የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በተሽከርካሪ እጥረት ምክንያት በባለጉዳይ መኪና እየተገለገሉ ነው

በኃይሌ ሙሉ | Reporter

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በተሽከርካሪ እጥረት ምክንያት በባለጉዳይ መኪና ለመገልገል እየተገደዱ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አስታወቁ፡፡ የዳኞች፣ የባለሙያዎችና የተሽከርካሪ እጥረት በፍርድ አፈጻጸም ላይ መስተጓጐል እየፈጠረ ነው፡፡ ትናንት በተካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የመሥሪያ ቤታቸውን የ2003 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር ሪፖርት ያቀረቡት አቶ ተገኔ ጌታነህ እንደገለጹት፣ በቂ ተሽከርካሪዎች ባለመኖራቸው ምክንያት የፍርድ አፈጻጸም መምሪያ የባለጉዳዮችን ተሽከርካሪዎች ለመገልገል የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ፍርድ ቤቶች በቂ ተሽከርካሪ የሌላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ያሉት ተሽከርካሪዎችም ከሌሎች ተቋማት በስጦታ የተገኙ አሮጌና በጥገና ኃይል ብቻ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በተሽከርካሪ እጥረት ምክንያት ተዘዋዋሪ ችሎቶች መስተጓጐል የገጠማቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አቶ ተገኔ እንዳሉት በፍርድ ቤቶች በቂ ተሽከርካሪዎች አለመኖራቸውን ተከትሎ፣ ለድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ከቤት ወደ ሥራና ከሥራ ወደ ቤት የሚመላለሱበት ሰርቪስ ማቅረብ ያልተቻለ ሲሆን፣ አንድ ተሽከርካሪ ለሦስትና ለአራት ዳኞች እንዲሰጥ መደረጉና ሰርቪሱ ሲበላሽም የሚተካ ሌላ መኪና ስለማይኖር ዳኞች በሕዝብ ትራንስፖርት እንዲገለገሉ ተገድደዋል፡፡

ተከላካይ ጠበቆች በማረሚያ ቤት እየተገኙ እስረኞችን ለማነጋገር መቸገራቸውና የቢሮ ሥራዎች በተሽከርካሪ እጥረት ምክንያት በተደጋጋሚ ጊዜ መስተጓጐላቸው ሊጠቀሱ የሚገባቸው ችግሮች መሆናቸውን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹አብዛኞቹ ተሽከርካሪዎች በጥገና ኃይል የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው የጥገና ወጪያችን በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ለጥገና የሚመደብልን በጀት ስለማይበቃን አማራጭ በማጣት ብቻ ከሌላ በጀት በየጊዜው እያዛወርን ለመጠቀም እንገደዳለን፤›› በማለት የተሽከርካሪ እጥረት በፍርድ ቤቶች ላይ ያስከተለውን ችግር አስረድተዋል፡፡

አሳሳቢ ነው ተብሎ በሪፖርቱ ላይ የተጠቀሰው ሌላው ጉዳይ የዳኞች መኖሪያ ቤት ችግር ነው፡፡ የመኖሪያ ቤት ሊሰጣቸው ለሚገቡ ዳኞች የመኖሪያ ቤት መስጠት አለመቻልና የመኖሪያ ቤት የተሰጣቸውም ዳኞች ቢሆኑ ከደረጃቸውና ከደኅንነታቸው ጋር የሚመጥን ቤት አለማግኘታቸውን የገለጹት አቶ ተገኔ፣ በቤት ችግር ምክንያት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዳኞች በተለይም ከክልሎች የመጡትን ጨምሮ አንድም ከወዳጅ ዘመድ ተጠግተው አለበለዚየም የግለሰብ ቤት ተከራይተው እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም፣ ‹‹ይህ ችግር እጅግ እየከፋ የመጣ በመሆኑ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በተደጋገሚ ላቀረብነው ጥያቄ ተገቢና ወቅታዊ ምላሽ ሊሰጡበት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

የቢሮና የማስቻያ ቦታ ችግርን በሚመለከት ፕሬዚዲንቱ በሪፖርታቸው እንደገለጹት፣ በሁሉም ፍርድ ቤቶች የማስቻያ ቦታዎች ችግር ያለ ቢሆንም፣ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያለው ችግር ግን አሳሳቢና ጊዜ የማይሰጥ ነው፡፡ ባለጉዳዮች ለችሎት አመቺ ባልሆኑ ቦታዎች ስለሚስተናገዱ እየተጉላሉና እየተቸገሩ መሆናቸውንም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

‹‹ለተገልጋዩም ሆነ ለሠራተኞች ምቹ የሥራ አካባቢን ከመፍጠር አኳያ ቢሮ መገንባት ዘላቂው መፍትሔ በመሆኑ ጥያቄው ለሚመለከተው አካል የቀረበ ቢሆንም፣ እስከአሁን ድረስ የተገኘ መልስ ባለመኖሩ በአንድ ክፍል ሦስትና አራት ዳኞችን ማስቀመጥ ግድ ሆኗል፡፡ የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ሁኔታም ከዚህ የሚብስ እንጂ ያነሰ አይደለም፤›› ያሉት አቶ ተገኔ፣ የቢሮ ጉዳይ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ ዘላቂው መፍትሔ እውን እስከሚሆን ድረስ የልዩ ዓቃቤ ሕግ ይጠቀምበት የነበረው ሕንፃ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲሰጥ በመንግሥት ቢፈቀድም፣ ርክክብ ለማድረግ ዝግጁነት ባለመኖሩ እስካሁን ድረስ ተግባራዊ ሊሆን አለመቻሉን አስታውቀዋል፡፡

በሪፖርቱ ላይ እንደተገለጸው ባለሙያን በተመለከተ እያገጠሙ ካሉት ችግሮች መካከል በእጅ ያሉትን ባለሙያዎች ይዞ ማቆየት አለመቻል አንደኛው ሲሆን፣ በሚለቁት ባለሙያዎች ምትክ ከገበያ ፈልጐ መቅጠር አለመቻልም ሌላው ችግር ነው፡፡

የባለሙያ ችግር በሁሉም የፍርድ ቤት የሥራ መደቦች ያለ ቢሆንም ይበልጥ ጐልቶ የሚታየውና አሳሳቢ የሆነው በገበያው ላይ እጥረት በሚታይባቸው የሥራ መደቦች ላይ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተገኔ፣ በእነዚህ የሥራ መደቦች ላይ ሠራተኛ ለመቅጠር በተደጋጋሚ ጊዜ የቅጥር ማስታወቂያ ቢወጣም የሚቀጠር ይቅርና ለውድድር የሚቀርብ አመልካች እንኳን ማጣት የተለመደ እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት ለእነዚህ ችግሮች ዋነኛው ምክንያት ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም መሆኑ ቢገመትም፣ የተመቻቸ የሥራ አካባቢ አለመኖር ያልተናነሰ ችግር እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ችግሮቹን ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውንና ከእነዚህ ጥረቶችም መካከል ከፍርድ ቤቶቹ ልዩ ባህሪይና በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን የፍርድ ቤቶች ነፃነት ከማረጋገጥ አንጻር፣ ለፍርድ ቤቶች ሠራተኞች ራሱን የቻለ የደመወዝ ስኬል እንዲኖር ማድረግ አንደኛው እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ የደመወዝን ስኬሉን የማሻሻሉ ጥረት ባለመሳካቱ ችግሩ አሁንም ተባብሶ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቶች ተገልጋዩን ኅብረተሰብ በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማስተናገድ በሚያደርጉት ጥረት ማነቆ እየሆኑ ካሉት ችግሮች መካከል አንዱና ዋነኛው የዳኞች እጥረት መሆኑም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት በተለያዩ ወቅቶች የተሾሙና ልምድ ያካበቱ ዳኞች ሥራ በመልቀቃቸው ምክንያት በሁሉም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኞች እጥረት በጉልህ እየታየ ሲሆን፣ ይህንን ችግር ተከትሎም በጥቂቱም ቢሆን የመዝገብ ክምችት ተከስቷል፡፡ የማጣራት አቅምና የበጀት ዓመቱ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ዘጠና ወራት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸርም ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጓል፡፡

የኅብረተሰቡን የፍትሕ ፍላጐትን ለማርካት ጉልበት፣ ጊዜና ወጪን በመጠቀም ቀልጣፋና ተደራሽ የሆነ አሠራር ለማስፈን በተደረገው የወንጀልና የፍትሐ ብሔር መሠረታዊ ሥራ ሒደት ጥናቶች ሊኖር ይገባል ተብሎ ከተቀመጠው የዳኞች ቁጥር አሁን ያለው በጣም ያነሰ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተገኔ፣ ይህንን ችግር ለመፍታት የዳኞች ሹመት ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

‹‹በተለይ የማስቻያ ቦታዎችንና ቢሮዎችን፣ ተሽከርካሪዎችን፣ የዳኞች መኖርያ ቤቶችን እንዲሁም ጥቅማ ጥቅሞችን በተመለከተ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ አቅም የፈቀደውን እንዲያደርግ በዚህ አጋጣሚ በትህትና ማሳሰብ እንወዳለን፤›› በማለት አቶ ተገኔ ለችግሩ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡