አውራምባ ታይምስ ‘ጋዜጠኛዬ ታሰረ’ አለ

(Reporter) — በየሳምንቱ ቅዳሜ የሚታመው የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እሑድ ሰኔ 12 ቀን 2003 ዓ.ም. ከመኖሪያ ቤቱ በፀጥታ ኃይሎች ተወስዶ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ መታሰሩን የዝግጅት ክፍሉ አስታወቀ፡፡ ጋዜጠኛ ውብሸት በመኖሪያ ቤቱ በቁጥጥር ሥር የዋለው በርካታ ቁጥር ባላቸው የፀጥታ ኃይሎች መሆኑን ያስታወቀው ዝግጅት ክፍሉ፣ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ሰነዶች፣ ሲዲዎች፣ ካሜራዎችና የጋዜጣው የተለያዩ ጊዜያት ዕትሞች በፀጥታ ኃይሎቹ መወሰዳቸውን ተናግሯል፡፡

ዝግጅት ክፍሉ ጋዜጠኛ ውብሸት የታሰረበትን ምክንያት እንዲገለጽለት ለሚመለከታቸው የመንግሥት የፀጥታ ተቋማት ጥያቄ አቅርቦ፣ ‹‹ጉዳዩ ከጋዜጣው ጋርም ሆነ ከሙያው ጋር ተያያዥነት የለውም›› የሚል ምላሽ ማግኘቱን ገልጿል፡፡

የምክትል አዘጋጁ መታሰር በሁሉም የጋዜጣው ባልደረቦች ሥነ ልቦና ላይ ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው የገለጸው ዝግጅት ክፍሉ፣ በተለይ ጋዜጠኛ ውብሸት የታሰረበት ምክንያት አለመታወቁ እንዳሳሰባቸው አስታውቋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ከግምት በማስገባት ጋዜጠኛው ለእስር የተዳረገበትን ምክንያትና የሚገኝበትን ሁኔታ መንግሥት እንዲያሳውቀው ዝግጅት ክፍሉ ጠይቋል፡፡