የከተማውና የዞኑ አስተዳዳሪዎች ጭንቅ ላይ ናቸው – ብስራት ወ/ሚካኤል
ሐምሌ 5 ቀን 2005 ዓ.ም
በሰሜን ጎንደር ዞን ዋና ከተማ፣ ጎንደር፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ(አንድነት) ሐምሌ 7 ቀን 2005 ዓ.ም ለጠራው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ፣ ህዝቡ እንዳይገኝ ለማድረግ የከተማውና የዞኑ አስተዳዳሪዎች ከፍተኛ ውጥረትና ጭንቅ ላይ ናቸው፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከፍተኛ አመራሮቹ የብአዴን/ኢህአዴግ አባላትንና የዞኑ የየወረዳው አመራሮችን በከተማው መምህራን ማኀበር አዳራሽ ትናንት ሐምሌ 4 ቀን 2005 ዓ.ም. በመሰብሰብ መመሪያ ማስተላለፋቸው ታውቋል፡፡
በዕለቱ ስብሰባ ፣ የብአዴን/ኢህአዴግ አባላት ሰልፉን እንዳይሳካ፣ በየቤቱ እየሄዱ ህዝቡ በሰልፉ ላይ እንዳይገኝ ቅስቀሳና ማስፈራሪያ ሊያደርጉ እንደሚገባ፣ «ሰላማዊ ሰልፉ ላይ ብጥብጥ ይፈጠራል ብላችሁ ህዝቡን አሳምኑ» የሚል ትዕዛዝ መተላለፉ ተጠቁሟል፡፡
በተለይ ፓርቲው የፀረ-ሽብርተኝነት ህጉ እንዲሰረዝ የሚጠይቀውን ፒቲሽን ህዝቡ እንዳይፈርም፣ «ህገ ወጥ ነው በሉ። ፔቲሽኑን ለማስፈረም ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰዎችንም እንደሚታሰሩ ከማስፈራራት በተጨማሪ ከተቻለ ሰነዱን ንጠቋቸው» የሚሉ መመሪያዎች መተላለፋቸውን፣ ስማቸውን መግለፅ ያልፈቀዱ ያነጋገርኳቸው አንዳንድ የስብሰባው ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በሰሜን ጎንደር ዞን ያሉ የጎንደር ከተማ ፖሊሶች ክህዝቡ ጋር ስለተላመዱ ለጊዜው ወደ ደሴ እንዲሄዱ፣ ደሴ ያሉት ደግሞ ወደ ጎንደር እንዲመጡ ከፌደራልና ከክልሉ አመራሮች ጋር መስማማታቸውንም አመራሮቹ መናገራቸው ተጠቁሟል፡፡
መመሪያው በሚሰጥበት ወቅትም አንዳንድ አባላት ድርጊቱን እንደተቃወሙና «ብአዴን/ኢህአዴግ በጎንደር ህዝቡ ሙሉ ለሙሉ መርጦኛል እያለ እንዲህ ሊሸበር አይገባም፤ ነዋሪው እውነት እኛን የመረጠን ከሆነ ሰላማዊ ሰልፉ ላይ ሊገኙ አይችሉም፤ ስለዚህ አንድነት ፓርቲ በጠራው ህጋዊ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የፈለገ እንዲገኝ በመፍቀድ ድክመቶቻችንን ልናይና የህዝቡን ጥያቄ ልናደምጥ ይገባል» ሲሉ ምላሽ የሰጡ እንደነበሩ ያነጋገርኳቸው ተሳታፊዎች አስታውቀዋል፡፡
በዚህም አመራሮቹ ቅር መሰኘታቸውንነና መመሪያውን ሁሉም ተቀብሎ ሊተገብረው እንደሚገባ፣ አልቀበልም ያለ ደግሞ የድርጅቱ ብአዴን/ኢህአዴግን ትዕዛዝ እንደጣሰ ተቆጥሮ «እርምጃ ይወሰድበታል» ሲሉ ማስፈራራታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በአሁን ወቅትም የፊታችን እሁድ ሐምሌ 7 ቀን 2005ዓ.ም. በጎንደር ለሚካሄደው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ለመገኘት ትናንት የተንቀሳቀሱት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች አቶ ዘካርያስ የማነብርሃን፣አቶ አስራት ጣሴ፣ አቶ ስዩም መንገሻ፣ አቶ አበበ አካሉ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌውን ጨምሮ ሌሎችም ከአዲስ አበባ ዛሬ ሐምሌ 5 ቀን 2005ዓ.ም. ጎንደር መግባታቸውንና ከሰሜን ጎንደር ዞን የአንድነት ፓርቲ አመራሮችና አባላት ጋር የቅስቀሳ ስራ መጀመራቸው ታውቋል፡፡