ኦብነግ በኦጋዴን ክልል ተጠልፈው የነበሩትን ሁለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዕርዳታ ሠራተኞችን እንዳስረከበ አስታወቀ
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ ባለፈው ሰኞ ሰኔ 20 ቀን ባወጣው መግለጫ ከወር በላይ በክልሉ ታግተው የሰነበቱትን ሁለት የአለም አቀፍ ድርጅቱን ሠራተኞች ማስረከቡንና የወያኔ ወታደሮች ርክክቡን ለማደናቀፍ አድርገውት የነበረውን ተከታታይ ጥቃት ማክሸፉን አስታወቀ።
የወያኔ አገዛዝ የኦብነግን የድጋፍ መሠረት ለማድረቅ በተከተለው እርምጃ ምንም አይነት የምግብና ህክምና ዕርዳታ አገልግሎት የሚሠጡ የአገር ውስጥና የውጪ ድርጅቶች በክልሉ ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ በማገዱ በርካታ ሽማግሌዎች፤ ህጻናትና ሴቶች በከፍተኛ ረሃብ እንደቅጠል እየረገፉ መሆናቸውን ታዋቂው የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት ሂውማን ራይትስዎች በተደጋጋሚ ከመዘገቡም በላይ በኦጋዴን ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደሆነ ገልጾ በአስቸኳይ እንዲቆም በተደጋጋሚ ጠይቆአል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ፕሮግራም በክልሉ በረሀብ ለተጎዱ ወገኖች ስንዴ በማከፋፈል ተግባር ላይ ተሰማርቶ የነበረ ሲሆን፣ በወያኔ እገዳ ምክንያት አገልግሎቱን እንዳቋረጠ ለማወቅ ተችሎአል።
ሰሞኑን በሲ ኤን ኤን አይ ሪፖርት ላይ ለህዝብ ይፋ የሆነው የቪዲዮ ምስል በ1977 በአገራችን ደርሶ ከነበረው አስከፊው የድርቅ ረሃብ በከፋ ሁኔታ ዜጎችና የቤት እንስሳት በምግብና ውሃ እጦት በሚያሳዝን አሟሟት እየረገፉ መሆኑን አሳይቶአል። መለስ ዜናዊና ግብረአበሮቹ የአገሪቱን ሃብትና ንብረት ዘርፈው በልጆቻቸውና ዘመዶቻቸው ሥም በየፈረንጅ አገር ሲያጠራቅሙ ህዝብ ለ እንዲህ አይነት የከፋ ሰቆቃ መዳረጉ ይዋል የደር እንጂ እንደሚያስጠይቅ ይታወቃል።