መደናበር ያመጣው “የሽብርተኝነት” ፍረጃ
የመለስ ዜናዊ አሻንጉሊት ፓርላማ ሰኔ 7 ቀን 2003 ዓ.ም. ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄን (ግንቦት 7)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን (ኦነግ) እና የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባርን (ኦብነግ) በሽብተኝነት መፈረጁ ተሰምቷል።
ለመሆኑ ፓርላማው በምን ሥልጣኑ ነው ድርጅቶችን የሚፈርጀው? እሱ ራሱ ማን ነውና?
የመለስ ዜናዊ ፓርላማ ለዚህ ፍረጃ መነሻ ያደረገው በ2001 ዓ.ም. የወጣው “የፀረ- ሽብርተኝነት አዋጅ” መሆኑም በፍረጃው ዜና ተነግሯል።
ለመሆኑ “የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ” ምንድነው?
ግንቦት 7፣ በሰኔ 4 ቀን 2001 ዓ.ም ርዕሰ አንቀጽ ቁጥር 56 ላይ እንደገለፀው “የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ” ህገ-አልባነትን ህጋዊ ያደረገ አዋጅ ነው። በዚህ ህገ-ወጥ አዋጅ መነሻነት እና ህገወጥ በሆነ ፓርላማ ውሳኔ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ድርጅቶች “ሽብርተኛ” ተብለው ተፈረጁ ማለት አስቂኝ ነው።
መለስ ዜናዊ እና ቡድኑ በሽብር ተጸንሰው፤ በሽብር ማደጋቸውን እናውቃለን። እነሱ በኢትዮጵያዊያን ደም ተረማምደው፤ ብዙ ድልድዮችን አፍርሰው እና በርካታ ባንኮችን ዘርፈው ምኒሊክ ቤተመንግሥት መድረሳቸውን እናስታውሳለን። እነዚህ እኩይ ኃይሎች ቤተመንግሥት ከገቡም በኋላ ኢትዮጵያዊያንን መግደልና መዝረፋቸውን ቀጥለዋል፤ ከኢትዮጵያ ጫንቃ እስካልወረዱ ድረስ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን መዋረድ መቀጠሉ አይቀርም።
በአንፃሩ ግንቦት 7፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላማዊ ምርጫ መሪዎቹን እንዲመርጥ ቀስቅሰው የግንቦት 97ን ታሪካዊ ድል እንዲመጣ ጥረት ባደረጉ ሰዎች የተጀመረ ንቅናቄ መሆኑ የታወቀ ነው። ግንቦት 7፣ በምርጫ 97 ህዝብ መለስንና ፓርቲውን ባለመምረጡ መጨፍጨፉ፣ መጋዙና መታሰሩ ሳያንስ ለወደፊቱም የሰላማዊ ምርጫ በር ተከርችሞ የተዘጋ በመሆኑ ምክንያት የተፈጠረ ድርጅት ነው። ግንቦት 7፣ የግንቦት 7 ቀን 1997 የተስፋ ብርሃን እና ከማግስቱ ጀምሮ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያጠላው ጭለማ የፈጠሩት መስተጋብር ውጤት ነው።
ግንቦት 7፣ ካልተገደደ በስተቀር ጉልበትን የመጠቀም ፍላጎት የሌለው፤ ከጽንሱ ጀምሮ ሰላማዊና ስልጡን (civic) ድርጅት ነው። ኃይል ለመጠቀም ቢገደድ እንኳን ለሰላማዊ ዜጎች ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጥ ህዝባዊ ድርጅት ነው። እስከዛሬም ሰላማዊ ዜጎችን አደጋ ላይ የጣለ እርምጃ ወስዶ አያውቅም፤ ወደፊትም አያደርግም። እንዲህ ዓይነቱን ለህግ ልዕልና የቆመ ሰላምተኛና ህዝባዊ ድርጅትን “ሽብርተኛ” ተብሎ በመለስ ዜናዊና ፓርላማው መፈረጁ በራሱ ምፀት ነው።
ይሁን እንጂ ፍረጃው ከማስገረም ባለፈ በግንቦት 7 ሥራ ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ለውጥ የለም። ግንቦት 7 ከሌሎች የኢትዮጵያ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ህዝብን የሥልጣን ባለቤት የማድረግ ትግሉን ይገፋበታል።
ከሽብርተኝነት ፍረጃው ጋር ሰሞኑን እየታዘብናቸው ያሉት የመለስ ዜናዊ መራወጦች በርካታ ናቸው።
ለምሳሌ
- ረሃብ ከተሜውን ሳይቀር እያጠቃ ባለበት በአሁኑ ወቅት በ100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር 200 ታንኮች ከዩክሬን ተገዝተዋል።
- የህዝባችንን ብሄራዊ ስሜት በመቀስቀስ አባይ አዲስ የማዘናጊያና የዘረፋ ፕሮጀክት ሆኗል።
- ከፍተኛ ባለሥልጣኖችን በመላክ በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያንን መጎነታተል ተጀምሯል።
- ሃብታም ነጋዴዎችንና አርቲስቶችን ለማማለል የሚደረገው ስብሰባና ሩጫ ደርቷል።
- ድሃውን ነጋዴ ሙሉ በሙሉ ከገበያ ለማስወጣት የሚያስችሉ የንግድ ህጎችና ደንቦች ተረቀው ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ ለማዋል ዝግጁ ሆነዋል።
በጥንቃቄ ያስተዋለ ሰው እነዚህ ሁሉ የተበታተኑ ክስተቶች አለመሆናቸውን ይረዳል። ሁሉም በአንድነት ሲጤኑ መለስ ዜናዊ በብርቱ ስጋት ውስጥ ያለ መሆኑን ያስረዳሉ። መለስን እያቅበጠበው ያለው ደግሞ የሁኔታዎች መሳከር ነው።
በአንድ በኩል መለስ የተሟሟቀ ገበያ ውስጥ ነው። ለም መሬቶቻችንን ለባዕዳን ቱጃሮች በመቸብቸብ በመቶ ቢሊዮኖች ብር የሚቆጠር ሃብት ማሸሽ ችሏል። ይህንን የተባበሩት መንግሥታት የልማት መርሃግብር (ዩ.ኤን.ዲ.ፒ) አረጋግጧል፤ መለስም ፊት ለፊት ሲነገረው አላስተባበለም። ይህን የጦፈ ቢዝነስ መተው አይፈልግም። ስልጣንና ሃብት ጥሞታል።
በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያዊያን በአገዛዙ ተንገሽግሸዋል። በየቦታው የሚሰማው ቃል “በቃ!” የሚል ነው። ኢትዮጵያዊያን “ኑሮ መሮናል፤ አገዛዝ አንገሽግሾናል። እኛም እንደ ጎረቤቶቻችን አምርረን እንነሳ!” እያሉ ነው። የስልጣኑ ማብቂያ መዳረሱ ተሰምቶታል።
ወዳጆቹ የሆኑት ዩ.ኤን.ዲ.ፒ፣ የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይ. ኤም. ኤፍ) ውሸቱን ከመጠራጠር አልፈው ማጋለጥ ጀምረዋል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሆኑት ሚስ ክሊንተን አዲስ አበባ ውስጥ የተናገሩትም እረፍት የሚነሳው ነገር ነው። ሚስ ክሊተን የመብራት መጥፋት እንኳን ሳይበግራቸው ፊት ለፊት “የአፍሪካ አምባገነኖች መሄጃችሁ ደርሷል” ብለዋቸዋል።
እነዚህን ኩነቶች ሁሉ በአንድ ላይ ስናይ ነው የአሻንጉሊቱ ፓርላማ ውሳኔ እንድምታ የሚገባን። መለስ ስልጣን ጥሞታል፤ ወዳጁም ጠላቱም እየነገረው ያለው ግን በጊዜ እንዲለቅ ነው። ነብሱ ተጨንቃለች።
ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስተላልፈው መልዕክት አለው። በጣር ላይ ያለው መለስና የዘረፋ ጓዶቹ በተለያዩ ስሞች ሊጠሩን ይችላሉ፤ እኛ ግን ከዓላማችን ዝንፍ አንልም። የመለስን ዜናዊ አገዛዝ ማብቃትና በምትኩም የህዝብ የሥልጣን ባለቤትነትን በዓይኖቻችን ሳናይ እረፍት አይኖረንም። እኛ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ “በቃን!” ብለናል፤ አንተም አንቺም “እኔም በቃኝ!” ብለህ ተነስ፤ ተነሺ።
በሁሉም ቋንቋዎቻችን መፈክራችን አንድ ነው።
በቃ!!! ጋዬ!!! ይአከል!!! አሎኒ!!! ዲታህ!!! ወጣንደም!!! በስ!!! ጊዴስ!!!