና የተቸራቸው ስለመሆኑ የባለሙያ ምስክርነቱን ሰጥቷል። በሦስተኝነት የቀረበው ምስክር አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ እዮብ ማዕከላዊ እያለ አናግሮት እንደነበር፣ ዮናታንን ፍፁም እንደማያውቀው፣ በኋላ ግን በድብደባ ብዛት እግሩ ተጎድቶ ማንከስ ሲጀምር እና ሥራ የሌላት ሚስቱና ልጁ ዕጣ ሲያሳስበው ተስፋ በመቁረጥ ሌሎቹ ላይ መስክሮ ሊፈታ መሆኑን እንደነገረው ለችሎቱ ነግሯል። በአራተኝነት ዘላለም ወ/አገኘሁ ቀርቦ እዮብ “ዘላለም በዮናታን ሥር ቡድን አለ ብሎ ነግሮኛል ያለው ሐሰት ነው” ብሏል።
ዘላለም ወርቅአገኘሁም ለራሱ እስካሁን 4 መከላከያ ምስክሮችን ያስደመጠ ሲሆን በቀዳሚነት የቀረበው ጥበቡ የተባለው አብሮ አደግ ጓደኛው ነበር። ጥበቡ፣ በክሱ ላይ የግንቦት 7 አመራር ተብሎ የተጠቀሰው ተድላ ደስታ አብሮ አደግ ጓደኛቸው እንደሆነና፣ እንግሊዝ አገር ከሄደ በኋላም ተማሩ እኔ ገንዘብ እልክላችኋለሁ ብሎ ገንዘብ ለሁለቱም እንደላከላቸውና ዘላለም ከመያዙ በፊት ማስተርሱን መማር እንደጀመረ ተናግሯል። የዘላለም እናት ወ/ሮ የኔእናትም በበኩላቸው ተድላ ደስታን ከልጅነቱ ጀምሮ የሚያውቁት የልጃቸው ጓደኛ በመሆኑ መሆኑን ጠቅሰው በ2005 ብር ልኮለት እሳቸው ጨምረውበት ዘላለም ትምህርት መጀመሩን ለችሎቱ ገልጸዋል። ቀሪዎቹ ሁለት ምስክሮች ሙዘሚል እና አዲሱ የተባሉ በክሱ ላይ በዘላለም ለግንቦት 7 የተመለመሉ እንደሆኑ የተገለጹ ወጣቶች ናቸው። ሁለቱም ወጣቶች በየተራ ከዘላለም ጋር ያላቸው ዕውቂያ በሰፈር ልጅነት እንደሆነና ምንም ዓይነት የሚያውቁት ቡድን እንደሌለ እና በቁም ነገር ቁጭ ብለው ያወሩበት አጀንዳም እንደሌለ ተናግረዋል።
ዘላለምና ዮናታን በሰጡት መከላከያ ቃላቸውም ላይ ወደውጪ ለሰብኣዊ መብትና ሚዲያ ነክ ሥልጠናዎች ለመሄድ ክሱ ላይ የግንቦት ሰባት አመራር ተብሎ የተጠቀሰው እና እነርሱ በጋዜጠኝነቱ እንደሚያውቁት የተናገሩት አርጋው አሽኔ ጋር ከመነጋገራቸው በቀር ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል። ዘላለም፣ ሌሎችን ላለማስፈራራት ሲል ዝርዝሩን እንደማይናገር ነገር ግን በሐምሌ ወር፣ በቀዝቃዛ እና ዘጠና ሳንቲሜትር በሆነች ጨለማ ክፍል ውስጥ 41 ቀን መቆየቱንና ጠባሳ የማይተው ነገር ግን የነርቭን ስርዓት በሚያዛባ ምት እየተመታ መመርመሩን ተናግሯል።
በጥቅሉ ዐ/ሕግ ያቀረበው ክስ እና ማስረጃ ጠቅላላ ምስል፣ «ከውጭ አገር ገንዘብ በሚላክለት ዘላለም አማካኝነት የተመለመለው እዮብ ለግንቦት ሰባት ወታደሮችን እየላከ፣ ዘላለምም በሠላማዊ ትግል ሥም ቡድኖችን እያዋቀረ እንደሆነ» ለማሳየት ሲሞክር፣ እነዘላለምም በመከላከያቸው «ከውጭ አገር የተላከው ገንዘብ የዘላለም አብሮ አደግ ጓደኛ ለዘላለም የግል ፍላጎት የላከው መሆኑን፣ እዮብ ለግንቦት ሰባት ወታደርነት [እያታለለ] በወሰዳቸው ሰዎች ውስጥ ዘላለም እጁ እንደሌለበት፣ ቡድን እየተባለ የሚጠራ ነገር እንደሌለ እና ዜጎች ሁሉ ቢወስዱት የሚመከር ሥልጠና ለመውሰድ መጻጻፋቸውን በዚያ መንገድ እንደተተረጎመባቸው» የሚያስረዳ የመከላከያ ምስል ለመፍጠር እየሞከሩ ነው።

በፍቃዱ ዘ ኃይሉ

‹‹…ይወስዳል መንገድ፣ ያመጣል መንገድ 

አንድ የሚጠላ፣ አንድ የሚወደድ…››

ሕይወት መንገድ ነች፡፡ በየመንገዱ ከሰው ታወዳጀናለች፤ ከተወዳጀናቸው ታለያየናለች፡፡ እኔም በሕይወቴ ጎዳና በገጠመኝ የእስር ሕይወቴ ካፈራኋቸው ወዳጆቼ ዘላለም ወርቅአገኘሁ አንዱ ነው፡፡ ሁሌ ‹‹ለምን ሳንታሰር አልተዋወቅንም?›› እንባባላለን፡፡ ቀድሞ መተዋወቁ የተለየ ነገር ይፈጥር ይመስል፡፡

ዘላለም ወርቅአገኘሁ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለው ሐምሌ 1፣ 2006 ነበር፡፡ ልክ ከእኛ ውስጥ (ከአቤል በቀር) ወንዶቹ ሁሉ ‹‹ሳይቤሪያ›› ከሚባለው ቀዝቃዛ የምድር ክፍል ወጥተን ‹‹ሸራተን›› ወደሚባለው አንፃራዊ ምቹ ክፍል የተዘዋወርን ዕለት ማለት ነው፡፡ እኛ ወደ‹‹ሸራተን›› የተዛወርነው ለካስ እሱን ጨምሮ ለነሀብታሙ አያሌው፣ አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋ፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ እንዲሁም ለነባሕሩ፣ ዮናታን፣ አብርሃም እና ሌሎችም ቦታ መልቀቅ ስላለብን ነበር፡፡ አንድም እንዳንቀላቀል፣ አንድም ምሥጢር እንዳንለዋወጥ መሆኑ ነው፡፡ ዘላለም ወርቅአገኘሁ የገባው፣ የኛው ዘላለም ክብረት ወደነበረበት 5 ቁጥር ነበር፡፡ እዚያ ግን ብዙ አልቆየም፡፡ ከዚያ ክፍል ወጥቶ ጭራሹኑ መብራት ወደሌለው እና ከአንድ ሰው በላይ በማያሳድረው ጭለማ ክፍል (ስምንት ቁጥር ) ውስጥ ገብቷል፡፡ ስምንት ቁጥር ውስጥ 41 ቀናት ቆይቷል፡፡

በጨለማ ቤት 24 ሰዓት፣ ለብቻ መቆየት ምን ያክል ከባድ እንደሆነ መገመት ይከብዳል፡፡ ለተወሰኑ ቀናት ከአብርሃ ደስታ ጋር ተጎራብተዋል፡፡ ከዚያ በፊት ባይተዋወቁም (ዘላለም በሥም ያውቀው ነበር) ግድግዳ እየደበደቡ ይነጋገሩና ማፅናኛ ቃላትም ይለዋወጡ እንደነበር ሁለቱም ነግረውኛል፡፡ ዘላለም ከታሰረ ዓመት ሲሞላው ‹‹በእስር ቆይታዬ የተረዳሁት የ24 ሰዓትን ርዝመት፣ የዓመትን እጥረት ነው›› አለኝ፡፡ ‹እንዴት?› አልኩት፤ ‹‹ስምንት ቁጥር እያለሁ 24 ሰዓት ማለት ፈፅሞ የማያልቅ ረዥም የጊዜ ዓይነት ነው፡፡ ዓመት ደግሞ በእስር ዓይን መለስ ብለህ ስትመለከተው በጣም አጭር ነው፡፡ አሁን ሳስበው የገባኝ የሁለቱ አያዎ (paradox) ነው›› አለኝ፡፡ እውነቱን ነው፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ‹‹በእስር ቤት አንዱ ቀን ከሌላኛው ቀን፣ አንዱ ሳምንት ከቀጣዩ ሳምንት፣ ወሩ ከሚቀጥለው ወር ጋር አንድ ዓይነት ናቸው›› ብለው ጽፈዋል፡፡ እውነት ነው፤ ስለዚህ መለስ ብለው ሲመለከቱት ዓመቱ በጣም አጭር ይመስላል፡፡ ዘላለም የተረዳው ያንኑ ነው፤ የጨለማ ቤቷን ተሞክሮ የገለፀልኝ ደግሞ እኔ ልገልፀው ስቸገር የነበረውን ነው፡፡

ዘላለም ወርቅአገኘሁ ካየኋቸው ክሶች ሁሉ የተንዛዛ ክስ ነው የተመሠረተበት፡፡ ክሱ ብቻውን ዘጠኝ ገጽ ነው፡፡ ፌስቡክ ላይ ያደረገው ቻት፤ ቤቱ የተገኙ የትምህርት እና ሌሎችም ጽሑፎች በሙሉ ክሱ ውስጥ ተተንትነዋል፡፡ ማስረጃ ተብለው ተያይዘዋል፡፡ ከተያያዙበት የሰነድ ማስረጃዎች መካከል ጥቂቶቹን ለትዝብታችሁ ያክል ልንገራችሁ፡፡

አንድ ገጽ ሙሉ በእስኪርቢቶ የተጻፈ ጽሑፍ ነው፤ እንዲህ ይነበባል፣

“If Blogging is a Crime,

then I am a Blogger too.

Free Zone9 Bloggers”

እንዳየሁት በጣም ነበር የደነገጥኩት፡፡ ብዙ ሰዎች በእጃቸው ‹‹መጦመር ወንጀል ከሆነ እኔም ጦማሪ ነኝ፤ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ይፈቱ›› የሚል ጽሑፍ ይዘው ፎቶ እየተነሱ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየለጠፉ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን የሽብር ክስ ማስረጃ ሰነድ ሆኖ ይመጣል ብዬ ግን ጠርጥሬ አላውቅም፡፡ ኢሕአዴግ ብዙ ጊዜ ያስገርመኛል (surprise ያደርገኛል)፡፡ በዚህም አስገረመኝ ከማለት ውጪ ቋንቋ የለኝም፡፡

ሌላም በጣም አስገራሚ ሰነድ ‹‹የሠራኸውን ወንጀል›› ያስረዳል ተብሎ ቀርቦበታል፡፡ ሰነዱ አንዳንዶች እንደሚሉት ‹‹ለኢሕአዴግ ብሉይ ኪዳኑ ነው››፡፡ ሰነዱ “On the Questions of Nationalities in Ethiopia” ይላል፡፡ የብሔር ጥያቄን በወረቀት ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ አቀንቅኗል የሚባልለት የዋለልኝ መኮንን መጣጥፍ ነው፡፡ ታዲያ የዚህ መጣጥፍ ገጽ ዘላለም ወርቅአገኘሁ ክስ ላይ ማስረጃ ሰነድ ተብሎ ተያይዟል፡፡ ይህንን ሰነድ ምን ብለው ያስተባብሉታል?

እነዚህም ብቻ አይደሉም፡፡ ዘላለም በታሰረበት ወቅት በፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን ማስተርሱን በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ እያጠና ነበር፡፡ ታዲያ በወቅቱ ያገላብጣቸው የነበሩ ጥናቶችም ማስረጃ ተብለው ከክሱ ጋር ተያይዘው ቀርበውበታል፡፡ ለምሳሌ የሚከቱሉት ርዕሶች ያሏቸው ጽሑፎች አሉ፤ “Academic freedom” (የትምህርት/ማስተማር ነጻነት)፣ “University for Society” (ዩንቨርስቲ ለማኅበረሰብ)፣ እና “Social Service” (ማኅበራዊ አገልግሎት)፡፡ እንግዲህ እነዚህ በይፋ የሚታወቁ ትምህርት ነክ የሆኑ አጀንዳዎችን የሚታወቁ ጥናቶችን ማስረጃ ብሎ የሽብር ክስ ላይ ማያያዝ አንድም የከሳሾቹን አላዋቂነት ያሳብቃል፡፡ ያውቃሉ ቢባል እንኳ እያወቁ አጥፊነታቸውን ይናገራል፡፡ በተጨማሪም፣ የኔልሰን ማንዴላ ‘Long Walk To Freedom’ የተሰኘውና ከዋናው እትም አጥሮ የተጻፈው መጽሐፍ ገጽ 25 ላይ የሰፈረው፣ ኔልሰን ማንዴላ ‹የሕንድ ብሔራዊ ኮንግረስ›፣ ፓርቲያቸው ‹የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ› ለሚያደርገው ትግል አርኣያ እንደሆነው የሚያትቱበት ጽሑፋቸው ዘላለም ላይ ማስረጃ ተብሎ ተጠቅሶበታል፡፡

ዘላለም በዐቃቤ ሕግ ምስክር ሳይቀር የተነገረበት አንዱ ‹‹በሽብር ተፈርዶበት ውጪ አገር ከሚኖር የግንቦት 7 አመራር ገንዘብ ተልኮለታል›› የሚለው አንዱ ሲሆን፣ ይህንኑ ያስረዳል ተብሎ የተያያዘው ሰነድ ግን የሚያስረዳው ሌላ ነገር ነው፡፡ ሰነዱ የሚያስረዳው ተድላ ደስታ የተባለ ሰው ሦስት መቶ ዶላር እንደላከለት ነው፡፡ ተድላ ደስታ የ‹ደ ብርሃን› ጦማር ጸሐፊ ሲሆን፣ የግንቦት 7 አመራር ቀርቶ አባል ስለመሆኑ ምንም መረጃ ያልቀረበ ከመሆኑም በላይ ‹‹የተፈረደበት›› የሚለው ገሀድ ውሸት ነው፡፡

እንዲህ እና መሰል ክሶችን ታቅፎ የቆየው ዘላለም ነሐሴ 14/2007 ቀድሞ የተከፈተበት አንቀጽ 4 (ሲያንስ 15 ዓመት፣ ሲበዛ ሞት የሚያስቀጣ) ተቀይሮለት በአባልነት ብቻ፣ ማለትም 7/1 (ቢበዛ 10 ዓመት የሚያስቀጣ) አንቀጽ ተደርጎለት እንዲከላከል ተወስኖበታል፡፡ የዛኑ ዕለት በእሱ መዝገብ የተከሰሱት አራቱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አብርሃም ሰለሞንም ‹‹ነጻ›› ተብለው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ በማለቱና የፍቺ እግድም ከጠቅላይ ፍ/ቤት በማሳዘዙ እስከዛሬ አልተፈቱም፡፡ ሌሎቹ የዘላለም ጓደኞች ባሕሩ እና ዮናታንም ቀድሞ በተከፈተባቸው አንቀጽ 7/1 እንዲከላከሉ ተበይኖባቸዋል፡፡ የዘላለም ጓደኞች የተያዙት ከዘላለም ጋር በመሆን ወደውጭ አገር በመጓዝ የኢንተርኔት ደኅንነት ሥልጠና ሊወስዱ በተለዋወጡት ኢሜይል ሳቢያ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ሥልጠናውን እያመቻቸላቸው የነበረው በስደት ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ አርጋው አሽኔ ሲሆን፣ አርጋው በክሱ መዝገብ ላይ ‹‹የግንቦት 7 አመራር›› ተብሎ ነው የተጠቀሰው፡፡ አርጋው አሽኔም እንደ ተድላ ደስታ ሁሉ እንኳን የግንቦት 7 አመራር ሊሆን አባል መሆኑንም የሚያስረዳ ማስረጃ የለም፡፡ ዛሬ ዘላለምና አራቱ ፖለቲከኞች በወኅኒ 500ኛ ቀናቸውን ያከብራሉ፡፡ ያከብራሉ ይባላል ወይ ብላችሁ እንዳትጠይቁኝ! ሌሎቹም በዘላለም ሥም በሚጠራው መዝገብ ላይ ያሉ የሕሊና እስረኞች ከሰሞኑ 500 ቀን ይሞላቸዋል፡፡

እኛ ስንያዝ የተረፉ (እና የተሰደዱ) ጓደኞቻችን ሰው ሊረዳላቸው ያልገባቸው ፈተና ውስጥ እንደነበሩ ሲያደርጉ ከነበሩት እና ሲልኩብን ከነበሩ መልዕክቶች ሰምተናል፣ ተረድተናል፡፡ ፈረንጆች ይህ ዓይነቱን ጉዳይ ‘survival’s guilt’ (‹የተራፊዎች የጥፋተኝነት ስሜት› እንበለው?) ይሉታል አሉ፡፡ ከዚያ ደግሞ ድንገት ክሳቸው ተቋርጦ የወጡት አባሪዎቻችን እኛን የከዱን ዓይነት ስሜት ይንፀባረቅባቸው ነበር፤ ይኸው ‹የተራፊዎች የጥፋተኝነት ስሜት› ሳይሆን አይቀርም፡፡ ቀሪዎቹም ተራችን ደረሰና ተንጠባጥበን ስንወጣ እኔ የጓደኞቼን ሕመም በከፊልም ቢሆን የተረዳሁት የመሰለኝ ዘላለምን ተሰናብቼ ስወጣ ነው፡፡

ዘላለም እስሬን ካቀለሉልኝ ሰዎች ውስጥ ዋነኛው ነው፡፡ ውይይታችን፣ ንትርካችን ሁሉ የማይዘነጋ ነበር፡፡ ማታ፣ ማታ መታጠቢያ ክፍሉ ውስጥ ካለች ጠባብ ኮሊደር ውስጥ የባጥ የቆጡን እየቀባጠርን እስከ ሌሊቱ ሰባትና ስምንት ሰዓት የምንቆይበት ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ አምስቱ አባሪዎቼ ድንገት የወጡ ጊዜ የነበረውን የሐሳብ ውዥንብር እና የእንቅልፍ መዋዠቅ ከእሱ ጋር በማውራት ነበር ሰውነቴን ያላመድኩት፡፡ በእስር ቤት ቋንቋ ገበታ በጋራ የሚቋደሱ ሰዎች፣ መቅዱስ ነበር የሚባሉት፡፡ ዘላለም መቅዱሴ ብቻ አልነበረም፡፡ ወኅኒ የሰጠኝ ጓደኛዬም ነው፡፡ አሁን እቤቴ ቁጭ ብዬ አስበዋለሁ፡፡ ሳያመሽ መተኛት አይችልበትም፤ በጣም ያመሻል፡፡ ለቆጠራ 12፡30 በራችን ሲንኳኳ ‹ሀንጎቨር› እንዳለበት ሰው ዓይኑ ቅልትልት ብሎ፣ ፎጣ ደርቦ ሲወጣ ይታወሰኛል፡፡ ኳስ ጨዋታ ሲኖር (እኔ ባልወድም) ከጎረምሳው ሁሉ ጋር ሲሟገት ይታየኛል፡፡ ሰው መንከባከብ ይችልበታል፤ ሲንከባከበኝ ትዝ ይለኛል ልበል? አዎ፣ እንደሚንከባከበኝ ስለማውቅ እኔም እቀብጥ ነበር፤ እሱም ሲንከባከበኝ አስገራሚ ነው፡፡

ዘላለም ወርቅአገኘሁ እና ጓደኞቹ (5 ሆነው) የመጪው ሰኞ፣ ሕዳር 13፣ 2008 ራሳቸውን ለመከላከል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡ እኔም እንደተመልካች ላያቸው እሄዳለሁ፡፡ አልጨብጣቸውም፡፡ እጄን የማውለበልብላቸው ከሆነ እንኳን ፈራ ተባ እያልኩ ነው፡፡ እኔ ከትልቁ እስር ቤት ሆኜ፣ እነርሱ ደግሞ ከጠቧቧ ሁነው ያዩኛል፡፡ ‹ሁላችንም ነጻ ካልወጣን፣ አንዳችንም ነጻ ወጣን ማለት አይቻልምና!›

መልካም ዕድል ከመመኘት በላይ ምን አቅም አለኝ፡፡ መልካም ዕድል፣ የክፉ ቀን ጓዴ! መልካም ዕድል!

Zelalem Workagenegu drawing by Melody Sundberg


 በበፍቃዱ ዘ ኃይሉ
የሰለሞን ስዩምን ‹‹የኦሮሞ ጉዳይ እና የኢትዮጵያ ብያኔ›› የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ (ሁለተኛ እትም) አነበብኩት፡፡ በጥቅሉ ወድጄዋለሁ፡፡ ጥቂት ቅሬታዎች ግን አሉኝ፡፡ ሰለሞን በአማርኛ የኦሮሞ ጉዳይን ከጻፉ (እና እኔ ካነበብኩላቸው) ጸሐፍት ሁሉ በተሻለ ልለው በምደፍረው ደረጃ ምሁራዊ ታማኝነት (intellectual honesty) ተስተውሎበታል፡፡ አልፎ፣ አልፎ ግን ምሁራዊ ታማኝነቱ ከሚጎድላቸው ምሁራን ማጣቀሱ ሚዛን አስቶ ያንገዳገደው ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ የታቦር ዋሚ ‹‹የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች››ን ማንሳት ይቻላል፡፡ ታቦር ትልቅ ርዕስ ይዞ ትንንሽ ክርክር የተከራከረባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ አንዱ የቋንቋ ተናጋሪዎች ብዛትን በተመለከተ የሚሰጠው ምንጭ አልባ ድምዳሜ ነው፡፡ ሰለሞን ያንን በኦሮሞ ጉዳይ ላይ ያንፀባርቀዋል፡፡ ‹‹. . . መረጃዎች አሉ›› በሚል ብቻ፡፡ በተጨማሪም አጠራጣሪ (አከራካሪ) ሁኔታዎች ላይ እምነቱን ለዘውግ ብሄርተኞቹ ትርክት ወደመስጠቱ አዘንብሎብኛል፡፡

ይህ በእንዲህ አያለ፣ መጽሐፉን አንብቤ ስጨርስ የጎደለ ነገር ያለ-ያለ ተሰማኝ፡፡ ታዲያ የጎደለ የመሰለኝን ምዕራፍ ለምን አልጽፈውም አልኩና ተነሳሁ፡፡ ጽሑፉን የምጽፈው የሰለሞንን ሐሳብ እየተዋስኩ፣ የኔን እየጨመርኩበት ነው፡፡ እሱም ይጭንብኛል፤ እኔም እጭንበታለሁ፡፡ ስለዚህ ከታች የማሰፍረው ጽሑፍ ላይ ‹እኔ›› እኔ አይደለሁም፡፡ ሰለሞን ስዩም ነው፡፡ እኔ ሁን እንዳልኩት፡፡

የተጣመመው የብሔርተኝነት ቅርንጫፍ
በኢትዮጵያ ቀኝ ዘመሞች አና ግራ ዘመሞች ሁሌም እርስ በርስ እንደተዋቀሱ ነው፡፡ እነዚህ ‹‹ትምክህተኛ ብሔርተኞች ፍፁም አሀዳዊ አገር ለመፍጠር ሊፍጨረጨሩ አገሪቱን ይበታትኗታል፡፡ ሲሉ፣ እነዚያ ‹‹ጠባብ ብሔርተኞች ሁሉንም ነገር በዘውግ ዓይን እያዩ አገሪቱን ሊበጣጥሷት ነው›› ይላሉ፡፡ መጽሐፉ በኦሮሞ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ስለሆነም አሁን ማተኮር የምፈልገው የዘውግ ብሔርተኞች የሚከሰሱባቸው ችግሮች እና መፍትሔዎች ላይ ነው፡፡

አማራ-ሰግነት (Amhara Phobia)
ኦሮሞ ብሔርተኝነት ከገጠሙት ፈተናዎች መካከል አንዱ የኦ&#4654

በዛሬው ዕለት የልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በነሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ ፩ኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ፪ተኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ሃይሉ ፫ተኛ ተከሳሽ ናትናኤል ፈለቀ ፭ተኛ ተከሳሽ አጥናፍ ብርሃኔ እና ፯ተኛ ተከሳሽ አቤል ዋበላ ተጠርጥረው ከነበረበት የሽብርተኝነትና የኅብረተሰቡን ደህንነት አደጋ ላይ የመጣል ክስ ነጻ መውጣታቸውን በበጎ መልኩ የምንቀበለው ቢሆንም 
  1. ፪ተኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ሃይሉ በሃይል ተገዶ ማዕከላዊ ምርመራ ውስጥ በማሰቃየት ስር የሰጠው ቃል ተቆጥሮ አመጽን በማነሳሳት ወንጀል በወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 257 መሰረት አንዲከላከል መባሉን አጥብቀን እንቃወማለን ፡፡ 
  2. ሃሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው ከአንድ አመት ከአምስት ወር በላይ በእስር የቆዬት የዞን9 ጦማርያን የመፈቻ ወረቀት ከችሎቱ መጠናቀቅ በኋላ በአስቸኳይ በፍርድ ቤቱ አማካኝነት ተጽፎ ለማረሚያ ቤቱ ተወካይ ቢሰጥም ማረሚያ ቤቱ እስከ አርብ የስራ ሰዓት መጠናቀቂያ ድረስ መፈቻው አልደረሰኝም በሚል ሰበብ ሶስቱን ጦማርያን በእስር ማቆየቱን አስጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ 

ይህ ተግባር ከዚህ በፊት እንደታየው ሁሉ አቃቤ ህግ ለይግባኝ ጊዜ አንዲገዛ ከማረሚያ ቤቱ የሚደረግለት የጓሮ ትብብር አንዳይሆን እጅግ ከፍተኛ ስጋት አለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተለመደው የፍርድ ቤቶችን ስልጣን ዝቅ አድጎ የማየት እና የማረሚያ ቤቶች የእጅ አዙር ፍርድ ሰጪነት ማሳያም ነው ፡፡ በመሆኑም ከዚህ በፊት አንደታየው በአደባባይ በሕግ አግባብ የተሰጠን ነጻነት በጓሮ ከሕግ ውጪ ሊነጠቅ የሚችልበት ከፍተኛ ስጋት አሁንም የዞን9 ጦማርያን ፊት ተጋርጧል ፡፡
539 ቀናት ያለአግባብ እስር መቆየታችን ሳያንስ በራሱ መቆም የማይችል እና ምንም ማስረጃ ያልቀረበበትን ክስ አቃቤ ሕግ በጓሮ ከማረሚያ ቤት ጋር በመመሳጠር የመንፈግ ሌላ ተጨማሪ ግፍ አንዳይሰራብን አጥብቀን እንጠይቃለን ፡፡

ስለሚያገባን አንጦምራን!
ዞን9