ክቡር ሚኒስትሩ ከሹፌራቸው ሲነታረኩ ከትራፊክ ፖሊሱ ሲሞዳሞዱ ዋሉ::
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
– ምን አዲስ ነገር አለ?
– ሪፖርቱ ነዋ፡፡
– የትኛው ሪፖርት?
– ሰሞኑን የወጣው፡፡
– በምን ላይ?
– በሕገወጥ ዝውውር፡፡
– የሕገወጥ ዶላሩን ነው?
– እ…
– ለእነዚህ ኒዮሊብራሎች ግን የት እንሂድላቸው?
– ምን እያሉ ነው?
– ዶላር ከአገር ሸሸ ነው የሚሉት?
– ኧረ እኔ ሕገወጥ የሰው ዝውውሩን ነው የምልዎት፡፡
– እእእ…
– ምነው ደነገጡ?
– የምን ሕገወጥ ዝውውር ነው?
– በአፍሪካ ቀንድ የሚደረገው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ነዋ፡፡
– ሰዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተባለ እንዴ?
– በዚህ ወንጀል ላይ ባለሥልጣናትም ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
– እኛ?
– አይ የለም የኤርትራ ባለሥልጣናትን ነው፤ ምነው ደነገጡ?
– እኔን ያልከኝ መስሎኝ ነዋ?
– እርስዎማ በዚህኛው ዝውውር መቼ ይጠረጠራሉ?
– በየትኛው ዝውውር ነው የምጠረጠረው?
– እ…
– ለመሆኑ ምንድን ነው ባለሥልጣናቱ የሚያደርጉት?
– ሰዎች በሕገወጥ መንገድ ከአገራቸው እንዲፈልሱ ያደርጋሉ፡፡
– እኮ ለምን?
– ዶላር ለማግኘት ነዋ፡፡
– እንዴት ሆኖ?
– በቃ ከሰዎቹ ዶላር ይቀበላሉ፡፡
– ዕቃ ኤክስፖርት ማድረግ ሲያቅታቸው ሰው ኤክስፖርት ማድረግ ጀመሩ ማለት ነው?
– እንደዚያ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ዘዴኛዎች ናቸው ባክህ፡፡
– እንዴት?
– ያው በተዘዋዋሪም ቢሆን እያገኙት ነዋ፡፡
– ምኑን?
– ዶላሩን፡፡
– ክቡር ሚኒስትር ይህ እኮ ከፍተኛ ወንጀል ነው፡፡
– ማነው ያለው?
– የሰዎች ዝውውር እኮ ነው፡፡
– ቢሆንስ?
– ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
– ይኼ የኒዮሊብራሎች ትምክህት ነው፡፡
– እንዴት ሆኖ?
– እነሱ በገንዘብ ሰው ያዘዋውራሉ አይደል እንዴ?
– መቼ ነው ያዘዋወሩት?
– ይኼው እግር ኳስ ተጫዋቾቹ ከአንድ ክለብ ወደ ሌላው ክለብ በከፍተኛ ገንዘብ አይደል እንዴ የሚዘዋወሩት?
– እሱ እኮ ሕጋዊ ነው፡፡
– ይኼኛውስ?
– ሕገወጥ ነዋ፡፡
– ለምን እኛ አንሞክረውም ግን?
– ምኑን? ዝውውሩን?
– ሕጋዊ ዝውውሩን፡፡
– በኳስ ተጨዋቾቻችን?
– በእነሱ ሳይሆን በአትሌቶቻችን፡፡
– ክቡር ሚኒስትር አያውቁም እንዴ?
– ምኑን?
– በአትሌት ስም ስንቱ በርካታ ገንዘብ እየከፈለ ከአገር እንደሚወጣ፡፡
– ምን?
– ትንሽ ዘገዩ፡፡
– ለምኑ?
– ለዚህኛው ቢዝነስ፡፡
– እንዴት?
– በሌሎች ተቀድመዋል፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ቦታ ከሾፌራቸው ጋር እየሄዱ ነው]
– እዚህ ጋ አቁም!
– ኧረ አይቻልም ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ለምንድነው የማይቻለው?
– የተከለከለ ቦታ ነው፡፡
– ማን ነው የከለከለው? አቁም!
– ኧረ የእንጀራ ገመዴን ያስበጥሱብኛል፡፡
– ከእኔ ውጪ ማን ነው የአንተን የእንጀራ ገመድ የሚበጥሰው?
– አዲስ ሕግ ወጥቷል፡፡
– ምን የሚል?
– ተደጋጋሚ ጥፋት ያጠፋ ይቀማል የሚል፡፡
– ምኑን ነው የሚቀማው?
– መንጃ ፈቃዱን?
– መፍጃ ፈቃዱን ነው ያልከኝ?
– በሉት፡፡
– በል አሁን አቁም፡፡
– ኧረ ይኼ ሦስተኛ ቅጣቴ ነው የሚሆነው ክቡር ሚኒስትር?
– ሕጉን ያወጣነው እኛው አይደለን እንዴ?
– የሚተገበረው እኛ ላይ ነዋ፡፡
– እንዲያውም ትራፊኩ ያውና ንገረውና አቁመው፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር ትራፊኩን ክላክስ አድርጐ ጠራው]
– እዚህ ጋ ላቁም?
– አዲስ የወጣውን ሕግ ታውቃለህ አይደል?
– በሚገባ፡፡
– እዚህ ጋ ላቁም ብለህ በማሰብህ ራሱ ልቀጣህ እችላለሁ፡፡
– ይቅርታ እንግዳ ስለያዝኩ ነው፡፡
– አይደለም እንግዳ ለምን ባለሥልጣን አትይዝም?
– ምን አልከኝ?
– የእንጀራ ገመድህን እንዳልበጥስልህ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከኋላ የመኪና መስታወታቸውን አወረዱት]
– እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
– እዚህ ጋ አንድ ቀጠሮ ነበረኝ፡፡
– ምን ላድርግልዎት ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
– እዚህ ጋ ብናቆም ብዬ ነው፡፡
– አይደለም ማቆም አዝለህ ውሰደኝ ቢሉኝ አልወስድዎትም እንዴ?
– እንዲህ ነው እንጂ፡፡
– ሊጋልቡኝ ይችላሉ ስልዎት፡፡
– እሱን ሌላ ጊዜ፡፡
– ክቡር ሚኒስትር እኔም እፈልግዎት ነበር፡፡
– ቢሮ ና፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋ ወሬያቸውን ቀጠሉ]
– እኔ እኮ አይገባኝም፡፡
– ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
– የመልካም አስተዳደር ችግር አለ የሚባለው፡፡
– እንዴት?
– ከዚህ በላይ መልካም አስተዳደር አለ?
– መልካም አስተዳደር ያለው እኮ ለእኛ አይደለም፡፡
– ለማን ነው ያለው ታዲያ?
– ለእናንተ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከቀጠሯቸው የውጭ ዜጐች ጋር ተገናኙ]
– ክቡር ሚኒስትር እዚህ አገር ብዙ ሥራ መሥራት እንፈልጋለን፡፡
– የሚሠራን ሰው እናበረታታለን፡፡
– አገራችሁን እንደ አገራችን ለማሳደግ ቆርጠን ተነስተናል፡፡
– አገራችሁ አድጋለች እንዴ?
– ለዓለም ሁሉ ዕቃ የምናቀርበው እኛ አይደለን እንዴ?
– ለነገሩ እውነታችሁን ነው፡፡
– እዚህ አብዮት ማስነሳት ነው የምንፈልገው፡፡
– ኒዮሊብራሎች ናችሁ እንዴ? የምን አብዮት ነው?
– የለም የለም፤ የገበያ አብዮት ነው የምልዎት፡፡
– እሱኛውን አብዮት ማስነሳት ትችላላችሁ፡፡
– አገሪቷን እናስመነድጋታለን ስልዎት፡፡
– ለልማት በራችን ክፍት ነው፡፡
– አንዳንድ ነገሮች ግን አስቸግረውናል፡፡
– ምን ዓይነት አንዳንድ ነገሮች?
– ቀረጥና ፈቃድ ማውጣት የመሳሰሉት፡፡
– ያስቸገሯችሁ ከሌላ ጋር እየሠራችሁ በመሆኑ ነው፡፡
– ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ወሳኝ መሆንዎት ገብቶን እኮ አሁን ወደ እርስዎ የመጣነው?
– ቢሆንም ዘግይታችኋል፡፡
– አንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢዎች አሳስተውን ነው፡፡
– ለማንኛውም እነዚህን ነገሮች እኔ እጨርሳቸዋለሀ፡፡
– ምን እናድርግ ታዲያ?
– በአስቸኳይ እንፈራረማ፡፡
– ስለእሱ አያስቡ፤ አሁኑኑ ድርጅቱን እንመሠርታለን፡፡
– እኔም ሌላውን እጨርሳለሁ፡፡
– ክቡር ሚኒስትር…
– አቤት፡፡
– ልንሠራው ያሰብነው ቢዝነስ ግን ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተፈቀደ ነው፡፡
– ታዲያ ምን ችግር አለው?
– እኛ የውጭ አገር ዜጐች ነና፡፡
– ኢትዮጵያውያን ትሆናላችኋ፡፡
– እንዴት?
– በእኔ በኩል!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው ቁጭ ብለው በሞባይላቸው ካንዲ ክራሽ የሚባለውን ጌም ሲጫወቱ ጸሐፊያቸው ገባች]
– ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ምን ፈለግሽ?
– እንግዳ ይፈልግዎታል፡፡
– ሥራ ይዟል በይ፡፡
– ኧረ ስድስት ወር ሙሉ ሲመላለስ ነበር፡፡
– በቃ ሌላ ስድስት ወር ይጠብቃ፡፡
– ምን እየሠሩ ነው ግን?
– ከባድ ሥራ ይዣለሁ፡፡
– እንዴ ክቡር ሚኒስትር ካንዲ ክራሽ እየተጫወቱ ነው እንዴ?
– ትጫወቻለሽ እንዴ አንቺም?
– አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
– እንዴት አዕምሮ የሚያሠራ ጌም መሰለሽ?
– አውቃለሁ ስንተኛው ሌቭል ላይ ነዎት?
– 100 ደርሻለሁ፡፡
– እርስዎና ኢሕአዴግ ግን ይኼን ቁጥር ትወዱታላችሁ፡፡
– የቱን ቁጥር?
– 100!
[ክቡር ሚኒስትሩ የጌሙን ሌቭል ማለፍ አቅቷቸው ተክዘው ቁጭ ብለው ሚስታቸው መጡ]
– ምን ሆነህ ነው የተከዝከው?
– ኧረ ተይኝ እባክሽ፡፡
– ምን ሆንክ?
– ማደግ አቃተኝ እኮ፡፡
– ያቺ 11 ፐርሰንቷ ቀረች እንዴ?
– እሷማ እንደቀጠለች ነው፡፡
– የሥራ ዕድገት ጠየቅክ እንዴ ታዲያ?
– ሕይወት ተቀጥፎብኝ ነው፡፡
– ምን ሆነሃል ሰውዬ? ሁላችንም ሰላም ነን እኮ፡፡
– አይ እኔ መቼ የእናንተ ሕይወት አሳሰበኝ?
– የማን ሕይወት ነው ያሳሰበህ ታዲያ?
– የጌሙ ነዋ፡፡
– የምን ጌም?
– ምን ይቺ ልጅሽ ጊዜ ሲኖርህ ተጫወተው ብላ አንድ ጌም አሳይታኝ ይኸው ሱስ ይዞኝ አርፏል፡፡
– ጌም ነው ያልከኝ?
– አዎን፡፡
– ሥራውን ትተህ ጌም?
– እንዴት ጭንቅላት የሚጠይቅ ጌም መሰለሽ?
– ምን የሚሉት ጌም ነው?
– ካንዲ ክራሽ፡፡
– በል ተጠንቀቅ፡፡
– ምኑን?
– አንተ ካንዲ ክራሽ ስታደርግ …
– እ…
– አንተ ራስህ ክራሽ እንዳትደረግ፡፡
– በማን?
– በሕዝቡ!