ቅዱስ ሲኖዶስ ስለምን ጉዳይ ይነጋገራል?
(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 22/2010፤ ጥቅምት 12/2003 ዓ.ም):- ዛሬ የሚጀመረው የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ በብዙ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ መልካም ውሳኔዎች ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል። ስለጉዳዩ የሚያጠኑ ደጀ ሰላማውያን እንደሚናገሩት ከሆነ፦
- በአምናው ጉባዔ ላይ ወሳኝ መነጋገሪያ የነበረው የ“ሕገ ቤተ ክርስቲያን” ጉዳይ፤
- ስለ “ቀኖና ቤተ ክርስቲያን” ማለትም ከቦሌው ሐውልት ጀምሮ በየጊዜ ስለሚጣሱ ቀኖናዎች ጉዳይ፤
- ከዚህ በፊት በቅ/ሲኖዶሱ ተሰይሞ ፓትርያርኩ ከሥራ ስላገዱት “የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ’ በድጋሚ ሥራ መጀመር ጉዳይ፤
- በቅርቡ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተለያዩ እርከኖች ላይ ስለተሾሙት ባለ ሥልጣኖች ጉዳይ፤
- በፓትርያርኩ አቅራቢነት ይነሣል የሚባለው “የአዳዲስ ጳጳሳት ሹመት” ጉዳይ፤
- አሁንም በቅ/ፓትርያርኩ ለውይይት ይቀርባል የሚባለው ለፓትርያርኩ “እንደራሴ የመሾም” ጉዳይ፤
እነዚህ እና እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮች ለውይይት ይቀርባሉ ተብሎ ይገመታል። ደጀ ሰላም ስለነዚህ አጀንዳዎች ማንነትና ምንነት የምታጠናቅረውን ዘገባ እንደደረሰልን ለማቅረብ እንሞክራለን። ተከታተሉን።