የፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ መታሰቢያ ሥነ ሥርዐት ተካሄደ
- ለሐውልቱ ሥራ የተዋዋለው ተቋራጭ አድራሻውን አጥፍቶ ጀርመን ከረመ
- በውሉ መሠረት ከነሐስ የሚሠራውን ሐውልት በ186 ቀን ሠርቶ ማስረከብ ነበረበት
- ለጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ‹‹ዝክረ አበው›› እንዲያደርስ ታዝዟል
ነሐሴ ፲ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም ሌሊት ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ የተለዩት የአምስተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ኅልፈት አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ሥነ ሥርዐት በዛሬው ዕለት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በማሕሌት፣ በጸሎተ ፍትሐትና በቅዳሴ ታስቦ ውሏል፡፡
በቤተ ክርስቲያናችን የሙታን መታሰቢያ ቀኖና መሠረት በዐጸደ ነፍስ ያሉትን ዕጣን፣ ጧፍ እና መሥዋዕት በማቅረብ ተዝካረ ጸሎት ማድረግ ሥርዐት መኾኑን ከመጽሐፈ ግንዘት እና መጽሐፈ ሢራክ በመጥቀስ ያስረዱት ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ የአቡነ ጳውሎስ ዕረፍት አንደኛ ዓመት መታሰቢያ የሚካሄደው ‹‹ቅዱስነታቸው በሁሉም አቅጣጫ ያስመዘገቧቸውን የሥራ ውጤቶች በማዘከር›› መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከዐሥራ አንድ ያህል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ የሙት ዓመት መታሰቢያ ሥነ ሥርዐቱን መርተዋል፤ ንግግራቸውም ‹‹ነፍሰ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያሪክ አባ ጳውሎስን ከማኅበረ መላእክት፣ ከማኅበረ ጻድቃን እንድትደምርልን እንለምንሃለን›› የተወሰነና የተጠቃለለ ነበር፡፡
ጸሎተ ፍትሐቱ በተከናወነበት የካቴድራሉ ዐጸድ ውስጥ የሚገኘውና ሥራው ያልተጠናቀቀው መካነ መቃብራቸው በእብነ በረድ ተዘግቷል፤ በቆርቆሮ የታጠረው ዐጸድ ዙሪያው ጒንጒን አበባ ተደርጎበት የቀድሞውን ፓትርያሪክ ግዙፍ ምስል በያዘ ባነር ተሸፍኗል፤ ‹‹መልካሙን ገድል ተጋድያለኹ. . .›› የሚለው የቅዱስ ጳውሎስ ጥቅስ በታላላቅ ፊደላት ሰፍሮበታል፡፡ የመታሰቢያ ሥነ ሥርዐቱ ተካፋዮች ከጸሎተ ፍትሐቱ በኋላ ወደተቀጸረው የመካነ መቃብሩ ዐጸድ ቢዘልቁም ከዚህ በቀር የሚያዩት ነገር አልነበረም፡፡