በሕዋስ እና በማኅበር የተደራጁ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆች የምሥራቅ ኢትዮጵያ አህጉረ ስብከትን እያናወጡ ነው

  • በአሰበ ተፈሪ በዓላማ የሚመስሏቸውንና በጥቅም የገዟቸውን የሀ/ስብከቱን ሥራ አስኪያጅና ጸሐፊ በመያዝ የደ/ጽዮን ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት እና በወረዳው የማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤቶች እንዲታሸጉ አድርገዋል፡፡
  • ራሱን ‹‹ማኅበረ ናታኒም›› እያለ የሚጠራው በቅ/ሲኖዶስ የተወገዘው ሃይማኖተ አበው ርዝራዥ፣ የደ/ጽዮን ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤን ምርጫ በአባላቱ ብቻ ባቋቋመው አስመራጭ ኮሚቴ በኩል ለመቆጣጠርና አባላቱን በማስመረጥ በደብሩ ተጽዕኖውን ለማጠናከር ያደረገው ሙከራ በሰንበት ት/ቤቱ አባላት ጥረት ተጋልጧል፡፡
  • የምርጫው አፈጻጸም በቃለ ዐዋዲው መሠረት የሚካሄድና የሁሉም መብት የተጠበቀበት እንዲኾን በብርቱ በመቃወም የ‹‹ማኅበረ ናታኒም››ን ሤራ ካጋለጡት የሰንበት ት/ቤቱ አባላት መካከል አንዲት ወጣት ታረቀኝ በተባለው የማኅበሩ አባል ተደብድባለች፤ የወረዳው ፖሊስ ጉዳዩን እንዲያውቅ የተደረገ ቢኾንም የወሰደው ርምጃ ባለመኖሩ ወጣቷ ለሴቶች ጉዳይ ጽ/ቤት ለማመልከት ተገዳለች፡፡
  • የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ሓላፊዎች የሰንበት ት/ቤቱ እና ወረዳ ማእከሉ ጽ/ቤቶች የታሸጉት ‹‹ጽ/ቤቶቹ የታሸጉት የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ምርጫ እስከሚካሄድና ሰንበት ት/ቤቱ በአዲስ መልክ እስኪቋቋም ድረስ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህም ዋነኛ ዓላማቸው ተወግዞ የተባረረውን ሃይማኖተ አበው አባላት በመመለስ ሰንበት ት/ቤቱን መቆጣጠር፣ የወረዳ ማእከሉ የማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት ለዘለቄታው እንዲዘጋ በማድረግ አገልግሎቱን ማቋረጥ /በእነርሱ አነጋገር ዘግቶ ለማስቀረት/ እንደኾነ ይጠቁማል፡፡ ለዚህም ‹‹የዞኑ ካቢኔ ተነጋግሮበት ወስኗል›› ሲል ታረቀኝ የተባለው የሁከቱ መሪ መናገሩ ተዘግቧል፡፡ 
  • የማኅበረ ቅዱሳን አሰበ ተፈሪ ወረዳ ማእከል ሥራ አስፈጻሚ አባላትና የማኅበሩ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ማስተባበርያ ጽ/ቤት ሓላፊዎች የድሬዳዋ እና ምዕራብ ሐረርጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆምን በድሬዳዋ አነጋግረዋል፤ ሊቀ ጳጳሱ ሰንበት ት/ቤቱም ይኹን የማኅበረ ቅዱሳን ወረዳ ማእከል እንዲታሸግ የሰጡት መመሪያ አለመኖሩን አስታውቀዋቸዋል፤ ቦታው ድረስ በመሄድም ችግሩን እንደሚፈቱ አረጋግጠውላቸዋል – ‹‹የቤተ ክርስቲያን ችግር በቤተ ክርስቲያን ይፈታል፡፡››
  • በዚያው በድሬዳዋ፣ በሕዋስ የተደራጁ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆች መንበረ ጵጵስናው የሚገኝበትን የደብረ ምሕረት ቅ/ሚካኤል ካቴድራል ሰንበት ት/ቤት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸው ነው የተሰማው፡፡ በዚህ ሳቢያ የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ የሰንበት ት/ቤቱን ጽ/ቤት የማሸግ ርምጃ ወስዷል፡፡ ይኹንና የሥራ አስፈጻሚው አባላት የሰበካ ጉባኤውን እግድ በመተላለፍ ጽ/ቤቱን በኀይል ገንጥለው ለመግባት ሞክረው በፖሊስ ርምጃ መገታታቸው ተዘግቧል፡
  • በጣም የሚያሳዝነው በድሬዳዋ ሀ/ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ ክፍል ሓላፊው ከሀ/ስብከቱ የተሰጠውን የትምህርት ፈቃድ ተገን በማድረግ ‹‹በመቐለ ዩኒቨርስቲ ትምህርቴን እየተከታልኩ›› በሚል በአዲስ አበባ አንድ የፕሮቴስታንት ቤተ እምነት ሥልጠና እየወሰደ መኾኑ ነው፡፡ ሓላፊ ተብዬው በአዲስ አበባ በሚወስደው ሥልጠና ድሬዳዋ ላይ የኑፋቄ ሕዋስ እያደራጀ ነው፡፡ ለአብነት ያህል መንበረ ጵጵስናው የሚገኝበት የካቴድራሉ ሰንበት ት/ቤት ሰበካ ጉባኤ ውስጥ የሰንበት ት/ቤቱ ተወካይ ኾኖ የገባው ግለሰብ በሕዋሱ የታቀፈ ሲኾን በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ‹‹ያለወላዲተ አምላክ አማላጅነት ዓለም አይድንም የሚለው አነጋገር የማይሞች ነው›› በሚል ያሰፈረውንና ከሰበካ ጉባኤው አባላትና ከደብሩ ካህናት ጋራ ውዝግብ የቀሰቀሰውን ጽሑፍ ሁሉም የሰንበት ት/ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ‹‹መብቱ ነው፤ የእኛም አቋም ነው›› በማለት እንደደገፉት ተገልጧል፡፡
  • በተያያዘ ዜና ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ለሐምሌ ፲፱ ቀን የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል ወደ ቁሉቢ ርእሰ አድባራት ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ለማምራት ሲዘጋጁ ጥቂት ዕረፍት ባደረጉበት በድሬዳዋ ሀ/ስብከት መንበረ ጵጵስና /ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል/ ድረስ ለ‹‹አቤቱታ›› የመጡ በሐረር የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኞችና ጥቅመኞቻቸው አፍረው መመለሳቸው ተነግሯል፡፡