ጥፋተኞችም እኛ … መፍትሄዎችም እኛው …..የለውጥ ሃይሎች ነን የምንል ቆም ብለን ልናስብ ይገባል::
Minilik Salsawi – መቸም ራስን ማወቅ ራስን ማግኘት የመሰለ ነገር የለም::ይህ እውቀት አዘል ለሆነ ለበሰለ ሰው ይገባዋል:: ስሜትና ፕሮፓጋንዳ ለተደበላለቁበት ጫፍ አንባቢ ዘራፍ ባይ ደግሞ ላይዋጥለት ይችላል::የለውጥ ሃይል ነን የምንል ከሆነ ቆም ብለን ራሳችንን ልንዳብስ ይገባል ልንፈትሽም ይገባል:: ሃገር እየፈረሰ ወገን እየታሰረ እየሰደደ እየተንገላታ ከዚህም አልፎ እየተገደለ ነው:: በየማህበራዊ ድህረገጹ የሚወራው ሆይሆይታ እና መሬት ላይ ያለው ጉዳይ ደሞ አይገናኝም::እውነተኛ የትግል መንፈስ ይዞ ትክክለኛውን ግብ ለመምታት መፍትሄ መሆንን የመሰለ ነገር የለም:: መፍትሄው ደሞ እኛ ራሳችን ነን::ስለ ዘረኝነት ስለ ጀግንነት ስለ ልማት ስለ አዋቂነት ስለ ጡዘት ስላሌለ ነገር ወዘተ እየተሰበክን ነው:: እኛም ከየወገን ወገኑ ሆነን እየተቧደንን በየአጀንዳው ውሮሸባውን እያቀለጥነው ነው::
ከአመት አመት የምንናገረው ነገር አለ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለውጥ ይፈልጋል::የፖለቲካ ጫና ከጫንቃው ላይ እንደወርድ ይሻል::የኑሮ ውድነት ወገቡን ቆርጦታል::የማህበረሰቡ መዘበራረቅ ራስ ምታት ሆኖበታል ከዚህ ጋር በተመሳሰሉ ሂደቶች በአምባገነኖች ጡጫ የሚዋዥቀው ሕዝብ ለውጥ ይፈልጋል::ለዚህ ለውጥ ደግሞ ሁላችንም በየፊናችን እየሮጥን ነው::ሲለን ተቧድነን ሲለን ተነጣጥለን ሲለን ተፈራርጀን ሲለን አሽሟጠን ሲለን ተሰዳድበን ሲለን ሲለን ሲለን .. ኧረ ስንት ጉድ አልፈናል::ካልፈው መማር ከጥፋታችን መታረም መፍትሄም ማበጀት ለትግሉ ጠቀሜታ አለው::አንዱን እየፈረጀ አንዱ ቢሮጥ ባለህበት እርገጥ ካልሆነ በስተቀር ምንም አይፈይድም ከወያኔ ምን እንማራለን?ልብ ብለን ከተመለከትን የወያኔ ካድሬዎች ከአንድ ፋብሪካ ተመርጦ የወጣ እባብ ይመስል ሁሉም አንድ አይነት መርዝ በኛ ላይ ይረጫሉ::እኛ ደሞ እርስ በርሳችን ስንበራረዝ ለነሱ በር በመክፈት መርዛቸው እናራባለን::ይህ መሆን የለበትም::እኛም ወያኔን ለመጣል እስከተነሳን ድረስ በጋራ ሆነን እርስ በርስ ሳኮራኮም ሳንፈራረጅ ከኛ በላይ ላሳር ሳንል መርዞቻችንን በጋራ ጠላታችን በሆነው ወያኔ ላይ መርጨት ያስፈልጋል::
ድርጅታዊ ዲሲፒሊን ግለሰባዊ ግብረገብነትን መተግበር ይጠበቅብናል::የለውጥ ፈላጊ ሃይሎች ነን ማለት ጠላታችን ወያኔ ነው ማስወገድ ያለብን ወያኔን ነው ማለት ነው::ቆም ብለን ረጋ ብለን ማሰብ አለብን::አንዱ የለውጥ ሃይል ሌላውን ቢንቀው ምንም የሚመጣ ለውጥ የለም ባለንበት ከመርገጥ ውጪ::አትኩሮታችን ሁሉ ወያኔን ማስወገድ ይሁን::እኛ የለውጥ ሃይሎች ስንባላ ወያኔ ስራዋን ትሰራለች::እኛ ስንተባበር ግን ወያኔ ያሰበችውን ሁሉ እናኮላሽባታለን::በየማህበራዊ ድህረገጹ ላይክ ኮሜንት እና ሼር ከመቁጠር ይልቅ ከመፈራረጅ ይልቅ እየፈረሰች ያለችውን አገር በጋራ እናቅና::በማይሆን ነገር ራስን ማጭበርበር ይብቃ::በጋራ በአንድነት እንቁም::መንቃት ያስፈልጋል::አትኩሮቶች ሁሉ ወያኔን እና የወያኔን እኩይ ተግባራት ወደ መደምሰስ ይሁኑ::በማይሆን አጀንዳ ተዘናግተን አንባላ::ሃገራችንን ከአውሬዎች እናድን::እንንቃ::ከባለፈው እንማር::አትኩሮቶች ሁሉ በወያኔ መደምሰስ ላይ ከሆኑ ተረባርበን በጋራ ከቆምን ከባለህበት እርገጥ ወጥተን አሸናፊነታችንን እናረጋግጣለን::ድል የሰፊው ሕዝብ ነው!!#ምንሊክሳልሳዊ