ሽብርን የሚያወግዝ በሕዝብ ላይ ሽብርን አይነዛም! ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
1997 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሕዝብ የአፈናም ሆነ የዴሞክራሲ ብልጭታ ታሪክ ውስጥ ሁነኛ ስፍራ አለው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብና የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ግራ ሲያጋባ የነበረው አፋኝ ስርዓት ዕርቃኑን የቀረበትም ዓመት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተገኘችውን ትንሽ የመፈናፈኛ ኮሪደር በመጠቀም የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ በመስጠት የሚታወቀውን አገዛዝ ከጫንቃው ለማውረድ ዓለምን ያስደመመና ስልጡንነቱን ያስመሰከረ የምርጫ እንቅስቃሴም ያደረገበት ዓመት ነው፡፡ በሌላ ወገን አገዛዙ የሕዝብን ድምፅ በከፍተኛ ሁኔታ መዝረፉ ይታወቃል፡፡ አገዛዙ ይህም ሳይበቃው ድምፃቸውን የተነጠቁ ንፁሃንን ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በየታዛቸውና በየአደባባዩ በጠራራ ፀሐይ የጨፈጨፈበት ሁኔታ የታሪካችን አሳፋሪ ገጽ ሆኖ ሲታወስ ይኖራል፡፡
በዚህ ያልረካውና በሕዝብ ተቀባይነት እንዳጣ የተረዳው አምባገነናዊ አገዛዝ ከ19/97 በኋላ ሕዝብን ቀይዶ ለመግዛት ያስችሉኛል ያላቸውን ልዩ ልዩ ሕጐች ማውጣት ግንባር ቀደም ስራው ሆነ፡፡ ካወጣቸው በርካታ አዋጆች ውስጥ “ዝነኛው” እና ገዥዎቻችን ንፁሃንን ባሻቸው መንገድ ግዳይ እየጣሉበት ያለው የ”ፀረሽብርተኝነት” አዋጅ 652/2ዐዐ1 አንዱ ነው፡፡ በገዥዎቻችን የሽብር ትርጓሜ ሳይሆን የሽብርን ዓለማቀፋዊ ትርጓሜ በመቀበል አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ሽብር በግለሰብም ይፈፀም በቡድን አሊያም በመንግሥት ለሃገርና ለሕዝብ ሠላምና ፍትህ ጠንቅ መሆኑን ያምናል፡፡ ነገር ግን ሽብርን በመከላከል ሰበብ ሕዝብን የሚያሸብር አዋጅ ማውጣት በምንም ዓይነት መልኩ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው፡፡
አዋጅ 652/2ዐዐ1 በሙስና ተጠርጥሮ የተከሰሰን ዜጋ ዋስትና ለመንፈግ በብርሃን ፍጥነት ከወጣው አዋጅ 239/93 ጋር ሲነፃፀር ሁለቱም አዋጆች ሕገ-መንግስቱን በመጣስና አምባገነን መሪዎች የሚጠሉትን ሁሉ ለማጥቃት የሚጠቀሙበት አርጩሜ በመሆን ተመሳሳይነታቸው የጐላ ነው፡፡ ለምሳሌ በህገ-መንግሥቱ አንቀፅ 79 ንዑስ አንቀፅ 2 “በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የዳኝነት አካል ከማንኛውም የመንግሥት አካል ከማንኛውም ባለስልጣንም ሆነ ከማንኛውም ሌላ ተፅኖ ነፃ ነው” ይላል፡፡ በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 3 መሠረት ደግሞ “ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነፃነት ያከናውናሉ፡፡ ከህግ በስተቀር በሌላ ሁኔታ አይመሩም” ይላል፡፡ ታምረኛው የፀረሽብርተኝነት አዋጅ 652/2ዐዐ1 ደግሞ የሚከተለውን ይተርካል፡፡ “ፖሊስ በበቂ ምክንያት ያመነ ከሆነ በድብቅ የሚደረግ የብርበራ ማዘዣ ከፍ/ቤት እንዲሰጠው በፅሁፍ ወይንም አስቸኳይ ሁኔታ ሲኖር በስልክ ፈቃድ ሊጠይቅ ይችላል” ይላል፡፡ በዚህ አስገራሚ አዋጅ መሠረት የቀረበው መረጃ በቂ ነው ወይንም አይደለም ብሎ የመመዘን የፍ/ቤት ሰልጣን ለፖሊስ ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡ ፍትህን ያክል ክቡርና ታላቅ ጉዳይ እንደማንኛውም ተራ የንግድ እንቅስቃሴ በስልክ ወደ ሚፈፀም ተራ ጉዳይ አውርዶታል፡፡
የፍ/ቤት ነፃነት ለይስሙላ እንኳን አለመኖሩን የዚህ አዋጅ ድንጋጌ በማያሻማ መልኩ ያሳያል፡፡ ባለስልጣናት ቀጭን ትዕዛዝ በቀጭን ሽቦ ለፍ/ቤት የማስተላለፍ ስልጣን እንዳላቸው በዚህ አዋጅ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያውያን በባለስልጣናት እስከ ተፈለጉ ድረስ እንደ አውሬ ታድነው እንደሚያዙ ያሳያል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በአስፈፃሚው አካልና በፍ/ቤት መካከል ሊኖር የሚገባው ልዩነት ለምልክትም መጥፋቱን ይኸው አዋጅ ይደነግጋል፡፡
በ”ፀረሽብርተኝነት” አዋጅ ቁጥር 652/2ዐዐ1 ክፍል ሁለት መሠረት ገዥዎቻችን ማንኛውንም ዜጋ በማንኛውም ምክንያት እንዳሻቸው ለመክሰስ ያመቻቸው ዘንድ የቀረ አንዳች የክስ ዓይነት ያለ አይመስልም፡፡ ይህ ደግሞ ለመጥቀስ በሚያታክት ሁኔታ ከአያሌ የህገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎችና ከሌሎች አዋጆች ጋር እርስ በእርሱ የሚጋጭ ሲሆን የህገ-መንግሥቱን አስፈላጊነትን ፈፅሞ ትርጉም አልባ አድርጐታል፡፡ በአዋጅ 652/2ዐዐ1 መግቢያ የመጀመሪያው ረድፍ ላይ ስለ አዋጁ አሰፈላጊነት “ሕዝቦች በሰላም፣በነፃነትና በተረጋጋ ሁኔታ ለመኖር ያላቸውን መብት ከሽብርተኝነት አደጋ ሁልጊዜ መጠበቅ ያለበት በመሆኑ” ቢልም የአዋጁ ዓላማ በዋናነት በህገ-መንግሠቱ የተቀመጡ መብቶችን ገዢዎች እንደፈለጉ ጠዋትና ማታ ለመግፈፍ ብሎም በዜጎች ላይ ሽብርን ለመንዛት ያመቻቸው ዘንድ የወጣ አዋጅ ስለመሆኑ ብዙ አያከራክርም፡፡ አንድም ቀን ቢሆን ያለአግባብ መታሰር የማይገባቸው ዜጐች በ”ፀረሽብርተኝነት” አዋጅ 652/2ዐዐ1 አንቀፅ 2ዐ ንዑስ አንቀፅ 3 መሠረት በሽብር ተግባር ተጠርጥሮ የታሰረ ግለሰብ እስከ አራት ወር ድረስ ፍ/ቤት ከመቅረቡ በፊት በምርመራ ሰበብ እንደፈለገ ለማጐር ያስችል ዘንድ እንዲሁ ተደንግጓል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትና አያሌ ያልጠቀስናቸው በርካታ በአዋጁ ሊካተቱ የማይገባቸው አንቀፆች በዚሁ አስከፊ አዋጅ ተካተዋል፡፡ በዚህ ፀረ-ሕገ-መንግሥት አዋጅ ምክንያት አያሌ ዜጐች ሰበአዊ መብታቸውን ተገፈው በአፈና ስር እየማቀቁ ይገኛሉ፡፡
አዋጁ የታለመለትን ግብ ይመታ ዘንድ እንደ ተለመደው በቅርቡ መደላድሉ ተሠርቷል፡፡ መደላድሉ ስራውን የጀመረው ሦስት አገር በቀልና ሁለት ኢትዮጵያውያን ላልሆኑ ድርጅቶች ሽብርተኛ የሚል ስም በማውጣት ነው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ለገዥዎች በማያመች ርቀት ላይ እንዳሉ ገዥዎች አይዘነጉትም፡፡ ወይንም በሽብርተኝነት የተፈረጁት አካላት በያዙት ስም ላይ ሌላ ተቀፅላ ስለተጨመረላቸው የሚለወጥ ነገር እንደሌለም ግልፅ ነው፡፡ ለመሆኑ ፀረ-ሽብርተኝነት ዛሬ ለገዥዎቻችን ለምን ትልቁ አጀንዳቸው ሆነ? እስካሁን የዘነጉዋቸውን እነ አልቃይዳንስ ዛሬ ለምን አስታወሷቸው? ዋናው የሰሞኑ ሽርጉድ ዓላማ በኢህአዴግ መዳፍ ስር የሚገኙትን ልዩ ልዩ አካላትና የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማሸማቀቅ ብሎም ለማሸበር ያለመ ነው፡፡ መልዕክቱም እየተላለፈ ያለው መድረሻ ላጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ ከ19/97 ዓ.ም ምርጫ በኋላ የተዘረጋው የአፈና መዋቅር ከመቸውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ሕዝብን በፍርሃት ቀይዶ ለመግዛት ያለመ ነው፡፡ የዚህ አዋጅ ዓላማም የተጀመረውን አፈና አጠናክሮ ለመቀጠል ነው፡፡
አምባገነን መሪዎቻችን ሽብርን በአዋጅ መከላከል እንደማይቻል ያጡታል ብለን አናምንም፡፡ በአዋጅና በፕሮፖጋንዳ ብዛት ቢሆን ኖሮ ደርግ የአሁኖቹን አምባገነን ገዥዎቻችንን ከዋሻቸው ባላስወጣቸው ነበር፡፡ ሽብርን በመንዛትና ዕርስ በዕርሱ የተምታታ ብሎም ህገ-መንግሥቱን እርባና የሚያሳጣ አዋጅ በማውጣትም ሽብርን መከላከል አይቻልም፡፡
ዕብሪት የደፈናቸው የገዥዎቻችን ጆሮዎች ከ2ዐ ዓመታት በኋላ እንኳን የሚሰሙ ከሆኑ መፍትሄው ለሽብር መፈልፈል ምክንያት የሆኑ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን በፍፁም ቀናነትና በፍፁም ልበ ሙሉነት ተጋፍጦ መፍታት ነው፡፡ ለተፈጠረውና ለሚፈጠረው ችግር ሁሉ ስም በማውጣት፣አዋጅ በማወጅና ንፁሃንን በማደን ተጨማሪ ችግር መፍጠር እንጂ ችግርን ማቃለል አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በየጊዜው ስልጣን ላይ የሚወጡ አምባገነኖች መፈንጫ መሆናቸው በአስቸኳይ ሊቆም ይገባዋል፡፡ ኢትዮጵያ የኢትዮትያውያን ሁሉ እንጂ የጥቂት አምባገነኖች አንጡራ ንብረት አይደለችም፡፡ የኢትዮጵያም መከራም ሆነ ደስታ የኢትያጵያውያን ሁሉ እንጂ የጥቂት እናውቅላችኋለን ባዮች አይደለም፡፡ ገዥዎቻችን መገለጫቸው ከሆነው ተራ ዕብሪትና ሕዝብን ግራ ማጋባት ተላቀው በሰከነና በሰለጠነ መንገድ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከሚመለከታቸው ሁሉም ወገኖች ጋር ለመወያየት በራቸውን ክፍት እንዲያደርጉ አንድነት ይመክራል፡፡
ከዚህ ውጭ አሁን የተጀመረው ታፔላ የመለጠፍና ይህንንም ተከትሎ በመላ ሃገሪቱ እየተፈፀመ ያለው ሕዝብን የማዋከብ ተግባር በሕዝብ ላይ እንዳይደርስ ልንዋጋው የሚገባውን የሽብር ተግባር ከመፈፀም የዘለለ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡ ሽብርን በሕዝብ ላይ መንዛት ደግሞ ኢህአደግ የጀመረውን ፈጣን የቁልቁለት ጉዞ ከማፋጠን ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ በመሆኑም፡-
1ኛ. የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የሰሜን ወሎ የላሊበላ ተወካይ የሆነው አቶ ዘመድዬ አገዘ በዚሁ በተሳከረ የሽብር አዋጅ መሠረት ታፍኖ ዘመድ ወዳጅ ሊጠይቀው በማይችልበት ሁኔታ በቃሊቲ ወህኒ ቤት እየማቀቀ ይገኛል፤በአስቸኳይ እንዲፈታ እንጠይቃለን፡፡
2ኛ. በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በአሶሳ፣በአርባምንጭ፣በሐዋሳ፣በአፋር፣በቦረና፣በክብረ መንግሥት፣በግርጃ ወረዳ፣በጉጂ ዞን በሚገኙ 12 ወረዳዎችና ሌሎች ቦታዎች በአንድነት አባላት፣ደጋፊዎችና በአጠቃላይ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ የአፈና ተግባር በስርዓቱ ካድሬዎች አማካኝነት እየተፈፀመ ይገኛል፡፡ ይህ የውንድብና ተግባር ሳይውል ሳያድር ሊቆም ይገባል፡፡
3ኛ. “አስፈላጊው መደላድል” ከተመቻቸ በኋላ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ አቶ ውብሸት ታዬ፣የፍትህ ጋዜጣ አምደኛ መምህርት ርዕዮት ዓለሙ፣የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር እና ሌሎች 6 ኢትዮጵያውያን በዚሁ ሕገ-መንግሥቱን በሚጥሰው የ”ፀረሽብርተኝነት” አዋጅ አማካኝነት ተከሰው ወህኒ ወርደዋል፡፡ በህገ-መንግሥቱ አንቀፅ 24 ንዑስ አንቀፅ 1 መሠረት “ማንኛውም ሰው ሰብአዊ ክብሩና መልካም ስሙ የመከበር መብት አለው” ቢልም የስርዓቱ ባለሥልጣናት ግን እንደግል ንብረት በሚጠቀሙባቸው የሕዝብ የመገናኛ ብዙሃን በመቅረብ ስለተከሳሾቹ ወንጀለኛነት በስፋት በመለፍለፍ ለፍ/ቤት መልዕክታቸውን በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ተደጋግሞ በአምባገነን ገዥዎቻችን በመጣስ የሚታወቀው የህገ-መንግሥቱን አንቀፅ 21ም በእነዚህ ተከሳሾች ላይ ተደጋግሞ እየተረገጠ ነው፡፡ በዘመድ አዝማድና በህግ አማካሪ የመጐብኘት መብታቸውንም ተነጥቀዋል፡፡ ይህን መሰሉ የአፈና ተግባር እንዲሁ ተደጋግሞ በመጣስ የሚታወቀውንና ድሮውንም በቋፍ ላይ የነበረውን የህገ-መንግሥቱን አንቀፅ 29 ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብት ትልቅ ችግር ውስጥ የጣለ በገዥዎች የማሸማቀቂያ ወይንም “እኔን ያየህ ተቀጣ” መልዕክት ለመላክ የታለመ ስለመሆኑ ብዙ አያከራክርም፡፡ አንድነት እነዚህ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ዜጎች ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸው ሳይሸራረፍ በአስቸኳይ እንዲጠበቅላቸው አጥብቆ ይጠይቃል፡፡
ሽብርን ከስሩ ማድረቅ የሚቻለው ዜጐች ሁሉ ነፃነታቸው የማይሸራረፍበትን ሥርዓት በማስፈንና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ መወያየት ተወያይተውም መፍትሄ መስጠት ሲችሉ መሆኑን አንድነት አበክሮ ያምናል፡፡ ገዥዎቻችን ካለፈው በመማር ይህ መሰሉን የሰከነ የውይይት መድረክ ሊያዘጋጁ ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭ የተያያዙት ሕግን በማስከበር ሰበብ ሕግን መጣስ፣ሽብርን በመከላከል ሰበብ ሽብርን መንዛት ሃገራችንን አሁን ካለችበትም ወደ ከፋ ችግር የሚያወርድ ሲሆን የኢህአዴግንም አይቀሬ ውድቀት የሚያፋጥን ይሆናል፡፡
ሰኔ 29 ቀን 2ዐዐ3 ዓ.ም
አዲስ አበባ