ስምዐ ጽድቅ ታተመች
(ደጀ ሰላም፤ ጁን 7/2011)፦ ከሥርዓት ውጪ በተደረገ የደብዳቤ እና የስልክ ልውውጥ ሕትመቷ ተስተጓጉሎ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ጋዜጣ ስምዐ ጽድቅ በዛሬው ዕለት በሌላ ማተሚያ ቤት ታትማ መሠራጨት ጀምራለች። ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ በመታተም በሕትመት ብዛት እና ረዥም ዓመታት በማሳለፍ ቀዳሚ የሆነችው ይህች ጋዜጣ ለብዙ ጊዜያት ያለመታተም እንቅፋት ቢገጥማትም እንደ አሁኑ ከፍ ያለ ፈተና እንዳልደረሰባት ምንጮች አስረድተዋል። ብዙዎች ምዕመናን “መምህራችን” የሚሏት ጋዜጣዋ መቋረጧ በደጀ ሰላም ከተዘገበበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ቁጣ መቀስቀሱን የተረዳን ሲሆን ቤተ ክህነቱ አሁን በያዘው መልኩ የሚሔድ ከሆነ ምዕመናን የራሳቸውን መፍትሔ ወደ መፈለግ እና በደብረ አሚን አቡነ ተ/ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን እንደታየው ዓይነት “ጉልበት ወደ መጠቀም” የመሰለ አላስፈላጊ መፍትሔ እንዳይዘዋወሩ አስግቷል።