ዘገባ ከጎንደርና ደሴ – የሚሊዮኖች ድምጽ ግብረ ኃየል

ሐምሌ 5 ቀን 2005 ዓ.ም

– የደሴ ከንቲባ «ሰልፉ ይተላለፍ አሉ»። በጽሁፍ እስካልቀረበ ድረስ አንድነት ጥያቄዉን ዉድቅ አደረገው!
– በጎንደርና በደሴ ለፌደራልና ለክልል ፖሊሶች አበባ ይበረከታል!

የደሴ ከንቲባ ሰልፉ ለሳምንት እንዲራዘም ጠየቁ። ነገር ግን የአንድነት አመራር አባላት ሕጉ እንደሚፈቅደው በጽሁፍ እስካልቀረበላቸው ድረስ ከንቲባዉ በቃል የጠየቁትን እንደማይቀበሉ አረጋግጠዉላቸዋል።

በጎንደር የከተማዋ አስተዳዳሪዎች «ሕዝቡ እናንተን አይሰማም። አምሳ ሰው አታገኙም» በማለት የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች ተስፋ ለማስቆረጥ እየሞከሩም ቢሆን በሜዳ በሕዝቡ ዘንድ እየታየ ያለው ስሜትና ተነሳሽነት ግን ባለስልጣናቱ ከሚሉት ፍጹም የራቀ እንደሆነ የሚደርሱ ዘገባዎች ይሳያሉ።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ «የፊታችን እሁድ ጎንደርና ደሴ የታፈነ ድምጻቸውን ለማሰማት ወደ አደባባይ በሚወጡ ዜጎች ይደምቃሉ» የሚል እምነት ያላቸው የአንድነት የሚሊዮን ድምጽ ግብረ ኃይል አባላት፣ ሕገ መንግስታዊ መብቱን ለመጠቀም የሚንቀሳቀሰው የጎንደርና የደሴ የተከበረ ሕዝብ የሁልግዜ አላማው ሰላምና ፍቅር መሆኑን ለማሳየት፣ አበባና በአካባቢው ልማድ መሰረት የፍቅርና የሰላም መገለጫ የሆኑ ስጦታዎችን ለፌደራልና ለክልል ፖሊሶች እንደሚያበረክት አስረድተዋል።

«ገዢው ፓርቲ ወደ አደባባይ የሚወጡ ዜጎችን ‹‹ህገ መንግስታዊውን ስርዓት በሃይል ለመገልበጥ የሞከሩ››በማለት የሚፈርጅበትና ታጣቂውን ከህዝብ የሚያጋጭበት ቀዳዳ ይደፈን ዘንድ ከአበባ ወይም ከእርጥብ ቄጤማ የሚበልጥ መልእክት ከወዴት ይገኛል» ይላሉ የሰልፎቹ አስተባባሪዎች።

ወደ ሰልፎቹ የሚመጡ ሰዎችም ሰላማዊነታቸውን የሚገልጽ ማናቸውም አይነት ስጦታ ከፊት ለፊታቸው የሚያገኙትን ፖሊስ ‹‹እንደሚወዱት ጭምር እየነገሩት እንዲያበረክቱለት» ጥሪ ቀርቧል።