በቦሌ፣ በቂርቆስና በልደታ ክፍላተ ከተሞች በጦር መሣርያ የታገዘ ዝርፊያ ተካሄድ
በታምሩ ጽጌ | ሪፖርት
ከሰኔ 3 ቀን እስከ ሰኔ 17 ቀን 2003 ዓ.ም. ባሉት 15 ቀናት ውስጥ በቦሌ፣ በቂርቆስና በልደታ ክፍላተ ከተሞች ውስጥ በጦር መሣርያ በመታገዝ በዝርፊያ ወንጀልና በነፍስ ግድያ የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች፣ ሰኔ 24 ቀን 2003 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው፣ ሰኔ 3 ቀን 2003 ዓ.ም. በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በቀድሞ ቀበሌ 02/03 ልዩ ቦታው መስቀል ፍላወር በሚባለው አካባቢ፣ አራት የወንጀል ድርጊት ፈጻሚዎች አንድ ኡዚ ጠመንጃና አንድ ሽጉጥ ይዘው በግለሰብ መኖርያ ግቢ ውስጥ ይገባሉ፡፡ በጥበቃ ላይ የነበሩ ግለሰቦችን በማገት ወደ መኖርያ ቤት ዘልቀው ሞባይሎች፣ አራት ሺሕ ብር፣ ከወርቅ የተሠሩ የጆሮ ጉትቻዎችንና የአንገት ሀብሎችን፣ ሌሎች የብር ጌጣጌጦችንና አንድ ኮልት ሽጉጥ ዘርፈው ተሰውረዋል፡፡
ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ሁለቱ ከ11 ቀናት ቆይታ በኋላ ሰኔ 14 ቀን 2003 ዓ.ም. በቦሌ ክፍለ ከተማ በቀድሞው ቀበሌ 10 ልዩ ቦታው አብሽሮ ሕንፃ አካባቢ፣ ዶ/ር መሐመድ መሐሙድ በሚባሉ ግለሰብ ቤት ውስጥ ገብተው ዘረፋ ማካሄዳቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ወደ ዶክተሩ ቤት ገብተው በመኖርያ ቤቱ ውስጥ ከተገኙት ሰዎች ላይ የተለያዩ ወርቆችን፣ የጆሮ ጉትቻዎችን፣ ሀብሎችን፣ ሞባይሎችን፣ 500 ብርና የእጅ ሰዓት ከዘረፉ በኋላ፣ የቤቱን ባለቤት ዶ/ር መሐመድን በታጠቁት ሽጉጥ ግንባራቸውን በመምታት መሰወራቸውን ኮሚሽኑ ተናግሯል፡፡
ዶ/ር መሐመድ የተባሉት ግለሰብ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ኮሚሽኑ ገልጾ፣ ግለሰቡ የሒሳብ ባለሙያ አማካሪና የዩኒቨርሲቲ መምህር እንደነበሩ አስታውቋል፡፡
ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ከሦስት ቀናት ቆይታ በኋላ ሰኔ 17 ቀን 2003 ዓ.ም. በዚያው በቦሌ ክፍለ ከተማ በቀድሞው ቀበሌ 01/02 ልዩ ቦታው ቤተሰብ ካፌና ሬስቶራንት ውስጥ በመግባት፣ በያዙት ኡዚ ጠመንጃና ሽጉጥ በማስፈራራት በሬስቶራንቱ ውስጥ የነበረውን ስምንት ሺሕ ብርና የገንዘብ መመዝገቢያ ማሽንና (ካሽ ሬጅስተር) ሁለት ሞባይሎች ዘርፈው መሰወራቸውን ኮሚሽኑ አስረድቷል፡፡
በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሌሎች ሰባት ግለሰቦች ሲሆኑ፣ በልደታ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 12 ልዩ ስፍራው ጎላ ሚካኤል ሰፈር ሰኔ 9 ቀን 2003 ዓ.ም. ከአንድ ግለሰብ ላይ 1.2 ሚሊዮን ብር መዝረፋቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
ግለሰቡ መኪና ለመግዛት 1.2 ሚሊዮን ብር ይዞ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ሲሆን ወደ መኪና ሻጮቹ እንደሄደ፣ ማንነታቸውን የማያውቃቸው ሰባት ግለሰቦች አስገድደው ከዘረፉት በኋላ መሰወራቸውን የተናገረው ኮሚሽኑ፣ ፖሊስ ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቋል፡፡ የወሰዱትንም ገንዘብ እያንዳንዳቸው 150 ሺሕ ብር መከፋፈላቸውንና 800 ሺሕ ብር ሊያስመልስ መቻሉን ተናግሯል፡፡
በቦሌና በቂርቆስ ክፍለ ከተማም ዝርፊያ የፈጸሙትንና የሰው ነፍስ ያጠፉትን አራት ተጠርጣሪዎች ፖሊስ ባደረገው ልዩ ክትትል በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገልጾ፣ ሁለቱን አዲስ አበባ ውስጥ፣ አንዱን በአማራ ክልል፣ አንዱን ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ከነጦር መሣሪያዎቻቸው በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል፡፡