‹መድኃኒቱ የትኛችንም ፋርማሲ ውስጥ የለም›
ግብጽ ከድጡ ወደ ማጡ እየተጓዘች ነው፡፡ ሀገርን ማናጋትና ማፍረስ ምንኛ ቀላል እንደሆነ እየተማርንም ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የአስተሳሰብ፣ የበሰለ አመራር፣ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታና ብስለት፣ የታመነና የበሰለ ሚዲያ፣ መብቱንና ግዳጁን የተረዳና የሚወጣ ማኅበረሰብ፣ ልካቸውንና መልካቸውን የሚያውቁ የፍትሕ፣ የጸጥታና የውትድርና ተቋማት አጠቃላይ ውጤት እንጂ የምርጫ ሂደትና ውጤት ብቻ እንዳልሆነም እየተማርን ነው፡፡
የእሥራኤልና ፍልስጥኤምን የሰላም ድርድር አስመልክቶ በቅርቡ የተጠየቁት የእሥራኤል ፕሬዚዳንት ሺሞን ፔሬዝ ‹‹ድርድር ማለት እኛ መፍትሔ ነው ብለን የምናስበውን ለሌላ ለማሳመን የምናደርገው ውይይት አይደለም፤ ድርድር ማለት ሁለታችንም በጋራ የምንፈልገው ሌላ ሦስተኛ መፍትሔ ነው፡፡›› ብለው ነበር፡፡ ሌላ ሦስተኛ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ‹እንትን ወይም ሞት‹ ብለው የተሰለፉ የግብጽ ልጆች ሀገራቸውን ወደ ማትወጣበት ኪሣራ እየተከተቷት ነው፡፡
አንድ ‹ተረት በሥዕል› የሚባል መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ የሚል ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ሁለት ውሾች መንገድ ላይ ሲሄዱ ከሥጋ ቤት መኪና የወደቀ ምርጥ ሥጋ ያያሉ፡፡ ሁለቱም ወደ ሥጋው ይፈተለካሉ፡፡ ሁለቱም ግን ሥጋው ጋ ከመድረሳቸው በፊት ይፋጠጣሉ፡፡ ሥጋውን እኔ ብቻ ነኝ መብላት ያለብኝ በሚል አባዜ ውስጥ ገብተው ከሥጋው ጎን መናከስ ጀመሩ፡፡ በእግር እየተገፋፋ፣በጥርስ እየተቧጨቁ ቀኑን ሙሉ ሲናከሱ ዋሉ፡፡ በመጨረሻም ተዳከሙ፡፡ ደማቸው ፈስሶ፣ ቆዳቸውም ተሰነጣጥቆ ምድር ላይ ተዝለፍልፈው ወደቁ፡፡
በዚህ መካከል እንዲት ቀን የሰጣት ቡችላ መጣች፡፡ ስታይ ሁለት ደቦል የሚያክሉ ውሾች መሬት ላይ ተጋድመው ያቃስታሉ፡፡ ከአጠገባቸውም ምን የመሰለ ጮማ ሥጋ ተጋድሟል፡፡ ብታያቸው ካሉበት የሚንቀሳቀሱ ዓይነት አይደሉም፡፡ መጀመሪያ ወደ ሥጋው ጠጋ አለች፡፡ በድካም ተገላብጦ ከማየት በቀር ለማስጣል ዐቅም ያለው አልነበረም፡፡ ሥጋውን መንጨት ስትጀምር ከሚያቃስት ድምጽ በቀር የከለከላት የለም፡፡ በመጨረሻም እየጎተተች ወሰደችው፡፡
ቀማኛ ሲጣላ
ተስማምቶ እንዳይበላ
መንትፋቸው ሄደች ዘዴኛ ቡችላ
የሚል በተረቱ መጨረሻ ላይ ሠፍሯል፡፡
በአብዮቱ ዘመን ልሂቃኑ መግባባት፣ ከሚከተሉት ርእዮተ ዓለም ውጭም ሌላ ሦስተኛ መፍትሔ ማምጣት አቅቷቸው እርስ በርሳቸው ሲባሉና ሲናከሱ ሀገሪቱን ለወታደራዊው ጁንታ አስረከቧት፡፡ በተግባቦትና በውይይት፣ በዕውቀትና በልምድ እንዴት መፍትሔ እንደሚመጣ ከመሥራት ይልቅ ከማርክስና ሌኒን፣ ከማኦና ከኤንግልስ መጻሕፍት ውስጥ መፍትሔውን ሲፈልጉ በጠመንጃው መፍትሔ አመጣለሁ ለሚለው ደርግ ሁሉንም አስረከቡት፡
አብዛኞቹ የግብጽ የፖለቲካ ኃይሎች ሙባረክን ሕዝቡ ሲያነቃንቀው የተደራጁ ናቸው፡፡ የተግባባ ኃልይ፣ አቋም ያለው አባል፣ የተዘረጋ መዋቅር፣ የተጠና ፕሮግራም፣ በሕዝቡ ልብ ውስጥ የገባ ሃሳብ አልነበራቸውም፡፡ የሙስሊም ወንድማማቾች ግን ይህንን በበጎውም በክፉውም ዘመን ሲሠራ ነው የኖረው፡፡ ሀገሪቱ ወደ ምርጫ ስትሄድ የአንዳንድ ፓርቲዎች ሰዎች የተማሩ፣ የታወቁ፣ የተከበሩ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሠሩ ስለሆኑ ብቻ ሕዝብ ይመርጠናል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ የተደራጀ ኃይል፣ የተዘጋጀ መዋቅር፣ የተግባባ አባል ግን አልነበራቸውም፡፡ አንዳንዶቹም ከፓርቲያቸው በላይ ሰዎቹ የገዘፉ ነበሩ፡፡ ፓርቲዎቻቸውም የሚጠሩት በፓርቲያቸው ስም ሳይሆን የእገሌ ፓርቲ እየተባሉ ነበር፡፡ ምርጫው ሲመጣ በሚገባ የሠራውና የተደራጀው የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ አሸነፈ፡፡ ልሂቃኑም ሀገሪቱን አሳልፈው ሰጧት፡፡ ይኼው ዛሬ የመውጫ መንገዱ ጠባር በር ሆነ፡፡
ምንጊዜም ሀገራዊ መፍትሔ ውጤታማ የሚሆነው ሀገር ከመፍረሷ በፊት ከተከናወነ ነው፡፡ በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታን፣ በሶማልያና በኮንጎ የምናየው ነገር ይኼንን ይነግረናል፡፡ ሀገር ከፈረሰች፣ ሰው ደም ከተቃባ፣ ሀገራዊ ተቋማትም የሚመጣውን ችግር ሊሸከሙት ከማይችሉበት ደረጃ ከደረሱ በኋላ መፍትሔው ከሁሉም ወገኖች እጅ ይወጣል፡፡ አንድ በሽተኛ ሊድን የሚችለው በተቻለው ፍጥነት በቶሎ ወደ ሕክምናው ቦታ ከደረሰ ነው፡፡ በዘገየ ቁጥር የመዳን ዕድሉ እየጠበበ ይሄዳል፡፡ ሀገራዊ ችግርም እንደዚሁ ነው፡፡
አውስትራልያውያን ‹መድኃኒቱ የትኛችንም ፋርማሲ ውስጥ የለም› የሚሉት ነገር አለ፡፡ ሰሞኑን በሀገራቸው የምርጫ ዘመቻው ተጀምሯል፡፡ ዋናው አጀንዳቸው የሆነውን የሕገ ወጥ ስደት ጉዳይ ሲከራከሩበት ነበር ይህን ያሉት፡፡ በሀገሪቱ ያሉት ፓርቲዎች ሥልጣን በያዙ ቁጥር ሕገ ወጥ ስደትን ያስቆማል የሚሉትን መፍትሔ ሁሉ ወስደዋል፡፡ በየወሩ 1440 ስደተኞች በጀልባ ለሚገቡባት አውስትራልያ ግን የማንም ፓርቲ መድኃኒት ፍቱን መድኃኒት ለመሆን አልቻለም፡፡ ‹‹ችግሩን ለመፍታት የወሰድናቸው መንገዶችም አልፈቱትም፡፡ ሁሉንም መድኃኒት ሞክረናል፤ ግን በሽታው አልዳነም፡፡ ስለዚህ ሌላ መድኃኒት ነው የሚያስፈልገን፡፡ መድኃኒቱ ደግሞ በየትኛውም ፋርማሲ ውስጥ የለም›› ነው ነገሩ፡፡ አዲስን በሽታ በድሮ መድኃኒት ማከም በሽታውን ራሱን ማወሳሰብ ነው፡፡ እናስ? ከተባለ የተለመደውን የመድኃኒት ማዘዣ እየጻፉ የማያድን መድኃኒት ከመስጠት ይልቅ፣ አዲስ መድኃኒት እንፈልግ፣ እንፈልስፍ፡፡ ለዚህ ደግሞ የሁሉም የመድኃኒት ዐዋቂዎችን ዕውቀትም፣ ትጋትም፣ ዐቅምም፣ ቆራጥነትም ይፈለጋል፡፡
ነባር መድኃኒት የሚሠራው በሽታው መድኃኒቱን ሳይለምደው ወይም በሽታ ከዐቅም በላይ ከመሆኑ በፊት ነው፡፡ ያን ጊዜ ከሆነ ከአንዱ ፋርማሲ የተሻለውን መድኃኒት ገዝቶ መውሰድ ይቻላል፡፡ በሀገራችን እንደሚደረገው የሕንድ ነው፣ የቻይና ነው፣ የጀርመን ነው፣ የእንግሊዝ ነው፣ የአሜሪካ ነው፣ የደቡብ አፍሪካ ነው? ብለን የተሻለውን መድኃኒት ገዝተን እንውጣለን፡፡ በሽታው ከዐቅም በላይ ሲሆን ግን ሌላ አዲስ መድኃኒት ነው የሚጠይቀው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሽታው ራሱ አዲስ ስለሚሆን፡፡ ያለበለዚያ አዲሱን ወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ይሆናል፡፡
ሞያ ከጎረቤት ነውና ሀገራችን ከጎረቤት ግብጽ መማር ያለባት ይመስለኛል፡፡ አሁን መድኃኒቱ ከሁሉም ወገኖች ፋርማሲዎች ውስጥ ያለ አይመስልም፡፡ ሀገራዊ ችግሮቻችንን ለማከም በድሮ መድኃኒቶች ነው እየተጠቀምን ያለነው፡፡ አንዳንድ መድኃኒቶች በንጉሡ ጊዜ፣ በወታደራዊው መንግሥት ጊዜ፣ በነጭ ሽብርና ቀይ ሽብር ጊዜ፣ በአሲምባና በደደቢት፣ ተሞክረው ያልሠሩ ናቸው፡፡ በኢዲዩ፣ በኢሕአፓ፣ በመኢሶን፣ በኢጭአት፣ በወዝ ሊግ፣ በአኢሴማ፣ በአኢወማ፣ በ66ና በ97 ተሞክረው ማዳን ያቃታቸው ናቸው፡፡ በሽታው ግን አዲስ ነው፡፡
አሁን የሚበጀን የእኔ ፋርማሲ ውስጥ ያለው መድኃኒት ፍቱን ነው ማለቱን ትቶ ለአዲሱ በሽታ አዲስ መድኃኒት ለመፍጠር መነሣት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሁሉንም ዕውቀት፣ ትጋት፣ ቁርጠኛነትና ዐቅም ይጠይቃል፡፡ ሀገር የአንዱ ወገን ብቻ ልትሆን አትችልም፡፡ ሀገር የሁሉም ካልሆነች የማንም አትሆንም፡፡ ያለበለዚያ ግን በግብጻውያን ላይ እንደምናየው ሁላችንም ወደ ጽንፍ ሄደን ‹እንትን ወይም ሞት› ካልን ሁላችንም ሥጋውን እናጣውና ያልታሰበ ቡችላ ነጥቆ የሚሄድበትን ዕድል እናመቻቻለን፡፡ መድኃኒቱ የሁላችንም ፋርማሲ ውስጥ ያለ አይመስልም፡፡ የሚበጀው የእኔን መድኃኒት ብቻ ካልዋጥክ አትድንም የሚለው አሮጌው መፍትሔ ሳይሆን መድኃኒቱን ሊያስገኙ የሚችሉትን አካላት ሁሉ ተጠቅሞ ለአዲሱ በሽታ አዲስ መድኃኒት መፈለግ ነው፡፡