መጋቢት ፲፪ ‹‹የደቀ መዛሙርት ቀን›› ተብሎ በየዓመቱ ይታሰባል
- ‹‹በድል ኮረብታ ላይ ወጥታችኋል፤ መምህራን ኮርተናል›› /ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሣ/
- ‹‹የተቃወምነው ሰውን ሳይኾን ሥርዐቱን ነው›› /የደቀ መዛሙርቱ መማክርት አመራር/
- የደቀ መዛሙርቱ ምረቃ ሐምሌ ፳፯ ቀን ይካሄዳል
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲስ ኪዳን መምህር በኾኑት ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሣ አገላለጽ የኮሌጁ ደቀ መዛሙርት ያሣመሯት የዛሬ ሐምሌ ፳፭ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ምሽት ለሚቀጥለው ትውልድ የተሰጠች መሠረታዊ የትውስታ ዕለት፣ የትውስታ ምሽት፣ የኢያሱ ሐውልት ናት፡፡
ደቀ መዛሙርቱ የኮሌጁ አካዳሚያዊ እና አስተዳደራዊ ችግሮች እንዲፈቱ ላለፉት ስድስት ወራት ሲያካሂዱ የቆዩት ትግል በውጤት መጠናቀቁን በማስመልከት በዛሬው ዕለት ምሽት በምግብ ቤት አዳራሻቸው የራት መርሐ ግብር አዘጋጅተዋል፡፡
በራት መርሐ ግብሩ ላይ ‹‹እግዚአብሔርን ግሩም ነኽ በሉት፤ ሥራኽ ድንቅ ነው በሉት›› በሚል ርእስ የተሰብሳቢዎችን ቀልብ የሳበ ትምህርት የሰጡት ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም÷ ‹‹የእናንተ ረኀብ ያላዛለው ክንድ፣ የእናንተ ጥም ያልዘጋው አንደበት አባቶቻችን ሐዋርያትንና አባቶቻችን ሊቃውንትን የሚያስታውሰን ኾኗል፤ ይህ የአባቶቻችን ሥራ ነበር፤ ለብዙ ጊዜ ሻግቶ ነበር፤ በእናንተ ደግሞ ተወልውሎ አበራ፤ በድል ኮረብታ ላይ ወጥታችኋል፤ እውነተኛ የወንጌል ማሕፀን ልጆች በመኾናችኁ መምህራን ሊኮሩባችኁ ይገባል፤ ኮርተናል፤›› በማለት ለውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎች ሳይበገሩ ለወራት በጽናት ዘልቀው ለውጤት የበቁ ደቀ መዛሙርትን አወድሰዋል፡፡
ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ‹‹የግራ የቀኝ ጠላታችን›› ሰው ሳይኾን ክፉ መንፈስ መኾኑን በመግለጽ፣ ‹‹እውነት ነው፣ የላይ ፈሪ የታች ፈሪ እያለ ያጣላን የሁለታችን ጠላት ክፉ መንፈስ ተወግዷል፤ አሁን ድል ያደረገ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ እናንተ ታሪክ ሠርታችኋል፤ ታሪክ ያሠራችኹ እግዚአብሔር ስቡሕ ዉዱስ ነው፤›› ሲሉ ኀያሉን ደካማ፣ ደካማውን ኀያል የሚያደርገውን እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡
ደቀ መዛሙርቱ የቆሙት አባቶቻችን በደማቸው ባረጓት፣ በአጥንታቸው በገነቧት፣ በቆዳቸው ባለሰለሷት ሃይማኖተ ወንጌል ላይ መኾኑን ያዘከሩት መምህሩ÷ ደቀ መዛሙርቱ አፋቸውን በጸሎት፣ እጃቸውን በትዕግሥት፣ ሰውነታቸውን በትሕትና ገዝተው የሃይማኖታቸውን ልዕልና ማስመስከራቸውን በመጥቀስ የተቃውሞ እንቅስቃሴያቸውን ሰላማዊነት አስረድተዋል – ‹‹ማንም ማንንም በጥላቻ የሚያይበት ዘመን አከተመ፤ ልክ እንደ ማንዴላ ኾናችኁ፡፡›› ይህም በኢትዮጵያ እና በውጭ ሀገር ላሉት የቀድሞ ምሩቃን ወንድሞች መኩሪያና መመኪያ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
መምህሩ አያይዘውም ‹‹ነፍሳቸውን የገነት ውኃ ያጠጣልንና›› በማለት የቀድሞውን ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ስም ከጠሩ በኋላ የሚከተለውን ቃላቸውን አስታወሱ – ‹‹በዚህ መንገድ የሚያልፈው ሁሉ ይህን ግቢና ተቋም እያየ መንቀጥቀጥ አለበት፡፡ በግቢው እነማን ያላችኁበት መኾኑን ማወቅ አለበት፡፡›› አነጋገራቸውን በማስረገጥም ‹‹ዘንድሮ ተተረጎመ›› ሲሉ ሙሉ አዳራሹ በደማቅ ጭብጨባ አስተጋባ፡፡ በይቀጥላልም ደቀ መዛሙርቱ አባቶቻቸውን አርኣያ አድርገው ሞራላቸውን ጠብቀው ልቡናቸውን በማራቀቅ የኮሌጁን ተመልካቾች ሁሉ እንዲያስገርሙ፣ እንዲያስከብሩ መክረዋል፡፡
በመጨረሻም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍሬ ሽቶባት ሳለ ፍሬ አልባ ኾና ያገኛትን ‹በለስ› በኮሌጁ ተጨባጭ ኹኔታ በማመስጠር መምህሩ ሰፊ ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ዘንድሮ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይኹን፤ ፍቅር ለሲኖዶስ አባላት ይኹን፤ በቋሚ ሲኖዶስ አሳሳቢነት፣ በመምህራን መስካሪነት እና በእናንተ ጩኸት በአንጻረ በለስ ትዝህርት፣ ትዕቢት፣ ስስት፣ ክፋት ደርቀውላችኋል›› በማለት ትምህርታቸውን ቋጭተዋል፡፡ ሙሉ አዳራሹ ቆሞ በሚያሰማው የጋለ ጭብጨባ መካከል ወደ መቀመጫቸው ሲያመሩም በትምህርታቸው ዲያቆን ኀይለ ጽዮን መንግሥት በተባለ ሳተና ደቀ መዝሙር የቆሎ ተማሪነት ጊዜያቸውን የሚያስታውሳቸውና ዐይናቸው የትዝታ እንባ ያቆረዘዘበትን የተማሪ አኩፋዳ ተሸልመዋል፡፡
በዚሁ የራት ምሽት የትውስታ መርሐ ግብር ወረብ በኮሌጁ ደቀ መዛሙርት ቀርቧል፤ ቅኔዎች ተሰምተዋል፤ ከቅኔዎችም መካከል በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ላይ የአርዮስ፣ በእመቤታችን ወላዲተ አምላክነት ላይ የንስጥሮስ ኑፋቄ በአንዱ በዘላለም ረድኤት ላይ ተባብረው የተገኙበትን ኹኔታ የሚያመለክቱ ይገኙበታል፡፡ የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበሩ መ/ር ማንያዘዋል ማሞ ‹‹ደቀ መዝሙር መኾን አማረኝ›› በሚል ርእስ የኮሌጁን መዋዕለ ትምህርት ከወቅቱ ፈተናና መከራ ጋራ አሰናኝቶ በቋጠረው ግጥሙ፡-
ብረር ብረር አለው ሸነጠው ልቤን፣
ዳግመኛ ሊመለስ ተማሪ ሊኾን፤
የእውነትን ፋና ከዳር ዳር አድርሶ፣
የእውነትን ፋና ከዳር ዳር ለኩሶ፣
ስለፍትሕ መጮኽ ሁሉንም ታግሦ፣
ስለፍትሕ መጮኽ መልሶ መልሶ፡፡
በማለት የደቀ መዛሙርቱ የተዋሐደ ትግል በቀደሙት ትውልዶች ከተደረገው ጥረት ልቆ ባስገኘው ውጤት ያሳደረበትን አድናቆት፣ መነሣሣትና የመንፈስ ቅንዐት ገልጧል፡፡ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተመስግነዋል፤ የደቀ መዛሙርቱን እንቅስቃሴ በተለይ የምግብ ቤቱን አገልግሎት በተነፈጉበት ወቅት በሚያስፈልገው ሁሉ ሲያግዙ ከነበሩት መካከል የኮሌጁ የቀድሞ የመጀመሪያ ዲግሪ እና የድኅረ ምረቃ ዲፕሎማ መርሐ ግብሮች ምሩቅ የወ/ሮ ዘውዴ ገብረ እግዚአብሔር አለኝታነትና ያለተመልካች የቀረ አልነበረም፡፡ ከማንም ሳይኾን በግል ጥሪቷና ጥረቷ ያደረገችው አስተዋፅኦ ብዙ ምስጋና፣ ብዙ ውዳሴ የተቸረው ነበር፡፡
የኮሌጁን ዕድገት ለማገዝ እና ጥቅሞቹን ለማስጠበቅ እንደ ቤተሰብ የሚደረገው ጥረት ቦታና ጊዜ ሳይገድበው ቀጣይነት እንደሚኖረው ከደቀ መዛሙርቱ መማክርት አመራር በተሰማው መግለጫ ላይ ተመልክቷል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ጥያቄዎቻቸውን ማሰማት በጀመሩበት ስድስት ወራት በፊት ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ለመጀመሪያ ጊዜ የታዘዙበትና ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉበት መጋቢት ፲፪ ቀን በየዓመቱ ‹‹የደቀ መዛሙርት ቀን›› ተብሎ እንደሚታሰብም አመራሩ አስታውቋል፡፡
ኮሌጁ በቀንና በማታ መርሐ ግብሮች ያሠለጠናቸውን ደቀ መዛሙርት ከነገ በስቲያ ሐምሌ ፳፯ ቀን እንደሚያስመርቅ ተዘግቧል፡፡