‹‹ገንዘብ የለሽም ተብዬ ከሆስፒታል ተባረርኩ›› ያሉ ነፍሰጡር መንገድ ላይ ተገላገሉ

ትዕግሥት ዘሪሁን | ሪፖርተር

በቅርቡ ከሐረር ወደ አዲስ አበባ እንደመጡ የሚናገሩት ወ/ሮ ከድጃ አብዱላህ፣ ባለፈው ዓርብ ከሰዓት በኋላ ምጥ ይዟቸው የወሊድ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ቢሄዱም፣ ካርድ ከወጣላቸው በኋላ ለአገልግሎቱና ለጓንት የሚከፍሉት ገንዘብ ስላልነበራቸው ተባረው መንገድ ላይ መውለዳቸውን አስታወቁ፡፡

ከጳውሎስ ሆስፒታል ፊት ለፊት በጠራራ ፀሐይ መንገድ ላይ የተገላገሉት ወ/ሮ ከድጃ በአስተርጓሚ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ምጥ የያዛቸው ሐሙስ እለት ቢሆንም፣ ለአገሩ እንግዳ በመሆናቸው የሚሄዱበትን ስለማያውቁ እስከ ዓርብ ከሰዓት በኋላ ድረስ ወደ ጤና ተቋም ሳይሄዱ ቆይተዋል፡፡ ዓርብ ከቀኑ 10፡30 ሰዓት ባጋጣሚ መንገድ ላይ ባገኙት ፖሊስ አማካኝነት ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ቢሄዱም፣ አገልግሎቱን ሳያገኙ መባረራቸውን ገልጸዋል፡፡ ባጋጣሚ መንገድ ላይ የተገኙ አንዲት ሴትና የጎዳና ተዳዳሪዎች እንዳዋለዷቸውም ተናግረዋል፡፡

‹‹ሁለት ብር ከፍለን ካርድ ካወጣን በኋላ ወደማዋለጃ ክፍል (22 ቁጥር) ውሰዷት ተባልን፡፡ ወደ ክፍሉ ከገባች በኋላ ለምታገኘው አገልግሎት ብር እንድንከፍልና ጓንትም እንድንገዛ ጠየቁን፡፡ ብር የለንም፣ ከጎዳና ነው የመጣነው ስንላቸው ‹ይዛችኋት ውጡ› ብለው አባረሩን፡፡ ወላዷ ስቃይ ላይ ስለነበረች እንዲያዋልዷት ጠይቀናቸው ማዋለጃ ክፍል ውስጥ ጥለናት ብንወጣም፣ ጎትተው ከማዋለጃ ክፍሉ ስላወጧት ከሆስፒታሉ ይዘናት ወጣን፤ ብዙም ሳትቆይ ልብሳችንን አውልቀን መንገድ ላይ አንጥፈንላት ልትገላገል ችላለች፤›› በማለት የነበረውን ሁኔታ የገለጸልን እዛው ጎዳና ላይ ከወላዷ ጎን ቁጭ ብሎ ያገኘነው የጎዳና ተዳዳሪ ነበር፡፡

ወ/ሮ ከድጃ በቅርቡ በረመዳን ፆም ወቅት ለድሆች የሚሰጥን ዘካ (ምፅዋት) ለማግኘት ከሐረር የመጡ ሲሆን፣ ‹‹ቤቴን ትቼ ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት በዚህ ጊዜ እወልዳለሁ ብዬ ስላልገመትኩ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ሦስት ልጆች የወለዱ ሲሆን፣ እንዳሁኑ ምጥ ቆይቶባቸውና ተሰቃይተው እንደማያውቁም ይናገራሉ፡፡

ወ/ሮ ከድጃን በአካል ያገኘናቸው ከወለዱ ከሁለት ሰዓታት በኋላ ሲሆን፣ ከድካማቸው የተነሳ መናገር ተስኗቸዋል፡፡ ‹‹እያመመኝ ነው ያለሁበትንም አላውቅም፤›› በማለት መታመማቸውን ገልጸውልናል፡፡ እስከዚያን ሰዓት ድረስም ልጃቸውን እንዳላጠቡት ይናገራሉ፡፡

ከሐረር መጥተው ከሦስት ልጆቻቸውና ከባለቤታቸው ጋር ጎዳና ላይ ያረፉት ወ/ሮ ከድጃ፣ ለመጓጓዣ የሚሆን ገንዘብ ካገኙ በፍጥነት ወደ ሐረር ለመመለስ እንደሚፈልጉም ገልጸዋል፡፡ ‹‹እዚያ ቤት አለኝ እንዲህ በብርድ አልሰቃይም፤›› ብለዋል፡፡

ከጳውሎስ ሆስፒታል ወረድ ብሎ ከሚገኘው የነዳጅ ማደያ ፊት ለፊት ጎዳና ላይ ተኝተው ያገኘናቸው ወ/ሮ ከድጃ፣ አልጋ ልብስ ለብሰው ከላይ በላስቲክ ተጠቅልለዋል፡፡ በግርጌያቸው እሳት እየነደደላቸው ቢሆንም ብርዱን እንዳልቻሉት ይናገራሉ፡፡

ወላዷ ከተገላገሉበት ጊዜ ጀምሮ እዚያው እንደቆዩ የሚናገሩት አቶ ሚካኤል መላኩ የተባሉ የዓይን እማኝ በበኩላቸው፣ ‹‹እዚህ አካባቢ የመጣሁት ጫማዬን ላስጠርግ ነበር፡፡ ሴትዮዋ ስትጮህና ስትሰቃይ ምን እንደሆነች ስጠይቅ ልትወልድ መሆኑን ነገሩኝ፡፡ በቅርቡ ሆስፒታል መኖሩን ነግሬያቸው በፍጥነት እንዲወስዷት ብነግራቸውም ተባረው መመለሳቸውን ገልጸውልኛል፡፡ ወዲያውም የጎዳና ተዳዳሪ ወንዶች ልብሳቸውን እያወለቁ አንጥፈውላት በጠራራ ፀሐይ እዚሁ ስትወልድ በዓይኔ አይቻለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ መረጃ ለማግኘት ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት ሲሆን ወደ ሆስፒታሉ አምርተን የማታ ተረኛ የነበሩትን ጉዳይ አስፈጻሚ ነርስ ካላየሁ አሸብርን አግኝተን አነጋግረናቸዋል፡፡ ሆስፒታሉ ለድሆች አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን በመግለጽ ገንዘብ የሌላቸው በርካታ ሴቶች በነፃ የሚወልዱበት አጋጣሚ መኖሩን አስረድተዋል፡፡

‹‹በሆስፒታሉ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን የሚያስፈጽም ሶሻል ወርክ የሚባል ቡድን አለ፡፡ በርካታ ገንዘብ የሌላቸውና የጎዳና ሴቶችም በቡድኑ ጉዳይ አስፈጻሚነት በነፃ አገልግሎት አግኝተዋል፤›› በማለት ወ/ሮ ከድጃ ገንዘብ የለሽም ተብለው ሊባረሩ እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ለወላዷ የወጣውን ካርድ በማየት በምን ምክንያት ከሆስፒታሉ እንደወጡ ለማጣራት ‹‹የልማታችን መሠረት ስለሆኑ እናቶችንና ሕጻናትን እንንከባከባቸው›› የሚል ፖስተር ወደተለጠፈበት ማዋለጃ ክፍል ቢሄዱም፣ መረጃ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ ለወ/ሮ ከድጃ የወጣላቸውን ካርድ ቢያገኙትም እላዩ ላይ ምንም ዓይነት ነገር አልተጻፈበትም፡፡ ‹‹ይህም ሴትዮዋ በሐኪም አለመታየታቸውን፣ ሕክምናም እንዳላገኙና ወደ ሌላ ሆስፒታልም ሪፈር እንዳልተባሉ ያመለክታል፡፡ ካርዱ ላይ ያገኘሁት መረጃ ባለመኖሩም በምን ምክንያት ከሆስፒታሉ ወጥተው እንደሄዱ መገመት አልችልም፤›› ብለዋል፡፡

በሕክምና የባለሙያዎች የሚተገበሩ ሥነምግባር የጎደላቸው ሥራዎች እየተደጋገሙ ለመሆናቸው በተለያዩ የመገናኛ ብዙኅን የሚወጡ ዘገባዎች ያመላክታሉ፡፡ ባለፈው ሰኔ ወርም ከሕክምና ተቋማት ተባራ ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት ዝናብ በሚወርድበት አስፓልት ላይ ስለወለደች እናት ጋዜጣችን መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በቅርቡ በሥነምግባር ጉድለት ‹‹አሰገደች የእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታል›› እንዲሁም ‹‹የሜሪስቶፕስ አራዳ ቅርንጫፍ›› ከሥራ መታገዳቸው በመገናኛ ብዙኅን ይፋ ሆኗል፡፡ ይህ ሁኔታ የሕክምና ተቋማት ሥነምግባር ጉዳይ ወዴት እያመራ ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡